Wednesday, August 12, 2026

የተርጓሚው ብቃት

የመጽሓፍ ቅዱስ ተርጓሚ ሊኖረው ስለሚገባው  ብቃት።


BIBLICAL HERMENEUTICS ON THE INTERPRETATION OF THE OLD AND NEW TESTAMENTS. ከተሰኘው የሚልተን ቴሪ ሰፊ መድብል ካለው መጽሃፍ ላይ መጽሓፍ ቅዱስን ለማጥናት፣ በአግባቡ ለመተርጎምና ገልጦ ለማስተማር የሚያስችሉ መሰረታዊ ሆነው በስፋት ትንታኔ ከተሰጠባቸው ነጥቦች ላይ በብርቱ የተሞገትኩባቸውን ጉዳዮች ላካፍላችሁ።

  

ቅዱሳት መጻሕፍትን ብቃት ባለው እና ትክክለኛ በሆነ የትርጓሜ መርህ ለመረዳት ተፈጥሯዊም ሆነ ማናቸውም በልምድ የዳበሩ የተለያዩ ብቃቶች ያስፈልጉናል። ምንም እንኳን ይህ ከፍተኛ መጠን እና ስፋት ያለው የቅዱሳት መጽሐፍት ምንባብ በልጆች የመረዳት ችሎታ ልክ ሊቀርብ የሚችል፣ ህጻናትም እንኳ በበቂ ሁኔታ ሊማሩት እስኪቻላቸው ቀላል የሆነ፣ ለማንኛውም ሰው፣ ለተራውም ሕዝብ ሆነ ላልተማረው እንኳ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ለጽድቅ የሚጠቅም ብዙ ነገሮችን ሊያገኝ የሚያስችል ትምህርት ያለበት እንደሆነ ቢታመንም፤ ያም ሆኖ ትክክለኛውን ግንዛቤ እና ማብራሪያ ለማግኘት ግን እጅግ የላቀ የአዕምሮ ብቃት እና ሰፊ የሆነ የትምህርት ዝግጅት የሚያስፈልጋቸው ብዙ ነገሮችም አሉበት። ብቃት ያለው ተርጓሚ ካሉት በርካታ ዝግጅቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የመጀመሪያው አእምሯዊና ምሁራዊ ሲሆን እርሱን የአዕምሮ ዝግጅት ብለን እንጠራዋለን፣ ሁለተኛውንም ትምህርታዊ ብቃት ስንለው፣ ሶስተኛውን ደግሞ የመንፈሳዊ ህይወት አቋም ብለን ልንጠራው እንችላለን። የመጀመሪያዎቹ በአብዛኛው ከነፍስ ጋር ባላቸው ቁርኝት ሲታወቁ ለነፍሳችን ተፈጥሯዊ ዝምድና አላቸው፤ ሁለተኛው ደግሞ በትጉህ ጥናት እና ምርምር የሚዳብር ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ በልደታችን እንደተገኘ ውስጣዊ መሳብ እና ዝንባሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። 


ሀ. የአዕምሮ ዝግጅት፡


1. ጤናማ፣ እና ሚዛናዊ የሆነ አእምሮ፣ 

  • በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ሆነ ሌላ ማናቸውንም መጽሐፍ ለመተርጎምና ለመረዳት የሚወድ ሰው ጤናማና ሚዛናዊ አእምሮ ሊኖረው ይገባል። በቂ ያልሆነ ግንዛቤ፣ ጉድለት ያለበት ፍርድ እና ከልክ ያለፈ የቅዠት አሳብ የአንድን ሰው አስተሳሰብ ከማዛባቱም ባለፈ ወደ ብዙ ከንቱ እና የሞኝነት ሀሳቦች ይመራል። 


2. ፈጣን እና ግልጽ የሆነ የግንዛቤ ችሎታ፣ 

  • የደራሲውን ሀሳብ የመረዳት ሙሉ ኃይል እንዲሁም የንባብ ክፍሉን መቼት በዓይነ ሕሊና የመመልከት ብቃት ሊኖረው ይገባል።)


3. የአዕምሮ ብቃት 


  • የተለያዩ አስተሳሰቦችን ትስስር እና የሃሳቦችን ቁርኝት ወዲያውኑ ለመለየት የሚያስችል ወሳኝ እና ስል የሆነ የአዕምሮ ብቃት


4. ምናባዊ አስተሳሰብ ያለው ሆኖ ነገር ግን ያንን በቁጥጥር ስር አድርጎ እየገራ የሚጠቀምበት፣

  • እውነተኛ የሆነ ተርጓሚ ብዙውን ጊዜ ራሱን ወደ ቀደመው ታሪካዊ ዘመን መለስ እያደረገ የጥንቱን ዘመን ትዕይንቶች በነፍሱ ውስጥ መሳል መቻል ያስፈልገዋል። እራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ቦታ ለማስቀመጥ እና እነርሱ ይታያቸው እንደነበሩ ለማየት ይሰማቸውም እንደነበሩ እንዲሰማው የተፈጥሮ እና የሰው ሕይወት ተሞክሮ ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን በኃይለኛው ምናባዊ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከልኵ ያልፉና  ሰው ለማይገባውና ለማይረዳው ትንታኔ የተጋለጡ ተንታኞች መሆናቸው አይቀርም፤ ስለዚህ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ልጓም ሊበጅለት ያስፈልጋል። በቃላት ተሽሞንሙኖ የተንቆጠቆጠ አስተሳሰብ ከትክክለኛ የህሊና ፍርድ ሸሽቶ ተገቢነት ባለው ትርጓሜ ምትክ የገዛ ራስን ግምትና መላ መት መጋበዝ የሚችል ነው። የተገሠጸውና ስራአት የያዘ አስተሳሰብ ግን ከፅንሰ-ሀሳብ እና ረቂቅ ከሆኑ እሳቤ ኃይል ጋር ወስዶ ያቆራኛል። አስፈላጊ ከሆነም በማብራራት ሂደት ወይም በክርክር ውስጥ እውነትን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ አሳማኝ መላምቶችን መገንባት ይችላል።


5. ግልጽና ጤናማ  የሆነ ፍርድ ያለው 


  • ህቡዕ በሆኑ ትርጉሞች፣ በማመናፈስ  ሂደቶች እና አሳማኝነት በጎድላቸው ግምቶች ተጽዕኖ ስር እንዲወድቅ መፍቀድ የለበትም።


6. ጣዕም እና ጣፋጭነት ያለው ትክክለኛነት 

  • የትክክለኛነቱ ጣዕም እና በሚከተለው ትርጉም የሚደርስበት ድምዳሜው በእውነተኛ እና በሐሰተኛ ዕሳቤዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት መሰልጠን አለበት።


7. ትክክለኛ የአመክንዮ አጠቃቀም፣ 

  • መጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠን በሰው ቋንቋ ነው፣ ወደ እኛም ሲደርስ አመክንዮአችንን እና ፍርዳችንን ይጠይቃል፤ ምርመራንም ይጋብዛል፣ በዚያው ልክ ዕውር የሆነ የደቦ እምነትና አስተሳሰብን  ያወግዛል።


8. የማስተማር ብቃት፣ 

  • ቅዱሳት መጻሕፍትን ለራስ መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ እሱ ራሱ የተረዳውን ለሌሎች ግልጽና ሕያው በሆነ መንገድ መግለጽና ማስተማር ማስረዳትም፣ ራስን ለመጠየቅና በሌሎች ለመጠየቅ፣ ለሚጠይቁትም መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጀ መሆን አለበት።


ለ. የትምህርት ብቃት 


ቅዱሳት መጻሕፍትን ፕሮፌሽናል በሆነ ብቃት ለመተርጎም የተዘጋጀ ሰው ሚዛናዊ የሆነ አእምሮ፣ ብልህነት የተላበሰ አስተሳሰብ እና የአዕምሮ ጥልቀት ከማሳየት የበለጠ ነገር ሊኖረው ያስፈልገዋል። በተለያዩ የታሪክ፣ የሳይንስ እና የፍልስፍና ዘርፎች ሰፋ ያለ ግንዛቤና መረጃዎችን ቆፍሮ የማሰስ እና የማከማቸት ትጋት ይፈለግበታል። የሌሎች አስተማሪ ለመሆን ይቻለው ዘንድ ብዙ የአስተሳሰብ ነጻነት (ሊበራሊቲ) ሊኖረው ይገባል። መጻህፍትን በፍቅር የሚወድ፣ ልዩ ልዩ ጥናቶችን የማገላብጥ ችሎታውን በንባብ የሚያዳብር፣ የንባብ ዲሲፕሊን ያለው፥ በሚያደርገው ጥናቱና ምርምሩ ጠቃሚና ተግባራዊ የሆነ ዲሲፕሊን የሚከተል ሆኖ ብርቱ የሆነ የሃሳብ ልቀት፤ ሰፊ እና ትክክለኛ የሆነ እውቀትም ኖሮት ያንን ለሌሎች ለማስተላፍ እና ለማስተማር የተዘጋጀ እንዲሆን ያስፈልገዋል። የትምህርቱ  ብቃት ሊያካትታቸው የተገቡ ጉዳዮችን እንመልከት፦


1. የጂኦግራፊ እና የታሪክ እውቀት፣ 

  • የጥንታዊት እስራኤል እና በአጠቃላይ ፍልስጤም ምድር እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ አጎራባች ክልሎች ጂኦግራፊን፤ ጨምሮም ጥንታዊውን የእስራኤል ታሪክ ማወቅ የግድ ነው።


2. የዘመን አቆጣጠር እና የዘመን ልዩነት እውቀት፣ 

  • የክስተቶችን ቅደም ተከተል፣ የዘመናትን ልዩነት እና የክፍለ ዘመናትን አከፋፈል፣ የዘር ሐረግ ሰንጠረዦችን ወሰን እና የቀናትን ወሰን መለየት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ይህም ትእግስት የተሞላበት ጥናት እና አድካሚ የሆነ ጥንቃቄን ይጠይቃል።


3. የፖለቲካ፣ የሕግ እና የሲቪል መንግሥት ጥናት፣ 

  • ብዙውን ጊዜ በዕብራውያን ልማዶች ላይ ብርሃንን ሊሰጡን የሚችሉ በመሆናቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ የሆኑ የሌሎች ህዝቦችን ልማዶች፣ ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት በመቃርም የወቅቱን ጥንታዊ ብሔራትና ዘሮች ሁሉ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ዳራ መመርመር ያስፈልጋል።


4. የተፈጥሮ ሳይንስ እውቀት፣ 

  • በጂኦሎጂ፣ በማዕድን ቁፋሮ ጥናት እና በአስትሮኖሚ በጥቅሉ በተፈጥሮ ሳይንስ የተገኙ መረጃዎችና ማስረጃዎች እዚህ ላይ ተጠቃሽ ናቸው፤ የቅዱሳት መጻህፍት ጸሐፊዎች በሚያነሷቸው መግለጫዎች ወይም በሚያቀርቧቸው ማጣቀሻዎች እነዚህን ጉዳዮች ሊያመለክቱ ይችላሉ፤ ስለዚህም የጥንት ሰዎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያላቸው እውቀት ምንም ይሁን ምን፣ ዘመናዊው ተርጓሚ በዘመኑ የደረሰበትን እና ዘመናዊው ሳይንስ ያሳየውን አስታርቆ ማወቅ አለበት።


5. ፍልስፍና እና ሥነ ልቦና፣ 

  • ስለ ግምታዊ አስተሳሰብ፣ስለ ታሪክ እና ታሪካዊ ስርዓቶች፣ ስለተለያዩ የፍልስፍና እና የስነ-ልቦና አስተምህሮዎች ከላይ በቁጥር 4 እንደተጠቀሰው ሁሉ ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። በርካቶቹ እነዚህ ፍልስፍናዊ ውይይቶች በሥነ-መለኮታዊ ዶግማ ውስጥ ተሳትፎ ሊኖራቸው የሚችሉ ሲሆን እነርሱም ለየት ወዳሉ መርሆዎች እና የትርጓሜ ዘዴዎች ሊያመሩ ይችላሉ፤ ለአንድ ፕሮፌሽናል ለሆነ የቅዱሳት መጻህፍት ተርጓሚ እንዲህ ካሉ ፍልስፍናዊ ጉዳዮች ጋር ፍትሃዊ በሆነ ምንገድ መላመድ፥ ጥንቃቄ በተላበሰ መልኵ ጥቃቅን በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ያላቸውንም ተፅእኖ  ማወቅ ያስፈልገዋል።


6.የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎች እና የንጽጽር ፊሎሎጂ እውቀት፣

  • እንደዚህ አይነት እውቀት የሌለው ማንም ሰው ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን በማብራራት እና ገልጦ በማስተማር ሊቅ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። ከዕብራይስጥ እና ከጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ ጋር እንዲሁም ከጥንቶቹ የከለዳዊያን ሴማዊ ቋንቋ ጋር በደንብ መተዋወቅ ያስፈልጋል፣ በንጽጽራዊ ፊሎሎጂ ሳይንስ ውስጥም ማለትም የአንድን ቋንቋ ወይም የቋንቋዎችን አወቃቀር፣ ታሪካዊ እድገት እና ግንኙነቶችን የሚያካትት የእውቀት ዘርፍ ነው፤ በዚህ ውስጥም የተወሰነ ችሎታን መጨመር ያስፈልጋል።


7. ከአጠቃላይ ሥነ ጽሑፋዊ ዘውግ ጋር መተዋወቅ፣ 

  • የእግዚአብሔር ቃል ተርጓሚ የሆነ ሰው ከአጠቃላይ ሥነ ጽሑፋዊ ዘውግ ጋር ሊተዋወቅ እና በዘርፉ እውቀት ሊጨምር መቻል አለበት። የሰው ልጅ የጥበብ ችሎታና በዘመኑ የሰራቸው ታላላቅ ስራዎቹ፣ በዓለም ላይ የተፈጸሙ የታወቁት የታሪክ ክስተቶች፣ በሁሉም ታላላቅ ህዝቦች ዘንድ ያሉ የጽሁፍ ስራዎችና ክላሲኮች እንዲሁም በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ የአምላክን ንግግሮች ለሰው ያቀርባሉ ተብለው የሚታመኑ ቅዱሳት መጻህፍት ለሰው የቀረቡበት ስነ ጽሁፋዊ መንገድ ቃሉን በመተርጎም ረገድ ጠቀሜታ እንዳላቸው ማስተዋል ያስፈልጋል። በብዙዎቹ የስነ-ጽሑፍ ብቃቶች ውስጥ እጦት የማይገኝባቸው ብቁ የሆኑና ጥሩ የሆኑ ተንታኞች መኖራቸው አይካድም። ልቆ የሚገኝ መምህር ነኝ የሚል ማንም ሰው የትኛውንም የስነ-ጽሑፍ ስኬት እንደ አላስፈላጊ ተራ ነገር አድርጎ ሊቆጥረው አይችልም፤ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠንን እምነት ከጥርጣሬ እና ከክህደት በመጠበቅ እና በመከላከል ረገድ ክርስቲያናዊ የእምነት ተሟጋች እና የዕቅበተ እምነት ተጋድሎ የሚፈጽም የቃሉ ተንታኝ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ብቃቶች ሁሉ አስፈላጊነታቸውን አይጠራጠርም።


ሐ. መንፈሳዊ ህይወት አቋም


1. እነዚህ በከፊል የተገኙ ስጦታዎች ናቸው፣

  • አንድ ተርጓሚ ሊኖሩት ከሚገቡት ብቃቶች መካከል ይህ መንፈሳዊ ብለን የምንጠራው አንድ በከፊል እንደ ስጦታ ተደርጎ መታየት ያለበት ሲሆን በከፊል ደግሞ በግል ጥሞና እና በተገቢው ተግሣጽ ራስን ዲስፕሊን እያደረጕ የተገኙ ፍሬዎች ናቸው። በዚህ አይነተኛ የህይወት አቋም ስር ሁሉንም አይነት የሞራልና የእምነት ህይወት ባሕርያት፣ መንፈሳዊ ዝንባሌዎቻችንንና ስኬቶቻችንን እናስቀምጣለን። መንፈስ ሰውን ከአለማዊ መሻቱና ከስጋዊ ባህርይ ባርነት የሚለየው እና እግዚአብሔርን የማወቅና የመውደድ ፈቃድና አቅም እንዲኖረው የሚያደርገው ከፍ ያለ የሞራል ተፈጥሮ ነው። የዚህን መንፈሳዊ ተፈጥሮ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችል አስደናቂ መርህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገባ የተቀመጠ ሲሆን፤ ነገር ግን ያልዳነ ጠማማ ልብና ያልተለወጠ ሥጋዊ አእምሮ ክቡሩን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማስተናገድ የሚችል ፈቃደኛነት ላይኖረው ይችላል። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 2፡ 14 ላይ ሲናገር “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም” ይላል።


2. እውነትን የማወቅ ፍላጎት፣ 

  • ማንም ሰው ቢሆን እውነትን ለማወቅ ውስጣዊ ጉጉት እና ጥማት ከሌለው፣ የሚማር ልብም ከሌለው፣ ልቡም እውነትን በሚቃወም መሻት ተጸእኖ ስር ከወደቀ ወይም  ለህሊናውና ለፍርዱ ግልጽ ሆኖ  የሚቀርብለትን ነገር እንዳለ ለመቀበል የሚያመነታ ከሆነ እንግዲያውስ  የእግዚአብሔር መገለጥ ነው ተብሎ የሚታሰበውን ቃል ተገቢ በሆነ መንገድ ማጥናትና ማብራራት ከቶ አይቻለውም። እውነትን ለማግኘት ልባዊ ፍላጎትና ቁርጠኛ ዓላማ ሊኖር ይገባል፣ እውነት ላይ ሲደረስም ያንን በአክብሮትና በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል።


3. ጥልቀት እና ርኅራኄ ያለው ፍቅር፣ 

  • እውነትን የማወቅ ንፁህ ፍላጎት የሚጎለብተው ሥነ ምግባሩ ክቡር ለሆነ ለማናቸውም ነገር ባለን ጥልቅ ፍቅር ነው። እንዲህ ዓይነቱ ርኅራኄ የእግዚአብሔርም ሆነ የሰው የንጹህ ፍቅር መቀመጫ ነው።


4. ለእግዚአብሔር ቃል ጉጉት፣ 

  • በነፍስ ውስጥ ያለ እውነትን የመውደድ ጽኑ ፍቅር በውስጣችን ለእግዚአብሔር ቃል ጉጉትና ናፍቆት የሚያሰፍን የጋለና  ምንጊዜም ሲያበራ የሚኖር መንፈሳዊ ቅንዓት መሆን አለበት። ጥልቀትና ብቃት ባለው ትጋት ቃሉን የሚያጠናና የሚተረጉም ሰው እግዚአብሔር መንፈሱን የነካው እና ነፍሱን በሰማያዊ መገለጥ ሕያው ያደረገለት ሰው ነው።


5. ለእግዚአብሔር እና ለህጎቹ አክብሮት፣ 

  • እንዲህ ዓይነቱ የተቀደሰ ቅንዓት በእውነተኛ አክብሮት የተገዛ እና የምንቆጣጠረው ሊሆን ይገባል። በንጹህ ፍቅር የሚቀና አእምሮ እንዲሁም እውነትን የማወቅና ላወቁት እውነት የመገዛት ንፁህ ፍላጎት መኖር አለበት። የእግዚአብሔርን እውነተኛ እውቀት ለማግኘት ተግተው የሚፈልጉ ሁሉ በዚያው ልክ የተከበረና እውነትን የሚወድ መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያሉትን ይፈልጋቸዋል ራሱንም ይገልጥላቸዋል።


6. ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት፣ 

  • በመጨረሻም፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚወድና የሚማር ሰው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሕያው ኅብረት እና አንድነት ሊኖረው ይገባል። ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተሰጡ እስከሆኑ ድረስ (2ኛ ጢሞ. 3፥16)፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፊዎችም ከእግዚአብሔር የሆነውን ቃል በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የተናገሩ እስከሆኑ ድረስ (2ኛ ጴጥ. 1፥21)፣ ልክ እንደዚያው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉሞ የሚረዳ ሰውም አንዱን  መንፈስ ቅዱስ የተካፈለ መሆን አለበት። ያኔም በነፍሱ ውስጥ ባለው ጥልቅ ተሞክሮ የክርስቶስን የማዳን እውቀት እያገኘ በጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ ይሳባል፣ ከዚያ ተሞክሮ ጥልቀት እና ሙላት ጋር በሚመጣጠን መልኩም የመንፈስን አሳብ፣ መንፈሳዊውን ሕይወትና መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን ሰላም ያውቃል።


ማጠቃለያ

ይህንን ታላቅ የሆነ የቅዱሳት መጻህፍት መድብል ተራ በሆነ አካዳሚክ አቀራረብ ጠንቅቀን ልንረዳው አለመቻላችን ግልጽ ነው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የመንፈስ ቅዱስን አብርሆት አጥብቀን በጸሎት መፈለግ አለብን፡፡ አብርሆት ደግሞ እግዚአብሔር በነዚያ የቅዱሳት መጻህፍት ጽሁፎች አማካኝነት ራሱን ለእኛ መግለጹ ነው፡፡ አብርሆትም ት ጥ ቅ  የተባለ ሦስት ነገሮችን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ትምህርት በዚህ እናጠቃልላለን፦


  • unknown.png ትህትና (Humility) ይህ ፍጹም መደገፍ ነው፡፡ “ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (1ጴጥ 5፥ 5) እንደሚል ትህትና በእጅጉ ያስፈልገናል። ከፍጥረታችን እውሮች የሆንን እኛ አይናችንን ለቅዱሳት መጻህፍት መረዳት እንዲከፍትልን በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ አለብን፡፡ የተማሪ ልብ ይኑረን።


“ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።” (መዝ 119÷ 18)


“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህማስተዋል አትደገፍ” (ምሳ 3፥ 5)


“አለን የምንለው ላይብረሪ እና ጥናት ሁሉ እርሱን በትህትና ከመጠጋታችን ጋር ሲነጻጸር ባዶና ተራ ይሆናል” (ቻርልስ ስፕረጂዮን)


“ትህትና ጸጋን ሁሉ ሲመገብ ትዕቢት ግን ይራባል!” (ሪቻርድ ባክስተር)


  • unknown.png ጥንካሬ (Hard Working) ቃሉን በጥልቀት ለመረዳት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል

    “ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳ 2÷ 1-5)


የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ጊዜና ትጋት ይጠይቃል፡፡ ሥራው ለሰነፍ ሰዎች የሚሆን አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን እና ፈቃዱን ማወቅ ለየቀኑ ኑሯችን ጥንካሬን ይሰጠናል፣ ይኸውም ደግሞ ያለማቋረጥ ቃሉን ከማጥናት የሚመጣ ነው፡፡ በትጋት ውስጥ ለሚቆዩ ሰዎች መረዳቱ በጊዜ ውስጥ ቆይቶ መጣል፡፡ ይህንን ታላቅ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ለመረዳት ብርቱ ጥረት እያደረጋችሁ ከጸሎት ጋር ደግማችሁ ደጋግማችሁ ሳታቋርጡ አንብቡት፡፡


“በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤” (ቆላስ 4፥ 3)


“ተግቶ ማሰብ ሕይወት/ ኑሮ ነው” (ስፕረጂዮን)
“ተግቶ ማሰብ ትግል ነው” (ሲ.ኤስ. ሎቬት)


  • unknown.pngቅ ቅድስና (Holiness) እግዚአብሔር ራሱን በቃሉ በኩል እንዲገልጽልን የምንጠይቅ ከሆነ በቅድስና መመላለስ አለብን፡፡


“ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።” (ያዕ 1÷ 21)


“ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” (ዕብ 12÷ 14)


“እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” (1ጴጥሮስ 2÷ 1-3)



አምላክ ተሸፍኖ

Deus Absconditus

አምላክ ተሸፍኖ


የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። (ኢሳይያስ : 45: 15)


በሰሞነኛው ንባቤ ወደ ልጅነቴ ዘመን ትዘታ መልሶኝ ህይወቴንና አገልግሎቴን ለመቅረጽ በብዙ የናፈቅሁበትንና በዙሪያዬም የነበሩትነ በርካታ ከንቱ ትምሀርቶችና እሳቤዎች እያጠለልሁ ንጹሁንና በጎውን እውነት ለመጠጣት የተጋሁበትን አንድ ብርቱ ጉዳይ ለመዳሰስ እድል ሰጥቶኛል። ይኸውም ሉተር ያስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት በመባል ይታወቃል። ከንባቤ ግምገማ ተነስቼ ያቀረብኩላችሁን መለስተኛ እጥጥር ለማንበብ ትዕግስቱ ካላችሁ ትጠቀማላችሁ።


ይህ የነገረ መስቀል ትምህርት ማርቲን ሉተር በሥነ-መለኮት መረዳቱ ወስጥ በብርቱ ካነሳቸው ማዕከላዊ ጭብጦች መካከል አንዱና ዋናው ነው። ይህንንም በ1518 ሄይድልበርግ ላይ በተካሄደው ሥነ መለኮታዊ ሙግቱ ውስጥ በግልፅ አዘጋጅቶ፣ “የመስቀሉን ሥነ-መለኮት” ከ “ክብር ሥነ-መለኮት” ጋር ባለዉ ተቃርኖ አነጻጽሮ ያቀረበበት፣ የሉተርን ቁልፍ የተሃድሶ እሳቤዎች ቀደምትነት የሚወክል፣ በሉተራን አብያተ ክርስቲያናትም የሥነ መለኮት አውድ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።


መሠረታዊው ሀሳብ


ሉተር እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጠው በሰው ኃይል፣ በጥበብ፣ በስኬት ወይም ፍልስፍናዊነት በመላበት በሃይማኖታዊ ችሎታና ግኝት ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተቀበለው ስቃይና መከራ፣ በደረሰበት ድካም እና በመራር ሞቱ በኩል ነው ሲል ተከራክሯል።


ይህም ተሃድሶውን ያቀጣጠሉና ይመሩ የነበሩ ሥነ መለኮታዊ ሊቃውንት እግዚአብሔርን ማወቅንና መዳንን በተመለከተ እንዴት ያለ መግነጢሳዊ መረዳት እነደነበራቸውና መሠረታዊ የሆነ ለውጥን የሚያመጣ አቀራረብ እንደነበራቸው ማሳያ ነው፤ ይህም ከሰው አስተሳሰብ ወይም ከሚታዩ የሰው ሥራዎች ይልቅ የእግዚአብሔርን የማይታይ መለኮታዊ ባህርይ እና የክርስቶስን ስቃይ ማዕከላዊነት አፅንዖት የሚሰጥ ነው።


ሰዎች በተፈጥሮ እግዚአብሔር በክብርና በብርታት እንዲገለጥ ይጠብቃሉ። ሉተር ግን ይህ ተስፋ የተሳሳተ ነው ብሎ ያምን ነበር፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ታላቅ የማዳን ሥራ የመጣው ሽንፈት በሚመስል ነገር ተሰውሮ ነው - እርሱም የክርስቶስ ስቅለት ነው። በዚያ መስቀል ላይ ኃያሉ አምላክ የባሪያን መልክ ይዞ ድካምን ለበሰ። ለወደቀው ሰው አምላክን የማወቅ፣ የመገናኘትና በአውነተኛው አምላክ የመነካት እድል ሁሉ ተሰብሰቦና ተሸሽጎ ያለው በመስቀሉ መከራ ውስጥ ነው።


አስገራሚው ነገር፣ አስቀድሞ ሉተር በዊተንበርግ ካቴድራል በራፍ ላይ የቸነከራቸው እነዚያ 95ቱ የመቃወሚያ ፅንሰ ሀሳቦቹ ለሥነ-መለኮታዊ ክርክር የታሰቡ የነበሩ ቢሆኑም፣ ያ ክርክር ግን በሉተር የአገልግሎት ዘመን ፈጽሞ አልተካሄደም። ይሁን እንጂ ይህ የሄይደልበርግ ሙግት ሉተር በአካዳሚክ ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ላይ እንዲሳተፍ እና በቀደመው የተሃድሶ ዘመን የያዘውን ሥነ-መለኮታዊ አቋሙን እንዲያዳብር የበለጠ ተደማጭነትንም እንዲያገኝ አስፈላጊ ቦታን ሰጥቶታል። ክርክሩም የተሃድሶው ዘመን አዳሾች የነበራቸውን ብሩህ የአዕምሮ ልቀት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ሉተርም ሥነ-መለኮታዊ ግንዛቤዎቹን በመደበኛ የአካዳሚክ መከራከሪያ ነጥቦች እንዴት እያዳበረ እና እየተሟገተ እንደነበር የሚያመለክት የተባረከ አዕምሮው ማሳያ ነው።


የሄይደልበርግ ክርክር


በሄይደልበርግ ክርክር ውስጥ፣ ሉተር ፡-


# የክብር ስነ መለኮትን የሚያቀነቅን ‘ምሁር’ ክፉውን መልካም እና መልካሙንም ክፉ ብሎ የሚጠራ ነው፣  ​​ምክንያቱም በመልክ ብቻ ይፈርዳልና።


# በነገረ መስቀል ተቃኝቶ የመስቀሉን ስነ መለኮት የሚሰብክ ምሁር ግን አንድን ነገር በእውነቱ የሆነውን ያንንው ነገር ሳያሻሽልና ሳይቀባባ ምን እንደሆነ በምንነቱ ይገልጠዋል፣ ይጠራዋልም፤ ​​ምክንያቱም በክርስቶስ ስቅለት ብርሃን እውነታውን ስለሚያይ ነው ሲል በጽኑ ተከራክሯል።


ስለዚህ የምንከተለው ስነ መለኮት የክብር ይሁን የመስቀል፣ አተያየታችንን እና ፍርዳችንን ይወስናል። ለሉተር፣ የእግዚአብሔር እውነተኛ እውቀት የሚመጣው በፍልስፍናዊ ግምቶች ወይም በሰው ልጅ ስኬቶች ላይ በመተማመን ሳይሆን በተሰቀለው ክርስቶስ ውስጥ እና በኩል ነው ሲል ሞገቷል።


የክብር ሥነ-መለኮት የመስቀል ሥነ-መለኮትን ይቃረናል


# የክብር ሥነ-መለኮት፣ እግዚአብሔርን በኃይል፣ በስኬት፣ በተአምራት እና በሰው ጥበብ ሲፈልግ፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን እግዚአብሔርን በተሰቀለው ክርስቶስ በኩል ያገኛል።

 

# የክብር ሥነ-መለኮት፣ በሰው ልጅ ችሎታ እና በመልካም ሥራ ላይ ሲተማመን፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ብቻ ይደገፋል።


# የክብር ሥነ-መለኮት፣ የሰውን አእምሮና ያስተሳሰብ ልቀት ከፍ ከፍ  ሲያደርግ፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን በክርስቶስ ለተገለጠው ለእግዚአብሔር መገለጥ ብቻ ይገዛል፣ ይሰግዳልም።


# የክብር ሥነ-መለኮት፣ በገጽታ ግንባታ ስካር፣ በምድራዊ ክብር ጥማት፣ በኃይማኖታዊ የሥጋ ጥጋብ እና ልታይ ልታይ በሚል መጋጋጥ የሰውን ምስጋና ሲፈልግ፤ የመስቀል ሥነ-መለኮት ግን በትሕትናና በየዋህነት ከክርስቶስ ጋር መከራን ይቀበላል


የመስቀሉ ሥነ መለኮት ዋና ዋና ጭብጦች


1. እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ተሰውሯል

ሉተር እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ደካማ ወይም ሞኝነት ወይም ሽንፈት በሚመስል ነገር እንደሚሠራ አስተምሯል። መስቀሉ እንደ ሽንፈት ቢመስልም፣ በኃጢአት፣ በሞት እና በሰይጣን ላይ እግዚአብሔር የተቀዳጀው ፍጹሙ እና የመጨረቫው ድል ነው።


2. በእምነት ብቻ መጽደቅ

መስቀሉ መዳን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ያሳያል። ሰዎች ጽድቅን በክርስቶስ በማመን ብቻ ይቀበሉታል እንጂ በሥራ ሊያገኙት አይችሉም፤

 

3. የሰው ኃጢአት

መስቀሉ የኃጢአትን ከባድነት እና አስፈሪ የሆነውን መዘዙን ያጋልጣል። ከዚህም የኃጢአት ብርታት የሰው ልጅ ራሱን ማዳን ስላልቻለ የክርስቶስ ሞት የግድ አስፈላጊ ነበር።


4. የእግዚአብሔር ጸጋ

መስቀሉ ለኃጢአተኞች የእግዚአብሔር ፍቅር እና ምሕረት የላቀ ማሳያ ነው።


5. የክርስቲያን ሕይወት

አማኞች ዓለማዊ ክብርን ከመፈለግ ይልቅ ክርስቶስን በትሕትና፣ በንስሐ እና በመከራ እንዲከተሉ ተጠርተዋል። ሉተር መከራን ራሱን እያከበረው አልነበረም ፣ ነገር ግን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ተስፋዎች እየታመኑ ልዩ ልዩ ፈተናዎች እንዳሉባቸው በመጠበቅ በነገር ሁሉ ሥቃይን እና መከራን መታገሥ እንዳለባቸው አስተምሯል።


የመስቀሉ ሥነ መለኮት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቶች


ሉተር በክብር ሥነ-መለኮት እና በመስቀል ሥነ-መለኮት መካከል ያለውን  ልዩነት በያዘው ሥነ-መለኮታዊ አቋም ማዕቀፍ ውስጥ ማዕከላዊ ጭብጥ ሰጥቶ የተጠቀመበት አይነተኛ የንባብ ክፍል የሚከተለው ነው 


“እርሱም። እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። እግዚአብሔርም። እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። ደግሞም። ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። እግዚአብሔርም አለ። እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤” (ዘጸአት 33:18-23 )


በዚህ ክፍል ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት ይጠይቃል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ማንም ፊቱን አይቶ በሕይወት መኖር እንደማይችል ይመልስለታል። በምትኩ ግን፣ እግዚአብሔር ሲያልፍ ፊቱን ሳይሆን "ጀርባውን" እንዲያይ ለሙሴ ፈቀደለት። ሉተር ይህንን ክፍል ሲፈታ ስለ መለኮታዊ መገለጥ ተፈጥሮ ጥልቅ የሆነ ሥነ-መለኮታዊ ማብራሪያ አድርጎ ይተረጉመዋል። ለሉተር፣ ይህንን ሁኔታ “አምላካዊ  መሰወር” (በላቲን Deus absconditus) ብሎ ይጠራዋል፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ማንነት ለሰው ልጅ አመክነዮ በመሠረታዊነት አለመታወቁን የሚያመለክት ሥነ-መለኮታዊ እና ፍልስፍናዊ ፅንሰ-ሀሳብ ነው።  የእግዚአብሔር እውነተኛ ባህርይ እና መለኮታዊ መገለጡ የሰው ልጅ ተስፋ አድርጎ በሚጠባበቅበት ከፍ ባለ ክብርና ኃይል የሚደርግ ሳይሆን የልቁንም ከዚያ በተቃራኒው በትሕትናና በየዋህነት በመከራ ውስጥ በማለፍ የሚገለጥ ነው የሚለውን ሀሳብ በጽኑ ያሳያል። ከክብር ይልቅ መከራ ይኸውም የአግዚአበሔር ልጅ መከራ፣ እግዚአብሔር ወደ ሰው የሚመጣበት ያልታሰበና ያልተገመተ መንገዱ ነው።


ይህን ክፍል መሰርት አድርጎ ሉተር የክብር ሥነ-መለኮት ብሎ የሚጠራው ጉዳይ እግዚአብሔርን ለመረዳት የሚደርግ ሰውን ማዕከል ያደረገ የስብአዊ ጥረት  አቀራረብ እንደሆነ ይተቻል። ይህ አይነቱ ሥነ-መለኮት እግዚአብሔርን በኃይሉ፣ በግርማው፥ በሞገሱ እና ለሰው ጥበብ በሚታዩ ምልክቶች በኩል ለማወቅ የሚፈልግ ሰው በስጋው የሚመርጠውና ለስሜቱ  የሚመቸው መንገድ ነው። ይኸውም ልክ ሙሴ የእግዚአብሔርን ፊቱን ለማየት ባቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄው አንጻር የእግዚአብሔር ክብር በቀጥታ ሊገለጥ እንደሚችል ያስባል ማለት ነው። ሉተር ግን እንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊ አካሄድ እግዚአብሔርን የመረዳት ጉዳይ ወደተዛባ ግንዛቤ የሚመራ እንደሆነ በጽኑ ያስጠነቅቃል፣ ምክንያቱም ይህ አይነቱ ሰብአዊ ዝንባሌ በእምነት ላይ ሳይሆን በሰው አእምሮ እና ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው።


በአንጻሩ፣ የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ግን የእግዚአብሔር የመጨረሻ መገለጥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በደረሰበት ስቃይና ሞት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን የሚያንፀባርቅ ፓራዶክስን ያካትታል። ይህ ሥነ-መለኮት እግዚአብሔር ለሙሴ በዘጸአት 33፡18-23 ላይ ከሰጠው ምላሽ ጋር ይጣጣማል፣ እግዚአብሔር ራሱን በሙሉ ክብሩ ሳይሆን በተሸፈነ መንገድ ይገልጣል - ይኸውም "ጀርባው" የሚለው ነው። ለሉተር፣ ይህ መሸፈኛ የእግዚአብሔር እውነተኛ ሥራና መገኘት በመከራና በድክመት ውስጥ እንደተደበቀ ያመለክታል፣ ይህም ከሰው ልጅ የመለኮታዊ ኃይል ተስፋዎች ጋር የሚቃረን ነው። ጀርባውን እንጂ ፊቱን ማየት ማንንም አያድንም፣ የመስቀሉ ታሪክ እንጂ የሲናው ተራራ አስገራሚና አስፈሪ ተእይንት ማንንም አያድንም። እግዚአብሔር በመከራው ተሰውሮ ነው የተገለጠው እንጂ በክብሩ ተገልጦ አልተገለጠም!!


ሉተር ይህንን ዘጸአት 33:18-23 ያለውን ክፍል መሰረት አድርጎ የእግዚአብሔርን መንገድ ሲያብራራ ከሰው መንገድ ጋር ያለውን ተቃርኖ አጉልቶ ያሳያል። የሰው ልጅ አለኝ ደረስኩበት የሚለው ምክንያታዊነትም ሆነ በመሠረታዊነት እግዚአብሔርን ለመረዳት በራሱ የሚሄድበት ሰብአዊው ዝንባሌ መዳን የማይቻልበት መንገድ ነው፥ የእግዚአብሔር እውነተኛ እውቀት የሚገኘው ግን በተሰቀለው ክርስቶስ ላይ ባለ እምነት ብቻ ነው በማለት ይከራከራል። ይህ ክፍል የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጠው ለሰው በሚመች መንገድ፣ በሚያበራ ፊት፣ በድል አድራጊነትል ከፍታ ሳይሆን በመስቀሉ ትህትና እና ስቃይ በኩል ጀርባውን በማየት ነው የሚለውን ሀሳብ አጉልቶ ያሳያል። ለዚህም ነው ሉተር የስነ መለኮት ሰው የክብርን መንገድ ከመከተል ይልቅ የመስቀሉን  መንገድ የሚከተል መሆን አለበት በማለት አጥብቆ የሚናገረው።


ስለዚህ ይህ የዘጸአት 33:18-23 ያለው ምንባብ ለሉተር የመስቀሉን ሥነ-መለኮት በማዳበር ረገድ ወሳኝ ነው። ይህም የተሰወረውን የእግዚአብሔርን ክብር ድብቅነት ያሳያል፤ ስለ መለኮታዊ ኃይልና ግርማ መገለጥ የሰው ልጅ ያለውን ግምቶቹንና ተስፋዎቹንም ይገዳደራል። ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የሚደረገውን የትኛውንም የሰው መንገድና ሙከራ ውድቅ ያደርጋል። ለሉተር ይህ ክፍል የእግዚአብሔር የመጨረሻ መገለጥ የሚገኘው በመስቀሉ ፓራዶክስ ውስጥ ነው የሚለውን ሀሳብ ያጠናክራል፣ በዚያም መንገድ መለኮታዊ ብርታት በድካም ፍጹም ይሆናል።


ሌሎቹ ሉተር በአግባቡ ተርጉሞ ላቀረበው ሙግት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የንባብ ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፡-


# ለቆሮንቶስ ሰዎች በተጻፈው የመጀመሪያው መልእክት 1፡18–25 — “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው።”


# ለፊልጵስዩስ ሰዎችል በተጻፈው መልእክት 2፡5–11 — ክርስቶስ በመስቀል ላይ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ በመሆን ራሱን አዋረደ።


#ለሮሜ ሰዎች ውበተጻፈው መልእክት 3፡21–26 — እግዚአብሔር በክርስቶስ መስዋዕትነት ኃጢአተኞችን ያጸድቃል።


#በማርቆስ ወንጌል እንደተሰጠው ትዕዛዝ  8፡34 — “መስቀሉን ተሸክመህ ተከተለኝ።”


የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ዘላቂ ጠቀሜታ


ሉተር ያስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ለሉተራን ቤተክርስቲያን ሥነ-መለኮት መሠረት የሆነ እና በብዙ የፕሮቴስታንት ወጎች ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳደረ አስተምህሮ ነው። በዚህም ክርስቲያኖችን የሚያስታውሳቸው፡-


መዳን የሚመጣው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን፤

የእግዚአብሔር ኃይል በድካም የሚፈጸም መሆኑን፤

የክርስቶስ መስቀል የክርስቲያናዊ ሥነ-መለኮት ሁሉ ማዕከል መሆኑን፤ እነዲሁም፣

የክርስቲያን ሕይወት በእምነት፣ በትህትና፣ በንስሐ እና በትንሣኤ ኃይልየተቀረጸ መሆኑን ነው


ባጭሩ ሲጠቃለል፤ 

ሉተር ያስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት ማለት እግዚአብሔር በመስቀሉ በኩል ተሰውሯል ማለት ነው፥ በዚህም ምክንያት ሰብአዊ የሆነ በራስ የመተማመን አቅም ሁሉ፣ ስለ እግዚአብሔርም የሚነገሩ ሰው ወለድ ግምቶችና መላ ምቶች  ሁሉ ፍጻሜአቸውን እንደሚያገኙ ያሳያል። መስቀሉ በሰው ላይ የተላለፈ የፍርድ ምልክት ሲሆን በዚህም በራሱ የሚተማመን ሰብአዊ የሞራል ደረጃ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር አለኝ የሚለውን ኅብረት ግባአተ መሬት ይሰጠዋል። መስቀሉ በተፈጥሮው እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል እና ከእርሱ ጋር ባለን ሕብረት ባዘጋጀልን ሕይወት ውስጥ አብዝተን እና ከሁሉ አብለጠን የምንለማመደው የእግዚአብሔር መከራ ብቻ ነው።


ሉተር ባስተማረው የመስቀሉ ሥነ-መለኮት እግዚአብሔር ጥልቅ ባህሪውን እንደሚገልጥ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይና ሞት መዳንን እንደሚያከናውን አብራርቷል። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በሰው ኃይል ወይም በሰባአዊ ክብር ከመፈለግ ይልቅ፣ የእግዚአብሔር መከራ ብለን በምናውቀው፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣  ምሕረት እና ጸጋ ተገናኝተው ባሉበት በተሰቀለው ክርስቶስ ውስጥ እና በኩል እግዚአብሔርን በእውነት እንዲያውቁና ወድቀው እንዲሰግዱለትና እንዲገዙለት ያደርጋል። ሉተርን፣ በርሱ የተመራውን የቤተክርስቲያን ተሃድሶ እና አጠቃላዩን የፕሮቴስታንት እምነት በወጉ ለመረዳት የመሰቀሉን ስነመለኮት መረዳት ያስፈልጋል።

ከወደዳቸ‍ሁት፣  ይጠቅመናል፣ ያንጸናል ካላችሁ ለሌሎች ማጋራት ኣትርሱ።


ቸር ሰንብቱ

የደቀ መዝሙርነት ዋጋ

ደቀ መዝሙር እና የሚያስከፍለው ዋጋ


የዶ/ር ማርቲን ሉተርን “የመስቀሉ ሥነ መለኮት” የተሰኘ ትምህርቱን ካነበብሁ በኋላ የዲትሪች ቦንሆፈርን THE COST OF DISCIPLESHIP የተሰኘውን መጽሐፍ አንሰቼ በትምህርቱ መመሰጤን ቀጥያለሁ። የንባቤን ማጠቃለያ ባይሆንም ትኩረቴን ከሳቡ አብይ የመጽሐፉ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል   “ደቀ መዝሙርነትና መስቀሉ” የተሰኘውን የጽሁፉን  አንድ ክፍል ትምህርት በወፍ በረር ላሰቃኛችሁ።


በጥቅሉ ይህ  “THE COST OF DISCIPLESHIP  “የደቀ መዝሙርነት ዋጋ” የተሰኘው መጽሐፍ ዋናው መልእክት ኢየሱስን መከተል ቀላል ጉዳይ ወይም ላይ ላዩን ለይስሙላ የምናደርገው ዋዛ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያሳይ ግሩም ሥራ ነው፤ እውነተኛ ታዛዥነትን፣ ራስን መካድን እና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። በዚህ መጽሐፍ ሰማእቱ ቦንሆፈር “ርካሽ ጸጋን” “ውድ ከሆነ ጸጋ” ጋር ያነጻጽራል፣ እውነተኛ እምነትም የአንድን ሰው ሙሉ ሕይወት እንደሚለውጥ፣ መከራ መቀበልንና መስዋዕትነት ያለበትን ኑሮ ሊያካትት እንደሚችልም በጽኑ ይከራከራል።


የመጽሐፉ ዋናው ሀሳብ

የቦንሆፈር መጽሐፍ ማዕከላዊ ነጥብ ደቀ መዝሙርነት ማለት ክርስቶስ እንደጠራህ ለመኖር እና ለመሞት መኖር ማለት ነው፣ ጸጋንም እንደ ነፃ የይለፍ ፈቃድ ማመን ወይም ለኃጢአት ማመካኛ እንደተሰጠ ሊቼንሳ አድርጎ ማየትም አይደለም። መጽሐፉ በዋናነት ያተኮረው በተራራው ስብከት ላይ ሲሆን፣ ቦንሆፈር ክርስቶስን በተግባር መከተል ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት የተራራውን ስብከት ይጠቀምበታል። በአብዛኛው ከዚህ መጽሐፍ ጋር የተያያዘው ታዋቂው መስመር የዚህን ስብከት መልእክት ያጠቃልላል የኸውም ክርስቶስ አንድን ሰው እርሱን እንዲከተል ሲጠራው መጥቶ ለርሱ እንዲሞት ይጠራዋል የሚል ነው።


በቀላል አነጋገር መጽሐፉ እውነተኛ ክርስትናን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- እውነተኛ ክርስትና ዋጋ የሚያስከፍል ደግሞ ነው እነጂ ይቅርታ የምንቀበልበት ብቻ አይደለም። ከምቾት ወይም አምኛለሁ ደኛለሁ ብሎ ተደላድሎ ከመቀመጥ በላይ ለኢየሱስ በመታዘዝ፣ በመስዋዕትነት እና በታማኝነት የተቀረጸ ሕይወት ነው።


 “ደቀ መዝሙርነትና መስቀሉ”


በዚህ የዲትሪች ቦንሆፈር “የደቀ መዝሙርነት ዋጋ” በሚለው ክፍል ውስጥ፣ ከፍ ሲል እንዳነሳነው ማዕከላዊው መልእክቱ እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ከመስቀል የማይለይ መሆኑን አጽንዖት መስጠቱ ነው። ኢየሱስን መከተል እርሱን ማድነቅ፣ የተወሰኑ ትምህርቶቹን ማመን ወይም ከክርስትና ዕሴቶች ጥቅም ማግኘት ብቻ አይደለም። ራስን በመካድ፣ በመታዘዝ፣ በመከራ እና በመስዋዕትነት መንገድ ላይ ክርስቶስን የመከተል ታላቅ የሕይወት ጥሪ ነው።


ዋናው ሀሳብ፡- “ኑና ተከተሉኝ”


ቦንሆፈር በዚህ መጽሐፉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ተከተሉኝ” ሲል ያቀረበውን ጥሪ አፅንዖት ሰጥቶ ይናገርበታል። ይህ ጥሪ እውነተኛ የሆነ ልባዊ ምላሽ ይፈልጋል። የክርስትና እምነትም ስለ ክርስቶስ መረጃ መቀበል ማቀበል ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ በመመላለስ የሚገለጥ ራሱ መታዘዝ የሆነ ሕይወት ነው።


መስቀሉ ለደቀ መዝሙርነት ማዕከላዊ ነው


ኢየሱስ ሊሰቀል እንደመጣ ሁሉ፣ ደቀ መዝሙሩም የኢየሱስ መንገድ ወደ መስቀሉ እንደሚያመራ በውል መረዳት አለበት። ስለዚህ፣ እሱን የሚከተሉ ሰዎች ከመከራ ወይም ከመሥዋዕትነት የጸዳ ሕይወት መጠበቅ የለባቸውም። ቦንሆፈር ክርስቲያኖች መከራን ለራሳቸው ጥቅም ወይም ለጀብደኝነት ሲሉ መፈለግ አለባቸው ማለቱ አይደለም። ይልቁንም፣ የክርስቶስ እሴቶች ከዓለም እሴቶች ጋር የሚጋጩ ስለሆኑ፣ ለክርስቶስ የተሰጠ ታማኝ መታዘዝ የመከራን ሕይወት ሊያስከትል ይችላል እያለን ነው።


መስቀሉን ተሸክሞ መሄድ


መስቀሉን መሸከም ማለት፦

🎚️ራስን መካድ ነው - የራስ ጥቅም ላይ ያተኮረ ፍላጎትን በመተው የነፍስን ምኞት መከልከልና መቆጣጠር


🎚️ለክርስቶስ ፈቃድ መገዛት ነው - ክርስቶስ ሕይወትን እንዲመራ መፍቀድ።


🎚️መታዘዝ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ እንኳ በታማኝነት ለመቆም፣ ስቃይንም ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን።


🎚️ዕለት ዕለት ኢየሱስን መከተል - የዘወትር ልምምድ እንጂ የአንድ ጊዜ ውሳኔ ማድረግ ብቻ አይደለም።


ጸጋ እና ደቀ መዝሙርነት


በቦንሆፈር ሥነ-መለኮት ውስጥ የተንጸባረቀው አንዱ ዋና ጭብጥ በርካሽ ጸጋ እና ውድ በሆነ ጸጋ መካከል ያለው ንፅፅር ነው።


# ርካሽ ጸጋ እንዲህ ይላል፡- “ጸጋ ይቅርታ ነው፣ ​​ስለዚህ የተለወጠ ሕይወት ባይኖር እንኳ ይቅርታን መቀበል እችላለሁ።”

#ዋጋ ያለው ጸጋ ማለት የእግዚአብሔር ጸጋ ለእኛ ነፃ የሆነውን ያህል በዚያዉ ለክ ግን ክርስቶስን እንድንከተልም  ይጠራናል። ጸጋው ዋጋ ያለው ነው ምክንያቱም ሙሉ ሕይወታችንን ይጠይቃል፣ ሆኖም ግን ክርስቶስ ራሱ በሙሉ ሕይወታችን እርሱን የመከተል ችሎታን እና ግብዣን ስለሚሰጠን የጸጋው ዋጋ ራሱም ቢሆን የሚያስመካ የሰው ጥረት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ጸጋ ነው።


የመስቀሉ ትርጉም ለክርስቲያን


መስቀሉ ማለት የክርስትና ሕይወት ነው፣ በመሠረቱ ይህ ህይወት ከክርስቶስ ጋር ያለ የአንድነት ሕይወት ነው። የየሱስ ደቀ መዝሙር ስለ ኢየሱስ ከሩቁ ብቻ እየሰማ አይማርም። ደቀ መዝሙሩ ኢየሱስን ተጠግቶ ከርሱ ጋር እየተራመደ የሕይወቱን ምሳሌነት ይከተላል፤ በክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ በደቀ መዝሙሩም ታዛዥነት፣ ትህትና፣ ሌሎችን ማገልገል፣ መከራን መቀበል እና በመጨረሻም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ መታመን ይገባል።


በአንድ ዓረፍተ ነገር 


ቦንሆፈር እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ማለት ኢየሱስን የትም ቦታ መከተል ማለት እንደሆነ ያስተምራል፣ የኢየሱስ መንገድ ወደ መስቀል ስለሚያመራ፣ ደቀ መዝሙሩ ራሱን ለመካድ፣ ለታማኝነት ለመሰቃየት እና ለክርስቶስ ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ለመኖር ፈቃደኛ መሆን አለበት።


ይህ ክፍል በተለይ በማርቆስ 8:34 ላይ ከኢየሱስ ቃላት ጋር በጥሩ ሁኔታ ይገናኛል፡- “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።”

ማቴዎስ 24 በጥቂቱ

በማቴዎስ 24 ላይ ጥቂት ነገር ልበል


የክርስቶስ ዳግም ምጻትና የአለም ፍጻሜን ጨምሮ በጥቅሉ የተፈጸመው ወንጌል ትምህርት የሚወሳበት philologus66 የተሰኘውን የፌስ ቡክ ገጽ እና በሎገሬን እየሰነበቱም ቢሆን በየጊዜው ፎሎው የሚያደርጉ ወገኖች መኖራቸውን ልብ ብያለሁ። ጥቁቶችም ቢሆኑ የተከታታዮቼ ትጋትም ለበለጠ ስራ አበረታች ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በገጼ ላይ ተሰድረው አንባቢዎችን የሚጠባበቁ በርካታ የነገረ ፍጻሜ ትምህርቶቼንና ዘለግ ያሉ ጥሁፎቼን፣ ከዚህም በኋላ በየደረጃው የማቀርባቸውን ክታቦቼን ለማንበብ እንድትታደሙ በድጋሚ ተጋብዛችኋል። ለዛሬ በየማህበራዊ ሚድያው ትንቢትን እየተርጎሙ የሚያሰተምሩ በርካታ ሰባክያን በሚከተሉት ልማዳዊ ስነ ሓቲት ሊያስተውሉት የማይችሉትን ወይም የማይፈልጉትን አንድ ጉዳይ በማቴዎስ 24 ላይ ጥቂት ነገር ልበል።


በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ማቴዎስ 24 የሚያመለክተው በ33 ዓ.ም ከሆነው የመስቀሉ ታሪክ ጀምሮ በ70 ዓ.ም ላይ እስከ ደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋትና የቤተመቅደሱ ውድመት ድረስ ያለውን የ40 ዓመት ጊዜ ብቻ የሚሸፍን እንደሆነ አይረዱም፡፡ እውነታው ግን ያንን ብሩክ የእግዚአብሔር ልጅ ለመግደል አይሁድ የፈጸሙትን ወንጀል የሚመጥነው መለኮታዊ ፍርድ ጌታ ኢየሱስ በትንቢታዊ ቃል ያጸናውና በማቴዎስ 24 ላይ ከ40 አመታት በፊት ቀደም ብሎ የተናገረው አስፈሪ ትንቢታዊ ጥፋት በዚያው አንድ ትውልድ ውስጥ በ70 አ.ም ላይ መፈጸሙ ነው።  በወራሪው የሮም ኃይል መሳሪያነት የተከናወነው የ70ው አ.ም ክስተት የዚያ አሰፈሪ ትንቢታዊ ፍርድ ታሪካዊ ፍጻሜ ነበር እንጂ ታሪካዊ አጋጣሚ ብቻ አልነበረም።


በመጀመሪያ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “የመምጣትህና የአለም (የዘመኑ) ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁት (ማቴ. 24:3)፣ በጌታ የተነገራቸውን አስደንጋጩን የቤተ መቅደሱን የመፍረስ ጉዳይ በአእምሯቸው ይዘው መሆኑን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። ያንን አይነተኛ ጥያቄ ሊቀሰቅስ የሚችል ብቸኛ ሰበብ ኢየሱስ ፍርጥም ብሎ “ይፈርሳል” ያለው የዚያ ቤተመቅደስ መጻኢ እጣ ፈንታ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተለየ እነርሱ ከሚያውቁት የገዛ ራሳቸው የዚያን ዘመን አለም በዘለለ ስለ አጠቃላዩ ፍጥረተ አለም ፍጻሜ ሃሳብ ሊገባቸውና ሊያስጨንቃቸው የሚያስችል ምንም የተለየ ምክንያት አልነበራቸውም። ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስ አሰረግጦ ነግሮአቸው ነበርና (ማቴዎስ 24:2)። 


የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ሰበቡና ምንጩ ከየት እንደሆነ የማይታወቅ፣ ፈጽሞም የሌለና ሊኖር ወይም ሊሆን የማይችል፣ ወደፊት በቅርቡ ወይም በርቀት ይሆናል ብላ የምታስበው የዚህ ግዑዝ አለም ፍጻሜ  ይደርሳል ስትል ታስባለች ታስተምራለችም። ለዚህም መጽሓፍ ቅዱስዋን በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ ፖለቲካ አዙሪት ወይም በዓለም ኃያላን መንግስታት የፖለቲካ ጡዘት መነጽር አጮልቃ እያየች ትንቢትን ለመተርጎም ባላት ሙከራ መንገዷን ስታለች። እንዲህ ያለው መረዳት ግን በደቀመዛሙርቱና በጥንት ቤተክርስቲያን ዘንድ ያልነበረ፤ እንዲህ ያለው የዓለም ፍጻሜም የሚያሳስባትም የምትጠብቀውም ያልነበረ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ የዘመናችን ግራ ገብ መምህራን እና ሰባክያን መገለጫ ነው።


በማቴዎስ 24 ላይ መሰራት ያለበት ዋና ስራ፣ ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውና በምዕራፉ የተባለው ነገር ሁሉ እነርሱ ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጣቸው ምላሽ መሆኑን አጥርቶ ማየት ነው። የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄና የጥያቄው ምግፋኤ የሆነውን መሰረታዊ ምክንያት መረዳት ያልቻለ ተርጓሚ ነኝ ባይ የመምህሩን መልስ ሳያሰተውል አጥርቶ የማያውቀውን ነገረ ትንቢት ላስተምር እያለ ዘባርቆ ሌሎችን ያስታል። እርግጥ ነው፥ ጌታ ኢየሱስ ስለ ብዙ ነገር ነግሯቸዋል፤ ጥያቄው ግን የነገራቸው ነገር ሁሉ ለእነርሱ (ለበኩረ ተደራሲያኑ) ምን ማለት ነበሩ የሚለው ነው (ጦርነቱ፣ የጦርነቱ ወሬ፣ ሕዝብ በህዝብ ላይ መነሳቱ፣ ራቡ፣ ቸኑፈሩ፣ የምድር መናወጡ፣ የሰማዩ ላይ ምልክት፣ ወንጌል በአለም ሁሉ መሰበኩ፣ ወዘተ…)።


የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ የሚያጠነጥነው በታሪክ ዘመን ሁሉ ስለሚከሰቱና ገና ወደፊትም ስለሚከሰቱ ጉዳዮች ነበር ብሎ ማሰብ በእውነቱ እማይመስል ነገር ነው። በአእምሯቸው ውስጥ “አለማቀፋዊ ጉዳዮችን” እና “በታሪክ ዘመን ሁሉ የሚከሰቱ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን” ይዘው እንደጠየቁ አስቦና በዚህ እሳቤ ላይ ቆሞ “መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት” መረመርኩ ብሎ ትንቢትን ለመተርጎም መሞከር ውሎ አድሮ ለገዛ ራስም ሆነ አሰተውሎ ለሚሰማ መሰቅጠጡ አይቀርም።



ለደቀ መዛሙርቱ፣ የዚያ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መፍረስ እንደ አንድ ታላቅ ነውጥ እና ጥፋት ወይም የመላው ሃይማኖታዊ/ፖለቲካዊ ዓለማቸው ፍጻሜ አድርገው ያዩት ነበር እንጂ እንደዘመናችን ‘የትንቢት ሊቀ ጠበብት’ ነን ባዮች ስለ ግዑዝ አለም ፍጻሜ እሳቤውም አልነበረባቸውም። ስለዚህም አስቀድሞ በትንቢት “የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል።”   (ኢሳ. 66: 6) እንደተባለ፣ የዚያን ቤተ መቅደስ መፍረስ እና የከተማይቱን ውድቀት ከመሲሑ የመጨረሻ መምጣት እና ከዘመኑ ፍጻሜ ጋር አገናኝቶ ማየታቸው በህጉና በነቢያት የተነገረ ስለሆነ መሆኑን እናስተውላለን። ጠያቂዎቹንና ለጥያቄአቸው ምላሽ የሰጣቸውን ነቢዩ ኢየሱስን በህጉና በነብያቱ ከተነገረው ቃል አውድ አውጥተን በአለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካና የሃይማኖት ስንክሳር አውድ ውስጥ እንደመፈለግ ያለ ግራ የገባው ስነ መለኮት አይግጠማችሁ።


ተመልከቱ፣ ኢየሱስ “ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ” (ማቴ. 24:24) ብሏቸዋል። የብዙ አስመሳዮችና ሃሰተኞች መነሳት የመጨረሻው ዘመን መድረሱን የሚያሳይ አይነተኛ ምልክት ነበር። ሐዋርያው ​​ዮሐንስም ይህ ያኔ ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ እየተፈጸመ መሆኑን ተረድቶ ስለ ነበር፣  “ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።” (1ኛ ዮሐንስ 2:18) ሲል ይጽፋል። ዮሐንስ በዚህ ጥቅስ ላይ ለአንባቢዎቹ “ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች” ስለተነሡ “የመጨረሻው ሰዓት” (የመጽሐፍ ቅዱስ የአይሁድ እምነት የመጨረሻ ሰዓት) መሆኑን ማወቅ እንደሚችሉ በግልጽ ይነግራቸዋል። በሌላ አነጋገር፣ ኢየሱስ ብዙ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት በመጨረሻው ዘመን እንደሚመጡ ስለተናገረ፣ ዮሐንስና ሌሎች ክርስቲያኖች ፍጻሜው ያኔ በእርግጥ እንደቀረበ ያውቁ ነበር፤ ምክንያቱም ብዙዎቹ አሳቾች አስቀድመው ያኔውኑ ታይተው ስለነበር ነው።


ጨምሮም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፣ “ይህ የመንግሥት ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” (ማቴ. 24:14)። ደቀ መዛሙርቱ ‘መቼ ነው’ ሲሉ የጠየቁት መጨረሻና ኢየሱስ ‘ይመጣል’ ያለው መጨረሻ አንድ መጨረሻ ነው፤ እርሱም ወንጌል ለአህዛብ ሁሉ ከተሰበከ በኋላ በገዛ ትውልዳቸው ውስጥ የሚመጣ የዚያ ዘመን ወይም አለም መጨረሻ ነው። የዚህን ፍጻሜ ማወቅ ብትሹ፣  የሮሜ መጽሐፍና የቆላስይስ መጽሐፍ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በተጻፉበት ጊዜ የምሥራቹ ወንጌል ያኔ በነበረው ዓለም ሁሉ ተሰብኮ እንደነበር ሓዋርያው ጳውሎስ በግልጽ መናገሩን ታስተውላላችሁ። ሮሜ 10: 18 ላይ፣ “ድምፃቸው (የምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች ድምፅ) ወደ ምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም (የስብከታቸው ቃል) እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ወጣ።” ይለናል፤ ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአለም  ዳርቻ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ወሰኑን አስበን ካላነበብነው በትርጉማችን ልንስት በአስተምህሯችንም ልናሳስት እንችላለን። በቆላሰይሰ. 1: 23 ላይ ደግሞ፣ “ይህ…ወንጌል… ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኳል።” ሲል አስረግጦ ይናገራል። የሮሜ ሰዎች እምነት ያኔ ገና በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዚያን ዘመን በነበረው የሮም ዓለም (በመላው ዓለም) የተወራ እንደ ነበረ ዻውሎስ ሲመሰክርና በዚህ ምክንያት ሰ‍ለሁላቸው እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ነገሩን እያጋነነ አለነበረም (ሮሜ 1፡ 7)። ስለዚህ ያኔ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ወንጌል በዓለም ሁሉ ተሰብኮ ከነበር እንግዲያውስ ከዚያ አለማቀፋዊ የወንጌልና የሚስዮን ስራ መጠናቀቅ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በመጣበት ፍርድ የአሮጌውን ኪዳን ዓለም ፍጻሜ ሰጥቶታል፤ ይኸውም በ70 ዓ.ም ላይ የክርስቶስ ጠላቶች የሆኑትን ክርስቶስንና ቤተክርስቲያኑን እስከ ጥግ ድረስ በጽኑ መከራ ያሳደዱትን ትውልዶች በዳግመኛ ምጻቱ  ሲያጠፋቸው በእሳት ፍርድ የመጣበት ምጻቱ ነው። ከዚህ ሌላ የሚጠበቅ ምጻት ሁሉ አዲስ ኪዳን የማያስተምረው ባዶ ተረትና እንግዳ ትምህርት ነው።


በመጨረሻም፣ በማቴዎስ 24 ላይ፣ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ አያልፍም” ብሏል። “ይህ ትውልድ” የሚለው ቃል እዚህ ላይ በአብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን ሌሎች ቦታዎች ላይ እንደሚናገረው ያው ተመሳሳይ ነገር ማለት ነው። ያኔ ይህ ሲነገር ቆመው ይሰሙ የነበሩትን ቀጥተኛ አድማጮቹን የትውልድ ዘመን ያመለክታል እንጂ እነርሱ ከነበሩበት ዘመን ወጭ በተለየ ሌላ ዘመን የሚኖሩትን ማናቸውንም ወይም እኛ ያለንበትን ትውልድ ወይም ገና የሚመጣ ሌላ ትውልድ አይመለከትም። የትንቢቱ ቃል በግልጽ በዚያን ጊዜ ስለሚኖሩት ሰዎች ብቻ ይናገራል። ይህ ትውልድ የሚለውን ያ ትውልድ ብሎ እንደማንበብና መተርጎም ያለ ድርቅና (ግግምና) ሌላ የሚገርመኝ ነገር የለም። ስለዚህ የማቴዎስ 24 በሙሉ በመስቀሉና በኢየሩሳሌም ጥፋት መካከል ባለው የአርባ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሆነውን አካቶ ይዟል፤ ፓሩሲያውንና የዘመኑን ፍጻሜ ጨምሮ ሁሉ ተፈጽሟል።


በልማዳዊው የመጻአኢነት ሸውራራ መነጽር የዘመን ቆጣርያንን ትርጉም እያየ፣ በቃሉ መንፈስ ሳይሆን በመካከለኛውን ምስራቅ የጂኦ ፖለቲካ ትኩሳት እየጋለ፣ በክርሰቲያናዊ ጽዮናዊነት ፈረስ የሚጋልበው ስነ ፍታቴ መጨረሻው መጽናናት በማይገኝበት የደነበረ የሸብር ወንጌል ተመርቶ ምህዋሩን ስቶ ገደል መግባት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ፊት ስለሚመጣ አለማቀፋዊ ክስተት የሚናገር የንግርት፣ የሟርትና የጥንቆላ መጽሐፍ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ፈቃድ ያልመጣ፣ ሰለ እኛ የተጻፈ እንጂ በቀጥታ ለእኛ ያልተጻፈ ትንቢት ነው። ትንቢትነቱም ለእኛ ሳይሆን ለገዛ ራሱ በኩረ ተደራስያንና ለታሪካዊ አውዱ ነው። መጠናትም መተርጎምም ያለበት በዚያው አውድ ማዕቀፍ ውስጥ ነው። አውድ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥናት ንግስቲቱ ናት፤ ለእርሷም ዋጋ የማይሰጥና ይሄንን መርህ ያላከበረ ተርጓሚና የትንቢት አሰተማሪ በግራ ገብ ልዩ ወንጌል ስብከቱ ታዋቂነትን እንጂ እውቀትን አያተርፍም።


በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ዘርዘር ያለ ማብራሪያን ለማግኘት ፍላጎቱ ያላችሁ የሚከተሉትን የብሎገር ማሰፈንጠሪያዎች እየከፈታችሁ ብትመለከቱ በማቴወሰ 24 ላይ በተከታታይ የቀረበ ትምህርት ታገኛላችሁ።


https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_60.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_33.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_91.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_95.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_32.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_93.html?m=1

https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_43.html?m=1


ግዛቸው።