ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ የንባብ ክፍሎች ለፕሪቴሪዝም
የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሱስ በእነርሱ የህይወት ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የነበራቸው መጠባበቅና፣ ይህንን አይነት መጠባበቅ እንዴት ሊኖራቸው እንደቻለ፣ ከየትስ እንዳገኙት፤ ማንንም ቢሆን፣ ከሃዲውንም ሆነ አማንያኑን ሁልጊዜ ሲያስገርም የሚኖር ጉዳይ ነው። በእኔ ግምጋሜ ይህ የዳግመኛ ምጽአቱ ተስፋ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች በልዩነት የተሰጠ መሆኑን ማየት የቻሉት በአመዛኙ ከአማንያኑ ይልቅ ከሃድያኑ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ይህም የከሃድያኑ እይታ ትንቢቱ በተያዘለት የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ ያልተፈጸመ መሆኑን በማራገብ ክርስትናችንን ውሸት ለማድረግ በአማንያኑ ላይ የሚሰነዘር ብርቱ የማጥቂያ መሳርያ ሆኗቸዋል። አማንያኑም ቢሆኑ ይህንን ጥቃት የሚመክቱበትንና በከሃድያኑ ትችት ፊት በጽናት ቆመው እምነታቸውን የሚከላከሉበትን አቅም ከዚያው እድሜ ጠገብ ከሆነው ልማዳዊ አመለካከታቸው ስለሚፈልጉት ሊቋቋሙት አልቻሉም። በአመለካከታችን የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ ሙጭጭ ባልን ቁጥር ክፉኛ የሚያገኘን የከሃድያኑ በትር ነው።
የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ኢየሱስ በእነርሱ የህይወት ዘመን ተመልሶ እንደሚመጣ የነበራቸው መጠባበቅና፣ ይህንን አይነት መጠባበቅ እንዴት ሊኖራቸው እንደቻለ፣ ከየትስ እንዳገኙት፤ ማንንም ቢሆን፣ ከሃዲውንም ሆነ አማንያኑን ሁልጊዜ ሲያስገርም የሚኖር ጉዳይ ነው። በእኔ ግምጋሜ ይህ የዳግመኛ ምጽአቱ ተስፋ ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች በልዩነት የተሰጠ መሆኑን ማየት የቻሉት በአመዛኙ ከአማንያኑ ይልቅ ከሃድያኑ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ይህም የከሃድያኑ እይታ ትንቢቱ በተያዘለት የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ ያልተፈጸመ መሆኑን በማራገብ ክርስትናችንን ውሸት ለማድረግ በአማንያኑ ላይ የሚሰነዘር ብርቱ የማጥቂያ መሳርያ ሆኗቸዋል። አማንያኑም ቢሆኑ ይህንን ጥቃት የሚመክቱበትንና በከሃድያኑ ትችት ፊት በጽናት ቆመው እምነታቸውን የሚከላከሉበትን አቅም ከዚያው እድሜ ጠገብ ከሆነው ልማዳዊ አመለካከታቸው ስለሚፈልጉት ሊቋቋሙት አልቻሉም። በአመለካከታችን የመጻኢነትን ነገረ ፍጻሜ ሙጭጭ ባልን ቁጥር ክፉኛ የሚያገኘን የከሃድያኑ በትር ነው።
መፍትሄው ግን ያ ለጥንት ቤተክርስቲያን ሰዎች ክርስቶስ በገዛ ትውልዳቸው ተመልሶ እንደሚመጣ በቃል የተነገራቸውም ሆነ በመልእክት የተጻፈላቸው ቃል በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ንግግርና ጽሁፍ የሆነውን ያህል፤ እንዲሁ እነዚያው የጥንት ክርስቲያኖች የጌታን ቀን ይናፍቁና ይጠባበቁ የነበረበት ያ ተስፋ፣ እምነትና ናፍቆት በመንፈስ ቅዱስ የተመራ እንደነበር አውቀን፣ ተስፋውም ለእነርሱ የተሰጠና የተፈጸመ መሆኑን መቀበል ብቻ ነው። ለእምነት ቤተሰብ ይህንን ለመቀበል ምንም ውጫዊ ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልገን (ደርዘን ውጫዊ ማስረጃ ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም) በቅዱስ ቃሉ ብቻ መሞገት እንችላለን።
ክርስቶስ ተመልሶ የሚመጣው "መቼ" እንደሆነ ክርስቶስ ራሱና ሐዋርያቱ ተናግረው ነበር ወይ? አዎን በግልጽ ተናግረው ነበር። ይህም በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ በጻፉትና ባስተማሩት ሁሉ ውስጥ በግልጽ የሚገኝ "ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ የንባብ ክፍሎች" በምንላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ በግልጽ የሚታይ እውነት ነው። ታዲያ መቼ ነው ተመልሶ ይመጣል ያሉት? ከዚህ ቀጥሎ ከብዙ በጥቂቱ በማቀርባቸው በእነዚህ ዝርዝር ምንባባት ውስጥ የተገለጠውንና በጣም በቅርብ እንደሚሆን የነበረውን ስሜት ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፦
ማቴ 10፥ 23 "በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።"
ማቴ 16፥ 27፣28 "የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።"
ማቴ 24፥ 34 " እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።"
ያዕ 5፥ 8 " እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።"
1ጴጥ 4፥ 7 "ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥"
ራእይ 1፥ 1-3 "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።"
ራእይ 22፥ 6-7 "እርሱም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ።"
ራእይ 22፥ 10 "ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።"
ራእይ 22፥ 12 "እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።"
ራእይ 22፥ 20 "ይህን የሚመሰክር፦ አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና"
በግሌ እነዚህ ምንባባት ያላቸውን ትርጉምና የያዙትን መልእክት ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን አውድ ነጥሎ በመረዳት ጌታን ኢየሱስን በቃሉ የማይታመን አድርጎ በማየት ፈተና ውስጥ መውደቅ አልፈልግም። ስለዚህ እንዲህ ስል አጥብቄ እጠይቃለሁ፣በዚያው ትውልድ ውስጥ ለመመለስ የሰጠውን የተስፋ ቃል ኢየሱስ ጠብቋል ወይ? ቃሉንስ አላጠፈምን? ሐዋርያቱስ ቢሆኑ በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ክርስቶስ በራሳቸው የሕይወት ዘመን በቅርቡ ተመልሶ እንደሚመጣ ሲናገሩ የነበረው ንግግራቸው ትክክል ነበር ወይ? አልተሳሳቱም ነበርን? እነዚህና መሰል ጥቅሶች ሁልጊዜም ቢሆን ተጠራጣሪ የሆኑና ማገናዘብ የሚጎድላቸውን "የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች" የሚረብሹና ምቾት የማይሰጡአቸው ናቸው፤ የሥነ መለኮት "አዋቂዎች" ለሚባሉ የለዘብተኝነትን አቋም ለያዙ ሊቃውንት ነን ባዮች ደግሞ የብዙዎችን እምነት ለመገልበጥ ይጠቀሙባቸዋል። ክርስትናችንን ለሚሳደቡ ከሃድያንም "እነዚህ ምንባባት ይፈጸማሉ በተባሉበትና እንዲፈጸሙ በተነገረላቸው የጊዜ ወሰን (በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ወቅት) አልተፈጸሙም፣ ስለዚህ ኢየሱስም ሆነ የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን በትንቢታቸው ወድቀዋል፣ በመሆኑም ቃሎቻቸውን በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡና ስህተት የሌለባቸው ናቸው ለማለት አንችልም" ሲሉ የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነተኛነት ለመንቀፍና ስህተት የለባቸውም ስንል የምናምነውን የእኛን እምነት ለማጥቃትና ለመተቸት ይጠቀሙባቸዋል።
የፕሪቴሪዝም ትርጉምና አመለካከት ግን በዚህ ሁሉ ነቀፋና ትችት ፊት በጽናት ቆሞ፣ ይህንን ለመቃወምና አቋሙን ለማስረዳት የቅዱሳት መጻህፍትን አስተምህሮ ብቻ ጠቅሶ የሚያቀርበው ሙግትና ማብራርያ፣ መጻእያን ከሚያቀርቡት ከየትኛውም እርስ በርሱ የተሳከረ የትርጉም መንገድ ይልቅ ጌታ ኢየሱስን እግዚአብሄር በወንድሞቹ መካከል ቀብቶ እንዳስነሳው ነብይና እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያከብረው ነው፤ የቅዱሳት መጻህፍትንም ተአማኒነት የሚያረጋግጥ፣ ቅዱሳት መጻህፍትም ለተሰጡበት አውድ ታማኝ ሆኖ የትርጉም ቀዋሚነትን (consistency) የሚጠብቅ እንደሆነ አይኑን ያልጨፈነ ሁሉ ሊያረጋግጠው ይችላል።
ለምሳሌ፣ ከትውልድ ሃገሬ ርቄ ባለሁበት አገር ቤት ላሉ ለሚወዱኝና ሊያዩኝ ለሚናፍቁ ወዳጅ ዘመዶቼ፣ "ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፣ በቅርቡ ወደ አገሬ እመለሳለሁ" ብዬ ቃል ብገባ፣ ቃሌ እውነተኛና ታማኝ ሊሆን የሚችለው እኔም ሆንኩ ወዳጅ ዘመዶች በህይወት እያለን የሰጠሁትን ተስፋ የፈጸምሁ እንደሆን ብቻ ነው። ለኢየሱስም እንደዚያው ነው፣ ተስፋ የሰጣቸው ሰዎች ካለፉ በኋላም ገና እስካሁን ካልመጣና ገና አሁንም ብዙ ዘመን ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ከሆነ "እነሆ በቶሎ እመጣለሁ" ብሎ እንዲጠብቁት መንገሩ ትርጉም የሌለው ከመሆኑም ባሻገር፣ ተስፋውን ለመፈጸም በሰጠው ጊዜ ባለመፈጸሙ ኃሰተኛ ያደርገዋል።
እነዚህ ጥቅሶች የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ከኢየሩሳሌም ውድቀት፣ ከቤተ መቅደሱ ውድመት፣ እንዲሁም በ70 አ.ም ላይ ከሆነው የአይሁድ ህዝብ እልቂትና የብሉይ ኪዳን የመስዋዕቱ ስርዓት ፍጻሜ ጋር ባለው ግንኙነት አንጻር የሚናገሩና የሚያስተምሩ ናቸው። እነዚያ የቤዛነት ትእይንት የመጨረሻ ኹነቶች ልክ እርሱ ይሆናሉ ሲል እንደተናገረው ተፈጽመው አልፈዋል እንጂ ገና ወደፊት የሚፈጸም፣ ሳይፈጸም የቀረና የዘገየ ተስፋ የለባቸውም። ስለዚህ ጊዜን አመልካች የሆነውን የትንቢቶቹን አቀራረብ ቸል ብሎ፣ "ትንቢቱ ገና ወደ ፊት ይፈጸማል እንጂ እስከ አሁን ገና አልተፈጸመም" ሲል፣ ሳይፈጸም እንደቀረ ወይም እንደዘገየ የሚያስተምረውን እድሜ ዘልዛላ አመለካከት ለማብራራትም ሆነ ለመተንተን መሞከር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ ጊዜው ያለፈበትና ምንም አስፈላጊነት የሌለው ነው። ስለዚህም ነው፣ "ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች የተነገረውንና "እነሆ በቶሎ ይመጣል" የሚለውን ይህንን በግልጽ አማርኛ የተነገረ ቃል እያነበብን፣ አሁንም ለእኛ የተባለ ያህል ቆጥረን ምጽአትን ገና የምንጠብቅ ከሆነ፣ በእውነት አስቀድሞ የሚያስፈልገን የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይመስለኝም።" ስል የምናገረው። በመጽሐፍ ቅዱስ ካልተግባባን ደግሞ ቢያንስ በአማርኛ የቋንቋ አገባብ እንግባባ ይሆናል ብዬ አስቤ ነው እንጂ የቃሉ ቡጢ ያነገለውን ቃሉ ራሱ ካልፈወሰው በቀር መዝገበ ቃላት ይፈውሰዋል ብዬ አይደለም።
ይህንን ልብ አንቀጥቅጥ የሆነ እውነት አንብባችሁ የኖረውን እድሜ ዘልዛላ አመለካከት ልትሞግቱ ከፈለጋችሁና ሙሉውን የጽሁፉን ይዘት ማየት ከወደዳችሁ እነሆ ሊንኩ፣
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/blog-post.html