ፕሪቴሪዝም፣ የተፈጸመው ሥነ-መለኮት
በታሪካዊ መዛግብት ከተረጋገጡ አንዳንድ ምልክቶች እና ምስክሮች ጋር
መግቢያ፦ ትንቢት ተፈጽሟል ብለን ለያዝነው አቋም ቀዳሚና ብቸኛው መሰረታችን የቅዱስ ቃሉ ትምህርት መሆኑ የልብ ስፋትና የአእምሮ ዝግጅት ባላቸው፣ በቅጡ ማሰብ በሚችሉም ሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። ለእምነት ቤተሰብ ቃሉ ብቻ ይበቃዋል ብለን እንጂ እንደ ደመና ከበውን ያሉ እርግጠኛ የታሪክ ምንጮችን ጠቅሰን ማስረዳትም ሆነ ለሚጠይቁን መልስ መስጠት አያስቸግረንም። በመሆኑም ሊመረመሩ ይገባቸዋል ብዬ የማስባቸውን አንዳንድ ታሪካዊ የመረጃ ምንጮችን ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። እነዚህ የመረጃ ምንጮች ለብዙዎቻችሁ ምን ማለት እንደሆኑ አላውቅም፤ ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ ትውልድ አያልፍም”፣ “ጌታ በደጅ ነው”፣ “ዘሙኑ አጭር ሆኖአል”፣ “ፈጥኖ”፣ "ቶሎ" ፣ “ሊሆን ያለ” ወዘተ." ሲል ለሚገልጣቸው ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ ንግግሮቹ ተገቢውን ዋጋ ሰጥተን ልናያቸው ይገባናል።
አስተውሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት ሊመጣ ያለው ፍርድ ከጌታ ዳግመኛ ምጽአቱ (ፓሮውዥያው) ጋር የተቆራኘና፣ በከሃዲዋ እስራኤል ላይ ሊደርስ የቀረበ ፍርድ ነበር (ማቴ. 19፡28፤ ሉቃ. 21፡22-23፣ 32፤ ሉቃ. 22፡30)፤ ይኸውም ከ66-70 ዓ.ም ባለው ጊዜ በተካሄደው የአይሁድ-ሮም ጦርነት ወቅት፣ ለ42 ወራት (3 ዓመት ተኩል) የሚቆይ ማለት ነው። ይህንን በግልጽ የሚናገሩና ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል ብለን ለያዝነው አቋም በቀዳሚነት ዋቢ የምናደርጋቸውን የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ከብዙ በጥቂቱ በሁሉት ምድብ በዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ በዝርዝር አስቀምጫለሁ። በዚህ ጽሁፍ ግን ዋናው ትኩረቴ በተለይ የፍላቪየስ ጆሳፈስን "Wars" እና የኢውሳብየስን "Ecclesiastical History" መጻህፍት ሳገላብጥ፣ ድረ ገጾችንም አስሼ ያገኘሁአቸውን ሰነዶች ተመልክቼ፣ ምን ያህል ከቃሉ ትምህርት ጋር የሚስማሙ እንደሆነ ግንዛቤ ከያዝሁና፣ ሰነዶችን በመጠቀም ረገድ ልምዱ ያላቸውን የተመሰገኑ ምሁራን የጽሁፍ ስራዎች አማክሬ፣ ሰነዶቹ የያዙአቸውን ታሪካዊ ማስረጃ የሚሆኑ ክስተቶችን በመጠኑ ጠቆም ጠቆም ማድረግ ነው። እኔን ግን በእጅጉ የሚገረመኝ ነገር ቢኖር ብዙ ክርስቲያኖች፣ ባስ ሲልም ምሁራኖቻችን ስለ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ምንም ሲሉ አለመሰማታቸው ነው። እስካሁን ባለኝ ምልከታ የተለያዩ የአገራችን "ሥነመለኮት አዋቂዎች" በትምህርታቸውም ሆነ በጽሁፎቻቸው እውቅና ሰጥተው ዋቢ ሲያደርጓቸውም ሆነ ሲተቹአቸው አልሰማሁም፣ አላየሁምም። ምናልባትም እነዚህ ሰነዶች ይኖሩ እንደሆነ ስለማወቃቸውም እጠራጠራለሁ።
የአዲስ ኪዳንን ታሪክና ስነመለኮት ለመመርመር ራሱን የሰጠ ማንም አማኝ ከነዚህ ታሪካዊ መዛግብትና ሰነዶች ጋር የሚፋጠጥበት ዕድል ከሌለው ስለ አዲስ ኪዳን የሚያውቀው በግርድፉ ነው ማለት ነው። ጌታ ቢፈቅድ በአዲስ ኪዳን ጥናት ውስጥ የሰነዶቹን ዋጋ የሚያስነብብ ጽሁፍ ሌላ ጊዜ አቀርባለሁ። እነዚህ ሰነዶች በጊዜው የተፈጸሙትን ክስተቶች የአይን ምስክር ሆነው በታሪክ ድርሳናቸው ከትበው ያስቀሩልንና የእነርሱን ምስክርነት ከቃሉ ትምህርት ጋር እያመሳከሩ የጻፉ የጥንት አባቶችና ምሁራን ስራ ስለሆኑ፣ ስለ ትንቢት ፍጻሜ ከቃሉ ምስክርነት ያለፈ ውጫዊ ማስረጃ ለሚፈልጉ አይነተኛ ግብዓት በመሆናቸው፣ በቀጥታ ወደ ማስረጃዎቹ ዝርዝር አልፋለሁ፦
1ኛ/ ጆሴፈስ (በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የኖረ፣ ስለ አይሁዶች ታሪክ እና ስለ ሮማ ግዛት በሰፊው የጻፈ አይሁዳዊ የታሪክ ምሁር ነው። የጆሴፈስ ጽሑፎች በተለይ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለተመዘገቡና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ለተከሰቱት ክስተቶች እና አንዳንድ ሰዎች ጠቃሚ ምስክርነት ስለሚሰጡ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ስብዕናዎች እና ቡድኖች በጆሴፈስ ውስጥም አሉ። የጆሴፈስ ጽሑፎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለተገለጹ ክስተቶች ውጫዊ የሆነ ታሪካዊ አውድን በማቅርብ ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው። ስራዎቹ በጊዜው ስለነበሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ እውነታዎች ብርሃንን ይፈነጥቃሉ። ስለዚህ፣ የጆሴፈስ ጽሑፎች አዲስ ኪዳንን ለሚማሩ የቃሉ ተማሪዎች ጠቃሚ የመረጃ ምንጭ ናቸው።) ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጆሴፈስ የአይሁድ ጦርነት በተሰኘው የታሪክ ድርሳኑ መጽሐፍ 6 ምዕራፍ 5 ክፍል 2 እና 3 ላይ ያሰፈረውን ዘገባ እንመልከት፦
War 6:286 (6.5.2.286) እንግዲህ፣ በዚያን ጊዜ የተነሱ እጅግ በጣም ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ነበሩ፤ እኑርሱም በሕዝቡ ላይ ቀንበርን እንዲጭኑ በወቅቱ ተነስተው በነበሩ አምባገነን ገዥዎች የሚታገዙ ነበሩ። ህዝቡንም መዳንን ከእግዚአብሔር ይጠባበቁ ዘንድ በውግዘትና በእርግማን ያስፈራሩአቹው ነበር (ልክ ቃል እንዳላወጣብህ እንደሚሉት እንደ ዘመናችን ሟርተኞች ማለት ነው )፤ እነዚህ ሟርተኛ ነብያት ይህንን ያደርጉ የነበሩት ህዝቡ በከተማይቱና በሚኖሩባት ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋት ሸሽተው እንዳያመልጡ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህም በላይ፣ ከእነዚያ እየመጡባቸው ካሉ፣ ከሚፈሩአቸው እና ከሚያስጨንቋቸው ጠላቶቻቸው እንደሚታደጉአቸው እንዲህ ያሉ አሳሳች ተስፋዎችንም ይሰጡአቸው ነበር።
War 6:288 (6.5.3.288) ስለዚህ እነዚህ የተታለሉ ምስኪን ሰዎች፣ እነዚያ በግልጽ የሚታዩትን እና የወደፊቱን መጻኢ ጥፋት በግልጽ የሚተነብዩና የሚያመለክቱ ምልክቶችን አስተውለው ሳይከታተሉ ወይም ተገቢውን ዋጋ ሳይሰጡአቸው፣ ይልቁንም፣ በዓይኖቻቸው እንዳያዩ ታውረው፣ ወይም አእምሮ እንደሌላቸው ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ እያወረደባቸው ያለውን ያንን ሁሉ መዓት ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ የእነዚህ አታላዮች እና እራሱን እግዚአብሔርን የካዱ ነብያቶቻቸው ሰለባ ሆኑ።
War 6:289 (6.5.3.289) ስለዚህም በከተማይቱ ሰማይ ላይ ከፍ ብሎ የቆመና የተመዘዘ ሰይፍ የመሰለ ኮከብ እና አመቱን ሙሉ የቀጠለ የኮሜት አስፈሪ ትዕይንት ነበረ።
War 6:290 (6.5.3.290) እንዲሁም ደግሞ፣ ያ የአይሁድ ዓመፃ ከመቀስቀሱ በፊትና፣ ከጦርነቱ አስቀድሞ ከነበረው የህዝብ ቁጣና ግርግር በፊት፣ በዛንቲከስ [ኒሳን] ወር በስምንተኛው ቀን እና በዘጠነኛው ሰዓት ሕዝቡ እጅግ ብዙ ሆነው ወደ ቂጣ በዓል ወጥተው ነበር፣ ገና ሌሊትም ሳለ በቀን ጊዜ እንደሚያበራ ብሩህ እስኪመስል ድረስ ታላቅ ብርሃን በመሠዊያውና በቅዱሱ ቤት ዙሪያ አበራ፤ ይህም ብርሃን ለግማሽ ሰዓት ያህል በዚያ ቆይቶ ነበር።
War 6:291 (6.5.3.291) ይህ ብርሃን ለነዚያ በዚያ ተከማችተው ለነበሩ ላልተማሩ ሰዎች እንደ አንድ ጥሩ ምልክት ተደርጎ ይታይ ነበር፣ ቅዱሳት መጻህፍትን በሚመረምሩ በጸሐፍቱ ዘንድ ግን ወዲያውኑ በእነርሱ ላይ የተከሰቱትን የጥፋት ክስተቶች ለማስረዳት አስቀድሞ እንደተሰጠ የክፉ ነገር ምልክት ተደርጎ ተተርጉሞ ነበር።
War 6:296 (6.5.3.296) ከዚህም በተጨማሪ ከበዓሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ አርጤምስዮስ (ጂያር) በተባለው ወር ከወሩም በሃያ አንደኛው ቀን ይህ ምልክት በእነርሱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት እንደሚያሳይ በይፋ ተናገሩ።
War 6:297 (6.5.3.297) “አንድ አስደናቂ እና ሁሉንም ያስገረመ ክስተትም ታየ፤ ያንን ክስተት በአይኖቻቸው ያዩ ምስክሮች ባይናገሩት ኖሮ ታሪኩ ተረት ይመስላል ብዬ እኔ ራሴም ባልዘገብኩት ነበር።
War 6:298 (6.5.3.298) የታየውና ያንንም ተከትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች እንደዚህ አይነት ምልክቶች የሚገባቸው አይነት ተፈጥሮ ያላቸው ክስተቶች ነበሩ። ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሠረገሎችና በላያቸው ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ የታጠቁ የሰራዊት ጭፍሮችም በደመናው መካከል ወዲህና ወዲያ እየተሯሯጡ ከተማይቱን ሲከብቧት ታዩአቸው።
War 6:299 (6.5.3.299) ከዚህም በላይ በዓለ ኀምሳ በተባለው በዚያ በዓል፣ ካህናት እንደ ልማዳቸው፣ ቅዱስ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም በሌሊት ወደ ውስጠኛው [ወደ ቤተ መቅደሱ] ገብተው ሳለ፣ በመጀመርያ ለራሳቸው ብቻ የሚታወቅ መሸበርና ፍርሃት ይሰማቸው እንደነበሩ ሲገልጡ አስከትለውም ታላቅ ድምፅን ሰሙ።
War 6:300 (6.5.3.300) ከዚህም በኋላ በታላቅ ድንጋጤም ውስጥ ሆነው እየተንቀጠቀጡ የሰሙት ታላቅ ድምፅ "ኑ ከዚህ በኋላ ለቅቀን ከዚህ እንሂድ” የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ነበር።
2ኛ/ ኢውሳብየስ (በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ ክርስቲያን የታሪክ ጽሐፊ እና የቂሳርያ ቢሾፕ ነበር።) "የቤተክርስቲያን ታሪክ" በተሰኘ ባለ አስር ጥርዝ ስራው፣ መጽሐፍ 3፣ ምዕራፍ 8፣ ክፍል 1-6 እንደተዘገበው የጆሴፈስን ትረካ ምንጭ አድርጎ በስድስተኛው የታሪክ መፅሃፉ ላይ ያሰፈረውን ዘገባ እንመልከት፣ ቃሉም እንደሚከተለው ነው፦
94 “በዚህም ጊዜ ምስኪኑ ሕዝብ በአስመሳዮችና በሐሰተኛ ነቢያት ተሸነፈ፤ 95 ነገር ግን ሊመጣ ስላለው ጥፋት ያለውን ራእይና ምልክት አልሰሙም፤ አላከበሩምም። በተቃራኒው ግን፣ ልክ በመብረቅ እንደተመታ ሰው፣ ዓይንና ማስተዋል እንደሌላቸው ሆነው፣ የእግዚአብሔርን አዋጅ ናቁ።
በአንድ ወቅት የተመዘዘ ሰይፍ የሚመስል ኮከብ፣ በከተማይቱ ሰማይ ላይ ቆሞ ታየ፤ ዳግመኛም ከዐመፁ በፊትና ወደ ጦርነቱ ያመራውን ግርግር ከመጀመሩ በፊት አንድ ዓመት ሙሉ የፈጀ የኮሜት ትዕይንትም ታይቶ ነበር። ሕዝቡም ለቂጣ በዓል በተሰበሰበ ጊዜ፣ በ ዛንቲከስ ወር በስምንተኛው ቀን፣ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ፣ ታላቅ ብርሃን በራ። በመሠዊያው በቤተ መቅደሱ ሁሉ ብሩህ ቀን የሆነ ይመስል ነበር፤ ይህም ለግማሽ ሰዓት ያህል ቀጠለ። አላዋቂዎች የሆኑ ይህንን እንደ ጥሩ ምልክት አድርገው ወስደውት ነበር፣ ነገር ግን በጊዜው የነበሩ የቅዱሳት ጸሐፍት ተርጓሚዎች ጉዳዩን የተረዱት ከዚያ ወቅት ብዙም ሳይቆይ የተከናወኑትን እነዚያን ከባባድ ክፉ ክስተቶች እንደሚያመለክቱ አድርገው ነው።
በዚያም በዓል አንዲት ላም ለመሥዋዕት ልትቀርብ በሊቀ ካህናቱ ተመርታ በቤተ መቅደሱ መካከል ሳለች ድንገት ጥጃዋን ወለደች።
ከናስም የተሰራው፣ በብረትም በተሠሩ ምሰሶዎች ላይ ያረፈው፣ በመሬት ውስጥም የተተከሉ መወርወሪያዎች የነበሩት፣ በመሸም ጊዜ በሃያ ሰዎች ጉልበት በጭንቅ ይዘጋ የነበረው የውስጠኛው ቤተ መቅደስ ምስራቃዊ በር፣ ገና ከሌሊቱ ስድስተኛ ሰአት ሲሆን ድንገት በራሱ ተበርግዶ ሲከፈት ታየ።
ከበዓሉም ብዙ ሳይቆይ በአርጤምስ ወር ከወሩም በሃያ አንደኛው ቀን ለማመን የሚያስቸግር አንድ አስደናቂ ራእይ ታየ። ይህም ራእይ ራእዩን ካዩት ሰዎች ህይወት ጋር ካልተዛመደ እና በኋላም ራእዩን ተከትለው የተከሰቱት ጥፋቶች በእንደዚህ አይነት ተጨባጭ ምልክቶች የታዩ ባይሆን ኖሮ ጉዳዩ ተረት ሊመስል ይችል ነበር። ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሰረገሎችና የታጠቁ ጭፍራዎች በአየሩ ላይ ሆነው በየአገሩ ሁሉ በደመና ሲሽከረከሩ ከተሞችንም ሲከብቡ ታይተዋልና።
በዓለ ኀምሳ ተብሎ በሚጠራው በዓልም ካህናቱ እንደ ልማዳቸው በሌሊት ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ሥርዓተ አምልኮውን እየፈጽሙ ሳሉ፣ በመጀመሪያ ላይ የሆነ እንቅስቃሴ የመሰለ መታወክና ታላቅ የጩኸት ድምጽ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ "ኑ ከዚህ ለቀን እንሂድ" የሚል እንደ ብዙ ሕዝብ ያለ ድምፅ ተሰማ።
3ኛ/ ታሲተስ (ጆሴፈስ በኖረበት በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የኖረ ሮማዊ የታሪክ ምሁር እና ፖለቲከኛ ነበር።) Histories, Book 5:
ይህ ሕዝብ አጉል ለሆነ እምነት የተጋለጠ ነበር፣ ነገር ግን ደግሞ ሁሉንም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚጠላ፣ ሕጋዊ እንደሆነ በማይቆጠር መባና የመሥዋዕት ማስተስረያን የሚለማመድ ነበር። ያኔም በሰማይ ላይ ለጦርነት የሚንቀሳቀሱና እርስ በርሱ የሚቀላቀል የሰራዊት ጭፍራ፣ የእሳታማ ክንድ ብልጭታም ታይቷል፤ ቤተ መቅደሱም ከደመና ወጥቶ በመጣ ድንገተኛ ብርሃን ወጋገን ያበራ ነበር። የመቅደሱ የውስጠኛው በሮችም በድንገት ተበርግደው ተከፈቱ፤ ከሟች ሲቃ ቃና በላይ የሆነ ድምፅ "አማልክት ለቅቀው እየሄዱ" ነው የሚል ታላቅ ጩኸት ተሰማ። በዚያው ቅጽበትም ተለይቶ እንደሚሄድ አይነት የብዙ ህዝብ ግርግር ሆነ። ጥቂቶች በእነዚህ ክንውኖች ላይ አስፈሪ ትርጉም ሰጥተዋል፣ ዳሩ ግን በጥንታዊ የካህናቶቻቸው ትንቢታዊ መዛግብት ውስጥ ከምሥራቅ የሆነው ኃይል በዚህ ጊዜ እንዴት ኃያላን ሆነው እንደሚነሱ እና ገዥዎችም ከይሁዳ እንደሚመጡ፣ መላውን አለምም የሚገዛ ኢምፓየርም እንደሚነሳ ትንቢት ተጽፎ ነበር የሚል ጠንካራ እምነት ነበራቸው።
4ኛ/ ሴፈር ዮሲፖን (በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ የጥንቷ እስራኤል ታሪክ፣ ስራዎቹም የአይሁድ እምነትን እና የጥንቷን እስራኤልን ታሪክ ለሚመረምሩ ምሁራን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች አሉት) ከዕብራይስጥ ቋንቋ በስቲቨን ቢ ቦውማን የተተረጎመ ሆኖ፤ ከምዕራፍ 87 “የመቅደሱ መቃጠል” ከሚለው ዘገባ ላይ የተወሰደ።
ቬስፓሲያን ከመምጣቱ አንድ ዓመት በፊት፣ ልክ እንደሚያበራ አንድ ታላቅ ኮከብ ከሰገባው የተመዘዘ ሰይፍ የሆነ ትዕይንት በቤተ መቅደሱ ላይ ታየ። ምልክቱ በታየበት ጊዜ በነዚያ ቀናት የፋሲካ በዓል ነበር፤ በዚያም ሌሊት እንደ ቀኑ ብርሃን ሆኖ ሙሉ ቤተ መቅደሱ እንዳለ አበራ፣ቀኖቹም ሁሉም የፋሲካው በአል ሰባት ቀናት ነበሩ። የኢየሩሳሌም ሊቃውንት ሁሉ ይህ ክፉ ምልክት እንደሆነ ያውቁ ነበር፣ ነገር ግን የቀሩት አላዋቂዎች ይህ መልካም ምልክት ነው አሉ።
. . . ከዚህም በኋላ ሌሊቱን ሙሉ የአንድ ሰው የፊቱ ገጽታ በቅድስተ ቅዱሳን ላይ ከላይ ሆኖ ታየ፤ በውበቱም የሚመስለውም በምድር ሁሉ ላይ እንደ እርሱ ያለ ከቶ አልታየም፣ መልኩም እጅግ የሚያስፈራ ነበረ።
ከዚህም በላይ በዚያን ጊዜ የእሳት ሰረገሎችና ፈረሰኞች፥ ታላቅ ሠራዊትም ሆነው ወደ ሰማይ እየበረሩ እንደገናም ወደ ምድር ሲመጡ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ምድር ሁሉ ሲከብቡ፥ ሁሉም የእሳት ፈረሶችና የእሳት ፈረሰኞች ሆነው ሲመጡ ታዩ። በዚያም ወራት፣ የሻቩት በዓል በደረሰ ጊዜ ካህናቱ በሌሊት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያስተጋባ የሰዎችን ድምፅ የሚመስል ነገር ሰሙ፤ ሕዝቡም ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገቡ የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ነገር ሰሙ፤ የሚያስፈራና ታላቅ ድምፅም እየተናገረ፡ “ኑ፣ እንሂድና ከዚህ ቤት እንውጣ" ሲል ተሰማ።
5ኛ/ Pseudo-Hegesippus፣ (በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ ማንነቱ ያልታወቀ አይሁዳዊ ክርስቲያን ጸሐፊ ሲሆን፣ ስራውም በጆሴፈስ የተጻፈውን የአይሁድ ጦርነት የተሰኘ ስራ ከልሶ በ70 አ.ም ላይ ሮማውያን በኢየሩሳሌም ላይ ያደረሱትን ጥፋት ይዘረዝራል) ምዕራፍ 44። (ይህ በዋድ ብሎከር ከላቲን የተተረጎመ ሲሆን በቪንሴንቴ ኡሳኒ ከላቲኑ ትርጉም ተቀንጭቦ የተጠቀሰ ነው)፡-
የአይሁድ መጻሕፍት እንደ ገለጹት ከሆነ ከብዙ ቀን በኋላ ብዙዎች ያዩት እጅግ ታላቅ የሆነ ምስል እና ምልክት ታየ፤ ፀሐይም ገና ሳትጠልቅ ሠረገላዎችና የጦር ሠራዊቶች በደመና ውስጥ ይታዩ ነበር፤ በዚያም የይሁዳ ሁሉ ከተሞችና ግዛቶቿ ሁሉ ተወርረው ነበር። በዓለ ሃምሳ የተባለው በዓል በሚከበርበት ወቅት ካህናቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል በሌሊት ሲገቡና የተለመደውን የዘወትሩን መስዋዕት ሲያቀርቡ መጀመሪያ ላይ የተወሰነ እንቅስቃሴ እና ድምፅ እንደተሰማቸው ራሳቸው አረጋግጠው መስክረዋል። ድምጹም በድንገት "ከዚህ ተሻግረን እንሄዳለን" ብሎ ይጮኽ ነበር።
ሌላ ተጨማሪ ላካፍላችሁ፦
6ኛ/ “ቤት ኮል” እና የቤተ መቅደሱ ጥፋት በ70 ዓ.ም።
[ቤት ኮል፣ ቃሉ የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም "የድምፅ ሴት ልጅ" ወይም "የመለኮት ድምፅ አስተጋባች" እንደ ማለት ነው። እሱም የሚያመለክተው በአይሁድ ምሥጢራዊ ልምምድ እና በትውፊታቸው ውስጥ የሚንጸባረቀውን የመንፈሳዊ ግንኙነት ዓይነት ነው። ይህም ከሰማይ የመጣ ድምጽ በግለሰቦች የሚሰማበት ልምምድ ነው። ዳሩ ግን በተፈጥሮው ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ከሚገናኙበት የጸሎትና የአገልግሎት ልምምድ የተለየ ነው። ነገር ግን እንደ መለኮታዊ ተመስጦ ሊቆጠር የሚችል መንፈሳዊ ልምምድ ነው። ቤት ኮል በነቢያት የተሰማውን እና በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበውን ሰማያዊ ድምጽ ሊያመለክትም ይችላል። በአይሁድ ሮም ጦርነት ወቅት ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ በቀጥታ ለኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎች ይሰማ የነበረ ድምጽ ነው።]
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የይሁዳ ክህደት በነበረበት ወቅት፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል የክብር ደመናው ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ወደ ምሥራቅ ወደ ደብረ ዘይት ሲሄድ አይቶ ነበር (ሕዝ. 10÷ 18-19፤ 11፥ 22-23)። በኋላም፣ ስለ አዲሲቱ እየሩሳሌም ባየው በራዕዩ፣ የክብር-ደመናው ወደ አዲሱ ቤተ መቅደስ፣ ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ ሲመጣ ደግሞ አይቷል (ሕዝ. 43፥ 1-5)። ይህም ራእይ የተፈጸመው ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር ከደብረ ዘይት ወደ አባቱ በደመና ሲያርግ (ሉቃስ 24፥ 50-51) እና በ30 ዓ.ም አካባቢ በበዓለ አምሳ ቀን- ቤተክርስቲያኑን እንዲሞላ መንፈሱን በላከ ጊዜ ነው።
በኋላም የዚህ የእግዚአብሔር ክብር ሽግግር አምሳል በአይሁድ ታሪካዊ ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። በ66 ዓ.ም በበዓለ አምሳ ዕለት፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያሉ ካህናት ገና ተግባራቸውን እየተወጡ ሳሉ፣ “ከዚህ እንሄዳለን!” እያለ የሚጮኽ ትላቅ ድምፅና “የሃይለኛ ግርግርና ሁካታ” ተሰማ።
ይህ በ66 ዓ.ም. በበዓለ አምሳ ዕለት መለኮት ከቤተ መቅደሱ የመውጣቱ ሁኔታ፣ ልክ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው በመጀመሪያው የክርስቲያን ጴንጤቆስጤ ላይ መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሐዋርያት እና ለሌሎች በኃይል በይፋ ከተሰጠ ከ36 ዓመታት በኋላ፣ አሁንም እንደገና ልክ በጰንጠቆስጤ ቀን፣ እግዚአብሔር ራሱ የኢየሩሳሌምን ቤተመቅደስ ትቶ እንደሄደ የተሰጠ ምስክርነት ነው። ይህ ማለት እግዚአብሔር ከተለየው በኋላ ቤተ መቅደሱ አሁን የተቀደሰ መቅደስ አይደለም፣ ሕንጻውም ከማንኛውም ዓለማዊ ሕንጻ የበለጠ የተቀደሰና የተለየ አይደለም ማለት ነው። መለኮት በይፋ አድሮበት የነበረውን ቤት በይፋ ተወው።
በሚያስደንቅ ሁኔታ በዚህ ጊዜ [በ66 ዓ.ም.] የእግዚአብሔር ሼክናህ ክብር ቤተ መቅደሱን ለቆ ወጥቶ በደብረ ዘይት ላይ ለ3 ዓመታ ከመንፈቅ እንደቆየ አይሁዶች ያንን እንደተገነዘቡት የአይሁድ ጽሑፎች ይገልጻሉ። በዚህ ወቅት አይሁድ ከሥራቸው ንስሐ እንዲገቡ የሚለምናቸው ድምፅ ከደብረ ዘይት አካባቢ ተሰምቷል (ሚድራሽ - ሰቆ. 2፡11)። ይህም በክርስትና ታሪክ ላይ አስገራሚ ተጽእኖ አለው፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እንደተሰቀለ እና እንደተነሳ ስለምናውቅ ነው፣ - የአይሁድ መዛግብት እንደሚናገሩት ከሆነ የእግዚአብሔር ሼክናህ ክብር በ66 አ.ም ላይ በጰንጠቆስጤ ዕለት ከቤተ መቅደሱ ከወጣ በኋላ፣ ለ3 ዓመት ከመንፈቅ እንደቆየ ትክክለኛውን የጊዜ ክልል ያመለክታሉ። አይሁድም ያላቸው የማመሳከሪያ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ ሮማውያን በ70 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ላይ ከፈጸሙት የመጨረሻ ወረራ አስቀድሞ ከሼክናህ ክብር የተሰጠውን ይህን ማስጠንቀቂያ ("ቤት ኮል" ብለው የሰየሙትን የእግዚአብሔር ድምፅ) እርሱም ምድርን ትቶ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ አይሁድ አልሰሙም ይላል።
ከክርስቲያኖች መካከል ማንም ቢሆን፣ በ66 ዓ.ም ከሆነው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ከቤተ መቅደሱ ጋር የተያያዙትን እነዚህን ግልጽ ተአምራዊ ምልክቶች አክብሮ የሚመለከት ሰው፣ ህንጻው በያዘው ውቅር ከአሁን በኋላ የእግዚአብሔር ቅዱስ መቅደስ እንደማይሆን ማመን ይችላል። ጆሴፈስም ራሱ እንኳ "መለኮት ከቅዱሳት ስፍራ ሸሽቶ" (Wars, 5.412) ከመውጣቱ የተነሳ፣ እግዚአብሔር “ከመቅደሱ ርቋል” ብለው የሚያምኑትን የብዙ ሰዎች እምነት ጠቅለል አድርጎ አቅርቦታል (Wars 2.539)።
7ኛ/ ከሌላ ተጨማሪ ምንጮች፦
እነዚህ ክንውኖች ያኔ በአይሁድ አእምሮ ውስጥ ከፍተኛውን ስፍራ ይዘው በነበሩበት ወቅት፣ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ሲጽፍ፣ "ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፦ ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤" (ራእይ 21፥ 9-11) በማለት፣ ያ የእግዚአብሔር ክብር የሆነው ሼክናህ፣ በእውነተኛይቱ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ማለትም የክርስቶስ ሙሽራ በሆነችው የፍጻሜው ገነት በከተማይቱ ላይ ያረፈ መሆኑን ገልጿል።
የያህዌህ “ሼክናህ” በመሲሑ የሕይወት ዘመንና በሞቱም ጊዜ ሁሉ እና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ በደብረ ዘይት ላይ ሲወርድ እስከታየበት ጊዜ፣ ማለትም እስከ 66 ዓ.ም. ድረስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆይቷል።
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ደብረ ዘይቱ ተራራ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳደረባቸው ሌላም ምክንያት አለ። ይኸውም በቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይታመን የነበረው ሼክናህ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዶ በዚያ ስፍራ ላይ ሰፍፎ ሲያንዣብብ የነበረው በ70 ዓ.ም በተጠናቀቀው የሮም/አይሁድ ጦርነት ወቅት ነው። ሼክናህ የሆነው የእግዚአብሔር ክብር ያንን አሮጌውን ቤተመቅደስ ትቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ከፍታ ላይ መውጣቱ [የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊና ምሁር ለነበረው፣ ከ260-340 ዓ.ም ለኖረው] ለኤውሳቢየስ በጣም አስፈላጊና ትልቅ ክስተት ነበር። (ኧርነስት ኤል. ማርቲን "የጎልጎታ ሚስጥሮች"፣ ሲል በአልሃምብራ፡ ካሊፎርኒያ በ1988፡ ያሳተመውን መጽሐፍ ገጽ 83 ላይ ይመልከቱ)
8ኛ/ ኤውሳቢየስ "Proof of the Gospel" በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ይህንን ምንባብ እናገኛለን
በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ከዓለም ዳርቻ ይሰበሰባሉ፣ ይኸውም እንደ ቀድሞው ዘመን ስለ ኢየሩሳሌም ክብር ወይም በኢየሩሳሌም ከተማ በታነጸው በጥንቱ ቤተ መቅደስ ሊሰግዱ ሳይሆን ይልቁንም... የእግዚአብሔር ክብር [የያህዌ የሼኪናህ ክብር] ከቀደመችው ከተማ ወጥቶ ወደፈለሰበት ከከተማይቱ አንጻር በምትገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ይሰግዱ ዘንድ ነው። (Book VI, Chapter 18 (288))
እንደ ኤውሳቢየስ አባባል “ሼክናህ” የሆነው ክብር ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሰፍፎ ያንዣበበው “ኢየሩሳሌም ስትከበብ” (ከ66 እስከ 70 ዓ.ም.) ነው። ሆኖም፣ “ሼክናህ” የሆነው ክብር መቅደሱ በጦርነቱ ማብቂያ ከመፍረሱ በፊት ቤተ መቅደሱን ለቆ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሰፍፎ እንዳንዣበበ የጠቀሰው ኤውሳቢየስ ብቻ አልነበረም። የኢየሩሳሌም ጥፋት የዓይን ምስክር የነበረው ዮናታን የሚባል አይሁዳዊ መምህርም (ራባይ) -- "ሼክናህ" ክብር ለሦስት ዓመታት ተኩል ቤተ መቅደሱን ለቅቆ ነበር ብሏል።
እስራኤል ንስሐ እንዲገቡ ተስፋ በማድረግ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አደረ፣ እነርሱ ግን እምቢ አሉ፤
"እናንተ ከዳተኞች ልጆች ተመለሱ" [ኤር. 3፥ 14]፤ "ወደ እኔ ተመለሱ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ" (ሚል. 3፥ 7) እያለ፣ ቤት ኮል ሲሉ የሚጠሩት ያ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነ ድምፅ] ከሰማይ መጣ፤ ያኔም "ንስሐም ባልገቡ ጊዜ፡— ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ" (ሆሴዕ 5፥ 15)፣ አለ። (Midrash Rabbah, Commentary on Lamentations 2:11). -- Secrets of Golgotha, by Ernest L. Martin. 84.
ከሮማውያን ጋር ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደሱ በመውጣት ተለይቶ የሄደውን “ሼክናህ” የተሰኘው የያህዌን ሃልዎት እውነታ የጻፈ ሌላም ጸሐፊ ነበር። ጆሴፈስ በ66 ዓ.ም የጸደይ ወቅት በቤተመቅደስ ውስጥ አንዳንድ አስገራሚ ክስተቶች እንደተከሰቱ በዘገባው ጠቅሷል። ሲጽፍም ከያህዌህ “ሼክናህ” እና ከቤተ መቅደሱ ጋር የተያያዙ ሦስት ተአምራትን ዘግቧል -- በእያንዳንዱም ዘገባው "ሼክናህ" ከቅድስተ ቅዱሳኑ ወጥቶ እየተለየ እንደነበር በግልፅ አሳይቷል።
War 6. 290 እንደሰፈረው፣ በ66 ዓ.ም. ከፋሲካ በዓል በፊት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ “ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል የቆየ ታላቅ ብርሃን በመሠዊያው ላይ አበራ፣ አስከትሎም ከዚያ ወጥቶ ሄደ። ሲናገርም፣ "የአይሁድ ቅዱሳን ጸሐፍት ይህንን ምልክት አስመልክቶ ሲናገሩ ለቤተ መቅደሱ መጻኢ እድል መጥፎ ምልክት አድርገው ተርጉመውታል" ብሏል። ልክ በምድረ በዳ ሳሉ የማደርያውን ድንኳኑን ነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ሲያጓጉዙ እንደነበረው ሼክናህ የሆነው ክብርም ከማደሪያው ርቆ ሲሄድ ነበር ።
ጆሴፈስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል “ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ (በፋሲካ በአል ወቅት) ሃያ ሰዎች ሆነው በጉልበ የሚከፍቱትና የሚዘጉት ግዙፍ የኒካኖር የናስ በሮች ገና መንፈቀ ሌሊት ሳለ በራሳቸው ፈቃድ ተበርግደው ተከፈቱ። (War 6. 293-295)። ይህም ክስተት ደግሞ በቤተ መቅደሱ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንደሚያሳይ ተተርጉሟል። ከዚያም፣ ከሃምሳ ቀናት በኋላ ቆየት ብሎ፣ በበዓሉ አምሳ ዕለት፣ ሌሎቹ ምልክቶች እንደሚያሳዩት የሼክናህ ክብር ቤተ መቅደሱን እየለቀቀ መሆኑን የሚያሳይ የመጨረሻው ምልክት ተሰጠ።
ከዚህም በላይ በዓለ ሃምሳ እየተባለ በሚጠራው በዓል ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም እንደ ልማዳቸው ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ፣ ያኔ በመሸ ጊዜ፣ ግርግርና ጩኸት መኖሩን በመጀመሪያ እንዳወቁና ከዚያም በኋላ "ኑ፣ ከዚህ እንሄዳለን" ሲል የብዙ ሕዝብ ድምፅ የሚመስል እንደሰሙ ዘግቧል (War 6. 299)።
የጆሴፈስን መረጃ ሌላው የዓይን ምስክር የነበረው ራባይ ዮናታን ነው፤ የዚህ ሰው ምስክርነት በጥንቷ እስራኤል ስለተፈጸሙ ክንውኖች የበለጠና የተሟላ ግንዛቤን ይሰጣል። የጆሴፈስን መረጃ ከዚህ ሰው ምስክርነት ጋር አጣምረን ስንመለከተው ከፀደይ ወራት 66 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 69 ዓ.ም አካባቢ፣ ቤተ መቅደሱ በሮማውያን ከመፍረሱ ከስምንት ወራት በፊት ለሦስት አመት ተኩል "ሼክናህ" የሆነው ክብር በቀጥታ ወደ ደብረ ዘይት ሄዶ ከተራራው ጫፍ ላይ - እንደቆየ፣ ከዚያም ወደ ሰማይ ተመልሶ እንደሄደና ይህ የራባይ ዮናታን ምክርነት እስከ ተጻፈበት ጊዜ ድረስም ወደ ምድር እንዳልተመለሰ እናያለን።
¶ የዳግመኛ ምጽአቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክሮች፦
የሰው ልጅ (ኢየሱስ) አስቀድሞ እርሱና ሐዋርያቱ እንደተነበዩት የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ያኔ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በክብር መጥቷል፡- ማቴ 13፥ 41-43፤ 16፥ 27-28፤ 24፥ 29-31፤ 25፥ 31፤ ማርቆስ 8፥ 38፤ 9፥ 1፤ 13፥ 26-27፤ ሉቃስ 9፥ 26-27፤ 1 ተሰ 4፥ 13-18፤ 2 ተሰ 1፥ 4-10፤ ይሁዳ 14-15
¶ እነዚህ ሁሉ ነገሮችም የሚጠበቁትና የሚፈጸሙት ደግሞ ራሱ ኢየሱስ በነበረበትና በሐዋርያቱ ትውልድ ውስጥ እንደነበር አዲስ ኪዳን በግልጽ ያስተምራል፦ ማቴ 11፥ 16፤ 12፥ 38፣ 41-45፤ 16፥ 4፤ 23፥ 36፤ 24፥ 34፤ ማርቆስ 8፥ 38፤ 9፥ 1፤ 13፥ 30፤ ሉቃስ 7፥ 31፤ 11፥ 29-32፣ 50-51፤ 17፥ 25፤ 21፥ 32፤ የሐዋርያት ሥራ 2፥ 40፤ ፊል 2፥ 15፤ ዕብ 3፥ 9-11።
ጥቂት መጻሕፍት ልጠቁማችሁ፦
- The New Complete Works Of Josephus, Translated by William Whiston.
_ Eusaebius, The History of the Church
- Mason, Steve. Josephus and the New Testament
- Stevens, Edward E. Final Decade Before the End. Jewish and Christian History Just Before the Jewish Revolt.
- Barrett, C.K. The New Testament Background: Selected Documents.
- Bruce, F.F. Israel and the Nation.
- Bruce, F.F. New Testament History.
- Gentry, Kenneth L., Jr. Before Jerusalem. Fell.