የመጽሓፍ ቅዱስ ተርጓሚ ሊኖረው ስለሚገባው ብቃት።
BIBLICAL HERMENEUTICS ON THE INTERPRETATION OF THE OLD AND NEW TESTAMENTS. ከተሰኘው የሚልተን ቴሪ ሰፊ መድብል ካለው መጽሃፍ ላይ መጽሓፍ ቅዱስን ለማጥናት፣ በአግባቡ ለመተርጎምና ገልጦ ለማስተማር የሚያስችሉ መሰረታዊ ሆነው በስፋት ትንታኔ ከተሰጠባቸው ነጥቦች ላይ በብርቱ የተሞገትኩባቸውን ጉዳዮች ላካፍላችሁ።
ቅዱሳት መጻሕፍትን ብቃት ባለው እና ትክክለኛ በሆነ የትርጓሜ መርህ ለመረዳት ተፈጥሯዊም ሆነ ማናቸውም በልምድ የዳበሩ የተለያዩ ብቃቶች ያስፈልጉናል። ምንም እንኳን ይህ ከፍተኛ መጠን እና ስፋት ያለው የቅዱሳት መጽሐፍት ምንባብ በልጆች የመረዳት ችሎታ ልክ ሊቀርብ የሚችል፣ ህጻናትም እንኳ በበቂ ሁኔታ ሊማሩት እስኪቻላቸው ቀላል የሆነ፣ ለማንኛውም ሰው፣ ለተራውም ሕዝብ ሆነ ላልተማረው እንኳ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ለጽድቅ የሚጠቅም ብዙ ነገሮችን ሊያገኝ የሚያስችል ትምህርት ያለበት እንደሆነ ቢታመንም፤ ያም ሆኖ ትክክለኛውን ግንዛቤ እና ማብራሪያ ለማግኘት ግን እጅግ የላቀ የአዕምሮ ብቃት እና ሰፊ የሆነ የትምህርት ዝግጅት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ነገሮችም አሉበት። ብቃት ያለው ተርጓሚ ካሉት በርካታ ዝግጅቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የመጀመሪያው አእምሯዊና ምሁራዊ ሲሆን እርሱን የአዕምሮ ዝግጅት ብለን እንጠራዋለን፣ ሁለተኛውንም ትምህርታዊ ብቃት ስንለው፣ ሶስተኛውን ደግሞ የመንፈሳዊ ህይወት አቋም ብለን ልንጠራው እንችላለን። የመጀመሪያዎቹ በአብዛኛው ከነፍስ ጋር ባላቸው ቁርኝት ሲታወቁ ለነፍሳችን ተፈጥሯዊ ዝምድና አላቸው፤ ሁለተኛው ደግሞ በትጉህ ጥናት እና ምርምር የሚዳብር ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ በልደታችን እንደተገኘ ውስጣዊ መሳብ እና ዝንባሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ሀ. የአዕምሮ ዝግጅት፡
1. ጤናማ፣ እና ሚዛናዊ የሆነ አእምሮ፣
- በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ሆነ ሌላ ማናቸውንም መጽሐፍ ለመተርጎምና ለመረዳት የሚወድ ሰው ጤናማና ሚዛናዊ አእምሮ ሊኖረው ይገባል። በቂ ያልሆነ ግንዛቤ፣ ጉድለት ያለበት ፍርድ እና ከልክ ያለፈ የቅዠት አሳብ የአንድን ሰው አስተሳሰብ ከማዛባቱም ባለፈ ወደ ብዙ ከንቱ እና የሞኝነት ሀሳቦች ይመራል።
2. ፈጣን እና ግልጽ የሆነ የግንዛቤ ችሎታ፣
- የደራሲውን ሀሳብ የመረዳት ሙሉ ኃይል እንዲሁም የንባብ ክፍሉን መቼት በዓይነ ሕሊና የመመልከት ብቃት ሊኖረው ይገባል።)
3. የአዕምሮ ብቃት
- የተለያዩ አስተሳሰቦችን ትስስር እና የሃሳቦችን ቁርኝት ወዲያውኑ ለመለየት የሚያስችል ወሳኝ እና ስል የሆነ የአዕምሮ ብቃት
4. ምናባዊ አስተሳሰብ ያለው ሆኖ ነገር ግን ያንን በቁጥጥር ስር አድርጎ እየገራ የሚጠቀምበት፣
- እውነተኛ የሆነ ተርጓሚ ብዙውን ጊዜ ራሱን ወደ ቀደመው ታሪካዊ ዘመን መለስ እያደረገ የጥንቱን ዘመን ትዕይንቶች በነፍሱ ውስጥ መሳል መቻል ያስፈልገዋል። እራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ቦታ ለማስቀመጥ እና እነርሱ ይታያቸው እንደነበሩ ለማየት ይሰማቸውም እንደነበሩ እንዲሰማው የተፈጥሮ እና የሰው ሕይወት ተሞክሮ ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን በኃይለኛው ምናባዊ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከልኵ ያልፉና ሰው ለማይገባውና ለማይረዳው ትንታኔ የተጋለጡ ተንታኞች መሆናቸው አይቀርም፤ ስለዚህ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ልጓም ሊበጅለት ያስፈልጋል። በቃላት ተሽሞንሙኖ የተንቆጠቆጠ አስተሳሰብ ከትክክለኛ የህሊና ፍርድ ሸሽቶ ተገቢነት ባለው ትርጓሜ ምትክ የገዛ ራስን ግምትና መላ መት መጋበዝ የሚችል ነው። የተገሠጸውና ስራአት የያዘ አስተሳሰብ ግን ከፅንሰ-ሀሳብ እና ረቂቅ ከሆኑ እሳቤ ኃይል ጋር ወስዶ ያቆራኛል። አስፈላጊ ከሆነም በማብራራት ሂደት ወይም በክርክር ውስጥ እውነትን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ አሳማኝ መላምቶችን መገንባት ይችላል።
5. ግልጽና ጤናማ የሆነ ፍርድ ያለው
- ህቡዕ በሆኑ ትርጉሞች፣ በማመናፈስ ሂደቶች እና አሳማኝነት በጎድላቸው ግምቶች ተጽዕኖ ስር እንዲወድቅ መፍቀድ የለበትም።
6. ጣዕም እና ጣፋጭነት ያለው ትክክለኛነት
- የትክክለኛነቱ ጣዕም እና በሚከተለው ትርጉም የሚደርስበት ድምዳሜው በእውነተኛ እና በሐሰተኛ ዕሳቤዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት መሰልጠን አለበት።
7. ትክክለኛ የአመክንዮ አጠቃቀም፣
- መጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠን በሰው ቋንቋ ነው፣ ወደ እኛም ሲደርስ አመክንዮአችንን እና ፍርዳችንን ይጠይቃል፤ ምርመራንም ይጋብዛል፣ በዚያው ልክ ዕውር የሆነ የደቦ እምነትና አስተሳሰብን ያወግዛል።
8. የማስተማር ብቃት፣
- ቅዱሳት መጻሕፍትን ለራስ መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ እሱ ራሱ የተረዳውን ለሌሎች ግልጽና ሕያው በሆነ መንገድ መግለጽና ማስተማር ማስረዳትም፣ ራስን ለመጠየቅና በሌሎች ለመጠየቅ፣ ለሚጠይቁትም መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጀ መሆን አለበት።
ለ. የትምህርት ብቃት፡
ቅዱሳት መጻሕፍትን ፕሮፌሽናል በሆነ ብቃት ለመተርጎም የተዘጋጀ ሰው ሚዛናዊ የሆነ አእምሮ፣ ብልህነት የተላበሰ አስተሳሰብ እና የአዕምሮ ጥልቀት ከማሳየት የበለጠ ነገር ሊኖረው ያስፈልገዋል። በተለያዩ የታሪክ፣ የሳይንስ እና የፍልስፍና ዘርፎች ሰፋ ያለ ግንዛቤና መረጃዎችን ቆፍሮ የማሰስ እና የማከማቸት ትጋት ይፈለግበታል። የሌሎች አስተማሪ ለመሆን ይቻለው ዘንድ ብዙ የአስተሳሰብ ነጻነት (ሊበራሊቲ) ሊኖረው ይገባል። መጻህፍትን በፍቅር የሚወድ፣ ልዩ ልዩ ጥናቶችን የማገላብጥ ችሎታውን በንባብ የሚያዳብር፣ የንባብ ዲሲፕሊን ያለው፥ በሚያደርገው ጥናቱና ምርምሩ ጠቃሚና ተግባራዊ የሆነ ዲሲፕሊን የሚከተል ሆኖ ብርቱ የሆነ የሃሳብ ልቀት፤ ሰፊ እና ትክክለኛ የሆነ እውቀትም ኖሮት ያንን ለሌሎች ለማስተላፍ እና ለማስተማር የተዘጋጀ እንዲሆን ያስፈልገዋል። የትምህርቱ ብቃት ሊያካትታቸው የተገቡ ጉዳዮችን እንመልከት፦
1. የጂኦግራፊ እና የታሪክ እውቀት፣
- የጥንታዊት እስራኤል እና በአጠቃላይ ፍልስጤም ምድር እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ አጎራባች ክልሎች ጂኦግራፊን፤ ጨምሮም ጥንታዊውን የእስራኤል ታሪክ ማወቅ የግድ ነው።
2. የዘመን አቆጣጠር እና የዘመን ልዩነት እውቀት፣
- የክስተቶችን ቅደም ተከተል፣ የዘመናትን ልዩነት እና የክፍለ ዘመናትን አከፋፈል፣ የዘር ሐረግ ሰንጠረዦችን ወሰን እና የቀናትን ወሰን መለየት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ይህም ትእግስት የተሞላበት ጥናት እና አድካሚ የሆነ ጥንቃቄን ይጠይቃል።
3. የፖለቲካ፣ የሕግ እና የሲቪል መንግሥት ጥናት፣
- ብዙውን ጊዜ በዕብራውያን ልማዶች ላይ ብርሃንን ሊሰጡን የሚችሉ በመሆናቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ የሆኑ የሌሎች ህዝቦችን ልማዶች፣ ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት በመቃርም የወቅቱን ጥንታዊ ብሔራትና ዘሮች ሁሉ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ዳራ መመርመር ያስፈልጋል።
4. የተፈጥሮ ሳይንስ እውቀት፣
- በጂኦሎጂ፣ በማዕድን ቁፋሮ ጥናት እና በአስትሮኖሚ በጥቅሉ በተፈጥሮ ሳይንስ የተገኙ መረጃዎችና ማስረጃዎች እዚህ ላይ ተጠቃሽ ናቸው፤ የቅዱሳት መጻህፍት ጸሐፊዎች በሚያነሷቸው መግለጫዎች ወይም በሚያቀርቧቸው ማጣቀሻዎች እነዚህን ጉዳዮች ሊያመለክቱ ይችላሉ፤ ስለዚህም የጥንት ሰዎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያላቸው እውቀት ምንም ይሁን ምን፣ ዘመናዊው ተርጓሚ በዘመኑ የደረሰበትን እና ዘመናዊው ሳይንስ ያሳየውን አስታርቆ ማወቅ አለበት።
5. ፍልስፍና እና ሥነ ልቦና፣
- ስለ ግምታዊ አስተሳሰብ፣ስለ ታሪክ እና ታሪካዊ ስርዓቶች፣ ስለተለያዩ የፍልስፍና እና የስነ-ልቦና አስተምህሮዎች ከላይ በቁጥር 4 እንደተጠቀሰው ሁሉ ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። በርካቶቹ እነዚህ ፍልስፍናዊ ውይይቶች በሥነ-መለኮታዊ ዶግማ ውስጥ ተሳትፎ ሊኖራቸው የሚችሉ ሲሆን እነርሱም ለየት ወዳሉ መርሆዎች እና የትርጓሜ ዘዴዎች ሊያመሩ ይችላሉ፤ ለአንድ ፕሮፌሽናል ለሆነ የቅዱሳት መጻህፍት ተርጓሚ እንዲህ ካሉ ፍልስፍናዊ ጉዳዮች ጋር ፍትሃዊ በሆነ ምንገድ መላመድ፥ ጥንቃቄ በተላበሰ መልኵ ጥቃቅን በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ያላቸውንም ተፅእኖ ማወቅ ያስፈልገዋል።
6.የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎች እና የንጽጽር ፊሎሎጂ እውቀት፣
- እንደዚህ አይነት እውቀት የሌለው ማንም ሰው ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን በማብራራት እና ገልጦ በማስተማር ሊቅ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። ከዕብራይስጥ እና ከጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ ጋር እንዲሁም ከጥንቶቹ የከለዳዊያን ሴማዊ ቋንቋ ጋር በደንብ መተዋወቅ ያስፈልጋል፣ በንጽጽራዊ ፊሎሎጂ ሳይንስ ውስጥም ማለትም የአንድን ቋንቋ ወይም የቋንቋዎችን አወቃቀር፣ ታሪካዊ እድገት እና ግንኙነቶችን የሚያካትት የእውቀት ዘርፍ ነው፤ በዚህ ውስጥም የተወሰነ ችሎታን መጨመር ያስፈልጋል።
7. ከአጠቃላይ ሥነ ጽሑፋዊ ዘውግ ጋር መተዋወቅ፣
- የእግዚአብሔር ቃል ተርጓሚ የሆነ ሰው ከአጠቃላይ ሥነ ጽሑፋዊ ዘውግ ጋር ሊተዋወቅ እና በዘርፉ እውቀት ሊጨምር መቻል አለበት። የሰው ልጅ የጥበብ ችሎታና በዘመኑ የሰራቸው ታላላቅ ስራዎቹ፣ በዓለም ላይ የተፈጸሙ የታወቁት የታሪክ ክስተቶች፣ በሁሉም ታላላቅ ህዝቦች ዘንድ ያሉ የጽሁፍ ስራዎችና ክላሲኮች እንዲሁም በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ የአምላክን ንግግሮች ለሰው ያቀርባሉ ተብለው የሚታመኑ ቅዱሳት መጻህፍት ለሰው የቀረቡበት ስነ ጽሁፋዊ መንገድ ቃሉን በመተርጎም ረገድ ጠቀሜታ እንዳላቸው ማስተዋል ያስፈልጋል። በብዙዎቹ የስነ-ጽሑፍ ብቃቶች ውስጥ እጦት የማይገኝባቸው ብቁ የሆኑና ጥሩ የሆኑ ተንታኞች መኖራቸው አይካድም። ልቆ የሚገኝ መምህር ነኝ የሚል ማንም ሰው የትኛውንም የስነ-ጽሑፍ ስኬት እንደ አላስፈላጊ ተራ ነገር አድርጎ ሊቆጥረው አይችልም፤ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠንን እምነት ከጥርጣሬ እና ከክህደት በመጠበቅ እና በመከላከል ረገድ ክርስቲያናዊ የእምነት ተሟጋች እና የዕቅበተ እምነት ተጋድሎ የሚፈጽም የቃሉ ተንታኝ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ብቃቶች ሁሉ አስፈላጊነታቸውን አይጠራጠርም።
ሐ. የመንፈሳዊ ህይወት አቋም
1. እነዚህ በከፊል የተገኙ ስጦታዎች ናቸው፣
- አንድ ተርጓሚ ሊኖሩት ከሚገቡት ብቃቶች መካከል ይህ መንፈሳዊ ብለን የምንጠራው አንድ በከፊል እንደ ስጦታ ተደርጎ መታየት ያለበት ሲሆን በከፊል ደግሞ በግል ጥሞና እና በተገቢው ተግሣጽ ራስን ዲስፕሊን እያደረጕ የተገኙ ፍሬዎች ናቸው። በዚህ አይነተኛ የህይወት አቋም ስር ሁሉንም አይነት የሞራልና የእምነት ህይወት ባሕርያት፣ መንፈሳዊ ዝንባሌዎቻችንንና ስኬቶቻችንን እናስቀምጣለን። መንፈስ ሰውን ከአለማዊ መሻቱና ከስጋዊ ባህርይ ባርነት የሚለየው እና እግዚአብሔርን የማወቅና የመውደድ ፈቃድና አቅም እንዲኖረው የሚያደርገው ከፍ ያለ የሞራል ተፈጥሮ ነው። የዚህን መንፈሳዊ ተፈጥሮ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችል አስደናቂ መርህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገባ የተቀመጠ ሲሆን፤ ነገር ግን ያልዳነ ጠማማ ልብና ያልተለወጠ ሥጋዊ አእምሮ ክቡሩን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማስተናገድ የሚችል ፈቃደኛነት ላይኖረው ይችላል። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2፡ 14 ላይ ሲናገር “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም” ይላል።
2. እውነትን የማወቅ ፍላጎት፣
- ማንም ሰው ቢሆን እውነትን ለማወቅ ውስጣዊ ጉጉት እና ጥማት ከሌለው፣ የሚማር ልብም ከሌለው፣ ልቡም እውነትን በሚቃወም መሻት ተጸእኖ ስር ከወደቀ ወይም ለህሊናውና ለፍርዱ ግልጽ ሆኖ የሚቀርብለትን ነገር እንዳለ ለመቀበል የሚያመነታ ከሆነ እንግዲያውስ የእግዚአብሔር መገለጥ ነው ተብሎ የሚታሰበውን ቃል ተገቢ በሆነ መንገድ ማጥናትና ማብራራት ከቶ አይቻለውም። እውነትን ለማግኘት ልባዊ ፍላጎትና ቁርጠኛ ዓላማ ሊኖር ይገባል፣ እውነት ላይ ሲደረስም ያንን በአክብሮትና በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል።
3. ጥልቀት እና ርኅራኄ ያለው ፍቅር፣
- እውነትን የማወቅ ንፁህ ፍላጎት የሚጎለብተው ሥነ ምግባሩ ክቡር ለሆነ ለማናቸውም ነገር ባለን ጥልቅ ፍቅር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ርኅራኄ የእግዚአብሔርም ሆነ የሰው የንጹህ ፍቅር መቀመጫ ነው።
4. ለእግዚአብሔር ቃል ጉጉት፣
- በነፍስ ውስጥ ያለ እውነትን የመውደድ ጽኑ ፍቅር በውስጣችን ለእግዚአብሔር ቃል ጉጉትና ናፍቆት የሚያሰፍን የጋለና ምንጊዜም ሲያበራ የሚኖር መንፈሳዊ ቅንዓት መሆን አለበት። ጥልቀትና ብቃት ባለው ትጋት ቃሉን የሚያጠናና የሚተረጉም ሰው እግዚአብሔር መንፈሱን የነካው እና ነፍሱን በሰማያዊ መገለጥ ሕያው ያደረገለት ሰው ነው።
5. ለእግዚአብሔር እና ለህጎቹ አክብሮት፣
- እንዲህ ዓይነቱ የተቀደሰ ቅንዓት በእውነተኛ አክብሮት የተገዛ እና የምንቆጣጠረው ሊሆን ይገባል። በንጹህ ፍቅር የሚቀና አእምሮ እንዲሁም እውነትን የማወቅና ላወቁት እውነት የመገዛት ንፁህ ፍላጎት መኖር አለበት። የእግዚአብሔርን እውነተኛ እውቀት ለማግኘት ተግተው የሚፈልጉ ሁሉ በዚያው ልክ የተከበረና እውነትን የሚወድ መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያሉትን ይፈልጋቸዋል ራሱንም ይገልጥላቸዋል።
6. ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት፣
- በመጨረሻም፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚወድና የሚማር ሰው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሕያው ኅብረት እና አንድነት ሊኖረው ይገባል። ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተሰጡ እስከሆኑ ድረስ (2ኛ ጢሞ. 3፥16)፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፊዎችም ከእግዚአብሔር የሆነውን ቃል በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩ እስከሆኑ ድረስ (2ኛ ጴጥ. 1፥21)፣ ልክ እንደዚያው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉሞ የሚረዳ ሰውም አንዱን መንፈስ ቅዱስ የተካፈለ መሆን አለበት። ያኔም በነፍሱ ውስጥ ባለው ጥልቅ ተሞክሮ የክርስቶስን የማዳን እውቀት እያገኘ በጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ ይሳባል፣ ከዚያ ተሞክሮ ጥልቀት እና ሙላት ጋር በሚመጣጠን መልኩም የመንፈስን አሳብ፣ መንፈሳዊውን ሕይወትና መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን ሰላም ያውቃል።
ማጠቃለያ
ይህንን ታላቅ የሆነ የቅዱሳት መጻህፍት መድብል ተራ በሆነ አካዳሚክ አቀራረብ ጠንቅቀን ልንረዳው አለመቻላችን ግልጽ ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የመንፈስ ቅዱስን አብርሆት አጥብቀን በጸሎት መፈለግ አለብን፡፡ አብርሆት ደግሞ እግዚአብሔር በነዚያ የቅዱሳት መጻህፍት ጽሁፎች አማካኝነት ራሱን ለእኛ መግለጹ ነው፡፡ አብርሆትም ት ጥ ቅ የተባለ ሦስት ነገሮችን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ትምህርት በዚህ እናጠቃልላለን፦
ት ትህትና (Humility) ይህ ፍጹም መደገፍ ነው፡፡ “ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (1ጴጥ 5፥ 5) እንደሚል ትህትና በእጅጉ ያስፈልገናል። ከፍጥረታችን እውሮች የሆንን እኛ አይናችንን ለቅዱሳት መጻህፍት መረዳት እንዲከፍትልን በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ አለብን፡፡ የተማሪ ልብ ይኑረን።
“ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።” (መዝ 119÷ 18)
“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” (ምሳ 3፥ 5)
“አለን የምንለው ላይብረሪ እና ጥናት ሁሉ እርሱን በትህትና ከመጠጋታችን ጋር ሲነጻጸር ባዶና ተራ ይሆናል” (ቻርልስ ስፕረጂዮን)
“ትህትና ጸጋን ሁሉ ሲመገብ ትዕቢት ግን ይራባል!” (ሪቻርድ ባክስተር)
ጥ ጥንካሬ (Hard Working) ቃሉን በጥልቀት ለመረዳት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል
“ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳ 2÷ 1-5)
የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ጊዜና ትጋት ይጠይቃል፡፡ ሥራው ለሰነፍ ሰዎች የሚሆን አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን እና ፈቃዱን ማወቅ ለየቀኑ ኑሯችን ጥንካሬን ይሰጠናል፣ ይኸውም ደግሞ ያለማቋረጥ ቃሉን ከማጥናት የሚመጣ ነው፡፡ በትጋት ውስጥ ለሚቆዩ ሰዎች መረዳቱ በጊዜ ውስጥ ቆይቶ መጣል፡፡ ይህንን ታላቅ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ለመረዳት ብርቱ ጥረት እያደረጋችሁ ከጸሎት ጋር ደግማችሁ ደጋግማችሁ ሳታቋርጡ አንብቡት፡፡
“በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤” (ቆላስ 4፥ 3)
“ተግቶ ማሰብ ሕይወት/ ኑሮ ነው” (ስፕረጂዮን)
“ተግቶ ማሰብ ትግል ነው” (ሲ.ኤስ. ሎቬት)
ቅ ቅድስና (Holiness) እግዚአብሔር ራሱን በቃሉ በኩል እንዲገልጽልን የምንጠይቅ ከሆነ በቅድስና መመላለስ አለብን፡፡
“ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።” (ያዕ 1÷ 21)
“ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” (ዕብ 12÷ 14)
“እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” (1ጴጥሮስ 2÷ 1-3)
No comments:
Post a Comment