Sunday, January 28, 2024

የፕላኔቷ ዕጣ ፈንታ

የፕላኔት ጥፋት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውን?

በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ብርሃን

መግቢያ፦

በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎችና ማብራሪያዎች ላይ እንደሰፈረው፣ በ2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3 ላይ ስላለው አሳብ፣ ፕላኔቷ ራሷ፣ ማለትም “የሰማይ ፍጥረት” /the elements/ “ይቃጠላሉ” የሚል አንድምታ ያለው ትርጉም በብዙዎች ተሰጥቶት እናነባለን።  የዛሬ ዘመን የቃሉ አንባቢዎችም ይህንን ክፍል ሲረዱ በብዙዎች ዘንድ ያለው የተለመደ አመለካከት፣ በእርግጥ ምንባቡ ስለ ሰው ልጆች የታሪክ ፍጻሜ እና ስለ አጥናፈ አለሙ /universe/ ዕጣ ፈንታ እየተናገረ ነው የሚል ግንዛቤን ይዘዋል። ዳሩ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በወጉ የምናጠና ከሆነ ይህ ምንባብ ቃል በቃል /literally/ ስለ ግዑዙ ፍጥረተ አለም መቃጠል ወይም ስለ ኮስሞስ ጥፋት የሚናገር ቃል አለመሆኑን፤ ይልቁን ግን እግዚአብሔር በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ፍርዱን ባደረገ ጊዜ ያኔ በ70 ዓ.ም ሊመጣ ስላለው ክስተት የተነገረ ቃል መሆኑን እናስተውላለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ በተነበየውና፣ በ70 ዓ.ም ላይ ሮማዊያን ሲመጡ በህዝቡና በከተማይቱ ላይ በሆነው የእልቂት ጥፋት፣ ያኔ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዶች እንደተጨፈጨፉ፣ ቤተ መቅደሱም እንደፈረሰ እና ከእርሱም ጋር የአሮጌው ኪዳን ሥርዓት ለመጨረሻ ጊዜ እስከወዲያኛው እንደተወገደ ከቅዱሳት መጻህፍት (ማቴ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ) እና ከታሪካዊ መዛግብት በግልጽ እናነባለን።

እንግዲህ የዚህ አይነተኛ ምዕራፍ ወሳኙና አከራካሪው ጥቅስም ምዕራፍ 3፥ 10 ላይ ያለው ነው፣ ቃሉም በአማርኛችን፦ “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” የሚለው ነው። 

ከመነሻዬ የቃሉን ባለቤት የማመሰግነው ይህ ይሆናል የተባለው “ኮስሚክ ውድመት” ድንገት ከሚመጣው የጌታ ቀን ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም መላው አዲስ ኪዳ ይመጣል ሲል የሚናገርለት አንዱ የጌታ ቀን ያ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት እና ከመሆን የማይቀር ምጽአት በመሆኑ ነው። የዚህ ጥቅስ ትርጉም ውሃ ልኩም የሚያርፈው መጽሐፍ ቅዱስ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት በመጀመሪያው ክፍለዘመን ላይ የሚፈጸም ተስፋ አድርጎ ባቀረበበት አጠቃላይ አውድ ላይ ነው። ስለዚህ ይህንን ጥቅስ ለመተርጎም ከዚህ በኋላ ለማነሳላችሁ ነጥቦች ሁሉ ይህ ኣሳብ ምን ያህል የጀርባ አጥንት እንደሆነልኝ በውነት አልሸሽግም።

የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ይህንን ጥቅስ እንዴት እንደሚያስቀምጡት አንዳንድ ማሳያዎችን ላቅርብ፣ 

አዲሱ ትርጉም፦ “የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ የጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል።”

አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል” ይላል።

ህያው ቃል፦ “ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ እንደማይትወቅ ሁሉ የጌታም ዳግም ምፅአት እንደዚያው ሳይታሰብ በድንገት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰማያት በታላቅ ድምፅ ተነዋውጠው ያልፋሉ። የሰማይ አካላት እንደ ሰም ይቀልጣሉ። ምድርና በላይዋ ያለ ነገር ሁሉ በእሳት የጋያል።”

በአንዳንድ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ደግሞ። 

But the day of the Lord will come as a thief in the night, in which the heavens will pass away with a great noise, and the elements [stoicheion] will melt with fervent heat; both the earth and the works that are in it will be burned up [katakaio].  (2 Peter 3:10, New King James Version)

But the day of the Lord will come like a thief, and then the heavens will pass away with a roar, and the heavenly bodies [stoicheion] will be burned up and dissolved, and the earth and the works that are done on it will be exposed [katakaio].  (2 Peter 3:10, English Standard Version)

But the day of the Lord will come as unexpectedly as a thief. Then the heavens will pass away with a terrible noise, and the very elements [stoicheion] themselves will disappear in fire, and the earth and everything on it will be found to deserve judgment [katakaio].  (2 Peter 3:10, New Living Translation)

ቀጥሎ በማነሳቸው ነጥቦች ቅዱሳት መጻሕፍትን በራሳቸው በቅዱሳት መጻሕፍት በመተርጎም ይህንን ጥቅስ እየመረመርን የነገሩን ውል በአውደ ምንባቡ ውስጥ እንፈልጋለን። ምናልባት የህንን የምታነቡ፥ ምድር ተቃጥላ ትጠፋለች፣ የሰው ልጆች ታሪክም በዕልቂት የዘጋል፣ ወዘተ… የሚል ትምህርት መጽናናት የሚሰጣችሁ ክርስቲያኖች ካላችሁ ከዚህ ቀጥሎ የማነሳቸው 12 ነጥቦች ሊያስቆጣችሁ ስለሚችል ጽሁፉን ታግሳችሁ እንደታነቡ እጠይቃለሁ።  

፩ኛ/ በምዕራፍ 3፥ 10 ላይ ይህ “ይቃጠላሉ” የተባለው “የሰማይም ፍጥረት” ለሚለው ሃረግ የግሪኩ አቻ ቃል “ስቶይቺዮን” ነው።  ይህ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለበት በሁሉም ስፍራ የሚያመለክተው ስለ ብሉይ ኪዳን “አካላት” ወይም የአይሁድን አካላትት /Jewish elements/ ነው እንጂ ስለ ተዳሳሹ አጥናፍ አለም ጉዳዮች አይደለም። ይህ  ስቶይቺዮን የተሰኘ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴትና በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚያሳዩንን እነዚህን ምንባባት በጥንቃቄ ተመልከቱ፡ 

ገላትያ 4፥ 3፣ 9፤ “እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤…  አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?”

እዚህ ላይ ቃሉ የሚያመለክተው ክርስትና ካስገኘላቸው ነጻነት በፊት በባርነት ይገዙበት የነበረውን ኃሰተኛ ትምህርት እና በእርሱ የሚዘወረውን የባርነት ኑሮ ነው። የገላትያ ሰዎች ዳግመኛ እየተወሰዱበት የነበረው ኃሰተኛ ሐይማኖት ደግሞ ይሁዲነት ነበር።

ቆላስይስ 2፥ 8-9፣ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤”

ቆላ 2፥ 20-22፤ “ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት (stoicheia tou Kosmou) ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና”

በዚህም አሮጌውን ኪዳን የመሰሉ የተለያዩ ኃሰተኛ ኃይማኖቶች ከባርነት በታች ገዝቶ ለማቆየት የሚያሳድሩትን ክፉ ተጽዕኖ ነው የሚያሳየው። 

ዕብራውያን 5፥ 12-13 “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት (stoicheia) እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።  ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤”

እዚህም ያለው ትርጉም በዐውደ ምንባቡ ውስጥ አነስተኛ ዋጋ ስላላቸውና  “የሕፃንነትን ትምህርት” በመባል ስለሚታወቁት ወይም በቁጥር 11 ላይ ጆሮቻቸውን ያፈዘዘ የህጉ ትምህርት ግልጽ ወይም የመጀመሪያ መርሆዎች በተመለከተ የተነገረ ነው።

እንግዲህ ይህ የግሪኩ “ስቶይቺዮን” የሚለው ቃል በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ያለው አጠቃቀም የቀደመውን አሮጌ ወይም አለማዊ የትምህርትና የባርነት አኗኗር በሚያመለክትበት ዘይቤ ቀርቦ ሳለ፣ 2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 3፥ 10 ያለውን ግን ከዚህ የቃሉ ጠቀሜታ ነጥሎ፣ የለም ግዑዙን ፍጥረተ ዓለም ነው የሚያመለክተው ብሎ ለመተርጎም መሞከር ወደ ፍጹም ስህተት ያመራል። 

፪ኛ/ በሌላ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ በትምህርቱ ቀዋሚነት፣ ያለተፋልሶ ምድር ወይም ይህ ግዑዝ ዓለም ፍጻሜ የሌለው እንደሆነ አድርጎ ያስተምራል (ለምሳሌ መክብብ 1፥ 4፤ መዝሙር 78፥ 69፤ 104፥ 5፤ 148፥ 3-6፤ ኤፌሶን 3፥ 21ተመልከቱ)፤ እእግዚአብሔር አምላክም ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ እንደማያጠፋ ቃል ገብቷል፣ (ዘፍጥረት 8፥  21፤ 9፥ 11)።

ይህንን ሃሳብ በተመለከተ ቀደም ሲል በብሎገሬ ላይ “ይህ አለም ፍጻሜ አለውን?” በሚል ርእስ በዝርዝር ያካፈልኩትን ጽሁፍ እንድታዩት ሊንኩን ላጋራችሁ፦

https://gizachewkr.blogspot.com/2016/11/blog-post.html?m=1

፫ኛ/ በጴጥሮስ መልዕክቶች እና ንግግሮች አውድ ካየነው ጴጥሮስ እየደጋገመ የሚያነሳው የመጨረሻው ዘመን ፍጻሜ፣ ያኔ ለእርሱና ለተደራስያኑ እጅግ የቀረበ ነበር። በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥ 7 እንደተነገረው “የነገር ሁሉ” ፍጻሜ ጴጥሮስ የመጀመሪያ መልዕክቱን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ያኔ “ቀረቦ” ነበር።  በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥ 17 ላይ እንደተነገረው ደግሞ “ፍርድ የሚጀምርበት ጊዜ” ያኔ ደርሶ ነበር።  በሐዋርያት ሥራ 2፥ 14-20 እና 1 ጴጥሮስ 1፥ 20 መሠረትም ጴጥሮስ ራሱ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ይኖር እንደነበር ያውቅና ያምን ነበር። 

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ መጨረሻው ቀን/ስለ ፍጻሜ ዘመን 19 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፣ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች ያለ ልዩነት ቃላቸው አንድ ሆኖ በአንድ ድምፅ ሲናገሩ - እነሱ ራሳቸው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ ይመሰክራሉ፣ ይህም እነርሱ የኖሩበት የመጨረሻ ዘመን ማለት የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ማለት ነው እንጂ የዚህ ተዳሳሽ ዓለም (የኮስሞስ) መጨረሻ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስም ያለ ልዩነት የሚያውቀው አንዱን የመጨረሻ ዘመን ብቻ ነው።

፬ኛ/ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት የተነገረው ይህ “የጌታ ቀን” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 10) ርዕሰ ጉዳይ እግዚአብሔር አምላክ በተለያዩ ህዝቦች ላይ በተከታታይ ስለሚያመጣው ፍርድ የሚናገር ነው እንጂ፣ ፈጽሞ ስለ ግዑዝ ፕላኔትና ስለ ተዳሳሽ ዓለም ጥፋት የሚናገር አይደለም። 

ለምሳሌ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ምንባባት ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፦ 

¶ በኢሳይያስ 34 ላይ ኤዶምያስን በተመለከተ ስለተነገረው የፍርድ ቀን ሲናገር በቁጥር 4 ላይ “የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።” ሲል ስለ ቀኑ ይናገራል፤  

¶ በኤርምያስ 46፥ 10 ላይ በስም በተጠቀሱ የተለያዩ ህዝቦች ላይ ስለሚመጣ ፍርድ ሲናገር “ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፤…” ሲል ይናገራል፤ 

¶ በሰቆቃወ ኤርምያስ 2፥ 22 በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣው የፍርድ ቀን ሲናገር “እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው” ያላል፤  

¶ በሕዝቅኤል 13፥ 5 ላይም የእስራኤልን ሐሰተኛ ነቢያት ሲከስሳቸው ”በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም” ሲል በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን እስራኤልን እንዳላዳንዋት ይመሰክርባቸዋል። 

¶ በሕዝቅኤል 30፥ 2-4 ላይም በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ስለሚሆን የፍርድ ቀን ሲናገር “የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል። ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል” ሲል ይናገራል፤ 

¶ በትንቢተ አሞጽ 5፥ 18-20 ባለውም ክፍልም የእግዚአብሔር ቀን በእስራኤል ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ ሲናገር “የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም። ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው። የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” ሲል ይናገራል፤  

¶ በአብድዩ ቁጥር 15 ላይም የእግዚአብሔር ቀንን አስመልክቶ “የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል” ሲል ኤዶምያስን ያስጠነቅቃል፤  

¶ በሶፎንያስ 1፥ 2-18 ባለውም ክፍል በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚደርሰው የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ይናገራል።  

እንግዲህ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ እንደሚመጣ የተነገረው የእግዚአብሔር ቀን ፍርድ አንዳንዶቹ በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል በጠላቶችዋ እጅ በወደቀችበት ወቅት የተፈጸሙ ሲህን፣ እንደ ሚልክያስ 3፥ 2-5፤  4፥ 1-5 ባሉ ክፍሎች “የሚነድ/ የሚቃጠል” የእግዚአብሔር ቀን ተብሎ የተገለጠው ደግሞ ከ70 ዓ.ም የኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር የተያያዘው ፍርድ ነው፤ ይህም የቁጣ ቀን በማቴዎስ 3፥ 7-12፣ ባለው ክፍል ላይ በሰፈረው የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት፦ “ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና፦ ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” በሚል የተረጋገጠው ነው።  

በተመሳሳይ ማቴዎስ 13፥ 49-50;  21፥ 33-45;  22፥ 7;  ወዘተ ያለውም ስለዚሁ ፍርድ የሚናገር ነው። መጥምቁ ዮሐንስ በሚልክያስ 3፥ 1፤ 4፥ 5 የተነገረውን  የኤልያስን ዳግመኛ መምጣት በመንፈስ እንደፈፀመ አስተውሉ፤ (ማቴዎስ 11፥ 14፣ 17፥ 11-13)።  አዲስ ኪዳን በግልጽ የሚናገርለት ታላቁ ፍርድም ግልጽ ትኩረት የሰጠው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በነበሩ አይሁድ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት ነው (ማቴዎስ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ.) እንጂ—በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ስለሚደርስ ‘የፕላኔት አለም ጥፋት’ አይደለም።

፭ኛ/ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ያኔ በዘመናቸው የጌታ ቀን አስቀድሞ መጥቷል ብለው ማሰባቸው በእውነት የሚደንቅና ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው፤ “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን” ይላልና (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 1-2)!  ስለዚህ፣ እነርሱ ስለ ጌታ ቀን ሲያስቡ አሁን በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች ካላቸው የተለየ ግንዛቤ እንደነበራቸ አስተውሉ። አያችሁ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የጌታ ቀን የፕላኔት ምድርና ሰማይ መቃጠልን ሳያካትት፣ ሳያውቁት ሊያልፋቸው እንደሚችል እንኳ ያስቡ ነበር ።

፮ኛ/ ስለተፈጥሮ ሥርዓት የኮስሚክ ነውጥን የሚያመለክት የንግግር ዘይቤ መደበኛ በሆነው የዕብራይስጥ አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ የተለመደ ነው፤ ቃል በቃል ባልሆኑ አገላለጾች ስለ ሥነ-መለኮታዊ ወይም ቃል ኪዳናዊ ክንውኖች፣ እንዲሁም በተለይ እግዚአብሔር በደለኛ በሆኑና ቁጣው በሚገባቸው ህዝቦች ላይ ስለሚያመጣው ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ እንዲህ ያለ ትዕምርታዊና አምሳላዊ የቋንቋ ዘይቤ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል እናያለን።  ጊዜ ወስዶ ቀጥሎ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች በመመልከት ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል:- 

¶ 2ሳሙኤል 22፥ 8-16፣ እግዚአብሔር በዳዊት ጠላቶች ላይ ያመጣውን ፍርድ በተመለከተ፤  

¶ ኢሳይያስ 13፥ 10-13፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ኢሳይያስ 34፥ 4፣ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ በተመለከተ፤

¶ ኤርምያስ 4፥ 1-31፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ሕዝቅኤል 32፥ 7-8፣ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፅ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ሚክያስ 1፥ 2-16፣ እግዚአብሔር በእስራኤልና በይሁዳ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ 

¶ ናሆም 1፥ 2-8፣ እግዚአብሔር በነነዌ ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ፤ እንዲሁም 

¶ ሶፎንያስ 1፥ 2-18፣ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በይሁዳ ጠላቶች ላይ የተናገረውን ፍርድ በተመለከተ 

ከፍ ሲል በተጠቀሱ ምንባባት በኮስሚክ ነውጥ የተወከለው ገለጻ፣ ንግግሩ የተፈጥሮ ሥርዓት ነውጥን ሳይሆን በኃጢአት ምክንያት በህዝቦችና በነገስታት ላይ የሚደርሰውን መለኮታዊ ቁጣ የሚያመለክቱ መሆናቸውን አስተውሉ።

፯ኛ/ የሐዋርያው ጴጥሮስ “ሰማይና ምድር” የሚል አነጋገሩን ልብ አድርጉ፦  “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 13) ሲል ያነሳውን ተስፋ በቀጥታ የወሰደው በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካለው የቃሉ አጠቃቀም ነው።  ስለ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ከሚናገሩት መሠረታዊ የንባብ ክፍሎች መካከል ኢሳይያስ 65-66 እና ራዕይ 21 ላይ የሚገኙት ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ እግዚአብሔር በጠላቶቹ ላይ ስለሚያደርገው ፍርድ በግልጽ እናያለን፤ ነገር ግን በክፍሉ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው ፍርዱ ከተፈጸመም በኋላ የተለመደው የሰው ልጅ ታሪክ ይቀጥላል እንጂ አይቋረጥም ። ይህም ማለት ኃጢአትና ሞት በተቀረው ፍጥረታዊ ዓለም ውስጥ መኖሩ ይቀጥላል ማለት ነው (ኢሳይያስ 65፥   20፤ ራእይ 22፥ 15)፤ አንዳንድ ሰዎችም ስለ እግዚአብሔር ገና ያልሰሙ በመሆናቸው የወንጌል ስብከት አገልግሎት አስቀድሞ በተፈጸመው ፍርድ ከመታወጅ ሳይቋረጥ ኃጢአተኞችን ውደ ጽድቅ በእምነትና በንስሃ የመጋበዙ ሥራ ይቀጥላል ማለት ነው (ኢሳይያስ 66፥ 19-24)።  ስለዚህ በአጠቃላይ አውዱ መሰረት አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድር ማለት ጨርሶ ቀድሞ ያልነበረ ሌላ ተዳሳሽ ግዑዝ ዓለም ይፈጠራል ማለት አይደለም፤ የአሮጌው ሰማይና ምድር ተጠቅልሎ ማለፍም ፍጥረታዊው የሰው ልጆች ዓለም  ታሪክ መጨረሻው ይሆናል ማለት ፈጽሞ አይደለም። በተጨማሪም በማቴዎስ 5፥ 17-18 ላይ ኢየሱስ አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርን ከጸጋ ዘመን መጀመር እና ከአሮጌው ኪዳን የህግ ዘመን ማብቂያ ጋር በማገናኘት መናገሩን ልብ ይሏል፤ እርሱም ያለፈውን አሮጌ ዘመን ፍጻሜ የሚያመለክት ሲሆን- ይህም የሰማይና የምድር ህልፈት በዕብራውያን 8፥ 13 “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል” በሚል የተነገረውንና በ70 ዓ.ም.  የሆነውን የአሮጌውን ኪዳን ፍጻሜ የሚያሳይ ነው። ጴጥሮስም በዚሁ የቃሉ መንፈስ ከፊቱ ያለውን 70 ዓ.ም እያየ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል” (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 7) ሲል ይመሰክራል። 

ስለዚህ ተስፋ የተገባው አዲሱ ሰማይ እና አዲሱ ምድር በውበቱ የሚያብረቀርቅና የሚያንጸባርቅ፣ መጻኢያንም እንደሚመስላቸው ይህኛው አለም ከጠፋ በኋላ ገና የሚፈጠር አዲስ ፕላኔት ማለት ሳይሆን፣ ይልቁንም ኃጢአትና ሞት የነገሰበት የአሮጌው ኪዳን አገዛዝ፣ እርሱም ይሁዲነት በእሳት ፍርድ ተወግዶ፣ ጽድቅ የሚገዛበት የአዲሱ ቃል ኪዳን መንግስት፣ እርሱም ክርስትናችን በህይወት የሚነግስበት ነው።

፰ኛ/ “ይቃጠላል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል “ካታካዮ” የሚለው ነው፤ በተለያዩ ትርጉሞች ውስጥ “የተጋለጠ፣” “ፍርድ የተገባው ሆኖ ተገኝቷል” ወይም “የተራቆተ” ተብሎ ተተርጉሟል።  እንደሚታወቀው ‘እሳት’ የፍርድ ምልክት ነው፣ ይኸውም ከፍ ሲል ካለው የንባቡ ክፍል የተሳበ ነው።  ይህም በ70 ዓ.ም በአሮጌው ኪዳን ላይ ለሆነው ጥፋት ተስማሚ ቋንቋ ነው።

፱ኛ/ በመልእክቱ ውስጥ “ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤” (2ጴጥሮስ 3፥ 6) በሚል የተገለጠው በኖህ ዘመን የሆነው ጥፋት ከዚህ በሰማይና ምድር መቃጠል ከተወከለ አነጋገር ጋር በንጽጽር ቀርቧል። በህጉ እንደተጻፈው ያኔ በኖህ የጥፋት ውሃ ዘመን ኃጢአተኞች ብቻ በጥፋት ውሃ ጠፍተዋል። “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥” (2ጴጥሮስ 2፥ 5) እንደተባለ፣ ኖህ እና ቤተሰቡ ግን ከዚህ ጥፋት በውሃ የዳኑበት ሁኔታ ነው ያለው።  ይህም በ70 ዓ.ም ከተፈጸመው ጥፋት ጋር ተመሳሳይ ነው። እግዚአብሔር በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ስለ ኃጢአታቸው እና ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የበቀል እርምጃ እንደወሰደባቸው (ማቴ 23፥ 29-24፥ 2፣ ወዘተ) ግልጽ ነውና።  ይህም የበቀል እርምጃ በቅዱሳት መጻህፍት ሁሉ ለዳግመኛ ምጽአቱ ከተቀጠረውና ከተነገረው ጊዜ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን፤ ይህ ጥፋትና በቀል በተፈጸመበት ታሪካዊው የ70ው አ.ም የኢየሩሳሌም ውድመት ጊዜ ግን ይህ ግዑዙ ፕላኔት ዓለም ምንም የሆነው ነገር አልነበረም።  ይልቁንም እግዚአብሔር በኖኅ የጥፋት ውኃ ዘመን ባደረገው ኪዳን መሰረት ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፈጽሞ እንደማያጠፋ ቃል መግባቱን እናውቃለን (ዘፍጥረት 8፥ 21)። 

፲ኛ/ “አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት” የሚለው አነጋገር (2ጴጥሮስ 3፥ 8) ብዙ ጊዜ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጊዜ ጠቋሚ ሆነው የተነገሩ አገላለጾችን፣ ማለትም “ይህ ትውልድ”፣ “እዚህ ከቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ”፣ “ቶሎ”፣ “ቅርብ”፣ “ሊሆን ያለ” ወዘተ ያሉትንና የመሳሰሉትን በርካታ የሆኑ መግለጫዎች ውድቅ ለማድረግ መጻኢያን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ነገር ግን "አንድ ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት" የሚለው፣ ቃል በቃል በጥሬው ሊወሰድና ሊተረጎም  ከቶ አይችልም፣ እንደዚያ የሚወሰድና የሚተረጎም ከሆነ ግን በአውደ ምንባብ ውስጥ ያለው አጠቃላይ የመጨረሻው ዘመን አሳብና ትምህርት ምንም እርባና ወይም ትርጉም የሌለው ይሆናል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር አጭር ጊዜ ማለት ረጅም ጊዜ ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ፣ ጌታ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ የቆየው ለ3,000 ዓመታት ነበርን? የሚል፣ ወይም እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ሰርቶ የጨረሰው በ6000 ዓመታት ነውን? ከሥራው ያረፈውስ በ7ኛው ሺህ ዓመት ነውን? የሚል እርባና የሌለው ጥያቄ ያስነሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን “አንድ ሺህ” የተሰኘው ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ የምልዓት ምሳሌያዊ ቃል ሆኖ ማገልገሉን አትዘንጉ።

በዚህ ሃሳብ ላይ “ጴጥሮስን በጴጥሮስ” በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ያካፈልኩትን አጭር ጽሁፍ እንድታነቡት ጋበዝኳችሁ፦

https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid0gnU6ufdWSxfXTMAs6WmR9AnZ8MVm8q7KYcFZmApgwyZEAtGeKs4iNx7W8kdEvfH3l&id=100002668627386&mibextid=Nif5oz

፲፩ኛ/ ጴጥይሮስ በመልዕክቱ 3ኛ ምዕራፍ ከቁጥር 11-13 ባለው ንግግሩ ለአንባቢዎቹ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እንዲጠብቁ እና እንዲያስቸኩሉ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ሲል ይመክራቸዋል። በዚህ ምክሩ ውስጥም ይፈጸማሉ የተባሉ ድርጊቶች የሚከናወኑበትን ጊዜ አስመልክቶ “አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን” ያህል ስለመሆኑ የተነገረውን፣ የመልዕክቱን ሃሳብ ማግኘት ካለብን ምናልባት ጉዳዩ በርካታ ክርስቲያኖች በጥሬው ከሚያስቡት በተለየ ተቃራኒውን ነገር ማለት እንደሆነ ልናስብበት ይገባል። ጴጥሮስ በዚህ ንግግሩ ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁት ጉዳዮች - በተለይ ጊዜውን አስመልክቶ በሌሎች ምንባባት ውስጥ ከተሰጡትና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይፈጸማሉ ከተባሉት መግለጫዎች አንጻር ለፍጻሜአቸው ወደ ፊት የቀራቸው አጭር ጊዜ ብቻ ነው እንጂ - ብዙም አይደለም ማለቱ ነበር (ሐዋርያት ሥራ 2፥ 14-20፤ 1 ጴጥሮስ 1፥ 20፤ 4፥ 7፤ 17)።

፲፪ኛ/ አንዴ እዚህ ጋር ቆም ብላችሁ እስቲ አስቡት!  እዚህ በ2ጴጥሮስ 3፥ 3 የተነገረው “የመምጣቱ ተስፋ!” በእርግጥ ስለ ኢየሱስ ዳግመኛ መምጣት ነውን?  ልብ አድርጉ አዲስ ኩዳን ያለ ልዩነት በየመጻህፍቱ ሁሉ በቀጥታም በተዘዋዋሪ የሚናገርለት ይህ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት ርዕሰ ጉዳይ ምንም ቢሆን ጊዜው የተነገረና የተገለጠ ነው። ይህም ጊዜ የሐዋርያቱ ዘመን፣ ያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን መሆኑ አያጠራጥርም። ያኔ ደግሞ ዛሬ መጻኢያን የሚያስቡት አይነት ጥፋት ግዑዝዋ ፕላኔት ምድር ላይ የደረሰ ነገር የለም። በርካታ መጻኢያን ግን ዛሬም ድረስ ግዑዙ አለም ቡን ብሎ ስላልጠፋ፣ ወይም ሲጠፋ ስላላዩ እርግጠኛ ሆነው፣ ጌታ በ70 ዓ.ም አልተመለሰም! ሲሉ ይደመጣሉ፤ እኛ ግን የለም “ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድ ተመልሷል” በሚል እርግጠኝነት ቆመናል። ይህን ያህል እርግጠኛ ለመሆን የሚያስፈልገው የጌታን ቃል ማመን ብቻ እንጂ ይህ አለም ሲቃጠል ማየት አይደለም። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ለማብራራት የሚሄዱቡት የተለያዩ መንገዶች አሏቸው።  አንዳንዶቹ ይህ ጥቅስ ስለ “ዳግመኛ ምጽአት” አይደለም ሲሉ በድፍረት ይክዳሉ።  ሌሎች ደግሞ ይህንን ጥቅስ ከዐውደ-ምንባቡ ይነጥሉና የቀረውን የምዕራፉን ክፍል ብቻ ባለፈው ታሪክ ውስጥ እንደተፈጸመ በማሰብ የዚህን “የፍጥረተ አለም ፍጻሜ” ግን ገና ወደፊት ላለ መጻኢ ዘመን ሊለጥጡትና ሊያሻግሩት ይፈልጋሉ። ይህንንም ባደረጉ መጠን ቃሉ የተነገራቸውን በኩረ ተደራስያን አግልለው የሌለና ያልተባለ ነገር ለማመንና ለመጠባበቅ ይገደዳሉ።  ሌሎቻችን ደግሞ በዚህ ክፍል የተነገረው የኢየሱስ “መምጣት” በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው ተደጋጋሚ የእግዚአብሔር “መምጣት” ጋር የሚመሳሰል “ለፍርድ መምጣት” እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተን እንናገራለን። ያም ሆነ ይህ፣ ጴጥሮስ በቅርቡ ይሆናል ሲል በሚያነሳው ማሳሰቢያ “ለዘባቾች” ከሰጠው ማስጠንቀቂያ በግልጽ የሚታይ አንድ ነገር አለ። በዚያን ዘመን ከ70 አ.ም በፊት የነበሩ አንዳንድ ዘባቾች (2ጴጥሮስ 3፥ 3) ኢየሱስ በትውልዳቸው መጥቶ ቤተ መቅደሱን እንደሚያፈርስ በገባው ቃል መሰረት (ማቴዎስ 24፥ 1-3፤ 29-34)፣ ቃሉን አክብሮ አልመጣም ሲሉ ክርስቲያኖች በነበራቸው ተስፋ ላይ ያፌዙና ይሳለቁ ነበር። ጴጥሮስ ግን “ጌታ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም” (2ጴጥሮስ 3፥ 9) በማለት ይመልሳል።  ጴጥሮስ እነዚያ በክርስቲያኖች ተስፋ ላይ ይሳለቁ የነበሩትን ሰዎች እያስጠነቀቀ፣ ጌታ ኢየሱስ አንዳንዶቹ በሕይወት እያሉ በእስራኤል ላይ ለመፈጸም የገባውን የፍርድ ቃል ቸል ብሏል ብለው በማመን ስህተት እንዳይሠሩ በጥብቅ እየነገራቸው ነበር (ማቴዎስ 10፥ 15-23፤ 16፥ 27-28፤ 26፥ 64፤ ራእይ 1፥ 1-3፤ ወዘተ.) ባለቤቱ ተኝቶ ሳለ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣበት” በነዚያ ፌዘኞች ላይ ሳያስቡትና ሳይዘጋጁ “የጌታ ቀን” እንደሚመጣባቸው በማሳየት በማያሻማ መንገድ ፌዘኞችን አስጠንቅቋል። ሌሎችም የአዲስ ኪዳን ማስጠንቀቂያዎች፣ ለምሳሌ ማቴዎስ 24፥ 34-43፣ 1ተሰሎንቄ 5፥ 2-4፤ ራእይ 16፥ 15፤ 22፥ 6-20 በዚሁ መንፈስ የቀረቡ ነበር።  በክፍሉ ውስጥ የተጠቆመው የመዘግየት ሃሳብ ወይም “ዝግታ” ግን በዚያ የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ለነበሩ ሰዎች “ሁሉ ወደ ንስሃ” ይመጡ እና ከጥፋት ይድኑ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን ትዕግስት ማሳያ ብቻ ነው።

ማጠቃለያ፦

የብሉይ ኪዳን ነቢያት በትውልዳቸው ውስጥ በነበሩ ህዝቦችና ነገስታት ላይ ሊሆን ያለውን መልኮታዊ  ፍርድ ሲገልጹ፣ የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያንም እነርሱ የነበሩበትን  የመጨረሻውን ዘመን የፍርድ እውነታዎች ሲያመለክቱ ሁሉም በአንድ አይነት የአነጋገር ዘይቤ የኮስሞቲክ ነውጥ አዘል ቋንቋዎችን ይጠቀማሉ። ጴጥሮስም ወደፊት የሚመጣውን ጥፋት (እርሱም የኢየሩሳሌምን ጥፋት) ሲያመለክት በንግግሩ የጠፈር መነዋወጥ ቋንቋን መጠቀሙ ሊሆን ያለውን ጥፋት ምንነት እና ትርጉሙን ያጎላዋል እንጂ አያደበዝዘውም።  በእርግጥም የጴጥሮስ አፖካሊፕቲክስ ንግግሩ በኢየሩሳሌም ላይ ቀርቦ ያለውንና ፈጥኖ የሚመጣውን የፍርድ ትንቢት ይጠቁማል። ያኔም እርሱ ይህንን እየጻፈ ሳለ በኢየሩሳሌምና በህዝቡ ላይ ያ የሚያስፈራው የጌታ ቀን፣ እርሱም የመጨረሻው የፍርድ ቀን ፈጥኖ ሊገለጥ ከአድማሱ ላይ ቀርቦ ነበር፤ ስለዚህም:- “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”  (2ጴጥሮስ 3፥ 10-13) ይላል። የጴጥሮስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ70 ዓ.ም. በሆነው በኢየሩሳሌም ጥፋት ነው። ጴጥሮስም ያንን በ70 ዓ.ም የሆነውን መለኮታዊ ፍርድ ለመግለፅ የተጠቀመበት የኮስሚክ ነውጥን የሚያንጸባርቅ ቋንቋ፣ ኃጢአት እና ሰይጣን በእግዚአብሔር አገዛዝ ላይ ያላቸውን የጠላትነት አቋቋም ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ እና ጽድቅን ለማንገስ የፍርድ ቀን በቅርቡ እንደሚመጣ ያሳየበት ነው።

በመጨረሻም ይህንን ጽሁፍ ሳጠቃልል፣ ምድር ትነዳለች ብለው ለሚያስቡ መጻኢያን አንዳንድ ቀላል ጥያቄዎችን ላንሳ፡- የሰው ልጆች መኖርያ ስለሆነችው፣ አንድ ቀን  ቡን ብላ ስለምትቃጠል ፕላኔት ምድር ማሰብ እንደምን ተስፋና መጽናናት ሊሰጣችሁ ይችላል?  ጌታ ኢየሱስን ለማወቅና ለማመን ገና ጊዜ ስላልነበራቸው፣ ስለሚጠፉት ሰዎችስ አይገዳችሁምን? ገናስ ለአለምና ለዘላለም ይኖሩባት ዘንድ በሚፈጠሩ ኃጢአተኛ የሰው ልጆች ትውልድ ደህንነትስ ደስ አይላችሁምን? ለትውልድ ስለሚታደል ደህንነትስ  አይናችሁ ለምን ትሰስታለች? ይህስ የእናንተ አስተሳሰብ ምድርን ላለማጥፋት ቃል ከገባ (ዘፍጥረት 8፥ 21፤ 9፥ 11) የአምላክ ደስታና ታማኝነት ጋር እንዴት ይስማማል? እግዚአብሔር አምላክስ ቁጣውንና ፍትሑን ያረካ ዘንድ የውድ ልጁ የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አልበቃውም ነበርን?

ግዛቸው

በግብዓትነት የተጠቀምኳቸው መጻህፍት፦

-አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የ1962 እትም፣ የ1997 ትርጉም(አዲሱ ትርጉም)፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ ህያው ቃል፤

- የእንግሊዝኛ ትርጓሜዎች(NKJV; ESV;NLT)

-The NASB, Interlinear Greek-English New Testament

-TKB, The Kingdom Bible

-Theological Dictionary of the New Testament

- Hnegraaff, Hank; The Apocalypse Code

-Meek, Charles S; Christian Hope through Fulfilled Prophecy

Bruce. F. F; The International Bible Commentary






Thursday, January 4, 2024

የዘዳግም 28 እርግማን እና ታሪካዊ ፍጻሜው

ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ሁሉ ይደቅቃሉ

መግቢያ:-

ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ሁሉ የሚያገኛቸው አስፈሪውን የዘዳግም 28 እርግማን እና ታሪካዊ ፍጻሜውን እናጠናለን።

በዘዳግም 28: 15 ላይ እግዚአብሄር እስራኤልን ሲያስጠነቅቅ “ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።” (ኦሪት ዘዳግም 28:15) ይላል::

በ70 ዓ.ም የሮማውያን ጦር ኢየሩሳሌምን ከበባት። ከዚያም በሮማውያን የጰኔሞስ ወር በአሥራ ሰባተኛው ቀን [ሐምሌ-ነሐሴ] በሙሴ ሕግ ከተወሰነው በተቃራኒው የዘወትሩ መሥዋዕት ተቋረጠ።  በጦርነቱም ወቅት በዘዳግም 28 ላይ ያሉት እርግማኖች በሙሉ ያለ ምንም ልዩነት በእስራኤል ላይ ደረሰባቸው። ያኔም ብዙ እስራኤላውያን በግዞት ወደ ግብፅ ተወስደዋል። በዘዳግም 28፥ 68 ላይ ባለውና “ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።” ተብሎ በተነገረው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በማዕድን ማውጫዎች ጉድጓድ ውስጥ እንዲሠሩ ባሪያዎች ሆነው ተወሰዱ። 

የኢየሩሳሌም ከተማና በዙሪያዋ ያለው መላው የእስራኤል ምድር አይሁዳውያን ወደዚያ ምድር ከመምጣታቸው አስቀድሞ የተቀደሰ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ብዙ ሊቃውንት ቅዱስ ንጉሥና ካህን የነበረው መልከ ጼዴቅ ይገዛት የነበረችው ሳሌም፣ በኋላም ኢየሩሳሌም ተብላ በምትጠራው ምድር ከጥንት ነገሥታት አንዱ እንደነበረ ያምናሉ። ዘዳግም 9፥ 5-6 የእስራኤል ቀደምት አህዛብ ነዋሪዎች በክፋታቸው ምክንያት ከምድሪቱ እንደተወገዱ ይናገራል። እስራኤልም ያችን ምድር በጦርነት ወርሶ በምድሪቱ በኖረበት ዘመን ሁሉ የእግዚአብሔር የተመረጠ ሕዝብ የመሆን ክብር ብዙ ዋጋ አስከፍሎታል። አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ካልተከተሉ፣ በፈንታው ለእርሱ ታማኝ ለሚሆለት ሕዝብ ሥፍራውን ለመስጠት ልክ በከነዓናውያን ላይ እንዳደረገው እንዲሁ እግዚአብሔር የገዛ ህዝቡንም ከምድሪቱ ላይ እንደሚነቅላቸውና እንደሚያጠፋቸው አስጠንቅቋቸዋል።

በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩት አይሁድ መሲሑንና ተከታዮቹን ለመግደል በብዙ ያሴሩ ነበር። ጌታ ኢየሱስም እነዚህን የግድያ ሴራዎች ይገነዘብ ስለነበር በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች “ክፉና አመንዝራ ትውልድ” (ማቴዎስ 12:፥ 39) ሲል ጠርቷቸዋል። እነዚህ ቃላት በጆሴፈስ የአይሁድ ሮም ጦርነት ታሪክ ውስጥ:- “ኢየሩሳሌም እንደደረሰባት ያለ መከራ ሌላ ከተማ አልደረሰባትም ወይም እንደዚህ ትውልድ ያለ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ በየትኛውም ዘመን በክፋትና በሴራ የተሞላ ትውልድ አልተፈጠረም ነበር፤’’ በሚል ተስተጋብተዋል። እነዚያ ለኢየሱስ ሞት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ክርስቶስን ብቻ ገድለው አላቆሙም። ኢየሱስ ከተሰቀለም በኋላ እንኳ በሐዋርያት ሥራ 8፥ 1-3 መሠረት የኢየሩሳሌም ከተማ አይሁዶች ቅዱሳን ክርስቲያኖችን ማሳደዳቸውን ቀጥለዋል። ዩሴቢየስ ይህን ስደት ሲናገር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በመጀመሪያ እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጅና የዮሐንስ ወንድም የነበረውን ያዕቆብን አንገቱን በሴራ አስቆረጡ። እና በመጨረሻም ከአዳኛችን ዕርገት በኋላ በመጀመሪያ ለኤጲስቆጶስ መንበር በቅቶ እንደነበር ሲገለጽ የነበረው ያዕቆብም ሕይወቱን አጥቷል፣ የተቀሩቱ ሐዋርያትም በገዳዮች ሴራ የማያቋርጥ ስጋት ውስጥ ሆነው በስደት ከይሁዳ ተባረዋል።”

የእስራኤል ሕዝብ በአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅት ሕጉን ተላልፈዋል፣ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያለው እርግማን ሁሉም በእነርሱ ላይ ተፈጽሟል።

በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ በማሴር የፈጸሙአቸው እነዚህ ወንጀሎች ሳይቀጡ አልቀሩም። በ70 ዓ.ም የሮማውያን ጭፍራ ኢየሩሳሌምን ከበባት። ከዚያም በጰኔሞስ (ሐምሌ-ነሐሴ) በአሥራ ሰባተኛው ቀን፣ የዘወትሩን መሥዋዕት “ሊያቀርበው የሚችል ሰው በመጥፋቱ ምክንያት” ቆመ። በዘጸአት 12 ላይ፣ እግዚአብሔር የፋሲካን በግ ሳያርድ የቀረውን የእያንዳንዱን (ግብጻዊ) ቤተሰብ የበኩር ልጅ ገደሏል። ከዘመናት በኋላም እስራኤላውያን የዘወትሩን መሥዋዕት ማቅረብ ካቆሙ በኋላ ተመሳሳዩ ዕጣ ደረሰባቸው።  በዘፀአት 12 ላይ እንደተገለጹት ግብፃውያን ሁሉ፣ ከሮም ጋር በተደረገው ጦርነት ወቅትም ብዙዎቹ የኢየሩሳሌም ሰዎች በፋሲካው በግ ምትክ ተገድለዋል። ክርስቶስ የፋሲካውን በግ ሆኖ እንደታረደላቸው መቀበልና ማመን ያልፈለጉ አይሁድ መሲሃቸውን ገድለው ደሙን ባፈሰሱበት የፋሲካ በአል እግዚአብሔር የእነርሱ ደም እንደ ጎርፍ ይፈስስ ዘንድ በጨካኞች እጅ ተዋቸው፤ ያኔ እርሱን ሊገድሉ ሲያሴሩ፣ ጲላጦስ እንኳ “እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም ገርፌ ልልቀቀው” እያለ ሲለምናቸው፣ የለም፣  “ይህንን ስቀለው፣ ደሙም በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ሲሉ በእግዚአብሔር ፍርድ ደማቸው በምድር ላይ ይፈስስ ዘንድ ለዕልቂታቸው ፈርመው ነበር።

የኪዳኑ እርግማን:-

በዘዳግም 28፡15-68 ላይ እንደተገለጠው፣ እግዚአብሔር እስራኤልን በብዙ የእርግማን ማስጠንቀቂያ ተናግሯቸው ነበር። እነዚህ እርግማኖች ግን ባዶ ማስፈራሪያዎች አልነበሩም። አንድ ጊዜ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ በባቢሎን በተደረገ ግዞት፣ በኋላም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እስራኤል ከሮም ጋር ባደረጉት ጦርነት እግዚአብሔር በዚህ ቃል ኪዳን መሰረት የሚገባውን ፍርድ አድርጓል። በዘዳግም 28 ላይ የተዘረዘሩት እርግማኖች ሁሉ የግብፅ መቅሰፍት፣ ጨለማ፣ ድርቅ፣ ክሳት፣ ጭንቀት፣ ደዌ፣ እባጭ፣ ጥብሳት፣ የሚያቃጥል ሙቀት፣ እብደት፣ ግፍ፣ ተገድዶ መደፈር፣ ክህደት፣ ግራ መጋባት፣ በምርኮ መወሰድ፣ የሰውን  ሥጋ መብላት፣ ሕፃናትን መግደል፣ ጭንቀት፣ እረፍት ማጣት፣ የግብፅ ባርነት፣ ስደትና ሞት እስራኤላውያን ከሮም ጋር ባደረጉት ጦርነት የደረሰባቸው ነገር ሁሉ ነው። ይህም አልበቃ ብሎ በስደት በተሰደዱበት የአሕዛብ ምድር ለንቀትና ለመሳለቂያነት ብቻ ሳይሆን ለአህዛብ ጣኦታት እንደ መስዋእት እየታረዱ፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብረ በዓል ማድመቅያ ጭዳ ሆነው ይገደሉ ነበር።

በዘዳግም 28 እና በዘሌዋውያን 26 የተንነገሩ እርግማኖች በእጅጉ ተመሳሳይ ናቸው። በሁለቱም ምዕራፎች ውስጥ ያሉት እርግማኖች በሙሉ የተፈጸሙት በአይሁድ ጦርነት ወቅት ነው። ዘዳግም 28 እና ዘሌዋውያን 26 ምንም እንኳን አንዳንድ አስገራሚ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፣ ተመሳሳይ የሆኑ እርግማኖችን ይዘረዝራሉ። ዘሌዋውያን 26፥ 18፣ 21፣ 23-24 እና 27-28 በ4 የተመደቡ ሰባት እጥፍ እርግማንን ይዘረዝራሉ። እነዚህ 4 ምድብ ሰባት እጥፍ ቅጣቶች በራእይ 6 ላይ ያሉትን ሰባቱን ማኅተሞች፣ በራእይ 8-10 የተገለጠውን ሰባቱን መለከቶች፣ በራእይ 16 የታየውን ሰባቱን ጽዋዎች እንዲሁም ምናልባትም በራእይ 10፥ 3-4 የተነገረውን ሰባቱን ነጎድጓዶች ይመስላሉ። [አንባቢዎች እነዚህን ክፍሎች በጥንቃቄ እንዲያዩ ይመከራል]። ከዚህም ባለፈ ዘሌዋውያን 26፥ 31 እግዚአብሔር “የእስራኤላውያንን መቅደሶች” እንደሚያፈርስ ይተነብያል። በእርግጥም ይህ የእርግማን ማስጠንቀቂያ በመጀመሪያውና በኋላም በሁለተኛው ቤተመቅደሶች ውድመት ወቅት ተፈጽሟል። በኢየሩሳሌም የነበረው የመጀመሪያው ቤተ መቅደስ ባቢሎናውያን ይሁዳን በወረሩበት ወቅት ፈራርሷል። ሁለተኛውም ቤተ መቅደስ ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 24 ላይ ይፈርሳል ብሎ እንደተናገረው የፈረሰው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ሮማውያን እስራኤልን በወረሩበት ወቅት ነው። ዘሌዋውያን 26 ንግግሩን ሲያበቃ ለየት ይላል። በዘሌዋውያን 26፥ 42-45 እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ለማሰብ፣  እንደማይጥላቸው እና ወይም እንደማይጸየፋቸው።” ቃል ይገባል። እነዚህ ጥቅሶች በሮሜ 11፥ 25-31 በተነገረው የጳውሎስ ትንቢት መሰረት በእስራኤል ቅሬታ ተሃድሶ ፍጻሜውን አግኝቷል።

የእርግማኑ ተፈጥሮ:-

ዘዳግም 28፥ 15 ንግግሩን የሚጀምረው በማስጠንቀቂያ ነው፦

ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል።በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ።17  እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል። የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል። አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ። እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል። እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ቸነፈርን ያጣብቅብሃል። እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል። በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፥ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች። እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ትቢያና አፈር ያደርጋል፤ እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።”

አብዛኛዎቹ እነዚህ እርግማኖች የማይቀሩና የማይቀየሩ የጦርነት ከበባ ውጤቶች ናቸው።

የመጀመሪያዎቹን በርካታ እርግማኖች ካጤንናቸው በጦርነት ጊዜ ሰለሚከሰት ዘረፋ አይቀሬነት የሚጠቁሙ ናቸው። ከዚያም በቁ.22 ላይ፣ እስራኤል በበሽታ፣ በትኩሳት፣ በእባጭ ፣ በጥብሳት፥ በፈንገስ፣ በሻጋታ እና በማያባራ ቀጣይ የቸነፈር ሞት፣ በነፍስ ክሳት እንደሚቀጡ የናገራል። እንደነዚህ ያሉት ቀጣቶች በስፋት በጦርነት ከበባ ወቅት የሚከሰቱ ተደጋጋሚ ውጤቶች ናቸው። ከዚያም በቁጥር 52 ላይ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ባዕድ ሕዝብ እንደሚያመጣ መናገሩም ያን ያህል አያስገርምም። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እስራኤል በእግዚአብሔር ፍርድ ስር ስትወድቅ ለጥፋትዋ ያመጣባት ይህ ባዕድ ኃይል የሮምን ጭፍራ ነበር።

በአይሁድ ጦርነት ወቅት ሮማውያን በመላው የእስራኤል ግዛት ያሉ ከተሞችን በከበባው ወቅት ጥርቅም አድርገው ዘግተው ያዙ። በከበባው ወቅትም አንድ ጦር በቅጥሮች ተጠብቃ የተመልሸገች ከተማን ከቦ የጠላቱን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እንዴት መቀነስ እንደሚቻለውና በአነስተኛ ድካምና ዋጋ ሊሰብረው የሚያስችለው አይነት  የጦርነት ስትራቴጂን  ፈጥሯል። አላማውም ረዘም ላለ ጊዜ በማስፈራራት እና ከተማይቱን በማሸበር እጃቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነው። ልክ እንደ ማንኛውም የከበባ ኃይል፣ ሮማውያን ማንኛውንም ነገር ወይም ማንም ሰው ወደ ከተማይቱ እንዳይገባ ወይም ከከተማይቱ እንዳይወጣ በጥብቅ ከልክለው ነበር። ያኔም መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን በማጣት የተራቡ አረጋውያን ሽማግሌዎች እና አቅመ ደካሞች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን እየተጠቁ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በውሃ እጦት የሚሞቱ ቀዳሚዎች ይሆናሉ። ይባስ ብሎም በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ አይሁድ የሙታናቸውን በድን መቅበር የሚችሉበት ሰላምና ጸጥታ አልነበራቸውም።  ከዚህ የተነሳ በየጎዳናዎቹ ላይ የተከማቹ የበሰበሱ የሙታን በድኖች እነዚያኑ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በጭንቀት የተዳከሙ ሰዎችን ለከፋ በሽታ ያጋልጣሉ።

ቁ.22 ላይ የተጻፈውን እርግማን ፍጻሜ በሚሰጠው መልኩ በአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅትም ድርቅ ነበር።

በቁጥር 22 ድርቅንም እንደሚያመጣ ያስጠነቅቃል። ኢየሩሳሌም በተከበበች ጊዜ ጆሴፈስ ከቅጥሩ ፊት ለፊት ቆሞ የአገሩን የእስራኤልን ሰዎች በሰላም እጅ እንዲሰጡ ተማጽኗቸው ነበር። ጆሴፈስ በዚህ የተማጽኖ ንግግሩ ላይ ቲቶና ሮማውያን ለከበባ ከመምጣታቸው በፊት በምድሪቱ ላይ ያጋጠመውን ከባድ ድርቅና ረሃብ ለወገኖቹ አስታውሷቸዋል። በመቀጠልም በብዛት የሚፈስሱት እነዚሁ የውኃ ምንጮችና የውሃ ጉድጓዶች በሮማውያን ይዞታ ስር በመሆናቸው እስራኤል በጥም እየተሰቃየ ጠላቶቻቸው ግን የአትክልት ቦታዎቻቸውን ለማጠጣት ሊጠቀሙባቸው ችለዋል። ተከታዩ ምንባብ የዚህን ከበባ ውጤት ያመለክታል።

እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፥ በሰባት መንገድ ከእነርሱ ትሸሻለህ ለምድርም መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ። ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራቸውም የለም። እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል በእባጭም በቋቁቻም በችፌም ይመታሃል።” (ዘዳግም 28፥ 25-27)

ከበባ:-

ከተማ በከበባ ስር ወድቃ ሳለ የሙታንን በድን መቅበር አለመቻል የሚያስከትለው ተፈጥሯዊ ውጤት በአስፈሪ አራዊት መከበብና፣ በበሽታ አምጪ ተህዋስ መጠቃት ነው።

የቁጥር 26 እና 27 ንግግሮች በምክንያት እና በውጤት ሰንሰለት የተቆራኙ ናቸው። የሙሴ ሕግ ሙታን እንዲቀበሩ ያዛል። አይሁድ ግን ይህን ትእዛዝ ተላለፉ።  ይህን ማድረግ አለመቻል የሚያስከትለው መዘዝ ቸነፈር መሆኑ በቁ.27 ላይ ተቀምጧል።  የቲቶ ሠራዊት ገና ከመድረሱ አስቀድሞ ኢየሩሳሌም በሦስት መንገድ የከተማ ውስጥ አመጽና ሽብር በሚያደርጉ ዘራፊዎች የእርስ በርስ ጦርነት ተወጥራ ነበር። በዚህ ግጭት ወቅት የአይሁድ ዓመፀኞች ሙታናቸውን አልቀበሩም ነበር። ስለዚህም ሬሳ በየመንገዱ ተጥለቀለቀ። በመጨረሻም፣ የኢየሩሳሌም ከተማ ሰዎች ብዙዎቹን አስከሬኖች በከተማይቱ ቅጥር ላይ አውጥተው ሰቀሉት፣ ሬሳውም እንዲበሰብስ ወይም በአእዋፍና በአውሬ እንዲበላ በመተው በቁ.26 ላይ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ፍጻሜውን አገኘ።

ዕብደት:-

እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል። በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም።” (ዘዳግም 28፥ 28-29)

ቁጥር 29 ላይ እንዲህ ይላል፡- “በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥”። ይህ ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜውን አግኝቷል። የኢየሱስን ስቅለት በገለጸበት ምንባቡ  ሉቃስ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥” (ሉቃስ 23፥ 44-45)። ስድስተኛው ሰዓት ማለት እኩለ ቀን ላይ ነው፣ በግምት ከሰአት ቀትር ላይ ነው። ይህ የቁ.29 ተአምራዊ ፍጻሜ የኤርምያስ 33፥ 20-21 ከፊል ፍጻሜንም ይወክላል። 

እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል” (ዘዳግም 28፥ 28-29)

በዚህ ተአምራዊ ጨለማ የተፈጠረው ዓይነ ስውርነትም ምሳሌያዊ ነው። ቁጥር 28 እና 29 የአይሁድን አመጽና ጦርነቱን ቀስቅሶ ያንን ሁሉ ጥፋትና ዕልቂት እንዲመራ እና እንዲያቀጣጥል ያደረገውን ድንቁርና ይገልፃል። ጆሴፈስ እንደገለጸው እነዚያ የአይሁድን ዓመፅ ይመሩ የነበሩ መሪዎች እንደ እነርሱም ሁሉ ደናቁርት ለሆኑ ለብዙ ሰዎች ጉቦ እየሰጡ ወይም በሆነ መንገድ ነቢያት መስለው እንዲታዩ ያባብሉና ያስገድዷቸው ነበር። ከሮም ጋር በተደረገው ጦርነት ወቅትም፣ ሕዝቡን ለማታለልና እንዲከተሉአቸው ለማድረግ አምላክ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው ነፃ እንደሚያወጣቸው፣ እነርሱም ለዚህ እንደተቀቡና እንደተመረጡ እንዲተነብዩላቸው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ትንቢቶች ግን ውሸት መሆናቸው ተረጋግጧል። ከትንቢቶቹ በተቃራኒው የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን በመጨረሻ ድል አደረጉ፤ ጆሴፈስ ሲጽፍ “በከተማዋም ውስጥ አስከሬን ያልነበረበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን [ከተማዋ] በረሃብም ሆነ በዓመፅ በተገደሉት ሰዎች ተሸፍናለች።” ይለናል። ከዚያም ጆሴፈስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:

“ስለዚህ እነዚህ የተጨነቁ ምስኪን ሰዎች በእነዚህ አታላዮች እና እራሱንም እግዚአብሔርን በካዱ ኃሰተኛ ነብያት እየተነዱ ነበር፤ እነርሱም በግልጽ ይታዩ የነበሩትን የጥፋት ምልክቶች ሳይከታተሉ ወይም ከፊት ለፊታቸው የሚጠብቃቸውን ጥፋት በተገቢው መንገድ ዋጋ ሳይሰጡ፣  በግልጽ ይተነብዩ ነበሩ። ነገር ግን ዓይን እንዳላቸው ሰዎች ሳይሆን፣ ዓይን እያላቸው ሳያዩ ወይም ሊያዩበትና ሊያስተውሉ የሚችሉበት አእምሮ ሳይኖራቸው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ያወረደባቸውን የእርግማን መዓት ልብ አላሉም”  [አጽንዖተ እኔ]

ከፍ ሲል ከጆሴፈስ ከተጠቀሰው ሃሳብ በኋላ “በግልጽ የታዩት ምልክቶችም ወደፊት ሊመጣ ስላለው ጥፋት በግልጽ የሚናገሩ ምልክቶች” ነበሩ።  ከእነዚ ምልክቶች መካከል አንዱን ሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ እንዲህ ሲል ዘግቦታል:- “በሰማይም ላይ ውጊያ የሚያደርጉ ጭፍሮችና የሚያብረቀርቅ የጦር ዕቃ ራእይ ታየ።” ይህ ትዕይንት አይሁዶች በመቃቢያን 5፥ 1-4 ላይ ያለውን ተመሳሳይ ክስተት ያኔም በማቃቢያን ጦርነቶች ድል ከማድረጋቸው በፊት የነበረውን ሁኔታ አስታውሷቸዋል። ቀነናውያን በዚህ ትዕይንት መሲሑ በቅርቡ እንደሚገለጥ የሚጠቁሙ ምልክቶችና በሮማውያን ጨቋኞቻቸው ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ገምተው ሊሆን ይችላል።  ይህ ምልክት ግን እንቅፋት ነበር።  ምልክቱን ተከትሎ የወረደባቸው መዓት እንጂ የተጠባበቁት እንዲህ ያለ ድል አልመጣላቸውም።  በሰማይ ላይ በታየው በዚህ ምልክት የተሳሳተ ትርጉም የተነሳ በተፈጠረ ግራ መጋባት፣ እነዚያ የአይሁድ ቀነናውያን በሁሉም የተቀደሰ ታሪካቸው ውስጥ አይተውት ወደማያውቁት  እጅግ አሳዛኝ ወደሆነው ዘግናኝ የዕልቂት ጦርነት “በእብድ ወኔ” ተንቀሳቅሰዋል።

እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል። … በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም” (ዘዳግም 28፥ 29)

በቁ 28 ላይ የተነገረውን የእርግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ በሚሰጠው መልኩ የቀነናውያንን እብደት አስመልክቶ ጆሴፈስ ሲገልጽ፣ የሚከተለውን ይላል፦ “የዓመፀኞቹ እብደት ከረሃባቸው ጋር ተጨምሮ፣ ሁለቱም ሰቆቃቸውን በየቀኑ ይጨምሩት ጀመር”። ይህ እብደት እና  የምግብ እጦት ወደ ቀጣዩ ቸነፈርና ዘረፋ አመራ። 

ጆሳፈስ በታሪክ ዘገባው የነዚያ የአይሁድ ሕዝብ  ውንብድንና ዝርፊያ በውስጣቸው ከሞላባቸው ንጥቂያ የተነሳ የአጋንንትን ባህሪይ እንዳንጸባረቁ ጽፏል፤ በዚህ አይነቱ የከተማ ቀውስ ውስጥ በቀጥታና ፊት ለፊት በሆነ የሰዎች ክፋት አጋንት እንደተወከሉ እናያለን። ስለዚህም፣  ‘’ይህ አሁን ያለው የህዝብ ዓመጽ ከሌላ ስውር ኃይል የተወለደ አመጽ ስለሆነ ልክ ሃይለኛና ክፉ ሆኖ እየጨከነ እንደሚመጣ፣ ካገኘበትም ሁሉ የሚበላውን ምግብ እንደሚፈልግ ቁጡ አውሬ፣ አሁን የገዛ ሥጋውን ወደ መብላት እየወደቀ ነው፡፡‘’ ይላል።

ተመልከቱ ጆሴፈስ ምን እንደሚል፦ 

‘’ከተማይቱ በሁሉም አቅጣጫ በጦርነት ተጠምዳ ሳለ፣ ከነዚህ ክፉ ሰዎች የህዝብ አታላይነት የተነሳ፣ በመካከላቸውም ያሉ የከተማይቱ ሕዝብ፣ ፣ በትንሹ እንደተቆራረጠ አካል አይነት ነበሩ፡፡ በእድሜ የገፉ አረጋውያን ወንዶችና ሴቶች ከውስጥ በተነሳ ሽብር ምክንያት እንዲህ ባለ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ፣ ከዚህም የተነሳ በአገሩ ውስጥ ካለው መራር ሁኔታ እንዲያድኑአቸው የሮማውያንን መምጣት እየተመኙ ከውጪ የሚመጣውን ጦርነት በጽኑ ተስፋ ያደረጉት ነበር፡፡ ዜጎች ራሳቸው እጅግ አስጨናቂ በሆነ ሽብርና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነበሩ‘’ ይላል። በመቀጠልም “የነዚያ እርስ በርሳቸው የሚዋጉ ሰዎች ሁከት፣ በቀንም ሆነ በማታ የማያቋርጥ ነበር፤ ነገር ግን የነዚያ የሚያለቅሱ ሰዎች ሰቆቃ የሌላውን ሰው የሚበልጥ ነበር፤ ሰቆቃቸውንና ሃዘናቸውን ለማስወገድና ለመተው ምንም አይነት አጋጣሚ ፈፅሞ አልነበረም፣ ምክንያቱም አደጋዎቻቸው ያለመቋረጥ አንዱ በሌላው ላይ እየተፈራረቁ ይመጡ ነበርና፡፡ እንዲሁም ደግሞ ጥልቅ የሆነ የጭንቀት ጩኸት እያሰሙ ውጫዊ ጩኸታቸው የተቃወሰ ነበር፤ ነገር ግን ውስጣዊ ጭከናችውን ለመደበቅ በፍርሃታቸው ተጨንቀው፣ በለቅሶ አፋቸውን ለመክፈት ሳይደፍሩ በውስጣቸው ይሰቃዩ (በግሪክ ebasanizonto፣ ማለትም ልክ በራዕይ 9÷ 5 ላይ እንዳለው አይነት ስቃይ) ነበር፡፡ ሁሉም ሰው በራሱ ተስፋ ቆርጦ፤ በህዝቡ አመጽ ተሳታፊ ያልነበሩት ሰዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚደመሰሱ እርግጠኛ ሆኖ ከመጠበቅ ውጪ፤ ሌላ ምንም ከፍ ያለ ፍላጎት ስለምንም ነገር አልነበራቸውም፤ ነገር ግን ራሳቸው አመጸኞቹ ደግሞ እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ፣ በተገደሉት ሬሳዎች ላይ እርስ በርሳቸው አንዱ በሌላው ላይ ተደርቦ በሚወድቅበት ጊዜ፣ ከነዚያ ከእግራቸው በታች ከረገጡአቸው የሙታን በድን፣ እንደገና የባሰ አስፈሪ አውሬ ሆነው በባሰ ጭከና ይታያሉ፡፡ በነሱ ላይ በጠላትነት እንደቆመ የሚያስቡትን ማንኛውንም ሰው፣ በዚህም ጉዳይ ምንም አይነት ማስረጃ ካገኙ ያለምህረት ይገድሉታል፣ የትኛውንም የማሰቀያ ዘዴ ወይም ጭቃኔ ሁሉ ይፈፅማሉ‘’ይላል፡፡ 

ጆሴፈስ ትረካውን በመቀጠል ስለ አንዱ የአመጹ መሪ እንዲህ ይላል፦ “የግስችላው ዮሐንስ በመባል የሚታወቀው አንዱና ዋነኛው የዓመጹ መሪ ‘መላው ሃገሩን በአስር ሺህ በሚቆጠር ዓመጽ የሞላው ሲሆን፣ እንዲህ ያለ በተፈጥሮው ከበቂ በላይ የደነደነና  በእግዚአብሔር ላይ ያመፀ ክፉና ተንኮለኛ ሰው መቼም አልነበረም።‘’ ስለመሪዎቹም “እነዚህ የህዝቡ መሪዎች እኛ ነን ያሉ ሰዎች ከሚከሰሱበት ከክፋታቸው ንሰሃ መግባት የማይችሉ ናቸው፣ (ከራዕይ 16÷ 9 ፣ 11 ጋር አነፃፀሩት) እነዚህም ነፍሳቸውን ከስጋቸው የነጠሉ ጨካኞች፣  ምስኪኑ ህዝብ የሌላ መንጋ እንጂ የራሳቸው ያልሆነ ያህል የቆጠሩአቸው ጨካኝ እረኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፉ ሰዎች ነፍሳቸውን የሚነካ ምንም ስሜት፣ ሥጋቸውንም የሚጎዳ ምንም ሕመም የለባቸውም፤ ውሾች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሙታንን በድን የሚገነጣጥሉ ናቸቅ፤ ወህኒ ቤቶችንም ታመው በተሰቃዩ ሰዎች የሚሞሉ እስከሆኑ ድርስ እነዚህ ምን ሰብአዊ ስሜት አላቸው?” ሲል ይጠይቃል።

ዘረፋ:-

ቁጥር 29 ላይ የተጻፈው “ከቀን ወደ ቀን ትጨቆናላችሁ ትዘረፋላችሁም” ማለት ነው።  ይህንን ጥቅስ ፍጻሜ በሚሰጠው ልክ ጆሴፈስ በዘገባው እንዲህ ሲል ጽፏል፦

[ዘራፊዎቹ ቀነናውያን] በከተማ መካከል በሩ የተዘጋ ቤት በሚያዩበት ጊዜ በነዚያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚበሉት አንዳች ምግብ እንዳላቸው  የሚያውቁበት ምልክታቸው ነበር። በሮቹንም ሰብረው በመግባት ወደ ውስጥ ተንደርድረው እዩገቡ፥ የቤተኞቹን ምግብ ከጉሮሮአቸው ላይ አንድም ሳያስቀሩ ይነጥቋቸውና በኃይል ይወስዱባቸው ነበር። ምግባቸውን ሸሽገው የሚይዙ አዛውንቶችም ይደበደቡ፣ ሴቶቹም በእጃቸው ያለውን ነገር ቢደብቁ ይህንን በማድረጋቸው ፀጉራቸውን ይነጩባቸው ነበር። ለአረጋውያንም ሆነ ለአራስ ሕፃናት ቢሆን ምንም ዓይነት ርኅራኄ አያሳዩም፤ ነገር ግን በሕጻናቱ አፍ ላይ ያገኙትን ማንኛውንም ቁራሽ ለመንጠቅ ሕፃኑን ከመሬት ላይ ጥለው ወለሉ ላይ ይፈጠፍጡት ነበር። ወደ ውስጥ እንዳይገቡ በሮቻቸውን ዘግተው የታገሉና ዘረፋውን የተከለከሉ፣ መብታቸውን በግፍ የተነጠቁ መስሎ የታያቸውን ተቆርቋሪዎች አይራሩላቸውም ነበር፣ የያዙትንም ማናቸውንም ምግብ በጭካኔ ይነጥቋቸው ነበር።  እንዲሁም ምግብ የት እንደሚገኝና ማን እንደሸሸገ ለማወቅ አሰቃቂ የስቃይ ዘዴዎችን ፈጠሩ። እና እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ የነዚያን የተጨነቁ ሰዎች የመራቢያ አካላቸውን በሹል እንጨት በመውጋት፣ ስለት ያላቸው እንጨቶችና ብረቶችን ወደ ውስጣቸው እንዲገባ በማድረግ ስቃያቸውን ያበዙባቸው ነበር። 

እንዲህ ያለ አሰቃቂ ሥቃይ የታየበት ከተማ ወይስ ዘመን፣ እንዲህስ ያለ በእርኩሰትና በአመጽ የተሞላ ትውልድስ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ይኖር ይሆንን? ጆሳፈስ ይቀጥላል፡- የአመጸኞቹ እብደት ከረሃባቸው ጋር አብሮ ያድግ ነበር፣ ሁለቱም አይነት አስጨናቂ ነገር በየቀኑ እየጨመረ ይቀጣጠል ነበር፤ በግልፅ የሚገኝ የእህል አይነት የትም ቦታ አልነበረም፣ ነገር ግን ዘራፊ ወንበዴወቹ ከአንዱ ወደ አንዱ እየተሯሯጡና እየተጣደፉ በየሰው ቤት እየገቡ ይፈተሻሉ፣ ከዚያም አንዳች ነገር ካገኙ ያገኙባቸው ሰዎች ሌላ የደበቁት እህል እንዳለ ስለሚያስቡ ያሰቃዩአቸዋል፣ ከካዱአቸውም ያሰቃዩአቸዋል፣ ፈልገው ካጡባቸውም የባሰ ያሰቃዩአቸዋል (በግሪክ basanizo በራዕይ 9÷ 5 እንዳለው)፣ ምክንያቱም ሌላም የተሸሸገ እህል እንዳለ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ የተለያዩ አሰቃቂ የማሰቃያ መንገዶችን ይፈለስፋሉ /basanismos፣ የ basanizo noun form ነው / ሌላ ምንም አይነት ምግብ ለማግኘት ሲሉ የማሰቃያ መንገዶችን የሚጠቀሙት እነርሱ ራሳቸው በራባቸው ጊዜ ብቻ አይደለም፤ ይህንን የሚያደርጉት ዝርፊያ አስፈላጊ መስሎ ስለታያቸው፣ ደግሞም እብደታቸውን ጠብቀው ለማቆየት ስለፈለጉ ነው፡፡

ይህ በሃይለኛው የክፉ አጋንንት ሞገድ አመልካች ይመስላል፡፡ ይህም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ክርስቶስ ሲናገር፦ “ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። በዚያን ጊዜም፦ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።” (ማቴዎስ 12÷ 43_45) እንዳለው ነው። “ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” (ማቴ 12÷ 43_45) ሲል የተናገረውን ምሳሌ በእርግጠኝነት ይህ ታሪክ ፍጻሜን ይሰጠዋል፡፡ ‘ትውልድ‘ የተባለው እርሱን የካደው ትውልድ ነው፣ በእርግጠኝነት እንደምናውቀው ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ በየምኩራቡ፣ በከተማዎችና በመንደሮች በአገልግሎታቸው ከአይሁድ ላይ የሚበዙ አጋንንትን አስወጥተው ነበር፣ አሁን ግን የሆነው ከበፊቱ የከፋ ነው፣ በትውልድ ላይ ሰባት እጥፍ ጋኔን ገባ ማለት እንዴት ከባድ ነገር ነው! በርካቶቹ አይሁድ መሞት ይመኙ ነበር ነገር ግን በብዙ ይሰቃዩ ነበር (ራዕ 9÷ 6)፣ ‘’በነበረው ረሃብ እጅግ ይሰቃዩ የነበሩት ሰዎች ለመሞት ይመኙ ነበር፤ እነዚያ ቀደም ብለው የሞቱ ሰዎች ደግሞ እድለኛ እንደሆኑ ይቆጠራሉ፣ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን አሰቃቂ ነገር ለመስማትም ሆነ ለማየት በህይወት መኖር ስላልቻሉ ነው፡፡‘’

ጭቆና:-

የፍሎረስ ጭቆና አይሁዶችን ከሮም ጋር ወደ ጦርነት እንዲገቡ የገፋፋቸው መንስኤ ነበር። (ዘዳግም 28፥ 29)

እንደ ጆሴፈስ ከሆነ የቁ.29 ጭቆና፣ የአይሁድ አመጽና የጦርነቱ ዋነኛ መንስኤ ነው።  ዓመፁ ከመቀስቀሱ በፊት የይሁዳ ገዥ የነበረው ሮማዊው ጌሲየስ ፍሎረስ በአይሁድ ሕዝብ ላይ ባደረገው ግፍ ዝነኛ ነበር።  ይህን እውነታ በመጠቀም አንድ ሄለናዊ የአምልኮውን ስፍራ በእርኩሰት ለማሳደፍ በአይሁድ ምኩራብ ደጃፍ ላይ ወፎችን አምጥቶ ሠዋ።  በፈጸመው በዚህ የሚያስቆጣ ድርጊቱ የተበሳጩት አይሁዶች ጉዳዩን ይዘው ለዐቃቤ ሕጉ አቤቱታ አቀረቡ።  ፍሎረስም ክሱን ለመስማት ስምንት መክሊቶችን በክፍያ መልክ ከተቀበለ በኋላ ቅሬታውን ለመፍታት ፈቃደኛ አልሆነም፣ ይልቁንም ጥያቄ ያነሱትን ሰዎች ወደ ወህኒ አገባቸው።  የኢየሩሳሌምም ሰዎች በዚህ ተናድደው ነበር።  ፍሎረስ ግን ወታደሮቹን ልኮ የላይኛውን ገበያ እንዲዘርፉ እና በየመንገዱ የሚያገኙትን ሁሉ በሰይፍ እንዲገድሉ በማድረግ ለአይሁድ ቁጣ ምላሽ ሰጠ።  በየመንገዱ ተይዘው የታሰሩትም ተገርፈው እንዲሰቀሉ ተደርጓል። ከዚያም የአይሁድ ጦርነት ተጀመረ።

ሚስት ታጫለህ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል፤ ቤት ትሠራለህ፥ አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፥ ከእርሱም አትበላም። በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚያድንህም አታገኝም።  ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፥ ዓይኖችህም ያያሉ፥ ሁልጊዜም ስለ እነርሱ ሲባክኑ ያልቃሉ፤ በእጅህም ኃይል ምንም አይገኝም።  የምድርህን ፍሬ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ የተገፋህም ትሆናለህ። ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል። እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካለህ። እግዚአብሔርም በሚያገባህ በአሕዛብ መካከል ሁሉ ድንጋጤ ምሳሌም ተረትም ትሆናለህ።” (ዘዳግም 28፥ 30-37)

ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ወረራን መቀልበስ ያለመቻልና በጦርነት የመሸነፍ ተፈጥሯዊ መዘዝ ነው። ከቁጥር 30 እስከ 35 ወረራው ያስከተለውን በጦርነቱ ሽንፈትን መከናነብ  ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ይኸውም በግዞት መወሰድን ይገልጻል።  በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት፣ ውድ የሆነው ንብረት ሁሉ - ሚስት ብትሆን፣ ልጆችም ቢሆኑ - ተዘርፈው በግዞት ይወሰዳሉ። እነዚያ ከአይሁድ ሮም የጦርኑት ዕልቂት የተረፉ የእስራኤል ሰዎች ምርኮኛ ሆነው ወደ ባዕድ ምድር ተበተኑ።  ከምርኮኞቹም መካከል የአይሁድን ተቃውሞ የመሩት ሁለቱ ዮሐንስ እና ስምዖን በቁጥር 36 ላይ “እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤” በሚል የተገለጠው የእርግማን ትንቢት ፍጻሜውን  በእነርሱ ላይ አግኝቷል።

በቁጥር 37 ላይ እንደተተነበየው እነዚህ ምርኮኞች ተግዘው በተወሰዱበት ሃገር ሁሉ ለአሕዛብ መሳለቂያና መሳቂያ ሆኑ።  የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጥሮች ተሰብረው በመጨረሻ በጦርነቱ ከተደመሰሰች በኋላ 97,000 የሚሆኑ አይሁዳውያን በመላው ሮም በግዞት ነበሩ።  በዚያም በሰይፍ የወደቁ፣ በአውሬ የተበሉ፣ ወይም በግላዲያተር የትግል ሜዳ ሊፋለሙ በባርነት የተሸጡ፣ ወይም እንዲሁ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብረ በዓል ለደስታቸው የተገደሉ ሆኑ።  የሮም ጎዳናዎችም የአይሁድን ሽንፈት በሚያሳዩ ታላላቅ ትርኢቶች ተሞሉ፣ ይህም ትርኢት ሲካሄድ ብርቱዎችና ጠንካራ ሆነው የታዩ ምርኮኞችን ለማዋረድ በሰንሰለት ታስረው በሮም ጎዳና ላይ እንዲጓዙ ይገደዱ ነበር።  ይህ ክብረ በዓል ሲያበቃም በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ያሉ የአይሁድ ምርኮኞችን ሽንፈት የሚያሳዩ የመገበያያ ሳንቲሞች እንዲቀረጹ ተደርጓል፣ ስለዚህ የአይሁድ ምርኮኞች በሮማውያን መሸነፋቸውን የሚያሳይ ምልክት ያለበትን የተቀረጸውን የቄሳርን ምስል ሳይይዙ መግዛትም ሆነ መሸጥ እንዳይችሉ የሚደነግግ ሕግ በንጉሣዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል።

አንዳች ማጣት:-

እጅግ ዘር ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ። ወይን ትተክላለህ ታበጀውማለህ፤ ትልም ይበላዋልና ከእርሱ ምንም አትሰበስብም፥ የወይን ጠጁንም አትጠጣም። የወይራ ዛፍ በአገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ወይራህም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም። ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይወለዱልሃል፤ በምርኮም ይሄዳሉና ለአንተ አይሆኑልህም። ዛፍህን ሁሉ የምድርህንም ፍሬ ኩብኩባ ይወርሰዋል።” (ዘዳግም 28፥ 38-42)

የአንበጣ፣ የትልና የኩብኩባ ሰራዊት ይመጣብሃል፣ ሁሉንም ያሳጣሃል። አንበጣዎች ወራሪውን ሠራዊት የሚያመለክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተምሳሌት ናቸው።  ይህ ተምሳሌታዊነት በኢዩኤል ምዕራፍ 1 ውስጥ በጣም ግልፅ ሆኖ ቀርቧል፣ በራእይ 9፥ 19 ውስጥም ቢሆን ይህንን ተምሳሌታዊ ምልክት እናያለን።  ከርቀት ሆኖ በሰፊ ሜዳ ላይ ሰፍሮ የሚታይ ሠራዊት የአንበጣ መንጋን ይመስላል፤ እነርሱም እንደ አንበጣ በመንገዳቸው ላይ ያለውን ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ እምሽክ አድርገው ይበላሉ፣ አንዳችም አያስቀሩም። ይህ ደግሞ የምግብና የውሃ አቅርቦቶችን አሟጦ መጨረስ ብቻ ሳይሆን፣ በአብዛኛው በዛፎች የተሞላውን የአገሪቱን  የመሬት ገጽታ በመጨፍጨፍ ለከበባቸው የሚያገለግላቸውን እሳት እና የእሳት ድንጋይ ማስወንጨፊያ መሳርያዎቻቸውን  በብዛት ይገነቡበታል።  ይህም በአይሁዶች ጦርነት ውስጥ በግልፅ ታይቷል፡- “[የሮማው ጄኔራል ቲቶም] .  .  .  ሰፈሩን በሞላ በእሳት እንዲያቃጥሉ ለወታደሮቹ ፈቃድ ሰጥቷቸው፣ እንጨቶችን እንዲሰበስቡና በከተማይቱ ላይ የሚንጠላጠሉበትን መሸጋገሪያ እንዲሰበሰቡ አዘዞ ነበር ።  .  .  .  ስለዚህም ዛፎቹ ወዲያው ተቆረጡ፣ የከተማይቱም ዳርቻዎችም ራቁታቸውን ቀሩ።” ከቁጥር 38-42 ባለው የእርግማኑ ምንባብ ላይ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን በአንበጣ መንጋ እንደሚቀጣቸው አስጠንቅቆ ነበር።  የራዕይ መጽሐፍም የዚህን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ በራዕይ 9፥ 21 ላይ ሲያመለክት የሮም ጭፍራን እንደ አንበጣ መንጋ በመግለጽ መዝግቦታል።

በባዕዳን መበለጥ:-

በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አንተም ዝቅ ዝቅ ትላለህ። እርሱ ያበድርሃል፥ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፥ አንተም ጅራት ትሆናለህ።” (ዘዳግም 28፥ 43-44)

ፍሎረስ የተከተለው ፀረ-አይሁድ የሆነው አድሏዊ ፖሊሲው እና ሮም ከአይሁዶች ጋር በነበራት ጦርነት ወቅት በመላው አይሁድ ላይ ያደረሰችው ዝርፊያ ከቁጥር 43-44 የተጻፈውን ቃል ፍጻሜ ይሰጠዋል።

ከፍ ሲል እንደተብራራው፣ በ66 ዓ.ም ተቀስቅሶ ከነበረው ሕዝባዊ አመጽ አስቀድሞ የይሁዳ አቃቤ ሕግ የነበረው ሮማዊው ጌሲየስ ፍሎሩስ ያራመደው ግሪኮችን የመደገፍና አይሁዶችን የመቃወም ፖሊሲዎች ለአይሁድ ጦርነት በዋነኛነት መንስኤ ነበሩ።  ፍሎረስ በግዛቱ ለነበሩት አይሁዶች ግልጽ ጥላቻን እያሳየ በእስራኤል የነበሩትን ግሪኮች በድብቅ ደግፏል።  እዚህ ላይ በቁጥር 43-44 ያለው የእርግማኑ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ፍጻሜውን እንዳገኘ ማየት ይቻላል።  ይህ ዜጎችን እየናቁና እያዋረዱ ባዕዳንን ከፍ ከፍ የማድረግ ዝንባሌ ከጦርነቱ በኋላም ተባብሶ ቀጥሏል።  ሮማውያን የይሁዳን ግዛት ካወደሙ እና ብዙ አይሁዳውያንን ወደ ሮም ግዛት በግዞተኝነት ካፈለሱ በኋላ፣ በዚያ ለመኖር የተፈቀደላቸው ብዙዎቹ ለባርነት ተሸጡ።  ከዚህም በላይ ከግዛቱ የተውጣጡ የውጭ አገር ወታደሮችን ያቀፈው የሮማውያን ሠራዊትና ረዳቶቻቸው በጦርነቱ ወቅት በዘረፋ የያዙት ብዙ ምርኮ ስለነበራቸው “በሶርያ አንድ ፓውንድ ወርቅ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ በግማሽ ይሸጥ ነበር።” ከተማይቱ ከወደመች በኋላ አሥረኛው ሌጌዎን በመባል የሚታወቀው የጦሩ ክፍልም በኢየሩሳሌም እንዲሰፍር ተደርጎ ነበረ። ስለዚህ ፍሎረስ የተከተለው የፀረ-አይሁዳውያን ፖሊሲዎቹና፣ በአይሁድ ጦርነት ወቅት የነበረው አይሁዳውያን በውጭ አገር ጠላቶቻቸው የተፈጸመባቸው ዘረፋ በቁጥር 43 እና 44 ላይ ያለውን ቃል ፍጻሜ ይሰጠዋል: “ያበድሩሃል አንተ ግን አታበድረውም

ጽኑ ራብ:-

የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዓቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፥ ያሳድዱህማል፥ ያገኙሁማል። በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘላለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ። ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህምና፣ በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል።” (ዘዳግም 28፥ 45-48)

በኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት በከተማይቱ የነበረው ረሃብ፣ ጥማት እና ድህነት የዘዳግም 28፥ 48 የእእግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜው ነው። ጆሴፈስ ከበባው ስላስከተለው ረሃብ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:-

ከዚያም ረሃቡ እድገቱን አስፍቶ ህዝቡን በየቤተሰባቸውና በየቤተሰቡ ይበላው ጀመር።  በየደርቡ ያለው ክፍልም በራብ የሚሞቱ ሴቶችና ሕጻናት ሞልተውት ነበር፤ የከተማይቱም መንገዶች በሽማግሌዎች ሬሳ ተሞልቶ ነበር።  ሕፃናቱና ወጣቶቹም እንደ ጥላ በገበያ ስፍራ እየዞሩ የሚላስ የሚቀመስ ፍለጋ ተንከራተቱ፥ ከመከራቸውም ብዛት የተነሳ በስፍራ ሁሉ ወድቀው ከራብ የተነሳ ስለሞቱ እሬሳቸው አብጦ አብጦ በየስፍራው ወደቆ ተጥሎ ነበር።  ታመው ለሞታቸው የሚያጣጥሩ ሌሎች ሰዎችም በዙሪያቸው ሞተው የወደቁ ሰዎች ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ እነርሱን መቅበር አልቻሉም። ደህነኞቹም ቢሆኑ ከሬሳዎች ብዛት የተነሳ፣ ሌሎችን ሲቀብሩ ብዙዎች መሞታቸውን አይተዋልና፣ ራሳቸውም እንዴትና መቼ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚሞቱ እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ይህንን ከማድረግ ተከለከሉ፣ ይልቁንም ቀባሪ ባያገኙም ለመሞት በሚሆን ቅድመ ዝግጅት ብዙዎቹ በከፈኖቻቸው ገብተው የሚሆነውን ይጠባበቁ ነበር።

ወረራ:-

እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን፥ ፊታቸው የደነደነውን፥ ሽማግሌውንም የማያፍሩትን፥ ሕፃኑንም የማይምሩትን ሕዝብ ንስር እንደሚበርር ከሩቅ አገር ከምድር ዳር ያመጣብሃል። እስክትጠፋ ድረስ የከብትህን ፍሬ የምድርህንም ፍሬ ይበላሉ፤ እስኪያጠፉህም ድረስ እህልን የወይንም ጠጅ ዘይትንም የላምህንና የበግህን ርቢ አይተዉልህም። በአገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ደጆች ሁሉ ከብበው ያስጭንቁሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ በደጆች ሁሉ ከብበው ያስጨንቁሃል።” (ዘዳግም 28፥ 49-52)

በቁ.52 ላይ ያለው ቃል ፍጻሜውን በሚያገኝበት መንገድ ሮማውያን የእስራኤልን ከተሞች በከበባ ውስጥ አአድርገው ነበር። ምንም እንኳን በቁጥር 51 ላይ በተጻፈው ቃል በአጭሩ ማተኮር ተገቢ ቢሆንም፣ በቁጥር 49-52 ያሉት የእርግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜዎች ግን አብዛኞቹ ቀደም ብለው ተብራርተዋል።  በዚህ ቁጥር የተገለጠው አንድ ግዙፍ ወራሪ ኃይል የምድሪቱን ፍሬ ከሚበላው የአንበጣ መንጋ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል በድጋሚ የሚያስታውስ ነው።  በሚቀጥለው ቁጥር፣ ይህ የባዕድ ጦር የተመሸገችውን የተስፋይቱን ምድር ከተማ በሙሉ ይከብባል ተብሏል።  በአይሁዶች ጦርነት ወቅት፣ የሮማውያን ጦር የእስራኤልን ግዛት በሙሉ የጎርፍ ውሃ ምድርን እንደሚከድን  ከተማይቱን ከበበ።  በተጨማሪም በቁጥር 49 ላይ የተጠቀሰውን ንስር ስናይ የሮም ኦፊሴላዊ ምልክት የንስር መልክ መሆኑን ልናስተውለው የሚገባን ነው። 

ሰው በላነት:- 

ጠላቶችህም ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። በአንተ ዘንድ የተለሳለሰና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ይኖር የነበረ ሰው በወንድሙ፥ አቅፋውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆች ይቀናል፤ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም። በአንተ ዘንድ ያለችው የተለሳለሰችና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ትኖር የነበረችው፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥ በወንድና በሴት ልጅዋም፥ በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅ፥ በምትወልዳቸውም ልጆች ትቀናለች፤ በደጆችህም ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች።” (ዘዳግም 28፥ 53-57)

ከተማይቱ ተከብባ በነበረበት ወቅት፣ ረሃቡ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ አንዲት ሴት የራሷን ልጅ እስከ መብላት መድረሷን ጠቅሶ በመተረክ ጆሴፈስ በከተማይቱ ነግሶ የነበረውን አስፈሪ የመበላላት ተግባር ያመለክታል። ይህም በዘዳግም 28፥ 53-57 የተዘረዘረውን የእርግማን ትንቢት ፍጻሜ ይሰጠዋል።

ጆሴፈስ በምግብ እጦት ምክንያት በከከማይቱ ተፈጥሮ የነበረውን ተስፋ አስቆራጭ ግጭት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- በከተማይቱም በራብ ከሞቱት ሰዎች ቁጥራቸው እጅግ የበዛና የደረሰባቸውም ሰቆቃ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አልነበረም።  የትኛውም ዓይነት የሚቀመስ የሚላስ ነገር ምልክቱ በየትም ቦታ ቢታይ፥ ወዲያውኑ ፍጅቱ ይጀመራል፣ የሚዋደዱ ባልንጀሮችም እርስ በርሳቸው መጣላት ይጀምራሉ፣ እጅግም በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ሰው ሕይወቱን ለማቆየት በሚሆን ስጋት የሸሸጋትን ቁራሽ እርስ በርስ ይነጣጠቁ ነበር”። 

ሱልፒቲየስ ሴቬሩስ ሲናገር በከበበው መሃል የነበሩ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሬሳዎቻቸውን ይበሉ ነበር ይላል።

ከዚህም በላይ በ70 ዓ.ም. በነበረው የኢየሩሳሌም ከበባ ወቅት በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ሆነው መውጣትም መግባትም የተከለኩሉ አይሁድ እጅግ አስጸያፊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለመብላት ይጎመጁና ደፋ ቀና እያሉ ነበር፣ የበሰበሰውን የሰውንም አካል እንኳ ቢሆን እንደ ምግብ ለመጠቀም አልተዉም ነበር።

በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ 6÷ 5-6 የተነገሩው የሦስተኛው ማህተም መፈታትና፣ በጉራቻው (በጥቁር) ፈረስ ላይ ያለው ጋላቢ መምጣት ይህን የመሰለ አስከፊ ረሃብ እንደሚመጣ በእርግማኑ ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሰውን ትንቢታው ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ ይሰጠዋል።

ጥቁሩ ፈረስ ላይ የተቀመጠው የሚወክለው በአይሁድ ሕዝብ ጦርነት የተነሳ የሚቀሰቀሰውን ረሃብ ወይም ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ሞት ነው፡፡  የቀለሙ ጥቁረት የረሃብ ወይም የችጋር መገለጫ ነው፣ “ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ” (ሰቆቃው ኤርምያስ 5÷ 10) ይላልና።  ይህ በጥቁሩ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ በእጁ የያዘው ሚዛን አለው፡፡ ይህም በምድሪቱ የሚገኘውን የምግብ እህል የሚለካበት እንደሆነ ከክፍሉ እንረዳለን፡፡ ይህም ሰዎች በእጃቸው ያለውን የገዛ ራሳቸውን እንጀራ የሚበሉት እየቆጠቡና በሚዛን እየሰፈሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ እግዚአብሄርም በእርሱ ላይ በማመጽ የሚበድሉ ከሆነ እንዲህ እንደሚሆንባቸው አስቀድሞ “የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም።” ሲል ነግሮአቸዋል (ዘሌ 26÷ 26)፡፡ 

አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥”  (ራዕይ 6፥ 6)፤ ተመልከቱ፣ ዲናር የበርካታ የቀን ሰራተኞች አማካይ የቀን ገቢያቸው ነው፡፡ እንግዲህ የቀን ገቢውን ይዞ ከስራው ሲመለስ በዚያች ሊሸምት የሚችለው በእርቦ የተሰፈረች ስንዴን ወይም ገብስን ብቻ ነው፣ ይህም የአንድ ሰው የቀን ሬሽኑ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ቀኑን ሙሉ ሰርቶ የሚያገኛት ገቢ የራሱን ሆድ ብቻ እንኳ ለመሙላት የማትበቃ ናት፡፡ ቤተሰብን መመገብ የማይታሰብ ሲሆን፣ በያዛት አንዲት ዲናር እህል መሸመት ከፈለገ ማድረግ ያለበት ረከስ የሚለውን አሰርና ብጣሪ ብቻ መግዛት ነበር፡፡ 

ሮማውያን ከተማይቱን ከበዋት በነበረበት ጊዜ አይሁድ እጅግ አስከፊ በሆነ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነበር፡፡ ይህም በእህል መጋዘናቸው በቂ ምግብ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፣ እንደውም የተወሰነ ጊዜ ሊያቆያቸው የሚችል ክምችት ነበራቸው፡፡ ሆኖም በከተማይቱ በተለያየ አቅጣጫ መሽገው እርስ በርሳቸው ይዋጉ የነበሩ ቡድኖችና የአመጹ መሪዎች አንዱ ሌላውን ለመጉዳት በሚወስዱት የእብደት እርምጃ የተቃዋሚያቸውን ጎተራ እና የእህል ክምችት በእሳት ያቃጥሉት ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ምግብ እጅግ ብርቅና ሊገኝ የማይችል እስኪሆን ድረስ ሁኔታው እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ ነበር፡፡ ጆሳፈስ የሁኔታውን ዘግናኝነት ሲዘግብ ዋቢ አድርጎ ካቀረባቸው ገጠመኞች መካከል የገዛ ራሷን ሕጻን ልጅ በቶፋ ቀቅላ ስለበላች ሴትናና የምግብ ሽታ ጥርቷቸው ምግብ ፍለጋ ድንገት ወደ ቤቷ ለገቡ እና ምግብ እንድታቀርብላቸው ለጠየቋት የሮም ወታደሮች “እኔ ለዛሬ የሚበቃኝን ያህል ተስተናግጃለሁ፣ ከዚህ ለከፋ ቀን ያስቀመጥኩትን ወስዳችሁ ብሉ” ስትላቸው ቶፋውን ሲከፍቱት የተበላ የህጻኑን ግማሽ አካል አዩ ሲል  የገጠማቸውን ሁኔታ ይተርካል።  ይህም በዘዳግም 28 ÷ 53 ላይ የተጻፈውን ፍጻሜ የሚሰጠው ሲሆን፣ ከ2 ነገስት 6÷ 28 ጀምሮ ካለው ጋርም የሚነጻጸር ነው። እነዚያ አረማውያን ወታደሮች ግን በሴትየዋ ቤት ያዩት አስፈሪ ተግብር ከፈጠረባቸው ድንጋጤ የተነሳ ፈርተው በፍጥነት ቤቷን ለቀው በሩጫ ወጥተው መሄዳቸውን ጆሴፈስ ይተርካል፡፡  ጌታችን ኢየሱስ ይህን አስከፊ ጊዜ እያመለከተ ሲናገር:- “ነገር ግን  ያን ጊዜ ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” ብሏል (ሉቃስ 21÷ 20-23፤ 23÷ 28-29 ተመልከት)፡፡ የራዕይ መጽሐፍ ይህ ሦስተኛ የጥቁር ፈረስ ጋላቢ ንግግርና በጆሳፈስ የታሪክ ዘገባ መካከል ያለውን ትይዩነት ልብ በሉ፡- ለአንዲት ሩብ ያህል ብቻ ለምትሆን ለዚያውም ለስንዴ ሲሉ ያላቸውን ነገር ሁሉ ፈጽመው ሸጠው የጨረሱ፣ ዋጋ ሊያወጣ የሚችል ጥሪት የነበራቸው ሰዎች የሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፣ ምንም የሌላቸው ድሆች የሆኑ እንደሆነ ግን ባዶ ሆነው የሚመጣባቸውን ይጠብቃሉ፡፡ 

የግብጽ ደዌ:-

በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ ባትጠብቅ፥ ይህንንም «አምላክህ እግዚአብሔር» የተባለውን የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ፥ እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመንም የሚኖረውን ታላቅ መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመን የሚኖረውንም ክፉ ደዌ ያደርግብሃል። የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደ ገና ያመጣብሃል፥ ይጣበቅብህማል።” (ዘዳግም 28፥ 58-60)

እነዚያ በግብጽ ላይ ዘንበው የነበሩ አሥሩ የዘጸአት መቅሰፍቶች በአይሁድ ጦርነት ወቅት በእስራኤል ላይ ወርደው ነበር። 

በራእይ መጽሐፍ ላይ በተብራራውና አጽንዖት በተሰጠው መሰረት፣ በዘፀአት ጊዜ በግብፃውያን ላይ የደረሱት አሥሩ መቅሰፍቶች የቃል ኪዳኑ እርግማን ሆነው በአንዳንድ መንገድ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው።  የራዕይ 16 ሰባቱ ጽዋዎች እያንዳንዳቸው የተለየ የዘፀአት መቅሰፍትን ያመለክታሉ።  የመጀመሪያው ጽዋ የእባጭ ቸነፈርን የተሞላ ነው።  ሁለተኛውና ሦስተኛው ጽዋዎች የደም መቅሰፍትን ያመለክታሉ። የአራተኛው ጽዋ ቸነፈር የዝንቦች ወይም የዱር አራዊቶች መቅሰፍት ስለመሆን አለመሆኑ በተርጓሚዎች ዘንድ አንዳንድ ክርክሮች አሉ።  አምስተኛው ጽዋ የጨለማ መቅሰፍት ነው።  ስድስተኛው ጽዋ የእንቁራሪቶችን መቅሠፍት ያስታውሳል፣ ሰባተኛው ደግሞ የበረዶ መቅሠፍት ነው።  የአንበጣ መቅሰፍት በራእይ 9፥ 27 በአምስተኛውና በስድስተኛው መለከቶች ውስጥ ተጠቅሷል። ስለ ዘጸአት አሥረኛው መቅሠፍት ጨለማ ማስታወሻ በራዕይ 13፥ 16-17 ላይ ከምድር የወጣው አውሬ እያንዳንዱ ሰው በእጁና በግንባሩ ላይ ምልክቱን እንዲቀበል ያስገድዳል። በዚህ መቅሠፍት ወቅት ዕብራውያን ባሪያዎች እና ዘሮቻቸው ከፋሲካ በግ መሥዋዕት በኋላ በእጃቸውና በግንባራቸው ላይ በመንፈስ ምልክት ተደርጎባቸዋል (ዘጸአት 13፥ 15-16)።  የቅማል እና የትንኝ መቅሰፍት እና የዝንቦች ወይም የአውሬዎች መቅሰፍት የኢየሩሳሌም አይሁዶች ከተማቸው በተከበበች ጊዜ የሙታኖቻቸውን በድን መቅበር ያለመቻላቸው ተፈጥሮአዊ ውጤት ነው።  አስከሬኖች በየጎዳናዎች ላይ ሲወድቁና ቀባሪ ሲያጡ ዝንቦችንና ትንኞች ይሰበስባል፣ እነርሱም ያንን ብስባሽ የሰው አካል ተመግበው እንቁላሎቻቸውን በእነዚሁ አስከሬኖች ውስጥ ይጥላሉ።  እነዚህ ትንኞችና ዝንቦች ይህን ያህል የተትረፈረፈ የምግብ ምንጭ ስለሚኖራቸው እጅግ በዝተው ከተማይቱንና ቤቶችን ሁሉ ይወርራሉ።  በቁ.26 ላይ እንደተተነበየው፣ የእነዚህ ሙታን አስከሬኖች ሬሳ ወፎችንና ሌሎች የዱር አራዊትንም ወደ ከተማው ይስባሉ።  በእንስሳት ላይ የሚደርስ ቸነፈር ደግሞ የጥንት ሮማውያን የሚያካሂዱት የጦርነት ውጤት ነው።  በቁጥር 18፣ 31-33 እና 49-51 የተገለጸውን የእርግማን ማስጠንቀቂያ ፍጻሜ በሚሰጠው መልኩ አይሁድ ከሮም ጋር ባደረጉት በዚያ ጦርነት ሮማውያን ሠራዊቶቻቸውን ለመመገብና ጠላቶቻቸው የሆኑትን እስራኤላውያንን ለማስራብ ከብቶቻቸውን ዘርፈው ይወሰዱባቸው ነበር።

ከርስት መነቀል:-

ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ መቅሠፍትም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል። እግዚአብሔርም በጎ ያደርግላችሁ ዘንድ ያበዛችሁም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋችሁ ሲያፈርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ። እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወዳሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን፥ ታመልካለህ።” (ዘዳግም 28፥ 61-64)

የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል።” (ዘዳግም 28፥ 62)

ጆሴፈስ እንዳለው፣ 1,100,000 ሰዎች በጦርነቱ ተገድለዋል፣ 97,000 የሚሆኑት ደግሞ በምርኮ ተወስደዋል። ሊቀ ጳጳስ ኡሸር የጆሴፈስን ጽሑፎች እንደ ማጣቀሻ ተጠቅመው በ70 ዓ.ም በተጠናቀቀው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ እስከ ወደቀችበት ጊዜ ድረስ 1,337,490 የተገደሉትን ሙታን ዘርዝረዋል።

“..... ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።” (ዘዳግም 28፥ 63)

በቁጥር 63 ላይ “ለመውረስ ከገባችሁባት ምድር እነቅላችኋል” ይላል።  ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በተካሄደው የአይሁድ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች የተገደሉና የተሰደዱ ቢሆንም፣ የዚህ ጥቅስ ማስጠንቀቂያ ግን  በመጨረሻ ፍጻሜውን ያገኘው ከሁለተኛው የአይሁድ አመፅ በኋላ ይመስላል።  በዚህ ጊዜ ሃድሪያን  ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የቀሩትን አይሁዶች ከይሁዳ ለቅቀው እንዲሰደዱ በጥብቅ አዘዘ። ማንኛውም አይሁዳዊ የሆነ ጎሳ ይህንን ከአገሩ ተባርሮ የመውጣት ትዕዛዝ ተላልፎ ቢገኝና ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ቢደፈር ያለምንም ርህራሄ ይገደላል። እግዚአብሔር አይሁድ የተባለውን  ዘር ራሱን የፈለገው አይመስልም ስለዚህ ምድሪቱን እንዳይረግጡ አድርጎ አሳደዳቸው። ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዶችም እንኳ ቢሆኑ በተመሳሳይ መልኩ ከኢየሩሳሌም እንዲባረሩ ተደርገዋል። ቤታር የተባለው የባር ኮክባ የመጨረሻው ምሽግ ከወደቀ በኋላም እንኳ በይሁዳ ምድር ውስጥ ከታወቁትና ከነበሩት ሰባ አምስት የአይሁድ ሰፈሮች መካከል የአይሁድ ሰዎች በአንደኛው ውስጥ እንኳን መኖር እንደቀጠሉ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።  አንዳንድ የአይሁድ መንደሮች ግን በዮርዳኖስ ሸለቆ፣ በበረሃው ጠርዝ በደቡብ እና በምዕራባዊው የባህር ዳርቻ ሜዳ ላይ ከሚገኙት የይሁዳ ኮረብቶች ዳርቻዎች ጋር ብቻ እዚያም እዚህ ተበታትነው ቀሩ።  ከዚያም የይሁዳ ሰዎች ከአገራቸው ተነቅለው ከሶርያውያንና ከአረቦች ጋር ተቀላቅለው ሰፈሩ። “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ያለው የኢየሱስ ትንቢትም ፍጻሜው በዚህ ደረጃ መራር ነበር። አይሁዶች ከተባረሩ በኋላ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት መቶ ዓመታት ግን በኢየሩሳሌም ታሪክ ውስጥ፣ ከተማይቱ ያለ አይሁድ በሽታዋ ለቅቆአት የሄደ ያህል ከሁሉም የበለጠ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰላማዊ ዓመታት ነበሩ።  በነዚህ ጊዜያት ውስጥ፣ የአሕዛብ ክርስቲያኖች ቁጥር በብዙ ጨምሯል “በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እንኳ፣ አይሁዶች አሁንም ወደዚያች ከተማ በዓመት አንድ ቀን ካልሆነ በስተቀር እንዳይገቡ ታግደው ነበር። ኢየሩሳሌምም ከታሪካዊ እሴት አንጻር በአገሪቱ ውስጥ ብቸኛ የክርስቲያን ከተማ ሆነች፣ ብቸኛዋ።

የስጋት ኑሮ:-

በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፥ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ፥ ፈዛዛ ዓይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል። ነፍስህም ታመነታለች፤ ሌሊትና ቀንም ትፈራለህ፥ በሕይወትህም አትታመንም፤ አንተ ስለ ፈራህበት ስለ ልብህ ፍርሃት፥ በዓይንህም ስለምታየው አስተያየት፥ ማለዳ፦ መቼ ይመሻል? ትላለህ፤ ማታም፦ መቼ ይነጋል? ትላለህ።” (ዘዳግም 28፥ 65-67)

ይህ የአይሁድ ምርኮኞችን ጭንቀት ያሳያል። ከላይ እንደተገለጸው፣ ሮማዊው ጄኔራል ቲቶ ኢየሩሳሌም ከወደቀች በኋላ 97,000 አይሁዳውያንን በግዞት ምርኮ ወሰዷል፤ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በሮማውያን አምፊቲያትሮች “በሰይፍና በአውሬ ተገድለዋል”። ለአህዛብ አማልክት መስዋእት እንዲሆኑ፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብርም በሰይፍ እንዲታረዱም ተደርገዋል። ታዲያ አይሁድ ምርኮኛና ባርያ በመሆናቸው እንዲሁ ጭዳ የተደረጉ የወንድሞቻቸው እጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ወይም  በሮማውያን አምፊቲያትሮች ውስጥ እንዳይገደሉ የነበረባቸው የየእለቱ ፍራቻና ሰቆቃ ከቁጥር 65-67 የተተነበየው የእርግማኑ ማስጠንቀቂያ ምናልባት የጭንቀታቸው መንስኤ ሊሆን ይችላል።

ወደ ግብጽ መመለስ:-

ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።” (ዘዳግም 28፥ 68)

የዚህ ምእራፍ የመጨረሻ ጥቅስ ምናልባት በጣም የሚገርም ነው። በዚህ ትንቢት መሰረት እስራኤላውያን በባርነት ወደ ግብፅ ተልከዋል።  ጆሴፈስ የቁ.68ን ፍጻሜ በግልፅ ሲጠቅስ፡- “ከአሥራ ሰባት ዓመት በላይ የሆናቸውን የቀሩትንም ሕዝብ አስሮ ወደ ግብፅ ማዕድን ማውጫ ላካቸው።” ይላል።    ሮማውያን ብዙ ምርኮኞችን በመርከብ መውሰዳቸውንም ሚድራሽ ውስጥ ተረጋግጧል። ከዚያም የተቀረው የቁጥር 68 ቃል ሲፈጸም፣ ሮማውያን ብዙ አይሁዶችን በባርነት ይዘው እንደነበርና በዚያው መጠንም የገዢዎች እጥረት እንደነበር ይናገራል፦

“ሕዝቡ እንደርካሽ  ሸቀጥ ሆኑ፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እያንዳንዳቸው በዝቅተኛ ዋጋ ይሸጡ ነበርና፤ ለሽያጭ የቀረቡትም እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ዋጋ ሰጥተው የሚገዙአቸው ጥቂቶች ነበሩ።”

ከላይ ባሉት ጥቅሶች ላይ እንደሚታየው እነዚያ ለእግዚአብሔር ያልታመኑ እስራኤላውያን ከዘጸአት በፊት ወደነበራቸው የጥንት የባርነት ታሪካቸው እንደገና ተመልሰው በግብፅ ባርያዎች ሆኑ። ባሪያዎችም ከመትረፍረፋቸው የተነሳ  ገዢዎች ጥቂት ብቻ ነበሩ። ይህ ጥቅስ በዘዳግም 28 ላይ በዝርዝር የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ ምን ያህል ሙሉ በሙሉ እና ትክክለኛ በሆነ መንገድ  ፍጻሜአቸውን እንዳገኙ የሚያሳይ ፍጹም ምሳሌ ነው። 

ስለ ቀሪው የፍጻሜ ዘመን ትንቢቶችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃል በሆነ መልኩ ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል።  ይህንን የምትጠራጠሩ ሰዎች ልትኖሩ ትችላላችሁ፣ የተፈጸመውን ወንጌል እንደሚያምንና እንደ ሚያስተምር ፕሪቴሪስት የቅዱስ ቃሉን ትንቢት አይቀሬ ፍጻሜ ከቃሉ ተነስተን፣ ታሪካዊ ፍጻሜውን መርምረን የምናቀርበውን ማስረጃ ግን ማስተባበል የሚቻልበት ስነ መለኮት የለም። እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንበያዎች እንዴት ፍጹም በሆነ እና በሚያስገርም ሁኔታ እንደተፈጸሙ ልትመለከቱ ብትወዱ ብሎገሬን ይጎብኙ።

ግዛቸው ከበደ

ለዚህ ጥናት እንደ ግብዓት ያገለገሉ የጽሁፍ ስራዎች ከሞላ ጎደል፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ

  • Bruce, F. F, The International Bible Commentary with the NIV

  • Coggins R. J & Houlden J.L. A dictionary of Biblical Interpretation

  • Eusebius, The History of The Church

  • Gentry,Jr. Kenneth L Before Jerusalem Fell, Dating the Book of Revelation

  • Whiston, William The New Compete Work of Josephus, 

  • Josephus, Flavius The Wars of the Jews

  • Duncan W. McKenzie, Ph.D., The Antichrist and the Second Coming: A Preterist Examination Volume 2: The Book of Revelation (USA: Xulon Press, 2012),

  • Tacitus The Histories 

  • M. Avi-Yonah, The Jews of Palestine: A Political History from the Bar Kokhba War to the Arab Conquest, (New York: Schocken Books, 1976)

  • Stevens, E. Edward. Final Decade Before the End.

  • Teddy Kollek and Moshe Pearlman, Jerusalem: A History of Forty Centuries, (New York: Random House, 1968)

  • Midrash Rabbah Lamentations

  • Mills, Jessie E, Jr Revelation survey and Research, 2004

  • Mason, Steve: Josephus and the New Testament 1992 Hendrickson Publisher