የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ
፭.
ታላቁ ተልእኮ ከጌታ ዳግም ምጽዓት በፊት ተጠናቆአል። የሐዋርያቱና የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በትውልዳቸው ውስጥ ፈጽመው ሰብከዋል። የዚያን ጊዜው አለም፣ ይኸውም የሮም አለም መላው የአህዛብ ምድር ከኢየሩሳሌም ከይሁዳ ጀምሮ በሰማርያ ሁሉ እስከ ምድር ዳርም ድረስ በእነርሱ ምስክርነት ተዳርሶአል። የጌታንም ትእዛዝ ፈጽመዋል። ይኼ ማለት ግን የወንጌል ስብከት በጌታ ምጽዓት አብቅቶአል፣ ቆሞአል ማለት አይደለም፤ ሲጀመር ወንጌል ቅዱስና የማይለወጥ የዘላለም ወንጌል ነው። በጌታ ዳግም ምጽአትም ሆነ በትንሳኤ የሚቆም ሳይሆን ይልቁኑ ለዘላለም የሚሰበክ እንደሆነ ቃሉ ያስተምራል። ስለዚህ በጊዜውም አለጊዜውም ደስ እያለን ወንጌልን የምንሰብከው፣ ስራችንና እድል ፈንታችን ስለሆነ ነው እንጂ፣ የዘመኑ ፍጻሜ ስለደረሰ ወይም የጌታን ምጽአት ለማፋጠን አይደለም። እርሱ አልፎአል!
♦የጥፋትን እርኩሰት ባዩ ጊዜ፣ ከይሁዳ ሁሉ ወደ ተራሮች ሸሽተው ማምለጥ እንዳለባቸው( ማቴ 24፣ 15- 20)።
እነዚህ ሁነቶች “ይህ” የተባለው የዚያ አንድ ትውልድ ሁነቶች ናቸው፡፡ ጆሳፈስ እንደ ጻፈው "ቤተመቅደሱ በተደመሰሰ ጊዜ የቲቶ ሰራዊት የሮማዊያን ግርማ ምልክት የሆነውን SPQR የተጻፈበትንና የሮምን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና የሕዝብ ኃይልና ብዛት የሚወክል የንስር ምልክት ይዘው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ዘልቀው በመግባት በዚያ አስቀመጡት፤ በዚያም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በግንባራቸው ወድቀው ቄሳርን አመለኩ" ሲል ይዘግባል /Wars, መጽሐፍ 6፣ ምዕራፍ 6 አንቀጽ 1/፡፡ ይህ እንግዲህ ቤተ መቅደሱን ያረከሰና በቅድስት ከተማ ላይ ጥፋትን ያደረገው ርኩሰት የመጨረሻ ተግባር ነው፤ የቁጥር 15 የጥፋት ርኩሰት በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ግልጽ በሆነ ቃል ቀርቦልናል፡፡ ይህ የጥፋት ርኩሰት የጀመረው በሉቃስ 21÷ 20 እንደተዘገበው ገና ኢየሩሳሌም በሮማውያን ጦር ተከባ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡
ወንጌላዊው ሉቃስ ይህንን የጥፋት ርኩሰት እንዴት እንደምናውቅ ተርጉሞ እንዲህ ሲል አቅርቦልናል “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ” (ሉቃስ 21÷ 20-21) ይላል፡፡
ኢየሱስ ሐዋርያቱን ነቅተው እንዲመለከቱ ከነገራቸው ብዙ ነገር መካከል፣ ኢየሩሳሌምን የሚከባት ሠራዊት ዋነኛው ምልክት ነው፡፡ ያ መሆን ሲጀምር ያ እርሱ በትንቢት የተናገረለት ጥፋት እና ፍርድ እንደቀረበና ጊዜው እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ሊመጣም ባለው እልቂት ከቅዱሳኑ መካከል ማንም እንዳይካፈል ፈጥነው በችኮላ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ አምልጠው በሽሽት መውጣት አለባቸው፡፡ የጥፋት ርኩሰቱ ገና ሲጀምር በይሁዳ ያሉ ፈጥነው ከዚያ እንዲወጡ የሚያሰጠነቅቅ ቃል በማቴዎስ 24÷ 16 ላይ እናገኛለን፡፡
ማቴ 24÷ 16 "በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥"
ይሄ በተለይ ለደቀ መዛሙርቱና በይሁዳ ለሚገኙ ለዚያን ዘመን ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያና መመርያ ነበር።
በ68 ዓ.ም በጦርነቱ መሃል ኔሮ በቤተ መንግስቱ ውስጥ ራሱን ካጠፋ በኋላ፣ ኢየሩሳሌምን ለመሰባበር ዘምቶ የነበረው የሮማውያን ጦር ዋና አዛዥ ጀነራል ቨስፓሲያን ወደ ሮም በመመለስ አዲሱ ተተኪ ንጉሰ ነገስት ለመሆን ውጊያ አደረገ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ክርስቲያኖች በማቴዎስ 24÷ 16 ያለውን ማስጠንቀቂያ ስላስተዋሉ ኢየሩሳሌምን ለቀው ወጡ፤ አይሁድ ግን በተቃራኒው የቨስፓሲያንን እና የጦሩን ወደ ሮም መመለስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነላቸው የድል መንሳት ምልክት አድርገው ስለ ወሰዱት በኢየሩሳሌም ከቀድሞው ይልቅ በብዙ ቁጥር በመሰባሰብ አመጹን ቀጠሉበት፡፡ ሮማውያንም ተመልሰው መጥተው ከተማይቱን ፈጽመው አወደሟት፡፡
(ወንድም መልካ ዊኪፒዲያን ጠቅሶ ዲያስፖራውን ጨምሮ መላው አይሁድ እንዴት የጦርነቱ ሰለባ እንደሆኑ የጻፈውን ማስታወሻ ማንሳት እፈልጋለሁ)
የሚቀጥለው ታሪካዊ ትንታቴ ዊኪፒዲያ ድህረ ገፅ ላይ ስናነብ፦ በ70 አመተ ምህረት ከተለያየ የአለም ክፋሎች ተጉዘው የፍሲካን በአል ለማክበር ወደ እየሩሳሌም የመጡ አይሁዶች ማምለጥ ስላልቻሉ በሮማዊያን ወራሪ ጦር እንዳለቁ ይጠቁመናል ፦
"According to Josephus, 1.1 million non-combatants died in Jerusalem, mainly as a result of the violence and famine. Many of the casualties were observant Jews from across the world such as Babylon and Egypt who had travelled to Jerusalem wanting to celebrate the yearly Passover but instead got trapped in the chaotic siege." [ትርጉም፦ ጆሴፈስ እንደዘገበው ከሆነ፣ 1,1 ሚልዮን የሚገመቱ በጦርነቱ መሃል የተጨፈጨፉ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተገድለዋል። አብዛኞቹ የጦርነቱ ሰለባዎች እንደ ባቢሎን እና ግብጽ ካሉ ሩቅ ሃገር ተጉዘው ታዋቂ የሆነውን አይሁዳውያንን ዓመታዊውን የፋሲካ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ዲያስፖራዎች ናቸው። ከከተማይቱ ሊወጡ እንዳይችሉ ሆነው የተታለሉና የተጠመዱ ነበሩ።]
በ60ዎቹ ዓ.ም አጋማሽ ላይ ሮማውያን ይሁዳን እና ኢየሩሳሌምን በጦርነት አጥቅተው በ70 ዓ.ም መላውን አገሪቱንና ቤተ መቅደሱን ጭምር እንዳወደሙ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከ 1,000,000 በላይ የሚሆኑ አይሁድ በጦርነቱ ተገድለዋል፣ የተረፉትንም ሮማውያኑ ማርከው በመውሰድ የሚበዙትን በየክብረ በዓላቱ ለጣኦቶቻቸውና ለነገስታቶቻቸው ክብር መስዋዕት አድርገዋቸዋል፤ የቀሩትንም ባሪያዎችና ግዞተኞች አድርገው ሸጠዋቸዋል፡፡ ቅድስት ከተማቸው፣ ቤታቸውና ምድራቸው፣ የተቀደሰው መቅደሳቸው፣ እንዲሁም እንደ አይሁድ የነበራቸው የአኗኗር ዘይቤአቸው ሁሉ ሙሉ በሙሉ ፈጽሞ ተደምስሶ ጠፍቶአል፡፡
♦ሆኖ የማያውቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ እንደሚሆን( ማቴ 24፣ 21- 22)።
ኢየሱስ “በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል” (ማቴ 23÷ 35-36) ሲል የተናገረው ፍርድና ፍጹም ጥፋት ይህ ነበር (ማቴ 23፥ 37-38)፡፡ የአይሁድ ሕዝብ በነዚሕ የጦርነት ዓመታት ያለፉበት አስፈሪ ሁኔታ እና መከራ ኢየሱስ በትንቢቱ ከአሁን በፊት ሆኖ የማያውቅ “ታላቁ መከራ” ሲል የጠራውን (ማቴ 24÷ 16-22) ክፉ ጊዜ ፍጻሜ ይሰጠዋል፡፡
ሮማውያኑ ያንን ከአይሁድ ጋር የገጠሙትን ጦርነት ቀጥለው ባሉበት ጊዜ እጅግ ጨካኞች በመሆን የሚያደርጉትን ሁሉ በከፋ በቀል ያደረጉ ነበር፡፡ ብዙ ደም መፍሰስ በምድሪቱ ሁሉ ሲሆን ቤቶች በእሳት ይጋዩ ነበር፡፡ በይሁዳ አውራጃዎችና በቅድስት ከተማ በኢየሩሳሌም የኖሩ የነበሩ ሕዝቡም ሁሉ የሚበሉት ስላልነበራቸው ምግብ ለማግኘት ሲሉ እርስ በእርሳቸው በግልጽና በከፋ ጭካኔ ይተራረዱ ነበር፣ እናቶችም የገዛ ልጆቻቸውን ቀቅለው ይበሉ ነበር፡፡ ስለዚህ መከራ ምን ተብሎ እንደተነገረ ልብ በሉ፣ "ምንም የሚስተካከለው የለም" ነው የተባው፡፡ የኢየሩሳሌም ውድመት ማለት በመለኮታዊው ፕሮግራም ውስጥ የሚሰጠው ትርጉም ከአንዲት የአይሁድ ከተማ አወዳደቅ በላይ ከፍ ያለ ነው፣ ይህ ውድመት ማለት የአሮጌው ኪዳን እስራኤል ውድመትና ፍጻሜ ማለት ነው፡፡
ስለ ኢየሩሳሌም መፈራረስ የተጻፉ በርካታ የታሪክ መዛግብት ስለ እነዚያ ሊታመኑ የማይችሉ በአይሁድ ሕዝብ ላይ ስለደረሱ የስቃይ አይነቶች በግልጽ ይነግሩናል፡፡ በተወደደችው ከተማና በገዛ ሕዝቡ ላይ ሊመጣ ያለውን ይህንን ታላቅ ጥፋት እና አስፈሪ ፍርድ በመንፈሱ እያየ ወደ ከተማይቱ ሲገባ፣ ኢየሱስን እንዲያለቅስ አድርጎታል፡፡ ሉቃስ በምዕራፍ 19 ይህንን ሁኔታ እንዲህ ሲል ይነግረናል፦
“ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።” (ቁጥር 41-44)
[እጅግ የሚገርመው አንዳንድ ዘመን ቆጣርያን የሆኑ የመጻዒነት አመለካከት ተከታዮች በዚህ ጥቅስ ላይ ተገቢ የሆነ ትርጉም ሰጥተውና ፍጻሜውንም ከ70 ዓ.ም ሁነት ጋር አገናኝተው አቅርበው ሳሉ በሌሎቹ የጌታችን ትንቢቶች ግን የማይመስል አውድ ዘለል ትርጉም መከተላቸው ነው፣ ለምሳሌ በቀለ ወ/ኪዳን፣ ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው? ገጽ 36-37]።
ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ሴቶች በተናገረውና በማቴዎስ 24 ቁጥር 19 ላይ “በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” ሲል የተናገረው ተመሳሳይ እንደሆነ አስተውሉ። ይህ በማቴዎስ ያለው ጥቅስ ሕጻናት ልጆች ላሏቸው ሴቶች ወደ ተራሮች ሸሽቶ ለማምለጥ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ያመለክታል፡፡ በዚህ በሉቃስ “ያልወለዱ ማህጸኖች ብጹአን ናቸው” የሚለው በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጣውን ታላቅ መከራ ሲያመለክት፣ ጊዜውን እጅግ ክፉና አስጨናቂ የሚሆን ስለሚያደርገው፣ በብዙ ሥቃይ ውስጥ የሚታለፍበትም ጊዜ ስለሚሆን ያኔ ወላጅ ከመሆን ወይም ልጅ ያለው ሰው ከመሆን ልጅ የሌለው ሰው መሆን እጅግ የተሸለና የሚመረጥ ይሆናል፡፡
♦ ማቴዎስ 24÷ 28 ስለ አሞሮች መሰበሰብ ይናገራል፡ ፡
ማቴ 24÷28 "በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ።"
አሞራ የሮማውያን ምልክት ነው፡፡ በሌላ አባባል ሮማውያን መሰብሰብ በሚጀምሩበት ጊዜ ያኔ እስራኤል የሚዘነጣጠል በድን ሆኖአል ማለት ነው፡፡
“በዚያን ጊዜ ተራራዎችን በላያችን ውደቁ ኮረብቶችንም ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ” (ሉቃ 23÷ 30) የሚለው በሕዝቡ ላይ የሚመጣውን እጅግ የበዛ ጭንቀት፣ ለመሞት እንኳ እስኪመኙ ድረስ በጭንቀትና ግራ በመጋባት ውስጥ እንደሚወድቁ የሚገጥማቸውን ያንኑ ክፉ ጊዜ ያመለክታል፡፡
የዮሐንስ ራዕይም መጽሐፍ በተመሳሳይ አገላለጽ በአይሁድ ሕዝብ ላይ ስለሚመጣው ስለዚሁ የጭንቀትና ግራ የመጋባት ጊዜ ይናገራል፡፡ በራዕይ 6÷ 15-17 ዮሐንስ የጌታን የኢየሱስን የራሱን ቃላት ተጠቅሞ በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጠረውን ያንንው የተስፋ መቁረጥ ሥሜት እና የጊዜውን ሁኔታ ያብራራል እንዲህም ሲል ይናገራል፦
“የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ተራራዎችንና ዓለቶችንም በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።”
እነዚህ ሁሉም ጥቅሶች በአይሁድ ሕዝብ ላይ ሊመጣ ያለውን የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያመለክቱ ነበሩ፣ ይኸውም በቅርቡ በእነዚያ ለኢየሱስ ያለቅሱ በነበሩ ሴቶች ዘመን በእነርሱ እድሜ የሚደርስ ቶሎ የሚመጣ ፍርድ ነበር፡፡
በሕዝቡ ላይ ሊደርስ ያለውን ያንን ሁሉ አስፈሪ ነገር በማወቁ ጉዳዩ የኢየሱስን ልብ በሓዘን እንዳደቀቀው ተመልከቱ፡፡ ምንም እንኳ እንደ ድል አድራጊ ንጉስ ወደ ኢሩሳሌም እየገባ ያለ ቢሆንም ፣ ልቡ ስለሕዝቡ ከመሰበሩ የተነሳ ያለቅስ ጀመር። ከቀናት በኋላ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ለእነዚያ ለሚያለቅሱለት ሴቶች እጅጉን እንደራራላቸው እንመለከታለን፡፡ ኢየሱስ ሕዝቡን እንዴት እንደሚወዳቸው ተመልከቱ። ሊመጣ ካለው ጥፋት ሊያድናቸው ይመኝ እንደ ነበር አሰተውሉ። ሕዝቡ ግን እርሱን መስማት አልፈለጉም ነበር። ለእነዚያ ላመኑና በዘመኑ ኢየሱስን ለተከተሉ ሰዎች ጳውሎስ “ከሚመጣው ቁጣ” ትድናላችሁ ይላቸዋል (1ተሰ1÷ 10)፡፡ በይሁዳ ላይ ሊደርስ ካለው እልቂትና ጥፋት በእርግጠኝነት ሊድኑ የሚችሉት “ኢየሩሳሌም በሠራዊት ተከባ ስታዩ ፈጥናችሁ ወደ ተራሮች ሽሹ” ያለውን የኢየሱስን መመሪያና ትዕዛዝ የታዘዙ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦
No comments:
Post a Comment