ሉቃስ 11፥ 13 "እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?"
ፍርድ "የጸሎት መልስ" ሆኖ ሊመጣ ይችላልን? ወይስ በመለኮታዊ ፍርድ የምንቀበለው "የጸሎት መልስ" ሊኖረን ይችላልን?
በወጉ የእግዚአብሔርን ቃል ያልተማሩና በቅዱስ ቃሉ በኩል ራሱን የገለጠውን የቃሉን ባለቤት እውነተኛውን አምላክ ያላወቁ፣ መንፈሳዊነትም በስሜት መጋለብ የሚመስላቸው ሰዎች ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ይህንን ጥቅስ ያለቦታው ሲጠቅሱትና ሲሰነቅሩት ብዙ ጊዜ ታዝቤያለሁ። መንፈስ ቅዱስ የአብ የተስፋ ቃል ነው፣ ደግሞም ለሚያምኑ ሁሉ ያለ ልየነት የተሰጠ ስጦታ ነው። በጸሎትና በምልጃ ተግተው ብዙ ጊዜአቸውን የሚሰዉ አማኞችም በስሜት ከሚከንፉ ወረተኞች ይልቅ በብዙ በተሻለ ጥሞና መንፈስ ቅዱስንና አሰራሩን እንደሚለማመዱ እሙን ነው።
አማኞች ግን እንደ እግዚአብሔር ልጆች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል መለመንም ሆነ ማንንም ማስለመን መለማመንም አያስፈልጋቸውም፣ ምክንያቱም ባመኑ ጊዜ የተሰጣቸውና የተቀበሉ ናቸው። የእግዚአብሔር ልጆቹ ሊሆኑ በጌታ ባመኑ ጊዜ ያኔውኑ መንፈሱ አላቸውና። እግዚአብሔር በጸጋው ያፈሰስውንና በሙላት በውስጣችን እንዲኖር የሰጠንን መንፈሱን ዳግም ስንወለድ ተቀብለነዋል እንጂ በማንም ወይም በምንም በኩል አንቀበለውም። ሐዋርያው ጳውሎስ "በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን?" (ገላ 3፥ 2፣ 5) ብሎ ወደ ህጉና ወደ አሮጌው ስርዓት እያፈገፈጉ የነበሩትን የገላትያን ምዕመናን ይጠይቃል፤ መልሱም የለም መንፈስ ቅዱስን የተቀበልነው "ከእምነት ጋር በሆነ መስማት" ነው፣ የሚል እንደሆነ ግልጽ ነው። "ሰው ወንጌልን ሰምቶ ሲያምን መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል" የሚለው እምነት ደግሞ ለዘመናት የኖረና በቅዱስ ቃሉ የሚረጋገጥ ትምህርት ነው። በአንጻሩ ሰው ዳግም ከተወለደ በኋላ ወዲያውኑ ወይም ቆይቶ፣ እጅ ተጭኖለት ወይም ጾም ጸሎት ይዞ፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ከፈጸመ በኋላ፣ ወይም ዘይት በመቀባት ወዘተ. በማናቸውም መንገድ መንፈስ ቅዱስን ይቀበላል የሚለው ግን በቃሉ ሊረጋገጥ የማይችል ዘመነኛ ትምህርት ነው። እንደ ሮማው ጳጳስ በሰዎች ነፍስ ላይ ለመሰልጠን ፍላጎት ያላቸው ተቀብተናል ባዮች የዘረጉት መዋቅር ብቻ ነው።
መሰረታዊ የሆነው የጰንጤ ቆስጤ ቤተ እምነት ልምምድ ከዚህ የቃሉ መሰረት ካለው አስተምህሮ ጋር እንደማይስማማ የታወቀ ነው። ስለዚህም ይህ ቤተ እምነት ስለ ድነት በሆነው አስተምህሮው መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል፣ አንዴ ዳግም መወለድ፣ ቀጥሎም በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ወይም መጠመቅ የተሰኙ ሁለት ደረጃዎችን መራመድ እንዳለብን ያስተምራል። ይህም "The doctrin of two stage initiation" የሚባለው ነው። በአብዛኛው የቤተ እምነቱ ተከታዮች ዘንድ በወጉ የማይታወቀውና የማይጠየቀው ይህ አይነቱ ትምህርት በመንፈስ ቅዱስ ማንነትና አስራር ላይ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሥነ መለኮታዊ ጥያቄዎችንና መፋለሶችን ያስነሳል። ለምሳሌ፦ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ወይም መሞላት ከዳግም ልደት በኋላ የሚመጣ ቀጣይ ልምምድ ከሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአማኙ በጥምቀት ሳይሰጠው በፊት ከመንፈስ ቅዱስ የተነጠለ ዳግም ልደት ይቻላል ማለት ነው? ወይስ በዳግም ልደት ጊዜ ለዳግም ልደት በሚሆን ስፍር ወይም ልክ መንፈስ ቅዱስ ከተሰጠ በኋላ ብዙ ወይም ጥቂት ቆይቶ አማኙ በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቅ ወይም ሲሞላ ያኔ መንፈስ ቅዱስ በሙላት የሚሰጠው ከሆነ መንፈስ ቅዱስ አንድነቱ ተከፍሎ ይመጣል ማለት ነው? ይህም ጥያቄ መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም ወይ? አካልስ ይከፈላል ወይ? የሚል ጥያቄ ያጭራል። ከዚህም በላይ መንፈስ ቅዱስ ያላቸውና የሌላቸው በሚል ይህ ትምህርት የክርስቶስ አካል የሆኑ አማኞችን በሁለት ደረጃ አይከፍልምን? የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እና በመንፈስ የመሞላት ልምምድስ ልዩነቱና አንድነቱ ምልክቱስ ምንድን ነው? ወዘተ....።
በርግጥ የዚህች አጭር ጽሁፍ ትኩረት እኒህን ጥያቄዎች መመለስ ባይሆንም አንባቢዎቼ ግን ላለፉት ጥቂት መቶ አመታት እየታወቀ ለመጣው የጰንጤ ቆስጤ ልምምድና ትምህርቱ እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቀው ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊውና አዲስ ኪዳናዊው የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት አስተምህሮ እይታቸውን እንዲመልሱ በእግረ መንገድ ማሳሰብ ፈልጌ ነው። በእኔ ግምገማ ወንጌላዊው እምነትና ተሃድሶ ከካቶሊካዊው የእንቶ ፈንቶ የሰው ስርአት ጥቃት በኋላ የገጠመው ሌላው ተግዳሮት የዚህ የሁለት ደረጃ እምነት አስተምህሮ ይመስለኛል። ሁሉ ወንጌል አማኝ ጰንጤ እንደሆነ በሚታሰብበትና በሚገመትበት ማህበረሰብ ውስጥ ላደገና ለኖረ እንደ እኔ ላለ ግለሰብ የጰንጤ ቆስጤ አስተምህሮና ልምምድ የወንጌላዊው እምነት ሌላ ተግዳሮት ነበር ብሎ አቋም መያዝ በሰዎች መንግስት መቆሚያም ሆነ መቋሚያ መቋቋሚያም የሚያሳጣ እንደሆነ ለማወቅ ነብይ መሆን ወይም ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም። ወንጌል አማኝ እንጂ ጰንጤ አይደለሁም እንዳንል ሁላችንን አንድ ሳጥን ውስጥ ከቶ ለቆለፈብን አስተሳሰብ እጅ የሰጠን እንመስላለን።
እርግጥ ነው ቃሉ በጸሎት እንድንተጋ በብርቱ ያስጠነቅቀናል (ኤፌ 6፥ 18፤ ቆላ 4፥ 2)፤ በጸሎት ወደ እውነተኛው አምላክ መቅረብ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከማይለወጥ ፈቃዱ ጋር መስማማት ደግሞ ያስፈልገናል። የሚጸልዩና የሚያጸልዩ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ማእከላዊነት ውስጥ የማይገኙ አማኞች ሁሉ የገዛ ፈቃዳቸውን ሲከተሉ ይስቱ ዘንድ በአደጋ ውስጥ ያሉ ናቸው።
ወደ ተነሳሀበት በርእሰ ጉዳይ ልመለስና፣ እግዚአብሔር ፍርድን ልኮ የሰዎችን ልመና ወይም መሻት እንደ መለሰ ምሳሌ የሚሆን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንብባችሁ ታውቃላችሁን? በኦሪት ዘሁልቅ 11፥ 4-6 ያለውን እስቲ ተመልከቱ፦ "በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤ አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ።" ይላል።
የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር የሰጣቸውንና ከሰማይ ያዘነበላቸውን መና በተመለከተ ያሳዩትን ንቀትና አስተያየታቸውን የምናነብበት ታሪክ ነው። በተለይ ቁጥር 4 ላይ "በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? ... አሉ " ሲል ይነግረናል። "ልዩ ልዩ ሕዝብ" ማለት ድብልቅ ሕዝብ ማለት ነው፣ የዳነውም ያልዳነውም ሲደባለቅ በተለይ ህዝብን የሚለውጥ ንጹህ የክርስቶስ ትምህርት ከሌለ፣ ሰዎችም ስሜታቸው ብቻ የሚያገለግላቸውን ሲከተሉ ያኔ የሕዝብ ምኞት ስጋዊ ይሆንና የእግዚአብሔርን ስጦታ እያቃለሉ ሥጋዊው ነገር ላይ ትኩረት ይበዛል። የግብጹን አመጋገብ የሚጎመዡና የሚመኙ በመለኮታዊ ጸጋ የተሰጣቸውንና ከሰማይ የወረደላቸውን የቃሉን መና ንቀው ከሚያለቃቅሱ ጋር ሲገናኙ፣ "ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ" በመጠመድ የሚያስቡትና የሚመኙት ሁሉ ከመና ያለፈ ፍላጎት ይሆንና ምንግዜም ቢሆን መደሰቻቸው ሥጋና የሥጋ ብቻ ይሆናል።
"እናስባለን" እለት እለት ያስቡት ዘንድ እግዚአብሔር በማይለወጥ ፈቃዱ በጸጋው የሰጣቸው ምን ነበር? ኢያሱ 1፥ 8 ላይ እንዲህ ይላል፦ "የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።" እስቲ የዳነ ሰው ይህንን ውድ ነገር ማሰብ ትቶ በመለኮታዊ መስፈርያ ለአቅመ መታሰብ ያልደረሰውንና የማይደርሰውን ርካሽ የሆነውን "ዓሣውን፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት" ያስባል? ምን አይነት የወደቀ አሳብ ነው? አይ "የብልጽግና ወንጌል" እግዚአብሔር ይይልህ! ሰዉ ሁሉ ሥጋውን እንዲከተል በምእመናን መካከል አሽሉከህ ያገባኸውን ግብጻዊ የሆነ የአስተቃይጦ ኑፋቄ ከማጋለጥ አንቦዝንም።
በመንፈሳዊው ሁኔታ የእኛ መና "ከሰማይ የወረደው እንጀራ" ኢየሱስ እንድንበላውና በሕይወት እንድንኖር በቃሉ በኩል የሰጠን ሥጋው ነው፣ ይህም የመስቀሉ ቃል እንደሆነ የዮሐንስ 6 አውደ ምንባብ ያስተምራል። ብዙ ጊዜ ለማስተማርም ለመውቀስም ለማስጠንቀቅም ባገኘሁት እድል ሁሉ እንደተናገርሁ አሁንም እላለሁ እግዚአብሄር እንዳዳነው ህዝብ "ቃሉ ብቻ ይበቃናል"። እርሱ መንፈሳዊ ምግባችንና የእለት መናችን ነው። ከዚያ ይልቅ ግን ሌላ አለፍ ያለ ሥሜታዊ ነገር ሁሉ፣ በማንኛውም ስምና ማእረግ የሚጠራ ሰው ልምምድና ትምህርት ሁሉ፣ ህልሙም ቢሆን ቅዠቱ፣ ራእዩም ቢሆን መገልበጡ ማለት "መገለጡ"፣ ማንኛውም በቃሉ ድጋፍ የሌለው እምነታችንን ያቆምንበት ከሰው የሰው የሆነ ነገር ሁሉ "ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነፋስንም እንደመከተል" ያለ ነገር ነው።
እንዲህ ያለው ፍለጋ በእግዚአብሔ ተላልፎ የመሰጠት ፍርድ ነው እንጂ በምንም መመዘኛ ጸጋና በረከት ሊሆን አይችልም። ቃሉን አቅልሎ ሌላ ተጨማሪ ለሚመኝ ሰው እግዚአብሔር ምኞቱን ሊሰጠው ይችላል፤ ደግሞም ይሰጠዋል። ሲሰጠው ግን በዚያ ነገር ውስጥ ክሳትን ሸሽጎ ይሰጠዋል። ያም ፈጽሞ በረከት አይደለም። ስታቲስቲካዊ መረጃ ማቅረብ ያስቸግር ይሆናል እንጂ እንዲህ ያለውን ቅዠት መከተል መንፈሳዊነትና ብስለት የመሰላቸው በኋላም ጌታን እስከ ወዲያኛው መከተል እስኪሳናቸው ድረስ ከእምነት የተሰናከሉ የምናውቃቸው ብዙዎች ናቸው። ቃሉን መታዘዝ እምቢ ብላችሁ ምንድን ነው የምትመኙት? ጥንቆላን ነው? ሃሰተኛ ልምምዶችን ነው? በፊታችሁ የሚሄድ ኮከብ ካርዝማቲክ ተብዬ አንድ ሰው ነው? ዝናና ሰም የሚያስገኝ የሃይል መገለጥ ነው? ምን ችግር አለ እግዚአብሔር እንደው ሲሰጥ አይጸጸትም፣ በአፍንጫችሁ እስኪወጣ ድረስ ይሰጣችኋል። ግን የሚሰጣችሁ ከነፍሱ ሃዘን ጋር ነው። እንዲህ ያለው እላፊ ፍለጋ ለእስራኤል ልጆች ለቅሶና ለልመናቸው የተሰጠ የእግዚአብሔር የፍርድ ምላሽ መሆኑን ከቃሉ እናስተውላለን።
በዘኁልቅ 11፥ 18-20 የተገለጸውን ተመልከቱ፦ " ሕዝቡንም በላቸው፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ። አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።
"የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል?" ሲሉ የሚበሉትን ሥጋ የሚሰጣቸው ማንም ይሁን፣ ሥጋው ብቻ ይገኝ እንጂ ስለ ምንጩ ግድ አይሰጣቸውም። የዚህ ፍላጎት ተፈጥሮው እግዚአብሔርን መናቅ እንደሆነ ይህ ምንባብ ያስተምረናል። ለዚህ ንቀትና በለቅሶ ለታጀበ ብርቱ ሥጋዊ ልመና አምላካዊው መልስ ለሕይወት እንደሚሆን ጸጋና በረከት የሚቆጠር ሳይሆን ይልቁንም ፍርድና ቅጣት ሆኖ የመጣ አስፈሪ ነገር ነበር "በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም .... ትበላላችሁ" ይላቸዋል። እየዋለ እያደረ የሚሰለችና የሚያንጽም ሆነ የሚያጽናና ምንም ምንም የማይገኝበትን "አገልግሎትና" "አገልጋይ" ሲያጋትረን ግሳቱን እየተቀበልን ለመኖር እንደተፈረደበት ሰው እንገዛለን ወይም ፈቅደን ሃሰትን እንከተላለን።
ዘማሪው ይህንን ታሪክ አንስቶ ምን እንደሚዘምር ተመልከቱ፦ መዝሙር 78፥ 29-31 "በሉ እጅግም ጠገቡ፤ ምኞታቸውንም ሰጣቸው። ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ።"
እግዚአብሔር ያለቀሱለትን ነገር ቢሰጣቸውም፣ የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ግን ከዚያ ካለቀሱለትና ከጠየቁት ደግሞም ከተቀበሉት ነገር ጋር አብሮ ነበር። መዝ 106:15 ደግሞ "የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ" ይላል። የነፍስ ክሳት እንዴት ይገባናል? እስቲ እንዚህን ጥቅሶች አዩና መንፈሳዊ ተዛምዶአቸውን አስተውሉ፦
ዘሌ 26፥ 16 "እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና።"
ዘዳ 28፥ 22 "እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል።"
ኢሳ 10፥ 16 "ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወፍራሞች ላይ ክሳትን ይልካል፤ ከክብሩም በታች ቃጠሎው እንደ እሳት መቃጠል ይነድዳል።"
ክሳት የነፍስ ሲሆን ከባድ ነው። ቃሉን እየተመገበች በተመጣጠነ መንፈሳዊ አቋም ውስጥ የሌለች ነፍስ በክህደትና በተግዳሮቶቿ ፊት አትጸናም። እውነትን መነጠቋና እምነቷን ማጣትዋም አይቀርም። ከምኞትዋና ከልመናዋ ቁንጣን እስኪቀበትታትና ቊዋቅ እስኪላት ድረስ ግብስብሱን ሃሰት ሁሉ እንድታግበሰብስ የተፈረደባት እውነትን የማታውቅ ናት። እንዲህ ላለችው ከሲታ ነፍስ የኃጢአት ይቅርታ ወንጌል ምኗም አይደለም። ለሕጻናት እንኳ የሚሆን ወተት እንደማይገኝባት ከሲታ ላም ትመስላለች። በዘመናችን የሚታየው የነፍስ ክሳት፣ በአብያተክርስቲያናት ዘንድ የሚዳሰስ እስኪሆን ድረስ ጉልህ ነው። ጽኑ የሆነው የባህርይ ችግር፣ የቅድስናና የታማኝነት ጉድለት፣ የእርስ በርስ ጭከናና የወንድማማች ፍቅር እጦት፣ በሚያምነውና በማያምነው፣ በክርስቲያኑና በአለማዊው መካከል ያለው ድንበር እስከማይታወቅ ድረስ የተደረሰበት ድብልቅ ሕይወት አይነተኛው ክሳት ነው። እግዚአብሄር ምኞታችንን የሰጠን፣ የወደድነውንም ያላሳጣን ሲመስለን፣ ነገር ግን ያ የተቀበልነውና ፈልገን ያገኘነው ጉዳይ ራሱን እግዚአብሔርን የሚያሳጣን ሲሆን፣ እንግዲያውስ በዚያ ተቀበልን አገኘነው ባልነው ነገር ውስጥ ተሸሽጎ ያገኘን ቁጣውና እርግማኑ ነው እንጂ በመንፈሳዊ ሚዛን ምንም በረከት የለበትም።
በሆሴዕ 13፥ 11 ላይ "በቁጣዬ ንጉስን ሰጠሁህ...." የሚለውም ከዚህ ጋር ይስማማል። ቁጣና ስጦታ እንዴት አብረው ሊሄዱ እንደሚችሉ እግዚአብሔርን ለማያውቅ ሰው በእውነት ገራ ያጋባል። እንደዚያ የሆነበትን ሁኔታ የሚገልጥ አንዱ ታሪክ ግን ይህ ነው። የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር እንዳይነግስባቸው ፈልገው በዙርያቸው እንደነበሩት አህዛብ ያለ ነገር እንዲኖራቸው በማሰብ እንደገዛ ምኞታቸው ንጉስን ፈለጉ። ታሪካቸውን በጥንቃቄ ከተከታተላችሁ ከንጉስ ሳኦል ጀምሮ በይሁዳ ኢየሩሳሌምም ሆነ በእስራኤል ሰማርያ የነገሱ የሚበዙት የእስራኤል ነገስታት እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን ሲያስቱ የሚታወቁ ናቸው። ዛሬስ ቢሆን ብዙዎች እንደፈለጉ የሚሰለጥኑባቸውንና የነገሱባቸውን ሰዎች የሆኑ ነብያትና ሐዋርያት ተብዬዎች በእግዚአብሔር ቁጣ ተቀብለው እንደሆነ ማን ያውቃል? እንደ አዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በምህረቱና በጸጋው አንዱን ሰው ኢየሱስን ሰጥቶናል። እርሱም ንጉሳችን፣ ነብያችን የሐይማኖታችንም ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ነው። እርሱ ይበቃናል! አለቀ። እርሱ መምህራችንና ሊቃችን ነው። እርሱም ሐዋርያትንና ነብያትን ሰጥቶናል፣ እነርሱም በቃላቸውና በመልእክቶቻቸው እየመሰረቱ ያንጹናል። ዘመናትን ተሻግሮ ለሁሉ የሚሰማ ድምጻቸው ሌላ ማንንም ሳይሆን ክርስቶስን ይገልጣል። ወደ ብሉይና ሐዲስ እየተመለስን የምንካፈለው ሐዋርያዊና ነብያዊ ሥልጣን የሞላበትን በራሱ በክርስቶስ የተሰጠ አገልግሎት አለን። እርሱ ብቻውን ይበቃናል። ሐዋርያትንና ነብያትን ሰጥቶናል ማለት በሌላ አገላለጽ የብሉይንና የሐዲስን ቅደሳት መጻህፍት ሰጥቶናል ማለት እንደሆነ ከማይገባውና ይህንን ከማይቀበል ሰው ጋር በክርስቶስ ትምህርት መግባባት ይቸግረኛል።
በመንፈሳዊ ጉዳይም ሆነ በየትኛውም ነገር ላይ የገዛ ራሳቸውን አስተያየት (opinion) ብቻ ማንጸባረቅ የሚችሉና በሌሎች ጥቃቅን የእለት ተለት ጉዳዮች ላይ እንኳ አጠቃላይ የሆነ ፍርድና ውሳኔ ማሳለፍ የማይችሉ፣ ከሚያገልግሉበት ማህበረሰብና ከቤተ እምነታቸው የዘለለ ተጽእኖ የሌላቸው ውሱኖች፣ እንዴት ሆኖ ነው ከቅዱሳን ሐዋርያት እና ነብያት ጋር የተካከሉ ሊሆኑ የሚችሉት? የመጽሐፍ ቅዱሱን ሐዋርያትኮ የክርስቶስ አካል ሁሉ ይሰማቸዋል፣ ቃላቸውም የመጨረሻው ስልጣንና ውሳኔ ነበር። "እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል የላከኝንም ይሰማል" የተባሉትኮ እነርሱና እነርሱው ብቻ ናቸው። በዚህ ዘመን ሐዋርያ አለ የለም ክርክር ላይ ለምን እንደክማለን? "እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል" የተባለለት ሌላ ዘመነኛ "ሐዋርያ" እንደሚኖረንኮ ምንም ፍንጭ ከቃሉ የለንም። ስም ተሸክሞ የገዛ ራሱን አመለካከት (opinion) ለዚያውም የብልጽግናን ወንጌልና የእምነት እንቅስቃሴን ኑፋቄ የሚያቀረሽብንን እንዴት ነው "ሐዋርያው" ለማለት የደፈርነው? ይህ የክርስቶስን ሐዋርያት እንደመሳደብና የአገልግሎቱን ዋጋ እንደማቃለል የቆጠራል።
ይህ ንግግሬ ከበድ ያለ ጠንካራ አጥንት ሆኖ ለበርካቶች ሊቆረጥሙት የሚስቸግራቸው እንደሆነ አውቃለሁ። ይህንን የምሞነጭረው ማንም ደስ እንዲለው ወይም እንዲከፋው እንዳልሆነ ቢያንስ የገዛ ህሊናዬን አዳምጫለሁ። የዘመናችን እብደት ግን ከዚህም በላይ ቢያናግረኝ አይደንቀኝም። "እኛን ሊገስጸን ተጻፈ" (1 ቆሮ 10፥ 6፣ 11) የተባለውን አስተውሉ። ተግሳጽን ሰምተን እንዳንመለስ ፈርዶብን ግን ያለ ጭድ በባዶ ጭቃ የሚለስነንን ለስሜታችን የማይቆረቁረንና የማይጎረብጠንን ምቾት ብቻ የሚሰጠንን እንጂ፣ ልክ ልካችንን እየመዘነ የሚነግረንን፣ አፍርሶ የሚሰራንን፣ አጥልቆ የሚቆፍረንን፣ አጥብቆም የሚመሰርተንን፣ አጽንቶም የሚመርገንን፣ የሚገስጸንን አንወደውም አንፈልገውምም። ብዙ አማኞች የሚለምኑት መሻታቸው ለምቾቶቻቸው ስለሆነ ልመናቸው በእግዚአብሔር ብርሃን ሲመረመር በክፉ ሆኖ ይገኛል (ያዕ 4፥ 3)።
"አትሳቱ" ይላል የአምላካችን ቃል። ይህንን አንድ ነገር እወቁ፣ ሚስጥርን ማወቅና ሊሆን ያለውንም ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ መናገር፣ ያም የተነገረው ነገር ተፈጽሞ ማየት ፈጽሞ የእውነተኛነት ማስረጃ አይሆንም፤ ወይም ተናጋሪውንም ሆነ የተነገረለትን ጉዳይና ግለሰብ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያደርግ አይደለም። ሟርተኛው በለአምም እኮ የእስራኤልንና የጠላቶቻቸውን እድል ፈንታ አስቀድሞ አይቶ ተናግሮ ነበር (ዘኁ 23፥ 1- 24፥ 25 ተመልከት)። በለአም ለንጉሱ ለባላቅ በገንዘብ የተገዛ ሟርተኛ እንጂ የእግዚአብሔር ነብይ አልነበረም፤ እግዚአብሔር ግን ጠመዘዘው።
ኖስተርዳሙስን የመሰሉ የተለያዩ ሰዎችምኮ በአለም ላይ ስለሚሆኑ የተለያዩ ክስተቶች አስቀድመው የመተንበይ ችሎታ ነበራቸው። ኖስተርዳሙስ በርካታ የአለም ላይ ክስተቶችን ሳይሆኑ በፊት እየተናገረ ክስተቶቹ ልክ እርሱ እንደተነበያቸው ሆነው በተፈጸሙለት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትን ከአለም ህብረተሰብ ዘንድ አግኝቶአል። ለምሳሌ የፈረንሳይን አብዮት፣ የናፖልዮን ቦናፓርቴ አነሳስ፣ የአቶሚክ ቦንብ መፈልሰፍን፣ የአዶልፍ ሂትለርን መነሳት፣ በአለም አቀፍ የገበያ ማእከል ላይ በመስከረም 11 ቀን ስለሆነው ጥቃት፣ እንዲሁም ስለ መጨረሻው ጳጳስ የተነበየ ሰው ነበር። ታዲያ ይህ ሰው ከእግዚያብሔር ነበር ማለት ነው? እንዲህ ያሉ የተናጋሩት የሚይዝላቸው በርካታ ተንባዮች ንግርታቸው ስለተሳካና ተፈጽሞ ስላየን ትክክለኛ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው ልንል አንችልም። "ምን አይነት መንፈስ" እንደሆነ መመርመርና መለየት አለብን። ከሂላሪ ክሊንተን እና ከዶናልድ ትራንፕ ማንኛቸው ምርጫውን አሸንፈው የአሜሪካን የፕሬዚደንት እንደሚሆኑ ጥቂቶች የማይባሉ "ነብያት ነን" ባዮች የሟርት ሙከራቸውን ሲያደርጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ታዲያ የፎረሹ እንዳሉ ሁሉ ቃላቸው የያዘላቸውም አሉ። ማናቸውንም ግን የእግዚአብሔር ነብያት ናቸው ለማለት በዚህ ስኬት ላይ መቆም አያስፈልገንም። ያልሰጣችኋቸውን የስልክ ቁጥር፣ ወይም የጫማ ቁጥር፣ ወይም የስፈራችሁን አድራሻ፣ ወይም የግል ጉዳያችሁን፣ ሌላም ሌላም...፣ ስለነገሩአችሁ በመገረም "አዎ! ልክ ነው የእግዚአብሔር ሰው...."፣ እያላችሁ ጮቤ ብትረግጡ፣ ያ የእውነተኛነት መለኪያው አይደለም።
ሟርተኛዋ የፊልጵስዩስዋ ገረድምኮ ጳውሎስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን በተመለከተ ስትናገር የነበረው ጉዳይ ምንም ሐሰት አልነበረበትም፣ " ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።" (ሐዋ 16፥ 16-18)። ምዋርተኛውን መንፈስና መንፈስ ቅዱስን የማይለዩ የዘመናችን "ታላላቅ" ሰዎች ይህቺን ሴት አግኝተዋት ቢሆን ኖሮ እርስዋንም ነብይ አድርጎ ለመቀባት የዘይት ብልቃጣቸውን ይዘው ይሄዱ ነበር። ምናልባት ይሄኔ የአንዱ አጥቢያ ነብይም ልትሆን ትችል ነበር። በልዩ መንፈስ አስራር ከስጋቸው እየወጡ "የብር ኩስኩስታቸው ሳይሰበር" በመንፈስ ጉዞ ይህንን ነባራዊ አለምና የስጋቸውን እውነታ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ትተው ወደ ሌላ "መንፈሳዊ" ወይም "ምናባዊ" አለም በመሻገር የተለየ የቅዠት አለም ውስጥ ገብተው የሚመላለሱ የተለየ መንፈሳዊ ልምምድ ያላቸው ያልዳኑ ሰዎች ይህንንው ትንግርታዊ አስማታቸውን በየመድረኮቻችን ላይ ለመተወን ምንም የሚከለክላቸው ነገር እንደሌለ አረጋግጫለሁ። ምክንያቱም ስር የሰደደ የመሰረታዊ የክርስትና ትምህርት ንቀት እንደ ወረርሽኝ ተዛመቶአልና።
"በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ። አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ። አምላክህ እግዚአብሔር ትሄድባት ዘንድ ካዘዘህ መንገድ ሊያወጣህ፥ ከግብፅ ምድር ካወጣችሁ ከባርነትም ቤት ካዳናችሁ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሮአልና ያ ነቢይ ወይም ያ ሕልም አላሚ ይገደል፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ አርቅ።" (በዘዳ 13፥ 1-5) በሕይወት ንጽህናውና በነገረ መለኮቱ አስተምህሮው ወድቆ ምልክቱና ተአምራቱ የሚፈጸምለት "ነብይ" መሆን በራሱ የእውነተኛነት ማስረጃ አይሆንም። እንዲህ ያሉ ነብያት ነን ባዮች አማልክት ያበዛሉ፤ ገንዘብ አምላካቸው፣ ዝናና ታዋቂነት ጣዖታቸው፣ ስምና ክብር መስገጃቸው፣ የሆነላቸው ናቸው። አማኞችን የሚያሰጋ የጣዖት አምልኮ ፈተና የለም እንደማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ (1ኛ ዮሐ 5፥ 21)። እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን አሳሳች ነብያት ለምን ያስነሳል? እንዴትስ ተጽእኖ ፈጣሪ ይሆናሉ? መልሱን ከጥቅሱ እናገኛለን፤ "አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና"፣ ይላል። እግዚአብሔር ሁልጊዜ ለእራሱና ለቃሉ ያለንን ፍቅርና ታማኝነት ይመዝናል፣ ይፈትናልም። ጸጋውንም የሚሰጠው በእውነት ለእርሱና ለእርሱው ብቻ የማይጠፋና የማይለወጥ ፍቅር ላላቸው ሰዎች ነው (ኤፌ 6፥24)። እንደ ንጽህት ድንግል የታጨንለትን አንዱን የእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ከሚያከብር ንጹህ ትምህርት ውጭ ለመንፈሳዊ ሕይወት የሚረባን ሌላ ምንም ነገር የለም(2ቆሮ 11፥3)።
እስቲ ይህንን ደግሞ ተመልከቱ፣ "በልብህም፦ እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው።" (በዘዳ 18፥ 21-22) አቤት ሰንት ያልሆነና ያልመጣ ወደፊትም የማይሆንና የማያመጣ ነገር ነው በእግዚአብሔር ሰም ሲነገር የኖረው። በእግዚአብሔር ሰም እየተናገሩ ቃሉን የማያውቁ የዋሃንን የሚያስፈራሩ ቀላማጆች በአፋቸው ቃል መያዝና መጠየቅ አለባቸው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ "በድንበሩ ላይ ደም አይፈስም" ያለን ሰው ምድሪቱ ደም በደም ከሆነች በኋላም ያለጠያቂ ትንቢት መናገሩን በቀጠለበት ሁኔታ የሌላውን ማረም እንዴት ነው የሚቻለው?
እስራኤል ሲጨንቃቸው እግዚአብሔርን ፍለጋ ብቻ ሳይሆን ሟርተኛም ፍለጋ ይሄዱ እንደነበር አይነተኛ ማሳያ ሊሆን የሚችል ሰው ንጉሱ ሳዖል ነው (1ሳሙ 28፥ 1-25 ተመልከት)። ይህም እግዚአብሔር ዝም ሲል በእምነትና በተስፋ ቃሉ ጸንቶ ፊቱን መፈለግና ደጅ መጥናት ሰው ሲያቅተው በገዛ ራሱ ምኞት እየተሳበ የሚገባበት ወጥመድ ነው፤ "የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ስትወልድበት ገደል ይገባል" እንዲሉ የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት በጭንቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔም መዘዙ ለዚህ ይዳርጋል፣ ያለ ብርሃን ያስቀራል።
ሰዎች ሃሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር ራሱ የስህተትን አሰራር እንደሚልክባቸውኮ ቃሉ ያስተምራል። እግዚአብሔር ለምን ይህንን በሰዎች ላይ ያውም በገዛ ህዝቡ ላይ ያደርጋል? ለሚሉ ጠያቂዎቼ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መልሴ የሚያድነውና የእውነት እውቀት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በአይናቸው ፊት ሲቀልባቸውና እግዚአብሔርና ቃሉ እንደማይበቃቸው ሁሉ ሰዎች ሌላ ተጨማሪ "ብርሃን" ሲፈልጉ እግዚአብሔር በሉአላዊ ፍርዱ ይህንን ያደርጋል። ተንኮል የሌለበትን የቃሉን ወተት መናፈቅ ትተው ከመነሻቸው ለመሳትና ለመውደቅ በሚሆን ዝግጅት ያሉና እንዲህ ባለ የወደቀ የሰው ፍላጎት ምኞታቸውን የሚከተሉ ሁሉ ሃሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በፍርዱ ምኞታቸውን እየሰጣቸው፣ የወደዱትን ሳይከለክላቸው፣ በአፍንጫቸው እስኪወጣና እስኪሰለቻቸው ድረስ ሃሰትን እየተጋቱ ይኖሩ ዘንድ ለስህተት አሰራር ይተዋቸዋል።
በዚህ ሰሞን በአስተምህሮ ዝንፈቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶች እና በሞራል ውድቀቶች ላይ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ይፋ ያደረገውን የአቋም መግለጫ እኔም ተመልክቼዋለሁ። ይበል የሚያሰኝ አንድ እርምጃ ነው። ዳሩ ግን ዘመነኛው ነቀርሳ ተግባራዊ አቋም በመውሰድ እንጂ በአቋም መግለጫ ብቻ የሚፈወስ እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። የማይድነውን ካንሰር መቁረጥና መጣል ይጠይቃል። እኛም እንደ ወንጌላውያን አብያተ ከርስቲያናት ሕብረት የአስተምህሮና የልምምድ ድንበራችንን፣ አባቶችም ያኖሩልንን የወሰን ምልክት ዘለን ከአጉል እንግዳ ትምህርትና ልምምድ ጋር የተሞዳመድንበትን በኪሳራ የተሞላውን የቀደመው ዘመናችንን በንስሃ ለማደስና፣ መለየት ካለብን ቆርጠን መለየት፣ ከመካከላችንም ልናወጣው የሚገባንን ለይተን ልናወጣው የግድ ነው። አለዚያ የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ጨዋታ ይሆንብናል። ይህን ሳነሳ በአንድ ወቅት አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን አስታውሳለሁ። የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በእምነት እንቅስቃሴና በሃሰተኛ አስተምህሮዎች ላይ አውደ ጥናት አዘጋጅቶ የየቤተ እምነቱን መሪዎች ሳር ቤት በሚገኘው ETC ሰብስቦ ያወያይ ነበር። ይህ ወዳጄ በዝግጅቱ ላይ ጽሁፍ እንዲያቀርብ ከተጋበዙት አገልጋዮች አንዱ ነበር። እና አውደ ጥናቱን በንግግርና በጸሎት የከፈቱት የወቅቱ የህብረቱ አመራር (ስማቸውን ዘልዬዋለሁ) ከመክፈቻ ንግግሩ በኋላ ተሰብሳቢውን አበረታተውና ከዚህ አውደ ጥናት አንዳች ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ፍሬ እንደሚገኝ ያላቸውን ተስፋ ተናግረው እሳቸው ግን በሌላ ተደራቢ ዝግጅት ምክንያት እዚያ እንደማይቆዩ ከገለጹ በኋላ ተሰናብተው ወጡ። ምክንያቱም ናዝሬት ላይ ደግሞ ከምእራቡ አለም በራሱ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ሕብረት ግብዣ ተደርጎላት የጀማ ስብከተ ወንጌል ልታደርግ የመጣች ማርሊን ሄይኪ የተባለች የእምነት እንቅስቃሴ አስተምህሮ አራማጅ ነበረች። እኝህ መሪ እዚያም ተገኝተው የተዘጋጀውን ፕሮግራም በንግግርና በጸሎት መክፈት ነበረባቸው። ሳስበው ሳስበው ሕብረቱ ራሱ የሁለት አለም... ይመስለኛል። አሁን ሁለት አይነት መሆናችን ለራሳችንም፣ በአገልግሎት እረኝነታችን ስራ ላለው መንጋም ሆነ በውጭ ላሉት ሁሉ ግልጽ እየሆነ መምጣት አለበት። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ወደንም ሆነ ተታለን በየአብያተ ክርስቲያኖቻችን እንዲገባና ከትምህርታችንና ከልምምዶቻችን ጋር ራሱን እንዲቀይጥ እድል በሰጠነው በገለሞተ ወንጌል፣ በእንግዳ ትምህርትና ልምምድ ላይ ጨከን ማለት አለብን።
በእግረ መንገዴ ግን ትክት ያለኝንና ያደከመኝ ነገር ጠቅሼ ልጨረስ። በግለሰቦችና በልምምዳቸው ላይ ተመስርቶ አስተያየት መቀበልና መስጠት የሚገባኝ እንደሆነና በዚያ ደረጃ ወርዶ መነጋገርም አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም። እንዲህ ያለው ነገር ምንም የሚያንጽ ጸጋ የለበትም፣ እንዲያው ጉንጭ አልፋ የህጻናት ክርክር ብቻ ነው የሚሆነው። መቼ ነው በስለን ጥበብን የምንነጋገረው? በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመስርተን እውነትን ስንናገርና በአሳሳች መናፍስት አሰራር፣ በተታለሉና በሚያታልሉ ኃሰተኛ ሐዋርያትና ነብያት የንዋይና የዝና ፍቅር የመወሰድ አደጋ እንዳለ በቃሉ የተሰጠንን ብርቱ ማስጠንቀቂያ አበክረን ስንናገር፣ በዘመናችን ነብይና ሐዋርያ በሚል ስምና ማእረግ የተንቆለጳጰሱትን "እነ እከሌን" እየጠቀሱ፣ "ነብይ እከሌን እንዴት ታየዋለህ?" "ሐዋርያው ማንትስንስ አትቀበለውም?" ወዘተ እያነሱ፣ ለምን አገልግሎታቸውን እንድንዳኝላቸው ሰዎች እንደሚፈልጉ በጭራሽ አይገባኝም። "የእግዚአብሔር ቃል እንደዚህ አይልም"፣ "የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል" ማለትና መባል ብቻውንኮ ሙሉ መልስና "ከተጻፈው አትለፍ" ሲሉ አባቶች ያሰመሩልን ድንበር ነው። ወደ ቃሉ ሳይሆን ወደ ሰዎችና ወደ አገልግሎታቸው የምንመለከተውስ እከሌ የሚባል ዝነኛ ሰው በዝናው የሚማርከን ደካማ ስለሆንን አይደለምን? በእውነት ልትወግሩን ካልሆነ በቀር በእኛ የእምነት ክህደት ቃል ላትድኑ የዝነኛ ከዋክብቶቻችሁን የእውነተኛነትና የሃሰተኝነት ምስክርነት ከእኛ መስማት ለምን ትፈልጋላችሁ? የማንንስ ሰው አገልግሎት ቢሆን ቃሉ ከመዘነው አይበቃም እንዴ? ቅዱስ ቃሉን ወግነንና ከአጠቃላዩ የቃሉ ብርሃን ተነስተን እንናገራለን እንጂ "እከሌ የእግዚአብሔር ሰው እከሌ ደግሞ የአመጽ ሰው" ብለን ጥቁሩንና ነጩን እንድንነግራችሁ አትጠብቁ። እስቲ ዝናቸውንና ቁጥራቸውን ያከማቹትንም የጉባኤና የገንዘብ መጠን ሳይሆን አይናችሁን ሳትጨፍኑ ትምህርታቸውን፣ ፍሬአቸውን፣ የህይወት ምስክርነታቸውንና ባህርያቸውን ተመልከቱ፣ ማን ምን እንደሆነኮ ለማወቅ የቃሉ ሚዛን እንጂ እንደ እነርሱ "ነብይ" ወይም ወልይ መሆን አያስፈልግም። እኔ እንደሚገባኝ የዘመኑ "ቴሌ ወንጌላውያን" የሚደሰኩሩትን የስብከታቸውን ይዘት ጌታ ኢየሱስም ሰብኮት ቢሆን ኖሮ አይሁድ ያነግሱት ነበር እንጂ በመስቀል ላይ አይገድሉትም ነበር እላለሁ። ስብከታችሁና ትምህርታችሁ የማያሰቅላችሁ አይነት ከሆነ አልቆላችኋል።
Thursday, March 29, 2018
መሻታቸውን በፍርድ ተቀበሉ።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment