Saturday, May 27, 2023

ፕሪቴሪዝምና ተስፋችን


ፕሪቴሪዝምና ተስፋችን 

ተስፋችን ምንድን ነው? ምንስ ተስፋ አለን?

2ቆሮ 5፥ 1 "ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።"

መግቢያ:-

ከበርካታ አመታት በፊት፣ የመካነ የሱስ ሴሚናሪ የስነመለኮት ትምህርት አጠናቅቄ እንደወጣሁና ገና በአፍላ የቅስና አገልግሎት ላይ እንዳለሁ ነው  በሙሉ ኃላፋውያን የነገረ ፍጻሜ ትምህርት መሳብና መገረም የጀመርኩት። ለማንበብና በወጉ ለማሰብ፣ እምነቴንም ለመመየቅ፣ ከማምነውና ከምወደው መጽሐፍ ቅዱሴም መልስ ለማግኘት ቀድሞ በብዙ ያልነበረኝ ትጋት የወቅቱ የለት ተለት ጥሞናዬም እንደነበር አስታውሳለሁ። ለበርካታ አመታት በውስጤ ሲያወዛግቡኝ የነበሩ ስነመለኮታዊ የነገረ ፍጻሜ ጥያቄዎቼም ቀስ በቀስ እየተመለሱ፣ የተፈጸመውን ወንጌል በደስታ ለመቀበልና ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል ብሎ ለማመን ብዙ ጊዜ አልፈጀኝም። ምናልባትም ያኔ ጥቂት አጠገቤ ለነበሩ ለሚሰሙኝና ለምሰማቸው ካልሆነ በቀር የነገረ ፍጻሜ አቋሜንና እይታዬን ማስተዋል የተቻላቸው ግን እምብዛም አልነበሩም። ይሁንና ከጊዜ ወደጊዜ ባንጽባርቅሁአቸው እይታዎቼ፣ ይልቁንም አብዛኛውን የብቸኝነት ወራት ባሳለፍሁበት የአራት አመት የቱርክ ምድር ቆይታዬ በሰፊው ለማንበብና ለማሰላሰል እድሉን በማግኘቴ ይህ የተፈጸመ የነገረ ፍጻሜ ምልከታ በእጅጉ እየማረከኝና እየወረሰኝ እንደመጣ ግን አስተውያለሁ። እኔም እሸሽገው እና እይዘው ዘንድ የማይቻለኝ የቃሉ ትምህርት መሆኑን ባወቅሁ መጠን፣ ምነም ያህል የሰላ ትችት ባያጋጥመኝም ተቃውሞውንና ነቀፋውን ለመሸከምና ቃሉን ይወዳሉ ብዬ ላሰብሁዋችው ሁሉ የገባኝን እውነት በፍቅር ለማካፈል እተጋለሁ። እንደሚታወቀው ሙሉ ኃላፋዊነት (ፕሪተርሪዝም) በ70 ዓ.ም በሆነው የኢየሩሳሌም ጥፋት ትንቢቶች ሁሉ በሙላት ተፈጽመዋል ሲል የሚያምንና የሚያስተምር የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ነው። እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱሴን ተጠግቼ ባጠናሁት ቁጥር፣ ፕሪቴሪዝም የለየለት እውነት መሆኑን ይበልጥ እርግጠኛ እየሆንኩ መጥቻለሁ። እኔ እንደማስበው ፕሪቴሪዝም የተስፋና የድል ህይወት ፍጻሜ ነው እንጂ፣ አንዳንዶች እንደሚመስላቸውና ሊተቹት እንአሚዳዳቸው ተስፋ ገዳይ እምነት አይደለም። ነገር ግን ይህንን የፕሪቴሪዝም አመለካከት ለሌሎች ለማካፈል ገና እፌን ስከፍት በርካቶች የሚያነሱትና የሚጠይቁኝ ጥያቄ፣ “ጌታ አስቀድሞ ተመልሶ መጥቶ ከሆነ፣ ታዲያ ምን ተስፋ አለኝ?” የሚለው ነው። በዚህች አጭር ምልከታ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እጥራለሁ።

ስለ ፕሪቴሪዝም አመለካከት ለሌሎች ለመናገር ደፈር ብለህ እምነትህን ስታካፍል ፈጥኖ ከሚቀርብልህ ጥያቄዎች መካከል አንዱና ዋነኛው “ታዲያ ምን ተስፋ አለኝ?" የሚለው የሰዎች ጥያቄ ነው። የቤተክርስቲያን ተስፋ ምን እንደሆነ ለመረዳት በዛሬው ዘመን ክርስቲያን ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ግራ መጋባት ያለ ይመስላል። እስቲ እንጠያየቅ፣ እንደ አማኝ ያለን ተስፋ በአካል ከምድር ገጽ ወደ ላይ መነጠቅ ነውን? በውኑ ተስፋችን ከመሞታችን በፊት ገና በዚሁ ሥጋ እያለን ወይም እርሱን አውልቀን ከምድር ላይ ሽቅብ እንደ ሮኬት መተኮስ ነውን? አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ፍርጥም ብለው “አዎ!” እሱ ነው የሚሉ ይመስለኛል። ስለዚህ፣ ቃሉን ብቻ መሰረት አድርገህ ዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ የተፈጸመና ያለፈ ክስተት መሆኑን ስትነግራቸውና ንጥቀትም ልበወለድ ተረት እንደሆነ ስታረዳቸውው፣ ልክ ጡጦውን እንደነጠቁት ህጻን ያለቻቸውን አንዲት ተስፋ የተነጠቁና ያጡ የሆኑ ያህል ይሰማቸዋል። በተስፋ ገዳይነትም ሊከሱህ ይጀምራሉ።

ፕሪቴሪዝም የሰዎችን ተስፋ ይገድላልን?

ፈጽሞ እንደዚያ አያደርግም፣ ፕሪቴሪዝም ተስፋችንን የበለጠ ያጠናክራል እንጂ ተስፋችንን አይገድልም። ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነጥብ ነው፣ ምክንያቱም "ተስፋ" ለሰው ልጆች በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ፕሪቴሪዝም የቤተ ክርስቲያንን ተስፋ ያጠፋል ብሎ መፈረጅ ደግሞ ከባድ የሆነ ውንጀላና ተቃውሞ ነው ምክንያቱም፡-  ሰዎች ኃይማኖተኝነትን ጨምሮ በየትኛውም የህይወት እርምጃ ውስጥ ተስፋ ያስፈልጋቸዋል!

እንበልና፣   "ይህ የ20 ዓመት ልጃችሁ ከደረሰበት አደጋ የተነሳ ቀሪ ህይወቱን ከአንገቱ በታች ሽባ ሆኖ ይኖራል፣  ምንም ማድረግ የምንችልም አይመስለንም" ተብሎ በሀኪሞች ለወላጆቹ ሲነገራቸው፣  ወላጆቹ የሚያደርጉትን በማጣት የሚያነሱት ጥያቄ "ታዲያ ምን ተስፋ አለ ትላላችሁ?" የሚል ነው" 

ተጋብተው ለሚኖሩ ባልና ሚስትስ ማባሪያ በሌለው የትዳር ጭቅጭቅ ውስጥ ሁልጊዜ እየተጣሉ ወደመለያየት ሲደርሱ አይተን ይህ እንዳይሆን ለሚፈልጉ ልጆቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ምን ተስፋ ይኖር ይሆን?

ወይም በአልኮል መጠጥ እየሰከረ ወይም ወሲብ ቀስቃሽ በሆኑ የብልግና ሥዕሎች የተጠመደ፣ ወይም በቁማር ጨዋታ ፍቅር የተለከፈ፣  ወይም በበርካታ ሱስ የሚያስይዙ ድርጊቶች ሰለባ የሆነ ሰው፣ እንዲህ ባለ አዘቅት ውስጥ ወድቆ ሳለ መቼም ከዚህ ጉድጓድ መውጫ መንገድ እንዳላገኝ ፈራሁ? ሲል  እንዲህ ላለው ሰው ምን ተስፋ ይኖረው ይሆን?

ነፍሰ ጡር ሆና የልጅ እናት ለመሆን የተዘጋጀች ሴት የጽንስ ክትትል የምታደርግበት የማህፀን ሐኪሟ ዘንድ ሄዳ ሳለ "እናዝናለን የጽንሱን የልብ ምት መስማት አልቻልንም?" ስትባል ያኔ ሊነገራትና ልትሰማው የምትችለው፤ ወይም ብቸኛ እናት ሆና በየቀኑ የሙሉ ጊዜ ሥራ እየሰራች፣ ሌሊቱንም  እንደ እናት እና አባት ሆና ልጆችዋን የምታሳድግና  የምታገለግል ሴት፣ "እንዲህ ሆኜ እስከ መቼ ልቀጥል እችላለሁ?" ብትል፤ ወይስ ድባቴንና ጭንቀትን እየታገለ ለሚኖር ሰው? ወይስ ሚስቱ ከሞት ጋር እየታገለች በምታጣጥርበት አልጋዋ አጠገብ ለቆመ አፍቃሪ ባል፣ ሊነገር የሚችል ምን ተስፋ ይኖር ይሆን?

በአደንዛዥ እፅ ቀንበር ስር ለወደቀ፣ በልቅ የወሲብ ልምምድ ሰበብ በሚተላለፉ በሽታዎች ለተበከለ ወጣት ትውልድ እና በፈረሰ ቤተሰብ ህመም ለሚሰቃይ ትውልድ  አንዳች ተስፋ የሚሆን ነገር ከወዴት አለ?

እኛ አማኞች የሆንን፣ ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች፣ “አዎ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ አለ" ብለን ልንመሰክር መድፈር አለብን። ወገኖች ሆይ፣ ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች ሁሉ እንደ ክርስቲያኖች ተስፋ መስጠት እንችላለን።

አንድ ጸሃፊ እንዲህ ሲል ገልጾታል, "ተስፋ የህይወት አስፈላጊ ዋና ነገር ነው፣ ሰው በተስፋ ይሠራል፣ በተስፋ ያድናል፣ በተስፋ ይሞታል፣ እያንዳንዱ ታላቅ ሃይማኖት፣ እያንዳንዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለሰዎች ተስፋን ይሰጣል."  ሌላው ጸሃፊ ደግሞ "ሰው 40 ቀን ያለ ምግብ፣ 4 ቀን ያለ ውሃ፣ 4 ደቂቃ ያለ አየር፣ ይኖራል ያለ ተስፋ ግን ሊኖር የሚችለው 4 ሰከንድ ብቻ ነው" ሲል ጽፏል።  ተስፋ በጣም አስቸጋሪ በሆነው የህይወት ዘመን ውጣ ውረድ ውስጥ ወደፊት እንድንራመድ የሚያደርገን ኃይል ነው።  ተስፋ እንቅፋቶችን ወስዶ ወደ እድሎች ይለውጣቸዋል።  ተስፋ ከሕይወታችን ምርጡን ለመጠቀም የሚያስፈልገንን ብርታት እና ድፍረት ይሰጠናል።

የተስፋን አስፈላጊነት እንደምትረዱት እርግጠኛ ነኝ።  ተስፋ ሊኖረን ይገባል፣ ነገር ግን ተስፋችን የተሳሳተ ተስፋ መሆን የለበትም።

የምታስታውሱ ከሆነ ከበርካታ አመታት በፊት 39 "የገነት በር" በመባል የሚታወቁት የከልት እንቅስቃሴ አባላት በኮሜት ሃሌ-ቦፕ መነቃቃት እየተካሄደ ነበር፣  በዚህ ንቅናቄ ተሳታፊ የነበሩ በርካታ ሰዎችም ከዩፎዎች ጋር ለመገናኘትና ይህንን ፕላኔት ትቶ ለመሄድ በማሰብ መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን አጥፍተዋል። ይህ የተሳሳተ ተስፋ ምሳሌ ነው። ሰዎቹም ከሞቱ በኋላ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት ባደረጉት ምርመራና ፍተሻ የአምልኮ ሥርዓቱ መሪ የአስትራል ትራቭል በማድረግ ስላለው ተስፋ ማብራሪያ የሰጠበትን የቪዲዮ ካሴት አግኝተው ተመልክተውታል። በቪዲዮውም ላይ አባላቱም ይህንን አለም ለመጨረሻ ጊዜ ለመሰናበት ሁለት ሁለት ሆነው አንድ ላይ በካሜራው ፊት ለፊት በመቅረብ ስንብት ያደርጉ እንደነበር ይታያል። በፊልሙ ላይ አንዲት ሴት፦ "ምናልባት እኔ እስከማውቀው ድረስ እነዚህ ሁሉ ሰዎች አእምሯቸውን የጣሉና ያበዱ ሊሆን ይችላል ነገር ግን በግሌ በዚህች ፕላኔት ላይ ለ 31 ዓመታት ኖሬ እዚህ ለእኔ የሚሆን ምንም ነገር ስለሌለ ወደዚያ ከመሄድ የተሻለ ሌላ ምንም ምርጫ የለኝም." ስትል ትደመጣለች። ያን አባባል ከሪፖርቱ ላይ ሳነብ በጣም አድርጌ አዘንሁ፣ ገረመኝም፡- ስለ ህይወት አንዳች ተስፋ የምትፈልግ ሴት ናት፣ ዳሩ ግን ምንም ተስፋ ለማይሆን ጉዳይ ክቡር ህይወቷን በከንቱ ሰጠች። የቅርቡ የኬንያው ጉድ የምስራች አለምአቀፍ ቤ/ክርስቲያን ፓስተር ፖል ማኬንዜ ህጻናት፣ ሴቶችና ወላጆቻቸውን ጨምሮ ከስድስት መቶ በላይ የሚቆጠሩ ተላላ አባላቱ ራሳቸውን አስርበው በጅምላ እንዲያልቁ ያደረገው በስብከቱ የአለም ፍጻሜ ደርሷል፣ ገነት ትገባላችሁ ተብለው ተሰብከው ነው፤ የፓስተራቸውን ሓሰተኛ የሆነ ገነት የመግባት ተስፋ አምነው ሁሉም ራሳቸውን በማስራብ ክቡር ህይወታቸውን አጡ። ከዩጋንዳ ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችን የአለም ፍጻሜ ቀርቧል ብለው ስላመኑ የምጽአትን ቀን በኢትዮጵያ ሆነው ለመቀበል መዘጋጀታቸው ነው። እንዲህ ያለ በተሳሳተ ተስፋ ላይ የተመሰረተ የበዛ ቅዠት በየስፍራው መስማት የተለመደ ነው።

የተወዳጁ አለንን በማስተዋል የተሰጠ ትንታኔ አዳምጡማ፣ "በታሪክ ውስጥ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የሰው ልጅ በህይወቱ ለምርጫ አስቸጋሪ የሆነ መስቀለኛ መንገድ ያጋጥመዋል። አንደኛው መንገድ ወደ ተስፋ ቢስነት እና ፍፁም ወደሆነ ተስፋ መቁረጥ የሚመራው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ መጥፋት። እንግዲህ ምንን በትክክል የመምረጥ ጥበብ እንዲኖረን አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል"።  ይህ ግን እንዴት ያለ አስከፊና አስጨናቂ  ምርጫ ነው! እኔ በግሌ የትኛውንም መንገድ አልመርጥም። ይህ የአለን ትንታኔ ግን  ዛሬ የብዙዎችን አስተሳሰብ ያንጸባርቃል።

ከጥቂት ጊዜ በፊት ስለተደረገ አንድ አስገራሚ ሳይንሳዊ ሙከራ አንብቤያለሁ። እነዚህ የሰው ልጆችን ባህርይ የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች አንዳንድ አይጦችን ይዘው በውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ አስቀመጧቸውና ከመስጠማቸው በፊት ምን ያህል ጊዜ በህይወት መቆየት እንደሚችሉ ተመለከቷቸው።  በአማካይ በህይወት የቆዩበት ጊዜ 17 ደቂቃዎችን ነበር።  ከዚያም ሙከራውን እንደገና ደገሙት፣ ነገር ግን በዚህ ጊዜ አይጦቹ ለመስጠም ገና ጥቂት ሲቀራቸው "አዳኑአቸውና"፣ ውሃውን ካደረቁላቸው በኋላ ወደ ሳጥኖቻቸው በመመለስ ምግብ እንዲበሉ እና ለጥቂት ቀናት እንዲጫወቱ ፈቀዱላቸው። ከዚያም እንደገና ያንን የመስጠም ሙከራውን ደገሙት። በዚህ ጊዜ፣ የእነዚህ አይጦች በአማካይ በህይወት የመትረፍ ጊዜ ከ17 ደቂቃ ወደ 36 ሰአታት አድጓል።  ሳይንቲስቶቹም ለሁለተኛ ጊዜ ባደረጉት ሙከራ አይጦቹ በህይወት ለመቆየት የሚያስችል ተስፋ እንደነበራቸው በመግለጽ ክስተቱን አብራርተዋል።  አይጦቹ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ልምምድ ውስጥ አልፈው ስለነበር በድጋሚ ይህንንም አልፈው በሕይወት መትረፍ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር። 

ስለዚህ ተስፋ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እናያለን። ተስፋ ሊኖረን ይገባል።

ተስፋ ምንድን ነው?

በዛሬው ዘመን ተርጓሚ ዘንድ “ተስፋ” የተሰኘው ቃል አስቀድሞ በአዲስ ኪዳን ከነበረው ትርጓሜ የተለየ ባዕድ ትርጉም እየያዘ ስለመጣ አስቀድሜ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የተስፋ ፍቺ ልሰጣችሁ እወዳለሁ። ዛሬ ዛሬ መደዴው የቃሉ አጥቃቀም ድንገተኛ ነገርን እንደመጠባበቅ ሆኖ ያመለክታል፤ የሆነ ነገር በድንገት እንደሚሆን መጠበቅ ማለት ነው። ነገር ግን በእርግጥ የሚከሰት መሆን አለመሆኑ ላይ አንዳንድ የሚነሳ ብዥታና ጥያቄ ግን አያጣውም። ለምሳሌ፣ ስለወደፊቱ አንዳንድ ጥርጣሬዎችን ወይም እርግጠኛ አለመሆንን በሚያሳይ መልኩ “ዛሬ አይዘንብም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ወይም “ወደሚቀጥለው የደመወዝ ቀን እንደምደርስ ተስፋ አደርጋለሁ” ልንል እንችላለን። ይህ ግን ተስፋ ለተሰኘው ለዚህ አይነተኛ ቃል የአዲስ ኪዳን እኩያ አጠቃቀም አይደለም።  በአዲስ ኪዳን ውስጥ ባለው አጠቃቀም ተስፋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ፍጹም እርግጠኝነትን፣ ጓጉቶ የመጠባበቅ ዝንባሌን፣ በእግዚአብሔር የመታመንን እና የገባውን ቃል የመፈጸም ችሎታውን ያመለክታል። የእብራይስጡ batach ወይም bittachown (baw-takh / bit-taw-khone) የተሰኘው ቃል ትርጉሙ፦ መሸሸጊያ ቦታን፣ መታመንን፣ መተማመንን ወይም እርግጠኛ መሆንን፣ እና ደፋር መሆንን ያመለክታል፤ ይህም የደህንነትን ወይም ደህና የመሆንን እውነታ እና ስሜት, የያዘ እምነት ወይም ዋስትና ነው። የግሪኩም elpizo ወይም elpis የተሰኘው ቃል ርትጉሙ እንደ እብራይስጡ ሁሉ ጓግቶ መጠበቅን ወይም ናፍቆትን መግለጽ፣ ተስፋ እና  እምነት፣ ወይም መተማመንን ያሳያል። ተስፋ፣ "ይህንን ዓለምና በውስጡ ያለውን ተግዳሮት ሁሉ ፊት ለፊት ለመገናኘት በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ተዝቆ የማያልቅ መዝገብ ሁሉ  አለኝ" የሚለው እርግጠኝነት ነው።

በርካታ ክርስቲያኖች ስለ ዳግመኛ ምጽአት አልፏል የሚለውን የፕሪቴሪዝም ትምሕርት በሚሰሙበት ጊዜ “ታዲያ ተስፋዬ ወዴት ነው” ብለው በርግገው ይጠይቃሉ፣ ምክንያቱም እንደ ክርስቲያን ተስፋችን ከክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ጋር የተጋመደ መሆኑን እንዲያምኑ ተደርገው እየተማሩ ስላደጉ ነው። ለምሳሌ፦

ጆን ፓይፐር። ሲጽፉ “አማኝ ለሆኑ ሁሉ የተባረከው ተስፋቸው የታላቁ አምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ነው” ብለዋል።

ጄሪ ፋልዌልም፣ “አብዛኞቹ ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ከሺህ አመት መንግስት አስቀድሞ፣ ከመከራው በፊት ለቤተክርስቲያኑ ሁሉ እንደሚመጣ  ያምናሉ፣ ይህም የተባረከ የቤተ ክርስቲያን ተስፋ ነው።  የክርስቶስን መምጣት በቅርቡ መጠበቅና ሙሽራውን ለመቀበል መዘጋጀት የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑትን ሁሉ  በዚህች ፕላኔት ከሚኖሩ ከሌሎች ነዋሪዎች የሚለያቸው አንዱ ምክንያት ነው" ሲሉ ጽፈዋል።

ይህ የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ የዘመን መዳቢነት ትርጉምን የሚከተሉ አማኞች ድምዳሜ ነው። ባነሳኋቸው ምሳሌዎች እንደተጠቀሱት እውቅ ሰባኪያን ሁሉ ይህ የመጻኢነት እምነት የአማኝን የተባረከ "ተስፋ" በቅርቡ ይሆናል ብሎ በሚጠባበቀው የጌታ ዳግም ምጽዓት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚያስተምር የነገረ ፍጻሜ ዘውግ ነው። እነዚህ ሰዎች በየዘመናቱ ምንም እርማት ሳያደርጉ ክርስቶስ በቅርቡ ይመጣል ብለው ያስተምራሉ። እንደ እነርሱ እምነት ከሆነ ይህ ተስፋ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ሲጠበቅ ያልተፈጸመ፣ እስካሁንም ዘግይቶ እየተጠበቀ ያለና አሁንም በሚበዙት ዘንድ ወደፊት አንድ ቀን ይፈጸማል ተብሎ እየተጠበቀ ብዙ የሚሰብኩለት፣ የሚዘምሩለትና አልፎም የሚጽፉለት ዋና ትምህርታቸው ነው።  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችም በአለም ዙሪያ በየዘመናቱ ለዚሁ እየጸለዩ የዚህ ተስፋ ፍጻሜ በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ እንደሚሆን ጠብቀው ሳያዩት ሞተዋል።  መጻኢነት ግን አሁንም ለስህተቱ እርማት ሳያደርግ የምጽአቱን ተስፋ ፍጻሜ እየጠበቀ አለ።  በዚህም ምክንያት የክርስቶስ ጠላቶች የሆኑ ከሃዲያን በስፋት የሚያውቁት የመጻኢነት አቋምና ትምህርት የክርስትናው አለም ብቸኛ እምነት የሆነ ይመስል እርሱኑ እንደ በቀቀን እየጮሁ የቅዱሳት መጻህፍትን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የጣሉ እየመሰላቸው እምነታችን ላይ ይሳለቃሉ የክርስትናን አስተምህሮም ውሸት ነው ሲሉ በጽኑ ይቃወማሉ።  መጻኢነት የብዙ ሰዎችን እምነት እያቀጨጨ ወደ ክህደት እንዲሳቡ የሚያደርግ፣ በምዕመናንና በሚወዷቸው ሰዎች ላይም በሚያሳዝን ሁኔታ ብስጭትና ተስፋ ማጣትን ያስከተለ ትምህርት ብቻ ሳይሆን፤ ከሃዲያንና የመስቀሉ ጠላቶች በክርስቶስ ላይ የሚያቀርቡትን ውንጀላ አመቻችቶ የሚያቀብል አደገኛ ስነ መለኮት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጠኝነት የክርስቶስ መምጣት የተባረከው ተስፋ እንደሆነ ያስተምራል። የፕሪቴሪዝም እምነትም ይኸው ነው። ፕሪተርዝም ለአማኙ የተፈጸመ ተስፋን እና የዘላለምን ሕይወት እምነት በሙላት ያቀርባል። ይህ የተፈጸመ ወንጌል ለአማኙ ፍጻሜውን ያገኘ መሻት እና የሕይወት ዛፍ ይሆንለታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ተስፋ መሰረት እርሱ በቀጠረው የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመለሰ ማወቃቸው ኃላፋዊያን ለሆኑ አማኞች የማይናወጥ ሰላምና ታላቅ መጽናናትን ይሰጣቸዋል። ፕሪቴሪዝም ጌታ ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ እነዚያን የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳንን በትውልዳቸው በቅርቡ እንደሚመጣ የሐሰት ትንቢት እየነገሩ እንዳላሳቷቸው በጽኑ ያረጋግጣል። መጥቶም የሰጠውን የተስፋ ቃል በመፈጸሙ እና ለመዳናችን ሙላት በመስጠቱ  ፕሪቴሪዝም በዚህ ሙሉ ደስታን  ያጣጥማል። እርግጥ ነው የክብር መገለጡ ለአማኞች የተባረከ ተስፋ ነው፣ ግን ለየትኞቹ አማኞች?

ቲቶ 2፥ 13 ".... የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥…." 

ችግሩ፣ የክርስቶስ ዳግመኛ  ምጽአት በተስፋነቱ በዚህ ክፍል "እኛ" ለተባሉት ወይም በቀጣዩ ጥቅስ "እናንተ" ለተባሉት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የተሰጠ ተስፋ መሆኑን አለማወቅ ነው።

ያዕ 5፥ 8 "እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።"
 
ተስፋውም ያኔ ለእነርሱ የተፈጸመ ተስፋ ነው ብለን ለማመን በቅዱስ ቃሉ ትምህርት እንገደዳለን። ዛሬ እኛ ግን የምንኖረውና እየኖርን ያለነው በምን አይነት ዘመን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፤ እኛ የምንኖረውና እየኖርን ያለነው እነዚያን የአዲስ ኪዳን ደብዳቤዎች ከተቀበሉና የምጽአቱ ተስፋ ተሰጥቷቸው የነበሩ የመጀመሪያዎቹ ተቀባዮች ከኖሩበት ዘመን በተለየ ዘመን ላይ ነው። በመላው አዲስ ኪዳን በስፋት ሲነገርለት የምናየውም ሁለት አይነት ዘመናትን ነው፣ እነርሱም፡-  "ይህ ዓለም" እና "የሚመጣው ዓለም" ወይም በተለዋጭ "ይህ ዘመን” እና “የሚመጣው ዘመን በመባል ይታወቃሉ።

ማቴዎስ 12፥ 32 "በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።" 

በጥቅሱ መጨረሻ ላይ በሚመጣው የተባለው (በእንግሊዝኛው the world to come) "ሊመጣ ያለው" የሚለው ሀረግ በግሪኩ "ሜሎው" ነው፤ ሲተረጎምም፦ ከጊዜው ቅርበት አንጻር "(እነሆ) ሊሆን ነው" ወይም "ሊሆን ቀርቧል"፣ ማለት ነው። እርሱም ለእነርሱ “ሊመጣ የቀረበ ዘመን ነው”። ለማን ነው "ሊመጣ ያለው"?  የሚመጣው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ለመጀመሪያዎቹ በኩረ ተደራስያን ነው፤ አለቀ፣ ይህንን መለጠጥም ሆነ፣ ዘመን አሻግሮ ማስፈንጠር አይቻልም።

ኤፌ 1፥ 21 "ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤"

እዚህም ላይ እንደገና ስለ ሁለቱ ዓለማት ወይም ዘመናት እናያለን። አዲስ ኪዳን ስለ ሁለት ዘመናት ሲያስተምር፣ “ይህ ዘመን” እና “የሚመጣው ዘመን” በማለት ይናገራል። እነዚህ ሁለት ዘመናት ምን አይነት ዘመናት እንደሆኑ እና አንዱ በሌላው የተተካበትንና ዘመናቱ የተለወጡበትን ጊዜ በወጉ መረዳት መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመተርጎም እና የዛሬ ተስፋችን ምን እንደሆነ ለመረዳት መሰረታዊ ነገር ነው። ይህንን ያስተማርሁበትን ጽሁፍ ማንበብ ለምትወዱ በብሎገሬ ላይ የከተብኩትን እንድትመለከት እጋብዛችኋለሁ፣ አሆ ሊንኩ፦

 https://gizachewkr.blogspot.com/2022/04/blog-post.html?m=1

የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩበት ዘመን  “ይህ ዘመን” ብለው ሲጠሩት በነበረ ዘመን ነው፣ እርሱም ለእነርሱ እያለቀና እየተዘጋ የነበረ የመጨረሻው ዘመን ነበር።  ለአዲስ ኪዳን ጸሓፊዎች፣ "የሚመጣው ዘመን" ብለው የሚጠሩት ወደፊት ይጠብቁት የነበረ ዘመን ተስፋቸው ነው። ነገር ግን "ይህ ዘመን" ሲሉ የጠሩትና የኖሩበት ዘመን ሊያበቃ ወደ ፍጻሜው ቀርቦ ስለነበር የሚጠባበቁትና "የሚመጣው ዘመን" ተስፋቸው ሊመጣ ለእነርሱ እጅግ ቀርቦ ነበር።

1ቆሮንቶስ 10፥ 11 "ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።"

የዘመናት ፍጻሜ በእነርሱ ላይ እንደደረሰ ጳውሎስ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን በግልጽ ይነግራቸዋል። ምክንያቱም እየኖሩበት የነበረውና  "ይህ ዘመን" እየተባለ የሚጠራው የእነርሱ ዘመን ሊያበቃ ተቃርቦ ነበርና።

መጽሐፍ ቅዱሳዊው “ይህ ዘመን” የአሮጌው ኪዳን ዘመን፣ እርሱም የአይሁድ ዘመን ነው።  ያ ዘመን ደግሞ ያበቃውና የተደመደመው በ70 ዓ.ም ቤተ መቅደሱ ሲፈርስ ነው። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ ዘመን” ብሎ ይጠራው በነበረው ዘመን መጨረሻ ላይ ነው። እኛ ግን  እየኖርን ያለነው መጽሐፍ ቅዱስ "የሚመጣው ዘመን" እያለ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው። "ይህ ዘመን" እየተባለ የተጠራው ያ የአሮጌው ኪዳን ዘመን የሚደመደመውና ሙሉ በሙሉ የሚያበቃው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በ70 ዓ.ም ላይ የአይሁድ ቤተ መቅደስ ሲፈራርስ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊው "ይህ ዘመን" አሁን ጥንታዊ ታሪክ ሆኗል።

ይህንን በአይምሮአችን ይዘን “ተስፋ” የሚለውን ቃል በአዲስ ኪዳን ስናስስ  መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ ዘመን” ብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን  ተስፋ የሆኑ በርካታ ነገሮችን እናገኛለን። የፕሪቴሪዝም አስተምህሮም እነዚህን ተስፋዎች ያጠፋቸው እንደሆነም እመልከት።

ተመልከቱ በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ ተስፋ ሆነው የተገለጡ  በርካታ ነገሮችን እናገኛለን፡-

1.ዳግመኛ ምጽአቱ፦

ቲቶ 2፥ 13 "ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤"

1ጴጥ 1፥ 13 "ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ።"

1ዮሐ 3፥ 2-3 "ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።"

ስለዚህ፣ ዳግመኛ ምጽአቱ “ይህ የአሁኑ ዘመን” እየተባለው በተጠራ የዘመን ምዕራፍ ውስጥ ለኖሩ ሰዎች የተሰጠ ተስፋ እንጂ "የሚመጣው ዘመን" ተብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ እየኖርን ላለን ቅዱሳን የተሰጠ ተስፋ  እንዳልሆነ በግልጽ እናያለን።

2. የሙታን ትንሣኤ፦ 

 ጳውሎስ ትንሳኤ ሙታን የእስራኤል እና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ተስፋ እንደሆነ በግልፅ አስተምሯል፡-

ሐዋ 23፥ 6፦ "ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ፦ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ።"

ሐዋ 24፥ 15፦ "እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።"

ሐዋ 28፥ 20፦ "ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።"

ሐዋ 26፥ 6-8፦ "አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል?"

ጳውሎስ እንደሚሰብከው ከሆነ ይህ የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ የሚመለከተው “እግዚአብሔር ለአባቶቻችን የገባውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም" እንደሆነ በተለይ ከዚህ የመጨረሻው ጥቅስ መረዳት ይቻላል።

3. ጽድቅ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ነበር፡-

ገላ 5፥ 5፦ "እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና።"

4. ድነት የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ነበር፡-

1ተሰ 5፥ 8፦ "እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤"

5. የዘላለም ሕይወት የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ነበር፡-

ቲቶ 1፥ 2፦ "በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥"

ቲቶ 3፥ 6-7፦ "ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።"

ለሰዎች አሁን የዘላለም ሕይወትን፣ መዳንን እና ጽድቅን ተቀብላችኋል፣ እነዚህ ነገሮች አሁን አሏችሁ፣ ብለን ብንነግራቸው፣ “ተስፋዬ ምንድን ነው፣ ወዴትስ አለ?” ብለው ይጠይቁን ነበርን?  በጭራሽ አይጠይቁንም፣ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች አሁን እንዳሏቸው ያምናሉና። ነገር ግን የዘላለም ሕይወት፣ ድነት እና ጽድቅ ሁሉም እነዚህ ነገሮች "ይህ ዘመን" እየተባለ ይጠራ በነበረ ዘመን ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ያኔ ተስፋቸው ነበሩ። የዘላለም ሕይወት፣ ድነት፣ እና ጽድቅ ሁሉ በብሉይ ኪዳን ዘመን መጨረሻ ላይ በሆነው በዳግም ምጽአቱ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ሙሉ ርስትና ውርስ ሆነዋል። እስከዚያ ድረስ ግን ተስፋ ነበር።

ኤፌ 1፥ 13-14 ፦ "እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።"

የርስት ጉዳይ ሲነሳ በመጻኢያንና በኃላፋውያን መካከል ያለው ልዩነት ጉልህ ነው። መጻኢያን በትምህርታቸው …..በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ በሰማይ የዘላለም ህይወት፣ ርስትና ሽልማትን እንደሚያገኙ ያስተምራሉ። ይህም ርስት መያዣው አሁን በመንፈስ ቅዱስ የታተመ ቢሆንም እንኳ በሙላት ይገለጥ ዘንድ ክርስቶስ በመጨረሻው ፍርዱ ዳግም እስኪመለስ ድረስ ገና ወደፊት ይጠበቃል እንጂ እስከ አሁን ድረስ ተጠናቆ አልተፈጸመም ይላሉ።

ፕሪተርዝም የሚያስተምረው ክርስቶስ አስቀድሞ በ70 ዓ.ም ተመልሶ ፍርድን ሁሉ በማጠናቀቁ፣ በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የተጠናቀቀውን የዘላለም ህይወት ርስት በሙላት ተቀብለዋል። ከ70ው ዓ.ም ዳግመኛ ምጽአቱ አንስቶ መንፈሳዊ በሆነው የአዲሱ ኪዳን የወንጌል መንግሥት ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ዳግመኛ ለተወለደ ክርስቲያንም የቤዛነት ስራው ያስጀመረውን መንፈሳዊውን ርስት ዳግም ምጽአቱ ለዘላለም አስገኝቶቷል ማለት ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሪቴሪዝም ቀድሞውኑ የተጠናቀቀውን ርስት በሙላት ሲያቀርብልን አንዳች የሚቀረውና የሚጎድለው ነገር የለውም።  መጻኢነት ግን ይህንን ርስት በሙላት ለማግኘት የክርስቶስን ዳግመኛ መምጣት ወደፊት መጠበቅ አለበት። 

በዚህ ጉዳይ ማጠቃለያ የሚሆን አሳብ አንስቼ ወደሚቀጥለው ጉድይ ልሻገር፡- በክርስቶስ የመጀመሪያ በሥጋ መምጣት እና ሁለተኛው የፍርድ ምጽአት መካከል ባለው የአርባ አመታት የሽግግር ወቅት ለነበሩት ለነዚህ የመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን የጳውሎስ ተደራስያን በትምህርቱ ገና ተጠናቅቆ ስላልተፈጸመ ርስት ይነግራቸዋል። 

በአጠቃላይ መጻኢያን ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የተጻፉ ጽሑፎችን በአለም ዙርያ በየትኛውም ታሪክ ውስጥ ለነበሩ እና ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ የተጻፉ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ፣ ተጠናቅቆ በሙላት የተሰጠውን ርስት አይገነዘቡትም። በመሆኑም እስከአሁን ድረስ የጌታ ዳግም ምጽአት አንድ ቀን ወደፊት ይሆናል ብለው ስለሚያምኑ ርስታቸውን በሙላት የሚቀበሉበትን ቀን እየተጠባበቁ ናቸው።

ፕሪቴርሪዝም ግን ጳውሎስ በቀጥታ ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አማኞች እየጻፈ መሆኑን እና የርስታቸው ሙላት  ወደፊት በቅርቡ ለእነርሱ የሚፈጸም እንደሚሆን እያስተማራቸው መሆኑን በሚገባ ተረድቷል።

በዚያ የሽግግር ወቅት ለነበሩ ቅዱሳን ሊቀበሉት ያለው ርስት ቃል የተገባላቸውና የተጠበቀላቸው ስጦታ፣ ተስፋቸው ነበር። የጳውሎስ ትምህርትም እንደሚያመለክተው ርስት እነርሱ በነበሩበት አሁናቸው ላይ በሙላት የተገኘና የተጨበጠ ሳይሆ ለእነርሱ ገና ወደፊት በምጽአቱ (ፓሮውዥያው) ላይ ሊሆን ያለና የሚጠባበቁት መሆኑን ያሳያል። ለምሳሌ ቀጥሎ ያሉትን የንባብ ክፍሎች በጥንቃቄ ስሙ:-

ሐዋ 20፥ 32 "አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።"

ኤፌ 1፥ 15-18 "ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ።  ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤"

ቆላ 3፥ 23-24 "ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥  ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና።"

ዕብራ 9፥ 11-15 "ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።"


ጴጥሮስም እነዚያ የሚጽፍላቸው የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ለእነርሱ በሆነ መጻኢ ጊዜ በሰማይ ስለሚጠብቃቸው የርስት ተስፋ ተናግሯል፣ ይህም ርስት ክርስቶስ በዳግመኛ ምጽአቱ ተመልሶ ሲመጣ በሙላት ስለሚቀበሉት ነው።

1ጴጥ 1፥ 3-5 " ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።"

በብሉይ ኪዳን ዘመን መጨረሻ ማለትም በ70 ዓ.ም ላይ (ይኸውም የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ቀን ነው)፣ ያኔ ብዙ ነገሮች ተከስተዋል፡-
1. ክርስቶስ ተመልሷል፡-

2ጢሞ 4፥ 1፦ "በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤"

ዕብ 10፥ 37፦ "ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤"

2. የሙታን ትንሣኤ ሆኗል፦

ዮሐ 11፥ 24፦ "ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።"

ይህ መጨረሻ “ይህ ዘመን" በመባል የሚታወቀው የአሮጌው ዘመን የመጨረሻ ቀን” ማለት ነበር፣ “የሚመጣው ዘመን” በመባል የሚታወቀው ዘመን ግን ዘላለማዊ ነው እንጂ የመጨረሻ ቀናት የሉትም፤  ስለዚህ፣ የሙታን ትንሳኤ የሚሆነው በአሮጌው ኪዳን ዘመን መጨረሻ ላይ ጌታ በተመለሰ ጊዜ ነው።

3. ፍርድ ተከናውኗል፡-

ማቴ 13፥ 40፦ "እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።"

መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ ዘመን” ሲል የሚያውቀው የአሮጌው ኪዳን ዘመን ያኔ በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በ70 ዓ.ም የቤተ መቅደሱ ውድመት ጊዜ በተከናወነው የጌታ ተመልሶ መምጣት ስላበቃ እኛ ዛሬ የምንኖረው መጽሐፉ “የሚመጣው ዘመን” ብሎ በሚያወቀው አዲሱ ዘመን ውስጥ መሆን አለበት።  እኛም አሁን እየኖርን ያለነው "የሚመጣው ዘመን" ተብሎ በሚጠራው አዲስ ዘመን ውስጥ ከሆነ እንግዲያውስ ክርስቶስ እንደ ተስፋ ቃሉ አስቀድሞ ተመልሷል፣ ትንሣኤም ከአሁን በፊት ሆኗል፣ የአሕዛብ ፍርድም ተፈጽሟል ማለት ነው።

አማኞች በሚመጣው ዘመን ምን እንደሚቀበሉ ኢየሱስ የተናገረውን አስተውሉ፡-

ማር 10፥ 29-30፦ "ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።"

ከፍ ሲል እንዳየነው የዘላለም ሕይወት “ይህ ዘመን” በመባል ይጠራ በነበረው ጊዜ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት የተሰጠ “ተስፋቸው” ነበር ነገር ግን አሁን ባለውና እኛ እየኖርንበት ባለው በዚህ  “የሚመጣው ዘመን” በተባለው ማለትም የአዲሱ ኪዳን ዘመን የአማኞች ሁሉ ርስት ነው።

እንግዲህ ዳግመኛ  ምጽአቱን  ጨምሮ የሙታን ትንሣኤ፣ ፍርድ፣ የዘላለም ሕይወት፣ መዳንና ጽድቅ ሁሉም ቀደም ሲል ተፈጽመዋል ተከናውነዋልም፤ ታዲያ ለምን ተስፋችን ይሆናሉ?  ያለህንና ያገኘኸውን ነገር ተስፋ አታደርግም፦

ሮሜ 8፥ 24-25፦ "በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?  የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።"

ፕሪተርስቶች የሆንን እኛ ተስፋን ተፈጽሟል ብለን እናፅናናለን እንጂ ወዲያ አሽቀንጥረን አንጥለውም። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ስታደርገው የነበረውን ሁሉ አሁን እኛ ወርሰነዋል፣ አሁን ለእኛ ይዞታችን ነው።

ታዲያ ዛሬ ተስፋችን ምንድን ነው?

በኢየሱስ ክርስቶስ ለማያምኑ ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም።

ኤፌ 2፥ 12፦ "በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።"

እምነታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ላደረግን ሁሉ ግን ሰማይ ተስፋችን ነው። ቀደም ሲል ያልነውን አትርሱ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ተስፋ የመልካም ምኞት መግለጫ ንግግር አይደለም፤ ይልቁንም ወደፊት ስለሚመጣ እርግጠኛ መልካም ነገር ፍጹም የሆነ መተማመን ነው።

2ቆሮ 5፥ 1 ፦ "ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።"

ጳውሎስ እዚህ ላይ “ድንኳን” የሚለውን ቃል ሥጋዊውን ተዳሳሽ  አካል በሚወክልበት መንገድ እየተጠቀመበት ነው።  ጴጥሮስም፦
 
በ2ኛ ጴጥሮስ 1፥ 13-14 ባለው ክፍል "ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና።" ሲል የተጠቀመበት ማደሪያ የተሰኘው ልቃ ተመሳሳይ አጠቃቀም አለው።

ምእመናን፣ ሁላችንም አንድ ቀን በአካል እንሞታለን፣ ይህም የማይለወጥ ተፈጥሯዊ ህግ ነው። "ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞት ከዚያም በኋላ ፍርድ ተመድቦላቸዋል" ተብሏልና፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን ወደ ሰማይ እንሄዳለን እንጂ እልም ብለን እንጠፋለን ማለት አይደለም፣ ወደ እሳት ባህርም እንጣላለን ማለት አይደለም፤ እንሞታለን ግን በተስፋ እንሞታለን። ተስፋ ያለው ሞት የአማኞች ሞት ነው፤ አማኝ ሲሞት "ከሞት ወደ ህይወት የተሻገረ" ሟች እንጂ "ወደ ፍርድ አይሄድም" ።

2ቆሮ 5፥ 6-8 "እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል።"

እንግዲህ ተስፋችን (ተስፋ ትርጉሙ፡- “ስለ ወደፊቱ ያለን ፍጹም እርግጠኝነት ነው)” ይኸውም በሞታችን ጊዜ ይህን አካል ትተን ስንሄድ በሰማያት ከጌታ ጋር ለዘላለም አብረን እንደምንሆን ያለን አለኝታ ነው።

የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ጠንቅቀው የሚያውቁ ሁሉ የሳባ ንግሥት የነበረችው ሰሎሞንን ለመጎብኘት ያደረገችውን የጉዞ ታሪክ ያስታውላሉ ብዬ አስባለሁ።  የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ታላቅነት፣ የክብሩንና የጥበቡን ዝና ሁሉ ሰምታ ነበር።  አገልጋዮቿም ስለሚያውቁት የዚህን ሰው ታላቅ ዝና ምን እንደሚመስል ሀሳብ ሊሰጧት ሞክረው ነበር።  እነርሱም የሰለሞንን ክብር በግልፅ እና በብርቱ ቃል ነገሯት።  እሷ ግን የሰማችውን ሁሉ በቀላሉ  ማመን አልቻለችም።  ይልቁንም ራሷ ሄዳ የሰማችውን በአይኗ ለማየት እንደወሰነች በ1ኛ ነገሥት 10 ላይ ከተጻፈው ታሪክ እናነባለን።  በመጣችም ጊዜ የሰሎሞንን ጥበብ በጆሮዋ ሰማች እርሱም በልቧ ያለውን ሁሉ ነገራት።  እሷም ብዙ የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠየቀችው፣ ክብሩን፣ ልብሰ መንግስቱን እና በመንግስቱ ላይ ያሉትን የከበሩ ነገሮች ሁሉ አየች።  የንጉሥ ሰሎሞንንም ክብር ሁሉ እያየች፣ ንጉሡንም አለችው፦

1ነገስት 10፥ 6-7 " ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል።"

"እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤" ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎችም የሚያጋጥማቸው እንዲህ ያለው ነገር ይሆናል።  ሰማይ ምን እንደሚመስልና ምን እንደሆነ ከፊሉ እንኳ ገና ሊነገርህ አልተቻለም። ሞተህ እዚያው ስትሄድ አንተው ራስህ ታየዋለህ።

ሰማይ ግን የት ነው?

ለዚህ ጥያቄ መልስ እንዲሆነን መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይ መንፈሳዊ እንደሆነ ይነግረናል።  ሰማይ እውን ነው፤ ሰማይ ከምድር በተለየ ግዛት ውስጥ ብቻ ያለ ነው።  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሰማያዊው ዓለም እና ስለ ምድራዊው ዓለም በግልጽ እናነባለን።  ምድራዊው ዓለም የሥጋ፣ የቁሳቁስና፣ ለዓይናችን የሚታየው ነገር ሁሉ ነው። ልናየው፣ ልንዳስሰው፣ ልናሸትተው፣ ልንሰማው፣  እና ልንቀምሰው የምንችለው ተዳሳሹ ግዛት ነው።

በሌላ በኩል ሰማይ መንፈሳዊ ነው። ሰማይ ተፈጥሮው ሰማያዊ (ቀለሙን እንዳይመስላችሁ) ነው።  በነዚህ አይኖቻችን ልናየው አንችልም።  በነዚህ ጆሮቻችን ልንሰማው አንችልም።  በእነዚህ እጆቻችን ልንዳስሰውና ሊሰማን አንችልም።  በምላሳችን ልንቀምሰውም ሆነ በአፍንጫችን ልናሸትተው  አንችልም።  ሰማይ ከምድር በሆነ ምንም ነገር አልተሰራምና ምድራዊ በሆነ የትኛውም እሳቤ አይተረክም። ጳውሎስ ለግሪክ ፈላስፋዎች ሲናገር ፦

ሐዋ17፥ 24 "ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤" ይላል።

ጳውሎስ ይህንን በግሪክ ፈላስፎች ፊት የተናገረው የማርስ ኮረብታ እያሉ በሚጠሩት አርዮስፋጎስ ላይ ቆሞ ነበር።  ግሪኮች ለአማልክቶቻቸው የድንጋይ ቤቶችን ይሰሩ ነበር። ለአማልክቶቻቸውም ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ይሰጡ ነበር፤ እንዲበሉላቸውም ፍራፍሬና ሥጋ ያቀርቡላቸው ነበር።  ምናልባትም የጥንት ጣዖት አምላኪዎች ለጣዖቶቻቸው ሰይፍና ታንኳ፣ እንዲሁም ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት የሚያገለግሉ ሁሉንም ዓይነት መሣሪያዎች ያቀርቡ ይሆናል።  ከዚህ ምድራዊ አለምን የህይወት ቅርጽ ጽንሰ አሳብ ተነስተው የአማልክቶቻቸውን ተፈጥሮና ግዛታቸውን ፅንሰዋል።  ጳውሎስም ሲናገር ይህ  ሞኝነት ነው አለ።  ሰማይ መንፈሳዊ ነው።  ሰማይ ዘላለማዊ እና ሕያው የሆነ አምላክ የፈጠረው ቦታ ነው።  መላእክት የሚኖሩበት ቦታ ነው።  በዕብራውያን ውስጥ እንደምናነበውም የጻድቃን መንፈሶች አሁን ፍጹማን ሆነው የተከማቹበት የክብር ስፍራ ነው።  ሰማይ ቅድስተ ቅዱሳን ናት፤ የከበረች ናት፤ ከፍ ያለች ናት፤ ፍትሐዊም ናት።

በሰማያዊውና በምድራዊው መካከል ያለውን ልዩነት መፅሃፍ ቅዱስ የሚነግረን ከክብር አንፃር ነው።  ሰማይ ከፍ ከፍ ያለ ነው። ሰማይ ከፍ ያለውና በከፍታው የሚኖረው - በአካላዊና በተፈጥሯዊ ሁኔታ አይደለም። ሊለካና ሊሰፈር በሚችል ከፍታም ከፍ ያለ አይደለም። ነገር ግን ሰማይ ከፍ ያለው፣ በግርማው የከበረ፣ በእግዚአብሔር ክብር ከፍ ከፍ ያለ፣ በእግዚአብሔር ቅድስና ከፍ ያለ ሰማያዊ ከፍታ በመሆኑ ነው። በመዝሙር 113 ላይ እንዲህ ይላል፦

 መዝ 113፥ 4-5፦ "እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ነው፥ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው። እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤"

በግርማው ከፍ ያለ! እንደገናም እንዲህ የሚል እናነባለን፦

ኢሳ 57፥ 15፦ "ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ።"

እንደገናም በኢሳይያስ 63 ላይ እንዲህ ይላል፦

ኢሳ 63፥ 15፦ "ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ።"

ሰማይ የእግዚአብሔር የቅድስናውና እና የክብሩ ቦታ ነው።  ሰማያት ንጹሕ፣ ቅዱስ ፣ የከበረም ነው።  ሰማይን ከማየትህ በፊት እግዚአብሔር አዲስ መንፈሳዊ ዓይኖችን ሊሰጥህ ይገባል።

ሰማይ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ስፍራ፡- ሰማይ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው ሲል መልስ ይሰጣል። ከሕያው እና ከእውነተኛው አምላክ ጋር ፍጹም የሆነ ኅብረት የሚኖረንበት ቦታ ነው።  ያ እውነት በሁሉም ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እንደ ሸማኔ መውርውሪያ ወዲና ወዲህ እያለ የሚፈስ የወርቅ ክር ነው።  ሰማይ ይህ ነው፡ የእግዚአብሔር ማደሪያ እንደሆነም በተደጋጋሚ ተነግሮናል።  ፍጡር የተባረከውን የሕያው እግዚአብሔር ኅብረት ሊደሰት በሚችልበት መጠን የእግዚአብሔር ኃልዎት በሙላት የሚገለጥበት እና የእግዚአብሔርን ፍጹም መገኘት ሙሉ በሙሉ የሚደሰትበት ስፍራ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይን ለመግለጽ እነዚህን ቃላት ይጠቀማል፡- ቅዱስ ማደሪያ፣ መኖርያው፣ የተቀደሰው ማደሪያው፣ ከፍ ያለው የመቅደሱ ከፍታ።  መጽሐፍ ቅዱስ በሰማያት ስለሚኖረው ስለ እግዚአብሔር ይናገራል። ሰማይ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው፣ እግዚአብሔርን በቅርብ የምናውቅበት ሕይወት እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ሕይወት የምንደሰትበት ስፍራ ነው። ታውቃላችሁ፣ "መኖርያ" የሚለው ቃል በጣም ሀብታም ቃል ነው፤ ቃሉ  በቀላሉ ከመኖር የበለጠ ማለት ነው።  እኔ የምኖርበት ቦታ ነው ስትል፣ ያለህበትን ቦታ እያልክ አይደለም።  ነገር ግን "መኖርያ" የሚለው ቃል የህብረትን ሀሳብ የተሸከመ ቃል ነው። የምትኖርበት ቦታ ማንነትህን የምትገልጥበት ነው።  በዚያ አንተ የተከፈትህ ነህ።  ፍቅርህን በዚያ ታሳያለህ፣ ቅርብ የሆኑ የህይወትህን ክፍሎች ታጋራለህ። ስለዚህ ሰማይ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ መገኛውና ኅብረቱ፣ የእግዚአብሔር ፍቅርና ጸጋ የሚታወቅበት ቦታ ነው።  ሰማይን ሰማይ የሚያደርገው ያ ነው። የሰማይ ክብሩም ይኸው ነው፣ እርሱም ከመታወቅ የሚያልፍ እኛ መገመት የማንችለው ነገር ነው። ጳውሎስ ስለ ሰማይ ያለውን ነገር ልብ ብላችሁ አስተውሉ፡-

2ቆሮ 12፥ 1-4 "ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።"

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማይ ብዙና ዝርዝር ነገር አይነግረንም፤ ይህም ጉዳዩ አሁን ከመረዳት አቅማችን በላይ ስለሆነና፣ "ሰውም ሊናገር የማይገባው የማይነገረው ቃል" በመሆኑ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ሰማይ በመሰረቱ ምጡቅ የእግዚአብሔር ማደሪያ መሆኑንም ጭምር በጥልቀት እንድንረዳና እንድንናፍቀው እግዚአብሔር ስለሚፈልግ ነው።  ሰማይን እጅግ የተባረከ፣ ግርማ ሞገስ ያለው፣ በግርማውም እጅግ አስፈሪ ስፍራ የሚያደርገው አንድ ማዕከላዊ ነገር አለው። ይህም  አንድ ነገር፤ በዚያ እግዚአብሔርን በዘላለማዊ ህያውነቱ የምናየው መሆኑን ነው።

ምእመን ልብ ብላችሁ ስሙ፣ ተስፋችን ያ ነው - እርሱም ሰማይ። በ1ኛ ተሰሎንቄ ትምህርት መሠረት፣ በሞታችን ቀን ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል እንወሰዳለን፣ እናም ከጌታ ጋር ለዘላለም እንሆናለን።  ይህ ታዲያ እንዴት ያለ በጽኑ የሚናፈቅ ታላቅ ተስፋ ነው።

1ተሰ 4፥ 17 "ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።"

"እንነጠቃለን" የሚለው ቃል በግሪኩ harpazo ይሰኛል፣ ትርጉሙም፡- “መወሰድ” ማለት ነው።  “መነጠቅ” የሚለው ቃልም የመጣው ከዚህ ነው። ነገር ግን በእርግጠኝነት “መወሰድ” ማለት ቁስ የሆነውን ሥጋዊ አካልን ከምድር ላይ ወደ ሰማይ ከባቢ አየር (ጠፈር) ከማስወጣት ተግባር የተለየ ነገር ነው።  ሃርጳዞ የሚለው ቃል የሚያመለክተው ክርስቲያን ያለ ቁሳዊ አካሉ "መወሰዱን" ነው።

የተነጠቀው ተዳሳሹ ሥጋዊው አካል አይደለም።  በሥጋዊው ሞት ጊዜ ሥጋውን ትቶ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ሲሸጋገር የተነጠቀው ራሱ ክርስቲያኑ ነው። ክርስቶስ በተመለሰ ጊዜ ያኔ አስቀድመው ሞተው የነበሩ አማኞች ተነስተዋል፣ ክርስቲያኖች ሁሉ ደግሞ በሥጋዊ ሞታቸው ጊዜ በደመና ይነጠቃሉ። 

(በዚህ ርዕሰ ጉዳይ "ንጥቀትና ትምህርቱ"፣ እንዲሁም "የተዋሩደው ስጋችን ልውጠት" በሚል ርዕስ በጽሁፍ ያስተማርሁበትን ማየት ለምትወዱ እነሆ ሊንኩ)፦

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/01/blog-post.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2021/08/blog-post.html?m=1


ወገኖች ሆይ፣ ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም ለመኖር ወደ ሰማይ ከመወሰድ የበለጠ ምን ተስፋ አለን?  ይህም ቤተክርስቲያን አሁን በምድር ያለችበትና የምትጋደልለት ተስፋዋ ነው፣ ፕሪተሪዝምም ይህንን ተስፋ አጥብቆ ያረጋግጣል እንጂ ፈጽሞ አይክደውም።

ምዕመናን ስሙኝ፣  ፍርድን እንጂ ሥጋዊውን ሞት ልናመልጥ የምንችልበት ምንም አይነት መንገድ የለም - ሁሉም ሰው ይሞታል።

 እብራ 9፥ 27፦ "ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው" ይላልና።

በአካል ስንሞት ግን ከጌታ ጋር ለዘላለም ወደምንኖርበት ሰማያዊው ዓለም በክብር እንሄዳለን! ይህ እንዴት ያለ መጽናናት የሞላበት የተባረከ ተስፋ ነው! ምዕመናን በሃሰተኛ ተስፋ አትታመኑ። ሞታችሁ በብጹዕ መሰናበት ከጌታ ጋር ለመሆን በቅጽበት አይን ትወሰዳላችሁ እንጂ በሞት መንገድ ሳትሄዱ የሰው ልብ ወልድ ቅዥት የሆነውን አካላዊ መነጠቅን ፈጽሞ አታዩም። በእምነትና በንስሃ ለሞታችሁ ቀን ተዘጋጁ እንጂ በማይፈጸም የንጥቀት ተስፋ ልባችሁን አታዝሉ።

ግዛቸው (ቄስ)



1 comment:

  1. what a wonderful and joyfully message 😯❤❤❤ ወንድም (ቄስ) ግዛቸው ፀጋና ጥበብ መገለጥ ይብዛልህ ብሩክ ነሕ አንተ በረከት ለኛ 🙏🙏

    ReplyDelete