ግርማን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት!
ኢየሱስ ወደ ሰማይ የማረጉ ትርክት በግልጽ የተብራራው በሉቃስ ወንጌል ላይ እና ሉቃስ በጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ነው። ሉቃስ በወንጌሉ ምዕራፍ 24፥ 51 ላይ "ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።" ሲለን፣ ከዚህ ባለፈ አብራርቶ ስለ ዕርገቱ የነገረን በሐዋርያት ሥራ 1፥ 6-11 ላይ በሚገኘው ገለጻ ነው። በዚህ የእርገት ትዕይንት ውስጥ የምናየው ዋነኛ ስዕል ከሁሉ በላይ የመሆንን ስዕል ነው። ኢየሱስ ያረገው ከምድር ወደ ሰማይ ሲሆን፣ የሚያመለክተውም ከአንድ የአኗኗር ሁናቴ ወደ ሌላው የተደረገውን ሽግግራዊ እንቅስቃሴ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኤፌሶን 4፥ 8 እየሱስ ሲያርግ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያብራራ፣ ቆላስይስ 3፥ 1-2 ደግሞ ወደ ላይ ያረገውን ክርስቶስን ከቦ በላይ ያለው ነገር በታች በምድር ካለው ጋር በተቃርኖ ሲነጻጸር እናያለን፤ በዚህም ዕርገቱ በአጠቃላይ የዋጆአዊው ሥራ ላይ ያለውን ከፍተኛ ትርጉም እንረዳለን።
አስቀድመን፣ ጌታ ኢየሱስ ከእርገቱ ቀደም ብሎ ለደቀ ምዛሙርቱ የነገራቸውን ተስፋ እና እርገቱ በምን ሁኔታ እንደተፈጸመ የሚያመለክተንን የሉቃስን ምስክርነት እንይ፦
"ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ፤ ይህንንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።" (ሐዋርያት 1፥ 8-11)
ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ወደ አብ ከማረጉ አስቀድሞ በነበሩት አርባ ቀናት፣ በኢየሩሳሌም በልዩ ልዩ ስፍራ እየታየ ለተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ይገለጥ ነበር። እነርሱም እርሱ ሕያው እንደሆነ እና ከመቃብር እንደተነሳ ከእርሱ በሚሰጣቸው ማረጋግጫዎች ያውቁ ነበር። በእነዚያ አርባ ቀናት ከሐዋርያቱ ጋር እየተነጋገረ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ይነግራቸው ነበር። ለምሳሌ ዮሐንስ በወንጌሉ ሲዘግብ፦ "ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት" ሲል ይጽፋል (ዮሐንስ 20፥ 16-17)።
ክርስቶስ ከመስቀል ሞቱና ከትንሣኤው በኋላ በመጀመርያ የታየው ለመግደላዊት ማርያም መሆኑን ይህ ትራኬ ይነግረናል። እርስዋም ባየችውና ባወቀችው ጊዜ ወደ እርሱ ስትንደረደር፣ እርሱ ግን ገና ወደ አባቱ ስላላረገ እንዳትነካው ይነግራታል። ይፋዊ የሆነው ዕርገቱ ከአርባ ቀናት በኋላ እንደተፈጸመ ከላይ የተጠቀሰው የሉቃስ ዘገባ ግልጽ ያደርግልናል። ማርያም ግን ራሱን በገለጠላት ጊዜ ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ ወደ አባቱ የሚያርግ መሆኑን እንድትነግራቸው አስቀድማ ተልካለች። "ዓርጋለሁ" የሚለው የኢየሱስ ማስታወቂያ የሚያመለክተው ኢየሱስ ወደ አባቱ ለማረግ በሂደትና በዝግጅት ላይ የነበረ መሆኑን ነው። ከዚያም በኋላ ራሱ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ቢታንያ ወደሚባል ስፍራ ውሰዳቸው፣ በዚያም ከእነርሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ወደ ላይ ተወስዶ ወደ አባቱ ዐረገ።
"እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።" (ሉቃስ 24፥ 50-53)
ለደቀ መዛሙርቱም ከእርገቱ በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ተስፋ ስጥቶአቸዋል። በኢየሩሳሌም ፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቹ እንደሚሆኑ ነግሮአቸዋል። እርሱም ተለይቶ ወደ ላይ ሲሄድና ሲወሰድም ትኩር ብለው ይመለከቱ ነበር። ሁኔታውን ስንመለከት ጉዳዩ ልክ በደመና ተጋርዶ እንደሚሰወር ሰው ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ኹነቶች የተከበበ ነው፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ስትቀበለው ያዩ ነበር። እርሱ ወደሄደበት ወደ ሰማይ አሻቅበው እየተመለከቱ ሳሉ ያኔ ሁለት መላዕክት ተገልጠው ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ እንዲሁ፣ ማለትም "በደመና" ተመልሶ እንደሚመጣ ነግረዋቸዋል። (በዚህ የሐዋርያት ሥራ 1፥ 11 ላይ የቀረበው ዘገባና ስለጌታ ምጽዓት ባህርይ የተነገረ ቃል እንዴት መተርጎም እንዳለበት የዳሰስሁበትን ጽሁፍ ጨምራችሁ ትመለከቱት ዘንድ ግብዣዬ ነውና እነሆ ሊንኩ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/02/1-9-11.html?m=1
ቀጥሎም፣ አካላዊ ከሆነው የዕርገቱ ኹነት ባልተናነሰ ከዕርገቱ ጋር የተገናኙና ዕርገቱን ከበው የሚገኙ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮችን ጨምረን ማንሳት እንችላለን። በመጀመርያ፣ ይህ የዕርገቱ ኩነት የሚያመለክተው የአንድን ጉዳይ ወሰን እና የሽግግር ሁናቴ ነው። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው፣ ዕርገቱ በሉቃስ ወንጌል መጨረሻው ላይ ሲዘገብ የኢየሱስን ምድራዊ የኑሮ ምዕራፍ መዘጋቱን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ሲዘገብ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ ኢየሱስን የመተካቱን ጅማሬ ያመለክታል። ዕርገቱ የክርስቶስን ወደ ምድር ወርዶ በስጋ የመምጣቱን ታሪካዊ እውነት ልክ እንደ ፊደል U ቅርጽ ወደታች የወረደውን መልሶ ወደ ላይ በማውጣት ዑደቱን ግልጽ የሆነ የመጠናቀቅና የፍጻሜ መልክ የሚሰጠው ነው። ኢየሱስም በሥጋ ወደ አለም የመጣበትን አላማ ሙሉ የሚያደርግ ታሪካዊ ሃቅ መሆኑንም ጨምረን እናስተውላለን። በዮሐንስ 6፥ 62 ኢየሱስ ስለ ዕርገቱ ሲናገር "እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?" ሲል ይጠይቃል። ኤፌሶን 4፥ 10 ደግሞ "ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።" ሲል የዕርገቱን ከፍታ ይነግረናል።
አስከትሎም፣ ዕርገቱ ከፍ ከፍ የማለት ዋነኛ መገለጫ ሆኖ አጠቃላይ የሆነ አወንታዊ ትርጉምን የሚያጎናጽፈው ከፍተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ መሆኑን ያመለክታል። በዚህም ውስጥ ያለው አብይ ትርጉሙ መክበር ነው። እንደ ትንሣኤው ሁሉ የኢየሱስ ዕርገትም የመለኮታዊ ማንነቱ መገለጫው ሲሆን ዋጆአዊ የቤዛነቱን ስራ ብቃትም የሚያረጋግጥ ነው። የክርስቶስ የመክበር ኹነቶች በዝርዝር በተብራሩበት የ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥ 16 የጥንት ቤተክርስቲያን የዝማሬ መድብል እንደተገለጸው የክርስቶስ ከፍተኛውና የመጨረሻው ኹነት "በክብር ያረገ" የሚለው ስንኝ ነው። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጋር የተያያዙ ሌሎቹም አምሳያዎች አጽንዖት የሚሰጡት የመክበርን ሁናቴ ነው። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የመቀመጥን ከፍተኛውን የክብር ስፍራ መውሰዱን እናስተውላለን። ማርቆስ ዕርገቱን አስመልክቶ በምዕራፍ 16፥ 19 ላይ "ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።" ይለናል። ( ኤፌሶን 1፥ 20፤ ቆላስይስ 3፥ 1፤ ዕብራውያን 1 ፥ 3፤ 8፥ 1፤ 10፥ 12፤ 12፥ 2)። ሰማዕቱ እስጢፋኖስም ሰማይ ትከፍቶለት ያየውን አስገራሚ ትዕይንት በሐዋርያት ሥራ 7፥ 55-56 ላይ ሲመሰክር "መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ" ነው ያለው። ያ ቀኝ የኃይልና የስልጣን ሁሉ የመጨረሻው ከፍታ ነው። ከሙታን ተነስቶ ያረገው ክርስቶስ የተቀዳጀውን ከፍታ ሐዋርያው ዻውሎስ እንዴት እንደሚገልጠው ተመልከቱ፦ "ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤" (ኤፌሶን 1፥ 21)።
እንዲሁም፣ በዕርገቱ ውስጥ ከክርስቶስ መክበር ጋር ግንኙነት ያለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በክፉ ኃይላት ላይ እና በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ እርሱ የተቀዳጀው ንጉሳዊው ድል ነሺነቱ ነው። ይህም በመዝሙር 68፥ 18 ውስጥ "ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ" የሚለው ነው። የመዝሙሩ አውደ ምንባብ እንደሚያረጋግጠው ድል ነሺ ንጉስ በውጊያ ነጥቆ ይወሰዳቸውን ምርኮኞቹን ይዞ በድል አድራጊነት ግርማ ወደተራሮች ከፍታ ላይ የመውጣቱን ስዕል በጉልህ የያዘ ነው። ይህ መዝሙር በኤፌሶን 4፥ 18 ላይ "ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ" ተብሎ ሲጠቀስ ቃሉ የሚዛመደው ክርስቶስ በድል አድራጊነት ግርማው ላደረገው ሥራ ነው። ጌታ ኢየሱስ በዕርገቱ አእላፋት ምርኮኞችን አስከትሎ ወደ ላይ ወጥቶአል። በሌላ መልኩ ደግሞ፣ በዚህ አለም በእኩይና ሰናይ መካከል በሚካሄደው የማያቋርጥ ግጭት ውስጥ፣ በእምነት የምናውቀው ክብርን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት የሚያረጋግጠው "ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዝቶለታል"፣ "ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶታል" (ኤፌሶን 1፥22)፣ ተብሎ እንደተጻፈ፤ አሮጌው አይሁዳዊ የሞት ሥርዓትም ይሁን ወይም ዘምኛለሁ የሚለው የግሪኮ ሮማ አህዛባዊ አምልኮተ አማክልክት፣ ማናቸውም ቢሆን ክርስቶስ ከእግሩ በታች አድርጎ ያልገዛውና የማይቆጣጠረው ቤተክርስቲያንን ሊቃወም የሚችል ኃይል ያኔም አሁንም የሌለ መሆኑን ነው። እርስዋን ሊቋቋም የሚችል ምንም የገሃነም ሃይል የለም።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ የምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ መሆኑን እንደሚያመለክት ሁሉ፣ ጨምሮም እንደገና ምድርን ለመጎብኘት ተመልሶ እንደሚመጣ ካለው ዝግጁነት ጋርም የተያያዘ ነው። ወደ ሰማያት የወጣው ለሺህ ዘመናት ሊከርም ወይም ሳይመለስ በዚያው ሊቀር ሳይሆን ይልቁንም በዚያ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በጽኑ ሥደትና መከራ ውስጥ ለምታልፈው ቤተክርስቲያኑ "ቶሎ" ሊመጣ ነው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደው ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ተከትለው ወደዚያው ይሄዱ ዘንድ ስፍራ ለማዘጋጀት ነውና። "ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ" (ዮሐንስ 14፥ 2-3)። ያረገው ክርስቶስ በክብር መገለጡ የሚጠበቅ የነበረውን ያህል የአማኞችም የክብር መገለጥ እርሱን ተከትሎ የሚሆን ነበር "ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ" (ቆላስይስ 3፥ 4)።
እንግዲህ ይህ አስገራሚ የሆነ የዕርገቱ ዘገባ፣ "ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 28)፣ ተብሎ እንደተጻፈ፣ በዚያው ትውልድ ዘመን ይኸውም በ70 ዓ.ም ለተፈጸመው ዳግመኛ ምጽአቱ (parousia) የተነገረ ማጣቀሻን የያዘ ነው። "ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል" (ሐዋ 1፥ 11) የሚለው የሉቃስ ዘገባም ከዚህ ጋር ይስማማል። ያድናቸው ዘንድ ሲጠባበቁት የነበሩት በዘመናቸውና በትውልዳቸው እንደሚመለስ ተስፋ የተገባላቸው፣ "እናንተ ሲሄድ ያያችሁት" የተባሉት ራሳቸው ናቸው፣ የሚመጣውም ለእነርሱው ነው።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲጽፍ፣ "ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤" (1ኛጴጥሮስ 3፥ 18-19) ይላል። የቤዛነታቸውን ቀን እየጠበቁ በሲኦል ወኅኒ የነበሩትን ሙታን እርሱ በሞቱ በፈጸመው ቤዛነት ከዚያ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባቸው ዘንድ የምስራቹን ሰበከላቸው። ክርስቶስ ወደ ሲኦል እንደወረደና ወደ ሰማይ እንደወጣ የጥንት ቤተክርስቲያን ማመንዋ በእግዚአብሔር ቃል የሚደገፍ እውነት ሲሆን፤ በእምነት መግልጫዎቻቸውም "...በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን መከራ በተቀበለ፣ በተሰቀለ፣ በሞተ፣ በተቀበረ፣ ወደ ሲኦል በወረደ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን በተነሳ፣ ወደ ሰማይም በወጣ፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በተቀመጠ፣ በህያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ከዚያ በሚመለስ...እናምናለን" ሲሉ እምነታቸውን ያስታውቁ እንደነበር ታሪካዊ ድርሳናት ያመለክታሉ። በዚህ ምስክርነታቸው ለእነርሱ ኃላፊና መጻኢ የነበሩ ኹነቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፣ ጌታ ግን እንደሰጣቸው የተስፋ ቃል በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በክብር የተመለሰ በመሆኑ በዚህ የታመነ ምስክርነት ውስጥ ያለው የመመለሱ መጻኢ ተስፋ ዛሬ ለእኛ ኃላፊ ሆኖአል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ገና በ63 ዓ.ም ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ፣ "ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው" (ኤፌሶን 4፥ 8-10) ይላል።
ከዚህ ሃሳብ ክርስቶስ "ሁሉን ይሞላ ዘንድ" ወደ ታች (ሃደስ) ወርዶ፣ በዚያ ለነበሩ ምርጦች ቅዱሳኑ፣ እርሱ ሕያው መሆኑን ምረጋገጫ ሰጥቶ እንደሰበከለቸውና፤ ከአርባ ቀናትም በኋላ በእርገቱ ወቅት ከዚያ ማርኮ ወደላይ እንዳወጣቸው፣ እርሱም ከፍ ከፍ ብሎ 'ዩም ኪፑር' የተሰኘውን የማስተሰርያውን ስራ ሊያጠናቅቅ በሰማያዊው ቤተመቅደስ ወዳለችው ሰማያዊት ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ከዚያ እስኪወጣ ድረስ በሰማያዊው ስፍራ በአውደ ምህረቱ ደጃፍ አከማችቶ እንደሰበሰባቸው እናስተውላለን።
ከሁሉ በላይ ሆኖ ከላይ የመጣው እርሱ አስቀድሞ ወደ ሙታን መቃብር ወደታች ወረደ፣ የወረደው እርሱ "ሁሉን ይሞላ ዘንድ" ከሰማያት ሁሉ በላይ ሲወጣ ግን የወጣው ብቻውን ሳይሆን፣ ይልቁንም ለምርጦቹ በአባቱ ቤት ስፍራን ያዘጋጅላቸው ዘንድ ምርኮውን ሰብስቦ ይዞ ወጣ።
ይህንን የሚያስተምር መጽሐፍ ቅዱሳችን ለአማኞች የሕይወት ተዛምዶን ያቀርብልናል። እኛ በክርስቶስ ያመንን አማኞች በእርሱ ከማመናችን የተነሳ ብቻ "ከእርሱ ጋር ተነስተን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር ተቀምጠናል" (ኤፌሶን 2፥ 6)፤ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ደግሞ እንድንሻ ጥሪ አለን፣ (ቆላስይስ 3፥ 1)
ነብዩ ኢሳይያስ ህማማተ ክርስቶስን ባስተማረበት ትንቢቱ ስለክርስቶስ ምርኮ ሲናገር፦ "እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።" (ኢሳይያስ 53፥ 10-12 ) ሲል ይመሰክራል። ከኃያላን ጋር ምርኮን የሚከፋፈል እርሱ ድል የነሳ ብቻ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ድል ነስቶአል፣ "እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር ….. ድል ነሥቶአል " (ራእይ 5፥ 5)
ጌታ በመስቀል ነፍሱን ሲሰጥ ከሆኑ አስገራሚ ክንውኖች መካከል በወንጌላዊው ማቴዎስ ዘገባ መሰረት የመቃብር መከፈትና ከሙታን ብዙዎች መነሳታቸው ሲሆን እነርሱም ከትንሳኤው በኋላ በኢየሩሳሌም ለብዙዎች መታየታቸው ነው። "ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።" (ማቴ 27፥ 50-53)
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሞት፣ መቃብርና ሲኦል የተሰኙ ኃያላን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ሙታናቸውን እስከ ወዲያኛው የተነጠቁት ክርስቶስ በነፍሱ ድካም። "ወደ ምድር ታችኛ ክፍል" ወርዶ በከፈለው ዋጋ ነው። ዮሐንስም በራእዩ ያየውን ሲመሰክር፦
"ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ" (ራእይ20 11-15) ይላል።
ይህ የሕይወት መጽሐፍ ምን እንደሆነ፣ በውስጡ የተጻፉትንና የሚድኑትን፣ ከመቃብር የሚነሱትንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚገቡትን በተመለከተ ነብዩ ዳንኤል በትንቢቱ ሲናገር "በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።" (ዳንኤል 12፥ 1-2) ይላል። ይህንንም ያስተማርሁበትን ጽሁፍ ለማንበብ ከወደዳችሁ እነሆ ሊንኩ፦
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/01/12.html?m=0
(gkr)
No comments:
Post a Comment