Wednesday, August 12, 2026

አምላክ ተሸፍኖ

Deus Absconditus

አምላክ ተሸፍኖ


የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። (ኢሳይያስ : 45: 15)


በሰሞነኛው ንባቤ ወደ ልጅነቴ ዘመን ትዘታ መልሶኝ ህይወቴንና አገልግሎቴን ለመቅረጽ በብዙ የናፈቅሁበትንና በዙሪያዬም የነበሩትነ በርካታ ከንቱ ትምሀርቶችና እሳቤዎች እያጠለልሁ ንጹሁንና በጎውን እውነት ለመጠጣት የተጋሁበትን አንድ ብርቱ ጉዳይ ለመዳሰስ እድል ሰጥቶኛል። ይኸውም ሉተር ያስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት በመባል ይታወቃል። ከንባቤ ግምገማ ተነስቼ ያቀረብኩላችሁን መለስተኛ እጥጥር ለማንበብ ትዕግስቱ ካላችሁ ትጠቀማላችሁ።


ይህ የነገረ መስቀል ትምህርት ማርቲን ሉተር በሥነ-መለኮት መረዳቱ ወስጥ በብርቱ ካነሳቸው ማዕከላዊ ጭብጦች መካከል አንዱና ዋናው ነው። ይህንንም በ1518 ሄይድልበርግ ላይ በተካሄደው ሥነ መለኮታዊ ሙግቱ ውስጥ በግልፅ አዘጋጅቶ፣ “የመስቀሉን ሥነ-መለኮት” ከ “ክብር ሥነ-መለኮት” ጋር ባለዉ ተቃርኖ አነጻጽሮ ያቀረበበት፣ የሉተርን ቁልፍ የተሃድሶ እሳቤዎች ቀደምትነት የሚወክል፣ በሉተራን አብያተ ክርስቲያናትም የሥነ መለኮት አውድ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።


መሠረታዊው ሀሳብ


ሉተር እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጠው በሰው ኃይል፣ በጥበብ፣ በስኬት ወይም ፍልስፍናዊነት በመላበት በሃይማኖታዊ ችሎታና ግኝት ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተቀበለው ስቃይና መከራ፣ በደረሰበት ድካም እና በመራር ሞቱ በኩል ነው ሲል ተከራክሯል።


ይህም ተሃድሶውን ያቀጣጠሉና ይመሩ የነበሩ ሥነ መለኮታዊ ሊቃውንት እግዚአብሔርን ማወቅንና መዳንን በተመለከተ እንዴት ያለ መግነጢሳዊ መረዳት እነደነበራቸውና መሠረታዊ የሆነ ለውጥን የሚያመጣ አቀራረብ እንደነበራቸው ማሳያ ነው፤ ይህም ከሰው አስተሳሰብ ወይም ከሚታዩ የሰው ሥራዎች ይልቅ የእግዚአብሔርን የማይታይ መለኮታዊ ባህርይ እና የክርስቶስን ስቃይ ማዕከላዊነት አፅንዖት የሚሰጥ ነው።


ሰዎች በተፈጥሮ እግዚአብሔር በክብርና በብርታት እንዲገለጥ ይጠብቃሉ። ሉተር ግን ይህ ተስፋ የተሳሳተ ነው ብሎ ያምን ነበር፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ታላቅ የማዳን ሥራ የመጣው ሽንፈት በሚመስል ነገር ተሰውሮ ነው - እርሱም የክርስቶስ ስቅለት ነው። በዚያ መስቀል ላይ ኃያሉ አምላክ የባሪያን መልክ ይዞ ድካምን ለበሰ። ለወደቀው ሰው አምላክን የማወቅ፣ የመገናኘትና በአውነተኛው አምላክ የመነካት እድል ሁሉ ተሰብሰቦና ተሸሽጎ ያለው በመስቀሉ መከራ ውስጥ ነው።


አስገራሚው ነገር፣ አስቀድሞ ሉተር በዊተንበርግ ካቴድራል በራፍ ላይ የቸነከራቸው እነዚያ 95ቱ የመቃወሚያ ፅንሰ ሀሳቦቹ ለሥነ-መለኮታዊ ክርክር የታሰቡ የነበሩ ቢሆኑም፣ ያ ክርክር ግን በሉተር የአገልግሎት ዘመን ፈጽሞ አልተካሄደም። ይሁን እንጂ ይህ የሄይደልበርግ ሙግት ሉተር በአካዳሚክ ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ላይ እንዲሳተፍ እና በቀደመው የተሃድሶ ዘመን የያዘውን ሥነ-መለኮታዊ አቋሙን እንዲያዳብር የበለጠ ተደማጭነትንም እንዲያገኝ አስፈላጊ ቦታን ሰጥቶታል። ክርክሩም የተሃድሶው ዘመን አዳሾች የነበራቸውን ብሩህ የአዕምሮ ልቀት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ሉተርም ሥነ-መለኮታዊ ግንዛቤዎቹን በመደበኛ የአካዳሚክ መከራከሪያ ነጥቦች እንዴት እያዳበረ እና እየተሟገተ እንደነበር የሚያመለክት የተባረከ አዕምሮው ማሳያ ነው።


የሄይደልበርግ ክርክር


በሄይደልበርግ ክርክር ውስጥ፣ ሉተር ፡-


# የክብር ስነ መለኮትን የሚያቀነቅን ‘ምሁር’ ክፉውን መልካም እና መልካሙንም ክፉ ብሎ የሚጠራ ነው፣  ​​ምክንያቱም በመልክ ብቻ ይፈርዳልና።


# በነገረ መስቀል ተቃኝቶ የመስቀሉን ስነ መለኮት የሚሰብክ ምሁር ግን አንድን ነገር በእውነቱ የሆነውን ያንንው ነገር ሳያሻሽልና ሳይቀባባ ምን እንደሆነ በምንነቱ ይገልጠዋል፣ ይጠራዋልም፤ ​​ምክንያቱም በክርስቶስ ስቅለት ብርሃን እውነታውን ስለሚያይ ነው ሲል በጽኑ ተከራክሯል።


ስለዚህ የምንከተለው ስነ መለኮት የክብር ይሁን የመስቀል፣ አተያየታችንን እና ፍርዳችንን ይወስናል። ለሉተር፣ የእግዚአብሔር እውነተኛ እውቀት የሚመጣው በፍልስፍናዊ ግምቶች ወይም በሰው ልጅ ስኬቶች ላይ በመተማመን ሳይሆን በተሰቀለው ክርስቶስ ውስጥ እና በኩል ነው ሲል ሞገቷል።


የክብር ሥነ-መለኮት የመስቀል ሥነ-መለኮትን ይቃረናል


# የክብር ሥነ-መለኮት፣ እግዚአብሔርን በኃይል፣ በስኬት፣ በተአምራት እና በሰው ጥበብ ሲፈልግ፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን እግዚአብሔርን በተሰቀለው ክርስቶስ በኩል ያገኛል።

 

# የክብር ሥነ-መለኮት፣ በሰው ልጅ ችሎታ እና በመልካም ሥራ ላይ ሲተማመን፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ብቻ ይደገፋል።


# የክብር ሥነ-መለኮት፣ የሰውን አእምሮና ያስተሳሰብ ልቀት ከፍ ከፍ  ሲያደርግ፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን በክርስቶስ ለተገለጠው ለእግዚአብሔር መገለጥ ብቻ ይገዛል፣ ይሰግዳልም።


# የክብር ሥነ-መለኮት፣ በገጽታ ግንባታ ስካር፣ በምድራዊ ክብር ጥማት፣ በኃይማኖታዊ የሥጋ ጥጋብ እና ልታይ ልታይ በሚል መጋጋጥ የሰውን ምስጋና ሲፈልግ፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን በትሕትናና በየዋህነት ከክርስቶስ ጋር መከራን ይቀበላል


የመስቀሉ ሥነ መለኮት ዋና ዋና ጭብጦች


1. እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ተሰውሯል

ሉተር እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ደካማ ወይም ሞኝነት ወይም ሽንፈት በሚመስል ነገር እንደሚሠራ አስተምሯል። መስቀሉ እንደ ሽንፈት ቢመስልም፣ በኃጢአት፣ በሞት እና በሰይጣን ላይ እግዚአብሔር የተቀዳጀው ፍጹሙ እና የመጨረቫው ድል ነው።


2. በእምነት ብቻ መጽደቅ

መስቀሉ መዳን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ያሳያል። ሰዎች ጽድቅን በክርስቶስ በማመን ብቻ ይቀበሉታል እንጂ በሥራ ሊያገኙት አይችሉም፤

 

3. የሰው ኃጢአት

መስቀሉ የኃጢአትን ከባድነት እና አስፈሪ የሆነውን መዘዙን ያጋልጣል። ከዚህም የኃጢአት ብርታት የሰው ልጅ ራሱን ማዳን ስላልቻለ የክርስቶስ ሞት የግድ አስፈላጊ ነበር።


4. የእግዚአብሔር ጸጋ

መስቀሉ ለኃጢአተኞች የእግዚአብሔር ፍቅር እና ምሕረት የላቀ ማሳያ ነው።


5. የክርስቲያን ሕይወት

አማኞች ዓለማዊ ክብርን ከመፈለግ ይልቅ ክርስቶስን በትሕትና፣ በንስሐ እና በመከራ እንዲከተሉ ተጠርተዋል። ሉተር መከራን ራሱን እያከበረው አልነበረም ፣ ነገር ግን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ተስፋዎች እየታመኑ ልዩ ልዩ ፈተናዎች እንዳሉባቸው በመጠበቅ በነገር ሁሉ ሥቃይን እና መከራን መታገሥ እንዳለባቸው አስተምሯል።


የመስቀሉ ሥነ መለኮት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቶች


ሉተር በክብር ሥነ-መለኮት እና በመስቀል ሥነ-መለኮት መካከል ያለውን  ልዩነት በያዘው ሥነ-መለኮታዊ አቋም ማዕቀፍ ውስጥ ማዕከላዊ ጭብጥ ሰጥቶ የተጠቀመበት አይነተኛ የንባብ ክፍል የሚከተለው ነው 


“እርሱም። እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። እግዚአብሔርም። እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። ደግሞም። ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። እግዚአብሔርም አለ። እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤” (ዘጸአት 33:18-23 )


በዚህ ክፍል ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት ይጠይቃል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ማንም ፊቱን አይቶ በሕይወት መኖር እንደማይችል ይመልስለታል። በምትኩ ግን፣ እግዚአብሔር ሲያልፍ ፊቱን ሳይሆን "ጀርባውን" እንዲያይ ለሙሴ ፈቀደለት። ሉተር ይህንን ክፍል ሲፈታ ስለ መለኮታዊ መገለጥ ተፈጥሮ ጥልቅ የሆነ ሥነ-መለኮታዊ ማብራሪያ አድርጎ ይተረጉመዋል። ለሉተር፣ ይህንን ሁኔታ “አምላካዊ  መሰወር” (በላቲን Deus absconditus) ብሎ ይጠራዋል፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ማንነት ለሰው ልጅ አመክነዮ በመሠረታዊነት አለመታወቁን የሚያመለክት ሥነ-መለኮታዊ እና ፍልስፍናዊ ፅንሰ-ሀሳብ ነው።  የእግዚአብሔር እውነተኛ ባህርይ እና መለኮታዊ መገለጡ የሰው ልጅ ተስፋ አድርጎ በሚጠባበቅበት ከፍ ባለ ክብርና ኃይል የሚደርግ ሳይሆን የልቁንም ከዚያ በተቃራኒው በትሕትናና በየዋህነት በመከራ ውስጥ በማለፍ የሚገለጥ ነው የሚለውን ሀሳብ በጽኑ ያሳያል። ከክብር ይልቅ መከራ ይኸውም የአግዚአበሔር ልጅ መከራ፣ እግዚአብሔር ወደ ሰው የሚመጣበት ያልታሰበና ያልተገመተ መንገዱ ነው።


ይህን ክፍል መሰርት አድርጎ ሉተር የክብር ሥነ-መለኮት ብሎ የሚጠራው ጉዳይ እግዚአብሔርን ለመረዳት የሚደርግ ሰውን ማዕከል ያደረገ የስብአዊ ጥረት  አቀራረብ እንደሆነ ይተቻል። ይህ አይነቱ ሥነ-መለኮት እግዚአብሔርን በኃይሉ፣ በግርማው፥ በሞገሱ እና ለሰው ጥበብ በሚታዩ ምልክቶች በኩል ለማወቅ የሚፈልግ ሰው በስጋው የሚመርጠውና ለስሜቱ  የሚመቸው መንገድ ነው። ይኸውም ልክ ሙሴ የእግዚአብሔርን ፊቱን ለማየት ባቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄው አንጻር የእግዚአብሔር ክብር በቀጥታ ሊገለጥ እንደሚችል ያስባል ማለት ነው። ሉተር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊ አካሄድ እግዚአብሔርን የመረዳት ጉዳይ ወደተዛባ ግንዛቤ የሚመራ እንደሆነ በጽኑ ያስጠነቅቃል፣ ምክንያቱም ይህ አይነቱ ሰብአዊ ዝንባሌ በእምነት ላይ ሳይሆን በሰው አእምሮ እና ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው።


በአንጻሩ፣ የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ግን የእግዚአብሔር የመጨረሻ መገለጥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በደረሰበት ስቃይና ሞት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን የሚያንፀባርቅ ፓራዶክስን ያካትታል። ይህ ሥነ-መለኮት እግዚአብሔር ለሙሴ በዘጸአት 33፡18-23 ላይ ከሰጠው ምላሽ ጋር ይጣጣማል፣ እግዚአብሔር ራሱን በሙሉ ክብሩ ሳይሆን በተሸፈነ መንገድ ይገልጣል - ይኸውም "ጀርባው" የሚለው ነው። ለሉተር፣ ይህ መሸፈኛ የእግዚአብሔር እውነተኛ ሥራና መገኘት በመከራና በድክመት ውስጥ እንደተደበቀ ያመለክታል፣ ይህም ከሰው ልጅ የመለኮታዊ ኃይል ተስፋዎች ጋር የሚቃረን ነው። ጀርባውን እንጂ ፊቱን ማየት ማንንም አያድንም፣ የመስቀሉ ታሪክ እንጂ የሲናው ተራራ አስገራሚና አስፈሪ ተእይንት ማንንም አያድንም። እግዚአብሔር በመከራው ተሰውሮ ነው የተገለጠው እንጂ በክብሩ ተገልጦ አልተገለጠም!!


ሉተር ይህንን ዘጸአት 33:18-23 ያለውን ክፍል መሰረት አድርጎ የእግዚአብሔርን መንገድ ሲያብራራ ከሰው መንገድ ጋር ያለውን ተቃርኖ አጉልቶ ያሳያል። የሰው ልጅ አለኝ ደረስኩበት የሚለው ምክንያታዊነትም ሆነ በመሠረታዊነት እግዚአብሔርን ለመረዳት በራሱ የሚሄድበት ሰብአዊው ዝንባሌ መዳን የማይቻልበት መንገድ ነው፥ የእግዚአብሔር እውነተኛ እውቀት የሚገኘው ግን በተሰቀለው ክርስቶስ ላይ ባለ እምነት ብቻ ነው በማለት ይከራከራል። ይህ ክፍል የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጠው ለሰው በሚመች መንገድ፣ በሚያበራ ፊት፣ በድል አድራጊነትል ከፍታ ሳይሆን በመስቀሉ ትህትና እና ስቃይ በኩል ጀርባውን በማየት ነው የሚለውን ሀሳብ አጉልቶ ያሳያል። ለዚህም ነው ሉተር የስነ መለኮት ሰው የክብርን መንገድ ከመከተል ይልቅ የመስቀሉን  መንገድ የሚከተል መሆን አለበት በማለት አጥብቆ የሚናገረው።


ስለዚህ ይህ የዘጸአት 33:18-23 ያለው ምንባብ ለሉተር የመስቀሉን ሥነ-መለኮት በማዳበር ረገድ ወሳኝ ነው። ይህም የተሰወረውን የእግዚአብሔርን ክብር ድብቅነት ያሳያል፤ ስለ መለኮታዊ ኃይልና ግርማ መገለጥ የሰው ልጅ ያለውን ግምቶቹንና ተስፋዎቹንም ይገዳደራል። ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የሚደረገውን የትኛውንም የሰው መንገድና ሙከራ ውድቅ ያደርጋል። ለሉተር ይህ ክፍል የእግዚአብሔር የመጨረሻ መገለጥ የሚገኘው በመስቀሉ ፓራዶክስ ውስጥ ነው የሚለውን ሀሳብ ያጠናክራል፣ በዚያም መንገድ መለኮታዊ ብርታት በድካም ፍጹም ይሆናል።


ሌሎቹ ሉተር በአግባቡ ተርጉሞ ላቀረበው ሙግት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የንባብ ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፡-


# ለቆሮንቶስ ሰዎች በተጻፈው የመጀመሪያው መልእክት 1፡18–25 — “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው።”


# ለፊልጵስዩስ ሰዎችል በተጻፈው መልእክት 2፡5–11 — ክርስቶስ በመስቀል ላይ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ በመሆን ራሱን አዋረደ።


#ለሮሜ ሰዎች ውበተጻፈው መልእክት 3፡21–26 — እግዚአብሔር በክርስቶስ መስዋዕትነት ኃጢአተኞችን ያጸድቃል።


#በማርቆስ ወንጌል እንደተሰጠው ትዕዛዝ  8፡34 — “መስቀሉን ተሸክመህ ተከተለኝ።”


የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ዘላቂ ጠቀሜታ


ሉተር ያስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ለሉተራን ቤተክርስቲያን ሥነ-መለኮት መሠረት የሆነ እና በብዙ የፕሮቴስታንት ወጎች ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳደረ አስተምህሮ ነው። በዚህም ክርስቲያኖችን የሚያስታውሳቸው፡-


መዳን የሚመጣው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን፤

የእግዚአብሔር ኃይል በድካም የሚፈጸም መሆኑን፤

የክርስቶስ መስቀል የክርስቲያናዊ ሥነ-መለኮት ሁሉ ማዕከል መሆኑን፤ እነዲሁም፣

የክርስቲያን ሕይወት በእምነት፣ በትህትና፣ በንስሐ እና በትንሣኤ ኃይልየተቀረጸ መሆኑን ነው


ባጭሩ ሲጠቃለል፤ 

ሉተር ያስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ማለት እግዚአብሔር በመስቀሉ በኩል ተሰውሯል ማለት ነው፥ በዚህም ምክንያት ሰብአዊ የሆነ በራስ የመተማመን አቅም ሁሉ፣ ስለ እግዚአብሔርም የሚነገሩ ሰው ወለድ ግምቶችና መላ ምቶች  ሁሉ ፍጻሜአቸውን እንደሚያገኙ ያሳያል። መስቀሉ በሰው ላይ የተላለፈ የፍርድ ምልክት ሲሆን በዚህም በራሱ የሚተማመን ሰብአዊ የሞራል ደረጃ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር አለኝ የሚለውን ኅብረት ግባአተ መሬት ይሰጠዋል። መስቀሉ በተፈጥሮው እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል እና ከእርሱ ጋር ባለን ሕብረት ባዘጋጀልን ሕይወት ውስጥ አብዝተን እና ከሁሉ አብለጠን የምንለማመደው የእግዚአብሔር መከራ ብቻ ነው።


ሉተር ባስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት እግዚአብሔር ጥልቅ ባህሪውን እንደሚገልጥ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይና ሞት መዳንን እንደሚያከናውን አብራርቷል። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በሰው ኃይል ወይም በሰባአዊ ክብር ከመፈለግ ይልቅ፣ የእግዚአብሔር መከራ ብለን በምናውቀው፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣  ምሕረት እና ጸጋ ተገናኝተው ባሉበት በተሰቀለው ክርስቶስ ውስጥ እና በኩል እግዚአብሔርን በእውነት እንዲያውቁና ወድቀው እንዲሰግዱለትና እንዲገዙለት ያደርጋል። ሉተርን፣ በርሱ የተመራውን የቤተክርስቲያን ተሃድሶ እና አጠቃላዩን የፕሮቴስታንት እምነት በወጉ ለመረዳት የመሰቀሉን ስነመለኮት መረዳት ያስፈልጋል።

ከወደዳቸ‍ሁት፣  ይጠቅመናል፣ ያንጸናል ካላችሁ ለሌሎች ማጋራት ኣትርሱ።


ቸር ሰንብቱ

No comments:

Post a Comment