Monday, October 11, 2021

ሞት ድል በመነሳት ተውጧል

ሞት ድል በመነሣት ተውጧል 

በዚህች ጥፈት፣ ከዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው በፊት እና ከዚያ በኋላ ባለው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ፣ የሙታንንና የሕያዋንን መዳረሻ አስመልክቶ ግልጽ መሆን ያለባቸውን ጉዳዮች ላካፍላችሁ መልካም ሆኖ ታይቶኛል። በቃሉ መንገድ የምታስቡ ጥቂቶች ያይደላችሁ እና እምነታችሁን የምትጠይቁ በርካቶች እንደምትጠቀሙበት፣ እንደምትጽናኑበትና፣ እንደምትሞገቱበት አስባለሁ። መልካም ንባብ።  

"ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም።…. ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።" (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 50፣ 53-54)

፩. ሟች አባቶች ከፓሮውዥያው አስቀድሞ
1)ገና የእስራኤል ታሪክ ሳይጀመር በፊት፣ በነበረው ርዥም የአባቶች የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አማኞች ሁሉ፣ በበርካታ ጊዜያት ከተገለጡ ጥንታዊ ኪዳናት አንጓዎች ስር ተካፋይ የነበሩ ናቸው። ለምሳሌ፦ አዳማዊ ቃል ኪዳን፤ የኖህ ቃል ኪዳን፤ አብርሃማዊ ቃል ኪዳን፤ የሙሴ ቃል ኪዳን ወዘተ እያልን ልንጠቅሳቸው እንችላለን። ከአዳም እስከ አብርሃም ዘመን ያሉት ሁሉም የተመረጡ አማኞች ልዩ ልዩ የምድር ህዝቦች  ነበሩ፣ እስራኤል ዘሥጋ ያኔ ገና አልነበረም። ሟቾች የዚያን ዘመን አባቶች ሁሉ በተስፋ ሞተው በሚቀበሩበት ጊዜ ከሥጋቸው ተለይተው ያለ ተዳሳሹ አካልና፣ ደም፣ ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ይሄዱ ወይም ይወሰዱና ይከማቹ የነበረው ሼዖል ወደተባለ ስፍራ (ወደሀደስ) ነበር። ተስፋቸውም በፍጻሜ ዘመን ላይ በሙታን ትንሳኤ ከዚያ ከተከማቹበት ሼዖል ወጥተው ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት ይገቡ ዘንድ ነበር። 

2)ከክርስቶስ የመስቀል ሞቱ አስቀድሞ፣ ማለትም ከአብርሃም እስከ ክርስቶስ ያሉ አባቶች አብዛኞቹ የተመረጡ አማኞች፣ ደግሞ በአመዛኙ ከአይሁድ ወገን የነበሩ ናቸው። ቃል ኪዳኑም ከአብርሃም ጋር ነበር፣ የቃል ኪዳኑ ህዝብ ዘሩም እስራኤል ነበር። ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጣቸው ኪዳንም ብሉይ ኪዳን ነው። እነርሱም በተስፋ በሚሞቱበት ጊዜ ከሥጋቸው ተለይተው ያለ ተዳሳሹ አካልና፣ ደም፣ ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት የሀደስ የእረፍትና የመጽናኛ ዞን ብለን ወደምንጠራው አብርሃምና አባቶች ሁሉ ወዳሉበት "ሀደስ ገነት" ወይም "የአብርሃም ዕቅፍ" ወደሚባለው ስፍራ ሄደው ከአባቶቻቸው ጋር ይከማቻሉ። በዚያም ክርስቶስ በእርገቱ ማርኮ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ የሚቀበሉትን ትንሣኤ ሊጠባበቁ ወደሰማያዊው መቅደስ የደጁ አደባባይ ወዳለው ሥፍራ እስኪወስዳቸው ድረስ፣ ከዚያ የሼዖል እስራት ነጻ የሚያወጣቸውን  መሲሁ ኢየሱስን እየተጠባበቁ ይቆያሉ (ዮሐንስ 20፥ 17) 

3) ከመስቀል እና ከትንሣኤው አንስቶ  በ70 አ.ም ላይ እስከተፈጸመው ዳግመኛ ምጽአቱ ድረስ ባለው መካከኛ ጊዜ በነበረው የሽግግር ወቅት፣ እነዚያ ተፈጥሯዊውን ሞት በተስፋና በእምነት የሞቱ የሽግግሩ ዘመን አማኝ ደቀመዛሙርት፣ ክርስቶስ በእርገቱ፣ ሀደስ ከሆነው ገነት ጋር በምርኮ የወሰዳቸውና በአብርሃም ዕቅፍ የነበሩ የአሮጌው ኪዳን አማኞች ተሰብስበው ወደነበሩበት የጻድቃን መንፈሶች ማህበር  ሊቀላቀሉ ይወሰዱ ነበር። በዚያም በዳግመኛ ምጽአቱ የሚቀበሉትን ትንሣኤ እየተጠባበቁ ይቆያሉ። ይህንን ገነት የተባለ ስፍራ ከክርስቶስ እርገት በኋላ የምናገኘው፣ ሀደስ /ሲዖል በተባለ የቀድሞ መገኛው ሳይሆን ይልቁንም በሦስተኛው ሰማይ እንደሆነ አስተውሉ (2ቆሮንቶስ 12፥ 2-4)። ሲዖልንና መቃብርን ድል ነስቶ ከሃያላን ጋር ምርኮን የተካፈለው ክርስቶስ  በእርገቱ ይህንኛውን የሀደስ ዞን/ ገነትን ማርኮ በመውሰድ ወደ ሰማያዊው ስፍራ የደጁ አደባባይ አምጥቶታልና። በዚያም በዳግመኛ ምጽአቱ የሚገለጠውን የቤዛነታቸውን ቀን ይጠባበቁ ዘንድ አስቀድሞ በእርገቱ የሰበሰባቸውና ከዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው አስቀድሞ በተለያየ ምክንያት ተፈጥሯዊውን ሞት የሞቱ የጻድቃን መንፈሶች ሁሉ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ሆነው  ትንሣኤን እየተጠባበቁ ተከማችተዋል።

4) በተጨማሪም ለየት ባለ ሁኔታ የሽግግሩ ዘመን ሰማዕታትን ጨምሮ፣ በአይነታቸው ለየት ያሉ ጥቂት የማይባሉ የብሉይ ኪዳን ሰማዕታትም ሁሉ፣ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት በሰማያዊው መቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን የውጭው አደባባይ ደማቸውን በምድር ላይ ባፈሰሱ ገዳዮቻቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድና በቀል እየጠየቁ በመሰዊያው ዙርያ ሆነው፣ ትንሣኤን ለማግኘት የክርስቶስን ፓሮዥያ እየተጠባበቁ ነበሩ። እነርሱም ከዳግመኛ ምጽአቱ አስቀድሞ የፍርዱንና የበቀሉን ቀን ለጥቂት ዘመን ታግሰው እንዲጠብቁ ነጩን መጎናጸፊያ የተቀበሉት ናቸው፤ ይኸውም "ጥቂት ዘመን" ጌታ እስኪመጣ ድረስ የነበረው የሽግግሩ ወቅት ሲሆን፣ በዚያ የሽሽግር ወቅት ዮሐንስ ራእዩን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ገና አዳዲስ የሰማዕታት ድል ነሺዎች እየተገደሉ በቁጥራቸው ላይ ሊጨመሩ ያለማቋረጥ ወደዚያ ስፍራ እየገቡ ነበር፤ ስለዚህ  ብዛታቸው ሊቆጠር የማይችል ነበር (ራእይ 4፥ 4፤ 7፥ 9፤ 7፥ 13-14)። 

¶ እንግዲህ ከላይ በተለያየ መልኩ ያየናቸው ሁሉም አይነት አማኝ ሟቾች፣ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ሆነው በዳግመኛ ምጽአቱ ትንሳኤን የሚቀበሉበትን የቤዛነታቸውን ቀን እስከ 70 አ.ም ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። 

# የማያምኑ ሟቾች እድላቸው፦
ከ70 አ.ም በፊት በነበረው የዘመን ምድብ የሞቱ የማያምኑ ሁሉ ግን ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት በሲኦል የስቃይ ስፍራ ሆነው በ70 አ.ም የሚገለጠውን የመጨረሻውን የክርስቶስን ፍርድ ይጠብቁ ነበር። እነዚህም ሁላቸውም ከአይሁድና ከአህዛብ ወገን የሆኑ ያልዳኑ፣ ያልተዋጁ፣ ያላመኑና ያልተመረጡ ናቸው። እነርሱም በ70 አ.ም በነጩ ዙፋን ፍርድ ይጠፉ ዘንድ ለዘላለም በእሳት ባህር ሊነዱ ፍርዳቸውን ተቀብለዋል። ይህም ማለት በብሉይ ኪዳን ዘመን ላይ እየኖሩ የማያምኑ የነበሩ ሟቾች ሁሉ በሞታቸው ጊዜ ከአጸደ ሥጋ ተለይተው በአጸደ ነፍስ ሳሉ በሀደስ የስቃይ ዞን ሆነው በ70 አ.ም የሚገለጠውን የመጨረሻ ፍርድ ይጠባበቁ ነበር ማለት ነው።

፪. ሟች ቅዱሳን በፓሮውዥያው ወቅት
5) በ70 አ.ም በተፈጸመው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ወቅት፣ ክርስቶስ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸውን እነዚህን ሟች ቅዱሳን ሁሉ በሰማያት ከያሉበት ሰብስቦ በአየር ላይ ወይም በሰማያት መካከል ወዳለ ሊታይ ወደማይቻል ሰማያዊ ስፍራና ግዛት ከራሱ ጋር አምጥቷቸዋል። እነርሱም እስከፍጻሜው ድረስ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው የተፈረደላቸው፣ ለአለምና ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር ሊነግሱ እና ሊገዙ መንፈሳዊና ሰማያዊ ሆኖ በከበረ የትንሣኤ አካል ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የገቡ ናቸው።

6) በ70 አ.ም ላይ በክርስቶስ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ወቅት ገና ሳይሞቱ በሕይወት የነበሩ እነዚያ ጥቂት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ደግሞ፣ ጌታ ሲገለጥ በቅጽበተ አይን ተለውጠው ተነጥቀዋል። [መነጠቅ በግሪኩ "harpazo" የተሰኘው ቃል ስትሮንግስ በተሰኘው የግሪክ የቃላት መፍቻ #726  ከሩቅ ፣ ወደ ላይ ይዞ ማንሳት፣ ነቅሎ ወይም ጎትቶ (በኃይል መውሰድ፣ መንጠቅ፣ መንቀል፣ ወደላይ ማንሳት፣ ወይም ይዞ በኃይል ወደላይ መሳብ የሚል ትርጉም ተሰጥቶትታል።] ይኸውም። ተለውጦ መነጠቅ ሥጋዊውን ሞትን መለማመድ ሳያስፈልጋቸው ጌታን በአየር ላይ ወይም በመካከለኛው ሰማይ ላይ መገናኘት የሚያስችላቸው ነው። እነርሱም እስከፍጻሜው ድረስ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው የተፈረደላቸው፣  ለአለምና ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር ሊንነግሱ እና ሊገዙ መንፈሳዊና ሰማያዊ ሆኖ በከበረ የተለወጠ አካል ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የገቡ ናቸው።

"አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። ታላቅም ድምፅ ከሰማይ፦ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።" (ራእይ 21፥ 1-4)

"ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ። ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።" (ራእይ 21፥ 22-27)

በ70 አ.ም ከእርሱ ጋር ያመጣቸው እነዚህ ቅዱሳን ሁሉ በሰማያዊቷ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስ ጋር የዘላለም ሕይወት አላቸው። በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ወቅት እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ቡድኖች የተዋጁ ፣ የተመረጡ የብሉይ ኪዳን እና የሽግግር ወቅት አማኞች አዲሱን፣ የማይበሰብሰውን ፣ የማይሞተውን ፣ የከበረውን ፣ መንፈሳዊውን ፣ ሊታይም የማይችለውን፣ ሰማያዊ አካል በትንሣኤ እና በመለወጥ ተቀብለዋል። "ትንሣኤና ሕይወት" ከሆነው ከኢየሱስ "የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤" (ዮሐንስ 11፥ 25) የሚል ጽኑ ተስፋ ይዘው፣ በሥጋ ቢሞቱም እርሱ በመጨረሻው ቀን እንደሚያስነሳቸው አምነው ሞተዋል፤ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሳይሞቱ ቢቆዩ ደግሞ በቅጽበት አይን ተለውጠው እንደሚነጠቁ ተስፋ አድርገው ኖረዋል። በመጨረሻውም ቀን ሙታንን አስነስቶ ከእርሱ ጋር አምጥቷቸዋል፣ ሕያዋንንም ለውጦ በንጥቀት ወስዷቸዋል።

፫. ሟች ክርስቲያኖች ከፓሮውዥያው በኋላ
7) በ70 አ.ም ከተፈጸመው የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ፓሮውዥያ በኋላ፣ የአዲሱ ኪዳን የወንጌል መንግስት እርሱም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር በሙላት ተመስርቶ ተገልጧል። የአሮጌው ኪዳን አይሁዳዊ የኃይማኖት መስተዳድር እርሱም አሮጌው ሰማይ አልፏል። በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ እግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ የሚታወቀው የእስራኤል ሕዝብ፤ የኢየሩሳሌም ከተማ እና መቅደሱ እርሱም አሮጌው ምድር፣ ሁሉም ተደምስሶ አልፏል። ከእንግዲህም በኋላ በእግዚአብሔር ዋጆአዊ እቅድ ውስጥ ፈጽሞ ምንም ቦታ የሌላቸው ሆነዋል። 

ከ70 አ.ም በኋላ ያለን እኛን በክርስቶስ ያመንነውንና፣ ከዚህም በኋላ ለአለምና ለዘላለም በእርሱ እያመኑ ወደአካሉ ህብረት የሚገቡትን ሁሉ ጨምሮ፣ ገና በዚህ ህይወት እያለን እግዚአብሔር የዋጀን ምርጦች ሁላችንም (የተመረጡ አይሁድ እና የተመረጡ አህዛብ ሁሉ) በክርስቶስ የተፈረደልንና የተጠናቀቀ ድነታችንን ፍጻሜና ሙላት የተቀበልን ነን። ዘላለማችንንም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስ ጋር ልናሳልፍ በእምነት ወደሀልዎቱ ገብተናል። ክርስቲያኖች ተብለን በክርስቶስ እንደተባበረ አንድ ሕዝብ እና አንድ አካል ነን እንጂ ወደፊት መቼም ቢሆን አይሁድ ወይም አህዛብ ተብለን አንጠራም (ገላትያ 3፥ 16፣ 28-29)። ሁላችንም በየግላችን በእንድ ወይም በሌላ ምክንያት በሥጋ እንሞታለን፣ ያኔም ወዲያውኑ በማይሞተው፣ በማይበሰብሰው፣ በከበረው፣ መንፈሳዊ በሆነው፣ ሊታይ በማይችለው ሰማያዊ አካል፣ ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ሀልዎቱ ፊት በክብር ለመሆን ወደ ሰማይ እንሄዳለን። *ትንሣኤና ሕይወት" ከሆነው ከኢየሱስ ዘንድ "ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም" (ዮሐንስ 11፥ 26) የሚል እንዲህ ያለ ጽኑ ቃል ያለን እኛ ይህንን እንዲሁ በጸጋ ያገኘነውን አዲሱን ዘላለማዊ ሕይወት ይዘን እንሞታለን፣ እርሱ ሕያው ስለሆነም ሕያዋን ነንና ለዘላለም አንሞትም።

# የማያምኑ ሟቾች ፍጻሜአቸው፦
ከ70 አ.ም በኋላ ባለው በዚህ ህይወት ሳሉ ባለማመን ጸንተው የሚሞቱ ሁሉ፣ ከላይ እንዳነሳነው እነርሱም አስቀድሞ በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው  በተፈጸመው በታላቁ የነጩ ዙፋን ፍርድ ውሳኔ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። እነዚህም ሁላቸው ከ70 አ.ም በኋላ የኖሩና የሞቱ በጠቅላላው የክርስቶስን ወንጌል የገፉ፣ ያልዳኑ፣ ያልተዋጁ፣ ያላመኑና ያልተመረጡ የጠፉ የምድር ህዝቦች ናቸው። ማናቸውም ቢሆኑ በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፉ ናቸው። "በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል" (ዮሐንስ 3፥ 18) እንደተባለ፣ ዘላለማዊው ፍርዳቸው እና ኩነኔያቸውም አስቀድሞ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተመደበ እና በይፋ የታወጀ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወታቸው ጌታቸውና መድሃኒታቸው እስካልሆነ ድረስ ማናቸውም ቢሆኑ በማናቸውም ምክንያት በሚሞቱበት ጊዜ በ70 አ.ም ላይ በይፋ የተገለጠውን ዘላለማዊ ቅጣታቸውን በየራሳቸው ይቀበሉ ዘንድ ከስጋቸው ተለይተው፣ ያለ ተዳሳሹ አካልና ደም፣  ነገር ግን በሌላ አንዳች አይነት አካላዊ ቅርጽና ይዘት ይጠፉ ዘንድ በቀጥታ ወደ እሳት ባህር ይሄዳሉ (ራእይ 21፥ 8)። ስለዚህ ወደ ጸጋው መግባትን ያገኘች ቤተክርስቲያን ሌሎች በውጭ ያሉ በሥጋ ከመሞታቸው በፊት ፈጥነው እንዲገቡ ሰውን ሁሉ በፍቅር እየለመነች ለንስሃ እና ለእምነት በወንጌል ትጣራለች።

በመጨረሻም፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የበለጠ ለማሰብ ፍላጎት ካደረባችሁ በፊልጵስዩስ 3፥ 21 ላይ ተመስርቼ፣ "የተዋረደው 'ሥጋችን' ልውጠት" በሚል ርዕስ በጸሎትና በንባብ ያቀረብኩትን ሰፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጊዜ ወስዳችሁ እንድትመለከቱት በአክብሮት እጋብዛለሁ። በውስጡም የሚያጽናና እና የሚሞግት የወንጌል ጸጋ ቀርቦበታልና ትካፈሉት ዘንድ እነሆ ሊንኩ፦  
https://www.facebook.com/1889309531297484/posts/3265218500373240/ 

ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

Sunday, September 26, 2021

ሜሎው፣ እርግጠኛው አይቀሬ


እርግጠኛው አይቀሬ


"μέλλω" (ሜሎው) የተሰኘው የግሪክ ቃል እና ነገረ ፍጻሜአዊ ጠቀሜታው ሲፈተሽ


 

አዲስ ኪዳን ከተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ በቀጥታ ወደ እንግሊዝኛም ይሁን ወደ ልዩ ልዩ ጥንታዊና ዘመናዊ ቋንቋዎች የተደረጉ ትርጓሜዎች በየዘመኑ ላሉ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅስዱ በገጾቹ የያዘውን ቁምነገር ለመረዳት እንዲችሉ ሲያግዟቸው ኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በተለያየ ቋንቋ ተርጉመው ያቀረቡልን አብዛኞቹ ተርጓሚዎች በተለይ ለበኩረ ቋንቋው ለግሪኩ ታማኝ ለመሆን የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ ያደረጉ መልካም ሰዎች ናቸው። በአማርኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ተሳትፎ ለነበራቸው አባቶችም ልዩ አክብሮት አለኝ። ዳሩ ግን የግሪኩን ቅጂ እያየን አማርኛችንንም ሆነ እንግሊዝኛውን እያጣቀስን እና እያመሳከርን ስናጠና ከቃላት አገባብንና ከሚሰጡት ትርጉም አንጻር ጉልህ ልዩነት የሚያደርጉ እንዳንድ ጉዳዮች ይኖራሉ፤ በተለይ መሰረታዊ አስተምህሮዎችን ሊቀርጹ ጉልበት ያላቸው ቃላትና ሃረጎች ሲሆኑ የበለጠ ያሳስባሉ። 


በዚህ ረገድ ከነገረ ፍጻሜአዊ ይዘቷ አንጻር ከፍ ያለ ዋጋ ያላት፣ ነገር ግን ብዙዎች ልብ ያላልዋት μέλλω "MELLO" የተሰኘች አንዲት የግሪክ ቃል እናገኛለን፤ ግሱ በእንግሊዝኛው "ABOUT TO BE" በአማርኛው "ሊሆን ያለው" በሚል መተርጎም የነበረበት ይህ ሐረግ የያዘው ቁም ነገር ብዙም ትኩረት ሳይስጠው በብዙዎች በቀላሉ እንደታለፈም እንታዘባለን።  ይህች μέλλω "MELLO" [በእንግሊዝኛው፣ ABOUT TO BE ጎግል ሲፈታው፦ Be (just) about to allows us to express an imminent action, or a very near future: ይልና፤ The train is just about to leave. The train will leave very soon. የሚል ምሳሌን ይሰጠናል] የተሰኘች አንዲት ቃል ግን በውስጧ ከጊዜ አንጻር በእጅጉ ቅርብ የሆነን ጉዳይ እርሱም የማይቀር እርምጃን ጓጉቶ የመጠባበቅን ጽንሰ አሳብ ይዛለች። ቃሉ ሊከሰት፣ ሊመለስ፣ ሊመጣ፣ ሊደርስ ወዘተ ያለ ነገርን 'ሰፍ ብሎ' መጠበቅን ሲያመለክት፣ የጉዳዩን ቅርበት የሚያሳይና 'እነሆ ሊሆን ነው' ብሎ በመጠባበቅ ስሜት፣ በተለይ ከጊዜ አንጻር በቅርብ ርቀት የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ የግድ መሆን ያለበትንና፣ እንዲሆን የተወሰነን አንዳች ነገርን  የሚያመለክት፣ ስለሚሆነውም ነገር እርግጠኛነት የሚናገር የግሪክ ቃል ነው። [ለበለጠ ግንዛቤ Strong's word 3195፤ እንዲሁም ግሪክ ሌክሲከን /Greek Lexicon/ ላይ መሰረቱን አድርጎ የተዘጋጀው የጣየር እና የስሚዝ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ በተጨማሪም ሌሎች እንደ Theological Dictionary of the New Testament ያሉ ሰነዶችን ማመሳከር ይቻላል።]


ዘመናዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተዘጋጁበት ጊዜ፣ μέλλω "MELLO" (ABOUT TO BE) የተሰኘችው ቃል/ሀረግ በኢየሱስና በሐዋርያቱ ንግግር ውስጥ ያላት ጠቀሜታ ተርጓሚዎችን እንዳስቸገራቸው በብዙ ልንታዘብ እንችላለን። እነዚህ ተርጓሚዎች በአመዛኙ በነገረ ፍጻሜ እምነታቸውና አቋማቸው ገና ወደፊት ይመጣል ባይ "መጻኢያን" ስለሆኑ፣ ከዚህ የተነሳ ምንም እንኳ ይህች ቃል በያዘችው ትርጉም "ሊመጣ እንዳለው" μέλλω MELLO (ABOUT TO BE) ብላ እያስተማረች ቢሆንም እንኳ፣ እነርሱ ግን የሚመጣው ገና ወደፊት የሚመጣ እንደሆነ μέλλω "MELLO" (ABOUT TO BE) ሲተረጉሙ፣ የፍጻሜውንም ጊዜ ቅርበት አዲስ ኪዳንን በጻፉልን ሰዎች የህይወት ዘመን ውስጥ ማሰብ እና በዚህ ደርዝ ትርጉሙን ማስቀመጥ እንዳልተቻላቸው በግልጽ እናያለን። ስለዚህ የቃሉን ጠቀሜታ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፣ ወይም ሆን ብለው በነገረ ፍጻሜ አመለካከታቸውና አቋማቸው ተጽዕኖ ስር ወድቀው፣ ቃሉ ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ጨርሶ እንዳልነበር ሁሉ፣ ይህንን MELLO የተሰኘ ቃል በአመዛኙ ትርጉማቸው ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው አድርገዋል። የዚህ ጽሁፍ አላማ የቃሉ ወዳጆችና ተማሪዎች የሆኑ የመሰማርያው በጎች በአንዲት ትንሽዬ ቃል የተነሳ ቅዱስ ቃሉ የሚለውን እንደማይል፣ የማይለውንም እንደሚል አድርገው የማሰብም ሆነ የመማር አደጋ ውስጥ እንዳይወድቁ፣ በእውነትም ግራ ከመጋባት የተጠበቁ ይሆኑ ዘንድና ከነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ አንጻር ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ ምንባባት ተገቢውን ትኩረት እንዳይነፍጉ ለመርዳት መሆኑን ልብ አድርጉ።


በዚህ መሰረት ምሳሌ የሚሆኑን ጥቅሶችን ከተወሰኑ ማብራርያዎች ጋር እየተመለከትን ይህ mello የተሰኘ አንድ ቃል በተለይ ከነገረ ፍጻሜ ጠቀሜታው አንጻር በየምንባባቱ ውስጥ ያለውን አገባብ አብረን እንድንፈትሽ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ።


  1. ማቴዎስ 3፥ 7 (ሉቃስ 3፥ 7) "ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው [ሊመጣ ካለው/ mello] ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?" ["ሊመጣ ያለው ቁጣ" እንጂ "የሚመጣ ቁጣ" አይደለም]


  • መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ አውድ ለአይሁድ ህዝብ እየሰበከ መሆኑን እናያለን፤ በስብከቱም በቅርቡ ስለሚደርስባቸው የእግዚአብሔር ቁጣ የአይሁድን የኃይማኖት መሪዎችን ያስጠነቅቃል። ቁጣው መቼ እንደሚመጣ የማይታወቅ ግን የሚመጣ ቁጣ ሳይሆን፣ የሚመጣበት ጊዜ የቀረበ ወይም በቅርብ የሚመጣ ቁጣ ነው። ኢየሱስም በሌላ ስፍራ በትምህርቱ “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች” ብሎ የጠራቸው እነዚሁኑ ቡድኖች ሲሆን፣ በዚህም ንግግሩ የእግዚአብሔርን ቁጣ “የገሃነም ፍርድ” በማለት ገልጾታል (ማቴዎስ 23፥ 33)። ኢየሱስ በዚያ ትውልድ ላይ ቤታቸው ባድማ ሆኖ የሚቀርበት ጊዜ እንደሚደርስ የተናገረው ፍርድ እና ይመጣል፣ "ከሰማይም ይገለጣል" የተባለው ቁጣ (ማቴዎስ 23፥ 38፤ ሮሜ 1፥ 18) ከ66-70 አ.ም ባለው ጊዜ (ለ3 አመት ተኩል) መጥቶ አልፏል። ያኔም የአሮጌው ኪዳን ቤተመቅደስ እና የኢየሩሳሌም ከተማ በሮማውያን ሰራዊት እጅ ወድቀው ተደምስሰው ወድመዋል። አስቀድሞ በእስራኤል ምድር ተቀስቅሶ ከነበረው አመጽ፣ የእርስ በርስ ውጊያና ጽኑ ረሃብ የተረፉ በሚልዮን የሚቆጠሩ የአይሁድ ሕዝብም በደረሰባቸው መቅሰፍተ ዕልቂት በገዛ ምድራቸው ተገድለው አልቀዋል፣ በምርኮ የተወሰዱትም በአለም ዙርያ ተበትነው ከእነርሱም የሚበዙት በአህዛብ ጣዖታት ክብረ በአላት ላይ ለጣዖታቱ እንደ መስዋእት ታርደው፣ ለነገስታቱና ለመኳንንቱ ክብር ጭዳ ሆነው፣ ገሚሱንም በጨዋታ ስፍራ ከአውሬ ጋር እያታገሉአቸውና እየተበሉ ዘራቸው ጥፍቷል፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በ70 አ.ም ነው (ዳንኤል 12፥ 7-13 እና ሉቃስ 21፥ 5-36 ተመልከቱ)። ከ70ው አ.ም ፍጅት በኋላ በእናቱም በአባቱም ንጹህ የአብርሃም ልጅ የሆነ እስራኤላዊ በምድር ዙርያ ማግኘት የማይታሰብ ሆኖአል። "ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል" ያለው አስፈሪው የኢየሱስ የፍርድ ትንቢትም ተፈጽሟል።


  1. ማቴዎስ 12፥ 32 "በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው [ሊመጣ ባለው/ mello] አይሰረይለትም።" [ ሊመጣ ባለው ዘመን እንጂ የሚመጣው ዘመን አይደለም]


  • እንደ ግሪኩ "ሜሎ" ሁሉ 'አለም' በሚል የትርጉም ስህተት የተሰራበት ሌላው የግሪክ ቃል 'ዘመን' (aion) የተሰኘው ነው። ኢየሱስ ግን "ይህ ዘመን" ሲል የሚጠራውንና ያኔ ይሰራ የነበረውን የብሉይ ኪዳንን አለም እና በ 70 ዓ.ም "ሊመጣ ያለውን" የአዲሱን ኪዳን ዘመን በተቃርኖ ያቀርባል እንጂ፣ የትርጉም ስህተቱ እንደፈጠረው እንግዳ ትምህርት "ይህ አለም" ማለት አሮጌው የሙሴ አለም መስተዳድር ካልሆነ በቀር፣  ይህ ግዑዝ አለም ማለት አይደለም፤ የሚመጣው ማለትም አሮጌውን የሙሴ አለም መስተዳድር ሽሮ የሚገለጥ አዲሱ ኪዳን የሚያበስረው የክርስቶስ ዘላለማዊ መንግስት ካልሆነ በቀር፣ ሌላ የሚመጣ አዲስ ግዑዝ አለም ማለት ፈጽሞ አይደለም። ለምንድነው ግን ኢየሱስ "በዚህ ዘመን ወይም ሊመጣ ባለው ዘመን" ይቅር አይባልም ሲል የተናገረው? በእርግጥ እርሱ እየተናገረ ያለው የአይሁድ ቤተ መቅደስ እንዲደመሰስ ከሆነበት ከ 70 አ.ም በፊት (ማለትም “ይህ ዘመን”) እና ከዚያ በኋላ (“በሚመጣው ዘመን”) ስለ ተፈጸሙ ኃጢአቶች ነው። ስለዚህ ይመጣል የተባለው ዘመን ቀኑና ጊዜው ቀርቦ የሚታወቅ እንጂ ሩቅ እና የጊዜውን ማእቀፍ ማወቅ የማይቻል አይደለም።


  1. ማቴዎስ 16፥ 27-28 "የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና [mello]፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።" [ይመጣ ዘንድ አለው እንጂ ይመጣል አይደለም]


  • mello የተሰኘውን ቃል ጠቀሜታ እውቅና ሰጥተው አማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ለተረጎሙ ሰዎች እዚህ ላይ ዋጋ መስጠት ይገባል። ይህ ምንባብ በግልጽ እንደሚናገረው ኢየሱስ ሊመጣ ያለው የሰው ልጅ ነው፤ ከዚህም የተነሳ እዚያ ቆመው ይህንን ንግግሩን ያደምጡ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሳይሞቱ በህይወት ቆይተው 'ይሆናል' የተባለው ይህ ጉዳይ ሲፈጸም ማለትም መምጣቱን ያያሉ። ይህ ንግግር በግልጽ ጓጉቶ መጠባበቅን የግድ ይላል። እንዲህ ያለ ፊትለፊት እና በግልጽ ቋንቋ ከኢየሱስ አፍ የወጣ ንግግር ልክ እንደተጻፈው እውነት ካልሆነ ግን፣ ኢየሱስን ሀሰተኛ ነብይ ሊያሰኘው የሚችል ጣጠኛ የሆነ መዘዝ ይጎትታል። ኢየሱስ ጌታ ነው ብለን እያመንን በጌታችን ላይ እንዲህ ያለ ስድብ እና ነቀፋ የሚያስከትል "ትንቢት እስካሁን አልተፈጸመም፣ ጌታም ገና ወደፊት እንጂ እስካሁን አልመጣም" የሚል የመጻኢነትን ትምህርት አዝለን መኖራችንን አለማወቅ በእውነት እውርነት ነው። ኢየሱስ መንግስቱን ከእግዚአብሔር ጠላቶች ነጥቆ ሁሉ በሁሉ ሆኖ አሁንና ለዘላለም ሁሉን ለሚገዛው ለእግዚአብሔር ይመልሰው ዘንድ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ተመልሷል ብዬ የማምነውም ከዚህ የተነሳ ነው። ታዲያ እርሱ በግልጽ ፊት ለፊት "እዚህ የቆሙት" ሲል በተለይ በጠራቸው ሰዎች የህይወት ዘመን ተመልሷል ብዬ እንዳላምን፣ ይልቁንም 'አይ ሊል የፈለገው እንደዚህ ሳይሆን እንደዚያ ነው" በሚል ማመካኛና ሰዎች ለቃሉ በሚሰጡት ማስተካከያ እና እርማት መሰል ድፍረት ሊል ያልፈለገውን ሌላ ነገር እንድረዳና እንዳምን፣ የሰጠውንስ ተስፋ እንዳልፈጸመ እንድቆጥር ለምን ይፈርዱብኛል? እንደተናገረው  እንደዚያው እንደ ተስፋ ቃሉ በፍርድና በክብር ተመልሷል ብዬ ላምነው የማልችለው 'ኢየሱስ' አዳኜስ ሊሆን እንዴት ይችላል?


  1. ማቴዎስ 24፥ 6 "ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ [millo]፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።" [ትሰማላችሁ ሳይሆን ትሰሙ ዘንድ አላችሁ ነው]


  • ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የሚናገረው ለነዚያ ከእርሱ ጋር በዚያ ለነበሩ የመጀመሪያው ከፍለዘመን ደቀመዛሙርቱ ነው፤ እንጂ ዛሬ ይህንን የምናነብ ማናችንም ብንሆን የዚህ ቃል በኩረ ተደራስያን አይደለንም። የሚነግራቸውም በገዛ ራሳቸው ትውልድ ወቅት (ማቴዎስ 24፥ 34) በቅርቡ ሊሆንባቸው ስላለ ነገር ነው። ሊሆን ያለው የሚሆነው "እናንተ" ተብለው በተለይ ለተጠቀሱ ለመጀመሪያዎቹ አድማጮች እንጂ ለማናችንም አይደለም። በዚህ ምንባብ "ትሰሙ ዘንድ" በሚል 'እናንተ' ለተባሉት "መጨረሻው" ገና ወደፊት ነበር፣ ዳሩ ግን ሩቅ ሳይሆን እናንተ በተባሉት ሰዎች የሕይወት ዘመን የሚሆን ነው። ትንቢቱ 'እናንተ ትሰማላችሁ' በተባሉት ሰዎች የህይወት ዘመንና ትውልድ ውስጥ  ያልሆነና ተፈጽሞ ያላለፈ ከሆነ፣ እንግዲያውስ እነዚህ ቃሎች ከተነገሩ ከ2000 አመታት በኋላ ለምናነባቸው ለእኛም ቢሆን መጨረሻው ገና ወደፊት ሊሆን ከቶ አይችልም።


  1. ሉቃስ 21፥ 36 "እንግዲህ ሊመጣ ካለው [mello] ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።" [ሊመጣ ካለው ነው እንጂ ከሚመጣው አይደለም]


  • የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳን ትርጉም በዚህም ጥቅስ ላይ mello ለተሰኘው የግሪክ ቃል ታማኝነቱን አሳይቷል። እንደ ኢየሱስ ግልጽ ንግግር ከሆነ እርሱ "ይህ ሁሉ" ሲል የዘረዘረው "ሊመጣ ያለው" ነገር ሁሉ ፍጻሜው በዘመንና በትውልድ ርቀት የሚታሰብ ሳይሆን፣ ይልቁንም በግል በእያንዳንዳቸው በደቀመዛሙርቱ የህይወት ዘመን የሚሆኑ ነገሮች ናቸው። ኢየሱስ የሚናገረው ለገዛ ራሱ ደቀ መዛሙርት ነው እንጂ ለእኛ ወይም ለሌላ ሦስተኛ ወገን እንዳልሆነ ልብ አድርጉ።


  1. ሐዋርያት 17፥ 31 "ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ [mello] ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።" [ይፈርዳል ሳይሆን ሊፈርድ ነው ማለት ነው]


  • አማርኛው ይህንንም ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ግልጽ ያደረገው አንድ ጉዳይ በራሱ ትውልድ እግዚአብሔር በአለሙ ሁሉ ላይ ሊፈርድ መሆኑን ነው። ኃላፋውያን በትምህርታቸው ቅዱሳት መጻህፍትን ሲተረጉሙ ጊዜ ጠቋሚ ለሆኑ እንዲህ ላሉ ንግሮች ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣሉ፣ ነገረ ፍጻሜአዊ ምልከታችንን መልክና ቅርጽ የሚሰጠው አንዱ ይኸው ነውና።  እግዚአብሔር በህያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ያለው፣ ቀን የቀጠረው በመጀመርያው ከፍለዘመን ትውልድ ወቅት ነበር። ይህንን በመለኮት የተመደበ ቀነ ቀጠሮ ከመጀመርያው ክፍለዘመን የጊዜ ማእቀፍ አውጥተን በየትኛውም ዘመናዊ ወይም መጻኢ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን እንድንጠባበቅ የሚያስችለን ምንም አይነት አዲስ ኪዳናዊ ድጋፍ የለንም፣ አይኖረንምም።


  1. ሐዋርያት 24፥ 14፣ 15 "ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው [mello] ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።" [ከሙታን ይነሳሉ ሳይሆን ከሙታን ይነሱ ዘንድ አላቸው ነው]


  • እዚህም ላይ የአማርኛው ትርጉም ጥሩ ነው። ጳውሎስ በዚህ ንግግሩ ግልጽ የሚያደርገው አንድ እውነት ምንድን ነው? "እኔ ከእነርሱ የምለየው በአምልኮዬ ነው፣ መንገዱንም ኑፋቄ ሲሉ ይጠሩታል፤ ሆኖም የማምነዉ እነርሱ እንደሚያምኑት በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ ነው፣ የሙታንን ትንሳኤ  የምጠብቀውም እነርሱ እንደሚጠብቁት ነው፣ ተስፋ የማደርገውም እነርሱ ተስፋ አንደሚያደርጉት ነው"፤ እያለ ነው። የሙታን ትንሳኤን ጨምሮ በህጉ የተጻፈው ሁሉ በቅርቡ ፍጻሜውን የሚያገኝ መሆኑን ጳውሎስ ይጠባበቃል። ጳውሎስ ለአገረ ገዡ ለፊሊክስ እየነገረው ያለው፣ የጻድቃንና የኃጢአተኞች ትንሳኤ የሚከናወነው በእርሱ የህይወት ዘመን መሆኑን ነው። ጉዳዩ በእርግጠኝነት በቅርቡ የሚከናወን (NO DELAY) መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ ጳውሎስ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን አድማጮቹ ባቀረበው ሙግት፣ ትንሳኤ በቅርቡ ሊሆን እንደሆነ እየነገራቸው ነበር ማለት ነው። በመላው አዲስ ኪዳን፣ ወንጌል አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለግሪክ እንደሚሆን የተገባው የእስራኤል ተስፋ መፈጸሙን በግልጽ እናያለን፤ ይህም በድህረ ጴንጤቆስጤ እየተካሄደ በነበረው ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን የሚደረገው ሽግግርም በዚያው የመጀመርያው ክፍለዘመን ውስጥ የፍጻሜው ዘመን እየቀረበ የነበረ መሆኑን እና ያም ጠንካራ ምስክርነት እንደነበር ያሳያል። 


  1. ሐዋርያት 24፥ 25 "እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም [ሊመጣ ስላለው/ mello] ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ፦ አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።" [ሊመጣ ስላለው ኩነኔ ነው እንጂ ስለሚመጣው አይደለም]


  • ፍርድ በገዛ ራሱ ትውልድ ውስጥ በቅርቡ ሊመጣ መሆኑን እየተናገረ ያለውን የጳውሎስን ግልጽ ንግግር ካልተረዳ በቀር ፊልክስ ለምን ይፈራል? ያኔ ጳውሎስ ለፊልክስ እየተናገረ ፊልክስም ጳውሎስን እየሰማው በነበረበት ዘመን ኩነኔ ሊመጣ በቅርብ ተዘጋጅቶ ነበር ማለት ነው።


  1. ሮሜ 8፥ 13 "እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና [mello]፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።" [ትሞታላችሁ ሳይሆን ትሞቱ ዘንድ አላችሁ ነው]


  • ለአማርኛው ትርጉም ያለኝን አድናቆት አልሸሽግም። ጳውሎስ አይሁድ አማኞች የሆኑ “ወንድሞችን”፣ የሚናገራቸው ወደ ሥጋ ፈቃድ ተመልሰው “በሥጋ ትምክህት የሚሄዱ” ከሆነ “ሊሞቱ” እንደሆነ አያስጠነቀቃቸው ነው። ይህም ሥጋዊ በሆነው ሥርዓታቸው ላይ በመመካት በመንፈስና በሕይወት የሚገለጠውን ኑሮ እምቢ በሚሉት ላይ ፈጥኖ ሊሆንባቸው ያለውን ፍርድ ያሳያል።


  1. ሮሜ 8፥ 18 "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው [mello] ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።" [ይገለጥ ዘንድ ያለው ነው እንጂ የሚገለጠው አይደለም]


  • በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን እነዚህን ነገሮች በምን ያህል ናፍቆት ጓጉተው ይጠባበቁና ተስፋ ያደርጉ እንደነበር ለማየት የዚህን ጥቅስ አጠቃላይ አውድ (ቁጥር18-25) በጥንቃቄ አንብቡት። ለምን እነዚህን ነገሮች መጓጓትና በግል መጠባበቅ አስፈለጋቸው? ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በግላቸው እነሱን ማሳተፍ የነበረባቸው ጉዳዮች በመሆናቸው ነው። ይገለጥ ዘንድ ያለው ክብር "ለእኛ" ነው፣ እኛ የተባሉትም ጳውሎስና የመጀመሪያው ክፍለዘመን ክርስቲያኖች ናቸው። "የአሁኑ ዘመን ሥቃይ" የተባለውም የእነርሱ ዘመን ሥቃይ ነው። በግል እያንዳንዳቸው ያልፉቡት የነበረው የመከራ ሕይወት የሚካሰውና የሚደመደመው ለእነርሱው ሊገለጥ ባለው ክብር ነው።


  1. ሮሜ 8፥ 38፣39 "ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • እዚህ ላይ ሁለቱን ኪዳናት እናያለን። "ያለውም" የተባለው እርሱም 'አሁን ያሉት ነገሮች (የሙሴ ዘመን)' እና "የሚመጣውም"  የተባለው እርሱም ሊመጣ ያለው (መሲሐዊው ዘመን) ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም ተብሎ ከተዘረዘረው፣ ከሞት ፣ ከህይወት ፣ ከመላእክት ፣ ወዘተ ጋር ተቆራኝተው መነገራቸውን ልብ በሉ። "ያለውም"  የተባለው በዚያ በአሮጌው ኪዳን እና በሙሴ ዘመን መስተዳድር ውስጥ ተካተው የነበሩ ያኔ እነርሱ ይኖሩበት የነበረው ስርአትና የሞት አገልግሎቱ ነው፤ "የሚመጣውም"  (ሊመጣ ያለው)  የተባለው ደግሞ አዲሱን ኪዳን ወይም የመሲሁን ዘመን የሚያካትት ነው። ይህም በእብራውያን 8 ላይ ስለ አሮጌው ዘመን፣ "አርጅቷል፣ አሮጌና ውራጅ ሆኖ ሊጠፋ ቀርቦአል!" (ቁጥር 13) እያለ ከሚናገረው ጋር የተቆራኘ ነው። አዲሱ በሙላት እስካልመጣ ድረስ አሮጌው ኪዳን አሮጌ ሊሆን እንደማይችል ይህንን አንድ ነገር አትርሱ። ያ በ70 አ.ም ላይ የተከሰተው የመቅደሱና የከተማይቱ ውድመት የዚያን አሮጌ ስርአት ፍጻሜው መሆኑን ያሳያል። አሮጌው ኪዳን በውስጡ የያዛቸው ሁሉም ዓይነት ነገሮች በኢየሱስ ተፈጽመዋል።


  1. 1ቆሮንቶስ 3፥21-23 "ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።"  [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • ከፍ ሲል ለሮሜ 8፥ 38 የተሰጠውን ማብራርያ ይመለከቷል። "የሚመጣውም [ሊመጣ ያለው mello] ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፥"  ሲል እዚህ ላይ "እናንተ" የተባሉት በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ የነበሩ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ናቸው። "የሚመጣውም" (ሊመጣ ያለው) የእነርሱ ከሆነ እንግዲያውስ የሚመጣው በእነርሱ የህይወት ዘመን ለእነርሱ ነው፣ እንጂ እነርሱ ካለፉ በኋላ ዘመናት ተቆጥረው ቢመጣ "የእናንተ ነው፥"  መባሉ ምንም ትርጉም አይሰጥም።


  1. ኤፌሶን 1፥ 20-21 "ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው [mello] ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤" " [በሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ባለው ነው]


  • ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው "ዓለም" የሚለውን ቃል እዚህ ያለቦታው የዶለው የተርጓሚዎች ስህተት ነው፤ ቃሉ "ዘመን" ተብሎ መተርጎም ነበረበት። ስለዚህ "ይህ ዘመን" (አሮጌው ኪዳን) እና "ሊመጣ ያለው ዘመን" (አዲሱ ኪዳን) በንጽይር የቀረቡልን ስለሆነ ትርጉማቸውን በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፣ ምክንያቱም አይሁድ ነገረ ፍጻሜን የሚረዱትና የሚተረጉሙት በነዚህ ቃላትና ሃረጎች ላይ ቆመው ነው። "በዚህ ዘመን" የተባለው ትርጉሙ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ሲሆን፣ "ሊመጣ ባለው ዘመን" የተባለው ደግሞ የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነው። በእብራውያን 8 የተገለጸውን እንዲሁም የአሮጌውን ፍጻሜ እዚህ ላይ ልብ በሉ።


  1. ቆላስይስ 2፥ 16-17 "እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት [mello] ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።" [የሚመጡ ነገሮች ሳይሆን ሊመጡ ያሉት ነገሮች ነው]


  • ይህ ምንባብ በክርስቶስ ፍጻሜውን ሊያገኝ ያለውን አሮጌውን ኪዳን (ማለትም የአይሁድን በአላት፣ ልዩ ልዩ ስርአቶቻቸውን ተስፋዎቻቸውን፣ ወዘተ) በአግባቡ ለመረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ በአሮጌው ኪዳን ዘመን ስለተካተው የአመጋገብ ስርአት፣ በአላትን ስለማክበር እንዲሁም ወቅቶችን አስመልክቶ ስለሚሰጥ ትምህርትና ሰንበትን ስለመጠበቅ እናያለን። እነዚህም ጉዳዮች ያኔ ሊመጡ ቀርበው ላሉት ጥላው ነበሩ፣ እነዚህ ጥላ የነበሩት፣  ያረጁ ፣ ያፈጁ እና ሊጠፉ የተቃረቡ ጉዳዮችና (እብራውያን 8)፣ ከክርስቶስ ጋር ተያያዥነት ባላቸውና እርሱ በሚገዛቸው ቁምነገሮች ሊተኩ የተዘጋጁ ነበሩ!። አንዳንድ መጻኢያን የሆኑ ወገኖቻችን እነዚህ ነገሮች በመስቀል ላይ ተጠናቀዋል ብለው ያምናሉ ዳሩ ግን ተመልከቱ ጳውሎስ ይህንን እየጻፈ በነበረበት ጊዜ ፍጻሜአቸው ገና እንደነበር እናያለን። ስለዚህ በግልጽ እንደምናየው እነዚህን ነገሮች በ 70 ዓ.ም. ተፈጽመው ያለቁ በመሆናቸው አሁን በዚህ ዘመን እንለማመዳቸው አንልም።


  1. 1ጢሞቴዎስ 4፥ 8 "ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው [ሊመጣ ያለው/ mello] ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።"" [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • በነ ጳውሎስ ዘመን ሕይወት የአሁንና የሚመጣው የተሰኘ ሁለት Dispensation ነበረው፤ ለእነርሱ የአሁኑ ሕይወት ማለት አጠቃላዩ አሮጌው የሙሴ ዘመን እና ከአሮጌው ወደ አዲሱ ኪዳን  ለመሸጋገር እነርሱ ራሳቸው ይኖሩበት የነበረው በብዙ ትግል ስጋን የመግራት ዘመን የምንለው ወቅት ሲሆን፤ የሚመጣው ግን እነርሱ "በህይወት እያለን የሚመጣ" ነው ብለው ተስፋ ያደረጉትና ከዚያን ጊዜ የጀመረውና እኛም ያለንበት፣ ለዘላለምም የማይዘጋው የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነውና ያም ሕይወት በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት በሙላት ተገልጧል። ለጥንት ክርስቲያኖች ያ የሚመጣው ሕይወት የሚመጣበት ጊዜ የማይታወቅ ሳይሆን፣ ይልቁንም mello /ሊመጣ ያለው/ የሚለው የግሪክ ቃል ጊዜው ያንን ሕይወት ተስፋ ያደርጉ ለነበሩቱ ቅርብ አይቀሬ እንጂ ሩቅና ጊዜውን ማሰብ የሚቸግር አልነበረም። ስለዚህ ያንን ሕይወት ለመቀበል እነርሱ ጋር የነበረውን ከፍ ያለ መጠባበቅና ጓጉቶ መናፈቅ በዚህ  mello በተሰኘ ቃል ውስጥ በጉልህ እናየዋለን።


  1. 2ጢሞቴዎስ 4፥ 1 "በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው [mello] በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤" [በሚፈርደው ሳይሆን ሊፈርድ ባለው ነው]


  • ይህ ጥቅስ የመጻኢያንን አመለካከት ለመደገፍ በሚደረግ ክርክር ላይ ያለውን ጉዳይ ሁሉ ይዘጋዋል። mello የተሰኘውን የግሪክ ቃል ፍትሃዊና አግባብነት ባለው መልኩ በትክክል እንተርጉመው ካልን ይህ በግልጽ የሚናገረው ስለ ምንድን ነው? ቃሉ እነደሚያሳየው ኢየሱስ ያኔ ነው በህያዋን እና በሙታን ላይ ሊፈርድ ያለው። እርሱ በህያዋን እና በሙታን ላይ በሚያደርገው ፍርዱ እና በመገለጡ መካከል ግልጽ ግንኙነት ያለ በመሆኑ ላይ ምንም ጥርጥር የለም። ፍርዱ ሊመጣ ያለው ከነበረ እንግዲያውስ መገለጡ እና መንግስቱም ሊመጣ ያለው ነበር ማለት ነው። ክርስቶስ በተመለሰበት ጊዜ ክፉዎች ሁሉ ተፈርደው ያኔውኑ ወደ ዘለአለማዊው ሥቃይ ተጥለዋል፣ ያም ደግሞ ሌሎች ክፉዎች ሁሉ በሚሞቱበት ቅጽበት የሚሄዱበት ስፍራ ነው። የሰው ዘር ሁሉ ወኪል የሆነው አዳም በገነት ውስጥ ሳለ ያጣውን ያንን የትንሣኤ ሕይወት፣ ጻድቃን የሆኑ ሁሉ ግን ለመጀመርያ ጊዜ በእግዚአብሔር ሀልዎት ፊት መልሰው ወርሰውታል። የትንሳኤ ህይወት "ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ" (ራእይ 2፥ 7) እንደሚል፣ ገነትን ማስመለስ ነው። የህይወት ዛፍ የሆነው ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት ሰጥቶናል።


  1. እብራውያን 1፥ 13-14 "ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው [mello] ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?"  [መዳንን ለሚወርሱ ሳይሆን ይወርሱ ዘንድ ላላቸው ነው]


  • ያኔ የክርስቶስ ጠላቶች እነማን ነበሩ? በማቴዎስ 23 "ግብዞች"፣ "የነብያት ገዳዮች ልጆች" ተብለው የተነቀፉ፤ በሉቃስ 19፥ 11-27 "ክፉ ባርያ" ደግሞም "ጠላቶቼ" ያላቸው፤ በሐዋርያት 7፥ 51-53 "አንገተ ደንዳኖች"፣ "ያልተገረዙ"፣ "ተቃዋሚዎች"፣ "አሳዳጆች"፣ "ነፍሰ ገዳዮች"፣ "ሕግን ያልጠበቁ" ተብለው የተወቀሱ፤ በሮሜ 11፥ 28 "የወንጌል ጠላቶች" በሚል መጠሪያ የተገለጡ፤ በፊልጵስዩስ 3፥ 2፣ 18፣ 19 "ውሾች"፣ "ክፉ ሰራተኞች"፣ ብሎም "የመስቀል ጠላቶች" ወዘተ እየተባሉ በግብራቸው የተጠቀሱት አይሁድ ናቸው። እነዚህ የክርስቶስ ጠላቶች የተባሉ ልባቸውን በምድራዊው ነገር ላይ ያደረጉ፣ በሰማያዊውም የተስፋ ቃል ላይ ያመጹ ናቸው። ክርስቶስ ግን የጠላቶቹን ራስ፣ ሞትንም ጭምር ቀጥቅጧል። ለዘላለምም ሁሉን ይገዛ ዘንድ በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል፤ ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም። ከውድቀት ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ በሰማይ ያለውን መዳናቸውን (ቤዛነታቸውን) ይወርሱ ዘንድ አላቸው። አማኞች ይወርሱት ዘንድ ያላቸው መዳን ምን ይሆን? አስቀድሞውኑስ ድነው አልነበርምን? በመላው አዲስ ኪዳን ሞልቶ በሚፈስ ምስክርነት አዎ ደግሞም አይደለም! ብለን ብንመልስ ግር የማይለው ይኖራልን? የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ከሞቱ በኋላ ሄደው የሚከማቹበት እና ሙሉ የሆነውን ቤዛነታቸውን እየተጠባበቁ የሚቆዩበት ሀደስ የተባለው ስፍራ ያኔ ገና በስራ ላይ ነበር። ኢየሱስ ለመጀመርያው ከፍለዘመን ደቀመዛሙርቱ በሉቃስ 21፥28 ላይ "ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና (እናንተ) አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ" ሲል የተናገራቸውን አስታውሱ። ይህ እንግዲህ ቀደም ሲል ሊሆን ያለው በሚል ለማሳየት የተሞከረው ለአዲስ ሕይወት የመነሳት ትንሳኤ ነው። ይህም በቅበት አይን ሊለወጡ ያለበት፣ ሞትም ድል በመነሳት ሊዋጥ ያለበት፣ የሚሞተውም የማይሞተውን ሊለብስ ያለበት፣ ፍጥረታዊው ሆኖ የሚታየውም መንፈሳዊ ሆኖ ሊነሳ ያለበት የ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ፍጻሜ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሞት አያሸንፍም፣ መውጊያም ደግሞ የለውም፤ ብንሞትም ህያዋን ነን፣ ህያዋንም ከሆንን ፈጽሞ አንሞትም! ልንል እንችላለን። ያለ ትንሳኤ ይህንን ለራሳችን ማድረግ አንችልም፣ ስለዚህ ሁላችንም በምንሞትበት ጊዜ በቀጥታ ወደ ሰማይ ሳይሆን በተቃራኒው ገና የወደፊቱን የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ልንጠባበቅ ወደሀደስ እንሄዳለን ማለት ነው፤ ይህ ግን በእግዚአብሔር ቃል ላይ መዋሸት ይሆናል። ትንሳኤ ገና ወደፊት እንጂ ከአሁን በፊት አልሆነም ብለው የሚያምኑ መጻኢያን አስተማሪዎች፣ ያኔ በመጀመርያው ክፍለዘመን እንደሚሆንና ሊሆን እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተናገረለት ያ ትንሳኤ ገና ሳይሆንና ያም ፍርድ እስካሁን ሳይፈጸም በፊት፣ አማኞች አሁን በሚሞቱበት ጊዜ የትንሳኤን ቀን ሊጠባበቁ ሁሉም ወደ ሀደስ የሚሄዱ ስለሆነ፣ ወደሰማይ እንደሚሄዱ አድርገው የሚያስተምሩትንና ምዕመናንን የሚዋሹትን ነገር ፈጽሞ ማቆም አለባቸው።


  1. እብራውያን 2፥ 5 " ስለ እርሱ የምንናገርበትን የሚመጣውን [ሊመጣ ያለውን mello] ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና።" [የሚመጣው ዓለም/ ዘመን ሳይሆን ሊመጣ ያለው ዓለም /ዘመን ነው]


  • እዚህ ላይ ጸሐፊው ለመላእክት ተገዝቶ የነበረውን ዓለም አንስቶ ይነጋገራል።  ለመላእክት ተገዝቶ ከነበረው አለም (ይህም የሙሴ ዘመን ነው) ጋር ይህ እንዴት ይነጻጸራል? በሐዋርያት 7፥ 51-53 "አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ" የተባሉትን ተመልከቱ። ነብያትን እያሳደዱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የነገሩአቸውን ይገድሉ እንደነበረው ሁሉ አይሁድም ልክ አባቶቻቸው ያደርጉ እንደነበረው አይነት አይሁድም መንፈስ ቅዱስን ይቃወሙ ነበር (ማቴዎስ 23 ተመልከት)። ሕጉን በመላእክት ትእዛዝ የተቀበሉ ቢሆኑም እንኳ ዳሩ ግን አልጠበቁትም፣ ይልቁንም በክፋታቸው ብሰው ነፍሰ ገዳዮችና አሳልፈው የሚሰጡ ከሃዲዎች ሆኑ። አሮጌው ኪዳን በመላእክት ትእዛዝ የመጣ ነበር፣ ይመጣ ዘንድ ያለው አዲሱ ግን ለኢየሱስ እንጂ "ለመላእክት የሚገዛ" አይደለም። የዚህ መልእክት ጸሐፊ ለመጀመርያው ከፍለዘመን ተደራስያኑ "ስለምንነጋገርበት" ብሎ መጻፉን ልብ አድርጉ። የ70ው አ.ም ፍርድ ገና የተከናወነ ባለመሆኑ፣ ይነጋገሩታል እንጂ ያኔ ሁሉም ነገር በኢየሱስ የተገዛ እንደነበር ገና አላዩም።


  1. እብራውያን 6፥ 5 "መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን [mello] የዓለም ኃይል የቀመሱትን" [ሊመጣ ያለው እንጂ የሚመጣው አይደለም]


  • ከክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በፊት የነበረው የጥንት ቤተክርስቲያን ዘመን፣ እርሱም ከበአለ ሃምሳ እስከ 70 አ.ም ያለው የአርባ አመታት የሽግግር ወቅት፣ በሙላት ሊገለጥ ያለውንና "ሊመጣ ያለውን [mello] የዓለም ኃይል" የተለማመዱበት የቅምሻ ወቅት ነበር። በሽግግሩ ወቅት በቅምሻ ደረጃ የተለማመዱት ሊመጣ ያለው የዓለም ኃይል በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በሙላት ተገልጧል። የእግዚአብሔርን ቃል እንደተጻፈ ብናምን አሁን እኛ በዚያ የአዲሱ አለም ኃይል ውስጥ እርሱም በአዲሱ ኪዳን ውስጥ እንኖራለን።


  1. እብራውያን 9፥ 11 "ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው [mello] መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥" [ለሚመጣው መልካም ነገር ሳይሆን ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ነው]


  • ይህ በዚያን ዘመን ከነበረው ቤተመቅደስና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ካላቸው ነገሮች ጋር ግልጽ የሆነ ተቃርኖ ነው። እንዲህ ያለው ንጽጽርና ተቃርኖ የእብራውያን መልዕክት አንዱ ገጽታ መሆኑን ለማስተዋል እብራውያን 8፥ 6-13፤ 9፥ 8-12፣ 15 ይነበብ። ይህ መልዕክት በሚጻፍበት ጊዜ ምድራዊው ቤተመቅደስ ገና በስፍራው ቆሞ ሳለ ሊቀ ካህናቱ ክርስቶስ በሰማያት ካለችው እውነተኛይቱ ቅድስት ወጥቶ ገና አልታየም ነበር። በብሉይ ኪዳን ሊቀካህናቱ የእንስሳውን መስዋእት ካቀረበ በኋላ በዚያ የስርየት ቀን ደሙን ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል። ሊቀ ካህኑም ከቅድስተ ቅዱሳን ወጥቶ ወደ ህዝቡ ወደ አውደምህረቱ ሲመጣ ያኔ ዋናውና ትክክለኛው የስርየት አዋጅ ይገለጣል። እግዚአብሔር ስለኃጢአት ስርየት የቀረበውን መስዋእት ተቀብሎ የህዝቡን መተላለፍ ይቅር እንዳለ አይነተኛ ማረጋገጫው የሊቀ ካህኑ ከቅድስተ ቅዱሳን ወጥቶ መታየቱ ነው (ዘሌዋውያን 16፥ 16-18)። ነገር ግን የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ሊያስወግድ አይችልም (እብራውያን 10፥ 4)። ኢየሱስ ግን ሊያስተሰርይ ከገባበት ቅድስት በዳግመኛ ምጽአቱ ወጥቶ የመጣ በመሆኑ አሁን መዳናችን ፍጹም ሆኖአል፤ ስለዚህም እርሱ ምርጦቹን ሁሉ በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ክብር፣ ወደ ሀልዎቱ አምጥቷቸዋል።  ጳውሎስ፣ በመጀመርያው ከፍለዘመን የ70 አ.ም ዳግመኛ ምጽአቱ ላይ፣ ያኔ አዲሱ ኪዳን በሙላት ተጠናቆ ሲገለጥ፣ "እስራኤል ሁሉ (በልባቸው የተገረዙ መንፈሳዊው እስራኤል) ይድናል" ሲል ሊተነበይ የተቻለውም ለዚህ ነው። ስለዚህ ነው እኛም በሮሜ 11፥ 5፣ 25-29 እንደተጻፈ ቤተመቅደሱ በወደመበት ጊዜ በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ በስጋ እስራኤል የሆኑ ሁሉም የተመረጡቱ ድነዋል የምንለው፣ (እብራውያን 9፥ 15፣ 28 ተመልከት)። የሐዋርያው ጳውሎስ "እስራኤል ሁሉ ይድናል" እና የነብዩ ዳንኤል "በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።" የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጽሟል። አብርሃም ሲጠብቃት የነበረውን "እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማም" (እብራውያን 11፥ 10) ክርስቶስ በመምጣቱ አምጥቷታል። ክርስቶስ ስላመጣው ነገር የሚበልጠውና እና ፍጹም የነበረው ምን ነበር? አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለዘላለም ኃጢአትን ማስወገዱ ነው። ከዚያም ወዲያ ኩነኔ የለም (ሮሜ 8- ሞት)፣ ከእግዚአብሔር ሀልዎት መነጠልም (ሮሜ 8- ሀደስ) የለም! ታዲያ ብዙዎች እነርሱ ለገዛ ራሳቸው ፈጽሞ የማይመኙትን ጉዳይ ይኸውም ሞትና ኩነኔን፣ ከእግዚአብሔርም ሀልዎት ተነጥሎ በሀደስ መሆንን ለአብርሃምና ለሌሎች የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ለምን ይናፍቁላቸዋል? ምጽአቱ እስካሁን አልሆነም የሚለው የመጻኢያን ትምህርት አብርሃምንና በእቅፉ ያሉትን ልጆቹን ከእግዚአብሔር ሀልዎት አርቆ፣ ሲናፍቋት ከነበረው ከተማ አርቆ በሀደስ ውስጥ ገና አሁንም ለሺህዎች ዘመናት ይረሳቸዋል። እነርሱ ግን የተስፋውን ቃል በሩቅ እያዩ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች ሆነው ራሳቸውን በባዕድ አገር እንደሚኖሩ አድርገው ይቆጥሩና ይጠባበቁ ነበር። የሚሻል ሰማያዊ አገርም ይናፍቁ ነበር። ያ የሚናፍቁት ደርሶላቸዋል። ከዚያን ጊዝ ጀምሮ ሁሉም የእግዚአብሔር ምርጦች ሞት አይገዛቸውም፣ ኩነኔም የለባቸውም፤ ሀደስ አያስፈራቸውም፣ ከእግዚአብሔር ሕይወትና ሀልዎት የመነጠል ስጋት የለባቸውም። እኛ የዳንን በምንሞትበት ጊዜ ይህንን ሰውነታችንን አውልቀን ጥለን በምንቀበለውና በተዘጋጀልን አዲስና መንፈሳዊ በሆነው የማይሞት አካል በሰማያት ከእግዚአብሔር ጋር እንደምንሆን በጽኑ አምናለሁ።


  1. እብራውያን 10፥ 1 "ሕጉ ሊመጣ ያለው [mello] የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።" " [የሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ያለው ነው]


  • የእብራውያን ጸሐፊ የአይሁድን ህዝብ ሊያስታውሳቸው የሚፈልገው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜውን ሊያገኝ ያለውን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ነው። "ጥላ" የተባለውም በቅርቡ "ሊመጣ ባለው በጎ ነገር" ሊተካ ያለው ሕጉ ነው።


  1. እብራውያን 10፥ 26፣ 27 "የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው [mello] የእሳት ብርታት አለ።" [የሚበላው ሳይሆን ሊበላ ያለው ነው]


  • ይህ ለነዚያ የለክርስቶስ ሆነው ለቀሩ ሁሉ በክርስቶስ ጠላቶች ላይ ሊደርስባቸው ስላለው የያኔው ፍርድ  የተሰጠ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ነው። ስለዚህ መልእክቱ በዘመኑ የነበሩትን አይሁድ ከያዙት የጥፋት ጎዳና ዘወር ብለው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለሱ ማስጠንቀቅ ነው፣ አለበለዚያ እየመጣ ያለውና ሊገናኛቸው የተዘጋጀው የእግዚአብሔር ቁጣ ይበላቸዋል። እብራውያን 10፥ 25-39 ያለው ምንባብ በአውዱ ቢነበብ የተሻለ ነው።


  1. እብራውያን 13፥ 14 "በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን [mello] እንፈልጋለን።" [ትመጣ ዘንድ ያላትን እንጂ የምትመጣዋን አይደለም]


  • እብራውያን 11 እና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ይጠባበቁት የነበረውን ጉዳይ አነጻጽሩት፤ ይህ ጥቅስ በግልጽ የሚናገረው ስለ የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ነው እዚህም ላይ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም (ያረጀ፣ አሮጌ፣ ውራጅ፣ ያኔ ሊጠፋ የቀረበ፣ ሊመጣ ላለውም ነገር ጥላ የሆነው -እብራውያን 8) እና ትመጣ ዘንድ ባላት በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (እብራውያን 11፥ 16፤ ራእይ 21፥ 1-7፣ 9-10) መካከል ያለውን ንጽጽርና ተቃርኖ እናያለን። አሮጌዋ ኢየሩሳሌም ፈጽሞ ተደምስሳ ከተወገደችና ውራጅ ሆና ከጠፋች በኋላ 

  • አዲሲቱ ትገለጣለች።


  1. 1ጴጥሮስ 5፥ 1 "እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው [mello] ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤" [ሊገለጥ ካለው ክብር እንጂ ከሚገለጠው አይደለም]


  • ይህ ጉዳይ የሚሆነው በዚያን ዘመን፣ በእነዚያ ቀናት ለነበሩ ሰዎች ነው። ጴጥሮስ ሊገለጥ ያለ ክብር እየመጣ መሆኑን ተረድቷል። በእግዚአብሔር መንፈስ እየተነዳና በመጨረሻው ዘመን ላይ መሆኑን እያወቅ  የሚጽፍ መሆኑን ልብ አድርጉ (1ጴጥሮስ 1፥ 4-13፣ 20፤ 2፥ 6-8፤ 4፥ 7 በጥንቃቄ ይነበብ)። በምዕራፍ 4፥ 13 ላይ ጴጥሮስ አስቀድሞ በመልዕክቱ እነዚያ የመጀመርያው ክፍለዘመን አንባቢዎቹን ሊመጣ ያለው ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ሐሴት አድርገው ደስ እንደሚላቸው ጽፎላቸው እንደነበር አስታውሱ።


  1. ያዕቆብ 2፥ 12 "በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው [mello] ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ።" [ፍርድን እንደሚቀበሉ ሳይሆን ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ነው]


  • የያዕቆብ መልዕክት ተደራስያን "የተበተኑ አስራ ሁለቱ ወገኖች" ማለትም ዳያስፖራው የአይሁድ ክርስቲያን ወገን ነው። ጥቅሱም የሚያወራው ያኔ ለእነርሱ ቀርቦ ስለነበር ፍርድ ነው። ሕጉም ያላቸውና በሕጉ የሚፈረድላቸውና የሚፈረድባቸው እነርሱው ናቸው፣ እንጂ ሕጉ የሌላቸውን ያለ ሕግ የሚፈረድባቸውና የሚፈረድላቸው አህዛብ ክርስቲያኖች አይደሉም። አይሁድም ያንን ፍርድና ዳኝነት የሚቀበሉበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ንግግሩ ያሳያል። ይኸውም በ70 እ.ም የተፈጸመ ሲሆን ሕጉ ሳላቸው ለሕጉ ባለመታዘዝ ክርስቶስን ያላመኑትን ሁሉ እንደ ሕጉ ፈርዶ ሲያጠፋቸው፤ ሕጉ የመሰከረለትን በክርስቶስ የማመን ነጻነትን ተቀብለው የዳኑትን ትሩፋን ግን ፈርዶላቸዋል።


  1. ራእይ 1፥ 19 "እንግዲህ ያየኸውን (ራእይ 1፥ 9-20) አሁንም ያለውን (ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላከው ደብዳቤ ይዘት ራእይ 2፥ 1-3፥ 22) ከዚህም በኋላ (ራእይ 4፥ 1-22፥ 5) ይሆን ዘንድ ያለውን [mello] ጻፍ።" [የሚሆነውን ሳይሆን ይሆን ዘንድ ያለውን ነው]


  • የራእዩ መጽሐፍ የያዛቸው ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ይህ "ይሆን ዘንድ ያለው" በሚል የተገለጸው የመጨረሻ ክፍል በዮሐንስ ትውልድ ውስጥ ሊከናወን መሆኑን ልብ በሉ። ይህንን የሚናገረው ኢየሱስ ነው፣ ጻፍ ብሎ ትዕዛዝ የሚሰጠውም በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ ይኖር ለነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ነው። ይህ "ከዚህ በኋላ ይሆን ዘንድ ያለው" በሚል የተጠቀሱት  ጉዳዮች ይፈጸማሉ ተብሎ በግልጽ ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸውና የተነገሩት ለመቼ ነው? ከተባለ ቶሎ፣ በቅርቡ፣ በቶሎ (ራእይ 1፥ 1፣ 3፤ 22፥ 6፣ 7፣ 12፣ 20) ነው፤ ይህም ያኔ ዮሐንስ ይኖርበት ለነበረው ዘመን ቅርብ የሆነ ጊዜ ማለት ነው (ራእይ 1፥ 3፤ 22፥ 10)። እነዚህ ቃሎች በውስጣቸው የፍጥነትን እና የችኮላን ሃሳብ የያዙ ሲሆን፣ በጥቅሉ ይሆናሉ የተባሉት አይቀሬ ጉዳዮች ለፍጻሜአቸው የማይዘገዩና በዘመኑም ይህንን ለሰሙ በኩረ ተደራስያኑ "ጊዜ የለም" የሚል መልዕክት አላቸው። በግልጽ ቋንቋ የተነገሩትን እነዚህን አይቀሬ ንግግሮች እንዳለ እንደተጻፈው ከመቀበል ይልቅ፤ መካድ፣ ማሻሻል፣ ማስተባበልም ሆነ ለገዛ ራሳችን አስተምህሮ ትክክለኛነት ተጨንቀን "አይ እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው" ብሎ ለቃሉ እርማት ለመስጠት የሚደረግ ሙከራና ማብራርያ ሁሉ፣ በማያምነው አለም ፊት ኢየሱስን ሐሰተኛ ነብይ፣ ሐዋርያቱንም ሐሰተኛ መምህራን፣ ክርስትናችንንም ሐሰተኛ ኃይማኖት ያደርጋቸዋል። ቅዱሳን ወንድሞቼ ሆይ፣ ቃሎቹ በያዙት አይቀሬነትና ጊዜ ጠቋሚነት ተስፋ ቆርጣችሁ፣ እነዚህ ንግግሮች ላይ 2ኛ ጴጥሮስ 2፥ 8 ላይ ያለውን ቃል ያለቦታው እየጠቀሳችሁ፣ ይግባኝ በማለት እንዲሰረዙላችሁ ወይም ቃሎቹ የሌሉ ያህል ወደ ጎን እንዲተውላችሁ አታስቡት፤ እግዚአብሔር ተናግሯቸዋልና የሚያድነን፣ የሚያቆመንና የሚያጸናን በተጻፈው እውነት አንጻር መጎንበስ ብቻ ነው እንጂ፤ አይቀሬነትን የያዙትን እነዚህን መግለጫዎች በራሳችን መንገድ ለማብራራት መሞከር ፈጽሞ የለብንም።


  1. ራእይ 3፥ 10 "የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው [mello] ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።"" [ከሚመጣው ሳይሆን ሊመጣ ካለው ነው]


  • "ዓለም ሁሉ" የሚለው መላውን የሮምን ግዛት ያመለክታል (ሉቃስ 2፥ 1) ፈተናውን ግዛቱን የሚያናውጥ ፈተና ነው። እንዲሁም በምድሪቱ በእስራኤል ነዋሪዎች ላይ ስለሚከሰት ፈተና እርሱም "ታላቁ መከራ"  የተነገረ ቃል ነው። በ 68 አ.ም ላይ የኔሮን ሞት ተከትሎ በ70 አ.ም ቨስፓስያን የሮም ንጉሰ ነገስት እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በሚቀሰቀስ የሮም የእርስ በርስ ጦርነት በመላው የሮም አለም ላይ ነውጥ ይኖራል፣ ይህም በተለይ አይሁድን ጭንቅ ውስጥ ይከታቸዋል። ጌታ የሚናገርለት የተለየ አለምአቀፋዊ ፈተና ይህ ነውና ይህ የፈተና ጊዜ የፊላደልፊያ ቤተክርስቲያን በነበረችበት ዘመን እና ስፍራም የሚኖር "ሊመጣ ያለው [mello]" ፈተና ነው። ጌታም ይህችን የፊላደልፍያ ቤተክርስቲያን ለመጠበቅ የሰጠው ተስፋ ሊፈጸም የሚችለውና የሚፈጸመው በዚያው በቤተክርስቲያኒቱ ዘመን ነው።


  1. ራእይ 12፥ 5 "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን [mello] ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።" [የሚገዛቸውን ሳይሆን ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ነው]


  • አማርኛው መጽሐፍ ቅዱሳችን "ይገዛቸው ዘንድ ያለውን" በማለት የግሪኩን mello በአግባቡ  አስፍሮታል። "ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።" (ዮሐንስ 3፥ 13)፣ እንደተባለ ሁሉን ሊገዛ በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የተነጠቀው ልጁ  ኢየሱስ ብቻ ነው። እርሱም እንደ ዮሐንስ ራእይ ገለጻ "አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለው" የተባለለት የእግዚአብሔር ወንድ ልጅ ነው። አገዛዙም የሚጀምረው ቀያፋ በነበረበት የሕይወት ዘመኑ፣ ኢየሱስ ሁሉን ሊገዛ "በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ" ይህንን ለማየት (ማቴዎስ 26፥ 64) የተነገረው ቃል ፍጻሜ ላይ ነው።



አንዲት አነስተኛ የምትመስል ቃል በአረፍተ ነገር ትርጉም ውስጥ ያላትን ቦታና ዋጋ አሳንሶ፣ በበኩረ ቋንቋው ውስጥ ያላትን ጠቀሜታ ሳይረዱ ለመተርጎም መሞከር፣ በእውነትም ከፍ ላለ የአስተምህሮ ህጸጽ ይዳርጋል። በዚህች አንዲት የግሪክ ቃል ላይ የተሰራ መቀባባትም ሆነ ማድበስበስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዳግመኛ ምጽአቱን አይቀሬነት የሚያመለክቱ እና፣ ከፍተኛ ጠቀሜታና ትርጉም ያላቸውን፣ ለምሳሌ እንደ "ቅርብ ነው"፣ "በደጅ ቆሟል"፣ "ፈጥኖ"፣ "ቶሎ"፣ "ቶሎ የሚሆነውን"፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" ወዘተ የመሳሰሉትን ቃላትና ሀርጎች አሁንም ገና ካልታወቁ ሺህዎች አመታት በኋላ ወደፊት በማናቸውም ጊዜ ሊሆኑ እንደሚችሉ አድርጎ በመውሰድ የሚያስከትለው የትርጉም ስህተት ጉልህ ከመሆኑም በላይ፣ አድካሚና የሌለ ነገር መጠበቅም ይሆናል። እነዚህ ሊሆኑ ያሉ (Mello) ነገሮችን የሚያመለክቱ ሀረጎች እና አረፍተ ነገሮች እንድናምናቸውና እንድንታዘዛቸው በቀጥታ የተሰጡትና የተነገሩት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በኢየሱስ፣ በሐዋርያቱና በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሆኖ ሳለ፣ የተያዝንበትን የኖረ አመለካከታችንንና የእምነት አቋማችንን ለማጽደቅ በሚሆን ግብዝነት ቃሉ ላይ አንዳች በመጨመር ወይም ከቃሉ አንዳች በማጉደል 'አይ የለም እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው' በሚል እግዚአብሔርን እና ቃሉን ለማረም የምናደርገው ጥምዘዛና ሙከራ ሁሉ በእውነትም በደል ነው (ዘዳግም 4፥ 2)። ቃሉ የማይለውን ወይም ሊል ያልፈለገውን እንዲል ልናስገድደው፣ ያለውንም ከማመን በቀር አላልክም ብለን ልንሸነግለው፣ ወይም ያለውን አይ እንዲህ ሊል ፈልጎ ነው ብለን ልንዋሸውና ልናታልለው ምንም መብት የለንም። ስለዚህ፣ በእውነት የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ያሉትን ነገር በእርግጥ የምራቸውን ብለውታልን? እነዚህስ ነገሮች በ70 አ.ም ላይ ተፈጽመዋልን? ለዚህ ጥያቄ ኃላፋውያን መልሳቸው ፍርጥም ያለ "አዎ"! ሲሆን፣ መጻኢያን ግን በመልሳቸው ሽምጥት አድርገው "አይደለም"! ይላሉ ።


አንድ ሰው በዚህ Mello በተሰኘ ቃል ጠቀሜታ ላይ ያፈጠጠውን እውነታ፣ እርሱም ለመጀመርያው ከፍለዘመን ቤተክርስቲያን መጨረሻው ሊደርስ እንደሆነ ትርጉም ይሰጣቸው የነበረውን የጉዳዩን እርግጠኝነት እና አይቀሬነት  ለመቀበል ቢያቅማማ እንኳን፣ የጌታን መመለስ እርግጠኝነቱና አይቀሬነቱ ቃሉ በተነገረበት አውድና ትውልድ ወቅት በቅርቡ ተፈጻሚ እንደሚሆን የሚያሳዩ ሌሎች ከፍ ሲል የጠቀስናቸው እንደ "ቅርብ ነው"፣ "በደጅ ቆሟል"፣ "ፈጥኖ"፣ "ቶሎ" "ቶሎ የሚሆነውን"፣ "ይህ ትውልድ አያልፍም" ወዘተ የመሳሰሉ ቃላትና ሀረጎችን ምን አድርጎ ሊያስተባብላቸው ይችላል? ተመልከቱ፣ መጻኢያን እነዚህን ከዮሐንስ ራእይ የተወሰዱትን ቃላትና ሀረጎች ሲተረጉሙ፣ "ትንቢቱና ራእዩ እስካሁን ድረስ ገና አልተፈጸመም ዳሩ ግን አንዴ መፈጸም ከጀመረ ቶሎ ቶሎ ይሚፈጸም መሆኑን ያመለክታሉ" ይላሉ፤ ከማቴዎስ 24 የተወሰደውንም "ይህ ትውልድ አያልፍም" የሚለውን "የእስራኤል መንግስት እንደገና መቋቋሙን በአይኑ የሚያየው ትውልድ ጌታ እስኪመጣ ድረስ የሚቆየው ትውልድ ነው" ሲሉ ይተረጉማሉ። ይህ ግን ቃሉ የማይለውን እንዲል መጠምዘዝ ነው። በመጀመርያው ከፍለዘመን ላይ ተመልሶ እንደሚመጣ የተናገረው የኢየሱስ ቃል በትክክል ያኔውኑ እርሱ እንደተናገረው ሆኗል ብለን ለማመን ግን በብዙ ማስረጃ ምስክር የምንጠራው ራሱን የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ነው (ለምሳሌ፣ ማቴዎስ 24፥ 33-34፤ ማቴዎስ። 10፥ 23፤ ማቴዎስ 16፥ 27-28፤ ያዕቆብ 5፥ 8-9፤ ራእይ። 1፥ 1፤ ራእይ 22፥ 7) 


በሦስተኛው መቶ ከፍለዘመን መገባደጃ ላይ የክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ኢውሳብዮስ የተናገረውን ልጥቀስ፤ የጌታ ወንድም ስለነበረው ስለ ያዕቆብ የጻፈው ይህ ነበር፣ ያእቆብ ተከሶ ከአይሁድ መሪዎች ጋር በተከራከረ ጊዜ "እርሱም (ያእቆብ) ድምጹን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፣ 'ኢየሱስን የሰው ልጅ ነው ብዬ እንዳከብረው ብቻ ለምን ትጠይቁኛላችሁ? እርሱ አሁን በታላቁ ኃይል ቀኝ በሰማያት ተቀምጧል፣ በሰማያት ደመናም ይመጣ ዘንድ አለው' ሲል ተናገራቸው" ይላል፤ (Eusebius Ecclesiastical History p. 77 ተመልከቱ)። የኃላፋውያን ምልከታ ከቅዱሳት መጻህፍት ጋር የሚስማማ ነው፤ የትርጉም ፍሰቱም ቀዋሚነትን ጠብቆ ከቃሉ ጋር አብሮ የሚፈስ ነው። አቋማችንም ከሁሉ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ይተርጎም የሚል ነው።  የግሪክ ቃላትንና አንዳንድ ታሪክ አዋቂዎችን ስፈትሹና ስተመልከቱ ያኔ የኃላፋውያን አቋምና አቋቋም በየትኛውም የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ላይ ጠንካራና አስተማማኝ መከላከያ እንዳለው ታያላችሁ። ከፍ ሲል በዝርዝር ባቀረብኳቸው ምንባባት አንጻር መጻኢያን ራሳቸውንና ትምህርታቸውን እንዴት መመከትና መከላከል እንደሚቻላቸው አላውቅም። የቃሉ ተማሪዎች ነን ካልን ግን "የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነን፥ የተፈተነውን ራሳችንን ለእግዚአብሔር ልናቀርብ ልንተጋ።" (2ጢሞቴዎስ 2፥ 15) ይገባናል እንጂ በቅጡ ባላጠናነውና ባላሰብንበት ርዕሰ ጉዳይ ቀደዳ ልናበዛ አይገባንም።


በዚህች አንዲት የግሪክ ቃል ላይ ሲሰራ የኖረውን ስህተት ለማረም በሚሆን ሰበብ ግን ትዕቢተኛና ተጨቃጫቂ የመሆን ፍላጎት የለኝም፤ ነገር ግን ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻችን እና በአስተምህሯችን ውስጥ በአግባቡ እንዲቀመጥና ዋጋ እንዲሰጠው መስራት እንዳለብን አምናለሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ በተለቀሙ ቃሎች፣ ሀረጎች እና ቋንቋዎች ላይ፣ ተገቢ ትርጓሜአቸውን እና ጠቀሜታቸውን ከማጣጣምና ከመማማር ባለፈ፣ እጅግ በበዛ የወግ አጥባቂነት አጽንዖት ተይዘው ክርክር የሚመቻቸው ሰዎችንም ሳይ መንገዴን ቀይሬ እሄዳለሁ እንጂ "ይዋጣልን" የምል አይደለሁም። ምክንያቱም ደጋግሜ ለማየት እንደታደልሁት እንዲህ ያሉ ጉንጭ አልፋ አድካሚ እሰጥ እገባዎች መጽናናት የሞላባቸውን ቅዱሳት መጻህፍት ያላቸውን ንጹህና ግልጽ ትምህርት አግኝቶ ከመታነጽና ከመተናነጽ ይልቅ ግልጽና ንጹህ የሆነውን ሌላውን የቅዱሳት መጻህፍት ትምህርት የሚደፈጥጡ ወይም ዋጋ የሚያሳጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ኪሳራ የሞላበት እንዲህ ያለው መታለል ድርሻዬና እድል ፈንታዬ እንዲሆንም አልፈቅድለትም። ለምሳሌ፣ በአሽከርካሪ የመንገድ ላይ ስርአትና ደንብ የተቀመጠው "ቁም" /STOP/ የተሰኘውን አስገዳጅ ምልክት ያየ አሽከርካሪ፣ "ቁም ማለት በእግርህ ቁም /STAND UP/ ማለት ነው" ብሎ በመተርጎም ከገገመና ከተሽከርካሪው ወጥቶ በእግሩ ሊቆም ከወደደ፣ "ስራህ ያውጣህ" ብዬ ከመተው በቀር ምን አድርጌ ላርመው እችላለሁ?። ልክ በዚሁ አይነት ብዙዎች የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ የሚያቀነቅኑ መምህራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ላሉ አንድንድ ወሳኝ ቃላት የሚሰጡት ትርጉም ቃሉ የማይለውን ሌላ ነገር እያስነበበን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ልንማማርና ልንደማመጥ ካልቻልን በቀር እንዲህ አይነቱ ጭቅጭቅ በሚፈጥረው ስሜት ወንድሞቼን ማጣት ግን ስለማልመኘው እየታዘብኩ ለማለፍ እገደዳለሁ።


በመጨረሻም፣ ወንጌል አማኝ ለሆኑቱ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ተስፋም ጸሎትም ያለኝ መሆኑን አልሸሽግም። ከሁሉ አስቀድሞ፣ በተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉ መጻኢያን ወንድሞቼና እህቶቼ የትኛውንም የነገረ ፍጻሜአዊ ጎራ ተተግነውና ያላቸውን የነገረ ፍጻሜ አቋም ይዘው ከዘመን መዳብያን (Dispensationalism) አስተምህሮም ሆነ ከየትኛውም የለዘብተኛው ስነ መለኮት 'ክህደትና' የዘመነኛው ኒዎ ጰንጠቆስጤ 'እብደት' እምነታቸውን መከላከል እንደማይችሉ ይህን አንድ ነገር ሊያውቁ ይገባል። ምክንያቱም የሚከተሉት የነገረ ፍጻሜ ትምህሮታቸው ክህደትን የሚያሾልክ አንዳች ቀዳዳ ነገር አለበት። "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" ብለው መቆም የሚፈልጉ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ኃላፋዊነትን ከመቀበልና ነገረ ፍጻሜአዊ አስተምህሮአቸውን ከመከለስና ከማረም ውጭ ቀዳዳቸውን የሚከድን ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም። ሙሉ ኃላፋዊነትን ከተቀበሉ ብቻ የተሃድሶው ቤተ እምነት ብቸኛ ጡንቻ የሆነው "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" የሚለው ታሪካዊው አቋማቸው ከማንኛውም የተሳሳተ ኃይማኖት እምነታቸውን መከላከል የሚችሉበት መሰረት ይሰጣቸዋል። ደርዝ ባለው አስተሳሰብ በቅንነት እምነታቸውን የሚጠይቁ፣ በትህትናም የቃሉ ተማሪ ለመሆን የሚወዱና ኃላፋዊነትን የሚቀበሉ የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ልዩነትን ማድረግ ይችላሉ። ዘመነኛው ክርስትና ለዛውን ከማጣት፣ ተረት ተረት ሆኖ እንደ ኃሰተኛ ኃይማኖት፣ ሴክትና ከልት መስሎ ከመቆጠር የሚታደገው ብቸኛ ተስፋው ወንጌላዊ መሰረት ያለውን ሙሉ ኃላፋዊነትን መቀበል ብቻ ነው።


ማንበብ ለምትወዱ ተዛማጅ የሆኑ የፕሪቴሪዝም ጽሁፎቼን ላጋራችሁ፦

http://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/blog-post.html?m=1

http://gizachewkr.blogspot.com/2020/01/blog-post.html?m=1


ቸር ያሰማን፣ ቸር ያሰንብተን!!

ግዛቸው ከበደ \ቄስ\



Wednesday, September 1, 2021

የሚበልጠው ትንሣኤ

የሚበልጠው ትንሣኤ


ሐዋርያው ጳውሎስ በእብራውያን መልዕክቱ "ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤" (እብራውያን 11፥ 35) ሲል የብሉይ ኪዳን አማኞችን ጠቅሶ ስለ ትንሣኤ ልምምዳቸው እና ዋጋ ስለከፈሉለት የሚልበጠው ተስፋቸው ይነግረናል።


እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች በዘመናቸው የአካላዊው ትንሳኤ ምስክሮች መሆናቸውን ያመለክተናል። ይህም  እውነት ነው፣ ምንም ጥርጥር የለውም። "ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤" ማለት ምን ማለት ነው? በብሉይ ኪዳን ቢያንስ ሁለት ሴቶች አሉ ሙታኖቻቸውን እንደገና በትንሳኤ የተቀበሉ፣ ማለትም የሞቱባቸው ሰዎች ከሞት የተነሱላቸው ማለት ነው። ሆኖም እነዚያ ሙታን ከተነሱ በኋላ ጥቂት ዘመን ኖረው እንደገና መሞታቸውም አይጠረጠርም። ለምሳሌ፣ ኤልያስ ልጅ የሞተባትን የሰራፕታዋን ባልቴት ልጅዋን ከሞት አስነስቶላታል (1ነገስት 17፥ 17-24)። ኤልሳዕም ልጅ የሞተባትን የሱናማዊቱን ሴት ልጅዋን ከሞት አስነስቶላታል (2ነገስት 4፥ 18-37)። የነብያቱ እምነትና አገልግሎት እነዚህን ልጆች ከሞት መልሶአቸዋል። በአዲስ ኪዳንም ኢየሱስ ማርታ እና ማርያም ለተሰኙ እህትማማቾች ወንድማቸውን አልአዛርን (ዮሐንስ 11፥ 43-44)፣  ከናይን ከተማ ለነበረችው መበለት ደግሞ አንድ ልጅዋን (ሉቃስ 7፥ 13-15)፣ ከሞት አስነስቶላቸዋል። ይህም "የሚበልጠው" ከተሰኘው የትንሣኤ አይነት በተፈጥሮው የሚለይና በይዘቱ "የማይበልጠው" ልንለው የምንችለው ነው።


አንድ ነገር ከሌላ ነገር ጋር በትክክለኛ መመዘኛ ተወዳድሮ፣ ተመዝኖና ተለክቶ የትኛው ከየትኛው በተሻለ የበለጠ ወይም የላቀ እንደሆነ፣ የትኛው ደግሞ ያነሰ እንደሆነ ይወሰናል። ጳውሎስም ለእብራውያን ክርስቲያኖች "የሚበልጠውን ትንሣኤ" ብሎ በሚጽፍበት ጊዜ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ፣ ይህ ትንሳኤ ከየትኛው ትንሳኤ የሚበልጥ ነው? የሚል ነው። መልሱም እነዚህ ሴቶች ከተለማመዱትና በነብያቱና ኋላም በክርስቶስ አገልግሎት በልጆቻቸውና በሚወድዱአቸው ላይ ሲፈጸም ካዩት አካላዊ ወይም ባዮሎጂካል ከሆነውና ጊዜአዊ ከሆነው የትንሳኤ አይነት የተለየው ትንሣኤ ነው። ታዲያ ከዚህ አይነቱ የሚበልጠው ትንሳኤ የትኛው ትንሳኤ ነው? በግልጽ ቋንቋ ለመናገር እንዲህ ካለው ትንሳኤ የሚበልጠው ትንሳኤ የአካላዊውና የተዳሳሹ ትንሳኤ ተቃራኒ የሆነው መንፈሳዊና ዘላለማዊ የሆነው ትንሳኤ ነው፤ ይኸውም "ሌሎች" ተብለው የተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሊቀበሉት ተስፋ ያደረጉት የትንሣኤ አይነት ነው። እነርሱም እስከሞት ድረስ በመደብደብ ዋጋ የከፈሉለትን የሚበልጠውን ትንሣኤ ለማግኘት ተጋድለዋል። ይህ ትንሣኤ በአይነቱ ሰው ከሲኦል ሀደስ ወጥቶ ከፈጣሪው ጋር በሰማያዊው አገር ዘላለማዊ በሆነው እርቅና ህብረት በእርሱ ሀውልት ፊት የሚደሰትበት የእግዚአብሔር ሕይወት ነው፣ እንጂ እንደገና ለመሞት ከሞት ወይም ከመቃብር ጉድጓድ ወጥቶ መምጣት አይደለም። ስለእነርሱም "..... ሌሎች ደግሞ መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ ተስፋ አድርገዋል" ሲል ይነግረናል፤ ተስፋቸውንም "የመዳን ትንሣኤ" ብለን ብንጠራው ተገቢ ነው።


ይህ ጥቅስ የሚነግረን አንድ እውነት፣ እነዚያ በዚህ ተስፋ የኖሩና የሞቱ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን የሚቀበሉት "መዳን" እና የሚያገኙት "ትንሣኤ"  የማይነጣጠል ነገር መሆኑን ነው። በዚህም የምናስተውለው እነዚያ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ተስፋ ያደረጉትን ነገር ሳያገኙ በፊት ማለትም ገና መዳንን ሳይቀበሉ እንኳ ያኔ በሆነ አይነት የትንሳኤ ተስፋ ወደፊት እንድናለን ብለው ያምኑ እንደ ነበር ነው፤ ይሄ በትንሣኤ የሚገኝ የወደፊቱ መዳናቸው ደግሞ በተፈጥሮው ሴቶቹ ከተለማመዱት የሚበልጥና የሚሻል ትንሣኤን እንጂ ተፈጥሮው የግድ አካላዊ (ጊዜአዊ) መሆን አያስፈልገውም። ለምሳሌ፦ ማርታ እንደዚያ ታምን ነበር፤ ኢየሱስ "ወንድምሽ ይነሳል" ባላት ጊዜ "በመጨረሻው ቀን በትንሳኤ እንዲነሳ አውቃለሁ" ( ዮሐ 11፥ 23-24) ከሚለው መልስዋ የምንረዳው በአይሁድ ዘንድ ይታመን ስለነበረው የትንሳኤ አይነት ነው። ይህም የመጨረሻው ቀን ትንሣኤ በዳንኤል 12 የተተነበየውና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ተስፋ ያደረጉት መዳናቸው ነው።


 ይህንን "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" የተሰኘ ቁልፍ ቃል በመላው የእብራውያን መልእክት ውስጥ ያለውን ቦታ ልብ ብላችሁ ካያችሁት፤ ለአዲስ ኪዳን በረከቶችና ትሩፋት ሁሉ መግለጫ የሆነ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተገለጡና ጉድለት ካለባቸው የህጉና የስጋ ከሆኑ ነገሮች ሁሉ በላይ የአዲሱን ኪዳን ስጦታ ከፍ አድርጎ የሚለይ ቃል ነው። "የሚበልጥ" ወይም "የሚሻል" በተሰኘ ደረጃ በእብራውያን መልእክት ውስጥ የተገለጡ ጉዳዮች ማለትም የአዲሱ ኪዳን ስጦታዎች በሙሉ ደግሞ በክርስቶስ የተገኙና የተያዙ ነገሮች እንጂ ገና እስካሁን ያልተፈጸሙ በብዙ ዘመን ርቀት የሚጠበቁ መጻኢ ተስፋዎች አልነበሩም፤ ለምሳሌ፣ የሚበልጥ ሊቀካህን፣ የሚበልጥ ኪዳን፣ የሚበልጥ መስዋእት፣ የሚሻል አገልግሎት ወዘተ። "የሚበልጥ ትንሳኤ" ኢየሱስ የእኛ ብልጫ! ለማርታ እንዲህ ሲል የሚበልጠውን ትንሳኤ አረጋግጦላታል፤ "ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም"። የሚበልጠው ትንሳኤ ሕይወት የሆነው ክርስቶስ ነው። የሚበልጠው ትንሳኤ ሞቶ ሕያው መሆን ነው። የሚበልጠው ትንሳኤ ለዘላለም አለመሞት ነው። የሌለውንና የማይኖረውን "የሥጋ ትንሣኤ" አለ የምትሉ ይህንን አጥርታችሁ ተመልከቱ፣  እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ የለም እንጂ፣ እንደፍላጎታችሁ ቢኖር እንኳ መጽሐፉ በማይሻር ሥልጣኑ የማይበልጠው አድርጎታል።

ሰላማችሁ ይብዛ!

ቄስ ግዛቸው

ጽሁፎቼን ማንበብ ለምትሹ የብሎገሬን መጠቆሚያ እነሆ


http://gizachewkr.blogspot.com/2017/11/1-2.html?m=1 


Wednesday, August 25, 2021

የሄሜኔዎስና የፊልጦስ ስህተት

"ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል!"

የሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ስህተት


ትንቢት ተፈጽሟል፣ ጌታ ኢየሱስም እንደ ተስፋ ቃሉ ዳግመኛ ተመልሷል፣ ፍርድም ትንሳኤም አልፏል ብለን የተፈጸመውን ወንጌል በምንሰብክና በምናስተምር ወንጌላውያን በሆንን በኃላፋውያን ላይ ከመጻኢያን ጎራ ያሉ አንዳንድ ወንድሞቻችን የሚሰነንዘሩት ትችትና ነቀፋ መኖሩ ግልጽ ነውን እነርሱም በሄሜኔዎስና በፊልጦስ ስህተት እኛን የሚከሱበትና ስማችንን የሚያጠለሹበትን ነቀፋ ይጠቀማሉ። በ2ኛ ጢሞቴዎስ መልዕክቱ ጳውሎስ "ትንሳኤ ከአሁን ቀደም ሆንዋል" የሚሉትን ሄሜኔዎስንና ፊልጦስን ተሳስተዋል ሲል ይመሰክርባቸዋል። ጥቅሱን እንመልከት፦


"ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ እነዚህም፦ ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ።" (2ጢሞቴዎስ 2፥ 17-18)


ጊዜ ወስደን ካሰብንበት ከሄሜኔዎስና ከፊልጦስ ትምህርት የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ትንሣኤ ምን ያምኑ እንደነበር ጠቃሚ ነገሮችን ማየት እንችላለን። በእርግጥም ይህ ጥቅስ ኃላፋውያን ስለ ትንሣኤ ያለንን ምልከታ በእጅጉ የሚደግፍ እንደሆነም እናስተውላለን። እንዴት? በጥንት ቤተክርስቲያን ውስጥ በተለመደውና ተይዞ በቆየው እምነትና አመለካከት መሰረት፣ ትንሣኤ የሚከናወነው በዚህ ነባራዊ አጽናፈ አለም ሰማይና ምድር መጨረሻ ላይ ከሆነ፣ ታዲያ ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ በትምህርታቸው የአንዳንዶችን እምነት እስኪገለብጡ ድረስ በማንስ ላይ ቢሆን እንዴት ያለ ተጽዕኖ ማሳደር ይቻላቸዋል? ወይንም ደግሞ የጥንት ክርስቲያኖች ልክ በዚህ ዘመን ብዙዎች እንደሚያምኑትና እንደሚያስተምሩት አይነት፣ ትንሳኤ በተፈጥሮው፣ ተዳሳሽ የሆኑ ስጋዊ አካላትን ከመቃብር አውጥቶ ማምጣትንም ያካትታል ብለው የሚያምኑ ከሆነ፣  ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ትንሳኤ ካሁን ቀደም ሆንዋል ብለው በማስተማራቸው አንድንም ሰው እንኳን ማሳመን ባልሆነላቸው ነበር። ምክንያቱም የሄሜኔዎስንና የፊሊጦስን ትምህርት የሰሙ ሰዎች የተባለው እውነት መሆኑን ዳስሶ ለማረጋገጥና መናፍቃንን ለማውገዝ ብዙ ምርምር ሳያስፈልጋቸው የዘመዶቻቸውንና የወዳጆቻቸውን መቃብር ሄዶ ማየት፣ ወይም ቀደም ብለው የሞቱ ሰዎች ተነስተው በዙሪያቸው ሲመላለሱ ማየት ብቻ ይበቃቸው ነበር። እኛ ከለመድነውና ሲነገረን ከኖረው የትንሣኤ አይነት የተለየውን ትንሣኤ ካላመኑ በቀር፣ የጥንት ክርስቲያኖች የሥጋ ትንሣኤን እያመኑ እንዴት በሄሜኔዎስና ፊልጦስ ትምህርት ሊወሰዱ ይችላሉ? ከዚህ በተቃራኒው ግን ጳውሎስም ሆነ መላው የጥንት ክርስቲያኖች ትንሣኤ በተፈጥሮው መንፈሳዊ እንደሆነና የትኛውንም ተዳሳሽ ማስረጃ ማረጋገጫ አድርጎ የማያቀርብ መሆኑን የሚያምኑ መሆን አለባቸው። 


ጳውሎስ የሄሜኔዎስንና የፊሊጦስን ትምህርት ሲነቅፍ እና ሲያርም፣ እነዚህ ሰዎች የትንሣኤን ተፈጥሮ በተመለከተ ስለተሳሳቱት ነገር አንስቶ የተናገረው ምንም ነገር አልነበረም። ጳውሎስ ያልተስማማውና የተቃወመው ነገር ስለትንሳኤ ጊዜውን አስመልክቶ "ከአሁን በፊት ሆኖአል" ሲሉ የሚያራምዱትን ትምህርት ነው። ጊዜውን አስመልክቶ ግን ጳውሎስ ያስተማረው ብዙም ሳይቆይ በቅርቡ የሚሆን መሆኑን ነው፦ "እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው (about to be) ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ" (ሐዋርያት 24፥ 15)። ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ገና የነገር ሁሉ ፍጻሜ ሳይሆን "ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆንዋል" በማለት የአንዳንዶችን እምነት እስኪገለብጡ ድረስ ከሳቱበትና ካሳቱበት ትምህርታቸው ይልቅ፣ "ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ አላቸው" የሚለው የያኔው የጳውሎስ ተስፋ የብዙዎችን እምነት ያጸና ነበር። 


እነዚያ "ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል" እያሉ ሲያስተምሩ በኑፋቄአቸው የአንዳንዶቹን እምነት የገለበጡበት ምክንያት፣ ገና ያ ምድራዊውና አሮጌው ቤተ መቅደስ አሮጌውን ኪዳን እያገለገለ በኢየሩሳሌም ቆሞ ሳለ ከጊዜው በፊት መንፈሳዊው መንግሥት በፍፁምነት ተገልጧል ብሎ የሚናገር በመሆኑ ነው።  ይህ ደግሞ ሕግንና ጸጋን ማደባለቅ ይሆናል።  ይህም የሕጉን ሥራ የአዲሱ ቃል ኪዳን ክፍል በማድረግ የአንዳንዶቹን እምነት ይገለብጣል። አሁን ግን ጳውሎስ ተስፋ ሲያደርገው የነበረው ሁሉ ያኔ በትውልዱ የተፈጸመና ያለፈ በመሆኑ እኛ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ በሙላት ያለን የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች "ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኗል" በለን ልንመሰክርና የብዙዎችን እምነት ልናጸና፣ በተፈጸመውም ወንጌል ልናጽናና በእግዚአብሔር ቃል ድፍረት አለን። ጉዳዩን ግን በወጉ ሳያስቡበት በሄሜኔዎስና በፊሊጦስ ኑፋቄ ሊከሱን ለሚወዱ ወንድሞቻችን ግን አዲስ ኪዳንን እና መንፈሱን መማር ሀ ብለው እንዲጀምሩ በትህትና እንመክራለን።


ተመልከቱ፣ ጳውሎስን ራሱን ጨምሮ መላው የመጀመርያው መቶ ክፍለዘመን ክርስቲያኖች የትንሣኤን አይነትና ተፈጥሮን አስመልክቶ የነበራቸው እምነት፣ እኛ የዛሬዎቹ ወንጌል አማኝ የሆንን ኃላፋውያን፣ አሮጌውን ወደኋላ በመተው በአዲስ አካል በቀጥታ ወደሰማይ የመሄድ ትንሳኤ ብለን ከምናምነውና ከምናስተምረው ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። ስለዚህም ጳውሎስና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አዲስ ኪዳንን እና አገልግሎቱን በማያውቁ ሰዎች አጠቃላዩ የሙታን ትንሳኤ በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም (MISSED ሊደረግ) እንደሚችል ያምኑ ነበር። ሄሜኔዎስ ፊሊጦስ የዚህ ሰለባ ነበሩ። እነጳውሎስ ግን አጠቃላዩ የሙታን ትንሣኤ ገና ወደፊት በብዙ ዘመን ርቀት ቆይቶ ሳይሆን በእነርሱው ዘመን መጨረሻ ማለትም በአሮጌው ኪዳን መጨረሻ ላይ እንደሚፈጸም ያምኑ ነበር (ዳንኤል 12)። እንዲሁም ትንሣኤ ከተፈጸመ በኋላ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ምንም አይነት ቁሳዊ ለውጥ ሳይደረግ ሕይወት በምድር ላይ የሚቀጥል እንደሆነ ያምኑ ነበር ማለት እንችላለን


ጳውሎስም ሆነ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በጠቅላላ፣ ዘመነኞቹ ቅድመ ሺህ አመታውያንም (Premillennialists) ይሁኑ ወይም አጠቃላዩ የመጻኢነት ዘመን መዳቢያን (Dispensationalists) በትምህርታቸው እንደሚያምኑት አይነት እምነት አልነበራቸውም፤ እነ ጳውሎስ ትንሣኤን የተቀበሉት ሁሉ በትንሣኤ ምክንያት በተሻሻለና በተለወጠ ፕላኔት-ምድር ላይ ይኖራሉ ብለው አያምኑም ነበር።


በሙታን ትንሣኤ ላይ ተከትበው የተለጠፉ ጽሁፎቼን philologus66 የፌስ ቡክ ገጽ እየገባችሁ፣ ወይም 

http://gizachewkr.blogspot.com/2021/07/blog-post.html?m=1 በመጠቀም በርካታ መረጃዎችን እንድትካፈሉ ተጋብዛችኋል።


ቃሉን ከሚወዱ ሁሉ ጋር ብዙ ደስታ ይሁን!

ግዛቸው ከበደ /ቄስ/





Thursday, August 12, 2021

የተዋረደው "ሥጋችን" ልውጠት

 "የተዋረደው ሥጋችን" ልውጠት
" እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።" ፊልጵስዩስ 3፥ 21

1. የማይስተባበለው እውነት
መጻኢያን የሆኑ የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ተከታዮች በዚህ ጥቅስ ላይ ተመስርተው "ጌታ አንድ ቀን ወደ ፊት ተመልሶ ሲመጣ፣ የፈረሰውን ሟችና በስባሽ አካላችንን የእርሱን ወደሚመስል መንፈሳዊ አካል (አንዳንዴም ራሱን ተዳሳሹን አካል የሚሉ ይመስላሉ) ይለውጠዋል፣ ያኔም በመቃብር ውስጥ አፈር የሆነው ሥጋችን ይነሳና በክብር በሰማይ ለዘላለም ይኖራል" ብለው ሲያስተምሩ ይደመጣሉ። በእውነት ግን የምር እንደዚህ የምናምን ከሆነ በመጀመሪያ የሚፋጠጠንና ልናስተባብለው የማይቻለን ዋና እውነት፣ ጌታ ተመልሶ ከመጣ ዘመናት የተቆጠሩ መሆኑ ነው። 
የጌታ ዳግመኛ ምጽአቱ ይጠበቅ የነበረውም ሆነ የተፈጸመው ወይም መፈጸም ያለበት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ መሆኑን በየትኛውም ሥነ መለኮት ማስተባበል አይቻልም!! በአዲስ ኪዳን ከደርዘን በላይ ሞልቶ በሚፈስ የምስክርነት ቃል አስረግጠን ልንናገረው የምንችለው እውነት፣ ጌታ ኢየሱስ ዳግመኛ ተመልሶ እንደሚመጣ ራሱ ጌታችንም ሆነ ሐዋርያቱ ሲያስተምሩና ሲጽፉልን፣ የመመለሻውን ጊዜ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ውጭ እንዳናስበው አድርገው መናገራቸውን ነው፤ [“ጊዜውን አመልካች የሆኑ አጠቃላይ (Gneric) የንባብ ክፍሎች”  የምንላቸው የሚከተሉት ምንባባት፦ ማቴዎስ  10÷ 22-23፤ 13÷ 39-43፣ በተለይ ቁ 40 እና 43 /ከዳንኤል  12÷ 3 የተወሰደ/፤ ማቴ 24÷ 14-15 /ከዳንኤል  9÷ 23 ጋረ የሚነጻጸር/፣ ማቴዎስ 24፥ 30-31 /ከዳንኤል 7÷ 13 እና 22 ጋር የሚነጻጸር/፣ ማቴዎስ 24፥ 34፤ ማቴዎስ 26÷ 64፤ ዮሐንስ 21÷ 22፤ ሮሜ 13÷ 11-12፤ ፊልጵስዩስ 4÷ 5 /ከማቴዎስ 4÷ 17 ጋር የሚነጻጸር፣ ማቴዎስ  3÷ 2፤ 1ጢሞቴዎስ 6÷ 13-14 /ከቲቶ 2÷ 13 እና ከ1ቆሮንቶስ  1÷ 2-8 ጋር የሚነጻጸር/፤ ዕብራውያን 10÷ 25፣ 37፤ የያዕቆብ 5÷ 1-9፤ 1ጴጥሮስ 1÷ 5፣ 9፤ 4÷ 7፣ 12፣ 17፤ 2ጴጥሮስ 1÷ 19፤ 2÷ 3፤ 1ዮሐንስ 2÷ 18 /ከማቴዎስ 24÷ 23-34 ጋር የሚነጻጸር/  1ዮሐንስ 2÷ 28፤ 4÷ 3 /ከ2ተሰሎንቄ  2÷ 1-3 እና 7 ጋር የሚነጻጸር/፤ ራዕይ 1÷ 1፣ 3፤ 2÷ 25፤ 3÷ 11 እና 22÷ 7፣ 12 እና 20፤ 11÷ 18፤ 14÷ 7 /ከ1ጴጥሮስ 4÷ 17 ጋር የሚነጻጸር/ ራዕይ 22÷ 6፣ 10 /ከዳንኤል 12÷ 4 ጋር የሚነጻጸር/፤ ይሁኑ፤ ወይም ደግሞ “ሊሆን ያለውን አመልካች (Mellonic) የሆኑ የሚከተሉት የንባብ ክፍሎች” ፡- ማቴዎስ 16÷ 22-28፤ የሐዋርያት ሥራ 17÷ 31፤ 24÷ 15 እና 25፤ ሮሜ 4÷ 23-24፤ ቆላስይስ 2÷ 16-17፤ 1ጢሞቴዎስ 4÷ 8፤ 6÷ 19፤ 2ጢሞቴዎስ 4÷ 1፤ ዕብራውያን 1÷ 14፤ 2÷ 5፤ 9÷ 11፤ 10÷ 1፤ 13÷ 14፤ 1ጴጥሮስ 5÷ 1፤ ራዕይ 12÷ 5 የትኞቹም ቢሆኑ ይህንንው ሀቅ የሚያስረዱ ናቸው]፡፡ በልብ ስፋትና ጠያቂ በሆነ አእምሮ እነዚህን ጥቅሶች በአውዳቸው አጥርቶ እያነበበ፣ የጌታን ዳግመኛ ምጽአት እንዳልተፈጸመና ገና ወደፊት እንደሚጠበቅ ተስፋ አድርጎ የሚያስብ ተላላ የቃሉ ተማሪ ሊኖር አይችልም።
ስለዚህ የጌታን መመለሻ ጊዜ እና የትንቢት ፍጻሜን አስመልክቶ በአዲስ ኪዳን በብዙ ማስረጃ በግልጽ የተጻፈውንና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን የተናገሩትን ብቻ እንጂ ልማድ ያቀበለንን፣ እኛ የመሰለንን፣ ልንሰማው የምንፈልገውንና እንዲሆን የምንመኘውን አናምንም። 
በመሆኑም ከላይ የዘረዘርኳቸው እነዚህ ጥቅሶች የያዙትን ቁምነገር እየደፈጠጠ፣ እግዚአብሔር ለነገር ሁሉ ጊዜን የመደበ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም "ጊዜን የሚናገር" አምላክ መሆኑን ጭምር ከሚጠራጠርና፣ እግዚአብሔር ለትንቢት ፍጻሜ የመደበውንና የገለጠውን ጊዜ እያስተባበለ፣ እግዚአብሔር ያልተናገረውን ጊዜ በመጠባበቅ ያለእውቀት "የእግዚአብሔር አራሚ" ለመሆን ከሚዳዳው ሥነ መለኮት ጋር የመስመር ልዩነት አድርገናል፤ አልተገናኘንም። እግዚአብሔር በግልጽ የተናገረውን ጊዜ ለእግዚአብሔር ተአማኒነት የተቆረቆርን መስሎንም ይሁን ወይም ለልማዳዊው ሥነመለኮታችን ትክክለኛነት ተጨንቀን፣ ጥብቅና በሚመስል አቋም ተይዘን፣ እንደተጻፈው ቃሉ ሳይሆን፣ "የለም እንዲህ ማለቱ ነው" ብንልና ቃሉን ልናርም ብንሞክር አሳች አስተማሪ መሆናችን ነው። ይህ በራሱ ንስሃን የሚጠይቅ ሥነመለኮታዊ ውድቀት ነው።
ስለዚህ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ምንም ነገር ይሁን ምንም፣ ሲፈልግ 'መንፈሳዊ' ከወደደም 'አካላዊ' ትንሣኤ ወይም ልዋጤ የትኛውም ቢሆን ያለጥርጥር ያኔውኑ የተፈጸመ ጉዳይ መሆን አለበት። "በዚህ ጥቅስ ላይ የተነገረው ነገር ሁሉ፣ 'ናፋቂያኑ' እንደሚጠባበቁት ያለ የመጻኢነት 'ተስፋም' ይሁን ወይም ሌላ ማናቸውም ከትንሣኤ ተፈጥሮና ባህርይ ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ ሁሉ፣ የአማኞች የተዋረደ ሥጋ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል መለወጡም ጭምር ተፈጻሚ የሆነው እና መፈጸምም ያለበት፣ ጌታ ተመልሶ በመጣበት በ70 አ.ም ላይ ያኔ ነው ስል፣ እነሆ በድጋሚ ድምጼን ከፍ አድርጌ አስታውቃለሁ። እንደ 'ንጣይ' እና 'ግንጣይ' ቢያስቆጥርም እንኳ ከተባረከው የቃሉ ምስክርነት ጋር ለመቆምና ለመሞት እመርጣለሁ። እነሆ የሙታን ትንሣኤም ሆነ ይህ የህያዋን የልዋጤ ተስፋ በተባረከው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው ተፈጽሟል፣ አልፏልም። በዚህ ጥቅስ አውድ ላይ እና በጠቅላላ በያዘው ቁም ነገር ላይ መነጋገር የምንችለው፣ ከሁሉ በፊት ይህ ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር የተጋመደ ትንሣኤም ይሁን ልዋጤ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክስተት እንደሆነ በገጾቹ ሁሉ ከሚያስተምረው የተፈጸመ ወንጌል ጋር የተግባባን እንደሆነ ብቻ ነው።

2. የአውደ ምንባቡ መልዕክት
የፊልጵስዩስ 3፥ 21 "የተዋረደው ሥጋችን" ልዋጤ በነገረ ፍጻሜና በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ አውድ ውስጥ የቀረበ የጽድቅ መገኘት እና የድነት ሙላት ተስፋ ፍጻሜ መሆኑን ጥቅሱን ከበው ያሉ ጉዳዮች ሁሉ በግልጽ ያመለክታሉ። ይህም የጽድቅ መገኘትና የድነት ሙላት፣ "በክርስቶስ በማመን ያለው"... "ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው" የተባለው "ጽድቅ" (ቁጥር 7-9) ነው። ጳውሎስ "በእርሱ እገኝ ዘንድ" ሲል በክርስቶስ ለመገኘት ያለው ምኞት ወደክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት የሚያመለክት መግለጫ ነው። ጴጥሮስም፣ "ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥" (2ጴጥሮስ 3፥ 13-14) ሲል ተመሳሳይ ነገር ይናገራል። ጳውሎስ በንግግሩ፣ "አሁን (ገና) እንዳላገኘሁ" ይላል፤ ያ ገና ያላገኘው ነገር ምንድን ነው? በግሪኩ lambano የተሰኘው ቃል ተሻጋሪ ግስ ነው፣ ነገሩ ግን አልተገለጸም። ጉዳዩ በቁጥር 11 ላይ ያነሳው ትንሣኤ ይሆንን? አዎ በዝርዝሩ ውስጥ ትንሣኤም ተካቶበታል፣ ነገሩ ከዚያም የሚሰፋ እንደሆነ ግን አያለሁ። ክርስቶስ በመምጣቱ ሥጋቸውን "የተዋረደ" ከተሰኘ አንድ የታወቀ መደብ ሊገለጥ ወደማይችል ወደ እርሱ አካል የላቀ የክብር ደረጃ ፍጽምና ይለውጠዋል፤ እርሱም አማኞች እንዲኖራቸው ያሰበላቸው የአካል አይነት በስራዎች ጽድቅ ላይ የሚመካ አካል ሳይሆን እርሱ ባጠናቀቀው ፍጽምና ላይ የሚመካውን የጽድቅ አካል ነው። ልብ ብለን ካየነው ፊልጵስዩስ 3 ደግሞ እንዳለ የሚያወራው ስለጽድቅ መገኘት ነው። የዚህ ጽድቅ ተቃራኒ ደግሞ ጳውሎስ እንደ ጉድፍ የቆጠረውና አይሁድ በከንቱ የሚመኩበት "በሕግ የሚገኝ ጽድቅ" ነው። ክርስቶስን ማግኘት እርሱም "በክርስቶስ በማመን ያለውን ጽድቅ"፣ ማለትም በእምነት በኩል ከእግዚአብሔር ዘንድ በጸጋ የሚታደለውን ጽድቅ ማግኘት ነው (ቁጥር 9)። አለፍ አለፍ እያልኩ ርእሰ ጉዳያችንን ከበው ያሉትን ቁምነገሮች ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
 በቁጥር 10 ላይ የሚያነሳው "የሙታን ትንሣኤ" ሙታን ከሞት ስለሚወጡበት ኩነት ነው፤ በእርግጥም ሙታን የሚለው አምነው በተስፋ የሞቱትን የብሉይ ኪዳን እስራኤልን ሲሆን፣ ጳውሎስም ራሱ ደግሞ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ ከሚሰበሰበው ከነገረ ፍጻሜአዊው መከር አስቀድሞ ካሉትና ይህንን የሙታን ትንሣኤ ከሚጠባበቁትና ከሚካፈሉት በኩራት መካከል ነው። "ልደርስ እመኛለሁ" ማለቱም ወቅቱ የራሳቸውን መዳን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የሚፈጽሙበት አይነተኛ የትግል ጊዜ በመሆኑ፣ በዚያ የትግል ወቅት ከእምነት አፈግፍገው የሚቀሩና በትንሣኤ ተካፋይ የማይሆኑ መኖራቸውንም ያሳያል። ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱና "መጨረሻቸው ጥፋት" የሆኑ "የመስቀሉ ጠላቶች" ነበሩና (ቁጥር 2-3፣ 18-19)። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በትምህርቱ፣ እርሱ ብቻ ነገረ ፍጻሜአዊው "ትንሣኤና ሕይወት" መሆኑን ግልጽ እድርጓል (ዮሐንስ 11፥ 25-26)፤ ስለሆነም የጳውሎስ ምኞት ገና እንዳላገኘው ሁሉ ክርስቶስን ማግኘት ነበር (ቁጥር 12)፤ ጳውሎስ የሚመኘው ራሱን ክርስቶስን ማግኘት እንጂ የገዛ ራሱን ሰብዓዊ ሥጋ የሚተካ ሌላ አካል ማግኘት አልነበረም። ክርስቶስን ማግኘት ደግሞ የመንፈሳዊ አካሉ ፍጽምና ነው። ጉዳዩ ከምናስበው በላይ የሰፋ መሆኑን በግርድፉ እንየው።
ጳውሎስ እያነሳ ያለው ጉዳይ ጽድቁ ገና የተጠናቀቀ አለመሆኑን ነው። ስለዚህም "አሁን (ገና) እንዳልያዝሁት" ወይንም 'ገና እንዳልጸደቅሁ ነኝ' እያለን ነው። ጳውሎስ መልዕክቶቹን ይጽፍ በነበረበት ጊዜ ለራሱም ሆነ ለአንባቢዎቹ ምዕመናን መጽደቅ ያኔ ገና ተስፋ ነበር። ጳውሎስና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ገና የእግዚአብሔር ጽድቅ አልነበራቸውምን? ብሎ የሚጠይቅ ሰው ይኖራል። በተጠናቀቀ እና ሙላቱን ባገኘበት መልኩ የእግዚአብሔር ጽድቅ ገና ወደፊት ለእነርሱ የሚገለጥ ነበር፣ ብለን መልስ እንሰጣለን። 
ይህንን ልዋጤ፣ እርሱም የጽድቅ ተስፋ ፍጻሜን አስመልክቶ ማጽናት የምፈልገው አንድ ጉዳይ፣ በጳውሎስ ነገረ መለኮት የተብራራውና  "ይገለጣል" የተባለው "የእግዚአብሔርን ጽድቅ" (ሮሜ 1፥ 17)፣ ጌታ ኢየሱስ በክብር እስኪመለስ ድረስ ገና ለፍሬ፣ ይኸውም ለመዳናችን ፍጽምና ያልደረሰ፣ ከነገረ ፍጻሜ መጠናቀቅ ጋር የተቆራኘ ዋና ጉዳይ የነበረ መሆኑን ነው። (ይህንን በጉልህ የሚያሳዩ በርካታ ምንባባት አሉ፤ ለምሳሌ፦ ዕብራውያን 9፥ 28፤ ሮሜ 13፥ 11፤ 1ተሰሎንቄ 5፥ 9፤ 2ጢሞቴዎስ 2፥ 10፤ ዕብራውያን 1፥ 14፤ 1ጴጥሮስ 1፥ 5፣ 9፤ እና 2ጴጥሮስ 3፥ 15፤ ከብዙ በጥቂቱ ሊጠቀሱ ይችላሉ)። ክርስቶስ ዳግመኛ ካልተመለሰና ነገረ ፍጻሜ ካልተጠናቀቀ መጽደቅ ተስፋ ብቻ ሆኖ ይኖራል። ክርስቶስ፣ ጽድቅ፣ ትንሣኤና ፍጽምና ወይም ሙላት የተሰኙት ቃላት ሁሉም የሚያመለክቱት ያንንው ጳውሎስ ሊያየውና ሊደርስበት የሚመኘውን አንዱን ተስፋ ነው። ይህም ተስፋ ያኔ "ቀድሞውኑ ሆኗል ግን እስካሁን ድረስ ገና አላለቀም" (the already  and not yet) አይነት ባህርይ ባለው በሽግግሩ ውቅት ላይ የነበረ እውነታ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ "ክርስቶስን ማግኘት" ያኔ ተጀምሯል ግን በሙላት አልተጠናቀቀም፣ ፍጻሜውን ወደፊት ይጠብቃል ማለት ነው። ስለዚህም ጳውሎስ እንደ ጴጥሮስ ሁሉ (2ጴጥሮስ 3፥ 13-14)፣  አዲሱን ሰማያዊ አገር ወደፊት (በቅርብ አመታት ውስጥ፣ በጣም በአጭር ጊዜ) እየተጠባበቀ ወደላይ አሻቅቦ ያያል (3፥ 21)። 
በዚህ አውድ ውስጥ ማንም የቃሉ ተማሪ በግልጽ የሚያየው አንድ እውነት ይህ መጠባበቅ እነርሱ ማመን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ ትውልድ የዘመን ርዝመት በላይ በጣም ረጅም ጊዜ የሚወስድ አለመሆኑን ነው፤ ምክንያቱም "በመጀመርያ ካመኑበት ጊዜ ይልቅ መዳናቸው ወደእነርሱ እየቀረበ ነበር"። ያን ጊዜም "ከእንቅልፍ የሚነሱበት" ሰዓት ደርሶ ነበር። ያኔም ለእነርሱ "ሌሊቱ አልፎ" የአሮጌውን ዘመን የጨለማ ኃይል ሙሉ በሙሉ አውጥተው የሚጥሉበት "ቀኑ ቀርቦ" ነበር (ሮሜ 13፥ 11-12)። ሊመጣ ባለው ዘመንም ጠላቶቻቸውን በመደምሰስ በሙላት የሚገለጠውን የሚመጣውን ዘመን ኃይል ቀምሰው ነበር (ፊልጵስዩስ 3፥ 18-21፤ ማቴዎስ 24፥ 2-3)። ስለዚህ እስከ ጌታችን ዳግመኛ ምጽአትና ከእርሱም ጋር የሚሆነው የሙታን ትንሳኤ እስኪፈጸም፣ ዘላለምም እስኪጀመር ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት ለጳውሎስና ለመልዕክቱ ተደራስያን እሩቅ እና እረጅም አልነበረም፤ "ዘመኑ አጭር ሆኖአል" (1ቆሮንቶስ 7፥ 29) ይሉ ነበርና። ያኔ ለአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ዘመኑ፣ መጨረሻው፣ ፍጻሜው፣ ቀኖቹ ቅርብ ብቻ ሳይሆን ሰአቱም የመጨረሻ ነበር (1ዮሐንስ 2፥ 18)፣ ስለዚህም እያጣደፈ በሚያልቅ የዘመን ሙጣጭ ውስጥ ነበሩ።
የእግዚአብሔር ጽድቅ መጻኢ ገጽታ የነበረው መሆኑን ጳውሎስ በግልጽ አስተምሯል፤  እነዚያም የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች በዘመናቸው ያገኙት ዘንድ ናፍቀውና ጓጉተው ይጠባበቁት የነበረ ጉዳይ መሆኑን ፣ "እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና።" (ገላትያ 5፥ 5) ሲል ግልጽ አድርጓል። ተመልከቱ፣ ጽድቅ ያኔውኑ የተፈጸመ ወይም የተጠናቀቀ ኩነት ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ጳውሎስ በእምነት መጽደቅን የተስፋ ጉዳይ በማድረጉ በንግግሩ ትልቅ ስህተት እየፈጸመ ነበር ማለት ነው። ጽድቅ ያለቀለትና የተጠናቀቀ ጉዳይ ከሆነ ታዲያ ጳውሎስ ለምን ተስፋ ያደርገዋል? ከፍ ሲል እንዳመለከትኩት ጳውሎስ ይኖር የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ "የመጨረሻው ቀኖች" ሲል በሚጠራው ዘመን ላይ ነበር፣ እነዚያም ቀኖች የአሮጌው ኪዳን የመጨረሻ ቀኖች ነበሩ። እነዚያ የመጨረሻዎቹ ቀኖች በክርስቶስ መወለድ ተጀምረው በ70 ዓ.ም ላይ የአይሁድ ቤተመቅደስ ሲደመሰስ ተፈጽመዋል። አሁን ግን እኛ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ "የሚመጣው ዘመን" እያለ በሚጠራው በአዲሱ ኪዳን ዘመን ውስጥ ነው። ከበአለ ሃምሳ ጀምሮ የእስራኤል መቅሰፍተ እልቂት እስከሆነበት ድረስ ያለው የአርባ አመታት ጊዜ ከአሮጌው ኪዳን ወደአዲሱ ኪዳን ሽግግር የሚደረግበት የሽግግሩ ወቅት ነው። በዚህ የሽግግር ወቅት አዲሱ ኪዳን ገና ተመርቆ ተጀምሯል እንጂ ተጠናቆ አልተፈጸመም ነበር። ያ ጊዜ "already but not yet" የተሰኘው ጊዜ ነው።
በዚህ የሽግግር ወቅት የጳውሎስ ምኞት እና አላማ ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ነው፣ ይኸውም ክርስቶስን ማግኘት፣ የክርስቶስን ጽድቅ ማግኘት ነው፣ (ፊልጵስዩስ 3፥13-14)። "እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ"፣ ምናልባት እንዲህ ያለ ንግግር በዚህ ምንባብ ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ የተደገመ ይመስላል። ግልጽ የሚያደርገው አንድ እውነት "የእግዚአብሔር መጥራት ዋጋ" ሲል የሚጠራውን የጽድቅን ብድራት ገና ያላገኘ ወይም ያልያዘ እና ገና ፍጹም ያልሆነ መሆኑን ነው። ዘመኑ ካልተፈጸመና አዲሱ ኪዳን በሙላት ካልተገለጠ በቀር ይህ ፍጹምነት እርሱም የእግዚአብሔር የመጥራት ዋጋ የተሰኘው የጽድቅ ብድራት ሊገኝ አይችልም። ስለዚህ፣ ትግሉን ስሙ፦ 
" በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ።" (ፊልጵስዩስ 3፥ 14)፤ በአዲሱ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ "ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው" ይላል። ያንን ሕይወት ገና ወደላይ ተጠርቶ ሲሄድ እንደሚቀበል እንጂ ተጠርቶ ወደላይ ከመሄዱ በፊት እንዳለው ወይም እንደያዘው ገና አያስብም። "እፈጥናለሁ" ማለት በግሪኩ dioko ነው፣ ይኸውም አንዳችን ነገር ለማግኘት እና ለመያዝ መሮጥ ነው። ያለማቋረጥ ወደ ግቤ እገሰግሳለሁ እያለ ነው። ለምን አጥብቆ ወደግቡ ይሮጣል? ቢባል የቤተክርስቲያን ፍጽምና ለሆነው ብድራት ነው፣ ይኸውም በዳግመኛ ምጽአቱ የክርስቶስን ጽድቅ መቀበል ነው። ከፍ ሲል የጠቀስናቸውንና በጻድቃን ትንሳኤ ተካፋይ የማይሆኑ ያልናቸውን፣ ጳውሎስም "የመስቀሉ ጠላቶች" ሲል የሚጠራቸውን ይሁዲዎችንና ወደ ጥፋት የሚያደርሳቸውን ለአሮጌው ኪዳን ያላቸውን ቅንአት ካነሳ በኋላ (ቁጥር 17-19)፤ ቀጥሎ በቁጥር 20 ላይ በቅርቡ ራሱን ጨምሮ "እኛ" ሲል ለሚጠራቸው ሁሉ ስለሚመጣው ብድራት ወደሚናገረው ርእሰ ጉዳይ ያልፋል። 
በቁጥር 20 " እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤" ሲል በመስቀሉ ጠላቶችና የሰማያዊ አገር ዜግነት ባላቸው መካከል ያለውን ተቃርኖ ያመለክታል። "እኛ" የሚለው ጳውሎስንና የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ጨምሮም ሌሎች አማኞችን ሁሉ ነው። ዳግመኛ የተወለድን ሁላችንም ዜግነታችን ሰማያዊ፣ አገራችንም በሰማይ ነው። ዜግነት ማለትም "አገራችን" የሚለው ቃል (በግሪኩ politeuma)፣ በአዲስ ኪዳን ጥቅም ላይ የዋለው እዚህ ላይ ብቻ ነው፣ ነገር ግን politeumai የተሰኘው ግስ በፊልጵስዩስ 1፥ 27 ላይ ጥቅም ላይ ሲውል አመልካችነቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው ማህበራዊ ተሳትፎውንና የዜግነት ድርሻውን የሚወጣ የክርስቲያናዊ አኗኗር ዘይቤን ነው። "አገራችን በሰማይ ነው"፦ ይህም አይገሰስም፣ አይለወጥምም፤ "ነው!" ይላልና፣ የጸናና የተመሰረተ በማንም የማይገፈፍ አስተማማኝ የዜግነት መብት ነው። ሰማያዊውን መንፈሳዊ፣ መሬታዊውን ደግሞ ፍጥረታዊ ሰው ሲል ባነጻጸረበት በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ቁጥር 47-48 ባለው ገለጻ ለሰው ልጆች የተመደበውን ሁለት አይነት ዜግነት በግልጽ ማየት ይቻላል። መደብህ ከሁለት በአንዱ ነው፤ ወይ መንፈሳዊ ሆነህ ሰማያዊ ነህ፣ አልያም ፍጥረታዊ ሆነህ መሬታዊ ነህ።
ሰማይ ግን ምንድን ነው? ብንጠየቅስ ምን ትርጉምና ማብራርያ ሰጥተን ልንገልጠው እንችላለን? ተመልከቱ፦ "ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።" ዕብራውያን 9፥ 24 ይላል፤ እዚህ እንደምናየው ሰማይ የእግዚአብሔር ማደርያ ነው። "በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ" ብለን ስንጸልይ እግዚአብሔር ማደርያው በሰማያት እንደሆነ እያወቅን ነው። ሰማይ እውነተኛይቱ ቅድስት ናት።
2ቆሮንቶስ 12፥ 1-4 "ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።"
እዚህም ላይ በድጋሚ ሰማይን የእግዚአብሔር ማደርያ፣ የመኖሪያው ስፍራ ሆኖ እናያለን። ሰማይ በዚህ ተዳሳሽ አለም የተወሰነ አንድ ቦታ ላይ ያለ የሆነ ስፍራ አይደለም። ሰማይ በእውነትም በሰማያዊው አለም የሚገኝ፣ አድራሻ ያለው ኑባሬ ነው። ጳውሎስ በሥጋ ይሁን ወይም ያለሥጋ መሆኑን የማያውቀው፣ እንዴት እንደሆነ ግን እግዚአብሔር ብቻ ወደሚያውቀው "ገነት" ሲል ወደሚጠራው ሦስተኛው ሰማይ ተነጥቆ በዚያ የነበረውን በሰው ቃል ሊገለጥ የማይችል ልምምዱን ይመሰክራል። እንግዲህ እንደ ክርስቲያን አገራችንና ዜግነታችን በሰማይ ነው። ከስፍራ አንጻር በአቀማመጥ (positionally) አሁን ያለነው በሰማይ ነው፣ ሥጋዊውን ሞት በምንሞትበት ጊዜ ነፍሳችን ይህንን ነባራዊ አለም ስትተው ሄዳ የምትገኝበት 'ይሄ'፣ 'እዚህ' ወይም 'እዚያ' የሚባል አድራሻና፣ ያ ኑባሬ ሰማያዊው አለም ነው። በሥጋ ስንሞት፣ የእግዚአብሔር መኖርያ በሆነው በመንፈሳዊው አለም በሰማይ እናድራለን። ጳውሎስ "ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" (ፊልጵስዩስ 1፥ 23) ይላል፤ እንደ አማኝ መናፈቅ ካለብን፣ ይህንን ያለና እውነታ የሆነ ነገር ብቻ እንናፍቃለን እንጂ፣ ተፈጽሞ ያለፈ ነገር መናፈቅ የሌለ ነገር መናፈቅና መድከም ነው።
ሰማይ የአማኙ ተስፋው ነው። ስሞት ወደጌታ፣ ወደ ሰማይ እሄዳለሁ፣ አስተማማኝና የምጠባበቀው የተረጋገጠ ተስፋ ይሄ ነው። "ከሞትኩኝ በኋላ በመቃብር ከርሜ እንደገና ተነስቼ እመጣለሁ" ስንል፣ ይህ ደግሞ የሌለ ነገር ከመጠበቅም በላይ በሃሰት መታመን ይሆናል። "ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።" (2ቆሮንቶስ 5፥ 1) እዚህ ላይ ጳውሎስ "ድንኳን" ሲል የሚጠራው "ምድራዊ መኖሪያ" ተዳሳሹ አካላችንን ነው። ጴጥሮስም በተመሳሳይ መንገድ ሥጋውን ምን ብሎ እንደሚጠራው ተመልከቱ፦ "ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና።" (2ጴጥሮስ 1፥ 13-14)፤ ሰዎች ሁሉ በሥጋ የሚሞቱበት አንድ የሆነ ቀንና አጋጣሚ አላቸው፣ ታዲያ ያ በሚሆንበት ጊዜ፣ እኛ በክርስቶስ ያመንን ፈጽሞ የማንኖርና የማንገኝ አንሆንም፣ ወደ እሳት ባህር የምንሄድም አንሆንም፣ በቀጥታ የምንሄደው ወደ ሰማይ ነው። ጳውሎስን ስሙት፦ "እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል።" (2ቆሮንቶስ 5፥ 6-8) ይላል። 
እንደ ክርስቲያን ተስፋችን፣ ማለትም ስለ መጻኢው ያለን ፍጹም እርግጠኝነት፣ ይህንን ሥጋዊ አካል የሆነ ማደሪያችንን በሞት ምክንያት ስንተወው፣ ወዲያውኑ በሰማይ ከጌታ ጋር መሆናችን ነው። ለጥንት ቤተክርስቲያን ተሰጥተው የነበሩ ሁሉም ተስፋዎች ተፈጽመዋል፤ ዳግመኛ ምጽአቱ፣ የሙታን ትንሳኤ፣ የጽድቅ ሙላት፣ የመዳን ተስፋ፣ የዘላለም ሕይወት፣ ይህ ሁሉ ለእነርሱ የሚጠባበቁት ተስፋቸው ነበር፤ በ70 ዓ.ም በአሮጌው ኪዳን መጨረሻ በፓሮውዥያው ተፈጽመዋል። ክርስቶስ ተመልሷል፣ ትንሳኤም ከአሁን በፊት ሆንዋል፣ ፍርድም አልፏል፤ ይህ ሁሉ ከዚህ በኋላ በእኛ ዘመንም ይሁን ወደፊት የማይሆንና የማይደገም የተፈጸመ ትንቢት ነው። የተፈጸመ ነገር ደግሞ የሚጠበቅ ተስፋችን ሊሆን አይችልም። የተሰጠና ያላችሁን ነገር ተስፋ ልታደርጉት አትችሉምና። ምን ተስፋ እንደሚያደርግና እንደማያደርግ ጳውሎስን ስሙት፦ "በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።" (ሮሜ 8፥ 24-25) ክርስትናን ልንኖረውና የድሉን ደስታ ልናጣጥመው የሚገባን ይህንን የተፈጸመ ተስፋ እውነታ ተቀብለን ነው። ትምህርታችንን እና እምነታችንን መረዳት የተሳናቸውና ለመረዳትም ፍላጎት የሌላቸው አንዳንድ ወገኖች ግን በተፈጸመው ወንጌል አስተምህሯችን ውስጥ ለክርስቲያን ምንም ተስፋ የለውም እንደምንል አድርገው ተመልክተውናል፤ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው። በተፈጸመው ወንጌል የሚታወጀው መጽናናት የሞላበት የተፈጸመው ተስፋ እርስዋም "የተገኘች እውነት" እንጂ፣ "ልብን የምታሳዝን የምትዘገይ ተስፋ" አይደለችም፣ (ምሳሌ 13፥ 12)። 'አስተምህሯችሁ ተስፋ ገዳይ ነው' ሲሉ ለሚነቅፉን ሁሉ ወደ መጽሐፍ ቅዱሳቸው ተመልሰው እግዚአብሔር በቃሉ ለሰጠው ተስፋ ፍጻሜ ጊዜን የመደበና፣ ያ ጊዜ መቼ እንደሚሆን በግልጽ የተናገረ እንደሆነ በትህትና እንዲማሩ እንመክራለን። ተስፋ ተፈጽሟል ባዮች የምስራች ተናጋሪዎች ነን እንጂ፣ ተስፋ ነጣቂዎች አይደለንም። የጥንት ቤተክርስቲያን ተስፋ ስታደርገው የነበረው ነገር ሁሉ ተፈጽሞ ተገልጧል፣ እኛም እነርሱ ተስፋ ያደረጉትንና የተፈጸመላቸውን አምነን ወርሰናል፣ አምነን የገባነው ወደተፈጸመው እውነታ ነው። ስለዚህ እኛ በየተራ ሞተን ወደሰማይ መሄዳችንን የምንጠብቅ ከመሆኑ በቀር እግዚአብሔር ተናግሮ ያልፈጸመው ምንም ተስፋ የለም። ክርስቶስ በፈጸመው ተስፋ ሞተን የምንሄድበትን መኖርያ፣ ሰማይን አዘጋጅቶልናል፤ ተስፋችን ይኸው ነው።
ጳውሎስ ይቀጥልና "ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤" ይላል። "እንጠባበቃለን" የተሰኘው ቃል በግሪኩ apekdechomai ነው፤ ትርጉሙም ጓግቶ መጠበቅ፣ የሚመጣውን የክብር እንግዳ በናፍቆትና በፍቅር እንኳን ደህና መጣህልን ብሎ ለመቀበል ተዘጋጅቶ መጠበቅን ያሳያል። ይህ የግሪክ ቃል በአዲስ ኪዳን ሰባት ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ በተጠቀሰበት ስፍራ ሁሉ አገባቡ ዳግመኛ ምጽአቱን በሚያሳይ መልኩ ነው። apekdechomai የተሰኘው ይህ ቃል በሮሜ 8 ላይ ሦስት ጊዜ ጥቅም ላይ ውላል፦
ሮሜ 8፥ 19 "የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና(apekdechomai)።" 
ጌታ በሚመለስበት ጊዜ የሚገለጡት "የእግዚአብሔር ልጆች" እነማን ናቸው? ያኔ ኢየሩሳሌምን በማጥፋት ክርስቲያኖች የእርሱ ልጆች መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።
ሮሜ 8፥ 23 "እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን (apekdechomai) ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።"
ቤዛነት ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር የተጋመደ ነው። " በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።" ሉቃስ 21፥ 27-28፤ በዚህ ጥቅስ አውድ "ይህ" ተብሎ ይሆናል የተባለው ነገር የኢየሩሳሌም ውድመት ነው። ቤዛነት የሚጠናቀቀው ኢየሩሳሌምን በፍርድ ሊያጠፋትና ለአሮጌው ኪዳን ፍጻሜውን ሊሰጠው ጌታ ሲመለስ ነው።
ሮሜ 8፥ 25 "የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን(apekdechomai)።"  
ሁሉም እነዚህ በሮሜ 8 ያለው የቃሉ አውዳዊ አገባብ ዳግመኛ ምጽአቱ ነው። (ለተጨማሪ ማጣቀሻ 1ቆሮንቶስ 1፥ 7፤ ገላትያ 5፥ 5፤ እና ዕብራውያን 9፥ 28 ተመልከቱ)፤ ስለዚህ ጓግተውና ናፍቀው የሚጠባበቁት ጌታ ሲመጣ በፓሮውዥያው ጽድቅን ያመጣላቸዋል ማለት ነው (ዕብራውያን 9፥ 28)።
ስለዚህ የፊልጵስዩስ 3፥ 21 የልዋጤ ተስፋም በዚሁ የዳግመኛ ምጽአቱና የጽድቅ መሰጠት አውድ ውስጥ መታየት ያለበት መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን ግልጽ የሆነው ይህ የቃሉ ትምህርት እና ቃሉን ልተካ ባዩ እድሜ ጠገብ ልማዳዊ ዶግማ በተለይ በዚህ ጉዳይ ነጭና ጥቁር ስለሆኑ፣ መጻኢያንም ቃሉን ብቻ ዋቢ አድርገን የምንመሰክርለትን ይህንን የዳግመኛ ምጽአቱን ተስፋ ፍጻሜ መቀበል ስለማይችሉ፣ ወይም ስለማይፈልጉ፣ የትንሳኤን ተፈጥሮ ወይም ባህርይ በተመለከተ ያለውን የኖረ ልማዳዊ ትምህርታቸውን ይዘው ቀርተዋል። ይህንን ጊዜ ያለፈበትን (expired ያደረገ) የመጻኢነት ትምህርት በቅዱሳት መጻህፍት ፈትነንና ፈትሸን ልናጸናውም ሆነ ልንሽረው ካልደፈርን በቀር ንጹሁንና ቅኑን ትምህርት ሳናውቅ ከሌሎች በወረስነው ልማድ እንደሳትን፣ ሳንታረም ቀናችን ያበቃል፤ በርዕሰ ጉዳዩም ላይ በበቂ ሳያስቡበት አዋቂ ነን የሚሉትንም መመለስና ማቅናትም በእውነት ከባድ ነው። አሁን ቁጥር 21ን በሌላ ርእስ ማየታችንን እንቀጥል።

3. ክቡር ሥጋው ማለት
ጌታችን ኢየሱስ ከሞት በተነሳ ጊዜ ሥጋው በአይነቱ የተለየ ነበርን? የነበረውስ የከበረ ሥጋ ነበርን? በርካቶች እንደዛ እንደሆነ ያስባሉ፣ የናገራሉም። እኔ ግን ቃሉ በግልጽ እንደሚያስተምረው፣ ከመቃብር የወጣው የኢየሱስ ሥጋ ያው ራሱ ወደ መቃብር ከወረደው ሥጋ ጋር አንድና አንድ አይነት ነው፣ ምንም የተለየ ነገር የለውም የሚለውን ማመን እመርጣለሁ። መጽሐፍ ቅዱሱን የሚያውቅ ሰው ታዲያ፣ "እንግዲያውስ ደህና፣ ማርቆስ ከትንሳኤው በኋላ የኢየሱስ ሥጋ የተለየ ነው ይለናል አይደለም ወይ?" ሲል ይጠይቃል፦
ማር 16፥ 11-12 እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤
እንዲህ ካሉ ጥቅሶችና "በሌላ መልክ" ከተሰኘው ሀረግ የተነሳ በርካቶች የኢየሱስ የትንሳኤው አካል ከትንሳኤው አስቀድሞ ከነበረው አካል የተለየ እንደሆነ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ማርቆስ በወንጌሉ ሌላ ክፍል ቀደም ሲል በመወለጥ ተራራ ላይ የተከናወነውን ሲተርክ የሚለውን ስሙ፦
ማር 9፥ 2  ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ
"ተለወጠ" የሚለው ቃል metamorphosis የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የሚተረጉም ሲሆን፤  የግሪኩ ቃል morphe ትርጉሙ 'ከ' ሲሆን meta ደግሞ መለወጥ ከተሰኘው ሁለት የቃላት ጥምረት የተገኘ ነው። ቃሉም እንደ ትርጉሙ የሚያሳየው ያው መለወጥን ነው። በቀላሉ ሊሰመርበት የሚገባው የቃሉ ትርጉም 'ከአንድ ነገር መለወጥን' ነው፣ ይኸውም "መልክ" የተሰኘው የሚታይ ውጫዊ መገለጫ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ከትንሳኤ በፊት መሆኑን አትርሱ። የማርቆስ 16 "በሌላ መልክ" የተሰኘው መግለጭም ያው ራሱ ሰብአዊው መልክ ሲሆን ዳሩ ግን ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ወቅት ከነበረው መልክ የተለየውን እንዳሳየና እንደገለጠ ነው እንጂ ተፈጥሮው ፈጽሞ እንደተለወጠ የሚያመለክት አይደለም። ሉቃስም ይህንንው ኩነት ሲተርክና በወቅቱ ደቀ መዛሙርቱ ስለነበሩበት ሁኔታ ሲዘግብ "... እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር" (ሉቃስ 24፥ 16) ይለናል። ስለዚህ ከትንሳኤው በፊትም ሆነ በኋላ ኢየሱስ ይህ በሌላ መልክ የመለወጥና የመገለጥ ልምምድ እንደነበረው አስተውሉ።
ታዲያኮ ከትንሳኤው በኋላ ኢየሱስ በተዘጉ ደጆችና መስኮቶች አልፎ ሄዶ ነበር ብላችሁም ታስቡ ደግሞ ይሆናል። መልካም፣ ታዲያ ይህ የተለየ ስጋ ነበር ወይ? በጭራሽ አይደለም፣ ቀጥሎ ያለውን ተመልከቱ፦
ሉቃ 4፥ 28-30 በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥ ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤  እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
ህዝቡ ኢየሱስን ከላይ ወደ ታች ገፍትረው ሊጥሉት ወደ ገደል አፋፍ የዘውት ወጡ፣ እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ። ያንን እንዴት አደረገው? ከሞት ከመነሳቱም በፊት እንኳ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ያደርግ ነበር።
ይልቁን ግን ጌታ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሉቃስ ምን ብሎ እንደጻፈ ልብ አድርጉ፦
ሉቃ 24፥ 38-39 እርሱም፦ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።
በመስቀል ላይ የተቸነከረው ቁስል በርግጥም በግልጽ በሰውነቱ ላይ የሚታይ እንደነበር ከዚህ እናስተውላለን። ደግሞም እርሱ ስጋና አጥንት እንጂ መንፈስ  እንዳልሆነም ተናግሮአል።
ሉቃ 24፥ 40-43። ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፦ በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ።
ብዙዎች ከሞት ከተነሳ በኋላ የኢየሱስ ስጋ በተለየ ተፈጥሮ የከበረ እንደሆነ ያስባሉ። እዚህ ላይ ግን ኢየሱስን ፍጥረታዊው ሰው የሚመገበውን አሳና ማር በደቀመዛሙርቱ ፊት ሲበላ እናየዋለን። የከበረ ሰጋ ይራባልን? ተርቦሳ ይበላልን? እንዲህ ያሉ አገላለጾች የሚያሳዪኝ ያው እውነተኛውን ተፈጥሮአዊ ስጋ ነው እንጂ ሌላ አይነት አዲስና እንግዳ አካል እንዳስብ አያደርጉኝም። ለዚህ ነው ከመቃብር የወጣው የኢየሱስ ሥጋ ያው ራሱ ወደ መቃብር ከወረደው ሥጋ ጋር አንድና አንድ አይነት ነው፣ ምንም የተለየ ነገር የለውም የሚለውን ማመን እመርጣለሁ፣ ስል አቋሜን መነሻዬ ላይ ያስታወቅሁት። በዮሐንስ የተዘገበውን ደግሞ ስሙ፦
ዮሐ 20፥ 27-28 ከዚያም በኋላ ቶማስን፦ ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው። ቶማስም፦ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።
እዚህም ላይ እንደገና ያንንው በሚስማር የተበሳውን የኢየሱስን የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካር እንዲሁም የጎኑን መወጋት እናያለን። ልክ ቀደም ሲል ከትንሳኤው በፊት መስቀሉ ላይ እንደሆነውና እንደነበረው አይነት ማለት ነው። እስቲ በአንክሮ አስቡት፣ "በትንሳኤ የምንቀበለው የከበረው ሥጋችን ፍጹም ይሆናል" ሲባልና ተደጋግሞ ሲነገረን ሰምተናል፤ የኢየሱስ ሥጋ ግን እንደዚያ እንዳልነበረ ብዙዎች አላስተዋሉም። በሥጋው ሞቶ በመንፈስ ሕያው የሆነው ኢየሱስ ከሞት በተነሳው አካሉ የመስቀሉ ችንካርና ጎኑን የወጋው ጦር ቁስል አብሮት እንደነበር፣ ይህንንም ለደቀመዛሙርቱ እንዳሳያቸው ወንጌላት በግልጽ ያመለክታሉ። ኢየሱስ ከትንሳኤውም በኋላ የነበረው አካል ያው ራሱ እግዚአብሔር ያዘጋጀለትና ከድንግል ማርያም የነሳው ሥጋው ነው እንጂ፣ ከትንሳኤው በኋላ የተቀበለው ሌላ የተለወጠ የከበረ ሰጋ አልነበረም። እኛም በትንሳኤ የምንቀበለው ሰውነታችን በእርግጥም እንደ ኢየሱስ አይነት እንደሚሆን እናውቃለን፣ ዳሩ ግን በልማድ ሲነገረን የኖረው የሥጋ ትንሳኤ ከዚህ ጋር አይጣረስም ወይ? የኢየሱስ የትንሳኤ አካል በጎኑ ላይ የተወጋውና በእጆቹ መዳፍ ላይ ያለው የችንካሩ ቁስል ይገኝበት ከነበረ፣ ታዲያ ይህ ማለት፣ እኛም በትንሳኤ የምንቀበለው ሰውነት ያለፍንበትንና የተለማመድነውን የማንኛውም አይነት ህመምና ስቃይ ጠባሳ ሁሉ ይገኝበታል ማለት ነውን? ለምሳሌ የኢየሱስ የችንካሩ ምልክት እና የቁስሉ ጠባሳ ከትንሳኤው በኋላ በአካሉ ላይ ይታይና ይዳሰስ ከነበረ፣ እግሩ ተቆርጦ በአካል ጉዳት የኖረና ቆይቶ የሞተ ሰው 'በትንሳኤ ቀን' ምን አይነት አካል ሊኖረው ነው? አይኑስ ጠፍቶ ወይም ወጥቶ የኖረ ሰው በትንሳኤ የሚቀበለው አካል ምን ይሆን? የትንሳኤን ሕይወት በምድር ሕግ ለመተርጎምና ለመረዳት መሞከር ጣጣው ብዙ ነው። በሥጋ ትንሳኤ የምታምኑ ወንድሞቼ ሆይ፣ እንዲህ ካለው አጉል እምነት ወደቃሉ ብርሃን እንድትመለሱ ጸጋውን በትህትና እየለመንሁ በክርስቶስ ፍቅር እመክራለሁ። ስለ ሥጋ ትንሳኤ ለማሰብ በወደድን መጠን እንግዲያውስ "የብልቶች ትንሳኤ"፣ የእግር እና የአይን ወዘተ እያልን፤ ሲልም ትንሳኤን የተቀበለ ሰው ይበላል አይበላም፣ ይተኛል አይተኛም፣ ይጸዳዳል ወይስ አይጸዳዳም በሚል መቋጫ በሌለው ተረት ውስጥ ሰምጠን እንቀራለን። 
 የኢየሱስ የሥጋው ትንሳኤ አልአዛር ከነበረው የተለየ አልነበረም ማለት እንችላለን። ወልድ በታሪኩ ሥጋን የለበሰው በልደቱ አንዴ ነው፣ በመስዋዕታዊ ሞቱም በመቃብር ያደረው ያው ሥጋው ወደ ሌላ አይነት የትንሳኤ ሥጋ ሳይለወጥ ራሱ ሥጋው ከመቃብር ወጥቷል። ትንሳኤው የኢየሱስን ሥጋ ወደ ምንም አለወጠውም፣ ከትንሳኤውም በኋላ የነበረው ያው ከመጀመርያ አብ ያዘጋጀለትና በመስቀል ላይ የቆሰለው ሥጋው ነው፤ ይልቁንም ቃል የሆነው ኢየሱስ በተዘጋጀለትና በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋው ከመሰረቱ ከትንሳኤው በፊትም ሆነ በኋላ ያው ኃጢአት ያላወቀው ክቡር ነበር፣ እንጂ ቀድሞ ያልነበረውን የተለየ አይነት አዲስን የትንሳኤ ሥጋ ለራሱ አልወሰደም። በኢየሱስ የሚሞተው የማይሞተውን፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አለበሰም፣ ይህ የሚሰራው ለሙታን ነው፤ ይልቁንም በኢየሱስ የማይሞተው ሞተ፣ የሞተውም ተነሳ። የሞተውና የተነሳው ክቡር ሥጋው ወደ ሰማይ አርጓል። ከፊልጵስዩስ 3፥ 21 ጋር ሊጠቀሱ የሚችሉና ኢየሱስ በሰማይ አካል ያለው መሆኑን የሚያመለክቱ ጠንካራ የሆኑ ማስረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት አሉ፣ ለምሳሌ፦ ማርቆስ 16፥ 19፤ ሉቃስ 24፥ 50-51፤ ሐዋርያት 1፥9-11፤ ኤፌሶን 4፥ 8-10፤ ቆላስያስ 2፥ 9፤ 1ጢሞቴዎስ 3፥ 16፤ እብራውያን 1፥ 3፤ 10፥ 12፤ 1ጴጥሮስ 3፥ 22፤ ራእይ 1፥ 9-18 ማየት ይቻላል።
ስለዚህ ጳውሎስ፦ "ክቡር ሥጋውን እንዲመስል" በሚልበት ጊዜ፣ ይህ "እንዲመስል" የተሰኘው ቃል በግሪኩ 'summorphos' ነው፤ [እንግሊዘኛ ትርጉሙ፦ Jointly formed, i.e. (figuratively) similar:--conformed to, fashioned like unto. ይሰኛል]፤ ቃሉ morphe ከተሰኘ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም "የአንድ ነገር አስፈላጊና መሰረታዊ ጠባይ፣ አማራጭና ተለዋጭ የማይገኝለት፣ አምሳያና እኩያ የሌለው አስፈላጊና መሰረታዊ ቅርጽ፣ አንድ አይነት፣ የተስማማ፣ "እንደ እርሱ ሆኖ የተሰራ"፣ ነው። በእርግጥ እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚጠቀምበት ቃል morphe የተሰኘውን ሳይሆን 'summorphos' የሚለውን ነው፤ በሁለቱ የቃል አጠቃቀም ላይ ጉልህ ልዩነት አለ። 'summorphos' ትርጉሙ፣ "ተጋጥሞ መሰራት" ነው። አብሮ መሆንን ወይም የአብሮነትን አንድነት ያሳያል። ይኸውም የስፍራ ደረጃ (positional) አንድነት ነው። አማኞች ከክርስቶስ ሥጋ ጋር የሚኖራቸውን አብሮነት የሚያሳይ ነው (ይህንን አብሮነት ወደኋላ ላይ እመለስበታለሁ)፣ እንጂ መመሳሰል ወይም አንድ አይነትነት አይደለም።

4. ልዋጤው
".....እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል" 
ጌታ ተመልሶ በመምጣቱ ምክንያት ይህ ጉዳይ ቀድሞ የሆነና ያለፈ ድርጊት ከሆነ፣ ታዲያ እነዚያ ጌታ ሲመጣ ሊቀበሉት የተዘጋጁቱ በሕይወት የነበሩት የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን የተዋረደው ሥጋቸው ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተለወጠው እንዴት ነው? "መቼ?" የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ "እንዴት?" የሚለውን ለመመለስ ብዙም አይቸገርም። የዚህ ልውጠት ጠቅላላ ነገሩ "ጊዜው" ላይ የተመሰረተ ነውና፣ ጊዜውም ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣል። በጌታ ዳግመኛ ምጽአት የአካላቸውን መለወጥ ይጠባበቁ የነበሩና በሕይወት እያሉ ይህ ተስፋ የነበራቸው የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አማኞች ናቸው። ስለዚህ ጥናታችንን በመቀጠል የልዋጤውን ተፈጥሮ ወይም ባህርይ እንዴት እንረዳለን? ወደሚለው እንለፍ። 
ይህንን የልውጠት ሁናቴ በአግባቡ ለመረዳት በመጀመርያ፦ "ይለውጣል" ወይም "ልዋጤ" የተሰኘውን ቃል እንይ፤ ቃሉ ጥቅም ላይ በዋለበት የንባብ ክፍል ውስጥ የበኩረ ቃሉን አገባብ መረዳት ያስፈልጋል። የግሪኩ ቃል "metaschematizo" ነው፣ [እንግሊዘኛ ትርጉሙ፦ "to Transform", "to alter", "to change the apperance", "transfigure" or "disguise"; figuratively, to apply /by accommodation/:--transfer, transform / self በሚል እንደሚተረጎም Geoffrey W. Bromiley ባዘጋጀው The Teological Dictionary of The New Testament በተሰኘው መጽሐፍ ማየት ይቻላል (በአማርኛችን መቀየር፣ መለወጥ፣ መልክን ወይም ገጽታን መለወጥ፣ በልዩነት ሌላ መሆን ወይም የተደበቀውን ሌላ መግለጥ፤ በምሳሌአዊ አገላለጽ ያለውን ሁኔታ፣ መተግበርን፣ ለራስ ማድረግን፣ ማስተላለፍን ራስን መለወጥን ያሳያል)]። የቃሉ ተገቢ ትርጉም 'አምሳላዊ ልውጠት' ነው። 
ለውጡ "ወደ አዲስ አይነትነት መለወጥ" መሆኑንም ከጥንታዊ የግሪክና የአይሁድ ጽሁፎች እንረዳለን። ሰማዕታት በሞታቸው ጊዜ ተለውጠው ወደ ሰማይ የሚሄዱበትን ክብር እንደሚያሳይ ለምሳሌ በተጨማሪው የብሉይ ኪዳን መጻህፍት የሰባ ሊቃናት ትርጉም ላይ ይታያል። ፋይሎ ግሱን ሲጠቀምበት 'ወደ አዲስ ቅርጽ ወይም መልክ መለወጥ' አድርጎ ያቀርበዋል፤ ጆሳፈስም ልብስን እንደመለወጥ ወይም እንደ ማስመሰል፣ እንዲሁም በገጽታ ተለውጦ እንደ መታየት ባለ መልኩ ይጠቀምበታል። በጥንት ቤተክርስቲያን ባሉ የጽሁፍ ስራዎች የቃሉንና የግሱን አጠቃቀም አስመልክቶ እንደምሳሌ ልንወስደው የምንችለው ምንም የሰነድ ማስረጃ ባይኖርም የሄርማ ራእዮች በተሰኘው ሰነድ ቅጽ 5.1 ላይ  'schema' የተሰኘው የግሪክ ቃል ጥቅም ላይ ውሏል ትርጉሙም ልብስ ወይም መልበስ እንደማለት ነው።
በአዲስ ኪዳን ግን ቃሉ በተለያየ አውዳዊ አገባብ አምስት ጊዜ ያህል ጥቅም ላይ ውሎ እናየዋለን። በአምስቱም ውስጥ ያለው የቃሉ መሰረታዊ ፍቺ፦ ልዋጤ፣ ዝውውር፣ ራስን መለወጥ፣ በምሳሌያዊነት ወደ መኖርያነት መቀየር ሲሆን፤ በአምስቱም ውስጥ ያለው ትርጓሜ የሚያመለክተው 'አምሳላዊ ልውጠትን' ነው፤ ይኸውም ከውስጥ የማይመጣ የውጫዊ መግለጫን ግምት እንደ ምሳሌ አድርጎ መስጠትን ወይም መውሰድን ነው [The outward expression that does not come from within]። ይኸውም 'መምሰል' እንጂ 'ራሱን ሆኖ መገኘት' አይደለም።
ለምሳሌ በዚህ በንባብ ክፍላችን ውስጥ አማኞች ወደ ፍጻሜው የሚያደርሳቸው መንፈስ ያላቸው መሆኑን፣ ዳሩ ግን ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ያላቸውን ይህንን "የተዋረደ" እርሱም የሚሞት አካል ክቡር ወደሆነው የማይሞት አካል የሚለውጠው መሆኑን ያመለክታል። በሌሎቹ የአዲስ ኪዳን ምንባባትም በተለያየ አውዳዊ አገባብ ቃሉ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልከቱ። ይህ የፊልጵስዩስ መልእክት ከተጻፈበት ጊዜ ጥቂት አመታት ቀደም ብሎ የተጻፈው 2ኛ ቆሮንቶስ ስለዚሁ የጽድቅና የልዋጤ ተስፋ በምዕራፍ 3፥ 18 ላይ ሲያበስር፣ "እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን" ሲል አለኝታቸውን ይመሰክራል።  በዚህ "metaschematizo" በተሰኘ የግሪክ ቃል ላይ የተሻለ መረዳትን ያስጨብጡን እንደሆነ እነዚህን ጥቅሶች ጨምረን እንመልከት፦
1ቆሮ 4፥6  ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ፦ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ (metaschematizo) ተናገርሁ።
ጳውሎስ እዚህ ላይ በመንፈስ ህጻናት ለሆኑ የቆሮንቶስ ሰዎች በደረጃቸው ልክ ወርዶ ስለ ራሱና ስለ አጵሎስ "እንደ ምሳሌ" ሆኖ (ከውስጥ የማይመጣ ውጫዊ መግልጫን ከግምት በማስገባት)፣ ማለትም እነርሱን ሆኖ ሳይሆን "እነርሱን መስሎ" የሚለምናቸውና የሚመክራቸው ይመስላል። በመካከላቸው ሰፍኖ ስለነበረው የህጻናት ክርክር አስቀድሞ በምእራፍ 3 ላይ ገስጾአቸው ነበር፤ አሁን ደግሞ ጳውሎስ ራሱና አጵሎስ ጭምር ከቆሮንቶስ ሰዎች ይልቅ በሳሎች መሆናቸውን እያወቀ፣ የሚሻልና የሚበልጥ ሆኖ ለመታየት ግን አልፈለገም፣ ከዚያ ይልቅ ግን ትኩረታቸውን በጌታ ላይ እንዲያደርጉ እንጂ፣ በራሳቸው ላይ  እንዲያደርጉ አይፈልግም። "ምሳሌነቱ" ከውስጥ የማይመጣ ውጫዊ አገላለፅን ከግምት በማስገባት በቆሮንቶስ ሰዎች ፊት የበላይና የሚሻል ሆኖ ከመታየት የሚያቅብ ይመስላል። በቆሮንቶስ ሰዎች ፊት የሚበልጥና የተሻለ ሐዋርያ ሆኖ ከመታየት የሚያቅብ መገለጫ ነው።
ጳውሎስ ይህንን metaschematizo የተሰኘ ቃል በሁለተኛው መልእክቱ ላይም ሲጠቀምበት እናያለን፣ የቃሉን አጠቃቀም በተመለከተ ይኼኛው በተለይ ጉልህ የሆነ ምሳሌ ነው፦
2ቆሮ 11፥13-15 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ (metaschematizo)፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና (metaschematizo)። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ (metaschematizo) ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።
ተመልከቱት ግሱ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ይታያል። ሐሰተኞቹ ሐዋርያት እነርሱም የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ወደ ሐዋርያነት ራሳቸውን ለውጠዋል፣ እውነተኞቹን የክርስቶስ ሐዋርያት ግን አልነበሩም፣  ሰይጣንም የብርሃን መልአክ አልነበረም፣ መምሰል ግን ችሏል፣ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች አልነበሩም፣ ራሳቸውን ግን ማስመሰል ችለዋል፣ ይህም ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን በሚያሳይ መግለጫ  ተመሳስለው ተገኙ እንደማለት ነው፣ እንጂ ያንን የመሰሉትን ነገር ሆነው ተገኙ ማለት አይደለም። በዚሁ አይነት መንገድ እነዚያም ቅዱሳን የተዋረደው ስጋቸው ተለውጦአል። ይህም በ70 አ.ም ላይ ከሆነው የቤዛነት ቀን ፍጻሜ ጀምሮ ክርስቲያኖች የሆኑ ሁሉ አለመሞትን እግኝተዋል፣ ማለት ነው።
ስለዚህ እነዚህ የግሪክ ቃላት በንባብ ክፍላችን አውድ ውስጥ ባላቸው ጠቀሜታ ላይ ቆመን "የተዋረደው ሥጋቸው "ክቡር ሥጋውን እንዲመስል" መለወጡ (ማለትም metaschematizo መደረጉ) አካሉን የመምሰል (የ summorphos) ውጤት ነው" ልንል እንችላለን። የተዋረደው ሥጋቸው አካሉን መስሎ (summorphon በመሆን) የተገለጠው፣ መስሎ እንዲለወጥ  metaschematizo በመደረጉ ምክንያት ነው። በመሆኑም፣ ቁጥር 21 እንደዚህ ሊነበብ ይችላል፦ እርሱም (ክርስቶስ) ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ (ይህንን የተዋረደው ሥጋችንን) ክቡር ሥጋውን እንዲመስል (summorphon) የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል (metaschematizo) ።
"Morphed" የሆነውና ከመሰረቱ ክቡር የሆነው የክርስቶስ አካል ነው። እኛም ከወደድን ስጋችን ይህንን ክብር የሚቀዳጀው በመተባበር ወይም በመምሰል (summorphed በመሆን) በዚህ ህይወት ብቻ ነው። ከክርስቶስ ጋር አንድ የምንሆንበንት እምነትንና ቅዱስ ጥምቀትን የምንለማመደው በዚህ ህይወት ብቻ ነው። ተዳሳሹ አካል አሁን ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን የሚያሳይ መገለጫ የሆነውም ለዚህ ነው፣ በዚያ መንገድ አይታይ ይሆናል እንጂ፣ አሁን በእምነትና በቅዱስ ጥምቀት ላገኘነው የማይሞት መንፈስ ተዳሳሹ አካል ቤቱ ነው። ይህ ማለት ግን አሁን የማይሞት ሥጋ አለን ማለት አይደለም። ሥጋ በሮሜ 6፥ 4 ውስጥ እንደተገለጠው ከመቀበሩ ሌላ ፈጽሞ morphed አይሆንም። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ተዳሳሽ የሆነ የከበረ ስጋ የሚታያቸው መጻእያን ግን በአውደ ምንባቡ ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለው የግሪክ ቃል ላይ ሲቀባቡ ይስተዋላሉ።
1ቆሮ 15፥ 51-53  እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን (metaschematizo)፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን (metaschematizo)። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።
እዚህ ላይ የተነገረለት ልዋጤ (metaschematizo) የማይሞተውን ( አለመሞትን) መልበስ ነው። ተዳሳሹ ሥጋ ለፍጥረቱ እንግዳና ባእድ ወደ ሆነ ሁናቴ ይወሰዳል። የሚለወጠው ፍጥረቱ አይደለም፣ መንፈስ የሚሰጠውን የማይሞተውን ሁናቴ በጊዜያዊነት መውሰዱ ብቻ ነው። ፍጥረታዊ የሆነው ተዳሳሹ የተዋረደው ሥጋ ራሱ "የማይሞት" ይሆናል ማለት አይደለም፣  ይልቁንም በቀላሉ የማይሞት ለሆነው ለክርስቲያን መንፈስ ማደርያ ቤት የመሆንን ደረጃ ይቀበላል እንጂ። metaschematizo የተሰኘው ቃል ትርጉምና ጠቀሜታውም ይኸው ነው፤ በእውነተኛው አካላዊ ተፈጥሮ ላይ ምንም አይነት መሰረታዊ ተጽእኖና ልዩነት የማያመጣ ነገር ግን በአይነቱ ልዩ የሆነውን ጥራት (ለጊዜው) መልበስ ነው። ያ ደረጃና የክርስቲያን ማዕረግ ከሞት በኋላ መንፈስ በሚለይበት ጊዜ አብሮን ይኖራል እንጂ፣ መቼም ቢሆን ሥጋ ወደ ሰማይ እንደማይሄድ ሁሉ አንድ ቀን ሥጋን ከመቃብሩ ውስጥ አውጥቶ ሊያመጣው ከሥጋ ጋር አብሮ የሚቀርም አይደለም። 
አንድ ማስተልዋ ያለብን እውነት፣ በዚህ በፊልጵስዩስ 3፥ 21 የተነገረለት ልዋጤ ከፍ ሲል በተራ ቁጥር 2 የአውደ ምንባቡን ዳሰሳ ባየንበት ጥናታችን አጽንዖት ሰጥቼ እንደጠቀስኩት በሽግግር ወቅት ላይ የተነገረ ተስፋ መሆኑን ነው፤ ልዋጤውም በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት የሽግግሩ ዘመን ሲያበቃ ያኔ በሕይወት ለነበሩት ላልሞቱት ቅዱሳን የሚሰራ ነው። ጌታ በመምጣቱ አስቀድመው ሙታን ለነበሩት ቅዱሳን ትንሳኤን ሲሰጣቸው፣ ገና ላልሞቱትና በናፍቆት ሲጠባበቁት ለነበሩ ሕያዋን ቅዱሳን ደግሞ ልዋጤን ይሰጣቸዋል፤ እንጂ ልዋጤ እና ትንሳኤ በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት የተፈጸሙ  ከመሆናቸው በቀር እርስ በርሳቸው ለአንድ አላማ የሚሰሩ ክስተቶች ናቸው። የትንሳኤም ሆነ የልዋጤ አላማ ቅዱሳንን በሰማያዊ አካል ከጌታ ጋር  ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት  መውሰድ ነው።
አማኞች ባመኑበት ቅጽበት ከጸጋው የተነሳ በቅዱስ ጥምቀት አሰራር ወደ ፍጻሜው የሚያደርሳቸውን መንፈስ ማግኘታቸው አዲስ ኪዳንን ሞልቶ የሚፈስ እርግጠኛ አለኝታ ነው፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ያኔ እርሱ ያንን የወቅቱን የተዋረደ ሥጋቸውን ወደ ክቡር አካል ይለውጠዋል፣ ምክንያቱም ያው አዲስ ኪዳን የአማኞችን የቤዛነታቸውን ሙላት ከዳግመኛ ምጽአቱ ጋር አቆራኝቶት ይገልጠዋልና ነው።

5. እነርሱ እና እኛ
ፊልጵስዩስ 3፥ 21 ከሁሉ በፊት የሚያመለክተው፣ ክርስቲያኖች ገና በሕይወት እያሉ በውስጣቸው እንዲኖር ከተሰጣቸው የማይሞት ምንፈስ ቀጥተኛ ተጽዕኖና ውጤት የተነሳ የማይሞተውን ስለ መልበሳቸው ነው እንጂ፣ ገና ወደ ፊት ይሆናል ተብሎ በብዙዎች ስለሚጠበቅ ከሞት የመነሳትና ከመቃብር ወጥቶ ስለሚመጣ ስለተዳሳሹ አካል መለወጥ ጉዳይ አይደለም። በቀራንዮ መስቀል ላይ በክርስቶስ ሞት ተመርቆ የተሰጠውን፣ በቅዱስ ጥምቀትም አማካኝነት በቅድስት ቤተክርስቲያን እንዲሰራና በእምነት እንዲታደል እግዚአብሔር በጸጋው ያደረገውንና፣ ደግሞም በ70 አ.ም ላይ ፍርዱን በአሮጌው ሥርአት ላይ አድርጎ ቤዛነታችንን በይፋ ያቀዳጀንን፣ የእግዚአብሔርን አሰራር አለመረዳት አሁንም ገና ወደ ፊት በዘመናት ርቀት ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል ድጋፍ የሌለውንና ፈጽሞ የማይኖረውን (NON EXISTENCE) "የሥጋ ትንሳኤ" ያስጠብቃል። እንደውም መጽሐፍ ቅዱስ በገጾቹ አንድም ቦታ ላይ 'የሥጋ ትንሳኤ'፣ ወይም 'አካላዊ ትንሳኤ'፣ ወይም 'ቁሳዊ ትንሳኤ' የሚል ቃልም ሆነ ሃረግ የለውም፤ በቅዱስ ቃሉ እውቅና የተሰጠው "የሙታን ትንሳኤ" ወይም "ከሙታን መነሳት" ብቻ ነው፤ በአንድ በኩልየአስተምህሮ ልዩነታችንም የሚነሳውም ከዚህ የቃል እና የስያሜ አጠቃቀም ዙርያ ነው።
በእነዚያ የሽግግሩ ወቅት በህይወት በነበሩ ቅዱሳን፣ ከእነርሱም አስቀድሞ ሞተው በነበሩት አማኞች እና ከ70 አ.ም በኋላ ባመንን በእኛ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ያስፈልጋል። እነርሱ፣ ማለትም በሕይወት የነበሩ ቅዱሳን የማይሞተውን አካል ተቀብለው በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለመኖር ሊወሰዱ የሞታቸውን ጊዜ ሳይሆን የዳግመኛ ምጽአቱን ፓሮውዥያ መጠበቅ ነበረባቸው። በሽግግሩ ወቅትና በአሮጌው ኪዳን በታች ሆነው ከፓሮውዥያው በፊት ያንቀላፉቱ ሙታን ቅዱሳን ደግሞ ክርስቶስ በትንሳኤው ከሃደስ ያወጣቸውን የቅዱሳን ነፍሳት ባከማቸበት በሰማይ ባለው መቅደስ አደባባይ በመሰዊያው ዙርያ የምጽአቱን ቀን ትንሳኤያቸውን እስኪቀበሉ ድረስ ይጠብቁ ነበር። እኛ ከ70 አ.ም በኋላ ያመንን የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ደግሞ በቅዱስ ጥምቀት አሰራር ባገኘነው አለመሞት ምክንያት ያንን የማይሞተውን አካል በሞታችን ቀን ወዲያውኑ ተቀብለን፣ ከፖሮውዥያው በኋላ ወደ መቅደሱ ውስጥ ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ድል ነስተው ከገቡት አእላፋት ጋር በዘላለማዊ ደስታና ክብር እንቀላቀላለን።
ከ70 አ.ም በኋላ ያሉ ክርስቲያኖች ሕያዋን ናቸውና በሥጋቸው በሚሞቱበት ጊዜ ከመስቀሉ በፊት የሞቱ ቅዱሳን እንደነበራቸው አይነት ትንሳኤ አይኖራቸውም። ትንሳኤ የሚያስፈልገው ለሙታን ብቻ ነው፣ እንጂ ለሕያዋን አይደለም። ትንሳኤን የሚለማመዱትም "ገነት ከሆነው ሃደስ" የወጡ ሙታን ቅዱሳን ብቻ ናቸው። ስለዚህም የእነርሱ ትንሳኤ ከሲኦል ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት የሆነ ትንሳኤ እንጂ፣ ልክ 'እንደ ዞንቢ ልቦለድ ፊልም' ከምድር  ጉድጓድ ከመቃብር ወጥቶ የመምጣት አይነት ክስተት አይደለም። እነዚያም የሽግግሩ ወቅት ቅዱሳን በሚሞቱበት ጊዜ ክርስቶስ በትንሳኤው ድል ነስቶ በእርገቱ በማረከውና፣ ወስዶ በሰማይ ወዳለው የመቅደሱ አደባባይ ባመጣው "ገነት በሆነው ሃደስ" የትንሳኤያቸውን ቀን እንዲጠብቁ ተደርገው ተከማችተዋል ብዬ አምናለሁ። ድል ነሺው ንጉሰ ነገስት ጌታ ኢየሱስ ሞትንና መቃብርን በትንሳኤው ድል ነስቶ፣ ግርማን በተጎናጸፈው ዕርገቱ አእላፋት ምርኮኞችን አስከትሎ በክብር ወደ ላይ ወጥቶአል።  በመዝሙር 68፥ 18 "ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ"  በሚለው  መሰረት፣ ከትንሳኤው በኋላ በድል አድራጊነት ግርማው ወደሰማይ ሲወጣ ያኔ ገነትን እና በዚያ በአብርሃም እቅፍ የነበሩትን ሁሉ ማርኮ እና አስከትሎ ወደ ሦስተኛው ሰማይ (2ቆሮንቶስ 12፥ 1-4) ይዟት አርጓል። "ከኃያላን ጋር ምርኮን ይከፋፈላል" እንደተባለ ኃያላኑን ሲኦልንና ሞትን ዲያብሎስንም ድል ነስቶ፣ አለቅነትንና ሥልጣንን ኃይላትንም ሁሉ ገፎ፣ ሥልጣንን ሁሉ በሰማይና በምድር የራሱ ያደረገው ጌታ ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ከፍታ ሲወጣ የማረካቸውን ነፍሳት ከዘላለም ለእርሱ ተጠብቀው ያሉትን ድርሻዎቹን ሁሉ ይዞ ወጥቷል። " ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው" (ኤፌሶን 4፥ 8-10)፤ ክርስቶስ ወደ ምድር ታችኛ ክፍል፣ ወደ ታች ወደ ሀደስ ወረደ፤ ደግሞም ከሰማያት ሁሉ በላይ ወጣ፣ ሲወጣም ምርኮውን ይዞ ወጣ። እንግዲህ ተመልከቱ ክርስቶስን ጨምሮ በአሮጌው ኪዳን የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ወርደው ይሄዱባት የነበረችይቱን ገነት ሀደስ፣ ጳውሎስ ግን ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ በነበረው የሰማያዊ ጉዞ ልምምዱ ተነጥቆ ገነትን በሰማይ አያት እንጂ አስቀድማ በነበረችበት ስፍራ ወርዶ አላያትም፣ (2ቆሮንቶስ 12፥ 2 እና 4)። ስለዚህ በክርስቶስ ወደ ላይ መውጣት ከሰማዕታትና ምርጦች ከሆኑት ቅዱሳን መካከል ብዙዎቹ ነፍሳት በሰማያዊው ቤተመቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ካለው የደጁ አደባባይ በመሰውያው ስር የቤዛነታቸውን ቀን እየተጠባበቁ እንዲከማቹ የተደረጉ ሁሉ አስቀድመው እንደ ምርኮ በእርግጥ  ወደዚያ ወደ ላይ የተወሰዱ ናቸው፤ ዮሐንስ በራእዩ፦
 
"አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።"(ራዕይ 6 9-11) ሲል ይነግረናል። 
[ዕርገቱንና ትሩፋቱን የዳሰስሁበትን ጽሁፍ እንደተጨማሪ መረጃ መመልከት ለምትሹ እነሆ ሊንኩ፦ 
http://gizachewkr.blogspot.com/2019/05/blog-post.html]

 እነዚህ በየዘመኑ የታረዱ ነፍሳት በታላቁ መከራ ወቅት የሚገደሉ የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪፈጸም ድረስ "ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ" ከተደረጉ በኋላ፣ በ70 አ.ም በሆነው ምጽአት ወዲያው ትንሣኤን አግኝተው ከክርስቶስ ጋር የተመለሱና በአዲሱ የማይሞት አካል ከክርስቶስ ጋር የነገሱ ቅዱሳን ናቸው። እኛም አካላዊውን ሞት ስንሞት አምነን ባገኘነው አዲሱ ሕይወት ለዘላለም ከጌታ ጋር ልንሆን በቀጥታ ወደ ሰማይ በክብር እንሄዳለን እንጂ፣ ከቆይታ በኋላ ከመቃብር ወጥተን በአካል ልንመጣ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሲሞቱ ይሄዱበት ወደነበረው መከማቻ ሲኦል አንሄድም። ለእኛ ወደ ሰማይ እንሄድ ዘንድ አሁን ትንሣኤ አያስፈልገንም። ምክንያቱም ከ70ው አ.ም የዳግመኛ ምጽአቱ ተስፋ ፍጻሜ በኋላ ሀደስ ከሆነው ሲኦል የሚነሱና የሚወጡ ሙታን አይኖሩም፤ ስለዚህም ከ70 አ.ም በኋላ ላሉ ቅዱሳን ትንሣኤ አስፈላጊያቸው አይደለም፣ ሙታን አይደሉም አይሆኑምና። ነገር ግን ትንሳኤ ከ70 አ.ም በፊት ሞተው በሲኦል ሀደስ ለነበሩ ቅዱሳን አስፈላጊያቸው ነበር። እነርሱ ወደ ሰማይ መሄድ ከመቻላቸው በፊት ከሲኦል ሀደስ መነሳት ነበረባቸው፤ ወደ ሰማይም ሊገቡ የሚችሉት በማይሞተው የትንሳኤ አካል ብቻ ነው። 'ጌታችን በተመለሰ ጊዜ ሙታን በትንሣኤ ሕያዋንም በመለወጥ ወደሰማይ ሄደዋል!!' ብለን ለማመን ከቅዱስ ቃሉ ግልጽ ትምህርት በቀር የታመነ ዋቢ የለንም። 
ከ70 አ.ም በኋላ ባለው የመንግስት ዘመን አምነን የዳንን እኛ ደግሞ ሰማያዊውን አካል ለብሰን ወደሰማይ ለመሄድ የሞታችንን ቀን እንጠብቃለን እንጂ አሁን "ሙሉ በሙሉ በሰማይ ነን፣ አካላችንም ሰማያዊ ነው" ማለት አይደለም። እርግጥ ነው ከስፍራ አንጻር በአቀማመጣችን (positionaly) "በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ" ነን፤ ዳሩ ግን በዚህ በምድር በምዋቲውና ፈራሹ አካል ገና እየኖርን በሙላት በሰማይ ልንሆንም ሆነ ሁሉንም የሰማይ በረከቶች አሁን በሙላት ልንለማመድ አንችልም፤ በጊዜ እና በቦታ ተገድቦ በሁኔታዎች የተወሰነው ይህ የለበሥነው ብስብስ ሥጋ ያንን ለመለማመድ የሚያስችለው ተፈጥሮ የለውምና። ስለዚህ ያ እንዲሆን ይህንን ልብስ አውልቀን ከዚህ ማደሪያችን እስክንወጣ ድረስ የሞታችንን ቀን እንጠብቃለን። በሰማያትም የምንቀበለው ሰማያዊው አካል መንፈሳዊ ገጽታ ያለው ሆኖ እውነተኛና እርግጠኛ አካል ነው እንጂ ቅዠት አይደለም። ኢየሱስ በሰማይ አካል ያለው መሆኑን የሚያመለክቱና ጠንካራ ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ ምንባባት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ (ማርቆስ 16፥ 19፤ ሉቃስ 24፥ 50-51፤ የሐዋርያት ሥራ 1፥ 9-11፤ ኤፌሶን 4፥ 8-10፤ ቆላስያስ 2፥ 9፤ ፊልጵስዩስ 3፥ 21፤ 1 ጢሞቴዎስ 3፥16፤ እብራውያን 1፥ 3፤ 10፥ 12፤ 1ጴጥሮስ 3፥22፤ ራእይ 1፥ 9-18)። ይህ ለእኛም እንደ አርአያ የሚታይ ነው፤ " ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።" (1ዮሐንስ 3፥ 2) ተብሏልና። ስለዚህ የምንቀበለው ሰማያዊው አካል እንደ ኢየሱስ ያለውን አይነት ነው (ሮሜ 6፥ 5፤ 1ቆሮንቶስ 15፥ 49፤ ፊልጵስዩስ 3፥ 20-21)። ይህ ማለት ግን የኢየሱስ ሥጋው እንደተነሳና ከመቃብር ወጥቶ እንደመጣ የአማኞችም ሥጋ ተነስቶ ይመጣል ማለት አይደለም። ሰማያዊው አካላችን ያለውን ተፈጥሮ ለመግለጥ ጳውሎስ የሚጠቀምባቸውን "የማይሞት"፣ "የማይጠፋ"፣ እና "የከበረ" የሚሉትን ቃላት ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁ፣ የሰማያዊውን አካላችንን ሁናቴ ትረዳላችሁ (1 ቆሮንቶስ 15፥ 35-55፤ 2ቆሮንቶስ 4፥ 17፤ ፊልጵስዩስ 3፥ 20-21፤ 1ጢሞቴዎስ 3፥ 16)።
በማቴዎስ 17፥ 2 ላይ የተተረከው የኢየሱስ መለወጥ፣ ሰማያዊ አካል ተፈጥሮው ምን ሊመስል እንደሚችል አንዳች ግንዛቤን ይሰጠናል። አካላችን እንደ መላእክት አይነት እንደሚሆንም ኢየሱስ ተናግሯል ( ሉቃስ 20፥ 36፤ ሉቃስ 24፥ 4፣ 23፤ ዮሐንስ 20፥ 12-13)። መላእክት አንዳንድ ጊዜ በምድር ላይ ተገልጠው በገሃድ የሚታዩ ቢሆኑም እንኳ፣ ከጊዜና ከቦታ ውሱንነት ውጭ የሚኖሩ መሆናቸው ደግሞ ግልጽ ነው። በራእይ 1፥ 12-20 ያለው ምንባብም ሰማያዊው አካላችን የሚጋራውን የኢየሱስን ሰማያዊ አካል እይታ ይሰጠናል። እንግዲህ ይህ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብርሃን፣ ሰማያዊውና ዘላለማዊው አካላችን በተወሰነ መልኩ ተዳሳሽ- አካላዊነት (corporal) እና ግለሰባዊ (personal) የሆነ መልክ እንደሚኖረው ግንዛቤያችንን ይጨምርልናል። በጊዜና በቦታ የማይገደብና የማይለካን ማንነት ምን እንደሆነና ምን እንደሚመስል በቋንቋ ውስጥ አስገብቶ መተረክ የማይቻል በመሆኑ፣ እንደ ቃሉ ተማሪ ከመጽሐፍ ቅዱስ በሚቀዳ ትምህርት እና እርሱ በሚሰጠን ማስረጃ ብቻ ልንረካ ይገባናል።
በ70 አ.ም የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ የሕያዋን አካላዊ ልዋጤ ሆኗል ወይ? ይህ ልዋጤ የህያዋን አካላዊ መለወጥ እንጂ የህያዋን ትንሣኤ እንዳልሆነ ልብ አድርጉ። ያኔ ሕያዋን ገና አልሞቱም፣ ስለዚህም ገና በምድር ላይ እንጂ በሲኦል ሀደስ አልነበሩም፣ በመሆኑም ሕያዋን ሆነው በምድር ላይ መለወጥን ሊለማመዱ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንጂ ከሲኦል ሀደስ መውጣትና መምጣት በሚቻላቸው ሁኔታ ላይ አልነበሩም። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 51-52 ሐዋርያው ጳውሎስ የሞቱ ቅዱሳን ከሲኦል ሀደስ ወጥተው በሚነሱበት ጊዜ ለሕያዋን ቅዱሳን ምን እንደሚሆንላቸው አንስቶ ሲናገር፦ "...የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም [ህያዋን ሆነን የቀረን ቅዱሳን] እንለወጣለን።" ይላል። በዳግመኛ ምጽአቱ ጊዜ "የኋለኛው መለከት ሲነፋ" በሙታን ላይ እና በሕያዋን ላይ የሚሆነውን ነገር ልዩነቱን ልብ በሉ። ሙታን የሆኑቱ ከሲኦል ሀደስ እንዲነሱና እንዲወጡ ተደርገው የማይሞተውን አካል እንዲለብሱ ይሰጣቸዋል፤  ህያዋን የሆኑት ቅዱሳንም ደግሞ በዚያንው ጊዜ አስቀድመው በሥጋ መሞት ሳያስፈልጋቸው አካላቸው የማይሞት ሆኖ ይለወጣል። ይህ በእውነት ከቃላት በላይ የሆነ ሊነገር የማይችል ክስተት ነው፣ ጳውሎስ ግን ልንገራችሁ የሚለንና እንድንሰማው የሚፈልገው "ምስጢር" ነው።
በዳግመኛ ምጽአቱ ወቅት ህያዋን ሆነው በምድር ላይ የነበሩ ቅዱሳን ግን ወደ ሰማይ መሄድ እንዲቻላቸው የአካላቸው ልዋጤ አስፈልጓቸው ነበር። ይህ ምናልባት በአብዛኞቹ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ በጣም ስውር የሆነ አደናጋሪ ልዩነት ሊሆን ይችላል፤ መቼም በቃሉ ውስጥ የሌለ ነገር፣ እርሱም የወደፊት የሥጋ ትንሳኤ አለ ብሎ በከንቱ ከማመንና ተስፋ ከማድረግ፣ ቃሉ በግልጽ የሚያስተምረውን የሙታንን ትንሳኤና የመጀመርያው ክፍለዘመን ቅዱሳንን ልዋጤ ማመን ለቅዱስ ቃሉ ትምህርት በብዙ ይቀርባል። ጳውሎስም በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፥ 1-4 ባለው ክፍል የሚያነሳውና አጥርተን እንድንሰማው የሚፈልገው ምስጢር ይህ ነው። በ70 አ.ም የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ሙታን ተነስተው ሕያዋንም ተለውጠው ከክርስቶስ ጋር ወደ ሰማይ ሄደዋል ብለን ይህንን ምስጢር ለማመን ቃሉ ይደግፈናል። "በድንገት በቅጽበት አይን"፣ ይህም ማለት ወዲያውኑ የህያዋን ተዳሳሹ መዋቲ አካላቸው ከመዋቲነት ወደማይሞት ተለውጧል። ምንም እንኳ ይህ ክስተት አካላዊ ትንሳኤ ወይም የነፍሳት ትንሣኤ ባይሆንም፣ ይህ ግን ትንሣኤን የተቀበሉት ሙታን አዲሱን የማይሞት አካላቸውን በተቀበሉበት በዚያው ጊዜ ህያዋን የነበሩ ቅዱሳንንም በዳግመኛ ምጽአቱ ኩነትና ትሩፋት ውስጥ ተሳታፊ የሚያደርጋቸው እና አዲሱን አካላቸውን እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አንድ ዋና ነገር ነበር። ስለዚህም ሙታን ትንሣኤያቸውን፣ ህያዋንም አካላዊ መለወጥን አግኝተዋል፤ ፊልጵስዩስ 3፥ 20 እና 21ም ያኔ በዳግመኛ ምጽአቱ ተፈጽሟል። እነዚያም ሙታን የነበሩና የተነሱቱ፣ እንዲሁም ሕያዋን የነበሩና የተለወጡቱ፣ ሁለቱም ወገኖች በአንድ ላይ ጌታን በአየር ለመገናኘትና ከእርሱ ጋር ሊታይ በማይችለው ሰማያዊ ግዛቱ ለዘላለም ለመሆን ተወስደዋል። ቅዱሳኑም ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ በፓሮዥያው እንዲፈጸምላቸው በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ናፍቀው ሲጠባበቁት የነበረው ተስፋቸው ይኸው ነበር።

6. ክርስቶስ በሥጋው መነሳቱ
ክርስቶስን በተመለከተ፣ እርሱ በሥጋ ተነስቶ አልነበረምን? በእርግጥም ያለጥርጥር አዎ! "ዮሴፍ ይዞ በንጹህ በፍታ የከፈነው ሥጋውን" (ማቴዎስ 27፥ 59) ነው። "ከገሊላ ጀምሮ እርሱን ተከትለው የመጡ ሴቶችም መቃብሩን፣ ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አይተውታል" (ሉቃስ 23፥ 55)። ነገር ግን በሰንበት ማግስት ማልደው ወደ መቃብሩ የመጡ እነዚሁ ሴቶች "ሥጋውን በመቃብሩ ባጡት ጊዜ፣ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ አይተው" ወጥተው መስክረዋል (ሉቃስ 24፥ 23)። "ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።" (ሉቃስ 24፥ 5) እንደተባለ፣ እነሆ ሥጋውን ያኖሩበት ስፍራ፣ መቃብሩም ባዶ ነው፣ የክርስቶስ ሥጋው ተነስቷል።  እግዚአብሔር በክርስቶስ ሥጋ ላይ ከመጀመርያ አንስቶ ያደረገው ጥበቃና ክልከላ አያስገርምምን? "መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።" (ሉቃስ 1፥ 35) ተብሎ እንደተጻፈ ከመጸነሱና ከልደቱ አንስቶ በሥጋው የአዳም ኃጢአት እንዳያውቀው በልዩ ሁኔታ የተጋረደ ነው። "ከእርሱ አጥንት አይሰበርም" (ዮሐንስ 19፥ 36) የተባለለት የኢየሱስ ሥጋ በእግዚአብሔር መሃላ "መበስበስን እንዳያይ" (ሐዋርያት ሥራ 2፥ 30-31) ተደርጓል። ነገርግን የክርስቶስ ትንሣኤ አካላዊና ተዳሳሽ እስከሆነ ድረስ የእኛስ እንደዚያው አይሆንምን? ብሎ ለሚጠይቅ፣ መልሳችን ፈጽሞ አይሆንም! የሚል ነው። የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ እርሱ የሰጣቸውን ተስፋ እንደፈጸመው ያውቁና የትንሣኤው ምስክሮች ይሆኑ ዘንድ ለሐዋርያቱ ምልክት እንዲሆናቸው እንጂ ሞቶ የበሰበሰው አፈር፣ በእሳት የተቃጠለው አመድ፣ በጎርፍ የተወሰደው ብስባሽ፣ አውሬ የበላው ግዳይ፣ በአደጋ ምክንያት ተቆራርጦ እዚህና እዚያ የተበታተነው ቁርጥራጭ፣ ቀባሪ ያጣው ጥንብና የአሞራ ሲሳይ ሁሉ ተሰብስቦ እንደገና እንደሚመጣ የምናስብበት አይደለም። የኢየሱስ የሥጋው ትንሣኤ ለደቀመዛሙርቱ በልዩነት የነፍሱን ትንሣኤ ያረጋግጥላቸዋል። ዳዊት የተናገረውን ትንቢት ስሙ ፦
መዝ 16፥ 10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። 
ጴጥሮስም ዳዊት ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ሲናገር አስቀድሞ ማየቱን ሲሰብክ፦
ሐዋ 2፥ 31  ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ።
እነዚህ ጥቅሶች መንፈሳዊውን ሞት ስለሚያመለክተው በሃደስ ስላለች ነፍስ እና አካላዊውን ሞት ስለሚያመለክተው የሥጋ መበስበስ የሚናገሩ ናቸው። ኢየሱስ ከሁለቱም አይነት ሞት ተነስቶአል። የኢየሱስ ሥጋ ከሞት የተነሳ ካልሆነ የእርሱ ነፍስ በሲኦል እንደነበረችና ከዚያ እንደተነሳች ደቀመዛሙርቱ ዋስትናና ማረጋገጫ አይኖራቸውም። 
የክርስቶስ አካላዊው ትንሣኤ ክርስቶስንና ድል መንሳቱን በተመለከተ ከእርሱ ጋር አብሮ የተቆራኘውን መንፈሳዊውን ትንሣኤ ለደቀመዛሙርቱ ለማረጋገጥ የግድ  አስፈላጊ ነበር። ኢየሱስ መቃብርንና ሲኦልን ድል መንሳቱ እኛን ከዘላለም ሞት ለመቤዠት የሰጠውን ተስፋ የሚታመንና እርግጠኛ ያደርገዋል። ከእርሱ ሞትና ትንሣኤ ውጭ በማይታየው መንፈሳዊ አለም በእርሱ ህልዎት ፊት በማይሞት አካል ለዘላለም ሕይወት ለመኖር ምንም አይነት እንጥፍጣፊ ተስፋ አይኖረንም። በሥጋ ከሞትን በኋላ በዚህ ፕላኔት ላይ የምድርን አየር እየተነፈስን እና የምድርን ምግብ እየተመገብን በምድር ሥርዓት የምንኖር እስካልሆነ ድረስ የእኛ ሥጋ አካላዊ ትንሣኤ ምንም ትርጉም የለውም። በእግዚአብሔር ቃል ተስፋ ያልተሰጠ "የሥጋ" ትንሣኤ መጠባበቅ ዝናብ የሌለበትን ደመና እንደመከተል ነው። 

7. የአማኙ ሥጋ
አማኙ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ እንዲሆን በተቀደሰው መዋቲ ሥጋው ላይ ኃላፊነት እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል ያስተምራል።
1ቆሮ 6፥ 12 -20 "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል። ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።"
መዋቲው የተዋረደው የክርስቲያን ሥጋ (ከ70 አ.ም ጀምሮ)፣ በውስጡ ካለው የማይሞት መንፈስ የተነሳ እና የክርስቶስ (እና የክርስቶስ ብቻ) ከሆነውና ከተለወጠው ደግሞም ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ከበረው ሥጋው የተነሳ ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን የሚያሳይ መገለጫን ለብሶአል። ይህ ማለት ክርስቲያን ኃጢአት እንዳይነግስበት በተገባው የሚሞት ሥጋው በእግዚአብሔር የጸጋ አሰራር አለመሞት ተሰውሮበታል። ይህ አለመሞት እርሱም መለወጡ ለጳውሎስና ለቆሮንቶስ ምዕመናን መቼና እንዴት እንደሚሆን በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 51-52 የተገለጠውን ማየት ይገባል፤ ጳውሎስ የሚናገረውን ስሙ፦ "ሁላችን አናንቀላፋም" ወይም አንሞትም፣ "ነገር ግን ሁላችን (የብሉይ ኪዳን ቅዱሳንን ጨምሮ) እንለወጣለን" ምን እየተናገረ እንደሆነ ታያላችሁ? ይህ ማለት አንዳንዶች ገና በሕይወት እያሉ ይለወጣሉ ማለት ነው። ጳውሎስ እየጻፈለት ያለው ይህ አይነቱ መለወጥ ተዳሳሽ ከሆነው ባዮሎጂካል አካላቸው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር ሳይኖረው እንዴት ሊሆን ይችላል?  ይህ እንግዲህ ጊዜን አመልካች ከሆኑትና በማቴዎስ 16፥ 28፤ 24፥ 34 ወዘተ ከመሳሰሉት ምንባባት ጋር ተስማሚ ነው። የሚለውን ስሙ፣ ይህ ለውጥ፣ ይህ መንፈሳዊ ክስተት ተፈጻሚ የሚሆነው "የኋለኛው መለከት" ሲነፋ ነው። ስለዚህ የዚህ "የኋለኛው መለከት" ጊዜ የተወሰነና የተመደበ ነው፤ እርሱም የዳግመኛ ምጽአቱ ፖሮውዥያ መለከት ነው፤ ስለሰባተኛው መለከት በራዕይ 11፥ ቁጥር 15 ጀምሮ ምን እንደተባለ ተመልከቱ።
" ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም፦ የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ፦ ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ። በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።"
አሁን በዚህ ፍጥረታዊ አካላችን ላይ ለሥጋችን ያለብንን ኃላፊነት ባጭሩ እንመልከት፤ "ሁሉ ተፈቅዶልኛል" በሚል ማመካኛ አርነታችንን በመጠቀም ሁሉን እንዳናግበሰብስ፣ ከአንድም ነገር በታች ለመገዛት ራሳችንን እንዳንሸጥ፣ ይልቁንም የክርስቶስ ብልቶች የሆነው ሥጋችን ንብረትነቱ የጌታ ነውና ሞቶ እስኪቀበር ድረስ ከጋለሞታ ጋር እንዳይተባበር፣ ከዝሙት እንዲሸሽ፣ በንጽህና እንዲጠበቅ፣ እንዳናረክሰው፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያም ነውና እግዚአብሔርን እንድናከብርበት ኃላፊነት አለብን። "እኛንም (ጳውሎስና የቆሮንቶስ ምዕመናን) በኃይሉ ያስነሳናል" ማለቱ ግን ስለሙታን ትንሳኤ ነው እንጂ ስለሥጋ ትንሳኤ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ይህም በ70 አ.ም በምጽአቱ መለከት በፓሮውዥያው ተፈጽሞአል።
ከ70 አ.ም በኋላ ባለው የመንግስት ዘመን የኃጢአታችንን ሥርየት አግኝተን ለዘላለም ሕይወት ዳግመኛ ልደትን የተቀበልን አማኞች በምንሞትበትበትና ከዚህ ሥጋ በምንለይበት ቅጽበት፣ ያኔውኑ የማይሞተውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ መንፈሳዊውን፣ ሰማያዊውን አካል ተቀብለን ከክርስቶስ ጋር በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ዘላለምን ማሳለፍ እንቀጥላለን። አሁን በዳግመኛ ልደት ያገኘነው አዲሱ ሕይወት፣ እርሱም ከጌታ ጋር የተባበረው አንዱ መንፈስ ለጊዜው ነዋሪነቱ በዚህ የተዋረደ ሥጋ ውስጥ ነው። ይህ ሕይወት ግን ከዚህ ምዋቲ ሥጋ ስንላቀቅ በማይሞተው በአዲሱ አካል የሚቀጥል ሕይወት ነው፤ አለመሞትም ይኸው ነው። ሥጋና ደም የሆነው የቀደመው አካላችን ይረግፋል፣ ወደአፈርና ብስባሽ ይመለሳል፣ ከዚያም ፈጽሞ አይኖርም አይታይምም። ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ያመኑ የእግዚአብሔር ምርጦች ብቻ፣ የማይሞቱ የጻድቃን መንፈሶች ናቸውና፣ እያንዳንዳቸው በሚሞቱበት ቀን ድል ነስተው ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ይገባሉ (ራዕይ 21፥ 27)። እነርሱ ብቻ አለመሞትን አግኝተዋል።  ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ ሥጋ በለበሰው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ግን በብቸኝነት መበስበስን እንዳያይ ተስፋ የተገባለት የክርስቶስ ሥጋ ብቻ ከመሆኑ የተነሳ፣ የእርሱ የከበረ ሥጋ ብቻ ሳይለወጥ ከማንኛውም ብልሽት ነጻ የሆነ ሆኖ ይኖራል። "የእኔስ ሥጋ?" ብላችሁ በቅናትም ይሁን በፉክክር አትጠይቁ፤ ለፊተኛው ሰው አፈር ሆኖ ከአፈር የተሰራው ወደ አፈር መመለሱ የተመደበለት ዕድሉ ነው፤ ልኩም ያው ነው። ይህ ደግሞ የተፈለገውን ያህል ቲዎሎጃይዝ ሊደረግ ቢሞከር ይበሰብሳል እንጂ አንዲት ጋት ያህል እንኳ አይለወጥም። መበስበስን እንዳያይ ሆኖ በከበረው አካል በሰማይ እንዲኖር የተገባው የክርስቶስ ሥጋ ብቻ ነው። "ሥጋዬ በተስፋ ያድራል" ሲል የዘመረው የንጉስ ዳዊት መቃብር እንኳ እስካሁን ድረስ አፈሩን ታቅፎ በኢየሩሳሌም አለ፤ ይህ ግን በእርሱ የተናገረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ መሲሁ ትንሳኤ አዘምሮት እንጂ ስለ ራሱ ብስብስ ሥጋ ዕጣ ፈንታ መናገሩ አይደለም። "ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም" እንደተባለ፣ አጽም የሌለበት መቃብር ግን የኢየሱስን ሥጋ ያኖሩበት ብቻ ነው።  

8. ከክርስቶስ ጋር አብሮነት
"ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች  ሆንዋል" እንደተባለ፣ ሥጋችን ከእርሱ ክቡር ሥጋ ጋር ህብረት በማድረጉ ከብሮአል እንጂ በራሱ የከበረ ሥጋ ወደ መሆን አልመጣም። አስቀድሜ እንዳነሳሁት፣ ቃል በቃል ለመግለጥ የክርስቶስ ሥጋ በራሱ  የከበረ ነው፤ መበስበስን እንዳያይ ቃል የተገባለት ብቸኛ ሥጋ፣ ይህ የክርስቶስ ሥጋ ብቻ ነው። የማንም ሰው ሥጋ ቢሆን የመጨረሻ መዳረሻው ወደ ምድር አፈር ይመለስ ዘንድ ነው። የክርስቶስ ሥጋ ግን በሦስተኛው ቀን ከመቃብር ወጥቶ በዕርገቱ ከብሮአል። "እነሆ ሥጋውን ያኖሩበት የእርሱ መቃብር ባዶ ነው"። በሥጋው የሞተውን እርሱን በትንሳኤው መንፈስ ሕያው አድርጎ ክቡር ሥጋውን ከመቃብር በማውጣት ታሪካዊ ትንሳኤው የአማኞችን መጻኢ ትንሳኤ እንደ በኩር መርቷል። ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ልንሞትና ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ከእርሱ ጋር ልንተባበር በእምነት እና በቅዱስ ጥምቀት የትንሳኤውን መንፈስ የተቀበልን እኛ ደግሞ ሥጋችን በጊዜአዊነት የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ለመሆን ከእርሱ ጋር በመተባበር ከእርሱ ጋር አብሮ የከበረ ሆኖአል። እኛ የከበርነው በአቋቋም (positional sense) ደረጃ ነው። ለምሳሌ፦
ሮሜ 6፥ 4  እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።
ተቀበርን የሚለው ቃል በግሪኩ sunthapto ነው። ቃል በቃል እኛ በአካል ተቀብረናልን? ከቶ አልተቀበርንም። ክርስቶስስ ተቀብሮ ነበርን? በእርግጥ ክርስቶስ ተቀብሮ ነበር። እኛ የተቀበርነው ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ብቻ ነው - ቀብሩ የእርሱ ቀብር ነበር፣ የእኛ ቀብር ግን በቅዱስ ጥምቀት ከእርሱ ጋር በትብብር (አብሮ) መቀበር ነው።
ይኸው ትብብር ራሱ ለፊልጵስዩስ 3፥ 21 ተጠቅሶ ሊያገለግል ይችላል፤ እርሱም (ክርስቶስ) ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ (የተዋረደው ሥጋችን) ክቡር ሥጋውን እንዲመስል (summorphon የእኛን ሳይሆን የእርሱን አይነት ለመሆን መተባበር፣ አብሮ መሰራት) የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል (metaschematizo - ከውስጥ ያልሆነ የውጫዊ አመስሎ ተግባርን የሚያሳይ መግለጫ) ።
ይህ summorphon የተሰኘ ቃል በሌላም ክፍል እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ደግሞ እንይ፦
ሮሜ 8፥ 29 ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ (summorphon) አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤
ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር በመጋጠማቸው ምክንያት እርሱን መስለዋል (summorphon ሆነዋል) - ማለትም፣ በእርሱ ምሳሌ አብረው ተሰርተዋል። ከ70 አ.ም ወዲህ በህይወት ለሚኖር አማኝ ለተቀበለው 'አምሳላዊ ልውጠት' (metaschematizo) ወይም ለአዲሱ ሁኔታ ሃላፊነት ያለበት  ከክርስቶስ ባህርይ ጋር ያለው ይህ አንድነትና ትብብር፣ ከክርስቶስ መልክ ጋር ያለው ይህ መመሳሰል (summorphon) ነው።
summorphon ከክርስቶስ ባህርይ ጋር መተባበርን እንጂ ከክርስቶስ ባህርይ ጋር  ትክክለኛ መመሳሰልን አያሳይም። ይህንን የስፍራ ትብብር (positional) በሮሜ 6 ላይ፦ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መቀበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መሰቀል፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳት፤ በኤፌሶን 2 ደግሞ፦ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ማግኘት፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳት፣ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው ስፍራ አብሮ መቀመጥ፤ በቆላስይስ 2 ላይም፦ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መቀበር፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሳት፣ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ማግኘት፣ በሚል ተብራርቶ እናየዋለን። ሁሉም የትብብር አገላለጽ ነው፣ የአማኙን ከክርስቶስ እውነታ ጋር ያለ የስፍራና የደረጃ (positional) አቋም የግድ ይላል። ክርስቶስ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ ተነስቶ፣ በህይወት በመኖር፣ በሰማያት ተቀምጦአል። አማኙ ደግሞ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ተሰቅሎ፣ አብሮ ሞቶ፣ አብሮ ተቀብሮ፣ አብሮ ተነስቶ፣ አብሮ በህይወት በመኖር፣ በሰማያት አብሮ ተቀምጦአል። በክርስቶስ ያለው እውነታው ነው፣ በአማኙ ያለው ደግሞ ከዚያ እውነታ ጋር መተባበር ነው።
እንግዲህ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለው አስፈላጊ ነገር መሰረታዊ ከሆነው ከክርስቶስ ባህርይ ጋር መተባበር ነው። የአማኙ 'አምሳላዊ ልውጠት' (metaschematizo)፣ አዲስን ሁናቴ መልበስ፣ አዲስ ፍጥረት ሆኖ እንደገና መሰራት፣ እንደገና መዋቀር  ሊኖር የሚችለው በዚያ መንገድና በእርሱ በኩል ብቻ ነው። 

ማጠቃለያ
ስለዚህ ጳውሎስ እያለ ያለው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ አማኞች ገና በተዳሳሹ አካል በስጋቸው ውስጥ እያሉ ይለወጣሉ፣ መንፈሳቸውም የማይሞት ይሆናል፣ ነው። ይህ ለውጥ ደግሞ የሚሆነው አማኞች ከክርስቶስ የከበረ አካል ጋር በመተባበራቸው ምክንያት ነው። በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 51 ላይ የተነገረለትም መለወጥ ይኸው ነው፦
1ቆሮ 15፥ 51-52 እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።
ለእርሱ የተመረጡትን ለመሰብሰብ መላእክቱን ከታላቅ መለከት ድምጽ ጋር ልኳቸዋል (ማቴዎስ 24፥ 31)፣ ይህም የጌታ ዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው ነው (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 16)፤ እነሆ የኋለኛው መለከት እርሱም ሰባተኛው መለከት ተነፍቷል (ራእይ 11፥ 15)፤ መንግስትም የጌታችን ሆኗል። ዘመኑም ተለውጧል። በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፍቷል። ትንሳኤም ልዋጤም ካሁን በፊት ሆኗል።
ይህ "ልዋጤ" እንዴት እንደሚሆን አሁን ጳውሎስ የሚናገረውን ተመልክተን እናብቃ፦
ፊል 3፥ 21 እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
"ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር"፥ ሲል ይናገራል። ይህ ልዋጤ በአማኞች ውስጥ የሚከናወነው ክርስቶስ ሁሉን ለራሱ በሚያስገዛበት አሠራርና ጊዜ ነው። ይህ አሠራር የእግዚአብሔር አሠራር ነው። ያ የሚሆነው መቼ ነው? 
1ቆሮ 15፥ 24-26 በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ 
አሠራሩና ሥራው የሚፈጸምበት ጊዜ አይተላለፉም፤ ነገር ሁሉ በጊዜው ውብ ሆኖ ተሰርቷል። በሞቱና በትንሳኤው ተሰርቶ የተመረቀው፣ ግርማን በሞላው የክርስቶስ ክቡር ኃይል በይፋ ተገልጦ በሙላት የተሰጠን አለመሞት የክርስቶስ የሁሉን ቻይነቱ አሰራር ነው። ይህም መንፈሳዊውን ሞት ደምስሶ አለመሞትን ያመጣበት አሰራር ይፋ የሆነው በዳግመኛ ምጽአቱ ነው። ከዚህ የተነሳ ምእመናን አሁን የማንሞት ሆነናል፣ በሚሞት ሥጋችን ውስጥ የማንሞት ሆነን እንኖራለን። በሥጋ ስንሞት ደግሞ፣ አስቀድሞ በዳግመኛ ልደት እንዳይሞት የተደረገው መንፈሳችን የማይሞተውን ሰማያዊ አካል ይለብስና ለዘላለም ከጌታ ጋር በሰማይ ይሆናል። ምክንያቱም ህይወትንና ህያውነትን ባመጣበት በክርስቶስ አምነን በቅዱስ ጥምቀት አለመሞትን ተቀብለናል።
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦

ለዚህ ጥናት እንደ ግብዓት ያገለገሉ የጽሁፍ ስራዎች ከሞላ ጎደል፦
Bromiley, Geoffrey W.; Theological Dictionary of the New Testament
Denton, T Everett; Pertinent Parousia Passages. Second coming Scripture Studies
Karl Rahner; Encycopedia of Theology. The Concise Sacramentum Mundi  
Meek, Charles S; Christian Hope through Fulfilled Prophecy. An Exposition of Evangelical Preterism
Martin, Brian L; Behind the Veil of Moses. Piecing Together The Mystery of the Second Coming
Nicholas, Michael Alan; preterism and the Afterlife. Plus Parousia, Resurrection,  Judgment, and The New Covenant Kingdom
Raphael, Simcha Paull; Jewish Views of the Afterlife
Spitz, Elie Kaplan (Rabbi); Does The Soul Suvive? A Jewish Journey to belief in Afterlife, past & Living withe purpose.
Stevens, Edward E; Final Decade Before the End. Jewish and Christian History Just Befotr the Jewish Revolt.
Terry, Milton S;  Biblical Apocalyptic.