ውድ ኢዮስያስ፣ (ጥያቄህን ባነሳህበት ገጼ ላይ ገብቼ መመለስ ባለመቻሌ በዚህ ገጽ ቀርቤ ላነጋግርህ) በብዙ የራሴ ጥቃቅን ምክንያቶች ዘግይቼም ቢሆን አሁን ስመልስልህ መልሴን ለማንበብ እንደማትሰለች ተስፋ አደርጋለሁ። ጽሁፎቼንና የማስተላልፈውን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ሳይደነብሩ በልብ ስፋት ከሚያዩና ልማድ ከማይተናነቃቸው ጥቂት አንባቢዎቼ አንዱ በመሆንህ ላመሰግንህ እፋልጋለሁ። እኔም የምታነሳቸውን የሰሉ ጥያቄዎችህን በሚገባ አያቸዋለሁ እንጂ እንዳመጣልኝ ልመልሳቸው አልሻም። በእርግጥ በዚህኛው ልጥፌ ላይ ያነሳሃቸው ጥያቄዎች ከዚህ ቀደሞ በጻፍኳቸው የተለያዩ አጭርና ዝርዝር ጽሁፎቼ ላይ ልመለከታቸው መሞክሬ አልቀረም። ስጽፍም አንባቢዎቼ የቀደሙትን ስራዎቼን ያስታውሳሉ ወይም ብሎገሬን ይበረብራሉ በሚል ታሳቢነት ስለሆነ አንዳንድ ጉዳዮችን ከድግግሞሽ ሽሽት የተነሳ ያለ ተጨማሪ ማብራርያ በቀጥታ በማለቴ ከአንዳንድ ደርሶ ተመላሾች ጋራ መተላለፋችን አልቀረም። ፕሪቴሪዝምና ትምህርቱን የሚያቀርብበት መንገድ የብዙዎችን ልማዳውያን (traditionalists) ጅማት የሚፈታ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ዋናው ሸክሜ ግን እኔ ልሄድ በመረጥኩበት መንገድ "ነገሩ እንዲህ ይሆንን?" የሚሉ እምነታቸውን የሚጠይቁና መጻህፍትን የሚመረምሩ ጥቂት ወገኖችን ማገዝ ነው። ጥያቄዎችህን ለማስታወስ ላስቀድምና የኔን መልስ ላስከትል። እንዲህ ነበር የጠየቅኸኝ፦
ቄስ እንድታብራራልኝ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ላንሳ- እንዳንተ እምነት በ70 አ.ም ያኔ ጌታ በክብር መጥቶ፦1- ከምጽሃቱ በፊት ለሞቱ ቅዱሳን ትንሳኤን፣ 2-በህይወት ለነበሩት መለወጥን፣ 3-ለእርኩሳንና ለማያምኑ ሃጢአተኞች ዘላለማዊ ፍርድና ጥፋት እንዲሁም ፣ 4- በእርሱ ለሚያምኑ ደግሞ የዘላለም ህይወት ከተሰጠና፣ 5- ከዛን ጊዜ ጀምሮ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር ያለን ከሆነ፦
ጥያቄ-
1- በ70 አ.ም ተካሄደ ያልከው ትንሳኤና መለወጥ ምን አይነት ትንሳኤና መለወጥ ነበር? ከዛን ጊዜ በኋላ ያለን አማኞች የትንሳኤ ጉዳይስ ምን አይነት ትንታኔ አለው? የትንሳኤውንና የመለወጡን ባህሪ ብታብራራልን (ከዚህ ቀደም ምናልባት ካብራራሃው ደግሞ link ብታጋራን)
2- ከዛ አመት በኋላ ያለን እኛ አማኞች ያልተፈጸመ የምንጠባበቀው ተስፋ አለን?
3- ከዛን ጊዜ በኋላ አዲስ ሰማይና ምድር ከሆነ አሁን የምንኑሮው ኑሮ በአዲስ ሰማይና ምድር ነው? ምክንያቱም የራእይ መጽሃፍ የመጨረሻ ምእራፍ ስለ አዲስ ሰማይና ምድር ሲያወራ በዛ ሀዘን፥ ለቅሶ፥ እምባ...ወዘተ እያለ የሚዘረዝራቸው የማኖሩ ከሆነ በዚህ ዘመን የምናያቸው ስቃዪች፥ ለቅሶዎች፥ እንባዎች...እንዴት ይዳኛሉ? ማለቴ አዲስ ሰማይና ምድር ውስጥ አለን ካልን እነዚህ እኩይ ክንዋኔዎች እንዴት አሁን በምንኖርበት አለም ሊገኙ ቻሉ? የአዲስ ሰማይና ምድር አስተምህሮው የእነዚህን እኩይ ክንዋኔዎች መኖር አይከላከልም?
4- ሃጢአተኞች (እርኩሳንና የማያምኑ) ዘላለማዊ ፍርድ ከተቀበሉ ዛሬ በክርስቶስ ማንነትና ስራ የማያምኑ የፍርድ ሁኔታ መች ሊሆን ነው?
ቄስ ከላይ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች ምናልባትም ለቀጣይ ውይይታችን መነሻ ይሆናል ባይ ነኝ።
¶ እኔም በቀጥታ ወዳነሳሃቸው ጥያቄዎች ስመለስ እነሆ መልሴ፦
1- እንደምታውቀው ትንሳኤ በአጠቃላይ ጻድቃንንና ዓመፀኞችን የሚያካትት መሆኑ፣ በአይሁድም ይጠበቅ የነበረና የቤተክርስቲያንም ተስፋ ሆኖ የኖረ እምነት ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ አጠቃላይ ትንሳኤ ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት ደግሞ በቀኑ መጨረሻ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ መሆኑ በሚበዙት ዘንድ ተቀባይነት አለው። እኔ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ የሚያውቀው የቀኑ መጨረሻ፣ ደግሞም ጌታ እንደተስፋ ቃሉ ተመልሶ የመጣው፣ በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ነው ብዬ ለማመን በቅዱስ ቃሉ ስለምገደድ፣ የዚህን አጠቃላይ ትንሳኤ መፈጸም ጊዜውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ነጥዬ ልረዳ አይሆንልኝም። ለሙታን ትንሳኤ በተቀጠረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጊዜ ላይ የጠራ አመለካከት የያዘ ሰው በትንሳኤ ተፈጥሮና ባህርይ ላይ፣ ማለትም ሙታን በምን አይነት አካል ወይም ሁናቴ ትንሳኤን ይቀበላላሉ በሚለው ላይ ግራ አይጋባም፤ ጊዜው ራሱ የትንሳኤን ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣልና። ትንሳኤ በተፈጥሮው መንፈሳዊ መሆኑንና የትኛውንም ተዳሳሽ ቁስ ማስረጃና ማረጋገጫ አድርጎ የማያቀርብ መሆኑ ግልጽ ነው። የጥንት ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን እንደሚታሰበው ሁሉ ትንሳኤ ተዳሳሽ ስጋዎችን ከመቃብር ውስጥ አውጥቶ ማምጣትን የሚጨምር መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ ለምሳሌ ሄሜኔዎስና ፊስጦስ "ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል" ብለው በማስተማር ማንንም ማሳመን ባልቻሉም ነበር። ስለዚህ ላነሳኸ የ"አይነት" ጥያቄ ቁልፉ "ጊዜው" ስለሆነ የነገረ ፍጻሜን ሀሁ ለመረዳት ኮስተር ብለህ ጊዜውን አጥና። በነገራችን ላይ ቀጣዩ ልጥፌ ስለ አጠቃላይ ትንሳኤ ስለሚያትት ዝርሩን እዚያ ላይ እንመለከተዋለን።
2- ባጭሩ፣ ያልተፈጸመ የምንጠባበቀው ምንም ተስፋ የለም። አለ የሚል ሊያቀርብ ይችላል፣ ያኔ መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ለእምነት ቤተሰቦች ቃሉን፣ ለተጠራጣሪዎች ደግሞ የታሪክ ሰነድ ጠቅሰን እናስረዳለን።
3- በኮስሞሎጂካል ለውጥ የተወከለው ለውጥ የኪዳን እንጂ የግዑዝ አለም ለውጥ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። አሮጌው ሰማይና ምድር እሮጌው ኪዳን ሲሆን የአሮጌው ኪዳን ሀዘን እንባ ልቅሶ የኪዳኑ ቀንበር፣ የሞት እዳና እርግማኑ ሁሉ ነው። ያ ኪዳን እስካለ ድረስ የኪዳኑ መርገምም ደግሞ አለ። በዚያ ኪዳን ስር ከብዷቸው ይቃትቱ የነበሩ ሁሉ፣ ከአሮጌው የሙሴ ሥርዓት ይቀበሉት ከነበረው መከራ ያረፉትና የተጽናኑት አዲሱ ኪዳን ያለ አሮጌው ኪዳን በሆነበት በአዲሱ ሰማይና ምድር ነው። አሁን በጌታ ዳግመኛ ምጽአት የተጀመረው አዲሱ የጸጋ ሥርአት ብዙ መጽናናት ያለበት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሃሴትና ደስታ ነው እንጂ የስጋዊ ተድላና ድሎት አይደለም። የዚህን አለም እውነታ መሸሽ አንችልም። አንተ ያነሳሃቸውን የዚህ ግዑዝ አለም ሃዘንና ስቃይ የምንሻገረው አንድም ለተሻለ አለም ስንሰራበት ነው፣ አልያም ለመከራ ከተፈጠረው ከዚህ ስጋችን በሞት ስንለይ ብቻ ነው። በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል የጌታ ዳግም ምጽአትም ሆነ ሌላ ነገረ ፍጻሜአዊ ክስተት እነዚህን አንተ ያነሳሃቸውን ጉዳዮች የሚያስቀር ተስፋ የለም። እኩይና ሰናይ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለ ምንም ከልካይ መሳ ለመሳ በፍጥረታዊው የሰው ልጅ አለም ነበሩ፣ አሉ፣ ይኖራሉም። በእምነት ጉዳይ "ይህ ግዑዝ አለም ተወግዶ ሌላ አለም ይመጣል፣ ያኔም አሁን የምናያቸው ሰቆቃዎች ይቀራሉ" እያልን ውዝፍ/ጉልት (passive) ሆነን የማይመጣ ነገር ከመጠበቅ ወጥተን ቢያንስ ከመሞታችን በፊት ለልጆቻችን የተሻለ ነገ ብንፈጥርኮ እግዚአብሔሩም ትውልዱም ያመሰግኑን ነበር።
4-ክርስቶስ በ70 አም በሆነው ፓሮዥያው ፍርድን ለመፈጸም በሚሆን አላማ፣ በአንድ በኩል አምነው ጽድቅን የተቀበሉትንና የተቀደሱትን ሁሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባለማመን የጸኑትን ኃጢአተኞችንና እርኩሳንን ሁሉ በቋሚነት መድቧቸዋል። ይህንንም ፍርድ ባደረገበት ጊዜ፣ ፍርዱ መላውን የሰው ዘር ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ከ70 አም በኋላ ለጥቆ ውዲህ ባለው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውልና የሚያገለግል ቋሚ አሰራር ሆኖ ይኖራል። (ራእይ 22፥ 10-11) አሁን ያለን የማመን አለማመን አቋምና አቋቋም ምድባችን ከየትኛው ወገን እንደሆነ ስለሚያመለክት ወደፊት የምንጠባበቀው ፍርድ አያስፈልገንም፣ የእግዚአብሔር ቃል "በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።" (ዮሐንስ 3፥ 18) ብሏልና። ወደፊት በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሚከናወን ወይም ሊከናወን ያለ የቀረ አንድም የፍርድ ስርዓት የለም። ከ70 አም በኋላ ለሚኖሩና ለሚሞቱ ሰዎች ከ70 አም በፊት በነበሩና በሞቱ ሰዎች ላይ በተፈጸመው አይነት የሚከናወን መጻኢ የሆነ ትንሳኤም ሆነ ወይም ፍርድ የለም። እግዚአብሔር ምርጦቹን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በእምነት በኩል ለዘላለም ጻድቃን አድርጎ ገልጧቸዋል፣ አጽንቷቸዋልም። ስሞቻቸውም አለም ሳይመሰረት አስቀድሞ በሕይወት መጽሐፍ ላይ ላይደመሰስ ተጽፎአል። ከ70 አም በኋላ ያሉ እያንዳንዳቸው ዳግመኛ የተወለዱ አማኞች በሚሞቱበት ጊዜ በየራሳቸው አዲሱን፣ የማያረጀውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ የማይችለውን፣ ስማያዊውን አካል ይለብሱና በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (በሰማያት) ለመሆን ወዲያውኑ ወደ ክርስቶስ ሀልዎት ይሄዳሉ። ከዚህ ውጭ ያሉ ያልዳኑ ያልተመረጡቱ ያልጸደቁት ናቸው፣ እነርሱም ያላመኑ ስለሆኑ አልተዋጁም። በህይወት መጽሐፍ ላይ የአንዳቸውም ስም የለም። ዕድላቸው በሚቃጠል የእሳት ባህር በዘላለማዊ ኩነኔ ሊቀጡ የተፈረደባቸው ናቸው። በ70 አም ምጽአቱ አንድ ጊዜ ለዘላለም በተሰጠ ብይን ሁሉም የማያምኑ ኃጢአተኞች አሁን በላያቸው ላይ ባለ የእግዚአብሔር ፍርድ ለዘላለም ሊኮነኑ ይቀጣሉ። ላሁኑ እዚህ ላይ ላቁም፣ በመስመሩ መጥተህ ባንግባባም እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ቸር ቆየኝ።
No comments:
Post a Comment