Friday, August 24, 2018

የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት? ክፍል አንድ

የጌታ ምጽዓት መቼ እና እንዴት ነው?
በማቴዎስ 24 እንደተገለጸ

ማቴ 24÷ 3
“እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።”
በዚህ ክፍል ደቀ መዛሙርት ለክርስቶስ የሚያቀርቡለት ጥያቄ ምን እንድሆነ መረዳት የትንቢቱን ተገቢና ትክክለኛ ትርጉም ልማግኘት አይነተኛ መነሻ ነው ነው? እንደሚታወቀው ደቀመዛሙርቱ ያቀረቡት ጥያቄ እርስ በርሳቸው ተያያዥነት ያላቸውን ሦስት ጥያቄዎች ነው፡፡ እነርሱም፣ 1) ይህ መቼ ይሆናል? 2) የመምጣትህ ምልክቱ ምንድን ነው? እና 3) የዓለም መጨረሻስ ምልክቱ ምንድን ነው? የሚሉት ናቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ላነሱአቸው ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱን የምናገኘው ከዚሁ  ምዕራፍ  ውስጥ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራፉም ስለዘመኑ ፍጻሜ፣ ስለኢየሩሳሌም ውድመት (የዘመኑ ፍጻሜ ለመድረሱ ምልከቱ በሉቃስ 21÷ 7 እና 20 እንደተገለጸው የኢየሩሳሌም በጦር ኃይል መከበብዋ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚገለጠው የጥፋት ርኩሰት ነው)፣ እንዲሁም ስለ ክረስቶስ ምጽዓት ገለጻ የተብራራበት ነው፡፡ 
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 በተለምዶ የደብረዘይቱ ፍካሬ በመባል ይታወቃል። ይህም የንባብ ክፍል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከተገለጠው በተጨማሪ ረጅሙ የነገረ ፍጻሜ ትንቢት የሆነና፤ በጌታ ምጽዓት ላይ የሚጠቀስ ዓይነተኛ ክፍል ስለሆነ በክፍሉ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቶ መተርጎም የግድ ይላል፡፡ ኢየሱስ በወንጌላት ውስጥ ምጽዓቱን አስመልክቶ መቼ እንደሆነ ያስተማረበት አይነተኛ የሆነው ተጠቃሽ ክፍል በተለይ የማቴዎስ 24 ነው፡፡
በዚህ ምዕራፍ ሐዋርያቱ ኢየሱስን ከጠየቁት ትክክለኛ ጥያቄዎች እንጀምራለን፡፡ “መቼ ይመለሳል?” የሚለው ጥያቄ የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የእርሱን አመጣጥና የምልክቶቹን አፈጻጸም እስካላወቅን ድረስ እኛም የምንጠይቀው ይሆናል፡፡ በዚህ የንባብ ክፍል ኢየሱስ የሚመለስበትን ጊዜ እጅግ አጥብቦ እንደወሰነው እና ጊዜውን እንዳመለከተው ስትማሩ በጣም ልትገረሙ ትችላላችሁ፡፡ ኢየሱስ ስለሚመለስበት ጊዜ መቼ ነው ብሎ እንዳስተማረ እና በሰጠው ምላሽ ውስጥ ያሉትን ምልክቶች አስቀድሞ መመርመር ተገቢ ነው፡፡
“እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል ( ማቴ 23÷ 36)።
“ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት” (ማቴ 24÷ 1-3)።
“የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም( ማቴ 24÷ 30-35)።
እነዚህን የወንጌሉን ክፍሎች እንደሚገባ ለመረዳት ክፍሎቹ የሚገኙበትን ዐውደ ምንባብ መመልከት የግድ ይላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ማን? ምን? መቼ? የት? እና ለምን? የሚሉትን ተገቢ የሥነ-ሐቲት ( ኤክስጀስስ) ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይሆናል። በማቴዎስ 24 ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ንግግር ለመረዳት የታሪኩን ዳራና መቼት ማየትም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ- ሐቲት እና ሥነ- ፍታቴ ብቸኛ ንግስት አውደ ምንባብ ናትና።
ስለዚህም ለአሁኑ የጥናት ፍጆታ እምብዛም ርቀን መሄድ ሳያስፈልገን ሁለት ምዕራፎች ብቻ ወደ ኋላ ተመልሰን ኢየሱስ ወደ  ኢየሩሳሌም በክብር የገባበትን ሁኔታ ከሚነግረን ከምዕራፍ 21 ጀምሮ ማየት ይጠቅመናል፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ የሚሸጡትን እና የሚገዙትን ገንዘብ ለዋጮችን አስወጣ፡፡ ከዚያም ሌሊቱን ወደ ቢታንያ ሄዶ እንደገና በማለዳ በመመለስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ያስተምር ጀመር (ምዕ 21-23)፡፡ በትምህርቱም ምዕራፍ 23 ላይ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን “ግብዞች”፣ “እባቦች”፣ “ክፉ ትውልድ” እያለ በመጥራት ከአገልግሎቱ ሁሉ እጅግ ዘለፋ የበዛበትን ስብከቱን አቀረበ፡፡ በመጨረሻም መልዕክቱን ያጠቃለለው በእነርሱና በኢየሩሳሌም ላይ ሊመጣ ያለውን ፍርድ በመናገር ነው፡፡
በማቴ 23÷ 35 ላይ የአይሁድ ሕዝብም ሆኑ የኅይማኖት መሪዎቹ ስለ ኃጢአታቸውና ስለአባቶቻቸው በደል ጭምር ዋጋ  እንደሚከፍሉ ሲናገር፦ 
“ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።” ይላል፡፡
በመቀጠልም በቁጥር 36 ላይ ስለ ፍርዱ እንዲህ ይላል፦
“እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል”
“በዚህ ትውልድ”  የሚለውን ሐረግ ለመተርጎም በተርጓሚዎች ዘንድ በርካታ ሓሳቦች እንደሚሰነዘሩ ይታወቃል። [የቤተመቅደሱን መፍረስ አስመልክቶ ከላይ በማቴ 24÷ 3 ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ የኢየሱስ ትንቢት በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው እርሱ የነበረበት “ይህ” የተባለው ትውልድ ከማለፉ በፊት እንደሆነ በግልጽ የሚያስረዳ በመሆኑ ከዚህ የተለየው ትርጓሜ ሁሉ እዚህ ነጥብ ላይ ውድቅ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህ ትውልድ እንጂ ያ ትውልድ አላለምን]።
ወንጌላዊው ሉቃስ በዘገበው የደብረዘይቱ ተራራ ትንቢት በምዕራፍ 21÷ 32 “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።”  ሲል፤ በማቴ 24÷ 33-34 ደግሞ እንዲህ ይላል“እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።” ይላል ። በዚህ ክፍል ይህ ትውልድ ሲል የትኛውን ትውልድ ማለቱ ነው? [ ኢየሱስ ሲናገራቸው ቆመው ይሰሙት የነበሩትና "ይህ ትውልድ" የተባሉት እነዚያው  ራሳቸው “ይህ ሁሉ” የተባለውን ያያሉ፡፡ ኢየሱስ የተዘረዘሩትም ጉዳዮች እርሱ “በደጅ እንደቀረበ” የሚያመለክቱ ሆነው ይቆጠራሉ፡፡ ቤተመቅደሱም የፈራረሰውና የወደመው በ70 ዓ. ም ላይ ነው፡፡ ስለዚህ የተቀሩት “ይህ ሁሉ” የተባሉት ነገሮች በዚያው ጊዜ መፈጸም አለባቸው፣ ማለት ነው፡፡ የሚያካትቱትም “በአለም ሁሉ” የሚሆነውን የወንጌል ስብከት (ቁ 14)፣ “የጥፋት እርኩሰት” መታየት(ቁ 15)፣ “የሰው ልጅ በሰማያት ደመና መምጣት” (ቁ 30)፣ እንዲሁም “የተመረጡት”መሰብሰብ (ቁ 31) ነው፡፡ ˝ኢየሱስ የእርሱ ደቀመዛሙርቱ ሞተው ሳያልቁ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ማብቂያ በፊት እንደሚመጣ ትንቢት እየተናገረ እንደሆነ ይታወቃል፤ አንድ ግራ የገባው የጥናት መምሪያ ግን "ይህ የሚያደናግር ንግግር ነው˝ ሲል  ያትታል፣ [NLT Study Bible (Carol Stream: Tyndale House Publishers, Inc.,2008)፡፡ ሲ. ኤስ ሉዊስ የተባለውም ጸሐፊ ሉቃስ 21÷ 32 ላይ ማብራሪያ ሲሰጥ " ….ተሳስቶአል፡፡ እርሱ (ኢየሱስ) ከማንም የበለጠ ስለ አለም መጨረሻ ምንም እንደማያውቅ ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥም ይህ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ ጥቅሶች ሁሉ እጅግ አስቸጋሪውና አሰናካዩ ጥቅስ ነው"፣ ብሎአል፡፡ {C,S. Lewis, The World Last Night and Other Essayea (New York: Harcourt Brace & Company, 1973) 98}]።
ስለ ትውልዱስ ምን የተገለጸ ነገር እንመለከታለን ? “ሁሉ እስኪፈጸም” ሲልስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸውን  ልብ በማለት እናስብ ! የቱን ማለቱ ነው? ኢየሱስ ይለው የነበረው ነገር ሁሉ በዚያው ትውልድ ይፈጸማል ማለቱ ነው፡፡ "የሰው ልጅ መምጣት" ከተባሉት ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው ነው (ሉቃ 21÷ 27]
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንቱ ቃሉ የሚያመለክተው እርሱ ሲናገር ይሰሙት የነበሩትን ሕዝብ ነው ሲሉ ይስማማሉ፡፡ [Gentry, ‘‘The Great Tribulation: Past or Future’’; Kregel publications, 1999 (co-authored with Tommy Ice) ገጽ 20-22; Schwertley,‘Brian ‘‘Mathew 24 and the Great Tribulation’’ ገጽ 6-8]
ለምሳሌ ግን ሚልተን ቴሪ በልማድ። በብዙዎች ዘንድ ሲታመን የኖረውን የአንዳንዶቹን መረዳት ሲጠቅሱ ቃሉ በከፍተኛ ደረጃ የትርጉም ልዩነትን ያስከተለ መሆኑን በማውሳት፣ ጄሮም “መላው የሰው ዘር” ማለቱን፣ ዶረን እና አውበርሌን “የአይሁድ ዘር”  ማለታቸውን፣ [ ከእነዚህም መካከል ደግሞ "ትውልድ" (በግሪኩ genea) ማለት ዘር ማለት ነው ይኸውም "ኢየሱስ በሚመለስበት ጊዜ ገና ወደፊት የአይሁድ ዘር እስከዚያ ዘመን ድረስ በምድር ላይ ይኖራል" ሲሉ ጉዳዩን ከአውዱ ነጥለው ክፍሉን በመለጠጥ ሲተረጉሙ ይደመጣሉ፣ ለምሳሌ፦ Edward E. Hindson and Woodrow Michael Kroll, KJV Bible Commentary (Nashville; Thomas Nelson, 1997, ይመለከቷል] ዮሐንስ አፈወረቅም (ክሪሶሶም) እና ላንግ “የክርስቲያን አማኞች ዘር” ማለታቸውን ሚልተን ቴሪ ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን ይላሉ ቴሪ፣ ይህንን ልማዳዊና አውድ ዘለል ትርጉም ሲተቹ፣ ˝ለማንስ ሰው ቢሆን በተለይም ለኢየሱስ “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ‘መላው የሰው ዘር’፣ ወይም ‘የአይሁድ ዘር’፣ ወይም ‘የክርስቲያን ሕዝብ’ አያልፍም” ብሎ መናገር ምን ያህል ትርጉም የሌለውና ዋጋ ቢስ ነገር ይሆን! …. በአዲስ ኪዳን የትርጉም ጥናት “ትውልድ” ተብሎ የተተረጎመው “ጌኔኦ” የተሰኘው የግሪክ ቃል በዋናነት የሚያመለክተው በአንድ ወቅት  የኖረን ትልቅ የሕዝብ አካልን - በአብዛኛው አብረው የኖሩበትን (ያው አንዱንንና ተመሳሳዩን) ክፍለ ጊዜ ነው˝ ሲሉ ተቃራኒውን ሃሳብ የጠቁማሉ [Terry Biblical Appocalyptics, ገጽ 244]።

ስለ ትውልድ ስናስብ አንድ ቀላል ጥያቄ እናነሳለን። ይኸውም የአንድ ትውልድ እድሜ ምን ያህል ዓመታት ናቸው? የሚለው ነው። ጆን ዋልቩርድ አንድ ትውልድ ከሠላሳ እስከ አንድ መቶ ዓመታት ያህል ነው ይላሉ፡፡ ከሌሎች ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች በተለየ አቀራረብ ጊዜውን እስከ መቶ ዓመታት ድረስ የሚያራዝሙ እኔ የማውቃቸው ብቸኛ ተርጓሚ እሳቸው ናቸው፡፡ መጋቢ በቀለ ወ/ኪዳን “ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው” በተሰኘው መጽሓፋቸው ይህንኑ ሓሳብ ይጋራሉ። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚያምኑት ከሆነ ግን “አንድ ትውልድ”” በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠላሳ እስከ አርባ ዓመታት ያህል ይሸፍናል የሚለው ሓሳብ ሚዛን ይደፋል ። በዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ ትውልድ የሚናገረውን ማየት እጅግ የተሻለ ነው፡፡

“እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው። (ማቴ 1÷ 17)
በዚህ የትውልድ ሓረግ መግለጫ የአንድን ትውልድ የጊዜ ርዝመት መገመት የሚያስችለንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዝርዝር እናያለን፡፡ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ድረስ አሥራ አራት ትውልድ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ ምርኮው በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ586 የሆነ ነበር፡፡ ከ586 ዓ.ቅ.ክ እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ በጠቅላላ 586 ዓመታት ገደማ ናቸው፣ ይህንንም ለአሥራ አራት ብናካፍለው የአንድ ትውልድ አማካይ የእደሜ ርዝመት 41 ዓመታት ይሆናሉ፡፡
ይህንን ደግሞ እዩ፦
ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤ ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ። ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ፤ (ዕብ 3÷ 8-10)።
በተጨማሪም፦
የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው። (ዘኁል 32÷ 13)።
አርባ ዓመታት በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቀ ቁጥር ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ለአርባ አመታት በምድረ በዳ ተጉዘዋል፡፡ የአዲስ ኪዳንም ቅዱሳን ከሰማይ ወደሆነችው ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከመግባታቸው አስቀድሞ ከክርስቶስ እርገት እስከ 70 ዓ. ም ድረስ ለአርባ ዓመታት በሽግግር ወቅት ውስጥ ነበሩ፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ የተነበያቸው እነዚያ ነገሮች ሁሉ ተፈጻሚ የሚሆኑት በእነዚህ በአርባ ዓመታት ውስጥ ነው፣ አለበለዚያ ሓሰተኛ ነቢይ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የሚያካትተው ሁሉንም በማቴዎስ 23 እና 24 የተጠቀሱትን፡- ጦርነቶች፣ ረሃብ፣ የምድር መንቀጥቀጥ፣ የኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት መከበብዋን፣ ክርስቲያኖች ከይሁዳ መሸሻቸውን፣ የሙሴ ዘመን (ዓለም) ፍጻሜን፣ እና የኢየሱስን በኃይልና በታላቅ ክብር ተመልሶ መምጣትን ሁሉ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ከአርባ ዓመታት በኋላ በ70 ዓ.ም ላይ በዚያው አንድ ትውልድ ልክ ኢየሱስ እንደተነበየው ያልተፈጸመ ከሆነ፣ እንግዲያውስ ኢየሱስ ሐዋርያቱን እያታለላቸው ነበር ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ እውነት መሆኑን (ዮሐ 14። 6)፣ እውነተኛም ሆኖ ለእውነት ሊመሰክር ለዚህ መወለዱን (ዮሐ 18፥ 37) እንጂ፣ ውሸተኛና አታላይ እንዳልሆነ በእርግጥ እናውቃለን፡፡ እርሱ እመለሳለሁ ሲል ተስፋ በሰጠበት ጊዜ እንደተመለሰ ከማመን በቀር ጌታን ኢየሱስን እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል እንዳስነሳው እንደ እውነተኛ ነብይ ልንሰማው የምንችልበት ሌላ ምንም ዕድል የለንም፡
በቁጥር 38 እንዲህ ይላል “እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል”፣ ይህ “ቤት” የተባለው ኢየሱስ  ቆሞ የነበረበት ቤተ መቅደስ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ማናቸውም አይሁዳዊ የሆነው ነገር ሁሉ፣ ጠቅላላውን የይሁዳን ሕዝብ ቤት፣ ኑሮአቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ምድራቸውን፣ ሕዝባቸውን፣ አገራቸውን፣ የኃይማኖት ሥርዓታቸውን፣ የክህነት አገልግሎታቸውንና የአኗኗር ዘይቤአቸውን ሁሉ የሚያካትት ቃል ነው፡፡ እንደ ኢየሱስ ቃል ከሆነ ይህ ሁሉ ፈጽሞ ሊጠፋ ተመድቦአል። ይህ እንዴት ያለ አስፈሪ ትንቢት ነው! ቃል በቃል አንድም ሳይቀር ትንቢቱ መፈጸሙን የ70ውን ዓም የእስራኤልን ውድመት ከታሪክ መዛግብት ማየት ይገባል።
♦♦♦♦♦♦

Friday, August 17, 2018

የፕሪቴሪዝም አመለካከት ምንድን ነው?

የፕሪቴሪዝም አመለካከት ምንድን ነው?
የአለም ፍጻሜ ቀርቦአል ወይ? የምንኖረውስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ወይም ዘመን ውስጥ ነው ወይ? የክርስቶስ መመለሻስ ከዚህ በኋላ ቶሎ የሚሆን ነው ወይ?
በግምት ላለፉት 150 አመታት በምእራቡ አለም አብያተ ክርስቲያናት ያለማቋረጥ የተስተጋባ  አንድ ጉዳይ፣ የምንኖረው በአለቀና በተሟጠጠ ዘመን ውስጥ እንደሆነ ሲነገረን የኖረው ሲሆን ክርስቶስም ተመልሶ ሊመጣ በደጅ እንደቀረበና ጊዜው እንደደረሰ በብዙዎች ዘንድ የተያዘ እምነት ነው። በክርስቲያኑ ማህበረሰብ ላይ ተጭኖና ተተብትቦ ከኖረው ልማዳዊ አመለካከት የተነሳ፣ ሳይሳኩ መና ሆነው የቀሩ በትንበያ ላይ ትንበያ፣ በሃሰተኛ ተስፋ ላይ ሌላ ሃሰተኛ ተስፋ የመጨማመሩ አባዜ "አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው" ጉዳይ ነው። ከዚህ አይነቱ አዙሪት የተነሳ በርካታ የተታለሉ ክርስቲያኖች ንብረቶቻቸውን የተጭበረበሩ ሲሆኑ፣ ሌሎቹም ደግሞ እምነትን እስከመተው የደረሱና በተስፋ መቁረጥ ራሳቸውን እስኪያጠፉ ድረስም መጨረሻቸው የማያምር ሆነዋል። ለምሳሌ በኮርያ አብያተ ክርስቲያናት ሰፊ መሰረት ያለውና ከቁጥጥር ውጭ የወጣው የመጨረሻው ዘመን መላምታዊ አስተንትኖ ለበርካታ ማህበራዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት ብዙዎችን ዳርጓል። አለማዊ የመገናኛ ብዙሃን (አዘውትረው ስህተትን የሚፈልጉ) ክርስትናን የሚያሳጡበትንና የሚያዋርዱበትን የስድብ ምክንያት አግኝተዋል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የትንቢት አስተምህሮ ልማዳዊ አመለካከት ዙርያ በተርጓሚዎች ዘንድ አንድ የተሳሳተ ነገር መኖሩ ግን ግልጽ ነው። ያ ችግር ምን ይሆን? እምነታችንን ከስድብና ከነቀፋ ለመከላከል ሲባል የመጨረሻው ዘመን ነገረ ፍጻሜአዊ የሆኑ አጠቃላይ ጉዳዮችን፣ የኖረውን አስተምህሮታዊ አቋምና ልማዳዊ አመለካከቶቻችንን እንደገና ማየት፣ መከለስ፣ መፈተሽና እርማት ማድረግ ይደር የሚባል ጉዳይ አይደለም።
"ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም" (ማቴ 13፥ 11) ተብሎ እንደተጻፈ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የትንቢት ቃል መረዳትና ማወቅ በእውነትም ለተጠሩትና ለተመረጡቱ  የሚቻል ነው። መጻኢያን (Futurists) የሆኑ ተርጓሚዎች ግን ከሚከተሉት የትርጉም አካሄድ ስህተት የተነሳ፣ ማለትም፦  ጽንፍ በያዙበት የተዳሳሽ ወይም በቁሙ የሆነ አቀራረባቸው የተነሳ፣ በምሳሌአዊ ወይም ምስል ከሳች በሆነው ቋንቋ እና በቁሙ በሚወሰድ የቋንቋ ዘይቤ መካከል ልዩነት ለማድረግ ካለመቻላቸው የተነሳ፣ እንዲሁም የትንቢቶችን ታሪካዊ - ሰዋሰዋዊ - ባህላዊ የሆነውን አውዳቸውን (በተለይም ለበኩረ ተደራስያኖቻቸው ምን ማለት እንደነበሩ) በትክክል ወስዶ ለመተርጎም ካለመቻላቸው የተነሳ ትንቢትን በወጉ መተርጎምና መረዳት ከቶ አልሆነላቸውም። ባደመጥናቸውና የጽሁፍ ሥራዎቻቸውን ባነበብን ቁጥር ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት ዝቅ አድርገው የሚያዋርዱ ትንታኔዎቻቸውን እስክናፍር ታዝበናል። ከዚህም ግራ የገባው ትምህርት የተነሳ በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በነገረ ፍጻሜ አስተንትኖ እርስ በርሳቸው የተለያዩ ለቁጥር የሚያታክቱ አመለካከቶች ተፈልፍለዋል። በአብዛኛው ታዋቂ ከሆኑት መካከል፦ የአልቦ ሺህ አመት መንግስት (Amillennialism) አመለካከት፣ የድህረ ሺህ አመት መንግስት (Post Millennialism) አመለካከት፣ የታሪካውያን (Historicism) አመለካከት፣ የታሪካዊ ቅድመ ሺህ አመት መንግስት (Historic Premillennialism) አመለካከት፣ የዘመን ቆጣሪው የቅድመ ሺህ አመት መንግስት (Dispensational Premillennialism) አመለካከት፣ የቅድመ መከራ ንጥቀት (Pre- Tribulation Rapture) አመለካከት፣ ወይም ቅድመ ቁጣ ንጥቀት (Pre Wrath Rapture) አመለካከት፣  የከፊል ንጥቀት (Partial Rapture) አመለካከት፣ በመከራው መካከል የመነጠቅ (Mid Tribulation Rapture) አመለካከት፣ የድህረ መከራ ንጥቀት (Post Tribulation Rapture) አመለካከት ወዘተ.. የሚጠቀሱት ናቸው። ማለቂያ የሌለው የነገረ ፍጻሜ የአመለካከት ልዩነቶች ቀድሞም ነበሩ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለአተረጓጎማቸው ካልተጠነቀቁ እንዲህ ያሉ የአስተምህሮ ህጸጾች ወደፊትም ይኖራሉ። ያው ዞሮ ዞሮ ግን ሁሉም  ማጠቃለያቸው መጻኢነት መሆኑ ግልጽ ነው።  ሁሉንም በተወሰነ ዝርዝር አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን የዳሰስኩበትን ጽሁፍ ሊንኩን ተጭናችሁ ልትመለከቱ ትችላላችሁ፦
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1932248943670209&id=1889309531297484
ወደተነሳሁበት ሃሳብ ስመለስ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶችን የምናጠናበትና የምንተረጉምበት አቀራረባችን በእውነት ትክክለኛና ተገቢ ከሆነ፣ በጣም ከባድና አስቸጋሪ የሚመስሉ ትንቢታዊ ምንባባት እንኳ መልእክታቸው ግልጽ ይሆንልናል። ስለዚህም አቋሞቻችንን እና እድሜ ጠገብ የሆኑ ልማዳዊ አመለካከቶቻችንን የምንፈትሽባቸው አንዳንድ አማራጮችን ለመመልከት አሁን ጊዜው ነው። የኃላፋውያን (Preterists) ምልከታ ደግሞ ሌሎች አማራጮችንም ማየት ለመጀመር በጣም ታላቅ ጠቀሜታ አለው።
የኃላፋውያን አመለካከት ምንድን ነው? ጌታ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ መጨረሻው ቀንና ስለ ፍጻሜ ጉዳዮች ያስተማሩት አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ያኔ በዚያው ትውልድና ዘመን ውስጥ ሁሉ ተፈጽሟል ብሎ የሚያምነውና የሚያስተምረው የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ኃላፋዊነት (preterism) ይሰኛል። preterist የተሰኘው ቃል የተወረሰው praeter ከተሰኘው የላቲን ቃል  ሲሆን ትርጉሙም "አልፎአል"፣ "አልፎ ሄዶአል" ማለት ነው። "ኃላፋዊ" ማለት የትንቢት ፍጻሜ አልፎአል፣ ካለፈም ቆይቶአል ማለት ሲሆን፤ መጻእያን ማለት ደግሞ የትንቢት ፍጻሜ ገና ወደ ፊት የሚጠበቅ ነው ማለት ነው። በመሰረቱ የኃላፋዊነት አመለካከት ማለት በሁሉ ረገድ የመጻኢነት አመለካከት ተቃራኒው ማለት ነው። መጻኢያን፣ አብዛኛዎቹ የመጨረሻው ዘመን ትንቢቶች (በተለይም ዋና ዋና የሆኑቱ) ገና ወደ ፊት ይፈጸማሉ እንጂ እስካሁን አልተፈጸሙም ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉም። ኃላፋውያን ደግሞ በበኩላቸው ሁሉም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች በክርስቶስና ቀጣይ በሆነው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን  እድገትና መስፋፋት ውስጥ ተፈጽመዋል ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉ።
ኃላፍያን የተሰኘው ስምም ሆነ ኃላፊ የተሰኘው ግስ ለኃላፊ ጊዜ አነጋገር የሚያገለግል ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የነገረ ፍጻሜ ጥናትን በተመለከተ የኃላፋውያን እይታ፣ የጌታን ዳግም ምጽአት ጨምሮ ሁሉም ትንቢት፣ የሙታን ትንሣኤና ፍርድ እኛ እየኖርንበት ካለነው ከዚህ ዘመን በፊት አስቀድሞ ድሮ ገና ተፈጽሞአል ብሎ ያስተምራል። ለኃላፍዊው ነገረ ፍጻሜ ትንቢት ሁሉ ያለፈ ታሪክ ነው። ይህንንም ለማስረዳት የቅዱሳት መጻህፍትን አስተምህሮ ጠቅሶ የሚያቀርበው ማብራርያ ከየትኛውም የትርጉም መንገድ ይልቅ ጌታ ኢየሱስን እግዚአብሄር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው ነብይና እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያከብረው፣ የቅዱሳት መጻህፍትንም ተአማኒነት የሚያረጋግጥ፣ ቅዱሳት መጻህፍትም ለተሰጡበት አውድ ታማኝ ሆኖ የትርጉም ቀዋሚነትን (consistency) የሚጠብቅ እንደሆነ አይኑን ያልጨፈነ ሁሉ ሊያረጋግጠው ይችላል። በርካታ መጻኢያን ግን ከሚከተሉት የትንቢት ትርጉም አካሄድ የተነሳ፣ ክርስቶስ በመንግስቱ ምስረታ ሙሉ በሙሉ ተሳክቶለታል ብለው በእውነት ለማመንም ሆነ ለመመስከር ይቸገራሉ።
የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት የኃላፋውያን ትርጉም ከመላው የክርስትና እምነት ጋር ተስማሚ የሆነና፣ ደግሞም ልባቸውን እልከኛ ካላደረጉ በቀር "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" (Sola Scriptura) የተሰኘውን የተሃድሶ አቋም ባነገቡ በሁሉም ቤተ እምነቶች ውስጥ ሊያዝና ሊንጸባረቅ ሰፊ እድል ያለው ደግሞም የሚችል እምነት ነው። እንደ Christianity Today, Christian News, World Magazine  በመሳሰሉት እና በሌሎችም በበርካታ ታዋቂና ተነባቢ የህትመት ስራዎች ሲጠቀስ ኖሮአል። በመላው አለም በሚደመጡ የራድዮና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች የኃላፍያንን ምልከታ የሚያንጸባርቁ የትምህርት ስርጭቶች፣ በየወሩና በየሶስት ወሩ ታትመው ለንባብ የሚበቁ በርካታ የህትመት ውጤቶች አሉት። በርካታ የኃላፋውያን መጻህፍት፣ በራሪ ወረቀቶች፣ የቪድዮና የኦዲዮ ትምህርቶች ተዘጋጅተው የሚበዙት ስራ ላይ ውለዋል። የኃላፍያንን መጻህፍት ጽፈው የሚያዘጋጁ ጸሐፍያን በተለያዩ የሬድዮ ማሰራጫዎች እየቀረቡ ለብዙ ጊዜያት ቃለ ምልልስ ተካሂዶላቸዋል። የኃላፋውያን አመለካከት በመላው የምእራቡ አለም የሥነመለኮት መምህራንና ተማሪዎች ዘንድም ብቻ ሳይሆን፣ በክርስቲያናዊው ማህበረ ሰብ ውስጥ ወደታች ወርዶ ከፍተኛ ትኩረት እየሳበ ያለና፣ በተለይ በድረ ገጽ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን (በዩቲዩብ፣ በፌስ ቡክ) እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለ ጉዳይ ነው።
የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሱስ በእነርሱ የህይወት ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የነበራቸው መጠባበቅና፣ ይህንን አይነት መጠባበቅ እንዴት ሊኖራቸው እንደቻለ፣ ከየትስ እንዳገኙት ሁልጊዜ ሲያስገርም የሚኖር ጉዳይ ነው። ለጥንት ቤተክርስቲያን ሰዎች ክርስቶስ በትውልዳቸው ተመልሶ እንደሚመጣ በቃል የተነገራቸውም ሆነ በመልእክት የተጻፈላቸው ቃል በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ንግግርና ጽሁፍ የሆነውን ያህል፣ እንዲሁ እነዚያው የጥንት ክርስቲያኖች የጌታን ቀን ይናፍቁና ይጠባበቁ የነበረበት ያ ተስፋ፣ እምነትና ናፍቆት በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ነበር። ክርስቶስ ተመልሶ የሚመጣው መቼ እንደሆነ ክርስቶስ ራሱና ሐዋርያቱ ተናግረው ነበር ወይ? ታዲያ መቼ ነው ተመልሶ ይመጣል ያሉት? ከዚህ ቀጥሎ ከብዙ በጥቂቱ በማቀርባቸው በእነዚህ ዝርዝር ምንባባት ውስጥ የተገለጠውንና በጣም በቅርብ እንደሚሆን የነበረውን ስሜት ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፦
ማቴ 10፥ 23 "በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።"
ማቴ 16፥ 27፣28 "የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።"
ማቴ 24፥ 34 " እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"
ያዕ 5፥ 8 " እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።"
1ጴጥ 4፥ 7 "ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥"
ራእይ 1፥ 1-3 "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።"
ራእይ 22፥ 6-7 "እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ።"
ራእይ 22፥ 10 "ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።"
ራእይ 22፥ 12 "እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።"
ራእይ 22፥ 20 "ይህን የሚመሰክር፦ አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና"
በዚያው ትውልድ ውስጥ ለመመለስ የሰጠውን የተስፋ ቃል ኢየሱስ ጠብቋልን? ቃሉንስ አላጠፈምን? ሐዋርያቱስ ቢሆኑ ክርስቶስ በራሳቸው የሕይወት ዘመን በቅርቡ ተመልሶ እንደሚመጣ ሲናገሩ የነበረው ንግግራቸው ትክክል ነበርን? አልተሳሳቱም ነበርን? እነዚህና መሰል ጥቅሶች ሁልጊዜም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የሚረብሹና ምቾት የማይሰጡአቸው ሲሆኑ፣ የሥነ መለኮት "አዋቂዎች" ነን ለሚሉ የለዘብተኝነትን አቋም ለያዙ ሊቃውንት ነን ባዮችና ከሃድያን ደግሞ የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነተኛነት ለመንቀፍና ስህተት የለባቸውም ስንል የምናምነውን የእኛን እምነት ለማጥቃት ይጠቀሙባቸዋል። "እነዚህ ምንባባት ይፈጸማሉ በተባሉበትና እንዲፈጸሙ በተነገረላቸው ጊዜ (በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት) አልተፈጸሙም፣ ስለዚህ ኢየሱስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን በትንቢታቸው ወድቀዋል፣ በመሆኑም ቃሎቻቸውን በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡና ስህተት የሌለባቸው ናቸው ለማለት አንችልም" ሲሉ ይተቻሉ። እነዚህ ጥቅሶች የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ከኢየሩሳሌም ውድቀት፣ ከቤተ መቅደሱ ውድመት፣ እንዲሁም በ70 አ.ም ላይ ከሆነው የአይሁድ ህዝብ እልቂትና የብሉይ ኪዳን የመስዋዕቱ ስርዓት ፍጻሜ ጋር ባለው ግንኙነት አንጻር የሚናገሩና የሚያስተምሩ ናቸው። እነዚያ የቤዛነት ትእይንት የመጨረሻ ኹነቶች ልክ እርሱ ይሆናሉ ሲል እንደተናገረው ተፈጽመው አልፈዋል፣ ስለዚህ ጊዜን አመልካች የሆነውን የትንቢቶቹን አቀራረብ ቸል ብሎ፣ "ትንቢቱ ገና ወደ ፊት ይፈጸማል እንጂ እስከ አሁን ገና አልተፈጸመም" ሲል፣ ሳይፈጸም እንደቀረ ወይም እንደዘገየ የሚያስተምረውን እድሜ ዘልዛላ አመለካከት ለማብራራትም ሆነ ለመተንተን መሞከር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ ጊዜው ያለፈበትና ምንም አስፈላጊነት የሌለው ነው።
ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ መንግስቱን ሰጥቶናል። አሁን በክርስቶስ "የዘላለም ሕይወት" አለን። የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት እስከ ትንሳኤ እና የፍርድ ቀን ድረስ በሀደስ ውስጥ የቤዛነታችንን ቀን እየጠበቅን መቆየት አያስፈልገንም። ያ ያስፈልጋቸው የነበሩት የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ነበሩ። እኛ ያመንን ግን በክርስቶስ ስራ ከፍርድ ወጥተን ወደ ዘላለማዊው መንግስት ሕይወት ተሸጋግረናል። እነዚህ በክርስቶስ አሁን ያሉን እና የተገኙ ከኛም ጋር በውስጣችን የሚኖሩ ባርኮቶቻችንና ጥቅሞቻችን ናቸው እንጂ፣ "ላም አለኝ በሰማይ ወተትዋንም አላይ" አይነት፣ ተስፋችን የተራበ ሰው እንደሚጓጓለት ርቆ እንደ ተሰቀለ እንቁልልጬ ዳቦ አይደለም።  ቅዱስ ቃሉ፦ "የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት" (ምሳሌ 13፥ 12) ይላል። መላው የራእይ መጽሐፍም የተፈጸመ መጽሐፍ ሲሆን፣ የሚታየውም መጽሐፉ በተጻፈበት ዘመን፣ በጸሐፊውና በበኩረ ተደራስያኑ ታሪካዊ አውድ ብቻ ነው። የመጽሐፉ አጠቃላይ ተዛምዶም በክርስቶስ ካገኘነውና ከተካፈልነው ከመንግስቱ ጋር የተቆራኘ ነው።
ቀጥተኛውና ግልጹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ይህ ነው። ትንቢትም ትርጉም የሚሰጠን አቀራረባችን በዚህ መንገድና አተያይ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህ አቀራረብ "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" (Sola Scriptura) በተሰኘው ብቸኛ የተሃድሶ ብርሃን እየተመራ በርካታ አወንታዊ፣ ገንቢና ተጨባጭ የሆነን ንጽረተ አለም ይሰጠናል። ይህ አይነቱ የትንቢት አቀራረብ በአቋሙ ወንጌላዊ የሆነውን ወግ አጥባቂነት የጨበጠ፣ በክርስቶስ ብዙ መጽናናትን የሚሰጥና ግርማ የሞላውን የክርስትናን የድልና የከፍታ ሕይወት የሚያለማምድ፣ በትርጉሙ ቀዋሚነት (consistency) ያለው፣ ብሩህ አመለካከትን ይዞ ጨለምተኛ ያልሆነ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚሰማው አቀራረብ ነው። ጣፋጩን የክርስትናን ሕይወት አጣጥሞ ከመኖርና አለምን በወንጌል ከመድረስና ከመለወጥ ያለፈ ሌላ ምኞትም ሆነ የተሰወረ ፍላጎት እንዳይኖረን የሚያደርገን ንጹህ ትምህርት ነው። በእግዚአብሔር መንግስት መንፈሳዊ ተፈጥሮ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ትርጉም ነው፣ እንጂ የእግዚአብሔርን መንግስት በተዳሳሽ አካላዊነት፣ በቁሳዊነት፣ በፍልቅ ሞቅታና በስሜታዊነት ፍንደቃ አይለካም አይተረጉምም። ለሌላ ጊዜ በተላለፈና ገና ወደ ፊት እንደሚገባበት የገነት መንገድ ስሜታዊ በሆነ ደስታ ከሚያደክምና ከሚያሰለች ተስፋ ይልቅ፣  አሁን በክርስቶስ የሆነውንና የተገኘውን የተረጋገጠ መዳንን እና የቤተ ክርስቲያንን እውነታነት ያስተምራል። የትንቢትን ፍጻሜ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የታሪክ ሰነድ ገጾች ጋር እያገናዘበ ታሪክን የኋሊት ይመለከታል እንጂ ስለ መጻኢው ደንግጦ ባፈጠጠና በፈራ አይን ያንንም ይሄንንም እየገመተ "ምን ይመጣብኝ ይሆን" እያለ ራሱን በስጋትና በቁም ቅዠት አይጠምድም፤ የመጻኢነት ትንተናም እያቀረበ ማንንም አያሸብርም። ይህ አለም እንደሆነ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ (ካስፈለገም ለዘላለም) እንዲሁ እንዳለ ይኖራል። የምስራች ልንገራችሁ፣ እግዚአብሔር ይህንን ግዑዝ አለም ሊያወድም ምንም እቅድ የለውም። የሰው ልጆች ቢፈልጉ እንኳ፣ ቢቆጡና ቢሞክሩ ይህንን ግዑዝ የእግዚአብሔር አለም ሊያጠፉት አይችሉም። ስለዚህ "ይህ አለም ይጠፋል" በሚል ተላላነት እየተደናበርን፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖረን ከሚገባ ተሳትፎና በጎ ተጽእኖ በጨለምተኝነት ከማፈግፈግ፣ ብሎም ከዚህ ነባራዊ አለም ለመውጣትና ማምለጫን በመፈለግ በከንቱ ከምንደክም፣ ይህ አለም የእግዚአብሔርና የሰው ልጆች አለም ነውና፣ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የተሻለ የመኖርያ ስፍራ  እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነታችንና አገልግሎታችንን በትጋት ብንቀጥል የእግዚአብሔርን ፈቃድ እናደርጋለን።
ባለፉት 300 አመታት ውስጥ አንዳንድ ታላላቅ የሥነ መለኮት ሰዎችና ሊቃውንት ይህንን አመለካከት ይዘው እንደ ነበር ግልጽ ነው፤ ነገር ግን የሚበዙት ክርስቲያኖች የሮማውን ካቶሊክ ጳጳስ ወይም ጳጳሳዊ ስርአቱን "የክርስቶስ ተቃዋሚው" ነው፣  ደግሞም የሮምን ቤተክርስቲያን የራእይ መጽሐፍ "ባቢሎን" ናት በሚል ወይም በሌላ አይነት የመጻኢነት አስተሳሰብና ትርክት ተይዘው ሲያስተምሩና ሲጽፉ ኖረዋል። በዋናነትም በታሪካውያን (Historicism) እና በአልቦ ሺህ አመት መንግስት (Amillennialism) የነገረ ፍጻሜ ተርጓሚዎች ዘንድ ይህ አይነቱ ትርክት የተለመደ ነው። ያ ግን አሁን ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ ሆኖ አጥብቀው በሚጠይቁና አድምተው በሚመረምሩ የቃሉ ተማሪዎች እየተተቸ በብዙ ተለውጦአል። አሁን ያለው ትውልድ (መደዴውን ማለቴ አይደለም) ከቀድሞው ይልቅ እምነቱንና አመለካከቱን አጥብቆ የሚጠይቅና የሚፈትሽ ነው ብዬ አስባለሁ። መቼም እነ ዊልያም ሚለር፣ ደርባይ፣ ረስል፣ ሩትፎርድ፣ ስኮፊልድ፣ ዋልቩርድ እና ሃል ሊንድሴይ በዘመን ቆጣሪነት (Despensationalism) ትርክት በብዙ ተታለው ሌሎችንም እንዳሳሳቱ እኛ በቀላሉ የምንሞኝ አይደለንም። በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ ሲቆለል የኖረው የአስተምህሮ ውሸትና እስካሁንም ብዙዎች በትንቢት ትርጉማቸውና በአስተምህሮታቸው የሚያራግቡት የሃሰት ትንበያ የበለጠ ጠያቂና ጠርጣሪ አድርጎናል። ከቅዱስ ቃሉ በቀር እንደወረደ የምንቀበለው፣ ሳናላምጥ የምንውጠው፣ የማንጠረጥረውና የማንጠይቀው ነገር የለንም። "ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን?" (ሐዋ 17፥ 11)
ከመቶ አመታት በፊት በእንግሊዝ አገር የባይስወተር ማህበረምእመናናዊት ቤተክርስቲያን መጋቢ የነበሩ ዶክተር ጀምስ ስቱዋርት ረስል (1816-1895) The Parousia - A Critical Inquiry Into The NT Doctrine Of Our Lord’s Second Comingበሚል ርእስ መጽሐፍ ጽፈው ነበር። ይህ መጽሐፍ አሁንም እንደገና በብዙ ቅጅ እየታተመ ሲሆን በአሜሪካን አገርና በሌሎችም አገሮች በበርካታ የክርስቲያን መጻህፍት መሸጫ ሱቆች ውስጥ በየሸልፉ ላይ ተሰድሮ ይገኛል። ይህ መጽሐፍ ቆየት ካሉትና የኃላፋውያንን አመለካከት ደግፈው ከተጻፉት መጻህፍት መካከል ዋነኛው ነው። በአውሮፓ የሚኖሩ በርካታ ክርስቲያናዊ የሥነ መለኮት ሰዎችም ተመሳሳይ አቀራርብን ይዘው ተስተውለዋል፤ በመሆኑም ከረስል ጋር በተመሳሳይ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ተርጓሚዎች ተመሳሳይ የሆነን ነገር ሲናገሩ ቢደመጡና ስለመጽሐፉም ጥሩ ጥሩ ነገር ቢናገሩ የሚያስገርም አይደለም፤ ለምሳሌ ኤፍ. ደብልዩ. ፌረር "ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀስና እንዲጠና የሚጠቆም" ብሎለታል። Biblical Hermeneuticsየተሰኘ መጽሐፍ የጻፉትና ከራስል መጽሐፍ ብዛት ያላቸውን ማጣቀሻና ማጣቆሚያ የተጠቀሙት የረስል ዘመን ሰው ሚልተን ቴሪ በስነ መለኮቱ አለም የነገረ ፍጻሜ ስነ ትርጓሜ ጥናት ዘርፍ ሰፊ ተቀባይነትን ባተረፉ ሥራዎቻቸው የረስልን የኃላፋዊ አቀራረብ ተከትለዋል። ስለ ረስል እና ስለ ኃላፋውያን አመለካከት ከተናገሩ እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ሊቃውንት መካከል አንዳንዶች የተናገሩትን እዚህ ላይ በጥቂቱ ልጥቀስ፦
"አስቀድሞ አእምሮአችሁን ይዞት ከነበረው የነገረ ፍጻሜ ስርአተ ትምህርት ጋር የሚጣጣሙ ባለመሆናቸው የተነሳ፣ ኢየሱስ ተመልሶ የሚመጣበትን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትንና እንዲህ ያሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ለመተርጎም ምን ያህል ጊዜ ስትታገሉ ኖራችኋል? The Parousia የተሰኘው የረስል መጽሐፍ የክርስቶስን መመለሻ ጊዜ ቅርበቱን በሚናገርበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በዋዛ የሚመለከተው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን እንዳለ በቁሙ እንተረጉማለን የሚሉ ሰዎች ሆን ብለው ወይም ሳያስቡት ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ከሚሉት በተቃራኒው ሌላ ትርጉም እየሰጡ የነዚህን ጊዜ አመልካች የሆኑ ምንባባትን ግልጽ ትርጉም ዘለው ያልፉታል። የራስልን መጽሐፍ ማንበብ ማለት በጭስ በታፈነ ክፍል ውስጥ ንጹህ አየር እንደ መተንፈስና በግልጽ የሥነ ፍታቴ መስታወት አጥርቶ እንደማየት ነው።"  (Gary DeMar - Author of Last Days Madness)
"የራስል መጽሐፍ ማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊው የነገረ ፍጻሜ ጥናት በአግባቡ የታየበት ለዛሬዋ ቤተክርስቲያን ተዘጋጅቶ ከቀረቡላት እጅግ አስፈላጊ ስራዎች መካከል አንዱ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ የተገለጸውና የፓሮዥያውን የጊዜ ማእቀፍ አመላካች የሆኑ ጥቅሶችና ምንባባት በዚህ ጥራዝ ውስጥ ተነስቶ በወጉ የተባለው ነገር ሁሉ ጠቀሜታው ለነገረ ፍጻሜአዊ ጥናት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ፊት በተቀደሰው መጽሐፍ ንጽህናና ታማኝነት ላይ በተቃውሞ ለሚነሱ ክርክሮች ሁሉ ፍቱን መድሃኒት ነው።"  (Dr. R. C. Sproul - Chairman, Ligonier Ministries)
"ምንም እንኳ የጄ. ስቱዋርት ረስል The Parousiaየተሰኘው መጽሐፍ ከደረሰበት ድምዳሜ ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ ባልልም፣ ነገር ግን ይህንን በወጉ የተደራጀና የተሰናሰለ፣ ክርክሩንም በጥንቃቃቄ ያቀረበ፣ ለእውነተኛና በሳል ለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጆችና አጥኝዎች የኃላፍያንን የነገረ ፍጻሜ ምልከታ በመከላከል የተጻፈ ዝርዝርና እምቅ የጽሁፍ ሃብት እንዲነበብና እንዲጠና በአንክሮ አሳስባለሁ። በነገረ ፍጻሜ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ካነበብኩአቸው መጻህፍት መካከል በእጅጉ አሳማኝ የሆነና የያዝኩትን አቋም በኃይል የተገዳደረ፣ በገዛ ራሴም የኖረና የቀደመ አስተሳሰቤ ላይ ታላቅ ተጽእኖን ያሳደረ አንዱ መጽሐፍ ነው። ይህ የረስል የአዲስ ኪዳን ነገረ ፍጻሜ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የሥነ መለኮት ጥናት የጥራት ደረጃ ከፍ አድርጎታል።"  (Dr. Kenneth L. Gentry, Jr. - Author of Before Jerusalem Fell)
በእርግጥም የራስል መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትንቢት ለመረዳት እጅግ የሚረዳ ሃብት ነው፣ ብዙዎች ግን ይህንንም መጽሐፍ ሳያነቡ በገዛ ራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በግላቸው እያነበቡና እያጠኑ ወደ ኃላፍያን ምልከታ እንደደረሱ እናውቃለን። እነርሱም አሁን የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት ትርጉምና መልእክት በርቶላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች ፍጻሜአቸው ገና ድሮ ያለፈ መሆኑን እስካሁን ገና ያላወቀና ያልባነነ የቃሉ ወዳጅና ተማሪ ከሆናችሁ፣ የምትነቁበትና የምትባንኑበት ጊዜው አሁን ነው ልላችሁ እወዳለሁ።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/