Friday, April 15, 2022

የአሁኑ እና የሚመጣው ዘመን

"የአሁኑ" እና "የሚመጣው" ዘመን

የአሁን ዘመን

በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ (1ቆሮንቶስ 2፥ 6-8)

መጽሐፍ ቅዱስን በአውዱ፣ በቋንቋው፣ በታሪካዊነቱ ለመተርጎም ከመትጋት የሚታክቱ፣ ይልቁንም እድሜ ዘመናቸውን ሲሰሙትና ሲመስላቸው በኖረው ልማዳዊ አመለካከት ብቻ የሚያስቡና ያንን የመረጡትን አስተምህሮ እንዲድግፍላቸው ጥቅስ ብቻ የሚፈልጉ፣ ከዚህም በላይ እምነታቸውን ለመጠየቅ የሚፈሩና አቅም የሌላቸው ወገኖች፣ እንዲህ ያለውን ጥቅስ ሲያነቡ በተለይ የዚች ዓለም የሚለውን ሃረግ በቀጥታ ከዚህ ግዑዝ አለም ጋር አገናኝቶ በመረዳት ለራሳቸው ሲሳሳቱና ሌሎችንም ሲያሳስቱ ይስተዋላል። ወደ በኩረ ቋንቋውና ወደ ተለያዩ ትርጉሞች ግን ስንመለከት ጉዳዩ ከአንድ የተለየ ዘመን ጋር እንጂ ከዚህ ነባራዊና ተዳሳሽ ግዑዝ ዓለም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እናስተውላለን። በአማርኛችን ዓለም በKJV world ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ትርጉሞች ውስጥ እንዲገባ የተደረገው ቃል ከበኩረ ቃሉ ጋር የማይስማማና ትክክለኛውን ትርጉም የማይመጥን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም እምነትን የሚያሳስት እንደሆነም ጭምር በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። እኛ በቋንቋችን ዓለም የምንለውን የግሪኩ ቃል cosmos ሲል ይጠራዋል፣ ቃሉም ጥቅም ላይ በዋለበት ስፍራ ሁሉ የሚወክለው ይህንን ግዑዝ ዓለምና በውስጡ ያለውን ሁሉ ነው። ነገር ግን እዚህ ጥቅስ ላይ እና በበርካታ ሌሎች የንባብ ክፍሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ባዘጋጁአቸው ቅጅዎች በግሪኩ ዓለም ወይም cosmos የማይለውን ሁሉ ያለጥንቃቄ ዓለም ወይም world  ሲሉ ተርጉመውታል። ለአውደ ምንባቡ የሚመጥነውና ትክክለኛ የሆነው የግሪክ ቃል ግን aion የተሰኘው ነው፣ ትርጉሙም ዘመን የሚል ነው። cosmos እና  aion በተሰኙት ቃላት መካከል ግዙፍ የትርጉምና የጽንሰ ሀሳብ ልዩነት እንዳለ አለመረዳት ደግሞ ለተንሸዋረረ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት ይዳርጋል። በስትሮንግስ የግሪክ ቃላት መፈለጊያ #165 aion ለሚለው ቃል የተሰጠው ማብራርያ ይመለከቷል፦  

የግሪኩ aion ዘመን ማለት ሲሆን የሚያመላክተውም አንድን የተወሰነ ዘመን ነው፣ የአሁኑ ዘመን ሲል የአሁድን አሮጌ የሙሴ ዘመንን ማለቱ ሲሆን፤ የሚመጣው ዘመን ሲል ደግሞ የወደፊቱን መሲሃዊ ዘመን የሚያመለክት ይሆናል። ይህ ዘመን እርሱም የአሁኑ ዓለም በተለይ የአይሁድን ዓለም የሚያመለክት ሲሆን፣ ውክልናውም የሙሴ ስርዓት ይሰለጥናበትና ሞት ይገዛበት ለነበረው አላፊና ጊዜአዊ ለሆነው፣ ዘላለማዊነትም ለሌለው የሕጉ ዘመን ነው። መጻኢ ሆኖ በአይሁድ ሲጠበቅ የኖረው ደግሞ (ለእነርሱ) የወደፊቱ አለም እንደሆነ የሚቆጠረው፣ መሲሐዊው ዘመን፣ ዘላለማዊው መንግስቱ ነው፣ እርሱም ለአለምና ለዘለዓለም ማለቂያ የሌለውን የጸጋ ዘመን ያመለክታል።

እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? (ሉቃስ 12፥ 56)

ይህ ዘመን የተሰኘው ሀረግ የሚያመለክተው ከ70 ዓ.ም በፊት የነበረውን ዘመን ነው። ይኸውም ከአሮጌው ኪዳን በታች ተገዝቶ የኖረው የአይሁድ ዘመን ነው። ክርስቶስ የተሰቀለው፣ የአይሁድ ገዦችና የማያምኑ ሁሉ ከኢየሩሳሌም ከተማ እና ከመቅደሱ ጋር በ70 ዓም ተደምስሰው እንዲጠፉ የተደረጉት ይህ ዘመን እየተባለ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው። ይህ ዘመን እየተባለ በሚጠራው ዘመን መጨረሻ ላይ በዳግመኛ ምጽአቱ ፍርድ ይሆናል። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል (ማቴዎስ 13፥40) ይህ የአለም መጨረሻ የፕላኔት ምድር መጨረሻ፣ የሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ፈጽሞ አይደለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ ይህ ግዑዝ ተዳሳሽ አለም መጨረሻ እንዳለው የሚያስተምር ጥቅስ ማግኘት አይቻልም። በሀሰተኛ አስተማሪዎቻችን ሟርት ከተሰራጨው የሀሰት ንግርት በቀር  እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ የለገጠው ይህንን ተዳሳሽ አለም የማሳለፍና የማጥፋት ምንም እቅድ የለውም። ይልቁን ግን ይህ የአለም መጨረሻ የተሰኘው ሀረግ የሚያመለክተው መጨረሻ የተመደበለትን የአይሁድ አለም እርሱም አሮጌው የሙሴ ሥርዓት ማብቂያን ነው። አዲሱን አለም እርሱም አዲሱን ኪዳን ለማምጣት አሮጌ ለሆነው ለዚህ አለም ማለትም ለአሮጌው ኪዳን የተመደበለትን ፍርድ ቃሉ ሲያስተምር፦ አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል (ዕብራውያን 8፥ 13) ይላል። ይህ ፍርድ የሚከናወነውም በ70 ዓ.ም ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ በፓሮዥያው ነው።

ደቀመዛሙርቱ በደብረዘይት ተራራ ላይ ለብቻቸው ወደ ኢየሱስ ቀርበው የጠየቁት ጥያቄ የመምጣቱና  የዘመኑ ፍጻሜ ምልክት ምን እንደሚሆን ነበር (ማቴዎስ 24፥ 3)። በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ይህ ዘመን የሚባለው፣ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፓሮዥያው የሚደመደመው አሮጌው የአይሁድ ዘመን ነው። ፍጻሜውንም ያገኘው በ70 ዓ.ም ላይ ኢየሩሳሌምንና ቤተመቅደሱን በማፈራረስ ነው። ይህ ሁሉ ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ ትውልዳቸው እንደማያልፍ ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሲል አረጋግጦ ነግሮአቸዋል (ማቴዎስ 24፥ 34)። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው፣ አይሁድም በቅዱሳት መጻህፍቶቻቸውና በነብያቱ አቡቀለምሲሳዊ ንግሮቻቸው የሚያውቁት የአለም ፍጻሜ፣ ቤተመቅደሱና ቅድስት ከተማቸው ኢየሩሳሌም የሚደመሰሱበት፣ የሙሴ ዘመን ማብቂያና ፍጻሜ ነው እንጂ፣ ብዙዎች እንደሚመስላቸው የፕላኔት ምድር እና የሰማይ መጥፋት፣ የሰው ልጅ ታሪክ ማክተም ጨርሶ አይደለም።

ክርስቶስ በፓሮዥያው በ70 ዓ.ም የሚመጣው በዘመኑ መጨረሻ የቅዱሳኑን ድነት ፍጹም  አድርጎ ሊያጠናቅቅ ነው። በዳግመኛ ምጽአቱም እጅግ ከመጠን በላይ ሥደትን እየተቀበሉበት ከነበረው ከዚያ ክፉ ከሆነ የአይሁድ ዘመን (ዓለም) ቅዱሳኑን ያድናል።

ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ገላትያ 1፥ 3-4

የሚመጣው ዘመን

በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። ማቴዎስ 12፥ 32

የሚመጣው ዘመን የሚለው የሚያመለክተው ከ70 ዓ.ም በኋላ ያለውንና ማለቂያ የሌለውን የአዲስ ኪዳን ወንጌል፣ የመንግስት ዘመን ነው። መንግስቱም በክርስቶስ ቤዛነት አምነው ዳግም የተወሉዱትን ክርስቲያኖች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውን ድነታቸውን ጠቅልሎ የያዘ መንፈሳዊ መንግስት ነው። እነሆ ከተጀመረ ከሁለት ሺህ አመታት በላይ ተቆጥሮአል እንጂ በርካታ መጻአኢያን እንደሚያስተምሩት ገና የሚጠበቅና እስካሁን ያልተጀመረ መንግስት የለንም። ጌታችን ኢየሱስም በመንግስቱ የሚገዛው ንጉሰ ነገስት ነው፤ ኢየስሱ በአባቱ ዙፋን ቀኝ ሰማዩንና ምድሩን ሁሉ እየገዛ ነግሷል፤ አሁን እና ለዘላለም የነገሰ እንጂ ገና ወደፊት መንገስን የሚጠባበቅ አልጋ ወራሽ የለንም።

በተጨማሪም ይህ የሚመጣው ዘመን ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠራው የዘመን ክፍል ከ70 ዓ.ም በኋላም ቢሆን እንኳ፣ አምነው የዳኑ የእግዚአብሔር ምርጦችም ይሁኑ ወይም ገና በክርስቶስ ማመንን ገፍተው ያልዳኑና ያልተመረጡም ቢሆኑ እንኳ፣ በምድር ላይ በአካል የሚኖሩበት ዘመን ነው። ወደ አዲሱ ኪዳን መንፈሳዊ መንግስት እያንዳንዳቸው በግላቸው በክርስቶስ አምነው የገቡ የእግዚአብሔር ምርጦች ግን፣ በቅድስት ጥምቀት አማካኝነት በሚታደል መንፈሳዊ ልደት በጸጋው በኩል የገቡ ሁሉ ናቸው።

አሁንም ገና በዚህ ህይወት እያሉ ይቅር የማይባለውን ኃጢአት በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚፈጽሙ ከመንፈሳዊው መንግስት ውጪ የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ የሚኖሩ እስከሆነ ድረስ ይህ የሚመጣው ዘመን ተብሎ የሚጠራው የዘመን ክፍል ሰማይ ማለት አይደለም። ይልቁንም ይህ የሚመጣው ዘመን ከ70 ዓ.ም በኋላ ያለውና፣ እኛ የሰው ልጆች በአካል በምድር ላይ አሁን በሥጋ እየኖርንም እንኳ በመንፈስ የሚሰራና የሚገዛ  የመሲሁ ዘመን ወይም የመንግስት ዘመን ተብሎ ይጠራል።

ከ70 ዓ.ም በኋላ ያሉ ዳግም የተወለዱ አማኝ የእግዚአብሔር ምርጦች በሙሉ በዚህ የሚመጣው ዘመን ተብሎ በሚታወቀው የመሲሁ መንግስት በክርስቶስ ያለውን የዘላለም ሕይወት በሙላት ተቀብለዋል፤ እርሱም አሁን ነው። እያንዳንዳቸውም ለአዲስ ልደት ሲጠመቁ ያኔውኑ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ሲሆኑ፣ በግላቸውም በአዲሱ ኪዳን ወንጌል የሚመላለሱና በመንፈሳዊው መንግስት ውስጥ የሚያገለግሉ የእግዚአብሔር ካህናት ናቸው። እርሱም፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው። (ሉቃስ18፥ 29-30)። የተቀበልነው የዘላለም ሕይወት አሁን ነው፣ ስለዚህ ያ የሚመጣው አለም ሲባልና ሲጠበቅ የነበረው የመንግስት ዘመን መጥቶአል ማለት ነው። የዘላለም ሕይወት የዚህ የሚመጣው አለም ስጦታ መሆኑ እርግጥ ከሆነ፣ በርካታ መጻኢያን እንደሚያስተምሩት ይህ አለም ደግሞ ገና ካልመጣ፣ እንግዲያውስ የዘላለምን ሕይወት ገና አልተቀበልንም፣ አሁንም ገና በአሮጌው ኪዳን ስር እንኖራለን ማለት ነው፤ አሮጌው ኪዳን ደግሞ ይገድለናል እንጂ  በሕይወት አያኖረንም። አሳዛኙ ነገር አሮጌው ኪዳንም እንኳ ሊያስመካን አለመቻሉ ነው፣ ምክንያቱም በፍጥረት አህዛብ እንጂ አይሁድ ባለመሆናችን ለእነርሱ ከተሰጠው የሙሴ ሥርዓትና ከኪዳናቸው ምንም ድርሻ የለንምና። አሁን ግን ሲጠበቅ የነበረው ይህ የሚመጣው አለም የተሰኘው ዘመን በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት እነሆ ደርሶአል። የመሲሁም መንግስት መግዛት ጀምሮአል። እኛም በእምነት በኩል በጸጋው እየኖርንበት ነው። ከክርስቶስ ጋር በመንግስቱ ስንኖርም ዘላለማዊው ጥሪአችንና ተልዕኮአችን በክርስቶስ እውቀት እያደግን፤ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ፤ ወንጌልንም በማዳረስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን እንድናፈራና ሌሎችን በክርስቶስ እውቀት እንድናሳደግ ነው። መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን (ዕብራውያን 6፥ 5) ተብሎ እንደተጻፈ፣ መንፈሳዊውንና ሊታይ የማይችለውን፣ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የቀመሱትንና ለእነርሱ ሊመጣ ያለው እየተባለ የተጠበቀውን፣ እኛም በዳግመኛ ምጽአቱ በሙላት የገባንበትን የክርስቶስን መንግስት መንፈሳዊ የሆነውን የጽድቅ ተጽእኖ በፍጥረቱ መካከል የምናደርገውም በዚህ ተልዕኮና ጥሪ በኩል ነው።

(gkr)

No comments:

Post a Comment