Wednesday, January 6, 2021

የዘመኑ ፍጻሜ

"የዘመኑን ፍጻሜ" 


መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጨረሻው ዘመን ይነግረናል እንጂ ስለ ጊዜ ማብቂያ/ ፍጻሜ አይነግረንም። የመጨረሻው ዘመን ወይም የዘመኑ ፍጻሜ ሲለንም የአሮጌው ኪዳን የአይሁድ ዘመን ማብቂያ፣ የአንድ አሮጌ ስርዓት ፍጻሜ ማለቱ ነው እንጂ፣ የሰው ልጆች ታሪክ ማብቂያ፣ የጊዜ ማብቂያ ማለቱ አይደለም። የዘመኑ ፍጻሜ የሚለውም ጊዜ መቆጠር ሲያበቃ ማለት ፈጽሞ አይደለም።


"ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።" (ገላትያ 4፥ 4-7)


በዚያ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ወቅት፣ ማለትም ያኔ "የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ"፣ ገናም ሕጉ እየገዛና እነዚያ የአሮጌው ኪዳን ሕግጋት በስራ ላይ እያሉ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሴት ተወልዶ በስጋ መጣ። ያ ክርስቶስ "ከህግ በታች" ሆኖ በስጋ የመጣበት ታሪክ የሕጉ ዘመን ወደፍጻሜው መድረሱን የሚያሳይ አይነተኛ ምልክት ነበር። ክርስቶስ ከልደቱ በኋላ በሰላሳዎቹ ሦስት የመጀመሪያ አመታት ላይ በእስራኤል የነበሩትን አይሁድ አገለገለ። እነርሱም "ከእስራኤል ቤት የጠፉት በጎች" (ማቴዎስ 15፥ 24) ናቸው። ለእነርሱም ተስፋ የተገባው መሲሁ እርሱ መሆኑን እና ራሱም በስጋ የተገለጠ አምላክ መሆኑን በብዙ ማስረጃ በሞቱና በትንሳኤው አሳያቸው። ለአይሁድ ዘመን የተመደበው የዘመኑ ፍጻሜም መቅረቡንና መንግስቱም በደጅ መሆኑን አሳያቸው። (ማቴዎስ 24፥ 33)።


ክርስቶስ ከህግ በታች ተወልዶ በኑሮው፣ በህይወቱ፣ በመከራው በሞቱ፣ በመቃብሩ፣ በትንሳኤውና በእርገቱ ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ስርአተ ህጎች ፈጽሟል። ለአይሁድም መንፈሳዊ የሆነውን የአዲሱን ኪዳን የመንግስት ወንጌል በስብከቱ፣ በትምህርቱና በአገልግሎቱ፣ አስተዋውቋል። በእርሱ የቤዛነትና ዋጆአዊ ስራ ተመርቆ የተገለጠው አዲሱ ኪዳንም የእርሱ የሆኑ ህዝቦቹ በክርስቶስ ባላቸው እምነት በኩል ለእግዚአብሔር እንደ ልጆች፣ ደግሞም በልጁ መንፈስ እንደ ሕጋዊ ወራሽ ሆነው ተለይተው የሚታወቁበት ኪዳን ነው። ዘመኑ ስለተፈጸመ ይልቁንም ከእንግዲህ ወዲህ የእግዚአብሔር  ሕዝቡ ሁሉ በልባቸው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ የተወደዱ ነጻ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው እንጂ፣ ፈጽሞ የሕግ ባሪያዎች አይደሉም። መንፈስ ቅዱስም በአማኞች ላይ የመሆኑ እና በልባቸው የማደሩ ታሪካዊ ኩነት የበአለ ሃምሳው ክስተት ሲሆን፣ እርሱም እንደነብያቱ ትንቢት እግዚአብሔር በህዝቡ ላይ ያፈሰሰው የመጨረሻው ዘመን ስጦታ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም በዘመኑ ፍጻሜ ያለውን የመለኮት ምክር ሲገልጠው:-


"በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።" (ኤፌሶን 1፥ 10) ይላል።


እንግዲህ የዘመኑ ፍጻሜ ማለት እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ትምህርት ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ የሚሆን ከሆነ፣ ይህ ሁሉን በክርስቶስ የመጠቅለል የመለኮት አሳብ ያኔ ዘመኑ ሲያበቃ ተፈጽሟል ብለን ለማመን መግፍኤውን ያገኘነው ብቻውን የእግዚአብሔር ምስክር ከሆነውና ከማይሻረው ቃሉ እንጂ እድሜ ጠገብ ከሆነውና ከሚሻረው የሰው ትምህርት አይደለም። ይህም በእግዚአብሔር ቃል እና በቅዱሳት ሚስጥራት አገልግሎት ብቻ የሚታወቀው መንፈሳዊ መንግስት ለተመረጡትና ዳግም ለተወለዱ ሁሉ የእግዚአብሔርን ጸጋ እና ምህረት ያቀርብላቸዋል። 


ይህም መንግስት ያመኑ አይሁድ እና ያመኑ አህዛብ ለሆኑ ለገዛ ሕዝቡ የተሰጠ አዲስ ኪዳን ነው። እኒህ አማንያን ክርስቶስ በስጋ ከተገለጠበት ዘመን አንስቶ ዳግመኛ በፍርድ እስከተገለጠበት ፓሮዥያው ድረስ ባለው የሽግግር ወቅት በእርግጥም ኃጢአታቸው የተሰረየላቸውና የታረቁ፣ ድነታቸውም በክርስቶስ ሞት ተመርቆ የተሰጣቸው ነበሩ፤ እነርሱም በእምነት በኩል በቅዱስ ጥምቀት የወንጌል ጸጋ  አሰራር ወደዚያ ተስፋ የገቡ ነበሩ። ዳሩ ግን በዚያው በመጀመርያው ክፍለዘመን፣ በ70 አ.ም በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ መዳናቸው ፍጻሜውን ያገኘና ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ፣ ገናም በይፋ የተገለጠ አልነበረም። ምክንያቱም ዘመናቸው ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን የሚደረግ የሽግግር ወቅት ነበርና ነው።


ይህም የሽግግር ወቅት "The already but not yet" የሚባለው ወቅት ነው፤ (The already but not yet ማለትም “ቀድሞውኑ ሆኗል ግን እስካሁን ድረስ ገና አላለቀም” እንደማለት ነው። የዚህ አባባል  ሥነ-መለኮታዊ ፅንሰ-ሀሳብ አማኞች በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ አሁን በንቃት ተካፋይ መሆናቸው እርግጥ ነው፣ ይሁንና ግን ለወደፊቱ እስከሚደረስበት የተወሰነ አንድ የተራዘመ ወቅት ወይም ቀን ድረስ የመንግስቱ ሙሉ መገለጫው ላይ ገና አልተደረሰም እንደ ማለት ነው፤ በዚህም አስተሳሰብ እኛ “ቀድሞውኑ” /already/ በመንግሥቱ ውስጥ ሆነናል ፣ ግን “ገና” /not yet/ በክብሩ ሙላት ውስጥ ተጠቃለን አልገባንም፤ ወይም "ገብተናል ግን ሙሉ በሙሉ አልገባንም፣ ገና የሚቀር ነገር አለ" የሚል ትምህርት ነው፡፡) ይህ ወቅት እና ጽንሰአሳቡ እውነትና ትክክል ሊሆን የሚችለው ባልተራዘመው የሽግግር ወቅት ብቻ የሚታሰብ ከሆነ ነው። ይህም ያልተራዘመው የሽግግር ወቅት ከአሮጌው ኪዳን ወደአዲሱ ኪዳን የተደረገውን የመጀመርያውን ክፍለ ዘመን ሽግግር የሚያመለክት ነው እንጂ ለ2000 አመታትና ገናም ከዚያ በላይ ላልታወቀ ዘመን የተራዘመ ሽግግር ውስጥ እንዳለን አድርጎ የሚቆጥረውን ወቅት የሚያመለክት ፈጽሞ አይደለም። 


በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበሩ አማኞች በዚያ የሽግግር ወቅት ሲኖሩ "ዘመኑ አጭር ሆኗል"፣ እኛም "የዘመኑ ፍጻሜ የደረሰብን" ነን እያሉ በምጥ ኖረዋል።  በዚህ የሽግግር ወቅት መዳናቸውን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እየፈጸሙ፣ ወንድሞቻቸው ከሆኑ ከአይሁድ የክርስቶስ ጠላቶች እና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከነበረው የአህዛብ አለም የሚደርስባቸውን ብዙ መከራና ስደት መታገስና በውስጡ ማለፍ ነበረባቸው። የሽግግሩ ወቅት አብቅቶ ዘመኑ ሲፈጸም ግን ያኔ በ70 አ.ም በኢየሩሳሌም ውድመት እና በቤተ መቅደሱ መፈራረስ፣ የዚያ የአሮጌው ዘመን ልምምድ የሆነውን ያንን የአይሁድ ኃይማኖታዊ ስርአት እርሱም "አሮጌውን ሰማይ እና አሮጌውን ምድር" ስፍራ እስከማይገኝለት ድረስ በእሳት ፍርድ አሳልፎ ለዘላለምም እንዳይታሰብ ደመሰሰው 


አሮጌው ሰማይና ምድር ተወግደዋል ሲባል ይህ ተዳሳሹ ዩኒቨርስና ፕላኔቱ ተቃጥለው አልፈዋል እንደምንል የሚያስብ ተላላ አንባቢና ተርጓሚ ሞልቷል። ጉዳዩ ግን እንደዚያ አይደለም። ይህ ፍጥረታዊና ተዳሳሽ አለም እንደሚጠፋ የሚናገር አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ማቅረብ በማይቻልበት ሁኔታ የሰው ትምህርት ተከትሎ የሌለ ነገር እያመኑና እያስተማሩ ምዕመናንን ግራ እንደማጋባት ያለ አለመማር አይታየኝም። እነሆ ዘመኑ ከተፈጸመ ግን 2000 አመታት አልፎታል፣ አሁን በተፈጸመ ተስፋ ውስጥ በክብሩ ሙላት ዘላለማችንን እንኖረዋለን እንጂ፣ The already but not yet እሚባለው የሽግግር ወቅት ካለፈ ቆይቷል። ከዚህ በኋላ የማያልፍና የማያልቅ ዘላለም እንጂ የሚፈጸም ዘመንም ሆነ የሚጠቀለልና የሚያልፍ ተዳሳሽ አለም የለም። እኛም በዳግመኛ ምጽአቱ በማያልፍ መንግስት እንኖራለን። እነሆ ክርስትና በክርስቶስ ደም የተመረቀው አዲሱ የጸጋ ኪዳን፣ የእግዚአብሔር እና የክርስቶስ መንግስት፣ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት በይፋ ታውጆ በጽድቅ ተመስርቷል። ከተማይቱም ቤተክርስትያን አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በክብሩ ተሞልታ በእምነትና በንስሃ  የሚገቡባትን ሁሉ ልትቀበል በሮቿ ተከፍተው ይኖራሉ፤ ለዘላለምም አይዘጉም። አሁን ዘመኑ የጌታችን የክርስቶስ ነው። እርሱም መንግስቱ የጸናች ንጉሰ ነገስት ኢየሱስ ነው፣ በአባቱም ዙፋን ላይ ለዘላለም ነግሷል፣ ጠላቶቹንም ከእግሩ በታች አድርጎ ሁሉን ይገዛል። ሃሌ ሉያ! 

gkr.

No comments:

Post a Comment