"የጌታ መምጣት ቀርቦአል"
ፓሮውዥያ
"እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።" (ያዕቆብ 5፥ 7-8)
"ምጽአት" ለተሰኘው የአማርኛ ቃል አቻ የግሪክ ቃል ፓሮዥያ የሚለው ነው። ሲተረጎምም ቅርብ መሆንን፣ መገኘትን፣ መምጣትን፣ መድረስን ያሳያል፤ በተለይም ክርስቶስ በፍጻሜው ኢየሩሳሌምንና ክፉዎችን ሊቀጣ የሚመለስ መሆኑን፣ እንዲሁም ቀጣይነት ባለውና በማይቋረጥ ሕልዎት አብሮ መሆንን በሚያመለክትበት መልኩ ይተረጎማል [ስትሮንግስ የተሰኘውን የግሪክ ቃላት መፍቻ #3952 ይመለከቷል]።
የጌታ ዳግመኛ ምጽአት ፓሮዥያው የተከናወነው ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ሲል እንደ መግቢያ የጠቀስኩትን የመልዕክቱን ንባብ ከጻፈበት ጊዜ ጥቂት አመታት በኋላ በግምት ሰባትና ስምንት አመታት ያህል ቆይቶ ነው። ያዕቆብ እነዚያን የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን "የጌታ መምጣት ቀርቦአል" ብሎ እስኪመጣ እንዲታገሱና መከራን እየተቀበሉ እንዲጸኑ ሲነግራቸው እና ሲያሳስባቸው፣ በተደራስያኑ ዘመንና ትውልድ ውስጥ ሊፈጸም ስላለው የጌታ ምጽአት እንጂ ሁለትና ሦስት ሺህ አመታት ቆይቶ ገና ወደፊት በብዙ ዘመን ርቀት ስለሚፈጸም ምጽአት እየነገራቸው አልነበረም። በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት በአይሁድ እና በሮማውያን እጅ ይቀበሉት ከነበሩት ከዚያ ጽኑ መከራና ስደት የሚያሳርፋቸው ብቸኛ የተባረከ ተስፋ የጌታ ምጽአት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው ዳግመኛ ምጽአት ደግሞ ያው አንዱ ምጽአት ሲሆን እርሱም ጌታ የተናገረለት እና እነዚያ በጽኑ መከራ ውስጥ የነበሩ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ሲጠባበቁት የነበረው ነው እንጂ ሌላ ምጽአት እንድንጠብቅ ለኛ የቀረልን "የስምንተኛው ሺ" ምጽአት የለም።
የዚህን የፓሮውዥያውን የጊዜ ማእቀፍ የሚያመለክት በያዕቆብ የተነገረን ግልጽ ቃል "ቀርቦአል" የተሰኘው ነው። ይህ "ቀርቦአል" ለእነርሱ ነው እንጂ ለእኛ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አይደለም። "ቀርቦአል" የተሰኘው ምጽአቱም የተፈጸመው ያኔውኑ በእነርሱ ዘመን፣ በ70 አም ላይ ነው። ያኔ ጌታ በክብር መጥቶአል፣ ከምጽአቱ በፊት ለሞቱ ቅዱሳን ትንሳኤን፣ በሕይወት ለነበሩቱ መለወጥን ሰጥቶአቸዋል፤ እርኩሳንና የማያምኑ ኃጢአተኞችም ዘላለማዊውን ፍርድና ጥፋት ተቀብለዋል። በእርሱ ለሚያምኑ የዘላለምን ሕይወት ለማያምኑ ደግሞ ዘላለማዊ ኩነኔን ሰጥቶ የመጨረሻውን ፍርድ ፈጽሞአል።
ክርስቶስ ያኔ በማያምኑት የእስራኤል ህዝብ ላይ ቁጣውንና ፍርዱን አድርጓል። ከተማይቱን ኢየሩሳሌምን እና መቅደሱን አውድሞ አጥፍቷቸዋል። የማያምኑት የክርስትና ጠላቶችና አሳዳጆች የነበሩ የዚያ ዘመን አይሁድ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የፈጸሙትን ግፍና ወንጀል የሚመጥን ፍርድና በቀል እንደተቀበሉ ለመረዳት ይደርስባቸው ዘንድ የተነገረባቸውን (ለምሳሌ ዘዳ 28 እና ማቴ 24) የፍርድ ቃል ከታሪካዊው የ70 አ.ም እልቂታቸው ጋር አስተያይቶ ማንበብ የአስተዋዮች መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ከታሪካዊ መዛግብት በላይ እጅግ የጸናው የትንቢት ቃል፣ "ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል" ሲል ጌታ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ነው እንጂ፤ ታሪካዊ መዛግብት የጌታ ትንቢት መፈጸሙን ለማመን ቀዳሚ መሰረታችን አይሆኑም። ያመንነው ቃሉን ብቻ ነው። ተጠራጣሪ ሰዎች ቃሉን ብቻ በማመን ስለማይረኩ ታሪካዊ ማስረጃ ቢቀርብላቸውም መጠራጠራቸውን አያቆሙም። ለእምነት ቤተሰብ ግን የእምነት ቃል ብቻ ይበቃዋል።
ይሁንና ግን የዚያ የ70ው አ.ም የአይሁድ አመጽና በሮማውያን የተወሰደው የማጥቃት ጦርነት በጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረባቸው መለኮታዊው ፍርድ እንደሆነ በውል አለመረዳት ደግሞ በታሪካዊው የስነ ትርጓሜ መረዳታችን ላይ ብዙ ውዥንብርን ሲያስከትል ኖሮአል። ይሁንና በጦርነቱ የቅድስቲቱ ከተማ ቅጥር መሰበር፣ የቤተመቅደሱ መቃጠልና በህዝቡ ላይ የመጣባቸው ዘግናኝ ጥፋት፣ በየዘመናቱ ነብያቱን አሳድደው ሲገድሉና፣ በዘመኑ ምጨረሻ ቅዱሱን ሰው ለአህዛብ ፍርድ በመስቀል እንዲሰቀል አሳልፈው ሲሰጡ ያኔ እነዚያ የእግዚአብሔር ፍርድ በራሳቸው ላይ እንደሚገባቸው የቆጠሩ አመጸኛ ሰዎችን በትውልዳቸው አግኝቶአቸዋል። ለአህዛብ ፍርድ አሳልፈው የሰጡት ንጹሁን ሰው ክርስቶስን ሲሰቅሉት "ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን" ሲሉ ያኔ ለጥፋታቸው ፈርመው ነበርና።
ይህም የጥፋት ፍርድ ለአሮጌውን ኪዳን የአይሁድ ኃይማኖታዊ ስርዓት (እርሱም የአሮጌው ሰማይና ምድር ነው) ሙሉ በሙሉ ፍጻሜ የሰጠው ነው። ያኔም የአዲሱን ኪዳን መንፈሳዊ የወንጌል መንግስት (እርሱም አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው) በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሊቀጥልና ላይቋረጥ ሙሉ በሙሉ ለዘላለም መስርቶታል። እንግዲህ እረፉት! መጽናናት የሞላበት ይህ የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮውዥያ የተባረከው ተስፋ መጻኢነቱ ለእነዚያ ለአዲስ ኪዳን ጸሐፍያንና ለበኩረ ተደራስያኖቻቸው ብቻ ነው፣ እነርሱም በጭንቅ ወደዚያ ሊገቡና ቀኑን ሊቀበሉ በተስፋና በምጥ ኖረዋል፤ ለእኛ ከ70አም በኋላ ላለን ለሁላችን ግን ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ የፈጸመው የምጽአቱ ፓሮውዥያ ኃላፊ ሆኖአል።
ይህ ፓሮውዥያ የተሰኘው ቃል በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባባት እንዴትና በምን አግባብ ጥቅም ላይ እንደዋለ ጥቂት ማሳያዎችን ላካፍላችሁና ላብቃ
"እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።" (ማቴዎስ 24፥ 3)
"ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤" (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥ 23)
"ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።" (1ኛ ተሰሎንቄ 3፥ 12 እና 13)
"በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤" (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥ 15)
"የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።" (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥ 23)
"ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።" (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 1 እና 2)
"በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል፤" (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥ 8)
"እርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።" (2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 4)
"አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።" (1ኛ ዮሐንስ 2፥ 28)
የሚያንቆራጥጡ ተጨማሪ የነገረ ፍጻሜ ኃላፋዊ ምልከታ ቢያሻዎት philologus66 ይተሰኘውን የፌስ ቡክ ግድግዳዬንና፣ እንዲሁም ብሎገሬን https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_81.html ይጎብኙ።
ግዛቸው ከበደ \ቄስ\