@ "M/D/YYYY"12/27/2016.
አስተምህሮተ ትንሳኤ "የሚሻል ትንሳኤ" መግባብያ ፩
አካላዊ ትንሣኤን (በሥጋ መነሳትን) በተመለከተ የሚናገሩ ምንባባት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አለው፣ እነዚህም ምንባባት ከጥቂቶቹ በቀር በዋናነት የራሱን የኢየሱስ ባዮሎጂካል ትንሳኤ የሚያመለክቱ ናቸው። ሆኖም ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አካላዊ ያልሆነን የትንሳኤ ተፈጥሮን የሚያመለክቱ በርካታ ምንባባት ያሉ መሆናቸው ደግሞ አግራሞትን ይፈጥራል። ይህ አይነቱ የትንሳኤ አይነት ደግሞ፣ የሙታን ትንሳኤ ማለት የሙታን በድኖች ከምድር ጉድጓድ ከመቃብራቸው ውስጥ ወጥተው የሚመጡበት አይነት ብቻ እንዳልሆነ ግንዛቤን ያጭራል።
ይህ አይነቱ የትንሳኤ ተፈጥሮ በኃጢአት ከሚሆን መንፈሳዊ ሙትነት ወደ አዲሱ ኪዳን መንግስት የዘላለም ሕይወት የሚያሻግር ትንሳኤ ነው። እነዚህም ትንሳኤ ተኮር የሆኑ ምንባባት አካላዊ ትንሳኤን በተመለከተ ከተነገሩት ይልቅ በቁጥር እጅግ የሚበዙ መሆናቸው ጠያቂ ለሆነ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝና ተማሪ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከምድር ጉድጓድ ከመቃብር ውስጥ የሚወጣ አካላዊ ትንሳኤን የማያምኑና የማያስተምሩ በርካታ የመጻኢነት ነገረ ፍጻሜን የሚከተሉ ተርጓሚዎች እንኳ እንዳሉ ብዙዎች አይገነዘቡም። ስለዚህ የተለየውን አይነት ትንሳኤ የሚያስተምሩ ኃላፋውያን ብቻ አይደሉም ማለት ነው።
አካላዊ የሆነው የኢየሱስ ትንሳኤ በዋናነት "ሥጋው መበስበስን እንዳያይ" (ሐዋ 2፥ 27) ለእርሱ ለቅዱሱ ብቻ የተገባለትን የተስፋ ቃል ፍጻሜ የሚሰጥ ኃይለኛና ብርቱ ስራ (ኤፌ 1፥ 19-21) የሆነውን ያህል፣ የኢየሱስ ከሆነው ከአካላዊው ትንሳኤ ባልተናነሰ ደግሞ ኃይለኛና ብርቱ እንደሆነ የተነገረለት ሌላ የነገረ ፍጻሜአዊ ትንሳኤ /Eschatological Resurrection/ አይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ይገኛል።
ለጥናታችን እንደ መግቢያ ይሆነን ዘንድ በሁለት ቀዳሚ ክፍሎች በምንመለከተው በዚህ የመግባቢያ ጥናት በቀላሉ የተወሰኑ ጥቅሶችን እያነሳን እንወያያለን። ለሚነሱት የጥናት መምሪያ ቀላል ሃሳቦች በምክንያታዊነት ጨዋነትን ለተላበሰ ውይይት ክፍት ሆኖ መቅረብና ቃሉን ብቻ ያማከለ ትጋት ወደሚፈለገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድምዳሜ ያደርሳል የሚልም ተስፋ አለኝ።
ክፍል 1
1ኛ/ እብራውያን 11፥ 35 " ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤" ሲል ይነግረናል
እነዚህ ሴቶች በዘመናቸው አካላዊ ትንሳኤን መስክረዋል። ይህም እውነት ነው ምንም ጥርጥር የለውም። "ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤" በብሉይ ኪዳን ቢያንስ ሁለት ሴቶች አሉ ሙታኖቻቸውን እንደገና በትንሳኤ የተቀበሉ። ኤልያስ ልጅ የሞተባትን የሰራፕታዋን ባልቴት ልጅዋን ከሞት አስነስቶላታል (1ነገስት 17፥ 17-24)። ኤልሳዕም ልጅ የሞተባትን የሱናማዊቱን ሴት ልጅዋን ከሞት አስነስቶላታል (2ነገስት 4፥ 18-37)። የነብያቱ እምነትና አገልግሎት እነዚህን ልጆች ከሞት መልሶአቸዋል። በአዲስ ኪዳንም ኢየሱስ ማርታ እና ማርያም ለተሰኙ እህትማማቾች ወንድማቸውን አልአዛርን (ዮሐንስ 11፥ 43-44)፣ ከናይን ከተማ ለነበረችው መበለት አንድ ልጅዋን (ሉቃስ 7፥ 13-15)፣ ከሞት አስነስቶላቸዋል። ጳውሎስ ግን ለእብራውያን ክርስቲያኖች "የሚበልጠውን ትንሣኤ" ብሎ በሚጽፍበት ጊዜ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ "ይህ ትንሳኤ ከየትኛው ትንሳኤ የሚበልጥ ነው?" የሚል ነው። መልሱም እነዚህ ሴቶች ከተለማመዱትና በነብያቱ አገልግሎት በልጆቻቸውና በሚወድዱአቸው ላይ ሲፈጸም ካዩት አካላዊ ወይም ባዮሎጂካል ከሆነውና ጊዜአዊ ከሆነው የትንሳኤ አይነት ነው። ታዲያ ከዚህ አይነቱ የሚበልጠው ትንሳኤ የትኛው ትንሳኤ ነው? በግልጽ ቋንቋ ለመናገር እንዲህ ካለው ትንሳኤ የሚበልጠው ትንሳኤ የአካላዊውና የተዳሳሹ ትንሳኤ ተቃራኒ መንፈሳዊና ዘላለማዊ የሆነው ትንሳኤ ነው፤ ይኸውም ሰው ከፈጣሪው ጋር በሰማያዊው አገር ዘላለማዊ በሆነው እርቅና ህብረት የሚደሰትበት የእግዚአብሔር ሕይወት ነው።
የሆነው ሆኖ ልክ እንደነዚሁ ሴቶች...... ሌሎች ደግሞ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ ተስፋ አድርገዋል። ይህም እውነት ነው።
ይህ ጥቅስ የሚነግረን አንድ እውነት አለ፣ ይኸውም እነዚያ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን በሆነ አይነት የትንሳኤ ተስፋ ያምኑ እንደ ነበር ነው፤ ይሄ ደግሞ ከዚያ የሚበልጥና የሚሻል እንጂ የግድ አካላዊ (ጊዜአዊ) መሆን አያስፈልገውም። ለምሳሌ፦ ማርታ እንደዚያ ታምን ነበር፤ ኢየሱስ "ወንድምሽ ይነሳል" ባላት ጊዜ "በመጨረሻው ቀን በትንሳኤ እንዲነሳ አውቃለሁ" ( ዮሐ 11፥ 23-24) ከሚለው መልስዋ የምንረዳው በአይሁድ ዘንድ ይታመን ስለነበረው የትንሳኤ አይነት ነው።
ይህንን "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" የተሰኘ ቁልፍ ቃል በመላው የእብራውያን መልእክት ውስጥ ያለውን ቦታ ልብ በሉ፤ ለአዲስ ኪዳን በረከቶችና ትሩፋት ሁሉ መግለጫ የሆነ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተገለጡና ጉድለት ካለባቸው የህጉና የስጋ ከሆኑ ነገሮች ሁሉ የአዲስ ኪዳኑን ስጦታ ከፍ አድርጎ የሚለይ ቃል ነው። "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" በተሰኘ ደረጃ በእብራውያን መልእክት ውስጥ የተገለጡ የአዲሱ ኪዳን ስጦታዎች በሙሉ ደግሞ በክርስቶስ የተገኙና የተያዙ ነገሮች እንጂ ገና በብዙ ዘመን ርቀት የሚጠበቁ መጻኢ ተስፋዎች አልነበሩም፤ ለምሳሌ፣ የሚበልጥ ሊቀካህን፣ የሚበልጥ ኪዳን፣ የሚበልጥ መስዋእት፣ የሚሻል አገልግሎት ወዘተ። "የሚበልጥ ትንሳኤ" ኢየሱስ የእኛ ብልጫ! ለማርታ እንዲህ ሲል የሚበልጠውን ትንሳኤ አረጋግጦላታል "ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም"
2ኛ/ ዘፍጥረት 2፥ 16-17 " እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።" የሚል ቃል እናነባለን፤
እግዚአብሔር አዳምን ከእውቀት ዛፍ እንዳይበላ ከልክሎታል። ይህም እውነት ነው። እግዚአብሔር ያስጠነቀቀው በበላህ ቀን "ሞትን ትሞታለህ" ብሎ ነው። ይህም የእግዚአብሔር እውነት ነው። የዲያብሎስ ውሸት ግን "ሞትን አትሞቱም" የሚል ነበር።
3ኛ/ ዘፍጥረት 3፥ 6 " ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።" ይላል፤
አዳም እግዚአብሔርን ያልታዘዘው ከተከለከለው የዛፍ ፍሬ በመብላት ነው። ሔዋንም ደግሞ ከዛፉ ፍሬ ከባልዋ ጋር አብራ የበላች እስከሆነ ድረስ ሁለቱም በፈጸሙት ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እኩል ጥፋተኞችና ለሞት ተጠያቂዎች ናቸው።
4ኛ/ ዘፍጥረት። 3፥ 22 - 4፥2ሀ "እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ። አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም፦ ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች።" የሚል ቃል እናነባለን፤
አዳምና ሔዋን የተከለከለውን የዛፍ ፍሬ በበሉበት በዚያው ቀን አካላዊ ሞትን እንዳልሞቱ እናውቃለን። ነገር ግን.... አዳምና ሔዋን ያኔውኑ ከእግዚአብሔር ፊት ከህልዎቱ ተነጥለዋል፣ (3፥ 8 ጀምሮ ተመልከቱ) ይህ ነው የሞቱት ሞት እውነቱ፣ በጠላትነት መለየት።
የተከለከለውን የዛፍ የፍሬ በበሉ ቀን ኃጢአትን የሰሩ እስከሆነ ድረስ (ኃጢአት ህግን መተላለፍ መሆኑን አትርሱ [1ዮሐንስ 3፥ 4 ተመልከቱ]) በዚያው ቀን ደግሞ አካላዊ ሞትን ባይሞቱም፤ በዚያው ቀን ግን ከእግዚአብሔር ፊት ክህልዎቱ ተነጥለው እንዲወጡ ተደርገዋል፣ ሰለዚህ በኃጢአታቸው ምክንያት የመጣባቸው መዘዝ ሆኖ በዚያኑ ቀን የሞቱት ሞት መንፈሳዊ ሞት እንጂ ስጋዊ/አካላዊ ሞት አልነበረም። በኢሳይያስ 59፥ 2 ያለውን ተመልከቱ፦ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። ይኼ ነው የሕይወት ትንሳኤ የሚያስፈልገው የዘላለም ሞት።
5ኛ/ ያዕቆብ። 1፥ 15 "ኃጢአትም...... ሞትን ትወልዳለች።" ይላል። በሮሜ 6፥ 16 ደግሞ ጳውሎስ "ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?" ሲል ይጠይቅና "ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ።" ሲል ይመልሳል፤ በ6፥ 23 ላይም የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።" ብሎ ይናገራል። ከዚያም በ7፥ 13 ላይ "ኃጢአትም...... ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር።" ሲል የናገራል። በመጨረሻም በ7፥ 24 ላይ " ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?" ሲል ይጮሃል።
ኃጢአት የሞት ውጤት አለው፤ ስለዚህም ኃጢአት በጳውሎስ ውስጥ ሞትን አስከትሎአል። እውነቱ ይህ ነው። ጳውሎስ ከዚህ ሞት የሚያድነውን ፈልጎ ገና እየጮኸ ባለበት ጊዜ እንኳን በስጋው በህይወት ነበር።
ሰለዚህ ይህ "ሞት" - ማለትም ይህ "መንፈሳዊ የሆነ መለየት"፣ ይኸውም "ከእግዚአብሔር ሕይወት መለየት" የተባለው ሞት (ሞት ማለት "መለየት" ማለት ነው፤ የመዝገበ ቃላትን ፍቺና ኢሳይያስ 59፥ 2 ያለውን ተመልከቱ) ቀጥተኛው የኃጢአት ውጤት ነው፣ እርሱም ገና በስጋ በሕይወት እያለንና እንዲሁም ስጋዊውን ሞት ከሞትንም በኋላ ልንለማመደው የምንችለው ሞት ነው።
"ሙታንን ተዉአቸው ሙታናቸውን ይቅበሩ" ያለእግዚአብሔር ሕይወት፣ ሟችም ቀባሪም ያው ተሰብስበው ሁሉም ሙታን ናቸው። ይህ ነው እውነቱ።
ቀጥተኛ የሆነውና ወዲያውኑ የሚመጣው የኃጢአት ውጤት የሆነው ሞት (ይኸውም ኃጢአት እንደ አዳምና ሔዋን ሁሉ እኛም ገና በስጋችን እየኖርን ሳለን የፈጸምነው ነው)፣ በእውነትም "የሞት ኃጢአት" ወይም "የኃጢአት ሞት" ወደ መሆን ይለወጣል። እግዚአብሔር በውድ ልጁ ሞት የሻረውንና መፍትሔ የሰጠውን የሞትን አይነት ተፈጥሮና ምንነቱን በቅጡ ያላወቀ ማንም ሰው ቢሆን የሙታንን ትንሳኤ ተፈጥሮና ምንነት ጊዜውንም ጭምር የማያውቅ ይሆናል።
6ኛ/ 1ቆሮንቶስ 15፥ 21-22 "ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።" ሲል ጳውሎስ ይነግረናል። ከዚያም በቁጥር 56 እና 57 ላይ " የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።" ሲል ይጽፋል።
አዳም ሞትን እንዳመጣብን ሁሉ ፣ ኢየሱስም እንዲሁ ሕይወትን አመጣልን። ይህ ነው የወንጌል እውነት። በአዳም ጦስ መዘዝ ሆኖ የመጣው ሞት 'የኃጢአት ሞት' ወይም 'የሞት ኃጢአት' ነው። በ "አዳም" ከሆነውና ከተገኘው ሞት (በማንኛውም ሞት ውስጥ እንደሚሆነው ሁሉ) ድኖ እንደገና በሕይወት መኖር የሚቻለው በትንሳኤ አማካኝነት ብቻ ነው - ይኸውም በ"ክርስቶስ" የሚገኝ 'የትንሳኤ ሕይወት' ወይም 'የሕይወት ትንሳኤ' ነው።
ሰለዚህ....... ያሉት ሁለት አካላት ናቸው፣ እነርሱም፦ የሞት ወይም የአዳም አካል (ሮሜ 7፥24) እና የሕይወት ወይም የክርስቶስ አካል (ዮሐንስ 1፥4) ናቸው። ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ "እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።" ስለዚህ በአንድ ወቅት ያጣነውን መንፈሳዊ ሕይወት መልሶ የሚሰጠውንና የሚመሰርተውን የእግዚአብሔርን አሰራር በአጭሩ አብራርተን እንመልከት።
7ኛ/ ቆላስይስ 3 ፥ 13ሀ ላይ "እናንተም በበደላችሁ... ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፤" የሚል እናነባለን። እንደዚሁም ኤፌሶን 2፥ 1 እና 5 " በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ " ይልና፣ "በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥" ሲል ይናገራል። ሰለዚህ ይህንን ከኃጢአት መዳንን አስመልክቶ ጳውሎስ በቁጥር 8 ሀ ላይ " ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ " ሲል ይጽፋል።
እነዚህ ቅዱሳን ጳውሎስ መልእክቱን በጻፈላቸው ጊዜ ገና በስጋ አልሞቱም ነበር፣ አካላዊ ከሆነው ሞትም ደግሞ ገና አልተነሱም ነበር። ይህ ፊት ለፊት ያለው እውነት ነው። ሰለዚህ....... እነዚህ ቅዱሳን በግልጽ እንደሚታወቀው (ኃጢአትን በተመለከተ) የሞቱ ነበሩ (ከእግዚአብሔር ተለይተው ነበሩ)፣ ነገር ግን (ከእግዚአብሔር ልጅ የተነሳ) ከእግዚአብሔር ጋር (ሕብረት በማድረግ) አንድ ለመሆን በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ከሞት ተነስተው ነበር። ይህም የተሃድሶ ስራ የተፈጸመው የእግዚአብሔር ልጅ በፈጸመው የመስቀል ስራ ላይ ባላቸው እምነት ነው
ኢየሱስ ለአማኞች "ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ" (ዮሐንስ 11፥ 25) አላቸው እንጂ፣ ትንሳኤ ከመሬት ውስጥ ቡልቅ ብሎ መውጣት ነው አላለም፤ "የሚያምንብኝም ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም" (ዮሐንስ 11፥26) አለ እንጂ መቃብርን አያይም አላለም። እንደውም ሳይሞቱ ተለውጦ በአየር ላይ እየተንሳፈፉ ወደ ሰማይ መብረርንም የሚናፍቁ የንጥቀት ተስፈኞች አይጠፉም፣ (ንጥቀትንና ትምህርቱ የተሰኘውን ጽሁፍ ጨምራችሁ በዚሁ ገጽ ላይ እንድታዩት እመክራለሁ)። "ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣም" ሆነ የሚወጣ "ማንም የለም፣ እርሱም የሰው ልጅ ነው"። በእውነት ሁላችንም "ትንሳኤና ሕይወት" በሆነው በኢየሱስ ያመንን ሕያዋን ሆነን የብጽዕናን ሞት እንሞታለን፣ ብንሞትም እንኳ በዮሐንስ ራዕይ 14፥ 13 "ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። .... አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል" ተብሎ እንደ ተጻፈ ለዘላለምም በብጽእናና በትንሳኤ እንኖራለን።
ከእንግዲህ ወዲህ እኛ ያመንን በጌታ እንሞታለን እንጂ በኃጢአት አንሞትም። ሕያው ከሆነው ከኢየሱስም የተነሳ ለዘላለም ሕያዋን ነንና። ሕያዋንም ሆነን "ስሞት ወደ ጌታ እሄዳለሁ" በሚል ዝማሬ በብጽእና ስንበት ሕያዋንን ወደ ጌታችን እየሸኘን በብጽዕና የሞታችንን ጊዜ የምንጠብቅ ሕያዋን ነን እንጂ ሙታናችንን የምንቀብር ሙታን አይደለንም። መቼም ቢሆን ቤተክርስቲያን አባሎችዋን በሞት የምርት አትሆ።
ትንሳኤ በዋዛ የሚታይ ቀላል ጉዳይ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስና የክርስትና አንዱና መሰረታዊ እውነት ሆኖ ኖሮአል ይኖራልም (እብ 6፥ 2)። እግዚአብሔርም ደግሞ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፦
"በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፦ እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።" (ማቴዎስ 22፥ 30-32)።
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 19 ላይ "በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።" ሲል እንደተናገረው፣ በእውነት ትንሳኤ የሚባል ነገር ከሌለ ክርስትናም ዋጋ የሌለው የምድር ላይ ምስኪኖች ተራ ሃይማኖት ብቻ ሆኖ ይቀራል።
ምእመናን ልብ አድርጉ፣ ኤፌሶን 2፥ 4-5 "ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥" ሲል እንደሚያረጋግጠው፤ እኛ እንደሆነ እንዴውኑ ከሞት ተነስተን ወደ ህይወት መጥተናል። ክርስትና የመነሳት ሕይወት ነው። የሚበልጠው ትንሳኤ በበደላችን ሙታን ከነበርንበት ሙትነት ወጥተን ከክርስቶስ ጋር የተሰጠን መዳንና የኃጢአት በይቅርታ የሞላበት የራሱ የክርስቶስ ሕይወት ማለትም ክርስትናችን ካልሆነ በቀር ወደ ፊት ገና የምንቀበለው ሌላ ነገር እንደሆነ እናስብ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ አይፈቅድልንም።
አሁን በመንፈስ ከሞት ተነስተን በሕይወት አለን! ሞት አሁን ለኛ ለዳንን ሰዎች አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም። ሁላችንም አንድ ቀን በስጋ እንሞታለን፣ ይህም ተፈጥሮአዊ ሕግ ተፈጥሮአዊ ሞት ነው፤ ያ በሚሆንበት ጊዜ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለን ወደማይገደበውና ወደማይበላሸው ማለቂያም ወደሌለው ዘላለማዊ ህብረት ወደ ሰማያዊውና መንፈሳዊው አለም በቀላሉ እንሸጋገራለን፤ ደግመንም አንሞትም።
ነገር ግን ወደ ፊት ይሆናል ተብሎ በብዙዎች በሚጠበቀው "የስጋ ትንሳኤ" ተብዬ ተስፋ ገና እሁንም የምትኖሩ ከሆነ፣ በእውነት ያሳዝናል፤ የመዳናችሁን ትርጉምና በቅዱስ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ለአዲስ ሕይወት የመነሳታችሁን መንፈሳዊውንና ዘላለማዊውን እውነታ ስታችሁታል ማለት ነው።
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦
አስተምህሮተ ትንሳኤ "የሚሻል ትንሳኤ" መግባብያ ፪
ክፍል 2
በመጀመሪያው ክፍል ጥናታችን እብራውያን 11፥ 35 ላይ "ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤"" የሚለውን ቃል መሰረት አድርገን "የሚሻል ትንሳኤ" በተሰኘው ርዕሰ ጉዳይ ላይ በጥቂቱ ተነጋግረናል፤ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ይህ አረፍተ ነገር የሐዋርያው ጳውሎስ የመጨረሻው ቃል አይደለም፤ ከቁጥር 39- 40 ስለ ብሉይ ኪዳን ቅዱሳን "እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።" የሚለውን የንባብ ክፍል አክለን በዚህኛው የጥናታችን ክፍል እንቀጥላለን።
በዚህ ነጥብ ላይ ብዙ ጊዜ ማባከን ሳያስፈልገን "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" እና "ፍጹም" በሚል ገላጭና ቁልፍ ቃላት፣ (ይህም ቁልፍ ቃል በመላው የእብራውያን መልእክት ውስጥ ያለውን ቦታ ቀደም ሲል አንስተናል) በዚህም ላይ የተነገረው ሃሳብ የሚያመለክተው ያው በቁጥር 35 ላይ "የሚበልጠውን ትንሣኤ" ተብሎ የተነገረለትን ነው፣ ያንን ግልጽ የሆነ የጋራ ስሜት ታሳቢ አድርጌ ወደ ፊት ልገስግስ)
1ኛ/ በዘፍጥረት 3፥19 እግዚአብሔር ለአዳም " ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና" አለው። በኋላም በመዝሙር 103፥ 14 ላይ ዳዊት ስለ እግዚአብሔር ሲናገር፦ "ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።" ብሎአል። በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፥ 7 ላይም ጳውሎስ ስለ ስጋው ወይም አካሉ ሲናገር "የሸክላ ዕቃ" እንደሆነ ይነግረናል። ሰለዚህ.... የአዳም ስጋ ወይም የአካሉ ምንጭና የመጨረሻ እጣ ፈንታ ያው የምድር አፈር ነው። ይህ እውነተኛ የቃሉ ምስክርነት ነው። ልክ እንደዚሁ የሁሉም ሰው ስጋ ምንጩና የመጨረሻ እጣ ፈንታው ደግሞ አሁንም ያው የምድር አፈር ነው።
እነዚህ ምንባባት ተዳሳሽና ተጨባጭ ስለሆነው (ፍጥረታዊውና ውጫዊው) የማንነታችን ክፍል የመጨረሻ እጣ ፈንታ በተመለከተ ምንም ጥርጣሬ አይታይባቸውም። ያው ወደ አፈር መመለስ ብቻ ነው። ነገር ግን ተዳሳሽ ስላልሆነው (መንፈሳዊውና ውስጣዊው) የማንነታችንን ክፍል የመጨረሻ እጣ ፈንታ በተመለከተስ ቃሉ ምን ያስተምራል?
በእውነቱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን የመጨረሻ እጣ ፈንታ የሚገልጠውን የቦታ ስያሜ፣ በእብራይስጡ "ሼኦል"፣ በግሪኩ ደግሞ "ሃደስ" የተሰኙትን ቃላት በቀጥታ እንዳለ ከመውሰድ ይልቅ፤ በትርምና የቃላት ፍቺ ችግር ውስጥ ገብተው፣ ሼኦልን 31 ጊዜ "መቃብር"፣ 3 ጊዜ ደግሞ "ጥልቁ" ብለው ተርጉመውታል፣ ሃደስን ደግሞ "ሲኦል" ሲሉ ለ11 ጊዜ ያህል ተርጉመውታል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 55 ላይ ደግሞ ለብቻው ለየት ባለ አቀራረብ "መቃብር" ተብሎ መተርጎሙ ግራ የሚያጋባ ነው። እነዚህን ስያሜዎች ግን ለምን እንዲህ በቀላሉ መተርጎም አስፈለገ? ምናልባት ምንም ሊያደርጉ ባለመቻላቸውና የትርጉም ሕጸጽ የሚያስከትለውን የመረዳት ችግር በሆነ ምክንያት ሳያስተውሉት ቀርተው ሊሆን ይችላል። ሲኦል በዚህ ጥናት ዘርዘር ተደርጎ ኋላ ላይ ይዳሰሳል። እዚህ ላይ ግን መጠነኛ ነገር ማንሳት ግድ ይላል፦
2ኛ/ መዝሙር 49፥ 15 ዘማሪው (ምናልባትም ከክ.ል.በ በ1000 ዓ.ዓ አካባቢ ይሆናል) "ነገር ግን እግዚአብሔር ይቀበለኛልና ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል።" ሲል እምነቱንና መረዳቱን የናገራል። ሲኦል በአሮጌው ኪዳን ጊዜ የነበሩ ሙታን ከአካላዊ ሞታቸው በኋላ በአጸደ ነፍስ የሚሄዱበት፣ መሲሁ እስኪመጣና ነጻ እስኪያወጣቸውም ድረስ የሚጠበቁበትና የሚከማቹበት ቦታ ስያሜ ነው። ለምሳሌ፦ የሟቾቹን የባለጠጋውን ሰው እና የአልአዛርን ታሪክ በምሳሌ የቀረበበትን ትርክት ልብ ይሏል፣ (ሉቃስ 16፥ 19-31)። ለኃጢአተኛው የስቃዩ ስፍራ የነበረው "ሲኦል" እና ለአልአዛር የእረፍቱና የመጽናኛው ስፍራ የነበረው "የአብርሃም እቅፍ" / ገነት የአንድ ስፍራ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ይመስላሉ።
አብርሃምና ዘሮቹ አንድ ቀን በሚያገኛቸውና በሚለማመዱት መንፈሳዊ ትንሳኤ፣ ይኸውም፦ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ/ ወደ እግዚአብሔር ኃልዎት መመለስ ያምኑና ተስፋ ያደርጉ ነበር፣
"አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።..... አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።..... ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤" (እብራውያን 11፥8- 10፣ 16 እና 35)።
3ኛ/ የሐዋርያት ሥራ 2፥ 27 " ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥" ሲል በንጉስ ዳዊት አፍ እንደተናገረ አድርጎ ጴጥሮስ ኢየሱስን ጠቅሶ ይናገራል
"ሲኦል" የሚለው የእብራይስጥ አቻ ቃል እዚህ ላይ የግሪኩ "ሃደስ" ነው፣ ይኸውም ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ በ70 አ.ም ላይ እስረኞችን ነጻ ለማውጣት ተመልሶ ሲመጣ ያኔ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ያጠፋው ቦታ ነው፣ "ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።" (ራእይ 20፥ 13-14)።
የሐዋርያት የሥራ 2፥ 27 ቢያንስ ከ70 አ.ም በፊት የነበሩ ነፍሳት በስጋ ከሞቱ ወይም አካላዊ መሞትን ከሞቱ በኋላ ወደ ሲኦል/ ሃደስ ይሄዱ እንደነበር ያረጋግጥልናል።
ከ70 አ.ም በፊት የተወለዱ ሁሉ፣ ልክ እንደ እኛ- የድህረ 70 አመተ ምህረት ላይ እንዳለን እንደ ዛሬዎቹ ሰዎች፣ ሊያደርጉት የተገባቸው ከሁለት አንድ ምርጫ ነበራቸው፦ እግዚአብሔር የተናገረውን ማመን ወይም አለማመን፤ ከዚያም በስጋ በሚሞቱበት ጊዜ፣ በ70 አ.ም የሚሆነውን የመጨረሻውን ፍርድና ውሳኔ ወደሚጠባበቁበት ሰፍራ ይሄዳሉ። በተያያዘም......
በክፍል አንድ የመግባቢያ ጥናታችን ማጠቃለያ ላይ ሕያዋን የሆኑ፣ ከእርሱ ጋር እርቅ ያደረጉ አንዳች የተለየ ነገር ቢያስቡ የሚያስገርም ይሆናል እንጂ ምንም ማድረግ አይቻልም። ስለዚህም በእርገቱና በመመለሱ መካከል በክርስቶስ ለሆነ ሕይወት በመንፈሳዊ ሁኔታ መነሳት እውን የሚሆነውና እንዲህ ያለውን ሕይወት የሚለማመዱት በእምነታቸው ምክንያት ነው (የኤፌሶን 2፥ 1-9)። አሁንስ ታዲያ ከሃደስ መወገድ በኋላ እንዴት ነው? መንፈሳዊ ትንሳኤ አሁንም እንኳ ሕያዋን ሳለን ከእምነታችን የተነሳ ተዘጋጅቶልናል፤ በሥጋ ከሞትን በኋላ ግን መጻኢ እድላችን እውን ሆኖ እስኪታወቅ ድረስ ለመቆየት እንድ የሆነ ቦታ መሄድ አያስፈልገንም።
4ኛ/ እንደገና እብራውያን 11 39-40 ያለውን እናንብብ፣ " እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።"
እዚህ ላይ የሚወራላቸው "እነዚህም" የተባሉ ሰዎች ወይም 'እነርሱ' የሚለው ቃል የሚያመለክተው በዳግመኛ ምጽአቱ "ፍጹማን" ለመሆን "የተሰጠውን የተስፋ ቃል" ይኸውም "እግዚአብሔር ስለ እኛ (እኛ የተባሉት ጳውሎስና የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የእብራውያን ክርስቲያኖች ናቸው) አስቀድሞ ያየልንን አንዳች የሚበልጥ ነገር" ሳያገኙ ከ70 አ.ም በፊት የሞቱትን ሰዎች ነው።
"ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ" በሚለው ንግግር ውስጥ እነዚህም" የተባሉትን ሰዎች ለብቻቸው ፍጹማን ከመሆን የሚከለክል ነገር አለው፤ ይህም እነዚያ ታማኝ የነበሩ የአሮጌው ኪዳን ቅዱሳን ሙታን እና ከ70 አ.ም በፊት በትንሳኤ ተስፋ ያንቀላፉ ክርስቲያን አማንይን፣ በ70 አመተ ምህረት ላይ በዳግመኛ ምጽአቱ መንፈሳዊ ትንሳኤን ለመቀበል ተዘጋጅተው በህይወት ኖረው ይጠባበቁ ከነበሩቱ ቅዱሳን ተነጥለው ምነፈሳዊ ትንሳኤን የማይለማመዱ መሆናቸውን የሚያመለክት አሳብ ነው (ፊልጵስዩስ 3፥ 8- 12 ያለውን ተመልከቱ፤ ኋላ ላይ በጥልቀት እናጠናዋለን)
"ፍጹም" በሚል ቃል የተገለጠው ኑሮ፣ ሊመጣ ባለው በመንግስቱ ውስጥ በልጁ ሕይወት አማካኝነት ሊገለጥ ያለውን "የሚበልጥ ነገር" እንደሚያመለክት አስታውሱ (1ቆሮንቶስ 13፥ 8ጀምሮ)።
5ኛ/ 1ተሰሎንቄ 4፥ 13-17 ያለው ክፍል ከእብራውያን 11 ጋር ፍጹም በሚባል ደርጃ ሊስተያይ የሚችል ክፍል ነው፤ እስቲ አብረን እናምብበው፦ " ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።"
ጳውሎስ "እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር" በሚልበት ጊዜ በንግግሩ የሚያመለክተው ሲጽፍላቸው የነበሩትን የተሰሎንቄን ቅዱሳንና ራሱን ጭምር ነው፣ እነርሱም ጌታ በሚመለስበት ጊዜ ሳይሞቱ በሕይወተ ስጋ ቆይተው ይኖራሉ ብሎ የሚያምናቸውን (ወይም በቀላሉ ይሆናል ብሎ የሚያስባቸውን) ነው። ጳውሎስ አንቀላፍተው ስላሉቱ በሚናገርበት ጊዜ የሚያመለክተው በስጋ ስለሞቱት፣ ነገር ግን ደግሞ ለህይወት ትንሳኤ ይነሱ ዘንድ በ70 አመተ ምህረት ላይ የሚሆነውን የመታደስን/ የመመለስን ጊዜ ሲጠባበቁ የነበሩትን በድሮ ጊዜ ስለነበሩ ቅዱሳን ነው።
ስለሆነም.... ወዳለፈው ጊዜ ስንመልከት እነዚያ ከ70 አ.ም በፊት በስጋ የሞቱ ቅዱሳን የራሳቸውን እርቅና እድሳት በተቀበሉበት በዚያው ጊዜ እነዚያም በሕይወተ ሰጋ የነበሩ ቅዱሳን የራሳቸውን ተቀብለዋል ማለት ነው።
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦
No comments:
Post a Comment