Wednesday, February 3, 2021

የሽግግሩ ወቅት

የሽግግሩ ወቅት


[ይህ ጥፈት ከዚህ ቀደም "የዘመኑ ፍጻሜ" በሚል ርዕስ ላቀረብኩት አጭር ሀተታ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲሆን ታስቦ የቀረበ ክትባት ነው፤ ይነበብ ዘንድ ጋበዝኋችሁ። የቀደመውን ጽሁፍ ለማየት ፍላጎቱ ላላቸው እነሆ ሊንኩ፦

https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/3099516486943443/ ]


እጅግ የሚበዙ አማኞች የጥንት ቤተክርስቲያን ከኖረችበት አይነተኛ የጊዜ ምዕራፍ በተለየ ዘመን ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን አይረዱም፡፡ ከዚህም የተነሳ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አማኞች የተነገረውን የትንቢት ቃል ሁሉ ለእነርሱም ደግሞ የተነገረ እንደሆነ በማሰብ በአብዛኛው በሚከተሉት ትርጉም ይሳሳታሉ። እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ግን የኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻ ቀናት” ብሎ በሚጠራው የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ነበር - እነዚያም ቀናት የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ነበሩ።  እነዚያ “የመጨረሻ ቀናት” የተጀመሩት ደግሞ ምናልባትም በጴንጤቆስጤ ዕለት ሲሆን ቀኖቹም በይፋ የተፈጸሙት ከአርባ አመታት በኋላ የአይሁድ ቤተ መቅደስ በተደመሰሰበት በ 70ው ዓ.ም የእስራኤል- ሮም ጦርነት ወቅት ነው። ይህ የአርባ ዓመት ጊዜ ፣ ይኸውም ​​በጴንጤቆስጤ ቀን ማለትም ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን ከተቀበለችበት ዕለት አንስቶ፣ እልቂተ መቅሰፍቱ እስከተከናወነበት እስከ ጭፍጨፋው ቀን ድረስ፣ ይኸውም የአይሁድ ህዝብ በእሳት ጥምቀት ፍርድን እስከተቀበሉበት ቀን ድረስ ያለውን፣ ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን ሽግግር የሚደረግበት ወቅት ነበር ፡፡  በዚህ የሽግግር ወቅት አዲሱ ኪዳን በክርስቶስ መስዋዕታዊ ሞት ተመረቆ፣ በሐዋርያቱ እየተሰበከ ነበር፤ ዳሩ ግን ገና ተጠናቆ በፍጹምነት እና በሙላት ሊገለጥ የጌታን ዳግመኛ መመለስ ይጠባበቅ ደግሞ ነበር። ስለዚህም የሽግግሩ ጊዜ “ቀድሞውኑ ሆኗል ግን እስካሁን ድረስ ገና አላለቀም” በሚል ስሜት የሚታወቀው "The already but not yet" የተሰኘው ጊዜ ነበር። አሁን እኛ ግን የምንኖረው ከሽግግሩ ወቅት በብዙ ዘመን ርቀን መጽሐፍ ቅዱስ “የሚመጣው ዘመን” እያለ በሚጠራው፣ የአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው።  


ይህ የሽግግር ወቅት ብለን የምንጠራው ክፍለ ጊዜ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በክርስቶስ የመጀመርያ መምጣት እና በዳግመኛ ምጽአቱ መካከል በነበረው ጊዜ አርባ አመታት ያህል የሚሸፍን ነው። ይህ ጊዜ እንደሚጀመር ወይም የሽግግሩ ወቅት ሊጀመር እንደሆነ አስቀድሞ አይነተኛ ወቅቱን በበለጠ ያመላከተው መጥምቁ ዮሐንስ "መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ" (ማቴዎስ 3፥ 2) እያለና እያጠመቀ ወደይሁዳ የመጣበት የአገልግሎቱ ወራት ነው።   ያም ወቅት ጌታ አገልግሎቱን በይፋ የጀመረበት በ30 አ.ም አካባቢ የሆነው መገለጡ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የሽግግሩ ወቅት በይፋ የሚጀመርበትን ዕለተ በአለ ሃምሳን እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ወደፊት እያየ የተናገረለት አይነተኛ የጊዜ ምዕራፍ በይፋ የሚጠናቀቀው በ70 አ.ም ላይ በሚሆነው የጌታችን በፍርድ ዳግመኛ ምጽአት በፓሮዥያው፣ እርሱም የእሳት ጥምቀት ነው። 


የሽግግሩ ወቅት የተጠናቀቀው ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን ሊያስነሳና ሊወስድ ዳግመኛ ተመልሶ በመጣበት በ70 አ.ም ላይ ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 16-17)። የጌታ ሐዋርያትም ይህንን በማያሻማ ቃል ሲያስታውቁ "የጌታ መምጣት ቀርቧል" (ያዕቆብ 5፥ 8)፤ "ጌታ ቅርብ ነው" (ፊልጵስዩስ 4፥ 5)፤ "የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቧል" (1ጴጥሮስ 3፥ 22)፤ እንዲሁም "ዘመኑ ቀርቧል" (ራእይ 22፥ 10)፤ ወዘተ ይሉ ነበር።


ከሽግግሩ ወቅት አስቀድሞ በነበረው አሮጌ ዘመን ያ ሊሻር የቀረበው የብሉይ ኪዳኑ አይሁዳዊ የሙሴ ስርአት ገና ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ ነበር። በ70 አ.ም ላይ ግን የኢየሩሳሌምን ከተማ እና ቤተመቅደሱን ፈጽሞ ባወደመበት በሽግግሩ ወቅት መጨረሻ ላይ መንፈሳዊ የሆነው የአዲሱ ኪዳን የወንጌል መንግስት ሙሉ በሙሉ ተገልጦ በመላው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ወደፊት ቀጥሎ በፍጹምነት ይሰራና ይሰለጥን ዘንድ መሰረተው።


በዚህ የሽግግር ወቅት የሁለቱ ኪዳናት ስርአቶች መሳ ለመሳ ሆነው አዲሱ አሮጌውን ሽሮ በሙላት እስኪተካው ድረስ ሁለቱም በስራ ላይ ነበሩ። አሮጌው በ70 አ.ም ላይ በእሳት ፍርድ ሊያልፍና ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር። አዲሱም በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ተመርቆና ተጀምሮ በ70 አ.ም ላይ በፍጽምና እና በሙላት እስኪገለጥ ድረስ እየታነጸና እየተሰራ ነበር። ክርስቲያን የነበሩት የክርስቶስ ሐዋርያት ሁሉም ራሳቸው አይሁድ የነበሩ እና በአይሁድ መካከል በነበሩበት ዘመን ሁሉ የብሉይ ኪዳኑን ስርአተ ህግን ይጠብቁና ይለማመዱም ነበር።


ሐዋርያት ህግጋትን ይጠብቁና ይፈጽሙ የነበረው በጊዜው የምድሪቱ የእስራኤል ህግ ስለ ነበረ ነው እንጂ፣ ለደህንነታቸውና ለጽድቃቸው አስፈልጓቸው፣ ወይም የጽድቅና የኩነኔ ቅድመ-መስፈርት ሆኖላቸው እንዳልነበር ግልጽ ነው። ሆኖም ይህንንም ሲያደርጉ፣ በዚያ በአሮጌው ኪዳን ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ አይሁድ ምስክርነታቸው ተቀባይነቱ እንዲጨምር ከፈሪሳውያን በተሻለ ታማኝነት ያደርጉት ነበር። ምስክርነታቸው በአይሁድ ዘንድ ተደማጭ ይሆን ዘንድ ጽድቃቸው ከፈሪሳውያን ጽድቅ የበለጠ እንደሆነ ማረጋገጥና ማሳየት ነበረባቸው (ማቴዎስ 5፥ 19-20)።


የወንጌሉ ግልጽ መልእክት፣ ጽድቅ በመሲሁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ የሚታደል መሆኑ ነው። የሽግግሩ ወቅት መልእክትም አይሁድ ወይም አህዛብ የሆኑ አማኞች ሁሉ ይድናሉ የሚል ነው። ያለ ልዩነት ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ ያለው እምነት አንድ ነው (ኤፌሶን 4፥ 4-5)

(gkr)



No comments:

Post a Comment