Monday, May 27, 2019

ትንቢትን ለመተርጎም የአውደ ተደራስያን ፋይዳ ለፕሪቴሪዝም

ትንቢትን ለመተርጎም የአውደ ተደራስያን ፋይዳ ለፕሪቴሪዝም
የትኛውንም የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ በአግባቡ ተርጉሞ ለመረዳት ዋናና አስፈላጊ የሆነ አንድ ጉዳይ ቢኖር የምንባባቱን አውድ ማወቅ ነው። ይህም በአይነቱ የጽሁፉ በኩረ ተደራስያን የነበሩበት አጠቃላይ አውድ ማለት ነው። በዋናነትም ምንባቡ አስቀድሞ የተጻፈው ለነማን ነው የሚለውን ማወቅን ያካትታል። ከዚህ በተለየ አብዛኛውን ጊዜ ቅዱሳት መጻህፍትን በትክክል ያለመረዳት ችግር የሚከሰተው አንባቢው ምንባባቱን ለግሉ ወይም ለግሏ እንደተጻፈ አድርገው ሲወስዱ ነው። በመሰረታዊነት አዲስ ኪዳን በመጀመሪያው ክፍለዘመን ጸሐፍያን የተጻፈው ለመጀመሪያው ክፍለዘመን ክርስቲያኖች ሲሆን የተጻፈውም የመጀመሪያውን ክፍለ ዘመን ኹነቶች ለመነጋገር ነው።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን የሚችል አንዱ ጉዳይ ጌታ ኢየሱስ የዳግመኛ ምጽዓቱን ፓሮዥያ በተመለከተ ለደቀመዛሙርቱ የነገራቸውን ሁሉ ዛሬ ለእኛ እንደተነገረ አድርጎ የመውሰድና፣ አሳስቶ የመረዳት፣ የመተርጎምም እሳቤ ነው። እርሱ የቤተመቅደሱ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ ወድቆ እንደሚፈራርስ አስቀድሞ ነግሯቸዋል። እነርሱም ያንን ከሰሙ በኋላ ይህ የተባለው ነገር የሚከሰተው መቼ እንደሆነ፣ እርሱም የሚመጣበት ምልክቱ ምን እንደሆነና፣ የአይሁድ ዘመንስ ማብቂያው መቼ እንደሆነ ጠይቀውታል (ማቴዎስ 24፥ 2-3)።

ኢየሱስ ንግግሩን ሲቀጥል፣ በዚያው በጠያቂዎቹ ትውልድና ዘመን ውስጥ ከምጽአቱ አስቀድሞ ስለሚሆኑ ጉዳዮች፣ ምልክቶችና ኹነቶች በዝርዝር ይነግራቸው ነበር። (ማቴዎስ 24፥ 4-32 ተመልከት)። በግልጽም የነገራቸው አንድ ጉዳይ እነርሱ እነዚህ ነገሮች ሲሆኑ እንደሚያዩና፣ በዚህም ሲሆኑ በሚያዩዋቸው ምልክቶች አማካኝነት መምጣቱ የቀረበ መሆኑን የሚያውቁ እንደሆነ ነው።

"እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።" (ማቴዎስ 24፥ 33-34)።

በርካታ ክርስቲያኖች ዛሬ ላይ ቆመው ይህንን የጌታን ንግግር ለመተርጎም ሲሞክሩ ከጠቅላላ ቃሉ ከተነገረበት አውድ ነጥለው፣ ልክ ጌታ ዛሬ ከአመታት በኋላ የመምጣቱ ምልክት ምን እንደሆነና በእኛው ትውልድ ውስጥ ሊሆን ያለውን ለእኛ የነገረን እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። ስለሆነም ወቅታዊውን የአለምን ፓለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ በተለይም እንደ እስራኤልና አረቦች ያሉ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን ውጥረት፣ እንደ አሜሪካና አውሮፓውያን ሸሪኮቿ ያሉ የኃያላን መንግስታትን የውጭ ፓሊሲ፣ እንደ ሩስያና ቻይና ያሉ ከምዕራባውያን በተቃራኒው የቆሙ ኃይሎችንና ትንንሽዬ የኒውክለር ጡንቻ እያበቀሉ ያሉ እንደ ኢራንና ሰሜን ኮርያ ያሉ መንግስታትን ሁኔታ የሚዘግብ ትኩስ የአለም ዜና እያነፈነፉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በአለም ወሬ እየተመሩ ለመተርጎም የሚደረግ "የስነመለኮት አዋቂ ነን" ባዮች ሙከራ ሁሉ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት አውደ ምንባብና የአውደ ተደራስያኑን ዋጋ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን ከንቱና የማይረባ ሆኖ በክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለበርካታ የስህተት ትምህርትና የስህተት እምነት መፈልፈያ ሰበብ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ አውደምንባብ እና የበኩረ ተደራስያኑ ተዛማጅነት ዋጋ ባለው ሁኔታ በቁሙ የሚወሰድ ከሆነ ግን፣ ያኔ በትንቢት ቃል  ምንባብ ላይ ግልጽ እና ቀጥተኛ የሆነ ትርጉም ሊኖረን ይጀምራል። ከተሳሳተ መረዳትና እምነትም እንጠበቃለን። ፍጻሜውንም በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ በማስተዋል የመጽናናትን ብዛት፣ የእምነትን ጽናትና የክርስቶስ ታማኝ ምስክርነት የሚሰጠውን ድልና ድፍረት ያለማምደናል።

ማቴዎስ 24ን መሰረት አድርጌና ረዘም ያለ ጊዜ ወስጄ በተከታታይ ባቀረብኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ባስነበብኩት ዘለግ ያለ ጽሁፍ ለማስረገጥ የወደድሁትም እያንዳንዳቸው እነዚህ ጉዳዮች በእርግጥም በዚያው በመጀመርያው ክፍለዘመን ውስጥ መሆን ጀምረው ሙሉ በሙሉ ፍጻሜአቸውን ያገኙት በ70 ዓም ላይ መሆኑን ነው። ፍላጎቱ ያላችሁ አንባቢዎቼ በማቴዎስ 24 ላይ "የጌታ ምጽአት መቼ እና እንዴት" በሚል ርዕስ ያስነበብኩትን ተከታታይ ጽሁፍ እንድትመለከቱ እነሆ ሊንኩን ጋበዝኳችሁ፦
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/24.html
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_60.html
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_33.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_91.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_95.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_32.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_93.html
http://gizachewkr.blogspot.com/2018/11/blog-post_43.html

እንደ  እውነቱ ከሆነ በእግዚአብሔር ቃል ጥናታችን ላይ አውዱን ያገናዘበ ምልከታ ሲኖረን፣ የክርስቶስን የዳግመኛ ምጽዓት ፓሮዥያ በተመለከተ የተነገሩት ሁሉም የትንቢት ቃላት ጌታ ኢየሱስ እና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ሐዋርያቱ በተደጋጋሚ ይሆናል ሲሉ እንደተናገሩት ልክ እንደዚያው ሳይዛነፍ በተባለለት ጊዜ እንደተፈጸመ አጥርተን እናያለን።

በርካታ ክርስቲያኖች ይህንን ለመቀበል እጅግ የሚቸግራቸው ስለ ጌታ ምጽአት ባህርይና ተፈጥሮ በተለምዶ ሲሰሙትና ሲያስቡት ከኖሩት ነገር የተነሳ ነው። ይኸውም፣ ቃሉ ከሚያስተምረው በተለየ ልማድና ትውፊት ያቀበላቸውን ያለ ጥያቄ አስቀድመው ውጠው በመገኘታቸው ነው። ከዚህም የተነሳ ይህንን የትንቢት ቃል በዚያው በተነገረበት የበኩረ ተደራስያኑ አውድ አንጻር እንዳለ ለመውሰድና ታሪካዊ ፍጻሜውንም በዚያው ትውልድ ውስጥ ለማየት አይችሉም፣  ይተናነቃቸዋል። በዙሪያቸውም ያለውን ተዳሳሽና ነባራዊ ሁኔታ እየተመለከቱ "ትንቢቱ አልተፈጸመም"፣ "ጌታም እስካሁን ገና አልመጣም" ሲሉ ደምድመው አቋም ይዘዋል። የሌለና ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር እይጠበቁ ስለሆነ፣ ከ"ተስፋቸው" እና ከ"እምነታቸው" በተለየ የሚሞግታቸውን የአማኝ ወንድሞቻቸውን አመለካከት እንኳ በልብ ስፋት ለማጤን አይታገሱም።  ለምሳሌ፣ በዚህ ተዳሳሽ አለም ያለውን የኅጢአትና  የክፋትን ሁኔት ተመልክተው ሲያበቁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሆን ያንን የሚያዩትን የአለምን ሁኔታ መሰረት አድርገው፣ ፍጻሜ ያገኘውን የተባረከ ተስፋ፣ እርሱም ጠሊቅና ምጡቅ የሆነውን የጌታን መመለስ እውነታ መቀበል አይችሉም። የሆነ ሆኖ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን በጥናታችን ብንተጋ ከዚህ ነባራዊና ተዳሳሽ ግዑዝ አለም ላይ ኃጢአትና ክፋት  እንደሚወገድ የተሰጠ አንዳችም ተስፋ አለመኖሩን አጥርተን ማየት ይቻለናል። ችግሩ ብዙዎች ለቃሉ ሥልጣን ከመገዛት ይልቅ፣ ከአውደ ምንባቡ ርቀው በወደቁበት፣ ፍጥረታዊ ምኞታቸውንና እድሜ ጠገብ ልማዳዊ አስተሳሰባቸውን እንዲያጸድቅላቸ ከመጽሐፉ ስለሚንታገሉ የቅዱስ ቃሉን ትምህርት ሳያገኙት መቅረታቸው ነው።

ጽድቅ ስለሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተሰጠው የታመነ ተስፋ ግን ፍጻሜውን ያገኘው በ70 ዓም ላይ ሙሉ በሙሉ በተመሰረተው በመንፈሳዊው የአዲሱ ኪዳን መንግስት ነው። አሮጌው የአይሁድ ቃል ኪዳን ኃይማኖታዊው ሥርአት በ70 ዓም ላይ ተደምስሶ ተወግዶ አልፎአል። ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለምና ለዘለዓለም መንግስቱን አጽንቶአል። ግዛቱም ወሰን፣ ዘመኑም ፍጻሜ የለውም። በዚህም የአዲሱ ቃል ኪዳን መንፈሳዊ መንግስት ውስጥ አሁን እየኖሩ ያሉት ደግሞ፣ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በእያንዳንዳቸውም ውስጥ እንዲኖርባቸው መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። በእያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ውስጥ በሚኖረው መንፈሳዊው መንግስት አንዳችም ጽድቅ ያልሆነ ነገር የለም።

"ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።" (2ኛ ዼጥሮስ 3፥ 130)

"እንጠብቃለን" ያሉት እንዲጠብቁ አስቀድሞ በጌታ የተስፋ ቃል የተነገራቸው የጥንት ቤተክርስቲያን ሰዎች ናቸው፤ እነርሱም እንዲህ ያለውን መጠባበቅ ከጌታ ቃል የተነሳ፣ በትልቅ ናፍቆትና ጉጉት በገዛ ዘመናቸውና ትውልዳቸው ውስጥ እንደሚፈጸም ከነበራቸው እርግጠኝነት ጋር፣ በሚቀበሉት መከራና በሚያልፉበት ስደት ውስጥ እይቃተቱ ተግብረውታል። እኛ ግን በተፈጸመ ተስፋ ጽድቅ በሚኖርባት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እየኖርን ነን እንጂ ጠባቂዎች አይደለንም።

በመጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት ቃል ላይ ፕሪቴሪዝም የሚያቀርብልን አፈታት ከየትኛውም የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ሥነ መለኮታዊ ትንታኔ ይልቅ ለአውደ ምንባቡና ለአውደ ተደራስያኑ የታመነ፣ አግባብነት ያለውን ሥነ ፍታቴ እየተከተለ ለትርጉም ቀዋሚነት የሚተጋ ነው። ፕሪቴሪዝም ምን እንደሆነ ለማታውቁ፦ ፕሪቴሪዝም በተፈጸመ ነገረ ፍጻሜ የሚያምን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ነው። ይኸውም ክርስቶስ የነብያቱን ትንቢት ሁሉ ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ወደ ፍጻሜ አምጥቶታል፣ በ70 ዓም ላይም በሆነው የዳግመኛ ምጽአቱ ፓሮዥያ  ሁሉንም አጠናቋል ብሎ የሚያምንና የሚያስተምር ነገረ ፍጻሜ ነው። ከፍ ሲል ለማሳየት እንደሞከርኩት ፕሪቴሪዝም ስለ ቅዱሳት መጻህፍት አውደምንባብ የሚገደው የነገረ ፍጻሜ አመለካከት ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ያለውን ማንኛውንም ምንባብ ትርጉሙን መወሰን ያለበት የምንባቡ አውድ ነው። ይኸውም ደግሞ፣ ማን ጻፈው? መቼ ተጻፈ? የተጻፍውስ ለማን ነው? ስለምንስ ጉድይ ነው የተጻፈው? ስፍራውስ የት ነበር? እንዴትስ ነው የሆነው? የሆነውስ ለምንድን ነው? የሚሉትን መርማሪ ጥያቄዎች ሁሉ ያካትታል።

በአጠቃላይ እነዚህ መጠይቆች መመለስ ያለባቸው በራሱ በምንባቡ እና በአውደ ምንባቡ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ተጨማሪ እይታን እንዲሰጡን ሌሎች የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት ሊያስፈልጉን ይችላሉ። አንድን የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ በወጉና በአግባቡ ለመረዳት ቃሉን የሚተረጉመው ቃሉ ብቻ ነው የሚለው መርህ ጠቃሚና እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። እንግዲህ የንባብ ክፍሉ አውድ ግልጽ ከሆነልን ያኔ ይኹነቱን ባሕርይና ተፈጥሮ በውል ለመረዳት ይቻለናል።

እጅግ የሚያሳዝነው ቤተክርስቲያን ላልፉት 2000 አመታት የጌታን ዳግመኛ ምጽአት "ባህርይና ተፈጥሮ" እንዲሁም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የነገረ ፍጻሜ ኹነቶች ሁሉ አሳስታ ስትተረጉም ኖራለች። ከዚህም የተነሳ የዳግመኛ ምጽዓቱን ፓሮዥያ አስመልክቶ በቅዱሳት መጻህፍት ያለውን አውድ ባለመረዳት ፈጽሞ የተሳሳተ የሆነ እሳቤና አመለካከት 'ተምረናል' በሚሉትም ላይ እንኳ ገዢ ሆኖ ኖሯል። ላለፉት 2000 አመታት ቤተክርስቲያን ነገረ ፍጻሜን በተመለከተ የተሳፈረችበት ባቡር ወደ 'ምዕራብ' ሊወስዳት ሲገባ በተቃራኒው እየተጓዘች ያለችው ወደ 'ምስራቅ' ነው። ፕሪቴሪዝም "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" (Sola Scriptura) በተሰኘው የቤተክርስቲያን አዳሾች መርህ ላይ የቆመና በዘመናት መካከል እንደገና የተገኘ ሌላው የተሃድሶ ጥሪ እና እድል ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ደግሞ የሚወድዱ ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንደሚሰጡ አምናለሁ።

ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር አብሮ መሆን ያለባቸው ተብለው በተሳሳተ መንገድ የሚታመኑ አንዳንድ ጉዳዮችን ቤተክርስቲያን እየተጠባበቀች እና እንዲህ ባሉ መላምቶች ላይ እያተኮረች፣ እነዚህ ጉዳዮች እስካሁን ገና ሲሆኑ ስላላየሁ፣ ክርስቶስ እስካሁን አልተመለሰም ስትል ደምድማለች። ከነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
(ሀ) ጌታ ዳግም ሲመጣ ኃጢአት ጨርሶውኑ መጥፋት አለበት፣ አሁን ግን ኃጢአት ያለ በመሆኑ ጌታ አልመጣም፤
(ለ) በዚያን ሰአት ክርስቲያኖች ሁሉ ጥርግ ብለው ከምድር ወደ ሰማይ መሄድ አለባቸው፣ አሁን ግን ክርስቲያኖች በምድር ስላሉ ጌታ አልመጣም፤
(ሐ) ለአንድ ሺህ አመት ክርስቶስ በምድር ላይ በገሃድ ነግሶ አስተዳደሩን ከኢየሩሳሌም ማድረግ አለበት፣ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ጌታ አልመጣም፤
(መ) እስራኤል ዘሥጋ እንደገና የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ መሆን አለባቸው፣ እነርሱ ገና መዳንን ስላልተቀበሉ ጌታ አልመጣም፤
(ሠ) ይህ ተዳሳሽ ሰማይ እና ተዳሳሽ ምድር ፈጽሞ በእሳት ተቃጥሎ መጥፋት አለበት፣ ይህ ግዑዝ አለም ገና አንዳችም ባልሆነበት ሁኔታ ጌታ አልመጣም፤
(ረ) ከዚያ ኹነት በኋላ ማንም አማኝ በምድር ላይ እስከማይታይ ድረስ ቤተክርስቲያን ተነጥቃ ሁሉም በአንድ ጊዜ ወደ ሰማይ መሄድ አለባቸው፣ ገና ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ጌታ አልመጣም፤
(ሰ) በአለም ላይ ላሉ ሰዎች ሁሉ የመዳን እድል ድንገት መዘጋት አለበት፣ አሁን ግን ሰዎች እየዳኑ ስለሆነ ጌታ ገና አልመጣም፤
(ሸ) ሰዎች ሁሉ እያንዳንዳቸው በህይወት ዘመናቸው ለሰሩት ሥራ ክርስቶስ ሊፈርድባቸውና ሁሉም የሥራቸውን ዋጋ መቀበል አለባቸው፣ ይህ ደግሞ አሁንም ሰዎች በምድር ላይ እይኖሩ በመሆኑ ጌታ ገና አልመጣም፤

ቤተክርስቲያን ላለፉት 2000 አመታት እውነት መስሏት አቅፋ የያዘቻቸውና፣ በ70 አም ላይ አስቀድሞ የተፈጸመውን የክርስቶስን የዳግመኛ ምጽአት ፓሮዥያ  በተመለከተ በእግዚአብሔር ቃል ያለውን ንጹሁን ትምህርት በሚያሳዝን ሁኔታ የጋረዱ፣ ብሎም የገደቡ ሌሎች በርካታ ከንቱ የሆኑ መላምታዊ እሳቤዎችን ነቅሶ ማውጣት ይቻላል። ሌላው ቢቀር በፕሪቴሪዝም የሚያምኑ እና "ከፊል ኃላፋውያን" በመባል የሚጠሩ ወገኖችም እንኳ እንዲህ ባሉ መላምታዊ የልማድ አስተሳሰቦች ተይዘው የትንቢትን ሙሉ ፍጻሜ አጥርቶ ከማየት ዘግይተው ይታያሉ። እነርሱም የፓሮዥያውን "ባህርይ ተፈጥሮ" በተሳሳተ መንገድ ከ"ጊዜው" በፊት አስቀድመው በማየት የተቸገሩ ናቸው።

የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት በግልጽ ለመረዳት መሰረታዊው ነገርና ከሁሉ በፊት የሚቀድመው መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የንባብ ክፍል በወጉ፣ በተጻፈበት አውድ ማጥናትና መረዳት ነው። ያኔ ብቻ የፓሮዥያው ባህርይና ተፈጥሮ ምን ምን እንደሚያካትት ለመወሰን የምንችል እንሆናለን። የትኛውንም የቅዱሳት መጻህፍትን ትምህርት በትክክል ለመረዳት አውደ ምንባቡን ማወቅ ተጨማሪ ነገር ሳይሆን ዋናና አስፈላጊ ጉዳይ ነው። 

ከ70 ዓም በኋላ በመንፈሳዊው መንግስት፣ በአዲሱ ኪዳን ወንጌል ውስጥ የምንኖር እኛ ክርስቲያኖች፣ በተለያየ የእምነት ብስለት፣ ጥልቀትና ስፋት ልንገኝ እንችል ይሆናል። ሁልጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ቃል አዲስ ነገር እየተማሩ የሚሻረውን ሽረው የሚጸናውን አጽንተው ወደፊት የሚራመዱ የቃሉ አማኞችና ተማሪዎች ይኖራሉ። ፕሪቴሪዝም ወይም የተፈጸመው ወንጌል ብለን የምንጠራው የትንቢት ፍጻሜ በልብ ስፋት ልንማራቸው ከሚገቡ ከነዚህ አዳዲስ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

ጥቂት በማይባሉ ባለፉት አመታት ነገረ ፍጻሜን ለማጥናት ባገኘሁት እድል ስለ ፕሪቴሪዝም የገባኝ አንድ እውነት ቢኖር በትህትና ተማሪ ሊያደርገኝ ከአውቃለሁ ባይነት ሰረገላ ላይ አውርዶ በቃሉ እግሮች ስር እንድቀመጥ ማስቻሉን ነው። ሁላችንም አንድ ወይም ሁለት ነገር እናውቅ ይሆናል፣ ይህንን ወይም ያንን ተረድተን ሊሆን ይችላል። ማናችንም ብንሆን ግን ሁሉን የምናውቅና መማር የበቃን አይደለንም። ከሁሉ የሚሻለው መንገድ ግን የፍቅርና የትህትና መንገድ ነው። ሁላችንም ተጋጥመን ባለንበት በክርስቶስ አካል እርስ በርሳችን እንዋደድ እንጂ፣ በመሰረታዊው የክርስትና አስተምህሮዎች ላይ እስካልተለያየንና ለኃጢአት ልምምድ በር የሚከፍት አካሄድ እስከሌለ ድረስ፣ "ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል" በማለታንም ሆነ በማናቸውስ ጉዳይ ቢሆን በልብ ስፋት እና በወንድሞች ሕብረት ለመነጋገር ለምን ይከብደናል? እያንዳንዱ ሰው በግሉ ያለ ገደብና ክልከላ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያጠና እና በክርስቶስ እውቀት ያድግ ዘንድ፣ በሚያስብና በሚጠይቅ ንቁ የክርስቲያን አእምሮ እንዲመራመር መፍቀድና አንዳችን ሌላውን ማደፋፈር ይጠበቅብናል። ሃሳቤን የማጠቃልለው ሐዋርያው ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተናገረው የመጨረሻ መልዕክቱ በመጥቀስ ይሆናል፦

"ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።" (2ጴጥሮስ 3፥ 18)

"የፕሪቴሪዝም አመለካከት ምንድን ነው?" የሚለውን ጽሁፍ በተጨማሪነት ለመመልከት እነሆ ሊንኩ፦ 
https://gizachewkr.blogspot.com/2018/08/blog-post.html

(gkr)

No comments:

Post a Comment