“የአሁኑ” እና የሚመጣው ዘመን
“የአሁን ዘመን”
“በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤” (1ቆሮንቶስ 2፥ 6-8)
መጽሐፍ ቅዱስን በአውዱ፣ በቋንቋው፣ በታሪካዊነቱ ለመተርጎም ትጋት የማያደርጉ፣ ይልቁንም እድሜ ዘመናቸውን ሲሰሙትና ሲመስላቸው በኖረው ልማዳዊ አመለካከት ብቻ የሚያስቡና ምንም ልምምዱ የሌላቸው ወገኖች እንዲህ ያለውን ጥቅስ ሲያነቡ በተለይ “የዚች ዓለም” የሚለውን ሃረግ በቀጥታ ከዚህ ‘ግዑዝ አለም’ ጋር አገናኝቶ በመረዳት ሲሳሳቱና ሲያሳስቱ ይስተዋላል። ወደ በኩረ ቋንቋውና ወደ ተለያዩ ትርጉሞች ግን ስንመለከት ጉዳዩ ከአንድ የተለየ ”ዘመን” ጋር እንጂ ከዚህ ነባራዊና ተዳሳሽ ግዑዝ አለም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እናስተውላለን። በአማርኛችን “አለም” በKJV “world” ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጧ የገባው ቃል ከበኩረ ቃሉ ጋር እንደማይስማማና ትክክልኛውን ትርጉም እንደማይመጥን በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። እኛ በቋንቋችን “አለም” የምንለውን የግሪኩ ቃል “cosmos” ሲል ይጠራዋል፣ ቃሉም የሚወክለው ይህንን ግዑዝ አለምና በውስጡ ያለውን ሁሉ ነው። እዚህ ጥቅስ ላይ እና በበርካታ ሌሎች የንባብ ክፍሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ባዘጋጁአቸው ቅጅዎች በግሪኩ አለም ወይም cosmos የማይለውን ሁሉ ያለጥንቃቄ አለም ሲሉ ተርጉመውታል። ለአውደ ምንባቡ የሚመጥነውና ትክክለኛ የሆነው የግሪክ ቃል ግን “aion” የተሰኘው ነው፣ ትርጉሙም “ዘመን” የሚል ነው። በስትሮንግስ የግሪክ ቃላት መፈለጊያ #165 aion ለሚለው ቃል የተሰጠው ማብራርያ ይመለከቷል፦
የግሪኩ “aion” ዘመን ማለት ሲሆን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን የአይሁድ አለም የሚያመለክት ቃል ነው፣ ይህ የአሁኑ አለም በተለይ የአይሁድን አለም የሚያመለክት ሲሆን፣ እርሱም የሙሴ ስርዓት ይሰለጥናበትና ይገዛበት የነበረው አላፊውና ጊዜአዊ የሆነው፣ ዘላለማዊነትም የሌለው የሕጉ ዘመን ነው። መጻኢ ሆኖ ሲጠበቅ የኖረው ደግሞ (ለእነርሱ) የወደፊቱ አለም፣ መሲሐዊው ዘመን፣ ዘላለማዊው መንግስቱ ነው፣ እርሱም ለአለምና ለዘለዓለም ማለቂያ የሌለውን የጸጋ ዘመን ያመለክታል።
“እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው?” (ሉቃስ 12፥ 56)
“ይህ ዘመን” የተሰኘው ሀረግ የሚያመለክተው ከ70 ዓም በፊት የነበረውን ዘመን ነው። ይኸውም ከአሮጌው ኪዳን በታች ተገዝቶ የኖረው የአይሁድ ዘመን ነው። ክርስቶስ የተሰቀለው፣ የአይሁድ ገዦችና የማያምኑ ሁሉ ከኢየሩሳሌም ከተማ እና ከመቅደሱ ጋር በ70 ዓም ተደምስሰው እንዲጠፉ የተደረጉት “ይህ ዘመን” እየተባለ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው። ይህ ዘመን እየተባለ በሚጠራው ዘመን መጨረሻ ላይ ፍርድ ይሆናል። “እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 13፥40) ይህ የአለም መጨረሻ የፕላኔት ምድር መጨረሻ፣ የሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ አይደለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ ይህ ግዑዝ አለም መጨረሻ እንዳለው የሚያስተምር ጥቅስ ማግኘት አይቻልም። እግዚአብሔርም ይህንን ተዳሳሽ አለም የማሳለፍና የማጥፋት ምንም እቅድ የለውም። ይልቁን ግን ይህ የአለም መጨረሻ የተሰኘው ሀረግ የሚያመለክተው መጨረሻ የተመደበለትን የአይሁድ አለም እርሱም አሮጌው የሙሴ ሥርዓት ማብቂያን ነው። አዲሱን አለም ለማምጣት አሮጌ ለሆነው ለዚህ አለም የተመደበለትን ፍርድ ቃሉ ሲያስተምር፦ “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል” (ዕብራውያን 8፥ 13) ይላል። ይህ ፍርድ የሚከናወነውም በ70 ዓም ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ በፓሮዥያው ነው።
ደቀመዛሙርቱ በደብረዘይት ተራራ ላይ ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው የጠየቁት ጥያቄ የመምጣቱና የዘመኑ ፍጻሜ ምልክት ምን እንደሚሆን ነበር (ማቴዎስ 24፥ 3)። በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ “ይህ ዘመን” የሚባለው፣ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፓሮዥያው የሚደመደመው አሮጌው የአይሁድ ዘመን ነው። ፍጻሜውንም ያገኘው በ70 ዓም ላይ ኢየሩሳሌምንና ቤተመቅደሱን በማፍራረስ ነው። ይህ ሁሉ ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ ትውልዳቸው እንደማያልፍ ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” ሲል አረጋግጦ ነግሮአቸዋል (ማቴዎስ 24፥ 34)። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው፣ አይሁድም በቅዱሳት መጻህፍቶቻቸውና በነብያቱ አቡቀለምሲሳዊ ንግሮቻቸው የሚያውቁት የአለም ፍጻሜ፣ ቤተመቅደሱና ቅድስት ከተማቸው ኢየሩሳሌም የሚደመሰሱበት፣ የሙሴ ዘመን ማብቂያና ፍጻሜ ነው እንጂ፣ ብዙዎች እንደሚመስላቸው የፕላኔት ምድር እና የሰማይ መጥፋት፣ የሰው ልጅ ታሪክ ማክተም ጨርሶ አይደለም።
ክርስቶስ በፓሮዥያው በ70ዓም የሚመጣው በዘመኑ መጨረሻ የቅዱሳኑን ድነት ፍጹም አድርጎ ሊያጠናቅቅ ነው። እጅግ ከመጠን በላይ ሥደትን እየተቀበሉበት ከነበረው ከዚያ ክፉ ከሆነ የአይሁድ ዘመን (ዓለም) ቅዱሳኑን ያድናል።
“ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።” ገላትያ 1፥ 3-4
"የሚመጣው ዘመን"
“በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።” ማቴዎስ 12፥ 32
የሚመጣው ዘመን የሚለው የሚያመለክተው ከ70 ዓም በኋላ ያለውንና ማለቂያ የሌለውን የአዲስ ኪዳን ወንጌል፣ የመንግስት ዘመን ነው። መንግስቱም በክርስቶስ ቤዛነት አምነው ዳግም የተወሉዱትን ክርስቲያኖች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውን ድነታቸውን ጠቅልሎ የያዘ መንፈሳዊ መንግስት ነው። እነሆ ከተጀመረ ከሁለት ሺህ አመታት በላይ ተቆጥሮአል እንጂ በርካታ መጻአኢያን እንደሚያስተምሩት ገና የሚጠበቅና እስካሁን ያልተጀመረ መንግስት የለንም።
በተጨማሪም ይህ የሚመጣው ዘመን ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠራው የዘመን ክፍል ከ70 ዓም በኋላም ቢሆን እንኳ፣ አምነው የዳኑ የእግዚአብሔር ምርጦችም ይሁኑ ወይም ገና በክርስቶስ ማመንን ገፍተው ያልዳኑና ያልመጡም ቢሆኑ እንኳ፣ በምድር ላይ በአካል የሚኖሩበት ዘመን ነው። አምነው የዳኑት የእግዚአብሔር ምርጦች ወደ አዲሱ ኪዳን መንፈሳዊ መንግስት እያንዳንዳቸው በግላቸው መንፈሳዊ በሆነ ዳግመኛ ልደት በመንፈስ የገቡ ናቸው።
አሁንም ገና በዚህ ህይወት እያሉ ይቅር የማይባለውን ኃጢአት በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚፈጽሙ ከመንፈሳዊው መንግስት ውጪ የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ የሚኖሩ እስከሆነ ድረስ ይህ “የሚመጣው ዘመን” ተብሎ የሚጠራው የዘመን ክፍል ሰማይ ማለት አይደለም። ይልቁንም ይህ የሚመጣው ዘመን ከ70ዓም በኋላ ያለውና፣ እኛ የሰው ልጆች በአካል በምድር ላይ አሁን በሥጋ እየኖርንም እንኳ በመንፈስ የሚሰራና የሚገዛ “የመሲሁ ዘመን” ወይም “የመንግስት ዘመን” ተብሎ ይጠራል።
ከ70ዓም በኋላ ያሉ ዳግም የተወለዱ አማኝ የእግዚአብሔር ምርጦች በሙሉ በዚህ የሚመጣው ዘመን ተብሎ በሚታወቀው የመሲሁ መንግስት በክርስቶስ ያለውን የዘላለም ሕይወት በሙላት ተቀብለዋል፤ እርሱም አሁን ነው። እያንዳንዳቸውም መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ሲሆኑ በግላቸውም በአዲሱ ኪዳን ወንጌል፣ በመንፈሳዊው መንግስት ውስጥ የእግዚአብሔር ካህናት ናቸው። “እርሱም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው።” (ሉቃስ18፥ 29-30)። የተቀበልነው የዘላለም ሕይወት አሁን ነው፣ ስለዚህ ያ “የሚመጣው አለም” ሲባልና ሲጠበቅ የነበረው የመንግስት ዘመን መጥቶአል ማለት ነው። የዘላለም ሕይወት የዚህ “የሚመጣው አለም” ስጦታ መሆኑ እርግጥ ከሆነ፣ በርካታ መጻኢያን እንደሚያስተምሩት ይህ አለም ደግሞ ገና ካልመጣ፣ እንግዲያውስ የዘላለምን ሕይወት ገና አልተቀበልንም፣ አሁንም ገና በአሮጌው ኪዳን ስር እንኖራለን ማለት ነው፤ አሮጌው ኪዳን ደግሞ ይገድለናል እንጂ በሕይወት አያኖረንም። አሳዛኙ ነገር አሮጌው ኪዳንም እንኳ ሊያስመካን አለመቻሉ ነው፣ ምክንያቱም በፍጥረት አህዛብ እንጂ አይሁድ ባለመሆናችን ለእነርሱ ከተሰጠው የሙሴ ሥርዓትና ከኪዳናቸው ምንም ድርሻ የለንምና። አሁን ግን ሲጠበቅ የነበረው ይህ የሚመጣው አለም የተሰኘው ዘመን በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት እነሆ ደርሶአል። የመሲሁም መንግስት መግዛት ጀምሮአል። እኛም በእምነት በኩል በጸጋው እየኖርንበት ነው። ከክርስቶስ ጋር በመንግስቱ ስንኖርም ዘላለማዊው ጥሪአችንና ተልዕኮአችን ራሳችን በክርስቶስ እያደግን፤ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ፤ ወንጌልንም በማዳረስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን እንድናፈራና ሌሎችን በክርስቶስ እውቀት እንድናሳደግ ነው። “መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን” (ዕብራውያን 6፥ 5) ተብሎ እንደተጻፈ፣ መንፈሳዊውንና ሊታይ የማይችለውን፣ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የቀመሱትንና ለእነርሱ “ሊመጣ ያለው” እየተባለ የተጠበቀውን፣ እኛም በዳግመኛ ምጽአቱ በሙላት የገባንበትን የክርስቶስን መንግስት መንፈሳዊ የሆነውን የጽድቅ ተጽእኖ በፍጥረቱ መካከል የምናደርገውም በዚህ ተልዕኮና ጥሪ በኩል ነው።
(gkr)
No comments:
Post a Comment