Monday, May 27, 2019

ትንቢትን ለመተርጎም የአውደ ተደራስያን ፋይዳ ለፕሪቴሪዝም

ትንቢትን ለመተርጎም የአውደ ተደራስያን ፋይዳ ለፕሪቴሪዝም
የትኛውንም የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ በአግባቡ ተርጉሞ ለመረዳት ዋናና አስፈላጊ የሆነ አንድ ጉዳይ ቢኖር የምንባባቱን አውድ ማወቅ ነው። ይህም በአይነቱ የጽሁፉ በኩረ ተደራስያን የነበሩበት አጠቃላይ አውድ ማለት ነው። በዋናነትም ምንባቡ አስቀድሞ የተጻፈው ለነማን ነው የሚለውን ማወቅን ያካትታል። ከዚህ በተለየ አብዛኛውን ጊዜ ቅዱሳት መጻህፍትን በትክክል ያለመረዳት ችግር የሚከሰተው አንባቢው ምንባባቱን ለግሉ ወይም ለግሏ እንደተጻፈ አድርገው ሲወስዱ ነው። በመሰረታዊነት አዲስ ኪዳን በመጀመሪያው ክፍለዘመን ጸሐፍያን የተጻፈው ለመጀመሪያው ክፍለዘመን ክርስቲያኖች ሲሆን የተጻፈውም የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ኹነቶች ለመነጋገር ነው።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን የሚችል አንዱ ጉዳይ ጌታ ኢየሱስ የዳግመኛ ምጽዓቱን ፓሮዥያ በተመለከተ ለደቀመዛሙርቱ የነገራቸውን ሁሉ ዛሬ ለእኛ እንደተነገረ አድርጎ የመውሰድና፣ አሳስቶ የመረዳት፣ የመተርጎምም እሳቤ ነው። እርሱ የቤተመቅደሱ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ ወድቆ እንደሚፈራርስ አስቀድሞ ነግሯቸዋል። እነርሱም ያንን ከሰሙ በኋላ ይህ የተባለው ነገር የሚከሰተው መቼ እንደሆነ፣ እርሱም የሚመጣበት ምልክቱ ምን እንደሆነና፣ የአይሁድ ዘመንስ ማብቂያው መቼ እንደሆነ ጠይቀውታል (ማቴዎስ 24፥ 2-3)።

ኢየሱስ ንግግሩን ሲቀጥል፣ በዚያው በጠያቂዎቹ ትውልድና ዘመን ውስጥ ከምጽአቱ አስቀድሞ ስለሚሆኑ ጉዳዮች፣ ምልክቶችና ኹነቶች በዝርዝር ይነግራቸው ነበር። (ማቴዎስ 24፥ 4-32 ተመልከት)። በግልጽም የነገራቸው አንድ ጉዳይ እነርሱ እነዚህ ነገሮች ሲሆኑ እንደሚያዩና፣ በዚህም ሲሆኑ በሚያዩዋቸው ምልክቶች አማካኝነት መምጣቱ የቀረበ መሆኑን የሚያውቁ እንደሆነ ነው።

"እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።" (ማቴዎስ 24፥ 33-34)።

በርካታ ክርስቲያኖች ዛሬ ላይ ቆመው ይህንን የጌታን ንግግር ለመተርጎም ሲሞክሩ ከጠቅላላ ቃሉ ከተነገረበት አውድ ነጥለው፣ ልክ ጌታ ዛሬ ከአመታት በኋላ የመምጣቱ ምልክት ምን እንደሆነና በእኛው ትውልድ ውስጥ ሊሆን ያለውን ለእኛ የነገረን እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። ስለሆነም ወቅታዊውን የአለምን ፓለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ በተለይም እንደ እስራኤልና አረቦች ያሉ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን ውጥረት፣ እንደ አሜሪካና አውሮፓውያን ሸሪኮቿ ያሉ የኃያላን መንግስታትን የውጭ ፓሊሲ፣ እንደ ሩስያና ቻይና ያሉ ከምዕራባውያን በተቃራኒው የቆሙ ኃይሎችንና ትንንሽዬ የኒውክለር ጡንቻ እያበቀሉ ያሉ እንደ ኢራንና ሰሜን ኮርያ ያሉ መንግስታትን ሁኔታ የሚዘግብ ትኩስ የአለም ዜና እያነፈነፉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በአለም ወሬ እየተመሩ ለመተርጎም የሚደረግ "የስነመለኮት አዋቂ ነን" ባዮች ሙከራ ሁሉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት አውደ ምንባብና የአውደ ተደራስያኑን ዋጋ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን ከንቱና የማይረባ ሆኖ በክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለበርካታ የስህተት ትምህርትና የስህተት እምነት መፈልፈያ ሰበብ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ አውደምንባብ እና የበኩረ ተደራስያኑ ተዛማጅነት ዋጋ ባለው ሁኔታ በቁሙ የሚወሰድ ከሆነ ግን፣ ያኔ በትንቢት ቃል  ምንባብ ላይ ግልጽ እና ቀጥተኛ የሆነ ትርጉም ሊኖረን ይጀምራል። ከተሳሳተ መረዳትና እምነትም እንጠበቃለን። ፍጻሜውንም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ በማስተዋል የመጽናናትን ብዛት፣ የእምነትን ጽናትና የክርስቶስ ታማኝ ምስክርነት የሚሰጠውን ድልና ድፍረት ያለማምደናል።

ማቴዎስ 24ን መሰረት አድርጌና ረዘም ያለ ጊዜ ወስጄ በተከታታይ ባቀረብኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ባስነበብኩት ዘለግ ያለ ጽሁፍ ለማስረገጥ የወደድሁትም እያንዳንዳቸው እነዚህ ጉዳዮች በእርግጥም በዚያው በመጀመርያው ክፍለዘመን ውስጥ መሆን ጀምረው ሙሉ በሙሉ ፍጻሜአቸውን ያገኙት በ70 ዓም ላይ መሆኑን ነው። ፍላጎቱ ያላችሁ አንባቢዎቼ በማቴዎስ 24 ላይ "የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት" በሚል ርዕስ ያስነበብኩትን ተከታታይ ጽሁፍ እንድትመለከቱ እነሆ ሊንኩን ጋበዝኳችሁ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_60.html
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_33.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_91.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_95.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_32.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_93.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_43.html

እንደ  እውነቱ ከሆነ በእግዚአብሔር ቃል ጥናታችን ላይ አውዱን ያገናዘበ ምልከታ ሲኖረን፣ የክርስቶስን የዳግመኛ ምጽዓት ፓሮዥያ በተመለከተ የተነገሩት ሁሉም የትንቢት ቃላት ጌታ ኢየሱስ እና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ሐዋርያቱ በተደጋጋሚ ይሆናል ሲሉ እንደተናገሩት ልክ እንደዚያው ሳይዛነፍ በተባለለት ጊዜ እንደተፈጸመ አጥርተን እናያለን።

በርካታ ክርስቲያኖች ይህንን ለመቀበል እጅግ የሚቸግራቸው ስለ ጌታ ምጽአት ባህርይና ተፈጥሮ በተለምዶ ሲሰሙትና ሲያስቡት ከኖሩት ነገር የተነሳ ነው። ይኸውም፣ ቃሉ ከሚያስተምረው በተለየ ልማድና ትውፊት ያቀበላቸውን ያለ ጥያቄ አስቀድመው ውጠው በመገኘታቸው ነው። ከዚህም የተነሳ ይህንን የትንቢት ቃል በዚያው በተነገረበት የበኩረ ተደራስያኑ አውድ አንጻር እንዳለ ለመውሰድና ታሪካዊ ፍጻሜውንም በዚያው ትውልድ ውስጥ ለማየት አይችሉም፣  ይተናነቃቸዋል። በዙሪያቸውም ያለውን ተዳሳሽና ነባራዊ ሁኔታ እየተመለከቱ "ትንቢቱ አልተፈጸመም"፣ "ጌታም እስካሁን ገና አልመጣም" ሲሉ ደምድመው አቋም ይዘዋል። የሌለና ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር እይጠበቁ ስለሆነ፣ ከ"ተስፋቸው" እና ከ"እምነታቸው" በተለየ የሚሞግታቸውን የአማኝ ወንድሞቻቸውን አመለካከት እንኳ በልብ ስፋት ለማጤን አይታገሱም።  ለምሳሌ፣ በዚህ ተዳሳሽ አለም ያለውን የኅጢአትና  የክፋትን ሁኔት ተመልክተው ሲያበቁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሆን ያንን የሚያዩትን የአለምን ሁኔታ መሰረት አድርገው፣ ፍጻሜ ያገኘውን የተባረከ ተስፋ፣ እርሱም ጠሊቅና ምጡቅ የሆነውን የጌታን መመለስ እውነታ መቀበል አይችሉም። የሆነ ሆኖ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን በጥናታችን ብንተጋ ከዚህ ነባራዊና ተዳሳሽ ግዑዝ አለም ላይ ኃጢአትና ክፋት  እንደሚወገድ የተሰጠ አንዳችም ተስፋ አለመኖሩን አጥርተን ማየት ይቻለናል። ችግሩ ብዙዎች ለቃሉ ሥልጣን ከመገዛት ይልቅ፣ ከአውደ ምንባቡ ርቀው በወደቁበት፣ ፍጥረታዊ ምኞታቸውንና እድሜ ጠገብ ልማዳዊ አስተሳሰባቸውን እንዲያጸድቅላቸ ከመጽሐፉ ስለሚንታገሉ የቅዱስ ቃሉን ትምህርት ሳያገኙት መቅረታቸው ነው።

ጽድቅ ስለሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተሰጠው የታመነ ተስፋ ግን ፍጻሜውን ያገኘው በ70 ዓም ላይ ሙሉ በሙሉ በተመሰረተው በመንፈሳዊው የአዲሱ ኪዳን መንግስት ነው። አሮጌው የአይሁድ ቃል ኪዳን ኃይማኖታዊው ሥርአት በ70 ዓም ላይ ተደምስሶ ተወግዶ አልፎአል። ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለምና ለዘለዓለም መንግስቱን አጽንቶአል። ግዛቱም ወሰን፣ ዘመኑም ፍጻሜ የለውም። በዚህም የአዲሱ ቃል ኪዳን መንፈሳዊ መንግስት ውስጥ አሁን እየኖሩ ያሉት ደግሞ፣ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በእያንዳንዳቸውም ውስጥ እንዲኖርባቸው መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። በእያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ውስጥ በሚኖረው መንፈሳዊው መንግስት አንዳችም ጽድቅ ያልሆነ ነገር የለም።

"ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።" (2ኛ ዼጥሮስ 3፥ 130)

"እንጠብቃለን" ያሉት እንዲጠብቁ አስቀድሞ በጌታ የተስፋ ቃል የተነገራቸው የጥንት ቤተክርስቲያን ሰዎች ናቸው፤ እነርሱም እንዲህ ያለውን መጠባበቅ ከጌታ ቃል የተነሳ፣ በትልቅ ናፍቆትና ጉጉት በገዛ ዘመናቸውና ትውልዳቸው ውስጥ እንደሚፈጸም ከነበራቸው እርግጠኝነት ጋር፣ በሚቀበሉት መከራና በሚያልፉበት ስደት ውስጥ እይቃተቱ ተግብረውታል። እኛ ግን በተፈጸመ ተስፋ ጽድቅ በሚኖርባት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እየኖርን ነን እንጂ ጠባቂዎች አይደለንም።

በመጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት ቃል ላይ ፕሪቴሪዝም የሚያቀርብልን አፈታት ከየትኛውም የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ሥነ መለኮታዊ ትንታኔ ይልቅ ለአውደ ምንባቡና ለአውደ ተደራስያኑ የታመነ፣ አግባብነት ያለውን ሥነ ፍታቴ እየተከተለ ለትርጉም ቀዋሚነት የሚተጋ ነው። ፕሪቴሪዝም ምን እንደሆነ ለማታውቁ፦ ፕሪቴሪዝም በተፈጸመ ነገረ ፍጻሜ የሚያምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ነው። ይኸውም ክርስቶስ የነብያቱን ትንቢት ሁሉ ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ወደ ፍጻሜ አምጥቶታል፣ በ70 ዓም ላይም በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያ  ሁሉንም አጠናቋል ብሎ የሚያምንና የሚያስተምር ነገረ ፍጻሜ ነው። ከፍ ሲል ለማሳየት እንደሞከርኩት ፕሪቴሪዝም ስለ ቅዱሳት መጻህፍት አውደምንባብ የሚገደው የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ያለውን ማንኛውንም ምንባብ ትርጉሙን መወሰን ያለበት የምንባቡ አውድ ነው። ይኸውም ደግሞ፣ ማን ጻፈው? መቼ ተጻፈ? የተጻፍውስ ለማን ነው? ስለምንስ ጉድይ ነው የተጻፈው? ስፍራውስ የት ነበር? እንዴትስ ነው የሆነው? የሆነውስ ለምንድን ነው? የሚሉትን መርማሪ ጥያቄዎች ሁሉ ያካትታል።

በአጠቃላይ እነዚህ መጠይቆች መመለስ ያለባቸው በራሱ በምንባቡ እና በአውደ ምንባቡ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ተጨማሪ እይታን እንዲሰጡን ሌሎች የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ሊያስፈልጉን ይችላሉ። አንድን የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ በወጉና በአግባቡ ለመረዳት ቃሉን የሚተረጉመው ቃሉ ብቻ ነው የሚለው መርህ ጠቃሚና እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። እንግዲህ የንባብ ክፍሉ አውድ ግልጽ ከሆነልን ያኔ ይኹነቱን ባሕርይና ተፈጥሮ በውል ለመረዳት ይቻለናል።

እጅግ የሚያሳዝነው ቤተክርስቲያን ላልፉት 2000 አመታት የጌታን ዳግመኛ ምጽአት "ባህርይና ተፈጥሮ" እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የነገረ ፍጻሜ ኹነቶች ሁሉ አሳስታ ስትተረጉም ኖራለች። ከዚህም የተነሳ የዳግመኛ ምጽዓቱን ፓሮዥያ አስመልክቶ በቅዱሳት መጻህፍት ያለውን አውድ ባለመረዳት ፈጽሞ የተሳሳተ የሆነ እሳቤና አመለካከት 'ተምረናል' በሚሉትም ላይ እንኳ ገዢ ሆኖ ኖሯል። ላለፉት 2000 አመታት ቤተክርስቲያን ነገረ ፍጻሜን በተመለከተ የተሳፈረችበት ባቡር ወደ 'ምዕራብ' ሊወስዳት ሲገባ በተቃራኒው እየተጓዘች ያለችው ወደ 'ምስራቅ' ነው። ፕሪቴሪዝም "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" (Sola Scriptura) በተሰኘው የቤተክርስቲያን አዳሾች መርህ ላይ የቆመና በዘመናት መካከል እንደገና የተገኘ ሌላው የተሃድሶ ጥሪ እና እድል ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ደግሞ የሚወድዱ ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንደሚሰጡ አምናለሁ።

ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር አብሮ መሆን ያለባቸው ተብለው በተሳሳተ መንገድ የሚታመኑ አንዳንድ ጉዳዮችን ቤተክርስቲያን እየተጠባበቀች እና እንዲህ ባሉ መላምቶች ላይ እያተኮረች፣ እነዚህ ጉዳዮች እስካሁን ገና ሲሆኑ ስላላየሁ፣ ክርስቶስ እስካሁን አልተመለሰም ስትል ደምድማለች። ከነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
(ሀ) ጌታ ዳግም ሲመጣ ኃጢአት ጨርሶውኑ መጥፋት አለበት፣ አሁን ግን ኃጢአት ያለ በመሆኑ ጌታ አልመጣም፤
(ለ) በዚያን ሰአት ክርስቲያኖች ሁሉ ጥርግ ብለው ከምድር ወደ ሰማይ መሄድ አለባቸው፣ አሁን ግን ክርስቲያኖች በምድር ስላሉ ጌታ አልመጣም፤
(ሐ) ለአንድ ሺህ አመት ክርስቶስ በምድር ላይ በገሃድ ነግሶ አስተዳደሩን ከኢየሩሳሌም ማድረግ አለበት፣ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ጌታ አልመጣም፤
(መ) እስራኤል ዘሥጋ እንደገና የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ መሆን አለባቸው፣ እነርሱ ገና መዳንን ስላልተቀበሉ ጌታ አልመጣም፤
(ሠ) ይህ ተዳሳሽ ሰማይ እና ተዳሳሽ ምድር ፈጽሞ በእሳት ተቃጥሎ መጥፋት አለበት፣ ይህ ግዑዝ አለም ገና አንዳችም ባልሆነበት ሁኔታ ጌታ አልመጣም፤
(ረ) ከዚያ ኹነት በኋላ ማንም አማኝ በምድር ላይ እስከማይታይ ድረስ ቤተክርስቲያን ተነጥቃ ሁሉም በአንድ ጊዜ ወደ ሰማይ መሄድ አለባቸው፣ ገና ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ጌታ አልመጣም፤
(ሰ) በአለም ላይ ላሉ ሰዎች ሁሉ የመዳን እድል ድንገት መዘጋት አለበት፣ አሁን ግን ሰዎች እየዳኑ ስለሆነ ጌታ ገና አልመጣም፤
(ሸ) ሰዎች ሁሉ እያንዳንዳቸው በህይወት ዘመናቸው ለሰሩት ሥራ ክርስቶስ ሊፈርድባቸውና ሁሉም የሥራቸውን ዋጋ መቀበል አለባቸው፣ ይህ ደግሞ አሁንም ሰዎች በምድር ላይ እይኖሩ በመሆኑ ጌታ ገና አልመጣም፤

ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 አመታት እውነት መስሏት አቅፋ የያዘቻቸውና፣ በ70 አም ላይ አስቀድሞ የተፈጸመውን የክርስቶስን የዳግመኛ ምጽአት ፓሮዥያ  በተመለከተ በእግዚአብሔር ቃል ያለውን ንጹሁን ትምህርት በሚያሳዝን ሁኔታ የጋረዱ፣ ብሎም የገደቡ ሌሎች በርካታ ከንቱ የሆኑ መላምታዊ እሳቤዎችን ነቅሶ ማውጣት ይቻላል። ሌላው ቢቀር በፕሪቴሪዝም የሚያምኑ እና "ከፊል ኃላፋውያን" በመባል የሚጠሩ ወገኖችም እንኳ እንዲህ ባሉ መላምታዊ የልማድ አስተሳሰቦች ተይዘው የትንቢትን ሙሉ ፍጻሜ አጥርቶ ከማየት ዘግይተው ይታያሉ። እነርሱም የፓሮዥያውን "ባህርይ ተፈጥሮ" በተሳሳተ መንገድ ከ"ጊዜው" በፊት አስቀድመው በማየት የተቸገሩ ናቸው።

የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት በግልጽ ለመረዳት መሰረታዊው ነገርና ከሁሉ በፊት የሚቀድመው መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የንባብ ክፍል በወጉ፣ በተጻፈበት አውድ ማጥናትና መረዳት ነው። ያኔ ብቻ የፓሮዥያው ባህርይና ተፈጥሮ ምን ምን እንደሚያካትት ለመወሰን የምንችል እንሆናለን። የትኛውንም የቅዱሳት መጻህፍትን ትምህርት በትክክል ለመረዳት አውደ ምንባቡን ማወቅ ተጨማሪ ነገር ሳይሆን ዋናና አስፈላጊ ጉዳይ ነው። 

ከ70 ዓም በኋላ በመንፈሳዊው መንግስት፣ በአዲሱ ኪዳን ወንጌል ውስጥ የምንኖር እኛ ክርስቲያኖች፣ በተለያየ የእምነት ብስለት፣ ጥልቀትና ስፋት ልንገኝ እንችል ይሆናል። ሁልጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ቃል አዲስ ነገር እየተማሩ የሚሻረውን ሽረው የሚጸናውን አጽንተው ወደፊት የሚራመዱ የቃሉ አማኞችና ተማሪዎች ይኖራሉ። ፕሪቴሪዝም ወይም የተፈጸመው ወንጌል ብለን የምንጠራው የትንቢት ፍጻሜ በልብ ስፋት ልንማራቸው ከሚገቡ ከነዚህ አዳዲስ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

ጥቂት በማይባሉ ባለፉት አመታት ነገረ ፍጻሜን ለማጥናት ባገኘሁት እድል ስለ ፕሪቴሪዝም የገባኝ አንድ እውነት ቢኖር በትህትና ተማሪ ሊያደርገኝ ከአውቃለሁ ባይነት ሰረገላ ላይ አውርዶ በቃሉ እግሮች ስር እንድቀመጥ ማስቻሉን ነው። ሁላችንም አንድ ወይም ሁለት ነገር እናውቅ ይሆናል፣ ይህንን ወይም ያንን ተረድተን ሊሆን ይችላል። ማናችንም ብንሆን ግን ሁሉን የምናውቅና መማር የበቃን አይደለንም። ከሁሉ የሚሻለው መንገድ ግን የፍቅርና የትህትና መንገድ ነው። ሁላችንም ተጋጥመን ባለንበት በክርስቶስ አካል እርስ በርሳችን እንዋደድ እንጂ፣ በመሰረታዊው የክርስትና አስተምህሮዎች ላይ እስካልተለያየንና ለኃጢአት ልምምድ በር የሚከፍት አካሄድ እስከሌለ ድረስ፣ "ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል" በማለታንም ሆነ በማናቸውስ ጉዳይ ቢሆን በልብ ስፋት እና በወንድሞች ሕብረት ለመነጋገር ለምን ይከብደናል? እያንዳንዱ ሰው በግሉ ያለ ገደብና ክልከላ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያጠና እና በክርስቶስ እውቀት ያድግ ዘንድ፣ በሚያስብና በሚጠይቅ ንቁ የክርስቲያን አእምሮ እንዲመራመር መፍቀድና አንዳችን ሌላውን ማደፋፈር ይጠበቅብናል። ሃሳቤን የማጠቃልለው ሐዋርያው ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተናገረው የመጨረሻ መልዕክቱ በመጥቀስ ይሆናል፦

"ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።" (2ጴጥሮስ 3፥ 18)

"የፕሪቴሪዝም አመለካከት ምንድን ነው?" የሚለውን ጽሁፍ በተጨማሪነት ለመመልከት እነሆ ሊንኩ፦ 
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/blog-post.html

(gkr)

Thursday, May 2, 2019

ግርማን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት

ግርማን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት!

ኢየሱስ ወደ ሰማይ የማረጉ ትርክት በግልጽ የተብራራው በሉቃስ ወንጌል ላይ እና ሉቃስ በጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ነው። ሉቃስ በወንጌሉ ምዕራፍ 24፥ 51 ላይ "ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።" ሲለን፣ ከዚህ ባለፈ አብራርቶ ስለ ዕርገቱ የነገረን በሐዋርያት ሥራ 1፥ 6-11 ላይ በሚገኘው ገለጻ ነው። በዚህ የእርገት ትዕይንት ውስጥ የምናየው ዋነኛ ስዕል ከሁሉ በላይ የመሆንን ስዕል ነው። ኢየሱስ ያረገው ከምድር ወደ ሰማይ ሲሆን፣ የሚያመለክተውም ከአንድ የአኗኗር ሁናቴ ወደ ሌላው የተደረገውን ሽግግራዊ እንቅስቃሴ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኤፌሶን 4፥ 8 እየሱስ ሲያርግ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያብራራ፣ ቆላስይስ 3፥ 1-2 ደግሞ ወደ ላይ ያረገውን ክርስቶስን ከቦ በላይ ያለው ነገር በታች በምድር ካለው ጋር በተቃርኖ ሲነጻጸር እናያለን፤ በዚህም ዕርገቱ በአጠቃላይ የዋጆአዊው ሥራ ላይ ያለውን ከፍተኛ ትርጉም እንረዳለን።
አስቀድመን፣ ጌታ ኢየሱስ ከእርገቱ ቀደም ብሎ ለደቀ ምዛሙርቱ የነገራቸውን ተስፋ እና እርገቱ በምን ሁኔታ እንደተፈጸመ የሚያመለክተንን የሉቃስን ምስክርነት እንይ፦

"ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ፤ ይህንንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።" (ሐዋርያት 1፥ 8-11)

ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ወደ አብ ከማረጉ አስቀድሞ በነበሩት አርባ ቀናት፣ በኢየሩሳሌም በልዩ ልዩ ስፍራ እየታየ ለተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ይገለጥ ነበር። እነርሱም እርሱ ሕያው እንደሆነ እና ከመቃብር እንደተነሳ ከእርሱ በሚሰጣቸው ማረጋግጫዎች ያውቁ ነበር። በእነዚያ አርባ ቀናት ከሐዋርያቱ ጋር እየተነጋገረ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ይነግራቸው ነበር። ለምሳሌ ዮሐንስ በወንጌሉ ሲዘግብ፦ "ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው። ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት" ሲል ይጽፋል (ዮሐንስ 20፥ 16-17)።

ክርስቶስ ከመስቀል ሞቱና ከትንሣኤው በኋላ በመጀመርያ የታየው ለመግደላዊት ማርያም መሆኑን ይህ ትራኬ ይነግረናል። እርስዋም ባየችውና ባወቀችው ጊዜ ወደ እርሱ ስትንደረደር፣ እርሱ ግን ገና ወደ አባቱ ስላላረገ  እንዳትነካው ይነግራታል። ይፋዊ የሆነው ዕርገቱ ከአርባ ቀናት በኋላ እንደተፈጸመ ከላይ የተጠቀሰው የሉቃስ ዘገባ ግልጽ ያደርግልናል። ማርያም ግን ራሱን በገለጠላት ጊዜ ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ ወደ አባቱ የሚያርግ መሆኑን እንድትነግራቸው አስቀድማ ተልካለች። "ዓርጋለሁ" የሚለው የኢየሱስ ማስታወቂያ የሚያመለክተው ኢየሱስ ወደ አባቱ ለማረግ በሂደትና በዝግጅት ላይ የነበረ መሆኑን ነው። ከዚያም በኋላ ራሱ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ቢታንያ ወደሚባል ስፍራ ውሰዳቸው፣ በዚያም ከእነርሱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ወደ ላይ ተወስዶ ወደ አባቱ ዐረገ።

"እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።" (ሉቃስ 24፥ 50-53)

ለደቀ መዛሙርቱም ከእርገቱ በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ተስፋ ስጥቶአቸዋል። በኢየሩሳሌም ፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቹ እንደሚሆኑ ነግሮአቸዋል። እርሱም ተለይቶ ወደ ላይ ሲሄድና ሲወሰድም ትኩር ብለው ይመለከቱ ነበር። ሁኔታውን ስንመለከት ጉዳዩ ልክ በደመና ተጋርዶ እንደሚሰወር ሰው ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ኹነቶች የተከበበ ነው፣ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ስትቀበለው ያዩ ነበር። እርሱ ወደሄደበት ወደ ሰማይ አሻቅበው እየተመለከቱ ሳሉ ያኔ ሁለት መላዕክት ተገልጠው ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ እንዲሁ፣ ማለትም "በደመና" ተመልሶ እንደሚመጣ ነግረዋቸዋል። (በዚህ የሐዋርያት ሥራ 1፥ 11 ላይ የቀረበው ዘገባና ስለጌታ ምጽዓት ባህርይ የተነገረ ቃል እንዴት መተርጎም እንዳለበት የዳሰስሁበትን ጽሁፍ ጨምራችሁ ትመለከቱት ዘንድ ግብዣዬ ነውና እነሆ ሊንኩ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/02/1-9-11.html?m=1

ቀጥሎም፣ አካላዊ ከሆነው የዕርገቱ ኹነት ባልተናነሰ ከዕርገቱ ጋር የተገናኙና ዕርገቱን ከበው የሚገኙ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮችን ጨምረን ማንሳት እንችላለን። በመጀመርያ፣ ይህ የዕርገቱ ኩነት የሚያመለክተው የአንድን ጉዳይ ወሰን እና የሽግግር ሁናቴ ነው። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው፣ ዕርገቱ በሉቃስ ወንጌል መጨረሻው ላይ ሲዘገብ የኢየሱስን ምድራዊ የኑሮ ምዕራፍ መዘጋቱን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ሲዘገብ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ ኢየሱስን የመተካቱን ጅማሬ ያመለክታል። ዕርገቱ የክርስቶስን ወደ ምድር ወርዶ በስጋ የመምጣቱን ታሪካዊ እውነት ልክ እንደ ፊደል U ቅርጽ ወደታች የወረደውን መልሶ ወደ ላይ በማውጣት ዑደቱን ግልጽ የሆነ የመጠናቀቅና የፍጻሜ መልክ የሚሰጠው ነው። ኢየሱስም በሥጋ ወደ አለም የመጣበትን አላማ ሙሉ የሚያደርግ ታሪካዊ ሃቅ መሆኑንም ጨምረን እናስተውላለን። በዮሐንስ 6፥ 62 ኢየሱስ ስለ ዕርገቱ ሲናገር "እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?" ሲል ይጠይቃል። ኤፌሶን 4፥ 10 ደግሞ "ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።" ሲል የዕርገቱን ከፍታ ይነግረናል።

አስከትሎም፣ ዕርገቱ ከፍ ከፍ የማለት ዋነኛ መገለጫ ሆኖ አጠቃላይ የሆነ አወንታዊ ትርጉምን የሚያጎናጽፈው ከፍተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ መሆኑን ያመለክታል። በዚህም ውስጥ ያለው አብይ ትርጉሙ መክበር ነው። እንደ ትንሣኤው ሁሉ የኢየሱስ ዕርገትም የመለኮታዊ ማንነቱ መገለጫው ሲሆን ዋጆአዊ የቤዛነቱን ስራ ብቃትም የሚያረጋግጥ ነው። የክርስቶስ የመክበር ኹነቶች በዝርዝር በተብራሩበት የ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥ 16 የጥንት ቤተክርስቲያን የዝማሬ መድብል እንደተገለጸው የክርስቶስ ከፍተኛውና የመጨረሻው ኹነት "በክብር ያረገ" የሚለው ስንኝ ነው። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጋር የተያያዙ ሌሎቹም አምሳያዎች አጽንዖት የሚሰጡት የመክበርን ሁናቴ ነው። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የመቀመጥን ከፍተኛውን የክብር ስፍራ መውሰዱን እናስተውላለን። ማርቆስ ዕርገቱን አስመልክቶ በምዕራፍ 16፥ 19 ላይ  "ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።" ይለናል። ( ኤፌሶን 1፥ 20፤ ቆላስይስ 3፥ 1፤ ዕብራውያን 1 ፥ 3፤ 8፥ 1፤ 10፥ 12፤ 12፥ 2)። ሰማዕቱ እስጢፋኖስም ሰማይ ትከፍቶለት ያየውን አስገራሚ  ትዕይንት በሐዋርያት ሥራ 7፥ 55-56 ላይ ሲመሰክር "መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ" ነው ያለው። ያ ቀኝ የኃይልና የስልጣን ሁሉ የመጨረሻው ከፍታ ነው። ከሙታን ተነስቶ ያረገው ክርስቶስ የተቀዳጀውን ከፍታ ሐዋርያው ዻውሎስ እንዴት እንደሚገልጠው ተመልከቱ፦ "ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤" (ኤፌሶን 1፥ 21)።

እንዲሁም፣ በዕርገቱ ውስጥ ከክርስቶስ መክበር ጋር ግንኙነት ያለው ሌላው ጉዳይ ደግሞ በክፉ ኃይላት ላይ እና በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ እርሱ የተቀዳጀው ንጉሳዊው ድል ነሺነቱ ነው። ይህም በመዝሙር 68፥ 18 ውስጥ "ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ" የሚለው ነው። የመዝሙሩ አውደ ምንባብ እንደሚያረጋግጠው ድል ነሺ ንጉስ በውጊያ ነጥቆ ይወሰዳቸውን ምርኮኞቹን ይዞ በድል አድራጊነት ግርማ ወደተራሮች ከፍታ ላይ የመውጣቱን ስዕል በጉልህ የያዘ ነው። ይህ መዝሙር በኤፌሶን 4፥ 18 ላይ "ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ" ተብሎ ሲጠቀስ ቃሉ የሚዛመደው ክርስቶስ በድል አድራጊነት ግርማው ላደረገው ሥራ ነው። ጌታ ኢየሱስ በዕርገቱ አእላፋት ምርኮኞችን አስከትሎ ወደ ላይ ወጥቶአል። በሌላ መልኩ ደግሞ፣ በዚህ አለም በእኩይና ሰናይ መካከል በሚካሄደው የማያቋርጥ ግጭት ውስጥ፣ በእምነት የምናውቀው ክብርን የተሞላው የክርስቶስ ዕርገት የሚያረጋግጠው "ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዝቶለታል"፣ "ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶታል" (ኤፌሶን 1፥22)፣ ተብሎ እንደተጻፈ፤ አሮጌው አይሁዳዊ የሞት ሥርዓትም ይሁን ወይም ዘምኛለሁ የሚለው የግሪኮ ሮማ አህዛባዊ አምልኮተ አማክልክት፣ ማናቸውም ቢሆን ክርስቶስ ከእግሩ በታች አድርጎ ያልገዛውና የማይቆጣጠረው ቤተክርስቲያንን ሊቃወም የሚችል ኃይል ያኔም አሁንም የሌለ መሆኑን ነው። እርስዋን ሊቋቋም የሚችል ምንም የገሃነም ሃይል የለም።

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ የምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ መሆኑን እንደሚያመለክት ሁሉ፣ ጨምሮም እንደገና ምድርን ለመጎብኘት ተመልሶ እንደሚመጣ ካለው ዝግጁነት ጋርም የተያያዘ ነው። ወደ ሰማያት የወጣው ለሺህ ዘመናት ሊከርም ወይም ሳይመለስ በዚያው ሊቀር ሳይሆን ይልቁንም በዚያ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በጽኑ ሥደትና መከራ ውስጥ ለምታልፈው ቤተክርስቲያኑ "ቶሎ" ሊመጣ ነው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደው ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ተከትለው ወደዚያው ይሄዱ ዘንድ ስፍራ ለማዘጋጀት ነውና። "ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ" (ዮሐንስ 14፥ 2-3)።  ያረገው ክርስቶስ በክብር መገለጡ የሚጠበቅ የነበረውን ያህል የአማኞችም የክብር መገለጥ እርሱን ተከትሎ የሚሆን ነበር "ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ" (ቆላስይስ 3፥ 4)።

እንግዲህ ይህ አስገራሚ የሆነ የዕርገቱ ዘገባ፣  "ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 28)፣ ተብሎ እንደተጻፈ፣ በዚያው ትውልድ ዘመን ይኸውም በ70 ዓ.ም ለተፈጸመው ዳግመኛ ምጽአቱ (parousia) የተነገረ ማጣቀሻን የያዘ ነው። "ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል" (ሐዋ 1፥ 11) የሚለው የሉቃስ ዘገባም ከዚህ ጋር ይስማማል። ያድናቸው ዘንድ ሲጠባበቁት የነበሩት በዘመናቸውና በትውልዳቸው እንደሚመለስ ተስፋ የተገባላቸው፣ "እናንተ ሲሄድ ያያችሁት" የተባሉት ራሳቸው ናቸው፣ የሚመጣውም ለእነርሱው ነው።

ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲጽፍ፣ "ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤" (1ኛጴጥሮስ 3፥ 18-19) ይላል። የቤዛነታቸውን ቀን እየጠበቁ በሲኦል ወኅኒ የነበሩትን ሙታን እርሱ በሞቱ በፈጸመው ቤዛነት ከዚያ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባቸው ዘንድ የምስራቹን ሰበከላቸው። ክርስቶስ ወደ ሲኦል እንደወረደና ወደ ሰማይ እንደወጣ የጥንት ቤተክርስቲያን ማመንዋ በእግዚአብሔር ቃል የሚደገፍ እውነት ሲሆን፤ በእምነት መግልጫዎቻቸውም "...በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን መከራ በተቀበለ፣ በተሰቀለ፣ በሞተ፣ በተቀበረ፣ ወደ ሲኦል በወረደ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን በተነሳ፣ ወደ ሰማይም በወጣ፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በተቀመጠ፣ በህያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ከዚያ በሚመለስ...እናምናለን" ሲሉ እምነታቸውን ያስታውቁ እንደነበር ታሪካዊ ድርሳናት ያመለክታሉ። በዚህ ምስክርነታቸው ለእነርሱ ኃላፊና መጻኢ የነበሩ ኹነቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፣ ጌታ ግን እንደሰጣቸው የተስፋ ቃል በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በክብር የተመለሰ በመሆኑ በዚህ የታመነ ምስክርነት ውስጥ ያለው የመመለሱ መጻኢ ተስፋ ዛሬ ለእኛ ኃላፊ ሆኖአል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ገና በ63 ዓ.ም ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ፣ "ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው" (ኤፌሶን 4፥ 8-10) ይላል።

ከዚህ ሃሳብ ክርስቶስ "ሁሉን ይሞላ ዘንድ" ወደ ታች (ሃደስ) ወርዶ፣ በዚያ ለነበሩ ምርጦች ቅዱሳኑ፣ እርሱ ሕያው መሆኑን ምረጋገጫ ሰጥቶ እንደሰበከለቸውና፤ ከአርባ ቀናትም በኋላ በእርገቱ ወቅት ከዚያ ማርኮ ወደላይ እንዳወጣቸው፣ እርሱም ከፍ ከፍ ብሎ 'ዩም ኪፑር' የተሰኘውን የማስተሰርያውን ስራ ሊያጠናቅቅ በሰማያዊው ቤተመቅደስ ወዳለችው ሰማያዊት ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ከዚያ እስኪወጣ ድረስ በሰማያዊው ስፍራ በአውደ ምህረቱ ደጃፍ አከማችቶ እንደሰበሰባቸው እናስተውላለን።

ከሁሉ በላይ ሆኖ ከላይ የመጣው እርሱ አስቀድሞ ወደ ሙታን መቃብር ወደታች ወረደ፣ የወረደው እርሱ "ሁሉን ይሞላ ዘንድ" ከሰማያት ሁሉ በላይ ሲወጣ ግን የወጣው ብቻውን ሳይሆን፣ ይልቁንም ለምርጦቹ በአባቱ ቤት ስፍራን ያዘጋጅላቸው ዘንድ ምርኮውን ሰብስቦ ይዞ ወጣ።

ይህንን የሚያስተምር መጽሐፍ ቅዱሳችን ለአማኞች የሕይወት ተዛምዶን ያቀርብልናል። እኛ በክርስቶስ ያመንን አማኞች በእርሱ ከማመናችን የተነሳ ብቻ "ከእርሱ ጋር ተነስተን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር ተቀምጠናል" (ኤፌሶን 2፥ 6)፤ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ደግሞ እንድንሻ ጥሪ አለን፣ (ቆላስይስ 3፥ 1)

ነብዩ ኢሳይያስ ህማማተ ክርስቶስን ባስተማረበት ትንቢቱ ስለክርስቶስ ምርኮ ሲናገር፦ "እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።" (ኢሳይያስ 53፥ 10-12 ) ሲል ይመሰክራል። ከኃያላን ጋር ምርኮን የሚከፋፈል እርሱ ድል የነሳ ብቻ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ድል ነስቶአል፣ "እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር ….. ድል ነሥቶአል " (ራእይ 5፥ 5)

ጌታ በመስቀል ነፍሱን ሲሰጥ ከሆኑ አስገራሚ ክንውኖች መካከል በወንጌላዊው ማቴዎስ ዘገባ መሰረት የመቃብር መከፈትና ከሙታን ብዙዎች መነሳታቸው ሲሆን እነርሱም ከትንሳኤው በኋላ በኢየሩሳሌም ለብዙዎች መታየታቸው ነው። "ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።  እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤  መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።" (ማቴ 27፥ 50-53)

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሞት፣ መቃብርና ሲኦል የተሰኙ ኃያላን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ሙታናቸውን እስከ ወዲያኛው የተነጠቁት ክርስቶስ በነፍሱ ድካም። "ወደ ምድር ታችኛ ክፍል" ወርዶ በከፈለው ዋጋ ነው። ዮሐንስም በራእዩ ያየውን ሲመሰክር፦

"ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።  በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ" (ራእይ20 11-15) ይላል።

ይህ የሕይወት መጽሐፍ ምን እንደሆነ፣ በውስጡ የተጻፉትንና የሚድኑትን፣ ከመቃብር የሚነሱትንና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚገቡትን በተመለከተ ነብዩ ዳንኤል በትንቢቱ ሲናገር "በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።" (ዳንኤል 12፥ 1-2) ይላል። ይህንንም ያስተማርሁበትን ጽሁፍ ለማንበብ ከወደዳችሁ እነሆ ሊንኩ፦
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/01/12.html?m=0
(gkr)