Wednesday, March 6, 2019

ሰዎች እግዚአብሔር በጽሁፍ የሰጠንን መገለጥ ከማጥናትና በቅዱሳት መጻህፍት ያለውን የመለኮት ምክር ፈልጎ ከማግኘት ይልቅ “በመንፈስ መመራት” ሲሉ በሚጠሩት ልምምዳቸው ላይ ሙጭጭ ይላሉ። ይህንንም ከሚያደርጉባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው፣ ቅዱሳት መጻህፍትን በወጉ፣ በአትኩሮትና ለዘወትር በሚሆን ትጋት የማጥናትን ሸክም ሰለሚወስድላቸውና ስለሚያስቀርላቸው ነው። የቅዱሳት መጻህፍትን ትምህርት ፈልጎ ማግኘት ለትጉሀን እንጂ ለሰነፎች የሚሆን ስራ አይደለም። በተጨማሪም ይህ ከአውዱ ነጥለው የሚያመናፍሱትና “በመንፈስ መመራት” የሚሉት ልምምዳቸው ከትችትና ከወቀሳም ፍጹም ነጻ የሚያደርግ ስለሚመስላቸውም ደግሞ ነው። ለምሳሌ በአንድ ጉዳይ አንድን አቋም ለመያዝ አንድን ግለሰብ መንፈስ በልዩ ሁኔታ የሚመራው ከሆነ፣ ወይም አንድን ተግባር ለመፈጸም ያን ሰው መንፈስ የሚናገረውና የሚያናግረው ከሆነ፣ ታዲያ መንፈስን ሊጠይቅና ሊተች የሚደፍር ምን አይነት ሰው ሊኖር ይችላል? እነዚህ “መንፈስ ተናገረኝ” ወይም “መራኝ” የሚሉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ “መንፈሳዊ ምሪት” የሚባል የማይጠየቅ ሌላ ስልጣን አቁመዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እውነተኛው በመንፈስ የመመራት ጸጋ በዳግመኛ ልደት የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ ሁሉ ያለ ልዩነት የተቀበሉት እንጂ፣ እንደ ዛር ውላጅ በጥቂት ብርቅዬ “ቅቡዓን” ላይ መጥቶ የሚሰፍር ውቃቢ አይደለም። “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና” (ሮሜ 8፥ 14) እንደተባለ፣ በመንፈስ መመራት ከሕጉ አርነት ወጥተን፣ አባ አባት ብለን በምንጮኽበት የልጅነት መንፈስ መመላለስ ነው እንጂ፣ በእያንዳንዱ የግልና ማህበራዊ ጉዳይ ድምጽ እየሰማን፣ “ታየኝ”፣ “ተገለጠልኝ”፣ የምንልበት “ጌታ ስለ አንተ/ ስለ አንቺ የተናገረኝ እንዲህና እንዲህ ነው” እያልን የሰዎችን ህይወትና ትዳር የምናመሳቅልበት “ልዩ ምሪት” አይደለም። አዲስ ኪዳን እንደሚያስተምረው ከህጉ አርነት ወጥተሃልን? ያ በሕይወትህ ከሆነ፣ በቃ አለቀ፣ አንተ በመንፈስ የምትመራ ልጅ ነህ። ከዚህ የተለየ በመንፈስ መመራት የሚባል የቅዠተኞችን ህልም አትመኘው፣ አያስፈልግህም። እነዚህ ቃሉን ለማጥናት በእጅጉ ዳተኞች የሆኑ ሰባኪ ነን ባዮች ግን አለን የሚሉትን “ሥነ መለኮት” ለመከላከልም ሆነ፣ በትምህርታቸውና በልምምዳቸው ላይ የሚቀርበውን የሰላ ትችት ለማስተናገድ አቅምም ሆነ የቃሉ ዝግጅት የላቸውም። በገጽታ ግንባታ ፍቅር ሰክረው ራሳቸውን ከሰቀሉበት “የእግዚአብሔር ሰው” በመባል ሰረገላ ላይ ተቀምጠው ቀርተዋል። በትህትና ተማሪ ለመሆን አይወርዱም። ሰዎች ስለ እነርሱ ከፍ ያለ አስተሳሰብና ግምት እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ፣ በጽሁፍ የተገለጠውን ብቸኛ የእግዚአብሔር መገለጥ አሳሳችና እጅግ አደገኛ ለሆነ “ውስጣዊ የመንፈስ ምሪት” ሲሉ አንቅረው ጥለውታል። ብቸኛ መልዕክታችን በሆነው በንጹሁ ወንጌል ስላፈሩ ሌላ ተጨማሪና እላፊ ብርሃን እየፈለጉ፣ በምዕመናኑ ላይ ሊነግሱባቸው በየምስባኩ ይቃዣሉ። እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ ባዶ ለሆነ የሰብአዊ ትእቢትና ኩራት ያጋልጣል። እነዚህ ሰዎች በቃሉ ብርሃን መመርመርን እና መመራትን እምቢ ያሉ ናቸው። “በመንፈስ መመራት” በሚሉት ጭምብል ውስጥ የተሸሸጉና ያለ እግዚአብሔር ቃል የቀሩ እነዚህ ምዋርተኛ “ነብያት” (fortune tellers) ምን እያደረጉ እንደሆነ እንኳ ሳያውቁ “ትባረካለህ፣ ትጠረምሳለህ” በሚል ባዶ ጩኸት ምዕመናንን “ዕድል” ለተባለ ሌላ አምላክ እንዲያጥኑ ያስቱአቸዋል። ብዙዎችም እንዲህ ያለውን የስኬትና የእድል ትምህርት መስማት ስለሚወዱ ነብያቶቻቸውን ሲያዳምጡ የእግዚአብሔርን ራድዮ ጣቢያ ያገኙ ይመስላቸዋል እንጂ የሟርተኛ ነብያቶቻቸው መነገጃ መሆናቸውን እንኳ አያውቁም። እግዚአብሔር  ግን ፈቃዱን ለማወቅ በብዙ ትጋት የሚጠና መጽሐፍ እንጂ ራድዮ ጣቢያ አልሰጠንም። መቼም በአንዱ ስህተት አፍረን ተሸማቀን ሳንጨርስ ሌላው አሸማቃቂ ነውራቸውን ለጸሐይ እያሰጡ ”አይኔን ግንባር ያርገው፣ ተገልጦልኝ ነው” በሚል መከላከያ የመድረክ ትወናቸውን ይቀጥላሉ፤ ታዳሚ ተመልካች ምዕመናኑም ያጨበጭባሉ እንጂ አይጠይቁም። እነሱ ከተገለጠላቸው ታዲያ ማን ይጠይቃቸዋል? ይብሱን ግን የሚያሳፍረው አየሩን ከሞላው ስማቸውና ዝናቸው የተነሳ በውጭ ባሉት ዘንድ እንኳ የምንወከለውና የምንታወቀው በእነርሱ መሆኑ ነው። እነዚህም ያልተማሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከእውቀት ነጻና ትምህርት ጠል ናቸው፤ በ”መድረክ አሙቁልኝ” ሱስ አብደው ሌሎችን ሁሉ ያለ እውቀት ያሳብዳሉ። ምዕመናንን “ፍጹምና ለበጎ ስራ የተዘጋጁ” የሚያደርገውን “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን፣ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይሚጠቅመውን”፣ የእግዚአብሔር ምክር ሁሉ የሆነውን መጽሐፍ ሳይሆን  ያው እንጨት እንጨት የሚለውን ዲስኩራቸውን በ”ልዩ መገለጥ” ስም ይዘው በየመድረኩ ይወራጫሉ። ኧረ ወዲያልኝ! እንደ ወንጌል አማኝ እንዲህ ባሉ ሰዎች እንደመወከል ምን የሚያሳፍር ነገር አለ?

No comments:

Post a Comment