Sunday, September 22, 2019

አጠቃላዩ ትንሣኤ

አጠቃላይ ትንሳኤ

መግቢያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቃንና አመጸኞች ከሙታን የሚነሱ እንደሆነ ማስተማሩ እሙን ነው፣ በአማኞችም ሁሉ ዘንድ የታወቀና ግልጽ ነው። ይኸውም "አጠቃላይ ትንሳኤ" የምንለው ሲሆን፣ "እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ።" (ሐዋ 24፥ 15) ተብሎ እንደተጻፈ፤ ትንሳኤ በአጠቃላይ ጻድቃንንና ዓመፀኞችን የሚያካትት መሆኑ፣ በአይሁድ ይጠበቅ የነበረና የጥንት ቤተክርስቲያንም ተስፋ ሆኖ የኖረ እምነት መሆኑ እርግጥ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ አጠቃላይ ትንሳኤ ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት ደግሞ በቀኑ መጨረሻ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ መሆኑ በሚበዙት ዘንድ ተቀባይነት አለው። እኔ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ የሚያውቀው የቀኑ መጨረሻ፣ ደግሞም ጌታ እንደተስፋ ቃሉ ተመልሶ የመጣው፣ በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ነው ብዬ ለማመን በቅዱስ ቃሉ ስለምገደድ፣ የዚህን አጠቃላይ ትንሳኤ መፈጸም ጊዜውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ነጥዬ ልረዳ አይሆንልኝም።

የትንሳኤ ተስፋ ተሰጥቶ የነበረው ለአሮጌው ኪዳን እስራኤላውያን ነበር። ሰለዚህ የትንሳኤ ተስፋ የብሉይ ኪዳን ተስፋ ነበር፣ እንጂ፣ ብሉይ ኪዳን የማያውቀውና በአዲስ ኪዳን የተሰጠ አንድ አዲስ ነገር አልነበረም። ለቤተክርስቲያን የተሰጠ አዲስና እንግዳ ተስፋ አልነበረም። ርዕሰ ጉዳዩን አጥርቶ ለመረዳት ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

አጽንዖት ሰጥቼ ልድገመው፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ የሙታን ትንሳኤ የሚፈጸመው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው፤ ተስፋውም ለእስራኤል የተሰጠ እስከሆነ ድረስ፣ መፈጸምም ያለበት በእስራኤል ዘመን መጨረሻ ላይ ነው እንጂ፣ "በአለም ፍጻሜ" ይኸውም በሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ ወይም በጊዜ መጨረሻ ላይ አይደለም። ምክንያቱም የታሪክ መጨረሻ ወይም የሰው ልጆች ታሪክ መጨረሻ እና የጊዜ ማብቂያ የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብ የሰው ልብ ወለድ ትምህርት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ገጹ ላይ እውቅና የነፈገው ርእሰ ጉዳይ ነው። ይህንን ያፈጠጠ የነገረ ፍጻሜ እውነት መቀበል ከሚቸገር ሰው ጋር ከመነሻው ስለማንግባባ ትምህርተ ትንሳኤያችንንም ማስታረቅ አይቻልም።  መጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ ግን የ70 አ.ም ነገረ ፍጻሜ ሲሆን፣ እርሱም የእስራኤል ነገረ ፍጻሜ ነው እንጂ የዚህ ግዑዝ አለም፣ የሰማይና የምድር ፍጻሜ አይደለም። ለእስራኤል የተሰጠው የነገረ ፍጻሜ ተስፋ የሚፈጸመው ደግሞ በእስራኤል ዘመን መጨረሻ ከሆነ ይህም መጨረሻ ነብያቱ፣ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ እንዳስተማሩት ቤተመቅደሱ የወደመበት  የ70ው አ.ም የእስራኤል ፍርድ የተፈጸመበት መጨረሻ ነው። ስለሆነም ትንሳኤ የሆነው ያኔ ነው። በአስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ የዘመኑን ፍጻሜ፣ የጌታን ዳግም ምጽአት፣ ትንሳኤንና ፍርድን የምናየው በዚያው በእስራኤል ዘመን ማብቂያ ውስጥ ነው።

ለሙታን ትንሳኤ በተቀጠረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጊዜ ላይ የጠራ አመለካከትን የያዘ ሰው በትንሳኤ ተፈጥሮና ባህርይ ላይ፣ ማለትም ሙታን በምን አይነት አካል ወይም ሁናቴ ትንሳኤን ይቀበላላሉ በሚለው ላይ ግራ አይጋባም፤ ጊዜው የትንሳኤን ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣልና።

ለትንሳኤ የተቀጠረውን ጊዜና የሙታን ትንሳኤ በአይነቱ ምን ባህርይ ወይም ተፈጥሮ እንዳለው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ በዚሁ ብሎገር ነገረ ፍጻሜን በጽሁፍ ሳስተምር በስፋት ያነሳሳሁት በመሆኑ በዚህችኛዋ ጽሁፌ እርሱን ብዙ አልሄድበትም። ምናልባትም ጌታ ቢፈቅድ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በጥልቀት ለማሰብ ሸክሙ ያላቸውን ተደራሽ የሚያደርግ ትምህርት ማቅረብን ወደፊት እቀጥላለሁ። ይሁንና ግን ይህንን የጻድቃንንና የአመጸኞችን ትንሳኤ አጠር ባለ መልኩ በወጉ ለመረዳት የሚያስችሉንን ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን በዚህ ጽሁፍ አንስተን እንድንካፈል እወዳለሁ። መልካም ምልከታ፦

1) ከሁሉ በፊት፦ 

ሁሉም ያለፉቱ፣ አሁን ያለነውና ገና ወደፊት የሚመጡቱ ሁሉም የእግዚአብሔር ህዝቦች ክርስቶስ በስጋው ወራት በመከራው አንድ ጊዜ በፈጸመው መስዋዕዊ የቤዛነት ስራው የተዋጁ መሆናቸው እሙን ነው። ለእነዚያ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ምእመናን መዳናቸው በመስቀሉ ደም ያኔ "ተመርቆ" (inaugurated ሆኖ) ነበር፤ ይሁንና ግን እርሱ በገዛ ደሙ ሊያስተሰርይላቸው ከገባባትና በሰማየ ሰማያት ካለችው ቅድስተ ቅዱሳን በ70 አ.ም በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ ተመልሶ እስኪወጣና እስኪታይ ድረስ፣ የህዝቡ ሁሉ ሙሉ መዳን ገና በሙላት ወደ "ፍጻሜ" ወይም ወደ "ሙላት" አልደረሰም፣ (consummated አልሆነም) ነበር። "እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (እብራውያን 9፥ 28)፣ ተብሏልና። በመስቀሉ ስራ እንደሚታረድ በግ የአለምን ኃጢአት ሊያስወግድ በራሱ ላይ የተሸከመው መስዋዕታችን እርሱ፣ እንደ ሊቀ ካህናቱ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገብቶ ካስተሰረየ በኋላ፣ ከቅድስት ወደ አውደ ምህረቱ ወጥቶ ሁለተኛ ጊዜ በሚሆነው መታየቱ ይኸውም በዳግመኛ ምጽዓቱ ይጠባበቁት የነበሩትን ካላዳናቸው በቀር የህዝቡ ድነት ሙሉእ እና ፍጹም አይሆንም። ይህም፣ የአሮጌው ኪዳን ሊቀ ካህናት ስለ ሕዝቡ ለማስተሰረይ ወደ ቅድስት ገብተው በሚወጡበት አምሳል የተፈጸመ ነው። በመስቀል የተፈጸመውን የሰው ልጆች ድነት ሙላት ሰጥቶ የሚጠቀልለውና ፍጹም የሚያደርገው በናፍቆትና በትእግስት ይጠበቅ የነበረው ዳግመኛ ምጽአቱ፣ እርሱም ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት መታየቱ እንደሆነ ይህን አንድ ነገር ከተስማማን፣ ዳግመኛ ምጽአቱ ወደፊት ይፈጸማል እንጂ ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት እስካሁን ድረስ ገና አልሆነም በምንልበት ጊዜ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ኢየሱስ ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ሆኖ ያልታየ በመሆኑ፣ ማንም ሰው ቢሆን መዳኑ ገና ጅምር እንጂ ሙላት አላገኘም ማለታችን ይሆናል።

2) ቀጥሎም፣ የፊተኛው ትንሳኤ፦ 

ዮሐንስ በራእዩ ሲመሰክር፣ "አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።" (ራእይ 6፥ 9) ይላል።

እነዚህ እዚህ ላይ የምናያቸው ነፍሳት የወንጌል ሰማእታት የሚባሉት ናቸው። ስለ መሲሁ በመመስከራቸው ምክንያት በግፍ የተገደሉ ሁሉ ናቸው። የብሉይ ኪዳን ሙታን የሆኑ ቅዱሳን ሰማእታትን በተመለከተም በክርስቶስ ትንሳኤ ጊዜ ህያዋን ሆነው ከመቃብር በመውጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ምስክርነታቸውን እንደሰጡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ሲዘግብ "መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤  ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።" (ማቴዎስ 27፥ 52-53) ሲል ይነግረናል።

ይህም ደግሞ ዮሐንስ በራእዩ፦ "ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።" (ራእይ 20፥ 4 እና 6) ሲል አይቶ፣ ከመሰከረው ጋር ይስማማል።

ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው፣ ስለ እነዚሁ ሰማዕታት ዮሐንስ ቀደም ሲል በራእዩ አምስተኛ ማህተም መፈታት ላይ ያየውን ሲመሰክር፦ "አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።" (ራእይ 6፥ 9-11) የሚለውን ስትመለከቱ ጉዳዩ ስለምን እንደሆነ ለማስተዋል አትቸገሩም።

በብሉይ ኪዳን ለመስዋእት የቀረበው እንስሳ ደሙ ከመሰዊያው እግር ስር እንደሚፈስስ ሁሉ (ዘሌዋውያን 4፥ 7)፣ እንዲሁ በአይሁድ ካህናትና በአለቆቻቸው ግፍ እንደ እንስሳ የታረዱት የቅዱሳን ሰማእታቱ ነፍሳት ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ "የስጋ ሁሉ ነፍስ [በእብራይስጡ nephesh] በደሙ ውስጥ ነው" (ዘሌዋውያን 17፥ 11) ብሎ እንደሚያስተምር፣ በዚህ ራእይ ውስጥ ከመሰዊያው በታች ሆነው ይታያሉ (ቁ9)። እንደ አቤል ደም ሁሉ የሰማእታቱም ደም ስለ ፍርድና ስለ መለኮታዊ በቀል ወደ እግዚአብሔር ይጮሃል (ዘፍጥረት 4፥ 10)። እነዚህ ሰማዕታት ካሉበት መንፈሳዊ አለም ሆነው፣ ደማቸው በምድር ላይ በግፍ  ስለመፍሰሱ ግድ ብሏቸው የእግዚአብሔርን በቀል "በምድር በሚኖሩት ላይ" (ቁ. 10) እንዲመጣ የመጠየቃቸው እውነታ የሚያሳየው አሳዳጆቻቸውና ደማቸውን ያፈሱሱ ሰዎች ያኔም ገና በምድሪቱ ላይ የነበሩ መሆናቸውን ነው። ከ70ው አም ፓሮውዥያ አስቀድሞ የጻድቃን አይሁድና የክርስቲያኖች ዋነኛ አሳዳጆች መቀመጫቸውን በኢየሩሳሌም፣ የማዘዣ ጣቢያቸውንም በቤተ መቅደሱ ያደረጉ የአይሁድ ህዝብ መሪዎችና አለቆች የነቡሩት የዚያ ዘመን ዳኞችና የዚያ ትውልድ ሰዎች ናቸው (ሉቃስ 13፥ 33)። ይህ ሃሳብ ደግሞ ኢየሱስ፦ "ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።  እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።" (ማቴዎስ 23፥ 35 ጀምሮ) ሲል በተናገረው ትንቢት ውስጥ በሚገባ የተንጸባረቀ ነበር።

በዚያን ዘመን ላይ የተፈጸመው የኢየሩሳሌም ውድመት በመሪዎችዋ ታርደው ለተገደሉት ለጻድቃን ደም (ነፍሳት) በእግዚአብሔር ፊት ለቀረበው ጩኸታቸው ምላሽ ሆኖ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የመለኮታዊው ዳኛ ፍርድ ነበር። ራስል ሲጽፉ፦ "በዚህ የአምስተኛው ማህተም ራዕይ ጭብጥ እና ጌታችን ስለ አመጸኛው ዳኛ "እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?" (ሉቃስ 18፥ 1-8) ሲል በተናገረው ምሳሌ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በጥንቃቄ ተመልከቱ፤ ይህ የሚያስገርም መመሳሰል አይደለምን? ጉዳዩ ግን ከመመሳሰልም በላይ ያለፈ እና ማነትታቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው" ይላሉ።

ሮማዊው ጲላጦስ ደማቸውን ከመስዋእታቸው ጋር ስለደባለቀው በገሊላ ስለነበሩ አይሁድ አምላኪዎች  ጌታ ኢየሱስ ወሬው በተነገረው ጊዜ ምላሹ ምን ነበር? "እናንተም (አይሁድ) ንስሃ ባትገቡ እንደዚሁ [ማለትም በሮማውያን እጅ] ትጠፋላችሁ" (ሉቃስ13፥ 1-3) ነበር ያላቸው። ይህ አምስተኛው ማህተም በኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸመውን ፍርድ ምክንያቱን ያሳስበናል "ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም " (ዘሁልቅ 35፥ 33) ተብሎ ተጽፏልና።

፨ይህንን የሰማዕታቱን ትንሳኤ አጥርቶ መረዳት ቁልፍ ነገር ነው። እነዚህ በመጀመርያው ትንሳኤ እድል ያላቸው ሁሉም የሞቱ ቅዱሳን (ራዕይ 20፥ 6)፣ በ70 አም ከሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያው አስቀድሞ የሞቱ ቅዱሳን ናቸው። ከእነርሱም መካከል በተለይ በብሉይ ኪዳን ዘመንና ብሎም በሽግግሩ ዘመን ውስጥ ሰማእታት ሆነው በግፍ የተገደሉ ቅዱሳን ነበሩበት። 

እነርሱም

(ሀ) ስለክርስቶስ እና ስለቃሉ ራሶቻቸው የተቆረጡባቸው (ስማእት የሆኑ) ነፍሳት ናቸው። ይህም የሰማዕታት ቡድን  ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው በክርስቶስ ትንሳኤ ጊዜ ከየመቃብሮቻቸው ወጥተው ለመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አይሁድ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ሕያዋን የሆኑትን ወይም እንደገና ሕያዋን የተደረጉትን (ገና የራሳቸውን ትንሳኤ ያላገኙ) ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ሰማእታት ሊያካትት ይችላል (ማቴዎስ 27፥ 52-53)። ለምሳሌ ስለምስክርነቱ በግልጽ ራሱ ተቆርጦ እንዲሞት የተደረገው መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ የብሉይ ኪዳን የሰማእታት ምድብ ውስጥ ሊካተት ይችላል። እነዚህም ከሲዖል የሙታን እረፍት ስፍራ ወጥተው ሊታይ በማይችለው ሰማያዊው ግዛት የሰማይ ደጅ ከሚገኘው "ከመሰዊያው በታች" ይሆኑ ዘንድ ከክርስቶስ ትንሳኤ የአርባ ቀናት ቆይታ በኋላ በእርገቱ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ወደ ላይ፣ ወደ ሰማያት ደጅ የተወሰዱ ናቸው። ገናም የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት እርሱም ሁሉተኛ መታየቱን እየተጠባበቁ ትንሳኤያቸውን ያላገኙ ነበሩ።

(ለ) በአውሬውና በምስሉ ፊት ያልሰገዱ ወይም ምልክቱን በእጆቻቸው እና በግንባራቸው ያልተቀበሉ ነፍሳትም ናቸው። እነዚህ ደግሞ ስለክርስቶስ መከራን እየተቀበሉ በአሳዳጆቻቸው እጅ በግፍ የተገደሉና እስከ ክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ድረስ ለጊዜው "ከመሰዊያው በታች" ይሆኑ ዘንድ ሊታይ ወደማይችለው ግዛት፣ ወደ ላይ፣ ወደ ሰማያት ደጅ በእያንዳዳቸው የተወሰዱ፣ የሽግግሩ ዘመን ሰማእታት ናቸው። እነዚህም "የጻድቃን መንፈሶች" ከክርስቶስ ጋር በእርገቱ ምርኮው ሆነው አስቀድሞ ከሲኦል ሓደስ የተወሰዱና፣ ለጥቂት ዘመንም እረፍት ይሆንላቸው ዘንድ ሊታይ ወደማይቻለው ሰማያዊ ስፍራ ተወስደው ከመሰዊያው በታች እንዲከማቹ የተደረጉ፣ ትንቢትም ሁሉ በሚፈጸምበት በምጽአቱ ቀን ከክርስቶስና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሊገለጡ የተጠበቁ ነፍሳት ናቸው። ዮሐንስ በራእዩ ሲመሰክር በዚያ የሽግግር ወቅት ላይ ለእነዚህ የሚለብሱት "ነጭ ልብስ"፣ "ዳኝነት" እና ደግሞም ከክርስቶስ ጋር ለሺህ አመት መንገስና መግዛት እንደተሰጣቸው ይናገራል። የእነዚህም ምድብ ማንም ሊቆጥራቸው የማይችለውን የ40 አመት የሽግግር ጊዜ ሰማእታት እነ እስጢፋኖስን፣ የዮሐንስ ወንድም የሆነውን ያእቆብን፣ ዮሐንስን፣ ጳውሎስን፣ የጌታ ወንድም የሆነውን ያእቆብን፣ ጴጥሮስን እና ሌሎችን በዚያ የሽግግር ወቅት ላይ ስለ እምነታቸው በግፍ የተገደሉትን ሁሉ ይጨምራል (ራእይ 6፥ 9-11፤ 7፥ 13-17፤ 20፥ 4)። እነርሱም ልክ በሞቱበት ቅጽበት ቀድሞውኑ ከሲኦል ሐደስ ምርኮ ከወሰዳቸውና በዚያ በሰማይ ደጅ በመሰዊያው በታች ካከማቻቸው ሌሎቹ ቅዱሳን ሰማእታት ጋር ተቀላቅለዋል (ራዕይ 6፥ 9-11፤ 7፥ 13-17፤ 20፥ 4)። እነርሱም ክርስቶስ በፓሮውዥያው እስኪመለስ ድረስ ገና ትንሳኤያቸውን ይላገኙ ነበሩ።

እንዴት እንደሆነ ባናውቅም፣ ምናልባትም ሁሉም እነዚህ በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታት፣ ማለትም "የጻድቃን መንፈሶች" ልክ ሳሙኤል ለዛች በዓይንዶር ለነበረች ሙታን ሳቢ ሴት እንደታየበት አይነትና ሁናቴ (1ሳሙአኤል 28፥ 7)፣ ወይም ሙሴና ኤልያስ በመለወጥ ተራራ ላይ ለኢየሱስና ለሦስቱ ደቀመዛሙርት በታዩ ጊዜ (ማቴዎስ 17፥ 1-3) እንደነበራቸው ያለ አንዳች (ጊዜያዊ) አይነት አካላዊ ሁናቴ ወይም መልክ ወይም ቅርጽ ሊኖራቸው ይችላል።

እነዚህ አስቀድመው ሰማእትነትን የተቀበሉ ነፍሳት በዚያ የሽግግር ዘመን ከክርስቶስ ጋር የነገሱና የሚገዙ ድል ነሺዎች ናቸው። ገናም ደግም ከዚያ ከነበሩበት (ጊዜያዊ) አካላዊ ሁናቴ፣ መልክ ወይም ቅርጽ ወደ ዘላለማዊው አካላዊ ሁናቴ ሊለወጡ ትንሳኤን መቀበል የተገባቸው ነበሩ። ከክርስቶስም ጋር ሊነግሱ በማይታየው ግዛት ከመሰዊያው በታች ተጠብቀዋል። በስጋቸው መከራን በመቀበላቸው ከኃጢአት ተለይተዋል (1ጴጥሮስ 4፥ 1-2)፤ በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት፣ ስለ ክርስቶስም በምድር ላይ በተቀበሉት በዚህ መከራና ባለፉበት ጽኑ ስደት ውስጥ በነበራቸው ታማኝነት ፍርድን (ይህም ሁለተኛውን ሞት) ተሻግረዋል "እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።" (ዮሐንስ 5፥ 24)። ተብሎ ተጽፎአልና። በሰማዕትነታቸውም የታመኑ መሆናቸው ተመስክሮላቸው ብይን ተሰጥቶአቸዋል። (ራእይ 20፥ 4)። ትንሳኤን የሚጠባበቁ የነበሩ እነዚህ ሰማዕታት በእርግጥም ብጹአንና የተባረኩ ነበሩ፣ በምሳሌያዊው የሺሁ አመት መንግስትም መሲሁ በተለየ መልኩ ሊያያቸውና ዙፋናቸው በዙፋኑ ዙርያ እንዲሆን እድሉ የነበራቸው ናቸው። (ራእይ 20፥ 5-6)።

3) አሁንም፣ የፊተኛው ትንሳኤ፦ 

"በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት    በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።" (ራእይ 20፥ 6)

እነዚህ ደግሞ በተፈጥሮአዊ መንገድ የሞቱትና እንደ ሰማዕታቱ ሁሉ ተመሳሳይ በሆነ የሰማዕትነት መንገድ ያላለፉ ወይም በነፍሳቸው ምስክርነታቸውን ያልሰጡ፣ ነገር ግን በሙታን ትንሳኤ ተስፋ አምነው የሞቱ የተቀሩት የብሉይ ኪዳን ሙታን (አማኞች ናቸው)፡፡ እነርሱም ደግሞ እንደ ሰማዕታቱ ሁሉ በአጸደ ነፍስ ከነበሩበት የሲኦል እረፍት ወደ ሦስተኛው ሰማይ ወደ ገነት በክርስቶስ እርገት የተወሰዱ እና፣ የሽግግሩ ጊዜ በ70 አም በሆነው የምጽአት ቀን እስኪያበቃ ድረስ በዚያ በሰማይ ደጅ በአውደ ምህረቱ የተጠበቁና በመሰዊያው ዙርያ የተከማቹ ነፍሳት ናቸው። እነርሱም እያንዳንዳቸው ትንሳኤን ሊካፈሉ ተስፋ አድርገው በዚያ በሽግግሩ ወቅትና ከዚያም አስቀድሞ በሰማእትነት  ከሞቱት ሌሎች ቅዱሳን ሁሉ ጋር በአንድነት የዳግመኛ ምጽአቱን ፓሮውዥያ ሊጠባበቁ በሰማይ ደጅ እንዲከማቹ የተደረጉ ነበሩ፡፡

ተፈጥሮአዊ በሆነ ምክንያት የሞቱት የተቀሩት እነዚህ ቅዱሳን ሙታንም በዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያው እስኪነሱ እና የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ዘላለማዊ የትንሳኤ አካላቸውን እስኪቀበሉ ድረስ በሰማይ ደጅ እንደነበሩ ሁሉ፣ እነዚያም ከፍ ሲል ያየናቸው ሰማዕታቱ አዲሱን፣ ዘላለማዊውን የማይበሰብሰውን፣ የማይሞተውንና፣ የከበረውን አካል ገና አልተቀበሉም ነበር።

እነዚህ የፊተኛው ትንሳኤ ሁለት ምድብ አማኞች እያንዳንዳቸው ተጠብቀው ከነበሩበትና ማንም ሊያየው ከማይችለው ሰማያዊ ስፍራ ተነስተው በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በሆነው የክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ወደክብሩ ገብተዋል። እነርሱም ደግሞ ለእርሱ የተወደዱ ምርጦቹና ቅዱሳኑ እንዲሆኑ የተዳኙት ሁሉ ናቸው። በእነርሱም ላይ ሁለተኛው ሞት ምንም ስልጣን የለውም (ራእይ 20፥ 6)።

4) በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተቀሩት ሙታን "ሁለተኛው ሞት"፦
"በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።" (ራእይ 20፥ 15)

"ማንኛውም" የተባሉት እነዚህ ሁሉም የማያምኑ ስዎች ሲሆኑ ያለጥርጥርም ደግሞ በነጩ ዙፋን ፍርድ የሚዳኙትንም ይጨምራል። በእምነት በኩል በክርስቶስ ያልሆኑ ሁሉ፣ የሚድኑበት እምነት የሌላቸው እስከሆኑ ድረስ "ማንኛውም" ናቸው፣ እነርሱም ተነስተው ከስራዎቻቸው የተነሳ ፍርዳቸውን ተቀብለዋል። መጨረሻቸውም በእሳት ባህር ውስጥ ተጥሎ የዘላለማዊ ኩነኔን ፍዳ መቀበል ብቻ ነው። ይህም ሁለተኛው ሞት ተብሎ ይጠራል። (ራእይ 20፥ 11-14)። እነዚህ እንግዲህ ሁሉም በየትኛውም የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የነበሩና ያሉ፣ ወደፊትም የሚኖሩ፣ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ የሌለ፣ ቀድሞውንም ቢሆን ካለማመናቸው የተነሳ ለእሳት ባህር ፍርድ የተመደቡና ታልፈው የተሰጡ፣ ያልዳኑ ኃጢአተኞች፣ ቤዛነቱን ያልተቀበሉ፣ ያልተዋጁ፣ ያልተመረጡ  ናቸው። (ራእይ 20፥ 15)።

5) ልብ አድርጉ፣ 

ክርስቶስ በ70 አም በሆነው ፓሮዥያው ፍርድን ለመፈጸም በሚሆን አላማ፣ በአንድ በኩል ጽድቅን የተቀበሉትንና የተቀደሱትን ሁሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኃጢአተኞችንና እርኩሳንን ሁሉ በቋሚነት መድቧቸዋል። ይህንንም ፍርድ ባደረገበት ጊዜ፣ ፍርዱ መላውን የሰው ዘር ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ከ70 አም በኋላ ለጥቆ ውዲህ ባለው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውልና የሚያገለግል ቋሚ አሰራር ሆኖ ይኖራል፤ (ራእይ 22፥ 10-11)። አሁን ያለን የማመን-አለማመን አቋምና አቋቋም ምድባችን ከየትኛው ወገን እንደሆነ ስለሚያመለክት ወደፊት የምንጠባበቀው ፍርድ አያስፈልገንም፣ የእግዚአብሔር ቃል "በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።" (ዮሐንስ 3፥ 18) ብሏልና።

6) ይህን ደግሞ አስተውሉ፣ 

ከ70 አም በኋላ የዳኑ ሁሉም የእግዚአብሔር ቅዱሳንና ምርጦች በትንሳኤም ሆነ ወይም በፍርድ ውስጥ ማለፍ አስፈላጊያቸው አይደለም። ይህም የሆነበት ምክንያት ክርስቶስ በ70አም በሆነው የምጽአቱ ፓሮዥያ የአማኝ ቅዱሳን ምርጦቹን ደህንነት ሙሉ በሙሉ ወደ ፍጻሜ ስላደረሰው (consummated ስላደረገው) ነው። ይህ ማለት፣ በእምነት በኩል በክርስቶስ ውስጥ ያለን በመሆናችን ከእርሱ ጋር ሞተናል፤ ከእርሱም ጋር ለአዲስ ሕይወት ተነስተናል፤ በእርሱም ውስጥ ተፈርደን ለማይጸድቁት በታደለ ጽድቅ በእርሱ ውስጥ ጻድቅ ሆነን ተገኝተናል (ዮሐንስ 5፥ 24፤ ሮሜ 6፥ 8-11፤ 2 ጢሞቴዎስ 2፥ 11፤ 1 ጴጥሮስ 3፥ 18)። አሁን በዚህ ሕይወት እያለን በስጋ በምንሞትበት ጊዜ በቅጽበት አይን እንለወጥና፣ በቀጥታ ያለምንም ጥበቃ፣ የማይበሰብሰውን፣ የማይሞተውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ ይማይችለውን፣ አዲሱን ሰማያዊ አካል እንለብሳለን። ስጋና ደም የሆነው አሮጌው አካላችን ይረግፍና ይበሰብሳል። እኛ ግን በቅጽበት አይን እንለወጥና የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን አዲሱን አካል ለብሰን ለዘላለም በሆነችው በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከክርስቶስና ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በዘላለማዊ ህይወት ለዘላለማዊ ክብር ለመኖር ወደከበረው ዘላለማዊ ሀልዎቱ እንገባለን። (1ቆሮንቶስ 15፥ 53-54)።

ስናጠቃልለው፦ 

ከ70 አም በፊት ለሰዎች መሞት አንድ ጊዜ ተመድቦላቸው ነበር፤ ያኔም ከሙታን ተነስተው የክርስቶስን ፍርድ ተቀበሉ። ትንሳኤና ፍርድ ይተከናወነው በ70 አም  በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ፓሮዥያ ላይ ነው። ይኸውም የተከናወነው የእርሱን ዳግመኛ ምጽአት ናፍቀው በብዙ መጓጓት ይጠባበቁ የነበሩ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ትውልድ በነበሩበት ወቅት ነው። ሁሉም አይነት ፍርዶችና ብድራቶች በዚያን ጊዜ እንዲፈጸሙ በእግዚአብሔር ተወስነዋል ፡፡

"ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት (ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅድሳን) ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል" (ዕብራውያን 9፥ 27-28)

ልክ በአንዱ ሰው (አዳም) በኩል ኃጢአት ለሰው ሁሉ ሞትን እንዳመጣ፤ እንደዚሁ በአንዱ ሰው (ክርስቶስ) ጽድቅ ለምርጦቹ ሁሉ ህይወትን አመጣ። ስለዚህም ደግሞ ክርስቶስ በ70 አም ባደረገው ፓሮዥያው በፈጸመው ፍርድ ለተመረጡቱ (ላለፉትም ለሚመጡትም) የሰማይን ዘላለማዊ ዕድል፤ እንደዚሁም ደግሞ ላልተመረጡቱ (ላለፉትም ለሚመጡትም) የሲዖልን ዘላለማዊ ዕድል ፍርዱ አስገኝቶላቸዋል። ለሰዎች ሁሉ፣ "ጸድቀሃል" ወይም "ተኮንነሃል" ተብሎ በእግዚአብሔር ዳኝነት የተላለፈው ብያኔና ዘላለማዊ ፍርድ የተዘጋጀው፣ የተመሰረተውና የጸናው በዚያን ጊዜ ያኔ ነው።

"ለእኔም፦ ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።" (ራእይ 22፥ 10-11) ወደፊት በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሚከናወን፣ ወይም ሊከናወን ያለ፣ የቀረ፣ አንድም የፍርድ ስርዓት የለም። ከ70 አም በኋላ ለሚኖሩና ለሚሞቱ ሰዎች ከ70 አም በፊት በነበሩና በሞቱ ሰዎች ላይ በተፈጸመው አይነት የሚከናወን መጻኢ የሆነ ትንሳኤም ሆነ ወይም ፍርድ የለም። እግዚአብሔር ምርጦቹን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በእምነት በኩል ለዘላለም ጻድቃን አድርጎ ገልጧቸዋል፣ አጽንቷቸዋልም። ስሞቻቸውም አለም ሳይመሰረት አስቀድሞ በሕይወት መጽሐፍ ላይ ላይደመሰስ ተጽፎአል። (ኤፌሶን 1፥ 4፤ ራእይ 21፥ 27)።

ከ70 አም በኋላ ያሉ እያንዳንዳቸው ዳግመኛ የተወለዱ አማኞች በሚሞቱበት ጊዜ በየራሳቸው አዲሱን፣ የማያረጀውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ የማይችለውን፣ ስማያዊውን አካል ይለብሱና በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (በሰማያት) ከክርስቶስና ከቅዱሳኑ ጋር ለመሆን በቅጽበት አይን ወዲያውኑ ወደ ክርስቶስ ሀልዎት ሄደው (1ቆሮንቶስ 15፥ 53-54፤ 2ቆሮንቶስ 5፥ 1-4) ለዘላለም በዚያ ይሆናሉ እንጂ፣ የሌለውን "የስጋ ትንሳኤ" አይጠባበቁም።

ከዚህ ውጭ ያሉቱ ደግሞ፣ ያልዳኑ፣ ያልተመረጡቱ፣ ያልጸደቁቱ ናቸው፣ እነርሱም ያላመኑ ስለሆኑ አልተዋጁም። በህይወት መጽሐፍ ላይ የአንዳቸውም ስም የለም። ዕድላቸውም ዘላለማዊ ሞት ሆኖ በሚቃጠል የእሳት ባህር በዘላለማዊ ኩነኔ ሊቀጡ የተፈረደባቸው ናቸው። በ70 አም ምጽአቱ አንድ ጊዜ ለዘላለም በተሰጠ ብይን ሁሉም የማያምኑ ኃጢአተኞች አሁን በላያቸው ላይ ባለ በማይለወጥ የእግዚአብሔር ፍርድ ለዘላለም ተኮንነው ይጠፋሉ። (ራእይ 20፥ 15፤ ራእይ 21፥ 8፤ ማቴዎስ 18፥ 9፤ ማርቆስ 9፥ 47-48)።

በመጨረሻም የህይወት ጥሪ፣ 

በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጽሁፌን የምታነቡና ስለ መጨረሻው እድላችሁ እርግጠኛ ያልሆናችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ በንስሃና በእምነት የሚገባባት፣ የማይዘጉ ደጆች ያሉአት የአምላካችንና የመድሃኒታችን መንግስት፣ ልትገቡ ብትወድዱ እና አሁን ለእምነት ብትታዘዙ እነሆ ከመሞታችሁ በፊት በፊታችሁ የተከፈተች ሆና ትጠብቃችኋለች። በጌታችንና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከዘላለም ጥፋት ወደ ዘላለም ሕይወት እንድትመጡ እየጋበዝን እንድትገቡ እንለምናችኋለን።
ቸር ቆዩኝ!
ግዛቸው 








የኢዮስያስ ጥያቄና የእኔ መልስ

ውድ ኢዮስያስ፣ (ጥያቄህን ባነሳህበት ገጼ ላይ ገብቼ መመለስ ባለመቻሌ በዚህ ገጽ ቀርቤ ላነጋግርህ) በብዙ የራሴ ጥቃቅን ምክንያቶች ዘግይቼም ቢሆን አሁን ስመልስልህ መልሴን ለማንበብ እንደማትሰለች ተስፋ አደርጋለሁ። ጽሁፎቼንና የማስተላልፈውን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ ሳይደነብሩ በልብ ስፋት ከሚያዩና ልማድ ከማይተናነቃቸው ጥቂት አንባቢዎቼ አንዱ በመሆንህ ላመሰግንህ እፋልጋለሁ። እኔም የምታነሳቸውን የሰሉ ጥያቄዎችህን በሚገባ አያቸዋለሁ እንጂ እንዳመጣልኝ ልመልሳቸው አልሻም። በእርግጥ በዚህኛው ልጥፌ ላይ ያነሳሃቸው ጥያቄዎች ከዚህ ቀደሞ በጻፍኳቸው የተለያዩ አጭርና ዝርዝር ጽሁፎቼ ላይ ልመለከታቸው መሞክሬ አልቀረም። ስጽፍም አንባቢዎቼ የቀደሙትን ስራዎቼን ያስታውሳሉ ወይም ብሎገሬን ይበረብራሉ በሚል ታሳቢነት ስለሆነ አንዳንድ ጉዳዮችን ከድግግሞሽ ሽሽት የተነሳ ያለ ተጨማሪ ማብራርያ በቀጥታ በማለቴ ከአንዳንድ ደርሶ ተመላሾች ጋራ መተላለፋችን አልቀረም። ፕሪቴሪዝምና ትምህርቱን የሚያቀርብበት መንገድ የብዙዎችን ልማዳውያን (traditionalists) ጅማት የሚፈታ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ዋናው ሸክሜ ግን እኔ ልሄድ በመረጥኩበት መንገድ "ነገሩ እንዲህ ይሆንን?" የሚሉ እምነታቸውን የሚጠይቁና መጻህፍትን የሚመረምሩ ጥቂት ወገኖችን ማገዝ ነው። ጥያቄዎችህን ለማስታወስ ላስቀድምና የኔን መልስ ላስከትል። እንዲህ ነበር የጠየቅኸኝ፦

ቄስ እንድታብራራልኝ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ላንሳ- እንዳንተ እምነት በ70 አ.ም ያኔ ጌታ በክብር መጥቶ፦1- ከምጽሃቱ በፊት ለሞቱ ቅዱሳን ትንሳኤን፣ 2-በህይወት ለነበሩት መለወጥን፣ 3-ለእርኩሳንና ለማያምኑ ሃጢአተኞች ዘላለማዊ ፍርድና ጥፋት እንዲሁም ፣ 4- በእርሱ ለሚያምኑ ደግሞ የዘላለም ህይወት ከተሰጠና፣ 5- ከዛን ጊዜ ጀምሮ በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር ያለን ከሆነ፦
ጥያቄ-
1- በ70 አ.ም ተካሄደ ያልከው ትንሳኤና መለወጥ ምን አይነት ትንሳኤና መለወጥ ነበር? ከዛን ጊዜ በኋላ ያለን አማኞች የትንሳኤ ጉዳይስ ምን አይነት ትንታኔ አለው? የትንሳኤውንና የመለወጡን ባህሪ ብታብራራልን (ከዚህ ቀደም ምናልባት ካብራራሃው ደግሞ link ብታጋራን)
2- ከዛ አመት በኋላ ያለን እኛ አማኞች ያልተፈጸመ የምንጠባበቀው ተስፋ አለን?
3- ከዛን ጊዜ በኋላ አዲስ ሰማይና ምድር ከሆነ አሁን የምንኑሮው ኑሮ በአዲስ ሰማይና ምድር ነው? ምክንያቱም የራእይ መጽሃፍ የመጨረሻ ምእራፍ ስለ አዲስ ሰማይና ምድር  ሲያወራ በዛ ሀዘን፥ ለቅሶ፥ እምባ...ወዘተ እያለ የሚዘረዝራቸው የማኖሩ ከሆነ በዚህ ዘመን የምናያቸው ስቃዪች፥ ለቅሶዎች፥ እንባዎች...እንዴት ይዳኛሉ? ማለቴ አዲስ ሰማይና ምድር ውስጥ አለን ካልን እነዚህ እኩይ ክንዋኔዎች እንዴት አሁን በምንኖርበት አለም ሊገኙ ቻሉ? የአዲስ ሰማይና ምድር አስተምህሮው የእነዚህን እኩይ ክንዋኔዎች መኖር አይከላከልም?
4- ሃጢአተኞች (እርኩሳንና የማያምኑ) ዘላለማዊ ፍርድ ከተቀበሉ ዛሬ በክርስቶስ ማንነትና ስራ የማያምኑ የፍርድ ሁኔታ መች ሊሆን ነው?
ቄስ ከላይ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች ምናልባትም ለቀጣይ ውይይታችን መነሻ ይሆናል ባይ ነኝ።

¶ እኔም በቀጥታ ወዳነሳሃቸው ጥያቄዎች ስመለስ እነሆ መልሴ፦
1- እንደምታውቀው ትንሳኤ በአጠቃላይ ጻድቃንንና ዓመፀኞችን የሚያካትት መሆኑ፣ በአይሁድም ይጠበቅ የነበረና የቤተክርስቲያንም ተስፋ ሆኖ የኖረ እምነት ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ፣ ይህ አጠቃላይ ትንሳኤ ሊፈጸም ቀን የተቀጠረለት ደግሞ በቀኑ መጨረሻ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ መሆኑ በሚበዙት ዘንድ ተቀባይነት አለው። እኔ ደግሞ ቅዱስ ቃሉ የሚያውቀው የቀኑ መጨረሻ፣ ደግሞም ጌታ እንደተስፋ ቃሉ ተመልሶ የመጣው፣ በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ነው ብዬ ለማመን በቅዱስ ቃሉ ስለምገደድ፣ የዚህን አጠቃላይ ትንሳኤ መፈጸም ጊዜውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ነጥዬ ልረዳ አይሆንልኝም። ለሙታን ትንሳኤ በተቀጠረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጊዜ ላይ የጠራ አመለካከት የያዘ ሰው በትንሳኤ ተፈጥሮና ባህርይ ላይ፣ ማለትም ሙታን በምን አይነት አካል ወይም ሁናቴ ትንሳኤን ይቀበላላሉ በሚለው ላይ ግራ አይጋባም፤ ጊዜው ራሱ የትንሳኤን ተፈጥሮውንና ባህርዩን ይገልጣልና። ትንሳኤ በተፈጥሮው መንፈሳዊ መሆኑንና የትኛውንም ተዳሳሽ ቁስ ማስረጃና ማረጋገጫ አድርጎ የማያቀርብ መሆኑ ግልጽ ነው። የጥንት ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን እንደሚታሰበው ሁሉ ትንሳኤ ተዳሳሽ ስጋዎችን ከመቃብር ውስጥ አውጥቶ ማምጣትን የሚጨምር መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ ለምሳሌ ሄሜኔዎስና ፊስጦስ "ትንሳኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል" ብለው በማስተማር ማንንም ማሳመን ባልቻሉም ነበር። ስለዚህ ላነሳኸ የ"አይነት" ጥያቄ ቁልፉ "ጊዜው" ስለሆነ የነገረ ፍጻሜን ሀሁ ለመረዳት ኮስተር ብለህ ጊዜውን አጥና። በነገራችን ላይ ቀጣዩ ልጥፌ ስለ አጠቃላይ ትንሳኤ ስለሚያትት ዝርሩን እዚያ ላይ እንመለከተዋለን።
2- ባጭሩ፣ ያልተፈጸመ የምንጠባበቀው ምንም ተስፋ የለም። አለ የሚል ሊያቀርብ ይችላል፣ ያኔ መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ለእምነት ቤተሰቦች ቃሉን፣ ለተጠራጣሪዎች ደግሞ  የታሪክ ሰነድ ጠቅሰን እናስረዳለን።
3- በኮስሞሎጂካል ለውጥ የተወከለው ለውጥ የኪዳን እንጂ የግዑዝ አለም ለውጥ አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። አሮጌው ሰማይና ምድር እሮጌው ኪዳን ሲሆን የአሮጌው ኪዳን ሀዘን እንባ ልቅሶ የኪዳኑ ቀንበር፣ የሞት እዳና እርግማኑ ሁሉ ነው። ያ ኪዳን እስካለ ድረስ የኪዳኑ መርገምም ደግሞ አለ። በዚያ ኪዳን ስር ከብዷቸው ይቃትቱ የነበሩ ሁሉ፣ ከአሮጌው የሙሴ ሥርዓት ይቀበሉት ከነበረው መከራ ያረፉትና የተጽናኑት አዲሱ ኪዳን ያለ አሮጌው ኪዳን በሆነበት በአዲሱ ሰማይና ምድር ነው። አሁን በጌታ ዳግመኛ ምጽአት የተጀመረው አዲሱ የጸጋ ሥርአት ብዙ መጽናናት ያለበት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሃሴትና ደስታ ነው እንጂ የስጋዊ ተድላና ድሎት አይደለም። የዚህን አለም እውነታ መሸሽ አንችልም። አንተ ያነሳሃቸውን የዚህ ግዑዝ አለም ሃዘንና ስቃይ የምንሻገረው አንድም ለተሻለ አለም  ስንሰራበት ነው፣ አልያም ለመከራ ከተፈጠረው ከዚህ ስጋችን በሞት ስንለይ ብቻ ነው። በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል የጌታ ዳግም ምጽአትም ሆነ ሌላ ነገረ ፍጻሜአዊ ክስተት እነዚህን አንተ ያነሳሃቸውን ጉዳዮች የሚያስቀር ተስፋ የለም። እኩይና ሰናይ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለ ምንም ከልካይ መሳ ለመሳ በፍጥረታዊው የሰው ልጅ አለም ነበሩ፣ አሉ፣ ይኖራሉም። በእምነት ጉዳይ "ይህ ግዑዝ አለም ተወግዶ ሌላ አለም ይመጣል፣ ያኔም አሁን የምናያቸው ሰቆቃዎች ይቀራሉ" እያልን ውዝፍ/ጉልት (passive) ሆነን የማይመጣ ነገር ከመጠበቅ ወጥተን ቢያንስ ከመሞታችን በፊት ለልጆቻችን የተሻለ ነገ ብንፈጥርኮ እግዚአብሔሩም ትውልዱም ያመሰግኑን ነበር።
4-ክርስቶስ በ70 አም በሆነው ፓሮዥያው ፍርድን ለመፈጸም በሚሆን አላማ፣ በአንድ በኩል አምነው ጽድቅን የተቀበሉትንና የተቀደሱትን ሁሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባለማመን የጸኑትን ኃጢአተኞችንና እርኩሳንን ሁሉ በቋሚነት መድቧቸዋል። ይህንንም ፍርድ ባደረገበት ጊዜ፣ ፍርዱ መላውን የሰው ዘር ያካተተ ሲሆን፣ ይህም ከ70 አም በኋላ ለጥቆ ውዲህ ባለው የሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውልና የሚያገለግል ቋሚ አሰራር ሆኖ ይኖራል። (ራእይ 22፥ 10-11) አሁን ያለን የማመን አለማመን አቋምና አቋቋም ምድባችን ከየትኛው ወገን እንደሆነ ስለሚያመለክት ወደፊት የምንጠባበቀው ፍርድ አያስፈልገንም፣ የእግዚአብሔር ቃል "በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።" (ዮሐንስ 3፥ 18) ብሏልና። ወደፊት በሚኖረው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሚከናወን ወይም ሊከናወን ያለ የቀረ አንድም የፍርድ ስርዓት የለም። ከ70 አም በኋላ ለሚኖሩና ለሚሞቱ ሰዎች ከ70 አም በፊት በነበሩና በሞቱ ሰዎች ላይ በተፈጸመው አይነት የሚከናወን መጻኢ የሆነ ትንሳኤም ሆነ ወይም ፍርድ የለም። እግዚአብሔር ምርጦቹን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት በእምነት በኩል ለዘላለም ጻድቃን አድርጎ ገልጧቸዋል፣ አጽንቷቸዋልም። ስሞቻቸውም አለም ሳይመሰረት አስቀድሞ በሕይወት መጽሐፍ ላይ ላይደመሰስ ተጽፎአል። ከ70 አም በኋላ ያሉ እያንዳንዳቸው ዳግመኛ የተወለዱ አማኞች በሚሞቱበት ጊዜ በየራሳቸው አዲሱን፣ የማያረጀውን፣ የማይበሰብሰውን፣ የከበረውን፣ ሊታይ የማይችለውን፣ ስማያዊውን አካል ይለብሱና በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም (በሰማያት) ለመሆን ወዲያውኑ ወደ ክርስቶስ ሀልዎት ይሄዳሉ። ከዚህ ውጭ ያሉ ያልዳኑ ያልተመረጡቱ ያልጸደቁት ናቸው፣ እነርሱም ያላመኑ ስለሆኑ አልተዋጁም። በህይወት መጽሐፍ ላይ የአንዳቸውም ስም የለም። ዕድላቸው በሚቃጠል የእሳት ባህር በዘላለማዊ ኩነኔ ሊቀጡ የተፈረደባቸው ናቸው። በ70 አም ምጽአቱ አንድ ጊዜ ለዘላለም በተሰጠ ብይን ሁሉም የማያምኑ ኃጢአተኞች አሁን በላያቸው ላይ ባለ የእግዚአብሔር ፍርድ ለዘላለም ሊኮነኑ ይቀጣሉ። ላሁኑ እዚህ ላይ ላቁም፣ በመስመሩ መጥተህ ባንግባባም እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ቸር ቆየኝ።