Friday, December 27, 2024

የአህዛብ ዘመን ተፈጽሟል


የአሕዛብ ዘመን ተፈጽሟል!!


ኢየሱስ የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም ትረገጣለች በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ይህ ጉዳይ ምንድን ነው? ወይስ ምን ነበር?  ከዚህ በኋላስ ይህ የአሕዛብ ዘመን መጨረሻው ወደፊት ቅርብ ነውን?


ሉቃስ 21፥ 23-24 “በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።”


የአህዛብ ዘመን የጀመረው፣ የሚፈጸሙውስ መቼ ነው? የአህዛብ ዘመን የጀመረው ባቢሎን ኢየሩሳሌምንና ይሁዳን ስትቆጣጠር እንደሆነ ዘመን መዳቢዎች (Dispensationalists) ሊነግሩን ይሞክራሉ።  ከእነርሱም መካከል አንዳንዶች ደግሞ የአሕዛብ ዘመን በ1967 ዓ.ም ላይ እንዳበቃ ይናገራሉ። ዘመነኞቹ ደግሞ ገና ወደፊት የሚያበቃ ነው ይሉናል። የቃሉ አማኝና ተማሪ ነኝ ባይ ማንም ሰው ቢሆን፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል እና በጥቅሉ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተገለጠው ትምህርት  ነጥሎ ሊተረጉምም ሆነ ክፍሉ ከተነገረበት መጽሐፍ ተፈጥሮ በተለየ ሊረዳው  እንደማይቻልና እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልገዋል።  ምንም ቢሆን ከመፅሃፍ ቅዱስ የተወሰደ የትኛውም ምዕራፍ ምንባቡ ከተወሰደበት ክፍል ተነጥሎ ሊተረጎምም ሆነ ሊብራራ አይችልም። እንዲሁም የትኛውንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ወይም ምዕራፍ አስቀድሞ በተደረሰበት ቅድመ ግንዛቤ፣ ወይም ሲነገረንና ሲመስለን በኖረው ቅድመ እሳቤ ፣ ወይም ብዙሃኑ በተቀበለውና በተለመደው የአተረጓጎም ዘዴ ተርጉሞ ማቅረብ አይቻልም። ቃሉ ራሱን በራሱ እንዲተረጉም የማይፈቅድ ተርጓሚ ነኝ ባይ ሁሉ ይስታል፣ ሌሎችንም ያሳስታል።


ለምሳሌ እንደ ራንዳል ፕራይስ ያሉ፣ Pretrib Premillennialists “የአህዛብ ዘመን ፍጻሜ” የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ በሮሜ 11፥ 25 ላይ ካለው “የአሕዛብ ሙላት” ከሚለው ጋር ያገናኙትና ሁለቱም ጥቅሶች ገና ወደፊት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ይጠባበቃሉ፤ በዚህም ጊዜ “ሁሉም  እስራኤል” ንስሐ ይገቡና፣ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ ለዘላለም እንዳይጠፉ አይሁድ  ኢየሱስን እንደ መሲሕ ይቀበላሉ፤ ሲሉ ያስተምራሉ።  በዚህም እይታቸው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ70 ዓ.ም ከሆነው ጥፋት ጀምሮ እነርሱ ገና ይመጣል ብለው እንደሚጠባበቁት እስከ መጪው እድሳት ድረስ ያለውን ጊዜ “የመረገጥ” ዘመን ወይም ባድማ የመሆን ጊዜ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በርካታ ኮሜንታተሮችም፣ (ለምሳሌ፣ አልበርት ባርነስ፣ አዳም ክላርክ፣ ቤዛ፣ ባለአራት ወንጌል፣ JFB እና ሌሎችም) በዚሁ መስመር እያሰቡ ይህንኑ አመለካከት ይጋራሉ።  


ጆኤል ቢ. ግሪንም በሉቃስ ወንጌል ማብራሪያው ላይ በገጽ 739 ላይ “የአህዛብ ዘመን” የሚለውን ሁለት መንታ ትርጓሜ አለው፣ አንዱ በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረውን የእግዚአብሔርን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ አሀዛብ የእግዚአብሔር ወኪል የመሆን ሚናቸውን ሲያመለክት፣ ከዚህ በላቀ ግን በአህዛብ መካከል የወንጌሉ የምስራች የሚታወጅበትን ጊዜ ያመለክታል ይላል:: ይህ በሉቃስ “የአህዛብ ዘመን” የተሰኘ ሃረግ በጳውሎስ የሮሜ መልዕክት ከተነገረው “የአህዛብ ሙላት” ከሚለው ጽንሰ አሳብ ጋር ለምን እንደሚሳከር አይገባኝም። 


ዲ. ኤ. ካርሰን አርታኢው በሆነበት NIV Biblical Theology Study Bible የሉቃስ ወንጌል ማብራርያው ላይ ይህንን ጥቅስ ሲተረጉም በዚሁ ፍሰት  [ከሰባ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም] በዘካርያስ 12፥ 3 “በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።” የሚለውን ጠቅሶ እንዲህ ይላል፦ ምንም እንኳ ይህ ጊዜ በሮሜ 11፥ 25 የተጻፈውን የአሕዛብን መዳን ሊመሰክር ቢችልም፣ የአሕዛብ ዘመን እርሱም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳድዱበት ጊዜ ማለት ነው።  ይህም ተፈጽሟል፤ ይልና፣ አክሎም እግዚአብሔር ቁጣውን እንደሚገድበው ይህ ይጠቁማል (ማቴዎስ 24፥ 22፤ ማርቆስ 13፥ 20) ይላል። ኤፍ. ኤፍ ብሩስም አርታኢው በሆነበት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ይህንንው ጥቅስ አንስቶ የአሕዛብ ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ ትረገጣለች የሚለውን የቁጥር 24 ቃል “ሲተረጉም ይህ ምናልባት የአሁኑን አለም ስርዓት መጨረሻ ያመለክታል”፤ ይልና ፍጻሜውን ከዚህ ዘመናዊ አለም መጻኢ ጊዜ ጋር ያገናኘዋል።


ለእንግሊዝኛ አንባብያን የተዘጋጀው የኤሊኮት ማብራርያም በጥቅሱ ላይ የሚያቀርበው ትንታኔ፣ የእስራኤል ቅጣትና የኢየሩሳሌም ጥፋት ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ሁለቱም የሚታደሱበት አንድ ቀን እንዳለ፣ ከጠቅላላው የቅዱስ ጳውሎስ ሐሳብ ጋር እንደሚስማማ የሚታወቅ ነው፤ ሲል በዚህ አንቀጽ ላይ የተገለጸውን  ሐሳብ ያስተጋባል።  በሮሜ 9-11፣ የተሰጠውን ትምህርትም በማምጣት በተለይ  በሮሜ 11፥ 25፣ “የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ”፣ የሚለውን ጥቅስ ሉቃስ “የአሕዛብ ዘመን” ሲል ከሚጠራው ጊዜ ጋር በማገናኘት ያ ጊዜ የአህዛብ የተሻሉ፣ ወቅቶች ናቸው፣ እነርሱም እስኪፈጸሙ ድረስ” የሚሉትን ቃላት ያስተገባሉ” ሲል ይተረጉማል። የቤንሰን ኮመንታሪም ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ ሲሰጥ  “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ - ማለት አሕዛብን ለመለወጥ በእግዚአብሔር ምክር የተወሰነውን ጊዜ የሚያካትት ነው፣ ይልና፣ ቀጥሎም ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ለዚህ ክፍል ግልጽ ማብራሪያ በሮሜ 11፥ 25 ላይ ሰጥቶናል ሲል ያክላል። ይህም የሉቃስ ወንጌል የትንቢቱ ክፍል በዳንኤል 9፥ 27 ላይ ኢየሩሳሌምን እስከ ፍጻሜ ድረስ ባድማ ያደርጋታል ለሚለው ትንቢታዊ ቃል መልስ ይሰጣል፤  በዚህ ሕዝብ ላይ ቁጣ ይፈስሳል፣ ምድሪቱንም ባድማ ያደርጋታል ይላል። እዚህ ላይ ያለው የሁለቱም ምንባቦች ትርጉም እንደሚያሳየው፣ በሉቃስ ላይ ከተነገረው ጥፋት በኋላ፣ ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና ትቀጥላለች፣ እግዚአብሔር የወሰነውን ቁጣ በእርሷ ላይ እስኪያፍሥባት ድረስ፥ አሕዛብም ወደ እግዚአብሔር ዘወር እስኪሉ ድረስ ይህ በምደሪቱ ላይ የተወሰነው ቁጣ አይጠናቀቅም ይላል።


የሆነው ሆኖ  እንደ ሜየር እና ላይትፉት ያሉ ተርጓሚዎች ደግሞ ይህ የአህዛብ ዘመን ሙላት በ70 ዓ.ም ላይ ሙሉ በሙሉ እንደተፈጸመ አድርገው ለበኩረ ተደራስያኑ አውድ ተስማሚ በሆነ መንገድ ያዩታል። ለምሳሌ፣ ሜየር “የአህዛብ ዘመን” የሚለውን ቃል ትርጉም “.  .  .  መለኮታዊ ፍርድ በፓሮዥያው እስከሚጠናቀቅ፥.  .  .  እንዲህ አይነቱ የአሕዛብ ዘመን በራሳቸው በበኩረ ተደራስያኑ የሕይወት ዘመን (ቁጥር 28) ላይ የሚያበቃና፣ የሚያልቅ ነው (ሉቃ. 21፥ 25-27) …. ስለዚህም እነዚያ ካይሮስ (አይነተኛ ጊዜዎች) የሆኑ የጊዜ መደቦች እንደ ረጅም የጊዜ ቆይታ ሊቆጠሩ አይችሉም…” ሲሉ ይረዱታል።


በተመሳሳይም ላይትፉት የተባሉ ኮሜንታተርም ይህ “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኘው የጊዜ ምዕራፍ ምልክቶቹን ባዩት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት እንዳበቃ ይገነዘባሉ፣ እንዲህም ይላሉ:- “… ከዚህ ከቁጥር 32 ይልቅ የበለጠ ግልጽ ሊባል የሚችል ነገር የለም፣ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም”። የሚገርመው ነገር ይህ ዘመን ወደ ፊት ድጋሚ እንዳይታይ ሆኖ መነገሩ ነው…  ”፤ ማለትም፣ ከአሁን በኋላ መታየት ወይም መደገም የሌለበት አስገራሚ ነገር ነው…[ምክንያቱም] እነዚህ ቃላቶች በጠቅላላው በምዕራፉ ውስጥ ትርጉምን አመልካች [ጠቋሚ] ናቸው…”


ሜየርም ሆኑ ላይትፉት ሁለቱም (በተለይ ከቁጥር 25-28 እና 32 የተጠቀሰውን) የፍጻሜውን ጊዜ የሚያመለክቱ በርካታ ጥቅሶችን በዐውደ-ምንባቡ አገባብ ጠቅሰው አቅርበዋል።  ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በርካታ የዐውደ-ምንባቡ ፍንጮችም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የተከሰተው  ይህ “መረገጥ” እና “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኙ ጽንሰ አሳቦች ፍጻሜእቸውን የሚያገኙ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ።


ጌታ ኢየሱስ በሉቃስ 21፥ 20 ላይ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ አይነተኛ ምልክት ሲሰጣቸው፥ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው በዘመኑ ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ነው እንጂ፣ ወደ ፊት በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች አይደለም። ይህም አይነተኛ ምልክት ኢየሱስ ሲናገር በዙሪያው ሆነው ሲሰሙት የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ብቻ የሚመለከት ካልሆነ ሌላ በየትኛወም ዘመን እና ትውልድ ያለን ሰው አይመለከትም። 


ሉቃስ 21፥ 22 “የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።” ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ስለተተነበዩት አጠቃላይ ስለሆኑ በርካታ ክንውኖች እየተናገረ ነው፣ እነዚህም ሁሉ (ማለትም “መረገጥን” እና “የአሕዛብ ዘመን”ን ጨምሮ) ተፈጻሚ የሚሆኑት በእነዚያ “የበቀል ቀናት”  ይኸውም በዘመኑ የነበሩ ደቀመዛሙርት በሕይወት እያሉ ነው። 


ሉቃስ 21፥ 23-27 “በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።” 


ጌታ ኢየሱስ በአይሁዶች እና በሮማውያን መካከል ስለሚደረገው ጦርነት እና በመጨረሻም ምን እንደሚመጣባቸው በግልጽ እየነገራቸው ነው።  በአጭሩ፦

  1. ብዙዎቻቸው በሰይፍ ስለት ተገድለው ይወድቃሉ፤  እንደ ጆሴፈስ እና ሌሎች የታሪክ ምሁራን ዘገባ ከሆነ በእነዚያ አይሁድ በቀሰቀሱት አመጽ እና የሮማውያን ወታደሮች የከተማይቱን ቅጥር ሰብረው በህዝቡ ላይ በከፈቱት ዘግናኝ ጦርነት ከአሥራ አንድ መቶ ሺህ በላይ ሰዎች በሰይፍ እንደተገደሉ ይገመታል።  ይህ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገው ከበባ ግልጽ ወታደራዊ ጭፍጨፋ ነበር።  

  2. የቀሩት ይማረካሉ፤ ይህ ቀደም ባለው ታሪካቸው  ከለዳውያን በእነርሱ ላይ ድል ተቀዳጀው ወደ ምድራቸውና ወደ ሕዝባቸው በምርኮ አግዘው እንደወሰዷቸው አይነት አይደለም፤ አዎ ያኔ ከአሁኑ በተሻለ የተወሰዱት ወደ አንድ ህዝብና አገር ነው፤ አሁን ግን በዚህኛው ምርኮ እርስ በርሳቸው ለመገናኘትና ሃሳብ ለመለዋወጥ እስከማይችሉ ድረስ፥ እርስ በርሳቸውም እስከማይዋሃዱ ድረስ በምድር ላይ ተንሰራፍተው ወዳሉ ወደ አሕዛብ ሁሉ ይበተናሉ።  

  3. ኢየሩሳሌም ራሷ በአሕዛብ ተረግጣለች።  ዓመፀኛና ክፉ ከተማ፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የምትጎዳ፣ ስለዚህም የተጠላች ከተማ ተደርጋ ባድማ እስክትሆን ድረስ ሮማውያን ራሳቸውን ገዥ አድርገው ይሰለጥኑባታል። ምድሪቱ የተነገረባትን መለኮታዊ የበቀል ጊዜ ለመንገር ግን ያዳግታል። ይህ የትንቢት ቃል የተፈጸመበት መንገድ በእውነቱ አስገራሚ እንደሆነ ጥቂት የታሪክ ማሳያዎችን እናንሳ:-    


አይሁዶች ከሮማውያን ጋር ባደረጉት ዘግናኝ ጦርነት ሞትን እና ግዞትን አስተናግደው ውድመት ከደረሰባቸው በኋላ፣ የሮማው ቄሳር ቬስፓሲያን የመንግስቱ ወኪሎች ለሆኑ ባለስልጣናት መላውን የይሁዳ ምድር እየሸነሸኑ እንዲሸጡ ትዕዛዝ አውርዶ ነበር፣ "በዚያን ጊዜ ቄሳር የአይሁድን ምድር በሙሉ እንዲሸጡ ለባሱስ እና ለሊቤርየስ ማክሲሞስ አቃቤ ህግ ትዕዛዝ ጻፈ፤ በዚያም ምንም አይነት ከተማን መልሶ አልሠራም፥ ነገር ግን አገራቸውን በሙሉ የራሱ ገንዘብ አድርጎ ያዘ፥ በዚያም ስምንት መቶ ወታደሮችን ብቻ ትቶ ከኢየሩሳሌም ሠላሳ ምዕራፍ የምትሆን ኤማሁስ የምትባል መኖሪያን ይሰፍሩባት ዘንድ ሰጣቸው።  ለአይሁድም ሁሉ ተበትነው በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ላይ ግብር ጣለባቸው፥ እንደ ቀድሞው ዘመን ለኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይከፍሉ እንደበረው ሁሉ፣ እያንዳንዳቸውም ሁለት ድርሃም ወደ ማዘዣው ጣቢያ ያመጡ ዘንድ አዘዛቸው፥ በዚያን ጊዜም አይሁድ የነበሩበት አስከፊ ሁኔታ ይህ ነበር። በተለይ ኢየሩሳሌም፣ ከመላ ግዛቷ ጋር፣ በአህዛብ እጅ የወደቀች፣ የቄሳሩ የቬስፓዢያን የግሉ ንብረት ሆናለች፣ በዚያም ሊኖሩ ምርጫቸው ላደረጉ አሕዛብም ተቸብችባ ተሸጠች።  ኢየሩሳሌም በዚህ ሁኔታ ባድማና ውድማ ሆና እንደቀጠለች ዲዮ ሲናገር፣ ንጉሠ ነገሥት አድሪያን መልሶ እንዲያሠራት፣ እንዲቀመጥባትም ቅኝ ግዛት የሚያደርጋትን ወኪል ልኮ ኤልያ ብሎ ሰየማት።  ነገር ግን ሁኔታውን ቀይሮ ጽዮንን እና ቤዛታን ትቶ ጌታችን ወደ ተሰቀለበት ቀራንዮ ድረስ ተስፋፍቶ ያዘ።  ከዚህም በላይ አድሪያን አንድም አይሁዳዊ ወደ ኢየሩሳሌም አካባቢ እንዳይጠጋና እንዳይገባ አስገዳጅ ሕግ እንዳወጣ ዩሴቢየስ በታሪካዊ ዘገባው ነግሮናል። ስለዚህ አይሁዶች ከርስታቸው እየተሳደዱ ተነቅለው ሲወጡ ብዙ እንግዶች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ገቡ፣ ከተማዋም የሮማውያን ቅኝ ግዛት ሆነች።  በኋለኛው ዘመን ግን ጁሊያን፣ ጌታችን ስለ አይሁድ ሕዝብ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ በአሕዛብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረና የመለወጣቸውም ዋና ምክንያት እንደነበረ በማስተዋሉ፣ ሃይማኖቱን ክዶ ይህንን ድጋፍ ከክርስትና ለመንፈግ ወስኖ ነበር። ያኔም አይሁዶች የራሳቸውን መሬት እንዲይዙ በማምጣትና ሃይማኖታዊ ሥርአታቸውን እንዲፈጽሙ የሲቪል መንግስት አይነት ፈቀደላቸው። አይሁድ ጸሎትና መስዋዕት የሚያቀርቡት በዚያ ስፍራ ብቻ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ለዚሁ ዓላማው ሲል ኢየሩሳሌምን እንደገና ለመገንባትና ቤተ መቅደሱን በጥንታዊ መሠረቱ ላይ ለማቆም ወስኖ ነበር። በዚህም እቅዱ መሰረት ለአይሁድ ማህበረሰብ ደብዳቤ ጽፎ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ጋብዟቸው ነበር፤ ደብዳቤውም ከሌሎች ሥራዎቹ መካከል አሁንም ድረስ አለ። ከሌሎች ብዙ ነገሮች ጋር ሲያበረታታቸውም፦ “ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ልትቀመጡባት ስትመኟት የነበረችውን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን እኔ ራሴ ባለኝ አቅም ሁሉ እሠራታለሁ አኖራታለሁም” ይላቸው ነበር። ንጉሠ ነገሥቱም ታላቅ ዝግጅት አድርጎ ቤተ መቅደሱን እንደገና በመገንባት እቅዱን መፈጸም ጀመረ፤  ነገር ግን እርሱ ለሥራው ያሰማራቸው ሠራተኞች ግልጽ በሆነ በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ወዲያውኑ ስራውን ለማቆምና ከስፍራው ለመሸሽ ተገደዱ። አሚያኑስ ማርሴሊኑስም ስለዚህ ሁኔታ ሲናገር “በኢየሩሳሌም ትልቅ ዋጋ ያለው ቤተ መቅደስ ለመሥራት ወሰኖ ነበር” ሥራውንም ያፋጥነው ዘንድ ለአንጾኪያው አሊጲዮስ ሰጠው ነገር ግን አሊፒዮስ በታላቅ ትጋት ሥራውን ለመፈጸም እየጣረ ሳለ፣ ስለ ስራውም ለግዛቲቱ ገዥ በማስረዳት ላይ እያለ ከህንጻው መሠረት አጠገብ እጅግ አስፈሪ የሆኑ የእሳት ኳሶች መፈንዳት ጀመሩ፣ ፍንዳታውም ተደጋጋሚ እና ለብዙ ጊዜ የቀጠለ በመሆኑ በፍንጣሪውና በሚተፋው እሳት ሠራተኞችን በማቃጠል ገደላቸው፣ ሰውም የማይደረስበትን ቦታ ሁሉ አቃጠለው፤ እሳቱ ያለማቋረጥ ስላባረራቸው በዚህ ምክንያት ስራው ቆመ።  ይህም ክስተት እና እውነታው የተረጋገጠው በአይሁዳዊው ዘሙት ዳዊት ሲሆን፣ ጁሊያንም ይህ ሙከራ በራሱ እግዚአብሔር እንደተደናቀፈ በሐቀኝነት መስክሯል።  በተመሳሳይም በናዚያንዜን እና በክሪሶስቶም በግሪኮች፣ በአምብሮስ እና በሩፊን በላቲን መካከል ነገሩ ሲነገር ኖሯል፣ ክስተቱም በተከሰተበት ጊዜ በህይወት የኖሩት፣ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ከተከሰቱ በኋላ ባሉት የሃምሳ አመታት ጊዜ ውስጥ ቆይተው ታሪኩን የፃፉና የአይን ምስክሮች ሆነው በህይወት ከነበሩ መካከል ቴዎዶሬት እና ሶዞሞን፣ ፊሊስተርዮስ፣ አርያን፣ ፎቲየስ  እና የኖቫታውያን ደጋፊ የነበረው ሶቅራጥስ ይጠቀሳሉ። ስለዚህ፣ አይሁዶች እና አረማውያን፣ በሮም ንጉሠ ነገሥት እየተመሩ፣ ጌታችን በኢየሩሳሌም ከተማና በቤተመቅደስዋ ላይ “እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ሲል የተናገረውን ወድሞ የመቅረት ትንቢት ለማደናቀፍ ኃይላቸውን ሁሉ አንድ አድርገው ቢያስቡም፣ ያሰቡትንም ቢያደረጉ፣ መለኮታዊ እርግማን ያለባትን ከተማ መልሰው ሊያነሷት ግን አልቻሉም። 


ጌታ ኢየሱስ ስለ እነዚያ “የበቀል ቀኖች” በድጋሚ ሲናገር ይህ አጠቃላይ ክንውን እንደማይቀር ነግሯቸዋል፣ እነርሱም ፦  

  1. ነፍሰ ጡር የሆኑ እርጉዞች እና ህጻናትን የሚያጠቡ ሴቶች በዚያን ጊዜ “ታላቅ ጭንቀት” ይደርስባቸዋል 

  2. የአይሁድ ሕዝብ ላይም “ቁጣ” ይደርስባቸዋል  

  3. “በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፣” 

  4. “ወደ አሕዛብ ሁሉ ተማርከው ይወሰዳሉ” 

  5. ከእግር በታችም “የተረገጡ” ይሆናሉ፤ 

  6. “በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ ያሉ ምልክቶች”  ይደረጋሉ፣ 

  7. “ድንጋጤ”፣ “ግራ መጋባት” እና “ፍርሃትም” ይሆንባቸዋል፣ 

  8. “የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ” እንዲሁም 

  9. “የሰው ልጅ ሲመጣ ያዩታል፤ የሚሉት ናቸው።

 

እነዚህም ክንውኖች “በእነዚያ ቀናት” ውስጥ የሚፈጸሙ እንደሆኑ በግልጽ  ያመለክታል። ይህ በአይሁድ ላይ እንደሚደርስ ሉቃስ የሚነግረን የበቀልና የቁጣ ቀን የአይሁድ ህዝብ ታላቁ መከራ ነው እንጂ የቤተክርስቲያን ታላቁ መከራ አይደለም። እርግጥ ኢየሱስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን የህንን ታላቁ መከራ የተሰኘውን ሃረግ በቤተ ከርስቲያንም ሆነ በአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን መከራ ለማመላከት ተጠቅመውበታል። ሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለው ግን ሮማውያን በየሩሳሌምና በመላው የአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት የሚያመለክት ነው።  ታሪክ አዋቂው ጆሴፈስም እነዚህን ሁሉ ነገሮች በታሪካዊው ድርሳኑ  ውስጥ ጠቅሶ ዘግቧቸዋል። የሚያጠቡ እናቶች ጡት ያልጣሉ ጨቅላ ልጆቻቸውን ቀቅለው የበሉበትን ታሪክ፤ በአይሁድ ላይ የደረሰባቸውን በቀል እና በከተማቸው መካከል በሰይፍ ስለት ተገድለው ስለመውደቃቸው፤ በሰማይ ኃይላት ላይ ሰለታዩ ምልክቶች በዝርዝር ያስነብበናል። አለማቀፍ የፕሪቴሪስት ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ስቲቨን ኤድዋርድም የነዚህን ክስተቶች ዝርዘር ታሪካዊ ፍጻሜ አደራጅተው ለንባብ ባበቁት ጥልቅ ጥናታዊ ሰነድ ሌሎችን በርካታ የታሪክ ምሁራን ጠቅሰው በማስረጃ ያቀርባሉ 


ሉቃስ 21፥ 28 “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።”


ጊዜን አመልካች በሆኑ በእነዚህ ክንውኖች መካከል ለተፈጻሚነታቸው ምንም አይነት የጊዜ ልዩነት የለም። ኢየሱስ ከላይ የተጠቀሱትን እነዚህን ዘጠኙንም ክንውኖች (“እነዚህ ነገሮች” ሲል) እንደ አንድ አጠቃላይ የክስተቶች ስብስብ ጠቅሷቸዋል፣ እነዚህም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ደቀ መዛሙርቱ በህይወት እያሉ የሚያዩአቸው ጉዳዮች ነበሩ፣ እነርሱም “እነዚህ ነገሮች” የተባሉትን ክንውኖች ሲያዩ በዚህ መንገድ ቤዛቸው እንደቀረበ ያውቃሉ ማለት ነው።


ሉቃስ 21፥ 31-32 “እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”


ኢየሱስ እዚህ ላይ “እናንተ” ሲል የሚጠቅሳቸውና በእርሱ ዘመን የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ  “እነዚህ ነገሮች” የተባሉ ክንውኖች ሲፈጸሙ እንደሚያዩ፣ ከሚያዩትም ነገር የተነሳም (ማለትም መረገጡን እና የአሕዛብን ዘመን ጨምሮ) በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት ልትመጣ እንደ ቀረበች እንደሚያውቁ ይነግራቸዋል። ይህም ፍጻሜ ሌላ ባዕድ ፍጻሜ ሳይሆን በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በደቀ መዛሙርቱ የህይወት ዘመን የሚጠበቅ ብቸኛ ፍጻሜ መሆኑን ንግግሩ ይበልጥ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በንግግሩ ሁለት ጊዜ (ቁ. 22፣ 24) “እነዚህ ነገሮች” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ እንደዋለ አስተውሉ (ቁ.22፣ 32)። ምናልባት የቀሩ ጥርጣሬዎች ቢኖርባቸው እንኳ ኢየሱስ እርሱ ስለተናገራቸው ስለ እነዚህ ጉዳዮች፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ሲል ጉዳዩን በመኃላ በማረጋገጥ ሁሉንም ጥርጣሬ ያስወግዳል። ይፈጸማሉ የተባሉት እነዚህ ጉዳዮች “ይህ ትውልድ” በተባለው የዚያን ዘመን ትውልድ ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮች መሆናቸውን እንዳንጠራጠር ኢየሱስ በመኃላ አስሮታል። መጻኢነት ግን የሚጠራጠረው ይህንን የእግዚአብሔር ልጅ መኃላ ነው።  በዚህ አውድ ውስጥ የተጠቀሱት ሁሉም ክንውኖች የሚፈጸሙት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ነው። ትንቢቱ አልተፈጸመም በሚል ሌላ ብዙ ተረት የመሰለ ‘የሊቃውንትን’ ግራ-ገብ ማብራሪያ ተቀብሎ እርሱኑ እንደበቀቀን ከማስተጋባትና ሃሰትን ከማመን ይልቅ፣ ጌታ ኢየሱስ በእውነት መኃላ የተናገረውን ብቻ አምኖ ትንቢቱ በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ተፈጽሟል ብሎ መቆም ይመረጣል። 


ላይትፉት ከላይ እንደተናገሩት፣ ኢየሱስ ከዚህ የበለጠ በንግግሩ ግልጽ ሊሆን አይችልም።  ከቁጥር 20-32 የተጠቀሱት ሁሉም ክንውኖች በአንድ ላይ የተጠቃለሉት “ሁሉ” (ቁ. 22)፣ “ነገሮች” (ቁ. 26)፣ “እነዚህ ነገሮች” (ቁ. 28፣ ቁ. 31) በሚሉት ቃላት ነው (። ልብ አድርጉ “ሁሉም ነገር” (ቁ. 32) ማለትም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜው ደግሞ (“እናንተ” እና “የእናንተ” የተባሉት ከቁጥር 20፣ 28 እና 31-32 ይመልከቱ) እነርሱ ራሳቸው በዘመኑ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አሁንም ይህንንው ፍጻሜ “ለማየት” “በእነዚያ የበቀል ቀናት” (ቁ. 22-23) በሕይወት ይኖራሉ (ቁ. 20፣ 27፣ እና 31) ተብሏል።  በዚህ ላይ የቀረ ጥርጣሬ ካለ፣ ኢየሱስ ሲናገር (ቁ. 32) እነዚህ ሁሉ ክንውኖች ማለትም “የመረገጡ” ጊዜ እና “የአሕዛብ ዘመን”ን ጨምሮ ይፈጸማሉ የተባሉት ነገሮች ሁሉ ተፈጻሚ የሚሆኑት “ይህ ትውልድ የተባለው የትውልድ ጊዜ ከማለፉ በፊት ነው ሲል የፍጻሜውን ጊዜ አንዴ አስረግጦ ነግር ጨርሷል። እዚህ ላይ ምንም ለመወዛገብ እድል የሚሰጥ ነገር  የለም።  ‘የመረገጡ’ እና “የአሕዛብ ዘመን” የሚባለው ምንም ይሁን ምን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ ሊፈጸሙ የተወሰኑ ክንውኖች አድርገን ልንገነዘባቸው ይገባል።


በተጨማሪም፣ በቁጥር 22 ላይ እዚህ የተጠቀሱት ሁሉም ክስተቶች በብሉይ ኪዳን እንደተተነበዩ ኢየሱስ ተናግሯል።  ይህም “ብሉይ ኪዳን “የመረገጡን” እና “የአሕዛብን ጊዜ” የሚተነበየው በየትኛው ክፍል ነው? የሚል ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል፤ መልሱም በቀላሉ የሚገኘው ሉቃስ 21፥ 20ን በማቴዎስ 24፥ 15 ካለው ተመሳሳይነት ጋር ስናነጻጽርና ስናስተያየው ነው።  ኢየሱስ ስለ “ጥፋት ርኩሰት” ሲናገር ምንጩን ከዳንኤል  መጥቀሱን ልብ ይሏል።  ስለዚህ በዳንኤል ላይ ስለ “መረገጥ” እና ስለ “አሕዛብ ዘመን” የሚናገሩ ሐሳቦችን ስናገኝ እምብዛም ሊያስገርመን አይገባም።  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መረገጥና ስለ አሕዛብ ዘመን ተጠቅሶ የምናገኘው በዳንኤል ብቻም አይደለም።  አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ ብለን እንመልከት፡-


ሰቆ.ኤር 1፥ 15 “ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፤ ጕልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፤ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ (የወይን መጥመቂያ) እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት።” በዚህ ጥቅስ የወይን መጥመቂያውን ረገጣ የሚያሳየውን ስዕል ልብ አድርጉ።  በ70 ዓ.ም. የአይሁድን ፍርድ በተመለከተ በራእይ መጽሐፍ በተነገረው ቃል ውስጥም ይኸው ተመሳሳይ ንግግር ጥቅም ላይ ውሏል፦ “መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ። የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ” (ራእይ 14፥ 19-20)። ይህ ቃል እንዴት እንደተፈጸመ በጥቂቱ አመልክቼ ወደኤርምያስ ሰቆቃ እመለሳለሁ። 


ስዕሉን ተመልከቱ፣ መልአኩ ማጭዱን ወደ ምድር ጥሎ የምድርን ወይን ሰበሰበና ፍሬውን ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ ወደሚጠመቅበት ወደ መጥመቂያው ጣለው (ይህንን ተመሳሳይ ስዕል በነዚህም ክፍሎችም ማየት ይቻላል፦ ኢሳ. 63፥ 1-6፤ ኤር 25፥ 29-33፤ ሰቆ. 1፥ 15፤ ሉቃ 19፥ 42-44)።  የወይን መጭመቂያው ከትልቅ ድንጋይማ አለት ተፈልፍሎ የተሰራ ወይም በድንጋይ የተገነባ ጉድጓድ ሆኖ ወይኑ እየተቆረጠ የሚጣልበት እና ጭማቂው ተንጠፍጥፎ እስኪወጣ ድረስ በሰው እግር የሚረገጥበት ቦታ ነው።  የወይኑ ደምም ከመጭመቂያው ጉድጓድ በታች ባለው ትንሽ ቀዳዳ ውስጥ ይንጠባጠባል፣ ከዚያም በየማድጋው ውስጥ ይደረጋል።  የምድር ወይን በሆነችው በእስራኤል ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ቁጣም ይህን ይመስላል።  በእርግጥ ይህንን በዓይነ ሕሊና ለመሳል አያስቸግርም።  በ70 ዓ.ም የጸደይ ወቅት፣ የእስራኤል ሕዝብ የፋሲካን በአል ለማክበር በኢየሩሳሌም በተሰበሰቡ ጊዜ፣ ሮማውያን በድንገት ከተማይቱን ከበቡ፣ በቅጥሮቿ ውስጥ ያለውን ሕዝብ እንዳይወጣና እንዳይገባ አጥምደው ዘግተው፣ ከተማይቱ እስክትፈርስ ድረስ አምስት ወራት የፈጀውን የኢየሩሳሌምን ከበባ ጀመሩ፤ ረገጣው የጀመረው ያኔ ነው።


ዮሐንስ በራእዩ ይህ የወይን መጥመቂያ ከከተማው ውጭ ሲረገጥ ተመልክቷል።  በተለመደው መንገድ ጭማቂውን ከወይኑ ፍሬ አሟጦ በማውጣት ዘዴ፣ ጭማቂው ሙሉ በሙሉ ወጥቶ እስኪያልቅ ድረስ በወይን መጭመቂያው ውስጥ መረገጥ አለበት፤ ሳይጨመቅ ባክኖ የሚቀር ወይም የሚያመልጥ የወይን ፍሬ የለም።  ይህ የወይን መጭመቂያ ግን ከከተማው ውጭ ተረገጠ።  በውስጧ ያለው የደም ጠብታ ፈስሶ እስኪያልቅ ድረስ ሮማውያን ከከተማይቱ ውጭ ሆነው እሳትና ሞት የሚተፉ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ያለማቋረጥ በእየሩሳሌም ላይ እያወረዱና እያዘነቡ ኢየሩሳሌምን ይረግጧት ጀመር።


የወይኑ መጭመቂያ “እስከ ፈረስ ልጓም” ድረስ ተረገጠ፣ ማለት ደሙም ከመጥመቂያው እስከ ሽህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ድረስ እስከ ፈረሶች ልጓሞች ድረስ ወጣ ማለት ነው። እንደ ጆሴፈስ ዘገባ  በኢየሩሳሌም ብቻ 1,337,490 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ተነግሯል። ይህ ምልክት በእስራኤል እና በኢየሩሳሌም ላይ የፈሰሰውን አስፈሪውን የእግዚአብሔርን ቁጣ አስከፊ ተፈጥሮ ያሳያል።  ቁጣው የተገለጠበት ቋንቋ ምሳሌያዊ ነው፣ ነገር ግን ጆሴፈስ የከተማዋን ውድመት አስመልክቶ ከሰጠው ቀጥተኛ መግለጫ ጋር በእጅጉ ይስማማል። ሲናገርም፦ “ከተማይቱ በሞላ በደም ተጥለቀለቀች፤ በብዙ ቤቶች የነደደ እሳትም በተገደሉት ሰዎች ደም ጠፋ” ይላል፤ እልቂቱም እጅግ በጣም ብዙ ነበር። ለፈሰሰው ለእያንዳንዱ ሰው ደም ስድስት ሳንቲም ከፍታ ደም እንኳ ብንወስድ ጎርፍ ሆኖ ወደ ሄኖም ሸለቆ የገባው የደም መጠን ከሁለት ሚሊዮን ጋሎን ደም በላይ ይደርስ ነበር። ከሰሜን እስከ ደቡብ (1600 ምዕራፍ ወይም ከ182 እስከ 200 ማይል ርቀት) መላውን የፓለስታይን ምድር የሰዎች ደም ሞላው።  


የከተማይቱም መከላከያ በረሃብና በጦርነት በተዳከመ ጊዜ በመጨረሻ ላይ የሮማውያን ጦር የቅጥሩን የተወሰነ ክፍል ደርምሰው ወደ ከተማይቱ ገባና የጭፍጨፋ ሥራውን አጠናቀቀ።  በእየሩሳሌም ላይ ስለተፈጸመው ስለዚህ ነገር አስፋፍቶ መግለጫ መስጠትም ሆነ ጥቂት ቃላት ተጠቅሞ በተሻለ ሁኔታ ዕልቂቱን መገለጽ በእውነት አይቻልም። 


ከፍ ሲል በተጠቀሰው በሰቆቃወ ኤርምያስ ያለው ንግግርም ከዚህ በታች በቀረበው የቃሉ አጠቃቀም፣ አገባብና ታርጉሙን ልብ በሉ፦


እግዚአብሔር ኃያላኖቼን ሁሉ በውስጤ አደቀቀ፤  የብላቴኖቼንም ብርታት ወደ ሚሰብርበት ጊዜ ውስጥ ስቦ እስገብቶኛል።  አሕዛብም ከጌታ ዘንድ በሆነ የአዋጅ ድምጽ በሜምራ [ሎጎስ ወይም ቃል] ትእዛዝ ወደ ይሁዳ ቤት ገብተው ደናግሉን አረከሱ፣ የወይን ፍሬ በሰው ሲረግጥ ከወይን መጭመቂያው የወይን ጠጅ እንደሚፈስ እንዲሁ የድንግልናቸውን ደም አፈሰሱ።  ይህ ትርጉም ኢየሩሳሌም በመለኮታዊ ፍርድ የደረሰባት መከራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል፣ ይህም መለኮታዊ ፍርድንና ጥፋትን እጅግ ግልጽና አሳዛኝ የሆነ ምስልን ያሳያል። በአዲሱ መደበኛ ትርጉም “በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ እግዚአብሔር ተቃወመ፣ ጎልማሶቼን ለማድቀቅ ሰራዊት በላዬ ጠራ፤ ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣ እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።” በሚል ተገልጧል።


እዚህ በሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15 ላይ “ረገጣት” የሚለው ቃል የኃላፊ ጊዜ አመልካች ግስ መሆኑን ተመልከቱ። ይህ መረገጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ586 የሆነ እንጂ ከዚያ በኋላ መረገጡ (እንደ ቀጣይ ጥፋት ሆኖ) እስከአሁን የቀጠለ አልነበረም። ይህ “መረገጥ” በተወሰነለት ቀጠሮ በባቢሎናውያን የአህዛብ መንግስት (በ586 ዓክልበ.) ተፈጽሞ ያለፈ አንድ ነገር ነው። ያ መረገጥ በ586 ዓክልበ በኢየሩሳሌም ላይ የተወሰነው “የአሕዛብ ጊዜ” ነበር።  ያም ጊዜ፣ ኤርምያስ ሰቆቃውን በጻፈበት ወቅት ያኔ ጨርሶ አልፎ ነበር። ከተማይቱም ሆነች በጠቅላላ ምድሪቱ ወድመው ነበሩ፣ ዳሩ ግን (እንደ ራንዳል ፕራይስ እና ሌሎች መጻኢያን ተርጓሚዎች እንደሚመስላቸው) ያ ቀጣይነት ያለው ጥፋት እንደ መረገጥ የሚወሰድ አልነበረም።


ኤርምያስ ይህን የኃዘን እንጉርጉሮ የጻፈው ናቡከደነፆር በ586 ዓክልበ. ስላደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋት ለማዘን ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ለነበሩት አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም ጠላት በሆኑ በአሕዛብ (እንደ ወይን መጭመቂያ) የመርገጧን አሳብን ኢየሱስ አንስቶ ሲናገር ለእነርሱ ጨርሶ የማያውቁት አዲስና እንግዳ ነገር አልነበረም። ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተ የታሪካቸው አካል ነው። ከሁሉ በላይ የሚታወሰው ግን በ586 ከክልበ. ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሰው ጥፋት ነው። የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ የተጻፈው የአሕዛብ መንግስት በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን ታላቅ “መረገጥ” አስመልክቶ ሙሾ እና የሐዘን እንጉርጉሮ ለማውረድ ነው። ይህ በናቡከደነፆር የተደረገ ‘መረገጥ’ “የተቀጠረ” ጊዜ” እንደሆነ ኤርምያስ መናገሩን ልብ አድርጉ። በእርግጥ፣ በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥ የተካተቱት አራቱም ነገሮች (ኢየሩሳሌም ለተወሰነ ጊዜ በአሕዛብ መረገጧን ጨምሮ፣) እዚህ በሰቆቃወ ኤር.  1፥ 15 ውስጥ ይገኛሉ። ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በአንድ ቀን አላሸነፋትም።  በኋላ ላይ ሮማውያን እንዳደረጉት ሁሉ እርሱም ያኔ ከተማይቱን በተመሳሳይ ጊዜ ከበባ ማድረግ ነበረበት።  ጦርነቱ በቬስፔዥያን (67 ዓ.ም.) ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቲቶ የከተማይቱን ቅጥር ንዶ በመዝለቅ ቤተ መቅደሱን እስካቃጠለበት ጊዜ ድረስ (70 ዓ.ም.) ሦስት ዓመት ተኩል ያህል ቆይቶ ነበር።


እዚህ በሰቆቃወ ኤርምያስ.  1፥ 15 የተነገረው "የተቆረጠ ጊዜ" [ማለትም፣ ጎልማሶቿን ለማድቀቅ የጠራው ጉባኤ ወይም የብላቴኖቿን ጉልበት የሚሰብርበት የተወሰነ ጊዜ] እንዲሁም "የመረገጡ" ሀሳቦች በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ካየናቸው “ከአሕዛብ ዘመን” እና “ከመረገጥ” ሃሳቦች ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ናቸው። “የተቀጠረው (የተወሰነው ጊዜ” ወይም “የአህዛብ ጊዜ” የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ወይም “አርባ ሁለት ወር” ሆኖ ከሚታይበት በቀር እነዚያን ሁለቱንም ሃሳቦች በራዕ 11፥ 2 ላይም በድጋሚ እናገኛቸዋለን።


በራዕ 11፥ 2 “በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።”


ስለዚህ  እዚህ ላይ ሰቆቃወ ኤርምያስ 1፥ 15፣ በሉቃ.21፥ 24፣ እና በራእ.11፥ 2 መካከል ብዙ መመሳሰል አለ። ሦስቱም ምንባባት ተመሳሳይ የሆኑት እነዚህ አራቱም ጉዳዮች (ማለትም አሕዛብ፣ ለአህዛብ የተወሰነው የመርገጥ ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም፣ የኢየሩሳሌም መረገጥ) አሏቸው።  ሰቆቃወ ኤርምያስ እነዚያን አራት ጉዳዮች በ586 ዓክልበ. የኢየሩሳሌምን ጥፋት ለማመልከት ተጠቅሞባቸዋል።


ራእይ 11፥ 2 ባቢሎን ከተባለችው ከጋለሞታይቱ ከተማ መውደቅ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ የሆኑ አራት ነገሮችን ይጠቅሳል።  መረገጡ ለሦስት ዓመታት ተኩል ብቻ የፈጀ ክስተት እንደነበር በሁሉም ምንባባት ላይ ትርጉሙ ግልጽ ነው፡- እነዚያ የአሕዛብ ጭፍሮች ማጥፋትን በጨረሱ ግዜ  መረገጡ ያበቃል።  አህዛብ ከተማይቱን የሚረግጡበት ዘመን ገና ወደፊት ከሺህ ዓመታት በኋላ ስለሚሆን ጥፋት ጨርሶ አያመለክትም።


ራእይ 11፥ 2 ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር በእጅጉ ተመሳሳይ ነው፣ እዚህ ላይ በግልጽ የሚናገረው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜም (42 ወራት) ነው።  በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተጠቀሱት አራቱም ተመሳሳይ ጉዳዮች (አሕዛብ፣ ለአህዛብ የተወሰነው የመርገጥ ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም፣ የኢየሩሳሌም መረገጥ)፣ እዚህ በራዕይ 11፥ 2 ውስጥ ተጠቅሰዋል።  ይህ በጣም ግልጽ የሆነ ጥቅስ ስለ ሉቃስ 21፥ 24 ትርጉም ምንም አይነት ጥርጣሬ አይፈጥርብንም።


በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ነገሮች በሙሉ ሊፈጸሙ ያሉ ነገሮች ናቸው። [ዮሐንስ ራእዩን የጻፈው በ62-63 ዓ.ም አካባቢ ማለትም የአይሁድ-ሮም ጦርነት ከመጀመሩ ሦስት ዓመታት በፊት ነው።] ራእይ 11፥ 2 የሚያመለክተው ይህ የኢየሩሳሌም ርኩስ በሆኑ አሕዛብ የመረገጧ ጊዜ ለሦስት ዓመት ተኩል የሚቆይ ሲሆን፣ ይህም የመጨረሻው የደም ጠብታ ከወይን መጥመቂያው እስኪረገጥ ድረስ ነው። እንግዲህ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በወይን መጭመቂያ ውስጥ ስትረግጥ ማለት ምን እንደሚመስል አስቡ!  ከእግራችሁ በታች ከዋለው የወይኑ ፍሬ ብዛት ውስጥ ምንም አይነት ያለ መጨመቅ የቀረ አንዳች ፍሬ አይኖርም።  ይህስ የነበረው ቁጣው በአጭሩ የቆመ አልነበረም።  ይልቁንም አይሁድ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፉ ድረስ ያለማቋረጥ ቀጥሏል።  ከዚያም ማምለጥ የሚባል ነገር አልነበረም። በተቀጠረለት ጊዜ ውስጥ የተያዘለትን  ሙሉ የሆነ ኮርስ መጨረስ ነበረበት።  ሁሉም ነገር ተፈጸሞ ባለቀ ጊዜ ብቻ ያኔ መረገጡ ቆመ፤ ያኔም ይረግጡ ዘንድ ለአሕዛብ የተወሰነው ጊዜ አብቅቷል።


“የአሕዛብ ዘመን” ቬስፓሲያን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃቱን ከጀመረበት ጊዜ (67 ዓ.ም.) ጀምሮ በ70 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ረግጦና ደምስሶ እስኪያጠፋት ድረስ ረገጣው የሶስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነበር። ዘመኑም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተፈጸሙበት “የበቀል ቀናት” ነበሩ። እዚህ ሉቃስ  21፥ 24 ላይ ዐውደ-ምንባብ  ብቻ ንጉሥ ነው። በተለይም ከቁጥር 20-24 ያለውን አስተውሉ።  ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ ያለውን ሠራዊት እንዲመለከቱ ለደቀ መዛሙርቱ ይነገራቸዋል። ከኢየሩሳሌም እና ከይሁዳ ፈጥኖ ለመውጣት እና ወደ ተራራዎች ለመሸሽ ይህ አይነተኛ ምልክት ይሆናቸዋል። በብሉይ ኪዳን የተነገረው ትንቢት ሁሉ ፍጻሜውን የሚያገኝበት የበቀል ጊዜ የሚጀምረውም ያኔ ነው። ያ የተወሰነው የኢየሩሳሌም ውድመት በብሉይ ኪዳን የተነገሩ እነዚያን ትንቢቶች ሁሉ  ፍጻሜ ይሰጣቸዋል። በሉቃ 21፥ 22 ላይ “እንዲፈጸም” የሚለውን ቃል ልብ አድርጉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? ይህ የሚፈጸመው በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የበቀል እርምጃ በተወሰደበት ጊዜ፣ ሠራዊትም በላያቸው ሰፍሮ እነርሱንና ከተማቸውን ባድማ ባደረጋቸው በዚያ ዘመን ነው። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ አህዛብ ይረግጧታል ሲል የተናገረውን ትንቢት በተጨባጭ ፍጻሜ የሰጠው፣ በአውደ ምንባቡም መሰረት በብቸኝነትም ፍጻሜ ሊሰጠው በቂ የሆነው ክስተት የ70ው ዓ.ም ውድመት ነው።


ስለዚህ፣ መጻኢያን እንደሚያስቡት ይህ የአሕዛብ ዘመን ለትርጉምም ሆነ ለክስተቱ ፍጻሜ ክፍት ሆኖ የተተው ነገር አልነበረም። ተጀምሮ የሚያበቃበት የተወሰነ የመጨረሻ ነጥብ አለው።  NIGTC [The New International Greek Testament Commentary] ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ተመልከቱ፤


እንደ ማርቆስ ዘገባ ከሆነ ይህ የሽብር ጊዜ ስለማጠሩ ምንም የተገለጸ ሀሳብ የለም። ሉቃስ ግን ከዚህ ይልቅ በአይሁዶች ላይ የሚደርሰውን ነገር እንደ ኤርምያስ ንግግር አንዳንዶች በሰይፍ ስለት ይወድቃሉ (ኤር. 20፥ 4–6፤ 21፥ 7) ሲል፤ እንደ ጳውሎስም… ታልፈው ይሰጣሉ  (ሮሜ. 7፥ 23፤ 2 ቆሮ 10፥ 5፤ 2ጢሞ 3፥ 6) ሲል እንዲሁም በሌሎች ብዙዎች እንደተነገረው ወደ አሕዛብም በምርኮ ይጋዛሉ፣ ይወሰዳሉ (ጦቢት 1፥ 10፤ ዘዳ 28፥ 64)… ኢየሩሳሌምም ራሷ ‘ትረገጣለች’ (ሉቃስ 10፥ 19) ሲል በግልጽ አስፍሯል። …ነገር ግን ይህ ሁሉ የጊዜ ገደብ የተደረገለት ወቅት ሲሆን፣ ይኸውም የተወሰነው ጊዜ፣ በዚህ በሉቃስ ዘገባ መሰረት የአሕዛብ ዘመን ተብሎ የሚጠራው ነው። አህዛብ በእስራኤል ላይ እንዲያደርጉት የተፈቀደላቸውን የእግዚአብሔርን ፍርድና በቀል ሁሉ ይፈጽሙና ኢየሩሳሌምን ይረግጡ ዘንድ  መለኮት በወሰነውና በቀጠረው ጊዜ እንዲሆን የተመደበ ነበር። ይህ በአይሁድ ላይ የሚደርስባቸው ፍርድ፣ ልክ ቤተ ክርስቲያን በታላቁ መከራ ወቅት እንደሚሆንላት አይነት ጊዜው እንደሚያጥር የሚጠቁም ነገር ጨርሶ የለም።  ስለዚህ አስጨናቂ የፍርድ ጊዜ የተነገረው ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ይህ የቁጣ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተሟጦ ማለቅ አለበት።


ኢየሱስ በተጨባጭ፣ እየተናገረ ያለው አሕዛብ አይሁዶችን እንደሚገድሉ፣ ወደ ሮም መንግሥት ሕዝቦች ሁሉ እንደሚማርኩ፣ እና ሙሴ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ የተናገረው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ አሕዛብ (ሮማውያን) በእነርሱ ላይ ሊያደርሱባቸው  የተተነበዩ ጉዳዮች ሁሉ እስኪያደርጉባቸው ድረስ - እነርሱም የድል ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ እንደሚያጠፏት ነበር። ሮማውያንም አይሁዶችን ፈጽመው እስኪያጠፏቸው ድረስ በምድሪቱ ውስጥ ቆዩ።


ይህንን የሶስት ዓመት ተኩል የጊዜ ወሰን የመረገጥን” ሃሳብ በቅርብ በአውደ ምንባቡ ውስጥ ያለ ሃሳብ ሆኖ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ውስጥም ሶስት ጊዜ የተደጋገመ ሆኖ እንደገና እናገኘዋለን።


ዳንኤል 7፥ 7 “ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።”


ዳንኤል 7፥ 19 “ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት ጥፍሮችዋም የናስ ስለሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛይቱ አውሬ፥”


ዳንኤል 7፥ 23 “እንዲህም አለ፦ አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፥ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፥ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።”


ዳንኤል 7፥ 25 “በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።”


በራእይ 11፥ 2 እና በዳንኤል 7፥ 7-25 የተጠቀሱት ምንባባት ይህ “የመረገጥ” ክስተት በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም ሁለቱም ያመለክታሉ።  ስለዚህ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ፍካሬው ላይ (ማቴዎስ 24 እና ምስስሎቹ) በእርግጥም የዳንኤልን ንግግር እያጣቀሰ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እርሱ እንደሚለው፣ በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተጠቀሰው ይህ “የኢየሩሳሌም መረገጥ” በእርግጠኝነት የሚያመለክተው የሦስት ዓመት ተኩሉን ጊዜ መሆኑን ያሳያል።  ያኔም ሮማውያን መጥተው ኢየሩሳሌምን አወደሙ (67-70 ዓ.ም.)  ያም የጊዜ ምዕራፍ እንደ ኢየሱስ ትምህርትና እንደነብያቱ ቃል ከሆነ አሕዛብ አይሁድን የሚረግጡበት ጊዜ ነበር።  ያ የተወሰነው “በአሕዛብ የተረገጡበት ጊዜ” ከ70 በኋላ ስላለው የጥፋት ዘመን እና አሁን ወደ ሁለት ሺህ ዓመታት የዘመን ርዝመት ስለሚጠጋ የአይሁድ ዲያስፖራ ትውልድ አይናገርም።  በራዕዩም ሆነ በዳንኤል የተነገረው የመረገጥ ዘመን አጭር የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ሲሆን እርሱም በ70 ዓ.ም የሚያበቃ መሆኑን በግልጽ ያመለክታሉ።


ይህንን ጥቅስ አስመልክቶ ከላይ መግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ በርካታ በመጻኢያን የተዘጋጁ ኮሜንታሪዎችን ለማገላበጥ ሞክሬአለሁ። በተጨማሪም እንደ ጄ.ኤስ. ራሰል፣ ሚልተን ቴሪ፣ ጆን ኤል ብሬይ፣ ኤፍ.ደብሊው ፌራር፣ ሜየር፣ እና ላይትፉት ያሉ መምህራን ባዘጋጁአቸው ጽሁፎች ርዕሰ ጉዳዩን እንዴት በአውዱ መሰረት መልስ እንደሰጡበት ለማየት ዕድሉን አግኝቻለሁ። እዚህ ላይ ሁሉንም ጠቅሶ ለማሳየት የቦታና የጊዜ ውስንነት ይገድበናል። ከዚህም ባለፈ የሙት ባሕር ጥቅልሎች መጽሐፍ ቅዱስን፣ የኩምራን ዶክመንቶችን፣ ፊሎ፣ ጆሴፈስ፣ ዮሲፖን፣ ታልሙድ፣ ሚድራሽ፣ ዞሃር፣ ታርጉምስ፣ ፕሴውዴፒግራፋ፣ ሴፕቱጀንት እና አፖክሪፋ የተባሉትን የዕብራይስጥ፣ የግሪክ እና የእንግሊዝኛ ጽሑፎችን ማስረጃ ጠቅሰው ስለ መረገጥ እና ስለ አህዛብ ዘመን ምንነት እንዴት ተመሳሳይ ቋንቋ እንደሚጠቀሙ ያሳዩበትን የተለያዩ ፕሪቴሪስት ጸሐፍያንን ስራዎችንም መዳሰስ ያስፈልጋል። በኮምፒውተር በመታገዝም የተለያዩ ድረ ገጾች ላይ ፍለጋን አድርጎ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቁ የምርምር ግብአቶችን ማሰስም ይገባል። ይህ ግን ለትጉሃን የቃሉ ተማሪዎች ብቻ ነው። 


ቀጥሎ በሚቀርቡ ዝርዝር የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ላይ ያለው የመጀመሪያው “የአሕዛብ ዘመን” የሚለውን ተመሳሳይ ሐረግ እንደሚጠቀሙ ያሳያል።


ሕዝቅኤል 30፥ 3 “የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።”


አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ሐረግ የሚገልጹት እንዴት እንደሆነ እነሆ ተመልከቱ፡- “የሕዝቦች ጊዜ” [WEB፣ ASV፣ Darby] እና “የአሕዛብ ዘመን” [ጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኪጄቪ]፤  “(ወራሪ) ብሔራት  (በሌሎች ብሄራዊ አገሮች ላይ)፤ የሚያደርሱት የጥፋት ሰዓት” [ታናካህ]  ወይም “አሕዛብ የሚያደርሱት የጥፋት ቀን/ ጊዜ” (አዲሱ መደበኛ ትርጉምና NASB)። በዚህ አይነተኛ አውድ ውስጥ፣ (የአህዛብ ጊዜ) የሚለው ሐረግ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ፣ በፑት፣ በሉድ፣ በአረቢያ እና በሊቢያ ሕዝቦች ላይ በናቡከደነፆር እጅ የሚፈጸመውን የጥፋት ጊዜን የሚያመለክት ይመስላል።  እነዚያ የአህዛብ አገሮች በእስራኤል ላይ የጥፋቷ “ጊዜ” በደረሰ ወቅት ተሳልቀውባት ነበር።  አሁን ደግሞ እነርሱ ራሳቸው ህመሙ የሚሰማቸው ተራቸው ወይም "ጊዜያቸው" ነበር። ይህ አይነቱ ትርጉም በሕዝቅኤል ዘመን ከነበረውና አንዱ ከሆነው የነብዩ  ኤርምያስ ቃል ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል።


ኤርምያስ 27፥ 7 “የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና [ለናቡከደነጾር] ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና [ሜዶንና ፋርስ] ታላላቆች ነገሥታት [ቂሮስ፣ ዳርዮስ] እርሱን ያስገዙታል።” እዚህ ላይ ይመጣል የተባለው “ጊዜ” የሚያመለክተው የቀደመው ወራሪ ሊመጣ ባለው ወራሪ ጦር በወራቱ እንዲጠፋ የተደረገበትን ጊዜ የሚያመለክት መሆኑ በጣም ግልፅ ይመስላል፤ እንጂ ከዚያ በኋላ ላልተወሰነው የጥፋት ዘመን የሚያመለክት ፈጽሞ አይደለም።


ማርቆስ 13፥ 33 “[የተቀጠረው/ የተወሰነው] ጊዜ(ው) መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።” [ይህ ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር ትይዩ የሆነ ምንባብ ነው። ይህ ፍርድ፣ እርሱም “የተወሰነው ጊዜ” ቀደም ሲል ካነሳነው ከሰቆቃወ ኤርምያስ  1፥ 15 ጋር፤ እንዲሁም ከዳንኤል፡ 8፥ 19፤  11፥ 27፤ 11፥ 29፤ እና 11፥ 35 ጋር የሚመሳሰል ነው። ለሰው ልጆች ዘመናትን ወስኖ የሚሰጥ ሉዓላዊው አምላክ መሆኑን በሐዋርያት ሥራ 17፥ 26 ላይ ጳውሎስ በግልጽ ይናገራ።


  • [Qumran War Scroll] 1QM 15:1] ለእስራኤል የጭንቀት ጊዜ ነውና፥ ከአሕዛብም ሁሉ ጋር ለመዋጋት የተወሰነው ጊዜ ነው።  የእግዚአብሔርም አላማ ዘላለማዊ ቤዛነትን ማምጣት ነው።  [ይህ በብርሃን ልጆች እና በጨለማ ልጆች መካከል ያለውን የምጽአት ፍጻሜ ጦርነት የሚገልጽ ከጦርነት የመጽሐፍ ጥቅልል ​​የተገኘ እጅግ አስደማሚ ምንባብ ነው። ይህ ጦርነት “አሕዛብ ሁሉ” ለጦርነት ወደ እርስዋ የሚመጡበትና በላይዋ ላይ የሚሰለፉበት “ለእስራኤል የጭንቀት ጊዜዋ” እንደሚሆን ልብ በሉ።  ስለ ተወሰነው ጊዜ እና ስለ አሕዛብ ህዝቦች የሚናገረውን ተመልከቱ።  እነዚህ ሁለቱም ጉዳዮች ማለትም የአህዛብ በእርሷ ላይ መምጣት እና የጭንቀቱ ጊዜ በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥም የሚገኙ ናቸው።  ይህ የጦርነት መጽሐፍ ጥቅልል ​​በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት አስቀድሞ የተጻፈ ነው። ይህም የሚያሳየው በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለው የቃላት አጠቃቀም አግባብነት ለክርስቲያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ተወስኖ የሚያገለግል እንዳልሆነ ያሳያል።  በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እና ከዚያ በፊት በኤሴናውያን እና በሌሎች የኩምራኒያውያን ቡድኖችም እንኳ ለብቻው ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር እናያለን።]


  • ሴፈር ዮሲፖን- የካርቴጅ ንጉሥ ሃኒባል እሱና መላ ሰራዊቱ ከነሙሉ ኃይሉ ሄዶ ምድራችንን [ጣሊያንን] ረግጦ፣ ምሽጎቻችንን አፍርሶ የሠራዊታችንን ብዛት በሰይፍ አላጠፋምን?  እኛ እናንተ ላይ  አድርገን እንደነበረው ለብዙ ቀናት በከበባ ውስጥ አቆየን;  ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ያዝነው…[እንግዲህ እዚህም ላይ ያለው ይህ የመረገጥ ሃሳብ የሚጠቁመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት የሚታይ አይደለም]።


  • 1ኛ መቃብ 4፥ 6 “በዚያን ጊዜ ደግሞ አሕዛብ መጥተው እንዳይረግጡት የጽዮንን ተራራ በረጃጅም ቅጥርና በጽኑ ግንብ ዙሪያ ሠሩ።” [እዚህም ላይ የመረገጥን ሃሳብ የሚጠቀመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት አይደለም።]


  • ሄኖክ 99፥ 2…“ወዮላቸው … የዘላለምን ሕግ ለሚተላለፉ… በምድር ላይ በእግራቸው ይረገጣሉ” [እዚህም ላይ የመረገጥን ሃሳብ የሚጠቀመው ጥፋትን ለማመልከት ነው እንጂ እንደ ተራዘመ ጥፋት አይደለም]


እነዚህ ቀኖናዊ ያልሆኑ ምንባባት እያንዳንዳቸው የመረገጥን ሐሳብ እንዴት እንደሚገልጹ ልብ በሉ።  በሚያጠፋ የጠላት ጦር ተከቦ መደምሰስን የሚያመለክት የአጭር ጊዜ ቆይታን እንጂ ከዚያ ጥፋት በኋላ የሚቆይ የተራዘመ የጥፋት ጊዜን የሚያመለክት አይደለም። ሙሉ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክቱ ሌሎች ተመሳሳይ የ"መረገጥ" አጠቃቀሞችን የሚያንጸባርቁ ምንባባትን ከተለያዩ ቀኖናዊ ከሆኑና ካልሆኑ ምኝጮች ተመልከቱ፣ ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ግሪክ ቴስታመንት ኮሜንታሪ (NIGTC) በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ማብራሪያ ሲያቀርብ፣ “እነዚህ ማጣቀሻዎች የሚያሳዩት በትንቢት ውስጥ ያለውን ጭብጥ እንጂ” ቀድሞ ያልነበረ በኢየሱስ እና በአዲስ ኪዳን ጸሃፊዎች እንደ አዲስ የተፈጠረ ነገርን አይደለም፤ ይላል።  


ከርዕሰ ጉዳዩ ጭብጥ በስተጀርባ ስላለው መሰረታዊ ትርጉም ተጨማሪ ግንዛቤን ለማግኘት እንዲረዳን ተመሳሳይ የጥፋት ጽንሰ ሐሳብ የሚስተናገድባቸውን ዘዳ 28፥ 45-68 እና ዳንኤል 12፥ 7 ሁለቱንም ክፍሎች ማስተያየት ይጠቅማል። በተሉይ በሉቃ 21፥ 24 ላይ “የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም” የሚለውን ሐረግ በዘዳ ምዕራፍ 28-33 በኋለኛው ዘመን ጠማማ እና ክፉ በሆነው የእስራኤል ትውልድ ላይ “ፈጽሞ እስኪጠፉ ድረስ” የሚተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ (ዘዳ 31፥ 29፤ 32፥ 5፤ 32፥ 20፤ ሐዋ 2፥ 40 እና ፊልጵ 2፥ 15) አስተያዩ። ኢየሱስ “የአሕዛብ ዘመን” ሲል የሚናገረው ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 31-32 ላይ እንደተነበየው አይሁዶች የሚሸነፉበት፣ የሚገደሉበት፣ የሚባረሩበት እና የሚበተኑበትን ከሮማውያን (ከአሕዛብ) ጋር ስለሚደረገው ጦርነት ነው።  ኢየሱስ ይህን በአሕዛብ የሚረገጡበትን ጊዜ ሲተነብይ በዘዳግም 28-33 ላይ የተጻፈውን በግልፅ ያሳሰበ ይመስላል።


በዘዳ 28-33፣ ሙሴ በቃል ኪዳኑ ፍርድ የሚቀበለውን የመጨረሻውን የአይሁድ ትውልድ በትንቢት ሲናገር፣ “እስክትጠፋ ድረስ” ወይም “እስኪያጠፋህ ድረስ” ወይም “እስክትጠፉ ድረስ” የሚለው ሐረግ ያለማቋረጥ ይደጋግማል።”  በተለይ የእነዚህን ሐረጎች አጠቃቀም በዘዳ 28፥ 49-52 እንዴት እንደተገለጠ ልብ አድርጉ። በዘዳግም 28-33 ስለ “መረገጥ” ወይም ስለ “ኢየሩሳሌም” ወይም ስለ “ዘመናት” የተነገረ ነገር እንደሌለ ልብ አድእጉ።  ነገር ግን አሕዛብ (አረማውያን) በመጨረሻው ዘመን ወደ አገራቸው ዘልቀው ገብተው “እስኪጠፉ ድረስ” እንደሚያጠቁአቸው ይጠቅሳል።


ይህ ዳንኤል በአሕዛብ ስለመረገጥ፣ ስለ ፍጻሜው፣ ስለተቀጠረው ጊዜና “በጊዜው፣ በዘመናቱም፣ በዘመኑም እኩሌታ” ወቅት ስለሚደረገው መፈራረስ ከተናገረው ጋር ተመሳሳይ ነው።


የአሕዛብ ህዝቦች “እስኪያጠፏት ድረስ” ወይም ሙሉ በሙሉ እስኪሰበሩአቸው (ወይም አሕዛብ ያደርጉባቸው ዘንድ የተተነበየላቸውን ሁሉ እስኪፈጽሙ ድረስ፣ ወይም “የአሕዛብ [የማጥፋት] ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ”) ኢየሩሳሌምን ይረግጧታል። ይህ የመረገጥ አሳብ አገሮች በሌላ ኃይል ወረራ በሚፈጸምባቸው ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል የተለመደ ሀሳብ ነበር።  “አትረገጡኝ” ማለት “ሰራዊቶቻችሁን ወደ ድንበሬ አታግቡ” ማለቱ እንደሆነ ይታወቃል። ሙሴ በዘዳ 28፥ 49-53 ሲናገር፣ በምድሪቱ ውስጥ ያሉት የአይሁድ ምሽጎች ሁሉ እስኪፈርሱ ድረስ (እነርሱ በመጀመሪያ ከነዓንን በወረሩበት ወቅት እንዳደረጉት ያለ) ይረግጡአችሁ ዘንድ “ቋንቋቸውን የማታውቁትን” የባዕድ ጭፍሮችን እግዚአብሔር ይጠቀማል፣ ይላቸዋል።  የዚህም መጨረሻው ማሳዳ ላይ የሆነው ነበር፤ ይህም የሆነው ከ66-73 ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው። ሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተነገረውም በእርግጠኝነት ፍጻሜውን ያገኘው በዚያ ጊዜ ነው።


ዳንኤል.  12፥ 7 ፍፁም የሆነ መሰበርን፣ የተቀጠረውን መጨረሻ ወይም የፍጻሜውን ጊዜ ያመለክታል። ጌታ ኢየሱስም በሉቃስ 21፥ 20 ላይ ሲናገር ትይዩ በሆኑት ምንባባት በማቴዎስ 24 እና በማርቆስ 13 ላይ ባለው የደብረ ዘይት ፍካሬው ዘገባዎቹ እንደተጠቀሰው፣ የዳንኤልን ትንቢት (የጥፋት ርኩሰት) ከዚህ ትንቢታዊ ጥፋት ጋር አያይዞ ይጠቅሳል። ስለዚህ ዳንኤል ይህንን ጥፋት አስመልክቶ የተናገረውን በጥንቃቄ ማየት አለብን።  ዳንኤል እንደተናገረው፣ በምዕራፍ 2፥ 44-45 በአራተኛው መንግሥት ዘመን (ሮም) ያኔ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱን ያቋቁማል። በዳን 7፥ 19 እና 7፥ 23 ላይ የተነገረውን ይኸውም አራተኛው መንግሥት ወይም አውሬ (ሮም) የብረት ጥርስ እንዳለውና ምድሪቱን ሁሉ እንደሚያደቅቅ ልብ በሉ። ከዚያም በዳንኤል 7፥ 25 ላይ ይህ መረገጥ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል እንደተባለ (ለዘመን፣ ለዘመናት እና ለዘመናት እኩሌታ ጊዜ - ማለትም፣ ለሶስት ዓመት ተኩል) እንደሆነ ጊዜውን አስተውሉ። ይህም ጊዜ አራተኛው አውሬ ምድሪቱን የሚረግጥበት ጊዜ ነው።  ከ67-70 ዓ.ም የሆነውም ይኸው ነው። ሮማውያን በቬስፔዥያን መሪነት ከ67 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁም በቲቶ ፊት አውራሪነት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ቀጥለው ባደረጉት ከበባ ከገሊላ እስከ ይሁዳ ያለውን መላውን ምድር ሁሉ ረግጠዋል፣ በዚህም ጌታ ኢየሱስ በሉቃስ ወንጌል የተናገረውን ትንቢት እና እዚህ በሉቃስ 21 ላይ የሚጠቅሰውን የዳንኤልን ትንቢት ሁሉ ፍጻሜ ይሰጠዋል።


ዳንኤል ስለ “ፍጻሜው” ሲናገር “የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል” (ዳን 12፥ 7) ይላል። ሙሴም እንዲህ ስላለው ፍጻሜ ሲናገር “ጠማማውና ክፉው የእስራኤል ትውልድ” ብሔራዊ ሕልውናቸው በሚያበቃበት በመጨረሻው ቀን ጠላቶቻቸው ሙሉ በሙሉ እስኪያጠፉአቸው ድረስ እንደሚያጠቁአቸው ተንብዮአል (ዘዳ. 28-33 ተመልከቱ)። ይህም የሙሴ ትንቢት፣ ከአዲስ ኪዳን የፍርድ ትንቢቶች ጋር ያለውን ግንኙነት እና ዘግናኝ ፍጻሜውን ያስነበብኩበትን ጽሁፍ ልትመለከቱ ትችላላችሁ።


“የአሕዛብ ዘመን” ( ሉቃስ 21፥ 24 ) የተሰኘው ጊዜ በዳንኤል 12፥ 7 ላይ ከተጠቀሰው “ፍጹም የመበተን” ሁኔታ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው።  ጂ.ቢ. ካየርድ በሉቃስ ወንጌል ማብራሪያው ስለዚህ የአህዛብ ዘመን ሲናገር “….እስራኤልን እንዲያስጨንቁ ‘ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኩሌታ’ እግዚአብሔር ለአህዛብ መንግስታት የሰጠውን ሥልጣን ያመለክታል። ይህም ጊዜ የበቀል ጊዜ በመባል ይታወቃል…፤” ይላል። ዳንኤል እንደ ተቀጠረ ጊዜ ገልጾታል።  ሮማውያን መጥተው መላውን የእስራኤልን ምድር እና በተለይም ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ሲረግጡ የተፈጸመ ነበር።  በ73 ዓ.ም የአይሁድን ምድር “መርገጣቸውን” ጨርሰው የቤተ መቅደሱ መዋቅር ፈርሶ የኢየሩሳሌም ምሽግ ሙሉ በሙሉ ተሰብሮ ፍጻሜውን ያገኘ ትንቢት ነበር።  


ክፍሉን በገዛ ራሱ አውድ ስንመለከተው የሚሰጠን ሰዕል ግልጽ ነው፤ ምንም እንኳን ይህ ቆመው እያዩት ያለው ቤተ መቅደስ ታላቅ አካላዊ ውበትና ግርማ ቢኖረውም፣ የሚፈርስበት እና የሚተውበት ጊዜ ግን እየመጣ ነበር (ቁ.5-6)።  ይህ መቼ እንደሆነ ማንም አያውቅም፣ ዳሩ ግን ይከሰታሉ የተባሉ በርካታ ምልክቶች ይቀድሙት ነበር። አስቀድሞ ጦርነቶች ይኖራሉ፣ ያኔም ኢየሩሳሌም ትጠፋለች "በአሕዛብም ትረገጣለች" ህዝቦቿም "ወደ አሕዛብ ሁሉ ይማረካሉ" (ቁ.24)።  የመረገጡም ጊዜ ቆይታው የተወሰነው “የአህዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ” (ቁ.24) የሚረዝም ነው።  ቀጥሎም በዳንኤል መጽሐፍ በትንቢት እንደተነገረው ከዚህ ሁሉ በኋላ የሰው ልጅ "በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና" ይመለሳል (ቁ.27)።  እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች” (ቁ.31) ማለት ነው።  “ይህም ሁሉ እስኪሆን” ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም (ቁ.32) የሚለውም የተፈጻሚነቱን እርግጠኝነትና የተያዘለትን ቀነ ቀጠሮ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይህም ፍጻሜ ሮም እስራኤልን ድል በማድረጓም የተጠናቀቀ ነበር።  ያኔም እስራኤል “ሙሉ በሙሉ ተሰበረች።  ስለዚህ፣ ይህ የአሕዛብ መርገጥ እና ጊዜው እንደ ዳንኤል ያሉ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህን ፍፁም የመፍረስ፣ የመበተን እና የፍርድ ጊዜ በእስራኤል ላይ እንደሚመጣ የተነበዩትን የሚያመለክት ነው።


እጄ ላይ የሚገኙትን በርካታ ሶፍት ኮፒና ሀርድ ኮፒ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች አገላብጬ በሉቃስ 21፥ 24 ላይ ያለውን “የአሕዛብ ዘመን” የሚለውን ሃረግ እንዲተረጉሙልኝ ባማክራቸውና እንዴት እንደሚተረጉሙት ብፈትሽ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሮሜ.  11፥ 25፤  ላይ ካለው “የአሕዛብ ሙላት” ከሚለው ሃረግ ጋር አጣምሮ የማየትና ተፈጻሚነታቸውንም ገና ወደፊት ባሉ ትውልዶችና ዘመናት የመጠበቅ ነገር አለባቸው። ይህ ግን ፈጽሞ ቃላቶቹ የተነገሩበትን መሰረታዊ አውድ ከማሳከር የመጣ ችግር ነው። ኤሊኮት፣ ቤንሰን፣ ቤንገል፣ ጄምሰን ፋውሴት ወዘተ ይህንኑ ያንጸባርቃሉ።


ዳሩ ግን ሉቃስ 21፥ 24 እና ሮሜ 11፥ 25፤ እነዚህ ሁለት ምንባባት የሚያወሩት (1) የአሕዛብ ዘመን (66-70 ዓ.ም.) እና (2) የአሕዛብ ሙላት (30-64 ዓ.ም.) የተሰኙ ሁለት የተለያዩ አሳቦችን ነው።  ሉቃ 21፥ 24 እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በአሕዛብ እጅ የሚፈጽመውን የፍርድ አውድ ሲሆን ሮሜ.  11፥ 25 ግን እግዚአብሔር ለአህዛብ ያቀደውን የድነት አውድ ነው።


ጆን ኤል ብሬይም እነዚህ ሁለት ጥቅሶች  የሚናገሩት ስለ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች እንደሆነ ይስማማሉ፡- “አንደኛው የሚናገረው አሕዛብ ኢየሩሳሌምን ስለሚቆጣጠሩበት ጊዜ ነው።  ሌላኛው ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ሁኔታ ለአሕዛብ የሚያደርገውን መግቦት እና ፍጻሜውን ነው።  እነዚህ በአጠቃላይ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው." ይብላሉ።


“የአሕዛብ ዘመን” የተባለው (ማለትም እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ላይ ለመፍረድ የአሕዛብን ሠራዊት አምጥቶ የተጠቀመበት ጊዜ ነው) እርሱም በ70 ዓ.ም. ፍጻሜውን አግኝቷል።  “የአሕዛብ ሙላት” ወይም የአሕዛብ ቁጥር ሲሞላ የተባለው (ማለትም፣ የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀን ከመዘጋቱ በፊት ወደ ክርስትና ስለሚጨመሩ አህዛብ የተነገረ ነው) ይኸውም ፓሮውዥያው በ66 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት በእግዚአብሔር ምርጫ እና ታሪካዊ እውነታ  ተፈጽሟል።


“የአሕዛብ ሙላት” (ሮሜ 11፥ 25) አሕዛብ ሙሉ በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ (ከአይሁዶች ጋር እኩል እንደሆኑ ተደርገው ተቀባይነትን ስያገኙ) ማለት ነበር።  አይሁድም አሕዛብም በክርስቶስ አንድ አካል እንዲሆኑ ጳውሎስ የአሕዛብን ውህደት ለመፈጸም በብዙ ደክሟል (በኤፌሶን 4 ያለውን ትምህርቱን ልብ ይሏል)። በቆላስይስ እና በሮሜ መልእክቶች ውስጥ አንስቶ በተናገረው ሐሳብ መሠረት ከአይሁድ ወገን ክርስቲያኖች የሆኑት ከአሕዛብ ወገን ክርስቲኖች የሆኑትን አማኞች ሊመጣ ያለው መንግሥት ተባባሪና ወራሾች አድርገው እንዲቀበሏቸው የማድረጉን ሥራ በእርግጥም ያከናወነ ይመስላል።  አህዛብ ከሆኑ ባልንጀሮቹ ጋር መስዋዕትን ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው ጉዞ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሕዛብን እንደ ወንድሞች እንዲቀበሏቸው መንገዱን እንዲያመቻች ረድቷቸዋል።  ለአብያተ ክርስቲያናት የጻፋቸው መልእክቶቹም፣ አህዛብ በመንግሥቱ ውስጥ መካተታቸውን ደግፈው አጥብቀው የሚከራከሩ ነበሩ፣ በመጨረሻም ቅዱስ ጴጥሮስ ኔሮ ባቀጣጠለው ታላቅ ስደት ሰማእት ሆኖ ከመሞቱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ (በ64 ዓ.ም. መጨረሻ) እነዚያ የቅዱስ ጳውሎስ መለዕክቶች በሐዋርያው ​​ጴጥሮስ ቀኖና የተደረጉ ናቸው (2ጴጥ. 3፥ 15-16) የአሕዛብ ሙላትም ኢየሩሳሌም ፈጽማ ከመውደሟ በፊት ቀደም ብሎ ያኔ የመጣ ይመስላል።


ስለዚህ፣ በሮሜ.  11፥ 25 ላይ ስለ “የአሕዛብ ሙላት” የሚያወራው ከ30-70 ዓ.ም ባለው የሽግግር ወቅት ስለ አህዛብ ወደ ቤተክርስቲያን መቀላቀል ነው። ይህም የአሕዛብ ሙላት የተጠናቀቀው በ64 ዓ.ም (ከጦርነቱ በፊት) ነው። መንግሥቱ ከነዚህ አመጸኞችና የማያምኑ ከሆኑ አይሁድ ተወስዶ  ያመኑ የአይሁድ ጻድቃን ቅሬታዎች ለተካተቱበት ስብስብ እና ለሚያምኑ አሕዛብ ተሰጠ።


ያ ሂደት በይፋ የጀመረውም ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ወደ ክርስትና በመመለሱ ነው፣ ቀስ በቀስም እየገፋና እያደገ ሄዶ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሁሉም ሐዋርያት ወንጌልን በአህዛብ ዘንድ እንዲሰብክ ቀኝ እጃቸውን በሰጡት ጊዜ የመገረዝን ስርዓትና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ሳያስገድዷቸው ወደ ቤተክርስቲያን እንዲቀላቀሉ ወስነዋል።  ይህን የአይሁድና የአህዛብን አንድነት ያነሳሳውና ያቀጣጠለው ሐዋርያው ​​ጳውሎስ ያደረጋቸው ተከታታይ ሚስዮናዊ ጉዞዎቹ ነበሩ።  ያኔም መንግሥቱ ከማይታዘዙትና ከማያምኑ አይሁድ ከመወሰዱ በፊት በአህዛብ ሁሉ ዘንድ (በሮማውያን ግዛት) ተበትነው የነበሩ ሁሉም ዲያስፖራ አይሁድ አማኞች ወደ መንግሥቱ ሙላት መምጣት ነበረባቸው። ያኔም መንግሥቱ ከማይታዘዙትና ከማያምኑት አይሁድ ተወስዶ ፍሬ ለሚያፈራ አዲስ ሕዝብ ተሰጥቷል፤ ይህም አዲስ ሕዝብ ከሁለቱ ወገን ጻድቃን የአይሁድ ቅሬታዎችንና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ አማኞችን ያቀፈ ነበር።

ማጠቃለያ


አንድ ሰው በአህዛብ መርገጡ መቼ ተጀምሮ መቼ የሚያበቃ ነው ብሎ አግባብነት ያለውን ጥያቄ ሊጠይቅ ይችላል። በእርግጥም ረገጣው እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ያልጀመረ ከሆነ በእርግጥም መጻኢያን በሚያቀርቡት የክርክር ጭብጥ ጠንካራ መከራከሪያ ይኖራቸዋል።  ነገር ግን እዚህ ላይ በዝርዝር የተመለከትናቸው የቃሉ ማስረጃዎች የሚያሳዩት ረገጣው የተፈፀመው ከ66-70 ዓ.ም መካከል ባለው በዚያ የበቀል እና የቁጣ ዘመን ላይ ነው።


ሚልተን ኤስ. ቴሪ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የስነ ፍታቴ መጽሐፋቸው ውስጥ ይህንው ጉዳይ በጥሩ ሁኔታ ጠቅለል አድርገው አቅርበውታል፦ በሉቃስ 21፥ 4 ላይ “የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” የሚለው ንግግር በዚያ ትውልድ ውስጥ ያልተከሰቱ ክስተቶችን ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል። "የአህዛብ ጊዜ" (kairoi eqnwn) በወንጌል ስር ለአሕዛብ የተሰጣቸው የጸጋ ጊዜያት እና አጋጣሚዎች እንደሆኑ በብዙዎች ይታሰባል። ነገር ግን ቫን ኦስተርዚ እንደተመለከተው ቃላቱን በዚህ መልኩ መረዳት አንድን ሀሳብ ለዐውደ-ምንባቡ ባዕድ ከሆነ እሳቤ ጋር መቀየጥ ይሆናል። ቤንገልም ሲያስረዳ “የአሕዛብ ዘመን የተባለው ከተማይቱን ለጥፋት እንዲረግጡ የተመደበላቸውን ጊዜ ነው” ይላል።  ነገር ግን በምንባቡ ወይም በዐውደ-ምንባቡ ውስጥ “አሕዛብ ወደ ክርስትና የሚለወጡበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን አግኝቶ በዚህ ዘመን ላይ ያበቃል” ወይም በሮማውያን፣ በፋርሳውያን፣ በሳራሴንሶች፣ በፍራንኮች እና በቱርኮች ለሺህዎች አመታት መረገጣቸውን የሚያስረዳ ምንም ነገር የለውም። ይህ ካይሮስ በግልጽ የሚያመለክተው በኢየሩሳሌም ላይ የሚሆነውን የፍርድ ጊዜ ነው እንጂ ለአሕዛብ የተሰጠውን የመዳን ጊዜ አይደለም። ከዚህ ምንባብ ጋር ግልጽ የሆነ ተመሳሳይነትና በእጅጉ ተፈጥሯዊ ስምምነት  ያለው በራእይ 11፥ 2 ላይ የተጻፈው ሲሆን “በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቷል” የተባለበት፣ በእነሱም ቅድስቲቱ ከተማ ለአርባ ሁለት ወር መረገጧ ከዚህ ጊዜ ጋር የሚስተያይና የሚመጣጠን ነው።  ይህም ለአርባ ሁለት ወር በዮሐንስ ራዕይ 12፥ 14 እና በዳንኤል 7፥ 25፤ 12፥ 7 “አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ” ከሚለው ጋር እኩያ ነው። ይህም የፍርድ ጊዜ ምልክት ነው፣ ነገር ግን ዘመናትን እና ትውልዶችን አያመለክትም። ይኸውም ሦስት አመት ተኩል ነው - እርሱም ለሁለት የተከፈለ አንድ አጭር ሰባት ሄኖ፣ ነገር ግን የወዮ ጊዜን አመልካች ኑው። ስለዚህ “የአሕዛብ ዘመን” ማለት የአሕዛብ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን የከበቡበትና አስጨንቀው የረገጡበት የሦስት አመት ተኩል ጊዜ ነው።


በሉቃስ 21፥ 24 ላይ የተገለጹት እነዚህ “መረገጥ” እና “የአሕዛብ ዘመን” የተሰኙት ጉዳዮች የሚያመለክቱት ማለትም ለሦስት ወይም ለአራት ዓመታት ያህል የሚቆይ በጣም አጭር ጊዜን እንደሆነ ጠቅሰን ካየናቸው ከእነዚህ ሁሉ ቀኖናዊ ከሆኑና ቀኖናዊ ካልሆኑ ጽሑፎች በግልጽ መረዳት ይቻላል።  የአህዛብ ጦር መላውን የፓለስታይን ምድር ይረግጣል፣ ምሽጎቿን ሁሉ ያወድማል፣ የአይሁድ ህዝብንም ሙሉ በሙሉ አፍርሶ ይበትናል። “የአህዛብ ዘመን” ቆይታው ለብዙ መቶ ዘመናት እንደሆነ ወይም ለሺህ ዓመታት አልያም ላልተወሰነ የጥፋት ጊዜ የሚዘልቅ እንደሆነ የሚገልጽ ምንም ዓይነት ምንባብ ከቅዱስ ቃሉ አናገኝም። “የአህዛብ ዘመን” ከ“መረገጥ” ዘመን ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጊዜ ርዝመት ያለው ሲሆን “መረገጡ” ያለፈ ጊዜ (“መርገጥ”፣ “የተረገጠ” ወዘተ) ብቻ የሚያመለክት መሆኑን በተለያዩ ምንባባት ላይ አስተውለናል።  ይኸውም በሽንፈት ወደተጠናቀቀው ጦርነት የሚያመለክት ነው እንጂ ከዚያ በኋላ ለመጣውና ዘመናት ላስቆጠረው የጥፋት ጊዜ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህም በኋላ እንዲህ ያለ ነገር የለም። በመካከለኛው ምሥራቅ የሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ፖለቲካዊትና ዘመናዊት እስራኤል ላይ እያፈጠጡ ግጭት ኮሽ ባለ ቁጥር የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እየመዠረጡ በተሰማው ኮሽታና በሚታዩ ነገሮች ተመርቶ ለመተርጎም የሚደረግ ጥረት ሁሉ ለአዲስ ኪዳን ክርስትና ባዕድ እምነት ጎጂ ባህል ነው።


ከሉቃስ 21፥ 24 ጋር በተያያዘ እያነሳን ከመረመርናቸው ከእነዚህ ሁሉ ጥቅሶች አንጻር ያየነው እንደሆነ፣ መጻኢያን የሚያቀርቡት የተራዘመ የጊዜ ቆይታም ሆነ ያልተገደበ የአሕዛብ ረገጣ ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመ ነው የሚለው መከራከሪያ በምንም በማስረጃ የተደገፈ አይመስልም። የሉቃስ ወንጌል አንባቢዎችም እነዚህ ቃላት በብሉይ ኪዳን የሚገኙ እነዚህን ፅንሰ-ሀሳቦች እና ጭብጦች፣ የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን፣ በተለይም የነብዩ የዳንኤል መጽሐፍ፣ እርሱም መፈፀም ስላለበት ስለተቀጠረው የፍጻሜ ጊዜ እንደሚናገር በእርግጠኝነት በሚገባ ተረድተዋቸዋል። በሉቃስ 21 ዐውደ-ምንባብ ውስጥ የተጠቀሱት ሁሉም ምልክቶች ይህንን በአሕዛብ የመረገጥ ጊዜን ጨምሮ ይህንን በሰሙ በደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ዘመን እና በትውልዳቸው ውስጥ የሚፈጸም ነገር መሆኑን ጄ. ኤስ ራስል በሚገባ አስተውሎ የሚከተለውን ብሏል፡-


እዚህ ላይ ትንቢቱ እና ምሳሌው የሚወክሉት አንድ አይነት ትዕይንትንና፣ ተመሳሳይ ጊዜን ነው፡- ይኸውም ስለ ግዑዝ ዓለም ፍጻሜ ወይም ስለ ቁሳዊው አጽናፈ ዓለም ውድመት የሚናገሩ ሳይሆኑ ይልቁንም ስለ አዮን ወይም ስለ ዘመን መቃረብ ይናገራሉ፤ በተመሳሳይ መልኩ ስለዚያ ታላቁ የፍርድ ዘመን ያመለክታሉ። ቅዱስ ሉቃስ የደብረ ዘይት ተራራን ፍካሬ በዘገብበት የትንቢት ቃል ላይ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።” (ሉቃስ 21፥ 28) ሲል ጉዳዩ እንዴት በደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ዘመን ውስጥ የሚደርስ ታላቅ ጥፋት እንደሆነ በግልጽ እንዳመለከተ አስተውሉ። ይህ ቃል የተነገረው ንግግሩን ይሰሙ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት አይደለምን? ይሆናሉ የተባሉትስ ጉዳዮች እነርሱን የሚመለከቱና ከእነርሱ ጋር የተዛመዱ ጉዳዮች አልነበሩምን? የኢየሱስን ቃል ጓግቶ እየጠጣ ላለ እዚያ ለቆመ አንድ ቡድን የተነገሩ ቃላት እንጂ፣ ከዚያ ቡድን ትውልድ በኋላ በሺዎች በሚቆጠሩ ሩቅ ዓመታት ለሚታሰብ ለሌላ ታዳሚ ወገን የተነገሩ ናቸው ብሎ ለመጠርጠር የሚያስችል አንዳች የንባብ ቦታ ይኖር ይሆንን? እንዲህ ዓይነቱ መሰረት አልባ መላምት ራሱን ውድቅ ለማድረግ በእርግጠኝነት የገዛ ራሱን ማስተባበያ ይሸከማል።


እዚህ ላይ የተጠቀሰው የአህዛብ ዘመን በሉቃስ 21፥ 24 ውስጥ የሚያመለክተው ለሦስት ዓመት ተኩል የቆየውን በአህዛብ የመረገጥን ሂደት ብቻ ነው።  በተጨባጭ ሁኔታ አሕዛብ ምድሪቱን ለዘመን፣ ለዘመናት እና ለዘመን እኩሌታ (በዳንኤል የተናገረውን የዘመን ቀመር ይመለከቷል) ይረግጣሉ፣ በዚህም ጊዜ በነብዩ ዳንኤል የተተነበዩትን ጥፋቶች ሁሉ ይፈጽማሉ እያለን ነው።  በዳንኤል የተጠቀሰው አሕዛብ ምድሪቱን የሚረግጡበት ጊዜም የሚፈጸመው በእነዚህ አምስት ቁጥሮች (ሉቃስ 21፥ 20-24) ውስጥ የተገለጹት ጉዳዮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ሲፈጸሙ (በተለይም ኢየሩሳሌም ራሷ በመጨረሻ ስትጠፋ)፣  የሮም የአህዛብ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ሲያፈርሱ፣ ነው። ያኔም ዘመናቸው ይኸውም ምድሪቱን የረገጡበት (የሦስት ዓመት ተኩል) ጊዜአቸው ያበቃል።  አሕዛብ እንዲያደርጉ የተነበየላቸውን ሁሉ እስኪፈጽሙ ድረስ ምድሪቱን ረግጠው ይቆያሉ፣ ይህም ለሦስት ዓመት ተኩል ብቻ ነው።  በነዚህም አመታት በነቢያቱ የተነገሩትን መቅሰፍቶችና ጥፋቶች ሳያደርጉ አንድም ነገር አልተዉም።  የተወሰነው የጥፋት ጊዜ ተሟጥጦ እስኪያበቃ ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈጽሟል።  ስለ መጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የማቴዎስ 24 ንግግር ፍጻሜዎች እንዲሁም በማርቆስ 13፣ በሉቃስ 17 እና በሉቃስ 21 ላይ ስላለው ተመሳሳይነት የበለጠ ለማጥናት ፍላጎቱ ካላችሁ አበክሬ የምመክረው አንዳንድ ግብዓቶችን እንድትመለከት ነው፣ ሁሉም በIPA ድህረ ገጽ ላይ በስፋትና በዝርዝር ይገኛሉ።


ግዛቸው





Sunday, December 8, 2024

የሕዝቅኤል ዳሰሳ


የሕዝቅኤል መጽሐፍ እጥጥር

አነሳሴ በሕዝቅኤል እና በዮሓንስ ራእይ ስለ ጎግ ማንጉግ የተሰጠውን ትምህርት ማጥናት እና በዚህ በኛ ዘመን ርዕሰ ጉዳዩን አስመልክቶ በስፋት የተሰራጨውን የዞረበት የመጻኢነት ስሁት ትምህርት ውድቅ ማድረግ ነው። ይሁንና የተነሳሁበትን ዋና አላማ ጠብቄ በጠቅላላ በሕዝቅኤል መጽሓፍ ላይ መለስተኛ እጥጥር በዳሰሳ መልክ ማቅረብ እንዳለብኝ የሰማኛል። ዳሰሳውም በስድስት ንኡስ ርዕሶች ዘርዘር ብሎ እንደሚከተለው ይቀርባል፦ 

  • በዚህ ዳሰሳ ክፍል አንድ መግቢያውንና የመጽሃፉን አከፋፈል አስቀደሜ፣ ስለ ጎግ ማንጎግ በመጠኑ አነሳለሁ፤ 
  • አስከትዬ በክፍል ሁለት የመጽሃፉ አብይ ትምህርት የሆነውን “እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” የተሰኘውን ርእሰ ጉዳይ ከሕዝቅኤል ራእይና መልዕክት ጋር አጣምሬ አቀርባለሁ፤ 
  • በመቀጠልም በዳሰሳችን ከፍል ሦስት የሕዝቅኤል መጽሐፍ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ምን እንደሆነና የመንፈሳዊ አገልግሎት ፍላጎትና አቅርቦትን አመለክታለሁ። 
  • በክፍል አራት ዳሰሳችን ደግሞ የሕዝቅኤል መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ወሰን አልባነት፣ የክርስቶስንና የአካሉንም ሁሉን አቃፊነት የሚገልጥልን መሆኑን ጨምሬ እንድናይ አደርጋለሁ። 
  • በክፍል አምስት ጥናታችንም በመጽሓፍ ቅዱስ የአጋግን እና ስለ አጋጋዊው ሐማ የተነገረውን አንስቼ በክፍል አንድ ካነሳሁት የጎግ ማንጉግን ትርክት ጋር ያለውን ግንኙነት በማውሳት ጉዳዩን እቋጫለሁ። 
  • በመጨረሻም በክፍል ስድስት ላይ የሕዝቅኤልን መንፈሳዊ መልዕክት፣ ስለ ከተማይቱ ቅጥር፣ ስለ በሮቿ እና ስለ መሠዊያው እንዲሁም በማጠቃለያችን በሕዝቅኤል ውስጥ ያለውን ወንዝ እና በራዕይ ውስጥ ያለውን ወንዝ በንጽጽር ተመልክተን የዳሰሳውን እጥጥር እደመድማለሁ።

gkr


ክፍል አንድ

መንደርደሪያ

ሕዝቅኤል የስሙ ትርጉም "እግዚአብሔር ያበርታል" ማለት ነው። ሕዝቅኤል ገና በወጣትነቱ በኢየሩሳሌም ባለው ቤተመቅደስ ካህን የመሆን ዕድል እና መብት የነበረው ወጣት ነበር። ያ ከመሆኑ በፊት ግን በምርኮው ዘመን በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰደ። በዚያም የነብይነት አገልግሎትን ተቀበለ። ሕዝቅኤል በነብይነት ያገለገለው ነብያቱ ዳንኤልና ኤርምያስ ያገለግሉ በነበረበት ተመሳሳይ ጊዜ ነው።  

አንዳንድ መጻህፍት በባህርያቸው ለመነበብ የማያስቸግሩ አይነት ሆነው ቶሎ ግን የሚረሱ አይነት ናቸው። ሌሎች ደግሞ ለመነበብ አስቸጋሪ ይሆኑና በያዙት ቁም ነገራቸው ግን በአንባቢዎቻቸው ህይወት በቀላሉ ሊረሱ የማይችሉ አይነት ሆነው ይቀራሉ። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በባህርዩ የሚመደበው እንደዚህ እንደ ሁለተኛው አይነት ካሉት መጻህፍት ተራ ነው።

ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት መጽሐፉን አንብቦ ለመረዳት በአንባቢዎች ዘንድ የታዩ በርካታ ተደጋጋሚ መሰናክሎች ታይተዋል። ይሁንና ግን አንባቢዎች መሰናክሎቹን ተቋቁመው መጽሐፉን በማንበብ መልእክቱን ለማስተዋል ተችሏቸው ከፍ ያለ ብድራትን አግኝተውበታል። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ውስጥ መካተት አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ጉዳይ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በነበሩ ምሁራን የአይሁድ ረቢዎች መካከል ክርክር ተካሂዶ እንደነበር ይታወቃል። ሃኒና ቤን ሕዝቅያስ የተባለ የአይሁድ ምሁር ረቢ የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ተቀባይነት ደግፎ ይሟገት ነበር የሕዝቅኤልን መጽሐፍ በባልደረቦቹና በተቃዋሚ ምሁራኑ ፊት ለመከላከል ሲል መጽሐፉን ቁጭ ብሎ እያደረ ሲያጠና ላበራው የመቅረዝ ብርሃን ሦስት መቶ ማድጋ ዘይት እንደፈጀ ይነገራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመጽሐፉ ላይ ብዙ ተንታኞች መልእክቱን ለመረዳት የተቸገሩበትን ስሜት ይገልጹ ነበር። ኤ.ቢ. ዴቪድሰን የተባለ የብሉይ ኪዳን ሊቅ ሲጽፍ “የዚህ መጽሐፍ ተማሪ የሆነ ማንም ሰው ቢሆን ተገቢውን ጥናት ያደርግ ዘንድ በተወሰነ የተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ የሚሰራውን ማናቸውንም ነገር መተው አለበት” ብሏል።

እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ድረስ ባለው የሥነመለኮት ጥናት፣ የሕዝቅኤልን መጽሐፍና መልዕክቱን ሙሉ በሙሉ የመረዳት ችግር በብዙዎች ዘንድ እንደተስተዋለ በርካታ የቃሉ ተማሪዎች ተረድተዋል። ነገር ግን ሁልጊዜ ባይገለጽም እንኳ ከሕዝቅኤል መጽሐፍ ጋር ተፋጠው ለማንበብና ለማጥናት የሚጋዱሉ ሰዎች ከገጠሙት ትግል ብዙ ባለጠግነትን ማትረፋቸው እውነት ነው፣ አይካድም። ምክንያቱም ሕዝቅኤል በሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻህፍት ውስጥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ በተመለሉተ በቀላሉ የማይገኘውን ማስተዋል ያቀርብልናል። የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ከማንበብ ጀምሮ ያለውን ተግዳሮት ማወቅ ብልህነት ነው፤ ነገር ግን በትግዳሮቱ ምክንያት መጽሐፉን ለማንበብ ፈቃደኛ አለመሆን ደግሞ ሞኝነት ነው። መልእክቱን ፍፁም በሚባል ደረጃ ጠንቅቀን ልንረዳው የስቸግረን ይሆናል፣ ነገር ግን ለማንበብብን ለማጥናት በምናደርገው ጥረት እጅግ በጣም እንባረክበታለን።

የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ለመረዳት ከሚያስቸግሩ ጉዳዮች መካከል ቢያንስ ቋንቋውን፣ ምልክቶቹን እና ትዕምርታዊ ምስል ከሳች አጠቃቀሙን የመተርጎም ነገር ነው። ኖርማን ፔሪን የተባለ ሰው በአንድ ወቅት የሳይንስ ሊቃውንት የራዕይ መጽሐፍን በመረዳት ረገድ ባሳዩት መላምት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ሲናገር “ገጣሚዎች፣ አርቲስቶች እና የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ግን መጽሐፉ እጅግ አድርጎ ከፍተኛ ስሜት ቀስቃሽና ኃይለኛ የሆኑ ምስል ከሳች ምልክቶችን ስለሚጠቀም ለስነ ጥበባቸው የማያልቅ የመነሳሳት ምንጭና ግብዓት ሆኖ አግኝተውታል”፣ ሲል ገልጾ ነበር። በሕዝቅኤል መጽሐፍም ያለው እውነታ በተወሰነ መልኩ ያው ተመሳሳይ ነው። በርካታ ሊቃውንትም ባዘጋጇቸው ጽሑፋዊ ትንተናዎቻቸው በሕዝቅኤል የተነገሩ ትንቢቶችን በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ በሚወጡ የጋዜጦች ላይ የፊት ለፊት ትኩስ የአለም ዜና ክንውኖች ጋር ለማዛመድና ቃሉን ለመተርጎም በሚያደርጉት ሙከራ ተቸክለው ራሳቸውን አቂለዋል። ከእነርሱ ይልቅ ግን “የሚዞሩ መንኮራኩሮች” እና “የደረቁ አጥንቶች” እያሉ ሲዘምሩ የኖሩ ቆየት ያሉ የተወሰኑ መንፈሳውያን ዘማሪዎች የሕዝቅኤልን መልእክት ሕያውነት ይበልጥ ተጠግተው እንደነበር ይታመናል ። የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ተምሳሌታዊነት እና ምሳሌያዊነት፣ የመልእክቱንም ምሥጢር እና ሕያውነቱን ገልጦ ለመረዳት፣ ጠንቃቃ በሆኑት የትንቢት አንባቢዎች መካከል ይህ የበለጠ የተገለጠ ነው። የትኛውንም ትንቢታዊ የሆነ መጽሐፍ በተለይም ሕዝቅኤልን ለማንበብና ለመረዳት ተገዳዳሪ ከሆኑ ፈተናዎች መካከል የተወሰኑ ቦታዎችን እና ምስሎችን የመለየት ጉዳይ ዋነኛው ነው። ጎግ እና ማጎግ (ምዕ. 38-39) ምንድን ናቸው? አዲሱ ቤተ መቅደስስ (ምዕ. 40-43) ምንን ያመለክታል? እነዚህ ትንቢቶች የሚፈጸሙትስ መቼ እና በማን ነው? የሚሉት በዚህ ረገድ የአንባቢዎችን ትኩረት የሚስቡ ሁለቱ ምሳሌዎች ሲሆኑ፣ በዚህ ዳሰሳም ትኩረት ያልተነፈጋቸው ናቸው።

የሕዝቅኤል ትንቢቶች፣ ባመዛኙ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ያልተለመደ እና በእንስሳት ተፈጥሮና ባህርይ የታጀበ ገጸ ባህሪያትን ይጠቀማል። በአብዛኛው ትንቢቶቹንና መልእክቶችን በንግግር ብቻ ከመግለጥ ይልቅ ራሱ ሆኖ ተውኔታዊ በሆነ አቀራረብ ይጫወታቸዋል። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ከማለት ይልቅ እግዚአብሔር ሊል የፈለገውን ሆኖ፣ ለመልእክቱም ሥጋና አካል ሰጥቶ መልዕክቱን ማስተላለፍ ከመናገር በላይ ስቃይና ህመሙ ላቅ ያለ ነው።  ይህ በተለይ የህዝቡ ጆሮ ደንቁሮ መስማትን እምቢ ሲል ትኩረታቸውን ለመሳብ በእጅጕ ያገለግላል። የሕዝቅኤል መልእክቶች በሕዝብ ዘንድ እምብዛም ተወዳጅነት ያልነበራቸውና ሊሰሟቸው የማይመርጧቸው አይነት ከመሆናቸውም በላይ መልእክቶቹን ወደ ህዝቡ ለማድረስ እንኳ ለራሱ ለነብዩም አስቸጋሪ አይነቶች ነበሩ። አንድ ሰው ስለ ሌላው ሰው ኃጢአት በሥጋው ሲሰቃይ መስማትና ማየት የሚፈልግ ማን ሰው አለ? የሕዝቅኤል የነብይነት ጥሪ ያንን ስቃይ መቀበልንም የሚጨምር ነበር። የነብይነት ጥሪው የሚጠይቀውን መታዘዝ ለመፈጸምና መልዕክቱን ለማስተላለፍ እስከ ምን ጥግ እንደሄደ ማሳያ የሚሆኑ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  • ቆሞ የእግዚአብሔርን መልእክት ተቀብሏል (2፡1) 
  •  በቤቱ ውስጥ ራሱን ዘጋ፣ ታሰረ፣ ድዳም ሆነ (3፡24-27)
  • የእግዚአብሔርን መልእክት ለአመጸኞቹ በታማኝነት ሰበከ (3፡27) 
  • የኢየሩሳሌም ከተማን በሸክላ ጽላት ላይ ስሎ መከበቧን ለማሳየት በሚያፈርስ ግንድ እና በብረት ምጣድ ቅጥር አደረገባት (4፡1 ጀምሮ)
  • በግራ ጎኑ ለ390 ቀናት ተኛ (4፡4፣ 5)
  • በቀኝ ጎኑ ለ40 ቀናት ተኛ (4፡6)
  • በተወሰነ መልኩ የእስራኤልን ተግሳጽ ለማሳየት እንግዳና ዘግናኝ የሆነ የምግብ አዘገጃጀትና የአመጋገብ መመሪያዎችን ተከትሏል (4፡9-17)
  • የሚመጣባቸውን መለኮታዊ ፍርድ ለማሳየት ራሱንና ጢሙን በተሳለ ጎራዴ ተላጨ (5፡1-4)
  • ምርኮውን ለማሳየት እንደስደተኛ እክትን ተሸክሞ ከቤት ወጥቶ ከስፍራ ወደ ስፍራ ተጓዘ (12፡3-7)
  • ሐሰተኛ ነቢያትን እያጋለጠ በእነርሱም ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ተናግሯል (13፡1 ጀምሮ)
  • በእስራኤል አለቆች ላይ ሙሾን እያወረደ እስራኤል የደረሰባትን ጥፋት አመለከተ (19፡1 ጀምሮ)
  • በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ ትንቢት ተነግሯል (21፡2)
  • የባቢሎን ንጉሥ በሟርቱና በሰይፉ በኢየሩሳሌምና በአህዛብ ነገስታት ላይ ጦሩን ለማዝመት የሚመጣናቸውን ሁለት መንታ መንገዶች አዘጋጅቷል (21፡19-23)
  •  በሚስቱ ሞት እንዳያዝን እና እንዳያለቅስ መመሪያን ተቀብሎ ተገበረው (24:16, 17)

በእውነቱ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ እና ፈቃዱን ለማድረግ የተጠራ ሰው አንዳንድ ጊዜ እርሱም ሆነ ያለበት ማህበረሰብ በቀላሉ የማይረዱትንና የማይገባቸውን መንገድ እንዲሄዱ ይደረጋሉ፤ ሕዝቅኤል የሆነው እንደዚያ ነው። በጊዜው የተነሱ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት እየሩሳሌም አትፈርስም፣ የምርኮውም ጊዜ አጭር ነው ሲሉ በግልጽና ብድፍረት ይናገሩ ነበር፤ አድማጭ ተመልካቾችም ነበሯቸው። በተቃራኒው፣ ሕዝቅኤልና ኤርምያስ የተነበዩት ግን ፍጹም ከዚህ የተለየውን ነው።

በዘሌዋውያን 26 እና ዘዳግም 28 ላይ ያሉት በረከቶች እና እርግማኖች ፍጻሜአቸውን እያገኙ በሥራ ላይ መዋል ጀምረው ነበር። ሕዝቡም እግዚአብሔርን አይታዘዙም ነበር፣ በዚህም ምክንያት በናቡከደነፆር እና በባቢሎናውያን ሠራዊት በኩል የሚሰራው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ፍርድ በእነሱ ላይ መጣ። ህዝቡም ያንን አስቸጋሪ እውነት መጋፈጥ ነበረባቸው፤ በደረሰባቸውም ፍርድ እግዚአብሔር አምላክን በማያውቁ ህዝቦች መካከል በባቢሎን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ በግዞት እንዲቀመጡ ሆኑ።  

በሚገርም ሁኔታ በአዲስ ኪዳናችን የሚገኘው የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የሕዝቅኤልን የትንቢት መጽሐፍ እንደገና የክርስቲያን መጽሐፍ አድርጎ ደግሞ የጻፈው ይመስላል። የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ በውስጡ ከሕዝቅኤል መጽሐፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተወሰዱ 130 የሚያህሉ ማጣቀሻዎችን ይዟል። በሥነጽሁፍ ዘውጋቸው አቡቀለምሲሳዊ የአጻጻፍ ዘይቤ ያላቸው እነዚህ መጻህፍት ሁለቱም በባህርያቸው የቃል ኪዳን ክሶች ናቸው። በአቡ ቀለምሲሳዊ ባህርያቸው በአመዛኙ ከትንቢታዊነት ለየት የሚያደርጋቸው ሁለቱም ለፍጻሜአቸው ከገዛ ራሳቸው ትውልድ የዘለለ የሩቅ ዘመን ፍጻሜን የማያመለክቱ የመሆናቸውን ያህል በቃል ኪዳናዊ ክስ ይዘታቸውም እስራኤል የሁለቱም ትኩረታቸው መሆንዋ ነው። በዚያውም ልክ ሁለቱም ተመሳሳይ የሆነ መሰረታዊ መዋቅር አላቸው። የእያንዳንዱ መጽሐፍ የመጀመሪያ አጋማሽ የእስራኤል ዘሥጋ ጥፋትን ያመለክታል፣ በሁለተኛው አጋማሽ ግን በእያንዳንዱ መጽሐፍ አዲሲቱና ቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም በውበቷና በግርማዋ ደምቃ ትታያለች። የህንን የመጽሓፍቱን ውቅር እና ምስስል ቆየት ብለን እንመለስበታለን፤ ለአሁኑ ግን የሚከተለውን ዝርዝር ለራሳችሁ አጥንታችሁ በሁለቱ መጻህፍት መካከል ያለውን ዝምድና መወስን እንድትችሉ ዝርዝር ነጥቦችን ላንሳላችሁ፦

  1. የዙፋኑ ራዕይ፤ (ሕዝቅኤል 1 እና ራዕይ 4) 
  2. መጽሃፉ፤ (ሕዝቅኤል 2-3 እና ራዕይ 5) 
  3. አራቱ መቅሰፍቶች፤ (ሕዝቅኤል 5 እና ራዕይ 6፥ 1-8) 
  4. ከመሠዊያው በታች ስለነበሩ ሰማዕታት፤ (ሕዝቅኤል 6 እና ራዕይ 6፥ 9-11) 
  5. የእግዚአብሔር ቁጣ፤ (ሕዝቅኤል 7 እና ራዕይ 6፥ 12-17) 
  6. የቅዱሳን ግንባር መታተም፤ (ሕዝቅኤል 9 እና ራዕይ 7) 
  7. ከመሠዊያው የወጣው ፍም፤ (ሕዝቅኤል 10 እና ራዕይ 8) 
  8. ወደፊት አይዘገይም፤ (ሕዝቅኤል 12 እና ራዕ 10፥ 1-7) 
  9. መፅሐፉን መብላት፤ (ሕዝቅኤል 2 እና ራዕይ 10፥ 8-11) 
  10. የቤተመቅደሱ መለካት፤ (ሕዝቅኤል 40-43 እና ራዕይ 11፥ 1-2) 
  11. እየሩሳሌም እና ሰዶም፤ (ሕዝቅኤል 16 እና ራእ 11፥ 8) 
  12. የቁጣው ጽዋ፤ (ሕዝቅኤል 23 እና ራዕይ 14) 
  13. የምድሪቱ ወይን፤ (ሕዝቅኤል 15 እና ራዕይ 14፥ 18-20) 
  14. ታላቂቱ ጋለሞታ፤ (ሕዝቅኤል 16 ፣ 23 እና ራእይ 17-18)
  15. ስለ ከተማይቱ የቀረበው የልቅሶ ሙሾ፤ (ሕዝቅኤል 27 እና ራዕይ 18) 
  16. የእግዚአብሔር የሰደቃ ድግስ፤ (ሕዝቅኤል 39 እና ራዕይ 19) 
  17. የፊተኛው ትንሳኤ፤ (ሕዝቅኤል 37 እና ራዕይ 20፥ 4-6) 
  18. ከጎግ እና ማጎግ ጋር ጦርነት፤ (ሕዝቅኤል 38-39 እና ራዕይ 20፥ 7 -9) 
  19. አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፤ (ሕዝቅኤል 40-48 እና ራዕይ 21) 
  20. የሕይወት ውሃ ወንዝ፤ (ሕዝቅኤል 47 እና ራዕይ 22) 

የሕዝቅኤል መጽሐፍ የኋለኞቹ ምዕራፎች ከዕዝራ፣ ከነህምያ፣ ከዘሩባቤል እና ከአስቴር ዘመን ታሪክ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። በእስራኤል ታሪክ የምርኮው ዘመን የነብያቱ ትንቢትና ራእያቸው መተርጎም ያለበት የምርኮው ዘመን መጻህፍት በሆኑት የብሉይ ኪዳን ታሪክ አውድ ውስጥ መሆኑን ማወቅ ይገባል። ለምሳሌ፣ በመጽሐፈ አስቴር ሀማ በመባል የሚታወቀው ገጸ ባህርይ በሕዝቅኤል 38፥ 11-15 ባለው ክፍል ከተገለጠው ግለሰብ ባህርይ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ልብ በሉ። ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁት፣ አስቴር 9፥16 ላይ ያለው ከሕዝቅኤል ምዕራፍ 38-39 ካለው ጋር በጥሩ ሁኔታ ይዛመዳል። 

ጎግ፣ በሕዝቅኤል 38-39 የማጎግ ምድር ገዥ ተብሎ የተገለፀው ነው። ጎግ በትንሿ እስያ የሚገኙ የሁለት ነገዶች የሞሣሕ እና የቱባል ምድር “ዋና አለቃ” ነው (የማጎግ ልዩ ቦታ ግን በካርታ ላይ አይታወቅም)። ጎግ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የድንበር ቦታዎች የአሕዛብን ጥምረት እየመራ እስራኤልን ለማጥቃት እንደመጣ (ሕዝ. 38.5-6) ​​በእስራኤል አምላክ በያህዌ ተጠቅሷል። ያም ሆኖ ያህዌ እስራኤልን ወክሎ ጣልቃ በመግባት የጠላቶቿን ጥምረት በአስደናቂ የኮስሞቲክ ነውጥ ለማጥፋት ቃል ገብቷል (ሕዝ. 38.19-23)። በራዕይ መጽሐፍም ስለ “ጎግ እና ማጎግ የተነገረው አመልካችነቱ ከተቀጠረው የሺህ አመት መንግስት ዘመን በኋላ ሰይጣን ቅዱሳንን ሊዋጋ በቅዱሳን ሰፈርና በተወደደችው ከተማ ላይ ያስከተተውን ወረራ” (20.7-10) ነው። 

ላድ የተባለ የዮሐንስ ራእይ ላይ ማብራሪያ የጻፈ የመጻኢያን ጎራ ጸሐፊ ስለ ጎግ እና ማጎግ ውክልና ሲናገር፦ “ጎግ እና ማጎግ በእግዚአብሔር ላይ ለሚያምፁ እና ሕዝቡን ለሚቃወሙ አሕዛብ የተሰጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስያሜዎች ናቸው”፤ ይላል። በመቀጠልም፣ “በሕዝቅኤል. 38፡ 1፣ ጎግ የማጎግ ምድር አለቃ ሲሆን በኋለኛው ዘመን ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሊዋጋ ከሰሜን ይመጣል”፣ ሲል የመጻኢነቱን ምልከታ ያጠናክራል። “በራዕይ መጽሐፍ ውስጥም ሁለቱም ቃላቶች የእግዚአብሔርና የቅዱሳኑ ጠላት የሆኑትን አህዛብን ያመለክታሉ”፣ ይላል። ላድ ጨምሮ በማብራሪያው፣ “አዲስ ኪዳን ስለ ጊዜያዊ መሲሐዊ መንግሥት የሚናገረው ጥቂት ቢሆንም፣ የሕዝቅኤል ትንቢት ግን ራዕይ 20 ላይ ካለው ጋር አንድ ዓይነት መሠረታዊ መዋቅር አለው። ምዕራፍ 36-37 ያለው የእስራኤልን መዳንና፣ ወደ ምድራቸው ተመልሰው በመሲሐዊ ድነት መባረካቸውን ያሳያል (36፥ 24-29 ያለውን ይመለከቷል)። ‘ሕዝቤ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ’ (ሕዝ. 36፡28) የሚለው አምላካዊ ቃልም የትንቢታዊውን ቃል ፍጻሜ የመጠባበቅ አይነተኛ ግብ ሲሆን፣ እርሱም አሁን እውን ሆኗል። የእግዚአብሔር ባርያ ዳዊትም በሕዝቡ ላይ ይገዛል፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ያድራል (37፡25, 28)”። ሆኖም ይላል ላድ፣ “ይህ ግን የመሲሐዊው መንግሥት በረከት መጨረሻ አይደለም። ከማጎግ በተነሳና በጎግ በሚመራው የፍጻሜ ጦርነት የመሲሁ መንግሥት እንደገና ይታወካል (ምዕራፍ 38-39)። ከመለኮታዊ ድል በኋላ ብቻም ዘላለማዊ አዲስ ስርዓት እንደ ሚመሰረት የሚያሳይ ምስል እዚህ ላይ አለን፤ ይህም ዘላለማዊ አዲስ ስርዓት በሕዝቅኤል መጽሐፍ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ እንደገና ከተገነባው ቤተመቅደስ አንፃር ተብራርቷል (ምዕራፍ 40-48)” ይልና፣ “ይህ የጊዚያዊ መሲሃዊ መንግሥት መዋቅር እና ዘላለማዊ መንግሥት አዲሱን ዘመን በምንተዋወቅበት በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ከተገለጠው ጋር አንድ ነው”፤ ይላል። ይህ የላድ ማብራሪያ በአመዛኙ የበርካታ መጻኢያንን አቋም ሊያንጸባርቅ እንደሚችል አስባለሁ። ይህንን የራእይ ትንቢት እና ፍጻሜውን በተመለከተ ቆየት ብለን እንመለስበታለን፣ እንደ ሕዝቅኤል መጽሐፍ ሁሉ በራዕይ መጽሐፍ የተነገረው የጎግ ማንጉግ ወረራ የሚቀለበሰው በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ተነግሯል። በዚህ ጥናት የራእይን መጽሐፍ የትንቢት ፍጻሜ ገና ወደፊት ይሆናል ብሎ ጠባቂ ለሆነው የመጻኢነት ምልከታ መጽሓፍ ቅዷስዊ ግባተ መሬቱን እንሰጠዋለን። አሁን ግን ትኩረታችንን በሕዝቅኤል ላይ አድርገን ጥቂት እንግፋ።

ጎግ እስራኤልን የወረረበት አንዱ ምክንያት የዕብራውያንን ከብቶች፣ ብርና ወርቅ ለመዝረፍ ነበር። በንባብ ክፍሉ ውስጥ ስለ ነዳጅ ዘይት ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም። መላው የጎግ ወታደሮች በፈረሰኞች ላይ ተቀምጠው ይመጡ ነበር እንጂ ከእነርሱ ማናቸውም በሚሊቴሪ የመጓጓዣ መኪና፣ በታንክ፣ በሄሊኮፕተር ወይም በአውሮፕላን የሚዘምቱ አልነበሩም። ይልቁንም የጎግ ወታደሮች በቀስት፣ በፍላጻ፣ በዱላ፣ በጎራዴ፣ በጦር ብቻ የሚዋጉና በእንጨት ጋሻ ብቻ የሚመክቱ ነበሩ። በራሪ ድሮንም ሆነ ተወንጫፊ ሚሳኤል፣ የእጅ ቦንብም ሆነ፣ የሞርተር መትረየስ ወይም አር.ፒ.ጂ፣ የነፍስ ወከፍ ጠብመንጃም ሆነ መድፍ ወይም ፈንጂ እና የኒውክለር አረር የተጠመደባቸው ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ወዘተ አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ ግን እግዚአብሔር በአስደናቂ የኮስሞቲክ ነውጥ ካጠፋቸው በኋላ እነዚያ ድል ነሺዎች ከእንጨት የተሰሩ የጎግን የጦር መሳሪያዎች ለሰባት አመታት በእሳት አቃጥለዋቸዋል። በዛን ጊዜ ኤሌክትሪክ፣ ጋስ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ሞተሮች ወይም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ማሽኖች ነበሩአቸውን? ፈጽሞ አልነበራቸውም። እንዲህ ያሉ መላ ምቶችን በመጽሓፉ ውስጥ እየሰነቀረ በቀጥታ ለዘመነኛው ዘመናችን እንደሚናገር አድርጎ የሚዘባርቀው ልማዳዊው የመጻኢነት አስተምህሮ ነው። አንድ ሰው ግን በቀላሉ ከምዕራፍ 38 - 39 ያለውን ምንባብ በአጠቃላይ በዐውደ-ምንባቡ አጥር ውስጥ ሊያነበው ከወደደ፣ ግልጽና ቀጥተኛ የሆነው የንባብ ክፍሉ ትርጉሙ በማያሻማ ሁኔታ በራሱ በሕዝቅኤል እና በምርኮኞቹ ዘመን ውስጥ የሚፈጸም እንደሆነ ጥርት ብሎ የሚታየው ይሆናል። 

ሌላው የተሳሳተ ትምህርት በሕዝቅኤል 38፡ 2 ላይ “ሞሳህ” የተሰኘውን ቃል በተመለከተ የሚሰነዘረው አስተያየት ነው። ይህ ቃል በእንግሊዝኛ ትርጉሞች “ሮሽ” ተብሏል፤ የትንቢት መጽሓፍ አዋቂዎች ነን የሚሉ የዘመናችን ሃሰተኛ መምህራን ይህንን ሲተረጉሙ የዘመናችን ሩሲያ ማለት ነው ሲሉ ይዘባርቃሉ። ሮሽ የሚለው ቃል ግን በመሰረታዊነት የዕብራይስጥ ቃል ነው እንጂ በጥቅሉ የስላቪክ ቋንቋ [ሩሲያኛ፣ ዩክሬንኛ እና ቤሎሩሲኛ (ምስራቅ ስላቪክ)፣ ፖላንድኛ፣ ቼክ፣ ስሎቫክ እና ሰርቢያን (ምዕራብ ስላቪክ) ቡልጋሪያኛ፣ ሰርቢያኛ፣ ክሮኤሺያኛ፣ መቄዶኒያ እና ስሎቬንን የሚያጠቃልለውን በኢንዶ-አውሮፓ የቋንቋ ዘውግ (ደቡብ ስላቪክ) ውስጥ የሚታወቅ ቃል አይደለም]። ይህም የእብራይስጥ ቃል “ራስ” ወይም “የበላይ አለቃ” ማለት ሲሆን በመላው ብሉይ ኪዳን ውስጥ ከ600 ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ ውሏል። አግባብነት ያለው የቃላትን ትርጉምና አጠቃቀም የተመለከተ ጥናት እንዲህ ያለውን ኢ- መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ መላምትን ጠርጎ ያስወግድልናል። ለምሳሌ “ሮሽ ሃሻናህ” የተባለውን የአይሁድን በዓል አስታውሱ? ሮሽ ሃሻናህ የሃሻና በዓል እርሱም የቀኖችና የአመቱ የመጀመሪያ ወይም ዋና ቀን ማለት ነው።  

በሕዝቅኤል 40 ላይ ከነቢዩ ንግግር የተወሰደው እጅግ የበለጸገ ምሳሌያዊ ገልጻ አዲሱን ቤተመቅደስ እና አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። የአዲሱ ቤተመቅደስ እና የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ክብር ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ክብር ይበልጣል። ነገር ግን ይህ በ21ኛውና በ22 ክፍለ ዘመን ስለሚሰራ ተዳሳሽ ቤተ መቅደስ እድሳት፣ በእርሱም ስለሚቀርብ የእንስሳት መሥዋዕት ፈጽሞ የሚናገር አይደለም። ምክንያቱም በምዕራፍ 43 ላይ እንስሶቹ የኃጢአት መሥዋዕት ናቸውና። እንደገና በሚሰራ መጻኢ አዲስ የአይሁድ ቤተመቅደስ የእንስሳት መስዋእት ይቀርባል ብሎ ማመንም ሆነ መጠባበቅ የክርስቶስን መስዋእታዊ ሞት ማክፋፋትና የተቀደሰ ደሙን መርገጥ ነው። እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ግልሙትና የሚያበረታታ መጻኢነትም ሆነ ዘመን ቆጣሪነት እንደወላጅ አባቱ የአሮጌው ኪዳን ሥርአት በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ወድቋል። 

ለሚያምኑ ሁሉ በጌታ እራት የታደለው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከእንስሶች መሥዋዕት ይልቅ እጅግ የከበረ ሆኖ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም እንዲህ ያሉ መስዋዕቶችን ሁሉ ሸፍኗል (ዕብ. 8-10)። ሊቀ ካህናታችን ክርስቶስ በሰማይ ባለችው ቅድስት፣ በእግዚአብሔር ፊት ካቀረበው መስዋዕት ሌላ የኮርማዎችና የእንስሶች ደም ከእንግዲህ አያስፈልግም። ጊዜ መዳቢ የሆነው መጻኢነት ግን የሌለና ከእንግዲህም የማይሆን፣ አስፈላጊነትም የሌለውንና በክርስቶስ መስዋዕት የተሻረውን በተዳሳሽ ቤተመቅደስ የሚቀርብ የእንስሶችን መስዋእት በዞረበት ነገረ ፍጻሜው በምድራዊትዋ ኢየሩሳሌም እንደገና ይጠባበቃል። ጽዮናዊያን እንዳሰቡት ሆኖላቸው ህንጻቸውን ገንብተው መስዋዕታቸውን ማቅረብ ቢጀምሩ እንኳ እንዲህ ያለውን በክርስቶስ መስዋዕታዊ ሞት ላይ የሚደረገውን መዘባበት የሚዋጋው እግዚአብሔር ነው። አዲሲቱ ቤተመቅደስ እና አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ማለት ግን በክርስቶስ ያሉ የአማኞች ጉባኤ ማለት ናቸው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16 “እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውስጣችሁ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?” ይላልና። 

ለሕዝቅኤል መጽሐፍ ሐተታ እንዲያመቻችሁ የመጽሃፉን አከፋፈል ልጠቁማችሁና ይህንን የጥናት ክፍል ላብቃ።

የሕዝቅኤል መጽሐፍ አከፋፈል

  •  የይሁዳ ውግዘት ምዕራፍ 1-24፡- 

¶ ከኢየሩሳሌም ከበባ በፊት 4 ዓመታት የተነገሩ ትንበያዎች - 592-588 ዓ.ዓ. . 

  •  የነቢዩ ጥሪና ተልእኮው (ምዕራፍ 1-3) 
  • የነብዩ ራዕይ-ምዕራፍ (ምዕራፍ 1፡1-28) 
  •  ድምጽ-ምዕራፍ (ምዕራፍ 2-3) 
  •  እየቀረበ ስለነበረው ፍርድ የተነገሩ ትንቢቶች (ምዕራፍ 4-7)  
  •  በምስል ከሳሽ አቀራረብ የተላለፈ (ምዕራፍ 4-5)  
  •  እንደሚፈጸም በግልጽ የተነገረ (ምዕራፍ 6-7) 
  •  ፍርድን ለመስጠት የሚያስፈልገው የሞራል አስፈላጊነት (ምዕራፍ 8-11) 
  •  የይሁዳ ጥፋተኝነት እና ቅጣቷ(ምዕራፍ 8-9)፣ 
  •  የኪሩቤል ራእይ (ምዕራፍ 10) 
  •  የመኳንንቱ ኃጢአት እና የንስሐ ተስፋ (ምዕራፍ 11) 
  •  የፍርድ ፍፁም እርግጠኝነት (ምዕራፍ 12-19) 
  • በትንቢት የተነገረው ምርኮ፣ እና በመሪዎቹ ላይ የተሰነዘረ ወቀሳ (ምዕራፍ 12-14) 
  •  የይሁዳ፣ ፍሬ አልባነት እና እምነት የለሽነት፣ ሲጋለጥ (ምዕራፍ 15-16) 
  • ውድቀቱ በግልጽ መብራራቱ፣ የሚገባ መሆኑና እና ልቅሶው (ምዕራፍ 17-19) 
  • የፍርዱ መንስኤ የይሁዳ ባሕርይ ነው (ምዕራፍ 20-24) 
  • የያህዌ ቸርነት እና የይሁዳ በደል (ምዕራፍ 20፡1-44) 
  • የያህዌ ሰይፍ ከሰገባው የተመዘዘ ነው (ምዕራፍ 20:45;- 21) 
  • የኢየሩሳሌም፣ የእስራኤል እና የይሁዳ ኃጢአት (ምዕራፍ 22-23) 
  •  የጽዮን ሴት ልጆች ውርደት (ምዕራፍ 23) 
  •  ምሳሌው እና ምልክቱ (ምዕራፍ 24) 

¶ የህዝቦች ጉብኝት በኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት ሊፈጽም የተነገረ ነው 2 ዓመታት - 588-586  

  •  በአሞን ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡1-7) 
  • በፍልስጥኤማውያን ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡15-17) 
  •  በሞዓብ ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡8-11) 
  •  በጢሮስ ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 26-28:19) "
  •  በኤዶም ላይ የተነገረ (ምዕራፍ 25፡12-14) 
  •  በሲዶና ላይ የቱነገረ (ምዕራፍ 28፡20-26) 
  • በግብፅ ላይ የተነገሩ ሰባት ትንቢቶች (ምዕራፍ 29-32) 
  •  የእስራኤል ተሃድሶ ምዕራፎች (ምዕራፍ 33-48) 

¶ ከኢየሩሳሌም ከበባ በኋላ የተነገሩ ትንበያዎች -14 ዓመታት 

  • ስለ አዲሱ ሕይወት መሰጠት የተነገሩ ትንቢቶች ምዕራፎች (ምዕራፍ 33-39) 
  • ጉበኛውንና እረኞችን በተመለከተ የተነገሩ ትንቢቶች ምዕራፎች (ምዕራፍ 33-34) 
  • የእስራኤል፣ የሞራል ስነምግባር እና የአንድነቷ ተሃድሶ (ምዕራፍ 35-37)
  • በጎግና በማጎግ ላይ የተሰጠ ፍርድ (ምዕራፍ 38-39) 
  • የሚቋቋመው የአዲሱ ስርዓት መግለጫ ምዕራፎች (ምዕራፍ 40-48) 
  •  የቤተ መቅደሱ ራእይ (ምዕራፍ 40-43)
  •  ሕዝቡና ቤተ መቅደሱ (ምዕራፍ 43፡13፤-46) 
  •  ምድሪቱና ቤተ መቅደሱ (ምዕራፍ 47-48)

gkr

ክፍል ሁለት

እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ

መግቢያ

ለዚህ የሕዝቅኤል ትንቢት ርእስ ሊሆንለት የሚገባው፡- “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ” የተሰኘው የመጽሐፉ ታዋቂና ተደጋጋሚ ሐረግ ነው። ይህ ሐረግ በመጽሐፉ ውስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለ65 ጊዜ ያህል በመደጋገም ሲገኝ 26 ጊዜ ግን በቀጥታ ተገልጾአል። ሕዝቅኤል ነቢይ ለመሆን ልመጠራቱንና የጥሪውን ባህርይ አስቀድሞ ሳይረዱ ስለ ትንቢታዊ መጽሐፉ መረዳት አይቻልም። 

ሕዝቅኤል በከለዳውያን ምድር በኮቦር ወንዝ አጠገብ ከምርኮኞች መካከል የነበረ በምርኮው ጊዜ ተግዞ የመጣ ካህን ነበር።

ከምዕራፍ 1-3 ባለው የመጽሐፉ የመግብያ ክፍል ካህኑ ሕዝቅኤል ከክህነት መብቱና ስፍራው በጌታ የተሰናበተ ሆኗል ማለት እንችላለን፤ በዚህ ሁኔታ ሕዝቅኤል ሥራውን ያጣ፣ የክህነት መብቱን ያጣ፣ መቅደሱን ያጣ፣ ከተማውንና የተስፋይቱን ምድር ያጣ ሲሆን። ነገር ግን በጌታ እጅ ላይ እንደገና ነቢይ ይሆን ዘንድ ሹመትንና ተልእኮን ተቀብሏል። በዚህም ሹመቱና ተልእኮው አምላክ የለሽ በሆነ የጨለማ ምድር፣ በዚያ ወዳለ ደረቅ ምድረ በዳ ተወስዶ በምርኮ ያሉትን የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ኃጢአት እንዲሸከም ራሱን ሰጠ።

ሥራውን የማጣት ሁኔታ የገጠመው ይህ ካህን ቀድሞ የነበረውን ጥሪ ሊፈጽም እንዳይችል ሆኖ ተለያይቶ ነበር፣ ይሁንና ግን አዲስ የተቀባ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን ስለ መጻኢው እጣ ፈንታቸው የተሳሳተ ተስፋ በነበራቸው ምርኮኞች ጉባኤ መካከል መገኘትና ማገልገል ነበረበት። የሚቆምበት ምስባኩ የኮቦር የወንዙ ዳርቻ ሲሆን የመኖርያ ቤቱ ደግሞ በዚያ የአሕዛብ ጨለማ ምድር ሽማግሌዎች ተሰብስበው ብርሃን ለማየት፣ የእግዚአብሔርን ምክር ለመጠየቅና ለመስማት የሚገናኙበት ስፍራ ነበር።

ነብዩ ሕዝቅኤል የትንቢታዊ አገልግሎቱ ምንጭና ውጤት ምን እንደሆነ የሚያብራሩ ቢያንስ አምስት የሚሆኑ ወሳኝ መግለጫዎች በመጽሐፉ ውስጥ አሉት። እነርሱም፦

¶ “ሰማያት ተከፈቱ”፤ 

¶ “የእግዚአብሔርን ራእዮች አየሁ”፤ 

¶ “የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሕዝቅኤል መጣ”፤ 

¶ "እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ" እንዲሁም

¶ “እግዚአብሔር በዚያ አለ” - (ያህዌ ሻማህ)፤ የሚሉት ናቸው።

በተከፈቱት ሰማያት እና እግዚአብሔር በዚያ በህያውነት ያለ አምላክ በመሆኑ መካከል በዚያ መለኮታዊ ሀልዎት ውስጥ የምናገኘው የሕዝቅኤል ራእይ፣ ነብዩ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበለበት ሁኔታ እና የነብዩ የሕዝቅኤልን የራሱን ታሪክ እንዲሁም በባቢሎን ግዞት ውስጥ ራሱ ከምርኮኞቹ አንዱ ሆኖ ምርኮኛ ለሆኑ ሰዎች ያደረሳቸውን መልእክቶች፣ መልዕክቱም በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌም እና በአንዳንድ የአህዛብ አገራትና ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን አስከፊ ተጽእኖ፣ ከዚያም ለሰው ልጆች ሁሉ ሕያው ሆኖ የሚታደለውን፣ መንፈሳዊውንና ሰማያዊ የሆነውን መሲሐዊ በረከት ጭምር ነው። 

በሕዝቅኤል ሕይወት እና አኗኗር ላይ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ጥሪ አጽንኦት ሰጥተን ማየት ይኖርብናል፤ ምክንያቱም በከፊልም ቢሆን እሱ ራሱ ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የተናገረውን ለመረዳት እና እሱና ምርኮኞቹ ሁሉ ከርስታቸው ተነቅለው በባቢሎን የተገኙበትን ምክንያት ለማስረዳት አይሁድ በገሃድ ሊያዩትና ሊሰሙት የሚገባቸው መልእክት ነው። በሕዝቅኤል ህይወትና አገልግሎት ውስጥ ነብዩ ለምርኮኞቹ መልእክተኛ ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ በምርኮኞች መካከል ያለ ምርኮኛ መልእክተኛ ነው።

ሕዝቅኤል በትንሳኤ እግዚአብሔርን በክብር ለማየት እና ህያው የሆነ ድምፁን ለመስማት ወደ ሞት መውረድ ነበረበት። ነብዩ ሕዝቅኤል ራሱ በሕይወቱ የእግዚአብሔር መልእክት ነው የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው። እርሱ ወደ ሞት እየወረደ መልእክቱን ለማሳየት እና ለማሰማት ኖሯል። ስለዚህም መሞት፣ መቀበር እና መነሳት እንደሆነ ሁሉ የሕዝቅኤል ታሪክና ህይወትም እንዲሁ ነው። ተመልከቱ፣ እስራኤል ፈርሳለች፣ ሞታለች፣ ከዚያም በባቢሎን መቃብር ተቀብራለች፤ ነገር ግን ደግሞ መቃብሮቿ ተከፍተው፣ ከሙታንም ወጥታ መቅደሱ፣ የልምላሜ ገነቱ ሆናለች፤ በውስጧም የሕይወት ውሃ ወንዝ የሚፈስባትና ያም ውሃ በሚፈስስበት ሥፍራም ሁሉ ህይወት እና ፈውስ ያለባት ሆናለች። ይህም የእስራኤል ፍጻሜዋ “ያህዌ በዚያ አለ”፣ የተሰኘው ነው፣ "እርሱም አለ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ናት!

ይህ ነቢይ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት ከቀደመው ርስቱ ከሥፍራው የተለየና በዚያ ሥፍራ ዋስትና እንዳላቸው ከሚመስላቸው ሁሉ ጋር ያልተደባለቀ ነቢይ ነው። ሕዝቅኤል ከተዳሳሹ፣ ምድራዊው ከሆነውና ከሚታየው ነገር መንፈሳዊ፣ ሰማያዊ እና እውነተኛ ወደሆነው የአገልግሎት ከፍታ መንቀሳቀስ ነበረበት። ከምርኮኞቹም ሕይወት ኃሰተኛ ተስፋዎችን ማስወገድና እውነተኛዎችን ተስፋዎች ማነቃቃት ነበረበት፤ ይህም የሕዝቅኤል አይነተኛ ሸክሙ ነበር። ከጌታ ዘንድ የሆኑ መሲሐዊ ተስፋዎችን ለማምጣት፣ የጌታ የክብር ዕቃ የመሆን ጥሪ ያላትን፣ አሁን ግን ምርኮኛ የሆነችውን ሀገር ወደ እውነተኛ መንፈሳዊ ተልእኮዋ ለመመለስ ተስፋ በማድረግ፣ የመንፈሳዊ ተሃድሶና የመልሶ ግንባታ ነቢይ ሆኖላታል።  

ዓለማዊና ኃሰተኛ ከሆኑ ምኞቶቻቸው ጋርም ምንም ትብብር ባለማድሩጉ፤ ምርኮኞቹ አይሁዶች ሕዝቅኤልን እንደ ሞኝ አድርገው ይመለከቱት ነበር፣፤ እንደ ዛሬው ባይሆንም፣ ነቢያቶቻቸው በቀደሙት ዘመናት ይናገሩ በነበረው ነገር ላይ ያን ያህል ተቃውሞ አልነበራቸውም ነበር። ለዛሬው ግን እንደ እንቅልፋም ውሾች ሆነዋል እንጂ ምንም የህይወት ራዕይም ሆነ ለብርሃን የሚሆን ሽራፊ መንፈሳዊ ፍላጎት አልነበራቸውም። የሕዝቅኤል አገልግሎት የደነቆሩ ጆሮዎችን መክፈት እና የእውሮችን አይን ማብራት ነው። ምርኮኞቹም በዚያ ሁኔታቸው ጌታ በነብዩ የሚናገረውን ወይም የሚያደርገውን ካልሰሙ ወይም ካላዩ መጨረሻቸው ወደ መጥፋት መውደቅ ነው። የነብዩን ቃል ካልሰሙ ብቻቸውን ይተዋሉ፣ በጨለማም ውስጥ ይርመሰመሳሉ፣ በጥፋት ውስጥ እንዲወድቁም ይገደዳሉ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ የሚያደርገውን የማያውቁ ሆነው ይቀራሉ።

ሕዝቅኤል የእስራኤል ትሩፋንን ከምርኮ ወደ መንፈሳዊ ድል ይመራ ዘንድ የተጠራ የተሃድሶ ነቢይ ነው። ይህም ጥሪ አዲሱን የክህነት ስርዓት ይጨምራል፣ አገልግሎቱ ግን በግዞት አገር ባለ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነበር እንጂ በኢየሩሳሌም አልነበረም። ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ርስት ባፈርሱት ምርኮኞች ርኵሰትና በኃጢአታቸው ላይ በግልጽ ይናገራል። እነዚያን የውሸት ተስፋዎቻቸውንና የማይፈጸሙ ናፍቆቶቻቸውን በመቃወምና በመገሰጽ ለእያንዳንዳቸውም በግል መታደስን ለማምጣት ይጋደላል። ሕዝቅኤል እነዚያን የውሸት ተስፋዎቻቸውንና በነዚህ ተስፋዎች በኩል የሚሰራውን ዕቅዳቸውን የሚያጋልጥ የቀንደ መለከት ድምጽ እና፣ ትምክህታቸውንና ትርክታቸውን ሁሉ ከአፈር ደባልቆ የሚፈጭ አውድማ ነው። ሕዝቅኤል በፍጥነት ከምርኮ የመመለሳቸውን የውሸት ተስፋ ለማስወገድ፣ ምርኮኞቹም የደረሰባቸውን ውድቀት ከባድነት ሳያውቁ፣ ገና በጨለማ ውስጥ እየተርመሰመሱ ሳሉ፣ ኢየሩሳሌም ከባቢሎን ጦርነት እንደምትተርፍ በከንቱ በመታመን፣ ብርሃንን ሳያዩ ስለ ብርሃን ሲናገሩ፣ እነዚያን ያልተሰበሩ አንገተ ደንዳና ምርኮኞችን በግልጽ ማነጋገር ነበረበት። ጉዳዩና አጀንዳውም መንፈሳዊ ጉዳይ እርሱም ሕይወትና ሞት፣ ጽድቅና ክፋት፣ በረከትና እርግማን፣ ምሕረት ወይም ፍርድ የሚል ነበር።

ትንቢታዊ ቃል ሲተላለፍ አይሁድ እንደ ሕዝብ በመጨረሻ የወደቁት በአንድ በኩል ተዳሳሽና ፊት ለፊት በሆነው፣ እንዲሁም በማይታየውና በሚታየው፥ በመንፈሳዊውና በአካላዊው መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ባለመቻልና ባለመረዳት ነበር፤ እንግዲህ የሕዝቅኤል ተግባር ይህንን በመግለጥ፣ እነዚያ በምርኮ የሚገኙ አይሁዶች በዚያ ባሉበት ሁኔታ ውስጥም ቢሆን እንኳ የመረዳትን ባለጠግነት አግኝተው የጌታን ድምፅ እንዲሰሙ ማድረግ ነበር። ሕዝቅኤል በአገልግሎቱ የእግዚአብሔርን ማንነትና እርሱም ለህዝቡ ለእስራኤል ያለውን የወደፊቱን ዓላማ በመግለጥ ታማኝ ነው። በዚህም እግዚአብሔር የሁሉ ጌታ እንደ ሆነ ህዝቡና መላው የእስራኤል ማህበር ያውቃሉ።

የሕዝቅኤል ትንቢቶች አምላክን በአንድ ልዩ ቅዱስ ስፍራ መገደብና መወሰን እንደማይቻል ያስተምሩናል። [እግዚአብሔርን በአንድ ሳጥን ውስጥ ማስገባትና መቆለፍ አይቻልም]። ሕዝቅኤል በጌታ ፊት ለመገኘት፣ ድምፁን ለመስማት እና ቃሉን ለመናገር እንደ አሮጌው ኪዳን ካህን በምድራዊ እና በቁሳዊ ቦታ ተወስኖ አልተከለከለም፤ የእግዚአብሔርን ራዕይ ለማየትም የግድ በኢየሩሳሌም በምድራዊው ቤተመቅደስ መሆን አላስፈለገውም። ሕዝቅኤል ጥሪው ከተስፋይቱ ምድር እና ከኢየሩሳሌም ርቀው ላሉ ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ክቡር ዙፋን ይገልጥ ዘንድ ተጠርቷል። ስለዚህም አሁን ስፍራ በማይወሰነው የአጥናፍ ዓለሙ አምላክ በያህዌ እና በምድሪቱ መካከል ያለውን ትስስር እየፈታ ነበር። እግዚአብሔር ሕዝቡን፣ ከተማይቱንና ቤተ መቅደሱን ትቶ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ሰጥቶአቸው ስለነበር፣ ራእዩም ወደ ሕዝቅኤል የመጣው ተነቅሎ ከተጋዘበት ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ተማርኮ ከተወሰደበት ከሰሜን ነው። 

የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት በይሁዳ ውድቀት አይጎዳም፣ ምንም እንኳን ህዝቡ በባቢሎን አረማዊ ሕዝብ እንደ ባርያ ቢረገጥም የልዑል ዘላለማዊ ንግስናውና መንግስቱ ግን አይቀንስም፤ እርሱ በዙፋኑ ሰማያዊነት እና በንፅህናው ጸንቶ ይኖራል። ይህም ከሁሉ በላይ ከፍ ብሎ ያለው እውነተኛ መኖሪያውና መገኛው በምድር ሁሉ ላይ ላሉ ህዝቦች ቅርብ መሆኑን ለማመልከት ነው። የዙፋኑም ሠረገላ በክልልና በቦታ ሳይገደብ በአጥናፍ አለሙ ላይ እየሰፈፈ ወደ ወደደበት ይሄዳል።

ራእዩ እና መልእክቱ

እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል የሰጠው ራእይና መልእክቱ ጌታ ከሰዎች ጋር ሊያደርገው የሚገባበትን የቃል ኪዳን ህብረት፣ በዓለምም ፊት ራሱን ለመቀደስ እና እርሱ በእውነት እንዳለ ለሁሉ ራሱን ለመግለጥ ያለውን ታላቁን ዓላማ ይገልጣል።

ይህ መጽሐፍ በአንድ በኩል የብሉይ ኪዳን ዘመን መዝጊያ፣ የነገሥታትና የመንግሥታቱ ፍጻሜ፣ [የአህዛብ ዘመን ፍጻሜ፣ የንጉሣዊው አገዛዝ የመጨረሻ ውድቀት፣ ለአይሁድም ዘመን እጅግ የከፋውን የመጨረሻ ምዕራፍ የሚያሳይ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አዲስ የትንቢት ድምጽ እና የሚመጣውን የተሻለ ዘመን መገለጥ የሚያበስር ነው። እንደ አሕዛብ ልማድ ንጉሥ እንዲኖራቸው የነበራቸው ምኞት ተሳካላቸውን? ሕዝቅኤል የዚህን ሁሉ ፍጻሜና የሚመጣውን አዲሱን መሲሐዊ ዘመን [የአዲሱን ኪዳን ዘመን]፣ እውነተኛ ንጉሥ ማንነትና መንግሥቱን ገልጦላቸዋል።

ሕዝቅኤል ለጉባኤው ያቀረበው መንፈሳዊ መግለጫ ከመልእክቱ ጋር እነሆ፦

በእግዚአብሔር መግቦት በምርኮ ወደ ግዞት የተወሰዱት ከእስራኤል ሕዝብ መካከል በጣም የተሻሉትና መልካሞቹ ነበሩ። የነቢያቱን የነኤርምያስን ትንቢት የናቁና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሆነው በኢየሩሳሌም የቀሩቱ በገዛ አገራቸው ለመቆየት ከባእዳን አለቆቻቸው ፈቃድ ያገኙ ዘንድ ማንኛውንም መሥዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነበሩ። እግዚአብሄርን የሚፈሩ ሰዎች ግን የከተማይቱ ጥፋት የማይቀር እንደሆነ በግልፅ አይተዋል። ነገር ግን የተሃድሶ አይቀሬነቱ አስፈላጊ ሁኔታ ነበር፤ ስለሆነም የመጀመሪያውን ጥሪ በፈቃደኝነት በመታዘዝ እና የህይወት ብቸኛ መግቢያ ለመሆን በደስታ ወደ ሞት ሄዱ።

ሕዝቅኤል ለምርኮኞቹ ባመጣው ኃይለኛ መልእክቱ ላይ ትልቅ ሸክም ያለው ሲሆን ይኸውም በኢየሩሳሌምና በባቢሎን ስላለው ሁኔታ ከሁሉ የተሻለው ማብራርያ በኤርምያስ ምዕራፍ 24፡1-10 ተገልጦ ይገኛል። ይህም ስለ መልካሙና እና ክፉው በለስ የተነገረው ነው። በተጨማሪም በምዕራፍ 29፡1-19፣ በምርኮ ምድር በግዞት ያሉ አይሁዶች ለሚቀጥሉት ሰባ የምርኮ ዓመታት ምን ማድረግና እንዴት መኖር እንዳለባቸው መመሪያን ይሰጣቸዋል። ልክ እንደ ኤርምያስ ሁሉ፣ ሕዝቅኤልም የተጠራው “እነሆ። ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ” ተብሎ ነው -

ሄንግስተንበርግ “እግዚአብሔር በጣም እንደረሳቸው የሚመሰክሩ የሚመስሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ፣ እነርሱም ፈጽመው (ከመቅደሱ) ተቆርጠው እና (በባዕድ አገር) እንዲቀመጡ ተደርገዋል፤ ቅድስቲቱን ምድር እና ቤተመቅደሱን ይዘው ከምርኮ የቀሩ ወንድሞቻቸውም በእነርሱ ላይ እጅግ የላቀ የንቀት ስሜት አሳይተዋል፣ ይዞታቸውንም እንደ አንዳች ትክክለኛ የመብት ማረጋገጫ ይመለከቱት ነበር። ይህ ሁሉ ግን በምርኮ የተጋዙትን ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸው ነበር፥ ሲል እንዳመለከተው ጌታ በባቢሎን የነበሩትን ምርኮኞች አይሁዶች አልረሳቸውም ነበር፡-

ጌታ ግን አሁን በኤርምያስ በኩል ለምርኮኞች የተናገረውን መልካም ቃል መፈጸም ጀመሯል (ምዕ. 24)፤ በመካከላቸውም እንደ መለከት ድምጽ፥ ድምጹን ከፍ አድርጎ ለእስራኤል ልጆች ኃጢአታቸውን የሚናገረውን፣ ቃሉም ባረፈባቸው ደስ በሚሉ ሕልሞቻቸውና ሥራዎቻቸው ሁሉ ላይ እንደ መዶሻ ወድቆ እየቀጠቀጠ፥ እንደ ዱቄትም የሚያደቃቸውን፣ በአቀራረቡም ሁሉ አሁንም እንኳ በዚህ የግዞት ሁኔታ ውስጥ ጌታ በሕዝቡ መካከል በህያውነት እንዳለ በሁለንተናው ጠንካራ ማስረጃ የሚያቀርበውን፣ እርሱ ራሱም የጌታ ቤተ መቅደስ የሆነውን፣ ያንን ቤተ መቅደስ ተብሎ የሚጠራውንና ለጥቂትም ጊዜ ቢሆን እንኳ ገና በኢየሩሳሌም ቆሞ የቀረውን ቤት በፊቱ በራሱ ምንም ማለት እንዳልሆነ በድፍረት የሚናገረውን፣ ይልቁንም ጠንካራ፣ ግዙፍ በሆነው ተፈጥሮ ብርቱዎችና አስፈሪ፣ ግዙፍና ጨካኞች የሆኑ የባቢሎንን የዘመናት መናፍስት ያረፈበትን የቤተ ጣዖቱን መቅደስ በኃይለኛ እጆቹ ይዞ ወደ ምድር እንደጣላቸው፥ ብቻውን እንደቀረ ነገር ግን ከነብያት ትምህርት ቤት የሚወጡ መቶ ተማሪዎች ያህል ግምት ያለውን ሰው፥ ያንን መንፈሳዊ ሳምሶን የሆነውን፣ ብርቱዎች፣ ግዙፍና አስፈሪ፣ የሚመስሉ የባቢሎንን የዘመናት መናፍስት በተሳካ ሁኔታ ብቻውን ቆሞ መታገል የቻለውን፣ ሕዝቅኤልን አስነሣላቸው። 

በግዞት ያሉቱ አይሁድ ምርኮኞች ያልተረሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ይልቁንም የዳዊት ልጅ የሆነው የመሲሐዊ መንግስት መምጣትን ተከትሎ እንደገና ማገገምና መታደስ፣ ከስደት ነፃ መውጣት፣ ይሆንላቸዋል (ሕዝ 34፥ 22-27)። ያኔም ከተበተኑበት ከአሕዛብም መካከል ይሰበሰባሉ (ሕዝ 36፥ 24-28)። የደረቁ አጥንቶቻቸውም ህያው ሆነው ይነሣሉ በህይወትም ይኖራሉ (ሕዝ ምዕራፍ 37)። ጠላቶቻቸውም ይጠፋሉ (ሕዝቅኤል 38-39)። ጌታም ማለቂያ የሌለው የሕይወት ውሃ ወንዝ ያለው አዲስን ቤተ መቅደስ ይሰጣቸዋል። እርሱም ለአሕዛብ ሁሉ በረከት ይሆናሉ (ሕዝቅኤል 40-48)።

የሕዝቅኤልን መልእክት ለመረዳት፡- ማቲው ሄንሪ ለሕዝቅኤል መጽሓፍ በሰጠው መግቢያ መጽሐፉን በእነዚህ ጥበብ የተሞላባቸው አስተያየቶች አስተዋውቋል። " ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር ለመረዳት ወደ ነቢያቱ መጻሕፍት ዘልቀን ስንገባ የምንሰማው ለቅዱስ ዮሐንስ እንደመጣለት ያለ ‘ወደዚህ ውጣ’ የሚል ተመሳሳይ ጥሪ መስሎ ሊታየን ይችላል (ራዕ. 4፡1) ። የዚህ መጽሐፍ ትንቢት ግን ወደ ፊት ወደ ላይ ውጡ የሚል ድምፅ ይመስላል (ሕዝቅኤል አስቀድሞ ኤርምያስ እንደተነበየው በግዞት ቤት ሳለ ተንብዮአልና፣) ስለዚህ ወደ ላይ ከፍ ብለን ወደ መለኮታዊ ክብር ግኝቶች እንሄዳለን። ስለዚህ ወደላይ ወደላይ ወደ ግኝቶች እንሄዳለን በዚያው መጠን የበለጠ ወደ መለኮታዊው ክብር እንሸጋገራለን። እነዚህ የመቅደሱም ውኃ ጥልቀቱ አሁንም እየጨመረ ያድጋል፣ እስከ አሁን ድረስም በአንዳንድ ሥፍራዎቹ በቀላሉ ሊገመት የማይችል ከመሆኑ የተነሳ ከጥልቀቱ በሚወጡ ፈሳሾች የአምላካችንን ከተማ የልዑሉን ማደሪያ ቅዱስ ስፍራ ደስ ያሰኛሉ።”

“ምንም እንኳን በዚህ ያሉት ራእዮች ዝሆን ሊያስዋኝ የሚያስችል ጥልቀት ያላቸው አይነት አስቸጋሪ ቢሆኑም ስብከቶቹ ግን በአብዛኛው የበግ ጠቦትም እንኳ ሊገባባቸው የሚችልባቸው አይነት ቀለል ያሉ ደግሞ ናቸው፤ አላማቸውም የእግዚአብሔር ህዝብ ምናልባት ይጸጸቱና ንስሃን ያደርጉ እንደሆነ ምርኮ ለምን እንደመጣባቸው ለማሳየት ያደረጉትን መተላለፋቸውን በግልጽ ማመልከት ነው።

የሕዝቅኤል መጽሐፍ የአይሁድ መንግሥት ውድቀት እና ጥፋት እንዲሁም የመፍረሱ ታሪክ ነው። ሕዝቅኤል የሚናገረው እና የሚጽፈው የአይሁድ ሃይማኖት ውጫዊና ቁሳዊ ተቋማት ሁሉ እንደሚፈርሱ ነው። እርሱም ከእነዚያ ውጫዊና ቁሳዊ ከሆኑ ነገሮችና ስፍራዎች የመለየት ህያው ምሳሌ ነበር። አሮጌው እስራኤል መሞት አለበት፣ ለራሳቸው እና ለአለም ሁሉ አዲስ የወንጌል መልእክት ይሆኑ ዘንድ ሞተው በሲኦል ሆድ ውስጥ ከተጣሉ በኋላ እንደገና ከሞት መነሳት አለባቸው። ይህም ተስፋ በተገባው መሲህ እና ለእስራኤል አዲስ ልብ እና አዲስ መንፈስ ወደሚሰጣቸው፣ የእግዚአብሔርን የቤዛነት ጸጋ ምን እንደሆነ ለማየት እጅግ የላቀ እይታን የሚሰጣቸውን አዲሱን ኪዳን ወደሚያመጣው አዲስ ቃል ኪዳን፣ ይመራቸዋል።

ሕዝቅኤል በኮቦር ወንዝ አጠገብ ትንቢት ሲናገር ኤርምያስ በኢየሩሳሌም፣ ዳንኤል ደግሞ በባቢሎን ትንቢት ይናገሩ ነበር። ከዘመናት በፊት ኢሳይያስም የወንጌላዊነትን ወርቃማ የቀንደ መለከት ድምጽ አሰምቶ ነበር። ኤርምያስ በይሁዳ ኃጢአት ላይ ሙሾን የሚያወርድ የሐዘን እንጉርጉሮ ዋሽንት ሲነፋ ነበር። ሕዝቅኤልም በዚያ ኃጢአት ምክንያት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍትሐዊ ፍርድ የሚገልጥ የብረት በገና ይመታ ነበር”

ልዩነቱ በኤርምያስ ሕዝቅኤል መካከል ካለው ንጽጽር በላይ ያልፋል፣ አንደኛው ለሕዝቡ ባለው ርህራሄ በእንባው ተለይቶ የሚታወቀው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ለእግዚአብሔር ባለው ቅንዓት ተለይቶ ይታወቃል። ምንም እንኳን እነዚህ ባህሪያት እርስ በርስ የሚጣረሱ ባይሆኑም፣ አንዱ በስሜት እና በተግባር ተለይቶ የሚታወቀው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአመክንዮው እና ያንን በሚረዳበት ነገሩ ይታወቃል። እያንዳንዳቸው ሁለቱም ነቢያት አንዱ ከሌላው ጋር ሳይገናኙና ሳይነጋገሩ አንዱ የሌላውን ሃዘን እንደ ማሚቶ የሚያስተጋባ ነው። ለአሦር ጥልቅ በረሃ ጥልቅ መልሶች፤ ከጽዮን ቅጥር ላይ ሆኖ ሲቃረብ ላየው ማዕበል ያሰማው ጥልቅ የሆነ የወዮታ ጥልቀት ልክ ነው፣ ያንን ባይበልጥ እንኳ፣ ከኖረበት ጠሊቅ ወዮታ አንጻር፣ እራሱን ሊገልጥ ከሰሜን እየመጣ ያለውን የአውሎ ነፋሱን ብርታት፣ ታላቁን የደመና ክምችት፣ የእሳቱን ወላፈን፣ ከመድረሱ አስቀድሞ መላውን የፓለስታይንን ድንበር አድማሱን ከቦ ተሰብስቦ ያለውን የማዕበሉን ጫፍ ዘርፉን ማየት የቻለ ነው (ስታንሊ)። በታሪኩ ውስጥ ሕዝቅኤል የነበረው መቼት እንዲህ ያለ ነበር።

ሕዝቅኤል በባቢሎን ምርኮ ለነበሩ ግዞተኞችና መንፈሳዊ ዐመፅ በሞላበት በኢየሩሳሌም አካባቢ ለነበሩት ምርኮኞች የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደሆነ ማሳወቅ ነበረበት፣ በስደት ያሉትን የአይሁድን ክፋት በማጋለጥ ሁሉንም ከእይታቸው ውጭ አርቀው ለመቅበር ብዙ በሚደክሙ በማያምኑ ምርኮኞች መካከል እየኖረ እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሆኖ በጽናት ቆመ። ምርኮኞቹ ሕዝቅኤል የሚናገረውን ለመስማት ይፈለጉ፣ ምናልባትም የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማወቅ ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን የሚሰሙትን ነገር አልወደዱትም። አብዛኛው ሕዝቅኤል የሚያመጣው መልእክት “ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” (ዕብራውያን 12፥ 3) በሚል ለክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ ለእርሱም ብዙ ፈተናና ሥቃይ አድርሶበታል።

ሕዝቅኤል ሃይማኖትን፣ ዘርን እና ቁሳዊ ነገርን ብቻ ማእከል ያላደረገውን የእስራኤልን መንፈሳዊ ሕይወት እና ተልዕኮ እውነተኛ ዓላማ እና ትክክለኛ ተፈጥሮ ለመመለስ እና እንደገና ለማደስ የሚፈልግ የተሃድሶ ነቢይ ነበር። እንደ ነብዩ ዕንባቆም ሁሉ፣ ሕዝቅኤልም ተስፋ ቢስ የሆነ ያህል ቢመስልም የግድ ግን ጠባቂ ደግሞ ነው። “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ። እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ፦ አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው። ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2፥ 1-3)

ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር መንግሥት ውጫዊ መሠረትና መዋቅራዊ መልኩ ሲፈርስ፣ በእግዚአብሔር እና በእምነት ላይ ያለው ማንኛውም ፍላጎት የወረደ መስሎ ሲታይ ያኔ የጌታን እውነት ደረጃውን ከፍ አድርጎ በማሳየት እየሞቱ ያሉትን ምርኮኞች የረሱትንና የማያውቁትን አምላካቸውን እንዲያውቁ እና እንዲታመኑት ማድረግ ይገባዋል። “ሕዝቅኤል እንዲይዘው የተጠራው ፍጹም የተለየ ሥፍራን ነበር። ጥሪውም የነቢይ ልዩ ሥራ እና ጥሪ ነበር። ከመወለዱም ጀምሮ በልዩ ልዩ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያደረ የክህነት መሰረት ያለው ነው፤ በተለይም መለኮታዊው መንግሥትን በተመለከተ ስላሉ ውስጣዊ ጉዳዮች የተለየ ትኩረትን ያደረግ ነበር። ከፍ ያለ ጥሪ እና የነቢይ ተአምራዊ ስጦታዎች የተሰጡትም መሰረታዊ ከሆነው ከዚህ መንፈሳዊ ጥሪው ጋር በተያያዘ ነው። እንግዲህ በግዞት ወደ ምርኮ ተወስዶ ለአገልግሎት ሲላክ የአገልግሎት ኃላፊነቱ ለጊዜው በኢየሩሳሌም ቆሞ ካለው ከሚታየው ተዳሳሽ ቤተ መቅደስ በከለዳውያን ምድር ወደሚጠብቀው ወደመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንዲዛወር፣ መደበኛና የተለመደ አይነት ከሆነው አገልግሎት ወደተመረጠና ከፍ ወዳለ ዓይነት አገልግሎት እንዲወጣ ተደርጓል። ስለዚህ፣ የመንግሥትን ተግባራት መምራት፣ እና የመንግሥት ጉዳዮችን ማሳለጥ የዳንኤል እጣ ክፍል የሆነውን ያህል፣ እግዚአብሔርን ወክሎ በሰዎች ልብ እና ሕሊና ውስጥ የእግዚአብሔርን ምክር ለማሳለጥ እና የእውነትንና የጽድቅን ደረጃ ከፍ አድርጎ ለማሳየት የተጠራው ደግሞ ሕዝቅኤል ነበር። አንዱ ዓለም አለኝ በምትሉው ግርማ ሞገስና ከበሬታ በተላበሱ ቦታዎች ላይ ሆኖ የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት ወክሎ ሲጋደል፣ ሌላው ደግሞ በምርኮኞቹ የአይሁድ ማኅበረሰብ እቅፍ ውስጥ ተሸርጠው ከተቀመጡት የክፋት ዓይነቶች ጋር መጋደልና እነዚያን የእግዚአብሔርን ርስት የሚያበላሹትን ርኩሰቶች መታገል ነበረበት” ሲል ፓትሪክ ፌይርበርን ይጽፋል። 

በመንፈስ እንመራለን በሚሉ ሐሰተኛ ነቢያት ሰበብ በኢየሩሳሌም የነበሩት አይሁዳውያን እግዚአብሔር የሰጣቸውን የመጀመሪያ የተስፋ ቃል እርሱም ያንን ምድራዊ ርስት ፈጽሞ ላለማጣትና በዚያም እስከ መጨረሻው ድረስ ለመታገል ቆርጠዋል። በዚህ ምክንያት ኤርምያስ እና ሕዝቅኤል በህዝባቸው መካከል እንደ አክራሪና እንደ ጽንፈኛ ቢያስቆጥራቸውም፣ ወደ ምድራቸው ከመመለስና ከመታደስ የተስፋ ቃል ኪዳን ጋር አይሁዳዊ በሆነው ኃጢአት ላይ እና እየመጣ ባለው ፍርድ አንጻር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መጮህ ነበረባቸው። እግዚአብሔር ከተቀደሰችው የእስራኤል ምድር በላይ ሊሰራ እንደሚወድና የሚገዛ መሆኑን እንደመቀበልና ከዚህ እውነት ጋር እንደመኖር ያለ እንደሚጠሉ ሌላ ነገር የላቸውም። አምላክ ከተቀደሰች አገራቸው ውጭ የሚናገር ስለመሆኑ ወይም ከምድሪቱ ውጭ በሚደረግ ነገር ስለመቀደሱ ወይም እንዲህ ያለ ማናቸውንም ዓይነት ሐሳብ ማሰብ ርኩስ ነገር እንደሆነና፣ የአምላክ እውነት ከቅድስት አገር በቀር በተለይም ከመቅደሱ በቀር በሌላ በየትም ቦታ ቢገለጥ ያንን በቁላሉ የማይታገሱት እንደሆነ አለን በሚሉት የተለየ እድል የሚመኩበት የኖረ ኩራት አላቸው። 

ነገር ግን ሕዝቅኤል በምርኮ አገር በግዞት መካከል ያቀረበላቸው ጥሪ እግዚአብሔር ከባቢሎን ጨለማ ምድር ነቢይን ጠርቶ ቃሉን ስለሰደደላቸው ይህ የእግዚአብሔር ቸርነት ማለቂያ የሌለው እንደሆነ ግልጽ ያደርግላቸው ነበር። እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ የሚሰራ፣ ከጨለማም ብርሃንን የሚያወጣ የማይገመት አምላክ ነው። የሕዝቅኤል ትንቢቶች ተራ በተራ ሳይቋረጡ የፈሰሰሱት በተረገመው የአሕዛብ ምድር ላይ ሳሉ ነው። ከሰማያት የሆኑት ብርሃናት እውነት የተራቡትንና በእርሱም የታመኑትን ዓይኖች ሲከፍቱ፣ ያኔም ንስሐ የሚገቡ እና ራሳቸውን የሚያዋረዱቱ የነቢዩንም መልእክት የሚረዱቱ የእግዚአብሔርን ሰማያዊ ክብር ለማየት ወደዚያ ብርሃን ዘልቀው መግባት ይችላሉ። ጌታ ሰማያትን ሲከፍት ለአገልጋዮቹ አዲስ ራዕይን ይሰጣል፣ ይህም አሰራሩ በአዲስ ኪዳንም ውስጥ በጉልህ ይታያል።

ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ማቴ. 3፡16፣ እስጢፋኖስም በሰማእትነት በተሰዋ ጊዜ፣ የሐዋርያት ሥራ 7፡56፣ እና ጌታ ኢየሱስም በትንሳኤው ጊዜ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር በኤማሁስ መንገድ ላይ ሲነጋገር ልባቸው በተቃጠለ ጊዜ ይህ እንደሆነ አስቡ።

የእግዚአብሔር ራእይ፣ የተከፈተስ ሰማይ ከባቢሎን ይገኛልን? መልካም ነገርስ ከናዝሬት ሊወጣ ይችላልን?፣ የእግዚአብሔር ፀጋ እውነተኛ ምስክርነትስ ከጣዖት ምድር ከሚፈለቅ ከተበከለው የአህዛብ ወንዝ ከኮቦር ሊቀዳ ይችላልን?

የእግዚአብሔር ሕዝብ ያለበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ በየትም ስፍራ ቢሆኑ እንኳ የእግዚአብሔር ቃል ግን በኢየሩሳሌም ሳሉ በኤርምያስ በኩል፣ በባቢሎን ሳሉ በዳንኤል በኩል፣ በኮቦር ወንዝ ሳሉ በሕዝቅኤል በኩል ይመጣ ነበር። ከቅድስት አገር ተነቅለው፣ ከመቅደሱም ርቀው ባሉበት የግዞት ምድርም ቢሆን እንኳ ቃሉ አልተዋቸውም። እርግጥ ምርኮኞቹ በአረማውያን ገዥዎቻቸው ክትትል ስር ሆነው ራሳቸውን ግን እንዲያስተዳድሩ እና የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን እንዲመሩ የተወሰነ ነፃነት ተፈቅዶላቸው ነበር። ምንም እንኳን ምርኮኞቹ ለብዙ አመታት በተወሰነ ጥብቅ ተግሣጽ ሥር ቢቆዩም፣ አሁንም ያለፈውን ክፉ መንገዳቸውን ከመከተል አልተመለሱም። ይልቁንም በቅርቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመለሱ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል፣ የግዞቱም ዘመን አጭር ነው በሚል አጉል ተስፋ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን በመለኮታዊ ፍርድ ሥር መሆናቸውን ሳያዩ፣ የደረሰባቸውን ተግሳጽ ሳይገነዘቡ ቀርተው ነበር።

ስለዚህ ክህነቱን ያጣው ሰው፣ ያ በኢየሩሳሌም ቆሞ ባለው ተዳሳሽ ቅዱስ ቤተመቅደስ ውስጠኛ ክፍል የመግባት እድልና ጥሪውን ያጣ ሰው፣ አሁን ነቢይ ተብሎ ለመጠራትና በኪሩቤል ላይ ከተቀመጠው ከእግዚአብሔር ዙፋን ሰረገላ ላይ ቆሞ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዲሰማ ወደ መቅደሱ መግባትን አገኘ። የሕዝቅኤል ትንቢት መለኮታዊ ቅደም ተከተል በራእይ፣ በሸክም እና ትንቢትን በመናገር ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚህ፣ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዳልተገደበ ወይም እንዳልተውሰነ ያውቅና ያይ ዘንድ፣ አሁንም በባቢሎን በግዞት ላሉት ለመልካሞቹ በለስ እና በኢየሩሳሌምም ለቀሩት ለክፉዎቹ በለስ፣ እንዲሁም ለአሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር “እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ታውቃላችሁ” ሲል እንደተናገረው ያለ መልእክት ይኖረው ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ ቅጣትን የሚያስከትልባቸውን የኃጢአት ብዛት ያውቁ ዘንድ የክብሩ መገለጥ ከሆነውና በሉአላዊነት ከሚሰራው የእግዚአብሔር ህልው ዙፋን፣ ከዚያም ከተንቀሳቃሹ የእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ሆኖ ራእዩን ያሳየዋል። ቅጣቱም በእግዚአብሔር የጽድቅ መርሆ ላይ የተመሰረተ የኃጢአት ቅጣት ነው። ተሀድሶውም የተማረኩት ግዞተኞች ንስሃን እንዲያደርጉ፣ እንዲለወጡ፣ ብሎም ወደ ጽድቅም እንዲደርሱ የቀረበ ትንቢታዊ ጥሪ ነው።

ጥሪውም አዲስ የሕይወት ተስፋን ይሰጣል፣ አዲሱንም እረኛ ያስነሳል፣ እርሱም አዲስ የሆነ የሰላም ቃል ኪዳን ከበረከት ዝናብ ጋር ይመግባቸዋል። ንጹሑን ውሃም በአዲሱ ልባቸውና በአዲሱ መንፈሳቸው ላይ ይረጫቸዋል። ለደረቁ አጥንቶቻቸውም ሕይወትን ይሰጣል፣ ጠላቶቻቸውንም ለማጥፋት እንደ ኃያል ሠራዊት ያስነሳቸዋል፤ በውጤቱም የታላቁ ቤተ መቅደስ አዲሱ ሥርዓት በሚሄድበት ስፍራ ሁሉ እውነተኛ የሆነ መንፈሳዊ ፈውስን የሚያፈስ የሕይወት ወንዝ እንደ ጅረት ያፈልቃል።

gkr


ክፍል ሦስት

የሕዝቅኤል መጽሐፍ መንፈሳዊ ጠቀሜታ

ሕዝቅኤል በእግዚአብሔር የክብር ዙፋን ሠረገላ ፊት እንዳለ ካህን ሆኖ አዲሱን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አይቶ ነበር።

እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ። (መዝሙር 99፥ 1)

ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ። (መዝሙር 80፥ 1)

ሕዝቅኤል ዐውሎ ነፋስና ደመና፣ እሳትና ብርሃን በክብር ሲያበራ፣ አይኖች የተሞሉት የሚሽከረከሩ መንኮራኩሮች፣ አራት ሕያዋን ፍጥረታትም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ በአንድነት ሲንቀሳቀሱ አየ። ከከፍታ ጠፈርን አየ፣ ከላይም ድምፅን ሰማ፣ የዙፋን አምሳያና የሰው ልጅም በዙሪያው በብሩህ ብርሃንና በቀስተ ደመና መልክ ተገለጦ ተመለከተ። የሚያየው ነገርም ማለቂያ የሌለውን የእግዚአብሔርን አደራርግ፣ የሕይወትን መንፈስ፣ በመንፈሳዊ የእውቀት አይኖች ብቻ የሚታየውን በብርሃንና በእሳት አምሳል የሚገለጠውን የጌታን ክብር የሚያመለክተውን ራእይ ነበር። ይህም ራእይ የክርስቶስን እና በእርሱ የሚመራውን ሰማያዊ ጉባኤ የሚያመለክት ምሳሌያዊ ነበር፣ ይህም አስፈሪ የሆነውን የእግዚአብሔርን ግርማ የሚያሳይበትና በደካማ እና በኃጢአተኛ ሕይወታችን ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ይገልጣል።

የእግዚአብሔርን ቤት፣ እና መቅደሱን፣ ክርስቶስንም በግርማ ዙፋኑ ላይ ከፍ ብሎ እዩት፣ ይህም የእግዚአብሔርን ፍፁም ሉዓላዊነት ያመለክታል። ጌታ በሁሉም ላይ እና በሁሉም ስፍራ ሆኖ ሲገዛ ከምድራዊው መቅደሱ የአምልኮ ስርዓት ጋር በተያያዙ ምልክቶች ላይ ሆኖ በክብር ይታያል። እርሱም በሰማይ እና በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሁሉን ቻይ ንጉስ ነው፤ እርሱም የሉዓላዊነቱን አላማ በማይከለከል ዘላለማዊ ኃያልነቱ ይፈጽማል፤ እንግዲህ እዚህ ግርማ ጋር ሲደረስ ሰው የሚቀረው በቸኛና ትልቁ እድሉ እንደሞተ ሰው በድንጋጤ በግንባሩ ወድቆ መስገድና ማምለክ ነው፣ ይህም የግርማውን ብርሃን ማየት ከታደለ ሰው ሁሉ የሚጠበቅ ነው። ያየውም ነገር ሁሉ ማለቂያ የሌለውን የእግዚአብሔርን አደራረግ፣ የሕይወትን መንፈስ፣ በዙሪያውም ሁሉን የሚመሩምሩና የሚያውቁ አይኖች የሞሉበትን፣ መንፈሳዊ አይኖችን ከፍቶ እውቀት የሚሰጠውን በብርሃንና በእሳት የተከበበውን የጌታን ክብር ነው።

ስለ ዙፋኑ ሠረገላ በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የሚታየው ነገር በታሪክ ውስጥ ባሉ መንፈሳዊ ኃይሎች እና ሁነቶች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያለውን ፍፁም ገዥነቱን የሚያመለክት ሲሆን ሁሉም ኃይላትና ሁነቶች ደግሞ በራሳቸው ሊቆጣጠሩትና ሊገዙት ከሚችሉት በላይ ከንቃተ ህሊናቸውና ከእውቀታቸው በሚያልፍ መገዛት የአላማው መሣሪያዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

አሁን የጌታ የተቀደሰ መቅደሱ በእርሱ የተቀደሰው ማኅበሩ ነው፣ እርሱም አካሉ፣ የመንግሥቱና የአገዛዙ መቀመጫ የመገኘቱም የመጨረሻ ማረፊያው ነው።

እስራኤል የገባችበት ውድቀት የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ሊነካ እንደማይቻለው፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም እርሱ ግን አሁንም በሉዓላዊነቱ ጸንቶ እንደሚኖር እና በሁሉ ላይ ነግሶ እንደሚገዛ ሕዝቅኤል ያሳያል።.ዙፋኑ በሕዝቅኤል ዘመን በሰማያዊ ንጽህናው ጸንቶ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም እንዲሁ በገዛ ጉባኤው ላይ በነጽህናው አርፎ ይኖራል።

እግዚአብሔር ከአሕዛብ፣ ከእስራኤል ወይም ከቅዱሳን ማኅበሩ ጋር ያለው ግንኙነት ለክብሩና ታላቅ ስሙን ለማክበር ባለው አላማ ስር የተገዛ ነው።

“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም።” (ሕዝቅኤል 36፥ 22)

እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚያደርገው ህብረት በዓለም ሁሉ ፊት ራሱን ለመቀደስና እርሱ በእውነት እንዳለ እንደ ማንነቱ ራሱን ለመግለጥ ካለው እጅግ የላቀ አላማው በታች የተገዛ ነው።

ሕዝቅኤል ጊዜያዊ ሁኔታውን ለማየት ችሏል፣ ነገር ግን በግዞት ቤት በምርኮ ሆኖ ያሳለፈበትን ጊዜ ምን መንፈሳዊና ዘላቂ ትርጉም እንዳለው ለማየት ደግሞ ተችሎታል። በኤርምያስ አፍ ለአይሁድ የተናገረው ቃል ይኸውም ቤተ መቅደሱ ተመልሶ በኢየሩሳሌም ሊገኝ አለመቻሉን ሲያይ፣ በአንጻሩ ግን በበላይ የተከፈተ ሰማይን እና የአምላክን ራእይ ለማየት ተችሎታል። በዚያ የባቢሎን ምድረ በዳ ሊማርባቸው የተዘጋጁ የጥናትና የምርምር፣ የትምህርት ተቋማት አልነበሩም፣ ወይም ሊያስተምሩት የሚችሉ የሴሚናሪ ምሁራኖች ወይም ቤተመጻሕፍት፣ አልያም ስብከት የሚሰማባቸው ሜጋ የሆኑ ታላላቅ ጉባኤዎች ወይም ህብረት የሚያደርግባቸው መለስተኛ ጉባኤያት ወይም የቲ.ቪ ሰባክያንና ሌሎች ሐሰተኛ የዩቱብ ነቢያት አልነበሩትም። ሕዝቅኤል ያየው ያ የተለየና የከበረ፣ በየትኛውም ምድራዊ ኢንስቲትዩት ኮርሱ የማይሰጥ ሰማያዊው ራእይ ግን በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን በክርስቶስ ያለውን እግዚአብሔርን የመምሰል ታላቅ ምስጢር ይገልጣል። “ እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፦ በሥጋ የተገለጠ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ ለአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ፣ ነው” (1ጢሞቴዎስ 3፥ 16)።

በሕዝቅኤል ራእይ በኪሩቤል ላይ የታየው የእግዚአብሔር መገለጥ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ በግልጽ የሚታይ ነው፣ የእግዚአብሔርን መልክ የሚወክሉ እነዚያ የሕዝቅኤል ራእይ አራቱ እንስሳት በወንጌላት ውስጥ በክርስቶስ ሕይወት የተገለጠውን መልክ ይዘዋል።  

  • በማቴዎስ ወንጌል እንደ ቀረበው ከሆነ ክርስቶስ እንደ አንበሳ ነው፣ ይህም አንበሳ የአራዊት ንጉሥ እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም ንጉሥ የይሁዳ አንበሳ መሆኑን የገለጠና እንደ ንጉሥ በሰዎች መንግሥት ላይ የሚሰለጥንና የሚገዛ መሆኑን ያሳየበት ነው።  
  • በማርቆስ ወንጌል እንደቀረበው ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ የሚያሳየው ደግሞ ክርስቶስ እንደ መሥዋዕቱ በሬ አገልጋይ መሆኑን ያሳየበት ነው። 
  • በሉቃስ ወንጌል መሠረት ደግሞ እግዚአብሔርን የሚመስል በጎ ምግባራትን እና መልካም ምግባሮችን የሚያሳይ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የእግዚአብሔርን ፍጹሙን ሰው ያሳያል። በመጨረሻም፣ 
  • በዮሐንስ ወንጌል መሰረት የእግዚአብሔርን ልጅ በአምላክነቱ ሲገልጠው እነደ ንስር ያቀርበዋል።  

ሰው በሚለው ጀምረን ካየነው አጠቃላዩ የክርስቶስ ማንነት በእግዚአብሔር አሰራር ውስጥ ሂደቱ በአራቱም መልክ ተገልጧል። ፍጹም ሰው ሆኖ ከሴቲቱ ዘር ሲወለድ ከሕግ በታች፣ ከውኃና ከደም በመወለድ ሥጋና ደም ለብሶ እናየዋለን። አምላክ ሰው ሆነ፣ ሕፃን ሆነ አንበሳም ሆኖ አደገም። 30 ዓመት በሞላውም ጊዜ የሰይጣንን አገዛዝ ለማፈራረስና ለመሻር መንግስቱንም በጽድቅ ለማጽናት ደፋር የአራዊት ንጉሥ ሆኖ በአባቱ ተቀባ። ከዚያም ለአብ በመታዘዝ ራሱን አዋርዶ የመጨረሻው መስዋዕት እስኪሆን ድረስ ለመስዋዕት እንደቀረበ በሬ ለዓለም ኃጢአት የቀረበ የዕርገት መስዋዕት ይሆን ዘንድ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ሕማምን እና በሽታን ሁሉ እየፈወሰ አገለገለ። በሲኦል ቆይቶ ከሦስት ቀናት በኋላ ከሞት በመነሳት፣ የትንሳኤ ጌታ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በኃጢአትና በሞት ላይ የተቀዳጀውን ድል ለአባቱ ክብር ለፍጥረት ሁሉ እያበሰረ እንደ ንስር ወደ ሰማያት ከፍ ከፍ እያለ ወጣ።

በሕዝቅኤል ራእይና እና ኋላም በወንጌላት የተገለጠው የእግዚአብሔር ባህርይ [እውነተኛ ተፈጥሮው] በሰው ልጆች ላይ የተዘረጋ የጨለማውን መጋረጃ በክርስቶስ ለማንሳት የተጠቀመበት አሰራሩ ነው፤ ሰው በሆነውና በእግዚአብሔር የክብር ዙፋን ላይ በተቀመጠው በክርስቶስ ኢየሱስ ህይወት እና ማንነት የተገለጸውን ወሰን የለሽ አላማውንና አስደናቂ ብርሃኑን እንዲሁም በእርሱ የሚሰራውን የህይወት ኃይል ዘላለማዊ እውነታ ያሳያሉ። ሕዝቅኤል በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ ይህ መገለጥ እና ራዕይ እራሱን በሥጋ የመግለጥ ምስጢር መቼ እና እንዴት እንደሚሰራ በትክክል አያውቅም፣ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ከመታወቅ የሚያልፉ እውነታዎች፣ ይኸውም እርሱ በአገልግሎትና በመስዋዕትነት ብቸኛ የበላይ እንደሆነ በዘመኑ አይቷል። ሕዝቅኤል ራሱም ሆነ ምርኮኞቹ አይሁድ ሁሉ ዛሬም ቢሆን መላው የእግዚአብሔር ጉባኤ "እግዚአብሔርን ያውቁት ዘንድ" አሁን እዚህ በመካከላችን ከእኛ ጋር እንዲሁም ለዘላለም በህያውነት በሁሉ ስፍራ ያለ አምላክ መሆኑን ማለትም "እግዚአብሔር በዚያ እንዳለ"፣ መማር አለባቸው። የሕዝቅኤል ወንጌል የእግዚአብሔርን እውነተኛ ተፈጥሮ፣ ባህርዩን ለማወቅ እና ማንነቱን ለመረዳት በፍርድ፣ በተሃድሶ እና በፅድቅ ወደ ጌታ ፊት ግቡ እያለ እየተጣራ ነው። ይህ ዛሬ ለእኛ እንደ ትንቢት የሚሠራ አይደለም፣ እግዚአብሔር ራቅ ባለ ቦታ በሚገኝ አንድ ሳጥን ውስጥ ተቆልፎ እንደተቀመጠና እንደተወሰነ እንደ አንድ የሆነ ነገር ሳይሆን፣ ይልቁንም በሁሉ ስፍራ ያለና የሚገኝ መሆኑን እንደ እግዚአብሔር ጉባኤ እንድንማርና እንድንረዳ እንደ መመሪያ ሆኖ የተሰጠን ነው። እርሱ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም “አማኑኤል! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ሆኖልናል። መቅደሱ፣ እርሱም ማኅበሩ ደግሞ የእግዚአብሔር በምድር ላይ መገኘት የሚገለጥበት የክብር ዕቃ ሊሆን ይገባዋል። እርሱም በተሃድሶ የተገለጠ የቲኦክራሲ አገዛዝ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። ይህም የክብር ዕቃ የድኅነት፣ የመታደስ እና የእግዚአብሔር ጸጋ መልእክት ወደ ዓለም ሁሉ የሚፈስበት ምንጭ ነው።

የመንፈሳዊ አገልግሎት ፍላጎትና አቅርቦት

ጂ ካምቤል ሞርጋን ስለ ዳንኤል በሰጠው ትንታኔ እንደተናገረው፣ የዚያ ዘመን ታሪካዊ ሌሊት ትንቢታዊ የሆነ ብርሃን ያስፈልገው ነበር ብሏል፤ እንደዚህ ባለው አስቸጋሪ ተግባር ውስጥ እንደ ኢየሩሳሌም፣ እንደ ባቢሎን፣ እና በኮቦር ወንዝ ዳርቻ እንዳሉ የጨለማ ስፍራዎች ላይ ሰማያዊ ራዕይንና ብርሃንን የማምጣት ሥራ ውስጥ ማንን እናገኛለን? ነብያቱ ኤርምያስ፣ ዳንኤል እና ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እነርሱ ሲመጣና የእግዚአብሔርን ራእይ ሲያዩ፣ ያኔ እንደ ሞኞች ይቆጠሩ ነበር። ባለራዕይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስም ራሱ እንደ ሞኞች ሆነው ዋጋ ከፍለዋል። ሕዝቅኤል ከምርኮኞቹ ጋር የገጠመው ፈተና ለእነዚያ መንፈሳዊ እውነታን መረዳት ለማይችሉና የእግዚአብሔርን ፍትህ፣ ጽድቁንና እና በጸጋ የተሞላውን የምህረት ቀስተ ደመና ማየት ለተሳናቸው ዓይነ ስውራን ለሆኑ አናሳ ምርኮኛ ነፍሳት የጌታን ቃል ማምጣት ነበረበት። ይህም ቃል በሚመጣው መሲሐዊ ዘመን ወይም በአዲሱ ኪዳን ዘመን የሚከፈትላቸው ነው። እነርሱ ግን በሚመጣላቸው የእግዚአብሔር የበረከት ቃል ውስጥ የሚደመጠውን የድምጹን ጥዑመ ዜማ ለመስማት የደነቆሩ ነበሩ። የሕዝቅኤልና የኤርምያስ ቃል ካልታያቸውና ካልተጠነቀቁ ድግሞ ምድሪቱን ወደ ጨለምተኝነት እና ወደ ምናምንቴነት እንድትወርድ ያደርጓታል።

ሕዝቅኤል ሰማያት በተሞሉት ነፃነት ውስጥ እየተመላለሰ፣ ከኢየሱስ ጋር በገበታው ተቀምጦ ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንና መንፈሳዊ ራእዮችን ሲከፍት ተችሎታል። ሕዝቅኤል ለእስራኤልና ለአሕዛብ የተናገረው ቃል፣ ፣ የሞራል ልዕልና፣ የኃጢአት ወቀሳ፣ እና ክፉ የሆኑ የሰው ልጆች ሊተነፍሱት የማይችሉት አዲስ የሞራል ድባብን የያዘ “የሕይወት ራእይ” ነበር። ሕዝቅኤል መለኮታዊ ምሥጢርን ለመግለፅ በመንፈስ የበቃ፣ አይኖቹ የተከፈቱለት ነብይ ነበር እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት የሚሞክር ምሁር አልነበረም።

ሕዝቅኤል እውነተኛው መንግሥት ምን እንደ ሆነ ለማወቅ፣ መስቀሉን፣ ደሙን፣ እውነተኛውን የክህነት አገልግሎት እና የስርየትን ሚስጥር ለማወቅ ይማር ዝንድ በመዋረድና በስብራት ወስጥ እያለፈ ነበር። ለራዕዩና ለትንቢቱ ይዘጋጅም ዝንድ በምስጢሩ ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በእግዚአብሔር ዙፋን ሠረገላ አጠገብ እግዚአብሔርና እርሱ ብቻ በሚገናኙበት በኮቦር ወንዝ አጠገብ ብቻውን ይገኝ ነበር። ሕዝቅኤል ሰባኪ ካህን ብቻ አልነበረም፣ ይልቁንም የሚሰማ ድምጽም ጭምር ነበር። እግዚአብሔር በሕዝቅኤል ሲናገርና ሕዝቅኤል ትንቢቱን ሲጽፍ እስራኤል ያኔ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት አስፈልጎት ነበር፣ ያም ድምጽ ደግሞ ሕያው የእግዚአብሔር መልእክት ነው። ሕዝቅኤል በባቢሎን ላሉት አድማጮቹ ሊጠቅማቸው የሚችሉትን እነዚህን ቃላት ሐዋርያው ​​ጳውሎስም በጲስድያ በምትገኘው አንጾኪያ በነበረው ምኩራብ ውስጥ፦ “በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤” (ሓዋርያት ሥራ 13፡ 27) ሲል አስተጋብቶታል።

ተጭኗቸው ከነበረው ብሄራዊ ጭፉንነት የተነሳና በዚያ በሚገድል የፊደል ስርአት ባርነት ውስጥ በመሆናቸው የእግዚአብሄርን ድምጽ እንዳይሰሙ ተስቷቸው ነበሩ፣ ሕዝቅኤልም ከነበረባቸው ዓይነ ስውርነት፣ ከግራ መጋባታቸው እና ከአቅመ ቢስነታቸው ጋር መስማማት አልተቻለውም ነበር።

ሕዝቅኤል እየተናገረ ያለውና የሚጽፈው ቃል በኢየሩሳሌም ከሚገኙ አንዳንድ የጥናትና የምርምር ተቋማት ከእነርሱ የተማረውን የተጠኑ የጽሑፍ ግልባጮችን ይዞ የሚናገር አልነበረም። እንደ ነቢይ ለመናገር፣ ንግግሩን አደራጅቶ አልቀረበም፣ ኮሚቴም አላቋቋመም፣ ወደ ወግ ወይም ወደ ሥርዓት አልወረደም፤ አዲስ የእምነት መግለጫዎችንም አላዘጋጀም። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በመድረክ አሙቁልኝ ጩኸት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕሎች፣ በሥርዓተ አምልኮ፣ በአልባሳት፣ በገጽታ ግንባታ ፣ በድራማ ትዕይንታዊ አቀራረብ፣ በድምጾች፣ ብልጭ ድርግም እያለ ውበትን በሚከስት ብርሃንማ ስሜታዊ አቀራረብ የነፍስን ስሜቶች እየማረከ አልቀረበም። ይህ የነቢያት ጉዳያቸውም፣ ጭንቀታቸውም አልነበረም፤ እንዲህም ያለ የእግዚአብሔር ነቢይም የለም!

የሕዝቅኤል መጽሃፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስም ራሱ ለመንፈሳዊ ሰዎች ብቻ ክፍት ነው እንጂ የተዘጋ መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በዚያን ጊዜም ሆነ ገና ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ሕዝቅኤል ለእስራኤልና ለአሕዛብ ሁሉ እየነገራቸው ነበር። በዙፋኑ ሰረገላ ላይ ከፍ ብሎ ያለው ያ አምላክ-ሰው ፍርድን፣ መመለስንና፣ መንፈሳዊ መነቃቃትን ወይም ተሀድሶን በሚመለከት ሁሉንም ነገር በሃይሉና በስልጣኑ በሰማይ እና በምድር ይገዛል ያስተዳድራልም። እርሱም ሁሉ የሚሰፈርበትና የሚለካበት የሁሉ ሚዛን ነው፣ ሁሉም ነገር የሚለካውና የሚሰፈረው በዚህ ሰው መሰረት ነው፤ እርሱም ወሰን የሌለውን የእግዚአብሔር አላማ እውን ለማድረግ ብቃት ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ መገለጥ ነው። የዚህ መጽሐፍ የመጨረሻው ፍጻሜ እና ታላቁ ዓላማ፣ እንዴት እንደሚጠናቀቅ የሚያሳየን ቃል "እግዚአብሔር በዚያ አለ' በሚለው ሐረግ ውስጥ ተሰብስቦ ይገኛል። ምንም ያህል አሁንም የሰው ኃጢያተኛነት፣ ዓመፀኛነት እና ውድቀት ቢኖርም እግዚአብሔር ግን ለክብሩ ሲናገር ይኖራል፣ የድል አድራጊው የእግዚአብሔር ዙፋን አሁንም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በመንግስቱና በአህዛብ ሁሉ ላይ በጸጋው በሚገዛ በዚያ ሰው በኩል ንቁና የሚሰራ ነው።

gkr

ክፍል አራት

ሕዝቅኤል ፡- የእግዚአብሄር ወሰን አልባነት፣ የክርስቶስንና የአካሉንም ሁሉን አቃፊነት ይገልጥልናል

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ መመራት ያለበት በመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው - የመለኪያውም በትር መንፈስ ቅዱስና ክርስቶስ ነው። እርሱ እንደ እግዚአብሔር አሳብ የሆነ የእግዚአብሔር ቤት መለኪያ ነው፤ ሕዝቅኤል በአገልግሎቱ የሚገልጠው ቅድስናንና፣ መለየትን፣ ተስፋፍቶ መዘርጋትን ሲሆን፤ በክርስቶስ ታላቅነት እንዱሁም የክብሩ ስፍራ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት፣ ግዛቱና ዙፋኑ እንዲሆኑ እርሱ ለጠራቸው ለማህበሩ በሚቀና ሞልቶ በሚፈስስ ሸክም ያገለግላል። በሕዝቅኤል ውስጥ የእውነተኛው መንፈሳዊ አገልግሎትና የሕይወት ሥርዓት፣ ሁሉም ነገር የሚለካው በክርስቶስ ነው። ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ዓላማ፣ የእግዚአብሔርን መንገድ እና "እግዚአብሔር በዚያ አለ" ያህዌ ሻማ! የተባለላትን የእግዚአብሔር ቤቱ የሆነችውን ከተማ በሚገባ ተረድቷል።

የሕዝቅኤልን መጽሐፍ እና የዮሐንስ ራእይን መጽሐፍ በንጽይር የሚያቁርቡ አንዳንድ ምንባባትን ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርበዋል። ሐዋርያው ​​ዮሐንስ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በተቀበለ ጊዜ የሕዝቅኤልን መጽሑፍ እንዴት ባለ መንገድ ጥቅም ላይ እንዳዋለው በዚህ ንጽይር ውስጥ ለማየት እንችላለን።

የሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 እና 39 መግቢያን እዚህ ላይ እንመለከታለን፤ እነዚህ ሁለት ምዕራፎች አይሁዳውያንን ለማጥፋት በሚጥሩና የእግዚአብሔርን መሲሐዊ መንግሥት የትኛውንም ተስፋ ለማብቃት በሚሰሩ በእስራኤል ጠላቶች ላይ እግዚአብሔር ስላደረገው የድል ታሪክ ይናገራሉ።

ያ ያልተማረና በውጭ ባለ የድንቁርና ጨለማ ውስጥ የሚኖረው አረማዊ ኃይል ስለ እስራኤልና ስል አማላኳ፣ እነርሱም ከአምላካቸው ጋር በነበራቸው የኖረ ታሪክ ስላገኙት መለኮታዊ መገለጥ እና ስላዩት የዘላለም ኃይሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለውም። አሁን በግዞት ምርኮኛ ሆነው ያሉት አምላካቸው ሊጠብቃቸውና ሊታደጋቸው አቅቶት ስለተሸነፈ ሳይሆን ይልቁንም ከቅድስናውና ከጽድቁ የተነሳ ስለ ኃጢአታቸው ሊቀጣቸው እንደሆነም አያስተውሉም።

ሕዝቅኤል የጎግንና የሰራዊቱን እጣ ፈንታ፣ እነዚህም በእግዚአብሄር በራሱ ወደ ተዘጋጀላቸው ወደ ጥፋታቸው እንደሚመሩ፣ በዚህም ቤተ መቅደሱንና ኢየሩሳሌምን ለመገንባት ከምርኮ የሚመለሱትን የኢየሩሳሌምን ቅሬታዎች እንደሚጠብቃቸው ያሳውቃል። “ነገር ግን ማጥፋት፥ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብን መቍረጥ በልቡ አለ።” (ኢሳይያስ 10፥ 7) እንደተባለው፣ በዚህም አውድ ውስጥ ጥቂቶች ያይደሉ አህዛብን ማጥፋትና ቆርጦ ማስወገድ የእግዚአብሔር ቀጣይ የፍርድ ዓላማ ሆኖ ቀርቧል። አላማውንም እግዚአብሔር ስያስታውቅ፣ “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” (ሕዝቅኤል 38፥ 23) ብሏል።

ጎግ በራሱ ላይ ሊፈፀም ላለው ፍርድ ግልጽ ዓላማ በአይሁድ ላይ ተነስቷል። ሕዝቅኤል ምዕራፍ 38-39 ላይ የተነገረው በእውነት አስገራሚ ትንቢት ነው፣ ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት ብዙዎች እንደተናገሩት፣ ማንስ ሰው ቢሆን በአውዱ እንደተረዳው ወይም እንደሚገባው ሆኖ ማንን ሊያስረዳ ይቻለዋል? ብዙዎች በመገረም እና በጉጉት እየተቃጠሉ፣ ያለ የሌለውን እየቧጠጡ፣ እዚህ ከተገለጠው ጎግ እና ማጎግ በላይ ያለ ሌላ የሌለ ጎግ ፈጥረዋል። የጎግንም ማንነት ለማግኘት ‘ትንቢታዊት ጽዮናዊት እስራኤልን’ በውስጣቸው ስለው፥ ገና ሊመጣ ባለው የወደፊት ጊዜና የአለም ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ያልማሰኑት፣ ያልያዙትና ያልጩበጡት ነገር የላቸውም። ለነዚህ ማሳኞች ግን ከሁሉ አስቀድሜ የምነግራቸው የመጀመሪያ ነገር፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትኛውም መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተነጥሎ መተርጎም ወይም መረዳት እንደማይቻል ልትገነዘቡ ይገባል የሚል ነው። ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የትኛውም ምዕራፍ የንባብ ክፍሉ ከተወሰደበት የመጽሐፉ አውድ ተነጥሎ ሊብራራ ወይም ሊተረጎም አይችልም፣ ማንኛውንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ወይም የመጽሐፉ ምዕራፍም ቢሆን አስቀድሞ በተያዘ ቅድመ ግንዛቤ ማለትም ዘመን ቆጣርያን (Dispensationalists) ወይም የቅድመ-ሺህ አመት አቀንቃኞች (premillennialists) ወይም ማናቸውም የትንቢት ሊቃውንት ነን የሚሉ ሰዎች በሚያደርጉት በኖረው ልማዳዊ የትርጓሜ ዘዴ በመጠቀም ሊፈታ አይችልም። እነዚያ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የተጻፉት ነገሮች ሁሉ ያኔውኑ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ከመሆናቸው ባለፈ ገና አሁንም የወደፊቱን የአለም ሁኔታ ይናገራሉ ብለን አንወስዳቸውም። እኛ ትክክለኛው ግንዛቤ አለን ብለው የሚያስቡ እነዚህ ሰዎች የሚያራምዱትን ተራ የሆነ አሳብ ወዲያ አሽቀንጥረን ጥለነዋል፣ እንደዚህ የሚጫወቱቱ ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት በየጊዜው እነርሱና ትንቢታዊ ግምታቸው እየተለዋወጠ ስናይ ግኝታቸውና አለን የሚሉት ትምህርታቸው የማይረባ ነገር ብቻ እንደሆነ ደርሰንበታል።

ስለዚህ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የምዕራፍ 38 እና 39ን አውድ እንመልከት። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሕዝቅኤል እንዲህ ሲል መጣ፡— “ፊትህን በጎግ (20 ጊዜ) ላይ እና በማጎግ ምድር ላይ … አቅናበት፣ እንዲህም በል፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል (15 ጊዜ) ይልና እንዲህም እንደዚያ፣ም "አደርጋለሁ" ይላል። እግዚአብሔር አደርጋለሁ የሚላቸውን ጉዳዮች ተመልከቱ፦

  • እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንም…ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥ (ሕዝቅኤል 38፥ 4)
  • በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ። (ሕዝቅኤል 38፥ 16)
  • በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ (ሕዝቅኤል 38፥ 21)
  • …በእርሱ ላይ… አዘንባለሁ (ሕዝቅኤል 38፥ 22)
  • (እኔም) ታላቅ እሆናለሁ (ሕዝቅኤል 38፥ 23)
  • እመልስሃለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • እነዳህማለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 2)
  • ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። (ሕዝቅኤል 39፥ 4)
  • በማጎግ ላይ… እሳትን እሰድዳለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 6)
  • ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 7)
  • ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ (ሕዝቅኤል 39፥ 7)
  • የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 11)
  • ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 21)
  • የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 25)
  • ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ (ሕዝቅኤል 39፥ 25)
  • ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ (ሕዝቅኤል 39፥ 25)
  • በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አልተውም (ሕዝቅኤል 39፥ 28)
  • ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም፤ (ሕዝቅኤል 39፥ 29)

ሰው ያስባል፣ እግዚአብሔር ግን ምክሩን ይፈጽማል ማለት ይህ ነው። በታሪክ ወስጥ ሰው ከማሰብ ያለፈ ምንም ሊያደርግ አይችለም፣ ጎግና ጭፍራው እስራኤልም ሁሉም አቅመ ቢስ ናቸው፣ ያስባሉ፣ አንዱ ለማጥፋት ሌላው ላለመጥፋት፣ የሚጸናው ግን የእግዚአብሔር ምክር ብቻ ነው፣ አንዱን ወደጥፋቱ ሌላውን ወደ ድነቱ ያደርሰው ዘንድ ሉአላዊሉ አንድ ብቻነው። በዚህም ጎግ ራሱና በእርሱ የሚመራው ጭፍራው ሁሉ፣ ከምርኮ የተመለሰውም እስራኤል “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” የእስራኤል አምላክ ያህዌ በምድር ኃያላን ላይ የወደደውን የሚያደርግ ሉዓላዊ አምላክ እንጂ "ፈጽሞ ቀን የሰጠው የአንድ ዘመን አምባገነን" እንዳልሆነ አስተውሉ።

ሰው በፈረሱ ለጓምን አስገብቶ እንደወደደ እንደሚያሾረው እንዲሁ እርሱ የጎግን ጭፍራ አፍንጫውን በመንጠቆ ይዞ ወደ ኋላ ሊመልሳቸው፣ ጥፋትንና ሞትን ካገለገሉ በኋላ ራሳቸው ወደጥፋታቸውና ሞታቸው እንዲነዱ ያደርጋቸዋል። ይህም እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት፦ 

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ሲል የተናጋረው ነው። 

ምዕራፍ 39 ቁ 1 “አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ እመልስሃለሁ፥ እነዳህማለሁ፥ ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ። ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፥ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ። አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። አንተ በምድር ፊት ላይ ትወድቃለህ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ በማጎግም ላይ ሳይፈሩም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ አሕዛብም እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነሆ፥ ይመጣል ይሆንማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው።” (ሕዝቅኤል. 38፥ 17- 39፥ 1-8) ሲል እንደተናገረው መሆኑ ነው።

ይህ እንግዲህ የጎግ ሠራዊት በያህዌ ብርቱ ቍጣ የሚጠፋ ስለመሆኑ የሚናገር መግለጫ ነው። ይህ ግን በዚህ ታላቅ ጥፋት ውስጥ ታላቁን ፍጻሜአቸውን የሚቀበሉትን ያኔ ገና ያልተፈጸሙ ትንቢቶችንም አካቶ የቀረበ ነበር። ልብ አድርጉ፦ ያህዌ ፍርዱን የሚገልጽበት ዘዴ በግነታዊ ቋንቋ የተሞላ ነው፣ ወይም እኛ ምስል ከሳች የአነጋገር ዘይቤ፣ የቋንቋ ውበትን የተሞላ፣ አልያም አጽንዖት መስጠት እንደምንለው አይነት ነገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በራሷ በእስራኤል ላይም ሆነ ወይም በእስራኤል ጠላቶች ላይ ያህዌ ቁጣውን ሲገልጥ ለእያንዳንዱ የፍርድ ተግባር ግነታዊ አገላለጽ ጥቅም ላይ መዋሉ የተለመደ ነው። ጌታ ኢየሱስም ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋትና ስለ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት መወገድ ሲናገር ተመሳሳይ ትንቢታዊ ቋንቋ እና ዘይቤ ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 24፥ 29፤ ማርቆስ 13፥ 24፤ ሉቃስ 21፥25)

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጠላቶች እጣ ፈንታ የሚተነብዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እዚህ ላይ እናንሳ፦

ኢሳይያስ 13፥ 10 “የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።”

ኢሳይያስ 13፥ 13 “ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች።”

ጌታ ኢየሱስም ኢሳ.13፥ 10 ላይ “የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።” የሚለውን ጠቅሶ፣ በኢየሩሳሌም ከተማ እና በቤተ መቅደሱ ላይ ስለሚሆነው ጥፋት ሲናገር ሊመጣ ያለውን ይህንን ፍርድ ለማመልከት ተጠቅሞበታል። ኢሳይያስ 13:13 ላይም “ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች።” የሚለውም እንደ ቁጥር 10 ሁሉ በሜዶናውያን እና በፋርሳውያን ስለሚደርስ ፍርድ፣ ባቢሎንም ስለ መውደቋ የተነገረ ትንቢት ነው። ጌታ ኢየሱስ ግን ከዚህ ትንቢት በተወሰደ የቋንቋ ዘይቤ ይህንን ፍርድ በኢየሩሳሌም ከተማ እና በቤተ መቅደሱ ጥፋት ላይ ተጠቀመበት።

ሕዝቂኤል 32፡ 2፣ 7-8 “የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው፦ የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔ” ያህዌ ግብፅን እና ፈርዖንን ሊያጠፋ በተቃረበበት ወቅት በተመሳሳይ ትንቢታዊ ቋንቋ የተናገረው እንዲሁ ነው። እንደገናም በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ኢየሩሳሌም በመንፈሳዊ ምሳሌ በራዕይ 11፡8 ላይ ስትጠቀስ “... እርስዋም…. ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።” በሚል ግብፅ ሆና መገለጧ የአጋጣሚ ጉዳይ አልነበረም፣። ዳግመኛም በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሩሳሌም በመንፈስ ግብፅ ሆና መገለጧ በአጋጣሚ አይደለም በራዕይ 11፡8። ከእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች የምንረዳው ኢየሱስ ባቢሎንን ያገኛት ታሪካዊ ጥፋት በኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሱ ላይ እንዴት እንደሚፈጸም እንዲሁም ዮሐንስ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ የደረሰው ጥፋት በኢየሩሳሌም ላይ የሚደርሰውን ፍርድ እንዴት እንደሚያመለክት እንደተጠቀመበት ያስረዳናል። ሐዋርያው ​​ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ ውስጥ እነዚያ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁድ የእግዚአብሄር ጠላቶቹ በመሆናቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ታላቁን የእግዚአብሔር የቁጣ ቀን በሚያሳይ ቃል ገልጾታል። ይህም በሉቃስ 19፡ 27 ላይ “እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው”፤ እንደተባለው ነው። 

ከሕዝቅኤል ንግግር የምናስተውለው አንድ ነገር እርሱ ቆየት ብሎ የተነበየው ጉዳይ በአይነቱ በአስቴር ዘመን የሚፈጸመውን ነው። እነዚያ አይሁዶች ተማርከው በተጋዙባቸው ግዛት የነበሩ ሰዎች ያኔ ከነበረው መንግስት ጋር ሰላም በነበራቸው ጊዜ ለአይሁድ ግን ጠላቶቻቸው ሆኑ። የሕዝቅኤል መጽሃፍ ጎግ ማንጉግ ሕዝቅኤል በኖረበት የአስቴር ዘመን በአስቴር መጽሓፍ የአይሁድ ሕዝብ ጠላቶች (የእግዚአብሄር ሕዝብ ጠላቶች) ሆነው እንደተገለጡ ሁሉ፣ የዮሓንስ ራእይ መጽሃፍ ጎግ ማንጉግም ዮሓንስ በኖረበት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሄር ሕዝብ የቅዱሳኑ ጠላቶችና አሳዳጆች የሆኑትን ተቃዋሚ አይሁድን የሚያመለክቱ ናቸው። ይህም ለእኛ ምሳሌ ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የማያምኑ አይሁዶች የእግዞአብሄር ቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ሆነው በግዛታቸው ውስጥ አማኞችን ከበው ያስጨንቁ ስለነበሩ በእግዚአብሔር ሕዝብ በክፋት ተነስተው የነበሩት የሕዝቄል ዘመን ጎግና ጭፍሮቹ በእግዚአብሄር ፍርድ እንዲጠፉ እንደተደረጉ እነዚህም ደግሞ በእግዚአብሄር ፍርድ ጠፍተዋል። በራዕይ 6፡12-17 እና በራዕይ 8፡12 ላይ የዚህን ተመሳሳይነት በጉልህ እናያለን። 

ራእይ 6፡ 12-17 “ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ተራራዎችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።” 

ራእይ 8፡ 12 “አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።” 

የጎግን ሽንፈት የሚጠቁሙ ሌሎች የብሉይ ኪዳን ምዕራፎች በኢዩኤል 3፡1 እና ዘካ. 12 እና 14፤ እንዲሁም በሶፎንያስ ትንቢትም እናገኛለን። እነዚህን የሕዝቅኤል መጽሓፍ ምዕራፎች በሕዝቅኤል ዘመን ከተከናወነውና በመጽሓፈ አስቴር ውስጥ ካለው ትረካ ጋር ጋር በተዛመደ ትክክለኛ ግንኙነት ውስጥ እያገናዘብን ነው ማየት ያለብን። ሕዝቅኤል ከ597 ዓ.ዓ እስከ 571 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ትንቢት የተናገረ እስከሆነ ድረስ፣ ከዚያ ጊዜ አንጻር ጥቂት ዓመታትን ወደፊት ወይም ወደኋላ ብንወሰድና ብንሰጥ ሁለቱም መጻህፍት የአንድ ዘመን ታሪክ እንዳላቸው እናስተወላለን። ሐማ የተባለው የአስቴር መጽሓፍ ከፉ ሰው ለአይሁዳዊው መርዶኪዮስ ባዘጋጀው የመሰቀያ ግንድ ላይ ተሰቅሎ የሞተው በ585 ዓ.ዓ አካባቢ ነበር። ምንም ያህል በመጻኢያን የሚቀነቀነው አስተምህሮ ያንን ቢልም እንኳን የአስቴርን መጽሐፍ ግን አሁን ወደፊት ባለችው በዘመናዊቷ ጽዮናዊት እስራኤል ላይ ከሚደርሰው እልቂት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለውም። እነዚህ የሕዝቅኤል ምዕራፎችንም ግልጽ በሆነ መንገድ በአውደ ምንባቡ ጎግንና ርኩሳን ጭፍሮቹን ሁሉ ወደ ጥፋታቸው እየመራቸው ያለው ጌታ እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ ያሳየናል። የአስቴር መጽሓፍ ከግዞት ታሪክ እና የኢየሩሳሌምን ከተማ ቤተመቅደሱንና የከተማይቱን ቅጥሮች እንደገና ለመገንባት ከግዞት ወደ ኢየሩሳሌም ከመመለስ ጋር ካለው ግኑኝነት አንጻር ሲታይ የሕዝቄል ትንቢት ከዚህ አውድ ጋር የስማማል፤ መጽሓፈ አስቴር በዕዝራ 5 እና 6 ላይ ያለው ታሪክ የተፈጸመበት የጊዜ ገደብ ወስጥ ያለ ነው።

ከ70ው ዓመት ምርኮ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ ቂሮስ ባዘዘው መሠረት ወደ አገራቸው መምጣት የቻሉት 50,000 የሚያህሉ አይሁዳውያን ብቻ ነበሩ። ኤርምያስ 25:11-13። ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱ ወይም በግዞት ላይ ተወልደው የነበሩት ሌሎቹ በሙሉ በዚያው በነበሩበት እንዲቆዩ መርጠዋል። የመጽሐፈ አስቴር አጠቃላይ ሁኔታ የሚያጠነጥነው እነዚያ በባቢሎን ቀርተው በነበሩቱ ላይ ነው። የታሪኩም ትዕይንት የተፈጸመው የፋርስ ዋና ከተማ በነበረቸው በሱሳ ነው፣ ዘመኑም አውሳብዮስ [Ahasuerus] ተብሎ የሚጠራው የንጉሱ የዳርዮስ ልጅ አርጤክስስ የገዛበት ዘመን ነበር። 

እግዚአብሔር በመጽሓፈ አስቴር ትረካ ውስጥ የሌለ ያህል ስሙ እንኳ አንዴ ሳይጠቀስ ተሸሽጓል፣ ያም ቢሆን ግን በስራ ላይ ደግሞ ነበር፣ ለህዝቡ በሚያደርገው ጥበቃና ማዳን ውስጥ ንቁ ሰራተኛ ነበር። ይህም እውነት ሎውል ባስቀመጠው ቃል ውስጥ “ታላቁ ተበቃይ ግድ የለሽ የሆነ ቢመስልም የታሪክ ገጾች ግን እየመዘገቡት ነበር። የሞት ድምጽ ያረጀው ስርዓቱና አስፈሪ ቃሉ፣ የሚውጠውን ፍለጋ በዚያ ጨለማ ውስጥ በኃይል እያገሳ ነበር። እውነት እስከ ወዲያኛው ሊሰቀል በመሞቻ ማማው ላይ፤ ስህተትም ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ያለ ይመስላል። ነገር ግን ያ የመሞቻ ማማ የመሰለ መንጠልጠያ ሊመጣ ያለውን የወደፊቱን ክብር ያውለበልባል፤ ከዚያ ድቅድቅ ጨለማ በስተጀርባ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን በጥላው እየጠበቀ ከበላዩ ቆሞአል” በሚል ቃል በግልፅ ሰፍሯል። 

ጄምስ ቢ. ጆርዳን አይሁዶችን ለመዝረፍ የተደረገውን ሴራ የምናገኘው በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ ነው ብሎ ያምናል፣ ይህ ደግሞ በምላሹ ያስከተለው ውጤት አይሁዳውያን በተራቸው ጠላቶቻቸውን በመዝረፍ የተደመደመ ነው። ይህም ክስተት ከዚያ በኋላ ከዓመታዊው የፑሪም ክብረ በዓል ጋር በታላቅ ስነ-ስርዓት ተከብሮ ያልፋል። ጆርዳን በመቀጠል የሕዝቅኤል 38 እና 39ን አውደ ምንባብ በማጽናት፡- “ሕዝቅኤል የማጎጉ ልዑል የሆነው፣ ጎግ እና አጋሮቹ የሚፈጽሙትን ጥቃት ገልጿል። ሕዝቅኤል በዓለም ዙሪያ ያሉ ድብልቅ ህዝቦች በምድሪቱ ላይ በሰላም የሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ብሎ የሳላቸውን እንደሚያጠቁ በግልጽ ተናግሯል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ግን ጠላቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ያሸንፏቸዋል፣ የሚበዘብዙት ምርኮም እጅግ በጣም ብዙ ይሆናል። በውጤቱም “ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” (ሕዝቄል 39፡ 21-23)፤ … የታሪኩን ቅደም ተከተል ካስተዋልነው ይህ ሁሉ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ ይጣጣማል። የአስቴር መጽሓፍ ታሪክ የተከናወነው በዳርዮስ የግዛት ዘመን ሲሆን፣ ይህም በታላቁ ሊቀ ካህናት በኢያሱ እና በዘሩባቤል ጊዜ ቤተ መቅደሱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደገና ከተገነባ በኋላ፣ እንዲሁም ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ለመገንባት ከመቻሉ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ ነው...። ሕዝቅኤል 38-39 ጎግ (ሃማን) እና አጋሮቹ በአይሁዶች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ይገልጻል። ስለዚህ፣ ይህንን ውድቅ የሚያደርግ አሳማኝ ሃሳብ እስካልቀረበ ድረስ እኔ በግሌ የምጠቁመው የትርጓሜ መላምት፡- ሕዝቅኤል 34-37፣ ምርኮኞቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘሩባቤል ተመርተው ምድራዊውን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመገንባት መመለሳቸውን ይገልፃል። ሕዝቅኤል 38-39 ጎግ (ሃማን) እና አጋሮቹ በአይሁዶች ላይ ያሴሩትን ጥቃት ይገልጻል፤ የሚል ነው።

የአስቴር መጽሐፍና የሕዝቅኤል መጽሐፍ እነዚያ የአይሁድ ጠላቶች ከየት እንደመጡ በሃሳብ ይስማማሉ። ሕዝቅኤል 38፡5-6 የእስራኤል ጠላቶች ከፋርስ፣ ከኩሽ እና ... ከሰሜን ራቅ ካሉ አካባቢዎች እንደመጡ ይነግረናል፣ እነዚህም ሁሉም ስፍራዎች በአስቴር ዘመን በፋርስ ግዛት ወሰን ውስጥ ይገኙ የነበሩ ናቸው። ከአስቴር እንደምንረዳው የፋርስ መንግሥት በጠቅላላ “ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ በ127 አውራጃዎች” የተስፋፋ ነበር፤ (አስቴር 8፡9)፣ ኢትዮጵያ (ኩሽ) እና ፋርስ በአስቴር 1፡1፣ 3 እና ሕዝቅኤል 38፡5 ላይ ተዘርዝረዋል፡ “ፋርስ ኢትዮጵያና ፉጥ ከእነርሱ ጋር ሁሉም ጋሻና ራስ ቁር ይይዙ የነበሩ ናቸው። ሌሎቹም አገራት የተመሠረቱት "ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ" ድረስ ባለው ጂኦግራፊያዊ ድንበር ውስጥ ሲሆን ንጉሡ አውሳብዮስ የሚገዛባቸው "127 አውራጃዎች" ነበሩ (አስቴር 1: 1) "በሌላ አነጋገር አይሁዳውያን ከሁሉም የፋርስ አውራጃዎች በመጡ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል የሚለው ግልጽ ሀሳብ በሁለቱም ምንባባት ውስጥ የተነገረ ነው፣ በሕዝቅኤል የተዘረዘሩ አገራት ሕዝቦችም ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኝበት የፋርስ ግዛት አካል ነበሩ። በሁለቱም የመጻህፍቱ ምንባባት ውስጥ የሚገኙት ነጽጽሮች ሊያሳስቱ የማይችሉ ናቸው። ግራንት ጄፍሪ ሊከራከር ሲሞክር “ቅጥር የሌላቸው መንደሮች” (ሕዝ. 38፡11) የሚለው የሕዝቅኤል አባባልም እንኳ የወደፊቱን ሩቅ ፍጻሜ አያመለክትም። ይህም ከአስቴር መጽሓፍ ትረካ ጋር ላለው ግንኙነት ተጨማሪ ማስረጃ ነው። እርሱም የሁለት ኢምፓየር ወግ እና ጎግ በአይሁዶች ላይ ያቀደው የሴራ እቅድ እና አላማ አካል ነው።

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ እንዲህም ትላለህ፦ ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ”፤ (ሕዝቅኤል 38: 10-11)፤ “አስቴርም እንደ ገና በንጉሡ ፊት ተናገረች በእግሩም ላይ ወድቃ እያለቀሰች የአጋጋዊውን የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው።” (አስቴር 8፡ 3)፤ ሴራ፣ እቅድ፣ ንድፍ ወይም አላማ በሚል የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “ቻሳብ” ወይም “ማቻሼቤት” የሚል ሲሆን እርሱም የክፉ አስተሳሰብ ዓላማ፣ ወይም የተንኮል እቅድ ነው፣ ክፉ ሐሳብ መጥፎ፣ ሴራ፣ ወይም ጥሩ ያልሆነ ምክር እንደ ማለት ነው። አስቴር 8:3፣ 5፤ 9፡25።

ስለዚህ ጎግ በአይሁድ ላይ ክፉ ዕቅድን፣ የተንኮል ሐሳብን፣ መጥፎ ሴራን፣ ጥሩ ያልሆነ ምክር ነድፎ ነበር፣ ማሰቡንስ እርሱ አሰበ፣ እግዚአብሔር ግን ሊመታው እጆቹን አዘጋጅቶ መለሰው፣ ጎግም በወጥመዱ ተሰናክሎ ወደቀ ተበላም፣ እግዚአብሔርም በማጎግ ላይ እሳትን ያወርዳል። ለዚህ ማጣቀሻ እንዲሆን በመዝሙር 21፡ 7-13 እንዲህ ይላል፦ “ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም። እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው። በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ እግዚአብሔር በቍጣው ያጠፋቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች። ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ። ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ። ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ። አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን።”

በመጽሓፈ አስቴር የቀረበው ታሪካዊ ዘገባም እነዚያ የሃማ ተንኮሎች እንዴት እንደተገለበጡ እና የአይሁድ ጠላቶች ወደ ኋላቸው እንደተመለሱ እንደጠፉም የሚገልጽ ዘገባ ነው። አስቴር 9:2, 5-6,12 እና 15-16 ያለውን ትረካ ከሕዝቅኤል 38:18-23: 39:2-6, 17-20 ካለው ትንቢት ጋር ለሚያነጻጸር አንባቢ የጎግንና የጭፍሮቹን መጨረሻ ለማወቅ ይህ አይታጣውም።

የአይሁዶች ጠላቶች ፍላጎታቸው አይሁድ ከተማይቱን መልሰው እንዳይገነቡ “ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋቺቱን ከተማ ይሠራሉ፥ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፥ መሠረትዋንም ጠገኑ።” (ዕዝራ 4፡ 6፣ 12 ) ሲሉ ባቀረቡባቸው ክስ ሊከለክሏቸው ነበር።

“የታሪክ መዛግብት ተፈልገው “ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ …” ምርመራ እንዲደረግ እነዚያ ተቃዋሚ ከሳሾቻቸው ይጠይቃሉ (ዕዝራ 4፡ 5) ይህም ወደፊት ከእስራኤል ዘንድ ወታደራዊ ስጋት እንዳለባቸው የሚያመለክት ነው። እንግዲህ እነዚህ ኹነቶች ሐማ የንጉሱ የአርጤክስስን ጆሮ ያገኘው ለምን እንደሆነ ሊገልጹ የሚችሉ ናቸው። በተጨማሪም ኢየሩሳሌም ቅጥር የሌላት ከተማ እንደነበረች ይህም በሕዝቅኤል 38:11 ላይ ያለውን የወቅቱን ትንቢታዊ መግለጫ እና በአስቴር 9:19 ላይ ካለው ታሪካዊ ፍጻሜ ጋር የሚስማማ ያደርገዋል። 

በቀጣዩ ክፍል በዚሁ ላይ ትኩረት አድርገን፣ በዮሓንስ ራእይ ስለ ጎግ ማንጉግ የተነገረውን ማጠቃለያ አድርገን ተጨማሪ ብርሃን በሚሰጡን ነጥቦች እንመለሳለን።

gkr

ክፍል አምስት

አጋግ የተባለው ሁሉ ስለ አጋጋዊው ሐማ ነው

በመጽሓፈ አስቴር ያለው ዋነኛ የአይሁድ ጠላት የአጋጋዊው የሐመዳታ ልጅ ሐማን ነው። አስቴር 3:1, 10; 8፡3፣ 5፡9፡24። አጋጋዊነት የአማሌቅ ዘር ነው፣ እርሱም ከእስራኤል ጽኑ ጠላቶች አንዱ ነበር። ይህንንም በዘኁልቁ 24፡20 ላይ እናነባለን። "አማሌቅ የአሕዛብ መጀመሪያ ነበረ ፍጻሜው ግን ጥፋት ሆነ" በዘፍጥረት 10፡2፣ “ከአባታቸው ከያፌት የተወለዱ የያፌት ልጆች ጋሜር፥ ማጎግ፥ ማዴ፥ ያዋን፥ ይልሳ፥ ቶቤል፥ ሞሳሕ፥ ቴራስ ናቸው። የሚል እናገኛለን። ጋሪ ዴማር፣ Why the End of the World Is Not in Your Future" በሚለው ኤሌክትሮኒክስ መጽሓፉ ውስጥ ይህንን ነጥብ ግሩም አድርጎ አስቀምጦታልክ። እርሱም እነዚህ አኃዞች በሕዝቅኤል መጽሓፍ ውስጥ መዕራፍ 38 እና 39 ላይ ጎልተው እንደሚታዩ ተናግሯል። ፣ ሃማ እና ልጆቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገኙት አማሌቃውያን መካከል የመጨረሻዎቹ ናቸው።

በዘኍልቍ 24፡7፣ ሴፕቱጀንት (LXX) አጋግ የሚሉውን ጎግ ተብሎ ተተርጉሟል። ለአስቴር 3:​1 እና 9:​24 ዘግየት ብሎ የተጻፈ አንድ ጥንታዊ የብራና ጽሑፍ ሐማን ሲጠቅስ ጎጋዊ መሆኑን ያመለክታል። አጋግ እና ጎግ በዕብራይስጥ ሆሄያቸው እና ትርጉማቸው በጣም ተመሳሳይ ናቸው። አጋጌት ማለት "ወደ እላይ እላለሁ" ማለት ሲሆን ጎግ ደግሞ "ተራራ" ማለት ነው። ሌዊስ ባይልስ ፓቶን ስለ አስቴር በሰጠው ቴክኒካል ሐተታ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- በብሉይ ኪዳን የተጠቀሰው አጋግ ብቸኛው የአማሌቅ ንጉሥ ነው (ዘኍልቍ 24፡7፤ 1 ሳሙ. 15:9]። አይሁድ ሁሉ እና በርካታ ክርስቲያን የመጽሓፍ ቅዱስ ተንታኞች ሃማን በተመለከተ የዚህ አጋግ ዘር እንደሆነ ያስባሉ። ይህ አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም የእርሱ ተቀናቃኝ የሆነው መርዶክዮስ ቀደም ሲል አጋግን ከዙፋኑ ያወረደው የቂስ ልጅ የሳኦል ዘር ነውና፣ 1ሳሙኤል 15፡ 8-16፤ በተለየ ሁኔታም በሕጉ የተረገመ ነው [ዘዳ. 25፡17]። ስለዚህም ምናልባት የታሪኩ ጸሐፊ ሐሳቡ ሐማን ከዚህ ሕዝብ የዘር ሐረግ የተገኘ እንደሆነ ውክልናውን ለማሳየት ሲሆን ይህም በእስራኤል ላይ ጥንታዊና እና ሊጠፋ በማይችል ጥላቻ መገለጡን ለማሳየት ነው፤ (አስቴር 3፡10 ተመልከቱ፣ ቃሉ ሓማን ሲያስተዋውስተዋው “የአይሁድ ጠላት” ነው፣ ይለዋል)።

ጥንታዊ ጽሑፍ ሐማን የጎግ ተወላጅ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። ፖል ሃውፕ ስለሃማ በተደረጉ ገለጻዎች ውስጥ ያለውን ግንኙነት ሲያብራራ እንደ አጋጋዊ እና የጎግ ተወላጅ አድርጎ ይመለከተዋል። “በዘኍልቍ 24፡7 ላይ ያለው የሰባ ሊቃናት ትርጉም አጋግ በሚለው ፈንታ “ጎግ” ያሚለውን የሚጠቀም ሲሆን በአሞጽ 7፡1 ደግሞ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ (ጎግ) አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ።” በሚለው ላይ ጎግ የሚለውን ስም ጨምሮ ይጠቀማል። በጽሁፍ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ተያያዥነቶች ልንተዋቸው አይገባንም። ለዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ትርጉም በሆነው የአስቴር መጽሐፍ ክፍል በአራማይክ ቋንቋ ትርጉምም የሚከተለው ይገኛል፡- "የፍርዱ መጠን በዓለሙ ሁሉ ጌታ ፊት በቀረበ ጊዜ፥ ያ ከፉ ሰው ሐማ የመቅደስህ ቤት እንዳይሠራ ማንም ሰው ከሱሳ ወደ ኢየሩሳሌም እግሩን አያነሳም ብሎ በእብሪት ተናግሮ አልነበረምን?" 

አንቶን ሾልዝ (1892) ሲጽፍ፣ “የአስቴር መጽሐፍ ሕዝቅኤል ስለ ጎግ ለተናገረው ትንቢት ተጨማሪ እድገትና ትንቢታዊ ድግግሞሽ ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። በፓይቶን የተጠቀሰውና የመጽሐፈ አስቴር ወሳኝና ገላጭ ሐተታ (Commentary) ገጽ 56 ላይ በእነዚህ ሁሉ የጎግ-አጋጋውያን ማጣቀሻዎች ውስጥ ያለው ነጥብ በሕዝቅኤል 38 እና 39 እንዲሁም በመጽሐፈ አስቴር መካከል ያለውን ጽሑፋዊ ተመሳሳይነት ማየት የቻሉ በርካታ ምሁራን እንዳሉ ለማመልከት ነው።

የሃሞና ከተማ እና የሃሞን ጎግ ሸለቆ። የጎግ ሰራዊት የተቀበረው እዚህ ነው። ሕዝቅኤል. 39:11, 15:- በሕዝቅኤል ውስጥ ሃሞን የሚለው ቃል በዕብራይስጡ አጠራር ሐማን ከሚለው ስም ጋር በትክክል ይመሳሰላል። የሚለያዩት አናባቢዎቹ ብቻ ናቸው።

ሐማ በንጉሥ በአርጤክስስ የመጀመሪያ ፈቃድ ከ127ቱ አውራጃዎች የሰበሰበው የብዙ አህዛብ የጦር “አለቃ” የሆነ እና ደካማ ፍጥረት የሆኑ ጠላቶቹን አይሁድን ለማጥፋት የተነሳ ነው። : ዘጸ. 17:8-16; ዘኁ. 24: 7፤ 1ሳሙ 15: 8, 1ዜና 4: 42-43፤ ዘዳ. 25: 17-19። እርሱም ከእርሱ ጋር በነበሩት አለቆች ሁሉ ላይ ሥልጣን የነበረው ነው” (አስቴር 3፡1፤ ደግሞ 1፡3 ተመልከት)። 

“ከእርሱ ጋር በነበሩት አለቆች ሁሉ ላይ ሥልጣን” ስላለው ይህ በራሱ “አለቃ” ያደርገዋል። ለምሳሌ በአስቴር 3፡12 ሐማ የመኳንንቱ፣ የገዥዎችና የመሳፍንቱ መሪ ሆኖ እንዴት እንደተገለጸ እናነባለን። በሕዝቅኤል 38፡2-3 እና 39፡1 ላይ፣ በምዕራፎቹ ቀጣይ ምንባባትም የዚህ ማዕረግ አስፈላጊነት ግልጽ ይሆናል።” በሕዝቅኤል 38፡2-3 እና 39፡1 ላይ ዋናው ልዑል ሃማ እንደነበረ እናያለን።

በሕዝቅኤል ትንቢትና በአስቴር መጽሐፍ ላይ የሚታየውን የገንዘብ ብዛት ተከተሉ ሕዝቅኤል የጻፈው አይሁዶችን ለመውረርና ለመዝረፍ፣ መታቀዱን ነው (ሕዝ. 38:12-13)፤ እነዚያ ከምርኮ የተመለሱት አይሁዶች ብዙ ብርና፣ ወርቅን ከብቶችንም ይዘው ነበር (ዕዝራ. 7፡15-16፣ 18፣22፣ እንዲሁም ነህምያ 7:71-72). “ንጉሡም ሐማን፦ ደስ የሚያሰኝህን ነገር ታደርግባቸው ዘንድ ብሩም ሕዝቡም ለአንተ ተሰጥቶሃል አለው” ይላል።

ትንቢተ ዘካርያስ ከመጽሐፈ አስቴር እና ከሕዝቅኤል ምዕራፍ 38-39 ጋር ያለው ግንኙነት።

አይሁድ ከምርኮ የተመለሱበት ወቅት ነበር። ሁለተኛውም ቡድን ደግሞ ከዕዝራ እና ነህምያ ጋር ተመልሰዋል። ያኔ አይሁድ ገና እንደገና እያገገሙና የኢየሩሳሌምን እና የቤተ መቅደሱን ግንቦች እንደገና እየገነቡ ያሉበት ሁኔታ ነበር። ዘካርያስ በምዕራፍ 12 የፍጻሜውን ጊዜ አስመልክቶ ከሕዝቅኤል 38-39 ካለው ትንቢት ጋር በተያያዘ ማስረጃን ይሰጣል።

  • ጦርነቱ የሚካሄደው በፈረስ ላይ ተቀምጠው በሚመጡ ሰዎች ነው። ዘካርያስ. 12፡4
  • በግዞት የነበሩት አይሁዶች በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። ዘካርያስ 12፡7 እና ኤር. 30፡10፣ 18
  • የደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ዋናው የሕዝብ ማዕከል ነው። ዘክ. 12:4, 6-8
  • ህዝቡም በየአባቶቻቸው ቤት ተዘርዝረው ይታያሉ፣ ዘካ. 12:5, 10, 12-13
  • የዳዊት ቤት ክብር አሁንም ድረስ እንኳ ይታወቃል። ዘክ. 12:7-8; ነህ. 3፡15፡; 12:24, 36, 45
  • ንጉሥ ኢዮስያስ በፈርዖን ኒኮ መገደሉም 2ኛ ነገሥት 23:28-30; 2ኛ ዜና 35፡22-27 እንደ ሀገር አሳዛኝ ክስተት አሁንም ይታወሳል። ዘክ. 12፡11።

ዘካርያስ 12 በመጽሐፈ ዕዝራና በመጽሐፈ አስቴር መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ክንውኖች በታሪካዊው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያያቸዋል። የኩነቶቹ ቅደም ተከተልም ይህን ይመስላል። በ598 ዓ.ዓ አይሁዶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የቂሮስ አዋጅ ወጣ ዕዝራ 1፡1-4፤ የቤተ መቅደሱ መልሶ ግንባታም ጅማሬው በ536 ዓ. ዓ ሲሆን የዘካርያስ ትንቢት ደግሞ በ520 ዓ.ዓ. ነበር፤ ቤተ መቅደሱም እድሳቱ የተጠናቀቀው በ516 ዓ.ዓ. ነው። በአስቴር መጽሐፍ እና በዕዝራ ውስጥ የተገለጹት አብዛኛዎቹ ክንውኖች የተፈጸሙት በዘካርያስ 12 ላይ ካለው ትንቢት በኋላ ነው። ነብዩ ሐጌና ነቢዩ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩት አይሁዳውያን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናገሩ፤ እነርሱም ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመሥራትና ለመጨረስ እንደ ተነበዩ እናውቃለን፤ ዕዝራ 5፡1-2።

ከፍ ሲል ለማለት እንደተሞከረው፣ የሕዝቅኤል መጽሃፍ ጎግ ማንጉግ ሕዝቅኤል በኖረበት የአስቴር ዘመን በአስቴር መጽሓፍ አውድ የአይሁድ ሕዝብ ጠላቶች (የእግዚአብሄር ሕዝብ ጠላቶች) ሆነው እንደተገለጡ ሁሉ፣ የዮሓንስ ራእይ መጽሃፍ ጎግ ማንጉግም ዮሓንስ በኖረበት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሄር ሕዝብ አውድ የቅዱሳኑ ጠላቶችና አሳዳጆች የሆኑትን ተቃዋሚ አይሁድን የሚያመለክቱ ናቸው። በብሉይ ኪዳን በተለያየ የታሪክ ምእራፍ እግዚአብሔር የፈረደባቸው የአህዛብ መንግስታት ግብጽ፣ ባቢሎን፣ ሰዶም፣ አሶር፣ ወዘተ እየተባሉ በየስማቸው ተጠቅሰዋል፤ በአመዛኙ እነዚህ የአህዛብ ነገስታተና ሕዝቦች በራእይ መጽሃፍ ውስጥ እግዚአብሔር ሊፈርድባት ባለችው በአመጸኛይቱና በአመንዝራይቱ እስራኤል ተወክለዋል። እስራኤልን ግብጽ፣ ባቢሎን፣ ሰዶም ወዘተ እያለ እንደሚጠራት ሁሉ ጎግ ማንጉግ ብሎ ደግሞ ይጠራታል። የሕዝቅኤል ዘመን ጎግ ማንጉግ እዚያው በነብዩ ዘመን ያለፈ የትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ባለመረዳት ጎትቶ አምጥቶ ገና ያለቀቀን የዘመናችን ጣጣ አድርጎ መተርጎምና ማስተማር በእውነቱ ልክ አይደለም። በይዘቱ እጅግ አድርጎ ምሳሌአዊና ምስል ከሳች በሆነው የራእይ መጽሃፍም ጎግ ማንጎግ መጠቀሱ ያን ያህል ግራ ሊያጋባን አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የራእይም መጽሓፍ ቢሆን መተርጎም ያለበት በጸሓፊውና በበኩረ ተደራስያኑ አውድ መሆን ስላለበት ነው። ይህንን የሚያሳይ ጥቂት ነገር ላንሳና አምስተኛውን ክፍል ጥናታችንን ላብቃ። 

በራእይ 20፥ 8 ላይ የተነገረው የጎግ እና ማጎግ ማጣቀሻ ወደ 70 ዓ.ም የትንቢት ፍጻሜ የሚጠቁም መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም ይህ ከ70 ዓም በፊት ቀደም ብሎ የተጻፈ አቡቀለምሲስ የትንቢቱ ፍጻሜ ከኢየሩሳሌም ውድመት ጋር የተያያዘ ነውና። በብሉይ ኪዳን ያለው የጎግ እና ማጎግ ማጣቀሻ ሁሉም አሕዛብ እግዚአብሔርን የሚያውቁበት አውድ መቼ እንደሆነ በሚያመለክትበት መልኩ መቅረቡን ከፍ ሲል ተመልከተናል (ሕዝቅኤል 38፡16፣ 23፤ 39፡21) -ይህም ጊዜ በእርግጥ የአዲስ ኪዳንን የመሲሁን ዘመን የሚያመለክት እንደሆነ ግልጽ ነው። በሕዝቅኤል 38:16 “ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።” የሚለው ጊዜን አመልካች የሆነው የሕዝቅኤል ትንቢት በመጨረሻው ዘመን (“በኋለኛው ዘመን”) ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ይናገራል። ሕዝቅኤል ሲናገር ብዙውን ጊዜ “በዚያ ቀን” የሚለውን ሃረግ ይጠቀማል (ሕዝቅኤል 38: 10, 18, 19፤ 39: 8, 11, 13, 22) እርሱም የጌታን ቀን የሚያመለክት ትንቢታዊ ማጣቀሻ ነው። ያም ቀን ለፍጻሜው በእስራኤል ላይ የሚመጣውን ፍርድ ምልክት ያደርጋል (ሕዝ 38፡18)።

ይህም ሁሉ ለ70 ዓ.ም. ፍጻሜ የተነገሩ ትንቢቶችን የሚጠቁሙ ናቸው። ሐዋርያው ​​ጴጥሮስ ሲናገር ከሳሙኤል ፊት የተነሡት ነቢያት ሁሉ ጴጥሮስ ይህ ዘመን ሲል የተናገረለትን ዘመን እንደሚጠቁሙ በግልጽ ተናግሯል (የሐዋርያት ሥራ 3፡24) ስለዚህ ሕዝቅኤልም ቢሆን እየተናገረ ያለው ወደዚያው ጴጥሮስ እየተናገረለት ላለው ዘመን መሆኑን መረዳት እንችላለን። ጌታ ኢየሱስም ያኔ ገና በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትንቢቶቹ በሙሉ በእርሱው ትውልድ እንደሚፈጸሙ በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርጎ ተናግሯል (ሉቃስ 21:22, 32፤ ራእይ 1:1፤ 22:6)።

ጴጥሮስ እና ኢየሱስ ያለ ልዩነት ግልጽ ባደረጉት የጊዜ መግለጫዎች ላይ ተገቢውን ትኩረት ሳናደርግ በራእይ 20 ስለተነሳው ስለ ጎግና ማጎግ የመጀመሪያውን መቶ ክፍለ ዘመን ማንነትም ሆነ ውክልና ሳናስተውል ልባችን የወለደውን ማናቸውንም ነገር መቀላመድ አንችልም። የራእይ መጽሐፍ ጎግ እና ማጎግ የሚያመለክቱት ምንም ይሁን ምንም ግን ፣ አንዳንድ የመጻኢነት ጎራ ዘመን ቆጣርያን እርግጠኛ ሆነው በለየለት ፈጠራ እንደሚያስተምሩት ዘመናዊውን ሩሲያ (ወይም በእኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለ ማናቸውንም አይነት ክፉ ተብሎ የተፈረጀ መንግስት ማለት ጨርሶ አይደሉም።

gkr

ክፍል ስድስት

 የሕዝቅኤል መንፈሳዊ መልዕክት ጠቀሜታ

ሕዝቅኤልን ለመረዳት የዮሐንስን ራዕይ ሕዝቅኤል እያየው ካለው ጋር ማነጻጸር አለብን። 

“በተማረክን በሀያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ ከተመታች በኋላ በአሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ” (ሕዝቅኤል 40፥ 1-2)። 

ከሕዝቅኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ አንስቶ እስከ አርባኛው ምዕራፍ ድረስ ሕዝቅኤል ከጌታ ጋር ያደረገው ሕብረት ወደ ሃያ ዓመት ግድም እንደሆነ እናውቃለን። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ክብር እና የአሮጌው ኪዳን ህዝቦችን መጥፋት፣ እንዲሁም ተስፋን እና ወደፊት የሚገለጠውን የትንሳኤ ክብር አይቷል። ከአሮጌው ጋር መውጣትን እና ከአዲሱ ጋር መግባትን ተመልክቷል። ሕዝቅኤል ነብይነቱን ሲጀምር የሠላሳ ዓመት ሰው ነበር አሁን ግን አምሳ ዓመት ሆኖታል። የኖረው ህይወቱ ራሱ እንኳ በዚህ ለውጥ ውስጥ የተጠበቀ ነው። ትንቢቱም የአንዳች አሮጌ ነገር ወጥቶ የመሄድ ትንቢት ነው። በሠላሳ አመት እድሜው ክህነቱ ተጀምሮ የሚያበቃው በሃምሳ አመቱ ነው። ይህ ሕዝቅኤል ከምዕራፍ 40 እስከ 48 ያለው ራዕዩ ስለ ዘሩባቤል ቤተ መቅደስም ይሁን ወይም ሄሮድስ በራሱ ጨምሮ ስለሚሰራው ፈጽሞ አይደለም። ዮሐንስም ይህን ቤተ መቅደስ አይቶ ነበር፣ እርስዋም በሙሽሪት ውበት የተሸለመች፣ በሰዎች መካከል ያለች የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነች፣ ከሰማይም የምትወርድ ከተማ ነበረች። እነዚህ ሁሉ ከጌታ ጋር ስላለን ግንኙነት መጠንና መልክ የሚገልጡ ምልክቶች ናቸው። ቤተ መቅደሱ እሱን የሚመለክበትና የምከበርበት ሥፍራ ነው። በራሱም የተቀደሰ ሥፍራ ነው! በባል እና በሙሽሪት ወይም በሚስቲቱ መካከል እንደሚታየው አይነት የፍቅር ሕብረት በከፍተኛ ደረጃ ያለ መቀራረብ ነው! እርሱ እንደሚያድርበት ያለ እንደ ማደሪያው ድንኳን ነው። እርሱ በእኛ ዘንድ በመካከላችን የማደሩና የመገኘቱ መገለጥ ነው! ሕዝቅኤል በረጅም ተራራ ላይ እንደነበረ ሁሉ ዮሐንስም ወደ ረጅም ተራራ ተወስዷል። ጽዮን የእግዚአብሔር ራዕይ እና የእግዚአብሔር ክብር የሚታይባት ከፍተኛ መንፈሳዊ ቦታ ነች። የሕዝቅኤልንና የዮሐንስን ንጽጽር ከዚህ በታች እንመለከታለን። 

“ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር። የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው።” (ራእይ 21፥ 9-16)።

በርካታ ሰዎች በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚታዩትን ሁሉንም ልኬቶች እና እያንዳንዳቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በቀጥታ አነጋገር እንዳለ በጥሬው ለመረዳት ሲጥሩ በትርጉማቸው የመጽሓፉን መልክት በመሳት ጠፍተዋል። በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው በቁጥሮች የተገለጡ ሁሉም ንግግሮች እና መስዋዕቶች እያንዳንዳቸው መንፈሳዊውን እውነታዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ​​ጴጥሮስ በመጀመሪያው መልእክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ቁጥር አምስት ላይ የሚናገረው፣ በአንድ ላይ እየተገነባ ስላለ መንፈሳዊ ቤት፣ ስለ ክህነት ቤተ መቅደስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን መንፈሳዊ መስዋዕቶች ስለ ማቅረብ ነው፣ በንጉሣዊ ክህነታችን ውስጥ አብረን ስለማምለካችን፣ ስለመስራታችንና ስለመሰራታችን በዝርዝር ያወሳል። እነዚህ በጴጥሮስ መልእክቶች ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ መሥዋዕቶች ነብያት አስቀድመው ያዩአቸውና በክርስቶስ ፍጻሜአቸውን ያገኙ መሆናቸው መመርመር አለባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ምእራፍ 3 ላይ ቤተክርስቲያንን ሲገልጻት የእግዚአብሔር ሕንፃ፣ የእግዚአብሔር መስክ እርሻ ይላታል። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ለማብራራት የጊዜና የቦታ ውስንነት ይገድበናል። ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በጻፉአቸው መልእክቶቻቸው ውስጥ በምልክቶች የተዋቀሩ፣ ዘይቤያዊነት የተላበሱ እና ምሳሌያዊነት የተንጸባረቀባቸው አጠቃቀሞችን እንመለከታለን። አንዳንዶች ቅዱሳት መጻሕፍትን አመናፈሳችኋቸው ብለው ይወቅሱ ይሆናል፣ ይህ ግን ማመናፈስ አይደለምን ይልቁንም ይህ በሐዋርያቱ አስተምህሮ የተለመደ ተግባር ነበር፣ በብሉይ ኪዳን ያሉትን አካላዊ እና ተፈጥሯዊ ጉዳዮች በአዲሱ ኪዳን ውስጥ ወደ መንፈሳዊ እውነታዎች ለውጦ የማምጣት ከፍተኛ ልምምድ ነበራቸው።

ቅጥሩ፣ በሮቹ እና መሠዊያው

የዚህ ራዕይ የሚታዩ ሌሎች ገጽታዎች ስለ ከተማይቱ ቅጥር፣ ስለ በሮቿ እና በዚያ ስላለው መሠዊያ የተነገረው ነው። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ያለው የከተማይቱ ቅጥር መሠረቶች አሉት እነርሱም አሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት መሆናቸው ተነግሯል። የቅጥሩ ግንብ አገልግሎቱ ለመከላከያ እና ልዩነትን ለማድረግ ነው። ሐዋርያቱ በአገልግሎታቸው ለከተማይቱ እንደ መከላከያ ቆመው ከተማይቱን ከሐሰት እና ከነጣቂ ተኩላዎች ጠብቀዋታል። ቅጥር በአገልግሎቱ ከከተማይቱ ውጭ ያለውን እና በከተማይቱ ውስጥ ያለውን ልዩነት ግልጽ በማድረግ የወሰን ድንበርን ይፈጥራል። “ቅጥር የሌላት ግን የፈረሰች ከተማ” (ምሳሌ 25፡ 28) ሆና ሁልጊዜ ለጥቃት ትጋለጣለች። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ያሉት እነዚህ የቅጥሩ ግንቦች በከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ናቸው። በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዱንም አንመለከትም ምክንያቱም እነዚህ ድንጋዮች የሚናገሩት እየሩሳሌም በሞትና በትንሣኤ ስለምታልፍበት ለውጥ ነውና። ዮሐንስ በራእዩ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት ያለው በዚህ ምክንያት ነው። አሮጌዋ እየሩሳሌም ግን ተፈርዶባት ተገድላለች። እርሱ ሲሞት ሰዎች ሁሉ ይሞቱ ዘንድ እስራኤል በጽድቅ ተገድሏል። በክርስቶስ ያመኑት ከክርስቶስ ጋር ሞተዋልና፣ ነገር ግን ደግሞ በክርስቶስ የትንሳኤ ሕይወት ለአዲስ ሕይወት ደግሞ ተነሥተዋል። (2 ቆሮ. 5፡ 14)

ለዚህ ነው የከተማይቱ በሮች በሌሊትና በቀን በየአቅጣጫው ክፍት ሆነው የተተዉት። ለሰዎች ሁሉ ክፍት ሆነው ለዘላለም አይዘጉም፣ የተጠሩና የወደዱ ሁሉ እየመጡ እንዲገቡ፣ አምነውም የዚህች የከበረች ሙሽራ አካል ይሆኑ ዘንድ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅ እና በምዕራብ ተከፍተው ሳይዘጉ ይኖራሉ። በራእዩ ገለጻ እንደተብራራው እያንዳንዱ ደጅ የተሰራው ከዕንቁ ነው። ዕንቁ ደግሞ በባህር ውስጥ ያለ ውድ የከበረ ድንጋይ ነው። በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ልዩ ልዩ አብረቅራቂና አብለጭላጭ ዕንቁዎችን ለመሰብሰብ የዛጎል ትሎችን ይሰበስባሉ። ይህንንም የሚያደርጉት በመጋቢት ወይም በሚያዝያ ወር ማለትም በፋሲካ በዓል ወቅት ነው። እንቁዎች የሚፈጠሩት የዛጎል ትል ሲሰቃይ እና በዚያ ምክንያት ሲሞት ነው፣ ምክንያቱም አንድ ባዕድ ነገር ወደ ዛጎል ትል ውስጥ ገብቶ የዛጎሉ ትል ውስጥ ሰርጾ ሲገባ ትሉ ይሞትና በዚያ ባዕድ ነገር ምክንያት ዕንቁው ይፈጠራል። እንግዲህ ያ የዛጎል ዕንቁ በመከራና በሞት የተፈጠረ አዲስ ንጥረ ነገር ምልክት ነው። እንግዲህ የከተማይቱ ደጆች እያንዳንዳቸው በዕንቁ የታነጹ ነበሩ፣ እርሱ ራሱንና ህይወታችንን ዋጋ ያስከፈለ በመሆኑ ራሳችንን ስለ ክርስቶስ አሳልፈን ስንሰጥ ያኔ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በሙላት እንገባለን። ክርስቶስ አሁን በመንፈስ ይኖር ዘንድ በስጋው መከራን ተቀብሎ ሞተ። እርሱም አሁን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በከተማይቱ ቤተመቅደስ አሥራ ሁለት ዕንቁዎች (የከበሩ ድንጋዮች) ነበሩ። በእያንዳንዱ ዕንቁ ላይ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስም ተጽፎአል። ግንቡ እና ደጆቹ በሆነ መንገድ ስለ ክርስቶስ ይነግሩናል። ተመልከቱ በዮሐንስ ራእይ 4፡ 3 ላይ “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የኢያስጲድ ድንጋይ ነበረ ይለናል”። የከተማይቱም ቅጥር የኢያስጲድ ድንጋይ ሲሆን ከተማይቱም እራሷ እንደ ክሪስታል ጥርት ያለ የኢያስጲድ ድንጋይ ብሩህ ነበረች።

ክርስቶስ ኢያስጲድ ነው፣ ከተማይቱም ኢያስጲድ ነው፣ ቅጥሩም ኢያስጲድ ነው፣ የዚህ ሕንፃ ተፈጥሮም የክርስቶስ ተፈጥሮ ነው። ይህም እርሱን የሚገልጽ እና ባህሪውን የሚያሳይ ነው። በሕዝቅኤል ውስጥ ያለው የመሠዊያው ባሕርይ መሥዋዕቱ ስለሚቀርብበት ስፍራ ነው። በብሉይ ኪዳን መሠዊያው ሲሆን በአዲስ ኪዳን ደግሞ መስቀሉ ነው። ከመስቀሉ በኋላ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። ይኸውም ለእግዚአብሔር በመንፈስ የመቀደስ ህይወት ነው። ይህም ሕይወታችንን ለመሠዊያው አሳልፈን የምንሰጥበት ነው። 

መሠዊያውን በተመለከተ የአዲስ ኪዳን መግለጫ እነሆ። ራእይ 16: 7 እንዲህ ይላል “ከመሰዊያውም፦ አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”

መሰዊያው ህያው ነው፣ ይናገራል፤ መሠዊያው እየተናገረ ያለውም ህይወታችንን የምንሰጠው እርሱ ስለሆነ ነው። እርሱ ለእርሱ የምንሰጥበት መሠዊያችን ነው። አስቀድመን መስዋዕት ሆኖ ለመሞት በመሠዊያው ላይ ካልተጋደምን በቀር ወደ ቤተመቅደሱ ውስጥ መግባት አንችልም። ከእርሱ ጋር ወደ ቅድስት ስፍራ ከፍ ብለን መውጣት የምንጀምረው እንደ ዕርገት መስዋዕት ስንሆን ነው። በመጀመሪያዎቹ ሰባት ደረጃዎች፣ ከዚያም ስምንት ደረጃዎች ወደ እግዚአብሔር የዙፋን ክፍል ውስጥ ከፍ ብለው ይገባሉ። እነርሱም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት እንደ ንጉሥና ካህን ሆኖ የእግዚአብሔርን ምሕረት በሚያገለግል በስርየቱ መክደኛ ላይ ካለው ከእርሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠዋል።

በኤደን ገነት ውስጥ ያሉት ሁሉም ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ የሚውሉበት ይህን መግለጫ በተመለከተ ተጨማሪ ነገር አለ። የዘንባባ ዛፎች፣ ወርቁ እና ሁሉም ተዳሳሽ የሆኑ ቁሳቁሶች አሁን በእግዚአብሔር ስራ ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ። አዳም በገነት ውስጥ ኃጢአት በሠራ ጊዜ ያኔ ከገነት ተባሮ ተጣለ። የተላለፈበት መርገምም አንዱ ክፍል በምድር ላይ ስራው ሁሉ አድካሚና ከንቱ ይሆን ዘንድ ጥረት ብቻ ነበር። እሾህና አሜከላም ያፈራ ነበር። በእሾህና በአሜከላም ምንም ነገር መሥራትና ምርታማ መሆን አይቻለውም። በገነት በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ እያለ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ሁሉ የሚሠራበትና የሚጠቀምበት ማንኛወም አስፈላጊ ነገር ሁሉ ነበረው፣ ወድቀቱና እርግማኑ ያሳጣውም ያንንው ነው። አሁን ቤዛነታችንን አግኝተን ወደ ጌታ ስራ በሙላት ገብተናል። “ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1ቆሮንቶስ 15፥ 58)

1ዜና 26፥ 30-31 “ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር።” 

እኔ እንደማስበው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው አንዳች ነገር በእኛ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን አላማ እና ስራ በተመለከተ ነበር። የጌታ ስራም ለክብሩ የሚሆን ስፍራን የማነጽ አላማ ነው። ክርስቶስም ሲናገር “ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” ብሏል። ተመልከቱ፣ አሁን ሕዝቅኤል ክብር ከምሥራቅ ሲመጣ ያያል። ምሥራቅ ደግሞ አዲስን ቀን የሚያመለክት የፀሐይ መውጣት ምልክት ነው። የሕዝቅኤል ራእይ ስለ አዲስ ቀን፣ ስለ አዲስ ጊዜ ነው። የጌታም ድምፅ በራእይ 1፡15 እና በራዕይ 14፡2 እና 19፡6 ላይ እንደ ብዙ ውሃ ድምፅ ነው። በኋለኞቹ ሁለት ጥቅሶች ድምጹ የመቶ አርባ አራት ሺህዎቹ እና እጅግ ብዙ ተብለው የተገለጹት ሰዎች ድምጽ ነው። ጌታ እና ህዝቡም አንድ ድምፅ አላቸው። እርሱ የሚናገረውን ያንን ተመሳሳይ ነገር ያዳናቸው ህዝቡም እየተናገሩት ነው። እንግዲህ አዲሱ ቃል ኪዳን ጌታን እና ህዝቡን አንድ ያደርጋቸዋል። ማደሪያውም ለእርሱ የዙፋኑ ከፍታ እና የእግሩ መረገጫ ያለበት ስፍራ ነው። ይህም የክርስቶስ መልክ በሕዝቡ ውስጥ የሚታየው እንደ አካሉ ነው። 

“እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር። ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮበር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ።” (ሕዝቅኤል 43፥ 2-3)።

“እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በግልሙትናቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም፤” (ሕዝቅኤል 43፥ 7)

“ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር። ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ ….እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ። በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል።” (ሕዝቅኤል 47፥ 1፣5፣7፣12)።

በሕዝቅኤል ውስጥ ያለው ወንዝ እና በራዕይ ውስጥ ያለው ወንዝ

ወንዙ የሚቀጥለው የጥናታችን ማጠቃለያ የሚያጠነጥንበት የውይይታችን ርእሰ ጉዳይ ነው። በተለይም ወንዙ እና በወንዙ ዙሪያ ያሉ ዛፎች ላይ ትኩርት አድርገን እናብቃ። ወንዙ የሕይወት ውሃ ወንዝ ነው። ይህም በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ያለው ያው ራሱ ወንዙ ነው (ራዕይ 22፡1)። በሕዝቅኤል መጽሃፍ ውስጥ ወንዙ በሚሄድበት ስፍራ ሕይወት ደግሞ አብሮ አለ። ይህ የሕይወት ወንዝ ነው፣ የሚፈሰውም በሕዝቅኤል እንደተገለጠው ከመቅደስ-ከተማ ነው። በራዕይ 22፡1 ላይ ሲናገር ወንዙ የሚወጣው ከእግዚአብሔር ዙፋን ነው ይላል። ሕዝቅኤል 43፡7 ደግሞ ሲናገር ይህ ስፍራ ዙፋኔ ነው ይላል። በሕዝቅኤል 47፡12 ላይ በወንዙ በሁለቱም በኩል ዛፎች ይበቅላሉ ይላል። በራዕይ 22፡2 ላይም የሕይወት ዛፍ በወንዙ በሁለቱም በኩል ይበቅላል ይላል። በሕዝቅኤል ውስጥ እንደተገለጠው ዛፎቹ በሁለት ቡድን ተከፍለዋል። በአዲስ ኪዳን አይሁድና አሕዛብ አንድ ሆነው አንድን አዲስን ሰው በራሱ በሠራው በእርሱ በመሆን ሁለቱ አንድ ሆነዋል። በሕዝቅኤል እና በራእይ በሁለቱም መጽሃፍት እንደተገለጠው የዛፎቹ ቅጠሎች ለመፈወስ ናቸው። በራእይ ውስጥ ዮሐንስ ማን እንደሚፈወስ ግልጽ አድርጓል። ቅጠሎቹ ለአህዛብ መፈወሻ ናቸው ይላልና። አህዛብን የፈወሳቸው ደግሞ ወንገል ነው። ያ የህይወት ዛፍ ፍሬን የሚያፈራ ነው። በመጻህፈ ምሳሌ መዕራፍ 11፡ 30 ላይ “የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው” ይላል። ይህ በግልጽ የሚያመሳስለው በሕዝቅኤል መጽሃፍ ካለው ቤተ መቅደስ ከከተማይቱ፣ ከማደሪያው ጋር ሲሆን፣ ይህም በራእይ ውስጥ ካለችው ከሙሽራይቱ፣ ከበጉ ሚስት ጋር ያው አንድ ነው። የሕዝቅኤል መጽሐፍ በአሥራ ሁለቱ ነገዶችና በእድል ፈንታቸው አንድነት የሚዘጋ ሲሆን ሕዝቅኤልም ቤተ መቅደሱን እንደ ከተማይቱ አድርጎ ትንቢቱን ሲያጠናቅቅ “እግዚአብሔር በዚያ አለ” በሚለው የታወቀ ንግግሩ ይደመድማል። ዮሐንስም ራእዩን ሲደመድም በከተማይቱ መካከል እግዚአብሔርና በጉ በዚያ መገኘታቸውን ይገልጥና “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” (ራእይ 22፥ 17) በሚለው ቃል ያጠቃልላል።

gkr








 






  







From Blogger iPhone client