የሙታን ትንሣኤ ቀነ ቀጠሮ፦ (የቪድዮውን መልእክት መከታተል ላልቻሉ)
ዳንኤል 12 ለትንሳኤ ስለ ተቀጠረው ጊዜ ምን ያስተምረናል?
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ትንቢተ ዳንኤልንና ትንሳኤን በተመለከተ የተሰጠውን ጊዜ ቀጠሮ ትምህርቱን እናያለን። በርካታ ክርስቲያኖች ትንሳኤን የሚጠባበቁት ገና ወደ ፊት በፍጻሜ ቀን ይሆናል ሲሉ ነው፤ አር. ሲ. ስፕሮውል ሙሉ ኅላፋዊ ከመሆን የሚከለክልዎ ምንድን ነው? ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ፣ "ትንሳኤ" የሚል ነው። ለኝህ ታላቅ የስነ ምለኮት ምሁር በ70 ዓ.ም ላይ ትንሳኤ ሆኖአል የሚለው የኃላፋውያን አመለካከት አይዋጥላቸውም። በርካታ የኃላፋዊነትን አቋም የያዙ ምሁራን ግን ዳንኤል 12 ላይ ያለውን ምን ታደርገዋለህ ሲሉ ይጠይቁታል። ይህ ክፍል ለትንሳኤ ስለ ተቀጠረው ጊዜ ምን እንደሚነግረን እንመለከታለን።
በቅድሚያ ዘመኑ፦
"በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" ዳንኤል 12፥ 1
"በዚያን ዘመን" በቀጥታ ምእራፍ 12 ላይ ዘለን ስለገባን ቀደም ያሉትን ምእራፎች መለስ ብለን በጥንቃቄ ካላየን በቀር ስለ የትኛው ዘመን እየተናገረ እንደሆነ ምንም ፍንጭ አይኖረንም። ስለዚህ ጥቂት ወደኋላ ተመልሰን እንይ፦
"ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።" ዳንኤል 10፥14
ዳንኤል እዚህ ላይ "ለሕዝብህ" ተብለው ለተጠሩት (ለእስራኤል) በኋለኛው ዘመን ላይ የሚሆነውን በተመለከተ ራእይ ይሰጠዋል። ይህ ራእይ ስለ ወደፊቱ የተሰጠ ራእይ ነው፣ ይኸውም የእስራኤል የመጨረሻው ዘመን ነው።
" በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፤ የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል።" ዳንኤል 11፥40
በምእራፍ 12 ላይ "በዚያን ዘመን" የተባለው በምእራፍ 10፥ 14 ላይ "የኋለኛው ዘመን" የተባለው ነው፣ በምእራፍ 11 ላይ ደግሞ "የፍጻሜ ዘመን" ተብሏል። ስለዚህ ዳንኤል 12 የሚናገረው ስለ ኋለኛው ዘመን፣ ይኸውም የአሮጌው ኪዳን ስርአት ማብቂያን የሚያመለክት ነው።
ሚካኤል፦
"ታላቁ አለቃ ሚካኤል" -- ይህ "ታላቁ አለቃ" የተባለው "ሚካኤል" ማን ነው? ሚካኤል ማለት ብእብራይስጥ ቋንቋ ሚካየል ሲሆን የስሙ ትርገምም "እንደ እግዚአብሔር ያለው" ማለት ነው። ስለዚህ ሚካኤል እንደ እግዚአብሔር የሆነው ማለት ነው።
" የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።" ይሁዳ 9
ይሁዳ ሚካኤልን "የመላእክት አለቃ" ሲል ይጠራዋል። የመላእክት አለቃ ማለት "የመላእክት ዋና አዛዥ" (chief of angels) ከማለት በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም። ታዲያ እንደ እግዚአብሔር የሆነው የመላእክት ዋና አዛዥ ማን ነው? ይህ ዋና አዛዥ ኢየሱስ በሥጋ ከመምጣቱ ወይም "ቃል ሥጋ" ከመሆኑ በፊት ይገለጥ የነበረበት ሁናቴና መልክ እንደ ሆነ እንድናይ እፈልጋለሁ።
ይህ ምን ሃሳብ ይሰጣችኋል? ግር የሚል እንግዳ ሃሳብ ነውን? ወይስ በቅዱስት መጻህፍት ትምህርት የሚደገፍ ነው? አንዳንዶች ይህ በይሁዳ 9 ላይ ያለው "ጌታ ይገስጽህ" ባይ የመላእክት አለቃ የሚካኤል እንደዚያ በማለቱ ኢየሱስ ሊሆን አይችልም ሲሉ ይደመጣሉ። ኢየሱስ ራሱ ጌታ ነው፣ ታዲያ ለምን "ጌታ ይገስጽህ" ይላል? ሲሉ ይከራከራሉ። ይህ ግን ጥሩ አድርጎ ሊያከራክር የሚችል ጭብጥ ነውን? በትንቢተ ዘካርያስ ላይ የተጻፈውን እስክናይ ድረስ እንደዚያ ሊመስል ይችላል፦
"እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም ይከስሰው ዘንድ በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ሰይጣን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን? አለው።" ዘካ 3፥1-2
እዚህ ላይ እንደምንመለከተው እግዚአብሔር ሰይጣንን "እግዚአብሔር /ጌታ/ ይገስጽህ" ይለዋል። ይህም በይሁዳ መልእክት ላይ የምናየው ሃረግ ነው፣ እዚህ ላይ ግን በግልጽ የምናየው እግዚአብሔር መናገሩን ነው። እዚህም ላይ የእግዚአብሔርን መልአክ እናያለን። ሚካኤል የእግዚአብሔር መልአክ ነው፣ እርሱም እግዚአብሔር የሆነው ኢየሱስ ነው።
ይህንን የበለጠ ግልጽ የሚያደርግልንን ሌላ ክፍል እንመልከት፦
"ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤" 1ተሰ 4፥ 16
እዚህ ላይ ስለ ማን ነው የሚናገረው? ስለ ኢየሱስ ነው የሚናገረው። ኢየሱስ "በመላእክት አለቃ ድምጽ" እንደሚመጣ ነው የተነገረው። ይሁዳ በመልእክቱ ሚካኤል የመላእክት አለቃ መሆኑን ነግሮናል። ይህ ሚካኤል የተባለው የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሱስ በስጋ ከመገለጡ በፊት የነበረው መገለጥ ሲሆን እርሱም ኢየሱስ ነው ብዬ አስባለሁ።
" እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።" ዮሐ 5፥ 25-29
እነዚህን ከዚህ በላይ ያነሳኋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ብናነጻጽራቸው (1ተሰ 4፥ 16 እና ዮሐ 5፥ 25-29) ኢየሱስ በመላእክት አለቃ ድምጽ ሙታንን እንደሚያስነሳ እንደምንመለከት ሁሉ፣ በዮሐንስ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው የኢየሱስ ድምጽ ሙታንን ሲያስነሳ እንመለከታለን። ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ነውን? ለእኔ እንደ እርሱ ይመስለኛል። ይህም የክርስቶስን ክብር የሚገልጥ እንጂ የሚጋርድ አይሆንም።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልበል፣ የመጠበቂያ ግንብ አማኞች ሚካኤል ኢየሱስ ነው ብለው እንደሚያስተምሩ አውቃለሁ። ያ በራሱ ችግር አይኖረውም። ነገር ግን ኢየሱስን ፍጡር ነው እንጂ አምላክ አይደለም ሲሉ ደግሞ ያስተምራሉ። ትልቁ ስህተት እዚያ ላይ ነው። ኢየሱስ ፍጡር ነው ብዬ እንደማምን ለአፍታም እንኳ እንዳታስቡኝ። ወይንም ኢየሱስ በኋላ ላይ ቆየት ብሎ ከአምላክ ዝቅ ብሎ ወደ መለኮትነት ደረጃ ከፍ ያለ መልአክ ነው ብዬም እንደማስብ አትገምቱኝ። ፈጽሞ ያንን ልል አልችልም። ኢየሱስ እንደ አባቱ ያለ ፍጹም አምላክ ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሊቀ መላእክት ሚካኤል ኢየሱስ ነው ስል ኢየሱስ እግዚአብሔር አይደለም እያልሁ ግን አይደለም።
መልአክ የተሰኘው ቃል በቀጥታ "መልእክተኛ" ማለት ነው። "የመላእክት አለቃ" ወይም "ሊቀ መላእክት" ማለት ደግሞ ከመላእክት ሁሉ የሚበልጥ የመላእክት ዋና አዛዥ (chief of angels) ማለት ነው። በመጀመርያው ኪዳን በጣም ለበርካታ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሰዎች እየተላከ ይመጣ እንደነበር እናነባለን። እነዚህ ሁነቶች የተገለጡባቸውን የንባብ ክፍሎች ግን በደንብ ተጠግተን ስናነባቸውና ስናጠናቸው ግን በመልአክ ገጽ የመጣውና የተገለጸው ራሱ ያህዌ መሆኑን በግልጽ እናያለን። መልአክ ሳይሆን ራሱ ያህዌ መሆኑን አጥርተን እናያለን። ታዲያ ኢየሱስ ሊሆን ይችላልን? "መልአክ" የተሰኘው ቃል ጥቅም ላይ ሲውል በማንነታቸው ፍጡር የሆኑትንና መላእክት እየተባሉ የሚጠሩትን የግድ ላያመለክት ይችላል።
" እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው። እርሱም፦ አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፦ ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው። የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፦ አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ።" ኢያሱ 5፥ 13-15
እዚህ ላይ ኢያሱ "የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ" ከሆነው ጋር ፊት ለፊት ሲገጣጠም እንመለከታለን። Young's Literal Translation የተሰኘው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም "Prince of Jehovah's host" ይለዋል። የእግዚአብሔር ሠራዊት የሚለው የሚያመለክተው መላእክትን ሲሆን፣ እዚህ ላይ የምንመለከተው ግን የሠራዊት አለቃ የተባለውን የሠራዊቱን ልኡል ነው። በዚህ ምንባብ ኢያሱ በዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ልኡል ፊት ለአምላክ ብቻ እንደሚደረግ ሁሉ በግንባሩ በአምልኮ ተደፍቶ ሲሰግድለት እናየዋለን። ይህም ልኡል የኢያሱን ስግደትና አምልኮ አላስቆመውም፣ ይልቁንም የእግሩን ጫማ እንዲያወልቅም ጭምር እያዘዘው አምልኮውን ያበረታታ ነበር።
በራእይ መጽሐፍ ግን ዮሐንስ ራእዩን ባሳየው መልአክ ፊት ሊሰግድ ሲሞክር መልአኩ ሲከለክለው እናያለን፦
" ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ።" ራእይ 19፥ 10
ይህ መልአክ አምላክ ስላልሆነ ስግደትም ስለማይገባው ዮሐንስን "እንዳታደርገው ተጠንቀቅ" ሲል ያቀረበለትን አምልኮ ተቃወመ። መመለክ ያለበትና ስግደት የሚገባው ያህዌ ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ኢያሱ በፊቱ ቆሞ ያየው ልኡል ራሱ ጌታን መሆን አለበት። ኢያሱ የእግሩን ጫማ እንዲያወልቅ ሲነገረው እናያለን። በእርግጥም በጌታ ፊት ነበር የቆመው። ይህም መለኮታዊ ማንነት ኢያሱ ያቀረበለትን አምልኮና አክብሮት ተቀብሎአል። በእርግጥም እንዲያመልከውና እንዲያከብረው ኢያሱን ሲጋብዘው እናያለን።
" የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ። ማኑሄም ሚስቱን፦ እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት። ሚስቱም፦ እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው።" መሳፍንት 13፥ 21-23
እዚህ ላይ የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔር መባሉን ተመልከቱ፣ በትክክልም ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በዙርያው ከነበሩ ሰዎች ስግደትንና አምልኮን ብዙ ጊዜ ይቀበል እንደነበር እናውቃለን (ማቴ 14፥ 33፤ 28፥ 9፣ 17፤ ሉቃ 24፥ 52፤ ዮሐ 9፥ 38፤ እብ 1፥6)።
ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚል ልብ በሉ፦
" ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ፥ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።" 1ቆሮ 10፥ 1-4
አለቱ ክርስቶስ ነበር። ጳውሎስ ስለማን ነው የሚናገረው? እስቲ ወደ ዘጸአት መጽሐፍ ሄደን በትክክል ጳውሎስ ማንን ጠቅሶ እየተናገረ እንደሆን እንይ፦
" በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፥ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፥ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ አሉ።" ዘጸአት 14፥ 19-25
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10 ላይ በትክክል እየተናገረ ያለው ቀይ ባህርን ስለመሻገራቸውና እግዚአብሔር በህልዎቱ ስለነበረበት ደመና ነው። ያንን ህልዎት ጳውሎስ "ክርስቶስ ነው" ሲል ይጠራዋል። በዘጸአት ላይ ስንመለከት ደግሞ በእስራኤል ሰፈርና በግብጻውያን መካከል ሆኖ ይሄድ በነበረው በደመናው ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ እናያለን
ስለዚህ ጳውሎስ ይህ የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሱስ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ ግብጻውያንን ሲያስጨንቃቸው በእርግጥም ያንን ያደርግ የነበረው ኢየሱስ እንደሆነ እናውቃለን።
ሚካኤልን ስንመለከት ኢየሱስ ከአዲሱ ኪዳን በፊት የነበረውን አሰራር ማየት አንችልምን? ከመላእክት አንዱ ያልሆነውና እርሱም ራሱ መልአክ ብቻ ያልሆነው የእግዚአብሔር መልአክ በትክክል ራሱ ኢየሱስ አይደለምን? እንደ ቃል በኖረበት ባለፈው ዘላለም በሰማያትስ የነበረው ስያሜ ሚካኤል ሊሆን አይችልምን?
" በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥" ራእይ 12፥ 7
በዚህም ክፍል በሰማያት ያሉ መላእክት የሚካኤል መላእክት መሆናቸውን እናያለን፤ እርሱም ዘንዶው የተባለውን ሰይጣንን ለመዋጋት መላእክቱን ሲያሰልፋቸውና ሲመራቸው ይታያል። ስለዚህ ሚካኤል የመላእክት ዋና አዛዥ እንደሆነ ማየት እንችላለን። መሪያቸውና አለቃቸው እርሱ ነው።
እንግዲህ ኢያሱ 5 ላይ ያለውንና ይህንን የራእይ 12 ቃል ብናስተያይና ብናነጻጽር፣ ኢያሱ ያየውና ራሱን "የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ" ነኝ ሲል የገለጠለት ሰው እናያለን። በዚያውም ወደ ምእራፍ 6 ተሻግረን ሰናይ ያ ሰው እግዚአብሄር ተብሎ ተጠርቶአል። ከፍ ሲል እንደተገለጸው ሊቀ መላእክት ማለት የመላእክት ሁሉ ዋና አዛዥ፣ አለቃቸው ሲሆን እርሱም የእግዚአብሄርን ሰማያዊ ሰራዊት ሁሉ የሚመራ የሰራዊት ጌታ ነው። ይህም ሊቀ መላእክት ሚካኤል የእግዚአብሔር ሰራዊት ሁሉ አለቃ ሲሆን እርሱ ራሱ ደግሞ የሰራዊት አምላክ የሆነ እግዚአብሔር ነው። ራእይ 19 ላይ ያለውን ስናነብ ደግሞ በሰማይ ያለውን ሰራዊት በሚመራው አለቃ ማንነት ላይ አስገራሚ የሆነ የመጠርያ ለውጥ እናያለን። ሚካኤልን ለየት ባለ መጠርያው ተመልከቱት፦
" ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም። ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል። በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።" ራእይ 19፥ 11-14
የእግዚአብሔር ቃል ማን ነው? ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፦
" በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።" ዮሐ 1፥ 1
የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ነው፣ በራእይ 19 ላይም በሰማይ ያለው ሰራዊት እርሱን ሲከተል እናያለን። ኢየሱስ የሰማይን ሰራዊት የሚመራ ዋና አዛዥ ነው። በራእይ 12 ላይም የመላእክትን ሰራዊት ሲመራ የምናየው ሚካኤልን ነው፣ በራእይ 19 ላይ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ኢየሱስ ይመራቸዋል። ይህም ሚካኤል ኢየሱስ በስጋ ከመምጣቱ ወይም ቃል ስጋ ከመሆኑ በፊት የነበረው የኢየሱስ መገለጥ ነው።
ጆን ጊል የተባለ ጸሐፊ በዳንኤል 12፥ 1 ላይ ማብራርያ ሲጽፍ "ሁሉንም የሰማይ መላእክት በስሩ አድርጎ የሚያዛቸውና የሚመራቸው የመላእክት አለቃ (chief of angels)፣ ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው፣ በእውነትና በትክክል እግዚአብሔር የሆነ፣ በባህርይ፣ በስልጣን፣ እና በክብር ከመለኮታዊ አባቱ ጋር የተካከለውና፣ ራሱ እግዚአብሔር የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣" ሲል ይጽፋል።
ማቲው ሄንሪም ሲጽፍ፣ "የሚካኤል 'እንደ እግዚአብሔር የሆነው' የተሰኘው የስሙ ትርጓሜ ታላቁ ልኡል ከሚለው ማእረጉ ጋር የሚያምለክተው መለኮታዊውን አዳኛችንን ነው" ይላል።
ዳንኤል 12 ሚካኤልን ማን ብሎ እንደሚጠራው ደግሞ ተመልከተ "ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ /ታላቁ ልኡል/ ሚካኤል ይነሳል" ይላል። የ"ሕዝብህ" ልጆች የተባሉት የእብራውያንን ሕዝብ እንደሆነ እናውቃለን። እዚህ ላይ ስለ እስራኤል የሚቆመው ታላቁ ልኡል ኢየሱስ ራሱ ነው።
መከራው፦
"ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል" -- ልብ አድርጉ ይህ የሚሆነው "በዚያ ዘመን" ተብሎ በተገለጠው የአይሁድ ዘመን ማብቂያ ላይ ነው። ስለዚህ ዳንኤል የሚተነብየው ጊዜ በዘመኑ መጨረሻ በእስራኤል ላይ ስለሚሆነው ታላቅ የመከራ ጊዜ ነው። በዚህ የመከራ ዘመን ከሕዝቡ አንዳንዶቹ እንደሚድኑ ዳንኤል ይነግረናል። ኤርምያስም በትንቢቱ ተመሳሳይ ነገር ይነግረናል፦
" እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ የሚያስፈራ ድምፅ ሰምተናል፤ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም። ጠይቁ፥ ወንድ ይወልድ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ ስለ ምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ ፊቱም ሁሉ ወደ ጥቁረት ተለውጦ አየሁ? ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል።" ኤር 30፥ 4-7
ኤርምያስም ስለ መከራ ቀን ሲናገር "እርሱንም የሚመስል የለም" ይላል። አክሎም ይህ ታላቅና የሚያስፈራ የመከራና የጭንቅ ጊዜ አንዳንዶች የሚድኑበት ጊዜ እንደሆነ ይነግረናል። ኢየሱስም ስለዚህ የመከራ ጊዜ ተናግሮ ነበር። በማቴዎስ 24 ስለ ኢየሩሳሌም ውድመት ደቀ ምዛሙርቱ ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ የተናገረው ነው። መቼ ነው ይህ ጥፋት የሚሆነው፣ የዘመኑን መፈጸምና መምጣቱን የሚቀድም ምልክትስ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄአቸው የተሰጠ ምላሽ ነው፦
"በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።" ማቴ 24፥ 21
ኢየሱስ የሚናገረው ለአይሁድ ነው፣ የሚነግራቸውም " በዚያን ጊዜ ... ታላቅ መከራ ይሆናል" እያለ ነው። ይህ "በዚያን ጊዜ" የሚለው ሃረግ የሚያመለክትተው ሉቃስ "ኢየሩሳሌም በጭፍራ ስትከበብ ስታዩ" ሲል እንደሚናገረው የጥፋት ርኩሰትን ባያችሁ ጊዜ የሚለውን አጠቃላዩን ከቁጥር 15-20 ያለውን አውደ ምንባብ ነው። ይህም የሆነው ከክ.ል.በኋላ በ67 አ.ም ላይ የሮማው ጀነራል ሲስቱስ ጋሉስ ኢየሩሳሌምን በከበበበት ወቅት ነው። ታላቁ መከራ ለኛ ገና ወደ ፊት የሚመጣ ሁነት አይደለም። ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ኢየሩሳሌም በሮማውያን ጭፍራ ተከባ በነበረበት ጊዜ ያለፈ ጉዳይ ነው። ይህ ተዛማጅ በሆነው የሉቃስ ወንጌል ምንባብ ላይ በብዙ ግልጽነት ተብራርቶ ተቀምጦአል፦
" ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና።" ሉቃስ 21፥ 20-22
ሉቃስ እዚህ ላይ "የተጻፈው ሁሉ" የሚፈጸመው በኢየሩሳሌም ውድመት ነው ሲል ይነግረናል። ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? "የተጻፈው ሁሉ" የሚለው የሚያመለክተው ትንቢትን ነው። ትንቢት ሁሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በኢየሩሳሌም ውድመት ነው። ዳንኤልም በትንቢቱ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ይነግረናል፦
"ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል።" ዳንኤል 9፥ 24
ዳንኤል እዚህ ላይ ሲነገረው የምንሰማው በሕዝቡ በእስራኤል እና በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ "70 ሱባኤ" የተቀጠረ መሆኑን ነው። ተቀጥሮአል የሚለው በእብራይስጥ ቋንቋ chatha ሲሆን የሚያመለክተው ቁርጥ ሆኖ የታወጀን ጉዳይ ነው። 70 ሱባኤ ምሳሌአዊ /symbolc/ ነው። በዚህ ትንቢታዊ በሆነ የጊዜ መርሃ ግብር መጨረሻ ላይ ስድስት ነገሮች ተጠናቀው እንደሚፈጸሙ እግዚአብሔር ተስፋ ይሰጣል። በዚህ መርሃ ግብር መጨረሻ ላይ ይሆናል ተብሎ ለዳንኤል ከተነገሩት ነገሮች መካከል አንዱ "ራእይንና ትንቢትን ማተም" ነው። ራእይንና ትንቢትን በማተም ምንነትና ትርጉም ላይ ሁሉም የእብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት ማብራርያዎች በአንድነት -- "የሁሉም ትንቢት ሙሉ በሙሉ መፈጸምና መጠናቀቅ ነው" ሲሉ ይስማማሉ።
ከዚያም የዳንኤል ትንቢት የሚነግረን ሁሉም ትንቢት መሰጠት የሚያቆምበትን ጊዜና አስቀድሞ የተሰጠ ትንቢት የሚፈጸምበትን ጊዜ ነው። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? የዳንኤል ራእይ የሚጀምረው ኢየሩሳሌም እንድትሰራና እንድትጠገን አዋጅ ከሚወጣበት ጊዜ አንስቶ፣ የሚጠናቀቀው በ70 አ.ም እንደተከናወነ የምናውቀው የኢየሩሳሌም ውድመት እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ነው፦
" ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል።" ዳንኤል 9፥ 25-26
እዚህ እንደምናየው መሲሁ የሚገደለው በሰባኛው ሱባኤ ላይ ነው። ይህ ደግሞ በስድሳ ዘጠነኛው ሱባኤና በሰባኛው ሱባኤ መካከል የ2000 አመታት ክፍተት የሚያስቀምጠውን የዘመን ቆጣርያንን (Dispensationalists) ሃሳብ ፈጽሞ ውድቅ ያደርጋል። ሉቃስም ደግሞ ዳንኤል የሚናገረውን ያንንው ተመሳሳይ ነገር ኢየሩሳሌም በምትፈራርስበት ጊዜ ትንቢት ሁሉ ይፈጸማል ሲል ይናገራል። ያ ምን ምን ነገር ነው የሚያካትተው? ከተባለ፣ የዳግመኛ ምጽአቱን ትንቢት፣ትንሳኤን፣ አዱሱን ሰማይና የአዲሱን ምድር፣ ማናቸውም ለእስራኤል የተነገረውን ትንቢት ሁሉ ኢየሩሳሌም ስትፈራርስ ተፈጻሚ ይሆናል።
በመለኮት አሰራር ውስጥ የኢየሩሳሌም ውድቀት ከአንድ ከተማ መፈራረስ በላይ ላቅ ያለ ክስተት ነው፣ ያ ክስተት የአንድ ዘመን ማብቂያ ነው። ለዚህ ነው ኢየሱስ ሲናገር " በዚያን ጊዜ ከአለም መጀመርያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል" ያለው።
በዚህ ምክንያት "በ70 አ.ም ላይ ከሆነው ጋር እኩል የሆነ ወይም ከዚያ የሚበልጥ የኢየሩሳሌም ውድመት ወደ ፊት ገና እንዴት ሊኖር ይችላል?" ስል እጠይቃለሁ። በጊዜ ውስጥ ሊሆን የሚችልና በ70 አ.ም ላይ ከሆነው ጋር የሚወዳደር ሌላ ነገር ኢየሱስ ፈጽሞ አልተናገረም።
እንግዲህ ታላቁ መከራ ከዚህ ቀደም በሆነው የአለም ታሪክ የሆነና ወደ ፊትም የማይሆን መሆኑን ስነግራችሁ አዝናለሁ። የሚበዙት አብያተ ክርስቲያናት ገና ወደ ፊት ይመጣል ብለው የሚጠባበቁት ታላቁ መከራ ያለፈ ታሪክ ነው። በዘመናችሁ ሳታዩት በመቅረታችሁና ከዚህም በኋላ የማይሆንና የማታዩት ነገር በመሆኑ እንደማታዝኑና ተስፋ እንደማትቆርጡ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም የሌለና ወደ ፊትም የማይኖር ነገር አለ ይመጣል ብዬ ከምነግራችሁ የተፈጸመውን ትንቢት ብነግራችሁ ነው መልካም የሚሆነው። ታላቁ መከራ አልፎ የሄደ ታሪክ ነው።
ወደ ማቴዎስ ተመልሰን በሚቀጥሉት ቁጥሮች ላይ ምን እንደሚል እንመልከት፦
"እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።" ማቴ 24፥ 22
ይህ በዳንኤል 12፥ 1 ላይ "በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" ሲል ካየነው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ዳንኤል፣ ኤርምያስ፣ እና ጌታ ኢየሱስ ሁሉም የሚናገሩት ኢየሱስ የራሱን ሕዝብ በሚያድንበት ተመሳሳይ ጊዜ ስለሚሆን ታላቅ መከራ ነው። በትክክል ይህ ጊዜ መቼ እንደሚሆን ኢየሱስ በግልጽ ነግሮናል፦
" እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።" ማቴ 24፥ 34
ጌታ ኢየሱስ እዚህ ላይ በጣም በግልጽ ጉልህ አድርጎ ለደቀ መዛሙርቱ የሚነግራቸው ከላይ ባሉት ቁጥሮች በዝርዝር ያነሳቸው ጉዳዮች ሁሉ አንድም ሳይቀር በደቀ መዛሙርቱ ትውልድ ውስጥ የሚከናወን መሆኑን ነው። ይህም ወንጌል በአለም ሁሉ የሚሰበክ መሆኑን፣ የጥፋት ርኩሰትን፣ ታላቁን መከራ፣ የሰውን ልጅ መምጣት ሁሉ ያካትታል። ይህም ሲሰሙትና ሲያምኑት የነበረውን ልማዳዊ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ስለሚያሳጣው መጻኢ የሆነውን ነገረ ፍጻሜ የሚከተሉትን ሰዎች ሁሉ በእጅጉ የሚረብሽና ምቾት የማይሰጣቸው ግልጽ ቋንቋ ነው።
ኢየሱስ "ይህ ትውልድ" ሲል የሚናገረው ሌላ ምንም ውስብስብ ትርጉም አያስፈልገውም። ያ አንድ ትውልድ ነው። አንድ ትውልድ ደግሞ ጠቅላላ ዘመኑ እስከ አርባ አመት ድረስ እንደሚቆጠር ይታወቃል። ኢየሱስ ትንቢቱን ባስተላለፈ በአርባ አመታት ውስጥ በጣም በቅርቡ በዚያው ትውልድ ተፈጻሚ ስለሚሆን ጉዳይ ነው እየተናገረ የነበረው እንጂ በሺህ አመታትና ከዚያ በላይ ላለ የዘመን ርዝመት የሚጠበቅ የትንቢት ቃል አልነበረም። ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ መቼም ቢሆን "ይህ" የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ሲውል "ያ" የሚል ትርጉም የለውም፤ ሁልጊዜም ቢሆን የሚያመለክተው በጊዜ ወሰን ውስጥ ቅርብ የሆነን ነገር ነው። ኢየሱስ "ያ ትውልድ" ብሎ መናገር ይችል ነበር። እንደዚያ ግን አላለም። ኢየሱስ ይሆናል ሲል የተናገረው ማናቸውም ነገር ሁሉ ተፈጽሞ ያለፈው እርሱ ሲናገር እነርሱም ቆመው ሲሰሙት የነበሩ የዚያ ትውልድ ሰዎች ሳያልፉ ገና በሕይወት እያሉ ነው።
ስለዚህ ዳንኤል የሚናገረው ይህ ሁሉ ሲፈጸም የሚያየው ኢየሱስ ይኖርበት ስለነበረው ትውልድ ጊዜ ነው።
መጽሐፉ፦
"በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" -- እዚህ ላይ "ሕዝብህ" የተባሉት እስራኤላውያን የሆኑትን የዳንኤልን ሕዝብ ነው። በታላቁ መከራ ወቅት በመጽሐፉ ውስጥ ስሞቻቸው የተገኘ እስራኤላውያን ሁሉ ከመከራው ይድናሉ።
ይህ "መጽሐፍ" ምንድን ነው?
" አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና።" ፊል 4፥ 3
ይህ "የህይወት መጽሐፍ" የሚል ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው እዚህ ላይና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ነው። አንዳንዶች 'የሰው ሁሉ ስም በመጽሐፍ ተጽፎአል፣ ክርስቶስን ካልተቀበሉ በሚሞቱበት ጊዜ ስማቸው ከመጽሐፉ ላይ ይደመሰስሳል' ይላሉ። በህይወት ያሉ ሰዎች ሁሉ በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተመዝግበው ከሆነ እንግዲያውስ ይህ የፊልጵስዩስ 4፥ 3 ጥቅስ ትርጉም የሌለው ዋጋ ቢስ ይሆናል። ከቅዱሳት መጻህፍት ስለዚህ መጽሐፍ ልንማረው የምንችለው ምን ነገር ይኖር ይሆን? በህይወት መጽሐፍስ ስሞች የሚጻፉት መቼ ነው?
" ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።" ራእይ 13፥ 8
በሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፉ ሰዎች እንዳሉ እዚህ ላይ እናነባለን። ከአለም ፍጥረት አስቀድሞ ክርስቶስ እንደ በግ የታረደው መቼ ነው?
" ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ።" ራእይ 17፥ 8
አንዳንዶች በሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው እንዳልተጻፈ ከእነዚህ ጥቅሶች እናያለን፣ እዚያ ላይ ስሞቻቸው ያለ ሰዎች ግን ከዘላለም አስቀድሞ የነበረ ነው። ገና በመጽሐፉ የሚጻፍ ሌላ ምንም አዲስ ስም የለም። እዚያ ላይ የተጻፉ ሁሉ ከአለም ፍጥረት አስቀድሞ የተጻፉ ናቸው።
እነዚያ ስሞቻቸው ያልተጻፉ ደግሞ ለእሳት ባህር የተመደቡ ናቸው።
" በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።" ራእይ 20፥15
በራእይ 21፥27 ላይ " ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።" ሲል እንደተጻፈው፣ እነዚያ ስሞቻቸው በመጽሐፍ የተጻፉ ብቻ ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም -- ወደ አዲሱ ቃል ኪዳን ሲገቡ እናያለን፦
ማን ነው ማ በመጽሐፉ መግባትና መጻፍ ያለበትን የሚወስንና ምርጫ የሚያደርግ? ያህዌ ብቻ ነው። መቼ ነው ይህንን ያደረገው? ከዘላለም በፊት። ለምን? "በበጎ ፈቃዱ እንደወደደ" እና እርሱን ደስ እንዳለው፦
" ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።" ኤፌ 1፥ 4-5
በአንዳንዶች ዘንድ ብዙ ግራ መጋባትን የሚፈጥረውን ጥቅስ እንድታዩ እፈልጋለሁ፦
" ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።" ራእይ 3፥ 5
ክርስቶስ የሰጠውን ተስፋ ተመልከቱ፦ "ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም" ይህ ንግግር ለትውልድ ሁሉ የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ኖሮአል። አማኝ ድነቱን ሊያጣ ይችላልን? የእግዚአብሔር ልጁ ያመሆንን እድል ያገኘ ሰው ከሕይወት መጽሐፍ ተደምስሶ ከልጅነት ሊባረር ይችላልን? ለነዚህ ጥያቄዎች በርካታ የተሳሳቱ መልሶች ሲሰጡ ኖረዋል።
አንዳንዶች በክርስቶስ ቤዛነት የዳኑ ሰዎች ሊወድቁና ለዘላለም ሊጠፉ ይችላሉ ሲሉ ይናገራሉ። ይህ ግን ፈጽሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የማይደገፍና ከቃሉ ትምህርት የወጣ ጥንታዊ የሆነ የአርሜንያውያን አቋም ነው። በክርስቶስ የተዘጋጀው ድነት ባህርዩ ዘላለማዊ ነው። በእግዚአብሔር ፊት መጽደቃችን የተመሰረተው ኢየሱስ በፈጸመውና ባጠናቀቀው የጽድቅ ሥራ እና በመስዋእታዊ የቤዛነት ስራው ብቻ ነው እንጂ በገዛ ምግባራችን ላይ የተመሰረተ አይደለም (ዮሐ 3፥ 16፤ ዮሐ 10፥ 27-30 እና ሮሜ 8፥ 29-30 ተመልከቱ)።
ታዲያ ይህ "ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም" ማለት ምን ማለት ነው? ይህ አረፍተ ነገር በስነ ጽሁፍና በለት ተለት ንግግር ውስጥ እዘውትረው የሚጠቀሙበትን "ምጸታዊ" ተብሎ የሚጠራውን የአነጋገር ዘይቤ የሚከተል ነው። ምጸት አሉታዊውን ሙግት በማቅረብ ለአወንታዊው አጽንኦት የሚሰጥ ንግግር ነው። የምጸት አቀራረብ በተለምዶ ግልጽ የሆነን አረፍተ ነገር ማመልከት ነው። ለምሳሌ፦ "ጣእሙ አይቀመስም" ብንል ጣእሙ መራራ ነው ፣ ይጎፈንናል ማለታችን ነው። "እየቀለደ አይደለም" ብንል የሚናገረው የእውነቱን ነው ማለታችን ነው፣ ወይም "በቀላሉ የማይገመት" ብንል የነገሩ አስፈላግነትና ክብደት ትልቅ ነው ማለታችን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማንም ሰው ስሙ ከሕይወት መጽሐፍ እንደሚደመሰስ የሚያመለክት ግልጽ ንግግርም ሆነ አረፍተ ነገር የለም። ጌታ እያለ ያለው አማኞች ሙሉ በሙሉ ዋስትናቸው የተጠበቀ ነው የሚል ነው። በወንጌል ካመንን ስማችን በሕይወት መጽሐፍ ለመጻፉና ለዘላለም በጌታ ሕልዎት ውስጥ በፊቱ እንዳለን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። የእግዚአብሔር ሰማያዊት ቤተክርስቲያን የአባልነት ሚና ከአለም ፍጥረት ጀምሮ ለዘላለም የማይቋረጥ ሆኖ ይኖራል።
የሚድኑት፦
ስለዚህ በታላቁ መከራ ወቅት ያህዌ የመረጣቸው ምርጦቹ ከዚያ መከራ ይድናሉ። ይህ እንዴት ይሆናል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውን ልብ በሉ፦
" እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።" ማቴ 24፥ 15-21
ስለዚህ የጦር ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ከቦ ሲመለከቱ፣ ያኔ ከከተማዋ ሸሽተው መውጣት አለባቸው። መከራው ከመጀመሩ በፊት ከተማዋን ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል። ሮማዊው የጦር ጀነራል ሴስቱስ ጋሉስ በሆነ ባልታወቀ ምክንያት በኢየሩሳሌም ላይ አድርጎት የነበረውን ከበባ አቋርጦና ኢየሩሳሌምን ለማጥቃት የጀመረውን ግስጋሴ ገትቶ ሮማውያን ቤተ መቅደሱን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩ ጥቂት ሲቀራቸው ለተወሰነ ጥቂት ጊዜ ጦሩን እንዲያፈገፍግ ማድረጉ ታሪካዊ ሃቅ ነው። ይህም ሁኔታ ሁሉም ያመኑት ክርስቲያን አይሁድ ከተማይቱን ትተው እንዲሸሹ የተነገራቸውን የጌታን መመርያ ለመታዘዝና ተግባራዊ ለማድረግ እድሉን የሰጣቸው ጊዜ ነበር።
አማኝ ያልነበረው የአይን ምስክርና ታሪክ ጸሐፊው ጆሳፈስ ራሱም ቢሆን ይህንን እውነትና ወረራው ከተጀመረ በኋላ በዚህ ጊዜ ባልታወቀ ምክንያት ውግያው መቋረጡን ጠቅሶ ይህንንው ጉዳይ ዘግቦታል። እኛ ግን የዚህን አስገራሚ ጉዳይ ምክንያቱን መናገር እንችላለን። በመዝሙረ ዳዊት 31፥ 21 ላይ፦ "በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን።" ተብሎ እንደተጻፈ፣ ጌታ ኢየሱስ ለህዝቡ ላመኑት አይሁድ ከዚያ ወደ ከተማይቱ እየቀረበ ካለ ጥፋትና ወደ በህዝቡ እየመጣ ካለ ጥፋትና እልቂት ሸሽተው የሚያመልጡበትን እድል ሰጥቶአቸው ደቀ መዛሙርቱም እድሉን እየተጠቀሙበት ነበር። ልክ በዳንኤል 12፥ 1 ላይ "በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል" እንደተባለው ነው። ዳንኤል ተናግሮታል፣ ኤርምያስ ተናግሮታል፣ ኢየሱስ ተናግሮታል። የተፈጸመውም ልክ እንደ ተተነበየው ሆኖ ነው።
ተከታዩን ክፍል በሚቀጥሉት ቀናት አስነብባችኋለሁ። ቸር ሰንብቱ ።
ቄስ ግዛቸው ከበደ
የሙታን ትንሳኤ ቀነ ቀጠሮ የመጨረሻ ክፍል ጽሁፍ
ትንሣኤ፦
በዳንኤል 12 ላይ ቀጥሎ ያለውን ደግሞ ተመልከቱ፦
"በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።" ዳን 12፥ 2
ይህ የጻድቃንና የኃጢአተኞች ትንሳኤ ነው። "ያንቀላፉቱ ይነቃሉ"፣ የሚነቁት ወዴት ነው? " የቃሉ እዚህ ላይ ወደ ምድር ይነቃሉ አይልም፤ ይልቁንም የሚነቁት ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እና ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና "፤ ነው። ይህ ደግሞ በኢ-ቁሳዊውና በመንፈሳዊው አለም ውስጥ ያለ ኹነት እንጂ በተዳሳሹ ቁሳዊ አለም ሊታሰብ የሚችል አይደለም። ስለዚህ የሙታን ትንሳኤ በመንፋሳዊው አለም እንጂ በቁሳዊው ተዳሳሽ አለም የሚታሰብ አይደለም። እንደገናም ይህ በመጨረሻው ዘመን ላይ ወይም በ70 አ.ም ላይ በሚጠናቀቀው የእስራኤል የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ በሚሆነው የታላቁ መከራ ጊዜ ውስጥ የሚታይ የቁጥር 1 አውደ ምንባብ እንደሆነ አስታውሱ። ይህ ትንሳኤ የሚከናወነው ከኢየሩሳሌም የውድመት ጊዜ በኋላ ነው እንጂ፣ በርካታ ምእመናን እንደሚያስቡትና እንደሚመስላቸው በመጨረሻው የጊዜ ማብቂያ ወይም የሰው ልጆች ታሪክ ማብቂያ ላይ አይደለም። በርካታ ክርስቲያኖች ግን ትንሳኤ ገና ወደ ፊት የሚሆን እንደሆነ አድርገው በልማድ ያስባሉ። ዳንንኤል ቀጥሎ የሚለውን ልብ በሉ፦
"ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ" ዳን 12፥ 3
ስለዚህ ከትንሳኤ በኋላም እንኳ በወንጌል ስብከት ብዙ ሰዎችን ወደ ጽድቅ የሚመልሱ አማኝ ሰዎች ይኖሩናል። በዚህ ክፍል መሰረት ከትንሳኤም በኋላ የወንጌል ስብከት አይቋረጥም። ብዙዎች እንደሚመስላቸው ትንሳኤ፣ 'በጊዜ ማብቂያ'፣ በሰው ልጆች ታሪክ ፍጻሜ ላይ፣ ወይም በመጨሻው ቀን ላይ የሚሆን ከሆነ፣ ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ጊዜ ካበቃና ታሪክ ከተዘጋ ትንሣኤም ከሆነ በኋላ፣ በየትኛው ጊዜ በየትኛውስ የሰው ልጆች ታሪክ ብዙ ሰዎችን ወደ ጽድቅ መመለስ እንዴት ይቻላል? ይህ ከቶ የማይታሰብ ነው። እንደ ሰማይ ጸዳል እንደ ከዋክብትም ለዘላለም የሚደምቁትስ በውኑ እነማን ናቸው? አማኞች ናቸው፦
" ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።" ኢሳ 60፥ 1-3
የሚያምኑ አይሁድ አህዛብን ወደ ብርሃን ያመጡ ዘንድ ያበራሉ። እንግዲህ በዳንኤል 12 ላይ ይህ ከትንሳኤ በኋላ ሲሆን እናያለን፣ ስለዚህ ትንሳኤ የሚሆነው መቼ ነው?
" አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።" ዳን 12፥ 13
በዚህ ጥቅስ መሰረት፣ ትንሳኤ የሚሆነው ታዲያ መቼ ነው? ትንሳኤ የሚሆነው በፍጻሜው "በቀኑ መጨረሻ" ላይ ነው። ይህም የዘመኑ መጨረሻ ነው። የምን ዘመን መጨረሻ? የአሮጌው ኪዳን መጨረሻ ነው ምክንያቱም አዲሱ ኪዳን መጨረሻ የለውም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረላቸው ሁለት አይነት ዘመናት ብቻ አሉ፣ "ይህ ዘመን" የተባለው መጨረሻ የተበጀለት የአሮጌው ኪዳን ዘመን እና "የሚመጣው ዘመን" የተባለው ማለቂያ የሌለው የአዲሱ ኪዳን ዘመን ናቸው። ስለዚህ የዘመኑ መጨረሻ የሚለው የሚያመለክተው የአሮጌውን ኪዳን ዘመን ማብቂያ ነው። አዲሱን ኪዳን ፍጻሜ የሚሰጠው ሌላ በጣም አዲስ የሆነ ኪዳን ደግሞ የለም።
ጳውሎስ የሚለውን በጥንቃቄ ተመልከቱ፦
" ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።" ሐዋ 24፥ 14-15
በሕያው ቃል ትርጉም " .. እነርሱ እንደሚያምኑት እኔም የጻድቃንና የኃጥአን ትንሣኤ መኖሩን አምናለሁ" (ሐዋ 24፥ 15) ይላል። ጳውሎስ በዚህ ንግግሩ ግልጽ ያደረገው፣ "ከእነርሱ የምለየው በአምልኮዬ ነው፣ መንገዱንም ኑፋቄ ሲሉ ይጠሩታል፤ ሆኖም የማምነዉ እነርሱ እንደሚያምኑት በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ ነው፣ የሙታንን ትንሳኤ የምጠብቀውም እነርሱ እንደሚጠብቁት ነው፣ ተስፋ የማደርገውም እነርሱ ተስፋ አንደሚያደርጉት ነው"፤ እያለ ነው። ይኸውም እምነት በነብዩ ዳንኤል የተነገረውን ያመለክታል፤ "በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።" ዳን 12፥ 2
"ከሙታን ይነሱ እንዳላቸው" የሚለው ሃረግ የግሪኩን 'mello' የያዘ በመሆኑ ጉዳዩ በእርግጠኝነት በቅርቡ የሚከናወን መሆኑን ያመለክታን። ስለዚህ ጳውሎስ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አድማጮቹን ትንሳኤ በቅርቡ ሊሆን እንደሆነ እየነገራቸው ነበር።
ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ የሚናገረውን ከተረዳን፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ አውዳዊ ጠቀሜታውንም አብረን መረዳት አለብን። ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ለእኛ አይደለም፤ የሚናገረው ለፊልክስ፣ ለአናንያስ፣ ለታርቴሉስ፣ እንዲሁም ለሽማግሌዎቹ ነበር። የሚነግራቸውም "ትንሳኤ ሊሆን እየተጠባበቅነው ነው" እያለ ነበር። ስለዚህ የትንሳኤ ጊዜው ያኔ ለአይሁድም ሆነ ለጳውሎስ ቅርብ ከነበረ፣ ይህ ታዲያ ስለ ትንሳኤ ተፈጥሮ ምን ይነግረናል? ለሙታን ትንሳኤ በመለኮት የተያዘለትን መርሃ ግብር እና ቀነ ቀጠሮውን ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን በፍርድ ከተጠናቀቀው የአይሁድ ዘመንና አውድ አርቀን፣ በሌላ ባልታወቀ ዘመን ውስጥ፣ ገና ወደ ፊት፣ የምንጠብቀው ከሆነ፤ እንግዲያውስ የምንጠባበቀው አይሁድም ሆኑ ጳውሎስና የመጀመርያይቱ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ያልተጠባበቁትን፣ እንግዳና ለቃሉ ባእድ የሆነውን የስጋ ትንሳኤ ይሆናል። ትንሳኤ ግን መንፈሳዊ መሆን አለበት፣ ጊዜው ተፈጥሮውን ያመለክታልና።
በ70 ዓ.ም በአሮጌው ኪዳን ማብቂያ ላይ የተከናወነው የሙታን ትንሣኤ፣ በሰማያዊው መንግስት ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅና ሕብረትን ለማድረግ ለዘመናት እየተጠባበቁ የነበሩትን ነፍሳት ከሲኦል የመፍታትና ማስለቀቅ ነው እንጂ፣ በአፈር ውስጥ የበሰበሱ ሰዎች አካል የተዳሳሹ ስጋ ባዮሎጂካል ትንሣኤ አልነበረም።
ሄሜኔዎስና ፊልጦስ የብዙዎችን እምነት ከገለበጡበት አስተምህሮአቸው በመነሳት የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ ምን ያምኑ እንደነበር በርካታ ነገሮችን ማየት እንችላለን፣ ጥቂቶቹን እንመልከት፦
" ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም፦ ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ።" 2ጢሞ 2፥ 17-18
ሄሜኔዎስና ፊልጦስ በዚህን ያህል ደረጃ በአማኞች ላይ አሉታዊ ተጽእኖን ማሳደር እንዴት ቻሉ? የጥንት ክርስቲያኖች ትንሳኤ በተፈጥሮውና በባህርዩ መንፈሳዊ እንደሆነ የሚያምኑ መሆን አለባቸው፣ ስለዚህም በእምነታቸውና በትምህርታቸው የትኛውንም አካላዊ/ተዳሳሽ የሆነ ማረጋገጫ አይከተሉም። የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ትንሳኤ የነበራቸው እምነት ልክ የዛሬዎቹ በርካታ አማኞች እንደሚያምኑትና እንደሚያስተምሩት ሁሉ አካላዊ/ተዳሳሽ የሆኑ ስጋዎች ከመቃብር ወጥተው የሚመጡበትንም አይነት የሚያካትት መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ፣ ሄሜኔዎስና ፊልጦስ "ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኗል" በማለታቸው ማንንም ማሳመን ባልቻሉ ነበር።
የጥንት ክርስቲያኖች ከትንሳኤ በኋላ ሕይወት በምድር ላይ ምንም አይነት የቁስ አካል ለውጥ ሳያደርግ ይቀጥላል ብለውም ጭምር የሚያምኑ መሆን አለባቸው። የጥንት ክርስቲያኖች የትንሳኤ ውጤት እንደሆነ ሁሉ በተለወጠችና በታደሰች ምድር እንኖራለን ብለውም የሚያምኑ አልነበሩም። አለበለዚያ የሄሜኔዎስና የፊልጦስ ትምህርት የብዙዎችን እምነት እስኪገለብጥ ድረስ በማንም ላይ ያን ያህል አፍራሽ ተጽእኖ ማሳደር ባልቻለም ነበር። ማንምም ሰው ትኩረት ባልሰጣቸው ነበር።
ሄሜኔዎስና ፊልጦስ ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል ብለው ሲያስተምሩ የአንዳንዶችን እምነት የገለበጡበት ምክንያት ምንድር ነው? የፍጻሜው ምልክት የሆነው ያ ምድራዊው ቤተመቅደስ ገና በኢየሩሳሌም ቆሞ ሳለ፣ መንፈሳዊው መንግስት በፍጹምነት ተገልጦአል ብሎ የሚናገር በመሆኑ ነው። ጊዜውን የቀደመ ንግግር በመሆኑ ነው፤ ይህ ደግሞ ሕግንና ጸጋን ማደባለቅ ይሆናል። ይህም የሕጉን ስራ የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል በማድረግ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣል።
ዳንኤል 12 ላይ ጥናታችንን ገፍተን እንቀጥል
"በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።" ዳን 12፥ 2
ይህ በግልጽ የሚናገረው ስለ ሙታን ትንሳኤ ሲሆን፣ ያንቀላፉት ሲነቁ የሚነቁትእኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና ነው። ይህም የመንፈሳዊው አለም ኹነት ነው እንጂ በዚህ በተዳሳሹ አለም ውስጥ ሊሆን የሚችል አይደለም። ምክንያቱም እነዚህ ሙታን የሚነቁባቸው የዘላለም ሕይወት እና የዘላለም ጉስቁልና የተባሉ ጉዳዮች/ ስፍራዎች በተፈጥሮአቸው አካላዊ ወይም ተዳሳሽ ስላልሆኑ ነው። በተጨማሪም በዚህ አውድ ውስጥ ይህ የሚሆነው ከዚህ ታላቅ መከራ በኋላ ነው። የዚህ ታላቅ መከራ ወቅት ደግሞ ካለፈ ቆይቶአል። ይህም ከሆነ በኋላም ብዙዎችን ወደ ጽድቅ የሚመልሱ አማኞች ይኖራሉ፦
"ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ።" ዳን 12፥ 3
የመንግስቱ ብርሃን ወጥቶ እየሄደ ብዙዎች ወደ ጽድቅ ይመለሳሉ። ትንሳኤ በርካቶች እንደሚያምኑት በመጨረሻው ጊዜ ላይ የሚሆን ከሆነ፣ ታዲያ ትንሳኤም ከሆነ በኋላ ብዙዎች ወደ ጽድቅ ሊመጡ እንዴት ይችላሉ? ትንሳኤ ከሆነም በኋላ ወንጌል ገና ይሰበካል ማለት ነው። ወንጌልን በጊዜዉም ያለጊዜውም የምንሰብከው የዘመኑ ፍጻሜ ስለደረሰም ሆነ የጌታን ምጽአት ለማፋጠን አይደለም፣ እርሱ አልፎአል፤ ይልቁንም ወንጌል የምንሰብከው ወንጌልን መስበክ ለአለምና ለዘለአለም እስከ ትውልዶች ሁሉ ስራችንና እድል ፈንታችን ስለሆነ ነው።
ስለዚህ ዳንኤል 12 የሚናገረው ስለ ታላቅ መከራ ስለ ትንሳኤና ብዙዎች ወደ ጽድቅ ስለ መምጣታቸው ነው። ኢየሱስ በማቴዎስ 13 ላይ ምን እንደሚል ተመልከቱ፦
"እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።" ማቴ 13፥ 40
ስለዚህ ኢየሱስ እዚህ ላይ የሚናገርለት ጊዜ "የአለም መጨረሻ" ይኸውም "የዘመን መጨረሻ" ነው። ይኸውም ደግሞ ዳንኤል በትንቢቱ የተናገረለት ያው አንዱ ፍጻሜ የቀኑ መጨረሻ ነው፦
"አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።" ዳን 12፥ 13
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ "ይህ ዘመን" ፣ ማለትም የአሮጌው ኪዳን ዘመን እና "የሚመጣው ዘመን" ማለትም የአዲሱ ኪዳን ዘመን" ተብሎ የተነገረላቸው ሁለት ዘመናት ብቻ ናቸው ያሉት። የአዲሱ ኪዳን ዘመን የፍጻሜ ቀንም ሆነ የዘመን መጨረሻ የለውም፤ ስለዚህ የዘመኑ መጨረሻ የሚለው የሚያመለክተው የአሮጌውን ኪዳን ማብቂያ ብቻ ነው። አዲሱን ኪዳን የሚያሳልፍ ሌላ የተሻለ አዲስ ኪዳን የለም።
ወደ ማቴዎስ 13 እንመለስ፦
"የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።" ማቴ 13፥ 41-43
ኢየሱስ ሲናገር፣ በዘመኑ መጨረሻ አመጸኞች ወደ እሳት ባህር ይጣላሉ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል ይላል። ይህ ዳንኤል የተናገረለት ታላቁ መከራ ነው። ከዚያም ዳንኤል 12፥ 3 ላይ ያለውን ጠቅሶ ፣ "ጻድቃን እንደ ጸሐይ ያበራሉ" ይላል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች፣ ታላቁ መከራ፣ ትንሳኤ፣ እና የጻድቃን እንደ ጸሐይ ደምቆ ማብራት የሚሆኑት በአይሁድ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው።
ዳንኤል 12 እና ማቴዎስ 13 ሁለቱም አስቀድመው በትንቢት የሚናገሩት በ70 አ.ም ላይ ስለሆነውና በታሪክ ስለተረጋገጠው የኢየሩሳሌም ውድመት ነው። እንግዲህ ትንሳኤ በ70 አ.ም ላይ የሆነ ኩነት ነው።
"ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።" ዳን 12፥ 4
ዳንኤል ቃሉን እንዲዘጋው የተነገረው እስከ መቼ ነው? "እስከ ፍጻሜ ዘመን"። አንዳንድ እንደ KJV እና NIV ያሉ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ግን "ጊዜ እስኪያበቃ" (end of time) ሲሉ መተርጎማቸው ስህተት ነው። ቁጥር 7 ላይ ያለውን ስንመለከት ግን ይህ መጨረሻ የጊዜ ማብቂያ እንዳልሆነ በግልጽ እንረዳለን፦
"ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፦ ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኵሌታ ነው፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል ብሎ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ።" ዳን 12፥ 7
የዚህን ጥቅስ መጨረሻ ልብ በሉ፣ "የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል" ይህ ሁሉ ሲል ምን ምን ኩነቶችን ነው? በቁ 1 ላይ ያለው ታላቁ መከራ፤ በቁጥር 2 ላይ ያለው ትንሳኤ፤ በቁጥር 3 ላይ ያለው የብዙዎች ወደ ጽድቅ መመለስ፤ እንዲሁም የተቀደሰው ሕዝብ ኃይል መበተን ናቸው። ይህ የሚሆነው ታዲያ መቼ ነው? በቁጥር 4 ላይ እደተጻፈው በፍጻሜ ዘመን ላይ ነውን? የተቀድደሰውስ ሕዝብ እነማን ናቸው? ከአውዱ እንደምንረዳው እነዚህ አይሁድ የሆኑ የዳንኤል ሕዝቦች ናቸው።
ሰባው ሱባኤ፦
ታዲያ የአይሁድ ሕዝብ ኃይል ፈጽሞ የተበተነውና የተጨረሰው መቼ ነው? ይህንን ለመረዳት ወደ ዳንኤል ምእራፍ 9 ላይ ሄደን እንይ፦
" ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል።" ዳን 9፥ 24
እዚህ ላይ የምናየው "በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ስባ ሱባኤ ተቀጥሮአል" ማለቱን ነው። ይህም የአይሁድን ህዝብና ኢየሩሳሌምን ማለቱ ነው። ቀደም ሲል ለማለት እንደሞከርኩት ይህንን ሰባ ሱባኤ በቁሙ እንዳለ ወስጄ እንደ አንድ የተገደበ ጊዜ አድርጌ አላየውም። ለምን እንደ ሆነ ልንገራችሁ። ዳንኤል ስለ ሰባው ሱባኤ ትንቢቱን በተቀበለ ጊዜ፣ የእስራኤል ልጆች በባቢሎን ምድር በምርኮ ውስጥ ነበሩ። ከ.ክ.ል.በ በ538 ላይ የባቢሎን መንግስት ከወደቀ በኋላ፣ የፋርስ ንጉስ ቂሮስ ኢየሩሳሌም እንደገና እንድትጠገንና እንድትሰራ አዋጅ አወጀ፦
"በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ፦" እዝራ 1፥1
ይህ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ። ስለዚህ ሰባው ሱባኤ የጀመረው ከ.ክ.ል.በ በ538 ላይ መቅደሱና ከተማይቱ እንደገና እንዲሰሩ የንጉሱ የቂሮስ የአዋጅ ቃል ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ሰባው ሱባኤም የሚፈጸመው በ70 አ.ም በኢየሩሳሌም ውድመት ነው፦
" ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል።" ዳን 9፥ 26
የገብርኤል ትንቢት የሚጀምረው በቁጥር 24 ላይ "በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ስባ ሱባኤ ተቀጥሮአል" ከሚለው ነው። ከዚያም በቁጥር 26 ላይ የከተማይቱንና የመቅደሱን ጥፋት እናያለን። ከተማይቱና መቅደስዋ ደግሞ የጠፉት በ70 አ.ም ላይ ነው።
ስለዚህ ከ538 ከ.ክ.ል.በ እስከ 70 አ.ም ድረስ ዘመኑ ሲሰላ በጠቅላላ 608 አመታት ናቸው እንጂ 490 አይደሉም። ከ538 ከ.ክ.ል.በ እስከ 70 አ.ም ድረስ ያለው ጊዜ፣ ከባቢሎን ውድቀት በቅዱሳት መጻህፍት ባቢሎን ተብላ እስከተጠራችው የኢየሩሳሌም ውድቀት ድረስ ነው። ስለዚህ ይህንን "ሰባ ሱባኤ" የማየው ከባቢሎን ውድቀት እስከ ባቢሎን ውድቀት እንደተሰመረ ምሳሌአዊ ክፍለ ጊዜ ነው።
"ሰባው ሱባኤ" ኢየሱስ ለጴጥሮስ እንደተናገረው አይነት ምሳሌአዊ ነው፦
" በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።" ማቴ 18፥ 21-22
ኢየሱስ 491ኛው ላይ ይቅርታ ማድረግ ታቆማለህ እያለው አይደለም። መልሱ እንዳለ በቁሙ የሚወሰድ አይደለም። ይልቁንም ኢየሱስ በመልሱ ጴጥሮስን እያስተማረው ያለው በእውነትም የይቅርታ መንፈስ ገደብ የሌለው መሆኑን እያመለከተው ነበር። "ይቅር ማለት አታቋርጥ" እያለው ነበር። ስለዚህ የኢየሱስ ሰባ ጊዜ ሰባትም ሆነ የዳንኤል "ሰባ ሱባኤ" እንዳለ በቁሙ የሚወሰድ አይደለም።
ሰባው ሱባኤ በታላቁ መከራ፣ በቤተ መቅደሱ ውድመት፣ በፓሮዥያው (ምጽአት) እና በትንሳኤ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በነገሮች አፈጻጸም ቅደም ተከተል በቁሙ የሚወሰድ አይደለም። በቁሙ እንዳለ የሚወሰድ ከሆነ የምጽአቱን ጊዜ በምን አመት ላይ እንደሚሆን አስልቶ ማወቅ የሚቻል በሆነ ነበር። የዳንኤልን ትንቢት የሚያነቡ የዚያ ዘመን ሰዎች መቅደሱና ከተማይቱ እንዲሰሩ በንጉሱ በቂሮስ አዋጅ ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ 490 አመታትን በመቁጠር ኢየሱስ በትክክል መቼ እንደሚመለስ ማወቅ በቻሉ ነበር። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦
" ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።" ማቴ 24፥ 35-36
በዚህ ዘመን በርካቶች ቁጥር 36 ላይ ያለውን እየጠቀሱ ከእኛ በኋላ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን የወደፊታችንን የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት የማናውቅ ለመሆናችን ማረጋገጫ አድርገው ያቀርባሉ። ነገር ግን "ያች ቀን" የተባለው የሚያመለክተው ሰማይና ምድር የሚያልፍበት ይኸውም የኢየሩሳሌም እና የአሮጌው ኪዳን ውድመት ቀን ነው። በቁጥር 34 ላይ ኢየሱስ ቀድሞውኑ ይህ መቼ እንደሚሆን በትውልዳቸው (በአርባ አመታት) ውስጥ እንደሚሆን ነግሮአቸዋል። ነገር ግን ይህ መቼ እንደሚሆን "ቅኒቱንና ሰአቲቱን" አያውቁም ነበር።
ለምሳሌ፦ አንዲት ሴት ስታረግዝ በአርባ ሳምንታት ውስጥ ልጇን እንደምትታቀፍ እናውቃለን። ቀኑን ወይም ሰአቱን ግን አናውቅም፣ ነገር ግን በአርባ ሳምንታት ውስጥ እንደሚሆን እናውቃለን። እዚህም ላይ ጌታ ኢየሱስ በትክክል እየተናገረ ያለው እንዲህ ያለውን ነገር ነው። የመንግስቱን መገለጥ ቀድሞ ያለው ጊዜም የምጥ ጣር በሚል መግለጫ መታወቁ በእውነትም አስገራሚ ነው።
ሰአቱንና ቀኑን የሚያውቅ ማንም የሌለ ከሆነ፣ ሰባው ሱባኤ መወሰድ ያለበት በምሳሌነቱ ነው።
" ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል።" ዳን 9፥ 26
እዚህ ላይ የአይሁድን ህዝብ የመጨረሻ ሱባኤ ይኸውም ሰባኛውን ሱባኤ እናያለን፣ "ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ"። የኢየሩሳሌም ከተማ እና የአይሁድ ቤተ መቅደስ ውድመት "የተቀደሰው ህዝብ ኃይል መበተን" ነው። ይህ ማለት ያህዌ ለሙሴ የሰጠው የአሮጌው ኪዳን ሥርአት በ70 አ.ም ላይ በአህዛብ ሰራዊት መወገዱ እንደሆነ እናውቃለን።
ይህም በአሮጌው ኪዳን ማብቂያ ላይ የሚሆን እንጂ በሰው ልጆች ታሪክ ማብቂያ፣ በጊዜ መጨረሻ ላይ የማይሆን ከሆነ የሚበዙት በልማዳዊ አተረጓጎሞች በዳንኤል 12፥ 4 ላይ ያስቀመጡት ትርጉም ትክክል እንዳልሆነ እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ጊዜ የሚል ትምህርት ፈጽሞ የለውም። የመጨረሻው ቀን የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊገኝ ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን የጊዜ ማብቂያ፣ የታሪክ ማብቂያ፣ የሚል አገላለጽ በየትኛውም ገጹ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ አያውቀውም። የመጨረሻው ቀን ወይም የቀኑ መጨረሻ የሚለው አገላለጽ የዘመኑን ፍጻሜ ሊያመለክት ይችላል፤ ነገር ግን የዘመኑ መጨረሻ ማለት የጊዜ መጨረሻ ወይም የመጨረሻ ጊዜ ወይም የሰው ልጆች ታሪክ ማብቂያ ማለት ፈጽሞ አይደለም። እግዚአብሔር ይህቺን የምንኖርባትን የእኛዋን ፕላኔት ምድርንም ሆነ የትኛውንም የተፈጠረ ፕላኔት አለም የመደምሰስ እቅድ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ አያመለክትም። እስቲ ቁጥር 4 ላይ ተመልሰን እንይ፦
"ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።" ዳን 12፥ 4
ዳንኤል "እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ" እነዚህን ቃላት እንዲዘጋና መጽሐፉን እንዲያትም ሲነገረው እናያለን። ይህም ማለት የፍጻሜው ዘመን እስኪሆን ድረስ እነዚህን ጉዳዮች መረዳት አይቻልም ማለት ነው። እነዚህ ነገሮች የማይታወቁ ሆነው ይቆያሉ ማለት ነው። የፍጻሜው ዘመን ሲመጣ ግን ኢየሱስ ዳንኤልን ጠቅሶ ምን እንዳለ ተመልከቱ፦
"ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥" ማር 13፥ 14
ማርቆስ "አንባቢው ያስተውል" ሲል ያክልበታል። ይህ የዳንኤልን አንባቢዎች አትኩሮታቸውን ወደ ምንባባቱ እውነተኛ ትርጓሜ ለመሳብ የታለመ አነጋገር ነው። በሌላ አባባል ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከባ በምታዩበት ጊዜ፣ ያኔ ይህ የኢየሩሳሌም ጥፋት ምልክት እንደሆነና የእርሱ መምጣትና የዘመኑ መጨረሻ ምልክት እንደሆነ ታስተውላላችሁ ማለቱ ነው።
"እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ዳንኤል ሆይ፥ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤" ዳን 12፥ 9
እንደገና ቃሉን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ወይም እስከ እስራኤል የመጨረሻ ቀኖች ድረስ የተዘጋና የታተመ እንደሆነ ለዳንኤል ሲነገረው እንሰማለን። በዳንኤል 12፥ 4 ይህ የፍጻሜ ዘመን እውቀት የሚበዛበት ዘመን እንደሆነ ተነግሮናል። እዚህ ጥቅስ ላይ እውቀት የሚለው የሚያሳየው ሳይንስና ቴክኖሎጂን ነው፣ ስለዚህም የእኛን ዘመን ያመለክታል ሲባል ስንቶቻችሁ ሰምታችኋል? በርካቶች እንደዚያ የሚያስተምሩ ሰዎች አሉ። ይህ ግን ፈጽሞ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን እውቀት የሚናገር ቃል አይደለም። ይህ ስለ አይሁድ ዘመን ፍጻሜ መሆኑን ፈጽሞ አትርሱ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውቀት በሚናገርበት ጊዜ ሁሉ የሚያመለክተው ያህዌን እውነተኛውን አምላክ ስለማወቅ ነው። ከበአለ ኃምሳው በፊትና ከአዱሱ ኪዳን መገለጥ በፊት ያህዌን ማወቅ ለማን ብቻ ነበር የተወሰነው? ለእስራኤል ብቻ የተወሰነ ነበር፦
"እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤" ሮሜ 9፥ 4
እስራኤል ብቻ ያህዌን ታውቅ ነበር። ከበአለ ኃምሳው ቀን በኋላ ግን የያህዌ እውቀት ይኸውም እግዚአብሔርን ማወቅ ወደ አህዛብ ሁሉ ዘንድ ደረሰ። ይህ ነው ዳንኤል የሚናገርለት እውቀት - የወንጌል እውቀት፣ እግዚአብሔርን በክርስቶስ ማወቅ። ኢስይያስም ስለዚህ ጉዳይ ተናግሮአል፦
"የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል። በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።" ኢሳ 2፥ 1-3
ይህም የሚሆነው በዘመኑ ፍጻሜ ላይ ነው፣ ይኸውም ዳንኤል የተናገረለት ያው አንዱ የፍጻሜ ዘመን ነው። አህዛብም "እርሱ መንገዱን ያስተምረናል" እያሉ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ይመጣሉ። አህዛብ የእግዚአብሔርን መንገድ በተማሩ ልክ እውቀት ይጨምራል ይበዛልም። እግዚአብሔርን ማወቅ ከታናሹ ጀምሮ ለሁሉ የተሰጠ የአዲሱ ኪዳን ትሩፋት ነው፤ የኤርምያስን ትንቢት በስሙ፦
" ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።" ኤር 31፥ 33-34
ጳውሎስ ይህ እውቀት ከእስራኤል ወጥቶ ወደ አህዛብ ሁሉ እንዲደርስና እንዲበዛ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ነበር፦
"በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።" 2ቆሮ 4፥ 6
ጳውሎስ እዚህ ላይ ወንጌልን ምን ብሎ እንደሚጠራው ተመልከቱ፦ "በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን የሚሰጥ" ሲል ይጠራዋል። ጳውሎስ ይኖር የነበረው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነበር፣ እርሱም ይህ እውቀት እንዲጨምር አግዞአል። ዳንኤል የሚናገረው እንግዲህ ስለዚህ ጉዳይ ነው። በመጨረሻው ዘመን እውቀት ይበዛል፣ ይኸውም የመሲሁ የጌታችን ኢየሱስ እውቀት ነው።
"እኔም ዳንኤል አየሁ፤ እነሆም፥ ሁለት ሌሎች ቆመው ነበር፥ አንዱ በዚህ በወንዙ ዳር፥ ሌላውም በዚያ በወንዙ ዳር። አንዱም ከወንዙ ውኃ በላይ የነበረውን በፍታም የለበሰውን፦ የዚህ ድንቅ ፍጻሜ እስከ መቼ ነው? አለው። " ዳን 12፥ 5-6
ይህ ጥያቄ ስለ ዳንኤል ሲባል የተጠየቀ ይመስላል። የእነዚህ ነገሮች ፍጻሜ ማለት ከዳንኤል 11፥ 40 እስከ 12፥ 3 ድረስ የተነገረው ፍጻሜ ማለት ሲሆን፣ በዚያም ውስጥ ተካተው እንዲፈጸሙ በመለኮት መርሃ ግብር የተያዘላቸውና ቀነ ቀጠሮ የተመደበላቸው ጉዳዮች፦ ታላቁ መከራ፣ የተመረጡት ሰዎች መዳን፣ ትንሳኤ ናቸው። ለዚህ ጥያቄ የተሰጠው መልስ በቀጣዩ ጥቅስ ላይ ይገኛል፦
"ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ፦ ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኵሌታ ነው፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል ብሎ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ።" ዳን 12፥ 7
"ይህ ሁሉ" የተባለው በቁጥር 2 ላይ ያለውን ትንሳኤም ይጨምራል። ለዳንኤል "ትንሳኤ የሚሆንበት ጊዜ" ተብሎ የተነገረው መቼ ነው ለሚለው ጥያቄ ሲመለስለት "የተቀደሰውም ሕዝብ (አይሁድ) ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይፈጸማል" ተብሎ ነው።
ስለዚህ ትንሳኤ የሚሆነው በአይሁድ ዘመን መጨረሻ ላይ፣ ይኸውም የአሮጌው ኪዳን ዘመን በፍርድ ሲዘጋ እንደሚፈጸም በሕያው እግዚአብሔር በመሃላ የተወሰነና ቀን የተቆረጠለት ነው። ይህም በአይሁድ ቤተ መቅደስ መፈራረስ 70 አ.ም ላይ እንደተጠናቀቀ እናውቃለን። ከዚህ የጊዜ ወሰን እና ማእቀፍ ርቆ ትንሳኤን መጠበቅ በመጽሐፍ ቅዱስ የቃሉ ድጋፍ የሌለውን ነገር መጠበቅ ነው።
"ሰማሁም ነገር ግን አላስተዋልሁም፤ የዚያን ጊዜም፦ ጌታዬ ሆይ፥ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድር ነው? አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ዳንኤል ሆይ፥ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤" ዳን 12፥ 8-9
ይህ ማለት እነዚህ የተባሉት ጉዳዮች ተፈጻሚ ሊሆኑ የተቀጠረላቸው ጊዜ እስኪደርስ ወይም እስኪቀርብ ማለት ነው፤ ለዳንኤል የፍጻሜው ዘመን ገና አልደረሰም ነበር፣ ገና በሩቅ ነው፤ እነዚህም ጉዳዮች እስከዚያ ጊዜ ድረስ ገና ግልጽ ሆነው ማንም የሚረዳቸው አይነት አልነበሩም። በራእይ መጽሐፍ ላይ ግን ይህንን እናነባለን፦
" ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።" ራእይ 22፥ 10
በዳንኤል መጽሐፍ "እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ " የታተመውና የተዘጋው አሁን ግን የሚፈጸምበት ዘመኑ ስለቀረበ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ በማኅተሙ መዘጋት ሳያስፈልገው ተገለጧል። ወደ ዳንኤል እንመለስ፦
"ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፥ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ። የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኵሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል።" ዳን 12፥ 10-11
የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኵሰት ከቆመ ጀምሮ 1,290 ቀናት ይኖራሉ። ይህ ማለት ስንት አመት ማለት ነው? ሦስት አመት ከመንፈቅ ማለት ነው፣ ይህም በአይሁድ ላይ የታወጀው ጦርነት ለመጠናቀቅ የወሰደው ጠቅላላ ጊዜ ነው። ይህም ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 24፥15 ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት እየተናገረ ሳለ የጠቀሰው ጉዳይ ነው፦
"እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥" ማቴ 24፥ 15
ዋልቩርድ የተባሉ ተርጓሚ በዚህ በማቴዎስ 24፥ 15 ጥቅስ ላይ አስተያየት ሲሰጡ፦ "ይህ ትንቢት ቃል በቃል እንዲፈጸም እንዲህ ያለ ቤተ መቅደስ እንደገና መታነጽ አለበት። ያ ደግሞ ከሆነና በሚታነጸው ቤተመቅደሳቸው ውስጥ የመስዋእት ስርአታቸውን እንደገና ከጀመሩ በኋላ ድንገት ቤተ መቅደሱን የሚያረክስ ነገር ይከሰታል፣ ከዳግም ምጽአቱም ቀደም ብሎ ከእስራኤል ጋር ውል የሚፈራረመው ውሉን አፍርሶ ታላቁ መከራ ያኔ ይጀምራል" ይላሉ፤ [ ይህንንም የሚሉት ልክ በ70 አ.ም የሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት በበቂ ሁኔታ ቃል በቃል የተፈጸመ ጉዳይ እንዳልሆነ ያህል ነው]። በዘመነኛይቱ ኢየሩሳሌም ላይ ፕሬዘዳንት ትራምፕ የሚከተሉትን ፖሊሲ ከዚህ ትንቢት ጋር ማያያዝ በምንም መመዘኛ ልክ ሊሆን አይችልም።
በእውነት በዚህ ምንባብ ውስጥ ኢየሱስ የሚናገረው እንዲህ ያለ ነገር ነውን? በጭራሽ አይደለም። ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በገዛ ራሱ ትውልድ ውስጥ ሊሆን ስላለ ነገር ነው (ማቴ 24፥ 34)።
እንደ ዋልቩርድ ያሉ በርካታ ተርጓሚዎች በዚህ "የጥፋት ርኲሰት" በተሰኘ ገለጻ ውስጥ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት የዘመተው ወራሪው የሮም ጭፍራ ወይም ሌጌዎን ያለውን ቦታ አያስተውሉትም። የንስር መልክ ያለው የተቀረጸ ምስል የነዚያ ወታደሮች የአምልኮ ምልክት ነበር። ጆሳፈስ ካሰፈረው የታሪክ ዘገባ እንደምንረዳው የሮማዊው ጀነራል ቪታልዩስ ጭፍራውን እየመራ በይሁዳና በጢባርዩስ አውራጃ በሰልፍ ለማለፍ ያደረገው ሙከራ በአይሁድ መሪዎችና ባለስልጣናት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ ምክንያቱም ያንን የጣኦት ምስል አንግበው ምድሪቱን መርገጣቸው ሕጉን የሚያረክስ እርግማንና ርኩሰት ነበርና ነው።
በእውነት ሉቃስ ግን ጉዳዩን ግልጽ ያደርግልናል፦
"ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።" ሉቃ 21፥ 20
ይህን ጥቅስ ከበው ያሉትን ሌሎቹን ጥቅሶች በማንበብ በማቴዎስ ከተዘገበው የደብረዘይቱ ተራራ ፍካሬ ጋር ትይዩ ጽሁፍ እንደሆነ መካድ አይቻለንም። ተመሳሳይና ትይዩ የሆኑ ዘገባዎች ደግሞ የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው አይችልም። የሉቃስን ንግግር ከታሪካዊው ዘገባ ጋር አገናኝተን ስናነበው በጀነራል ቨስፓስያን፣ በጀነራል ቲቶ፣ በጀነራል ሴስቱስ ጋሉስና፣ በጀነራል ቪታልዩስ የተመራው የሮም ሌጌዎን የጥፋት ርኩሰት መሆኑ ግልጽ ይሆንልናል። ይህም የተፈጸመው በ66 ዓ.ም ሮማውያን መጥተው የኢየሩሳሌምን ከተማ በከበቡበት ጊዜ ነው።
የጥፋት ርኩሰት ማለት ቅድስቲቱ ከተማ ትረክስ ዘንድ የጦር ሰራዊት ሲመጣባት እንደሆነ የሚያምኑና የሚያስተምሩ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ያሉ በርካታ አባቶች አሉ።
"አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።" ዳን 12፥ 13
በቁጥር 1፣ 7፣ 11 እና 12 ላይ ያለው ንግግር ትንሳኤን በ70 ዓ.ም ላይ የሚሆነውን የኢየሩሳሌምን ውድመት ተከትሎ ወዲያውኑ የሚሆን ነገር ያደርገዋል። ዳንኤልም የሚነሳውና በእጣ ክፍሉ የሚቆመው በቀኑ መጨረሻ የተቀደሰው ሕዝብ ኃይል ሲበተን ነው። ይህንን ትንሳኤ ወስደን ከኢየሩሳሌም ውድመት ጋር ያለውን ቁርኝት መነጣጠል እንዴት ይቻለናል? ያንን ማድረግ እንዴት ነው የሚቻለው? ያንን ማድረግ ጨርሶ አይቻልም።
ዳንኤል የሚጽፈው ነገር በአይሁድ ሕዝብ አስተሳሰብ ውስጥ በሚገባ ስር የሰደደና የሚታወቅ ነገር ነው። ኢየሱስ ከማርታ ጋር ካደረገው ንግግር ትንሳኤ መቼ እንደሚሆን ምንም ጥርጣሬ እንዳልነበራት እናያለን። ትንሳኤ የሚሆነው፦
"ኢየሱስም፦ ወንድምሽ ይነሣል አላት። ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።" ዮሐ 11፥ 23-24
የምን መጨረሻ ቀን? የሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ነውን? የፕላኔት የመጨረሻ ቀን ነውን? ፈጽሞ እንደዚያ አይደለም፣ እርስዋ እየተናገረች የነበረው ስለ አይሁድ ዘመን መጨረሻ ነው። በሕጉ የተጉ አይሁድ ያ ይኖሩበት የነበረው ስርአት አርጅቶ እንደሚወገድና ዘመኑ እንደሚፈጸም ያምኑ ነበር። እርሱን የሚያስረጅና የሚተካ አዲስ የመሲሁ ዘመንም እንደሚመጣ ይጠባበቁ ነበር፣ የሙታንንም ትንሳኤ የሚጠባበቁበት በመጨረሻው ቀን የአሮጌው የሙሴ ስርአት ማብቂያ ላይ ነው እንጂ፣ የዚህ ዘመን የመጻእያን የአለም መጨረሻ ጽንሰ አሳብ ለአይሁድ ጨርሶ የማይታወቅ እንግዳ ትምህርት ነው። ኢየሱስም ሲያስተምር ትንሳኤ በቅርቡ ቶሎ እንደሚሆን ተናገረ እንጂ በኋላ ቆይቶ ከሺህ አመታት በኋላ ይሆናል አላለም፦
"እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።" ዮሐ 5፥ 25
ኢየሱስም ደግሞ ትንሳኤ የሚሆነው በመጨረሻው ቀን እንደሆነ ተናግሮአል፦
"ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።" ዮሐ 6፥ 39-40
የመጨረሻው ቀን መቼ ነው? ለአይሁድ ጊዜ የሙሴ ዘመን እና የመሲሁ ዘመን ተብሎ በሁለት ታላላቅ ክፍለ ጊዜ ይከፈላል። መሲሁ አዲሱን አለም አዲሱን ዘመን እንደሚያመጣ ነው በአይሁድ የሚታየው። ስለዚህም የመሲሁ ዘመን በምኩራብ ዘንድ "የሚመጣው አለም" በሚል መጠርያውና ገጽታው በትክክል ይታወቃል። በመላው አዲስ ኪዳን ውስጥ "ይህ ዘመን" እና "የሚመጣው ዘመን" የተሰኙ ሁለት ዘመናት በንጽጽር ሲቀርቡ እናያለን።
" ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን ... ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ" 1ጴጥ 1፥ 20
ኢየሱስ የመጣውም ሆነ የሙታን ትንሳኤ የሆነው የአይሁድ ዘመን በሆነው የብሉይ ኪዳን ዘመን በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው። ዘመኑም የተፈጸመው በ70 አ.ም በኢየሩሳሌም ውድመት ነው። ዳንኤል 12 የሚናገረው ይህንን ነው። ትንሳኤ የሆነው ዳንኤል 12 በእውነትም ግልጽ እንደሚያደርገው በአሮጌው ኪዳን ዘመን መጨረሻ ላይ ነው።
በጎትነ ይሙባችሁ!
ቄስ ግዛቸው ከበደ
No comments:
Post a Comment