Saturday, May 16, 2020

አውሬው ማን ነው?

አውሬው ማን ነው?

ወንድም ነብዩ ኢሳይያስ በፌስ ቡክ ገጹ የ666ን ወይም የአውሬውን ማንነት አስመልክቶ በጥሙራውያን (eclecticism) የትርጉም ጎራ ያለውን አስተንትኖ በጽሁፍ በተከታታይ ካቀረበልን በኋላ እንደ ኃላፋውያን አተያይ ወንድማችን ከደረሰበት ድምዳሜ የምንለይበትን መሰረታዊ ምክንያት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በእውነቱ ጽሁፉ በርካታ ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ በፍላጎት አንብበው ከተጠቀሙት አንዱ ነኝ። ነብዩንም ለዚህ ትጋቱ ላመሰግነው እወዳለሁ። የነብዩ ጽሁፍ  ላላጋጠማችሁ በዚህ ሊንክ ፈልጉት፦ 


https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=3545055902188848&id=100000534203478


https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=3551996218161483&id=100000534203478


https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=3560230400671398&id=100000534203478


https://m.facebook.com/100000534203478/posts/3576034962424275/?notif_id=1589324735799045&notif_t=close_friend_activity&ref=notif



እንግዲህ በቅርብ እንዳለ ወንድምና ጓደኛ በልብ ስፋት ተደማምጠን በጓዳም ሆነ በአደባባይ የምንሟገትባቸው የሃሳብ ልዩነቶቻችን አሉ ይኖራሉም። ወንድማችን ያስተዋወቀንን ጥሙራውያንንና አመለካከታቸውን ጌታ ቢፈቅድ ብንኖር በሌላ ጊዜ ልመለስበት ይቆየኝ እያልኩ፣ በራእይ 13 የተገለጠውን አውሬ አስመልክቶ ግን ጥሙራውያንን ጨምሮ በበርካታ ተርጓሚዎች ለሚሰነዘሩ የተለያዩ መላምቶች ማጥሪያና ማጥለያ ሆኖ የሚያገለግል ግልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህ ማቆም ያስፈልጋል ባይ ነኝ። የዚህች አነስተኛ ክትባት ዋና አላማዋ ግን እንደ ኃላፋውያን አመለካከት ይህ አውሬ በታሪክ ውስጥ የሚታወቅ አንድ ግለሰብ እንጂ ሌላ ምንም ነገር ነው ብሎ ድምዳሜ ላይ እንዳይደረስ በቅዱስ ቃሉ የሚከለክሉ ባለ አምስት ነጥብ የትርጉም መርሆዎችን ማመልከት ብቻ ነው። ነጥቦቹም እነሆ:-


1ኛ/ 666 የተሰኘው የስሙ ቁጥር ግልጽ ሆኖ እንደተጠቀሰው "የሰው ቁጥር" (ራእይ 13 18) መሆን አለበት እንጂ ሌላ ምንም ነገር ሊሆን አይችልም። ሰው ብቻ። ይህም ማናቸውንም አጋንንታዊ ወይም መናፍስታዊ ማነትን፣ አልያም ፍልስፍናዊ አስተሳሰብን፣ ፖለቲካዊ ንቅናቄን፣ ኃይማኖታዊ ተቋማትን፣ ወይም ድርጅትን የሚያመለክትም የሚወክልም አይደለም። በታሪክ ውስጥ የሚታወቅ አንድን ግለሰብ ወይም ሰብአዊ ፍጡር ከመሆን ውጭ ማንኛውንም የዚህ ግዑዝ አለም ስርአተ ማህበርን ትርጉም አድርጎ አያካትትም። ሌላው ቢቀር ወንጌላውያን በሆኑ አንዳንድ የሙሉ ኃላፋውያን መምህራን ዘንድ "አውሬው ከኢየሩሳሌም መደምሰስ በፊት የነበረው አሮጌው የይሁዲነት ስርአት ነው" የሚለውንና ብርቱ ሙግት የሚያቀርበውን ድምዳሜ እንኳ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ "የሰው ቁጥር" ከሚለው መርህ ጋር ማስታረቅ ይቸግረዋል። ኅላፊያን የራእይ 13ቱን አውሬ በታሪክ ውስጥ ከኔሮ ጋር ብቻ አያይዘው  የተፈጸመና ያበቃ ጉዳይ አድርገው ለምን ይተረጉሙታል? ከተባለ፣ አውደ ምንባቡ "የሰው ቁጥር" በሚለው መግለጫው አንድን ግለሰብ ወይም 'ሰውዬ' እንድናስብ ብቻ እንጂ፣ ሌላ ማናቸውንም ጥንታዊና ዘመነኛ የአለም ስርአት እንዳናስብ ስለሚገድበን ነው። "የሰው ቁጥር" ከሁሉ በተለየ የሰው እንጂ የድርጅት፣ የተቋም፣ ወዘተ አይደለም። የራእይ መጽሐፍ በ70 ዓ.ም ላይ ከሆነው የእስራኤል ፍርድና የአይሁድ ህዝብ እልቂት በላይ ሌላ የሚለው ነገር ከሌለው፣ ከዚህ አይነተኛ አውድ ውጭ የሆኑና በታሪክ ውስጥ የሚጠቀሱት የሮም ፣ የጀርመን የናዚ ወዘተ.. ግዛተ - አፄዎች፣ ወይም የሂትለር፣ የሙሶሎኒ የሳዳም ሁሴንን፣ የኦባማ ወዘተ..- መንግሥታት እዚህ ውስጥ ምን ያገባቸዋል? እነዚህ ግዛተ አፄዎች እና መንግስታት የየራሳቸው ክፋት እንዳለባቸው ቢታወቅ እንኳ የራእይ 13ቱን አውሬ ለመሆን ግን አውድ ይገድባቸዋል። 


2ኛ/ በዚህ ቁጥር የሚወከል ይህ 'አውሬ ሰው' ክፉ የሆነ ዘማዊነትን የሚገልጥና በእርኩሰት የሚነዳ የስድብን ተፈጥሮ የተሞላ መሆን አለበት። ይህም በራእይ 13 በተለይም ከቁጥር 4-7 በተዘረዘረው መሰረት ባህርዩን፣ ተግዳሮቱንና የክፋት ስራውን መሰረት አድርገን ከመረመርን በራሱ በዩሐንስም ሆነ በመልእክቱ በኩረ ተደራስያን "እከሌ" ተብሎ ሊለይና ሊገለጽ የሚችል የሚታወቅ 'አውሬ ግለሰብ' ነው።


3ኛ/ ይህ አውሬ ሰው "ታላቅ ሥልጣን" የተሰጠው አንድ ግለሰብ መሆን አለበት (ራእይ 13፥ 2፣ 7)። ይህም በተለይ ትርጉሙን ካላወሳሰብነው በቀር በራሶቹ ላይ ካሉት አስር ዘውዶች የተነሳ ከአንድ ፖለቲካዊ ሥርዓተ ማህበር ባለፈ አንድን የተለየ ፖለትካዊ ስብዕናን በእርግጠኝነት እንድናስብ የግድ የሚል ነው። 


እነዚህ የመጀመርያዎቹ ሦስት ነጥቦች በኃላፋውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ወንጌላውያን በሆኑ የራዕይ መጽሐፍ ተንታኞች፣ በጥንቶቹም በዘመናውያኑም ዘንድ በስፋት ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። ቀሪዎቹ ሁለቱ ነጥቦች ደግሞ በእርግጠኝነት የአውሬውን ማነነትና ተልዕኮውን በተመለከተ ያለውን የመረዳት ስህተት የሚያርሙና፣ በትርጉማችን ላይ ችንካርን እየሰጡ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ያንንም በጽኑ የሚያሳዩ ምክንያቶችን የሚያቀርቡልን ናቸው። እነዚህንም በብዙ ማስረጃ ዘርዝሮ ማሳየት የሚቻል ቢሆንም ከጊዜ አንጻር ግን ነጥቦቹን በማሳየት ብቻ እገደባለሁ።


4ኛ/ ይህ የስሙ ቁጥር የግድ የሚያመለክተው ሐዋርያው ዮሐንስ በኖረበት ዘመን የኖረ አንድን ግለሰብ ነው። ይህንንም ማለት የምንችለው ዮሐንስ በጊዜው የትንቢቱን ፍጻሜ በገዛ ራሱ ዘመን ይጠባበቅ ከነበረበት ጽኑ እምነት በመነሳት ነው። በራዕይ መጽሐፍ የተገለጡና ይሆናሉ የተባሉ ኹነቶች ሁሉ ከጊዜ አንጻር "ቶሎ" ሊሆኑ ያላቸው ነገሮች ናቸው። ዮሐንስም "ዘመኑ ቀርቦአል" እያለ አጽንዖት የሰጠበት ጉዳይ ነው (ራእይ 1፥ 1፤ 3፥ 19፤ 22፥ 6)። ይህንንም ጊዜ ጠቌሚ የሆነ ሃሳብ በጉልህ የሚያሳዩ ማስረጃዎች በመጽሐፉ መግቢያ፣ በራእዩ መካከል እና በማጠቃለያው ባሉ ምዕራፎች ውስጥ ማየት ይቻላል (ራእይ 1፥ 1፣ 3፣ 7፣ 9፣ 10፣ 19፤ 2፥ 16፣ 25፤ 3፥ 10፣ 11፤ 4፥ 1፤ 6፥ 16-17፤ 8፥ 13፤ 10፥ 6-7፤ 11፥ 1-2; 22፥ 6-7፣ 10፣ 12፣ 20 ወዘተ )። አውሬው እንዲሰለጥን የተሰጠውንም የ42 ወራት ጊዜ ይህንንው ሙግት ለማጠናከር በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል። ኃላፋውያን በትርጉማቸው ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ ንግግሮችን አስመልክቶ የቀረቡ የራእዩን መግለጫዎች በአግባቡ ይጠቀሙባቸዋል እንጂ አልሞስሙሰው አይዟቸውም። ጊዜን አመልካች የሆነው የራእዩ ንግግር በመጽሐፉ መግቢያ መሐል ላይና በማጠቃለያው ላይ መጠቀሱ ትንቢቱ ሳይነጣጠል በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ የሚፈጸምበትን ዓይነተኛ የጊዜ ማዕቀፍ አመላካች ነው። ማንም ተርጓሚ ቢሆን በመጽሐፉ ላይ አውድ ዘለል የሆነ ትርጉምን ተከትሎ ስህተትን ሳይፈጽም የእነዚህን ሁነቶች ፍጻሜ በዘመን ሊከፋፍልም፣ በየዘመኑ ሊደጋግምም ሆነ የትንቢቱን ፍጻሜ በብዙ ዘመን አራዝሞ ሊጠባበቅ አይችልም። አውሬው አንድ ግለሰብ በመሆኑ፣ ይህም ግለሰብ ኖሮ የታወቀበት ዘመንና ትውልድ ያለው በመሆኑና፣ ያም ዘመን አንዱ የዮሐንስ ዘመን በመሆኑ፣ ስለማንነቱ ከሰብአዊነት አውጥተን፣ ዘመኑንም ከመጀመርያው ከፍለዘመን አሳልፈን በሌላ በየትኛውም ዘመን ላይ የሚከሰት ሌላ ማንኛውም ነገር ልናደርገው አንችልም። ይህ መሰረታዊ መመርያ ብቻውን ስለ አውሬው ማንነትና ተልዕኮውን በተመለከተ በየትኞቹም ጥንታዊና ዘመነኛ የመጽሐፉ ተንታኞች ሁሉ የሚሰነዘረውን  አስተያየት በእጅጉ ውድቅ ያደርገዋል። 


ወንድም ነብዩ በጽሁፉ የጥሙራውያንን (eclecticism) ድምዳሜ አጽንዖት ሰጥቶ ሲነግረን ስለ አውሬው የተነገረው ትንቢት "በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ አላበቃም ፣ የቀደመው ዘንዶና የእኩይ ኅይላት በክርስቶስ መመለስ እስኪፈረድባቸው ድረስ በተለያዩ መራሔ መንግሥታት እንዲሁም በተለያዩ ኅይማኖታዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገለጥን የትኛውንም ዓይነት ፀረ - ክርስቶስና ፀረ- ክርስቲያን አሠራርን ወካይ ቁጥር ነው" ብለው ማመናቸውን፣  ይህም አሠራር በግለሰብ ሆነ በተቋም ሊገለጥ ይችላል" ሲል ትርጉማቸውንና አቋማቸውን አስተዋውቆናል። በዚህም ጥሙራውያን የክርስቶስን መመለስና ፍርዱን ዮሐንስ በራእዩ "ቶሎ" ሲል ከገለጸው የጊዜ ማእቀፍ አውጥተው እንደ መጻእያን-ወታሪካውያን ሁሉ ገና ወደፊት እንደሚፈጸም የሚጠባበቁ መሆናቸውን ሲያመለክት፣ ጨምሮም "የሠይጣን፣ የራሱ የእኩይና የእኩይ ኅይላት ማብቂያ የክርስቶስ ደግመኛ መመለስ ነው" ብሎ፣ "እኩይና የእኩይ ኅይል ማብቂያ ጊዜ ወደ ፊታችን አለ" በማለት ሃሳቡን ያጸናል። ጥሙራውያን በሚከተሉት ትርጉምም አውሬው 'ሰው አውሬ' በመሆን የተገደበ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም ከሰብዓዊ ተፈጥሮ ያለፈና በስርዓተ ማህበር የሚወከል ሌላ 'አውሬ መንግስት'፣ 'አውሬ ኃይማኖት'፣ 'አውሬ ፖለቲካ'፣ 'አውሬ ኢኮኖሚ' ወይም 'አውሬ ማህበራዊ ሁኔታ' እንዳለ ወይም ገና እንደሚገለጥ የሚጠባበቁ መሆናቸውን ያመለክታል። ያየነውን ሁሉ "አውሬው" የሚል ስም እየሰጠን እንዴት እንዘልቀዋለን? በእውነቱ እንዲህ ካለውንስ የሽብር ኃይማኖት በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ ውስጥ አሾልኮ ያገባው ማን ነው? በጊዜ መዳቢነት (DespensetionLism) የሚዘወረው የመጻኢነት ነገረ ፍጻሜ (Futurist Eschatology) አይደለምን? እንግዲህ ይህንን የጥሙራውያንን መጽአዊ ድምዳሜ ራእዩ ስለ ፍጻሜው በግልጽ ባቀረበልን የጊዜ ማዕቀፍና በዚያ አውድ ብርሃን ስንመረምረው ከቅዱስ ቃሉ እውነተኛ ምስክርነት ርቆና ልማድ ወለድ ብቻ ሆኖ ቆሞ እናየዋለን። በአለም የሰው ልጆች ታሪክ የሚከሰቱትንና በትንሿ ሬድዮናችን የምንሰማቸውን ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ኃይማኖታዊ ወዘተ ጉዳዮች ይዘን ወደ ቃሉ ትምህርት እየቀረብን ትንቢትን በእነርሱ ልንፈታም ሆነ እነርሱን በቃሉ ልንተረጉም ብንደፍር እንስታለን። ቃሉ ከቃሉ ጋር ተመሳክሮ ብቻ እንጂ፣ በክራንች አይቆምም፤ በራሱ ቆሞ ራሱን ይመሰክራል! አለቀ!! ሌላ ምስክር አያሻውም።



በዚህም ላይ ጥሙራውያን እንዲህ ባሉ የትንቢት ዓይነቶች ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ በአለም ታሪክ በተደጋጋሚ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ዘመን ተሻጋሪ ክስተቶች (multiple occurrence) ባህርይ አላቸው ማለታችውም ብዙ አያስኬድም፤ ምክንያቱም  ጽንሰኣሳቡ የድግምግሞሽ ፍጻሜን የሚያቀነቅን ትወራ ነውና። ይህ አይነቱ ትወራ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አውድ የዘለለና፣ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነን የትንቢት ፍጻሜ እንድንጠባበቅ በር መክፈቱ ዋናው ችግሩ ነው። የአንድ ትንቢት ፍጻሜ ሁለቴ ይደገማል ብለን ካመንን፣ በራእይ 13 የተገለጠውም አውሬ በየዘመናቱ በተለያየ የአለም ሁናቴ ተደጋግሞ ሊገለጥ ይችላል ካልን፣ ታዲያ የሚደጋገመው ምነው አውሬው ብቻ? ሦስተኛ፣ ወይም አራተኛ ወይም አምስተኛ የክርስቶስ ምጽአት፣ ወይም ተደጋጋሚ የአለም ፍጻሜ ወዘተ እያልን ከመቀጠል የሚያስቆመን ምንም ነገር አይኖርም። እንዲህ አይነቱ ግራ የተጋባ የነገረ ፍጻሜ እሳቤ የትንቢት ፍጻሜን በተመለከተ በእጅጉ የተጨናበረና ለቃሉ እንግዳ የሆነን ሁሉንም አይነት እብድ ትወራ ወደ ቃሉ ትምህርት ይጋብዛል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮው የሚያውቀው አንዱን የክርስቶስ መመለስ፣ አንዱን የአለም ፍጻሜ፣ አንዱን የመጨረሻ ትንሳኤና ፍርድ ብቻ ከሆነ፤ እንግዲያውስ በመጨረሻው ዘመን ተገልጦ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፍርድ እንደሚወገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት የራዕይ 13ቱ አውሬም አንድ ብቻ ነው።  ሁለት ወይም ሦስት ወይም አራት የለም። ትንቢትም በአፈጻጸሙ ዘመን ተሻጋሪ፣ አሻሚ ሳይሆን ይልቁንም በዘመኑ፣ በተቀጠረው ጊዜ ሊፈጸም የታመነ ነው። ይህ አይነቱ የዘመን ተሻጋሪ ክስተቶች (multiple occurrence) ትወራ በነገረ ፍጻሜ የራእይ መጽሐፍ ትርጉም የታሪካውያንን (“Historicist”) አቀራረብ ከ "Realized Eschatology" (የብዝሃ ምጽአት) እሳቤ ጋር ያፈጣጠመ ትርጉም ነው። ሁሉም እነዚህ ትወራዎች ጊዜን አመልካች የሆኑትን የራእዩን ቃላትና ሀረጎች አልሞስሙሰው የሚያልፉ ናቸው። ኃላፍያን ግን አጽንዖት ሰጥተው ነገረ ፍጻሜን ሲያስተምሩ፣ የትንቢት ፍጻሜ ተፈጥሮና ባህርይ እሳቤው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ለትንቢት ፍጻሜ ከተቀጠረው ጊዜ ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበት አስረግጠው ይመሰክራሉ። ኃላፍያን በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮአቸው ለትንቢት ፍጻሜ የተቀጠረውን ጊዜና ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትን የትንቢቱን ቃላትና ሀረጎች በተገቢው ደረጃ ይጠቀሙባቸዋል። ለትንቢት ፍጻሜ የተቀጠረው ጊዜ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ ከተያዘ፣ እንግዲያውስ ትንቢቱ በምን አይነት መንገድ እንደሚፈጸም ባህርዩንና ተፈጥሮውን በተመለከተ አንሳሳትም።



5ኛ/ የቁጥሩ ስም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በእስያ ለነበሩና ዮሐንስ ለሚጽፍላቸው ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት (ራዕይ 1፥ 4፣ 11) በአግባቡ የሚታወቅ አንድ ግለሰብ መሆን አለበት። እርሱም የሚጽፍላቸውን ራእይ አስተውለው እንዲሰሙና እንዲጠብቁ (ራዕይ 1፥ 3) የአውሬውንም የስሙን ቁጥር እንዲያሰሉ (ራእይ 13፥ 18) ይጠይቃቸዋል። ታዲያ አውሬው እነርሱ ከነበሩበት ዘመንና አውድ ርቆ ያለ፣ ከሰብዓዊ ተፈጥሮ ያለፈ እና በስርዓተ ማህበር የሚወከል፣ በነበሩበትም አውድ ውስጥ ለእነርሱ በግልጽ ሊታወቅ የማይችል አንዳች ጥላ ቢስ ነገር ቢሆን ኖሮ ይህንን ቁጥሩን የማስላትና አውሬውን የመለየት ጥበብ እንዴት ይቻላቸው ነበር?


እንግዲህ እነዚህ በተራ ቁጥር 4 እና 5 የተገለጡ መርሆዎች የአውሬውን ማንነት በትክክል ለመረዳት መሰረታዊ ነጥቦች ናቸው ብዬ አምናለሁ። ከጊዜ አንጻር በስፋት ልሄድባቸው ቢያስቸግረኝም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ አጠቃላዩን የመጽሐፉን አውድ ጠብቀው ሊያጠኑ ለሚፈልጉና እርስ በርሱ ከተሳከረ መላ ምት መጠበቅ ለሚወዱ መጠነኛ መንደርደርያና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የስነ ፍታቴ ማዕቀፍ ይሰጣቸዋል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ። የአውሬውን ማንነት ጨምሮ በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ላይ ልንከተለው የሚገባንን ትርጉም በአጠቃላይ መግቢያ ደረጃ በጽሁፍ ለጥፌ philologus66 የፌስ ቡክ ገጼ ላይ ከአመታት በፊት በተከታታይ ያካፈልኩትን ልታዩ ከወደዳችሁ እነሆ ሊንኩ፦


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2194553230773111/


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2197517777143323/


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2211453562416411/


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2215447248683709/


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2217465978481836/


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2218770848351349/


https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/2222609127967521/


ቸር ሰንብቱ 

ከክፋት ሁሉ ተጠበቁ 

በክርስቲያን አዕምሮ ሞግቱ።


ግዛቸው ከበደ / ቄስ/



No comments:

Post a Comment