Saturday, December 5, 2020

የዲያብሎስ መጨረሻ

የዲያብሎስ መጨረሻ

ኢየሱስ ሲናገር፣ "የዚህ ዓለም (ዘመን) ፍርድ ደርሷል፣ አሁን የዚህ ዓለም (ዘመን) ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፣ /ወይም  ይፈረድበታል / ማለቱን ታስታውሳላችሁ? (ዮሐንስ 12፥ 31 ፤ 16፥ 11)፤ ይኸውም ተሸንፏል፣ አልቆለታል ማለት ነው።  እንደ አዲስ ኪዳን ትምህርት፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቱ እና ከሙታን ተለይቶ በመነሳቱ ይህንን ታላቅ የድል ተስፋ ያጎናጸፈን መሆኑ እሙን ነው፤ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው ደግሞ ያንን ታላቅ ድል በመጨረሻው መደምደሚያና በፍጻሜ ከፍታ ሙላት ሰጥቶ እና ገልጦ አቀዳጅቶናል። ድሉም ያለ ዳግመኛ ምጽዓቱ ሙላትና ፍጻሜ እንደማይኖረው ግልጽ ነው። ከአሮጌው የብሉይ ኪዳን ዘመን ወደ አዲሱ የቃል ኪዳን ዘመን የተደረገው የሽግግር ጊዜ፣ ልክ እንደ ጥንታዊት እስራኤል የ40 ዓመቱ የምድረ በዳው ጉዞ አይነት፣ ከመስቀል አንስቶ የዳግመኛ ምጽዓቱ ፓሮውዥያ እስከሆነበት 70 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የሽግግር ጊዜ ይሸፍናል (ዕብራውያን 8፥ 13 ፤ 9፥ 8)። የብሉይ ኪዳን እስራኤል በፋሲካው ደም ከግብጽ ባርነት አርነት ወጥቶ ከ40 አመታት የምድረ በዳ ጉዞ በኋላ የተስፋይቱን ምድር እንደወረሰ፣ እንዲሁ በመስቀል ላይ በታረደው በግ ደም ቤዛነቱን ያገኘው የአዲሱ ኪዳን ቅዱስ ህዝብ ከሌላ 40 አመታት የስደትና የመከራ ጉዞ በኋላ በዳግመኛ ምጽአቱ የተስፋ ቃሉን ፍጻሜና ሙላት ለማግኘት ጌታን እየጠበቀ መታገስ ነበረበት።

2 ቆሮንቶስ 4፥ 4 "የዚህ አለም / ዘመን/ አምላክ" ስለሆነው አሳዋሪ ይናገራል፣ ይህ አለም የተባለው ግን ዘመኑን ማለት እንጂ ተዳሳሹን ግዑዝ አለም ማለት አይደለም። በ“ዘመን” መጨረሻ ፣ ይኸውም በማቴዎስ 24፥ 3 በተጠቀሰው በብሉይ ኪዳን ዘመን ማብቂያ ፣ ሰይጣን ከገዥነቱ ስልጣን ወርዶ፣ ሉተር እንደሚያስተምረው፣ የተሸነፈ ጠላት ሆኗል፡፡  እንደ እግዚአብሔር ፕሮግራም ከላይ ሆኖ በአየሩ ላይ ይገዛ የነበረው አለቃ እርሱ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ከሚገዛበት ከሰማይ (ኤፌሶን 2፥ 2)፣ ከገዥነቱ ሥልጣንና ከፍታ እንደ መብረቅ መውደቅ ነበረበት (ሉቃስ 10፥ 18) የአወዳደቁ ሁኔታ ግን  ያኔ ሂደቱ ገና ጅምር ነበር፣ በዳግመኛ ምጽአቱም ፈጽሞ ተሸንፎ ከኢየሱስ እግሮች በታች መቀጥቀጥ እና መገዛትም ይገባው ነበርና (ሮሜ 16፥ 20 - ዘፍጥረት 15፥ 15 ፤ ራእይ 2፥ 26፣ 27) ፣ እግሮች የተባሉትም የአካሉ ክፍል የሆኑት ናቸው፡፡

ሰይጣን በዘመኑ ላይ የነበረውም አገዛዝ በሽግግሩ ወቅት ላይ በሂደት እየተገለበጠና እየተለወጠ ነበር፣ የሽግግር ዘመን የወንጌል አገልግሎት አንዱና ዋናው ተጽዕኖም ይኸው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 17፥ 6)። በራእይ 20፥ 7 ላይ ለጥቂት ጊዜ ከእስራቱ እንዲፈታ በተባለለት አኳኋን፣ ሰይጣን በቄሳር ኔሮ ዙፋን ላይ ሆኖ የመጨረሻውን የመልሶ ማጥቃት በቅዱሳን ላይ አድርሶ ነበር። ዲያብሎስ ራሱ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ያውቅ ስለነበር፣ ያኔ ይሰራ የነበረው፣ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ፣ በታላቅ ቁጣ ነበር (ራእይ 12፥ 12፤ 1 ጴጥሮስ 5፥ 8-9)፤ ስለዚህም የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን መከራዋ ታላቅና አለም አቀፋዊ ነበር። በሕጉ ስርአት በኩል ጉልበታም ሆኖ የሚሰራው የኃጢአት ኃይል ዋና የማዘዣ ጣቢያው የሚገኘው ደግሞ በቤተ መቅደሱ ነበር፣ "የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው" (1 ቆሮንቶስ 15፥ 56) ተብሏልና። የዚያ የአሮጌው ዘመን ስርዓት የሰይጣንን ክስ እና የውንጀላ ስድብን ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደታች እያወረደ  የሞትን እና የኩነኔን አገልግሎት ያስፈጽም ነበር። ከዚያም በኋላ ግን ሰይጣን በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ዘላለማዊ ሽንፈቱንና  ፍርዱን አገኝቷል (ራእይ 20፥ 10)፣ ይሄ ግን ፈጽሞ እስከወዲያኛው አጥፍቶታል ወይም ወደአለመኖር ቀይሮታል ማለት አይደለም። እርሱ ግን ሁልጊዜ እንደሆነውና እንደነበረው ያው የተፈረደበትና የተጣለ፣ በቁጥጥሩ ስር ያለ የእግዚአብሔር  ዲያብሎስ ሆኖ ይኖራል፡፡  

እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ከሽግግሩ ዘመን ማዶ ባለው፣ አሮጌው ዘመን በተሻረበት እና በዳግመኛ ምጽአቱ በተጀመረው በዘላለማዊው ዘመን በአዲሱ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው፣ (ኢሳይያስ 9፥ 7 ፤ ዕብራውያን 13፥ 20)። ይኸውም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው። በዚህ ክቡር ዘላለማዊ ኪዳን ስር አድረው ክርስቶስን የሚያከብሩት እነዚያ እርሱ የተቤዣቸው ሕዝቦቹ እና እያንዳንዳቸው ቅዱሳኑ ብቻ ናቸው (መዝሙር 2)፤ እነርሱም ብቻ ድል የነሱ እና የተባረኩ ፣ ከፍ ከፍ ብለው በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር ያሉ እና ሥልጣንና ኃይል የተሰጣቸው ናቸው።  ከመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት ጀምሮ ደግሞም ሁልጊዜ የማይበገሩ ኃያላን ሆነው በሰማያዊው ስፍራ ከክርስቶስ ጋር የነገሱ እና የሚገዙ ክርስቶስን የሚያከብሩ ሕዝቦች እነርሱ ብቻ ናቸው።  ክርስቶስንና የጽድቅ መንግስቱን የሚቃወሙ ማናቸውም የምድር ህዝቦች ተሰብረውና ተደምስሰው፣ እርሱ ከፍ ከፍ ባደረጋቸው፣ ክርስቶስንም ሊያከብሩ በተገባቸውና የእርሱን ጽድቅ በተሸከሙ ሕዝቦቹ እግር ስር ተጥለው ተረግጠዋል ፡፡ ክርስቶስ የዚህ የአዲሱ አለም /ዘመን ጌታና አምላክ ስለሆነ፣ ከኔሮ ዘመን በኋላ በቅዱሳኑ ላይ በዓለም ዙሪያ አለማቀፍ የሆነ ስደት ያልነበረው እና ደግሞም ከዚህ በኋላ በጭራሽ የማይኖረው ለዚህ ነው። ምክንያቱም የነገስታት ንጉስ እና የጌታዎች ጌታ የሆነው የቤተክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ረግጦ፣ ግዛትና መንግስትም ተሰጥቶት ለቅዱሳኑ ዘላለማዊ እረፍት በአባቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የሚገዛ በመሆኑ ዘመኑ ተቀይሯል።

ከዚህ ቀደም እንደ ፕሪቴሪስት፣ "እኩይ እና ፍጻሜው" ብዬ በዚሁ ግድግዳ ላይ ለጥፌ ያስነበብሁትን አጭር ጥፈት ለተጨማሪ ግንዛቤ እንዲሆናችሁ የልጥፉ ሊንክ እነሆ:-
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2021585444607057&id=100002668627386

No comments:

Post a Comment