በጌታ የተወደዳችሁ ቅዱሳን ወንድሞችና እህቶች የፍኖተ ኢየሱስ ወ/ሉ/ ቤተክርስቲያን ምዕመናንና መሪዎች ሰላም ይብዛላችሁ።
ከሁሉ አስቀድሜ በአካል ርቄ ካለሁበትም እንኳ በክርስቶስ ኢየሱስ የተካፈልነውን ንጹህ ፍቅርና ህያው ህብረት ሳስበው ብዙ መጽናናትን እንደሚሰጠኝ፣ በእናንተም ዘንድ እንዲሁ እንደሚሆን ሳስብ ሁልጊዜ ደስ እንደሚለኝ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ናፍቆታችሁም አብሮኝ ይኖራል፤ በጸሎታችሁም እንደምታስቡኝ አውቃለሁ። እግዚአብሄር አብ ቁርባናችሁን ያስብ፣ ጸሎታችሁንም ይሰማ!
ማኅበረ ምዕመናናችን ካለባት የእረኝነት ኃላፊነት አንጻር በመካከላችን በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ሊንሸራሸሩ የሚችሉ አስተምህሮታዊ የአመለካከት ልዩነቶች የሚያዙበትን አግባብ ማድነቅም እወዳለሁ። እኔም እንደ አንድ ቃሉን ሊማርና ሊያውቅ እንደሚፈልግ ሰው በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ላይ በግሌ ያደረግሁትን የአቋም ለውጥና በማኅበራዊ ሚድያ ላይ የለቀቅኋቸውን ጽሁፎች በተመለከተ ቤተክርስቲያኔ ከሉተራዊ የእምነት መግለጫዎቿ አንጻር ተመልክታ ጽሁፎቹና የሚያስተላልፉት መልእክት የማኅበረ ምእመናንዋ አቋም እንዳይመስሉና ብዥታን እንዳይፈጥሩ በሚል የተላለፈውን ውሳኔም አከብራለሁ። የውሳኔውን ፍሬ ነገር በማህበራዊ ሚድያ ተለጥፎ ያነበብሁት ቢሆንም፣ ሙሉውን ስሜት ለመረዳት እህታችን ምህረት አስፋው እዚህ ሰሜን አሜሪካ በመጣች ጊዜ አግኝቻት ከእርስዋ የበለጠ ተረድቼአለሁ። በግሌ ያደረግሁትንም የአመለካከት ለውጥ የኔ የራሴው የግሌ አቋም እንጂ የቤተክርስቲያኒቱ አመለካከት አለመሆኑን በመግለጫው ላይ መንጸባረቁ ተገቢና ከልቤ የምደግፈው ነው። ምንም እንኳ በጉዳዩ ላይ መልስ እንድሰጥበት የቀረበልኝ ይፋዊ ጥያቄ ባይኖርም ማህበረ ምእመናኔ ልትሰማኝ ትእግስት እንደማትነፍገኝ ስለማስብ በዚህች ጽሁፍ የሚሰማኝን ለመግለጥ እወዳለሁ።
ጌታ በጸጋው ያዳነን ሁላችን በግላችንም ሆነ በማኅበር መጽሐፍ ቅዱስንና አስተምህሮቱን ለማወቅ የምናደርገው ጥረት መቼም ቢሆን ምሩቅ የማንሆንበት፣ ሁልጊዜም ቢሆን የምንማረው ተፈጥሮአዊ ልምምድ ነው። ሁል ጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ አለመድረስ እንጂ ሁል ጊዜ ተማሪ መሆን በጎ ነው። በዚህ የተማሪነት የልምምድ ሂደት ውስጥ መደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ የእግዚአብሔርን ቃል እያጠናን እውነትን ስንፈልግ፣ ለብዙ ጊዜ በኃይማኖት፣ በልማድ፣ በባህል፣ በትውፊት ወዘተ ሲነገረንና ስንሰማው የኖርነውን፣ እውነት መስሎንም የያዝነውን ወይም ሌሎች የያዙትን አስተሳሰብ መጠየቃችንና መሞገታችን አይቀርም። የቤሪያ ሰዎች ተሞክሮና የቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ታሪክ የሚነግረን ቃሉን እየተማሩ የሚጠይቁ ሰዎች የሚደርሱበት የአቋምና የአመለካከት ለውጥ ሁልጊዜም ቢሆን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መገለጫ መሆኑን ነው።
ለእኔ እንደሚገባኝ ማንም ሊያሻሽለውና ሊለውጠው የማይችለው፣ እምነታችን የቆመበት መገለጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት "ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠ" ብርሃን፣ የቅዱሳን እምነትና ልምምድ ሁሉ ሚዛንና ሥልጣን፣ የቤተክርስቲያንም ፈጣሪ ቅዱስ ቃሉ ነው። ሁሉም ነገር ከቃሉ ኋላ እንጂ ከቃሉ በፊት ምንም የለም። ሉተራን የተሃድሶ መሪዎችም መነሻቸውን "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) ያደረጉት በዚሁ የዳኑ ሰዎች መርህ ነው። ይህ መገለጥ በእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። ስነ መለኮታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ምርምር ግን በባህርዩ ርምደታዊ (progressive ) ነው። ለዚህም ነው በቤተ ክርስቲያን ዘመንና ታሪክ ውስጥ በልዩ ልዩ ጎራ የተሰለፉ፣ የሚደጋገፉና የሚቀዋወሙ ዘርፈ ብዙ የሆኑ አመለካከቶች (views) እና የአስተሳሰብ ልዩነቶች (school of thoughts) ሲንሸራሸሩ የሚኖሩት። ይህ ሂደት መቼም ቢሆን አይቆምም። ሰዎች እውነት ነው ብለው ያነገቡትንና ብዙ ዋጋ የከፈሉለትን አመለካከት አንድ ቦታ ላይ ውድቅ የሚያደርጉበት አጋጣሚ ተፈጥሮአዊ ነው። በተለይም የእግዚአብሔር ቃል ብቻ አመለካከታችንና እምነታችንን እንዲፈትሽና እንዲፈርድ ስንፈቅድ በሂደቱ ውስጥ እያመመንም ቢሆን የምንሽረውና የምናጸናው ነገር እንደሚኖረን እገነዘባለሁ።
ወደ ዋናው ጉዳይ ልምጣና፣ ሉተራኑንም ጨምሮ በአብዛኛው የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያለውና ሁሉም የተቀበለው የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ መጻኢነት (futurism) እንደሆነ ግልጽ ነው። መጻኢነት በትምህርቱ ዳግመኛ ምጽአት ገና ወደፊት የሚጠበቅ ነው እንጂ እስከ አሁን ድረስ ገና አልሆነም፣ የትንቢትም ፍጻሜ ገና ወደፊት የሚጠበቅ ነው ሲል የሚያምን የነገረ ፍጻሜ ዘርፍ ነው። እኔም በአንድ ወቅት መጻኢነት ሊመልስልኝ ካልቻላቸው ጥያቄዎቼ ጋር ይህንንው አመለካከት ስከተልና ሳስተምር ረጅሙን የጌታ ቤት ቆይታዬን አሳልፌአለሁ። ምንም እንኳ ያደግሁበትና አሁንም የምኖርበት ሉተራዊው የአስተምህሮ መሰረቴ በነገረ ፍጻሜ ላይ ያሉብኝን ጥያቄዎች በበቂ ሊያስተናግድ የሚችል ሆኖ ባላገኘውም ቅሉ፣ "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) የተሰኘው የሉተራውያን መገለጫ መጻኢነትን እንድተው ገፊ ምክንያቴ ነበር።
እንደ አንድ ሉተራዊ አማኝ ጥቂት ለማይባሉ አመታት ነገረ ፍጻሜን ሳጠና ይታገለኝ የነበረው አሳብ "የእግዚአብሔር ቃል በንጹህ የተብራራባቸው ናቸው" የምላቸው ጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎች በመጨረሻዎቹ ነገሮች ላይ የያዙት አንቀጽ ነው። ነገር ግን ከማብራርያው በላይ "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) እንዲናገረኝ ስፈቅድ በነገረ ፍጻሜ ላይ ያሉብኝ ጥያቄዎቼ ሁሉ የጸሐይ ትኩሳት እንደወረደበት የበረዶ ግግር ይሟሽሻሉ። ስለመጨረሻው ዘመንና ስለ ዳግመኛ ምጽአቱም ለብዙ ጊዜ ትክክል መስሎኝ የያዝኩት የመጻኢነት አስተሳሰቤም የሚቆምበት መሰረት ያጣል። ነገረ ፍጻሜን ጨምሮ ማናቸውንም መንፈሳዊ ጉዳይ በብቃት ማስተማር ያለበት ቅዱስ ቃሉ ብቻ ነው። ይህ የአቋም ለውጥ ምንም እንኳ ቀድሞ ከተያዝሁበት አስተሳሳቤ ጋር ወይም ቤተ እምነታዊ (denominational) ባህልና ልማድ ጋር የሚጋጭ ቢሆንም አሁንም ምኞቴ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ብቻ ማስተማር ነው።
ማርቲን ሉተርንና የቤተክርስቲያን አዳሾችን አስተምህሮ ለመቃወም፣ የተጀመረውንም የተሃድሶ እንቅስቃሴ ሃሰት ነው ብሎ ለመፈረጅ፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መምህራን ጥንታውያኑን የእምነት መግለጫዎችና አጠቃላዩን የቤተክርስቲያን ታሪክ ይጠቀሙበት እንደነበር ከተሃድሶው ታሪክ እንረዳለን። ንጉሱ ቻርልስ አምስተኛ እንኳን በሉተር የተሃድሶ አስተምህሮ ላይ አስተያየት ሲሰጥ "ከወንድሞች አንድ ግለሰብ ብቻውን መላውን የክርስቲያን ማህበረሰብ ተቃውሞ ቢቆም ስህተት መሆኑ የተረጋገጠ ነው፣ አለበለዚያ ላለፉት ሺህ አመታትና ከዚያ በላይ ክርስትና ተሳስቶ ነበር ማለት ነው" ሲል ተናግሮ ነበር። ልክ እንደዚሁ ዮሐነን ኤይክ ሉተርን ተቃውሞ ባቀረበውና ዘለፋ በተሞላበት ክርክሩ "ቅዱሳት መጻህፍትን ጠቅሰህ እንድትደመጥ የምታቀርበው ልመና ሁልጊዜ በመናፍቃን ሲተገበር የነበረ ተግባር ነው። እጅግ የተከበሩና ታዋቂ የሆኑ ሰዎች እዚህ እያሉ እንዴት አንተ ከእነሱ የተሻለ እንደምታወቅ አድርገህ ስለ ራስህ ታስባለህ? ቅዱሳት መጻህፍትን የምትረዳ አንተ ብቻ እንደሆንክ ስለሚመስልህ ጥያቄ እንኳ ለማቅረብ ምንም መብት የለህም። እውነተኛ ሕግ ሰጪ የሆነው ክርስቶስ ባቋቋመው፣ በመላው አለም በሐዋርያት ሲታወጅ በነበረው፣ በሰማእታቱ ደም በታተመው፣ በቅዱሳን የአብያተ ከርስቲያናት የጉባኤ ውሳኔ በጸናው፣ ሁሉም አባቶቻችን እስከ ሞት ድረስ የታመኑለት ተብሎ በቤተክርስቲያን ሲገለጥ በኖረው በተቀደሰው ቀጥተኛና ትክክለኛ እምነት (Orthodoxy) ላይ የገዛ ራስህን ፍርድ ልትጭን ትወዳለህን?" ነበር ያለው።
በነዚህ የማርቲን ለተር ተቃዋሚዎች ብይን ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ይመስለኛል፣ ለሺህና ከዚያ በላይ ለተቆጠረ አመታት የኖረ የቤተክርስቲያንን ታሪክና ጥንታውያኑን የእምነት መግለጫዎች የሚያፋልስ ማንኛውም አስተምህሮ የስህተት ትምህርት ነው ማለት ነው። የተሃድሶው እንቅስቃሴ አስተምህሮ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለሺህ አመታትና ከዚያ በላይ ሲታመን የነበረውንና ጥንታዊውን የእምነት መግለጫ የሚያፋልስ ነበር ማለት ነው። ስለዚህም በዚህ አተያይ የተሃድሶው እንቅስቃሴ አስተምህሮ የስህተት ትምህርት ነበር ማለት ነው። ተቃዋሚዎቹ ሉተርንና አብረውት የቆሙትን በቅዱሳት መጻህፍት መሰረት ሊሞግቱአቸው ባለመቻላቸው የተሃድሶውን አስተምህሮ ውድቅ ለማድረግ ከቅዱሳት መጻህፍት ርቀው የተንጠለጠሉት በቤተክርስቲያን ታሪክና በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎች ላይ ነበር። ያም ሆኖ ሉተር በተቃውሞ የተሰበሰበበትን ጉባኤና የጉባኤው ውሳኔ የተንጠላጠለባቸውን ጥንታውያን የእምነት መግለጫዎች ውድቅ አደረጋቸው። ይህንንም ያደረገው እነዚያን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጉባኤ ውሳኔ የተዘጋጁ እንጂ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ያልተሰጡ የእምነት መግለጫዎችን ስለማያከብራቸው ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ተክተው የሙግት መሰረት እንዲሆኑ ስላልፈለገ ነው።
ሃሳቤን ግልጽ ለማድረግ ዛሬም ቢሆን የኃላፋውያንን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ውድቅ ለማድረግ በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎችና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ሙግትን መመስረት ትክክል ነው ብለን የምናምን ከሆነ፣ እንግዲያውስ ንጉሱ ቻርልስ አምስተኛና ዮሐነን ኤይክ በጥንታውያኑ የእምነት መግለጫዎችና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ሙግታቸውን መስርተው የተሃድሶውን አስተምህሮ ስህተት ነበር ብለው መበየናቸው ትክክል ነበር ማለት ነው።
ስለ ነገረ ፍጻሜ የሚናገሩ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን የሚገኙ ሁሉንም ምንባባት አገላብጬ በአንክሮ ስመለከት የደረስኩበት ድምዳሜ በብዙወች ዘንድ ታዋቂና እድሜ ጠገብ የሆነው የመጻኢነት አመለካከት ትምህርቱን ያቆመው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሳይሆን ይልቁንም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ የቤተ እምነታዊ ትውፊት ላይ መሆኑን ነው። የቤተ እምነታዊ ትውፊት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በየዘመኑ ከተፈጠሩ የአስተሳሰብ ልዩነቶች የተወለደ ጠቃሚ ሰነድ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጠ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። እርሱም ቢሆን የሚመዘነውና የሚዳኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው።
በክርስቶስ አካል ውስጥ በመጻኢነት ጎራ ተሰልፈው እርስ በርሳቸው በጥቂቱ የተለያዩና በብዙ የሚመሳሰሉ፣ በተለያዩ የእምነት ክፍሎችና ቤተ እምነት ውስጥ የሚንጸባረቁ ነገረ ፍጻሜአዊ አመለካከቶች በርካቶች ናቸው። በተቻለኝ መጠን የሁሉንም የአስተምህሮ መሰረትና ታሪካዊ ዳራ ለማየት ሞክሬአለሁ። የአልቦ ሺህ አመት መንግስት (Amillennialism) አመለካከት፣ የድህረ ሺህ አመት መንግስት (Post Millennialism) አመለካከት፣ የታሪካውያን (Historicism) አመለካከት፣ የታሪካዊ ቅድመ ሺህ አመት መንግስት (Historic Premillennialism) አመለካከት፣ የዘመን ቆጣሪው የቅድመ ሺህ አመት መንግስት (Dispensational Premillennialism) አመለካከት፣ የቅድመ መከራ ንጥቀት (Pre- Tribulation Rapture) አመለካከት፣ ወይም ቅድመ ቁጣ ንጥቀት (Pre Wrath Rapture) አመለካከት፣ የከፊል ንጥቀት (Partial Rapture) አመለካከት፣ በመከራው መካከል የመነጠቅ (Mid Tribulation Rapture) አመለካከት፣ የድህረ መከራ ንጥቀት (Post Tribulation Rapture) አመለካከት ወዘተ.. ማለቂያ የሌለው የነገረ ፍጻሜ የአመለካከት ልዩነቶች ነበሩ ወደፊትም ይኖራሉ። ያው ሁሉም ግን ማጠቃለያቸው መጻኢነት ነው። በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተ እምነቶች ውስጥ ከልዩ ልዩ የነገረ ፍጻሜ አመለካከቶቻቸው ጋር በዘመን ቆጣሪነት አስተምህሮ ለዚያውም ጌታ የሚመለስበትን ቀንና አመት መቼ እንደሆነ ደፍረው እየተነበዩ ያለ ከልካይና ያለ ጠያቂ የሚኖሩትን እዚህ ላይ መጥቀስ ያለብኝ አይመስለኝም።
ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ መጨረሻው ቀንና ስለ ፍጻሜ ጉዳዮች ያስተማሩት በሙሉ ያኔ በዚያው ትውልድ ዘመን ውስጥ ተፈጽሞአል ብሎ የሚያምነውና የሚያስተምረው የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ኃላፋዊነት (preterism) ይሰኛል። preterist የተሰኘው ቃል የተወረሰው praeter ከተሰኘው የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም "አልፎአል" ማለት ነው። ኃላፍያን የተሰኘው ስምም ሆነ ኃላፊ የተሰኘው ግስ ለኃላፊ ጊዜ አነጋገር የሚያገለግል ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የነገረ ፍጻሜ ጥናትን በተመለከተ የኃላፋውያን እይታ ሁሉም ትንቢት የጌታን ዳግም ምጽአት ጨምሮ፣ የሙታን ትንሣኤና ፍርድ እኛ እየኖርንበት ካለነው ከዚህ ዘመን በፊት አስቀድሞ ተፈጽሞአል ብሎ ያስተምራል። ለኃላፍዊው ነገረ ፍጻሜ ትንቢት ሁሉ ያለፈ ታሪክ ነው። ይህንንም ለማስረዳት የቅዱሳት መጻህፍትን አስተምህሮ ጠቅሶ የሚያቀርበው ማብራርያ ከየትኛውም የትርጉም መንገድ ይልቅ ጌታ ኢየሱስን እግዚአብሄር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው ነብይና እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያከብረው፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ተአማኒነት የሚያረጋግጥ፣ ቅዱሳት መጻህፍት ለተሰጡበት አውድ ታማኝ ሆኖ የትርጉም ቀዋሚነትን(consistency) የሚጠብቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሲ. ኤስ ሉዊስ ያሉ ፍልስፍናንና አመክንዮን መሰረት ያደረጉ "የሥነ መለኮት ምሑራን" ተብዬዎች፣ ክርስቶስ ያኔ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በሐዋርያት የሕይወት ዘመን ውስጥ ዳግመኛ ለመመለስ ቃል የገባላቸውንና የተናገረውን ትንቢቱን በመጥቀስና ስህተት መሆኑንም በመናገር፣ "ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ እናንተ ሳትሞቱ በቶሎ ብዬ እመጣለሁ ሲል የነገራቸው፣ ወደ ህይወቱ መጨረሻ ላይ መጨነቁንና ተስፋ መቁረጡን አይተው እንዳያፈገፍጉ ሊያባብላቸው ስለፈለገ ነው እንጂ፣ ስለ መጨረሻውም ሆነ ስለ መጻኢው ከማንም ሰው የተሻለ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም" በማለት፣ ቃሉን እንዳልጠበቀ ያህል በክርስቶስ ተዓማኒነት እና በቅዱሳት መጻህፍት እውነተኛነት ላይ የሚሰነዝሩትን ትችትና ጥቃት በአስተማማኝ የሚመክት ግልጽ አስተምህሮ የኃላፍያን አቋም መሆኑንም ተገንዝቤአለሁ።
ይህ አመለካከት "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) የተሰኘውን የተሃድሶ መሪዎችን አቋም አጥብቆ የያዘና በእርሱም ብቻ የሚጸና ሆኖ ስላገኘሁት ቃሉን ብቻ እንደሚወድ የቃሉ ተማሪ በእውነትም ማርኮኛል። ይህ አመለካከት በነገረ ፍጻሜ ላይ ያሉብኝን ጥያቄዎች በበቂ የመለሰልኝ ሆኖ ስላገኘሁት በአብያተ ከርስቲያናት ዘንድ በስፋት ከሚታወቁትና ተቀባይነት ካላቸው ከፍ ሲል ከጠቀስኳቸውና ከሌሎች የመጻኢነት ማጠቃለያ ካላቸው የነገረ ፍጻሜ አመለካከቶች በላይ ኢየሱስ ክርስቶስንና የትንቢት ቃሉን ያከበረ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት እንዳለው ተረድቼአለሁ። መቼም ቢሆን በመሰረታዊው የክርስትና አስተምህሮና በወንጌል እምነት እኔን ሊገልጠኝ የሚችል ብቸኛ አቋሜ ሉተራዊነቴ ነው። በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮቴ ደግሞ "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) የተሰኘው ሉተራዊው መሰረቴ ወደ ኃላፋዊነት አመለካከት ይገፋኛል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስነ አፈታትን ተከትለን እያንዳንዱን የነገረ ፍጻሜ ርእሰ ጉዳይ በአውዱ ውስጥ ለመረዳት ፈቃደኝነት ካለ ኃላፋዊነት በተለይ በየትኛውም የተሃድሶ አብያተ ከርስቲያናት ቤተ እምነት ውስጥ ተቀባይነትን ሊያገኝ የሚችልና የብዙዎችን የስነ መለኮት ተማሪዎች አእምሮ ሊማረክ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለኝም። የኃላፋዊነት ነገረ ፍጻሜ አስተምህሮን በከፊልም ሆነ በሙላት የሚቀበሉ፣ ካልሆነም ካሉት የወንጌላውያን የነገረ ፍጻሜ የአመለካከት ጎራ (school of thoughts) እንደ አንዱ የሚያዩት ከጥንቶችም ከአሁኖችም በርካታ ስመ ጥር የሆኑ የስነ መለኮት መምህራን እንዳሉ ግልጽ ነው። ዝርዝራቸውን እዚህ ላይ ማንሳት ያለብኝ አይመስለኝም።
በእኔ እምነት "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) የሚሉ ሉተራን ለኃላፋዊው የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ከማንም ይልቅ ይቀርባሉ ባይ ነኝ፤ ሙሉ በሙሉ ባይቀበሉትም እንኳ "የእግዚአብሔር ቃል በንጹህ የተብራራባቸው ናቸው" ብለው ከያዙአቸው የእምነት መግለጫዎች ውጭ አስተምህሮቱን የሚቃወሙበት ምንም የቃሉ መሰረት አይኖራቸውም። የኃላፋውያንን ትምህርት ውድቅ ለማድረግ የእምነት መግለጫዎችንና የቤተክርስቲያንን ታሪክ መሰረት ማድረግ ካቶሊኮች በተሃድሶው አስተምህሮ ላይ የሰሩትን ስህተት መድገም ይሆናል። ነገር ግን ከማብራርያው በላይ "ቃሉን ብቻ" ያከበረና ያነገሰ ማንም ሉተራዊ በኃላፋዊው የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ መማረኩ አይቀርም። ባይማረክም እንኳ አስተምህሮቱን እንደ አንድ አመለካከት (school of thoughts) በልብ ስፋት ያየዋል እንጂ አይበረግግም። ሉተራን ደግሞ ልበ ሰፊዎች ናቸው፤ እንኳንና "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" (Sola Scriptura) ብለው ቃሉን የአስተምህሮታቸውና የልምምዳቸው ዳኛ ያደረጉትን ኃላፋውያንን ቀርቶ፣ "መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም"፣ "ኢየሱስን ድንግል አልወለደችውም"፣ "ከመቃብርም አልተነሳም" ወዘተ... ሲሉ የሚክዱና እንደዚህ የሚያስተምሩ እንደ ቡልት ማን ያሉ የለዘብተኛ ስነ መለኮት አራማጆችንም እንደ ወንድምና አገልጋይ ተቀብለው ይኖራሉ።
ባለፉት ጥቂት በማይባሉ አመታት እርስ በርሳቸው የማይነጣጠሉ የትምህርተ ክርስቶስና የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮቶች በየቀኑ የማሰላስላቸው ርእሰ ጉዳዮቼ ከሆኑ ሰነበቱ። በተለይም የኃላፋውያን ነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ በገባኝ መጠን እየወደድኩት፣ በርእሰ ጉዳዩም ላይ የተጻፉትን ጽሑፎች ጌታ በረዳኝ መጠን አስሼ እያነበብሁ፣ እይታዬን ለማሳደግ እየጣርሁ ቆይቼአለሁ። ከአገሬ ስወጣ ይዤው የወጣሁት የአእምሮ ስንቅ፣ ምድረ በዳዬንም እንደ ኤደን ያለመለመልኝ፣ ከብዙ ከንቱ የአስተምህሮ ብዥታና ቀውስ ጠብቆ ያቆየኝ፣ ባገኘሁት ጥቂት የአገልግሎት አጋጣሚም የክርስቶስ አካል ከሆኑ ጋር የተካፈልኩት ይኸው የሉተራዊነት መሰረተ እምነትና የኃላፋውያን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ነው። ብዙ የአገልግሎት አጋጣሚ ባይኖረኝም፣ ዝም ልለው የማልችለውን የወንጌል እውነት የምናገርበት መልእክቴንም የማስተላልፍበት መንገድ ማህበራዊ ሚድያን በመጠኑ እጠቀማለሁ። በነጻነት የማሰብና የመናገር ተፈጥሮአዊ ስጦታም የአምላክ ጸጋ ነው ብዬም አምናለሁ። ይልቁንም ደግሞ እንደ ተማሪና አስተማሪ የመማር ማስተማር ነጻነት (academic freedom) ለሁሉም አይነት አስተሳሰብ አግባብ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ትምህርት እሸሽገው ዘንድ አይቻለኝም።
ወንድሞቼ ሆይ እምነቴና የምጽፈው ነገረ ፍጻሜ እንደ ቤርያ ሰዎች አቋም "እንዲህም ይታሰባል እንዴ?" የሚል ጥያቄ ቀስቃሽ ሆኖ ወደ ቅዱሳት መጻህፍት አስተምህሮ እየመለሰ በልብ ስፋት የሚያነጋግረን ከሚሆን በቀር ማንንም የሚያስቀይም፣ በክርስቶስ መስዋእታዊ ሞት ያገኘነውን ወንድምነትና እህትነትም የሚፍቅ ሊሆን አይገባውም። ጽሁፌ ያለ እውቀት ያንን አድርጎ ከሆነ ግን በእውነት አዝናለሁ፣ ይቅርታም እጠይቃለሁ። የእግዚአብሔር ቤት አግባብ ባለው አስተዳደር የሁላችንም ቤት እንዲሆንም ምኞቴ ነው። በእግዚአብሔር ቃል ይሁን እንጂ በልብ ስፋት ተነጋግረን የምንተማመንበት ወይም ትምህርታችንን የምንከላከልበት የነጻነት ቤት እንዲሆንም እፈልጋለሁ። በመሰረታዊው የክርስትና ትምህርት ላይ ሳንለያይ ያንን የክርስትና ትምህርት የበለጠ ግልጽ በሚያደርጉ አመለካከቶች ላይ በቅንነት መነጋገር፣ መከራከርና ሙግትን ማቅረብ ከስልጣኔም በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው።
ስለዚህ የምከተለው የኃላፋውያን የነገረ ፍጻሜ አቋም መሰረታዊውን የክርስትና አስተምህሮ አጥብቆ የያዘ እንጂ በመሰረታዊው የክርስትና ትምህርት ላይ ያደረገው ለውጥ እንደሌለው ግልጥ ላደርግላችሁ እወዳለሁ። ይህ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት የመጀመርያ ነገሮችን በተመለከተ ምን ያምናል?
1. የእግዚአብሔርን ባህርይ በተመለከተ፦
የአጥናፍ አለሙ ሁሉ ፈጣሪና ጠባቂ መሆንኑን ያምናል። እግዚአብሔር ሥሉስ ቅዱስ መሆኑንና አንድ አምላክ ከዘላለም አብረው በሚኖሩ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሆኑ ሦስት አካላት የተገለጠ አምላክ መሆንኑን ይቀበላል። በኒቅያ የሃይማኖት መግለጫ እንደተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ እንደ እግዚአብሔር አብ ሁሉ አንድ መለኮታዊ ባህርይና መሰረታዊ ጠባይ እንዳላቸው፣ ማናቸውም በስራና በማእረግ ከማናቸውም የማያንሱ ወይም የሚበልጡ እንዳልሆኑ በጥብቅ ያምናል ያስተምራልም።
2. የሰውን ተፈጥሮ በተመለከተ፦
ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ መሆንኑንና የእግዚአብሔር ክብር የጎደለው መሆኑን ያምናል።
3. ኃጢአተኛው ሰው ከቅዱሱ አምላክ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ በተመለከተ፦
ወንጌል ብቻ መንገዱ መሆኑን ያምናል። የዳንነው በእግዚአብሔር ጸጋ በኩል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ በሚሆን ህያው እምነት ነው። ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ፍጹም የመታዘዝ ሕይወት፣ ለኃጢአት ቅጣት የተከፈለው መስዋእታዊ የቤዛነት ሞቱ፣ የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ሊሰጠን ከሙታን መነሳቱ፣ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን የተሰጠውን ተስፋ በኪዳኑ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅና መፈጸም መዳናችንን ያተመበት ዳግመኛ ምጽአቱ የደህንነታችን ሙላት መሆኑን ያምናል።
4. መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ፦
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተሰጠ መሆኑንና፣ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያምናል። ስለዚህም እጅግ ብዛት ባላቸው ምንባብቱ ስለ መጨረሻው ቀን ሲናገር ያንንው የመጀመሪያውን ምዕተ አመት እያመለከተ፣ የሙሴ ሥርዓት (despensation) የሆነው አሮጌው ኪዳን በ70 አ.ም ላይ ያበቃለት መሆኑን በመናገሩ ለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የዘመን ምድብ ይገዛል። በዚያን ጊዜ ኢየሩሳሌምና መቅደስዋ ተደምስሰው ጠፍተዋል፤ ያ ተፈላጊ የነበረው የዘር ሃረግ ፈጽሞ ከምድር ገጽ በመደምሰሱ እንዲቋረጥ ተደርጎአል። ጥንታዊውም የአይሁድ የኃጢአት መስዋእት ስርአት እንዳይቀጥል ተዘግቶአል።
5. ስለ ሰማይ የሚሰጠውን አስተምህሮ በተመለከተ፦
ሰማይ አማኞች የምድር ላይ ሕይወታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለዘላለም የሚኖሩበት ስፍራ መሆኑ፣ ኢየሱስ ስለ ዘላለም ሕይወት ከሰጠው የተስፋ ቃል ጋር አብሮ የተሰጠ ተስፋ መሆኑን ያምናል። ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ቢሆን ስለ ሰማይ ያላቸው መረዳት ከምድር ላይ ኑሮ በተሻለና በሚበልጥ ሁኔታ አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖሩበት እንደሆነ ነው። መቼም ቢሆን ሰማይ የአማኞች የተረጋገጠ ተስፋ ነው።
6. ኃላፊነታችንና ግዴታችንን በተመለከተ፦
ለእግዚአብሔር ጸጋ በሚሆን ምላሽ በትህትናና በታማኝነት ቅንነትም በተሞላ አካሄድ ፈቃዱን ባወቅን ልክ እርሱን መታዘዝ እንደሚገባን ያምናል። ይህንንም ሰፋ ባለ መልኩ የሚገልጠው ጌታ አምላክን በፍጹም ልብ፣ ነፍስ፣ ሃሳብና ኃይል መውደድና ባልንጅራችንንም(ጠላቶቻችንንም ቢሆን እንኳ) እንደ ራስ መውደድ እንደሚገባን የተገለጠው ፈቃዱ ነው። ልናደርገው የሚገባንም ማናቸውም የርህራሔ ስራ ብዙ ሰዎችን ከክርስቶስ ጋር ወዳለ የመዳን ሕብረት የሚያመጣቸው መሆንም እንዳለበት ያስተምራል።
የሆነው ሆኖ ስለ"መጨረሻ ነገሮች" የተነገሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶችን አስመልክቶ የሚበዙትና ታዋቂ የሆኑት ዘመናዊ አመለካከቶች ፈጽሞ የተሳሳቱ እንደሆኑ ደግሞ ያምናል። "የሚበዙትም አብያተ ክርስቲያናት ስለ መጨረሻው ቀንና ስለ ዳግም ምጽአት የተሳሳተ ትርጉም ተከትለው ስህተት እንደሚያስተምሩ እናምናለን ስንል ይህንን ተቃውሞአችንና ወቀሳችንን አበክረን እናስታውቃለን እንጂ በቀላሉ አንመለከተውም" ሲሉ ኃላፋውያን በጥብቅ ያሳስባሉ።
ኃላፋዊ የተሰኘውና እኔም የተቀበልኩት ይህ የነገረ ፍጻሜ አመለካከት፣ ኢየሱስና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ካስተማሩት ትምህርት ጋር የሚስማማ መሆኑን፣ እነርሱ ራሳቸውም በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ደጋግመው በግልጽ ማስተማራቸውን፣ የመጨረሻው ዘመንም ገና ወደፊት የሚመጣ አለመሆኑን አረጋግጦልኛል። የመጨረሻውን ዘመን በአግባቡ ለመረዳትና እርማት ለማድረግ ክርስቲያኖች ከግልቢያ ንባብ ተቆጥበው ወደ አዲስና ብሉይ ኪዳን ገጾች በጥንቃቄ መመለስ እንዳለባቸው እመክራለሁ። ስለዚህም፦
♦ታዋቂ ከሆኑት የነገረ ፍጻሜ አመለካከቶች ርቄ፣ ምጽአቱን ጨምሮ ሁሉም ትንቢት በእርሱ ትውልድ ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን በበርካታ የወንጌላት የንባብ ክፍሎች በግልጽ ሲናገር በእርግጥም ጌታ ኢየሱስ እንዳልተሳሳተ፣ እውነቱንም ይናገር እንደነበር ለማመን በቅዱስ ቃሉ እገደዳለሁ (ለምሳሌ፦ ማቴ 10፥ 23፤ 16፥ 27-28፤ 23 ፥36፤ 24፥ 34፤ 26፥ 64፤ ማር 8፥ 38-9፥ 1፤ ሉቃ 21፥ 22፣ 32፤ ራእይ 1፥ 1-3፤ 22፥ 6-20፤ ወዘተ..) እንደውም ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትንና ከምጽአቱ ጋር ተቆራኝተው የተዘገቡትን የአዲስ ኪዳን ምንባባት በጥንቃቄ ለሚመለከት አንባቢ ፍጻሜአቸውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን አውድ አውጥቶ በሌላ ዘመንና ትውልድ ውስጥ ለመጠባበቅ የሚያስችለው ምንም የቃሉ ድጋፍ እንደሌለው ይረዳል።
♦የመጨረሻው ዘመንም ሆነ ወይም የመጨረሻው ቀን ማለት የአሮጌው ኪዳን ስርአት በ70 ዓ.ም ላይ በኢየሩሳሌምና በቤተመቅደሱ ውድመት ያበቃበት የመጨረሻ ቀን ማለት እንደሆነ ይህንን መረዳት ይዤአለሁ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የመጨረሻው ቀን ወይም የመጨረሻው ዘመን ተብሎ ከ15 ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ በንባብ ክፍሎቹ በአንዳቸውም ቢሆን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የዘለለ ሌላ ዘመን እንድናስብ የሚያግዘን አንዳች ሃሳብ የለባቸውም (ለምሳሌ፦ ሐዋ 2፥ 14-20፤ 1ቆሮ 7፥ 29-31፤ 10፥ 11፤ እብራ 1፥ 2፤ 9፥26፤ 1ጴጥ 1፥ 5፣ 20፤ 4፥ 7፣ 17፤ 1ዮሐ 2፥ 17-18፤ ወዘተ...)። የመጨረሻው ዘመን ማለት የአሮጌው አለም የሙሴ ዘመን መጨረሻ፣ የአሮጌው ኪዳን የአይሁድ ሥርአት (Despensation) ማብቂያ ማለት እንጂ፣ የፕላኔትና የተፈጥሮ ስርአት ማብቂያ ማለት ጨርሶ አይደለም።
ኃላፋውያን አፈንጋጭ የሆነውን የሺህ አመት መንግስት (Millennialism) አስተምህሮ፣ በተለይም ልዩ ወንጌል የሆነውን የዘመን ቆጣሪነት (Dispensationalism) አመለካከት አይቀበሉም። እምነታዊነት (Fideism)፣ ወግ አጥባቂነት (Nominalism)፣ ሕገ ወጥነት (Antinomianism)፣ ለዘብተኝነት (Liberalism)፣ ሕግ አክራሪነት (Legalsm)፣ እና ሁሉ አቀፋዊነት (Universalism) በኃላፋውያን ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። በተለይም ከ70 ዓ.ም በኋላ እግዚአብሔር በሰዎች ላይ መፍረድ አቁሞአል ፣ የእግዚአብሔር የማዳን ስራ በ70 ዓ.ም ላይ አቁሞአል፣ የሰው ኃጢአት ከ 70 ዓ.ም በኋላ ፈጽሞ የሚታሰብና ከቁጥር የሚገባ ጉዳይ አይደለም፣ ሰማይ እዚሁ ምድር ላይ ነው፣ ወይም አሁን በምድር ላይ ካለንና ካገኘነው የሚበልጥ ነገር ሰማይ የለውም፣ ክርስቲያኖች ቅዱስ ጥምቀትንና ቅዱስ ቁርባንን መቀበላቸው አስፈላጊ አይደለም የሚል አስተሳሰብ የሚያራምደውን "ምጥቀ ኃላፋውያንነትን" (Hyper preterism) አጥብቆ ይቃወማል።
ስለሆነም ዳግመኛ ምጽአቱን፣ ታላቁን ፍርድና የሙታን ትንሣኤን የሚያጠቃልለው ሁሉም ነገረ ፍጻሜአዊ ተስፋ በ 70 ዓ.ም ላይ መፈጸሙን ሳምን፣ የእግዚአብሔር ስራ ግን ከ70 ዓ.ም በኋላም ቀጥሎ ያለ፣ ያልተቋረጠና ቀጣይ እንደሆነም ጭምር አምናለሁ። የክርስቶስ ስራ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ጅማሬው ነበር እንጂ ፍጻሜው አልነበረም። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱሳዊው የመዳን ተስፋ ክርስቶስ አሁን ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ ለዘላለም የነገሰ እስከሆነ ድረስ ለአለምና ለዘለአለም እየተሰበከ፣ ሰዎችንም ወደ መንግስቱ እየጋበዘ ይኖራል (ኢሳ 9፥ 6-7፤ ሉቃ 1፥ 31-33፤ ኤፌ 3፥ 21)። የሰው ኃጢአተኛ ተፈጥሮ፣ ቀጣይ የሆነም የደህንነት ፍላጎት፣ በጽድቅ ላለው ምክር የሚጠቅም ተግሳጽና እርማት በ70 ዓ.ም ላይ ያበቃለት ጉዳይ እንዳልሆነ እረዳለሁ። በጥንታዊው የእምነት ማህበረ ሰብ ውስጥ ሥነ መለኮታዊ መሳሳቶችም የነበሩ መሆናቸውን ብረዳም፣ ከላይ በነጥብ ባሳየኋቸው የክርስትና የመጀመርያ አስተምህሮዎች አንጻር አንድነትን ጠብቆ ለመዝለቅ ከጥንታዊው ክርስትና ጋር ተጣብቆ መቆየት አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ክርስትና ታሪካዊ እምነት ነው፣ ያለነውም ከእኛ አስቀድሞ በነበሩና ባለፉ ሰዎች ትከሻ ላይ ነው።
ስለዚህ ነገሬን ለመጠቃለል፣ በእርግጥ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ የሆነው ምንድር ነው? ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የኃጢአታችንን እዳ ከፍሏል፣ መዳናችንም ያኔ ተመርቆ (inagurated) መገለጡን ሲነግረን በዚህ ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ግልጽ ነው (ሮሜ 8፥ 1-4፤ 1ቆሮ 15፥ 3፤ 2ቆሮ 5፥ 17-21፤ እብ 9፥ 15-26፤ ወዘተ..)።
ይሁን እንጂ የጌታችን የቤዛነት ዋጆአዊ ስራና አጠቃላዩ የደህንነት እቅድ የሚጠቃለለው በምጽአቱ እንደሆነም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል፣ - ይኸውም ክርስቶስ በ70 ዓ.ም ከተማይቱንና መቅደስዋን ለማጥፋት ሲመጣ ያኔ በይፋ እንደሚጠናቀቅ (consummet) እና ለቅዱሳኑም ፍጽምናን እንደሚያቀዳጅ መነገሩ ነው (ሉቃ 21፥ 28፤ ሮሜ 13፥ 11-12፤ እብራ 1፥ 14፣ በተለይም "ስላላቸው" ለተሰኘው የግሪኩ አቻ ግስ 'mello' በእንግሊዝኛው "about to" መሆኑን ስናስተውል ጉዳዩ ተፈጻሚ ስለሚሆንበት ጊዜ ላቅ ያለ ትርጉም ይሰጠናል፤ እብራ 9፥ 26-28፤ 1ጴጥ 1፥3-9፤ ራእይ 12፥ 10 ወዘተ...)። ይህም የአማኞችን ሁሉ መዳን ለወደፊቱም አትሞ የሚያጸናውና በይፋ የሚያቀዳጃቸው ተግባር ነው። እነዚያ ድነው የጌታን በፍርድ መመለስ በትውልዳቸው ውስጥ እየተጠባበቁ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናቸውን ይፈጸሙ የነበሩ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የነበሩበት ጊዜ የሽግግር ዘመን (The Olready not yet) የሚባለው ጊዜ ውስጥ ነበሩ። በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዘላላሙ ተጀምሮአል። እነሆ ክርስትናችን አዲሱ ሰማይና ምድር፤ በክርስቶስ ድል መንሳት በደስታ እንኑረው። ስለሆነም፣ ነገረ ፍጻሜአዊ የሆኑና የተሰጡ የመጨረሻው ዘመን ተስፋዎች፣ ፍጻሜ የሌለውንና ከክርስቶስ ጋር የተቀበልነውን የአዲሱን ኪዳን የመጀመርያ ነገሮች አስፈላጊነት በጉልህ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች ፍጻሜ ለጥንታዊው ክርስትና ያለንን አክብሮትና ታማኝነት በሚያጠናክር መረዳት ይሞላናል እንጂ፣ ከእርሱ አይነጥለንም። በእኔም ውስጥ የሆነው እንደዚያ ነው። "የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት።" (ምሳሌ 13፥ 12) ተብሎአልና።
በዚህ አጋጣሚ ልትሰሙኝና በመለኮት ቃል የያዝሁትን አቋም ልትፈትሹ በማሰባችሁ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። በበርካታ ህብረቶች ውስጥ ከትምህርታዊ አቋም በመለስ ምድራዊና ስጋዊ የሆኑ የገንዘብ፣ የሥልጣን፣ የማንነት፣ የስም፣ የመድረክ ወዘተ... ጥያቄዎች የልዩነትና የጸብ ምክንያት በሆኑበት ሁኔታ እኛ መካከል ግን ለምን ይህን ታምናለህ? ለምታምነውና ለምታስተምረው ነገርስ ምን የቃሉ ድጋፍ አለህ? መባባላችንን ሳስበው በእውነት ደስ ይለኛል። በቅዱስ ቃሉ ይሁን እንጂ ለጻፍሁትና ገናም ለምጽፈው ትምህርቴ መቼም ቢሆን ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ ነኝ።
ስለዚህ ከዚህ መልእክቴ ጋር ያቀረብኩትንና የአመለካከትና የአቋም ለውጥ ማድረጌን የገለጽሁበትን ምክንያት፣ አስተምህሮቴንም በከፊል ያስታወቅሁበትን መለስተኛ አባሪ ጽሑፍ (ተጽፎና ተጠናቆ የህትመት ጊዜውን እየጠበቀ ካለው የጀማሪ መጽሐፌ የተወሰደ) ለቅዱሳት መጻህፍት ብቻ በሚሆን ተጠያቂነት ትመለከቱት ዘንድ በአክብሮት እጋብዛለሁ።
በልቤ ትኖራላችሁ፤ ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን።
በአብ በውልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ። አሜን!
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
No comments:
Post a Comment