ፕሪቴሪዝምና ፓሮውዥያ (፩)
“የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” የሚለው ይህ በማርቆስ 14፥ 61-62 ያለው ቃል እና በዮሐንስ 21፥ 22-23፣ ያለው ቃል፣ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ እና ሐዋርያው ዮሐንስ የጌታን ዳግም ምጽአት በአይናቸው ለማየት በህይወት እንደሚኖሩ ኢየሱስ የተናገረው የታመነ ቃል ነው።
በማርቆስ 14፥ 61-62፣ ኢየሱስን እንዲገደል ለሮማውያን አሳልፎ የሰጠውን ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን በተመለከተ የሰው ልጅ በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ እንደሚያየው በግልጽ ነግሮታል። እንደገናም በዮሐንስ 21፥ 22-23፣ እንደተጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ በሕይወት ኖሮ እንደሚቆይ ተነግሮታል። ኢየሱስም በማቴዎስ 16፥ 27-28፣ በማቴዎስ 24 እና ማርቆስ 8፥ 38-9፥ 1 ባለው ክፍል ላይ በዚያው ትውልድ እንደሚመለስ ቃል ገብቷል። ኢየሱስ ስለዳግመኛ ምጽአቱ ደጋግሞ ከተናገራቸው እንደነዚህ ካሉት ንግግሮቹ የተነሳ ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ የጥንት ቤተክርስቲያን ምዕመናን በሙሉ ኢየሱስ በህይወት ዘመናቸው ተመልሶ እንደሚመጣ በብዙ ያምኑና ይጠባበቁ እንደነበር መላው የአዲስ ኪዳን መልዕክቶች ያሳያሉ። ይህንን በበቂ ሊያስተባብልና ሊቃወም የቻለ ሥነመለኮት ፈጽሞ የሌለ በመሆኑ ፓሮውዥያው ከፍ ሲል በተጠቀሱት አይነተኛ ሰዎችና በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ትውልድ ውስጥ ተፈጽሟል ብሎ በዚህ እምነት ለመቆም ፕሪቴሪዝም ከተረትና ከልማድ ርቆ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ መሰረት አድርጓል።
ፕሪቴሪዝም ይለመልማል።
አልጨረስኩም
(GKR)
ፕሪቴሪዝምና ፓሮውዥያ (፪)
ስለ ፓሮሺያ ቅድመ ፕሪተርስት እይታ–
“የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”፡-
"ታያላችሁ" የተባሉት እና ይህ ሲሆን ያዩ ዘንድ የተገባቸው እነማን እንደሆኑ ካላወቅን፣ "ታያላችሁ" የተባሉት ሊያዩ የተገባቸውን ካላዩ፣ ጌታም በኃይል ቀኝ መቀመጡንና በሰማይ ደመና መምጣቱን እስካሁን ካላሳያቸውና፣ ታያላችሁ የተባሉት ሊያዩ የተገባቸውን ሳያዩ ካለፉ፣ እኛን ጨምሮ ከዚያስ በኋላ ባለው ትውልድ የኖረና ገና ወደፊት የሚመጣ ሌላ ትውልድ ይህንን ሊያይ እንዴት ይችላል? ጌታስ እንዴት ታማኝ ይሆናል? እኛ እናይ ይሆናል የምትሉ ሁሉ እውነት እላችኋለሁ፣ ታያላችሁ ከተባሉት በቀር ማንም ቢሆን ይህ ሲሆን የሚያይ ከዚህ በኋላ እንደማይኖር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ።
ተመልከቱ፣ ዳግም ምጽአት በራእይ 19፥ 11-14 እንዴት እንደተገለጠ ተዘግቧል። በዚያም የራእዩ ክፍል ኢየሱስ የመላእክትን ሠራዊት በሰማይ ላይ ሲመራ ይታያል። እንዲህ ሲል፦
"ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም። ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል። በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።"
ፕሪቴሪዝም ይህ ቃል በጊዜው ለዚያውም በገሃድ እንደተፈጸመ ያምናል። የዚህ ትንቢታዊ ራእይ ታሪካዊ ፍጻሜ ደግሞ የሰው ልጅ የሆነው ጌታ ኢየሱስ፣ በ66 ዓ.ም በአይሁድ ሮም ጦርነት መጀመሪያ ላይ በደመና ውስጥ በገሃድ መታየቱ ነው። ይህንን ታሪካዊ ክስተት እና ዘገባውን ከዚህ ቀደም በግርድፉ አካፍያችሁ እንደነበር ይታወሳል። በቀጣዩ ጽሁፌ ሰፋ አድርጌ በማስረጃዎቹ ላይ እመለሳለሁ። ይሁንና ግን ይህ ታሪካዊ ማስረጃ ባይኖረን እንኳ፣ ክርስቶስ በዚያ ከተማይቱና መቅደስዋ ፈጽመው በሚፈራርሱበት የአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅት ተመልሶ ለመምጣት የሰጠውን ተስፋ እንደፈጸመ ያለጥርጥር ማመን ይቻለናል። ምክንያቱም እንደዚያ እንድናምን በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ተይዘናልና።
ተመልከቱ፣ ዳግመኛ ምጽአቱ በራዕይ 19፥ 11-14 በዝርዝር እንደተገለጸዉ ጌታ ኢየሱስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ የመላእክትን ሠራዊት እየመራ በደመና ላይ የታየበት ነው። ይህ ቃል እንዴት እንደተፈጸመና የዳግም ምጽአቱ ገሃዳዊ መታየት ምን እንደሚመስል፣ ታሪክም እንዴት ዘግቦ እንዳስቀመጠው በሚቀጥለው ክፍል እናያለን።
ከዝባዝንኬ ተረትና የቆየ ልማድ ርቃችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ማመንና መታዘዝ ይበዛላችሁ ዘንድ እጸልያለሁ። ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን።
(GKR)
ፕሪቴሪዝምና ፓሮውዥያ (፫)
የዳግም ምጽአቱ ቀዳሚ ፍጻሜ ታሪካዊ ምስክርነት—
“የሰው ልጅም . . . በሰማይ ደመና ይመጣል”፡-
አሁን የምታነቡትን ነገር ምናልባት ከዚህ ቀደም ያልሰማችሁት ታሪክ ሊሆን ይችላል። ዳሩ ግን ይህን ታሪካዊ ዘገባ ለሚያስተውለው ሰው ከዘሙኑ ፍጻሜና ከጌታ ዳግም ምጽአት ምንነት አንጻር አእምሮን ሊይዝ የሚችል ብርቱ ምስክርነትእንደሚሆንቡት አልጠራጠርም። የዳግም ምጽአቱ ኹነት በአይሁድ ሮም የጦርነት ታሪክ ተዘግቦ ትውልድ እንዲያነበው ተቀምጧልና። አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ ይህ ታሪካዊ ማስረጃ ፈጽሞ ባይኖረን እንኳ፣ ክርስቶስ በዚያ ከተማይቱና መቅደስዋ ፈጽመው በሚፈራርሱበት የአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅት ተመልሶ ለመምጣት የሰጠውን ተስፋ እንደፈጸመ ያለጥርጥር ማመን ግን ይቻለናል። ምክንያቱም እንደዚያ እንድናምን በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ተይዘናልና። ሆኖም የክርስቶስን ቃል ለሚጠራጠሩ ላልተማሩና ለሚስቱ ወገኖች ስንል ታሪካዊ ዘገባዎችን አንስተን እንይ፦
….ከዚያ ከበዓሉ ጥቂት ቀናት በኋላ፣’… በ21ኛው በአርጤምስየስ [ጂያር] ቀን… “አንድ አስደናቂ እና ሁሉንም ያስገረመ ክስተት ታየ። ይህ ክስተት ሲፈጸም ታሪኩን በገዛ አይናቸው ባዩት በነዚያ ሰዎች ህይወትና የእለት ተለት ኑሮ ውስጥ ምንም ተጽዕኖ ባይኖረውና፣ ከዚያም በኋላ ተከትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች የሚገባቸው አይነት ትላልቅ ተፈጥሮ ያላቸው ክስተቶች ባይሆኑ ኖሮ፣ እኔ ራሴ ታሪኩ ተረት ይመስላል ብዬ ባሰብሁና ትኩረት ሰጥቼ ሳልዘግበው በተውኩት ነበር፤ የታየውና የሆነው ግን ይሄ ነው፣ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሠረገሎችና በላያቸው ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ የታጠቁ የሰራዊት ጭፍሮች በደመናው መካከል ወዲህና ወዲያ እየተሯሯጡ ከተማይቱን ሲከብቧት ታዩአቸው። ከዚህም በላይ በዓለሃምሳ ብለን በምንጠራው በዚያ የበዓል ቀን ካህናቱ በሌሊት እንደ ልማዳቸው ወደ ውስጠኛው የቤተ መቅደሱ ክፍል ገብተው የዘወትሩን አገልግሎታቸውን እይፈጸሙ ሳለ፣ በመጀመሪያ ለራሳቸው ብቻ የሚታወቅ መሸበርና ፍርሃት ይሰማቸው እንደነበሩ ሲገልጡ፣ በታላቅ ድንጋጤም ውስጥ ሆነው እየተንቀጠቀጡ የሰሙት ታላቅ ድምፅ "ኑ ከዚህ በኋላ ይህንን ስፍራ ለቅቀን እንሂድ” የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ነበር። (Wars, 6-5-3, አንቀጽ 297-299)
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው አይሁዳዊ የታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ በራእይ 19፥ 11-14 ላይ ኢየሱስ ይመራው እንደነበረው ያለ ሠራዊት በደመና ውስጥ የተመመውን ሰማያዊ ሠራዊት በትረካው ገልጿል። ይህ ክስተት በሌሎች የታሪክ ተመራማሪዎችም ተዘግቧል። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው ሌላው አረማዊ የታሪክ ጸሐፊ ታሲተስም ይህን ክስተት ጠቅሶ "በሰማይ ውስጥ የሰራዊት ግጭትና የሚያብረቀርቅ የጦር ራእይ ታየ" ሲል ጽፏል [Tacitus The Histories 5.13.]። ፕስዩዶ ሄጌሲፐስም በዚያን ጊዜ ከኃያላን መላእክቱ ጋር የክርስቶስን በደመና ላይ መምጣቱን ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል፦"“የአይሁድ መጻሕፍት እንደ ገለጹት ብዙዎች ያዩት እጅግ ታላቅ የሆነ ምስል በሰማዩ ላይ ታየ፤ ፀሐይም ሳትጠልቅ በደመና ውስጥ ሰረገሎችና የታጠቁ የጦር ሠራዊቶች በደመናት ላይ ሆነው ሲርዋርዋጡ ታዩ፤ የይሁዳ ከተሞችንና ግዛቶቿንም ሁሉ ወረሩ።" [Pseudo-Hegesippus 44.] የመካከለኛው ዘመን አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር ሴፈር ዮሲፖንም በ66 ዓ.ም ሰማይ ላይ ስለነበረው የመላእክት ሠራዊት እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “በዚያም ወራት የእሳት ሰረገሎችና ፈረሰኞች፣ ታላቅ ሠራዊትም ሆነው በሰማዩ ላይ እየበረሩ ወደ ምድር በቀረቡ ጊዜ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ሁሉ ላሉ ሰዎች የእሳት ፈረሶችና የእሳት ፈረሰኞች ሲመጡ ታዩአቸው" [Sepher Yosippon A Mediaeval History of Ancient Israel በተሰኘውና Steven B. Bowman ከዕብራይስጥ ቋንቋ የተረጎመው ሲሆን በምዕራፍ 87 “Burning of the Temple” ከተሰኘው ክፍል ላይ የተጠቀሰ ነው] በተጨማሪም፦
http://fulfilledtheology.ning.com/forum/topics/historical-records-with-some (9/16/2014) በተሰኘው ድረ ገጽ ላይም ተጠቅሶ ይገኛል።
እንግዲህ ልብ ብለን ካየነው በእነዚህ ሦስት ዘገባዎች እና በራእይ 19 መካከል ያለው ተመሳሳይነት በእጅጉ አስደናቂ ነው። በመሆኑም፣ በዮሲፖን ዘገባ እንደሰፈረው 2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 7 ላይ ያለውና "ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ይገለጣል" የሚለው ቃል በ66 ዓ.ም ላይ በነበረው የአይሁድ ሮም ጦርነት መባቻ ላይ እንዴት ግልፅ እና ተዳሳሽ በሆነ መልኩ እንደተፈጸመ ማየት እንችላለን። ያ የመጅመርያው ክፍለ ዘመን የአይሁድ ሮም ጦርነት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ ይልቅ የከፋው ብቻ ተብሎ የሚወሰድ አይደለም። በሁለት ህዝቦች መካከል የተደረገ ግጭት ብቻም ሳይሆን፤ መለኮት ያስከተተው፣ የሰው ልጆችን ታሪክና መጻኢ እድል ሊቀይር ሰማይ ራሱ የዘመተበት፣ በአይሁድ ቅዱሳት መጻህፍት በብዙ የተነገረለት የፍጻሜው አርማጌዶን ነበር። ያ የጦርነት ታሪክ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ የሚደረግ የአዲስ ኪዳን ትንቢት ትርጓሜ ሁሉ ቤተክርስቲያንንና ትምህርቷን ወደማይረባ የተረት ዝባዝንኬ ውስጥ እየዶለ እምነቷንና ተስፋዋን የአለም መሳቂያና መሰደቢያ እያደረገ፣ ሰዎችንም ከእምነት ይልቅ ለክህደት የሚጋብዝ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም።
በሚቀጥለው ጥሁፍ ይህ ታሪካዊ ሰማያዊ ክስተት የትንቢት ፍጻሜ ሆኖ ለመወሰድ እንዴት የመለኮታዊ መገለጥን መስፈርት እንደሚያሟላ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ በማስረጃ እንመለከታለን።
ቸር ሰንብቱ
(GKR)
ፕሪቴሪዝምና ፓሮውዥያ (፬)
የዳግም ምጽአቱ ፕሪቴሪስታዊ እይታ— በቀደመው ጽሁፌ የዳሰስሁት ታሪክ ዘግቦ ያቆየልን ሰማያዊ ክስተት የትንቢት ፍጻሜ ሆኖ ለመውሰድ እንዴት የመለኮታዊ መገለጥ መስፈርትን እንደሚያሟላና፣ ያ በእስራኤል ሰማይ ላይ የታየው ትንግርት የጌታ መምጣት መሆኑን፣ እርሱም በቀደመው ኪዳን የአምላክ አመጣጥ ሁናቴ የተብራራ እንደሆነ ጨምረን እንመለከታለን፦
“የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”
ዮሲፖን በ66 ዓ.ም የሰማይ ላይ የእሳት ሠራዊት በሰማይ ላይ መታየቱን አስመልክቶ የሰጠው ታሪካዊ ዘገባ በብሉይ ኪዳን ቀደም ሲል በኢሳይያስ 66፥ 15፤ በመዝሙረ ዳዊት 68፥ 17 እና በዕንባቆም 3፥ 1-8 የተገለጠውን የጌታን መምጣት መግለጫና መስፈርት በሚገርም የቃል በቃል ንግግር የሚያሟላ ነው። ያህዌ በጥንቱ ዘመን ወደህዝቦችና መንግስታት በፍርድ እና በምርት ይመጣ የነበረበትን መንገድ በሚመስልና በሚስተካከል አኳኋን የ66ቱ ዓ.ም ክስተትም እንዲሁ ነው።
በ66 ዓ.ም በፈረሶችና በሰረገሎች እየጋለቡ በእስራኤል ሰማይ ላይ ለታዩ እሳትማ መላእክቶች ፊት አውራሪ ሆኖ ክርስቶስ መምጣቱ በ2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 7 ላይ "ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ይገለጣል"" ሲል የተተነበየውን ቃል በቃል ፍጻሜ ይሰጠዋል። ይህም በኢሳይያስ 66፥ 15 ላይ "እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ።" ሲል የተነገረውን የጌታን አመጣጥ በሚያስገርም ሁኔታና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። በመዝሙር 68፥ 17 እና ዕንባቆም 3፥ 1-8 ላይ የተገለጠው በፍርድ የሆነው የጌታ አመጣጥ ገለጻዎችም በተመሳሳይ መልኩ የሚታዩ ናቸው። የሚገርመው፣ በ66 ዓ.ም በእስራኤል ሰማይ ላይ ታይቶ የነበረው እሳትማ የመላእክት ፈረሰኞችና ሠረገላዎች በጥንታዊ የእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተለመደ በመሆኑ እንደዚህ ያለ ትዕይንት ሲዘገብ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም።
ይህ በዮሲፖን የተዘገበውና በ66 ዓ.ም በሰማይ ላይ የታየው የመላእክት የእሳት ሠራዊት መግለጫ በ2ኛ ነገሥት 6፥ 17 ላይ ከብዙ ዘመን በፊት የተገለፀውን የእሳት መላእክት ሠራዊት በትክክል ያንጸባርቃል።
በዳግም ምጽአቱ ኢየሱስን አጅበው ከእርሱ ጋር ወደ ክብሩ ለመግባት ሲጠበቁ እንደነበሩት ቅዱሳን ሁሉ በ2ኛ ነገሥት 6፥ 17 ላይ ኤልሳዕም በመላእክት ሠራዊት ይጠበቅ እንደነበር እናያለን። ይህ እሳትማ የመላእክት ሠራዊት በዮሲፖን እንደተዘገበው የፈረሰኞች፣ የፈረሶች እና የእሳት ሰረገሎች ሠራዊት ተብሎ በትክክል ተገልጿል። 2ኛ ነገ 6፥ 17 "ኤልሳዕም፦ አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።" እንግዲህ በሁለቱም ሁኔታዎች ውስጥ የመላእክት ፈረሰኞች ሠራዊት እንደ ፈረሰኞችና የእሳት ሠረገላዎች መከሰታቸውን ልብ በሉ።
በሐዋርያት ሥራ 9፥ 3-6 ሳውል በአሳዳጅነት መንገዱ ላይ ተገልጦ ያየው ኢየሱስና እና በራዕይ 1፥ 13-16 በፍጥሞ ለዮሐንስ ተገለጦ በታየው መሰረት፣ ኢየሱስ በትንሳኤው ያለው አካል ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ የበለጠ የከበረ አካል እንደሆነ፣ ይህም እንደ ነበልባል እሳት የሚያበራ መሆኑን እናያለን። ይህ ዕፁብ ድንቅ ብርሃን የሳውልን አይኖች አሳውሮ በምድር ላይ ጥሎታል፤ በተለይ ለዮሐንስ ደግሞ በደረቱ ላይ ተጠግቶ ምስጢርን ከእርሱ ይሰማ እንደነበረበት ጊዜ ሳይሆን፣ ትእይንቱ በእግሩ ስር እንደሞተ ሰው አድርጎ የሚደፋው ነበር።
"ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፥ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፥ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበረ። በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ።"
ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን የሚኖር እርሱ ሲገለጥ ብረቱንና ናሱን የሚያቀልጥ ሁሉን የሚበላ እሳት ይሆናል። ከሙታን ተነስቶ ወደክብሩ የገባው ይህ ኢየሱስ እንደ አባቱ ሁሉ የሚያስፈራ፣ በማንነቱ ("በተፈጥሮው") የሚባላና ማንም ሊቀርበው የማይችል የእቶን እሳት ነው። ስለዚህ ይህ የኢየሱስ አካል በ2ኛ ነገሥት 6፥ 17፣ በ2 ቆሮንቶስ 11፥ 14 እና በማቴዎስ 28፥ 2-3 ባለው መሠረት የሰማይ መላእክትን ዓይነት መልክ የያዘ ነበር።
በ2ኛ ነገሥት 6፥ 17 ላይ ያሉት መላእክት እና በ66 ዓ.ም በዮሲፖን ዘገባ የተገለጹት የእሳት ፍጡራን ተመሳስለው ለምን ተገለጡ? በ2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 7 ላይስ ጌታ ኢየሱስ በዳግም ምጽአቱ ወቅት የሚነድ እሳትን የመሰለ መልክ እንደሚይዝ የሚናገረው ለምንድን ነው? ምንም እንኳን የኢየሱስ የትንሳኤ አካል ከእርገቱ አስቀድሞ ገና በምድር ሳለ ከሥጋዊ አካሉ ጋር ቢመሳሰልም፣ ነገር ግን በሐዋርያት ሥራ 1 ላይ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ይህ የተለወጠ ይመስላል (የሐዋርያት ሥራ 9፥ 3-6፣ ራዕይ 1፥ 13-16)። ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ፣ በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የተገለጸው የኢየሱስ አካል በሰማይ ካለው አባቱና ስለ ሌሎች ሰማያዊ አካላት ከተሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫዎች ጋር በቅርበት ይመሳሰላል። ለምሳሌም፣ ነብዩ ሕዝቅኤል በትንቢቱ ምዕራፍ 1፥ 26-28 ባለው ክፍል የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክን በራእይ አይቶ፣ "የእግዚአብሔር ክብር እንደ እሳት ምስያ ያበራል" ብሎ ሲናገር፣ በሐዋርያት ሥራ 9፥ 3-6 እና በራዕይ 1፥ 13-16 ላይ ኢየሱስን አስመልክቶ ከተሰጡት መግለጫዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ተነግሯል፦ "በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።"
ተመልከቱ፣ ከዕርገቱ በኋላ ያለው የክርስቶስ ትንሳኤ አካል ብሩህነትና ግርማው እንደ ጸሐይ ብሩህነ የሚያበራ መሆኑ በሐዋርያት ሥራ 9፥ 3-6 ውስጥም ተጠቅሷል፤ ጌታ ካረገ በኋላ የነበረውንና ጳውሎስን ለጊዜው በእውርነት የመታውንና የጣለውን ታላቅ ብርሃን ክፍሉ ያመለክታል። ዮሲፖን በትረካው በሰማይ ላይ የታዩት እነዚያ ትንግርታዊ ፈረሶች ምን አይነት እንደነበሩ ሲገልጥ የእሳት ፈረሶች እንደነበሩ ይናገራል፤ በራእይ 19፥ 14 ላይ ግን መላእክቱ ነጭ ፈረሶችን ይጋልቡ እንደነበር ይናገራል፣ ይህ ታዲያ ተቃርኖ ነው ወይ? በጭራሽ አይቃረንም። ወደ ሞት የቀረቡና የዚያ ራእይ ልምምድ ያላቸው በርካታ ሰዎች ከነቁ በኋላ ስላለፉበት የሞት ጽልመት ሲናገሩ በሰማያዊው ግዛት ውስጥ ያሉ ፍጥረታት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያብረቀርቅ ነጭ ብርሃን እንደሚፈነጥቁ ሲገልጹ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ። ስለዚህ በዮሲፖን ትረካ የተገለጹት ፈረሶችና ፈረሰኞች በሰማይ እንዳሉት ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በሚያንጸባርቅ ነጭ ብርሃን ውስጥ ሆነው ሳይታዩ እንዳልቀረ ይመስላል ማለት ነው።
በዚያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ የዚህ ሠራዊት ፊት አውራሪና ራስ ሆኖ ተገኝቶ መሆን እንዳለበት ከታሪካዊው ዘገባ እናስተውላለን፤ ይህም ግምታችን ብቻ አይደለም። ምንም እንኳን ኢየሱስ በደመና ውስጥ ባለው በዚህ የመላእክት ሠራዊት ራስ ላይ በውል ተለይቶ ባይታወቅም፣ በዚያ ተአምራዊ ትዕይንት ውስጥ ግን ያንን ሰማያዊ ጭፍራ ድል ለመንሳት አስከትቶ በግርማው የመጣው እርሱ ራሱ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። በአገልግሎቱ ዘመን ሁሉ ሲናገር እንደነበረው ጌታ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት በነበሩት አድማጭ ተመልካቾቹ ሰዎች የህይወት ዘመን በትውልዳቸው ውስጥ የሰማይ ሰራዊትን እየመራ በደመና ላይ ሆኖ እንደሚመጣ ይተንብይ ነበርና። ኢየሱስ በዚያ ሁኔታ ተመልሶ እንደሚመጣ ተንብዮ ከነበረ፣ እኛ በትንሽዋ አእምሮአችን ታሪክንና ክስተትን አነጻጽረን ከምንደርስበት ድምዳሜ በላይ የትንቢት ቃል የጸና እውነት መሆኑን እናውቃለን። በእስራኤል ሰማይ ላይ የታየው ይህ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነ ክስተት ከሆነ፣ በእርግጥም የዮሐንስ ራእይ 19፥ 14 እና ሌሎች ስለ ዳግም ምጽአቱ የተነገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ገለጻዎችን ሁሉ አሟልቶ የሚፈጽመውም ከሆነ፣ እንግዲያውስ ኢየሱስ በደመና ላይ ባለው በዚህ ሠራዊት ራስ ላይ ፊት አውራሪው ሆኖ ተገኝቶ መሆን አለበት ማለት ነው። እሱ ባይሆን ኖሮ ግን ይህ ተአምራዊ ክስተት በጣም የአጋጣሚ ጉዳይ ብቻ ሊሆን ይችል ነበር ብለን ከትንቢት ፍጻሜ ደረጃ ማውረድ በቀለለን ነበር፤ ያንን እንዳናዱርግ ግን በትንቢቱ ቃል ተይዘኔል። ጌታ ኢየሱስ በስጋው ወራት ባገለገለው ማህበረሰብ እና በትውልዱ ውስጥ በሰማይ ደመናና በክብር ተመልሶ ለመምጣት ከሰጠው ጽኑና ተደጋጋሚ ተስፋው አንጻር ሲታይ ይህ ታሪክ ከትቦ ያስቀመጠው ተአምራዊ ክስተት የአጋጣሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም ይህ ክስተት የሰጠውን ተስፋ የሚሞላ በትክክልም የፓሮውዥያው ትንቢት ፍጻሜ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ በዚህ የሰማይ ሠራዊት መሪነቱ ተለይቶ የታወቀ ከሆነ በጥቅሉ ይህ በደመና ውስጥ የታየው የሰራዊቱ ታሪካዊ ዘገባ ትንቢት መፈጸሙን ለማስረዳትና በክርስቲያናዊ መስተጋብር ውስጥ እምነታችንን ከጥቃት ለመከላከል በእጅጉ የሚረዳ ጠንካራ ማስረጃችን ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል። ተመልከቱ፣ ክርስቲያን ያልሆኑ የታሪክ ሰዎች ስለ ክርስቲያናዊ የነገረ ፍጻሜ ጥናት ዝርዝሮች በጥልቀት ሊያውቁ የማይችሉ እንደመሆናቸው መጠን፣ እነዚያ ክርስቲያን ያልነበሩ ታሲተስ እና ጆሴፈስ የተባሉ የታሪክ ዘጋቢዎች በዘገባቸው እንዲህ ዓይነት ግልጽ መለያን ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። በአንጻሩ ግን የታሪክ ዘገባቸው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍና የማቴዎ 24 ፍካሬ ማብራሪያ እስኪመስል ድረስ ታሪክ ባይነት ባይነቱ ተቀናብሮ መገኘቱን ስናይ፣ ትንቢት ለመፈጸሙ ማስረጃ የሚሆን ውጫዊ ሰነድ እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ እንዳሰናዳልን እናስተውላለን። ይህ ውጫዊ የታሪክ ሰነድ ደግሞ በባህርይው ውስጣዊ ለሆነው ጽኑ የትንቢት ቃል ሲገዛ እንደ ማየት ለቃሉ አማኝና ለቃሉ ተማሪ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን! ታሪክ ለእግዚአብሔር ቃል ይሰግዳል። የዚህን ክስተት ታሪካዊ አስተማማኝነትና ማስረጃዎችን የበለጠ በዝርዝር ማብራሪያ ለማቅረብ የተሞከረበትን ጥናት ጊዜ ከተሰጠን ኋላ ላይ ቆየት እያልን እንመለስበታለን።
ለአሁኑ እዚህ ላይ ላብቃ፤ ቸር ሰንብቱ
(GKR)
ፕሪቴሪዝምና ፓሮውዥያ (፭)
“የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ”
እንደ ታሲተስ ታሪካዊ ዘገባ ከሆነ፣ ያኔ በአይሁድ አመጽ መጀመርያ ላይ መብረቅ በርቆ መቅደሱን መትቶት ነበር፤ ይህም
የማቴዎስ 24፥ 27 ትንቢትን ፍጻሜ በሚሰጥበት መልኩ በዳግመኛ ምጽአቱ ወቅት የሚጠበቅ ክስተት መሆኑን እናውቃለን።
ማቴዎስ 24፥ 27 እንዲህ ይላል፡- “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤"
ይህ ጥቅስ የሰው ልጅ በደመና ላይ ሲመጣ እንደ መብረቅ ሆኖ እንደሚመጣ የሚያመለክት ይመስላል። የመብረቅ መኖር ፓሮውዥያውን የሚያጅበው ክስተት መሆኑ በቃሉ እንደተገለጠ ሁሉ ከምጽአቱ ጋር ባለው ግንኙነት አብሮ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ የታሪክ ማስረጃዎች በ66 ዓ.ም የአይሁድ ዓመፅ መጀመሪያ ላይ በሮማውያን ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ ተመዝግቧል፦ "የጭፍሮች ግጭትና የሚያብረቀርቅ የጦር ትጥቅ፣ የፈረሶች ኮቴና የሰረገላ ድምጽ ራእይ ከፍ ብሎ በከተማይቱ ሰማይ ላይ ይታይ ነበር። ድንገትም ከደመናው መሃል በኃይል የሚያበራ የመብረቅ ብልጭታ፣ የገሞራ እሳትም በመቅደሱ ላይ አበራ። ብራቅም ሆነ፤ የቅዱሱ ቦታ በሮችም በድንገት ተበርግደው ተከፈቱ፣ አማልክት እንደሚለቁት ያለና ሰው ሊያወጣው ከሚችለው በላይ የሆነ ድምፅም ተሰማ፣ እናም በዚያው ቅጽበት በችኮላ ስፍራውን ለቅቀው መሄዳቸውን የሚያመለክት የመለከት ድምጽ ሆነ።" [Tacitus The Histories 5.13]
በማቴዎስ 28፥ 2-3 ላይ እንደተገለጸው ሰማያዊ አካላት እንደ ጸሐይ የሚያንጸባርቅ መልክ እንዳላቸው ተነግሯል፤ ስለዚህም በማቴዎስ 24፥ 27 ክርስቶስ መብረቅ በሚመስል ብሩህ፣ አንጸባራቂ መልክ እንደሚገለጥ ሲነገር በፓሮዥያውም እንዲሁ ይፈጸማል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ዳግመኛ ምጽአቱ ከምስራቅ ወጥቶ በስተምዕራብ ከሚታየው መብረቅ ጋር መነጻጸሩን ስናስተውል ያ የክርስቶስ መብረቃዊ ብርሃነ መለኮት ከዕርገቱ በኋላ በፓሮዥያው ላይ ያለውን ክብር የሚገልጽ መሆኑን እናያለን። ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ የታየው የጌታ መልአክም በማቴዎስ 28፥ 2-3 በተነገረው መሠረት መብረቅ በሚመስል መልክ መገለጡን አስታውሱ፡-"እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ።" በቀደመው የዚህ ጽሁፍ ክፍል እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ ከዕርገቱ በኋላ በሥጋው እንደሚታወቅ አይደለም፤ ይልቁን ግን በግርማው የማይቀረብና የሚያስፈራ ሆኖ ተመሳሳይ አንጸባራቂ መልክን ይዟል፣ እርሱም ደግሞ እንደ መብረቅ ብራቅ ይመስላል።
እንግዲህ በ66 ዓ.ም በሰማዩ ላይ ታይቶ የነበረው ያ የመላእክት ሠራዊትና የተሰማው የፈረሶች ኮቴና የሰረገላ ድምጽ ስለ ዳግመኛ ምጽዓቱ የተነገሩትንና የተገለጡትን ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በበቂ ያሟላል እያልሁ ደጋግሜ አጽንዖት የሰጠሁበትን ሃሳብ ልብ አድርጉ። ይህም ማለት ከላይ በታሪክ ጸሓፍያኑ ተዘግቦ ያየነው ያ ሰማያዊ ሰራዊት ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ በዝርዝር የተነገሩትን ሁሉንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫዎች ፍጻሜ ይሰጣቸዋል ማለት ነው። ከዚህ ቀጥሎ በምንመለከታቸው ስምንት ነጥቦች ወደ ማጠቃለያዬ አልፋለሁ። እነዚህን ነጥቦችና የጠቀስኳቸውን የቅዱሳት መጻህት ምንባባት ከተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ልትመለከቷቸው ካልወደዳችሁ ግን ኮስታራ የቃሉ ተማሪዎች ስላልሆናችሁ እዚህ ሩም ውስጥ ለናንተ የሚሆን ምንም መነባነብ አይኖርም። ነጥቦቹን እነሆ፦
በማቴዎስ 24፣ ማቴዎስ 16፥ 28፣ ማቴዎስ 10፥ 23፣ ማርቆስ 8፥ 38-9፥ 1፣ ማርቆስ 14፥ 61-62፣ ዮሐንስ 21፥ 22 እና ራእይ 1፥ 7 የተተነበየው ይህ ክስተት የተፈፀመው በራሱ ኢየሱስ ትውልድ እና ዘመን፣ በሐዋርያቱና በጥንት ቤተክርስቲያን ዘመንና ትውልድ ውስጥ መሆኑ የታመነ ነው። ይህን አለማመን የእግዚአብሔርን ቃል አለማመን ብቻ ሳይሆን ራሱን ጌታችንን ውሸተኛ ማድረግ ነው፤ ውሸተኛ ጌታ ደግሞ እውነተኛ አዳኝ ሊሆነን አይችልም። እውነተኛ አዳኝ ከሌለን ደግሞ ክርስትና የለም። ስለዚህ አስተውሉ፣ ይህ የምጽአቱ ትንቢት የመጀመርያውን ክፍለ ዘመን ከሚሽፍነው ከዚህ የጊዜ ወሰን ውጭ በሌላ በየትኛውም ሌላ መጻኢ ዘመን ውስጥ የሚፈጸም ለመሆኑም ሆነ የፍጻሜውን ጊዜ አራዝመን ወደፊት ለመጠባበቅ ምንም አይነት የቃሉ ድጋፍ የለንም። ይህም የትንቢት ፍጻሜ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ሲነገር በኖረው መሠረት እስከ ትራጃን ዘመነ መንግሥት ድረስ በህይወት እንደኖረ በሚገመተው በሐዋርያው ዮሐንስ የሕይወት ዘመን ውስጥ፣ ማለትም በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጨረሻዎቹ አስርት ዓመታት አልያም በሁለተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ማለት ነው። [Eusebius The History of the Church 3.23.]
በማቴዎስ 24፥ 30፤ ራእይ 1፥ 7 እና ማርቆስ 14፥ 62 ትንቢት መሠረት ይህ ክስተት በደመና ላይ የሚፈጸም እንደሆነ ተዘግቧል።
ይህ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነና ብዙ መላእክትን እየመራ የመጣው የሰው ልጅ የሆነው ኢየሱስን የሚመስለው ሰማያዊ ትዕይንት ታሪካዊ ዘገባ በማቴዎስ 16፥ 27፣ በማርቆስ 8፥ 38፣ በ2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 7 እና በይሁዳ 14-15 የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት ቃል መሰረት ያደረገ መሆኑን ያሳያል። የትንቢቱ ቃል እና የታሪክ ጸሐፍያኑ ዘገባ እርስ በርሳቸው የተስማሙ ናቸው።
ይህ በማቴዎስ 16፥ 27-28፣ በማቴዎስ 24፥ 27፣ በማቴዎስ 24፥ 30፣ በማርቆስ 14፥ 62፣ በራእይ 1፥ 7 እና በሐዋርያት ሥራ 1፥ 9-11 ያለውና በታሪክ ውስጥ በገሃድ ፍጻሜውን ያገኘው ክስተትና መገለጡ የታወቀው (ቢያንስ በራእይ መልክ) ነበር።
ይህ ክስተት የመብረቅ መኖርን በሚያሟላ ይዘቱ ታጅቦ በማቴዎስ ወንጌል 24፥ 27 ላይ የተጻፈውን ፍጻሜ ይሰጠዋል።
ኢየሱስ በማቴዎስ 24፥ 27 እና በ2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 7 የተነገረውን ፍጻሜ በሚስጥ መልኩ በገሞራ እሳትና የመብረቅ ብልጭታን በሚመስል ደማቅ ብርሃን በሚበርቅና በሚያንጸባርቅ ሰማያዊ ሠራዊት ላይ ሆኖ ተገለጧል።
ፓሮውዥያው የተጀመረው በራዕይ 8፥ 5 እና በራዕይ 14፥ 14 ላይ እንደተገለጸው የአይሁድ ሮም ጦርነት ሲጀመር ነው። ፓሮውዥያ የሆነው በ66 ዓ.ም ነበር ወይንስ በ70 ዓ.ም? የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን ሊያወዛግብ ይችል ይሆናል፤ ፓሮውዥያ የግሪክ ቃል ሲሆን ቀላል ትርጉሙ መገኘት ወይም መምጣት ማለት ነው። በጥቅሉ ግን ለረጅም ጊዜ ቆይታ መምጣት ማለት ደግሞ ነው። ፓሮውዥያ አጭርና፣ የአንድ ጊዜ ብቻ የክርስቶስ መገለጥ የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው፤ ይህ ግን የቃሉን መሰረታዊ አጠቃቀም ካለመረዳት የዳበረ ተለምዷዊ አመለካከት ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስለ ፓሮውዥያ ሲያስቡ፣ የክርስቶስን በደመና ላይ ለአንድ ጊዜ አጭር መገለጥ መምጣቱን ያስባሉ፣ ይህ ግን ልክ አይደለም። ፓሮውዥያ አጭርና፣ የአንድ ጊዜ ብቻ የክርስቶስ መገለጥ ከሆነ፣ እንግዲያውስ ፓሮውዥያ የተሰኘው ቃል ይህን ክስተት ለመግለፅ የሚጠቀምበት እንግዳ የሆነ፣ ወይም ትክክለኛና ተገቢ ያልሆነ፣ ወይም ክስተቱን የማይመጥን ቃል ይሆናል። ፓሮውዥያ አንድ ድል አድራጊ ጄኔራል፣ ወይም ንጉሠ ነገሥት ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣን ወደ አንዲት ከተማ መምጣቱን ለማመልከት የሚያገለግል ቃል ሲሆን፣ የመንግስቱ መቀመጫ ወደሆነችው ዋና ከተማው ከመመለሱ በፊት ለብዙ ጊዜ፣ ለብዙ ወራት ወይም ረዘም ላለ ዓመታትና ጊዜ የጉብኝት ቆይታ ማድረጉን የሚያሳይ ቃል ነው። ለምሳሌ፣ የኔሮ ቄሳር ፓሮውዥያ በግሪክ ግዛቱ ውስጥ ለብዙ አመታት ተራዝሞ ቆይቷል። ኔሮ በ66 ዓ.ም ላይ ግሪክ ደርሶ ወደ መንግስቱ መቀመጫ ወደ ታላቂቱ ሮም እስኪመለስ ድረስ ማለትም እስከ 67 ዓ.ም መጨረሻ ወይም በ68 ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ ቆይታ አድርጓል። ስለዚህ ቃሉ በመሰረታዊ ትርጉሙና ጠቀሜታው ብዙ ጊዜ ሊመጣ ያለው ተመልሶ ከመሄዱ በፊት ያለውን እና የተራዘመ መገኘቱን ወይም ቆይታውን ያሳያል። የሆነ ሆኖ፣ ፓሮውዥያ በፊልጵስዩስ 2፥ 12 ላይ ጥቅም ላይ በዋለበት መንገድ እንደሚታየው፣ ይህ ቃል ከተለመደው የብዙዎች እሳቤ በተለየ ሁኔታ በአጠቃላይ መምጣትን እና ረጅም ቆይታን ወይም መገኘትን ያመለክታል። ስለዚህ የኢየሱስ ዳግመኛ ምጽአት ወይም ፓሮውዥያም እንዲሁ ረጅም የጉብኝት ቆይታ ወይም መገኘት ያለው መምጣት እንደሆነ ይመስላል። ስለዚህም ፓሮውዥያ ከያዘው መስረታዊ ትርጉም ተነስተን በ66 ዓ.ም እንደጀመረ እና በ70 ዓ.ም እስከሆነው የእየሩሳሌም ውድቀት ድረስ እንደተራዘመ ልናምን እንችላለን።
ለ1ኛ ተሰሎንቄ 4:፥ 16 ፍጻሜ በሚሰጥ መልኩ ይህ ሰማያዊ ሠራዊት በ66 ዓ.ም በሰማዩ ላይ ታይቷል፣ በዚያው ዓመትም የሙታን ትንሣኤ መጀመሪያ በሚመስል ሁኔታ ብዙ መንፈሳዊ አካላት ከምድር ሲነሱ ታይተዋል።
[በ66 ዓ.ም የአይሁድ ዓመፅ ሲጀምርና ሠራዊቱ በደመና ውስጥ ከታዩ ጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት በኋላ፣ ብዙ መንፈሳዊ አካላት ከምድር ወጥተው እንደነበር ካሲየስ ዲዮ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “የመጀመሪያዎቹ ሠራተኞች ምድሪቱን በነኩ ጊዜ ያኔ ደም ከእርስዋ ወጣ፣ ከባድ ጩኸት እና እሪታም ተሰማ፣ ብዙ መናፍስታዊ ምስሎችም ታዩ። ኔሮ ራሱ ምንጣፉን በመያዝ ከአፈሩ የተወሰነውን እየበተነና እየነሰነሰ የተቀሩት ሁሉ እርሱን እንዲመስሉ አስገደዳቸው። ሱኢቶኒየስ ይህንን ክስተት ሲዘግብ ኔሮ መሬቱን ሲሰብር ያኔ የመለከት ድምፅ ተሰምቷል። የሙታን መናፍስት በተነሱበት ወቅት መለከት መሰማቱ ደግሞ በ1 ቆሮንቶስ 15፥ 52 ላይ ላለው ቃል ግልጽ ፍጻሜ ይሰጠዋል:- “መለከት ይነፋልና፣ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤….” በማለት ተናግሯልና። በራእይ 15፥ 8 ላይ እንደተገለጸው፣ እነዚህ የሙታን መንፈሶች ግን ሰባቱ መቅሰፍቶች እስኪፈጸሙ ድረስ ገና ህያዋን ሆነው ወደ ሰማይ አልገቡም ነበር። ይልቁን በአይሁድ ጦርነት መጀመሪያ ላይ የተነሡት እነዚህ መንፈሶች ግን ሰይጣን ሊደርስበት ወደማይችልበት ሥፍራ ለ1260 ቀናት ተወስደዋል፤ ይህም በ66 ዓ.ም በቲሽሪ ወር (መስከረም - ጥቅምት) ሮማውያን ለወረራ በመጡበት፣ የኔሮም ፓሮውዥያ በግሪክ በጀመረበትና ጀነራል ቲቶ በመጨረሻው መለከት በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት እስከጀመረበት እስከ 70 ዓ.ም ፋሲካ ድረስ ባለው ጊዜ መካከል ካለው የጊዜ ክፍተት ጋር ይዛመዳል ብዬ አምናለሁ።]
ይህንን የሱኢቶኒየስ ዘገባ ከሰማእታቱ ፊተኛ ትንሳኤ ፍጻሜ ጋር ባለው ተዛምዶ የምንመለከትበት ሌላ ጥናት እድሜ ከሰጠን በሌላ ጊዜ ይዤ እቀርባለሁ። ለአሁኑ ፕሪቴሪዝምና ፓሮውዥያን ከታሪክ መዛግብት አንጻር በመጠኑ ለማሳየት የሞከርሁበትን ጥናት በዚሁ አበቃሁ
No comments:
Post a Comment