Sunday, August 24, 2025

ለምን ፕሪተሪስት ሆንኩኝ?

ለምን ፕሪቴሪስት ሆንኩኝ?


የተፈጸመውን ወንጌል የተቀበልኩት ያለ ምክንያት አይደለም!!


የመጻኢነትን ጎራ በይፋ ለቅቄ ለምን ፕሪቴሪስት ሆንኩኝ? እንዲህ ያለ ትለቅ ውሳኔ ለመወሰን እና የአቋም ለውጥ ለማድረግ ያስቻሉኝ የማላስተባበላቸውን ምክንያቶቼን ማካፈል እንዳለብኝ ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል። ፈራ ተባ እያልኩ ለብዙ አመታት በተደከመበት የመጽሓፍ ቅዱስ ጥናት ልምምዴ አስቀድሞ “የጌታ ምጽአት ቀርቧል” እያልኩኝ ሳምነው እና ሳስተምረው የኖርኩትን አቋሜን እየተፈታተነ፣ አንዳንድ ጊዜም አለኝ የምለውን ተስፋ ከእጄ ላይ እያራገፈ ጡጦውን እንዳስጣሉት ህጻን ነጭናጫና ብስጩ ያደርገኝ የነበረውን የነገረ ፍጻሜ እውነት የሄ ደግሞ ምን ያመጥብኝ ይሆን ከሚል ስጋት ጋር ስጋፈጥ ኖሬአለሁ። ሳምነው ከኖርኩት ልማዳዊ የትምህርት ቀንበር ለመላቀቅ እና ቃሉ ብቻ በሚናገርለት እውነት ላይ ቆሞ ለመገኘት፣ በዚህ ሁሉ አድካሚ ጉዞ ውስጥ በነገረ ፍጻሜ አቋሙ የፕሪቴሪስት ምልከታ ብቻ ትክክለኛውና ተገቢው የመጽሓፍ ቅዱስ ፍቺ መሆኑን ስቀበል በግሌ “አናት ፈጥፍጥ” “ደብረ በጥብጥ” ሆኖብኝ አልፌዋለሁ። እውነት ከቀንበር ይከብዳል፣ ሲመጣም ብዙ ነውጥ እና መንቀጥቀጥ ስለሚፈጥር ያስፈራል፤ ፍሬውና ውጤቱ ግን ከማር ይጣፍጣል። ከህሊናዬ ጋር በመቆም የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ድጋፍ ያለውን ፕሪቴሪዝምን የእምነት አቋሜ አድርጌ ለመውሰድ፣ አስተምህሮዬንም በዚህ መስመር ለመቅረጽና ዘመኔን ሁሉ ለምቦጬ ላይ ተወትፎ ስጠባው ከኖርኩት የልማድ ጡጦ ለመላቀቅ የነበረብኝ ፈተና ቀላል አልነበረም። ምናልባትም እኔ እንደያዝሁት ያለ አይነት የእምነት አቋም ያላቸውን የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች አንድና ሁለት እንኳ ማግኘት በማልችልበት ወቅት ከብቸኝነቱ ፈተና ጋር ከማን ጋር ላውጋው፣ ማንስ ስራዬ ብሎ ሊሰማው ይችላል የሚል ጥያቄና፣ ከወገኞቹ ወዳጆቼ ዘንድ ሊፈጠርብኝ ከሚችል የመገለል ስጋት ጋር መታገል ነበረብኝ። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን በማመኔ ያጋጠመኝ ከባድ ችግር ነበር ብዬ ለመናገር ባልደፍርም ከተቋምም ሆነ ከግለሰቦች ሊሰነዘርብኝ የሚችል በትር እንደሚኖር ግን አላጣሁትም። እንደውም አንድ ወንድም የእግዚአብሔርን ደግነት አንስቶ ሲያወጋኝ፣ “እንኳንም ከዚህ እምነትህ ጋር ከአገር ወጣህ፣ እዚህ ብትሆን ኖሮ ይሰቅሉህ ነበር” ብሎ አስቆኛል። እኔም “ምን፣ መሰቀል ብርቅ ነው እንዴ? እንኳን እኔ አንድ ጭንጋፍ ቀርቶ የልዑል ልጅ የሆነውም ተሰቅሏል” ብየ መመለሴን አስታውሳለሁ። ዛሬ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ርዕሰ ጉዳዩን ዋጋ ሰጥተው የሚሰሙ፣ ሊማሩም የሚወዱ፣ እምነታቸውን አፋጠው የሚጠይቁ፣ ሲያምኑት የኖሩትን የትምህርት ድሪቶም አውልቆ ለመጣል የሚደፍሩ ጥቂት ያይደሉ የቃሉ ወዳጆችን ተዋውቄአለሁ። ቢያንስ ከነርሱ ጋር እጽናናበታለሁ። እህ ብለው ሊሰሙና ሊማሩ የሚወዱ ከተገኙም በልብ ስፋት የማካፍለው የተፈጸመው ወንጌል አለኝ። በዚህች አጭር ክትባት ፕሪቴሪዝምን ትክክለኛው የነገረ ፍጻሜ አቋም እና የተፈጸመው ወንጌል ትምህርት ነው ብዬ እንደቆምኩ የማሳይበትን ጥቂት ምክንያቶቼን በወፍ በረር ላካፍላችሁ፤ ምናልባትም በወገኖች መካከል የሰከነ ውይይት እንዲኖር መንደርደሪያ ነጥቦች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፦



  1. ሳዳምጣቸው የኖርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች እኔ በትንቢት ቃል ላይ ለተፈጠሩብኝ ፈታኝና መሰረታዊ ጥያቄዎች አንጀት አርስ የሆነ፣ አመክንዮአዊ ትርጉም ያለው መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም። እንዲያውም ርእሰ ጉዳዩ ሲነሳ፣ ይባስ ብለው ለእውነት ቃል ብዙም ፍላጎት የሌላቸው አይነት ይመስሉ ነበር። ከዚያ ይልቅ ግን ያንንው የኖረ የቤተክርስቲያን ልማዳዊ አመለካከትና አቋም በተሳሳተ ስነ ሃቲት ለመከላከል የበለጠ ፍላጎት ይታይባቸው ነበር። እነርሱ አውድ ዘለል በሆነ ስነ ሃቲት የሙጥኝ ብለው ከያዙት ዳተኝነታቸው ጋር መቀምጥን በመረጡ መጠን እኔ ደግሞ ከጥያቄዎቼ ጋር መቆየትን አልፈለግሁም። መልስ እሻ ዘንድ ብዙ ደከምሁ። መከተልም ያለብኝ እንደ እኔ በጎች ብቻ የሆኑትን ሳይሆን ራሱን የበጎቹን እረኛ ለመከተል እፈልግና አዘነብል ነበር። ፍላጎቴም ለእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነት መወገን እንጂ ለኖርኩበትና ላደግሁበት ተቋም መወገን አልነበረም። መልሴን ያገኘሁት በዚህ መስመር ነው። 
  2. እንደ ቃሉ ወዳጅ እና ተማሪ በተለይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለትንቢት ፍጻሜ ቀነ ቀጠሮውን በሚያመለክቱበት ልክ በግልጽ የተቀመጡትን ጊዜ አመልካች የሆኑ ምንባባትና ጥቅሶችን “ባላየ ማለፍም” አልሆንልኝም። በበዛ መቀመጥ ቃሉን እያጠናሁ ሳለ እነዚያ በትንቢት የተነገሩ ክንውኖች ለፍጻሜአቸው የተመደበውን ጊዜ በተመለከተ፣ ራሳቸው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በሕይወት በነበሩበት ዘመንና በትውልዳቸው ውስጥ የተገደቡ መሆናቸውን የሚያመለክቱ በቁጥር ከ100 በላይ የሆኑ ጊዜ ተኮር ንግግሮችን ምንም ሳልቀባባ እንዳለ ለመውሰድ በጎ ሕሊና ይኖረኝ ዘንድ ተግቻለሁ። ምክንያቱም እግዚአብሔር አንድን የሚፈጸም ኹነት ሲናገር የሚፈጸምበትንም ጊዜ የሚናገር የታመነ አምላክ ነው። ፊት ለፊት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ከ100 በላይ የሚቆጠሩ የኢየሱስና የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ጊዜ ተኮር ንግግሮች ችላ በማለት ድንቁርና ውስጥ እንዳልወድቅም ጸልያለሁ።
  3.  “የመጨረሻውን ቀን” ወይም “የዘመን ፍጻሜን” አስመልክቶ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ቋንቋ የተነገሩ ከአሥራ አምስት በላይ የሆኑ ልዩ ጥቅሶች አውደ ምንባባቸው ላይ የፍታቴ ጥሰት እና ድፍጠጣ ሳይፈጸም መቼታቸው ሲመረመር በመለኮት የተያዘላቸው የፍጻሜ ቀነ ቀጠሮ ከመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን በላይ የሚሻገር እና ሁለትና ሶስት ሺህ አመት የሚጠበቅ ፍጻሜ እንደሌላቸው የሚያመለክቱ መሆናቸውን ተረድቻለሁ። ስለዚህም አሁን በእኛ ዘመን ወይም ከእኛ ዘመን በኋላ በቅርብ ወይም በርቀት ላለ የዘመን ቁጥር የተቀጠረ ምንም የትንቢት ፍጻሜ አለመኖሩን የልቁንም የትንቢት ፍጻሜ ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እስራኤል እና ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተገንዝቤአለሁ።
  4. ታሪክን በወጉ እንደማላውቅ፣ ይልቁንም በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ላይ ስለተከሰተው ነገር፣ እነዚህም ክስተቶች ከትንቢት ፍጻሜ አንጻር መታየት እንዳለባቸው የያዙትንም ሥነ-መለኮታዊ ፋይዳና ጠቀሜታ በአግባቡ እንደማልረዳው የገባኝ አርፍጄ ነው። ታሪክንም ለማንበብ እድሉንና አጋጣሚውን ባገኘሁ መጠን እምነቴን የሚያስጥለኝ እየመሰለኝ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ እገባ ነበር። ምናልባትም ኤን.ቲ.ራይት “አብዛኛው ክርስቲያን ታሪክን ይፈራል፣ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የሆነውን ነገር በትክክል ካወቅን እምነታችን ተንኮታኩቶ ይወድቃል ብሎ ይፈራል።” ሲሉ እንደተናገሩት ሳይሆን አይቀርም። እኔም ጌታ ኢየሱስ በየሩሳሌምና በጠቅላላው በዚያ አሮጌ ስርዓት (sistem) ላይ ፈጥኖ ሊደርስ ስላለው ጥፋት የተናገረውን ትንቢት ከዚህ ታሪካዊ ፍጻሜው ለይቶ የማየት ነገር ልማድ ያቀበለኝ ኣባዜ ነበርብኝ። አሁን ግን ከብርድ የማያስጥለኝን ይህን ድሪቶ አውልቄ ጥየዋለሁ።
  5. የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በሙሉ ማለት በሚቻልበት መልኩ ፍጻሜአቸውን የሚያገኙት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በኖሩበት በራሳቸው ትውልድ ማለትም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እንደሆነ ስረዳ በእውነቱ ድንጋጤዬና ያሳለፍኩት ይህንን ያለማወቅ ወራት በተመለከተ የተሰማኝ ኃፍረት ልክ አልነበረውም።
  6. ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ራሳቸው ዘመን እና በትውልዳቸው ውስጥ እንደሚፈጸሙ በተነገሯቸው ትንቢታዊ ክንውኖች፣ ጊዜውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ተሳስተው ከነበረ እንግዲያውስ ኢየሱስም ሐሰተኛ ነቢይ፣ ደቀ መዛሙርቱም ሐሰተኛ ምስክሮች ናቸው በሚል በከሃዲዎችና በማያምኑ ሊቃውንት በክርስትና ላይ የሚቀርበው ክስና ትችት ልክ ነው ማለት ነው። እንዲህ ያለውን የተቺዎችን ክስና ነቀፋ በብቸኝነት መከላከል የሚቻለው እና ለተቃዋሚዎች ብረት መዝጊያ የሆነ መልስ ለመስጠት አቅም ያለው የፕሪቴሪስት እይታና መረዳት ብቻ ነው። ፕሪቴሪዝም በሚያቀርበው የትንቢት ትርጉም ብቻ ኢየሱስ ቃሉን እንደጠበቀ፥ ሐሰተኛ ነቢይም እንዳልሆነ፣ እመለሳለሁ ባለበት ጊዜም ተመልሶ እንደመጣ ማስረገጥ ይቻላል። አዎ፣ ፕሪቴሪዝም በሚሰጠን ብርሃን ብቻ፦ “ቃሉን ከቶ የማያጥፍ ታማኝ አምላክ ነውና፣ የነገረንን ሁሉ ፈጽሞት አይተናልና፥ ከፍ ከፍ እናደርገዋለን በምስጋና” ብለን መዘመር እንችላለን። ከዘላለም ከአብ ጋር የነበረ ቃል የሆነ እርሱ የመመለሻው ጊዜ በገዛ ራሱ ትውልድ መሆኑን አስረግጦ መናገሩን በምንም ልናስተባብለው የማይቻለን ያፈጠጠ እውነት ነው። እርሱ ለተናገራቸው ለነዚህ ቃላት ምንም አይነት ሰበብ እና ማመካኛ አቅርበን ቃሎቹን በማስተካከል ፈተና ውስጥ አንገባም። እነዚያን ፈታኝ እና አዕምሮን ወጥሮ የመያዝ አቅም ያላቸውን ቃላት እና አንቀጾችም ላይ ምንም አይነት “ምሁራዊ” የደናቁርት ማመቻመች አናደርግም። ለዘላለም ሕይወት ያመነውን ጌታ የመመለሻውን ጊዜ አስመልክቶ ተሳስቶ ነበር የሚለውን አጉል የምሁራን ድምዳሜም አንታገስም።
  7. ስለ መጨረሻው ቀን ምልክቶች፣ “ጨረቃ ወደ ደም ይለወጣል”፥ “በደመና የሚመጣ”፣ “የሰማያት ሃይሎች ይናወጣሉ” ወዘተ የመሳሰሉትን ንግግሮች በተመለከተ ቋንቋዎቹን በጥሬው ተርጉሞ መረዳት እንደሚገባ በርካታ ክርስቲያኖች ሲከራከሩ አድምጫለሁ፤ እንዲህ ያለ አቋም ከያዙቱ መካከል አንዳንዶቹ ብዙ ተምረዋል፣ መጻህፍትም አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል፣ በየመድረኩም ዝናን ያተረፉ ሰባኪያንና መምህራን ናቸው ከሚባሉት መካከል ይቆጠራሉ። አለማፈራቸው ያሳፍረኛል። የጠቀስኳቸውን እነዚህንና መሰል የኮስሞሎጂ ነውጥ አመልካች የሆኑ ሀረጎች እና ቃላት እንዳለ በጥሬው እና ቃል በቃል በሆነ ይዘታቸው መተርጎም የሚገባቸው በመሆን አለመሆን ላይ ሁል ጊዜ ስጠራጠር እና ስጠይቅ ኖሬአለሁ። የእግዚአብሔርን ቃል የንግግር ዘይቤዎቹንም በጥልቀት ለመረዳት ባደረግኩት ጥናት ይህ ጥርጣሬዬ ተገቢ መሆኑን አረጋግጫለሁ። እንደነዚህ ያሉት ሐረጎች በታሪክ ውስጥ በከተሞች ላይ ወይም በልዩ ልዩ ሕዝቦችና መንግስታት ላይ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት፥ ይኸውም ፍርዱ ማለት ነው፥ ያንን የፍርድ አሰራር ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለ በጥሬው የማይተረጎም ትዕምርታዊና ምሳሌአዊ የሆነ የዕብራይስጥ አቡቀለምሲሳው የስነጽሁፍ ዘይቤ ንግግሮች ናቸው።
  8. መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ገጹ ላይ ስለዚህ ተዳሳሽ ግዑዙ አጽናፈ ዓለም ወይም ስለ ፕላኔት ምድር ፍጻሜ ምንም እንደማይናገር ተገነዘቤአለሁ። በእርግጥም ይህ ግዑዝ አለም ያልፋል የሚልን ትምህርት በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ አምጥቶ የሰነቀረው የኖረ ልማዳዊ የቤተክርስቲያን አመለካከት ነው እንጂ እንዲህ ያለው ርዕሰ ጉዳይ በቃሉ ውስጥ ፈጽሞ ምንም መሰረት የለውም።  
  9. ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ በየዕለቱ በሚወጡት ትኩስ የዜና ክንውኖች መነጽር፣ በተለይም የመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ ፖለቲካ ወጥረት ላይ አይናቸውን ተክለው የማንበብና የመተርጎም ዝንባሌ እንዳላቸው አስተውያለሁ። ከዚህም የተነሳ ላለፉት 2,000 ዓመታት ያህል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ዓለም ፍጻሜ የለየለት ውሸትና በርካታ አሳፋሪ ትንበያዎች ሲነገሩ ቆይተዋል። እጅግ ከማከብራቸውና በተለያዩ ስራዎቻቸው ከተጠቀምኩባቸው አስደማሚ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና በታሪክ ሰመ ጥር ከሆኑቱ መካከል አንዳንዶቹ በዚህ ጉዳይ የፈጸሙት ስህተት ታሪክ በትዝብት ሲያወሳው ይኖራል። በምትኩ ግን ቃሎቹን በዋናዎቹ በኩረ ተደራሲያን አውድ መነፅር የሚያነቡ ቢሆን ኖሮ ስለሚያነቡት የትንቢት ቃል የተለየ ሥዕል ባገኙ ነበር። ስለዚህ ከመጽሓፉ ትንቢት ተነስቶ የአለምን ፖለቲካ እና ዘመናዊ ክስተቶችን መተንተን እንደማይገባ ሁሉ፤ ከአለም ፖለቲካና ከዘመናዊ ክስተቶች እየተነሳን የመጽሓፍ ቅዱስን ትንቢት ብንተረጉም ተመሳሳይ ስህተት ይሆናል። ቃሉ ራሱን እንዲተረጉም አውደ ምንምባቡ መጠበቅ አለበት።
  10. ከመቶሰላሳ በላይ የሆኑ የስነ መለኮት ሊቃውንት የራዕይ መጽሓፍ የተጻፈው ከ70 ዓ.ም በፊት እንደሆነ በማስተማር ይታወቃሉ። የራዕይ መጽሓፍ ቀደም ባለው ጊዜ ይኸውም ከ70 ዓ.ም በፊት ተጽፏል የሚለው እይታ አዲስና እንግዳ ግኝት አይደለም። የራዕይ መጽሓፍ በአብዛኛው የሚያወሳው ከ66-70 ዓ.ም በአይሁድ-ሮማውያን ጦርነት ወቅት በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ስለደረሰው ጥፋት መሆኑን ስንረዳ ትንቢቱ የሚያወራው ስለ አለም ምጨረሻ ሳይሆን እግዚአብሔር ያንን ጦርነት ተጠቅሞ እስራኤልን እንደሚያጠፋት፣ ይህም ከመሆኑ 5 እና 6 አመታት ቀደም ብሎ የተነገረ ትንቢት መሆኑን እናስተውላለን።
  11. በራዕይ መጽሓፍ ውስጥ (ሀ) ራዕዩ ከተፃፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቶሎ ፍጻሜውን የሚጠይቅና የሚጠበቅ ጉዳይ እንዳለ፣ እንዲሁም (ለ) የራዕይ መጽሓፍ አዲስና እንግዳ ጽንሰ-ሀሳቦችን እንደማያስተዋውቅ፥ ይልቁንም እነዚያ ይሆናሉ ተብለው የተገለጹትን ክስተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ቦታ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ መሆናቸውን የሚያስረዱ ከ30 በላይ ምንባቦች ያሉ እንደሆነ አስተውያለሁ።
  12. በፕሪቴሪዝም ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች ምንም ጥልቀት የሌላቸው፣ መያዣ መጨበጫቸው የማይታወቅ፣ አድሏዊነት እና ወገንተኝነት የተጠናወታቸው፣ በዘፈቀደ ትርጉም የሚለፈለፉ እና ወጥነት የሌላቸው መሆናቸውን አስተውያለሁ። ፕሪቴሪዝምን እንቃወማለን የሚሉ ሰዎች በሚያቀርቡት ትችት በአመዛኙ ሆነ ብለው ቁልፍ የትንቢት ምንባባትን ሲያጣምሙ ይስተዋላሉ። እውነታን ላለማየትም አይናቸውን አሳውረዋል፥ ስለጉዳዩም ተገቢውን ምርመራ ሳያደርጉ በአብዛኛው ሲናገሩ የሚደመጠው ጉዳዩን በትክክል ካላጠኑ ሰዎች የሰሙትን ነገር እንደ በቀቀን ሲደግሙ ነው። የደብረ ዘይቱን ፍካሬ አንድ ምዕራፍ ለማንበብ አቅምና ጊዜ የሌለው ሰው አስቦበት እንኳ በማያውቀው የነገረ ፍጻሜ ረዕሰ ጉዳይ አዋቂ ተናጋሪ ሆኖ ሲቀርብ ያሳፍራል። 


እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ለፕሪቴሪዝም አስተምህሮ ፍላጎት እንዳሳይና አመለካከቴን፣ እምነቴንና አስተምህሮዬን እንዳርም ምክንያት የሆኑኝ ነጥቦች ናቸው። ለኔ ታላቅ መጽናናትን ያጎናጸፈኝ የተፈጸመው ወንጌል ለሌሎችም እንዲሁ እንዲሆንላቸው ከመጸለይ፣ ለሚጠይቁኝም መልስ ለመስጠት ዘወትር እየተዘጋጀሁ በእግዚአብሔር ቃል ከማስረዳት በቀር ምንም ፍላጎት የለኝም። ብትወዱ ጉዳዩን ትመረምሩና የህሊናችሁን ፍርድ ትሰጣላችሁ እንጂ በጌታ ወንድማችሁ ከመሆን ጸጋ አታቅቡኝ። ደግሜ እላለሁ ባነሳኋቸው ጉዳዮች ምክንያታዊነት የምትበሳጩና ቁጣ የሚሞላባችሁ ብትሆኑ፣ ወይም ቃሎቼ ቢያስፈራችሁ እና ተስፋ ቢያሳጣችሁ አልያም ይሄ ደግሞ ምን ይቀባጥራል ብትሉ፥ ምክሬ ግን አንድ ነው፤ በተቻላችሁ መጠን ኢ-ምክንያታዊ ከመሆን ተቆጠቡ። ጉዳዩን በራሳችሁ አይን ከቃሉ እስክታዩት ድረስ እባካችሁ የኔን ቃል እንዳለ አትውሰዱት፤ ሰነፍ ፈራጅም አትሁኑ። አስቀድማችሁ ግን በዚህ አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተገቢውን የቤት ስራችሁን ስሩ። እኔም በጉዳዩ ላይ ምን ያህል ጊዜ ወስጄ እንዳሰብኩበት የሚያሳዩአችሁን የተለያዩ ጥሁፎቼን ታዩ ዘንድ ብሎገሬን ለመጎብኘት አትታክቱ፤ መክፈቻው እነሆ 


http://gizachewkr.blogspot.com/2025/02/blog-post.html


ይህንንም ሆነ ማናቸውንም ጽሁፎቼን ሌሎች ይማሩበትና የጠቀሙበት ዘንድ ላይክ እያደረጋችሁ ልታጋሩት ኮፒ አድርጋችሁ ልትይዙት፣ አስተያየታዊ ትችቶቻችሁን እና ሙግቶቻችሁን እያቀረባችሁ ልትጠይቍ መብታችሁ ነው።

 ግዛቸው።




From Blogger iPhone client

No comments:

Post a Comment