"ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል!"
የሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ስህተት
ትንቢት ተፈጽሟል፣ ጌታ ኢየሱስም እንደ ተስፋ ቃሉ ዳግመኛ ተመልሷል፣ ፍርድም ትንሳኤም አልፏል ብለን የተፈጸመውን ወንጌል በምንሰብክና በምናስተምር ወንጌላውያን በሆንን በኃላፋውያን ላይ ከመጻኢያን ጎራ ያሉ አንዳንድ ወንድሞቻችን የሚሰነንዘሩት ትችትና ነቀፋ መኖሩ ግልጽ ነውን እነርሱም በሄሜኔዎስና በፊልጦስ ስህተት እኛን የሚከሱበትና ስማችንን የሚያጠለሹበትን ነቀፋ ይጠቀማሉ። በ2ኛ ጢሞቴዎስ መልዕክቱ ጳውሎስ "ትንሳኤ ከአሁን ቀደም ሆንዋል" የሚሉትን ሄሜኔዎስንና ፊልጦስን ተሳስተዋል ሲል ይመሰክርባቸዋል። ጥቅሱን እንመልከት፦
"ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም፦ ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ።" (2ጢሞቴዎስ 2፥ 17-18)
ጊዜ ወስደን ካሰብንበት ከሄሜኔዎስና ከፊልጦስ ትምህርት የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ ምን ያምኑ እንደነበር ጠቃሚ ነገሮችን ማየት እንችላለን። በእርግጥም ይህ ጥቅስ ኃላፋውያን ስለ ትንሣኤ ያለንን ምልከታ በእጅጉ የሚደግፍ እንደሆነም እናስተውላለን። እንዴት? በጥንት ቤተክርስቲያን ውስጥ በተለመደውና ተይዞ በቆየው እምነትና አመለካከት መሰረት፣ ትንሣኤ የሚከናወነው በዚህ ነባራዊ አጽናፈ አለም ሰማይና ምድር መጨረሻ ላይ ከሆነ፣ ታዲያ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ በትምህርታቸው የአንዳንዶችን እምነት እስኪገለብጡ ድረስ በማንስ ላይ ቢሆን እንዴት ያለ ተጽዕኖ ማሳደር ይቻላቸዋል? ወይንም ደግሞ የጥንት ክርስቲያኖች ልክ በዚህ ዘመን ብዙዎች እንደሚያምኑትና እንደሚያስተምሩት አይነት፣ ትንሳኤ በተፈጥሮው፣ ተዳሳሽ የሆኑ ስጋዊ አካላትን ከመቃብር አውጥቶ ማምጣትንም ያካትታል ብለው የሚያምኑ ከሆነ፣ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ትንሳኤ ካሁን ቀደም ሆንዋል ብለው በማስተማራቸው አንድንም ሰው እንኳን ማሳመን ባልሆነላቸው ነበር። ምክንያቱም የሄሜኔዎስንና የፊሊጦስን ትምህርት የሰሙ ሰዎች የተባለው እውነት መሆኑን ዳስሶ ለማረጋገጥና መናፍቃንን ለማውገዝ ብዙ ምርምር ሳያስፈልጋቸው የዘመዶቻቸውንና የወዳጆቻቸውን መቃብር ሄዶ ማየት፣ ወይም ቀደም ብለው የሞቱ ሰዎች ተነስተው በዙሪያቸው ሲመላለሱ ማየት ብቻ ይበቃቸው ነበር። እኛ ከለመድነውና ሲነገረን ከኖረው የትንሣኤ አይነት የተለየውን ትንሣኤ ካላመኑ በቀር፣ የጥንት ክርስቲያኖች የሥጋ ትንሣኤን እያመኑ እንዴት በሄሜኔዎስና ፊልጦስ ትምህርት ሊወሰዱ ይችላሉ? ከዚህ በተቃራኒው ግን ጳውሎስም ሆነ መላው የጥንት ክርስቲያኖች ትንሣኤ በተፈጥሮው መንፈሳዊ እንደሆነና የትኛውንም ተዳሳሽ ማስረጃ ማረጋገጫ አድርጎ የማያቀርብ መሆኑን የሚያምኑ መሆን አለባቸው።
ጳውሎስ የሄሜኔዎስንና የፊሊጦስን ትምህርት ሲነቅፍ እና ሲያርም፣ እነዚህ ሰዎች የትንሣኤን ተፈጥሮ በተመለከተ ስለተሳሳቱት ነገር አንስቶ የተናገረው ምንም ነገር አልነበረም። ጳውሎስ ያልተስማማውና የተቃወመው ነገር ስለትንሳኤ ጊዜውን አስመልክቶ "ከአሁን በፊት ሆኖአል" ሲሉ የሚያራምዱትን ትምህርት ነው። ጊዜውን አስመልክቶ ግን ጳውሎስ ያስተማረው ብዙም ሳይቆይ በቅርቡ የሚሆን መሆኑን ነው፦ "እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው (about to be) ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ" (ሐዋርያት 24፥ 15)። ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ገና የነገር ሁሉ ፍጻሜ ሳይሆን "ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆንዋል" በማለት የአንዳንዶችን እምነት እስኪገለብጡ ድረስ ከሳቱበትና ካሳቱበት ትምህርታቸው ይልቅ፣ "ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ አላቸው" የሚለው የያኔው የጳውሎስ ተስፋ የብዙዎችን እምነት ያጸና ነበር።
እነዚያ "ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል" እያሉ ሲያስተምሩ በኑፋቄአቸው የአንዳንዶቹን እምነት የገለበጡበት ምክንያት፣ ገና ያ ምድራዊውና አሮጌው ቤተ መቅደስ አሮጌውን ኪዳን እያገለገለ በኢየሩሳሌም ቆሞ ሳለ ከጊዜው በፊት መንፈሳዊው መንግሥት በፍፁምነት ተገልጧል ብሎ የሚናገር በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ሕግንና ጸጋን ማደባለቅ ይሆናል። ይህም የሕጉን ሥራ የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል በማድረግ የአንዳንዶቹን እምነት ይገለብጣል። አሁን ግን ጳውሎስ ተስፋ ሲያደርገው የነበረው ሁሉ ያኔ በትውልዱ የተፈጸመና ያለፈ በመሆኑ እኛ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ በሙላት ያለን የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች "ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኗል" በለን ልንመሰክርና የብዙዎችን እምነት ልናጸና፣ በተፈጸመውም ወንጌል ልናጽናና በእግዚአብሔር ቃል ድፍረት አለን። ጉዳዩን ግን በወጉ ሳያስቡበት በሄሜኔዎስና በፊሊጦስ ኑፋቄ ሊከሱን ለሚወዱ ወንድሞቻችን ግን አዲስ ኪዳንን እና መንፈሱን መማር ሀ ብለው እንዲጀምሩ በትህትና እንመክራለን።
ተመልከቱ፣ ጳውሎስን ራሱን ጨምሮ መላው የመጀመርያው መቶ ክፍለዘመን ክርስቲያኖች የትንሣኤን አይነትና ተፈጥሮን አስመልክቶ የነበራቸው እምነት፣ እኛ የዛሬዎቹ ወንጌል አማኝ የሆንን ኃላፋውያን፣ አሮጌውን ወደኋላ በመተው በአዲስ አካል በቀጥታ ወደሰማይ የመሄድ ትንሳኤ ብለን ከምናምነውና ከምናስተምረው ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። ስለዚህም ጳውሎስና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አዲስ ኪዳንን እና አገልግሎቱን በማያውቁ ሰዎች አጠቃላዩ የሙታን ትንሳኤ በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም (MISSED ሊደረግ) እንደሚችል ያምኑ ነበር። ሄሜኔዎስ ፊሊጦስ የዚህ ሰለባ ነበሩ። እነጳውሎስ ግን አጠቃላዩ የሙታን ትንሣኤ ገና ወደፊት በብዙ ዘመን ርቀት ቆይቶ ሳይሆን በእነርሱው ዘመን መጨረሻ ማለትም በአሮጌው ኪዳን መጨረሻ ላይ እንደሚፈጸም ያምኑ ነበር (ዳንኤል 12)። እንዲሁም ትንሣኤ ከተፈጸመ በኋላ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ምንም አይነት ቁሳዊ ለውጥ ሳይደረግ ሕይወት በምድር ላይ የሚቀጥል እንደሆነ ያምኑ ነበር ማለት እንችላለን
ጳውሎስም ሆነ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በጠቅላላ፣ ዘመነኞቹ ቅድመ ሺህ አመታውያንም (Premillennialists) ይሁኑ ወይም አጠቃላዩ የመጻኢነት ዘመን መዳቢያን (Dispensationalists) በትምህርታቸው እንደሚያምኑት አይነት እምነት አልነበራቸውም፤ እነ ጳውሎስ ትንሣኤን የተቀበሉት ሁሉ በትንሣኤ ምክንያት በተሻሻለና በተለወጠ ፕላኔት-ምድር ላይ ይኖራሉ ብለው አያምኑም ነበር።
በሙታን ትንሣኤ ላይ ተከትበው የተለጠፉ ጽሁፎቼን philologus66 የፌስ ቡክ ገጽ እየገባችሁ፣ ወይም
http://gizachewkr.blogspot.com/2021/07/blog-post.html?m=1 በመጠቀም በርካታ መረጃዎችን እንድትካፈሉ ተጋብዛችኋል።
ቃሉን ከሚወዱ ሁሉ ጋር ብዙ ደስታ ይሁን!
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
No comments:
Post a Comment