በምድር ላይ እንድኖር በተሰጠኝ ዘመን መጽሐፍ ቅዱሴን ለመመልከት እድሉን ባገኘሁ ጊዜ ሁሉ ጌታዬና መድኃኒቴ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ መጽሐፍ ገጾች ውስጥ በፍቅሩ ኃይል፣ ግርማና ሞገስ በሞላው ሀልዎቱና ውበቱ ብዙ ጊዜ ነፍሴን ሲያነጋግራት አግኝቼዋለሁ፣ ሰምቼዋለሁም። እርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋናው ነው። የመጽሐፉ ማዕከል እና ልቡ እርሱ ነው። የሳሮን ጽጌረዳ እርሱ ነው፣ የተዋበው አበባ የሚያውደውም ጥሩው መዓዛ እርሱ ነው። መጽሐፍ ቅዱሴን በከፈትሁበት በየትኛውም ሥፍራ የመጽሐፉ ጌታ እዚያ ይገኛል። የሕይወት ቁልፍ ያለው እርሱ የሕይወት ቃል የሆነውን መጽሐፍ ይከፍትልኛል፣ የታተመውንም ይፈታልኛል። በትንሿ ቅንጭላቴ ሊገቡኝ የማይችሉትንና በሚጢጢዋ ልቤ ላስተውላቸው የሚከብዱኝን የመጽሐፉን እውነቶች፣ በድንግዝግዝ በመስታወት እንደሚያይ ሳይሆን ይልቁን ፍጻሜአቸውን ባገኙበት በክርስቶስ አያቸዋለሁ። እርሱ ለሰወራቸው ጉዳዮች ደግሞ አልጨነቅም። ሲያስገርመኝ የሚኖረው እውነት የጠፋሁ የነበርሁ እኔም በዚያ መጽሐፍ ገጾች ውስጥ በእርሱ የተገኘሁ፣ ሕያውም የሆንሁ መሆኔ ነው:: በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ለምድር ቅርጽና መልክ ያደርገላት እርሱ ዝብርቅርቁንና የተበላሸውን ማንነቴን በመጽሐፉ መንፈስ ሲያበጃጀው ማየት እንዴት ድንቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱሴን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በምድረ በዳ በቁጥቋጡ ውስጥ እንደሚቃጠል እሳት ሆኖ፣ እንደለመለመችም የዓሮን በትር ሆኖ የእግዚአብሔርን ልጅ በአግራሞት አየዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱሴን ከፍቼ ወደውስጡ በምመለከትበት ጊዜ ሁሉ በሞሪያ ተራራ ላይ እንዳለ አውራ በግ ሆኖ ከመሬት እስከ ሰማይ ከፍ ብሎ እንደ ተዘረጋ መሰላል፣ በረአብ መስኮትም ላይ እንደ ተሰቀለና ለደህንነት ከርቀት እንደሚታይ ሰንደቅ አላማ፣ በምድረ በዳም የተሰቀለውን እባብ፣ በበረሃም የተመታውን አለት፣ በእረኛም እጅ እንዳለ ማስውንጨፍያ እና ጠጠር ሆኖ የጌታዬን ፊት በውበቱ አየዋለሁ። እርሱ ከድንግሊቱ የተወለደ መድሃኒት የሴቲቱ ዘር ነው። ሰዎች እንዳይነግስባቸው የገፉት የዳዊት ልጅ እርሱ ነው። እንደ አሮናዊው የክህነት ወግ የውበት ልብስን የለበስው፣ በወርቅም የታጠቀውና የግርማ መጎናጸፊያውን የደረበው እርሱ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት የዘላለሙ ካህን ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕዩ ያየው ዘላለማዊው የክብር ጌታ የወርቃማዋ ከተማ ብርሃን፣ ነውር ወይም ነቀፋ የሌለበት ንጹህ በግ እርሱ ነው። ለሚጠባበቁት ለደናግሉ በሌሊት የደረሰላቸው ሙሽራ እርሱ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሴን ክፍቼ በተመለከትሁ ጊዜ ሁሉ ጌታዬን እንደዚያ አገኘዋለሁ። በቃ ምን አለፋችሁ አንድያውን ሆኖ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ እንደ ሸማኔ መወርወርያ ከወድያ ወዲህ በጥበብ ስራው የሚመላለሰውን ባለሟል በዚያ ጥቁር መጽሐፍ ገጾች ውስጥ በገሃድ እንደመመልከት ያለ ደስታ እና መጽናናት ከወዴት ይገኛል?
This comment has been removed by the author.
ReplyDeleteከወዴትም ❤ መፃህፍት ሑሉ ስለርሱ ብቻ ያወሩለት ውቡ ባለግርማው መሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር እና ግርማ ሐይል የነገሰው ለንጉሡ ክብር ለዘለዓለም ይሑን 🙏
ReplyDelete