Monday, February 19, 2018

ራእይ የተጻፈበት ጊዜ

የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበት ዘመን እና ታሪካዊ ዳራው
ማንኛውንም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ለመረዳት፣ መጽሐፉ የተፃፈበትን ጊዜ እንዲሁም ታሪካዊ ሁኔታውን እና ባህላዊ አውዱን ማወቅ የመጀመሪያ መሰረት ነው፡፡ የራዕይን መጽሐፍ ለመረዳተም ይኸው መንገድ አብይ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ የራዕይ መጽሀፍ የተፃፈላቸው የመጀመሪያዎቹ ተቀባዮች በስደትና በመከራ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ የተጻፈላቸውም ለእምነታቸው ሲሉ እስከ ሞት ድረስ መከራ ሊቀበሉ ጥሪ ያላቸውን ሊያበረታታቸው፣ በዚያው ልክ ብድራታቸው እየቀረበ መሆኑን እና የነዚያ የሚያሳድዷቸው ሰዎች ጥፋትና ፍርድም በጣም በእርግጠኝነት ቅርብ መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን ሊያመለክታቸው ነው፡፡
እንደ ዮሐንስ ራእይ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻህፍት የተጻፉበትን ጊዜያት በተመለከተ ጥያቄው ሲነሳ፣ ማንም የቃሉ ተማሪ ሊያውቃቸውና ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ሁለት ጉዳዮች አሉ። እነርሱም፦ "ውጫዊ" እና "ውስጣዊ" የተባሉ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ቃሉ እንደሚያመለክተው ውጫዊ ማስረጃ የምንላቸው ከራሱ ከመጽሐፉ ውጭ ያሉ ታሪካዊ ጽሑፎችን ሲሆን ይኸውም፦ የጥንታዊ ጸሐፊያን ምስክርነት፣ ትምህርቶቻቸው፣ በቃልና በጽሁፍ የተላለፉና ሊቀርቡ የሚችሉ ጥቅሶቻቸው፣ ወይም ከሌሎች ጸሐፊያን የሚለዩበት አመለካከቶቻቸው፣ አና የመሳሰሉትን የሚመለከት ነው፡፡     
ያም ሆኖ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ጊዜ ያመለክታል በሚል በሊቃውንቱ ዘንድ ለመሞገቻነት የሚቀርበው ኢራንዮሳዊው ብቸኛው ውጫዊ ማስረጃ በኅይለኛው ሲያከራክር ኖሮአል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በርካታ ሊቃውንታዊ የሆኑ አመለካከቶች የቤተ ክርስቲያንን ትንቢታዊ አስተምህሮ በዓመታት ውስጥ ወዲያና ወዲህ ሲያዋዥቁ ኖረዋል፡፡
በርካታ ሊቃውንት በራዕይ መጽሐፍ የተገለጸው ታላቅ ጥፋት በሮም መንግስት ከተቀሰቀሱትና ከተቀነባበሩት በመንግስታዊ አዋጅ ከተከናወኑት ስደቶች አንዱን የሚመለከቱ መሆናቸውን ያምናሉ፡፡ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ የነበሩ ተብለው የሚጠቀሱ አስር ነገስታት ነበሩ፡፡ ከእነርሱም መካከል ሁለቱ ዮሐንስ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ይገዙ የነበሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ እነርሱም፡- ቄሳር ኔሮ ከ 54 -68 ዓ.ም ባለው ጊዜ የገዛ፣ እንዲሁም ዶሚኑስ ከ81-96 ዓ.ም ባለው ጊዜ የገዛው ናቸው፡፡
በርካታ የዘመኑ ሊቃውንት የዮሐንስ ራዕይ የተጻፈበት ዘመን ነው ብለው የሚቀበሉት የኋለኛውን ዘመን ይኸውም በ96 ዓ.ም ላይ የዶሚኖስን ዘመነ መንግስት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ብዙዎች የለም ቀድም ያለው የኔሮ ዘመነ መንግስት ጊዜ ነው ሲሉ ከ68 ዓ.ም በፊት ያለውን ጊዜ ጠቅሰው ይከራከራሉ፡፡ በርካታ ወንጌል አማኞች የሆኑ ኃላፋውያን (ፕሪቴሪስቶች) ራዕዩ የተጻፈው ቀደም ባለው ጊዜ ነው ብለው አቋም ይዘዋል፡፡ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ ብቻ ነው በ70 ዓ.ም ላይ የሆነውንና የተፈጸመውን የኢየሩስአሌምን ጥፋትና ውድቀት አስቀድሞ በትንቢት መናገር የሚቻለው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ይህም አቋም መጽሐፉ ያንን ክስተት አስቀድሞ የተነበየ መሆኑን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ የሆነ ሆኖ ቀደም ያለውን ጊዜ የሚቀበሉ (ማለትም ከ69 ዓ.ም በፊት ተጽፎአል የሚሉ) ሁሉ ኃላፋውያን (ፕሪቴሪስት) ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ሆኖም ራዕዩ የተጻፈበትን ትክክለኛ ጊዜ መወሰን መጽሐፉን በአግባቡ ለመረዳት መሰረታዊ ነገር ነው ሲሉ ሊቃውንቱ ይከራከራሉ፡፡ ሁለቱም ጊዜያቶች ላይ የሚታይ መሳጭ የሆነ ክርክርና ሙግት ግን እስከ አሁን ድረስ እንደቀጠለ አለ፡፡
ኬኔት ኤል ጀንትሬይ ጄ. አር የተባሉ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሥነ መለኮት ምሁር ይህንን ክርክር አስመልክቶ በዶክትሬት ጥናታዊ የምርምር ስራቸው ውስጥ በስፋት በዳሰሱት በዘገባቸው እንዲህ ይጽፋሉ፡- "....በእጅጉ ወግ አጥባቂ የነበሩ ወገኖችን እስከ ተመለከተ ድረስ በ1800 አካባቢ ለአዲስ ኪዳን ቀኖና መጠናቀቅ ይሰጥ የነበረው የጊዜ ማእቀፍ በ50 ዓ.ም እና በ100 ዓ.ም መካከል ያለውን ጊዜ ይሸፍን ነበር፡፡ በ1850 ከቱቢንገን የፍልስፍና ትምህርት እና ከኤፍ ሲ  ባወር ተጽዕኖ የተነሳ ጊዜው ሰፋ ተደርጎ ከ50 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 160 ዓ.ም ድረስ ይሸፍናል የሚል ሃሳብ ተሰራጨ፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ጊዜ በተመለከተ በቱቢንገን በተደረገው የአመለካከት ለውጥ ላይ፣ 'በቱቢንገን ፍልስፍና ውስጥ ሊታሰብ የማይችል፣  እርስ በርሱ የሚጋጭ ትምህርት፣  ጳውሎስን ከአራት መልዕክቶች ጋር ብቻ ያስቀረ፣ ወይም እጅግ ዘመናዊ በሆነ አስተሳሰብ በአዶልፍ ሂልገንፊልድ እንደተፃፈው፣ ጳውሎስን ከሰባት መልፅክቶች ጋር ብቻ በማስቀረት፣ በርካታ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎችን ደግሞ የተጻፉበትን ዘመን ወደ ኋላ ላይ እንዲመጡ ያደረገ የአቡቀምሲሱንም መጽሐፍ በተመለከተም የመጽሐፉን ሐዋርያዊ ሥልጣን በማረጋገጥ የተፃፈበትን ጊዜ በተለምዶ ይታመን ከነበረው ይልቅ የክፍለ ዘመኑን ቀዳሚ ሩብ ይጠቅስ ነበር'" ይላሉ፡፡
   
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ያሉ በርካታ የስነ መለኮት ሊቃውንት ምድቦች የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከ 70 ዓ.ም በኋላ የተፃፈ ነው ብለው ቢያምኑም እንኳ፣ ጀንትሬይ ግን በርካታ የስነ መለኮት ሊቃውንት ከ 70 ዓ.ም በፊት ተጽፎአል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ደግሞ በዝርዝር ያስታውቃሉ፡፡ በዝርዝሩ ከተከታተት መካከል ግሬግ ኤል ባህንስን፣ አዳም ክላርክ፣ ኤፍ ደብልዩ ፌረር፣ ጆን ኤ.ቲ ሮቢንሰን፣ ሄንሪ ባርክሌይ ስዊት፣ ሚልተን ኤስ ቴሪ፣ ዊልሄልም ቦውሰት፣ ኤፍ ኤፍ ብሩስ፣ ሩዶልፍ ቡልትማን፣ ሳሙኤል ዴቪድሰን፣ አልፍሬድ ደድርሼይም፣ ጆሃን ኢክሆርን፣ ጆሴፍ ኤ. ፊትዘርሜየር፣ ጂ፡ቢ ላይትፉት፣ ሲ. ኤ.ኤፍ.ዲ ሞውል፣ እና አውግስጦስ ኤች ስትሮንግ የተባሉት ሊቃውንት ሰምቻቸው ከተጠቀሱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጄንትሬይ በጠቅላላ 138 ሊቃውንትን ዋቢ አድርገው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ከ70 ዓ.ም በፊት መጻፉን የሚያምኑና የሚቀበሉ ምሁራን ያሉ መሆናቸውን በጥናታቸው ይጠቅሳሉ፡፡
   
ስለዚህ ዝርዝር ሁለት ነገሮችን ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ፣ ዝርዝሩ ከየትኛውም የስነ መለኮት ጎራ የሚመደቡ ሊቃውንትን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ዝርዝሩ ብቻውን በራሱ የራዕይ መፅሐፍ ቀደም ያለው ጊዜ ላይ እንደተፃፈ አያረጋግጥም፣ ሰዎችን በመቁጠር ላይ የተመሰረተ አመለካከት ብቻ መሆን ያለበትምና፡፡ ዝርዝሩ የሚያስታውቀው አንድ ነገር ግን አለ፣ ይኸውም "የራዕይ መጽሐፍ ቀደም ባለው ጊዜ ነው የተፃፈው" የሚለው አመለካከት ያለ ጥርጥር እንግዳ ወይም አዲስ አመለካከት አለመሆኑን ነው። እዚህ ላይ ስለ ኬኔት ኤል ጀንትሬይ ጄ. አር መጽሐፍ ተጽዕኖ ምሁራኑ የሰጡትን አስተያየት ጠቀስ አድርጌ ወደ ዋናው ክርክር ልለፍ።
(ጄይ ኢ. አዳምስ ስለዚህ መጽሐፍ "አንዳንዶቻችን ለዓመታት ስንጠብቀው የነበረ መጽሐፍ ይህ ነው! አሁን እዚህ አለ ልናጣጥመው እንችላለን፡፡ ሚስተር ጀንትሬይ ማንም ካደረገው በላይ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈው በ70 ዓ.ም ከሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት በፊት ቀደም ብሎ እንደተፃፈ እውነታውን አሳማኝ በሆነ መልኩ አቅርቦልናል፡፡ ብዙዎች ሊያነቡት የሚባ ደግሞም በርካታ እይታዎችን ሊሰጠን የሚችል መጽሐፍ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በነገረ ፍጻሜ አመለካከታቸው ኃላፋዊ ያልሆኑ ጆርጅ ደብልዩ ናይት የተባሉም ሰው "ይህ የጀንትሬይ መጽሐፍ የራዕይ መጽሐፍ ቀደም ሲል እንደተፃፈ ባለው ጉዳይ ላይ ጥልቅና የሚደነቅ አገላለጽ አለው፡፡ መጽሐፉ ማስረጃዎቹን በመጽሐፉ ማለትም በራሱ በራእይ ውስጥ፣ እንዲሁም በጥንት ቤተክርስቲያን  ምንጮች ውስጥ፣ እያደረገ፣ ደግሞም የዚህን ዘመን እና ቀደም ያሉ ዘመናት የአዲስ ኪዳን ሊቃውንት የሆኑ ሙግቶችን እያቀረበና እየተነተነ ጥያቄውን ለመፍታት አንድም ድንጋይ ሳያስቀር መጽሐፉ የተጻፈበትን ትክክለኛ ጊዜ ያመለክታል፡፡" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  የበዛውን ዘመናቸውን የአልቦ ሺህ አመት አገዛዝ አስተምህሮን ሲከተሉና ከፊል ኃላፋዊ ሆነው የኖሩት፣ "The Las days according to Jesus" መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት፣ ከጥቂት አመታት በፊት በሞት የተለዩን አር. ሲ ሰፕሮውል የተባሉ ሊቅ ስለ ጄንትሬይ መጽሐፍ አስተያታቸውን ሲሰጡ፡- "እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ስራ" ይሉና "መጽሐፉ የተጻፈው ከ70 ዓ/ም በፊት ቀደም ባሉት ጊዜያት በቄሳር ኔሮ ዘመን ኢየሩሳሌም ሳትደመሰስ እና መቅደስዋ ገና ቆሞ እያለ ነው የሚለው የጄንትሬይ ሙግት ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ፣ እንግዲያውስ የራዕይ መጽሐፍ የተጻፈበትን ጊዜ በተመለከተ የሚደረስበት ድምዳሜ የመጽሐፉን ይዘት እና ትኩረቱን ለመረዳትና ለመተርጎም ባለን ዝግጅትና ጥረት ላይ ሰፊ የሆነ የክለሳ ሥራ መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉ ያክላሉ፡፡)
አሁን ወደአውራው ክርክር ባጭሩ ልለፍና ላጠቃልል
1.በኔሮ ዘመን በነበረው ስደት ጊዜ ተጽፏልን?
ይህንን ሃሳብ ለመደገፍ የተለያዩ ውስጣዊ ማስረጃዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነርሱም መካከል፦
፩. በርካታ “ቶሎ” እና “ቀርቦአል” የሚሉት ጊዜን አመልካች የሆኑ ቃላት በምንባባቱ (1÷ 1፤ 2÷ 16፤ 3÷ 11፤ 22÷ 6-20) ውስጥ ትርጉም ሊሰጡን የሚችሉት ሁነቶቹ በራእይ መጽሐፍ ከተገለጹት ምልክቶችና ምስሎች ጋር ተጋጥመው ፍጻሜያቸው ወደ ፊት ሊሆን ላለው ፍርድና ብድራት በጣም ሩቅ ያልሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ 
፪. ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ ቤተ መቅደሱ በኢየሩሳሌም ታይቷል፣ ተለክቷልም (11÷ 1-2)፡፡ ያኔ ገና አልፈረሰም ነበር ማለት ነው። ይኸውም ከ70 ዓ.ም በፊት መሆኑ ነው፡፡  ራዕዩ ከመጻፉ በፊት ቀደም ብሎ ቤተ መቅደሱ ፈርሶ ቢሆን ኖሮ ግን ያንን የሚገልጥ አንድ ሃሳብ በመጽሐፉ አንድ ቦታ ላይ መኖር ነበረበት፡፡ ከዚህም በላይ የፈራረሰ፣ ያበቃለትንና የሌለ ቤተ መቅደስ በራእይ መለካት ፈጽሞ ትርጉም የሌለው ጉዳይ ነው።
፫. በእስያ 7 አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የነበረበት ጊዜ በ60ዎቹ መጀመርያ ላይ ነበር፡፡ ራእዩ በ96 ዓ.ም ላይ ተጽፎ ቢሆን ኖሮ በዚያን ጊዜ በአካባቢው የነበሩት አብያተ ከርስቲያናት ከ7 በላይ ስለነበሩ የሁሉንም ዝርዝር በጠቀሰ ነበር።
፬. ራዕይ 2÷ 2 ሌሎች ሐዋርያት እንደነበሩ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ከዮሐንስ በቀር ሁሉም ከ70 ዓ.ም በፊት እንደሞቱ ይታመናል፡፡
፭. ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ አይሁዳዊ ከሆነው ተቃርኖ ጋር የነበረው ውጥረት ገና እንዳለ ነበር (ለምሳሌ 2÷ 9 ፤3÷ 9)፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ የተለወጠው ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም በሮማውያን ስትደመሰስ በመሆኑና ከ70 ዓ.ም በኋላ ይህ የማይታሰብ በመሆኑ ይሁዲነትና ሐይማኖታዊ መሰረቱ ከአቅመ ክርክር ውጭ ሆኖአል፡፡ ይሁዲነት ሕልውናው ቤተ መቅደሱ ቆሞ እስካለና የመስዋእት ስርአቱ እሰከተካሄደ ድረስ ብቻ ነበር። የአይሁዳዊነት ርዕሰ ጉዳይና ሌጋሲ ከ70 ዓ.ም በኋላ ምንም ትርጉም የለውም፣ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ የቀረ ምንም የአይሁድ ዘርም ሆነ ሐይማኖታዊ አገዛዝ የለም፡፡ የራእይ መጽሐፍ በ96 ዓ.ም ላይ ተጽፎአል የሚለው የሊቃውንቱ ድምድዳሜ ግን የመጽሐፉን ውበት ያጠፋዋል። ጥንታዊው የራዕይ መጽሐፍ ቅጅ ግን "ራዕዩ የተጻፈው ኔሮ ቄሳር በነበረበት ዘመን (ማለትም ከ68 ዓ.ም በፊት) ነው" ይላል፡፡
፯. ሌላው አስፈላጊ መከራከሪያ በራዕይ 17÷10 ላይ ራዕዩ በተጻፈበት ጊዜ ይገዛ ስለነበረው ንጉስ የሚናገረው ነው፡፡ “ሰባት ነገስታት…አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ የቀረውም ገና አልመጣም ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል::" የዚህ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ራዕዩ ከመጻፉ በፊት አምስት የሮም መንግስታት በተፈራራቁነት እንደነበሩ እና እንደወደቁ ፣ ስድስተኛው ድግሞ ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ ይገዛ የነበረ ንጉስ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ በሮም ግዛት ኔሮ ስድስተኛ ንጉስ ሆኖ የገዛ በመሆኑ ራእዩ የተጻፈው በዚያው በኔሮ ዘመነ መንግስት ውስጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡
፰. ሌላው ማረጋገጫ ኔሮ የተሰኘው ስያሜ 666 ከተሰኘውና በራእይ 13 ከተጠቀሰው የአውሬው ቁጥር ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በዚያን ዘመን የፊደል ገበታ (Alphabetical Symbols) ቁጥርን ወክለው ያገለግሉ እንደነበር የታወቃል። ጽኑ ሥደትና መከራ በነበረበት በዚያ ክፉ ዘመን ዮሐንስና ጠቅላላው ቤተ ክርስቲያን ያለ ጊዜው ራሳቸውንና ሌሎችን ለአደጋ ላለማጋለጥ በዋናነት ምልክቶችን  ለመግባቢያነት የመጠቀም ልምምድ ነበራቸው። በዚህ መሰረት  "ቄሳር ኔሮ" የሚለው ስያሜ በግሪኩ የፊደል ገበታ ቅደም ተከተል በሚሰጠው ቁጥር የሂሳብ ቀመር 666 የተሰኘውን ቁጥር በምልክትነት ያመጣል፣ ይኸውም፡-

      N = 50                 q = 100
      R = 200                o = 60
      W = 6   ደግሞም   r = 200
      N = 50  
           =306                    =360
(ስለዚህ 306 + 360= 666 እንደ ማለት ነው)፡፡

፱. በተጨማሪም የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያንን ዝምታ ዋቢ የሚያደርጉ አጥኝዎች የሚሰጡት አስገራሚና አወዛጋቢ ምክንያት "ቅዱሳን ተነጥቀው ሰለነበር ያንን ሁነትና ታሪክ ዘግቦ ለማስቀረት የቻለ ማንም አልነበረም" የሚል ነው። (ይህ "የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አካላዊ ንጥቀት" ርዕሰ ጉዳይ ግን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በወጉ ጥናት ሊደርግበት ይገባል፤ ምናልባት እንድተባለው ክርስቲያኖች ያኔ ተነጥቀው ከምድር ላይ መወሰዳቸው እውነት ከሆነ የአመለካከት ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት አለኝ።)
2. በዶሚኑስ ዘመን ተጽፎአልን?
ለዚህም የሚቀርቡ ውጫዊ ማስረጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
፩. ነገስታትን ማምለክ /ለነገስታት መስገድና ማጠን/ በምዕራፍ 13 ያለው አይነት ስግደት ማለት ነው፣ እስከ ደሚኑስ ዘመነ መንግስት ድረስ በግድ አልተጫነም የሚለው ነው፡፡
፪. በራዕይ 13 የተፈወሰውም ለሞት የሆነው ቁስል በኔሮ ዘመን ታውጆ የነበረው የክርስቲያኖች ስደት በደሚኑስ ዘመን በባሰ መንገድ በመቀጣጠሉ ምክንያት ዶሚኑስ ሁለተኛው ኔሮ እየተባለ በመጠራቱና ዮሐንስን እና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁሉ ከቀድሞ በባሰ መንገድ ያሳደደ በመሆኑ ነው፡፡
፫. ሌላው መከራከሪያ የኔሮ ዘመን ስደት ከሮም ከተማ ያልዘለለ መሆኑ እና በደሚኑስ ዘመን የሆነው ሰደት ግን መላውን የሮምን ግዛቶች ያጥለቀለቀ መሆኑ ነው፡፡ ከሮም ከተማ ርቀው ይገኙ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ቱርክ ያሉት የኔሮን ሰደት ሳይሆን የሚያውቁትና የተለማመዱት የዶሚኑስን ሰደት ነው ብለው ያስባሉ፡፡
፬. በራዕይ 2 እና 3 የተጠቀሱት ሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት በአካባቢያቸው ከነበሩት ተቃዋሚዎች የሚደርስባቸው ስደት እንዳለ እንጂ ደብዳቤው በተጻፈላቸው ጊዜ ከገዢ ይቀበሉት የነበረ መከራ እንዳለ አልተገለጸም በማለት በኋላኛው ጊዜ ተጻፈ የሚለውን ይደግፋሉ፡፡
፭. የኋለኛው ዘመን ላይ እንደተጻፈ የሚቀርብ ውጫዊ ማስረጃ ጠንካራው መከራከሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያለ ምስክርነት ሆኖ የሚቀርበው እና በርካታ የቤተክርስቲያን አበው ዩሐንስ ራዕዩን በጻፈበት ጊዜ ዶሚኑስ ንጉሰ ነገስት ነበር የሚሉት በኢራኒዮስ ምስክርነት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ኢራኒዮስ “ኑፋቄን በመቃወም” በተሰኘው መጽሐፉ እንዲህ የሚል ቃል አስፍሯል፡-
“እንግዲህ ይህ እንደዚህ ከሆነ፣ ይህም ቁጥር (666) በሁሉም መልካም የጥንት ቅጂዎች ውስጥ የሚገኝ ከሆነ፣ ዮሐንስንም ፊት ለፊት ያዩት ሰዎች ከመሰከሩ፣ እንዲሁም የአውሬው ስም ቁጥርም በግሪኩ የፊደል ገበታ ቀደም ተከተል መሰረት እንደሆነ አመክንዮ ካስተማረን፣ እንግዲያውስ የክርስቶስ ተቃዋሚ የተሰኘውን ስም በአወንታዊ መልኩ የመጥቀስን ኃላፊነት አንወስድም፤ ስሙም በዚህ በአሁኑ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ መገለጥ ያለበት መሆኑ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ፣ የአቡቀለምሲሱን ራዕይ ባስተላለፈልን በእርሱ በራሱ በተነገረን፡፡ የታየውም በእኛው ዘመን በደሚኖስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ ነው እንጂ፣ ከታየ በጣም ረጅም ጊዜ አላስቆጠረምና ነው፡፡”
ይህ የኢራኒዩስ አባባልግን በትርጉሙ ሲያከራክር ኖሯል፡፡ በዶሚኖስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ ምን ነበር የታየው? ዮሐንስ ያስተላለፈው ራዕይ? ወይስ በነዚያ በመሰከሩ ሰዎች ፊት ለፊት ታይቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ራሱ? “የታየው” (ታይቶ የነበረው) የሚለው ቃል/ ሐረግ ምን አልባት የመጀመሪያውን ትርጉም ‹ታይቶ የነበረው እርሱ› የሚለውን አነባበብ የለወጠ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ እንዲያውስ ሊያረጋግጥ የሚችለው ዮሐንስ አቡቀለምሲሱን ቀደም ብሎ ጽፎ፣ የኖረው ግን እስከ ዶሚኑስ ዘመነ መንግስት ድረስ ነው የሚለውን ያረጋግጣል፡፡
ኢራኒዮስ፣ ራዕዩ የተጻፈው በኋለኛው ዘመን ነው የሚል ከሆነ፣ እንግዲያውስ የእርሱ ምስክርነት ትኩረት የሚሰጠው እና ክብደት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ኢራኒዮስ ሐዋርያው ዮሐንስን በአካል የሚያውቀውን ፖሊካርፕን በአካል ያውቀዋልና በዚህ ምክንያት ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት የታሰረበትን ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በርካታ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ኢራኒዮስን ተከትለው ራዕዩ የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ ተመሳሳይ የሆነን ጊዜ ያመለክታሉ፡፡
ነገር ግን ጥያቄው የኢራኒዮስ አባባል ትክክለኛ ትርጉም ይህ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡
የኢራኒዮስን አባባል ለመተርጎም በዶሚኖስ ዘመነ መንግስት የታየው ዮሐንስ ራሱ እንጂ ራዕዩ አይደለም በማለት ከፍ ሲል ዋቢ ያደረግኋቸው   የኃላፊያኑ አመለካከት ሊቂ ዶክተር ኬኔት ጄንትሬ   አንዳንዱ ቋንቋዊ፣ አንዳንዱ አውዳዊ፣ አንዳንዱ ደግሞ አመክኒዮአዊ የሆኑ ሰባት ጠንካራ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡
ለምሳሌ፡- ከኢራኒዮስ በተወሰደው ጽሁፍ የመጀመሪያው መስመር ላይ የራዕይ መጽሐፍ “በሁሉም… የጥንት ቅጂዎች” ሲል ይጠቅሳል፡፡ ይህም የሚያሳየው ይህ አረፍተ ነገር ከመጻፉ በፊት አስቀድሞ መጽሐፉ ለረጅም ጊዜ በዚያው ዘመን አካባቢ ነበር እንደ ማለት ነው፡፡ “የጥንት ቅጂዎች” ከነበሩ የመጀመሪያው ታዲያ የበለጠ ጥንታዊ አይሆንምን? ሆኖም በኢራኒዮስ ግምት የዶሚኑስ መንግስት ዘመን በጣም የጥንት ታሪክ ነው ተብሎ አይወሰድም፣ ምክንያቱም ስለ ጊዜው ሲናገር “በእኛው ዘመን” ብሏልና፡፡ ኢራኒዮስ በእርሱ ዘመን እንደተጻፈ ስለሚናገርለት ስለ መጀመሪያው መጽሐፍ እንዴት ጥንታዊ ቅጂ ብሎ መናገር ይቻለዋል? የዶሚኑስን ዘመነ መንግስት በመጥቀሱ ኢራኒዮስ የተናገረለት ዘመን ዮሐንስ አቡቀለምሲሳዊውን ራዕይ ካየበት ጊዜ ይልቅ ዮሐንስ በወንድሞቹ የታየ የመጨረሻ መሆኑን ነው፡፡
ሌላው የኢራንዩስ ምስክርነት ችግር የጽሁፎቹ ተዓማኒነት ችግር እንደሆነ በሰፊው ይታወቃል፡፡ የራዕይ መጽሐፍ ስለተጻፈበት ትክክለኛ ጊዜ በግልጽ ምንም ያለው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ ኢራንዩስ ከጽሁፎቹ በአንዱ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ቆይታ ሲነግረን እንኳ አገልግሎቱ የተጠናቀቀው በግምት በሃምሳ አመታት ውስጥ ነው በማለት ኢየሱስ የኖረው 50 ዓመት ያህል እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዚህ ምክንያት ጀንተሬይ ሲያጠቃልሉ “ራዕይ የተጻፈው በኋለኛው ጊዜ ላይ ነው ብሎ ኢራንዩስን ዋቢ ማድረግም ሆነ፣ በወፍራም ድምጸት ጮክ ብሎ "ኢራንዩስ እንዲህ ይላል" ማለት ተዓማኒነት ይጎድለዋል” ይላሉ፡፡
በመጨረሻም መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜ በመወሰን ላይ ማጠቃለያ አድርጌ ላቀርብ የምወደው ታዋቂው የሥነ አፈታት ሊቅ ሚልተን ቴሪ የተናገሩትን በመጥቀስ ነው፡- “የዮሐንስ አቡቀለምሲስ የተጻፈበትን ትክክለኛ ወቅት መቼ እንደሆነ በሚሰነዘሩ የክርክር ሃሳቦች ላይ እና ታሪካዊ አቋሞች ላይ እርግጠኛ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ይህ የትንቢት መጽሐፍ ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት ቀደም ባለው ጊዜ የተጻፈ ከሆነ እንግዲያውስ በርካታ የሆኑ እነዚያ ከዚያች ከተማና ከውድቀትዋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እያንዳንዳቸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ ከትንቢቱ ፍጻሜ ጋር የተገናኙ መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን በርካቶቹ እንደሚያምኑት በዶሚኑስ ዘመን ማብቂያ ላይ (በ96 ዓ.ም አካባቢ) ተጽፎ ከሆነ፣ እነዚያን ታሪካዊ ሁነቶች ለመተርጎምና ለማብራራት ሌላ የትርጉም መንገድ መፈለግ የግድ ይሆናል፡፡”
እነዚህ እንግዲህ ሁሉም ተርጓምያን ራእይን ለመተርጎም ከመነሳታቸው በፊት በመጀመርያ ሊያውቁአቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። አለበለዚያ በትምህርታቸው ቤተ ክርስቲያንን በዝባዝንኬ ተረት ተረት ይሞሏታል።
ይህ ጽሁፍ አገርኛውን የሥነ ፍጻሜ ጥናት ደርዝ ለማስያዝ መለስተኛ መነሻ እንዲሆን ጸሎቴ ነው። ለበለጠ ንባብ የምጠቁመው ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን መጻህፍት ነው፦
Gentry, Kenneth L., "Before Jerusalem Fell, Dating the Book of Reveltion," 1989. 
"The beest of Revelation," 1989.
Terrry Milton S., "Biblical Apocalyptics, A Study of The Most Notable Revelation of God and of Christ," Baker Book House, 1988.
Chilton, David., "The Days Of Vengeance, An Exposition of the Boook Of Revelation," Dominion Press Ft.Worth, Texas, 1987.
Arthur S. Peake, "The Revelation of John", Hartley Lectures (London: Joseph Johnson, 1919

No comments:

Post a Comment