ግርማን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት!
ትምህርት አንድ
መግቢያ
በቤተክርስቲያን የፑልፒት አገልግሎት አዘውትረው ከማይሰበኩ፣ ትምህርት ከማይሰጥባቸው፣ መጽሐፍ ከማይጻፍባቸው እና በመዝሙሮቻችን እንኳ አዘውትረን ከማንቀኛቸው በርካታ የቅዱስ ቃሉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ የማረጉ ታሪካዊ እውነታ ነው። በግሌ ይህ የሆነበትን ምክንያት ብዙ አልመረመርኩትም፤ ቢሆንም በአመዛኙ ትኩረታችንን የሚስቡ ነገሮችን ስከታተል ከእውቀት ማነስ ወይም ማጣት የተነሳ እንዲህ ላሉ እውነቶች (ለምሳሌ፣ ስለ ኃጢአት ይቅርታ የፈሰሰው የክርስቶስ ደምና መስቀሉ፣ የሰዎች ኃጢአተኝነት እና የንስሃ አስፈላጊነት፣ የእግዚአብሔር ሉአላዊነት እና ጽኑ ፍርዱ፣ የጸጋው ባለጠግነት እና ምህረቱ፣ ወዘተ) በልባችን ቦታ እንደማንሰጣቸው አስተውያለሁ። ጌታ ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ የማረጉ ታሪካዊ እውነታ በግልጽ የተብራራው በሉቃስ ወንጌል ላይ እና ሉቃስ በጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ መሆኑ ይታወቃል። በወንጌል የተዘገበልን ታሪካዊው የክርስቶስ የዕርገቱ እውነታ በተቀሩት የአዲስ ኪዳን መልዕክታት ጸሐፍያን ሥነመለኮት ውስጥ እንዴት እንደተተረጎመ እና ከመዳናችን ጋር ያለውን ቀጥተኛ ተዛምዶ ተብራርቶ እናገኘውለን።
ሉቃስ በወንጌሉ ምዕራፍ 24፥ 51 ላይ፦
"ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።"ሲለን፤ ከዚህ ባለፈ አብራርቶ ስለ ዕርገቱ የነገረን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ 1፥ 6-11 ላይ በሚገኘው ገለጻው ነው።
በዚህ የእርገት ትዕይንት ውስጥ የምናየው ዋነኛ ስዕል ከሁሉ በላይ ሆኖ ከፍ ከፍ የማለትን ስዕልነው። ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ያረገው ከምድር ወደ ሰማይ፣ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ሲሆን፣ የሚያመለክተውም ከአንድ የአኗኗር ሁናቴ ወደ ሌላው የተደረገውን ሽግግራዊ ሂደት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ኤፌሶን 4፥ 8 ላይ፦
"ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል" በማለት ሥነ መለኮታዊ ተዛምዶውን እያብራራ፣ ኢየሱስ ሲያርግ ወደ ላይ መውጣቱንና በምርኮና በስጦታ መታጀቡን ያብራራል።
ቆላስይስ 3፥ 1-2 ደግሞ
"እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።"
ሲል፤ በእግዚአብሔር ቀኝ ለመቀመጥ ወደ ላይ ያረገውን ክርስቶስን ከቦ በላይ ያለውን በታች በምድር ካለው ነገር ጋር በተቃርኖ እያነጻጸረ አማኞች አጥብቀው ሊሹትና ሊጋደሉለት የሚገባ መሆኑን ያሳያል። በዚህም ዕርገቱ በአጠቃላዩ የዋጆአዊው ሥራ ላይ ያለውን ከፍተኛ ሥነ መለኮታዊ ትርጉም እንተጽፎአልና።
"በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና"(ሮሜ 15፥ 4) እንደተባለ የዚህ ትምህርት አላማም ቅዱሳንን በቃሉ ማጽናትና ማጽናናት፣ የተጻፈውን አስረድቶ በማስተማር የተፈጸመውን ተስፋ ማስረገጥ ነው። ይህንንም በማስረዳት በከበረው የክርስቶስ ዕርገት ውስጥ ለተዋጁ ቅዱሳን ሁሉ ያለውን ታላቅ ድል እና ዘላለማዊ ዋስትና በማወቅ የሚገኘውን መጽናናት መካፈል ነው። ስለዚህ በሁለት በተከፈለው በዚህ ትምህርት በመጀመርያው ክፍል ስለ ዕርገቱ በአዲስ ኪዳን ምን እንደተዘገበ እና ዕርገቱ በዋናነት የሚያመለክታቸውን ጉዳዮች፤ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከዕርገቱ ጋር የተቆራኘውን ምርኮና ድል ነሽነቱን ጨምረን እናያለን። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የእግዚአብሔር ቃል ብዙ መጽናናትን እንደሚያደርግልን አምናለሁ።
1ኛ/ የዕርገቱ ዘገባ
አስቀድመን፣ ጌታ ኢየሱስ ከእርገቱ ቀደም ብሎ ለደቀ ምዛሙርቱ የነገራቸውን ተስፋ እና፣ እርገቱ በምን ሁናቴ እንደተፈጸመ የሚያመለክተንን ከፍ ሲል በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ የተዘገበውን የሉቃስን ምስክርነት እንይ፦
"ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ፤ ይህንንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።"(ሐዋርያት 1፥ 8-11)
ጌታ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ወደ አብ ከማረጉ አስቀድሞ በነበሩት አርባ ቀናት፣ በኢየሩሳሌም በልዩ ልዩ ስፍራ እየታየ ለተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ይገለጥ ነበር። እነርሱም እርሱ ሕያው እንደሆነ እና ከመቃብር እንደተነሳ ከእርሱ በሚሰጣቸው ማረጋግጫዎች ያውቁ ነበር። በእነዚያ አርባ ቀናት ከሐዋርያቱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ይነግራቸው ነበር።
ለምሳሌ ዮሐንስ በወንጌሉ ሲዘግብ፦
"ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት"(ዮሐንስ 20፥ 16-17)። ሲል ይጽፋል
ክርስቶስ ከመስቀል ሞቱና ከትንሣኤው በኋላ በመጀመርያ የታየው ለመግደላዊት ማርያም መሆኑን ይህ ትራኬ ይነግረናል። እርስዋም ባየችውና ባወቀችው ጊዜ ወደ እርሱ ስትንደረደር፣ እርሱ ግን ገና ወደ አባቱ ስላላረገ እንዳትነካው ይነግራታል። ይፋዊ የሆነው ዕርገቱ ከአርባ ቀናት በኋላ እንደተፈጸመ ከላይ የተጠቀሰው የሉቃስ ዘገባ ግልጽ ያደርግልናል። ግን ራሱን በገለጠላት ጊዜ ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ ወደ አባቱ የሚያርግ መሆኑን እንድትነግራቸው አስቀድማ ተልካለች።
"ዓርጋለሁ" የሚለው የኢየሱስ ማስታወቂያ የሚያመለክተው ኢየሱስ ወደ አባቱ ለማረግ በሂደትና በዝግጅት ላይ የነበረ መሆኑን ነው። ከዚያም በኋላ ራሱ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ቢታንያ ወደሚባል ስፍራ ወሰዳቸው፣ በዚያም ከእነርሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ወደ ላይ ተወስዶ ወደ አባቱ ዐረገ።
"እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።"(ሉቃስ 24፥ 50-53)
ለደቀ መዛሙርቱም ከእርገቱ በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ተስፋ ስጥቶአቸዋል። በኢየሩሳሌም ፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቹ እንደሚሆኑ ነግሮአቸዋል። ከሳምንታት በኋላም በዓለ አምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ በምድር ባሉ ምዕመናኑ ውስጥ እንዲያድር መንፈስ ቅዱሱን ልኮታል (ሐዋርያት 1፥ 8፤ 2፥ 1-4፤ 2፥ 16-17፤ ዮሐንስ 14፥ 26፤ 15፥26)። ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ በመስዋዕታዊ ሞቱ የሰራውን ቤዛነት ያጠናቀቀው ወደሰማይ ባረገ ጊዜ በሰማያት ባለችው ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ገብቶ በማስተሰረይ ነው።
የእብራውያን መልዕክት ይህንን ትዕይንት እንዴት እንደሚያቀርበው ተመልከቱ፦
"ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው፤ በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።" (እብራውያን6፥ 19-20)
"ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤" (እብራውያን 7፥ 26)
"የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።" (እብራውያን 9፥ 12)
"ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።" (እብራውያን 9፥ 24)
ሉቃስ እንደዘገበው ሐዋርያቱ እርሱ ተለይቶ ወደ ላይ ሲሄድና ሲወሰድ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። ሁኔታውን ስንመለከት ጉዳዩ ልክ በደመና ተጋርዶ እንደሚሰወር ሰው ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ኹነቶች የተከበበ ነው፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ስትቀበለው ያዩ ነበር።እርሱ ወደሄደበት ወደ ሰማይ አሻቅበው እየተመለከቱ ሳሉ ያኔ ሁለት መላዕክት ተገልጠው ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ እንዲሁ፣ ማለትም "በደመና" ተመልሶ እንደሚመጣ ነግረዋቸዋል። እርገቱ ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደኋላ ላይ እመለስበታለሁ። በዚህ የሐዋርያት ሥራ 1፥ 11 ላይ የቀረበው ዘገባና ስለጌታ ምጽዓት ባህርይ የተነገረ ቃል ግን እንዴት መተርጎም እንዳለበት የዳሰስሁበትን ጽሁፍ ጨምራችሁ ትመለከቱት ዘንድ ግብዣዬ ነውና እነሆ ሊንኩ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/02/1-9-11.html?m=1
2ኛ/ ዕርገቱ ምንን ያመለክታል?
"ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።"(ማርቆስ። 16፥ 19)
በዚህ የትምህርት ክፍል አካላዊ ከሆነው የዕርገቱ ኹነት ባልተናነሰ ከዕርገቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ዕርገቱን ከበው የሚገኙ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮችን ጨምረን ቢያንስ ጉልህ የሆኑ አራት ያህሉን ማንሳት እንችላለን፦
፩) ይህ የዕርገቱ ኩነት የሚያመለክተው ከሁሉ በፊት የአንድን ጉዳይ ወሰን እና የሽግግር ሁናቴ ነው። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው፣ ዕርገቱ በሉቃስ ወንጌል መጨረሻ ላይ ሲዘገብ ጌታ ኢየሱስ በሥጋው ወራት የነበረው ምድራዊ የኑሮ ምዕራፍ መዘጋቱን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ሲዘገብ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ ኢየሱስን የመተካቱን ጅማሬ ያመለክታል። ዕርገቱ የክርስቶስን ወደ ምድር ወርዶ በስጋ የመምጣቱን ታሪካዊ እውነት ልክ እንደ ፊደል U (ሀሌታው ሀ) ቅርጽ ወደታች የወረደውን መልሶ ወደ ላይ በማውጣት ዑደቱን ግልጽ የሆነ የመጠናቀቅና የፍጻሜ መልክ የሚሰጠው ነው (like U turn)። ኢየሱስም በሥጋ ወደ አለም የመጣበትን አላማ ሙሉ የሚያደርግ ታሪካዊ እውነት መሆኑንም ጨምረን እናስተውላለን።
በዮሐንስ 6፥ 62 ኢየሱስ ስለ ዕርገቱ ሲናገር፦
"እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?" ሲል ይጠይቃል።
ኤፌሶን 4፥ 10 ደግሞ "ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።" ሲል የዕርገቱን ከፍታ ይነግረናል።
፪) ዕርገቱ ከፍ ከፍ የማለት ዋነኛ መገለጫ ሆኖ አጠቃላይ የሆነ አወንታዊ ትርጉምን የሚያጎናጽፈው ከፍተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ መሆኑን ያመለክታል። በዚህም ውስጥ ያለው አብይ ትርጉሙ መክበር ነው። እንደ ትንሣኤው ሁሉ የኢየሱስ ዕርገትም የመለኮታዊ ማንነቱ መገለጫው ሲሆን ዋጆአዊ የቤዛነቱን ስራ ብቃትም የሚያረጋግጥ ነው።
የክርስቶስ የመክበር ኹነቶች በዝርዝር በተብራሩበት በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥ 16 "እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።" በሚለው የጥንት ቤተክርስቲያን የዝማሬ መድብል እንደተገለጸው የክርስቶስ ከፍተኛውና የመጨረሻው ኹነት "በክብር
ያረገ"የሚለው ስንኝ ነው።
ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጋር የተያያዙ ሌሎቹም አምሳያዎች አጽንዖት የሚሰጡት የመክበርን ሁናቴ ነው።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የመቀመጥን ከፍተኛውን የማዕረግና የክብር ስፍራ መውሰዱን እናስተውላለን። ለምሳሌ፣
"ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።"(ኤፌሶን 1፥ 20-22) የሚለውን ተመልከቱ።
ማርቆስ ዕርገቱን አስመልክቶ በምዕራፍ 16፥ 19 ላይ፦
"ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።"ይለናል።
ይህ የማርቆስ ትራኬ እና በኤፌሶን 1፥ 20 የታወጀው ቃል፤ በቆላስይስ 3፥ 1፤ በዕብራውያን 1 ፥ 3፤ 8፥ 1፤ 10፥ 12፤ 12፥ 2 ካለው ጋር የሚጣቀስ ነው።
ሰማዕቱ እስጢፋኖስም ሰማይ ተከፍቶለት ያየውን አስገራሚ ትዕይንት በሐዋርያት ሥራ 7፥ 55-56 ላይ ሲመሰክር፦
"መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ" ነው ያለው።
ያ ቀኝ የኃይልና የስልጣን ሁሉ የመጨረሻው ከፍታ ነው።
ከሙታን ተነስቶ ያረገው ክርስቶስ የተቀዳጀውን ከፍታ ሐዋርያው ዻውሎስ እንዴት እንደሚገልጠው ደግሞ ተመልከቱ፦
"ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤"(ኤፌሶን 1፥ 21) ይላል።
ጨምሮም በዕብራውያን መልዕክቱ፣
"እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤…..ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤" (ዕብራውያን1፥3፤ 8፥ 1) ሲል የግርማውን ቀኝ ከፍታ እና በዚያ ከፍታ ውስጥ ያገኘነውን አለኝታ ያውጅልናል።
፫) በዕርገቱ ውስጥ ከክርስቶስ መክበር ጋር ግንኙነት ያለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በክፉ ኃይላት ላይ እና በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ እርሱ የተቀዳጀው ንጉሳዊው ድል ነሺነቱ ነው።
ይህም በመዝሙር 68፥ 18 ውስጥ፦
"ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ"
የሚለው ነው።
የመዝሙሩ አውደ ምንባብ እንደሚያረጋግጠው ድል ነሺ ንጉስ በውጊያ ነጥቆ የወሰዳቸውን ምርኮኞቹን ይዞ በድል አድራጊነት ግርማ ወደተራሮች ከፍታ ላይ የመውጣቱን ስዕል በጉልህ የያዘ ነው።
ይህ መዝሙር በኤፌሶን 4፥ 8- 10 ላይ፦
"ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።" ተብሎ ሲጠቀስና የጳውሎስ ማብራርያ ሲታከልበት ቃሉ የሚዛመደው ክርስቶስ በድል አድራጊነት ግርማው ላደረገው ሥራ ነው።
ይህንን ታላቅ ድል የሚያበስርልን የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ፦
"እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል"(ራእይ 5፥ 5) በሚል ድንቅ አገላለጽ ድል ነሽነቱን ይተርከዋል።
ጌታ ኢየሱስ ሞትንና መቃብርን ድል ነስቶ በዕርገቱ አእላፋት ምርኮኞችን አስከትሎ በግርማው ወደ ላይ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደጽዮን ተራራ ወጥቶአል።
"ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል" (ዕብራውያን 12፥ 22-24)
ወደሰማይ ሲወጣ፣ ምርኮውን የበኩራት ማኅበርን፣ ሁሉንም የጻድቃንን መንፈሶች፣ ራስዋን ገነትንም አስከትሎ ወደ ሦስተኛው ሰማይ (2ቆሮንቶስ 12፥ 1-4) አርጓል። ከሰማዕታትና ምርጦች ከሆኑት መካከል ብዙዎቹ በሰማያዊው ቤተመቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ካለው የደጁ አደባባይ በመሰውያው ስር የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባበቁ እንዲከማቹ የተደረጉ አስቀድመው ወደዚያ የተወሰዱ ናቸው፤
ዮሐንስ በራእዩ፦
"አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።"(ራዕይ 6 9-11) ሲል ይነግረናል።
በሌላ መልኩ ደግሞ፣ በዚህ አለም በእኩይና ሰናይ መካከል በሚካሄደው የማያቋርጥ ግጭት ውስጥ፣ በእምነት የምናውቀው ክብርን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት የሚያረጋግጠው፦
"ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዝቶለታል"፣ "ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶታል" (ኤፌሶን 1፥ 22)፣ ተብሎ እንደተጻፈ፤ አሮጌው አይሁዳዊ የሞት ሥርዓትም ይሁን ወይም ዘምኛለሁ የሚለው የግሪኮ ሮማ አህዛባዊ አምልኮተ አማልክት፣ ማናቸውም ቢሆን ክርስቶስ ከእግሩ በታች አድርጎ ያልገዛውና የማይቆጣጠረው ቤተክርስቲያንን ሊቋቋምም ሆነ ሊቃወም የሚችል ኃይል ያኔም አሁንም ወደፊትም የሌለ መሆኑን ነው። እርስዋን ሊቋቋም የሚችል ምንም የገሃነም ሃይል የለም፣ ምክንያቱም እርስዋም ድል ከነሳው ጌታዋ ጋር አብራ ድል የነሳች ናትና።
፬) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ የምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ መሆኑን እንደሚያመለክት ሁሉ፣ ተመልሶ እንደሚመጣ ካለው ዝግጁነት ጋርም የተያያዘ ነው። ወደ ሰማይ ማረጉ እና ከሰማይ መገለጡ የተያያዙ ናቸው።
ወደ ሰማያት የወጣው ለሺህ ዘመናት ሊከርም ወይም ሳይመለስ በዚያው ሊቀር ሳይሆን ይልቁንም በዚያ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሥደትና መከራ ውስጥ ለምታልፈው ቤተክርስቲያኑ "ቶሎ" ሊመጣ ነው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደው ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ተከትለው ወደዚያው ይሄዱ ዘንድ ስፍራን ለማዘጋጀት ነውና።
"ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ"(ዮሐንስ 14፥ 2-3)።
"እሄዳለሁ"፣ "እመጣለሁ"፣ "እወስዳችኋለሁ" ብሏቸዋል።
በትንሳኤው ክብር ያረገው ክርስቶስ በክብር መገለጡ የሚጠበቅ የነበረውን ያህል የአማኞችም የክብር መገለጥ እርሱን ተከትሎ የሚሆን የድነት
ታሪክ
ሙሉ
ዑደት ነበር።
"ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ" (ቆላስይስ 3፥ 4)።
የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በመላው አዲስ ኪዳን የተገለጸው ከመሆን የማይቀርና ቶሎ የሚሆን፤ እመጣለሁ፣ እመለሳለሁ፣ ጠብቁኝ ለተባሉት ለመጀመርያዎቹ ምዕመናን የተነገረና ለእነርሱ ሊፈጸም የተቀጠረ ሆኖ ነው።
ምጽአቱም የድነትን መጠናቀቅ የሚያሳይ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ እዚህ ላይ እንመለከተዋለን፦
"ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል"(ዕብራውያን 9፥ 28)፤
ይህ ጥቅስ በዚያው ትውልድ ዘመን ይኸውም በ70 ዓ.ም እንደሚፈጸም ለሚጠበቀው ዳግመኛ ምጽአቱ (parousia) የተነገረ ማጣቀሻን የያዘ ቃል ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የክርስቶስ መመለስ "ሁለተኛ"ጊዜ ወይም ዳግመኛ እንደሚሆን የተጠቀሰበት ብቸኛ ጥቅስም ነው። Young's Literal Translation የተሰኘው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም "ያለኃጢአት መስዋዕት ለሁለተኛ ጊዜ ይታያል"ይላል። ሌሎችንም በርካታ እንግሊዝኛና አማርኛ ትርጉሞች ብናመሳክር ይህ ጥቅስ የሚያወራው ስለ ዳግመኛ መታየቱ ወይም መገሉጡ መሆኑን እናስተውላለን።
በዕብራውያን 9 ላይ የተነገሩ ሦስት አይነት የክርስቶስ መታየቶች አሉ እነርሱም:-
በመጀመርያ፣ በቁጥር 26 ላይ ራሱን ለኃጢአት መስዋእት አድርጎ ለማቅረብ በስጋ ስለመምጣቱ፣ "አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።" በሚል የተጠቀሰው ነው ፤
ቀጥሎም፣ በቁጥር 24 ላይ አሁን በእግዚአብሔር ፊት እየታየ እንደ ሊቀ ካህናት እያገለገለ ስለመሆኑ፣ "በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።" በሚል የተጠቀሰው ነው፤
በመጨረሻም ባነሳነው ጥቅስ በቁጥር 28 ላይ ለነዚህ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ለነበሩ ቅዱሳን፣ ለእነርሱ በሚሆን መጻኢ ጊዜ የሚሆነው መታየቱ፣ "ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" ተብሎ የተነገረው ነው።
ለዚህ የዕብራውያን 9 ትምህርት የጀርባ ታሪክ ትርጉም እንደሚፈልግ ምልክት ወይም
ጥላ ሆኖ ያዋቀረው በሥርየት ቀን ሊቀ ካህኑ የሚፈጽመው የአሮጌው
ኪዳን
አገልግሎት አይነት ነው። የክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ እና በዕብራውያን መልዕክት እንደተገለጸው በገዛ ደሙ ወደሰማያዊቱ መቅደስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የመግባቱ እውነታ፣ በብሉይ ኪዳን የክህነት አገልግሎት ሊቀ ካህኑ በአመት አንድ ጊዜ የማስተሰርያውን መስዋዕት ካቀረበ በኋላ ለህዝቡ ሊያስተሰርይላቸው የእንስሳውን ደም ይዞ ወደ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል እንደሚገባ አይነት ስዕል ነው። በቀደመው ኪዳን ሊቀ ካህናቱ
ሊያስተሰርይላቸው ወደ ቅድስተ ቅዱንሳ ይዞ የገባውን የእንስሳ ደም በስርየት መክደኛው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ረጭቶ፣ አገልግሎቱን በመፈጸም በሰላም እስኪወጣና በአውደ ምህረቱ ላይ ለሚጠባበቁት ሕዝብ እስኪታይ ድረስ፣ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ እያማጡ በጭንቀት ከመቆየት ሌላ እግዚአብሔር መስዋዕታቸውን እንደተቀበለና በደላቸውና መተላለፋቸው እንደተሰረየ የኪዳኑ ሕዝብ የሚያውቁበት ምንም ማረጋገጫና ዋስትና አይኖራቸውም። ሊቀ ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ሊያስተሰርይላቸው ከገባበት ከመቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ሳይወጣ ከዘገየ ወይንም ከቀረ እግዚአብሔር የሊቀ ካህኑን መስዋዕት ሳይቀበለው ቀርቶ፣ ይልቁንም ገድሎት ሊሆን ስለሚችል ሕዝቡ ኃጢአታቸው ያልተሰረየ ሆነው ይቀራሉ። በድኑንም በገመድ ጎትተው ወደ ውጪ ከማውጣት በቀር ምንም ማድረግ አይችሉም። ሊቀ ካህኑ ከገባበት መቅደስ ወደ ውጭ፣ ወደ አውደ ምህረቱ፣ ይጠባበቁት ወደነበሩ ሕዝብ አልወጣም አልታየም ማለት የስርየትና የምህረት ዋስትናና ማረራገጫ ፈጽሞ የለም ማለት ነው።
ሁሉም ያለፉቱ፣ አሁንም ያለነውና ገና ወደፊት የሚመጡቱ፣ ሁላቸውም፣ የሁለቱ ኪዳናት የእግዚአብሔር ህዝቦች፣ ክርስቶስ በስጋው ወራት በመከራው አንድ ጊዜ በፈጸመው መስዋዕዊ የቤዛነት ስራው የተዋጁ መሆናቸው እሙን ነው። ለእነዚያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምእመናን "ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል" እንደተባለ፣
መዳናቸው በመስቀሉ ደም በተፈጸመ ሥራ ያኔ "ተመርቆ"(inaugurated) ነበር። ይሁንና ግን፣ እርሱ "በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ" ተብሎ
ደግሞ እንደተጻፈ፣ እንደታመነ ሊቀ ካህናት በገዛ ደሙ ሊያስተሰርይላቸው ደግሞ ገብቷል። በሰማየ ሰማያት ካለችው የእግዚአብሔር ቅድስተ ቅዱሳን በ70 አ.ም በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው ተመልሶ እስኪወጣና እስኪታይ ድረስ ግን፣ በዚያ የሽግግር ወቅት ሆነው በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የመዳናቸውን ፍጻሜ ይጠባበቁ ለነበሩ ህዝቡ ሁሉ ያ የሚጠባበቁት ሙሉ መዳን፣ እርሱም ቤዛነታቸው ገና በሙላት ወደ "ፍጻሜ" ወይም ወደ "ሙላት" አልደረሰም፣
(consummated አልሆነም) ነበር።
በመስቀሉ ስራ እንደሚታረድ በግ ሆኖ፣ የአለምን ኃጢአት ሊያስወግድ፣ ፍርዳችንን በራሱ ላይ የተሸከመው መስዋዕታችን እርሱ፣ እንደ ሊቀ ካህናቱ ሁሉ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገብቶ ካስተሰረየላቸው በኋላ፤ ቃሉ "ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" እንደሚል ከቅድስት ወደ አውደ ምህረቱ ወጥቶ፣ ሁለተኛ ጊዜ በሚሆነው መታየቱ፣ ይኸውም በዳግመኛ ምጽዓቱ፣ መገለጡን ይጠባበቁ የነበሩትን ሊያድናቸው ይገባልና። እግዚአብሔር በአሰራሩ ከዚህ "እሄዳለሁ"፣
"እመጣለሁ"፣
"እወስዳችኋለሁ"
ከተሰኘው ሙሉ ዑደት በቀር የህዝቡን ድነት ሙሉዕ እና ፍጹም አድርጎ የሚገልጥበት ሌላ ዕድልና መንገድ አልነበረውም።
"ይጠባበቁ የነበሩት"ለሚለው ቃል ግሪኩ apekdechomai (አፔክዴኮህማይ) ይለዋል፤ ይኸውም፣ ስለ ጌታ መምጣት፣ ስለ ታላቅ መጓጓት፣ እና ጒግቶ ስለ መጠባበቅ ባህሪ የሚገልጥ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው። የክርስቶስን መምጣት በታላቅ መጓጓት ናፍቀው ይጠብቁ የነበሩት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች መሆናቸው ደግሞ የማይታበል ነው። ይህ የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰባት ጊዜ ብቻ ነው ጥቅም ላይ የዋለው፤ ጥቅም ላይ በዋለበት ቦታ ሁሉ ደግሞ ዳግም ምጽአቱን የሚያመለክት ሆኖ ቀርቧል። ለምሳሌ፦
"እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ /apekdechomai/ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤"(1ቆሮንቶስ 1፥ 7፤ በተጨማሪ ሮሜ 8፥19፣ 23፣ 25፤ ገላትያ 5፥ 5፤ ፊልጵስዩስ 3፥ 20፤ ተመልከቱ)
ጳውሎስ እዚህም ላይ የሚነግረን እነዚያ የመጀመርያው ከፍለዘመን የቆሮንቶስ ምዕመናን የጌታን ዳግመኛ መገለጥ ናፍቀው በጉጉት ይጠባበቁ የነበሩ መሆናቸውን ነው። ክርስቶስን ጓግተው ይጠብቁት የነበሩት የመጀመርያው ከፍለዘመን ክርስቲያኖች ነበሩ። ማንነታቸውን በተመለከተ "ለሚጠባበቁት፣ ይታይላቸዋል" የሚለው
ገለጻ ውስጥ ለእነርሱ የሚል ጥቆማ አለው።
"ሁለተኛ ጊዜ … ይታይላቸዋል" በሚለው
ሃረግ አሁን በድጋሚ የሚታየው እንደመጀመርያው መታየቱ ኃጢአትን በተመለከተ ድጋሚ መስዋዕትን ሊያቀርብ ሳይሆን፣ ነገር ግን ጓግተው የሚጠባበቁትን ሊያድናቸው ነው። በዳግመኛ ምጽአቱ የሚገለጠው እርሱን በመጠባበቅ ናፍቆት ውስጥ ያሉትን ለማዳን ነው። ሊያድናቸው ሲል ምን ማለቱ ነው? መዳን በግሪኩ soteria ነው። ቃሉም በተለያየ አውድ ጥቅም ላይ ሲውል ሰፋ ያለ ትርጉም አለው። እዚህ የተነገረበት አውዱ ግን ከሥርየት ቀን ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ የሚነግረንም ስለቤዛነት ነው። ፍጹምና ሙሉ የሆነው ቤዛነት የሚመጣው ደግሞ በዳግመኛ ምጽአቱ ነው።
ጌታችን ተመልሶ እንደሚመጣ ባስተማረበትና ሉቃስ በዘገበው የደብረዘይቱ ተራራ ፍካሬው እንዲህ ይላል፦
"በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ"(ሉቃስ 21፥ 27-28)።
የዚህ ጥቅስ አውድ ኢየሩሳሌም ናት፣ ይሁዳና በዚያ የሚኖሩ፣ ጨምሮም በይሁዳ የገጠር አውራጃዎች ያሉት ናቸው። ኢየሩሳሌም በሚያጠፏት ኃያላን የጦር ኃይል መከበብዋም በደመና የመምጣቱ ምልክት ነው። እንግዲህ ይህ የተባለው ጉዳይና የሚሆነው፣
የሚጀመረውም ነገር የኢየሩሳሌም ውድመት ነው። ፍጹም የሆነ ቤዛነት በሙላት የሚገለጠው ኢየሩሳሌምን ለማውደም እና አሮጌውን ኪዳን እስከወዲያኛው ለማስወገድ ጌታ በሚመለስ ጊዜ ነው። ቤዛነት ሙሉ የሆነው የክርስቶስ ጽድቅ የሚሰጥበትን ተግባር ወይም ሂደት አካቶ የያዘ ነው።
ጳውሎስ መልዕክቶቹን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ መጽደቅ ገና ተስፋ ብቻ ነበር፦
"እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና"(ገላትያ 5፥ 5)።
ጽድቅ ያኔውኑ በሙላት ወይንም ፈጽሞ የተገኘ እንጂ፣ ገና ወደፊት የማይጠበቅ ኹነት ከሆነ፣ እንግዲያውስ ጳውሎስ በንግግሩ በእምነት መጽደቅ የተስፋ ጉዳይ ነው በማለቱ ታላቅ ስህተትን እየፈጸመ ነበር ማለት ነው። ምክንያቱም ያገኛችሁትን፣ የተቀበላችሁትን፣ያላችሁንና የያዛችሁትን ነገር ተስፋ አታደርጉም።
"ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን"(ዮሐንስ 3፥ 2)።
ክርስቶስ ሲመለስ ያኔ ምዕመናን ሁሉ እርሱን የሚመስሉ ይሆናሉ። መዳን በመጀመርያው ከፍለዘመን አማኞች የህይወት ዘመን የተጠናቀቀ አልነበረም፣ ያኔ ለእነርሱ የተስፋው
ቃል
ኪዳን
ፍጻሜ
ጅምር
ወይም ተስፋቸው ነበር፤ በቅርቡም በሙላት የሚመጣላቸው እንደሆነ
የቤዛነታቸውን
ቀን በመጠባበቅ
ገና ወደፊት የሚመለከቱት (The already and not yet) ጉዳይ ነበር። ጴጥሮስም በዚሁ መስመር መዳናቸው ገና እንዳልተፈጸመ፣ እንደሚጠበቅ አይነት አገላለጽ በንግግሩ ይጠቀማል፦
"ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።"(1ጴጥሮስ 1፥ 3-5)
ያኔ ጴጥሮስ ይህንን ሲጽፍ መዳን ገና ሊገለጥ የተዘጋጀ ነበር፤ መቼ ነው የሚገለጠው? ከተባለ፣ ይህ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች መልዕክቶቻቸውን እየጻፉ የነበረበት የሽግግር ወቅት ሲያበቃ፣ የትንቢት ሁሉ ፍጻሜ በሆነው በክርስቶስ መመለስ፣ በመጨረሻው ዘመን ላይ ነው።
በመስቀል ቤዛነት የተፈጸመውን የሰው ልጆች ድነት ሙላት ሰጥቶ የሚጠቀልለውና ፍጹም የሚያደርገው በናፍቆትና በትእግስት ይጠበቅ የነበረው ዳግመኛ ምጽአቱ እንደሆነ ይህን አንድ ነገር ማስተዋል ያስፈልጋል፤ ይሁንና ግን ዳግመኛ ምጽአቱ ወደፊት ይፈጸማል እንጂ ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት እስካሁን ድረስ ገና አልሆነም በሚባልበት ጊዜ፣ ከዚህ በተቃራኒው መገለጡን እየተጠባብቁ የነበሩትን የእነዚያን የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምዕመናን ጨምሮ፣ የማንም ሰው ቢሆን፣ ደግሞም ከሺህ አመታት በኋላም በእምነታቸው የመሰልናቸው የእኛ መዳን ቢሆንም እንኳ፣ ገና ጅምር እንጂ ሙላት አላገኘም ማለታችን ይሆናል።
ይህንንም
ስንል
እስካሁን
በአሮጌው
ኪዳን
የሙሴ
ሥርአት
ስር
ለሞት
አገልግሎት
ተገዝተን
እንደምንኖር፣
ከቀንበሩም
እንዳልተፈታን
ያሳያል።
ይሄም
ከአስተምህሯችን
ፈጽሞ
መወገድ
የሚገባውና
ላለፉት
ሁሉት
ሺህ
አመታት
የእግዚአብሔርን
ቃል
በቅጡ
ሳይማሩ
ሊያስተምሩ
ይደፈሩ
ሰዎች
ታላቁ
ተፋልሶ
ነው።
የአዲሱ ኪዳን ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ግን በገዛ ደሙ ሊያስተሰርይ በሰማያት ወዳለችው መቅደስ መግባቱን እናውቃለን፤ ነገር ግን እስካሁን ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ካልታየ፣ ላለፉት ሁለት ሺህ አመታትም ሳይታይ በገባበት እዚያው ከቀረና ከዘገየ፣ ከላይ የዕብራውያንን መልዕክት ዋቢ አድርገን ባነሳነው የብሉይ ኪዳን ምሳሌ መሰረት ይህ ምን ማለት ይሆናል? ወደ አውደምህረቱ መውጣቱ፣ ተመልሶ መታየቱም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ፣ ብሎም በናፍቆትና በጉጉት፣ የሚጠበቅ ነበርና። ክርስቶስ ግን እንደ ተስፋ ቃሉ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት
በ70 አ.ም በሆነው ዳግመኛ ምጽአቱ ታይቶላቸዋል። ያኔ ኢየሩሳሌም በጭፍራ መከበቧን ሲያዩ እርሱ በሰጣቸው በዚህ ምልክት ቤዛቸው መቅረቡን አሻቅበው ይመለከታሉ። ስለዚህም ሙሉ የሆነውን የሥርየትና የድነት ዋስትናና ማረጋገጫን የሚያጎናጽፈው ቤዛነታቸው የሆነው የክርስቶስ መመለስና መታየት ብቻ ነው።
"ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል"(ሐዋ 1፥ 11) የሚለው የሉቃስ ዘገባም ከዚህ ጋር ይስማማል።
ያድናቸው ዘንድ ሲጠባበቁት የነበሩት በዘመናቸውና በትውልዳቸው እንደሚመለስ ተስፋ የተገባላቸው፣ "እናንተ ሲሄድ ያያችሁት" የተባሉት
ራሳቸው የመጀመሪያው ከፍለዘመን ክስቲያኖች ናቸው። ጥቅሱን ከአውዱ ነጥለን "በመሰለኝና በደስ አለኝ" ካላደናበርነው በስተቀር፣ ተመልሶ የሚመጣውም ለእነርሱው ነው፤ እንጂ "እናንተ"
ከተባሉት መካከል ማናችንም የለንበትም። "እናንተ"
ለተባሉት የተሰጠውን የትንቢት ተስፋ እና ለእነርሱው የሆነውን የተስፋውን ፍጻሜ አምነን ብቻ ክርስቲያኖች ሆነናል እንጂ፣ የፍጻሜውን ትሩፋት እያጣጣምን በዘላለማዊ ኃሴት በእምነት ደስ ከሚለን በቀር፣ ተስፋው በተስፋነቱ ከእኛ የ21ኛው ክፍለዘመን ሰዎች አውድ ጋር አይገጥምም።
♤♧♡♧♡♧♡♧♡♧♡♧♡♧♡♧
ትምህርት ሁለት
3ኛ/ እርገቱና ምርኮው
ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲጽፍ፦
"ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤"(1ኛጴጥሮስ 3፥ 18-19) ይላል።
የቤዛነታቸውን ቀን እየጠበቁ በሲኦል ወኅኒ የነበሩትን ሙታን እርሱ በሞቱ በፈጸመው ቤዛነት ከዚያ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባቸው ዘንድ የምስራቹን ሰበከላቸው። ይህም ማለት በመስቀል ተሰቅሎ ከሞተ እና ሥጋው በመቃብር ከተቀበረ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ወዲያውኑ ወደ ሲዖል ሀደስ ወርዶ በዚያ በአባታቸው የአብርሃም እቅፍ (ገነት) ሆነው ይጠባበቁት ለነበሩት ምርኮኞች እና ለተመረጡ ቅዱሳን የብሉይ ኪዳን ሟቾች ሰበከላቸው ማለት ነው። ከሞት እንደሚነሳ እና ከእርሱ ጋር ወደ ሰማይ ይዟቸው እንደሚሄድ አረጋገጠላቸው፣ እስከ እርገቱ ድረስ ግን አርባ ቀን መጠበቅ ነበረባቸው።
ክርስቶስ ወደ ሲኦል እንደወረደና ወደ ሰማይ እንደወጣ የጥንት ቤተክርስቲያን ማመንዋ በእግዚአብሔር ቃል የሚደገፍ እውነት ሲሆን፤ በእምነት መግልጫዎቻቸውም ስለ እግዚአብሔር ወልድ በተነገረው ሁለተኛው አንቀጽ፣ "...በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን መከራ በተቀበለ፣ በተሰቀለ፣ በሞተ፣ ፣ ወደ ሲኦል በወረደ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን በተነሳ፣ ወደ ሰማይም በወጣ፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በተቀመጠ፣ በህያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ከዚያ በሚመለስ...እናምናለን" ሲሉ እምነታቸውን ያስታውቁ እንደነበር ታሪካዊ ድርሳናት ያመለክታሉ። በዚህ ምስክርነታቸው ማለትም "በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን መከራ በተቀበለ፣ በተሰቀለ፣ በሞተ፣ በተቀበረ፣ ወደ ሲኦል በወረደ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን በተነሳ፣ ወደ ሰማይም በወጣ፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በተቀመጠ፣...እናምናለን"በሚለው የአንቀጹ ክፋይ ለእነርሱ በኃላፊ ጊዜ የሚታዩ ኹነቶች የመኖራቸውን ያህል እንዲሁም "በህያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ከዚያ በሚመለስ...እናምናለን"በሚለው የአንቀጹ ክፋይ ደግሞ አሁንም ለእነርሱ መጻኢ የነበሩ ኹነቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፤ ጌታ ግን እንደሰጣቸው የተስፋ ቃል በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በክብር የተመለሰ በመሆኑ በዚህ የታመነ ምስክርነት ውስጥ ለእነርሱ ያለው የመመለሱ መጻኢ ተስፋ ዛሬ ለእኛ በኃላፊ ጊዜ የሚታይ ከሁለት ሺህ አመታት በፊት ተፈጽሞ ያለፈ ተስፋ ሆኖ ይቆጠራል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ገና በ63 ዓ.ም ላይ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ፦
"ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው"(ኤፌሶን 4፥ 8-10) ይላል።
ከዚህ ሃሳብ ክርስቶስ "ሁሉን
ይሞላ ዘንድ"ወደ ታች (ሃደስ) ፣ በዚያ ለነበሩ ምርጦች ቅዱሳኑ፣ እርሱ ሕያው መሆኑን ምረጋገጫ ሰጥቶ እንደሰበከለቸውና፤ ከአርባ ቀናትም በኋላ በእርገቱ ወቅት ከዚያ ማርኮ ወደላይ እንዳወጣቸው፣ እርሱም ከፍ ከፍ ብሎ 'ዩም ኪፑር'(ዮም ኪፑር በአይሁድ ሃይማኖት የቀን መቁጠሪያ ውስጥ የስርየት ቀንበመባል የሚጠራ አመታዊ የበአል ቀን ነው። በአይሁድ እምነት መሠረት የዩም ኪፑር ዓላማ በእርሱ ላይ ለተፈጸሙ ኃጥአቶች በእግዚአብሔር ፊት ማስተሰረይ ነው ፡፡ይኸውም፣ ያለፈውን ዓመት ኃጢአት ለማስተሰረይ መስዋዕት የሚቀርብበት የተለየ ቀን ነው) የተሰኘውን የማስተሰርያውን ስራ ሊያጠናቅቅ በሰማያዊው ቤተመቅደስ ወዳለችው ሰማያዊት ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ከዚያ እስኪወጣ ድረስ በሰማያዊው ስፍራ በአውደ ምህረቱ ደጃፍ አከማችቶ እንደሰበሰባቸው እናስተውላለን። ምርኮኞቹ ድነታቸውን ተጠናቆ የሚፈጸምበትን የቤዛነታቸውን ቀን እርሱም የ70 ዓ.ምህረትን ዳግመኛ ምጽአት እየተጠባበቁ ነበር።
"ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል"(ዕብራውያን 9፥ 28) ይላልና።
እንግዲህ ቀዋሚ በሆነው በተዘጋጀላቸው ሥፍራ በዘላለማዊ ቤታቸው በሰማያዊት አዲሲቱ ኢየሩሳሌም እንዲሆኑ የተደረገው ያኔ ዳግመኛ ሲመጣ ነው። ያኔም አዲሱንና የማያረጀውን፣ የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን፣ የከበረውንና መንፈሳዊውን፣ ሊታይና ሊዳሰስ የማይችለውንና ሰማያዊውን አካል የተቀበሉት።
ከሁሉ በላይ ሆኖ ከላይ የመጣው እርሱ አስቀድሞ ወደ ሙታን መቃብር ወደታች ወረደ፣የወረደው እርሱ "ሁሉን ይሞላ ዘንድ"ከሰማያት ሁሉ በላይ ወጣ፤ሲወጣ ግን የወጣው ብቻውን ሳይሆን፣ ይልቁንም ለምርጦቹ በአባቱ ቤት ስፍራን ያዘጋጅላቸው ዘንድ ምርኮውን ሰብስቦ ይዞ ወጣ።
ይህንን የሚያስተምር መጽሐፍ ቅዱሳችን ለአማኞች የሕይወት ተዛምዶን ያቀርብልናል። እኛ በክርስቶስ ያመንን አማኞች በእርሱ ከማመናችን የተነሳ ብቻ "ከእርሱ ጋር ተነስተን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር ተቀምጠናል"(ኤፌሶን 2፥ 6)፤ ኃጢአታችንን በራሱ ያነጻው ክርስቶስ ወደ ሰማያት ሄዶ በእግዚአብሔር ግርማ ቀኝ ተቀምጧል። እርሱ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ደግሞ እንድንሻ ጥሪ አለን፣ (ቆላስይስ 3፥ 1)።
ነብዩ ኢሳይያስ ህማማተ ክርስቶስን ባስተማረበት ትንቢቱ ስለክርስቶስ ምርኮ ሲናገር፦
"እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።"(ኢሳይያስ 53፥ 10-12) ሲል ይመሰክራል።
ከኃያላን ጋር ምርኮን የሚከፋፈል እርሱ ድል የነሳ ብቻ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ድል ነስቶአል፣
"እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር ….. ድል ነሥቶአል" (ራእይ 5፥ 5)
ጌታ በመስቀል ነፍሱን ሲሰጥ ከሆኑ አስገራሚ ክንውኖች መካከል በወንጌላዊው ማቴዎስ ዘገባ መሰረት የመቃብር መከፈትና ከሙታን ብዙዎች መነሳታቸው ሲሆን እነርሱም ከትንሳኤው በኋላ በኢየሩሳሌም ለብዙዎች መታየታቸው ነው።
"ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ"(ማቴ 27፥ 50-53)።
አንቀላፍተው ከነበሩ ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ከመቃብር ወጥተው ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ በኢየሩሳሌም ከተማ ለብዙዎች ታይተዋል። እነዚያ የመጀመሪያው ከፍለዘመን የአይሁድ ትውልድ ከየትኛውም ሌላ የሰው ልጆች ታሪክ ይልቅ በተለየ፣ ኢየሱስ መሲሁን እንደሆነ በብዙ ማስረጃ የሚያረጋግጥ የመጀመርያ እማኝ ነበራቸው።
በክርስቶስ ዕርገት ወደ ሰማይ የተወሰዱ እነዚያ ምርኮዎቹ በአጸደ ነፍስ የነበራቸው አካል እንደምን ያለ ነው? አካላቸው ከሥጋና ከደም የተሰራ እንዳልነበረ ግልጽ ነው፣ ያም ሆኖ በሙላት ሊብራራ በማይቻልበት አኳኋን አካላዊ ቅርጽና ሁናቴ ያላቸው ደግሞ ነበሩ። ይኸውም በሙታን ትንሳኤ ሊቀበሉት ካሉት መንፈሳዊ የከበረ አካል በመለስ፣ በአይን ሊታይ፣ በእጅ ሊዳሰስና በስሜት ሊታወቅ የሚችል አንዳች አይነት አካል መሆኑ ግልጽ ነው። በምሳሌም የቀረበ ቢሆን እንኳ ይህንን ስለ አብርሃም እቅፍ እና ስለ ደሃው አልዓዛር ከተነገረው የክርስቶስ ምሳሌ መረዳት እንችላለን፦
ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ፦ አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። አብርሃም ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ(ሉቃስ 16፥ 19-31)
እነዚህ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በየነበሩበት ሥፍራና ሁኔታ፣ አልዓዛር የመጽናናት ስሜት የነበረው ሲሆን በአንጻሩ ባለጸጋው ሰው ደግሞ በሃደስ የስቃይ ስፍራ ውስጥ ሆኖ ከርቀት አልዓዛርን በአብርሃም እቅፍ አይቶታል። የነበረበትንም የስቃይ ሁናቴ በመግለጥ አልዓዛርን መጥቶ በጣቱ ምላሱ ላይ የውሃ ጠብታ እንዲያቀምሰው ጠይቋል ።
ይህ "የአብርሃም እቅፍ" የተሰኘው ይህ ሃረግ ገነትን ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ገነት በግሪኩ paradeisos ሲሆን፣ በስትሮንግስ የግሪክ ቃላት መፈለጊያ #3857 ሲተረጉመው፦ አትክልት ለሞላበት አረንጓዴ ፓርክ፣ ወይም የመናፈሻና የመዝናኛ ስፍራ የሚል ትርጉምን የሚሰጥ ምስራቃዊ ቃል ነው፣ እርሱም ኤደን ይባላል፣ ይኸውም እጅግ ደስ የሚልና ደስታ የሞላበት ስፍራ ነው፤ ሲል ያብራራዋል።
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከጎኑ ተሰቅለው ከነበሩ ወንበዴዎች ንስሃ ለገባው ለአንዱ፦
"እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ" (ሉቃስ 23፥ 43) ሲል እንደ ነገረው እናውቃለን።
ገነት የሆነው የአብርሃም እቅፍ፣ ማለት ሃደስ (ሲኦል) በተሰኘው ስፍራ የሚገኝና የሞቱ ጻድቃን መንፈሶች ትንሳኤን የሚቀበሉበትን የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባቡቁ የሚቆዩበት ቦታ ነው። በመላው መጽሐፍ ቅዱስም ይህ የአብርሃም እቅፍ የተሰኘ ሃረግ የተጠቀሰው ከላይ እንዳየነው በሉቃስ 16፥ 22-23 ባለው ክፍል አድ ጊዜ ብቻ ነው። ክርስቶስ ይህንን የተናገረውም ፈሪሳውያን ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሊሰሙት በተገኙበት ነው። ሲኦል በእብራይስጥ ሼኦል፣ በመጀመርያው ኪዳን ወቅት ከአጠቃላዮ ትንሣኤ አስቀድሞ ሙታን የሚከማቹበት ቦታ ነው። በአይሁድ እምነት በኪዳኑ የታመኑ እስራኤላውያን በሞታቸው ጊዜ "ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ" እስከ ተባለላችው ድረስ፣ ያ የሚከማቹበት ስፍራ ወይም ሲኦል የአብርሃም
እቅፍ ተብሎም ይታወቃል። ስለዚህ ሲኦል ሁልጊዜ እና የግድ የስቃይና የቅጣት ቦታ ብቻ ላይሆንም ይችላል ማለት ነው። ለምሳሌ፣ ከአባቶች መካከል እንደ ያእቆብ ያሉ ታማኝ የያሕዌ ባሪያዎችም ከሞትን በኋላ እንሄድበታለን ብለው የሚጠብቁት ስፍራ እንደሆነ እናያለን፦
"ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ፦ ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።" (ዘፍጥረት 37፥ 35)
"እርሱም አለ፦ ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።" (ዘፍጥረት 42፥ 38)
"ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። .... ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ።" (ዘፍጥረት 44፥ 29፣ 31)
በእነዚህና መሰል በርካታ የብሉይ ኪዳን ምንባባት፣ አባቶች በሞታቸው ጊዜ እንወርድበታለን የሚሉት የሙታን
ስፍራ እርሱም መቃብር
ሲኦልን የሚያመለክት እንደሆነ፣ በዚያም አንቀላፍተው ከአባቶቻቸው ጋር የሚከማቹበት የአብርሃም
እቅፍ መሆኑን እናስተውላለን።
እንግዲህ በዚህ የክርስቶስ ምሳሌ ገለጻ ውስጥ ሲኦል
የተባለውን ሃደስን፣ እርሱም ሙታን ከአጸደ ሥጋ ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚሄዱበትን ሥፍራ፣ ከአንዱ ወደ ሌላው ማንም አቋርጦ ማለፍ እንዳይችል በመካከሉ በጥልቅ ጉድጓድ፣ በገደል፣ ወይም በታላቅ መለያየት በተከፈለ ሁለት ምድብ ገጽታው ያቀርበዋል። ስፍራውም የሲኦል የእረፍት ቦታን እና የሲኦል የስቃይ ቦታን በሁለት ከፍሎ የያዘ ነው። ምሳሌው የሚያመልክተን አንዱ እውነታ ኃጢአተኞችም ሆኑ ጻድቅን ሁለቱም ወገኖች ስጋና ደም ከሆነ ተዳሳሽ አካል ተለይተው በአጸደ ነፍስ ሆነው ያሉበት ሀደስ ውስጥ ንቁ እና የሚያውቁ (self conscious) መሆናቸውን ነው። በተጨማሪም ለነዚያ በስቃይ ሃደስ ውስጥ ላሉ ሙታን ሁለተኛ የይግባኝ እድልም ሆነ ወይም አጠቃላይ (universal) እርቅ የሌለ መሆኑን ይህ ምሳሌ ያረጋግጥልናል።
ክርስቶስ ሲናገር አልዓዛር የሚባል አንድ ደሃ ለማኝ ሰው በሞተ ጊዜ መላእክት ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት ይለናል። አንድ ባለጠጋ ሰው ደግሞ ሲሞት ተቀበረና በስቃይ ስፍራ ሆነ ይለናል። ይህንን የስቃይ ስፍራ በግሪኩ bsanos ይለዋል፣ ስትሮንግስ የተሰኘው የግሪክ ቃላት መፈለጊያ #931 ሲተረጉመው፣ እጅግ የከፋ ስቃይን የቀላቀለ በቀል ባለበት ሁኔታ፣ በምስያው ጥቋቁር ድንጋዮች እየተሰቃዩ እንደሚፈተኑባቸው፣ ብረቶችም እንደሚቀልጡባቸው ያለ ጥልቀት ውስጥ መውረድ ይለዋል። ይህ እንግዲህ አማኝ ያልነበሩ የአሮጌው ኪዳን ኃጢአተኞች፣ ከሞቱ በኋላ በ70 ዓ.ም የሚሆነውን ይግባኝ የሌለውን የመጨረሻ ፍርድ እየተጠባበቁ የሚቆዩበት በሃደስ ውስጥ የተዘጋጀላቸው የስቃይ ስፍራ ያለበት ምድብ ነው። ያ ሟች ባለጠጋ ሰው ከሲዖል የስቃይ ስፍራ ሆኖ አሻቅቦ ሲያይ አብርሃምንና አልዓዛርን ተመለከተ።
ባለጠጋው ሰው በእሳት ነበልባል እየተሰቃየ ስለነበር፣ ለአብርሃም ያቀረበው ጥያቄ አልዓዛር በጣቱ ጥቂት ውሃ ይዞ ምላሱን እንዲያረጥብለት ነበር። አብርሃም ግን ለባለጠጋው ሲመልስለት ይህ አይቻልም! ምክንያቱም አንተ በምድር ሳለህ እጅግ ተመችቶህ መልካሙን እየተቀበልህ በመጽናናት ስትኖር አልዓዛር ደግሞ በከፋ ስቃይ ውስጥ መከራን እየተቀበለ ነበር። አሁን ግን ሁለቱም ከሞቱ በኋላ በአጸደ ነፍስ ሆነው አልዓዛር መጽናናትን ባለጠጋው ደግሞ ስቃይን እየተቀበሉ መሆናቸውን ያመለክታል። ጨምሮም አብርሃም ሲናገር መጽናናት ባለበት የሃደስ ምድብ (ይኸውም የአብርሃም እቅፍ ነው) እና ስቃይ ባለበት የሃደስ ምድብ መካከል ማንም ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው ማለፍ እንዳይችል በመካከል የሚከፍል፣ ጥልቅ የሆነ ታላቅ ገደል ተደርጎአል የሚል ነው። ይህ የአብርሃም እቅፍ የተባለ ስፍራ ገነትም ይሁን ወይም ሲኦል፣ በምንም ስም ቢጠራ ከክርስቶስ ትንሳአኤና ከእርገቱ በፊት በነበረው አሮጌ ኪዳን ውስጥ ለኖሩ ቅዱሳን ግን ሰማይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
በዚህ የክርስቶስ ምሳሌ እንደምንመለከተው አብርሃም ጨምሮ የሚናገረውን አስተውሉ፣ እነዚያ በሲኦል የስቃይ ስፍራ ያሉ ነፍሳት ገና በህይወት እያሉ ሙሴና ነብያት ስለ መሲሁ የሚሉትን ሊሰሙ ያልፈለጉ ናቸው፤ ስለዚህም ከሙታን አንድ ቢነሳላቸው እንኳ የሚሰሙም የሚያምኑም አይሆኑም። ይህ ባለጠጋ ሰው ሙሴና ነብያት ስለመሲሁ የተናገሩትን ከማመን ልባቸውንና አንገታቸውን ያደነደኑትን የእስራኤልን ቤት ይወክላል። አልዓዛር ደግሞ በህጉና በነብያት የተነገረውን አምኖ የሚጠባበቅን ጻድቅ እስራኤላዊ ይወክላል። እንደ ወንጌላት ምስክርነት፣ ክርስቶስ ከመስቀሉ ሞት በኋላ ከመቃብር ተነስቷል፣ ብዙዎች ሟች የሆኑ ቅዱሳንንም በኢየሩሳሌም እንዲመሰክሩ ከሃደስ አውጥቶአል (ማቴዎስ 27፥ 52-53፤ ሉቃስ 23፥ 27-31)። ምንም እንኳ ከትንሳኤው በኋላ ሕያው ሆኖ ክርስቶስ ለብዙዎች ቢታይም፣ ከሙታን የተነሱትን ቅዱሳን ምስክርነት ለመስማትም ቢታደሉ፣ ከዚህም በላይ የትንሳኤው የአይን ምስክር በሆኑ ሐዋርያት ለ40 ዓመታት ቢሰበኩም፣ የሚበዙት አይሁድ ግን እንደ ሟቹ ባለጠጋና በአባቱ ቤት እንዳሉ የማያምኑ አምስት ወንድሞቹ ለእምነት ሳይታዘዙ ቀርተው ሁሉም በ70 ዓም በሚያጠፋው ጠፉ። ይህንን የአልዓዛርንና የባለጠጋውን ሰው ምሳሌ ኢየሱስ ለአይሁድ የተናገረው ገና በስጋው ወራት እያለ መሆኑንም ልብ አድርጉ። የአብርሃምን እቅፍ ወደሚናገረው ሃስብ እንመለስ
ይህ የአብርሃም እቅፍ የተባለው ስፍራ ማለትም ገነት ራሱ ክርስቶስ ሞትንና ሲኦልን ድል ነስቶ በትንሳኤው ግርማ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ሃደስ ከሚባለው ስፍራ ተለይቶ ወደ ሶስተኛው ሰማይ እንደ ተወሰደ ማመን እንችላለን። ይህም የሆነው ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ ከ40 ቀን በኋላ ነው ( ሐዋ 1፥ 3፣ 9)። ይህም የሆነው፦
ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። (ኤፌ 4፥ 8-10) ሲል ጳውሎስ እንደሚጽፈው ክርስቶስ በዕርገቱ ምርኮኞችን በማረከ ጊዜ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ጨምሮም ስለ ገዛ ራሱ መንፈሳዊ ልምምድ ሲናገር፣ እርሱ ራሱ ደግሞ ገነት ወዳለበት ወደ ሦስተኛው ሰማይ ተወስዶ ቃላት ሊገልጡት የማይችሉትን ድምጽ እንደሰማ ያኔ ገና በ57 ዓ.ም ላይ፦
ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። (2ቆሮ 12፥ 2-4) ሲል ይጽፋል።
ጳውሎስ ይህንን በሚጽፍበት ጊዜ ይህ ገነት የተባለው ስፍራ የመገኛው ቦታ በሦስተኛው
ሰማይ እንደሆነ እናስተውላለን።
እነዚያ ሟች የነበሩ ያንቀላፉት የአሮጌው ኪዳን ምርጦች እና ከዳግመኛ ምጽአቱ በፊት የሞቱ ቅዱሳን፣ በአንድነት ከሙታን እስኪነሱ እና ክርስቶስ በ70 ዓ.ም በዳግመኛ ምጽአቱ ከዚያ እስኪፈታቸው ድረስ በዚያ ምርኮኛ ሆነው የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባበቁ ነበር።
አሁን ግን
ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ (ዮሐንስ 11፥ 25-26) ተብሎ እንደተጻፈ፤
በአሮጌው ኪዳን ስር ሳሉ አስቀድመው ሞተው በዳግመኛ ምጽአቱ ትንሳኤን የተቀበሉ አባቶች፣ ትንሳኤ ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ በዚያ በሃደስ እንደሌሉ ሁሉ፤ በክርስቶስ ሆነን በብጽእና የምንሞት ሁላችን ደግሞ ህይወት ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ ወደ ጌታ ሃልዎት ሄደን "ሁልጊዜ ከጌታ
ጋር እንሆናለን"
እንጂ ስንሞት ወደዚያ ወደ ሀደስ ሄደን ከአሁን በፊት የሆነውን የትንሳኤን ቀን መጠባበቅ አያስፈልገንም።
ጌታ ኢየሱስ ለማርታ ይህንን ከተናገረ በኋላ የጠየቃት ቀላል ጥያቄ ይህንን ታምኛለሽን? የሚል ነበር፤
ዛሬም የሚያስፈልገው ቀላሉ ነገር የክርስቶስን ቃል ማመን ብቻ ነው።
ይህንን ደግሞ ስሙ፦
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። (1ተሰሎንቄ 4፥ 13-17)።
ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም! የተባለለት ጌታ፣ እነሆ በቶሎ ብዬ እመጣለሁ ባለው
ቃሉ መሰረት፣ ቃሉን ጠብቆ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ወርዷል፤ ትንሳኤም ንጥቀትም ሆኖአል። እግረ መንገዴን ልንገራችሁ ብዬ ነው፣ ይህ መፈጸሙን አለማመን ብዙ የፎረሸ ትምህርት ውስጥ ያስገባል። አሁን ስለ ገነት የጀመርነውን እንቋጭ...
ገነት የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አካል ለመሆን ወይም ራስዋን ከተማይቱን ለመሆን በክርስቶስ ትንሣኤ እና በእርገቱ ከፍ ከፍ ካለችበት ከሦስተኛው ሰማይ በላይ፣ ከሰማያትም
ሁሉ በላይ
በዳግመኛ ምጽአቱ ከፍ እንዳለችም ጭምር ማየት እንችላለን። ይህም ሰማይ የእግዚአብሔርና የልጁ ሰማይ፣ ድል ነሺው ንጉሰ ነገስት ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ለዘላለም የሚገዛበት፣ ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ሆና የተመሰረተችበት መንፈስዊው ሰማይ ነው። ይህም የሆነው ክርስቶስ በ70 ዓ.ም ዳግመኛ ሲመጣ በፓሮዥያው ነው።
ዮሐንስ በራእዩ ሲጽፍ፦
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ (ራእይ 2፥ 7)፣ ሲል ክርስቶስ ማወጁን ይነግረናል።
እንግዲህ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ሞት፣ መቃብርና ሲኦል የተሰኙ ኃያላን ድል ተነስተው በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ሙታናቸውን እስከ ወዲያኛው የተነጠቁት ክርስቶስ በነፍሱ ድካም። "ወደ
ምድር ታችኛ
ክፍል" ወርዶ በከፈለው ዋጋ ነው። ዮሐንስም በራእዩ ያየውን ሲመሰክር፦
"ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ"(ራእይ20 11-15) ይላል።
ይህ የሕይወት መጽሐፍ ምን እንደሆነ፣ በውስጡ የተጻፉትንና የሚድኑትን፣ ከመቃብር የሚነሱትንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚገቡትን በተመለከተ ነብዩ ዳንኤል በትንቢቱ ሲናገር፦
"በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።"(ዳንኤል 12፥ 1-2) ይላል።
ይህ እንግዲህ የጻድቃንና የኃጢአተኞች ትንሳኤ ነው። "ያንቀላፉቱ ይነቃሉ"፣ የሚነቁት ወዴት ነው? ቃሉ እዚህ ላይ ወደ ምድር ይነቃሉ አይልም፤ ይልቁንም የሚነቁት "ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እና ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና "፤ ነው። ይህ ደግሞ በኢ-ቁሳዊውና በመንፈሳዊው አለም ውስጥ ያለ ኹነት እንጂ በተዳሳሹ ቁሳዊ አለም ሊታሰብ የሚችል አይደለም። ስለዚህ የሙታን ትንሳኤ በመንፋሳዊው አለም እንጂ በቁሳዊው ተዳሳሽ አለም የሚታሰብ አይደለም። እንደገናም ይህ በመጨረሻው ዘመን ላይ ወይም በ70 አ.ም ላይ በሚጠናቀቀው የእስራኤል የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ በሚሆነው የታላቁ መከራ ጊዜ ውስጥ የሚታይ የቁጥር 1 አውደ ምንባብ እንደሆነ አስታውሱ፤
"ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" ዳንኤል 12፥ 1።
ይህ ትንሳኤ የሚከናወነው ከኢየሩሳሌም የውድመት ጊዜ በኋላ ነው እንጂ፣ በርካታ ምእመናን እንደሚያስቡትና እንደሚመስላቸው በመጨረሻው የጊዜ ማብቂያ ወይም የሰው ልጆች ታሪክ ማብቂያ ላይ አይደለም። በትንቢት የተነገረው የኢየሩሳሌም ጥፋትና ውድመት በ70 አ.ም እንዳለፈው ሁሉ ጌታ በነብያቱና በሐዋርያቱ አፍ አስቀድሞ የተናገረለትና ተስፋ የሰጠው የሙታን ትንሳኤና ፍርድም በዚያው አውድ ያለፈ መሆኑ አያጠራጥርም።
ይህንን የትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 12 ዋቢ አድርጌ ለሙታን ትንሳኤ የተቀጠረው ጊዜ መቼ እንደሆነ ያስተማርሁበትን ጽሁፍ ለማንበብ ከወደዳችሁ እነሆ ሊንኩ፦
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/01/12.html?m=0
(gkr)
No comments:
Post a Comment