Friday, August 7, 2026

አይንም ሁሉ ያዩታል

ዓይንም ሁሉ … ያዩታል

አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ይህን ንግግር የሚረዱት በተሳሳተ መንገድ ነው።

"ዓይን ሁሉ ያዩታል" የሚለው አባባል ብዙ ሰዎች የሚመስላቸውነና የሚገምቱትን ነገር እንደማያመለክት ለመረዳት ይቸገራሉ።

እስቲ ልጠይቃችሁ፣ "ከደመና ጋር መምጣት" የተባለው ይህ ጉዳይ ምን ማለት ይመስላችኋል? እንዴትስ ትረዱታላችሁ? ይህንን በተመለከተ ሰባኪዎቻችሁ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎቻችሁ ምን ይነግሯችኋል? በደመና መምጣት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናቸ‍እሁ ለማየት ሞክራችሁ ታውቃላችሁ? ምስሉን በአእምሮ ውስጥ ለመገመትና ለመሳል አልሞከራችሁምን? አንዳች አርቲስቲካዊ ፈጠራ የሚከስተው ትዕይንት ውል አይልባችሁምን?

በዚህ ሁሉ መንገድ የዳበሩ እና የደነበሩ እነዚህ ሁሉ ግምቶቻችሁ የተሳሳቱ ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱን ለመፈተሽም ጊዜው አሁን ነው።

እሰቲ ኢሳይያስ 19: 1 ላይ የተጻፈውን አንብቡና ራሳችሁ ጉዳዩን ለማወቅ ሞክሩ። እንዲያውም፣ “ሁሉንም ፈትኑ” ስለተባልን እያንዳንዱ ክርስቲያን አማኝ ማድረግ ያለበት ይህንኑ ነው። ስለዚህ፣ መጽሐፉን ለማንበብ እንከፍታለን…

 ¹ ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።  

² ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።  

³ የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ምክራቸውንም አጠፋለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በድግምት የሚጠነቍሉትንም መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ጠንቋዮቻቸውንም ይጠይቃሉ። 

ይህ የያህዌ አሰራር ነው። ጉዳዩም የአምላክ መምጣት (አመጣጥ) ይባላል። አምላክ በደመና ክብር በፍርድ ይመጣል። ያህዌ ሲመጣ መምጣቱን በሚያመለክቱ በውጤቶቹ ውስጥ ይታያል  እንጂ በአካላዊ ዓይን በፍፁም እየታየ አይመጣም።

ኢየሱስ በትንቢት የተናገረለት መምጣቱም ተመሳሳይ ትርጉም አለው፤ ኢየሱስ ሲመጣም የሚመጣው በአምላከአዊ አመጣጥ ነው፣በአካላዊ ዓይን የሚታይ ሳይሆን በውጤቶቹ ውስጥ የሚታይ ነው።

ኢየሱስ “ … እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።” (ዮሓንስ 19 : 5) ሲል አባቱ ሲያደርግ የሚያየውን ብቻ እንደሚያደርግ ተናግሯል፣ስለዚህ "በአባቱ ክብር በሰማይ ደመና መምጣት" ማለት "በተመሳሳይ መንገድ" ወይም "አብ እንዳደረገው" ማለት ነው።

በአባቱ ክብር በሰማይ ደመና ለመምጣት የሰጠውን የተስፋ ቃል እንደተናገረው እንዲሁ ፈጽሞታል፤ ይህ ታላቅ የጥንት ቤተክርስቲያን የተባረከ ተስፋ በተየ‍ዘለት ቀነ ቀጠሮ አስቀድሞ ሆኖ አልፏል። ይህንን እንዴት እናውቃለን? ይህ ትንቢት ሊፈጸም በተያዘለት የጊዜ ወሰን በዚያው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ተፈጽሞ ባይሆን ኖሮ እንግዲያውስ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ሲናገር ውሸታም ነበር አልያም እብድ ነበር ማለት ነው። ልብ አድርጉ፣ ጌታን ኢየሱስን እንደ እግዚአብሔር ልጅ እና እንደ እውነተኛ ነብይ ለምናምን ለኛ እርሱ ስለመምጣቱ የሰጠውን የተሰፋ ቃል እመለሳለሁ ባለበት በገዛ ዘመኑ በትውልዱ ውስጥ ፈጽሞታል ብለን እውነታውን ከመቀበል ውጪ ለታማኝነቱ አምላክን የሚያከብር ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። ቤተ ክርስቲያን ለታማኝነቱ አምላክን ከሚያዋርድ ከንቱ የመጻኢነት ትምህርት ራሰዋን መነጠል ይገባታል።

ይህን ደግሞ ተመልከቱ፡-

ማቴዎስ 26:63-64

 ⁶³ ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው።  ⁶⁴ ኢየሱስም። አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው። 

ልብ አድርጉ፣ ቀያፋ የሞተው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ነው። ይህ “በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” የተባለውን ጉዳይ ሲሆን ለማየት እርሱም ሆነ በዚያን ቀን በካሀናቱ ሸንጎ ላይ የነበሩ የሊቀ ካህናቱ ባልደረቦች ክሰተቱን ለማየት ቃል ተገብቶላቸው ወይም በግልጽ ተነግሯቸው ነበርና ሲሆን እንዲያዩት በህይወት መኖር አለባቸው።

ጌታ ኢየሱስ ተመሳሳዩን ተስፋ ከደቀ መዛሙርቱ ለአንዳነዶች ሰጥቶ እንደነበረም እዩ፡-

ማቴዎስ 16:27-28

 ²⁷ የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።  ²⁸ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ። 

ኢየሱስ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለያዕቆብም ተመሳሳይ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። እንደ ቤተክርስቲያን ታሪክ ዘገባ ከሆነ ከዮሐንስ በስተቀር፣ ልክ ኢየሱስ ይፈርሳል ሲል በተናገረው ጊዜ ያኔ ቤተ መቅደሱ በፈረሰበት ጊዜ ከ70 ዓ.ም በፊት የሚበዙት አስቀድመው ሞተዋል።

ከዚያም ኢየሱስ የሰጠው ከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲህ ይላል፡-

ሉቃስ 23

 ²⁸-²⁹ ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ። እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን። መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ።  ³⁰ በዚያን ጊዜ ተራራዎችን። በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም። ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ 

ኢየሱስ ለእነዚያ በመስቀሉ መንገድ ለሚያለቅሱለት ሴቶች ሊደርስ ያለውን አስፈሪ ፍርድና ጥፋት እያመለከተ “ለእኔ አታልቅሱ፤ ነገር ግን ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ” ይላቸዋል።

ልብ አድርጉ፣ እንደገና… ኢየሱስ “ለራሳቸው እንዲያለቅሱ” ነው የነገራቸው። ለምን ለራሳቸው? ለምንስ ለልጆቻቸው አልቅሱ ይላቸዋል? ሊመጣ ያለው አስፈሪ ፍርድና ታላቁ ጥፋት እነርሱንና ልጆቻቸውን የማይመለከት፣ ገና ወደፊት ከሺሀዎች አመታት በኋላ የሚደርስ ጥፋት ከሆነ ማልቀሳቸው ጥቅሙ ምንድን ነው?

ኢየሱስ ስለ 2,000 ዓመታት የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው እየተናገረ ከሆነ እነዚያን ምስኪን ሴቶች ዋሽቶ ያለምንም ምክንያት እንዲፈሩ አድርጓቸዋል ማለት ነው። በግሌ ግን፣ ኢየሱስ እንደዋሻቸው ወይም እንዳታለላቸው አላምንም። ኢየሱስ የተናገራቸውን እነዚህን የመሰሉ የመምጣቱን ተስፋና የፍርዱን  ማስጠንቀቂያ ከመጽሐፍ ቀዱሴ ሳነብ ዛሬ ያሉት አብዛኛዎቹ 'የቅርብ ጊዜ መነጠቅ' ሰባኪዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መንጋዎቻቸውን እያታለሉ እና በከንቱ እያስፈራሩ እንደሆነ ይሰማኛል። ለምን እርግጠኛ ያልሆኑበትን እና በወጉ ያላጠኑትን ርዕሰ ጉዳይ አንጠልጥለው ወደ አትሮንሱ እንደሚሮጡ አይገባኝም። 

እስቲ ጥቂት ጨምረን ማንበባችንን እንቀጥል።

አሁን የምናነበው ይህ ክፍል ኢየሱስ እነዚያን ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ሲሆን እንደሚያዩት ያስጠነቀቃቸውን ያንንው ክስተት፣ እንዲሁም ለምን መፍራትና ማዘን እንዳለባቸው የሚገልጽ ሌላ መሰል ምንባብ  ነው፡

ራዕይ 6

 ¹³ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥  

¹⁴ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ።  

¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥  

¹⁶ ተራራዎችንና ዓለቶችንም። በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤  

¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው። 

ደግመን እንጠይቅ፣ ኢየሱስ ለእነዚያ ምስኪን ሴቶች ዋሽቷቸዋልን? ልክ የዛሬዎቹ እና የሚበዙቱ 'የቅርብ ዘመን ሰባኪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ እርሱም እነሱን ለማስፈራራት የሌሉና የማይመለከቷቸውን ነገሮች እየፈጠረ ነበርን? ኢየሱስ ሊመጣ ሰላለው ጉዳይና፣ ጉዳዩ ሊፈጸም ስለተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውምን? ሐሰተኛ ነቢይሰ ነበርን? ወይስ ትንቢቱ አንድም ሳይቀር በ70 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ጥፋት ወቅት ተፈጽሟል?ኢየሱስን እንደ እግዚአብሔር ልጅ እና እግዚአብሔር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው እንደ እውነተኛ ነብይ የሚያከብረው የትኛው ድምዳሜ ነው? ‘የምታመልኩተን ዛሬ ምረጡ” እንደተባለ በቃሉ ውስጥ አፍጦ ያለ እውነታን ለመቀበል ትመርጣላችሁ ወይስ ዘመን ጠገብ ኃሰት ታነግሳላችሁ? ምርጫው የናንተ ነው።

ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት የሚገዳችሁ ከሆነ ያንን የፈጠራ ትረካ ወይም የመጻኢነት የሰባኪ ዲሰኩር፣ ሰባኪው ምንም ያህል ተወዳጅና ዝነኛ ቢሆንም፣ ያ የመነጠቅ ሰባኪ በስብከቱ ቃል እያዋዛ ያቀረበውን ትረካና ዲስኩር አፋጦ መጠየቅ ምክንያታዊ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ለእነዚያ የኢየሩሳሌም ሴቶች በተናገረው ነገር ላይ ዋሽቷል ወይም ምን እያለ እንደነበር ለራሱም ግራ ተጋብቷል ወይም ያለውን ያለው ስለ ፍጻሜው ምንም ሳያውቅ እንደሆነ ማመን እና መቀበል ፈጽሞ ምክንያታዊ አይደለም፣ ምክንያቱም እርሱ እንዲህ ብሏል፡

ዮሐንስ 14

 ¹⁰ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። 

ይህ ጥቅስ  የዘዳግም 18:18 ትንቢት ፍጻሜ ነበር

 ¹⁸ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ 

እግዚአብሔር አብ እርሱ ራሱ ከዘላለም ቃል በሆነው በእግዚአብሕር ወልድ አፍ ቃሉን አድርጓል ብለን ለምናምን የቃሉ አማኞች ቃሉን እንዳለ በቀጥታ መውሰድን ሰጥቶናል።

አንድ ሰው ለእነዚያ ሴቶች በግልጽ የሚናገረውን ያንን የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ እርሱ በቀጥታ የተናገረውን ጉዳይ እንደማይናገር አድርጎ ለማመንስ ሆነ ለማስተማር እንዴት ይቀለዋል? ይህኮ የክህደት ጥግ ነው! አንዳንድ ሊቃውንት ተብየ ሰባኪዎች ኢየሱስ "በሰው መልክ" ሆኖ ስለሁሉም ነገር ምንም አያውቅም ሲሉ ይደመጣሉ፣ ነገር ግን ይህ ኢየሱስ አብ እንዲናገር የሰጠውን ቃል ብቻ እንደነገረን ሳይሆን የመሰለውን ከራሱ ነግሮናል ወደሚል ክህደት ውስጥ ወስዶ ይዶላል። 

ለእነዚያ ለሚያለቅሱ ሴቶች የተሰጠው ትንቢት በ67-70 ዓ.ም - ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው - በእነሱና በልጆቻቸው ትውልድ ተፈጽሟል። ስለ ታላቁ መከራ የተናገራቸው ትንቢቶች በኢየሩሳሌም ጥፋት ተፈጽመዋል፣ ይህም ማለት ኢየሱስ አልዋሸም ደግሞም አልተሳሳተም ማለት ነው። ማንም ሰው "ለኢየሱስ ውግኖ በመናገር" ቃሎቹን ለማቃናት ትብብር ማደረግ አያስፈልገውም፤ ይህንን ለማደረግ ጥረት ባደረግን መጠን ጌታችንን እና ትምህርቱን ለከሃድያንና ለተሳዳቢዎች ዱላ እናመቻቻለን። እንደ መጻኢነት እና እንደ ዘመን ቆጣሪው የነገረ ፍጻሜ የዞረበት ትምህርት ለክርስትናችን ስድብ የሆነ ትርጉም ያለ አይመስለኝም። የዕብራውያን 10:37 ጸሐፊ "ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይም!" ሲል" ያኔ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ተናግሮ ሳለ፣ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጽሐፉ አንባቢ መምጣቱ ዘገየ ብሎ ለማመን" ምንም ሰበብ ማቅረብ አያስፈልገውም።

ዮሐንስ 3፡ 16 ላይ የተሰጠውን ተስፋ አንብባችሁ ኢየሱስን ለዘላለም ህይወት ያመናችሁ ክርስቲያኖች፣ በትውልዳቸው በክብር ደመና በፍርድ እንደሚመጣ እና  ፍጻሜ እንደሚሆን የተናገረውን ቃሉን ከማመን የዘገያችሁት ማንን ፈርታችሁ ወይስ ማንን አፍራችሁ ነው? በእርግጥ ኢየሱስ በቃሎቹ ሁሉ የታመነ፣ በትክክልም የሚናገረውን የሆነ ነው። ሰው ግን በወደቀ ፍጥረቱ ውስጥ ምርጫ አለው፣ መንፈስ ቀዱስ አግዞት የእርሱን  ቃል ያምናል ወይም በተጣመመ ፈቃዱ አለማመንን እና ክህደትን ይከተላል። አንተስ የቱን ትመርጣላችሁ? ስለዚህስ ነገር ምን ትላላችሁ? ኢየሱስ ዋሽቷል፣ ተሳስቷል ብሎ ለማሰብ ትደፍራላችሁ? ይሄን ማለትስ ይቻላችኋል? መጻእኢነትን እና ዘመን ቆጣሪነትን ባመቻመቻችሁ መጠን ራሳችሁን ለዚህ ድፍረት ትሸጣላችሁ። በእውነት ስለዚህ ጉዳይ በጥሞና ለማሰብ ጊዜ ውሰዱ። የእግዚአብሔርን ቃል በተነገረበት አውድ አንብቡና አሰላስሉ። እውነቱ እንዲገለጥላችሁም ጸልዩ።

ልብ አድርጉ፣ ይህ የኢየሱስ ትንቢት ከ67-70 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ጥፋት ጊዜ ያልተፈጸመ ከሆነ፣ እንግዲያውስ በዘዳግም 18: 20-22 “  ²⁰ ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል።  ²¹ በልብህም። እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥  ²² ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው።” ሲል በተጻፈው በህጉ ቃል መሠረት፣ ኢየሱስ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር ማለት ነው፣ እናም መጽሐፍ ቅዱሳችን የማይጠቅም ከንቱ ድርሳን በመሆኑ ወዲያ መወርወር ያለበት ጊዜው ያለፈበት መጽሓፍ ነው ማለት ነው።

ለእኔ ግን እርሱ ውሸታም፣ ሐሰተኛ ነቢይ ወይም እብድ እንደሆነ ከማመን ይልቅ ትንቢት ገና ወደፊት ይፈጸማል ሲሉ የሚያስተምሩ የሚበዙት የዘመናችን የትንቢት ሊቃውንት ራሳቸው የሐሰት አስተማሪዎች ሆነው እንደተሳሳቱ ማመን በጣም ይቀለኛል። እኔን የቀለለኝ እንዲቀልህ የምትሻ ከሆነ ውሳኔው የአንተ ነው። እምታምነው ምንድን ነው? በውኑ ላንተ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው ወይስ እውነት አይደለም?

እሰቲ ምን ታምናለህ? የኢየሱስን ቃል በተነገረበት አውድ ልታምነው ትችላለህ ወይስ እንደ ቶማስ በራስህ ዓይን ካላየህ፣ ዳስሰህ ካላወቅህ አላምንም ትላለህ። ከሞት የመነሳቱን ዜና ሰምቶ ካላየሁ አላምንም ላለው ተጠራጣሪው ቶማስ እንደገና በአካል ተገልጦ በተጨባጭ ማስረጃ “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” (ዮሐንሰ 20:29) ሲል ትንሳአኤውን እንዳረጋገጠለት ሁሉ፣ የዳግመኛ ምጽዓቱን ፍጻሜ እርሱ ከሰጠው የታመነ ቃሉ ተነስተው ማመን ለሚቸገሩ ተጠራጣሪ “ክርስቲያኖች” ለትንቢቱ ፍጻሜ ደርዘን ሙሉ ተጨባጭ ታሪካዊ ማስረጃ ማቅረብ አይቸግረንም። ለእምነት ቤተሰብ ግን ቃሉን ማመን ብቻ ይበቃዋል። ችግሩ በኢየሱስ እናምናለን የሚሉ ብዙ ሰዎች እሱ የተናገረውን ነገር በትክክል አያምኑም ወይም አይረዱም።

አንዳንዶች እዚህ ጋር ቆም ይሉና፣ እንዴ ፓስተሬኮ በራዕይ 1:7 መሠረት ሲመጣ የሚያዩት እርሱ በሚመጣበት ጊዜ በሕይወት የኖሩ ሁሉ ናቸው ብሏል” ይሉ ይሆናል። ቃሉ ግን በትክክል ምን እየተናገረ እንደሆነ አያስተውሉም፣ 

እነሆ ቃሉ:-

ራዕይ 1:7

 ⁷ እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን። 

ይህ በአለም ታሪክ "በሕይወት የኖሩ ሁሉ" እነርሱም በዐይነ ሰጋ ስለማየታቸው፣ እርሱም በገሃድ በአካል ስለመታየቱ ምንም አይናገርም። በአፍሪካም ሆነ በአሜሪካ ውስጥ፣ ወይም በየትኛውም የምድር  ጥግ ስላለ ማንኛውም ተመልካች ማንንም አያመለክትም። በሰው ሰራሽ ስዕለ ስዕላት፣ ወይም ግምት ላይ በተመሰረተ አፈ ታሪክ፣ ወይም በፊልምና በድራማ ድርሰት ተጽዕኖ ውስጥ ወድቀን፣ በምናባችን ውስጥ የተከሰተ ቅዠት ተከትለን፣ ኢየሱስ ጥጥማ ደመናን እንደፈረስ እየጋለበ፣ ነጭ ክንፎች ያሏቸው መላእክትን በአጀብ አስከትሎ አየሩን ሰንጥቆ ሲመጣ ወይም ሲገለጥ የሚያሳዩት ምስሎች በአእመሯችን ውስጥ ይዘን፣ የዳግመኛ ምጽአቱን ተፈጥሮና ባሀርይ እነዲህና እንዲያ ነው ብንል ተረት ተከትለን እንስታለን። ከእነዚህ ዕሳቤዎች መካከል አንዳቸውም በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አይገኙም።

እስቲ ይህንን ታዋቂ ጥቅስ በጥቂቱ ቆፈር ቆፈር አድርገን እንመልከት፡-

የምድር ነገዶች ሁሉ”  (በግሪኩ pasai\ ai\ phylai\ tēs\ gēs) (ፓሳይ\አይ\ፊላይ\ቴስ\ጌስ) ከሚለው ሐረግ የተተረጎመው በተገቢ ሁኔታ ተተርጉሟል ይኸውም-- “የምድር ነገዶች ሁሉ- የሚለው በተለይም የብሔራዊ ማንነታቸው እና የቤተ መቅደስ ሥርዓታቸው ተንኮታኩቶ በመውደቁ በደረሰባቸው ሰብራት እጅግ አድርገው የሚያዝኑትን መላውን የእስራኤል ነገዶች ያመለክታል። ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን የሰሙ ወይም ያነበቡ ሰዎች እነርሱ የሚገባቸው በከሃዲዋ እስራኤል ላይ ኢየሱስ  ለፍርድ የሚመጣ እንደሆነ ብቻ ነው፣” -የንግግሩም ይዘት በዕብራይስጥ የፍርድን ቋንቋ አመላካች  አእንደሆነ ነው።

ነገር ግን ራዕይ 1፡7 ጨምሮ “የወጉት” ሰዎች ያዩታል ይላል፣ ይህም ያ የሚጠበቀው ክስተት በአካባቢ አውድ እና በጊዜ ሰሌዳ የተገደበ ጉዳይ መሆኑን እንድንረዳ በቂ ብርሃን ይሰጠናል። ይህም ኢየሱስን ለግፍ ፍርድ፣ በመስቀል ሞት ተወግቶ እንዲሞት አሳልፎ በመሰጠቱ ቀጥተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ለነበረው ለቀያፋ “ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” ሲል ከተናገረው ቃል ጋር በእጅጉ ይጣጣማል። እንዲሁም ቃላቱና ንግግሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነገሩላቸው እነ ጴጥሮስና እነ ዮሐንስ ገና በህይወት በነበሩበት ትውልድና ዘመን ውስጥ ያስቀምጠዋል።

ቀያፋ ወይም ጴጥሮስ ወይም ዮሐንስ ከሞቱ ከ2000 አመታት በኋላ ዛሬ እኔና እናንተ ባለንበት ትውልድና ዘመን ውስጥ እንዴት ሊያዩት ይችላሉ? አንዳንድ ሰባክያን እና የትንቢት ሊቀ ሊቃውንት ሁሉም ሰው ክስተቱን ማየት እንዲችል ትንሣኤን ያገኛል ብለው ምንጩ የማየታወቅ ትምህርት ያሰተጋባሉ፣ ዳሩ ግን እንደዚያ የሚናገር ጥቅስ ማንም ሰው ማግኘትና ጉዳዩን ግልጽ በሆነ የቃሉ ስነ ፍታቴ ሊያረጋግጥ አይችልም። ክርሰቲያኖች አትሳቱ፣ ማንም የሌለ ነገር እየደሰኮረና በልማድ እየተነዳ  እንዲያስታችሁም አትፍቀዱ። እምነታችሁን ጠይቁ፣ የምትሰሙትንና የምታነቡትን ሁሉንም ነገር ፈትናችሁ አረጋግጡ።

ወደ ኢሳይያስ 19:1 ተመልሰን አናንብቡ፤ በዚህ ከፍል መሰረት ያህዌ ፈጣን ደመና ላይ ወጥቶ እየጋለበ መጥቶ ነበር ወይ? ይህ ማለት በአካል ታይቷል ማለት አይደለም፣ እንደዚያ ብለው የሚያስቡ ግን አይታጡም። ይህ አይነቱ ንግግር ጌታ ኢየሱስም የተጠቀመበት ተመሳሳይ ምሳሌያዊ የፍርድ ቋንቋ ነው። 

ልብ አድርጉ፣ እንደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ያለ፣ አንድ ህጉንና ነቢያትን እያነበበና እየተማረ ያደገ አይሁዳዊ ልብሱን እስኪቀድና ተሳደቧል ተሳደቧል እያለ እሰኪጮህ ያደረሰው ጉዳይ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ለአይሁድ ከደመናት በላይ ከፍ ብሎ በደመናት ላይ የሚራመድ፣  ደመናን መሰወሪያው ያደረገ፣ በደመናት ላይ እየበረረ  የሚመጣ ያህዌ ብቻ ነው። ኢየሱስ በዚያ የሊቀ ካህናቱ ሸንጎ ፊት ቀያፋን ፊት ለፊት እያየ ቅጭም ብሎ “የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” ሲለው ይህንን የኢየሱስን ንግግር ስድብ ነው ብሎ በመጥራት የገዛ ራሱን ልብስ (ልብሰ ተክህኖውን) ቀደደ፣  በሌላ አነጋገር “ጨርቁን ጥሎ አበደ” እንደ ማለት ነው። ቀያፋ በቀጥታ የገባው ያ ከፊቱ ተጎሳቁሎ ለፍርድ የተጎተተ ሰው ልክ እንደ ያህዌ በደመና ለፍርድ እንደሚመጣ ነው። እግዚአብሔር አባቴ ነው በማለቱ ተከሶ የሞትን ፍረድ ሊቀበል እፊታቸው የቆመው ሰው በአባቱ ክብር  በሰማይ ደመና የሚመጣው ነው ብሎ ማሰቡ ራሱ ለቀያፋ አናት ፈጥፍጥ ደብረ በጥብጥ የሆነ መረዳት ነው።

ይህ የጌታችን ቃል ተፈጸመ፣ እንደ ሰጠው የተሰፋ ቃል በ70 ዓ.ም ላይ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም እና በመላው እሰራኤል ላይ በፍርድ ደመና ተመልሶ መጣ፣ ኃያሉን የሮማውያንን ጭፍራ በመጠቀም፣  ልክ እግዚአብሔር በባቢሎን፣ በግብፅና በኤዶም ላይ አሶርን ተጠቅሞ በፍርድ ይመጣ እንደነበረው ሁሉ፣ ጌታ ኢየሱስም ሮማውያንን ተጠቅሞ በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ በፍርድ መጣ።  

ነብያትን ሁሉ እና ራሱን መሲሁን የገደለችውን ታማኝ ሆና መገኘት ያልቻለችውን አመንዝራ ሚስት በፍርድ ለማስወገድ እመጣለሁ ባለበት መንገድ ለክ እንደተናገረው፣ አባቱም ያደርግ እንደነበረው ልጁም  በክብር ደመና "በአባቱ ክብር  መጥቶ ተዳሳሹን ፍርድ ፈጸመ። ይህ  የክብር ደመና የፍርድ ቋንቋ ነው። ኢየሱስና ያህዌ በደመና ላይ ተፈናጠው አይጋልቡም - ምናልባት ከምትወዱት ሰባኪ ወይም ዝነኛ ከሆነ የመድረክ ሰው የሰማችሁትና ስትሰሙት የኖራችሁት ወይም ከዘመናዊ ፊልም እና ስዕላ ስዕል  የወረሳቸሁት ምናባዊ ግምት ቢኖራችሁ እንዲህ ላለው ቅዠተኛ ግምት ግድ የለኝም። የምመክራችሁ ይህ ሁሉ የሰባኪ ትርክት እውነት ይሁን ውሸት ሁሉንም ነገር በቃሉ ሚዛን እየለካችሁ በራሳችሁ እንድታረጋግጡ ብቻ ነው።

ኢየሱስ እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድ ደመና ተመልሶ የመጣው በ70 ዓ.ም. ነው፤ ገና የሚፈጸም የቀረ የአዲስ ኪዳን ትንቢት፣ ወይም የሚጠበቅ ሌላ መጽዓት የለም። ይሄን ስለሰማ እንደ ቀያፋ ጨርቁን ጥሎ የሚያብድ መቼም አይታጣም። ልብ አድርጉ፣ በአይሁድ ሮም ጦርነት እስራኤል ተሸንፋ ከተማይቱ ስትሰበር ያኔ ሴፕቴምበር 8 ቤተ መቅደሱ በዕሳት ተቃጥሎ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፤ ያኔም ፍጻሜ ሆኗል። አዲሰ ኪዳን የሚናገርለት ፍጻሜ ሁሉ ከአሮጌው ኪዳን መወገድ ጋር የተጋመደ ሲሆን የዚያ ቤተመቀደስ የድንጋይ ክምር ሆኖ መፈራረስ የዚህ ፍጻሜ አይነተኛ ምልክት ነው። ይህም ኢየሱስ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለያዕቆብ (ማርቆስ 13:3) ለተቀሩትም በትውልዳቸው ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል ከገባላቸው ከ40 ዓመታት ገደማ በኋላ የተፈጸመ መሆኑ ነው።

ነገር ግን አሰቀድሞ በተያዘ የደቦ መረጃ እና ከተለያዩ ምንጮች በተገኘ እውቀት (ኮግኒቲቭ) አለመስማማት ምክንያት፣ የተለየ ታሪክ እየተነገራችሁ ካደጋችሁ እና ያንን መረጃ ለመፈተን እና ለመጠየቅ ድፍረቱ ከሌላችሁ፣ ይህንን የትንቢትአሰቀድሞ መፈጸም ጉዳይ አታምኑም። እንግዲህ የእውቀት (ኮግኒቲቭ) አለመግባባት የሚሰራው በዚህ መንገድ ነው። ግዴለም ዘሬ አትመኑ፣ የህችን ትንሽ ጽሑፍ ግን ኮፒ ፔስት አደርጋችሁ ለራሳችሁ ያዙት። በኋላ ላይ እንደገና መልሳችሁ ተመልከቱት። የተጠቀሱትንም ጥቅሶች ለራሳችሀ‍ኡ ከመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ላይ አንብቡ። ኢየሱስ ግልጽ በሆነ መልኩ ስለ ፍጻሜው ጊዜ ጠቋሚ በሆነ መንገድ የሰጠው ተስፋዎችም ላይ በቅንነት አሰላስሉ። የቅዱሳት መጻሕፍትን መገለጥ እና መረዳት እንዲሰጣተችሁም ጸልዩ። በመረጃ ብዛት ማስረጃን የሚያደበዝዝ የእውቀት (ኮግኒቲቭ) አለመግባባት ክምችትን ለማሸነፍ እና ምሽጎቹን ለማፍረስ ትህትናን እንደ ልብስ ታጠቁ -- የትንቢት መጻህፍት ሊቃውንትነት የሚሰማቸው እነዚያ የተሳሳቱ አስተማሪና ዝነኛ ሰባኪያን የነገሯችሁን እንደ ወረደ ተቀብላችሁ በትምህርታቸው ቆማችሁ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ያንን ትምህርት የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቅማችሁ እውነተኛነቱን ማረጋገጥ አትችሉም። 

ግዛቸው ———————


No comments:

Post a Comment