ደቀ መዝሙር እና የሚያስከፍለው ዋጋ
የዶ/ር ማርቲን ሉተርን “የመስቀሉ ሥነ መለኮት” የተሰኘ ትምህርቱን ካነበብሁ በኋላ የዲትሪች ቦንሆፈርን THE COST OF DISCIPLESHIP የተሰኘውን መጽሐፍ አንሰቼ በትምህርቱ መመሰጤን ቀጥያለሁ። የንባቤን ማጠቃለያ ባይሆንም ትኩረቴን ከሳቡ አብይ የመጽሐፉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል “ደቀ መዝሙርነትና መስቀሉ” የተሰኘውን የጽሁፉን አንድ ክፍል ትምህርት በወፍ በረር ላሰቃኛችሁ።
በጥቅሉ ይህ “THE COST OF DISCIPLESHIP “የደቀ መዝሙርነት ዋጋ” የተሰኘው መጽሐፍ ዋናው መልእክት ኢየሱስን መከተል ቀላል ጉዳይ ወይም ላይ ላዩን ለይስሙላ የምናደርገው ዋዛ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያሳይ ግሩም ሥራ ነው፤ እውነተኛ ታዛዥነትን፣ ራስን መካድን እና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። በዚህ መጽሐፍ ሰማእቱ ቦንሆፈር “ርካሽ ጸጋን” “ውድ ከሆነ ጸጋ” ጋር ያነጻጽራል፣ እውነተኛ እምነትም የአንድን ሰው ሙሉ ሕይወት እንደሚለውጥ፣ መከራ መቀበልንና መስዋዕትነት ያለበትን ኑሮ ሊያካትት እንደሚችልም በጽኑ ይከራከራል።
የመጽሐፉ ዋናው ሀሳብ
የቦንሆፈር መጽሐፍ ማዕከላዊ ነጥብ ደቀ መዝሙርነት ማለት ክርስቶስ እንደጠራህ ለመኖር እና ለመሞት መኖር ማለት ነው፣ ጸጋንም እንደ ነፃ የይለፍ ፈቃድ ማመን ወይም ለኃጢአት ማመካኛ እንደተሰጠ ሊቼንሳ አድርጎ ማየትም አይደለም። መጽሐፉ በዋናነት ያተኮረው በተራራው ስብከት ላይ ሲሆን፣ ቦንሆፈር ክርስቶስን በተግባር መከተል ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት የተራራውን ስብከት ይጠቀምበታል። በአብዛኛው ከዚህ መጽሐፍ ጋር የተያያዘው ታዋቂው መስመር የዚህን ስብከት መልእክት ያጠቃልላል የኸውም ክርስቶስ አንድን ሰው እርሱን እንዲከተል ሲጠራው መጥቶ ለርሱ እንዲሞት ይጠራዋል የሚል ነው።
በቀላል አነጋገር መጽሐፉ እውነተኛ ክርስትናን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- እውነተኛ ክርስትና ዋጋ የሚያስከፍል ደግሞ ነው እነጂ ይቅርታ የምንቀበልበት ብቻ አይደለም። ከምቾት ወይም አምኛለሁ ደኛለሁ ብሎ ተደላድሎ ከመቀመጥ በላይ ለኢየሱስ በመታዘዝ፣ በመስዋዕትነት እና በታማኝነት የተቀረጸ ሕይወት ነው።
“ደቀ መዝሙርነትና መስቀሉ”
በዚህ የዲትሪች ቦንሆፈር “የደቀ መዝሙርነት ዋጋ” በሚለው ክፍል ውስጥ፣ ከፍ ሲል እንዳነሳነው ማዕከላዊው መልእክቱ እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ከመስቀል የማይለይ መሆኑን አጽንዖት መስጠቱ ነው። ኢየሱስን መከተል እርሱን ማድነቅ፣ የተወሰኑ ትምህርቶቹን ማመን ወይም ከክርስትና ዕሴቶች ጥቅም ማግኘት ብቻ አይደለም። ራስን በመካድ፣ በመታዘዝ፣ በመከራ እና በመስዋዕትነት መንገድ ላይ ክርስቶስን የመከተል ታላቅ የሕይወት ጥሪ ነው።
ዋናው ሀሳብ፡- “ኑና ተከተሉኝ”
ቦንሆፈር በዚህ መጽሐፉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ተከተሉኝ” ሲል ያቀረበውን ጥሪ አፅንዖት ሰጥቶ ይናገርበታል። ይህ ጥሪ እውነተኛ የሆነ ልባዊ ምላሽ ይፈልጋል። የክርስትና እምነትም ስለ ክርስቶስ መረጃ መቀበል ማቀበል ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ በመመላለስ የሚገለጥ ራሱ መታዘዝ የሆነ ሕይወት ነው።
መስቀሉ ለደቀ መዝሙርነት ማዕከላዊ ነው
ኢየሱስ ሊሰቀል እንደመጣ ሁሉ፣ ደቀ መዝሙሩም የኢየሱስ መንገድ ወደ መስቀሉ እንደሚያመራ በውል መረዳት አለበት። ስለዚህ፣ እሱን የሚከተሉ ሰዎች ከመከራ ወይም ከመሥዋዕትነት የጸዳ ሕይወት መጠበቅ የለባቸውም። ቦንሆፈር ክርስቲያኖች መከራን ለራሳቸው ጥቅም ወይም ለጀብደኝነት ሲሉ መፈለግ አለባቸው ማለቱ አይደለም። ይልቁንም፣ የክርስቶስ እሴቶች ከዓለም እሴቶች ጋር የሚጋጩ ስለሆኑ፣ ለክርስቶስ የተሰጠ ታማኝ መታዘዝ የመከራን ሕይወት ሊያስከትል ይችላል እያለን ነው።
መስቀሉን ተሸክሞ መሄድ
መስቀሉን መሸከም ማለት፦
🎚️ራስን መካድ ነው - የራስ ጥቅም ላይ ያተኮረ ፍላጎትን በመተው የነፍስን ምኞት መከልከልና መቆጣጠር
🎚️ለክርስቶስ ፈቃድ መገዛት ነው - ክርስቶስ ሕይወትን እንዲመራ መፍቀድ።
🎚️መታዘዝ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ እንኳ በታማኝነት ለመቆም፣ ስቃይንም ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን።
🎚️ዕለት ዕለት ኢየሱስን መከተል - የዘወትር ልምምድ እንጂ የአንድ ጊዜ ውሳኔ ማድረግ ብቻ አይደለም።
ጸጋ እና ደቀ መዝሙርነት
በቦንሆፈር ሥነ-መለኮት ውስጥ የተንጸባረቀው አንዱ ዋና ጭብጥ በርካሽ ጸጋ እና ውድ በሆነ ጸጋ መካከል ያለው ንፅፅር ነው።
# ርካሽ ጸጋ እንዲህ ይላል፡- “ጸጋ ይቅርታ ነው፣ ስለዚህ የተለወጠ ሕይወት ባይኖር እንኳ ይቅርታን መቀበል እችላለሁ።”
#ዋጋ ያለው ጸጋ ማለት የእግዚአብሔር ጸጋ ለእኛ ነፃ የሆነውን ያህል በዚያዉ ለክ ግን ክርስቶስን እንድንከተልም ይጠራናል። ጸጋው ዋጋ ያለው ነው ምክንያቱም ሙሉ ሕይወታችንን ይጠይቃል፣ ሆኖም ግን ክርስቶስ ራሱ በሙሉ ሕይወታችን እርሱን የመከተል ችሎታን እና ግብዣን ስለሚሰጠን የጸጋው ዋጋ ራሱም ቢሆን የሚያስመካ የሰው ጥረት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ጸጋ ነው።
የመስቀሉ ትርጉም ለክርስቲያን
መስቀሉ ማለት የክርስትና ሕይወት ነው፣ በመሠረቱ ይህ ህይወት ከክርስቶስ ጋር ያለ የአንድነት ሕይወት ነው። የየሱስ ደቀ መዝሙር ስለ ኢየሱስ ከሩቁ ብቻ እየሰማ አይማርም። ደቀ መዝሙሩ ኢየሱስን ተጠግቶ ከርሱ ጋር እየተራመደ የሕይወቱን ምሳሌነት ይከተላል፤ በክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ በደቀ መዝሙሩም ታዛዥነት፣ ትህትና፣ ሌሎችን ማገልገል፣ መከራን መቀበል እና በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ መታመን ይገባል።
በአንድ ዓረፍተ ነገር
ቦንሆፈር እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ማለት ኢየሱስን የትም ቦታ መከተል ማለት እንደሆነ ያስተምራል፣ የኢየሱስ መንገድ ወደ መስቀል ስለሚያመራ፣ ደቀ መዝሙሩ ራሱን ለመካድ፣ ለታማኝነት ለመሰቃየት እና ለክርስቶስ ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ለመኖር ፈቃደኛ መሆን አለበት።
ይህ ክፍል በተለይ በማርቆስ 8:34 ላይ ከኢየሱስ ቃላት ጋር በጥሩ ሁኔታ ይገናኛል፡- “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።”
No comments:
Post a Comment