በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ብርሃን
መግቢያ፦
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎችና ማብራሪያዎች ላይ እንደሰፈረው፣ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ላይ ስላለው አሳብ፣ ፕላኔቷ ራሷ፣ ማለትም “የሰማይ ፍጥረት” /the elements/ “ይቃጠላሉ” የሚል አንድምታ ያለው ትርጉም በብዙዎች ተሰጥቶት እናነባለን። የዛሬ ዘመን የቃሉ አንባቢዎችም ይህንን ክፍል ሲረዱ በብዙዎች ዘንድ ያለው የተለመደ አመለካከት፣ በእርግጥ ምንባቡ ስለ ሰው ልጆች የታሪክ ፍጻሜ እና ስለ አጥናፈ አለሙ /universe/ ዕጣ ፈንታ እየተናገረ ነው የሚል ግንዛቤን ይዘዋል። ዳሩ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በወጉ የምናጠና ከሆነ ይህ ምንባብ ቃል በቃል /literally/ ስለ ግዑዙ ፍጥረተ አለም መቃጠል ወይም ስለ ኮስሞስ ጥፋት የሚናገር ቃል አለመሆኑን፤ ይልቁን ግን እግዚአብሔር በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ፍርዱን ባደረገ ጊዜ ያኔ በ70 ዓ.ም ሊመጣ ስላለው ክስተት የተነገረ ቃል መሆኑን እናስተውላለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ በተነበየውና፣ በ70 ዓ.ም ላይ ሮማዊያን ሲመጡ በህዝቡና በከተማይቱ ላይ በሆነው የእልቂት ጥፋት፣ ያኔ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዶች እንደተጨፈጨፉ፣ ቤተ መቅደሱም እንደፈረሰ እና ከእርሱም ጋር የአሮጌው ኪዳን ሥርዓት ለመጨረሻ ጊዜ እስከወዲያኛው እንደተወገደ ከቅዱሳት መጻህፍት (ማቴ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ) እና ከታሪካዊ መዛግብት በግልጽ እናነባለን።
እንግዲህ የዚህ አይነተኛ ምዕራፍ ወሳኙና አከራካሪው ጥቅስም ምዕራፍ 3፥ 10 ላይ ያለው ነው፣ ቃሉም በአማርኛችን፦ “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” የሚለው ነው።
ከመነሻዬ የቃሉን ባለቤት የማመሰግነው ይህ ይሆናል የተባለው “ኮስሚክ ውድመት” ድንገት ከሚመጣው የጌታ ቀን ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም መላው አዲስ ኪዳ ይመጣል ሲል የሚናገርለት አንዱ የጌታ ቀን ያ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት እና ከመሆን የማይቀር ምጽአት በመሆኑ ነው። የዚህ ጥቅስ ትርጉም ውሃ ልኩም የሚያርፈው መጽሐፍ ቅዱስ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት በመጀመሪያው ክፍለዘመን ላይ የሚፈጸም ተስፋ አድርጎ ባቀረበበት አጠቃላይ አውድ ላይ ነው። ስለዚህ ይህንን ጥቅስ ለመተርጎም ከዚህ በኋላ ለማነሳላችሁ ነጥቦች ሁሉ ይህ ኣሳብ ምን ያህል የጀርባ አጥንት እንደሆነልኝ በውነት አልሸሽግም።
የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ይህንን ጥቅስ እንዴት እንደሚያስቀምጡት አንዳንድ ማሳያዎችን ላቅርብ፣
አዲሱ ትርጉም፦ “የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ የጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል።”
አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል” ይላል።
ህያው ቃል፦ “ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ እንደማይትወቅ ሁሉ የጌታም ዳግም ምፅአት እንደዚያው ሳይታሰብ በድንገት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰማያት በታላቅ ድምፅ ተነዋውጠው ያልፋሉ። የሰማይ አካላት እንደ ሰም ይቀልጣሉ። ምድርና በላይዋ ያለ ነገር ሁሉ በእሳት የጋያል።”
በአንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ደግሞ።
But the day of the Lord will come as a thief in the night, in which the heavens will pass away with a great noise, and the elements [stoicheion] will melt with fervent heat; both the earth and the works that are in it will be burned up [katakaio]. (2 Peter 3:10, New King James Version)
But the day of the Lord will come like a thief, and then the heavens will pass away with a roar, and the heavenly bodies [stoicheion] will be burned up and dissolved, and the earth and the works that are done on it will be exposed [katakaio]. (2 Peter 3:10, English Standard Version)
But the day of the Lord will come as unexpectedly as a thief. Then the heavens will pass away with a terrible noise, and the very elements [stoicheion] themselves will disappear in fire, and the earth and everything on it will be found to deserve judgment [katakaio]. (2 Peter 3:10, New Living Translation)
ቀጥሎ በማነሳቸው ነጥቦች ቅዱሳት መጻሕፍትን በራሳቸው በቅዱሳት መጻሕፍት በመተርጎም ይህንን ጥቅስ እየመረመርን የነገሩን ውል በአውደ ምንባቡ ውስጥ እንፈልጋለን። ምናልባት የህንን የምታነቡ፥ ምድር ተቃጥላ ትጠፋለች፣ የሰው ልጆች ታሪክም በዕልቂት የዘጋል፣ ወዘተ… የሚል ትምህርት መጽናናት የሚሰጣችሁ ክርስቲያኖች ካላችሁ ከዚህ ቀጥሎ የማነሳቸው 12 ነጥቦች ሊያስቆጣችሁ ስለሚችል ጽሁፉን ታግሳችሁ እንደታነቡ እጠይቃለሁ።
፩ኛ/ በምዕራፍ 3፥ 10 ላይ ይህ “ይቃጠላሉ” የተባለው “የሰማይም ፍጥረት” ለሚለው ሃረግ የግሪኩ አቻ ቃል “ስቶይቺዮን” ነው። ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለበት በሁሉም ስፍራ የሚያመለክተው ስለ ብሉይ ኪዳን “አካላት” ወይም የአይሁድን አካላትት /Jewish elements/ ነው እንጂ ስለ ተዳሳሹ አጥናፍ አለም ጉዳዮች አይደለም። ይህ ስቶይቺዮን የተሰኘ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴትና በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳዩንን እነዚህን ምንባባት በጥንቃቄ ተመልከቱ፡
ገላትያ 4፥ 3፣ 9፤ “እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤… አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?”
እዚህ ላይ ቃሉ የሚያመለክተው ክርስትና ካስገኘላቸው ነጻነት በፊት በባርነት ይገዙበት የነበረውን ኃሰተኛ ትምህርት እና በእርሱ የሚዘወረውን የባርነት ኑሮ ነው። የገላትያ ሰዎች ዳግመኛ እየተወሰዱበት የነበረው ኃሰተኛ ሐይማኖት ደግሞ ይሁዲነት ነበር።
ቆላስይስ 2፥ 8-9፣ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤”
ቆላ 2፥ 20-22፤ “ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና”
በዚህም አሮጌውን ኪዳን የመሰሉ የተለያዩ ኃሰተኛ ኃይማኖቶች ከባርነት በታች ገዝቶ ለማቆየት የሚያሳድሩትን ክፉ ተጽዕኖ ነው የሚያሳየው።
ዕብራውያን 5፥ 12-13 “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት (stoicheia) እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤”
እዚህም ያለው ትርጉም በዐውደ ምንባቡ ውስጥ አነስተኛ ዋጋ ስላላቸውና “የሕፃንነትን ትምህርት” በመባል ስለሚታወቁት ወይም በቁጥር 11 ላይ ጆሮቻቸውን ያፈዘዘ የህጉ ትምህርት ግልጽ ወይም የመጀመሪያ መርሆዎች በተመለከተ የተነገረ ነው።
እንግዲህ ይህ የግሪኩ “ስቶይቺዮን” የሚለው ቃል በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አጠቃቀም የቀደመውን አሮጌ ወይም አለማዊ የትምህርትና የባርነት አኗኗር በሚያመለክትበት ዘይቤ ቀርቦ ሳለ፣ 2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3፥ 10 ያለውን ግን ከዚህ የቃሉ ጠቀሜታ ነጥሎ፣ የለም ግዑዙን ፍጥረተ ዓለም ነው የሚያመለክተው ብሎ ለመተርጎም መሞከር ወደ ፍጹም ስህተት ያመራል።
፪ኛ/ በሌላ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ በትምህርቱ ቀዋሚነት፣ ያለተፋልሶ ምድር ወይም ይህ ግዑዝ ዓለም ፍጻሜ የሌለው እንደሆነ አድርጎ ያስተምራል (ለምሳሌ መክብብ 1፥ 4፤ መዝሙር 78፥ 69፤ 104፥ 5፤ 148፥ 3-6፤ ኤፌሶን 3፥ 21ተመልከቱ)፤ እእግዚአብሔር አምላክም ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ እንደማያጠፋ ቃል ገብቷል፣ (ዘፍጥረት 8፥ 21፤ 9፥ 11)።
ይህንን ሃሳብ በተመለከተ ቀደም ሲል በብሎገሬ ላይ “ይህ አለም ፍጻሜ አለውን?” በሚል ርእስ በዝርዝር ያካፈልኩትን ጽሁፍ እንድታዩት ሊንኩን ላጋራችሁ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2016/11/blog-post.html?m=1
፫ኛ/ በጴጥሮስ መልዕክቶች እና ንግግሮች አውድ ካየነው ጴጥሮስ እየደጋገመ የሚያነሳው የመጨረሻው ዘመን ፍጻሜ፣ ያኔ ለእርሱና ለተደራስያኑ እጅግ የቀረበ ነበር። በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥ 7 እንደተነገረው “የነገር ሁሉ” ፍጻሜ ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልዕክቱን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ያኔ “ቀረቦ” ነበር። በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥ 17 ላይ እንደተነገረው ደግሞ “ፍርድ የሚጀምርበት ጊዜ” ያኔ ደርሶ ነበር። በሐዋርያት ሥራ 2፥ 14-20 እና 1 ጴጥሮስ 1፥ 20 መሠረትም ጴጥሮስ ራሱ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ይኖር እንደነበር ያውቅና ያምን ነበር።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ መጨረሻው ቀን/ስለ ፍጻሜ ዘመን 19 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፣ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች ያለ ልዩነት ቃላቸው አንድ ሆኖ በአንድ ድምፅ ሲናገሩ - እነሱ ራሳቸው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ይመሰክራሉ፣ ይህም እነርሱ የኖሩበት የመጨረሻ ዘመን ማለት የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ማለት ነው እንጂ የዚህ ተዳሳሽ ዓለም (የኮስሞስ) መጨረሻ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስም ያለ ልዩነት የሚያውቀው አንዱን የመጨረሻ ዘመን ብቻ ነው።
፬ኛ/ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት የተነገረው ይህ “የጌታ ቀን” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 10) ርዕሰ ጉዳይ እግዚአብሔር አምላክ በተለያዩ ህዝቦች ላይ በተከታታይ ስለሚያመጣው ፍርድ የሚናገር ነው እንጂ፣ ፈጽሞ ስለ ግዑዝ ፕላኔትና ስለ ተዳሳሽ ዓለም ጥፋት የሚናገር አይደለም።
ለምሳሌ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ምንባባት ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፦
¶ በኢሳይያስ 34 ላይ ኤዶምያስን በተመለከተ ስለተነገረው የፍርድ ቀን ሲናገር በቁጥር 4 ላይ “የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።” ሲል ስለ ቀኑ ይናገራል፤
¶ በኤርምያስ 46፥ 10 ላይ በስም በተጠቀሱ የተለያዩ ህዝቦች ላይ ስለሚመጣ ፍርድ ሲናገር “ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፤…” ሲል ይናገራል፤
¶ በሰቆቃወ ኤርምያስ 2፥ 22 በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣው የፍርድ ቀን ሲናገር “እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው” ያላል፤
¶ በሕዝቅኤል 13፥ 5 ላይም የእስራኤልን ሐሰተኛ ነቢያት ሲከስሳቸው ”በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም” ሲል በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን እስራኤልን እንዳላዳንዋት ይመሰክርባቸዋል።
¶ በሕዝቅኤል 30፥ 2-4 ላይም በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ስለሚሆን የፍርድ ቀን ሲናገር “የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል። ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል” ሲል ይናገራል፤
¶ በትንቢተ አሞጽ 5፥ 18-20 ባለውም ክፍልም የእግዚአብሔር ቀን በእስራኤል ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ሲናገር “የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም። ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው። የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” ሲል ይናገራል፤
¶ በአብድዩ ቁጥር 15 ላይም የእግዚአብሔር ቀንን አስመልክቶ “የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል” ሲል ኤዶምያስን ያስጠነቅቃል፤
¶ በሶፎንያስ 1፥ 2-18 ባለውም ክፍል በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚደርሰው የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ይናገራል።
እንግዲህ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ እንደሚመጣ የተነገረው የእግዚአብሔር ቀን ፍርድ አንዳንዶቹ በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል በጠላቶችዋ እጅ በወደቀችበት ወቅት የተፈጸሙ ሲህን፣ እንደ ሚልክያስ 3፥ 2-5፤ 4፥ 1-5 ባሉ ክፍሎች “የሚነድ/ የሚቃጠል” የእግዚአብሔር ቀን ተብሎ የተገለጠው ደግሞ ከ70 ዓ.ም የኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር የተያያዘው ፍርድ ነው፤ ይህም የቁጣ ቀን በማቴዎስ 3፥ 7-12፣ ባለው ክፍል ላይ በሰፈረው የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት፦ “ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፦ ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” በሚል የተረጋገጠው ነው።
በተመሳሳይ ማቴዎስ 13፥ 49-50; 21፥ 33-45; 22፥ 7; ወዘተ ያለውም ስለዚሁ ፍርድ የሚናገር ነው። መጥምቁ ዮሐንስ በሚልክያስ 3፥ 1፤ 4፥ 5 የተነገረውን የኤልያስን ዳግመኛ መምጣት በመንፈስ እንደፈፀመ አስተውሉ፤ (ማቴዎስ 11፥ 14፣ 17፥ 11-13)። አዲስ ኪዳን በግልጽ የሚናገርለት ታላቁ ፍርድም ግልጽ ትኩረት የሰጠው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በነበሩ አይሁድ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት ነው (ማቴዎስ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ.) እንጂ—በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ስለሚደርስ ‘የፕላኔት አለም ጥፋት’ አይደለም።
፭ኛ/ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ያኔ በዘመናቸው የጌታ ቀን አስቀድሞ መጥቷል ብለው ማሰባቸው በእውነት የሚደንቅና ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው፤ “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን” ይላልና (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 1-2)! ስለዚህ፣ እነርሱ ስለ ጌታ ቀን ሲያስቡ አሁን በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች ካላቸው የተለየ ግንዛቤ እንደነበራቸ አስተውሉ። አያችሁ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የጌታ ቀን የፕላኔት ምድርና ሰማይ መቃጠልን ሳያካትት፣ ሳያውቁት ሊያልፋቸው እንደሚችል እንኳ ያስቡ ነበር ።
፮ኛ/ ስለተፈጥሮ ሥርዓት የኮስሚክ ነውጥን የሚያመለክት የንግግር ዘይቤ መደበኛ በሆነው የዕብራይስጥ አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ የተለመደ ነው፤ ቃል በቃል ባልሆኑ አገላለጾች ስለ ሥነ-መለኮታዊ ወይም ቃል ኪዳናዊ ክንውኖች፣ እንዲሁም በተለይ እግዚአብሔር በደለኛ በሆኑና ቁጣው በሚገባቸው ህዝቦች ላይ ስለሚያመጣው ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ እንዲህ ያለ ትዕምርታዊና አምሳላዊ የቋንቋ ዘይቤ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል እናያለን። ጊዜ ወስዶ ቀጥሎ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች በመመልከት ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል:-
¶ 2ሳሙኤል 22፥ 8-16፣ እግዚአብሔር በዳዊት ጠላቶች ላይ ያመጣውን ፍርድ በተመለከተ፤
¶ ኢሳይያስ 13፥ 10-13፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤
¶ ኢሳይያስ 34፥ 4፣ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ በተመለከተ፤
¶ ኤርምያስ 4፥ 1-31፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤
¶ ሕዝቅኤል 32፥ 7-8፣ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፅ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤
¶ ሚክያስ 1፥ 2-16፣ እግዚአብሔር በእስራኤልና በይሁዳ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤
¶ ናሆም 1፥ 2-8፣ እግዚአብሔር በነነዌ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ እንዲሁም
¶ ሶፎንያስ 1፥ 2-18፣ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በይሁዳ ጠላቶች ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ
ከፍ ሲል በተጠቀሱ ምንባባት በኮስሚክ ነውጥ የተወከለው ገለጻ፣ ንግግሩ የተፈጥሮ ሥርዓት ነውጥን ሳይሆን በኃጢአት ምክንያት በህዝቦችና በነገስታት ላይ የሚደርሰውን መለኮታዊ ቁጣ የሚያመለክቱ መሆናቸውን አስተውሉ።
፯ኛ/ የሐዋርያው ጴጥሮስ “ሰማይና ምድር” የሚል አነጋገሩን ልብ አድርጉ፦ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 13) ሲል ያነሳውን ተስፋ በቀጥታ የወሰደው በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካለው የቃሉ አጠቃቀም ነው። ስለ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ከሚናገሩት መሠረታዊ የንባብ ክፍሎች መካከል ኢሳይያስ 65-66 እና ራዕይ 21 ላይ የሚገኙት ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ እግዚአብሔር በጠላቶቹ ላይ ስለሚያደርገው ፍርድ በግልጽ እናያለን፤ ነገር ግን በክፍሉ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው ፍርዱ ከተፈጸመም በኋላ የተለመደው የሰው ልጅ ታሪክ ይቀጥላል እንጂ አይቋረጥም ። ይህም ማለት ኃጢአትና ሞት በተቀረው ፍጥረታዊ ዓለም ውስጥ መኖሩ ይቀጥላል ማለት ነው (ኢሳይያስ 65፥ 20፤ ራእይ 22፥ 15)፤ አንዳንድ ሰዎችም ስለ እግዚአብሔር ገና ያልሰሙ በመሆናቸው የወንጌል ስብከት አገልግሎት አስቀድሞ በተፈጸመው ፍርድ ከመታወጅ ሳይቋረጥ ኃጢአተኞችን ውደ ጽድቅ በእምነትና በንስሃ የመጋበዙ ሥራ ይቀጥላል ማለት ነው (ኢሳይያስ 66፥ 19-24)። ስለዚህ በአጠቃላይ አውዱ መሰረት አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድር ማለት ጨርሶ ቀድሞ ያልነበረ ሌላ ተዳሳሽ ግዑዝ ዓለም ይፈጠራል ማለት አይደለም፤ የአሮጌው ሰማይና ምድር ተጠቅልሎ ማለፍም ፍጥረታዊው የሰው ልጆች ዓለም ታሪክ መጨረሻው ይሆናል ማለት ፈጽሞ አይደለም። በተጨማሪም በማቴዎስ 5፥ 17-18 ላይ ኢየሱስ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን ከጸጋ ዘመን መጀመር እና ከአሮጌው ኪዳን የህግ ዘመን ማብቂያ ጋር በማገናኘት መናገሩን ልብ ይሏል፤ እርሱም ያለፈውን አሮጌ ዘመን ፍጻሜ የሚያመለክት ሲሆን- ይህም የሰማይና የምድር ህልፈት በዕብራውያን 8፥ 13 “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል” በሚል የተነገረውንና በ70 ዓ.ም. የሆነውን የአሮጌውን ኪዳን ፍጻሜ የሚያሳይ ነው። ጴጥሮስም በዚሁ የቃሉ መንፈስ ከፊቱ ያለውን 70 ዓ.ም እያየ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 7) ሲል ይመሰክራል።
ስለዚህ ተስፋ የተገባው አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር በውበቱ የሚያብረቀርቅና የሚያንጸባርቅ፣ መጻኢያንም እንደሚመስላቸው ይህኛው አለም ከጠፋ በኋላ ገና የሚፈጠር አዲስ ፕላኔት ማለት ሳይሆን፣ ይልቁንም ኃጢአትና ሞት የነገሰበት የአሮጌው ኪዳን አገዛዝ፣ እርሱም ይሁዲነት በእሳት ፍርድ ተወግዶ፣ ጽድቅ የሚገዛበት የአዲሱ ቃል ኪዳን መንግስት፣ እርሱም ክርስትናችን በህይወት የሚነግስበት ነው።
፰ኛ/ “ይቃጠላል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል “ካታካዮ” የሚለው ነው፤ በተለያዩ ትርጉሞች ውስጥ “የተጋለጠ፣” “ፍርድ የተገባው ሆኖ ተገኝቷል” ወይም “የተራቆተ” ተብሎ ተተርጉሟል። እንደሚታወቀው ‘እሳት’ የፍርድ ምልክት ነው፣ ይኸውም ከፍ ሲል ካለው የንባቡ ክፍል የተሳበ ነው። ይህም በ70 ዓ.ም በአሮጌው ኪዳን ላይ ለሆነው ጥፋት ተስማሚ ቋንቋ ነው።
፱ኛ/ በመልእክቱ ውስጥ “ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤” (2ጴጥሮስ 3፥ 6) በሚል የተገለጠው በኖህ ዘመን የሆነው ጥፋት ከዚህ በሰማይና ምድር መቃጠል ከተወከለ አነጋገር ጋር በንጽጽር ቀርቧል። በህጉ እንደተጻፈው ያኔ በኖህ የጥፋት ውሃ ዘመን ኃጢአተኞች ብቻ በጥፋት ውሃ ጠፍተዋል። “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥” (2ጴጥሮስ 2፥ 5) እንደተባለ፣ ኖህ እና ቤተሰቡ ግን ከዚህ ጥፋት በውሃ የዳኑበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም በ70 ዓ.ም ከተፈጸመው ጥፋት ጋር ተመሳሳይ ነው። እግዚአብሔር በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ስለ ኃጢአታቸው እና ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የበቀል እርምጃ እንደወሰደባቸው (ማቴ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ) ግልጽ ነውና። ይህም የበቀል እርምጃ በቅዱሳት መጻህፍት ሁሉ ለዳግመኛ ምጽአቱ ከተቀጠረውና ከተነገረው ጊዜ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን፤ ይህ ጥፋትና በቀል በተፈጸመበት ታሪካዊው የ70ው አ.ም የኢየሩሳሌም ውድመት ጊዜ ግን ይህ ግዑዙ ፕላኔት ዓለም ምንም የሆነው ነገር አልነበረም። ይልቁንም እግዚአብሔር በኖኅ የጥፋት ውኃ ዘመን ባደረገው ኪዳን መሰረት ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፈጽሞ እንደማያጠፋ ቃል መግባቱን እናውቃለን (ዘፍጥረት 8፥ 21)።
፲ኛ/ “አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት” የሚለው አነጋገር (2ጴጥሮስ 3፥ 8) ብዙ ጊዜ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጊዜ ጠቋሚ ሆነው የተነገሩ አገላለጾችን፣ ማለትም “ይህ ትውልድ”፣ “እዚህ ከቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ”፣ “ቶሎ”፣ “ቅርብ”፣ “ሊሆን ያለ” ወዘተ ያሉትንና የመሳሰሉትን በርካታ የሆኑ መግለጫዎች ውድቅ ለማድረግ መጻኢያን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ነገር ግን "አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት" የሚለው፣ ቃል በቃል በጥሬው ሊወሰድና ሊተረጎም ከቶ አይችልም፣ እንደዚያ የሚወሰድና የሚተረጎም ከሆነ ግን በአውደ ምንባብ ውስጥ ያለው አጠቃላይ የመጨረሻው ዘመን አሳብና ትምህርት ምንም እርባና ወይም ትርጉም የሌለው ይሆናል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር አጭር ጊዜ ማለት ረጅም ጊዜ ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ፣ ጌታ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ የቆየው ለ3,000 ዓመታት ነበርን? የሚል፣ ወይም እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ሰርቶ የጨረሰው በ6000 ዓመታት ነውን? ከሥራው ያረፈውስ በ7ኛው ሺህ ዓመት ነውን? የሚል እርባና የሌለው ጥያቄ ያስነሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን “አንድ ሺህ” የተሰኘው ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ የምልዓት ምሳሌያዊ ቃል ሆኖ ማገልገሉን አትዘንጉ።
በዚህ ሃሳብ ላይ “ጴጥሮስን በጴጥሮስ” በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ያካፈልኩትን አጭር ጽሁፍ እንድታነቡት ጋበዝኳችሁ፦
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid0gnU6ufdWSxfXTMAs6WmR9AnZ8MVm8q7KYcFZmApgwyZEAtGeKs4iNx7W8kdEvfH3l&id=100002668627386&mibextid=Nif5oz
፲፩ኛ/ ጴጥይሮስ በመልዕክቱ 3ኛ ምዕራፍ ከቁጥር 11-13 ባለው ንግግሩ ለአንባቢዎቹ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እንዲጠብቁ እና እንዲያስቸኩሉ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ሲል ይመክራቸዋል። በዚህ ምክሩ ውስጥም ይፈጸማሉ የተባሉ ድርጊቶች የሚከናወኑበትን ጊዜ አስመልክቶ “አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን” ያህል ስለመሆኑ የተነገረውን፣ የመልዕክቱን ሃሳብ ማግኘት ካለብን ምናልባት ጉዳዩ በርካታ ክርስቲያኖች በጥሬው ከሚያስቡት በተለየ ተቃራኒውን ነገር ማለት እንደሆነ ልናስብበት ይገባል። ጴጥሮስ በዚህ ንግግሩ ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁት ጉዳዮች - በተለይ ጊዜውን አስመልክቶ በሌሎች ምንባባት ውስጥ ከተሰጡትና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈጸማሉ ከተባሉት መግለጫዎች አንጻር ለፍጻሜአቸው ወደ ፊት የቀራቸው አጭር ጊዜ ብቻ ነው እንጂ - ብዙም አይደለም ማለቱ ነበር (ሐዋርያት ሥራ 2፥ 14-20፤ 1 ጴጥሮስ 1፥ 20፤ 4፥ 7፤ 17)።
፲፪ኛ/ አንዴ እዚህ ጋር ቆም ብላችሁ እስቲ አስቡት! እዚህ በ2ጴጥሮስ 3፥ 3 የተነገረው “የመምጣቱ ተስፋ!” በእርግጥ ስለ ኢየሱስ ዳግመኛ መምጣት ነውን? ልብ አድርጉ አዲስ ኩዳን ያለ ልዩነት በየመጻህፍቱ ሁሉ በቀጥታም በተዘዋዋሪ የሚናገርለት ይህ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት ርዕሰ ጉዳይ ምንም ቢሆን ጊዜው የተነገረና የተገለጠ ነው። ይህም ጊዜ የሐዋርያቱ ዘመን፣ ያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን መሆኑ አያጠራጥርም። ያኔ ደግሞ ዛሬ መጻኢያን የሚያስቡት አይነት ጥፋት ግዑዝዋ ፕላኔት ምድር ላይ የደረሰ ነገር የለም። በርካታ መጻኢያን ግን ዛሬም ድረስ ግዑዙ አለም ቡን ብሎ ስላልጠፋ፣ ወይም ሲጠፋ ስላላዩ እርግጠኛ ሆነው፣ ጌታ በ70 ዓ.ም አልተመለሰም! ሲሉ ይደመጣሉ፤ እኛ ግን የለም “ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድ ተመልሷል” በሚል እርግጠኝነት ቆመናል። ይህን ያህል እርግጠኛ ለመሆን የሚያስፈልገው የጌታን ቃል ማመን ብቻ እንጂ ይህ አለም ሲቃጠል ማየት አይደለም። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ለማብራራት የሚሄዱቡት የተለያዩ መንገዶች አሏቸው። አንዳንዶቹ ይህ ጥቅስ ስለ “ዳግመኛ ምጽአት” አይደለም ሲሉ በድፍረት ይክዳሉ። ሌሎች ደግሞ ይህንን ጥቅስ ከዐውደ-ምንባቡ ይነጥሉና የቀረውን የምዕራፉን ክፍል ብቻ ባለፈው ታሪክ ውስጥ እንደተፈጸመ በማሰብ የዚህን “የፍጥረተ አለም ፍጻሜ” ግን ገና ወደፊት ላለ መጻኢ ዘመን ሊለጥጡትና ሊያሻግሩት ይፈልጋሉ። ይህንንም ባደረጉ መጠን ቃሉ የተነገራቸውን በኩረ ተደራስያን አግልለው የሌለና ያልተባለ ነገር ለማመንና ለመጠባበቅ ይገደዳሉ። ሌሎቻችን ደግሞ በዚህ ክፍል የተነገረው የኢየሱስ “መምጣት” በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው ተደጋጋሚ የእግዚአብሔር “መምጣት” ጋር የሚመሳሰል “ለፍርድ መምጣት” እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተን እንናገራለን። ያም ሆነ ይህ፣ ጴጥሮስ በቅርቡ ይሆናል ሲል በሚያነሳው ማሳሰቢያ “ለዘባቾች” ከሰጠው ማስጠንቀቂያ በግልጽ የሚታይ አንድ ነገር አለ። በዚያን ዘመን ከ70 አ.ም በፊት የነበሩ አንዳንድ ዘባቾች (2ጴጥሮስ 3፥ 3) ኢየሱስ በትውልዳቸው መጥቶ ቤተ መቅደሱን እንደሚያፈርስ በገባው ቃል መሰረት (ማቴዎስ 24፥ 1-3፤ 29-34)፣ ቃሉን አክብሮ አልመጣም ሲሉ ክርስቲያኖች በነበራቸው ተስፋ ላይ ያፌዙና ይሳለቁ ነበር። ጴጥሮስ ግን “ጌታ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም” (2ጴጥሮስ 3፥ 9) በማለት ይመልሳል። ጴጥሮስ እነዚያ በክርስቲያኖች ተስፋ ላይ ይሳለቁ የነበሩትን ሰዎች እያስጠነቀቀ፣ ጌታ ኢየሱስ አንዳንዶቹ በሕይወት እያሉ በእስራኤል ላይ ለመፈጸም የገባውን የፍርድ ቃል ቸል ብሏል ብለው በማመን ስህተት እንዳይሠሩ በጥብቅ እየነገራቸው ነበር (ማቴዎስ 10፥ 15-23፤ 16፥ 27-28፤ 26፥ 64፤ ራእይ 1፥ 1-3፤ ወዘተ.) ባለቤቱ ተኝቶ ሳለ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣበት” በነዚያ ፌዘኞች ላይ ሳያስቡትና ሳይዘጋጁ “የጌታ ቀን” እንደሚመጣባቸው በማሳየት በማያሻማ መንገድ ፌዘኞችን አስጠንቅቋል። ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ማስጠንቀቂያዎች፣ ለምሳሌ ማቴዎስ 24፥ 34-43፣ 1ተሰሎንቄ 5፥ 2-4፤ ራእይ 16፥ 15፤ 22፥ 6-20 በዚሁ መንፈስ የቀረቡ ነበር። በክፍሉ ውስጥ የተጠቆመው የመዘግየት ሃሳብ ወይም “ዝግታ” ግን በዚያ የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ለነበሩ ሰዎች “ሁሉ ወደ ንስሃ” ይመጡ እና ከጥፋት ይድኑ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን ትዕግስት ማሳያ ብቻ ነው።
ማጠቃለያ፦
የብሉይ ኪዳን ነቢያት በትውልዳቸው ውስጥ በነበሩ ህዝቦችና ነገስታት ላይ ሊሆን ያለውን መልኮታዊ ፍርድ ሲገልጹ፣ የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያንም እነርሱ የነበሩበትን የመጨረሻውን ዘመን የፍርድ እውነታዎች ሲያመለክቱ ሁሉም በአንድ አይነት የአነጋገር ዘይቤ የኮስሞቲክ ነውጥ አዘል ቋንቋዎችን ይጠቀማሉ። ጴጥሮስም ወደፊት የሚመጣውን ጥፋት (እርሱም የኢየሩሳሌምን ጥፋት) ሲያመለክት በንግግሩ የጠፈር መነዋወጥ ቋንቋን መጠቀሙ ሊሆን ያለውን ጥፋት ምንነት እና ትርጉሙን ያጎላዋል እንጂ አያደበዝዘውም። በእርግጥም የጴጥሮስ አፖካሊፕቲክስ ንግግሩ በኢየሩሳሌም ላይ ቀርቦ ያለውንና ፈጥኖ የሚመጣውን የፍርድ ትንቢት ይጠቁማል። ያኔም እርሱ ይህንን እየጻፈ ሳለ በኢየሩሳሌምና በህዝቡ ላይ ያ የሚያስፈራው የጌታ ቀን፣ እርሱም የመጨረሻው የፍርድ ቀን ፈጥኖ ሊገለጥ ከአድማሱ ላይ ቀርቦ ነበር፤ ስለዚህም:- “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2ጴጥሮስ 3፥ 10-13) ይላል። የጴጥሮስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ70 ዓ.ም. በሆነው በኢየሩሳሌም ጥፋት ነው። ጴጥሮስም ያንን በ70 ዓ.ም የሆነውን መለኮታዊ ፍርድ ለመግለፅ የተጠቀመበት የኮስሚክ ነውጥን የሚያንጸባርቅ ቋንቋ፣ ኃጢአት እና ሰይጣን በእግዚአብሔር አገዛዝ ላይ ያላቸውን የጠላትነት አቋቋም ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ እና ጽድቅን ለማንገስ የፍርድ ቀን በቅርቡ እንደሚመጣ ያሳየበት ነው።
በመጨረሻም ይህንን ጽሁፍ ሳጠቃልል፣ ምድር ትነዳለች ብለው ለሚያስቡ መጻኢያን አንዳንድ ቀላል ጥያቄዎችን ላንሳ፡- የሰው ልጆች መኖርያ ስለሆነችው፣ አንድ ቀን ቡን ብላ ስለምትቃጠል ፕላኔት ምድር ማሰብ እንደምን ተስፋና መጽናናት ሊሰጣችሁ ይችላል? ጌታ ኢየሱስን ለማወቅና ለማመን ገና ጊዜ ስላልነበራቸው፣ ስለሚጠፉት ሰዎችስ አይገዳችሁምን? ገናስ ለአለምና ለዘላለም ይኖሩባት ዘንድ በሚፈጠሩ ኃጢአተኛ የሰው ልጆች ትውልድ ደህንነትስ ደስ አይላችሁምን? ለትውልድ ስለሚታደል ደህንነትስ አይናችሁ ለምን ትሰስታለች? ይህስ የእናንተ አስተሳሰብ ምድርን ላለማጥፋት ቃል ከገባ (ዘፍጥረት 8፥ 21፤ 9፥ 11) የአምላክ ደስታና ታማኝነት ጋር እንዴት ይስማማል? እግዚአብሔር አምላክስ ቁጣውንና ፍትሑን ያረካ ዘንድ የውድ ልጁ የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አልበቃውም ነበርን?
ግዛቸው
በግብዓትነት የተጠቀምኳቸው መጻህፍት፦
-አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የ1962 እትም፣ የ1997 ትርጉም(አዲሱ ትርጉም)፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ ህያው ቃል፤
- የእንግሊዝኛ ትርጓሜዎች(NKJV; ESV;NLT)
-The NASB, Interlinear Greek-English New Testament
-TKB, The Kingdom Bible
-Theological Dictionary of the New Testament
- Hnegraaff, Hank; The Apocalypse Code
-Meek, Charles S; Christian Hope through Fulfilled Prophecy
Bruce. F. F; The International Bible Commentary
No comments:
Post a Comment