Saturday, October 12, 2019

ሞት በሌለበት የትንሳኤ ፋይዳ

ሞት በሌለበት የትንሳኤ ፋይዳ። 

1ቆሮ 15፥ 54-57 "ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?  የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤  ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።"

በዚህ የንባብ ክፍል የተገለጸው ሃሳብ ከጊዜ ጋር የተገናኘ መሆኑን ማስተዋል የሚቸግረው ሰው በአጠቃላይ ስለ ትንሳኤም ሆነ ስለ ነገረ ፍጻሜ የሚያስበው፣ የሚያምነውና የሚያስተምረው ነገር ሁሉ የተሳሳተ ይሆናል። የነገረ ፍጻሜን ብልቱን ለማግኘት ጊዜውን ማወቅ ይቀድማል። እዚህ እንደተገለጠው ጊዜው፣ "ሞት ድል በመነሣት" የሚዋጥበት ጊዜ፤ የተጻፈው የትንቢት ቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት ጊዜ ነው። ጊዜው ደግሞ መቼ እንደሆነ ጳውሎስ ቀደም ሲል በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 51-52 ሲናገር "እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።" ይላል። ጊዜው "የኋለኛው መለከት ሲነፋ" ነው። 

መለከቱ እንደሚነፋ የሚጠበቅበት ጊዜ ደግሞ፣ ከእነርሱ መካከል ብዙዎቹ ወይም አንዳንዶቹ ገና በሕይወት እያሉ እንደሚደርስ ጳውሎስ በግልጽ ከሚናገርለት ጊዜ ጋር የሚስማማ ነው። ያም ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም የምትወድቅበት ጊዜ፣ ቤተመቅደሱ የሚፈራርስበት ጊዜ፣ የአሮጌው ኪዳን የክህነት ስርዓት የሚያበቃበት ጊዜ፣ ህጉ የሚወገድበት ጊዜ፣ ወዘተ. እንደሆነ ለማስረዳት በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ከደርዘን በላይ ምስክርነት ማቅረብ ቀላል ነው።

ጳውሎስ ቀደም ሲል በቁጥር 26 ላይ "የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤" ሲል የገለጠውንና፣ የዚህን የመጨረሻው ጠላት የተባለውን  የሞትን ድል መነሳት እዚህ ቁጥር 54 ላይ በጊዜ መደብ ውስጥ የተወሰነ ጉዳይ አድርጎ ያቀርበዋል። ይኸውም ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም የፍርድ ፍጻሜዋን ከሚሰጥበት ጊዜ ጋር፣ ለቤተ መቅዱሱ፣ ለብሉይ ኪዳን የክህነት ስርዓትና ለሕጉ ፍጻሜውን ከሚሰጥበት ጊዜ ጋር፣ ሰውን ከፈጣሪው ለይቶ ባስቀረው በመጨረሻ ለቀረው ሞት ለተባለው ጠላት፣ ማለትም 'የኃጢአት ሞት' ወይም 'የሞት ኃጢአት' ፍጻሜውን ከሚሰጥበት ጊዜ ጋር፣ እንዲሁም በትንቢተ ኢሳይያስ 25፥ 8 "ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።" ሲል የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ከሚያገኝበት ጊዜ ጋር የተቆራኘው ያው አንዱ ጊዜ ነው።

ኃጢአትም ፍጻሜውን የሚያገኘው በዚያው ጊዜ ነው።  ኃጢአት ፍጻሜውን ያገኝ ዘንድ በዳንኤል 9፥ 24-27 "ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።  ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።" ተብሎ የተተነበየው ቃል ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው ያኔ የጥፋት ርኩሰት በሚሆንበት ጊዜ ላይ ነው። የጥፋት ርኩሰት ምንነት ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ ለምትሹ በዚህ ግቡ፤

https://gizachewkr.blogspot.com/2019/02/blog-post.html

የተነሳንበትን ጥቅስ አጠቃላዩን የንባብ ክፍሉን አውደ ምንባብ ግምት ውስጥ አስገብተን ጉዳዩን ስናየው ጳውሎስ በቁጥር 54 ላይ "የሚበሰብሰው"፣ "የሚሞተው" እያለ የሚናገርለት፣ ይህ "ለሞት የተሰጠ ሰውነት" (ሮሜ 7፥ 24 እና 8፥ 10 ተመልከቱ)፣ ይኸውም መዋቲ የሆነው በስባሹ አካል፣ "የማይበሰብሰውን"፣ "የማይሞተውን"፣ በክርስቶስ የሆነውን የሕይወት አካል ይለብሳል፤ ሰውን ከእግዚአብሔር የለየው መንፈሳዊው ሞት፣ እርሱም የኃጢአት ሞት/ የሞት ኃጢአት ድል ተነስቶ በሕይወት ይዋጣል፣ የሚል ነው።

ትንሳኤ ያስፈለገው "ይሻራል" የተባለው "የኋለኛው ጠላት" የሚባል ሞት በሰው ላይ ስለነበረ ነው። ሞት የሚሻርበትን ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ "የኋለኛው ዘመን" ወይም የመጨረሻ ዘመን" ሲል እንደሚጠራው በሚበዙት የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው "የኋለኛው ዘመን" ወይም የመጨረሻው ዘመን" ደግሞ ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ቀድሞ ያለፈ ዘመን መሆኑን ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ መሆን አይጠይቅም። ሞት ያበቃለት ያኔ ነው፤ የሞት አገልግሎት የነበረው አሮጌው ኪዳንና ስርአቱ ሁሉ በ70 አም በእሳት ፍርድ ሲበላ፣ አዲሱ ኪዳንም በክብሩ ብዛት ሲገለጥ፤ ሞትን ሊሽር በተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ሞት የተረታው ሞት ያኔ እስከወዲያኛው ሊቀር ተወግዷል። በወንጌሉም የሚሰበከው የምስራች ይሄ ነው። የዳግመኛ ምጽአቱም ደስታ ይኸው ነው። ያለ ዳግመኛ ምጽአቱ የትንቢት ሙላት አይታሰብም። አስተሳሰባችንን ግን ከዚህ እውነት አርቀን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀውን "የመጨረሻ ዘመን" የሚባል ትምህርት በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ አምጥተን ስንሰነቅርና፣ ፍጻሜውንም ከመጀመርያው ክፍለዘመን ነጥለን፣ ለእኛ ባልተሰጠን ተስፋ ገና ወደፊት ስንጠባበቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀው እንግዳ የሆነ የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ እና "የሥጋ ትንሣኤ"  ተረት ይወለዳል። ከዚህም የተነሳ በቃሉ ምንም ድጋፍ የማይገኝለትንና በእጅጉ እርማት የሚያስፈልገውን "በሥጋ ትንሣኤ አምናለሁ" የሚል፣ ያለ እውቀት የሆነ ምስክርነት ስንሰጥ ኖረናል። ይህ ምስክርነት ግን "በሙታን ትንሳኤ አምናለሁ!" ተብሎ ቢታረም የተሻለ ድጋፍ ከቅዱስ ቃሉ ይኖረናል። "በሙታን ትንሳኤ አምናለሁ!" ስንልም ሙታን ትንሳኤያቸውን አስቀድመው እንደተቀበሉ በታሪካዊነቱ ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት እንደሚጠቀስ ማስረጃና ምስክርነት እንጂ፣ ገና ወደፊት እንደሚፈጸም የሙታን መጻኢ እድል የምናወራው አይደለም።
 
አሁን ግን በዚህ የመንግስት ዘመን ተረግመው በወንጌል ካላመኑት በቀር ሙታንም ሞትም የሉም፤ ይሰማል? ስለዚህ ሙታንም ትንሳኤን፣ ሞትም ሽረቱን ባገኙበት ሁኔታ፣ መጻኢ ትንሳኤ አስፈላጊነቱ ትርጉም የለውም። አሁን ሞት በሕይወት ተውጧል። ሞት ራሱ ሞቷል! እኛም በክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት ስለተቀበልን ከእንግዲህ ወዲያ በመንፈስ መሞት አይቻለንም። ክርስቶስም ሕይወታችን በመሆኑ ለዳንን ለእኛ አካላዊው ሞት ጥቅማችን ሲሆን፣ መንፈሳዊው ሞት ደግሞ ስጋታችን አይደለም። ተስፋ በተገባው የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፍጻሜው ይገለጥ ዘንድ የተጠበቀው የሙታን ትንሣኤ ተስፋም፣ ተስፋው ለተሰጣቸውና ሲጠባበቁት ለነበሩት የመጀመርያው ክፍለዘመን ቅዱሳን ተፈጽሞላቸው አልፎአል። አሁን ግን ለእኛ በወንጌሉ ለምናምን ብሩካን፣ ተጠብቆ ያለውና በጸጋ ወንጌል የሚታደለው ሕይወትና ሕያውነት ነው። ሕይወትንና ሕያውነትን ካመጣው ሕያው ከሆነው ከክርስቶስ የተነሳ፣ በሕያው እግዚአብሔር ፊት ለአዲስ ልደት በሚሆን ሕያው እምነት ለዘላለም ሕያዋን ሆነን እየኖርን ስለሆነ፣ ከዘላለማዊው ሞት ድነን፣ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆነን በምንኖርበት በዚህ የአዲሱ የጸጋ ኪዳን፣ በአዲሱ ስማይና በአዲሱ ምድር ሞት የለም፤ "ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም" ተብሎ ተጽፎአልና። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሕያዋን ኢየሩሳሌም ናት። ትንሳኤም ለሙታን ከአሁን በፊት ሆኖአል እንጂ ገና ወደፊት የሚሆን አይደለም። ሰለዚህ ሞት በሌለበት ትንሳኤ ማስፈለጉ ትርጉም አይሰጥም። ትንሣኤ አስፈላጊነቱ ሞት ይሰለጥንበት በነበረው በአሮጌው የሞት አገልግሎት በታች ተገዝተው ለኖሩና ለሞቱ፣ የቤዛነታቸውንም ቀን እየናፈቁ በመቃተትና በምጥ ለነበሩ የቀደመው ኪዳን ቅዱሳን ነው። እኛ ግን ተፈጥሮአዊውን ሞት በሥጋ ስንሞተው ክርስቶስን በማመን የጀመርነውን ይህንን የማያልፍ ሕይወት ኑሮ ለመቀጠል ያኔውኑ ከዚህ ቁርበት ከሆነ ማደርያችን ተለይተን ወዲያውኑ ወደ ሰማይ እንሄዳለን። ተፈጥሮአዊው ሞት ለክርስቲያን ጥቅሙ የሚሆነው በዚህ መንገድ ነው። ምነው? ቀድሞውንስ ቢሆን በክርስትና ወንጌል የተሰበከልንና ክርስቶስን አምነን የምንጠብቀው የሞታችን ጊዜ ሲደርስ በብጹዓን ስንብት ከጌታ ጋር ለመሆን ወደጌታ እንሄድ ዘንድ አይደለምንዴ? የዘላለም ሕይወትስ እርሱ አይደለምንዴ? በመሰረቱ እኔ ክርስቲያን የሆንኩት የኃጢአቴን ስርየት አግኝቼ፣ በምሞትበት ጊዜ ወደጌታ ለመሄድ ነው፣ ከዘላለም ሕይወት በመለስ ያለው ሁሉ ትርፍ ነገር ነው።

የሙታን ትንሳኤ ግን የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሲጠብቁት የኖሩትና በመጨረሻም በዘላለም ሕይወት ከጌታ ጋር ለመሆን ሞትን ድል በመንሳት ከሲኦል ነጻ የወጡበት የማይደጋገም የአንድ ጊዜ ሁኔታና ክስተት ነው። አሁን ግን እኛ፣ የቅዱሳን ትንሣኤ ከተፈጸመ በኋላ በብዙ የዘመን ርቀት የምንኖርና በክርስቶስ ያመንን ሁሉ፣ ትንሳኤና ሕይወት የሆነውንና የማይሞተውን ክርስቶስን ለብሰናል። በሥጋ ስንሞትና ይህ አሮጌ ቁርበት ሲወልቅ ቀድሞውኑ ለአዲስ ልደት በሚሆን ቅዱስ ጥምቀት ክርስቶስን ለብሰናልና በእግዚአብሔር ፊት ራቁታችንን አንሆንም። ካመንበት ቅጽበት ጀምሮ ለዘላለም በእግዚአብሔር ሕልዎት ውስጥ በሕይወት እየኖርን ነው። የምድር ላይ ቆይታችንን ጨርሰን በማንኛውም ምክንያት በጌታ ሆነን በሥጋ ስንሞት ያኔ ይህንን ሥጋ አውልቀን ጥለን የምንኖረው በአዲሱ መንፈሳዊ አካል በመንፈሳዊው አለም (realm) ብቻ ነው። ክርስቲያን በሥጋው የሚሞተው መጽናናት በሞላበት ደስታ ነው። ሁላችንም በስጋ እንሞታታለን እንጂ በስጋው ሞትን ሳያይ የሚነጠቅ ማንም የለም፤ የማንኛውም ሰው ስጋም ከበሰበሰበት ከመቃብሩ ወጥቶ አይመጣም። ለክርስቲያን የተሰጠ እንዲህ ያለም ተስፋ የለም። እንደ ክርስቲያን ደግሞ ደስ ብሎት የሚሞት ማንም የለም። አምነው የሞቱ በርካታ ቅዱሳን ወንድሞችና እህቶችን ስጋ ቀብሬ አውቃለሁ፣ በሞታቸው ሰአት የሞታቸውን ጣር ሰብሮ በገጻቸው ላይ የታየው ጸዳል በጌታ የመሆን የህይወት ደስታ ነበር። እኔም አንተም አንቺም በዚያ ደስታ እንሄዳለን እንጂ አንፈራም፤ "በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤" ተብሎ ተጽፎአልና። መጽናናት በሞላበት እንዲህ ባለ የእግዚአብሔር ሕይወት ውስጥ የመኖርና የመሞት ሚስጥር ከቀለለብንና፣ የክርስትናን ሕይወት ወደ ምድር ዝቅታ አውርደን፣ ትንሳኤን ቃሉ በማይመሰክርለት የስጋ ሰፈር ያለ አድራሻው የምንፈልገውና የምንጠባበቀው ከሆነ ግን፣ ገና ከወንጌሉ ጋር አልተግባባንም፣ የጥምቀታችንንም ኪዳን አላወቅንም ማለት ነው። 

ስለዚህ ወደፊት ይሆናል ብለን ልንጠባበቀው የሚያስፈልገን የተዳሳሹ ሥጋ ባዮሎጂካል ትንሳኤ ሊኖረን የማይችል እስከሆነ ድረስ፣ የሌለ ነገር ማመንም ሆነ ማስተማር አይገባንም። ምን ይሻላል ጎበዝ? ሰዉ ሊያነበውም ሊሰማውም የማይታገሰውን እውነት ይዘን አፋችንን እንዳንዘጋ ተቸገርንኮ! ለእኛ በእምነት ለጸደቅን ሰዎች ታዲያ በሥጋ ከሞትን በኋላ ምን ይቆየን ይሆን? ለምትሉ፤ በውኑ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ፕሪቴሪዝም የሚሰብከው የተፈጸመው ወንጌል ተስፋ ገዳይ አስተምህሮ ነውን? ከቶ አይደለም። በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን የመጽናናት ቃል ስሙኝና ላብቃ፦ 

"ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።" (ራእይ 14፥ 13)

ሃሌሉያ! እኔ ይህንን የተጻፈ ድምጽ ዛሬም እሰማዋለሁ። እናንተስ አይሰማችሁም? "ከእንግዲህ ወዲህ" ከተባለበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን፣ ደግሞም ለአለምና ለዘላለም በጌታ ሆኖ መሞት ብፅዕና ነው። እረፍትና ብድራት ያለበት፣ ከሚታየው ወደማይታየው የሚደረግ የብፁዓንና የድል ነሺዎች ሽግግርም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፣ "ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና፤ ….ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና" (ፊልጵስዩስ 1፥ 21 እና 23)፤ ሲል መስክሮአል።

እንግዲህ የክርስቲያን "ልዩ ጥቅም" ስለሆነ፣ ሞተን በዚህ የብጹአን ስንብት ለመካፈል ያብቃን! አሜን።

ቸር ሰንብቱ
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/ 

No comments:

Post a Comment