ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ዘመንና ትውልድ ሲወስንና፣ ተከታዮቹም የትንቢቱን ፍጻሜ እርሱ ባመለከታቸው የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ እንዲጠባበቁ ሲያመለክታቸው፣ ጌታ ኢየሱስ ፈጽሞ አልተሳሳተም ነበር። እርሱ ስለ መመለሱ የተናገረውን የትንቢት ቃል ለማብራራት 'ዘግይቶ የመፈጸምን አስተምህሮ' ወይም የመመለሻውን ጊዜ የሚያራዝምና በመቶዎችና በሺህዎች አመታት ለሚቆጠር ለሌላ የተራዘመ ጊዜ የሚያስተላልፍ 'ስነ መለኮታዊ መተጣጠፍ' እየሰራን ትንቢቱን ማቃናትም ሆነ ድጋፍ ልናደርግለት አያስፈልገንም፣ አይገባንምም። "ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም" (ማቴ 24፥ 35) ተብሎ እንደተጻፈ፣ የትንቢቱ ቃል ብቻውን በራሱ የቆመና ራሱን የሚተረጉም ነው። ትንቢቱ ተፈጻሚ ስለሚሆንበትም ጊዜ በራሱ ግልጽና እርግጠኛ ነው። ነብዩም ሆነ የትንቢቱ ቃል ለእውነተኝነታቸው ታማኞች ናቸው።
ሁሉም ነገር ተፈጻሚ የሆነው፣ "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" (ማቴ 24፥ 34)፣ "ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል" (ማቴ 23፥ 36)፣ "የሰው ልጅ በመንግስቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ" (ማቴ ) በሚል አነጋገር በተገለጠ፣ በተቀጠረው ዘመንና በተያዘለት መርሃ ግብር ነው። እንደዚያ ካልሆነ መሰረታዊ እምነታችን ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ማለትም፦ ኢየሱስ ያኔ ለተከታዮቹ "በቶሎ እመጣለሁ" (ራእይ 22፥ 12) ብሎ ለእነርሱው በትውልዳቸው ውስጥ በቶሎ ካልመጣ፣ ይልቁንም ከሺሆች አመታት በኋላም የምጽአቱ ተስፋ ሳይፈጸም ዘግይቶና ለሌላ ላልታወቀ ጊዜ ተላልፎ ገና አሁንም እየተጠበቀ ከሆነ፣ ወይም ከናካቴው ቀርቶ አልያም መምጣት አቅቶት ከሆነ፣ በአንጻሩም እኛም ለእነርሱ በትውልዳቸው ሳይመጣ የቀረውን ገና ወደፊት እንደሚመጣ አሁንም የትንቢቱን መፈጸም እየተጠባበቅን ተስፋ የምናደርግ ከሆነ፣ የምጽአቱን ተስፋ "እስካሁን ያልፈጸመ ኢየሱስ" እንዴት አዳኛችን ሊሆን ይቻለዋል? በማቴዎስ 24 ትንቢቱና ተስፋው ልንጠረጥረው ከተፈተንን በዮሐንስ 3፥ 16 ተስፋውና ስጦታውስ እንዴት ልንታመነው ይቻለናል? ይህንን በበቂ የሚመልስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ከሌለን እንዲሁ በሜዳ "ይመጣል" ስላልን ብቻ ክርስትናችንን ከከሃዲዎች ነቀፋና ትችት መከላከል አንችልም።
በርካታ የስነ መለኮት ሰዎች በ70 አ.ም ላይ የሆነውን የኢየሩሳሌምን ውድመትና የቤተመቅደሱን መፈራረስ በተመለከተ በእግዚአብሔር የደህንነት ታሪክ መርሃ ግብር ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት በግርድፉ ቢያውቁም ቅሉ፣ ሙሉ ዋጋ የሚሰጠውን ትርጉም ግን አያስተውሉትም። በ70 አ.ም በእስራኤል ህዝብ ላይ የደረሰው እልቂተ መቅሰፍትና፣ በኢየሩሳሌም ከተማና በተወደደው ቤተመቅደስ ላይ የመጣው ውድመት /Anathema/ አጠቃላይ ተዛምዶውና ግንኙነቱ የደህንነት ታሪክ እቅድ በዳግመኛ ምጽአቱ ተጠቃሎ ከመፈጸሙ /Maranatha/ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው።
እግዚአብሔር ከዘላለም ያቀደው የደህንነት ታሪክ ተመርቆ የተሰጠው በመስቀሉ ስራ ሲሆን ትእይንቱ ተጠናቆ በይፋ የታወጀበትና የተገለጠበት የመጨረሻ ሁነት ሐዋርያቱ በነበሩበት በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ትውልድ በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌምና በቤተመቅደሱ ላይ በሆነው ፍርድና ጥፋት በተገለጠው ምጽአቱ ነው። ሐዋርያቱ በጽሁፎቻቸው እየደጋገሙ እንዳስተማሩት መዳናቸው እንደተፈጸመና ደግሞም ገና እንደሚፈጸም አይነት ያመለክቱ ነበር። ወደ መስቀሉ የነበራቸው የእምነት እይታ እና ወደ መጻኢው ክቡር የምጽአቱ ተስፋ የነበራቸው የመጠባበቅ እይታ አዲስ ኪዳን በብዙ ዋና ዋና ትምህርቶቹ የሚያንጸባርቀው ግልጽ አሳብ ነው። በትውልዳቸው ውስጥ ሲጠባበቁት የነበረው ትንቢት ፍጻሜውን ያኔውኑ አግኝቶአል። ብዙዎች ግን አሁንም ደግሞም በየዘመናቱ ይህንን ፍጻሜና ምጽአቱን "በቅርቡ ይሆናል" እያሉ ገና ወደ ፊት ይጠባበቁታል፤ ሁልጊዜም በቅርቡ ይመጣል እያሉ ለዘመናት "ማራናታ" ሲሉ እንደሚናገሩ ልብ ይሏል። ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ እንደሚፈጸም ይጠበቅ ከነበረውና ያኔውኑ ተፈጽሞ ካለፈው የተለየ "ማራናታ" ወይም ገና ወደ ፊትም ፍጻሜውንና የምጽአቱን ተስፋ እንድንጠብቅ የሚገፋን አንዳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትም ሆነ ሳይፈጸም የቀረ ሌላ ምንም ተስፋ በቅዱስ ቃሉ ውስጥ የለም። ተስፋ የነበረው ነገር ሁሉ አሁን ተገኝቶአል እንጂ ተስፋ መሆኑ አልፎአል።
እንደው ለመሆኑ ቃሉን አክብረን "ትንቢት ተፈጽሟል" ብለን ብንቀበል፣ "ጊዜ መዳቢ" (dispensationalist) ከሆኑ ቅዠታም መምህራን፣ መያዣ መጨበጫ ከሌለው የተሳከረ ትንታኔአቸው፣ የወንጌሉንም ማጽናናት ከማናገኝበት የአሸባሪነት ትምህርታቸውና ከሐሰተኛ ትንቢታቸው እናርፋለን እንጂ ምን ይለናል? ምንስ ይቀርብናል? በምእራቡ አለም ያሉ "ትንቢት ገና ይፈጸማል" ባይ የሆኑ እና የእነርሱን አስተንትኖ የሚከተሉ የሦስተኛ አለም አገሮች ሰባክያን በሚያዘጋጇቸው የጽሁፍና የኦዶ ቪዥዋል ገበያ ከሚገባው በላይ ቢዝነስ እየሰሩበት ሰለሆነ፣ አሳማኝ ማስረጃዎችን በተሞላውና በሚፋጠጣቸው ስነ መለኮታዊ ተግዳሮት እውነቱን ቢያውቁ እንኳ ላይቀሰቀሱ አውቀው ተኝተዋል። ምክንያቱም ለዘመናት የገነቡት ልማዳቸው ከስሩ ቢናድ ምናልባት እዚያ ላይ የመሰረቱት የደራው ገበያቸውም ይወድቃልና ነው።
የምጽአቱ ተስፋ (parousia) ያኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ላይ ሲነገር ያኔውኑ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ፣ በጣም በቅርቡ ማለትም በ70 አ.ም ላይ ከመሆን የማይቀር፣ ቀንም የተቆረጠለት ጉዳይ ነበር እንጂ፣ 2000 አመታትና ከዚያ በላይ ተራዝሞ አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ሆነ ወይም ገና ወደ ፊት የሚጠበቅ የዘገየ ተስፋ አይደለም። ሁሉም የመጻኢነት የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ፈተናውን የወደቀው አጠቃላይ የሆነውን የዳግመኛ ምጽአቱን ባህርይና ይህንን ጊዜ ተኮር የሆነ የአዲስ ኪዳንን የቋንቋ አጠቃቀም እውነታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነጥብ ላይ ነው።
እኛ ኃላፋውያን (preterists) ነገረ ፍጻሜን (eschtology) ስናስብ የምናስበው ለሁነቱ መፈጸም በመለኮት የተሰጠውንም የጊዜ ማእቀፍና ቀነ ቀጠሮውንም ጭምር ነው። እንደዚህ እንደምናስብ የማይረዳንን ሰው ማስረዳት በእውነት አስቸጋሪ ነው። ሁሉም የመጻኢነት (Futurists) የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮም ፈተናውን የወደቀው አጠቃላይ የሆነውን ይህንን የዳግመኛ ምጽአቱን ባህርይና ጊዜ ተኮር የሆነውን የአዲስ ኪዳንን የቋንቋ አጠቃቀም እውነታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነጥብ ላይ ነው። በውጭ ካሉት ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛነትና በትምህርቱ ላይ የሚሰነዘር ትችትና ጥቃት በግሌ አያስፈራኝም፤ "ያመንኩትን አውቃለሁ" ተብሎአልና። ይልቁንም የሚያስፈራኝ ለዚህ ትችትና ስድብ መጻኢያን የሚሰጡት እርስ በርሱ የተሳከረ ምላሽ ነው። ከዘመናዊው "መንፈሳዊ" እንቅስቃሴ ባልተናነስ የምእራቡን አለም አብያተ ክርስቲያናት ጠርጎና ባዶ አድርጎ ለክህደት የተዋቸው ይኸው የተንሸዋረረ የመጻኢነት ነገረ ፍጻሜ ነው።
የመጻኢነት አመለካከት በሚያቀነቅነው "ያልተፈጸመና የዘገየ ተስፋ" አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ የተናገሩትን የትንቢት ኣቃል እውነተኛነቱን ማረጋገጥም ሆነ ክርስትናችንን ከጥቃትና ከስድብ መከላከል ከቶውንም ቢሆን አይቻለንም። የኖሩና እድሜ ጠገብ የሆኑትን ተረቶቻችንን ታጥቀን ክህደትንና የለዘብተኛውን ስነመለኮት ልንጋፈጠውም አንችልም። እስቲ በአገራችን ለንባብ የበቁትን ምጽአት ተኮር የሆኑ መጻህፍት እዩአቸው፣ በእውነት እነዚያ የህትመት ስራዎች የያዙት ፍሬ ከርስኪ እየመጣና እያደባ ካለው የክህደት ጅብ ያስጥሉናል? ከቶውንም አያስጥሉም! ወደ ቃሉ በንስሃ እንመለስ! ኃላፋውያን (Preterists) ግን በትንቢት መጻህፍት ላይ የሚያቀርቡት የትርጉም ቀዋሚነትን መሰረት ያደረገው ትንታኔና ተስፋውም በመለኮት በተያዘለት መርሃ ገብሩ እና በጊዜ ቀጠሮው እንደ ተፈጸመ ለማስረገጥ ራሱን የቅዱሱን መጽሐፍ ቃል እና ታሪካዊ ማስረጃዎችን መሰረት ማድረጋቸው በስነ ፍታቴ መርህ የሚረጋገጥ ንጹህ ትምህርት ነው። ስነ መለኮትን ሙያቸው ያደረጉ ሰዎች ይህንን በወጉ እንዲያስቡበት በማትሰማዋ ትንሿ ድምጼ እጣራለሁ።
በኃላፋዊው ነገረ ፍጻሜ የሚስተጋባው የተፈጸመ ትንቢትና የተጨበጠ ተስፋ የሚሰጠውን መጽናናት በእምነት እያጣጣምን፣ ከዚህ ሥጋችን በሞት ተለይተን በተሰጠን የዘላለም ሕይወት ሙሉ ደስታ በቅጽበት አይን እስክንወሰድ ድረስ፣ በዚህ ህይወት አሁን በምድር ላይ የክርስትናችንን ግርማና ክብር እንለማመደው። የክርስቶስ መንግስት፣ እርሱም መንፈሳዊ መንግስት አሁንና እዚህ ነው፣ ዮሐ 18 36። ወደ ሕይወት መግባት አሁን በክርስቶስ ተሰጥቶናል፣ በክርስቶስ ያገኘነው አዲሱ ሕይወት፣ ይህ ክርስትናችን፣ ዘላለማችን፣ አዲሱ ሰማይና ምድር ነው። አሁን የምንኖርበት ይህ አዲሱ ኪዳን፣ አዲሱ የጸጋና የእውነት ሥርአት በሙሉ ክብሩና ዋጋው በሚሰለጥንበት በአዲሲቱ በኢየሩሳሌም፣ እንደ እግዚአብሔር እስራኤል አዲስ ፍጥረት ሆነንም የምንኖርበት መንፈሳዊው ግዛት ነው። ከሞትንም በኋላ በሞት የማይቋረጠውን፣ በላይ በሰማያት የሚቀጥለውን የዘላለም ሕይወት አሁን አግኝተናል። ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ በማያልቅ ሰላም የተሞላውንና ፍጻሜ የሌለውን ዘላለማዊ መንግስቱን በሙላት ሰጥቶናል፣ (ኢሳ 9፥ 6-7)።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለራሱ ደቀ መዛሙርት በገባላቸው የተስፋ ቃል መሰረት ያኔውኑ በትውልዳቸው ውስጥ ብድራታቸውን ሊከፍላቸው በአባቱ ክብር እንደመጣ፣ ጠላቶቹንም የእግሩ መረገጫ ሊያደርግ በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ከተማ ውድመትና በቤተ መቅደሱ ጥፋት በፍርድ እንደተመለሰ፣ ቅዱስ ቃሉ አረጋግጦልኛል፤ ታማኝ የታሪክ ምንጮችም አጽንተውልኛል። ይህንን ለማስተባበል የሚበቃ አንዳችም ትምህርት የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ቅዱሳን ሆይ፣ ይህንን የምጽፈው በቅድሚያ ለህሊናዬ ነው፤ በእግዚአብሔርም ቃል እንድትሞግቱኝ እጋብዛለሁ። የቃሉ ተማሪ የሆነ ማንም አማኝ ቢሆን እነዚህን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑና ስለ ምጽአቱ የሚናገሩትን የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች በጠያቂ የአንባቢነት ደረጃ እያነበበ ለተፈጻሚነታቸው ጥቅሶቹ በራሳቸውና በአውዳቸው ውስጥ የቋጠሩትን "ጊዜ ቀጠሮ" እንዳላየ ሆኖ ማለፍ አይችልም። እኔ በግሌ እንደዚያ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ተፈትኛለሁ፣ ቃሉን ግን መሸወድ አይቻልም። አሁን እንኳ ብዙዎቻችሁ ይህንን እያነበባችሁ በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ መሆናችሁን እረዳለሁ። ገሚሶቻችሁም እንደሳትሁ ያህል በፍቅር ታዝኑልኛላችሁ፣ አንዳንዶቻችሁም ቄሱን ምን ነካው ስትሉ ትቆጡኛላችሁ። በእውነት ስሜታችሁን ለመረዳት ነብይ መሆን አያስፈልገኝም፣ ፈተናችሁ በአንድ ወቅት ፈተናዬ ነበርና። በፍቅር የምንይዘው እውነት እንጂ ስለፍቅር የምንሸጠው እውነት የለንም። "እውነትን ግዛት አትሽጣትም" ተብሎአልና።
የመጻኢነት አመለካከት በሚያቀነቅነው ያልተፈጸመ ትንቢትና የዘገየ ተስፋ አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ "በቶሎ"፣ "በቅርቡ"፣ "ሳይዘገይ" ይሆናልና ይፈጸማል ሲሉ የተናገሩትን የትንቢት ቃል ገና ወደ ፊት ይፈጸማል ብሎ በመናገር እውነተኛነቱን ማረጋገጥም ሆነ፣ ክርስትናችንን ከጥቃትና ከስድብ መከላከል ከቶ አይቻለንም። ኃላፋውያን ግን በትንቢት መጻህፍት ላይ የሚያቀርቡት የትርጉም ቀዋሚነትን የሚከተለው ትንታኔና ተስፋውም ያኔ ድሮ ለመጀመርያይቱ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠና እንደተፈጸመ ለማስረገጥ ራሱን የቅዱሱን መጽሐፍ ቃል እና ታሪካዊ ማስረጃዎችን መሰረት ማድረጋቸው በስነ ፍታቴ መርህ የሚረጋገጥ ንጹህ ትምህርት ነው።
የምጽአቱ ተስፋ (parousia) ያኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ላይ ሲነገር ያኔውኑ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ፣ ከቤተመቅደሱ ውድመትና ከአሮጌው ስርአት ማብቃት ጋር ተጣምሮ ያለ፣ በጣምም በቅርብ ጊዜ ማለትም ያኔ በዚያው የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት በ70 አ.ም ላይ የሚፈጸም፣ ከመሆን የማይቀር፣ ቀንም የተቆረጠለት፣ ለሌላ ጊዜ የማይተላለፍ ጉዳይ ነበር እንጂ፣ 2000 አመታትና ከዚያ በላይ ተራዝሞ አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ሆነ ወይም ገና ወደ ፊት የሚጠበቅ የዘገየ ተስፋ አይደለም አልነበረምም።
ለነፍስ ሙሉ መጽናናትን የሚሰጠው የተፈጸመ የትንቢት ተስፋ የነፍስን ሃዘን ከሚጨምረውና ከሚያባብሰው የዘገየ ተስፋ ይልቅ ሺህ ጊዜ ይመረጣል። "ማራናታ" በምንም ሂሳብ የእኛ የዚህ ዘመን ምእመናን መዝሙር ሊሆን አይችልም። የምጽአቱን ናፍቆትና መጠባበቅ የተሞላ ይህ " አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና" የሚል ጸሎትና ዝማሬ ተስፋ በተገባላቸው መሰረት ላይ ቆመው ለተስፋው መፈጸም በብርቱ መከራ ውስጥ በነፍሳቸው እየተወራረዱ ለለመኑትና ለጸለዩት ሰዎች ያኔውኑ ተመልሶላቸዋል። ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ መጥቶአል። በእውነት ከመከራው ጽናት የተነሳ ያለቀሱ እነርሱ ነበሩ፤ እንባዎቻቸውን ሁሉ ከአይናቸው ሊያብስ ፈጥኖ የሚፈርድላቸው የሚራራና አፍቃሪ ጌታ እንጂ፣ 2000 አመት የሚያስጠብቃቸው ጨካኝና ዳተኛ ጌታ አልነበራቸውም። " እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?" (ሉቃ 18፥ 7-8) እንደተባለ፣ ፈጣን ፍርዱ /Anathema/ እና ዳግመኛ ምጽአቱ /Parousia- Maranatha/ አብረው የተቆራኙ ኹነቶች ናቸው። ስሙ ለዘላለም ከፍ ይበል።
ቄስ ግዛቸው ከበደ
ለተጨማሪ መረጃ philologus66 የተሰኘውን የፌስ ቡክ ገጼን ይጎበኙ ዘንድ እጋብዛለሁ።
Tuesday, November 28, 2017
ማራናታ ተፈጽሞአል!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment