Saturday, October 12, 2019

ሞት በሌለበት የትንሳኤ ፋይዳ

ሞት በሌለበት የትንሳኤ ፋይዳ። 

1ቆሮ 15፥ 54-57 "ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?  የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤  ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።"

በዚህ የንባብ ክፍል የተገለጸው ሃሳብ ከጊዜ ጋር የተገናኘ መሆኑን ማስተዋል የሚቸግረው ሰው በአጠቃላይ ስለ ትንሳኤም ሆነ ስለ ነገረ ፍጻሜ የሚያስበው፣ የሚያምነውና የሚያስተምረው ነገር ሁሉ የተሳሳተ ይሆናል። የነገረ ፍጻሜን ብልቱን ለማግኘት ጊዜውን ማወቅ ይቀድማል። እዚህ እንደተገለጠው ጊዜው፣ "ሞት ድል በመነሣት" የሚዋጥበት ጊዜ፤ የተጻፈው የትንቢት ቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ ነው። ጊዜው ደግሞ መቼ እንደሆነ ጳውሎስ ቀደም ሲል በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 51-52 ሲናገር "እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።" ይላል። ጊዜው "የኋለኛው መለከት ሲነፋ" ነው። 

መለከቱ እንደሚነፋ የሚጠበቅበት ጊዜ ደግሞ፣ ከእነርሱ መካከል ብዙዎቹ ወይም አንዳንዶቹ ገና በሕይወት እያሉ እንደሚደርስ ጳውሎስ በግልጽ ከሚናገርለት ጊዜ ጋር የሚስማማ ነው። ያም ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም የምትወድቅበት ጊዜ፣ ቤተመቅደሱ የሚፈራርስበት ጊዜ፣ የአሮጌው ኪዳን የክህነት ስርዓት የሚያበቃበት ጊዜ፣ ህጉ የሚወገድበት ጊዜ፣ ወዘተ. እንደሆነ ለማስረዳት በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ከደርዘን በላይ ምስክርነት ማቅረብ ቀላል ነው።

ጳውሎስ ቀደም ሲል በቁጥር 26 ላይ "የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤" ሲል የገለጠውንና፣ የዚህን የመጨረሻው ጠላት የተባለውን  የሞትን ድል መነሳት እዚህ ቁጥር 54 ላይ በጊዜ መደብ ውስጥ የተወሰነ ጉዳይ አድርጎ ያቀርበዋል። ይኸውም ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም የፍርድ ፍጻሜዋን ከሚሰጥበት ጊዜ ጋር፣ ለቤተ መቅዱሱ፣ ለብሉይ ኪዳን የክህነት ስርዓትና ለሕጉ ፍጻሜውን ከሚሰጥበት ጊዜ ጋር፣ ሰውን ከፈጣሪው ለይቶ ባስቀረው በመጨረሻ ለቀረው ሞት ለተባለው ጠላት፣ ማለትም 'የኃጢአት ሞት' ወይም 'የሞት ኃጢአት' ፍጻሜውን ከሚሰጥበት ጊዜ ጋር፣ እንዲሁም በትንቢተ ኢሳይያስ 25፥ 8 "ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።" ሲል የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ከሚያገኝበት ጊዜ ጋር የተቆራኘው ያው አንዱ ጊዜ ነው።

ኃጢአትም ፍጻሜውን የሚያገኘው በዚያው ጊዜ ነው።  ኃጢአት ፍጻሜውን ያገኝ ዘንድ በዳንኤል 9፥ 24-27 "ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።  ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።" ተብሎ የተተነበየው ቃል ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው ያኔ የጥፋት ርኩሰት በሚሆንበት ጊዜ ላይ ነው። የጥፋት ርኩሰት ምንነት ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ ለምትሹ በዚህ ግቡ፤

https://gizachewkr.blogspot.com/2019/02/blog-post.html

የተነሳንበትን ጥቅስ አጠቃላዩን የንባብ ክፍሉን አውደ ምንባብ ግምት ውስጥ አስገብተን ጉዳዩን ስናየው ጳውሎስ በቁጥር 54 ላይ "የሚበሰብሰው"፣ "የሚሞተው" እያለ የሚናገርለት፣ ይህ "ለሞት የተሰጠ ሰውነት" (ሮሜ 7፥ 24 እና 8፥ 10 ተመልከቱ)፣ ይኸውም መዋቲ የሆነው በስባሹ አካል፣ "የማይበሰብሰውን"፣ "የማይሞተውን"፣ በክርስቶስ የሆነውን የሕይወት አካል ይለብሳል፤ ሰውን ከእግዚአብሔር የለየው መንፈሳዊው ሞት፣ እርሱም የኃጢአት ሞት/ የሞት ኃጢአት ድል ተነስቶ በሕይወት ይዋጣል፣ የሚል ነው።

ትንሳኤ ያስፈለገው "ይሻራል" የተባለው "የኋለኛው ጠላት" የሚባል ሞት በሰው ላይ ስለነበረ ነው። ሞት የሚሻርበትን ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ "የኋለኛው ዘመን" ወይም የመጨረሻ ዘመን" ሲል እንደሚጠራው በሚበዙት የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው "የኋለኛው ዘመን" ወይም የመጨረሻው ዘመን" ደግሞ ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ቀድሞ ያለፈ ዘመን መሆኑን ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ መሆን አይጠይቅም። ሞት ያበቃለት ያኔ ነው፤ የሞት አገልግሎት የነበረው አሮጌው ኪዳንና ስርአቱ ሁሉ በ70 አም በእሳት ፍርድ ሲበላ፣ አዲሱ ኪዳንም በክብሩ ብዛት ሲገለጥ፤ ሞትን ሊሽር በተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ሞት የተረታው ሞት ያኔ እስከወዲያኛው ሊቀር ተወግዷል። በወንጌሉም የሚሰበከው የምስራች ይሄ ነው። የዳግመኛ ምጽአቱም ደስታ ይኸው ነው። ያለ ዳግመኛ ምጽአቱ የትንቢት ሙላት አይታሰብም። አስተሳሰባችንን ግን ከዚህ እውነት አርቀን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀውን "የመጨረሻ ዘመን" የሚባል ትምህርት በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ አምጥተን ስንሰነቅርና፣ ፍጻሜውንም ከመጀመርያው ክፍለዘመን ነጥለን፣ ለእኛ ባልተሰጠን ተስፋ ገና ወደፊት ስንጠባበቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀው እንግዳ የሆነ የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ እና "የሥጋ ትንሣኤ"  ተረት ይወለዳል። ከዚህም የተነሳ በቃሉ ምንም ድጋፍ የማይገኝለትንና በእጅጉ እርማት የሚያስፈልገውን "በሥጋ ትንሣኤ አምናለሁ" የሚል፣ ያለ እውቀት የሆነ ምስክርነት ስንሰጥ ኖረናል። ይህ ምስክርነት ግን "በሙታን ትንሳኤ አምናለሁ!" ተብሎ ቢታረም የተሻለ ድጋፍ ከቅዱስ ቃሉ ይኖረናል። "በሙታን ትንሳኤ አምናለሁ!" ስንልም ሙታን ትንሳኤያቸውን አስቀድመው እንደተቀበሉ በታሪካዊነቱ ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት እንደሚጠቀስ ማስረጃና ምስክርነት እንጂ፣ ገና ወደፊት እንደሚፈጸም የሙታን መጻኢ እድል የምናወራው አይደለም።
 
አሁን ግን በዚህ የመንግስት ዘመን ተረግመው በወንጌል ካላመኑት በቀር ሙታንም ሞትም የሉም፤ ይሰማል? ስለዚህ ሙታንም ትንሳኤን፣ ሞትም ሽረቱን ባገኙበት ሁኔታ፣ መጻኢ ትንሳኤ አስፈላጊነቱ ትርጉም የለውም። አሁን ሞት በሕይወት ተውጧል። ሞት ራሱ ሞቷል! እኛም በክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት ስለተቀበልን ከእንግዲህ ወዲያ በመንፈስ መሞት አይቻለንም። ክርስቶስም ሕይወታችን በመሆኑ ለዳንን ለእኛ አካላዊው ሞት ጥቅማችን ሲሆን፣ መንፈሳዊው ሞት ደግሞ ስጋታችን አይደለም። ተስፋ በተገባው የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፍጻሜው ይገለጥ ዘንድ የተጠበቀው የሙታን ትንሣኤ ተስፋም፣ ተስፋው ለተሰጣቸውና ሲጠባበቁት ለነበሩት የመጀመርያው ክፍለዘመን ቅዱሳን ተፈጽሞላቸው አልፎአል። አሁን ግን ለእኛ በወንጌሉ ለምናምን ብሩካን፣ ተጠብቆ ያለውና በጸጋ ወንጌል የሚታደለው ሕይወትና ሕያውነት ነው። ሕይወትንና ሕያውነትን ካመጣው ሕያው ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ፣ በሕያው እግዚአብሔር ፊት ለአዲስ ልደት በሚሆን ሕያው እምነት ለዘላለም ሕያዋን ሆነን እየኖርን ስለሆነ፣ ከዘላለማዊው ሞት ድነን፣ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆነን በምንኖርበት በዚህ የአዲሱ የጸጋ ኪዳን፣ በአዲሱ ስማይና በአዲሱ ምድር ሞት የለም፤ "ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም" ተብሎ ተጽፎአልና። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሕያዋን ኢየሩሳሌም ናት። ትንሳኤም ለሙታን ከአሁን በፊት ሆኖአል እንጂ ገና ወደፊት የሚሆን አይደለም። ሰለዚህ ሞት በሌለበት ትንሳኤ ማስፈለጉ ትርጉም አይሰጥም። ትንሣኤ አስፈላጊነቱ ሞት ይሰለጥንበት በነበረው በአሮጌው የሞት አገልግሎት በታች ተገዝተው ለኖሩና ለሞቱ፣ የቤዛነታቸውንም ቀን እየናፈቁ በመቃተትና በምጥ ለነበሩ የቀደመው ኪዳን ቅዱሳን ነው። እኛ ግን ተፈጥሮአዊውን ሞት በሥጋ ስንሞተው ክርስቶስን በማመን የጀመርነውን ይህንን የማያልፍ ሕይወት ኑሮ ለመቀጠል ያኔውኑ ከዚህ ቁርበት ከሆነ ማደርያችን ተለይተን ወዲያውኑ ወደ ሰማይ እንሄዳለን። ተፈጥሮአዊው ሞት ለክርስቲያን ጥቅሙ የሚሆነው በዚህ መንገድ ነው። ምነው? ቀድሞውንስ ቢሆን በክርስትና ወንጌል የተሰበከልንና ክርስቶስን አምነን የምንጠብቀው የሞታችን ጊዜ ሲደርስ በብጹዓን ስንብት ከጌታ ጋር ለመሆን ወደጌታ እንሄድ ዘንድ አይደለምንዴ? የዘላለም ሕይወትስ እርሱ አይደለምንዴ? በመሰረቱ እኔ ክርስቲያን የሆንኩት የኃጢአቴን ስርየት አግኝቼ፣ በምሞትበት ጊዜ ወደጌታ ለመሄድ ነው፣ ከዘላለም ሕይወት በመለስ ያለው ሁሉ ትርፍ ነገር ነው።

የሙታን ትንሳኤ ግን የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሲጠብቁት የኖሩትና በመጨረሻም በዘላለም ሕይወት ከጌታ ጋር ለመሆን ሞትን ድል በመንሳት ከሲኦል ነጻ የወጡበት የማይደጋገም የአንድ ጊዜ ሁኔታና ክስተት ነው። አሁን ግን እኛ፣ የቅዱሳን ትንሣኤ ከተፈጸመ በኋላ በብዙ የዘመን ርቀት የምንኖርና በክርስቶስ ያመንን ሁሉ፣ ትንሳኤና ሕይወት የሆነውንና የማይሞተውን ክርስቶስን ለብሰናል። በሥጋ ስንሞትና ይህ አሮጌ ቁርበት ሲወልቅ ቀድሞውኑ ለአዲስ ልደት በሚሆን ቅዱስ ጥምቀት ክርስቶስን ለብሰናልና በእግዚአብሔር ፊት ራቁታችንን አንሆንም። ካመንበት ቅጽበት ጀምሮ ለዘላለም በእግዚአብሔር ሕልዎት ውስጥ በሕይወት እየኖርን ነው። የምድር ላይ ቆይታችንን ጨርሰን በማንኛውም ምክንያት በጌታ ሆነን በሥጋ ስንሞት ያኔ ይህንን ሥጋ አውልቀን ጥለን የምንኖረው በአዲሱ መንፈሳዊ አካል በመንፈሳዊው አለም (realm) ብቻ ነው። ክርስቲያን በሥጋው የሚሞተው መጽናናት በሞላበት ደስታ ነው። ሁላችንም በስጋ እንሞታታለን እንጂ በስጋው ሞትን ሳያይ የሚነጠቅ ማንም የለም፤ የማንኛውም ሰው ስጋም ከበሰበሰበት ከመቃብሩ ወጥቶ አይመጣም። ለክርስቲያን የተሰጠ እንዲህ ያለም ተስፋ የለም። እንደ ክርስቲያን ደግሞ ደስ ብሎት የሚሞት ማንም የለም። አምነው የሞቱ በርካታ ቅዱሳን ወንድሞችና እህቶችን ስጋ ቀብሬ አውቃለሁ፣ በሞታቸው ሰአት የሞታቸውን ጣር ሰብሮ በገጻቸው ላይ የታየው ጸዳል በጌታ የመሆን የህይወት ደስታ ነበር። እኔም አንተም አንቺም በዚያ ደስታ እንሄዳለን እንጂ አንፈራም፤ "በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤" ተብሎ ተጽፎአልና። መጽናናት በሞላበት እንዲህ ባለ የእግዚአብሔር ሕይወት ውስጥ የመኖርና የመሞት ሚስጥር ከቀለለብንና፣ የክርስትናን ሕይወት ወደ ምድር ዝቅታ አውርደን፣ ትንሳኤን ቃሉ በማይመሰክርለት የስጋ ሰፈር ያለ አድራሻው የምንፈልገውና የምንጠባበቀው ከሆነ ግን፣ ገና ከወንጌሉ ጋር አልተግባባንም፣ የጥምቀታችንንም ኪዳን አላወቅንም ማለት ነው። 

ስለዚህ ወደፊት ይሆናል ብለን ልንጠባበቀው የሚያስፈልገን የተዳሳሹ ሥጋ ባዮሎጂካል ትንሳኤ ሊኖረን የማይችል እስከሆነ ድረስ፣ የሌለ ነገር ማመንም ሆነ ማስተማር አይገባንም። ምን ይሻላል ጎበዝ? ሰዉ ሊያነበውም ሊሰማውም የማይታገሰውን እውነት ይዘን አፋችንን እንዳንዘጋ ተቸገርንኮ! ለእኛ በእምነት ለጸደቅን ሰዎች ታዲያ በሥጋ ከሞትን በኋላ ምን ይቆየን ይሆን? ለምትሉ፤ በውኑ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ፕሪቴሪዝም የሚሰብከው የተፈጸመው ወንጌል ተስፋ ገዳይ አስተምህሮ ነውን? ከቶ አይደለም። በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን የመጽናናት ቃል ስሙኝና ላብቃ፦ 

"ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።" (ራእይ 14፥ 13)

ሃሌሉያ! እኔ ይህንን የተጻፈ ድምጽ ዛሬም እሰማዋለሁ። እናንተስ አይሰማችሁም? "ከእንግዲህ ወዲህ" ከተባለበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን፣ ደግሞም ለአለምና ለዘላለም በጌታ ሆኖ መሞት ብፅዕና ነው። እረፍትና ብድራት ያለበት፣ ከሚታየው ወደማይታየው የሚደረግ የብፁዓንና የድል ነሺዎች ሽግግርም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፣ "ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና፤ ….ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና" (ፊልጵስዩስ 1፥ 21 እና 23)፤ ሲል መስክሮአል።

እንግዲህ የክርስቲያን "ልዩ ጥቅም" ስለሆነ፣ ሞተን በዚህ የብጹአን ስንብት ለመካፈል ያብቃን! አሜን።

ቸር ሰንብቱ
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/ 

Sunday, September 22, 2019

አጠቃላዩ ትንሣኤ

አጠቃላይ ትንሳኤ

መግቢያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቃንና አመጸኞች ከሙታን የሚነሱ እንደሆነ ማስተማሩ እሙን ነው፣ በአማኞችም ሁሉ ዘንድ የታወቀና ግልጽ ነው። ይኸውም "አጠቃላይ ትንሳኤ" የምንለው ሲሆን፣ "እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።" (ሐዋ 24፥ 15) ተብሎ እንደተጻፈ፤ ትንሳኤ በአጠቃላይ ጻድቃንንና ዓመፀኞችን የሚያካትት መሆኑ፣ በአይሁድ ይጠበቅ የነበረና የጥንት ቤተክርስቲያንም ተስፋ ሆኖ የኖረ እምነት መሆኑ እርግጥ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ አጠቃላይ ትንሳኤ ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት ደግሞ በቀኑ መጨረሻ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ መሆኑ በሚበዙት ዘንድ ተቀባይነት አለው። እኔ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ የሚያውቀው የቀኑ መጨረሻ፣ ደግሞም ጌታ እንደተስፋ ቃሉ ተመልሶ የመጣው፣ በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ነው ብዬ ለማመን በቅዱስ ቃሉ ስለምገደድ፣ የዚህን አጠቃላይ ትንሳኤ መፈጸም ጊዜውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ነጥዬ ልረዳ አይሆንልኝም።

የትንሳኤ ተስፋ ተሰጥቶ የነበረው ለአሮጌው ኪዳን እስራኤላውያን ነበር። ሰለዚህ የትንሳኤ ተስፋ የብሉይ ኪዳን ተስፋ ነበር፣ እንጂ፣ ብሉይ ኪዳን የማያውቀውና በአዲስ ኪዳን የተሰጠ አንድ አዲስ ነገር አልነበረም። ለቤተክርስቲያን የተሰጠ አዲስና እንግዳ ተስፋ አልነበረም። ርዕሰ ጉዳዩን አጥርቶ ለመረዳት ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

አጽንዖት ሰጥቼ ልድገመው፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ የሙታን ትንሳኤ የሚፈጸመው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው፤ ተስፋውም ለእስራኤል የተሰጠ እስከሆነ ድረስ፣ መፈጸምም ያለበት በእስራኤል ዘመን መጨረሻ ላይ ነው እንጂ፣ "በአለም ፍጻሜ" ይኸውም በሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ወይም በጊዜ መጨረሻ ላይ አይደለም። ምክንያቱም የታሪክ መጨረሻ ወይም የሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ እና የጊዜ ማብቂያ የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ የሰው ልብ ወለድ ትምህርት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ገጹ ላይ እውቅና የነፈገው ርእሰ ጉዳይ ነው። ይህንን ያፈጠጠ የነገረ ፍጻሜ እውነት መቀበል ከሚቸገር ሰው ጋር ከመነሻው ስለማንግባባ ትምህርተ ትንሳኤያችንንም ማስታረቅ አይቻልም።  መጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ ግን የ70 አ.ም ነገረ ፍጻሜ ሲሆን፣ እርሱም የእስራኤል ነገረ ፍጻሜ ነው እንጂ የዚህ ግዑዝ አለም፣ የሰማይና የምድር ፍጻሜ አይደለም። ለእስራኤል የተሰጠው የነገረ ፍጻሜ ተስፋ የሚፈጸመው ደግሞ በእስራኤል ዘመን መጨረሻ ከሆነ ይህም መጨረሻ ነብያቱ፣ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ እንዳስተማሩት ቤተመቅደሱ የወደመበት  የ70ው አ.ም የእስራኤል ፍርድ የተፈጸመበት መጨረሻ ነው። ስለሆነም ትንሳኤ የሆነው ያኔ ነው። በአስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ የዘመኑን ፍጻሜ፣ የጌታን ዳግም ምጽአት፣ ትንሳኤንና ፍርድን የምናየው በዚያው በእስራኤል ዘመን ማብቂያ ውስጥ ነው።

ለሙታን ትንሳኤ በተቀጠረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጊዜ ላይ የጠራ አመለካከትን የያዘ ሰው በትንሳኤ ተፈጥሮና ባህርይ ላይ፣ ማለትም ሙታን በምን አይነት አካል ወይም ሁናቴ ትንሳኤን ይቀበላላሉ በሚለው ላይ ግራ አይጋባም፤ ጊዜው የትንሳኤን ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣልና።

ለትንሳኤ የተቀጠረውን ጊዜና የሙታን ትንሳኤ በአይነቱ ምን ባህርይ ወይም ተፈጥሮ እንዳለው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ በዚሁ ብሎገር ነገረ ፍጻሜን በጽሁፍ ሳስተምር በስፋት ያነሳሳሁት በመሆኑ በዚህችኛዋ ጽሁፌ እርሱን ብዙ አልሄድበትም። ምናልባትም ጌታ ቢፈቅድ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በጥልቀት ለማሰብ ሸክሙ ያላቸውን ተደራሽ የሚያደርግ ትምህርት ማቅረብን ወደፊት እቀጥላለሁ። ይሁንና ግን ይህንን የጻድቃንንና የአመጸኞችን ትንሳኤ አጠር ባለ መልኩ በወጉ ለመረዳት የሚያስችሉንን ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን በዚህ ጽሁፍ አንስተን እንድንካፈል እወዳለሁ። መልካም ምልከታ፦

1) ከሁሉ በፊት፦ 

ሁሉም ያለፉቱ፣ አሁን ያለነውና ገና ወደፊት የሚመጡቱ ሁሉም የእግዚአብሔር ህዝቦች ክርስቶስ በስጋው ወራት በመከራው አንድ ጊዜ በፈጸመው መስዋዕዊ የቤዛነት ስራው የተዋጁ መሆናቸው እሙን ነው። ለእነዚያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምእመናን መዳናቸው በመስቀሉ ደም ያኔ "ተመርቆ" (inaugurated ሆኖ) ነበር፤ ይሁንና ግን እርሱ በገዛ ደሙ ሊያስተሰርይላቸው ከገባባትና በሰማየ ሰማያት ካለችው ቅድስተ ቅዱሳን በ70 አ.ም በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ተመልሶ እስኪወጣና እስኪታይ ድረስ፣ የህዝቡ ሁሉ ሙሉ መዳን ገና በሙላት ወደ "ፍጻሜ" ወይም ወደ "ሙላት" አልደረሰም፣ (consummated አልሆነም) ነበር። "እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (እብራውያን 9፥ 28)፣ ተብሏልና። በመስቀሉ ስራ እንደሚታረድ በግ የአለምን ኃጢአት ሊያስወግድ በራሱ ላይ የተሸከመው መስዋዕታችን እርሱ፣ እንደ ሊቀ ካህናቱ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገብቶ ካስተሰረየ በኋላ፣ ከቅድስት ወደ አውደ ምህረቱ ወጥቶ ሁለተኛ ጊዜ በሚሆነው መታየቱ ይኸውም በዳግመኛ ምጽዓቱ ይጠባበቁት የነበሩትን ካላዳናቸው በቀር የህዝቡ ድነት ሙሉእ እና ፍጹም አይሆንም። ይህም፣ የአሮጌው ኪዳን ሊቀ ካህናት ስለ ሕዝቡ ለማስተሰረይ ወደ ቅድስት ገብተው በሚወጡበት አምሳል የተፈጸመ ነው። በመስቀል የተፈጸመውን የሰው ልጆች ድነት ሙላት ሰጥቶ የሚጠቀልለውና ፍጹም የሚያደርገው በናፍቆትና በትእግስት ይጠበቅ የነበረው ዳግመኛ ምጽአቱ፣ እርሱም ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት መታየቱ እንደሆነ ይህን አንድ ነገር ከተስማማን፣ ዳግመኛ ምጽአቱ ወደፊት ይፈጸማል እንጂ ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት እስካሁን ድረስ ገና አልሆነም በምንልበት ጊዜ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ኢየሱስ ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ሆኖ ያልታየ በመሆኑ፣ ማንም ሰው ቢሆን መዳኑ ገና ጅምር እንጂ ሙላት አላገኘም ማለታችን ይሆናል።

2) ቀጥሎም፣ የፊተኛው ትንሳኤ፦ 

ዮሐንስ በራእዩ ሲመሰክር፣ "አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።" (ራእይ 6፥ 9) ይላል።

እነዚህ እዚህ ላይ የምናያቸው ነፍሳት የወንጌል ሰማእታት የሚባሉት ናቸው። ስለ መሲሁ በመመስከራቸው ምክንያት በግፍ የተገደሉ ሁሉ ናቸው። የብሉይ ኪዳን ሙታን የሆኑ ቅዱሳን ሰማእታትን በተመለከተም በክርስቶስ ትንሳኤ ጊዜ ህያዋን ሆነው ከመቃብር በመውጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ምስክርነታቸውን እንደሰጡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ሲዘግብ "መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤  ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።" (ማቴዎስ 27፥ 52-53) ሲል ይነግረናል።

ይህም ደግሞ ዮሐንስ በራእዩ፦ "ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።" (ራእይ 20፥ 4 እና 6) ሲል አይቶ፣ ከመሰከረው ጋር ይስማማል።

ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው፣ ስለ እነዚሁ ሰማዕታት ዮሐንስ ቀደም ሲል በራእዩ አምስተኛ ማህተም መፈታት ላይ ያየውን ሲመሰክር፦ "አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።" (ራእይ 6፥ 9-11) የሚለውን ስትመለከቱ ጉዳዩ ስለምን እንደሆነ ለማስተዋል አትቸገሩም።

በብሉይ ኪዳን ለመስዋእት የቀረበው እንስሳ ደሙ ከመሰዊያው እግር ስር እንደሚፈስስ ሁሉ (ዘሌዋውያን 4፥ 7)፣ እንዲሁ በአይሁድ ካህናትና በአለቆቻቸው ግፍ እንደ እንስሳ የታረዱት የቅዱሳን ሰማእታቱ ነፍሳት ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ "የስጋ ሁሉ ነፍስ [በእብራይስጡ nephesh] በደሙ ውስጥ ነው" (ዘሌዋውያን 17፥ 11) ብሎ እንደሚያስተምር፣ በዚህ ራእይ ውስጥ ከመሰዊያው በታች ሆነው ይታያሉ (ቁ9)። እንደ አቤል ደም ሁሉ የሰማእታቱም ደም ስለ ፍርድና ስለ መለኮታዊ በቀል ወደ እግዚአብሔር ይጮሃል (ዘፍጥረት 4፥ 10)። እነዚህ ሰማዕታት ካሉበት መንፈሳዊ አለም ሆነው፣ ደማቸው በምድር ላይ በግፍ  ስለመፍሰሱ ግድ ብሏቸው የእግዚአብሔርን በቀል "በምድር በሚኖሩት ላይ" (ቁ. 10) እንዲመጣ የመጠየቃቸው እውነታ የሚያሳየው አሳዳጆቻቸውና ደማቸውን ያፈሱሱ ሰዎች ያኔም ገና በምድሪቱ ላይ የነበሩ መሆናቸውን ነው። ከ70ው አም ፓሮውዥያ አስቀድሞ የጻድቃን አይሁድና የክርስቲያኖች ዋነኛ አሳዳጆች መቀመጫቸውን በኢየሩሳሌም፣ የማዘዣ ጣቢያቸውንም በቤተ መቅደሱ ያደረጉ የአይሁድ ህዝብ መሪዎችና አለቆች የነቡሩት የዚያ ዘመን ዳኞችና የዚያ ትውልድ ሰዎች ናቸው (ሉቃስ 13፥ 33)። ይህ ሃሳብ ደግሞ ኢየሱስ፦ "ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።  እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።" (ማቴዎስ 23፥ 35 ጀምሮ) ሲል በተናገረው ትንቢት ውስጥ በሚገባ የተንጸባረቀ ነበር።

በዚያን ዘመን ላይ የተፈጸመው የኢየሩሳሌም ውድመት በመሪዎችዋ ታርደው ለተገደሉት ለጻድቃን ደም (ነፍሳት) በእግዚአብሔር ፊት ለቀረበው ጩኸታቸው ምላሽ ሆኖ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የመለኮታዊው ዳኛ ፍርድ ነበር። ራስል ሲጽፉ፦ "በዚህ የአምስተኛው ማህተም ራዕይ ጭብጥ እና ጌታችን ስለ አመጸኛው ዳኛ "እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?" (ሉቃስ 18፥ 1-8) ሲል በተናገረው ምሳሌ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በጥንቃቄ ተመልከቱ፤ ይህ የሚያስገርም መመሳሰል አይደለምን? ጉዳዩ ግን ከመመሳሰልም በላይ ያለፈ እና ማነትታቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው" ይላሉ።

ሮማዊው ጲላጦስ ደማቸውን ከመስዋእታቸው ጋር ስለደባለቀው በገሊላ ስለነበሩ አይሁድ አምላኪዎች  ጌታ ኢየሱስ ወሬው በተነገረው ጊዜ ምላሹ ምን ነበር? "እናንተም (አይሁድ) ንስሃ ባትገቡ እንደዚሁ [ማለትም በሮማውያን እጅ] ትጠፋላችሁ" (ሉቃስ13፥ 1-3) ነበር ያላቸው። ይህ አምስተኛው ማህተም በኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸመውን ፍርድ ምክንያቱን ያሳስበናል "ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም " (ዘሁልቅ 35፥ 33) ተብሎ ተጽፏልና።

፨ይህንን የሰማዕታቱን ትንሳኤ አጥርቶ መረዳት ቁልፍ ነገር ነው። እነዚህ በመጀመርያው ትንሳኤ እድል ያላቸው ሁሉም የሞቱ ቅዱሳን (ራዕይ 20፥ 6)፣ በ70 አም ከሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው አስቀድሞ የሞቱ ቅዱሳን ናቸው። ከእነርሱም መካከል በተለይ በብሉይ ኪዳን ዘመንና ብሎም በሽግግሩ ዘመን ውስጥ ሰማእታት ሆነው በግፍ የተገደሉ ቅዱሳን ነበሩበት። 

እነርሱም

(ሀ) ስለክርስቶስ እና ስለቃሉ ራሶቻቸው የተቆረጡባቸው (ስማእት የሆኑ) ነፍሳት ናቸው። ይህም የሰማዕታት ቡድን  ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በክርስቶስ ትንሳኤ ጊዜ ከየመቃብሮቻቸው ወጥተው ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁድ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ሕያዋን የሆኑትን ወይም እንደገና ሕያዋን የተደረጉትን (ገና የራሳቸውን ትንሳኤ ያላገኙ) ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ሰማእታት ሊያካትት ይችላል (ማቴዎስ 27፥ 52-53)። ለምሳሌ ስለምስክርነቱ በግልጽ ራሱ ተቆርጦ እንዲሞት የተደረገው መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ የብሉይ ኪዳን የሰማእታት ምድብ ውስጥ ሊካተት ይችላል። እነዚህም ከሲዖል የሙታን እረፍት ስፍራ ወጥተው ሊታይ በማይችለው ሰማያዊው ግዛት የሰማይ ደጅ ከሚገኘው "ከመሰዊያው በታች" ይሆኑ ዘንድ ከክርስቶስ ትንሳኤ የአርባ ቀናት ቆይታ በኋላ በእርገቱ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ወደ ላይ፣ ወደ ሰማያት ደጅ የተወሰዱ ናቸው። ገናም የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት እርሱም ሁሉተኛ መታየቱን እየተጠባበቁ ትንሳኤያቸውን ያላገኙ ነበሩ።

(ለ) በአውሬውና በምስሉ ፊት ያልሰገዱ ወይም ምልክቱን በእጆቻቸው እና በግንባራቸው ያልተቀበሉ ነፍሳትም ናቸው። እነዚህ ደግሞ ስለክርስቶስ መከራን እየተቀበሉ በአሳዳጆቻቸው እጅ በግፍ የተገደሉና እስከ ክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ድረስ ለጊዜው "ከመሰዊያው በታች" ይሆኑ ዘንድ ሊታይ ወደማይችለው ግዛት፣ ወደ ላይ፣ ወደ ሰማያት ደጅ በእያንዳዳቸው የተወሰዱ፣ የሽግግሩ ዘመን ሰማእታት ናቸው። እነዚህም "የጻድቃን መንፈሶች" ከክርስቶስ ጋር በእርገቱ ምርኮው ሆነው አስቀድሞ ከሲኦል ሓደስ የተወሰዱና፣ ለጥቂት ዘመንም እረፍት ይሆንላቸው ዘንድ ሊታይ ወደማይቻለው ሰማያዊ ስፍራ ተወስደው ከመሰዊያው በታች እንዲከማቹ የተደረጉ፣ ትንቢትም ሁሉ በሚፈጸምበት በምጽአቱ ቀን ከክርስቶስና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሊገለጡ የተጠበቁ ነፍሳት ናቸው። ዮሐንስ በራእዩ ሲመሰክር በዚያ የሽግግር ወቅት ላይ ለእነዚህ የሚለብሱት "ነጭ ልብስ"፣ "ዳኝነት" እና ደግሞም ከክርስቶስ ጋር ለሺህ አመት መንገስና መግዛት እንደተሰጣቸው ይናገራል። የእነዚህም ምድብ ማንም ሊቆጥራቸው የማይችለውን የ40 አመት የሽግግር ጊዜ ሰማእታት እነ እስጢፋኖስን፣ የዮሐንስ ወንድም የሆነውን ያእቆብን፣ ዮሐንስን፣ ጳውሎስን፣ የጌታ ወንድም የሆነውን ያእቆብን፣ ጴጥሮስን እና ሌሎችን በዚያ የሽግግር ወቅት ላይ ስለ እምነታቸው በግፍ የተገደሉትን ሁሉ ይጨምራል (ራእይ 6፥ 9-11፤ 7፥ 13-17፤ 20፥ 4)። እነርሱም ልክ በሞቱበት ቅጽበት ቀድሞውኑ ከሲኦል ሐደስ ምርኮ ከወሰዳቸውና በዚያ በሰማይ ደጅ በመሰዊያው በታች ካከማቻቸው ሌሎቹ ቅዱሳን ሰማእታት ጋር ተቀላቅለዋል (ራዕይ 6፥ 9-11፤ 7፥ 13-17፤ 20፥ 4)። እነርሱም ክርስቶስ በፓሮውዥያው እስኪመለስ ድረስ ገና ትንሳኤያቸውን ይላገኙ ነበሩ።

እንዴት እንደሆነ ባናውቅም፣ ምናልባትም ሁሉም እነዚህ በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታት፣ ማለትም "የጻድቃን መንፈሶች" ልክ ሳሙኤል ለዛች በዓይንዶር ለነበረች ሙታን ሳቢ ሴት እንደታየበት አይነትና ሁናቴ (1ሳሙአኤል 28፥ 7)፣ ወይም ሙሴና ኤልያስ በመለወጥ ተራራ ላይ ለኢየሱስና ለሦስቱ ደቀመዛሙርት በታዩ ጊዜ (ማቴዎስ 17፥ 1-3) እንደነበራቸው ያለ አንዳች (ጊዜያዊ) አይነት አካላዊ ሁናቴ ወይም መልክ ወይም ቅርጽ ሊኖራቸው ይችላል።

እነዚህ አስቀድመው ሰማእትነትን የተቀበሉ ነፍሳት በዚያ የሽግግር ዘመን ከክርስቶስ ጋር የነገሱና የሚገዙ ድል ነሺዎች ናቸው። ገናም ደግም ከዚያ ከነበሩበት (ጊዜያዊ) አካላዊ ሁናቴ፣ መልክ ወይም ቅርጽ ወደ ዘላለማዊው አካላዊ ሁናቴ ሊለወጡ ትንሳኤን መቀበል የተገባቸው ነበሩ። ከክርስቶስም ጋር ሊነግሱ በማይታየው ግዛት ከመሰዊያው በታች ተጠብቀዋል። በስጋቸው መከራን በመቀበላቸው ከኃጢአት ተለይተዋል (1ጴጥሮስ 4፥ 1-2)፤ በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት፣ ስለ ክርስቶስም በምድር ላይ በተቀበሉት በዚህ መከራና ባለፉበት ጽኑ ስደት ውስጥ በነበራቸው ታማኝነት ፍርድን (ይህም ሁለተኛውን ሞት) ተሻግረዋል "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።" (ዮሐንስ 5፥ 24)። ተብሎ ተጽፎአልና። በሰማዕትነታቸውም የታመኑ መሆናቸው ተመስክሮላቸው ብይን ተሰጥቶአቸዋል። (ራእይ 20፥ 4)። ትንሳኤን የሚጠባበቁ የነበሩ እነዚህ ሰማዕታት በእርግጥም ብጹአንና የተባረኩ ነበሩ፣ በምሳሌያዊው የሺሁ አመት መንግስትም መሲሁ በተለየ መልኩ ሊያያቸውና ዙፋናቸው በዙፋኑ ዙርያ እንዲሆን እድሉ የነበራቸው ናቸው። (ራእይ 20፥ 5-6)።

3) አሁንም፣ የፊተኛው ትንሳኤ፦ 

"በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት    በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።" (ራእይ 20፥ 6)

እነዚህ ደግሞ በተፈጥሮአዊ መንገድ የሞቱትና እንደ ሰማዕታቱ ሁሉ ተመሳሳይ በሆነ የሰማዕትነት መንገድ ያላለፉ ወይም በነፍሳቸው ምስክርነታቸውን ያልሰጡ፣ ነገር ግን በሙታን ትንሳኤ ተስፋ አምነው የሞቱ የተቀሩት የብሉይ ኪዳን ሙታን (አማኞች ናቸው)፡፡ እነርሱም ደግሞ እንደ ሰማዕታቱ ሁሉ በአጸደ ነፍስ ከነበሩበት የሲኦል እረፍት ወደ ሦስተኛው ሰማይ ወደ ገነት በክርስቶስ እርገት የተወሰዱ እና፣ የሽግግሩ ጊዜ በ70 አም በሆነው የምጽአት ቀን እስኪያበቃ ድረስ በዚያ በሰማይ ደጅ በአውደ ምህረቱ የተጠበቁና በመሰዊያው ዙርያ የተከማቹ ነፍሳት ናቸው። እነርሱም እያንዳንዳቸው ትንሳኤን ሊካፈሉ ተስፋ አድርገው በዚያ በሽግግሩ ወቅትና ከዚያም አስቀድሞ በሰማእትነት  ከሞቱት ሌሎች ቅዱሳን ሁሉ ጋር በአንድነት የዳግመኛ ምጽአቱን ፓሮውዥያ ሊጠባበቁ በሰማይ ደጅ እንዲከማቹ የተደረጉ ነበሩ፡፡

ተፈጥሮአዊ በሆነ ምክንያት የሞቱት የተቀሩት እነዚህ ቅዱሳን ሙታንም በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው እስኪነሱ እና የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ዘላለማዊ የትንሳኤ አካላቸውን እስኪቀበሉ ድረስ በሰማይ ደጅ እንደነበሩ ሁሉ፣ እነዚያም ከፍ ሲል ያየናቸው ሰማዕታቱ አዲሱን፣ ዘላለማዊውን የማይበሰብሰውን፣ የማይሞተውንና፣ የከበረውን አካል ገና አልተቀበሉም ነበር።

እነዚህ የፊተኛው ትንሳኤ ሁለት ምድብ አማኞች እያንዳንዳቸው ተጠብቀው ከነበሩበትና ማንም ሊያየው ከማይችለው ሰማያዊ ስፍራ ተነስተው በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በሆነው የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ወደክብሩ ገብተዋል። እነርሱም ደግሞ ለእርሱ የተወደዱ ምርጦቹና ቅዱሳኑ እንዲሆኑ የተዳኙት ሁሉ ናቸው። በእነርሱም ላይ ሁለተኛው ሞት ምንም ስልጣን የለውም (ራእይ 20፥ 6)።

4) በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተቀሩት ሙታን "ሁለተኛው ሞት"፦
"በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።" (ራእይ 20፥ 15)

"ማንኛውም" የተባሉት እነዚህ ሁሉም የማያምኑ ስዎች ሲሆኑ ያለጥርጥርም ደግሞ በነጩ ዙፋን ፍርድ የሚዳኙትንም ይጨምራል። በእምነት በኩል በክርስቶስ ያልሆኑ ሁሉ፣ የሚድኑበት እምነት የሌላቸው እስከሆኑ ድረስ "ማንኛውም" ናቸው፣ እነርሱም ተነስተው ከስራዎቻቸው የተነሳ ፍርዳቸውን ተቀብለዋል። መጨረሻቸውም በእሳት ባህር ውስጥ ተጥሎ የዘላለማዊ ኩነኔን ፍዳ መቀበል ብቻ ነው። ይህም ሁለተኛው ሞት ተብሎ ይጠራል። (ራእይ 20፥ 11-14)። እነዚህ እንግዲህ ሁሉም በየትኛውም የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የነበሩና ያሉ፣ ወደፊትም የሚኖሩ፣ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ የሌለ፣ ቀድሞውንም ቢሆን ካለማመናቸው የተነሳ ለእሳት ባህር ፍርድ የተመደቡና ታልፈው የተሰጡ፣ ያልዳኑ ኃጢአተኞች፣ ቤዛነቱን ያልተቀበሉ፣ ያልተዋጁ፣ ያልተመረጡ  ናቸው። (ራእይ 20፥ 15)።

5) ልብ አድርጉ፣ 

ክርስቶስ በ70 አም በሆነው ፓሮዥያው ፍርድን ለመፈጸም በሚሆን አላማ፣ በአንድ በኩል ጽድቅን የተቀበሉትንና የተቀደሱትን ሁሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኃጢአተኞችንና እርኩሳንን ሁሉ በቋሚነት መድቧቸዋል። ይህንንም ፍርድ ባደረገበት ጊዜ፣ ፍርዱ መላውን የሰው ዘር ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ከ70 አም በኋላ ለጥቆ ውዲህ ባለው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውልና የሚያገለግል ቋሚ አሰራር ሆኖ ይኖራል፤ (ራእይ 22፥ 10-11)። አሁን ያለን የማመን-አለማመን አቋምና አቋቋም ምድባችን ከየትኛው ወገን እንደሆነ ስለሚያመለክት ወደፊት የምንጠባበቀው ፍርድ አያስፈልገንም፣ የእግዚአብሔር ቃል "በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።" (ዮሐንስ 3፥ 18) ብሏልና።

6) ይህን ደግሞ አስተውሉ፣ 

ከ70 አም በኋላ የዳኑ ሁሉም የእግዚአብሔር ቅዱሳንና ምርጦች በትንሳኤም ሆነ ወይም በፍርድ ውስጥ ማለፍ አስፈላጊያቸው አይደለም። ይህም የሆነበት ምክንያት ክርስቶስ በ70አም በሆነው የምጽአቱ ፓሮዥያ የአማኝ ቅዱሳን ምርጦቹን ደህንነት ሙሉ በሙሉ ወደ ፍጻሜ ስላደረሰው (consummated ስላደረገው) ነው። ይህ ማለት፣ በእምነት በኩል በክርስቶስ ውስጥ ያለን በመሆናችን ከእርሱ ጋር ሞተናል፤ ከእርሱም ጋር ለአዲስ ሕይወት ተነስተናል፤ በእርሱም ውስጥ ተፈርደን ለማይጸድቁት በታደለ ጽድቅ በእርሱ ውስጥ ጻድቅ ሆነን ተገኝተናል (ዮሐንስ 5፥ 24፤ ሮሜ 6፥ 8-11፤ 2 ጢሞቴዎስ 2፥ 11፤ 1 ጴጥሮስ 3፥ 18)። አሁን በዚህ ሕይወት እያለን በስጋ በምንሞትበት ጊዜ በቅጽበት አይን እንለወጥና፣ በቀጥታ ያለምንም ጥበቃ፣ የማይበሰብሰውን፣ የማይሞተውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ ይማይችለውን፣ አዲሱን ሰማያዊ አካል እንለብሳለን። ስጋና ደም የሆነው አሮጌው አካላችን ይረግፍና ይበሰብሳል። እኛ ግን በቅጽበት አይን እንለወጥና የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን አዲሱን አካል ለብሰን ለዘላለም በሆነችው በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በዘላለማዊ ህይወት ለዘላለማዊ ክብር ለመኖር ወደከበረው ዘላለማዊ ሀልዎቱ እንገባለን። (1ቆሮንቶስ 15፥ 53-54)።

ስናጠቃልለው፦ 

ከ70 አም በፊት ለሰዎች መሞት አንድ ጊዜ ተመድቦላቸው ነበር፤ ያኔም ከሙታን ተነስተው የክርስቶስን ፍርድ ተቀበሉ። ትንሳኤና ፍርድ ይተከናወነው በ70 አም  በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ፓሮዥያ ላይ ነው። ይኸውም የተከናወነው የእርሱን ዳግመኛ ምጽአት ናፍቀው በብዙ መጓጓት ይጠባበቁ የነበሩ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ትውልድ በነበሩበት ወቅት ነው። ሁሉም አይነት ፍርዶችና ብድራቶች በዚያን ጊዜ እንዲፈጸሙ በእግዚአብሔር ተወስነዋል ፡፡

"ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት (ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅድሳን) ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 27-28)

ልክ በአንዱ ሰው (አዳም) በኩል ኃጢአት ለሰው ሁሉ ሞትን እንዳመጣ፤ እንደዚሁ በአንዱ ሰው (ክርስቶስ) ጽድቅ ለምርጦቹ ሁሉ ህይወትን አመጣ። ስለዚህም ደግሞ ክርስቶስ በ70 አም ባደረገው ፓሮዥያው በፈጸመው ፍርድ ለተመረጡቱ (ላለፉትም ለሚመጡትም) የሰማይን ዘላለማዊ ዕድል፤ እንደዚሁም ደግሞ ላልተመረጡቱ (ላለፉትም ለሚመጡትም) የሲዖልን ዘላለማዊ ዕድል ፍርዱ አስገኝቶላቸዋል። ለሰዎች ሁሉ፣ "ጸድቀሃል" ወይም "ተኮንነሃል" ተብሎ በእግዚአብሔር ዳኝነት የተላለፈው ብያኔና ዘላለማዊ ፍርድ የተዘጋጀው፣ የተመሰረተውና የጸናው በዚያን ጊዜ ያኔ ነው።

"ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።" (ራእይ 22፥ 10-11) ወደፊት በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሚከናወን፣ ወይም ሊከናወን ያለ፣ የቀረ፣ አንድም የፍርድ ስርዓት የለም። ከ70 አም በኋላ ለሚኖሩና ለሚሞቱ ሰዎች ከ70 አም በፊት በነበሩና በሞቱ ሰዎች ላይ በተፈጸመው አይነት የሚከናወን መጻኢ የሆነ ትንሳኤም ሆነ ወይም ፍርድ የለም። እግዚአብሔር ምርጦቹን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በእምነት በኩል ለዘላለም ጻድቃን አድርጎ ገልጧቸዋል፣ አጽንቷቸዋልም። ስሞቻቸውም አለም ሳይመሰረት አስቀድሞ በሕይወት መጽሐፍ ላይ ላይደመሰስ ተጽፎአል። (ኤፌሶን 1፥ 4፤ ራእይ 21፥ 27)።

ከ70 አም በኋላ ያሉ እያንዳንዳቸው ዳግመኛ የተወለዱ አማኞች በሚሞቱበት ጊዜ በየራሳቸው አዲሱን፣ የማያረጀውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ የማይችለውን፣ ስማያዊውን አካል ይለብሱና በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (በሰማያት) ከክርስቶስና ከቅዱሳኑ ጋር ለመሆን በቅጽበት አይን ወዲያውኑ ወደ ክርስቶስ ሀልዎት ሄደው (1ቆሮንቶስ 15፥ 53-54፤ 2ቆሮንቶስ 5፥ 1-4) ለዘላለም በዚያ ይሆናሉ እንጂ፣ የሌለውን "የስጋ ትንሳኤ" አይጠባበቁም።

ከዚህ ውጭ ያሉቱ ደግሞ፣ ያልዳኑ፣ ያልተመረጡቱ፣ ያልጸደቁቱ ናቸው፣ እነርሱም ያላመኑ ስለሆኑ አልተዋጁም። በህይወት መጽሐፍ ላይ የአንዳቸውም ስም የለም። ዕድላቸውም ዘላለማዊ ሞት ሆኖ በሚቃጠል የእሳት ባህር በዘላለማዊ ኩነኔ ሊቀጡ የተፈረደባቸው ናቸው። በ70 አም ምጽአቱ አንድ ጊዜ ለዘላለም በተሰጠ ብይን ሁሉም የማያምኑ ኃጢአተኞች አሁን በላያቸው ላይ ባለ በማይለወጥ የእግዚአብሔር ፍርድ ለዘላለም ተኮንነው ይጠፋሉ። (ራእይ 20፥ 15፤ ራእይ 21፥ 8፤ ማቴዎስ 18፥ 9፤ ማርቆስ 9፥ 47-48)።

በመጨረሻም የህይወት ጥሪ፣ 

በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጽሁፌን የምታነቡና ስለ መጨረሻው እድላችሁ እርግጠኛ ያልሆናችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ በንስሃና በእምነት የሚገባባት፣ የማይዘጉ ደጆች ያሉአት የአምላካችንና የመድሃኒታችን መንግስት፣ ልትገቡ ብትወድዱ እና አሁን ለእምነት ብትታዘዙ እነሆ ከመሞታችሁ በፊት በፊታችሁ የተከፈተች ሆና ትጠብቃችኋለች። በጌታችንና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከዘላለም ጥፋት ወደ ዘላለም ሕይወት እንድትመጡ እየጋበዝን እንድትገቡ እንለምናችኋለን።
ቸር ቆዩኝ!
ግዛቸው 








የኢዮስያስ ጥያቄና የእኔ መልስ

ውድ ኢዮስያስ፣ (ጥያቄህን ባነሳህበት ገጼ ላይ ገብቼ መመለስ ባለመቻሌ በዚህ ገጽ ቀርቤ ላነጋግርህ) በብዙ የራሴ ጥቃቅን ምክንያቶች ዘግይቼም ቢሆን አሁን ስመልስልህ መልሴን ለማንበብ እንደማትሰለች ተስፋ አደርጋለሁ። ጽሁፎቼንና የማስተላልፈውን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ሳይደነብሩ በልብ ስፋት ከሚያዩና ልማድ ከማይተናነቃቸው ጥቂት አንባቢዎቼ አንዱ በመሆንህ ላመሰግንህ እፋልጋለሁ። እኔም የምታነሳቸውን የሰሉ ጥያቄዎችህን በሚገባ አያቸዋለሁ እንጂ እንዳመጣልኝ ልመልሳቸው አልሻም። በእርግጥ በዚህኛው ልጥፌ ላይ ያነሳሃቸው ጥያቄዎች ከዚህ ቀደሞ በጻፍኳቸው የተለያዩ አጭርና ዝርዝር ጽሁፎቼ ላይ ልመለከታቸው መሞክሬ አልቀረም። ስጽፍም አንባቢዎቼ የቀደሙትን ስራዎቼን ያስታውሳሉ ወይም ብሎገሬን ይበረብራሉ በሚል ታሳቢነት ስለሆነ አንዳንድ ጉዳዮችን ከድግግሞሽ ሽሽት የተነሳ ያለ ተጨማሪ ማብራርያ በቀጥታ በማለቴ ከአንዳንድ ደርሶ ተመላሾች ጋራ መተላለፋችን አልቀረም። ፕሪቴሪዝምና ትምህርቱን የሚያቀርብበት መንገድ የብዙዎችን ልማዳውያን (traditionalists) ጅማት የሚፈታ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ዋናው ሸክሜ ግን እኔ ልሄድ በመረጥኩበት መንገድ "ነገሩ እንዲህ ይሆንን?" የሚሉ እምነታቸውን የሚጠይቁና መጻህፍትን የሚመረምሩ ጥቂት ወገኖችን ማገዝ ነው። ጥያቄዎችህን ለማስታወስ ላስቀድምና የኔን መልስ ላስከትል። እንዲህ ነበር የጠየቅኸኝ፦

ቄስ እንድታብራራልኝ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ላንሳ- እንዳንተ እምነት በ70 አ.ም ያኔ ጌታ በክብር መጥቶ፦1- ከምጽሃቱ በፊት ለሞቱ ቅዱሳን ትንሳኤን፣ 2-በህይወት ለነበሩት መለወጥን፣ 3-ለእርኩሳንና ለማያምኑ ሃጢአተኞች ዘላለማዊ ፍርድና ጥፋት እንዲሁም ፣ 4- በእርሱ ለሚያምኑ ደግሞ የዘላለም ህይወት ከተሰጠና፣ 5- ከዛን ጊዜ ጀምሮ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር ያለን ከሆነ፦
ጥያቄ-
1- በ70 አ.ም ተካሄደ ያልከው ትንሳኤና መለወጥ ምን አይነት ትንሳኤና መለወጥ ነበር? ከዛን ጊዜ በኋላ ያለን አማኞች የትንሳኤ ጉዳይስ ምን አይነት ትንታኔ አለው? የትንሳኤውንና የመለወጡን ባህሪ ብታብራራልን (ከዚህ ቀደም ምናልባት ካብራራሃው ደግሞ link ብታጋራን)
2- ከዛ አመት በኋላ ያለን እኛ አማኞች ያልተፈጸመ የምንጠባበቀው ተስፋ አለን?
3- ከዛን ጊዜ በኋላ አዲስ ሰማይና ምድር ከሆነ አሁን የምንኑሮው ኑሮ በአዲስ ሰማይና ምድር ነው? ምክንያቱም የራእይ መጽሃፍ የመጨረሻ ምእራፍ ስለ አዲስ ሰማይና ምድር  ሲያወራ በዛ ሀዘን፥ ለቅሶ፥ እምባ...ወዘተ እያለ የሚዘረዝራቸው የማኖሩ ከሆነ በዚህ ዘመን የምናያቸው ስቃዪች፥ ለቅሶዎች፥ እንባዎች...እንዴት ይዳኛሉ? ማለቴ አዲስ ሰማይና ምድር ውስጥ አለን ካልን እነዚህ እኩይ ክንዋኔዎች እንዴት አሁን በምንኖርበት አለም ሊገኙ ቻሉ? የአዲስ ሰማይና ምድር አስተምህሮው የእነዚህን እኩይ ክንዋኔዎች መኖር አይከላከልም?
4- ሃጢአተኞች (እርኩሳንና የማያምኑ) ዘላለማዊ ፍርድ ከተቀበሉ ዛሬ በክርስቶስ ማንነትና ስራ የማያምኑ የፍርድ ሁኔታ መች ሊሆን ነው?
ቄስ ከላይ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች ምናልባትም ለቀጣይ ውይይታችን መነሻ ይሆናል ባይ ነኝ።

¶ እኔም በቀጥታ ወዳነሳሃቸው ጥያቄዎች ስመለስ እነሆ መልሴ፦
1- እንደምታውቀው ትንሳኤ በአጠቃላይ ጻድቃንንና ዓመፀኞችን የሚያካትት መሆኑ፣ በአይሁድም ይጠበቅ የነበረና የቤተክርስቲያንም ተስፋ ሆኖ የኖረ እምነት ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ አጠቃላይ ትንሳኤ ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት ደግሞ በቀኑ መጨረሻ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ መሆኑ በሚበዙት ዘንድ ተቀባይነት አለው። እኔ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ የሚያውቀው የቀኑ መጨረሻ፣ ደግሞም ጌታ እንደተስፋ ቃሉ ተመልሶ የመጣው፣ በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ነው ብዬ ለማመን በቅዱስ ቃሉ ስለምገደድ፣ የዚህን አጠቃላይ ትንሳኤ መፈጸም ጊዜውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ነጥዬ ልረዳ አይሆንልኝም። ለሙታን ትንሳኤ በተቀጠረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጊዜ ላይ የጠራ አመለካከት የያዘ ሰው በትንሳኤ ተፈጥሮና ባህርይ ላይ፣ ማለትም ሙታን በምን አይነት አካል ወይም ሁናቴ ትንሳኤን ይቀበላላሉ በሚለው ላይ ግራ አይጋባም፤ ጊዜው ራሱ የትንሳኤን ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣልና። ትንሳኤ በተፈጥሮው መንፈሳዊ መሆኑንና የትኛውንም ተዳሳሽ ቁስ ማስረጃና ማረጋገጫ አድርጎ የማያቀርብ መሆኑ ግልጽ ነው። የጥንት ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን እንደሚታሰበው ሁሉ ትንሳኤ ተዳሳሽ ስጋዎችን ከመቃብር ውስጥ አውጥቶ ማምጣትን የሚጨምር መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ ለምሳሌ ሄሜኔዎስና ፊስጦስ "ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል" ብለው በማስተማር ማንንም ማሳመን ባልቻሉም ነበር። ስለዚህ ላነሳኸ የ"አይነት" ጥያቄ ቁልፉ "ጊዜው" ስለሆነ የነገረ ፍጻሜን ሀሁ ለመረዳት ኮስተር ብለህ ጊዜውን አጥና። በነገራችን ላይ ቀጣዩ ልጥፌ ስለ አጠቃላይ ትንሳኤ ስለሚያትት ዝርሩን እዚያ ላይ እንመለከተዋለን።
2- ባጭሩ፣ ያልተፈጸመ የምንጠባበቀው ምንም ተስፋ የለም። አለ የሚል ሊያቀርብ ይችላል፣ ያኔ መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ለእምነት ቤተሰቦች ቃሉን፣ ለተጠራጣሪዎች ደግሞ  የታሪክ ሰነድ ጠቅሰን እናስረዳለን።
3- በኮስሞሎጂካል ለውጥ የተወከለው ለውጥ የኪዳን እንጂ የግዑዝ አለም ለውጥ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። አሮጌው ሰማይና ምድር እሮጌው ኪዳን ሲሆን የአሮጌው ኪዳን ሀዘን እንባ ልቅሶ የኪዳኑ ቀንበር፣ የሞት እዳና እርግማኑ ሁሉ ነው። ያ ኪዳን እስካለ ድረስ የኪዳኑ መርገምም ደግሞ አለ። በዚያ ኪዳን ስር ከብዷቸው ይቃትቱ የነበሩ ሁሉ፣ ከአሮጌው የሙሴ ሥርዓት ይቀበሉት ከነበረው መከራ ያረፉትና የተጽናኑት አዲሱ ኪዳን ያለ አሮጌው ኪዳን በሆነበት በአዲሱ ሰማይና ምድር ነው። አሁን በጌታ ዳግመኛ ምጽአት የተጀመረው አዲሱ የጸጋ ሥርአት ብዙ መጽናናት ያለበት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሃሴትና ደስታ ነው እንጂ የስጋዊ ተድላና ድሎት አይደለም። የዚህን አለም እውነታ መሸሽ አንችልም። አንተ ያነሳሃቸውን የዚህ ግዑዝ አለም ሃዘንና ስቃይ የምንሻገረው አንድም ለተሻለ አለም  ስንሰራበት ነው፣ አልያም ለመከራ ከተፈጠረው ከዚህ ስጋችን በሞት ስንለይ ብቻ ነው። በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል የጌታ ዳግም ምጽአትም ሆነ ሌላ ነገረ ፍጻሜአዊ ክስተት እነዚህን አንተ ያነሳሃቸውን ጉዳዮች የሚያስቀር ተስፋ የለም። እኩይና ሰናይ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለ ምንም ከልካይ መሳ ለመሳ በፍጥረታዊው የሰው ልጅ አለም ነበሩ፣ አሉ፣ ይኖራሉም። በእምነት ጉዳይ "ይህ ግዑዝ አለም ተወግዶ ሌላ አለም ይመጣል፣ ያኔም አሁን የምናያቸው ሰቆቃዎች ይቀራሉ" እያልን ውዝፍ/ጉልት (passive) ሆነን የማይመጣ ነገር ከመጠበቅ ወጥተን ቢያንስ ከመሞታችን በፊት ለልጆቻችን የተሻለ ነገ ብንፈጥርኮ እግዚአብሔሩም ትውልዱም ያመሰግኑን ነበር።
4-ክርስቶስ በ70 አም በሆነው ፓሮዥያው ፍርድን ለመፈጸም በሚሆን አላማ፣ በአንድ በኩል አምነው ጽድቅን የተቀበሉትንና የተቀደሱትን ሁሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባለማመን የጸኑትን ኃጢአተኞችንና እርኩሳንን ሁሉ በቋሚነት መድቧቸዋል። ይህንንም ፍርድ ባደረገበት ጊዜ፣ ፍርዱ መላውን የሰው ዘር ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ከ70 አም በኋላ ለጥቆ ውዲህ ባለው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውልና የሚያገለግል ቋሚ አሰራር ሆኖ ይኖራል። (ራእይ 22፥ 10-11) አሁን ያለን የማመን አለማመን አቋምና አቋቋም ምድባችን ከየትኛው ወገን እንደሆነ ስለሚያመለክት ወደፊት የምንጠባበቀው ፍርድ አያስፈልገንም፣ የእግዚአብሔር ቃል "በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።" (ዮሐንስ 3፥ 18) ብሏልና። ወደፊት በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሚከናወን ወይም ሊከናወን ያለ የቀረ አንድም የፍርድ ስርዓት የለም። ከ70 አም በኋላ ለሚኖሩና ለሚሞቱ ሰዎች ከ70 አም በፊት በነበሩና በሞቱ ሰዎች ላይ በተፈጸመው አይነት የሚከናወን መጻኢ የሆነ ትንሳኤም ሆነ ወይም ፍርድ የለም። እግዚአብሔር ምርጦቹን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በእምነት በኩል ለዘላለም ጻድቃን አድርጎ ገልጧቸዋል፣ አጽንቷቸዋልም። ስሞቻቸውም አለም ሳይመሰረት አስቀድሞ በሕይወት መጽሐፍ ላይ ላይደመሰስ ተጽፎአል። ከ70 አም በኋላ ያሉ እያንዳንዳቸው ዳግመኛ የተወለዱ አማኞች በሚሞቱበት ጊዜ በየራሳቸው አዲሱን፣ የማያረጀውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ የማይችለውን፣ ስማያዊውን አካል ይለብሱና በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (በሰማያት) ለመሆን ወዲያውኑ ወደ ክርስቶስ ሀልዎት ይሄዳሉ። ከዚህ ውጭ ያሉ ያልዳኑ ያልተመረጡቱ ያልጸደቁት ናቸው፣ እነርሱም ያላመኑ ስለሆኑ አልተዋጁም። በህይወት መጽሐፍ ላይ የአንዳቸውም ስም የለም። ዕድላቸው በሚቃጠል የእሳት ባህር በዘላለማዊ ኩነኔ ሊቀጡ የተፈረደባቸው ናቸው። በ70 አም ምጽአቱ አንድ ጊዜ ለዘላለም በተሰጠ ብይን ሁሉም የማያምኑ ኃጢአተኞች አሁን በላያቸው ላይ ባለ የእግዚአብሔር ፍርድ ለዘላለም ሊኮነኑ ይቀጣሉ። ላሁኑ እዚህ ላይ ላቁም፣ በመስመሩ መጥተህ ባንግባባም እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ቸር ቆየኝ።

Thursday, August 22, 2019

ፖሮውዥያ

  "የጌታ መምጣት ቀርቦአል"  
ፓሮውዥያ
"እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።" (ያዕቆብ 5፥ 7-8)

"ምጽአት" ለተሰኘው የአማርኛ ቃል አቻ የግሪክ ቃል ፓሮዥያ የሚለው ነው። ሲተረጎምም ቅርብ መሆንን፣ መገኘትን፣ መምጣትን፣ መድረስን ያሳያል፤ በተለይም ክርስቶስ በፍጻሜው ኢየሩሳሌምንና ክፉዎችን ሊቀጣ የሚመለስ መሆኑን፣ እንዲሁም ቀጣይነት ባለውና በማይቋረጥ ሕልዎት አብሮ መሆንን በሚያመለክትበት መልኩ ይተረጎማል [ስትሮንግስ የተሰኘውን የግሪክ ቃላት መፍቻ #3952 ይመለከቷል]።

የጌታ ዳግመኛ ምጽአት ፓሮዥያው የተከናወነው ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ሲል እንደ መግቢያ የጠቀስኩትን የመልዕክቱን ንባብ ከጻፈበት ጊዜ ጥቂት አመታት በኋላ በግምት ሰባትና ስምንት አመታት ያህል ቆይቶ ነው። ያዕቆብ እነዚያን የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን "የጌታ መምጣት ቀርቦአል" ብሎ እስኪመጣ እንዲታገሱና መከራን እየተቀበሉ እንዲጸኑ ሲነግራቸው እና ሲያሳስባቸው፣ በተደራስያኑ ዘመንና ትውልድ ውስጥ ሊፈጸም ስላለው የጌታ ምጽአት እንጂ ሁለትና ሦስት ሺህ አመታት ቆይቶ ገና ወደፊት በብዙ ዘመን ርቀት ስለሚፈጸም ምጽአት እየነገራቸው አልነበረም። በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት በአይሁድ እና በሮማውያን እጅ ይቀበሉት ከነበሩት ከዚያ ጽኑ መከራና ስደት የሚያሳርፋቸው ብቸኛ የተባረከ ተስፋ የጌታ ምጽአት ነበር። መጽሐፍ  ቅዱስ የሚያውቀው ዳግመኛ ምጽአት ደግሞ ያው አንዱ ምጽአት ሲሆን እርሱም ጌታ የተናገረለት እና እነዚያ በጽኑ መከራ ውስጥ የነበሩ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ሲጠባበቁት የነበረው ነው እንጂ ሌላ ምጽአት እንድንጠብቅ ለኛ የቀረልን "የስምንተኛው ሺ" ምጽአት የለም።

የዚህን የፓሮውዥያውን የጊዜ ማእቀፍ የሚያመለክት በያዕቆብ የተነገረን ግልጽ ቃል "ቀርቦአል" የተሰኘው ነው። ይህ  "ቀርቦአል" ለእነርሱ ነው እንጂ ለእኛ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አይደለም። "ቀርቦአል" የተሰኘው ምጽአቱም የተፈጸመው ያኔውኑ በእነርሱ ዘመን፣ በ70 አም ላይ ነው። ያኔ ጌታ በክብር መጥቶአል፣ ከምጽአቱ በፊት ለሞቱ ቅዱሳን ትንሳኤን፣ በሕይወት ለነበሩቱ መለወጥን ሰጥቶአቸዋል፤ እርኩሳንና የማያምኑ ኃጢአተኞችም ዘላለማዊውን ፍርድና ጥፋት ተቀብለዋል። በእርሱ ለሚያምኑ የዘላለምን ሕይወት ለማያምኑ ደግሞ ዘላለማዊ ኩነኔን ሰጥቶ የመጨረሻውን ፍርድ ፈጽሞአል።

ክርስቶስ ያኔ በማያምኑት የእስራኤል ህዝብ ላይ ቁጣውንና ፍርዱን አድርጓል። ከተማይቱን ኢየሩሳሌምን  እና መቅደሱን አውድሞ አጥፍቷቸዋል። የማያምኑት የክርስትና ጠላቶችና አሳዳጆች የነበሩ የዚያ ዘመን አይሁድ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የፈጸሙትን ግፍና ወንጀል የሚመጥን ፍርድና በቀል እንደተቀበሉ ለመረዳት ይደርስባቸው ዘንድ የተነገረባቸውን (ለምሳሌ ዘዳ 28 እና ማቴ 24) የፍርድ ቃል ከታሪካዊው የ70 አ.ም እልቂታቸው ጋር አስተያይቶ ማንበብ የአስተዋዮች መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ከታሪካዊ መዛግብት በላይ እጅግ የጸናው የትንቢት ቃል፣ "ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል" ሲል ጌታ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ነው እንጂ፤ ታሪካዊ መዛግብት የጌታ ትንቢት መፈጸሙን ለማመን ቀዳሚ መሰረታችን አይሆኑም። ያመንነው ቃሉን ብቻ ነው። ተጠራጣሪ ሰዎች ቃሉን ብቻ በማመን ስለማይረኩ ታሪካዊ ማስረጃ ቢቀርብላቸውም መጠራጠራቸውን አያቆሙም። ለእምነት ቤተሰብ ግን የእምነት ቃል ብቻ ይበቃዋል።

ይሁንና ግን የዚያ የ70ው አ.ም የአይሁድ አመጽና በሮማውያን የተወሰደው የማጥቃት ጦርነት በጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረባቸው መለኮታዊው ፍርድ እንደሆነ በውል አለመረዳት ደግሞ በታሪካዊው የስነ ትርጓሜ መረዳታችን ላይ ብዙ ውዥንብርን ሲያስከትል ኖሮአል። ይሁንና በጦርነቱ የቅድስቲቱ ከተማ ቅጥር መሰበር፣ የቤተመቅደሱ መቃጠልና በህዝቡ ላይ የመጣባቸው ዘግናኝ ጥፋት፣ በየዘመናቱ ነብያቱን አሳድደው ሲገድሉና፣ በዘመኑ ምጨረሻ ቅዱሱን ሰው ለአህዛብ ፍርድ በመስቀል እንዲሰቀል አሳልፈው ሲሰጡ ያኔ እነዚያ የእግዚአብሔር ፍርድ በራሳቸው ላይ እንደሚገባቸው የቆጠሩ አመጸኛ ሰዎችን  በትውልዳቸው አግኝቶአቸዋል። ለአህዛብ ፍርድ አሳልፈው የሰጡት ንጹሁን ሰው ክርስቶስን ሲሰቅሉት "ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን" ሲሉ ያኔ ለጥፋታቸው ፈርመው ነበርና።

ይህም የጥፋት ፍርድ ለአሮጌውን ኪዳን የአይሁድ ኃይማኖታዊ ስርዓት (እርሱም የአሮጌው ሰማይና ምድር ነው) ሙሉ በሙሉ ፍጻሜ የሰጠው ነው። ያኔም የአዲሱን ኪዳን መንፈሳዊ የወንጌል መንግስት (እርሱም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው) በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሊቀጥልና ላይቋረጥ ሙሉ በሙሉ ለዘላለም መስርቶታል። እንግዲህ እረፉት! መጽናናት የሞላበት ይህ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ የተባረከው ተስፋ መጻኢነቱ ለእነዚያ ለአዲስ ኪዳን ጸሐፍያንና ለበኩረ ተደራስያኖቻቸው ብቻ ነው፣ እነርሱም በጭንቅ ወደዚያ ሊገቡና ቀኑን ሊቀበሉ በተስፋና በምጥ ኖረዋል፤ ለእኛ ከ70አም በኋላ ላለን ለሁላችን ግን ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ የፈጸመው የምጽአቱ ፓሮውዥያ  ኃላፊ ሆኖአል። 

ይህ ፓሮውዥያ የተሰኘው ቃል በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባባት እንዴትና በምን አግባብ ጥቅም ላይ እንደዋለ ጥቂት ማሳያዎችን ላካፍላችሁና ላብቃ

"እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።" (ማቴዎስ 24፥ 3)

"ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤" (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 23)

"ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።" (1ኛ ተሰሎንቄ 3፥ 12 እና 13)

"በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤" (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 15)

"የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።" (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥ 23)

"ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።" (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 1 እና 2)

"በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል፤" (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 8)

"እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።" (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 4)

"አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።" (1ኛ ዮሐንስ 2፥ 28)

የሚያንቆራጥጡ ተጨማሪ የነገረ ፍጻሜ ኃላፋዊ ምልከታ ቢያሻዎት philologus66 ይተሰኘውን የፌስ ቡክ ግድግዳዬንና፣ እንዲሁም ብሎገሬን  https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_81.html ይጎብኙ። 

ግዛቸው ከበደ \ቄስ\