በማቴዎስ 24 ላይ ጥቂት ነገር ልበል
የክርስቶስ ዳግም ምጻትና የአለም ፍጻሜን ጨምሮ በጥቅሉ የተፈጸመው ወንጌል ትምህርት የሚወሳበት philologus66 የተሰኘውን የፌስ ቡክ ገጽ እና በሎገሬን እየሰነበቱም ቢሆን በየጊዜው ፎሎው የሚያደርጉ ወገኖች መኖራቸውን ልብ ብያለሁ። ጥቁቶችም ቢሆኑ የተከታታዮቼ ትጋትም ለበለጠ ስራ አበረታች ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በገጼ ላይ ተሰድረው አንባቢዎችን የሚጠባበቁ በርካታ የነገረ ፍጻሜ ትምህርቶቼንና ዘለግ ያሉ ጥሁፎቼን፣ ከዚህም በኋላ በየደረጃው የማቀርባቸውን ክታቦቼን ለማንበብ እንድትታደሙ በድጋሚ ተጋብዛችኋል። ለዛሬ በየማህበራዊ ሚድያው ትንቢትን እየተርጎሙ የሚያሰተምሩ በርካታ ሰባክያን በሚከተሉት ልማዳዊ ስነ ሓቲት ሊያስተውሉት የማይችሉትን ወይም የማይፈልጉትን አንድ ጉዳይ በማቴዎስ 24 ላይ ጥቂት ነገር ልበል።
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ማቴዎስ 24 የሚያመለክተው በ33 ዓ.ም ከሆነው የመስቀሉ ታሪክ ጀምሮ በ70 ዓ.ም ላይ እስከ ደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋትና የቤተመቅደሱ ውድመት ድረስ ያለውን የ40 ዓመት ጊዜ ብቻ የሚሸፍን እንደሆነ አይረዱም፡፡ እውነታው ግን ያንን ብሩክ የእግዚአብሔር ልጅ ለመግደል አይሁድ የፈጸሙትን ወንጀል የሚመጥነው መለኮታዊ ፍርድ ጌታ ኢየሱስ በትንቢታዊ ቃል ያጸናውና በማቴዎስ 24 ላይ ከ40 አመታት በፊት ቀደም ብሎ የተናገረው አስፈሪ ትንቢታዊ ጥፋት በዚያው አንድ ትውልድ ውስጥ በ70 አ.ም ላይ መፈጸሙ ነው። በወራሪው የሮም ኃይል መሳሪያነት የተከናወነው የ70ው አ.ም ክስተት የዚያ አሰፈሪ ትንቢታዊ ፍርድ ታሪካዊ ፍጻሜ ነበር እንጂ ታሪካዊ አጋጣሚ ብቻ አልነበረም።
በመጀመሪያ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “የመምጣትህና የአለም (የዘመኑ) ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁት (ማቴ. 24:3)፣ በጌታ የተነገራቸውን አስደንጋጩን የቤተ መቅደሱን የመፍረስ ጉዳይ በአእምሯቸው ይዘው መሆኑን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። ያንን አይነተኛ ጥያቄ ሊቀሰቅስ የሚችል ብቸኛ ሰበብ ኢየሱስ ፍርጥም ብሎ “ይፈርሳል” ያለው የዚያ ቤተመቅደስ መጻኢ እጣ ፈንታ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተለየ እነርሱ ከሚያውቁት የገዛ ራሳቸው የዚያን ዘመን አለም በዘለለ ስለ አጠቃላዩ ፍጥረተ አለም ፍጻሜ ሃሳብ ሊገባቸውና ሊያስጨንቃቸው የሚያስችል ምንም የተለየ ምክንያት አልነበራቸውም። ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስ አሰረግጦ ነግሮአቸው ነበርና (ማቴዎስ 24:2)።
የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ሰበቡና ምንጩ ከየት እንደሆነ የማይታወቅ፣ ፈጽሞም የሌለና ሊኖር ወይም ሊሆን የማይችል፣ ወደፊት በቅርቡ ወይም በርቀት ይሆናል ብላ የምታስበው የዚህ ግዑዝ አለም ፍጻሜ ይደርሳል ስትል ታስባለች ታስተምራለችም። ለዚህም መጽሓፍ ቅዱስዋን በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ ፖለቲካ አዙሪት ወይም በዓለም ኃያላን መንግስታት የፖለቲካ ጡዘት መነጽር አጮልቃ እያየች ትንቢትን ለመተርጎም ባላት ሙከራ መንገዷን ስታለች። እንዲህ ያለው መረዳት ግን በደቀመዛሙርቱና በጥንት ቤተክርስቲያን ዘንድ ያልነበረ፤ እንዲህ ያለው የዓለም ፍጻሜም የሚያሳስባትም የምትጠብቀውም ያልነበረ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ የዘመናችን ግራ ገብ መምህራን እና ሰባክያን መገለጫ ነው።
በማቴዎስ 24 ላይ መሰራት ያለበት ዋና ስራ፣ ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውና በምዕራፉ የተባለው ነገር ሁሉ እነርሱ ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጣቸው ምላሽ መሆኑን አጥርቶ ማየት ነው። የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄና የጥያቄው ምግፋኤ የሆነውን መሰረታዊ ምክንያት መረዳት ያልቻለ ተርጓሚ ነኝ ባይ የመምህሩን መልስ ሳያሰተውል አጥርቶ የማያውቀውን ነገረ ትንቢት ላስተምር እያለ ዘባርቆ ሌሎችን ያስታል። እርግጥ ነው፥ ጌታ ኢየሱስ ስለ ብዙ ነገር ነግሯቸዋል፤ ጥያቄው ግን የነገራቸው ነገር ሁሉ ለእነርሱ (ለበኩረ ተደራሲያኑ) ምን ማለት ነበሩ የሚለው ነው (ጦርነቱ፣ የጦርነቱ ወሬ፣ ሕዝብ በህዝብ ላይ መነሳቱ፣ ራቡ፣ ቸኑፈሩ፣ የምድር መናወጡ፣ የሰማዩ ላይ ምልክት፣ ወንጌል በአለም ሁሉ መሰበኩ፣ ወዘተ…)።
የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ የሚያጠነጥነው በታሪክ ዘመን ሁሉ ስለሚከሰቱና ገና ወደፊትም ስለሚከሰቱ ጉዳዮች ነበር ብሎ ማሰብ በእውነቱ እማይመስል ነገር ነው። በአእምሯቸው ውስጥ “አለማቀፋዊ ጉዳዮችን” እና “በታሪክ ዘመን ሁሉ የሚከሰቱ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን” ይዘው እንደጠየቁ አስቦና በዚህ እሳቤ ላይ ቆሞ “መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት” መረመርኩ ብሎ ትንቢትን ለመተርጎም መሞከር ውሎ አድሮ ለገዛ ራስም ሆነ አሰተውሎ ለሚሰማ መሰቅጠጡ አይቀርም።
ለደቀ መዛሙርቱ፣ የዚያ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መፍረስ እንደ አንድ ታላቅ ነውጥ እና ጥፋት ወይም የመላው ሃይማኖታዊ/ፖለቲካዊ ዓለማቸው ፍጻሜ አድርገው ያዩት ነበር እንጂ እንደዘመናችን ‘የትንቢት ሊቀ ጠበብት’ ነን ባዮች ስለ ግዑዝ አለም ፍጻሜ እሳቤውም አልነበረባቸውም። ስለዚህም አስቀድሞ በትንቢት “የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል።” (ኢሳ. 66: 6) እንደተባለ፣ የዚያን ቤተ መቅደስ መፍረስ እና የከተማይቱን ውድቀት ከመሲሑ የመጨረሻ መምጣት እና ከዘመኑ ፍጻሜ ጋር አገናኝቶ ማየታቸው በህጉና በነቢያት የተነገረ ስለሆነ መሆኑን እናስተውላለን። ጠያቂዎቹንና ለጥያቄአቸው ምላሽ የሰጣቸውን ነቢዩ ኢየሱስን በህጉና በነብያቱ ከተነገረው ቃል አውድ አውጥተን በአለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካና የሃይማኖት ስንክሳር አውድ ውስጥ እንደመፈለግ ያለ ግራ የገባው ስነ መለኮት አይግጠማችሁ።
ተመልከቱ፣ ኢየሱስ “ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ” (ማቴ. 24:24) ብሏቸዋል። የብዙ አስመሳዮችና ሃሰተኞች መነሳት የመጨረሻው ዘመን መድረሱን የሚያሳይ አይነተኛ ምልክት ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስም ይህ ያኔ ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ እየተፈጸመ መሆኑን ተረድቶ ስለ ነበር፣ “ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።” (1ኛ ዮሐንስ 2:18) ሲል ይጽፋል። ዮሐንስ በዚህ ጥቅስ ላይ ለአንባቢዎቹ “ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” ስለተነሡ “የመጨረሻው ሰዓት” (የመጽሐፍ ቅዱስ የአይሁድ እምነት የመጨረሻ ሰዓት) መሆኑን ማወቅ እንደሚችሉ በግልጽ ይነግራቸዋል። በሌላ አነጋገር፣ ኢየሱስ ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት በመጨረሻው ዘመን እንደሚመጡ ስለተናገረ፣ ዮሐንስና ሌሎች ክርስቲያኖች ፍጻሜው ያኔ በእርግጥ እንደቀረበ ያውቁ ነበር፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ አሳቾች አስቀድመው ያኔውኑ ታይተው ስለነበር ነው።
ጨምሮም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፣ “ይህ የመንግሥት ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” (ማቴ. 24:14)። ደቀ መዛሙርቱ ‘መቼ ነው’ ሲሉ የጠየቁት መጨረሻና ኢየሱስ ‘ይመጣል’ ያለው መጨረሻ አንድ መጨረሻ ነው፤ እርሱም ወንጌል ለአህዛብ ሁሉ ከተሰበከ በኋላ በገዛ ትውልዳቸው ውስጥ የሚመጣ የዚያ ዘመን ወይም አለም መጨረሻ ነው። የዚህን ፍጻሜ ማወቅ ብትሹ፣ የሮሜ መጽሐፍና የቆላስይስ መጽሐፍ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በተጻፉበት ጊዜ የምሥራቹ ወንጌል ያኔ በነበረው ዓለም ሁሉ ተሰብኮ እንደነበር ሓዋርያው ጳውሎስ በግልጽ መናገሩን ታስተውላላችሁ። ሮሜ 10: 18 ላይ፣ “ድምፃቸው (የምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች ድምፅ) ወደ ምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም (የስብከታቸው ቃል) እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ወጣ።” ይለናል፤ ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአለም ዳርቻ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ወሰኑን አስበን ካላነበብነው በትርጉማችን ልንስት በአስተምህሯችንም ልናሳስት እንችላለን። በቆላሰይሰ. 1: 23 ላይ ደግሞ፣ “ይህ…ወንጌል… ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል።” ሲል አስረግጦ ይናገራል። የሮሜ ሰዎች እምነት ያኔ ገና በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዚያን ዘመን በነበረው የሮም ዓለም (በመላው ዓለም) የተወራ እንደ ነበረ ዻውሎስ ሲመሰክርና በዚህ ምክንያት ሰለሁላቸው እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ነገሩን እያጋነነ አለነበረም (ሮሜ 1፡ 7)። ስለዚህ ያኔ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ወንጌል በዓለም ሁሉ ተሰብኮ ከነበር እንግዲያውስ ከዚያ አለማቀፋዊ የወንጌልና የሚስዮን ስራ መጠናቀቅ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በመጣበት ፍርድ የአሮጌውን ኪዳን ዓለም ፍጻሜ ሰጥቶታል፤ ይኸውም በ70 ዓ.ም ላይ የክርስቶስ ጠላቶች የሆኑትን ክርስቶስንና ቤተክርስቲያኑን እስከ ጥግ ድረስ በጽኑ መከራ ያሳደዱትን ትውልዶች በዳግመኛ ምጻቱ ሲያጠፋቸው በእሳት ፍርድ የመጣበት ምጻቱ ነው። ከዚህ ሌላ የሚጠበቅ ምጻት ሁሉ አዲስ ኪዳን የማያስተምረው ባዶ ተረትና እንግዳ ትምህርት ነው።
በመጨረሻም፣ በማቴዎስ 24 ላይ፣ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ አያልፍም” ብሏል። “ይህ ትውልድ” የሚለው ቃል እዚህ ላይ በአብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ሌሎች ቦታዎች ላይ እንደሚናገረው ያው ተመሳሳይ ነገር ማለት ነው። ያኔ ይህ ሲነገር ቆመው ይሰሙ የነበሩትን ቀጥተኛ አድማጮቹን የትውልድ ዘመን ያመለክታል እንጂ እነርሱ ከነበሩበት ዘመን ወጭ በተለየ ሌላ ዘመን የሚኖሩትን ማናቸውንም ወይም እኛ ያለንበትን ትውልድ ወይም ገና የሚመጣ ሌላ ትውልድ አይመለከትም። የትንቢቱ ቃል በግልጽ በዚያን ጊዜ ስለሚኖሩት ሰዎች ብቻ ይናገራል። ይህ ትውልድ የሚለውን ያ ትውልድ ብሎ እንደማንበብና መተርጎም ያለ ድርቅና (ግግምና) ሌላ የሚገርመኝ ነገር የለም። ስለዚህ የማቴዎስ 24 በሙሉ በመስቀሉና በኢየሩሳሌም ጥፋት መካከል ባለው የአርባ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሆነውን አካቶ ይዟል፤ ፓሩሲያውንና የዘመኑን ፍጻሜ ጨምሮ ሁሉ ተፈጽሟል።
በልማዳዊው የመጻአኢነት ሸውራራ መነጽር የዘመን ቆጣርያንን ትርጉም እያየ፣ በቃሉ መንፈስ ሳይሆን በመካከለኛውን ምስራቅ የጂኦ ፖለቲካ ትኩሳት እየጋለ፣ በክርሰቲያናዊ ጽዮናዊነት ፈረስ የሚጋልበው ስነ ፍታቴ መጨረሻው መጽናናት በማይገኝበት የደነበረ የሸብር ወንጌል ተመርቶ ምህዋሩን ስቶ ገደል መግባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ፊት ስለሚመጣ አለማቀፋዊ ክስተት የሚናገር የንግርት፣ የሟርትና የጥንቆላ መጽሐፍ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ፈቃድ ያልመጣ፣ ሰለ እኛ የተጻፈ እንጂ በቀጥታ ለእኛ ያልተጻፈ ትንቢት ነው። ትንቢትነቱም ለእኛ ሳይሆን ለገዛ ራሱ በኩረ ተደራስያንና ለታሪካዊ አውዱ ነው። መጠናትም መተርጎምም ያለበት በዚያው አውድ ማዕቀፍ ውስጥ ነው። አውድ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥናት ንግስቲቱ ናት፤ ለእርሷም ዋጋ የማይሰጥና ይሄንን መርህ ያላከበረ ተርጓሚና የትንቢት አሰተማሪ በግራ ገብ ልዩ ወንጌል ስብከቱ ታዋቂነትን እንጂ እውቀትን አያተርፍም።
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ዘርዘር ያለ ማብራሪያን ለማግኘት ፍላጎቱ ያላችሁ የሚከተሉትን የብሎገር ማሰፈንጠሪያዎች እየከፈታችሁ ብትመለከቱ በማቴወሰ 24 ላይ በተከታታይ የቀረበ ትምህርት ታገኛላችሁ።
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_60.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_33.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_91.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_95.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_32.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_93.html?m=1
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_43.html?m=1
ግዛቸው።
No comments:
Post a Comment