የሚበልጠው ትንሣኤ
ሐዋርያው ጳውሎስ በእብራውያን መልዕክቱ "ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤" (እብራውያን 11፥ 35) ሲል የብሉይ ኪዳን አማኞችን ጠቅሶ ስለ ትንሣኤ ልምምዳቸው እና ዋጋ ስለከፈሉለት የሚልበጠው ተስፋቸው ይነግረናል።
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች በዘመናቸው የአካላዊው ትንሳኤ ምስክሮች መሆናቸውን ያመለክተናል። ይህም እውነት ነው፣ ምንም ጥርጥር የለውም። "ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤" ማለት ምን ማለት ነው? በብሉይ ኪዳን ቢያንስ ሁለት ሴቶች አሉ ሙታኖቻቸውን እንደገና በትንሳኤ የተቀበሉ፣ ማለትም የሞቱባቸው ሰዎች ከሞት የተነሱላቸው ማለት ነው። ሆኖም እነዚያ ሙታን ከተነሱ በኋላ ጥቂት ዘመን ኖረው እንደገና መሞታቸውም አይጠረጠርም። ለምሳሌ፣ ኤልያስ ልጅ የሞተባትን የሰራፕታዋን ባልቴት ልጅዋን ከሞት አስነስቶላታል (1ነገስት 17፥ 17-24)። ኤልሳዕም ልጅ የሞተባትን የሱናማዊቱን ሴት ልጅዋን ከሞት አስነስቶላታል (2ነገስት 4፥ 18-37)። የነብያቱ እምነትና አገልግሎት እነዚህን ልጆች ከሞት መልሶአቸዋል። በአዲስ ኪዳንም ኢየሱስ ማርታ እና ማርያም ለተሰኙ እህትማማቾች ወንድማቸውን አልአዛርን (ዮሐንስ 11፥ 43-44)፣ ከናይን ከተማ ለነበረችው መበለት ደግሞ አንድ ልጅዋን (ሉቃስ 7፥ 13-15)፣ ከሞት አስነስቶላቸዋል። ይህም "የሚበልጠው" ከተሰኘው የትንሣኤ አይነት በተፈጥሮው የሚለይና በይዘቱ "የማይበልጠው" ልንለው የምንችለው ነው።
አንድ ነገር ከሌላ ነገር ጋር በትክክለኛ መመዘኛ ተወዳድሮ፣ ተመዝኖና ተለክቶ የትኛው ከየትኛው በተሻለ የበለጠ ወይም የላቀ እንደሆነ፣ የትኛው ደግሞ ያነሰ እንደሆነ ይወሰናል። ጳውሎስም ለእብራውያን ክርስቲያኖች "የሚበልጠውን ትንሣኤ" ብሎ በሚጽፍበት ጊዜ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ፣ ይህ ትንሳኤ ከየትኛው ትንሳኤ የሚበልጥ ነው? የሚል ነው። መልሱም እነዚህ ሴቶች ከተለማመዱትና በነብያቱና ኋላም በክርስቶስ አገልግሎት በልጆቻቸውና በሚወድዱአቸው ላይ ሲፈጸም ካዩት አካላዊ ወይም ባዮሎጂካል ከሆነውና ጊዜአዊ ከሆነው የትንሳኤ አይነት የተለየው ትንሣኤ ነው። ታዲያ ከዚህ አይነቱ የሚበልጠው ትንሳኤ የትኛው ትንሳኤ ነው? በግልጽ ቋንቋ ለመናገር እንዲህ ካለው ትንሳኤ የሚበልጠው ትንሳኤ የአካላዊውና የተዳሳሹ ትንሳኤ ተቃራኒ የሆነው መንፈሳዊና ዘላለማዊ የሆነው ትንሳኤ ነው፤ ይኸውም "ሌሎች" ተብለው የተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሊቀበሉት ተስፋ ያደረጉት የትንሣኤ አይነት ነው። እነርሱም እስከሞት ድረስ በመደብደብ ዋጋ የከፈሉለትን የሚበልጠውን ትንሣኤ ለማግኘት ተጋድለዋል። ይህ ትንሣኤ በአይነቱ ሰው ከሲኦል ሀደስ ወጥቶ ከፈጣሪው ጋር በሰማያዊው አገር ዘላለማዊ በሆነው እርቅና ህብረት በእርሱ ሀውልት ፊት የሚደሰትበት የእግዚአብሔር ሕይወት ነው፣ እንጂ እንደገና ለመሞት ከሞት ወይም ከመቃብር ጉድጓድ ወጥቶ መምጣት አይደለም። ስለእነርሱም "..... ሌሎች ደግሞ መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ ተስፋ አድርገዋል" ሲል ይነግረናል፤ ተስፋቸውንም "የመዳን ትንሣኤ" ብለን ብንጠራው ተገቢ ነው።
ይህ ጥቅስ የሚነግረን አንድ እውነት፣ እነዚያ በዚህ ተስፋ የኖሩና የሞቱ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን የሚቀበሉት "መዳን" እና የሚያገኙት "ትንሣኤ" የማይነጣጠል ነገር መሆኑን ነው። በዚህም የምናስተውለው እነዚያ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ተስፋ ያደረጉትን ነገር ሳያገኙ በፊት ማለትም ገና መዳንን ሳይቀበሉ እንኳ ያኔ በሆነ አይነት የትንሳኤ ተስፋ ወደፊት እንድናለን ብለው ያምኑ እንደ ነበር ነው፤ ይሄ በትንሣኤ የሚገኝ የወደፊቱ መዳናቸው ደግሞ በተፈጥሮው ሴቶቹ ከተለማመዱት የሚበልጥና የሚሻል ትንሣኤን እንጂ ተፈጥሮው የግድ አካላዊ (ጊዜአዊ) መሆን አያስፈልገውም። ለምሳሌ፦ ማርታ እንደዚያ ታምን ነበር፤ ኢየሱስ "ወንድምሽ ይነሳል" ባላት ጊዜ "በመጨረሻው ቀን በትንሳኤ እንዲነሳ አውቃለሁ" ( ዮሐ 11፥ 23-24) ከሚለው መልስዋ የምንረዳው በአይሁድ ዘንድ ይታመን ስለነበረው የትንሳኤ አይነት ነው። ይህም የመጨረሻው ቀን ትንሣኤ በዳንኤል 12 የተተነበየውና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ተስፋ ያደረጉት መዳናቸው ነው።
ይህንን "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" የተሰኘ ቁልፍ ቃል በመላው የእብራውያን መልእክት ውስጥ ያለውን ቦታ ልብ ብላችሁ ካያችሁት፤ ለአዲስ ኪዳን በረከቶችና ትሩፋት ሁሉ መግለጫ የሆነ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተገለጡና ጉድለት ካለባቸው የህጉና የስጋ ከሆኑ ነገሮች ሁሉ በላይ የአዲሱን ኪዳን ስጦታ ከፍ አድርጎ የሚለይ ቃል ነው። "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" በተሰኘ ደረጃ በእብራውያን መልእክት ውስጥ የተገለጡ ጉዳዮች ማለትም የአዲሱ ኪዳን ስጦታዎች በሙሉ ደግሞ በክርስቶስ የተገኙና የተያዙ ነገሮች እንጂ ገና እስካሁን ያልተፈጸሙ በብዙ ዘመን ርቀት የሚጠበቁ መጻኢ ተስፋዎች አልነበሩም፤ ለምሳሌ፣ የሚበልጥ ሊቀካህን፣ የሚበልጥ ኪዳን፣ የሚበልጥ መስዋእት፣ የሚሻል አገልግሎት ወዘተ። "የሚበልጥ ትንሳኤ" ኢየሱስ የእኛ ብልጫ! ለማርታ እንዲህ ሲል የሚበልጠውን ትንሳኤ አረጋግጦላታል፤ "ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም"። የሚበልጠው ትንሳኤ ሕይወት የሆነው ክርስቶስ ነው። የሚበልጠው ትንሳኤ ሞቶ ሕያው መሆን ነው። የሚበልጠው ትንሳኤ ለዘላለም አለመሞት ነው። የሌለውንና የማይኖረውን "የሥጋ ትንሣኤ" አለ የምትሉ ይህንን አጥርታችሁ ተመልከቱ፣ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ የለም እንጂ፣ እንደፍላጎታችሁ ቢኖር እንኳ መጽሐፉ በማይሻር ሥልጣኑ የማይበልጠው አድርጎታል።
ሰላማችሁ ይብዛ!
ቄስ ግዛቸው
ጽሁፎቼን ማንበብ ለምትሹ የብሎገሬን መጠቆሚያ እነሆ
http://gizachewkr.blogspot.com/2017/11/1-2.html?m=1
No comments:
Post a Comment