Sunday, April 21, 2024

የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ተራዝሟልን?

የዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ ተራዝሟልን?

ጌታ ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ ተመልሶ ለመምጣት በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ዘግይቶ እንደሚመለስ አስተምሮ ነበር ወይ? ለዚህ ጥያቄ መልሳቸው  “አዎን! አስተምሮ ነበር” ብለው የሚሉ የቃሉ አንባብያን ብዙውን ጊዜ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ወደተዘገቡ ወደሚከተሉት ሁለት ምንባባት ጠቅሰው ያመለክታሉ።  በአስሩ ቆነጃጅት ምሳሌ፣ ሙሽራው ራሱ ጌታችንን የሚወክል ሲሆን፣ እርሱም በዚያ ምሽት ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ እስኪላቸውና እስከ እኩለ ለሊት ድረስ መምጫውን እንዳዘገየ በንባብ ክፍሉ ተነግሯል (ማቴ. 25፥ 1–13)።  በተመሳሳይም፣ መክሊትን በተቀበሉ ባሮች ምሳሌ፣ ጌታው የተባለው ራሱን ጌታችንን የሚወክል ሲሆን ፣ እርሱም ወደ ሩቅ አገር ተጉዞ “ከብዙ ዘመን በኋላ” እንደተመለሰ (ማቴ. 25፥ 14–30) ተነግሯል።  በእነዚህ በሁለቱም ምሳሌዎች ገጸ ባህርዩ በሙሽራው ወይም በጌታው የተወከለው ጌታ ኢየሱስ፣  ረዘም ላለ ጊዜ፣ ምናልባትም (አንዳንድ የድህረ-ሺህ ዓመታት እምነት አራማጆች እንደሚሉት) በሺህዎችና በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሳይመጣ እንደሚዘገይ ወይም ምጽአቱ ከመሆኑ በፊት ብዙ ዘመን እንደሚያልፍ ተናግሯል፣ ሲሉ ይደመጣሉ።

ይህንን መደምደሚያ ውድቅ ለማድረግ ሁለት ዋና ዋና ምላሾችን ከራሱ ከምንባብ ክፍሉ ልንገራችሁ፦ 

# በመጀመሪያ፣ በምሳሌው ውስጥ ሙሽራው ተመልሶ የመጣው እነዚያው ቆነጃጅት በህይወት እያሉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፣ የሚል ነው።  በቆነጃጅቱ ምሳሌ ላይ ሙሽራው የተመለሰው እነዚያው ያልተዘጋጁ ቆነጃጅት ገና በህይወት እያሉና ዘይት ሊገዙ በሄዱበት ወቅት ነው፤ ስለዚህ እነርሱ ገና በሕይወት እያሉ በገዛ ዘመናቸው ያኔውኑ ምጽአቱ ሳይደርስ አልቀረም።  መክሊትን በተቀበሉ ባሮች ምሳሌም ውስጥም ያየነው እንደሆነ ጌታው ሊቆጣጠራቸውና አደራውን ከትርፉ ጋር መልሶ ሊረከብ ተመልሶ የመጣው ወደነዚያው መክሊቱን ወደ ሰጣቸው የሰዎች ቡድን ነው። ወደ እነርሱም ተመልሶ መክሊታቸውን እንዴት እንደተጠቀሙበት ካየ በኋላ ከእነርሱ መካከል በጎ ያደረጉትን ሸልሟቸዋል። ከእነርሱም መካከል ክፉ ያደረጉትን ዘልፎ ቀጥቷቸዋል።  ይህ በግልጽ የሚያሳየን ተመልሶ የመጣው አደራውን በተቀበሉት ሰዎች የሕይወት ዘመን ውስጥ መሆኑን ነው። ጌታ አደራውን ወደተቀበሉት እንጂ አደራውን ሲሰጥ ወዳልነበሩት ሰዎች አልመጣም፣ አይመጣምም።

ጌታ ኢየሱስ ይህንን  በማቴዎስ  ወንጌል የተዘገበ ንግግሩን ሲያደርግ ጊዜው  በ30 ዓ.ም አካባቢ ነበር - ተመልሶ ለመምጣት ተስፋ የሰጠውም እርሱ እየተናገራቸው በነበሩት ሰዎች የሕይወት ዘመን/ትውልድ ውስጥ የመሆኑ እውነታ  ኢየሱስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በሌሎች በርካታ የአዲስ ኪዳን ምንባባትና መግለጫዎች ውስጥ  ከተናገራቸው  ሌሎች ንግግሮቹ ጋር ፍጹም ይዛመዳል።  ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 16፥ ​28 ላይ፣ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ  በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች መካከል [የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አድማጮቹን ነው]፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ” ብሏል። በማቴዎስ 24፥ 30-34 ላይም፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡- “የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል… ይህ ሁሉ (ዳግመኛ ምጽአቱን ጨምሮ) እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም" በማለት ተናግሯል። (በተጨማሪ ማቴዎስ 10፥ 23 እና 26፥ 64 ላይ ያለውን ተመልከቱ)። 

ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ባሉት ሁለት ምሳሌዎች ውስጥ ከተናገረውና በነዚህ ንግግሮቹ ከተገለጠው አመጣጡ በተለየ ሊታሰብና ሊገመት የሚችል ሌላ አመጣጥን በሌላ በየትም የንባብ ክፍል ተናገሮ እንደነበር ሊጠቁም የሚችል አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ በየትኛውም የአዲስ ኪዳን ገጽ ማግኘት አይቻልም።  ኢየሱስ በእርግጠኝነት ስለ ሌላ አይነት መምጣት ተናግሮ ቢሆን ኖሮ፣  የወንግሉ ጸሐፊ ማቴዎስም ያንንው በዘገበልን ነበር።  ስለ ዳግም ምጽአቱም ሆነ ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች በወንጌላዊው የተዘገበ ማንኛውም የኢየሱስ ንግግር  መነበብ ያለበትም በአውዱ ውስጥ ነው፣ እንጂ የራሳችንን ግምትና ትርጉም በምንባቡ ውስጥ ለመሰንቀር ምንም መብት የለንም። እንደዚያ በማድረግ ቃሉን ለራሳችን ፍጆታ ግምቶቻችን ውስጥ የምንፈልገው ከሆነም ይህ  Exegesis [ኤክሰጀሲስ] ሳይሆን Eisegesis [ኢይሴጀሲስ] ይሆናል። [ማስታወሻ፣ Eisegesis ማለት፡- “የአንድን ሰው ቅድመ-ግምት እና የአስተሳሰብ ዝንባሌውን በምንባብ ውስጥ አስገብቶ (ሰንቅሮ) ማንበብ” ማለት ነው።  በሌላ በኩል ግን  Exegesis ፡- “የንባብ ክፍሉ ራሱ ስለራሱ እንዲናገር ማድረግ” ማለት ነው።]

ኢየሱስ በምሳሌዎቹ ውስጥ ስለ ሌላ መምጣት እየተናገረ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ኢየሱስ ራሱ ወይም ማቴዎስ እንዲሁ ያለ ነገር ይናገሩ ነበር!  ያንን ግን አላደረጉም።.

# ሁለተኛ፣ ዳግመኛ ምጽአቱ ረዘም ላለ ጊዜ ይዘገያል እንጂ ቶሎ አይሆንም ሲሉ  ይጠብቁ የነበሩት በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ዓመፀኛ ሰዎች ናቸው እንጂ ጻድቃን የሆኑ የቤተክርስቲያን ቅዱሳን አልነበሩም። በምሳሌዎቹ  በክፉ አገልጋይ ምሳሌ የጠቀሳቸው፣ "ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል" ያሉትን እነዚህን ሰዎች ጌታ ኢየሱስ “ክፉ ባርያዎች” ብሏቸዋል (ማቴ. 24፥ 48)።  ጳውሎስም “የጨለማ ልጆች” በማለት ገልጿቸዋል (1 ተሰ. 5፥ 3-5)።  ጴጥሮስም “ዘባቾች” ብሏቸዋል (2ጴጥ. 3፥ 3-4)።  ጻድቃን ግን ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚመጣ ያምኑና ይጠባበቁ፣ ያስጠነቀቁም ነበር (ያዕ. 5፥ 7፣ 1 ጴጥ. 4፥ 17፣ ፊልጵ. 4፥ 5፣ ራዕ. 22፥ 6–12)።

ኢየሱስ በእስሩ ቆነጃጅት ምሳሌ ስለ “መዘግየት” መናገሩ እውነት ነው፣ (ይህም በ30 ዓ.ም ላይ የተነገረ ነው)።  በ60 ዓ.ም ላይ ግን፣ የዕብራውያን ጸሐፊ፦ "ሊመጣ ያለው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይመጣል አይዘገይምም" (ዕብራ. 10:36) ሲል መዘግየት እንደማይኖር በግልጽ ተናግሯል።

የኢየሱስ በምሳሌዎቹ ያነሳው "የመዘግየት" ሀሳብ ለአርባ ዓመት (ለአንድ ትውልድ) የሚቆየውን መዘግየት ነበር፣ እንጂ ይሄን ያህል በሺህዎች ለሚቆጠር ዘመን ሳይመጣ ይቆያል ማለት አይደለም። ይልቁንም፣  ኢየሱስ በፍርድ ከመገለጡ በፊት ለትውልዱ ሰዎች እሱ ማን እንደሆነ ለማወቅና ወደ ንስሃ ለመምጣት የሚያስችል በቂ ጊዜ እየሰጣቸው ነበር፤ ጴጥሮስም ስለዚሁ ነገር ሲያመለክት፦ “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ [ስለ መምጣቱ] አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉም ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለእኛ ይታገሣል” (2ጴጥ. 3፥ 9) ብሏል። ይህ ትእግስት ወይም በመዘግየት ሃሳብ የተገለጠ የቆይታ ጊዜ፣  ጌታ ኢየሱስ ፍርዱን ከማምጣቱ በፊት የገዛ ትውልዱ ሰዎች እርሱ ማን እንደሆነ እንዲያውቁና እንዲያምኑበት ዕድል እንዲያገኙ በጊዜው ለነበሩት ሰዎች በምሕረት የተሰጣቸው ነበር።  ሆኖም ጌታ ኢየሱስ ከፍ ሲል በማቴዎስ ወንጌል እንዳየነውና በእነዚያ የጊዜ መግለጫዎች ላይ ደጋግሞ እንደተናገረው ይህ መዘግየት የተባለው የቆይታ ጊዜ ማብቂያው “ይህ ትውልድ” ከተባለው ዘመን አያልፍም።

እዚህ ላይ በግልጽ የሚታየውን ንጽጽር ልብ በሉ፤ ጌታ ኢየሱስ በ30 ዓ.ም አካባቢ የዳግመኛ ምጽአቱን ጊዜ አስመልክቶ የተናገረውን ንግግር አስተያዩ።  በ30 ዓ.ም ላይ፣ ኢየሱስ በአንድ ትውልድ ውስጥ እንደገና ተመልሶ እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር (ማቴ. 10፥ 23፤ 16፥ 28፣፤ 24፥ 30–34፤ 26፥64)።  ሆኖም ከሠላሳ አምስት ወይም ከዚያ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ፣ “ይህ ትውልድ” በተባለው ዘመን መሟጠጫ ላይ፣ ኢየሱስ አሁንም በመልአኩ አማካኝነት “እነሆ፣ እኔ በቶሎ እመጣለሁ…" (ራዕይ. 22፥ 7፣ 10). ማለቱን ልብ በሉ።  በመካከል ያለው ወደ ሠላሳ አምስት ዓመት ያህል የሚጠጋ የጊዜ መደብ መሆኑንም አስተውሉ። 

ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደሚመጣ በገባላቸው የተስፋ ቃል መሰረት፣ በ70 ዓ.ም ላይ ኢየሩሳሌምና መቅደስዋ በወደሙ ጊዜ፣ ዳግመኛ በፍርድ ተመልሶ መጥቷል። ይህንን የተፈጸመ የዳግመኛ ምጽአቱን የፕሪቴሪስት ነገረ ፍጻሜ አቋማችንን አስረግጠን የምንናገርበት ደርዘን ሙሉ ውስጣዊ የቃሉ ማስረጃና ውጫዊ የታሪክ ምስክርነት ለማወቅ፣ ለመጠየቅና ስታምኑ የኖራችሁትን የመጻኢነት አቋም በቃሉ ሚዛን ላይ አስቀምጦ ለመለካት የሚይስችሏችሁ፣ በዚህም የቃሉ ትምህርት ላይ በተቃውሞ ሊቀርቡ በሚችሉ ልዩ ልዩ ክርክሮች ምካቴ የሚሆኑ ሃሳቦችን የሚጠቁሙ ተጨማሪ ጽሁፎችን ማየት ቢያስፈልጋችሁ፣ ብሎገሬን እንድትጎበኙ እጋብዛለሁ።

https://gizachewkr.blogspot.com/2023/12/blog-post.html?m=1

ግዛቸው።

Saturday, April 13, 2024

ዩኒቨርሳሊዝም


ዩ ኒ ቨ ር ሳ ሊ ዝ ም፤ 

የአስተምህሮ ሕጸፅ!!

“በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።” (ቆላስይስ 1፥ 20)

መግቢያ

በአብዛኛው ይህ ጥቅስ የዩኒቨርሳሊዝምን (ሉል አቀፋዊነትን) ትምህርት ለመደገፍ  ጥቅም ላይ ሲውል ይስተዋላል። ስለዚህ በዚህ ጥናታችን የዩኒቨርሳሊዝምን ትምህርት ህጸፅና ቅዱሳት መጻሕፍት በዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሉ እንመለከታለን። ወደዚህ የተሳሳተ አስተምህሮ ዘወር የሚሉ ሰዎች እየበዙ መምጣቱን በተለያየ አጋጣሚ እየታዘብሁ መጥቻለሁ፣ ስለዚህ ጉዳዩን እንድናነሳውና ጭንብሉን እንድንገልጠው እፈልጋለሁ።


ዩኒቨርሳሊዝም ምንድን ነው?

በትርጉም እንጀምር፦ ዩኒቨርሳሊዝም ኢየሱስ በከፈለው የኃጢያት ዕዳ ክፍያ አማካኝነት በእግዚአብሔር እና በታሪክ ሰዎች ሁሉ መካከል ያለገደብ የሆነ እርቅን እግዚአብሔር አምጥቷል ሲል የሚያስተምር ትምህርት ነው። ዩኒቨርሳሊዝም በአስተምህሮው ስዎች ሁሉ (በጅምላ) በመጨረሻ ላይ ይድናሉ፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ይታረቃሉ የሚል እምነት ነው። ይህ እርቅ የሚከናወነውም ሰዎች  በህይወት ዘመናቸው ጌታ ኢየሱስን እንደ አዳኝ አድርገው  ቢያምኑም ወይም ባያምኑም፣ ቢቀበሉም ባይቀበሉትም ልዩነት ሳይደረግ ነው ይላል።

እንደማንኛውም አስተምህሮ፣ ብዙ ዓይነት የዩኒቨርሳሊዝም አስተምህሮታዊ ምልከታዎች አሉ። ለምሳሌ፣ ኮንዲሽናል ኢሞርታሊቲን ማንሳት ይቻላል። ኮንዲሽናል ኢሞርታሊቲ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ አለመሞት ወይም የነፍስ ዘላለማዊነት ነው። ይህ ምልከታ የክፉዎች ነፍስ ፈጽማ ትጠፋለች እንጂ ዘላለመምዊነት የላትም ብሎ የሚያምን ሲሆን፣ በተለይ የኃጢአተኛ ነፍስ ዘላለማዊ ንቃተ ህሊና ካለው ስቃይ ይልቅ በገሃነመ እሳት ፈጽሞ ይጠፋል የሚል እምነት ነው። እንደዚህ ምልከታ ከሆነ የሰው ልጅ በሞት ከተለየ በኋላ አለመሞት ተፈጥሮው አይደለም። ይሁንና በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ግን በእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ ነው። የዚህ ምልከታ ስነ መሉኮታዊ ችግሩ የማያምኑ ሰዎች ሲሞቱ ነፍሳቸው ዘላለማዊ ንቃተ ህሊና ካለው ስቃይ ይልቅ ፈጽማ ተደምስሳ የምትጠፋ ትሆናለች ማለቱ ነው። ይህም ማለት የእግዚአብሔርን የማዳን እቅድ የማይቀበሉ ነፍሳት በመጨረሻ ላይ ሕልውና የሌላቸው ሆነው ይጠፋሉ፣ ማለት ነው። ይህንን እሳቤ የሚደግፉ ሰዎች ይህ አመለካከት የክፉዎችን ነፍስ መጥፋትና መደምሰስ፣ የዘላለም ሕይወት ስጦታ በክርስቶስ በማመን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ከሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ይስማማል ብለው ይከራከራሉ።

ዩኒቨርሳሊዝም ግን በተቃራኒው ነፍስ በዚህ ህይወት ንስሃ ገብታ አመነችም አላመነችም፣ አለመሞትን ዕጣ ክፍሏ ያደረገች የማትሞት ነፍስ በመሆንዋ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ከሞት በኋላም እንኳ ክርስቶስን ለመቀበልና (በጅምላ) ለመዳን እድል እንደሚኖራት አይነት ሆኖ የቀረበ ትምህርት ነው፤ በዚህ ምልከታ መሰረት መቀበል ማለት ድነትን ማግኘት ነው። 

እነዚህ ሁለት አመለካከቶች፣ ኮንዲሽናል ኢሞርታሊቲ እና ዩኒቨርሳሊዝም በገሃነም ውስጥ በዘላለማዊ ንቃተ ህሊና ስላለው ዘላለማዊ ስቃይ ለዘመናት ሲታመን የኖረውን የክርስትና አመለካከት በአንድነት ይቃረናሉ።  ኮንዲሽናል ኢሞርታሊቲ የዘላለም ስቃይ ሃሳብን የሚክድ እና የክፉዎችን ነፍስ መጥፋትና መደምሰስ የሚያቀነቅን ሲሆን፣ ዩኒቨርሳሊዝም ደግሞ በሌላ ጽንፍ አንዳንዶች የማይድኑ ሆነው ከእግዚአብሔር ለዘላለም ይለያሉ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ያደርጋል።  ሁለቱም አመለካከቶች ታሪካዊውን የገሃነመ እሳት ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ይቃወማሉ፣ ነገር ግን የክፉዎችን እጣ ፈንታ በተመለከተ በመጨረሻው መደምደሚያቸው ላይ ይለያያሉ።

በሁሉም ዓይነት ዩኒቨርሳሊዝም ጎራ ውስጥ በጋራ የተያዙ ሐሳቦች አሉ፦ ሁሉም በሚባል ደረጃ የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚረዱት ቅዱስ ፍቅር እንዳለው አድርገው ሳይሆን በጎ ፈቃደኛ አምላክ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ ናቸው። ዩኒቨርሳሊዝም እግዚአብሔር ፍቅር ነው ይበል እንጂ ፍቅሩ ቅዱስ መሆኑን አይገነዘብም።


ዩኒቨርሳሊዝም እና ኖስቲሲዝም

በዩኒቨርሳል ድነት የማመን ጽንሰ አሳብ እድሜው እንደ ክርስትና ሁሉ ከሞላ ጎደል ጥንታዊ ሲሆን ከጥንታዊ የኖስቲሲዝም አስተማሪዎች አሳብ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። 

ኖስቲሲዝም፣ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እና ፍልስፍናዊ እንቅስቃሴ ነው፤ ከዩኒቨርሳሊስት አስተሳሰቦች ጋር የተያያዙ አንዳንድ ዘርፎችም ነበሩት።  ኖስቲሲዝም በጥንታዊው የክርስትና ዘመን ላይ ብቅ ያለና በኋላም (ከክርስቶስ ልደት በኋላ) በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በእጅጉ ታዋቂ እንደነበር ይታወቃል።  ስለ አጽናፈ ሰማይ ተፈጥሮ፣ ስለ ክርስቶስ ማንነት እና የክርስቶስን በምድር ላይ የመታየቱን ትርጉም በአመስጥሮ እውቀት (በኖሲስ) አማካኝነት የሚያምን በመሆኑ ተለይቶ ይታወቃል።

ክርስቲያን ሆነው ኖስትሲዝምን የሚያራምዱ አንዳንድ አስተማሪዎች፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በአሌክሳንድሪያ ግብፅ ይኖሩ የነበሩ መሆኑ ይታወቃል። እነርሱም በመጀመሪያ ዩኒቨርሳል ድነትን እንደ አንድ የተለየ ሃይማኖታዊ ትምህርት አድርገው ያዘው ነበር። ክፉዎችን ጨምሮ ሁሉም ነፍሳት በመጨረሻ ላይ በሽግግር ወይም በቅጣት ይነጻሉ ብለውም  ያምኑ ነበር። ሆኖም ግን፣ ሁሉም የኖስቲሲዝም ኑፋቄዎች ዩኒቨርሳሊዝምን የሚያራምዱ ክፍሎች እንዳልነበሩና አመለካከቶቹን በሙሉ የሚከተሉ እንዳልሆኑ እንዲሁም በኖስቲሲዝም ውስጥ ያሉት እምነቶችና አመለካከቶችም አንዱ ከሌላው የተለያየ እና የማይገናኙ እንደነበሩ ልብ ሊባል ይገባል።

ኖስቲሲዝም በዩኒቨርሳሊዝም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በክርስቲያናዊ ዩኒቨርሳሊዝም አስተሳሰብ ታሪካዊ እድገት ውስጥ የሚታይ ነው።  የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዩኒቨርሳሊዝም ስነ መለኮት ሊቃውንት የነበሩ እንደ ዳግማዊ ሆሴአ ባሎው እና እንደ ሪቻርድ ኤዲ ያሉ ሰዎች የሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስክንድርያው የኖስቲክ አስተሳሰብ አራማጆች ቅድመ አያቶቻቸው እንደሆኑ በግልጽ ተናግረዋል።

ሆኖም በኖስቲሲዝም እና በዩኒቨርሳሊዝም መካከል ያለው ግንኙነት የሊቃውንቱ የክርክር ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ከመሆኑ በቀር ሁሉም ሊቃውንት በዚህ ኖስቲሲዝም ባሳደረው የተጽዕኖ መጠን ላይ የሚስማሙ አይደሉም።

ስንጠቀልለውም፣ አንዳንድ የኖስቲሲዝም አስተሳሰብ ደረጃዎች የዩኒቨርሳሊዝም እሳቤ የነበረባቸው ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ መቶ ክፍለ ዘመናትም ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያን የኖስቲሲዝም አስተማሪዎች በዩኒቨርሳል ድነት ላይ እምነትና ዝንባሌ ነበራቸው።  ሆኖም በኖስቲሲዝም እና በዩኒቨርሳሊዝም መካከል የነበረው ግንኙነት ውስብስብ ያለ እና አሁንም ድረስ ለልዩ ልዩ ምሁራዊ ትርጓሜ የተጋለጠ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።


ዩኒቨርሳሊዝምና የተሃድሶ አብያተክርስቲያናት

የመጀመሪያው ግልጽ የሆነ የዩኒቨርሳሊስት ጽሑፎች መጻፍ የጀመሩት ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በተለይም ከአሌክሳንደሪያው ቀሌመንጦስ፣ የእርሱ ተማሪ ከነበረው ኦሪገን እና ከኒሳው ጎርጎርዮስ ነው። ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደተቻለው፣ የዩኒቨርሳሊዝም ጽንሰ አሳብ ኦሪገን በአሌክሳንድሪያ ይመራው በነበረ ትምህርት ቤት ውስጥ፣ በዚህ ዓለም ሳሉ ንስሐ የማይገቡ፣ ከዲያብሎስና ከእርኩሳን መላእክቱ በቀር፣ የወደቁ ፍጥረታት ሁሉ በሚመጣው ዓለም ረዥም ቅጣትን ተቀብለው እንደሚያልፉ ጽንፍ በያዘ ሁኔታ ትምህርቱ ተሰጥቷል። በመጨረሻም፣ እነዚህን ስቃዮች ካለፉና በከፍተኛ መናፍስት መመሪያ ውስጥ ካለፉ በኋላ  በዚያው በተካሄደ ለውጥ ሁሉም ወደ ደስታ ይመጣሉ፣ ይላሉ። ይህ የኦሪገን አመለካከት በሂፖው አውጉስጢኖስ ከፍተኛ ተቃውሞ የደረሰበት ሲሆን ኋላም በቁስጥንጥንያው ጉባኤ (543 ዓ.ም.) ተወግዟል።  በተሃድሶው ወቅትም አናባፕቲስቶች በመባል የሚታወቁ መናፍቃን ስለ ሰዎችም ሆነ አጋንንትን በሚመለከት ይህንን የአለክሳንደሪያ አመለካከት ተቀብለው አስተጋብተውታል፤ ጆን ካልቪንም ያኔ ይህን የሚያወግዝ በራሪ ጽሁፍ እንዳሰራጨ ይታወቃል።

የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ተጽኖ ፈጣሪ የሆነው ማርቲን ሉተር የዩኒቨርሳል ድነት አስተምህሮን ፈጽሞ ሲደግፍ አይታይም።  የማርቲን ሉተር ሥነ-መለኮት የክርስትና አስተምህሮ ዋና አንቀፅ አድርጎ አጽንዖት በመስጠት የገለጠው ትምህርቱ በእምነት ብቻ የመጽደቅን ፅንሰ-ሀሳብ ነው።  እንደ ሉተር እምነት መዳን የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ነው፣ የሚገኘውም በክርስቶስ በማመን ብቻ ነው።  የሰው ልጅ በኃጢአትና በሰይጣን ባርነት ተገዝቷል፣ እናም በፈቃዱ ለጸጋው ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ለድነት ሊተባበር እንደማይችል ሉተር ያምን ነበር።  ሉተር መዳን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ተስፋዎች ላይ የተመሰረተ እንጂ በሰዎች ስራ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ አጥርቶ ተመልክቷል። ስለዚህም የዩኒቨርሳሊዝም ድነት በሉተር ዘንድ ምንም ተቀባይነት አልነበረውም። ሉተር በቅዱሳት መጻሕፍት ቀዳሚነት ላይ የሰጠው አጽንዖት እና እንደ አውግስጢኖስ ያሉ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለጻፏቸው ጽሑፎች የነበረው አክብሮት፣ ጥንታዊውን የመዳንን ግንዛቤ አጥብቆ እንደያዘ ያሳያል።  ሉተር በመራው ተሃድሶ አንዳንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮዎችን ውድቅ ሲያደርጋቸው፣ ዩኒቨርሳል ድነትን ወይም ለእምነትና ለድነት መገኘት የስራዎችን ፋይዳ ሲደባልቅ አይታይም። የማርቲን ሉተር ስነ-መለኮት በእምነት መጽደቅ ላይ አጽንዖት የሚሰጥ ሲሆን የጅምላ ድነትን የሚያቀነቅነው የዩኒቨርሳል ድነት ትምህሮትን ፈጽሞ አይደግፍም።

ሌላው የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የነገረ መለኮት ምሁር እና ለተሐድሶው ሥነ-መለኮት እድገት ቁልፍ ሰው የነበረው  ጆን ካልቪን ነው፤ እርሱም በትምህርቱ የሉል አቀፋዊነትን (የዩኒቨርሳሊዝምን) እሳቤ ፈጽሞ አይቀበልም። ከፍ ሲል እንደጠቀስነው ዩኒቨርሳሊዝም በአስተምህሮው ስዎች ሁሉ በመጨረሻ ላይ (በጅምላ) ይድናሉ ከእግዚአብሔርም ጋር ይታረቃሉ የሚል እምነት ነው። በእርግጥ የካልቪኒስት አቋማቸውን ከዩኒቨርሳሊስት እሳቤአቸው ጋር ቀይጠው የሚያምኑ በታሪክ ተለይተው የሚታወቁ አንዳንድ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት እንደነበሩ ግልጽ ነው፣ ይሁንና ግን  ይህ የዩኒቨርሳሳሲዝም አስተሳሰብ በካልቪኒዝም አስተምህሮ ውስጥ ዋጋ ያለው ዋና ጉዳይ ወይም ሰፊ ተቀባይነት ያለው አቋም አለመሆኑን በሚገባ ልብ ማለት ያስፈልጋል።

የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እና ፍቅር የሚረዱበትን ግንዛቤ በመጥቀስ ከካልቪኒዝም ወደ ዩኒቨርሳሊስትነት ዘወር ያሉ አንዳንድ የነገረ መለኮት ምሁራን እንደነበሩም መጥቀስ ተገቢ ነው። ለምሳሌ፣ ፍሬድሪክ ሽሌየርማቸር እና ካርል ባርዝ፣ ሁለቱም ሰዎች በካልቪኒዝም አስተምህሮ ተጽዕኖ ሥር ሆነው በዩኒቨርሳሊዝም እሳቤ ተይዘው እንደነበሩ ይጠቀሳሉ።

ሆኖም፣ እነዚህ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት ዩኒቨርሳሊዝምን መቀበላቸው ካልቪኒዝም በተፈጥሮው ወደ ዩኒቨርሳልነት ያመራል ማለት እንዳልሆነ በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዳንድ ግለሰቦች የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እና ፍቅር በተመለከተ ያሉትን የካልቪኒዝም ፅንሰ-ሀሳቦች በተረጎሙበት መንገድ  የወሰዱት ግላዊ ሥነ-መለኮታዊ እሳቤ ነው።  ካልቪኒስት ሆነው በዩኒቨርሳል እሳቤአቸው  ተለይተው የሚታወቁ የነገረ መለኮት ምሁራን ቢኖሩም፣ ይህንን ብቻ አንጠልጥሎ ካልቪኒዝም በማያወላዳ መልኩ ወደ ዩኒቨርሳሊስት እሳቤ ያመራል ማለት ፈጽሞ ትክክል አይደለም። በካልቪኒዝም እና በዩኒቨርሳሊዝም መካከል ያለው ግንኙነት ውስብስብ ያለና ግለሰቦች በሥነ-መለኮታዊ አመለካከቶች ላይ በሚይዙት አቋም መካከል ባለው ጠባይ ይለያያል።

ዩኒቨርሳሊስቶች እና አርሜንያኒስቶች

ዩኒቨርሳሊስቶች እና አርሜንያኒስቶች በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ ሁለት ጉልህ የተለያዩ ሥነ-መለኮታዊ አመለካከቶች ቢሆኑም፣ በመጠኑ የሚጋሩዋቹው ተመሳሳይነቶች ግን አሏቸው።

አርሜንያኒዝም፣ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ያቆጠቆጠ፣ ጄኮቡስ አርሜኑስ በሚባል የደች ተወላጅ የተጀመረ፣  በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት እና በሰዎች ነፃ ምርጫ መካከል ያለውን ተዛምዶ በተለይም ይህ ከድነት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማስረዳት የሚጥር ሥነ-መለኮታዊ ዘውግ ነው። 

አርሜንያውያን የክርስቶስ የኃጢያት ዕዳ ክፍያን አስመልክቶ የሚያነሱት ሃሳብ ሥርየቱ ለተመረጡት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች የታሰበ ነው ብለው ያምናሉ።  ይህም ማለት በወንጌል የቀረበው የድነት ግብዣ ሉል አቀፋዊ ነው፣ ለሁሉም ሰው ያለ ልዩነት መቅረብ አለበት የሚል ሲሆን፤ በዚህም ከዩኒቨርሳሊስቶች የድነት አስተምህሮ ጋር በተወሰነ መልኩ የሚስማሙ ይመስላል።

አርሜኒያኒዝም በትምህርቱ የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት እና የሰው ነፃ ፈቃድ መሳ ለመሳ መሆናቸውን ሲያጎላና ሰዎች መዳናቸውን ይመርጡ ዘንድ ድነት ለሁሉ ያለ ልዩነት የቀረበ ነው ሲል፤ ዩኒቨርሳልዝም ደግሞ ድነት ለሁሉ ያለ ልዩነት የቀረበ ነው የሚለውን የአርሜንያውያንን ጽንሰ አሳብ በመዋስ፥ አመኑ አላመኑ ሰዎች ሁሉ በመጨረሻ ላይ ይድናሉ ከእግዚአብሔርም ጋር ይታረቃሉ ሲል መከራከሪያውን ያቀርባል። ለዚህ ነው ዩኒቨርሳሊዝም የ አርሜንያኒዝም አመክንዮአዊ ውጤት እንደሆነ አድርጌ የማየው።

እንግዲህ ይህ የዩኒቨርሳሊዝም ትምህርት ቆዳውን ሲያዩት ለሰው ልጅ ተፈጥሮ ተስማሚ ይመስላል።  አብዛኞቹ የማያምኑ ሰዎች አንድ ሰው ሲሞትባቸው ወደ ሰማይ እንደሚሄድ ያስባሉ፤  ብዙውን ጊዜ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ?  “አሁን የተሻለ ቦታ ላይ እንዳለ/ች እናውቃለን” ይላሉ።  የዛሬዎቹ የዩኒቨርሳሊዝም አስተምህሮ አቀንቃኞች ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለአዳምና ለሄዋን ከተሰበከውና  "መሞትን በፍፁም አትሞቱም" ከሚላው የእባብ ትምህርት የተቀዳ ትምህርት ይመለሳል።  ሰውን ሁሉ 'አትሞቱም፣ በእግዚአብሔርም ፍርድ አትጠፉም' ሲል ይሸነግላልና። ሰውም እንዲህ ያለውን የዲያብሎስ ማባበል እንደ መስማት የሚያስደስተው ሌላ ነገር የለም። እግዚአብሔር ግን ከመጀመሪያው “ኃጢአት ወደ ሞት ይመራል” ሲል በግልጽ ተናግሯል። እኛ ደግም እግዚአብሔር "ሞትን ትሞታለህ" ብሎ ሲነግረን ከማመን ይልቅ  እባቡ አትሞትም ብሎ ሲነግረን በቀላሉ ማመን ይቀናናል።

ዩኒቨርሳሊዝም በወንጌላችን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው ብዬ አምናለሁ።  መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ከእግዚአብሔር ፍርድ ይድን ዘንድ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምን” ደጋግሞ ይጣራል። ይህም የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት የወንጌላዊው ክርስትና የድነት አስተምህሮ መሰረቱ ነው።  ዩኒቨርሳሊዝም ግን በተቃራኒው የእግዚአብሔርን ቃል እያጣመመ እና የእግዚአብሔርን ፍርድ እየካደ "ለማንም ቢሆን በኢየሱስ ማመን ሳያስፈልገው እንዲሁ ይድናል” በማለት ያስተምራል።


ዩኒቨርሳሊስቶች የሚመዝዟቸው ጥቅሶች

ሁሉም የዩኒቨርሳሊዝም አቀንቃኞች የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶችን በመጥቀስ አመለካከታቸውን ሊደግፉ ሲጥሩ ይታያል።  አውድ ዘለል የሆኑ ጥቅሶችን በመጠቀማቸው፣ ለያዙት አቋም አሳማኝ ማስረጃ ያቀረቡም ይመስላቸዋል።  ከቤዛነት ሥራ ጋር በተያያዘም "ሁሉ" እና "ዓለምን" በሚል ጥቅም ላይ የዋሉ ብዙ ጥቅሶችን እያሳከሩ ያቀርባሉ። እነዚህን ጥቅሶች ስንመለከት፣ “የእምነት ምሳሌ” የተሰኘውን የሥነ ትርጓሜ (hermeneutics) ቀዳሚ ህግ - ይኸውም ቅዱሳት መጻሕፍትን በቅዱሳት መጻህፍት የመተርጎም መመሪያን ማስታወስ አለብን።  ይህ ማለት የትኛውም የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ ከተነገረው ጋር የሚጋጭ ሆኖ ሊተረጎም አይችልም አይገባምም ማለት ነው።

ዩኒቨርሳሊስቶች ሃሳባቸውን ለማስደገፍ ከአውዱ ነጥለው የሚጠቅሱትንና በዚህ ጽሁፍ መነሻ ጥቅስ ያደረግሁትን በቆላስይስ መልዕክት የሚገኘውን ምንባብ በመመልከት ጥናታችንን እንቀጥል፡-

“በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ” (ቆላስይስ 1፥ 20 አ.መ.ት)

ጳውሎስ በዚህ ንግግሩ ዩኒቨርሳሊዝምን እያስተማረ ነውን? ማለትም፣ ፍጥረታት ሁሉ በመጨረሻ ላይ እንደሚድኑ እና አንዳቸውም ለዘላለም እንደማይቀጡ እየተናገረ ነውን?  ይህ ማለት አንድ ቀን እግዚአብሔር በምድር ላይ ተፈጥረው የኖሩትን የማያምኑትን እና ራሱን ዲያብሎስንም እንኳን («በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ») ከራሱ ጋር በጅምላ ያስታርቃል ማለት ነውን?  በጭራሽ እንደዚያ አይደለም። በዚህ ጥቅስ የጳውሎስ ንግግርም ይህ እንዳልሆነ እናውቃለን። እንዲህ የሚያስቡ ዩኒቨርሳሊስቶች ግን ይህንንና መሰል ጥቅሶችን ለሃሳባቸው መደገፊያ እየመዘዙ ብዙዎችን እንደሚያወዛግቡ አስተውያለሁ። አንዳንዶችም በማህበራዊ ሚዲያ እንዲህ ያሉ ጥቅሶችን እየጠቀሱ ሲያወናብዱ ታዝቤያለሁ። ታዲያ ይህ ጥቅስ ምን እያለ ነው? እስቲ በአውደምንባቡ ለማስረዳት ልሞክር፡-

“የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።” (ቆላስይስ 3፥ 10-11)

ጳውሎስ “አዲሱን ሰው ለብሶ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰው” በማለት ክርስቲያኖችን ገልጿቸዋል።  ከዚያም በቁጥር 10 ላይ ያነሳውን ይህንን የታደሰ ሰው  ማንነት ለማሳየት የዚህን ሰው መገኛ “በዚያም” በሚለው ቃል የተገደበ መሆኑን በቁጥር 11  ላይ ያመለክታል ። በዚያ ያለው በክርስቶስ ያለው ነው እንጂ መላው የሰው ዘር ማለት አይደለም። ሲናገርም “በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።” ይላልና።

እግዚአብሔር ያቀረበላቸውን የእርቅ ስጦታ በፈቃደኝነት በእምነት እና በንስሃ ከመቀበል በቀር ለሰው ለጆች ሌላ ዩኒቨርሳል ዕድል የላቸውም። ቆላስይስ 1፥ 20ን ልንረዳው የሚገባን በዚህ መንገድ ሊሆን እንደሚገባው አስባለሁ። አንቀጹ እንዴት እንደተደራጀ ተመልከቱ።  ከቁጥር 15-17 ያለው ቃል ዳርቻው ፍጥረት ሁሉ ነው።  መላው አጽናፈ አለምም (ዩኒቨርስ) በዚህ እይታ ውስጥ ነው።  ነጥቡም ክርስቶስ ​​ሁሉንም አንድ ላይ አድርጎ ስላያያዘ ከፍጥረት ሁሉ የበላይ ነው፣ የሚል ነው።

ነገር ግን ከቁጥር 18-21 ላይ ባለው ንግግሩ፣ የትኩረት አቅጣጫው ይቀየራል፣ ወሰኑም አሁን መላው አጽናፈ አለም (ዩኒቨርስ) ሳይሆን ይልቁንም አዲሱ ፍጥረት ይሆናል፣ ይኸውም ቤተ ክርስቲያን። ቁጥር 18 ላይ ንግግሩ ከፍጥረት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚዞር አስተውሉ፡- “እርሱ የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው።”  ይህንን የቤተ ክርስቲያን አውድ ተከትሎ በቁጥር 20 “በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ” የሚል ቃል እናነባለን። እኔ እንደማስበው በቁጥር 20 ላይ ያለው “ሁሉም ነገር” የሚለው አገላለጽ በተመሳሳይ መንገድ በምዕራፍ 3፥ 11 ላይ ባለውና ለቤተክርስቲያን በተገደበው “ሁሉም” በሚለው ቃል ወሰን ውስጥ ያለ መሆን አለበት።

በግሌ በአመለካከቴ ፕሪቴሪዝም ወደሚያስተምረው ወደ ተፈጸመው ወንጌል ያደረግሁት  ለውጥ ምክንያቱ በእውነት ጌታ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት ተመልሶ እንደመጣ በሚያስተምሩ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ባሉ እጅግ አስደናቂ ማስረጃዎች ተይዤ ነው ብዬ ልመሰክር እወዳለሁ።  የዩኒቨርሳሊዝምን ትምህርት በተመለከተ ግን ለማሳየት የምፈልገው በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ማስረጃዎችን ከማግኘት ይልቅ አስተሳሰቡን በጽኑ የሚቃወሙ ጥቅሶች፣ ምንባባት እና ትምህርት ያለበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ዩኒቨርሳሊዝም የአስተምህሮ ድሪቶ እንጂ የቅዱሳት መጻህፍት ንጹህ ትምህርት አካል አይደለም።


የዩኒቨርሳሊዝም አስተምህሮ ያረፈባቸውን አንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦች፦

እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ይወዳል የሚለው አንዱ ነው።  ይህም የዩኒቨርሳሊዝም ኑፋቄ ሁለንተናዊ አቋሙ መሆኑን ለማሳየት እንዲረዳን፣ "Plain Guide to Universalism" ከተሰኘ ድረ-ገጽ ላይ የተገኙ የተወሰኑ ጥቅሶችን እንመልከት

  • ተፈጥሮው ፍቅር የሆነ አንድ አምላክ እንዳለ እናምናለን።  እርሱም በአንዱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስና በአንዱ የጸጋ መንፈስ ቅዱስ በኩል ተገልጧል፣ ይህም አምላክ በመጨረሻ ላይ መላውን የሰው ልጅ ቤተሰብ ወደ ቅድስና እና ወደ ደስታ ይመልሳቸዋል።

  • እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፍቅርም ክፉን አይሠራም።  'አምላክ ፍቅር ነው፤ ( 1 ዮሐንስ 4፥ 8 ) 'ፍቅር ደግሞ ክፉን አያደርግም'  ( ሮም 13፥ 10 ) ይህ ተጽዕኖ ፈጣሪ ክርክር ነው።  

  • የእግዚአብሔር ተፈጥሮ የቸርነት ዋና ነገር ነው፣ እና በጎነት የሆነ ባህርይ ማለቂያ ለሌለው ክፋት መነሻው ሊሆን አይችልም።  ፍቅር በባህርይው ክፉ ነገርን የማይሰራ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እግዚአብሔር ምንም አይነት ክፉ ነገር አይሰራም፣ እና ስለዚህ፣ እግዚአብሔር በባህርዩ ማለቂያ የሌለው የክፋት ባለቤት ሊሆን አይችልም። 

  • በእርግጥ እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ሁሉ ይወዳል።  “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ ለሰው ሁሉ እንደ ሞተ እንዲሁ እግዚአብሔርም ሰዎችን ሁሉ ይወዳል።  

የቀድሞ የማርስ ሂል ፓስተር የነበረው ሮብ ቤል Love Wins በተሰኘው መጽሃፉ Universalism በተሰኘው በዚህ አስተምህሮ ላይ ስነ-መለኮታዊ ውዝግብን አስነስቶ ነበረ።  የቤል መጽሐፍ ፍሬ ነገር እያንዳንዱ ኃጢአተኛ በዚህ ሕይወትም ሆነ ወይም በሚመጣው ሕይወት ወደ እግዚአብሔር ዘወር ብሎ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀ እንደሆነ ይገነዘባል።  ይህ መጽሐፍ "በመጨረሻ ፍቅር ያሸንፋል" ሲል ይደመድማል። በእኛም አገር እንዲሁ ያለ መፈክር በየመድረኩ እንደ በቀቀን ሲደጋገም ይደመጣል።

ስለዚህ ዩኒቨርሳሊዝም በዋነኛነት ቀድሞ የያዘው አቋምና ትምህርቱን ያቆመበት መሰሩቱ እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ሁሉንም ሰው  (በጅምላ) ይወዳል፣ የሚለው አጠቃላይ ምልከታው ነው። 

እግዚአብሔር በጅምላ ይወድዳልን?

በውኑ ግን እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው በጅምላ እንደሚወድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራልን?  በፍጹም!

ይህ አቋሜ የሚያስቆጣችሁ አንባቢዎቼ በወንጌላዊው ክርስትናችሁ ላይ የደረባችሁት የዩኒቨርሳሊዝም እከከኝ ልከክልህ የአስተሳሰብ ድሪቶ እንዳይኖርባችሁ እሰጋለሁ።  እስቲ ይህን ጥቅስ እንየው፦ 

ሮሜ 9፥ 13 ”ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። “ 

ጳውሎስ ይህንን የጠቀሰው ከሚልክያስ መጽሐፍ ነው፦

ሚልክያስ 1፥ 2-3 “ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን፦ በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤ ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው።”

አንዳንዶች ይህንን ሲተረጉሙ እዚህ ላይ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው አንድን ብሔር ከሌላው ብሔር በላይ አስበልጦ ስለ መምረጥ ነው እንጂ የግለሰቦችን ምርጫ የሚያሳይ አይደለም ይላሉ።  ያ ግን በእውነት የሞኝነት ክርክር ነው።  እግዚአብሔር አንዱን ሰው ከሌላው አስበልጦ መምረጡ ተገቢ ካልሆነ፣ አንዱን ብሔር ከሌላው አስበልጦ ቢመርጥ ለምን ችግር ይኖረዋል?  ብሔሮች የግለሰቦች ድምር ውጤት አይደሉምን?

በሚልክያስ 1፥ 2 ላይ ያለው ጥቅስ የያዕቆብና የኤሳውን ዘር፣ ማለትም ከእስራኤልና ከኤዶም የተገኙትን ህዝቦች ያመለክታል። እዚህ ላይ ነቢዩ አይሁዶችን አመስጋኝ ባለመሆናቸው እየወቀሳቸው ነው።  እግዚአብሔር ለእነርሱ ለየት ያለ ሞገስ እንዳለው ማረጋገጫ ይሆናቸው ዘንድ፣ ከመነሻው ለእነሱ የነበረውን ምርጫ ይጠቅስላቸዋል።

አንዳንዶች እዚህ ላይ “ጠላሁ” ሲል ጥላቻ ማለት አይደለም፣ ነገር ግን "አነስተኛ መውደድ" ወይም "አነስ ባለ ሞገስና እውቅና ማስተናገድ" ማለት ነው በማለት ቃሉን ዘወር ለማድረግ ይሞክራሉ።  መጥላት የሚለው ቃል ግን በተለያዩ ምንባቦች ውስጥ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልከቱ፦

ሉቃስ 14፥ 26 “ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።”

እዚህ ላይ መጥላት የሚለው ቃል አጠቃቀም “አነስ ያለ ውለታ (favor) በተመለከተ.” የሚል ሀሳብ ይኖረዋል።  ነገር ግን በሚልክያስ 1፥ 1-5 የመጀመሪያው አውድ ውስጥ፣ መውደድ በፍርድ ከሚሆን ጉብኝት ጋር እምብዛም አይገናኝም።

ሚልክያስ 1፥ 3-4 “ዔሳውንም ጠላሁ፤ ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው። ኤዶምያስ፦ እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ፦ የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል።”

“ያዕቆብንም ወደድሁ፥” እግዚአብሔር ፍቅሩን ሲገልጥ ሉዓላዊ መሆኑን አስተውሉ።  እያልሁ ያለሁት እሱ የመረጠውን ይወዳል፣ እንጂ እግዚአብሔር ሁሉንም፣ ማነኛውንም፣ እንዳለ በጅምላ አይወድም ማለት ነው።  አሁንም ይህን ስናገር ሰዎችን እንደሚያስቆጣ አውቃለሁ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ይህንን የሚያስተምረው ሳያድበሰብስ በግልጽ ነው።  በቃ ምን ይደረጋል ኤሳውን እንደሆነ አልወደደም፣ ያ በጣም ግልፅ ነው። ታዲያ አሁን ለእግዚአብሔር እየተከራከርክ የለም ከኤሳው በቀር ሁሉንም ይወዳል እንዴት ትላለህ?

በዘመናችን ካሉት በጣም ታዋቂ እምነቶች አንዱ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው (በጅምላ) ይወዳል የሚለው ነው።  ይህ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው ይወዳል የሚለው አስተሳሰብ ግን ዘመን አመጣሽ እምነት ነው እንጂ የቃሉ ድጋፍ የለውም።  ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የተሃድሶ አራማጆች ይሁኑ ወይም የፒዩሪታን ጽሑፎች እንዲህ ዓይነት ጽንሰ ሐሳብ ይገኝባቸው እንደሆነ መመርመር ከንቱ ፍለጋ ነው።  እርግጠኛው ነገር የእግዚአብሔር ፍቅር ለመረጣቸው ለቅዱሳኑ ብቻ የመሆኑ እውነት ነው።


የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፥ 16 በተለይ

ከዮሐንስ 3፥ 16 በስተቀር፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን እግዚአብሔር እንደወደዳቸው ሲነግራቸው በአራቱም ወንጌላት ውስጥ አንድ ጊዜም እንኳ አናነብም። ይልቁንም በወንጌላቱ ሁሉ ውስጥ ከመጠሪያው ይልቅ ፍቅርን በግብሩ በብዙ ማየት ይቻላል። የሐዋርያት የወንጌል ሥራ እና ተልዕኮ በተዘገበበት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥም እንኳ፣ ሐዋርያቱን በፍቅር እንግድነት ተቀብሎ በቤቱ ካስተናገደው የፑፕሊዮስ ደግነት በቀር (ሐዋርያት ሥራ 28፥ 7) የእግዚአብሔር ፍቅር በፍጹም አልተጠቀሰም።  ይህ ለብዙዎቻችሁ እንግዳ ነገር ሊመስል እንደሚችል አላጣውም። ነገር ግን ለቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ወደ ተጻፉት መልእክቶች ስንመጣ የዚህን ቅዱስ ፍቅር እውነታ ሙሉ መግለጫውን እናገኛለን። ለምሳሌ፦

ዕብራውያን 12፥ 6 “ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።”

የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት እንደሚሰራና በራሱ ቤተሰብ አባላት ላይ ሁሉ (ብቻ) ላይ የተገደበ መሆኑን ተመልከቱ።  እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው በጅምላ የሚወድ ከሆነ፣ እዚህ የተጠቀሰው ልዩነት እና ገደብ ትርጉም የለሽ ንግግር ይሆናል።  እግዚአብሔር ግን የሚቀጣውና የሚገስጸው  የሚወደውንና የእርሱ የሆነውን ብቻ ነው፣ ይህም የሚያመለክተው አማኝ የሆኑትንና በእርሱ የተመረጡትን ሁሉ ነው።

ስለ ዮሐንስ 3፥16ስ ምን ሊባል ይችላል?  አምላክ ሁሉንም ሰው እንደሚወድ ጥቅሱ ያስተምራልን?  እንደዚያ የሚመስል ነገር ያለው ይመስላል፣ በማስረጃ እንጂ በመሰለኝና በደሳለኝ ግን አንመላለስም።

ዮሐንስ 3፥16 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”

ስለዚህ በጥቅሱ ላይ መጠነኛ አስተያየት ሰጥቶ ማለፍ ያስፈልጋል፦

“ወደደ” የሚለው በግሪኩ agapa ነው፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥም በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው፤  ይኸውም የእግዚአብሔር መስዋዕታዊና ታማኝ ፍቅር ሲሆን ይህም ለአለም ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ለራቁ ሁሉ ማለትም ፍቅሩ ለማይገባቸው ለሰው ዘር ሁሉ ነው።  ይህም ዓለም በዮሐንስ 1፥ 10 ላይ እንደተገለጠው ፈጣሪውንና አዳኙን ያላወቀ አመጸኛ ዓለም ነው። በማንነቱም የእግዚአብሔር ቁጣ እንጂ ፍቅሩና ርህራሄው አይገባውም። እግዚአብሔር ግን ፍቅሩን የገለጠው አንድያ ልጁን በመስጠት ነው፤ ሰጠ ሲልም እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው ብቻ ሳይሆን ለዓለም ስጦታ አድርጎ አቀረበው ማለት ነው።  የስጦታውም ልክ መስዋዕታዊ ሞቱ ነው። እርሱ ለእኛ የስርየት መስዋዕት ሆነ። እርሱም አንድያና ብቸኛ ልጁ ነው። ስጦታ ካለ ሰጪና ተቀባይ አለ ማለት ነው። ስጦታ የሰጭውን ደግነት፣ የተቀባዩንም ምስኪንነት ያሳያል። እንግዲህ ጥቅሱ በተነገረበት አውድ ቁጥር 18 ላይ የሰውን ልጆች የሚያምኑ እና የማያምኑ ብሎ ለሁለት ምድብ ከፍሎ እንዳስቀመጣቸው ተመልከቱ።  በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምኑ ሁሉ ምንም አይነት ጠንካራ ወይም ደካማ እምነት ያላቸው ቢሆኑ የዘላለም ሕይወት ሊኖራቸው ይችላል፣ ስጦታውን በምስኪንነትና በእምነት ተቀብለዋልና። ስጦታው ለሚቀበሉት ሁሉ ነው። የሚጠፉቱ ደግሞ ባለማመናቸው የሚጠፉ ናቸው። መዳናችን የሚያርፈው  በክርስቶስ መልካምነት ላይ ነው እንጂ፣ በእኛ ማንነት ወይም ለእግዚአብሔር ባደረግነው በማናቸውም ነገር፣ በብቃታችን ወይም በእምነታችን ማነስና ጥንካሬ ላይ አይደለም። አለመዳንም የሚያርፈው በሰዎች አለማመን ላይ ነው። ሉተር በዚህ ጥቅስ ላይ ሲናገር “እንዴት እና ስለማን እንደሚናገር ታውቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ፣ ቃላቱን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ... እዚህ ላይ “ዓለም” ብሎ “የሚያምን” በሚል ቅድመ ሁኔታ የሚድኑት ሲገለጡ፣ በዚህ በሚያምን አለም ከድነት የተገለለ ማንም የለም።  የእግዚአብሔር ልጅ የተሰጠው ለሰዎች ሁሉ እንዲያምኑ፣ ያመኑትም ሁሉ (ብቻ) እንዳይጠፉ ነው፣ ወዘተ”. ይላል። እንግዲህ ይህ የዩኒቨርሳሊዝምን እሳቤ ከመሰረቱ የሚንድ ነው።

ይህ የዮሐንስ 3፥ 16 ጥቅስ ታዲያ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው (በጅምላ) እንደሚወድ አያረጋግጥምን?  በጭራሽ፣ ከፍ ሲል ባነሳነው ክፍል እግዚአብሔር ኤሳውን ይጠላ እንደነበረም አስታውሱ። እግዚአብሔር ኤሳውን ሲጠላው ቅዱስ ነው፣ ጥላቻውም ጽድቁን አያቆሽሸውም። እስራኤልንም ሲወደው በቅዱስ ፍቅር ይወደዋል፣ ለእስራኤል በማድላቱም ፍቅሩ እግዚአብሔርን አድሏዊ አያደርገውም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ልክ እንደ እርሱ አድርገህ መቀበል አለብህ፣ እንጂ ቃሉን አታወሳስበው። ዮሐንስ 3፥ 16 ላይ ያለውን አንብበህ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው (በጅምላ) ይወዳል ስትልና የእግዚአብሔር እውነት ይህ ብቻ ሲመስልህ፣ እግዚአብሔር ኤሳውን እንደጠላ ያለውን እውነትም አትርሳ። እስቲ በሲሎጅዝም መልክ እናስቀምጠው (ሲሎጅዝም ማለት ሁለት የሚገናኙ ነገሮችን በማመዛዘን የሚደረስበትን መደምደሚያ የሚያካትት የተቀናጀ ዘዴ ነው። ሲሎጅዝም የተወሰነ መዋቅርን የሚከተል ሆኖ በትክክለኛነት እና ጤናማነት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ አመክንዮአዊ ክርክርም ነው።) በዚህ መሰረት፡-

  • ዋነኛው መነሻ፡ እግዚአብሔር ኤሳውን መጥላቱ ነው

  • አነስተኛው መነሻ፡- ኤሳው የዓለም ክፍል መሆኑ ነው።

  • ማጠቃለያውም፡ እግዚአብሔር በዓለም ላይ ያለውን ሰው ሁሉ (በጅምላ) አይወድም ማለት ነው። 

በግሌ እግዚአብሔር የወደደው ሰው እንጂ እግዚአብሔር የጠላው ሰው አያስደንቀኝም፤ ምክንያቱም የወደቀ ኅጢአተኛ ሰው ለመጠላት እንጂ ለመወደድ አይመጥንምና ነው። ስለዚህ የኤሳው መጠላት ሳይሆን የእስራኤል መወደድ ሲያስገርመኝ ይኖራል። በእግዚአብሔር መወደዴንና መመረጤን ባሰብሁ ቁጥር ምንም የሚያስወድድ ነገር ተገኝቶብኝ እንዳልሆነ እያሰብሁም አነባለሁ።

እንግዲህ እዚህ ላይ “ዓለም” የሚለው ቃል መላውን የሰው ዘር ለማመልከት ጥቅም ላይ አልዋለም ማለት ነው።  ይህን አስታውሱ፦

አሞጽ 3፥ 2 “እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ።”

ለምንድነው እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ብቻ የተለየ ህብረት እንዲኖረው ፈቅዶ የተቀሩትን የምድር ህዝቦች በጨለማ እንዲመላለሱ የተዋቸው?  ምክንያቱም እርሱ ስላልወደዳቸው ነው፣ እስራኤልን ግን ወደዳቸው። የምድር አህዛብን አለመውደዱ አያስወቅሰውም፣ እስራኤልንም ብቻ መውደድ አድሏዊ አያደርገውም።


ዓለም

"ዓለም" የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል ደረቁን ትርጉም የሚያሳይ ሳይሆን ይልቁንም በተዛማጅ ትርጉሙ የሚወክለው ነገር አለው።  ለምሳሌ፦

ዮሐንስ 12፥ 19 “ስለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፦ አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ።”

በዓለም ላይ ያለው ሰው ሁሉ ኢየሱስን ይከተል ነበርን? በጭራሽ! ኢየሱስን የተከተሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ ማለት ነው እንጂ ሌላ አይደለም።

ሐዋርያት 19፥ 27 “ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል።”

በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ሰዎች አርጤምስን ያመልኩ ነበርን?  በጭራሽ! ብዙ ሰዎች ግን ያመልኳት ነበር።

ሮሜ 1፥ 8 “እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ።”

በዓለም ላይ ያለ ሰው ሁሉ ስለ ሮማውያን አማኞች እምነት ይናገር ነበርን?  አይመስለኝም። በዚያን ዘመን የነበረው የሮም አለም ማለት ነው እንጂ ሌላ አይደለም።

በዮሐንስ 3 ላይ ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ለአይሁዳዊው ኒቆዲሞስ ነው።  አይሁዶች እግዚአብሔር የሚወዳቸው እነርሱን ብቻ እንደሆነ ያምኑ ነበር።  ታዲያ ዮሐንስ 3፥ 16 ከፍ ሲል በቀረበው ማብራርያ መሰረት እያለ ያለው የእግዚአብሔር ፍቅር ዳርቻው ዓለም አቀፋዊ ነው፣ ማለትም በእርሱ የሚያምኑ እስከሆነ ድረስ ብቻ አሕዛብንም አይሁዶችንም ሁሉ ይወዳል፣ እነርሱም አይጠፉም ማለት ነው።

ዮሐንስ 6፥ 33 “የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው።”

ይሰጣል እንጂ ሕይወትኖ ያቀርባል አላለም።  እዚህ ላይ መስጠት የግድ ተቀባይን ያመለክታል።  ክርስቶስ ለሁሉ (በጅምላ) ሕይወት ይሰጣልን?  በፍጹም፣ እዚህ ላይም ዓለም የሚለው የተገደበው ሊቀበሉት በተመረጡት ዓለም ብቻ ነው።

ዮሐንስ 13፥ 1 “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።”

ኢየሱስ የእርሱ የሆኑትን (ወገኖቹን) ይወድ ነበር።  እግዚአብሔር ያዕቆብን ወደደ ኤሳውንም ጠላው።  ለምን? ለምን ይህንን አደረግህ ተብሎ የማይጠየቅ እግዚአብሔር ፍቅሩን ሲገልጥ በዚህ ግብሩ ሉዓላዊ ነው። ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ስለወዳጆቹ ነው፦

ዮሐንስ 15፥ 13 “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።”

የኢየሱስ ወዳጆች እነማን ናቸው? እርሱ ከአለም የመረጣቸው ሁሉ (ብቻ) አይደሉምን? እርሱ ነፍሱን የሰጠው ለወደዳቸውና ለመረጣቸው ሁሉ ነው። 


የተመረጡት “ሁሉ” ወይስ “ብዙዎች”?፦

እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው በጅምላ ይወዳል አልልም፣ ክርስቶስም የሞተው ከአለም ለጠራቸው ሁሉ ነው፣ የኃጢያት እዳ ክፍያውም ያምኑበት ዘንድ በእግዚአብሔር ተመርጠው ለተወሰኑት ሁሉ ነው።  ክርስቶስ የሞተውም የመረጣቸውን ለማዳን በማሰብ ነው።  ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ ሰጥቷል (ዮሐንስ 10፥ 11)።  በእርግጠኝነት ለመናገር፣ የክርስቶስ ማንነትና ሥራ ዋጋው ከፍ ያለና ወሰን የሌለው ነው።  ስለዚህም ሞቱ በምድር ላይ  ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ለማስተስረይ ሙሉ በሙሉ በቂ ነበር።  ዳሩ ግን በመለኮታዊው ምክር ያንን ለማድረግ በእርግጥ አልተነደፈም።  ይህንንም በቀላሉ እናውቀዋለን፥ ምክንያቱም እርሱ በግልጽ እንደተናገረው ተልእኮው “አብ የሰጠውን” ለማዳን ነበር (ዮሐንስ 6፥ 37-39)።  ክርስቶስ የሞተው “ስለ በጎቹ” ነው።

ዮሐንስ 17፥ 2 “ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።”

ዮሐንስ 17፥ 9 “እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤”

ይህንን አንድ ነገር አስተውሉ፣ ክርስቶስ ስለ አለም ሁሉ አልጸለየም፣ ነገር ግን የጸለየው ስለ በጎቹ ነው - ከአለም ለተሰጡት፣ ለተመረጡት ብቻ።

ማቴዎስ 20፥ 28 “እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”

ነፍሱን ቤዛ የሰጠው ለሁሉም ሳይሆን ለብዙዎች ነበር። እነዚህም “ብዙዎች” ስጦታውን የሚቀበሉ ሁሉ ናቸው።

ዕብራውያን 9፥ 28 “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።”

እንደገናም ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ተሸከመ እንጂ የሁሉንም አይደለም።  እዚህም ላይ ዋናው ጉዳይ የኃጢያት ክፍያን ባህሪ የሚመለከት ነው።  የክርስቶስ የኃጢያት እዳ ክፍያ “ለብዙዎች” ብቻ የተወሰነ ነበር፣ እንጂ ስለዚህ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው (በጅምላ) አልወደደም፣ ክርስቶስም የሞተው ለተመረጡት ሁሉ (ብቻ) እንጂ ስለ ሁሉም ሰው በጅምላ አልሞተም።

ዩኒቨርሳሊስቶች ይህንን እውነት ዘወር ሊያደርጉት ሲፈልጉ "ኢየሱስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ ባደረገው ድርጊት ላይ ምንም ነገር መጨመር አንችልም፣ እምነትንም እኛ ልንጨምር አንችልም፤ ማመን / እምነት ራሱ የእግዚአብሔር ነው፣ እና የሚሰጠውም እግዚአብሔር ነው"  ይላሉ። እስከዚህ ድረስ እስማማለሁ!  ንግግሩም ልክ ነው፥ እምነት ራሱ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፣ ​​ዳሩ ግን እምነትም የሚሰጠው ለተመረጡት ብቻ ነው፣ ፣ምክንያቱም “እምነት ለሁሉ አይሆንም” (2ተሰሎንቄ 3፥ 1-2) ተብሏልና። እምነትም በእግዚአብሔር የመመረጥ ማስረጃ ነው፡-

ሐዋርያት 13፥ 48 “አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤”

እነማን ያምኑ እንደነበር አስተውሉ።  ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁት ናቸው ያመኑት።  ማን አዘጋጃቸው?  ራሱ እግዚአብሔር!  በግልጽ የታወጀላቸውን የእግዚአብሔር ቃል ያመኑበት ምክንያት በእግዚአብሔር ለዚያ የተዘጋጁ በመሆናቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። 

ይሁዳም በመልዕክቱ ይሁዳ 1፡ 1 ላይ “በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤” ብሎ የጻፈላቸውን ቅዱሳን ምን ብሎ እንደሚለያቸው አስተውሉ። የኢየሱስ ክርስቶስ ሊሆኑ በእግዚአብሔር የተወደዱ ሁሉ ከዘላለም ለእርሱ የተጠበቁ ናቸው። የህም ለእርሱ ያልተጠበቁ ሌሎች መኖራቸውን ይጠቁማል።

ዮሐንስ10፥ 24-26 “አይሁድም እርሱን ከበው፦ እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት።  ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።”

ብዙዎች ዛሬ “አናንተ ስለማታምኑ ከበጎቼ አይደላችሁም” ይላሉ።  ጌታችን ግን የተናገረው እንደዚያ አይደለም፣  እናንተ የማታምኑት የእኔ በጎች ስላልሆናችሁ ነው ነበር ያለው። እኔ ከመረጥኳቸው ወገን አይደላችሁም ነው ያለው።  ያላመኑት ለዘላለም ሕይወት ስላልተመደቡ ነው። በኢየሱስ ያላመኑት በእግዚአብሔር ተወደው ለኢየሱስ የተጠበቁ ስላልሆኑ ነው።  የሚያምኑ ሁሉ (ብቻ) ሊድኑ፣ የዘላለም ህይወትን ሊወርሱ፤ ያላመኑ ግን ባለማመናቸው ሊጠፉ፣ ከዘላለምም ህይወት ሊጎድሉ ይህ ነው የመለኮት ምክር። ስለዚህ፣ አመንክ አላመንክ አትጠፋም የሚል የዩኒቨርሳሊስቶች እባባዊ ማባበል እንጂ እንዲህ የሚያስተምር የእግዚአብሔር ወንጌል የለም።


ዘላለማዊ ቅጣት:-

የእግዚአብሔር ወንጌል ግን ስለዘላለማዊ ሕይወትና ስለዘላለማዊ ጥፋት ያለው ትምህርቱ ግልጽ ነው፥ ይህንን ተመልከቱ፦

ዬሐንስ 3፥ 36 “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።”

በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ (ብቻ) የዘላለም ሕይወት አላቸው፣ የማያምኑት ግን ባለማመናቹው በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ናቸው።

ማቴዎስ 25፥ 46 “እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”

እዚህ ላይ “ቅጣት” በሚል የተተረጎመው ዋነኛ ቃል ማለት፡- “በወንጀል ምክንያት የሚፈጸም መሰቃየት ወይም ፍዳ” ማለት ነው።  ስያሜው በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ቦታ ብቻ ተጠቅሷል - 1 ዮሐንስ 4፥ 18 "ፍርሃት ቅጣት አለውና"  ስያሜው የተገኘበት ግስ ሁለት ጊዜ ጥቅም ላይ ይውላል፤ ተመልከቱ፡-

ሐዋርያት 4፥ 21 “እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና።”

2ጴጥሮስ 2፥ 9 “በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤”

ይህ ቃል ክፉዎች እንዴትና በምን እንደሚሰቃዩ ካላስተማረን ሌላ ምንም ቃል ሐሳቡን ሊገልጽን አይችልም። "ዘላለማዊ" ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ አዮኒዮስ ነው። በአዲስ ኪዳን ይህ "ዘላለማዊ" የተሰኘው ቃል ስድሳ ስድስት ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል።  ከእነዚህ ውስጥ ለአምሳ አንድ ጊዜ የጻድቃንን ደስታ ለማመልከት፣ ሁለት ጊዜ ደግሞ የእግዚአብሔርን መኖር ለማመልከት፣ ለስድስት ጊዜ የመሲሑ መንግሥት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት፣ በተቀሩት በሰባቱ ውስጥ ደግሞ ክፉዎች የሚቀበሉትን የወደፊት ቅጣት ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። በእነዚህ በሰባቱ ውስጥ ባለው የቃሉ አጠቃቀም ይህንን በዘላለማዊነት የተገደበ የቅጣት ቆይታ እሳቤን ከቃሉ ጋር ካያያዝነው፣ የጻድቃንን የወደፊት ክብር በተመለከተ  ለሃምሳ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለውን ገለጻ፣ በእግዚአብሔር ህልውና ላይ የተጠቀሱት ሁለቱን ሁኔታዎች፣ እንዲሁም ስለ መሲሁ ግዛት እና ስለ ቤተ ክርስቲያን ይህን ዘላለማዊነት የሚመለከቱትን ስድስቱን ጉዳዮች ለተወሰነ ጊዜ ይኸውም በዘላለማዊነት ተመሳሳይን ሀሳብ እንዲሰጥ ለማድረግ የትርጉም ቀዋሚነት የግድ ይላል።

ቅጣቱም ሆነ ሕይወት የተመደቡት “ዘላለማዊ” በተሰኘ ተመሳሳይ ቅጽል ነው፣ “አዮኒዮስ”፣ እኩል የሆነ የቆይታቸውን ወሰን አልባነት በግልጽ ያሳያል።  አዮኒዮስ የሚለውን ቃል ለመተርጎም ተርጓሚዎቹ የተለያዩ ቅጽሎችን ለመጠቀም መሞከራቸው በእጅጉ ያሳዝናል። የአንዱ የቆይታ ወሰን በወሰን አልባነት የተገደበ እንደሆነ ከተረጋገጠ፣ ሌላኛውም ቢሆን የቆይታ ወሰኑ በተመሳሳይ መከራከሪያ የጸና ሊሆን ይችላል፣ የቆይታ ጊዜውም ማለቂያ የሌለው ነው።

ዮሐንስ 5፥ 24 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።”

በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑት ሁሉ ሕይወትን አያዩም፣ ሁሉም በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ናቸው።  አማኞች ግን ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገሩ ስለሆኑ ወደ ፍርድም አይመጡም።

እግዚአብሔር ቁጣውን የመግለጽ መብት አለውን?  ፍትሑንስ የማሳየት መብት አለውን?  በእርግጥ ፣ አዎ!  እርሱ የቁጣ አምላክ ነውና የፍትህ አምላክ ነው። ቁጣው እና ፍትሁ እንደ ምሕረቱ፣ እንደ ጸጋው እና እንደ ፍቅሩ ሁሉ የባህርይውና የማንነቱ አካል ናቸው።  ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ቁጣውን ሲገልጥ እንደማይከብር አድርገው በስህተት ይገምታሉ፤ ልብ አድርጉ፣ እሱ ግን በቁጣውም ይከብራል። በቁጣው ይደሰታል፣ ፈቃዱንም ይፈጽማል። ቁጣው እንደሰው ቁጣ አይደለም፣ ቁጣው አያረክሰውም፣ በቁጣው ይቀደሳል፣ ከፍ ከፍም ይላል።  ቅዱስ ቁጣው ልክ እንደ ቅዱስ ፍቅሩ የቅዱስ እግዚአብሔር ባህርይ ነው።

Almighty Over All በተሰኘው መጽሐፋቸው አር.ሲ.  ስፕሮውል ይህን ግሩም መግለጫ ጽፈዋል፦

"እግዚአብሔር የገዛ ራሱን ቁጣ መለስ ብሎ በሚመለከትበት ጊዜ፣ ቢቻለው እንደ አንዳች የማይፈለግ ሸክም ሊያስወግደው በወደደ ነበር፣ ብለን ማሰብ አንችልም። ፈጽሞ፣ እግዚአብሔር በሁሉም ባህሪያቱ የሚደሰት የሆነውን ያህል  በቁጣውም የሚደሰት ነው። ይልቁንም እንዲህ ብሏል እንበል፣ “እኔ የማደርገው ነገር ቁጣዬን የሚመጥን አንዳች ነገር መፍጠር ነው፣ በእርሱም ላይ የቁጣዬን ክብርና ዋጋ ላሳይ የምችልበትን ነገር መፍጠር ነው።  በዛም ላይ ደግሞ ቁጣዬ በሚገባቸው በእነዚህ ፍጡራኔ መካከል በብዙዎች ላይ ጸጋዬን በማሳየት ምህረቴን እገልጣለሁ።” 

እኔም ከስፕሮውል ጋር እንዲህ እላለሁ፣ እግዚአብሔር ቅዱስ ፍቅሩን ከገዛ ራሱ መለኮታዊ ባህርይ ማስቀረት ወይም መነጠል እንደማይሆንለት ሁሉ ቅዱስ ቁጣውንም የባህርዩ አካል አድርጎ ይጠብቃል።


“ሁሉ” የዩኒቨርሳሊስቶች መንጠልጠያ   

ዩኒቨርሳሊስቶች ይህንን ቅዱስ አምላክ በቅዱስ ፍቅሩና በቅዱስ ቁጣው መረዳት አይችሉም። ይልቁንም ቀደም ሲል እንዳየነው ከቅዱሳት መጻህፍት ገጾች “ሁሉ” ወይም “ዓለም” የሚሉትን ቃላት ነቅሰው እያወጡ፣ የቃላት ጨዋታ በሚመስል አቀራረብ ምህረት ለሁሉ፣ ድነትም ለአለም እንደሆነ በማስተማር፣ “እግዚአብሔር ፍቅር የሆነ ባህርዩን በመቃረን ቁጣን ማድረግ አይቻለውም” ይላሉ። ለምሳሌም ከሚመዝዟቸው ጥቅሶች መካከል የሚከየሉትን ማየት ይቻላል፣ ጌታ ኢየሱስ እንድህ ብሏል፦

ዮሐንስ 12፥ 32 “እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።”

የዚህ ጥቅስ ትምህርት፣ እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ ወደ ራሱ ሲስብ የቀረው የለም ማለት ነውን?  ፈጽሞ እንደሱ አይደለም፣ እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ (በጅምላ) እንደማይወድ ወይም እንደማይመርጥ ቀደም ብለን አይተናል። በዚህም ምክንያት፣ እርሱ ራሱ ከዘላለም የመረጣቸውን ብቻ እንጂ ሰውን ሁሉ (በጅምላ) ወደ ራሱ አልሳበም።  የዚህን ጥቅስ አውድ መመልከት አለብን፡-

ዮሐንስ 12፥ 20-22 “በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው፦ ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት። ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት።”

እዚህ ላይ ኢየሱስን ማየት የሚፈልጉ የግሪክ ሰዎችን እናያለን።  በፍጥረታቸው አሕዛብ የሆኑ የግሪክ ሰዎች ክርስቶስ ምን ያደርግላቸዋል፣ ለምንስ ይፈልጉታል? ከክርስቶስ ጋርስ ምን የሚያገናኛቸው ጉዳይ ይኖራል?  እርሱ እንደሆነ የአይሁድ መሲህ ነው!  ታዲያ ባነሳነው ጥቅስ ላይ "ሁሉን" የሚለው ቃል ከአህዛብ ሁሉ በሚል ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው፣ ይኸውም "ከሁሉም የሰው ዘር" ማለት ነው። እግዚአብሔር አይሁድንና አህዛብን፣ ባለጠጎችንና ድሆችን፣ ባርያዎችንና ነፃ የሆኑትን ሊስብ ነው ማለት ነው እንጂ፤ ጥቅሱ ዩኒቨርሳሊዝምን አያስተምርም።

1ጢሞቴዎስ 2፥ 3-4 “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።”

እግዚአብሔር ሁሉም ሰዎች (በጅምላ) እንዲድኑ እንደሚፈልግ ይህ ጥቅስ አያስተምርምን?  በጭራሽ አያስተምርም!  የዚህንም ጥቅስ ዐውደ-ምንባብ መመልከት አለብን፡-

1ጢሞቴዎስ 2፥ 1-4 “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።”

ጳውሎስ ስለ ሰዎች ሁሉ፣ ስለ ነገሥታትና በሥልጣን ላይ ስላሉት ሁሉ እንዲጸለይ ይመክራል።  ክርስትና ገና ከጅማሬው በዋነኛነት በባሪያዎች እና በተራ ሰዎች የተዋቀረ እምነት ነበር።  ጳውሎስም “ስለ ሰዎች ሁሉ፣ ስለ ነገሥታትና ስለ ገዥዎችም እንኳ ሲናገር፣ እግዚአብሔር ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹን ደግሞ ያድናቸዋልና ጸልዩ” ብሏል እንጂ ሁሉም ሰው እንዳለ በጅምላ ይድናል አላለም።  "ሰዎች ሁሉ" ማለት በሁሉም አይነት የአኗኗር ደረጃ እና ዘር የሚወከሉ ሰዎች ማለት ነው። ይህም በዋናነት የዘር እና የማህበረሰብ ልዩነቶችን የሚያስወግድ አቀራረብ ነው።

2ጴጥሮስ 3፥ 9 “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”

ማንም እንዳይጠፋ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን?  እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ (በጅምላ) ማዳንስ ይፈልጋልን?  አስቀድመን ስናየው በነበረው መሰረት ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት እንደማይቸግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።  አሁንም የዚህን ጥቅስ አውድ መመልከት አለብን፡-

2ጴጥሮስ 3፥ 3-4 “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።”

እዚህ ላይ የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት እንመለከታለን፣ ዘባቾች በመባል የተገለጡት ሰዎች ፌዝ በቀላቀለ አገላለጽ "የተስፋ ቃሉ የት ነው ያለው? በቶሎ እንደሚመጣ ቃል የገባ መስሎን አልነበር ወይ" ሲሉ ይደመጣሉ።  በጊዜው የነበሩ ክርስቲያን ያልሆኑት አይሁዶች፣ የአይሁድን እምነት የሚከተሉና ሌሎችም የክርስትና ተቺዎች አሮጌውን አጥፍቶ አዲሱን ሰማይና ምድር ለማምጣት ክርስቶስ የተናገራቸው ትንቢቶች በመዘግየታቸው በቅዱሳን ላይ ይሳለቁባቸው ነበር።  ቁጥር 8 እና 9 ላይ የተጻፈው እነዚህ ዘባቾች የሚያነሱትን ጥያቄ ይመልሳል፡-

2ጴጥሮስ 3፥ 8-9 “እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”

የቁጥር 8 "ወዳጆች" የተባሉት እነማን ናቸው?  ክርስቲያን የሆኑ አይሁድ ናቸው።  እግዚአብሔር የገባውን የተስፋ ቃል አልረሳም፤ አሮጌውን ሰማይና ምድር አጥፍቶ አዲሱን ሰማይና ምድር ለማቋቋም በፍርድ ተመልሶ እንደሚመጣ የገባውን የተስፋ ቃል እየተናገረ ነው። “የተስፋው ቃል” ሲፈጸም የሚያዩት እነማን እንደሆኑ ጴጥሮስ ምን እንዳለ አስተውሉ።  ገና ወደፊት የሚመጣ ትውልድ ነውን?  በጭራሽ እንደሱ አይደለም፣ አውዱን ተመልከቱ (ቁ. 11፣ 12፣ 13፣14፣ 16)። ጴጥሮስ በዘመኑ ለነበሩት “እነዚህን ነገሮች ማየት እንፈልጋለን” ለሚሉ እየተናገረ ነው (ቁ. 13)።  "ስለ እኛ ይታገሣል" የሚለው በጥቅሉ ታዳጊያቸው ከጽዮን እስኪመጣ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ያሉትን የተመረጡትን አይሁዶች ያመለክታል። “ማንም እንዳይጠፋ ወዶ” በዚህ “ማንም” የተባሉት ቀደም ሲል በቁጥር 1 ላይ ወዳጆች የተባሉት ናቸው። እዚህ ላይ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጴጥሮስ እግዚአብሔር ሁሉንም ሰው (በጅምላ) ማዳን እንደሚፈልግ እየተናገረ አይደለም።  የጄ ግሪን ኢንተርሊንየር ባይብል ይህንን እንዲህ ብሎ ይገልጸዋል 

"ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም ነገር ግን ሁላችን ወደ ንስሐ እንድንደርስ እንጂ ከእኛ አንዳችን ስንኳ እንድንጠፋ ወዶ ስለ እኛ ይታገሣል።" “እናንተ” ማለትም  "እኛ" በሚል ተለይተው የሚታወቁት የተመረጡትን ያመለክታል።

1ዮሐንስ 2፥ 2 “እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።”

ይህ ጥቅስ ኢየሱስ የሁሉንም ሰው ኃጢያት (በጅምላ) ያስተሰርያል የሚለውን ትምህርት የሚያስተምር አይደለም፣ ይልቁንም በአለም ያለው ብቸኛው ማስተስረያ እርሱ እንደሆነ የሚያስተምር ነው።  እየተናገረ ያለውም ስለ ብቸኛው ማስተስረያ ነው እንጂ ስለ ዩኒቨርሳሊስት ማስተስረያ አይደለም።  በሌላ አነጋገር ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ማስተስረያ የለም።  ወደ ክርስቶስ ካልተመለከቱ በቀር ለሰዎች ኃጢአታቸውን የሚያስተሰርይ ሌላ ምንም ተስፋ የለም።  ለዓለም ሁሉ ያለው ብቸኛ ማስተሰረያ ኢየሱስ ነው ማለቱ ነው እንጂ፣ በአለም ያሉ ሁሉ ኃጢአታቸው በጅምላ ተሰርዮአል ማለቱ አይደለም።  ጴጥሮስም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ይኸንንው አስረግጦ ይነግረናል፡-

ሐዋርያት ሥራ 4፥ 10-12 “እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።”

ስለዚህ 1ኛ ዮሐንስ 2፥ 2 የዩኒቨርሳሊዝምን ትምህርት ኣይደግፍም።


መብት የእግዚአብሔር ወይስ የሰው ፦

ሮሜ 9፥ 15 “ለሙሴ፦ የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና።”

እዚህ ላይ እግዚአብሔር ለሙሴ ሥራውን የሚሰራበትን መርህ ሲነግረው እናያለን “የምምረውን ሰው እምረዋለሁ” ይላል፣ ማለትም የመማር መብቱ የእኔ ነው እንደማለት ነው።  ይህም መለኮታዊ መብት ያለው በማንም የማይገሰስ የሉአላዊ አምላክ ድንጋጌ ነው።  ምርጫ በእግዚአብሔር ምህረት ላይ የተመሰረተ ነው።  እግዚአብሔር አንዳንዶችን ለመዳን ይመርጣል ማለት እግዚአብሔር ለእነዚያ ሰዎች ምሕረትን ያደርጋል ማለት ነው።  እግዚአብሔር ለሚሻውና ለወደደው ሰው ምሕረትን ለማድረግ በራሱ ነፃ ነው። ማዳን የእግዚአብሔር መብቱ ነው፤ መጥፋት የሰው ዕድሉን ድርሻው ነውና መዳንን ግን በጸጋ ይቀበላል።

እግዚአብሔር በምሕረቱ ተግባር ሉዓላዊ ነው።  ምህረት ለየትኛውም የሰው ልጅ የሚገባው መብቱ አይደለም። የሰው ልጅ በማንነቱ የሚገባው ቁጣ ብቻ ነው። ምህረት እግዚአብሔር በአምላካዊ ባህሪው የሚራራበት እና ምስኪኖችን ከጭንቅ የሚያሳርፍበት ስጦታው ነው።  ስለዚህም እርሱ የምሕረት ዕቃዎች ያደረጋቸው ሰዎች ሁሉ ከመነሻው ምስኪኖች ናቸው እንጂ ለተደረገላቸው ምህረት ባለ መብቶች አይደሉም። ምስኪኖችም ምህረት ሳይሆን ቅጣት የሚገባቸው ናቸው። ምህረትን መቀበል እና መብትን ማስከበር ፈጽሞ ተቃራኒ ጉዳዮች ናቸው። ምህረት እንደሚገባው ሆኖ መናገርም የቃላት ተቃርኖ ነው። በምህረት ጉዳይ የመለኮታዊ አሰራር መርሁ የኸው ነው፥ እግዚአብሔር ለሚሻውና ለወደደው ሰው ምሕረትን ይሰጣል፥ ለራሱም መልካም መስሎ እንደታየው ምሕረትን ይከለክላል።


ማጠቃለያ

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ (ብቻ) የእግዚአብሔርን ምሕረት ያገኛሉ፣ እግዚአብሔርም የመረጣቸው ሰዎች ብቻ ያምናሉ። የእግዚአብሔር የቁጣ እና የፍትህ ባህሪያት ግን ባልተመረጡት ላይ ይገለጣሉ። እግዚአብሔር ሁሉንም (በጅምላ) አይወድም፣ “ሁሉንም” ሰዎች ደግሞ (በጅምላ) አያድናቸውም። በክርስቶስ እናምን እና እንድን ዘንድ ምህረት ያደረገልን እኛን ግን ለምህረት እንጂ ለቁጣ አልመረጠንም። 

ይህም እርሱ ብቻውን የሆነ፣ ከእርሱም በቀር ማንም ያልሆነ አምላካችን የኃይሉን ታላቅነት ያሳይ ዘንድና የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ነው። ለአለምና ለዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን! አሜን!! 

ግዛቸው።

ለዚህ ጥናት ግብአት የሆኑ ሰነዶች

አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የ 1962 እትም እና አዲሱ መደበኛ ትርጉም

Augustine; On Free Choice of the Will

Barth, Karl; The Epistle to the Romans

Bruce, F. F; The International Bible Commentary with the NIV

Beeke & Smalley; Reformed Systematic Theology: Spirit and Salvation, Vol. 3

Calvin; The Institute of Christian Religion

Carson, D. A; NIV Biblical Theology Study Bible

Engelbrecht, Edward. A (general editor); The Lutheran Study Bible

Hendriksen, William; New Testament Commentary :The Gospel of John

Kepler, Thomas S; The Table Talk of Martin Luther

Luther, Martin; The Bondage of the will

Sproul, R.C; Almighty Over All

Steele N. David and Thomas C. Curtis; Romans: An Interpretive Outline

Whittemore, Thomas; The Plain Guide to Universalism