Monday, February 19, 2018

ራእይ የተጻፈበት ጊዜ

የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበት ዘመን እና ታሪካዊ ዳራው
ማንኛውንም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ለመረዳት፣ መጽሐፉ የተፃፈበትን ጊዜ እንዲሁም ታሪካዊ ሁኔታውን እና ባህላዊ አውዱን ማወቅ የመጀመሪያ መሰረት ነው፡፡ የራዕይን መጽሐፍ ለመረዳተም ይኸው መንገድ አብይ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ የራዕይ መጽሀፍ የተፃፈላቸው የመጀመሪያዎቹ ተቀባዮች በስደትና በመከራ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ የተጻፈላቸውም ለእምነታቸው ሲሉ እስከ ሞት ድረስ መከራ ሊቀበሉ ጥሪ ያላቸውን ሊያበረታታቸው፣ በዚያው ልክ ብድራታቸው እየቀረበ መሆኑን እና የነዚያ የሚያሳድዷቸው ሰዎች ጥፋትና ፍርድም በጣም በእርግጠኝነት ቅርብ መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን ሊያመለክታቸው ነው፡፡
እንደ ዮሐንስ ራእይ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻህፍት የተጻፉበትን ጊዜያት በተመለከተ ጥያቄው ሲነሳ፣ ማንም የቃሉ ተማሪ ሊያውቃቸውና ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ሁለት ጉዳዮች አሉ። እነርሱም፦ "ውጫዊ" እና "ውስጣዊ" የተባሉ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ቃሉ እንደሚያመለክተው ውጫዊ ማስረጃ የምንላቸው ከራሱ ከመጽሐፉ ውጭ ያሉ ታሪካዊ ጽሑፎችን ሲሆን ይኸውም፦ የጥንታዊ ጸሐፊያን ምስክርነት፣ ትምህርቶቻቸው፣ በቃልና በጽሁፍ የተላለፉና ሊቀርቡ የሚችሉ ጥቅሶቻቸው፣ ወይም ከሌሎች ጸሐፊያን የሚለዩበት አመለካከቶቻቸው፣ አና የመሳሰሉትን የሚመለከት ነው፡፡     
ያም ሆኖ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ጊዜ ያመለክታል በሚል በሊቃውንቱ ዘንድ ለመሞገቻነት የሚቀርበው ኢራንዮሳዊው ብቸኛው ውጫዊ ማስረጃ በኅይለኛው ሲያከራክር ኖሮአል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በርካታ ሊቃውንታዊ የሆኑ አመለካከቶች የቤተ ክርስቲያንን ትንቢታዊ አስተምህሮ በዓመታት ውስጥ ወዲያና ወዲህ ሲያዋዥቁ ኖረዋል፡፡
በርካታ ሊቃውንት በራዕይ መጽሐፍ የተገለጸው ታላቅ ጥፋት በሮም መንግስት ከተቀሰቀሱትና ከተቀነባበሩት በመንግስታዊ አዋጅ ከተከናወኑት ስደቶች አንዱን የሚመለከቱ መሆናቸውን ያምናሉ፡፡ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ የነበሩ ተብለው የሚጠቀሱ አስር ነገስታት ነበሩ፡፡ ከእነርሱም መካከል ሁለቱ ዮሐንስ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ይገዙ የነበሩ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ እነርሱም፡- ቄሳር ኔሮ ከ 54 -68 ዓ.ም ባለው ጊዜ የገዛ፣ እንዲሁም ዶሚኑስ ከ81-96 ዓ.ም ባለው ጊዜ የገዛው ናቸው፡፡
በርካታ የዘመኑ ሊቃውንት የዮሐንስ ራዕይ የተጻፈበት ዘመን ነው ብለው የሚቀበሉት የኋለኛውን ዘመን ይኸውም በ96 ዓ.ም ላይ የዶሚኖስን ዘመነ መንግስት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ብዙዎች የለም ቀድም ያለው የኔሮ ዘመነ መንግስት ጊዜ ነው ሲሉ ከ68 ዓ.ም በፊት ያለውን ጊዜ ጠቅሰው ይከራከራሉ፡፡ በርካታ ወንጌል አማኞች የሆኑ ኃላፋውያን (ፕሪቴሪስቶች) ራዕዩ የተጻፈው ቀደም ባለው ጊዜ ነው ብለው አቋም ይዘዋል፡፡ ምክንያቱም በዚያ ጊዜ ብቻ ነው በ70 ዓ.ም ላይ የሆነውንና የተፈጸመውን የኢየሩስአሌምን ጥፋትና ውድቀት አስቀድሞ በትንቢት መናገር የሚቻለው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ይህም አቋም መጽሐፉ ያንን ክስተት አስቀድሞ የተነበየ መሆኑን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ የሆነ ሆኖ ቀደም ያለውን ጊዜ የሚቀበሉ (ማለትም ከ69 ዓ.ም በፊት ተጽፎአል የሚሉ) ሁሉ ኃላፋውያን (ፕሪቴሪስት) ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ሆኖም ራዕዩ የተጻፈበትን ትክክለኛ ጊዜ መወሰን መጽሐፉን በአግባቡ ለመረዳት መሰረታዊ ነገር ነው ሲሉ ሊቃውንቱ ይከራከራሉ፡፡ ሁለቱም ጊዜያቶች ላይ የሚታይ መሳጭ የሆነ ክርክርና ሙግት ግን እስከ አሁን ድረስ እንደቀጠለ አለ፡፡
ኬኔት ኤል ጀንትሬይ ጄ. አር የተባሉ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሥነ መለኮት ምሁር ይህንን ክርክር አስመልክቶ በዶክትሬት ጥናታዊ የምርምር ስራቸው ውስጥ በስፋት በዳሰሱት በዘገባቸው እንዲህ ይጽፋሉ፡- "....በእጅጉ ወግ አጥባቂ የነበሩ ወገኖችን እስከ ተመለከተ ድረስ በ1800 አካባቢ ለአዲስ ኪዳን ቀኖና መጠናቀቅ ይሰጥ የነበረው የጊዜ ማእቀፍ በ50 ዓ.ም እና በ100 ዓ.ም መካከል ያለውን ጊዜ ይሸፍን ነበር፡፡ በ1850 ከቱቢንገን የፍልስፍና ትምህርት እና ከኤፍ ሲ  ባወር ተጽዕኖ የተነሳ ጊዜው ሰፋ ተደርጎ ከ50 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 160 ዓ.ም ድረስ ይሸፍናል የሚል ሃሳብ ተሰራጨ፡፡ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈበትን ጊዜ በተመለከተ በቱቢንገን በተደረገው የአመለካከት ለውጥ ላይ፣ 'በቱቢንገን ፍልስፍና ውስጥ ሊታሰብ የማይችል፣  እርስ በርሱ የሚጋጭ ትምህርት፣  ጳውሎስን ከአራት መልዕክቶች ጋር ብቻ ያስቀረ፣ ወይም እጅግ ዘመናዊ በሆነ አስተሳሰብ በአዶልፍ ሂልገንፊልድ እንደተፃፈው፣ ጳውሎስን ከሰባት መልፅክቶች ጋር ብቻ በማስቀረት፣ በርካታ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎችን ደግሞ የተጻፉበትን ዘመን ወደ ኋላ ላይ እንዲመጡ ያደረገ የአቡቀምሲሱንም መጽሐፍ በተመለከተም የመጽሐፉን ሐዋርያዊ ሥልጣን በማረጋገጥ የተፃፈበትን ጊዜ በተለምዶ ይታመን ከነበረው ይልቅ የክፍለ ዘመኑን ቀዳሚ ሩብ ይጠቅስ ነበር'" ይላሉ፡፡
   
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ያሉ በርካታ የስነ መለኮት ሊቃውንት ምድቦች የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ ከ 70 ዓ.ም በኋላ የተፃፈ ነው ብለው ቢያምኑም እንኳ፣ ጀንትሬይ ግን በርካታ የስነ መለኮት ሊቃውንት ከ 70 ዓ.ም በፊት ተጽፎአል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ደግሞ በዝርዝር ያስታውቃሉ፡፡ በዝርዝሩ ከተከታተት መካከል ግሬግ ኤል ባህንስን፣ አዳም ክላርክ፣ ኤፍ ደብልዩ ፌረር፣ ጆን ኤ.ቲ ሮቢንሰን፣ ሄንሪ ባርክሌይ ስዊት፣ ሚልተን ኤስ ቴሪ፣ ዊልሄልም ቦውሰት፣ ኤፍ ኤፍ ብሩስ፣ ሩዶልፍ ቡልትማን፣ ሳሙኤል ዴቪድሰን፣ አልፍሬድ ደድርሼይም፣ ጆሃን ኢክሆርን፣ ጆሴፍ ኤ. ፊትዘርሜየር፣ ጂ፡ቢ ላይትፉት፣ ሲ. ኤ.ኤፍ.ዲ ሞውል፣ እና አውግስጦስ ኤች ስትሮንግ የተባሉት ሊቃውንት ሰምቻቸው ከተጠቀሱት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጄንትሬይ በጠቅላላ 138 ሊቃውንትን ዋቢ አድርገው የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ከ70 ዓ.ም በፊት መጻፉን የሚያምኑና የሚቀበሉ ምሁራን ያሉ መሆናቸውን በጥናታቸው ይጠቅሳሉ፡፡
   
ስለዚህ ዝርዝር ሁለት ነገሮችን ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ፣ ዝርዝሩ ከየትኛውም የስነ መለኮት ጎራ የሚመደቡ ሊቃውንትን የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ዝርዝሩ ብቻውን በራሱ የራዕይ መፅሐፍ ቀደም ያለው ጊዜ ላይ እንደተፃፈ አያረጋግጥም፣ ሰዎችን በመቁጠር ላይ የተመሰረተ አመለካከት ብቻ መሆን ያለበትምና፡፡ ዝርዝሩ የሚያስታውቀው አንድ ነገር ግን አለ፣ ይኸውም "የራዕይ መጽሐፍ ቀደም ባለው ጊዜ ነው የተፃፈው" የሚለው አመለካከት ያለ ጥርጥር እንግዳ ወይም አዲስ አመለካከት አለመሆኑን ነው። እዚህ ላይ ስለ ኬኔት ኤል ጀንትሬይ ጄ. አር መጽሐፍ ተጽዕኖ ምሁራኑ የሰጡትን አስተያየት ጠቀስ አድርጌ ወደ ዋናው ክርክር ልለፍ።
(ጄይ ኢ. አዳምስ ስለዚህ መጽሐፍ "አንዳንዶቻችን ለዓመታት ስንጠብቀው የነበረ መጽሐፍ ይህ ነው! አሁን እዚህ አለ ልናጣጥመው እንችላለን፡፡ ሚስተር ጀንትሬይ ማንም ካደረገው በላይ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ የተፃፈው በ70 ዓ.ም ከሆነው የኢየሩሳሌም ውድመት በፊት ቀደም ብሎ እንደተፃፈ እውነታውን አሳማኝ በሆነ መልኩ አቅርቦልናል፡፡ ብዙዎች ሊያነቡት የሚባ ደግሞም በርካታ እይታዎችን ሊሰጠን የሚችል መጽሐፍ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በነገረ ፍጻሜ አመለካከታቸው ኃላፋዊ ያልሆኑ ጆርጅ ደብልዩ ናይት የተባሉም ሰው "ይህ የጀንትሬይ መጽሐፍ የራዕይ መጽሐፍ ቀደም ሲል እንደተፃፈ ባለው ጉዳይ ላይ ጥልቅና የሚደነቅ አገላለጽ አለው፡፡ መጽሐፉ ማስረጃዎቹን በመጽሐፉ ማለትም በራሱ በራእይ ውስጥ፣ እንዲሁም በጥንት ቤተክርስቲያን  ምንጮች ውስጥ፣ እያደረገ፣ ደግሞም የዚህን ዘመን እና ቀደም ያሉ ዘመናት የአዲስ ኪዳን ሊቃውንት የሆኑ ሙግቶችን እያቀረበና እየተነተነ ጥያቄውን ለመፍታት አንድም ድንጋይ ሳያስቀር መጽሐፉ የተጻፈበትን ትክክለኛ ጊዜ ያመለክታል፡፡" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  የበዛውን ዘመናቸውን የአልቦ ሺህ አመት አገዛዝ አስተምህሮን ሲከተሉና ከፊል ኃላፋዊ ሆነው የኖሩት፣ "The Las days according to Jesus" መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት፣ ከጥቂት አመታት በፊት በሞት የተለዩን አር. ሲ ሰፕሮውል የተባሉ ሊቅ ስለ ጄንትሬይ መጽሐፍ አስተያታቸውን ሲሰጡ፡- "እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ስራ" ይሉና "መጽሐፉ የተጻፈው ከ70 ዓ/ም በፊት ቀደም ባሉት ጊዜያት በቄሳር ኔሮ ዘመን ኢየሩሳሌም ሳትደመሰስ እና መቅደስዋ ገና ቆሞ እያለ ነው የሚለው የጄንትሬይ ሙግት ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ፣ እንግዲያውስ የራዕይ መጽሐፍ የተጻፈበትን ጊዜ በተመለከተ የሚደረስበት ድምዳሜ የመጽሐፉን ይዘት እና ትኩረቱን ለመረዳትና ለመተርጎም ባለን ዝግጅትና ጥረት ላይ ሰፊ የሆነ የክለሳ ሥራ መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉ ያክላሉ፡፡)
አሁን ወደአውራው ክርክር ባጭሩ ልለፍና ላጠቃልል
1.በኔሮ ዘመን በነበረው ስደት ጊዜ ተጽፏልን?
ይህንን ሃሳብ ለመደገፍ የተለያዩ ውስጣዊ ማስረጃዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነርሱም መካከል፦
፩. በርካታ “ቶሎ” እና “ቀርቦአል” የሚሉት ጊዜን አመልካች የሆኑ ቃላት በምንባባቱ (1÷ 1፤ 2÷ 16፤ 3÷ 11፤ 22÷ 6-20) ውስጥ ትርጉም ሊሰጡን የሚችሉት ሁነቶቹ በራእይ መጽሐፍ ከተገለጹት ምልክቶችና ምስሎች ጋር ተጋጥመው ፍጻሜያቸው ወደ ፊት ሊሆን ላለው ፍርድና ብድራት በጣም ሩቅ ያልሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ 
፪. ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ ቤተ መቅደሱ በኢየሩሳሌም ታይቷል፣ ተለክቷልም (11÷ 1-2)፡፡ ያኔ ገና አልፈረሰም ነበር ማለት ነው። ይኸውም ከ70 ዓ.ም በፊት መሆኑ ነው፡፡  ራዕዩ ከመጻፉ በፊት ቀደም ብሎ ቤተ መቅደሱ ፈርሶ ቢሆን ኖሮ ግን ያንን የሚገልጥ አንድ ሃሳብ በመጽሐፉ አንድ ቦታ ላይ መኖር ነበረበት፡፡ ከዚህም በላይ የፈራረሰ፣ ያበቃለትንና የሌለ ቤተ መቅደስ በራእይ መለካት ፈጽሞ ትርጉም የሌለው ጉዳይ ነው።
፫. በእስያ 7 አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የነበረበት ጊዜ በ60ዎቹ መጀመርያ ላይ ነበር፡፡ ራእዩ በ96 ዓ.ም ላይ ተጽፎ ቢሆን ኖሮ በዚያን ጊዜ በአካባቢው የነበሩት አብያተ ከርስቲያናት ከ7 በላይ ስለነበሩ የሁሉንም ዝርዝር በጠቀሰ ነበር።
፬. ራዕይ 2÷ 2 ሌሎች ሐዋርያት እንደነበሩ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ከዮሐንስ በቀር ሁሉም ከ70 ዓ.ም በፊት እንደሞቱ ይታመናል፡፡
፭. ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ አይሁዳዊ ከሆነው ተቃርኖ ጋር የነበረው ውጥረት ገና እንዳለ ነበር (ለምሳሌ 2÷ 9 ፤3÷ 9)፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ የተለወጠው ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም በሮማውያን ስትደመሰስ በመሆኑና ከ70 ዓ.ም በኋላ ይህ የማይታሰብ በመሆኑ ይሁዲነትና ሐይማኖታዊ መሰረቱ ከአቅመ ክርክር ውጭ ሆኖአል፡፡ ይሁዲነት ሕልውናው ቤተ መቅደሱ ቆሞ እስካለና የመስዋእት ስርአቱ እሰከተካሄደ ድረስ ብቻ ነበር። የአይሁዳዊነት ርዕሰ ጉዳይና ሌጋሲ ከ70 ዓ.ም በኋላ ምንም ትርጉም የለውም፣ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ የቀረ ምንም የአይሁድ ዘርም ሆነ ሐይማኖታዊ አገዛዝ የለም፡፡ የራእይ መጽሐፍ በ96 ዓ.ም ላይ ተጽፎአል የሚለው የሊቃውንቱ ድምድዳሜ ግን የመጽሐፉን ውበት ያጠፋዋል። ጥንታዊው የራዕይ መጽሐፍ ቅጅ ግን "ራዕዩ የተጻፈው ኔሮ ቄሳር በነበረበት ዘመን (ማለትም ከ68 ዓ.ም በፊት) ነው" ይላል፡፡
፯. ሌላው አስፈላጊ መከራከሪያ በራዕይ 17÷10 ላይ ራዕዩ በተጻፈበት ጊዜ ይገዛ ስለነበረው ንጉስ የሚናገረው ነው፡፡ “ሰባት ነገስታት…አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ የቀረውም ገና አልመጣም ሲመጣም ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል::" የዚህ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ራዕዩ ከመጻፉ በፊት አምስት የሮም መንግስታት በተፈራራቁነት እንደነበሩ እና እንደወደቁ ፣ ስድስተኛው ድግሞ ራዕዩ በተጻፈ ጊዜ ይገዛ የነበረ ንጉስ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ በሮም ግዛት ኔሮ ስድስተኛ ንጉስ ሆኖ የገዛ በመሆኑ ራእዩ የተጻፈው በዚያው በኔሮ ዘመነ መንግስት ውስጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡
፰. ሌላው ማረጋገጫ ኔሮ የተሰኘው ስያሜ 666 ከተሰኘውና በራእይ 13 ከተጠቀሰው የአውሬው ቁጥር ጋር ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በዚያን ዘመን የፊደል ገበታ (Alphabetical Symbols) ቁጥርን ወክለው ያገለግሉ እንደነበር የታወቃል። ጽኑ ሥደትና መከራ በነበረበት በዚያ ክፉ ዘመን ዮሐንስና ጠቅላላው ቤተ ክርስቲያን ያለ ጊዜው ራሳቸውንና ሌሎችን ለአደጋ ላለማጋለጥ በዋናነት ምልክቶችን  ለመግባቢያነት የመጠቀም ልምምድ ነበራቸው። በዚህ መሰረት  "ቄሳር ኔሮ" የሚለው ስያሜ በግሪኩ የፊደል ገበታ ቅደም ተከተል በሚሰጠው ቁጥር የሂሳብ ቀመር 666 የተሰኘውን ቁጥር በምልክትነት ያመጣል፣ ይኸውም፡-

      N = 50                 q = 100
      R = 200                o = 60
      W = 6   ደግሞም   r = 200
      N = 50  
           =306                    =360
(ስለዚህ 306 + 360= 666 እንደ ማለት ነው)፡፡

፱. በተጨማሪም የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያንን ዝምታ ዋቢ የሚያደርጉ አጥኝዎች የሚሰጡት አስገራሚና አወዛጋቢ ምክንያት "ቅዱሳን ተነጥቀው ሰለነበር ያንን ሁነትና ታሪክ ዘግቦ ለማስቀረት የቻለ ማንም አልነበረም" የሚል ነው። (ይህ "የመጀመርያው ክፍለ ዘመን አካላዊ ንጥቀት" ርዕሰ ጉዳይ ግን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በወጉ ጥናት ሊደርግበት ይገባል፤ ምናልባት እንድተባለው ክርስቲያኖች ያኔ ተነጥቀው ከምድር ላይ መወሰዳቸው እውነት ከሆነ የአመለካከት ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት አለኝ።)
2. በዶሚኑስ ዘመን ተጽፎአልን?
ለዚህም የሚቀርቡ ውጫዊ ማስረጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
፩. ነገስታትን ማምለክ /ለነገስታት መስገድና ማጠን/ በምዕራፍ 13 ያለው አይነት ስግደት ማለት ነው፣ እስከ ደሚኑስ ዘመነ መንግስት ድረስ በግድ አልተጫነም የሚለው ነው፡፡
፪. በራዕይ 13 የተፈወሰውም ለሞት የሆነው ቁስል በኔሮ ዘመን ታውጆ የነበረው የክርስቲያኖች ስደት በደሚኑስ ዘመን በባሰ መንገድ በመቀጣጠሉ ምክንያት ዶሚኑስ ሁለተኛው ኔሮ እየተባለ በመጠራቱና ዮሐንስን እና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁሉ ከቀድሞ በባሰ መንገድ ያሳደደ በመሆኑ ነው፡፡
፫. ሌላው መከራከሪያ የኔሮ ዘመን ስደት ከሮም ከተማ ያልዘለለ መሆኑ እና በደሚኑስ ዘመን የሆነው ሰደት ግን መላውን የሮምን ግዛቶች ያጥለቀለቀ መሆኑ ነው፡፡ ከሮም ከተማ ርቀው ይገኙ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ቱርክ ያሉት የኔሮን ሰደት ሳይሆን የሚያውቁትና የተለማመዱት የዶሚኑስን ሰደት ነው ብለው ያስባሉ፡፡
፬. በራዕይ 2 እና 3 የተጠቀሱት ሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት በአካባቢያቸው ከነበሩት ተቃዋሚዎች የሚደርስባቸው ስደት እንዳለ እንጂ ደብዳቤው በተጻፈላቸው ጊዜ ከገዢ ይቀበሉት የነበረ መከራ እንዳለ አልተገለጸም በማለት በኋላኛው ጊዜ ተጻፈ የሚለውን ይደግፋሉ፡፡
፭. የኋለኛው ዘመን ላይ እንደተጻፈ የሚቀርብ ውጫዊ ማስረጃ ጠንካራው መከራከሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያለ ምስክርነት ሆኖ የሚቀርበው እና በርካታ የቤተክርስቲያን አበው ዩሐንስ ራዕዩን በጻፈበት ጊዜ ዶሚኑስ ንጉሰ ነገስት ነበር የሚሉት በኢራኒዮስ ምስክርነት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ ኢራኒዮስ “ኑፋቄን በመቃወም” በተሰኘው መጽሐፉ እንዲህ የሚል ቃል አስፍሯል፡-
“እንግዲህ ይህ እንደዚህ ከሆነ፣ ይህም ቁጥር (666) በሁሉም መልካም የጥንት ቅጂዎች ውስጥ የሚገኝ ከሆነ፣ ዮሐንስንም ፊት ለፊት ያዩት ሰዎች ከመሰከሩ፣ እንዲሁም የአውሬው ስም ቁጥርም በግሪኩ የፊደል ገበታ ቀደም ተከተል መሰረት እንደሆነ አመክንዮ ካስተማረን፣ እንግዲያውስ የክርስቶስ ተቃዋሚ የተሰኘውን ስም በአወንታዊ መልኩ የመጥቀስን ኃላፊነት አንወስድም፤ ስሙም በዚህ በአሁኑ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ መገለጥ ያለበት መሆኑ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ፣ የአቡቀለምሲሱን ራዕይ ባስተላለፈልን በእርሱ በራሱ በተነገረን፡፡ የታየውም በእኛው ዘመን በደሚኖስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ ነው እንጂ፣ ከታየ በጣም ረጅም ጊዜ አላስቆጠረምና ነው፡፡”
ይህ የኢራኒዩስ አባባልግን በትርጉሙ ሲያከራክር ኖሯል፡፡ በዶሚኖስ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ላይ ምን ነበር የታየው? ዮሐንስ ያስተላለፈው ራዕይ? ወይስ በነዚያ በመሰከሩ ሰዎች ፊት ለፊት ታይቶ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ ራሱ? “የታየው” (ታይቶ የነበረው) የሚለው ቃል/ ሐረግ ምን አልባት የመጀመሪያውን ትርጉም ‹ታይቶ የነበረው እርሱ› የሚለውን አነባበብ የለወጠ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እውነት ከሆነ፣ እንዲያውስ ሊያረጋግጥ የሚችለው ዮሐንስ አቡቀለምሲሱን ቀደም ብሎ ጽፎ፣ የኖረው ግን እስከ ዶሚኑስ ዘመነ መንግስት ድረስ ነው የሚለውን ያረጋግጣል፡፡
ኢራኒዮስ፣ ራዕዩ የተጻፈው በኋለኛው ዘመን ነው የሚል ከሆነ፣ እንግዲያውስ የእርሱ ምስክርነት ትኩረት የሚሰጠው እና ክብደት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ኢራኒዮስ ሐዋርያው ዮሐንስን በአካል የሚያውቀውን ፖሊካርፕን በአካል ያውቀዋልና በዚህ ምክንያት ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት የታሰረበትን ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በርካታ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ኢራኒዮስን ተከትለው ራዕዩ የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ ተመሳሳይ የሆነን ጊዜ ያመለክታሉ፡፡
ነገር ግን ጥያቄው የኢራኒዮስ አባባል ትክክለኛ ትርጉም ይህ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡
የኢራኒዮስን አባባል ለመተርጎም በዶሚኖስ ዘመነ መንግስት የታየው ዮሐንስ ራሱ እንጂ ራዕዩ አይደለም በማለት ከፍ ሲል ዋቢ ያደረግኋቸው   የኃላፊያኑ አመለካከት ሊቂ ዶክተር ኬኔት ጄንትሬ   አንዳንዱ ቋንቋዊ፣ አንዳንዱ አውዳዊ፣ አንዳንዱ ደግሞ አመክኒዮአዊ የሆኑ ሰባት ጠንካራ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡
ለምሳሌ፡- ከኢራኒዮስ በተወሰደው ጽሁፍ የመጀመሪያው መስመር ላይ የራዕይ መጽሐፍ “በሁሉም… የጥንት ቅጂዎች” ሲል ይጠቅሳል፡፡ ይህም የሚያሳየው ይህ አረፍተ ነገር ከመጻፉ በፊት አስቀድሞ መጽሐፉ ለረጅም ጊዜ በዚያው ዘመን አካባቢ ነበር እንደ ማለት ነው፡፡ “የጥንት ቅጂዎች” ከነበሩ የመጀመሪያው ታዲያ የበለጠ ጥንታዊ አይሆንምን? ሆኖም በኢራኒዮስ ግምት የዶሚኑስ መንግስት ዘመን በጣም የጥንት ታሪክ ነው ተብሎ አይወሰድም፣ ምክንያቱም ስለ ጊዜው ሲናገር “በእኛው ዘመን” ብሏልና፡፡ ኢራኒዮስ በእርሱ ዘመን እንደተጻፈ ስለሚናገርለት ስለ መጀመሪያው መጽሐፍ እንዴት ጥንታዊ ቅጂ ብሎ መናገር ይቻለዋል? የዶሚኑስን ዘመነ መንግስት በመጥቀሱ ኢራኒዮስ የተናገረለት ዘመን ዮሐንስ አቡቀለምሲሳዊውን ራዕይ ካየበት ጊዜ ይልቅ ዮሐንስ በወንድሞቹ የታየ የመጨረሻ መሆኑን ነው፡፡
ሌላው የኢራንዩስ ምስክርነት ችግር የጽሁፎቹ ተዓማኒነት ችግር እንደሆነ በሰፊው ይታወቃል፡፡ የራዕይ መጽሐፍ ስለተጻፈበት ትክክለኛ ጊዜ በግልጽ ምንም ያለው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ ኢራንዩስ ከጽሁፎቹ በአንዱ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ቆይታ ሲነግረን እንኳ አገልግሎቱ የተጠናቀቀው በግምት በሃምሳ አመታት ውስጥ ነው በማለት ኢየሱስ የኖረው 50 ዓመት ያህል እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዚህ ምክንያት ጀንተሬይ ሲያጠቃልሉ “ራዕይ የተጻፈው በኋለኛው ጊዜ ላይ ነው ብሎ ኢራንዩስን ዋቢ ማድረግም ሆነ፣ በወፍራም ድምጸት ጮክ ብሎ "ኢራንዩስ እንዲህ ይላል" ማለት ተዓማኒነት ይጎድለዋል” ይላሉ፡፡
በመጨረሻም መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜ በመወሰን ላይ ማጠቃለያ አድርጌ ላቀርብ የምወደው ታዋቂው የሥነ አፈታት ሊቅ ሚልተን ቴሪ የተናገሩትን በመጥቀስ ነው፡- “የዮሐንስ አቡቀለምሲስ የተጻፈበትን ትክክለኛ ወቅት መቼ እንደሆነ በሚሰነዘሩ የክርክር ሃሳቦች ላይ እና ታሪካዊ አቋሞች ላይ እርግጠኛ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ይህ የትንቢት መጽሐፍ ከኢየሩሳሌም ውድቀት በፊት ቀደም ባለው ጊዜ የተጻፈ ከሆነ እንግዲያውስ በርካታ የሆኑ እነዚያ ከዚያች ከተማና ከውድቀትዋ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እያንዳንዳቸው ተጨባጭ በሆነ መልኩ ከትንቢቱ ፍጻሜ ጋር የተገናኙ መሆን አለባቸው፡፡ ነገር ግን በርካቶቹ እንደሚያምኑት በዶሚኑስ ዘመን ማብቂያ ላይ (በ96 ዓ.ም አካባቢ) ተጽፎ ከሆነ፣ እነዚያን ታሪካዊ ሁነቶች ለመተርጎምና ለማብራራት ሌላ የትርጉም መንገድ መፈለግ የግድ ይሆናል፡፡”
እነዚህ እንግዲህ ሁሉም ተርጓምያን ራእይን ለመተርጎም ከመነሳታቸው በፊት በመጀመርያ ሊያውቁአቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። አለበለዚያ በትምህርታቸው ቤተ ክርስቲያንን በዝባዝንኬ ተረት ተረት ይሞሏታል።
ይህ ጽሁፍ አገርኛውን የሥነ ፍጻሜ ጥናት ደርዝ ለማስያዝ መለስተኛ መነሻ እንዲሆን ጸሎቴ ነው። ለበለጠ ንባብ የምጠቁመው ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን መጻህፍት ነው፦
Gentry, Kenneth L., "Before Jerusalem Fell, Dating the Book of Reveltion," 1989. 
"The beest of Revelation," 1989.
Terrry Milton S., "Biblical Apocalyptics, A Study of The Most Notable Revelation of God and of Christ," Baker Book House, 1988.
Chilton, David., "The Days Of Vengeance, An Exposition of the Boook Of Revelation," Dominion Press Ft.Worth, Texas, 1987.
Arthur S. Peake, "The Revelation of John", Hartley Lectures (London: Joseph Johnson, 1919

Tuesday, February 6, 2018

ሐዋ 1፥ 9-11

በዚህ የጥናት ጽሁፍ  ስለ ጌታ ዳግመኛ መምጣት የተነገረውን የተስፋ ቃል ወንጌላዊው ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 9-11 ባለው ክፍል እንዴት እንደዘገበልን እንመልከታለን፡፡ ክፍሉም እንዲህ ይልል፡-
“ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።”

እንደ መግቢያ፦
መጻኢያን የሆኑ ተርጓሚዎች ይህንን ጥቅስ ይወዱታል፡፡ ምናልባትም የጌታን ምጽኣት ጨምሮ “ትንቢት ሁሉ ተፈጽሟል” ብለው የሚያምኑትን ኃላፋውያንን ለመቃወም ምቹ የሆነ ጥቅስ እንዳገኙ ያህልም ይሰማቸዋል፡፡ ለበርካቶች መጻኢያን ለሆኑ ተርጓሚዎች የህንን ክፍል ያኔ በ70 ዓ.ም ከሆነው ሁናቴ ጋር አጣጥመው በዚያው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተርጉሞ መረዳት ስለሚቸግራቸው፣ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባባት የተሰጠውን ቀጥተኛና ግልጹን ትምህርት ስተው፣ ይህንን ጥቅስ ብቻውን ለመተርጎም በሚያደርጉት ሙከራ፣ በትርጉማቸው ውስጥ የቀዋሚነት (Consistency) ስህተት እንደሚፈጽሙ አይታያቸውም።
ክፍሉን ተጠግተን ለማየት ስንሞክር ከዚህ ጥቅስ ጋር መነሳት ያለባቸውና ወደ አውዳዊው ማእቀፍ የሚመሩን መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳሉ ልብ እንበል፣ እነርሱም፡- ኢየሱስን ወደ ሰማይ ሲሄድ ያዩት እነማን ናቸው? የየትስ አገር ሰዎች ናቸው? የተሰጣቸው ተስፋስ ምንድን ነው? የሚሉት ናቸው፡፡ ይህንን ክፍል ለመረዳት የቃሉ ተማሪዎች በሆኑ ወገኖች ዘንድ የጋራ ስምምነት የሚሹና መንደርደሪያ የሆኑ ሁለት መሰረታዊ መርሆዎች አሉ።
የመጀመሪያው፦ ከዚህ በታች በዚህ ጥቅስ ላይ የሚቀረቡ ዝርዝር ሓሳቦች የተመሰረቱቱት፣ ይህ የንባብ ክፍል በ70 ዓ.ም ወደ ሆነው የክርስቶስ መምጣት ያመለክታል፤ አልያም በተቃራኒው የለም የንባብ ክፍሉ አመልካችነቱ አሁንም ገና ወደ ፊት ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቀው ምጽዓት ነው በሚል ከሁለት በአንዱ አማራጭ ስምምነት ላይ  ነው። አለበለዚያ ይህንን ክፍል ከነዚህ የጋራ መግባባት ከሚሹ አማራጮች በተለየ ማሰብና ለመተርጎም መታገል ፋይዳው አይታየኝም፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፦ የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ማለትም “የነገረ ፍጻሜ” አስተምህሮ የሚያጠነጥነው በትንቢቱ ባህርይ እና በያዘው የጊዜ ማዕቀፍ ዙርያ መሆኑን በግልጽ ማስተዋል ያስፈልጋል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለሆኑ ሰዎች የሥነ ፍታቴ መርህ እንደሚያስተምረው፣ “የትንቢቱን የጊዜ ማዕቀፍ” የሚናገር ሆኖ ለመረዳት ግልጽ ወይም ቀላል የሆነውና ፊት ለፊት የተገለጠው ንግግር፣ ስውር ወይም እጅግ ውስብስብ የሆነውን ትርጉም ማለትም፣ በዚህ ጉዳይ ተፈጥሮው “ቁሳዊም” ሆነ ወይም “ኢ ቁሳዊ የሆነውን” የሚገዛውና የሚመራው ሃሳብ መሆን አለበት። ከበርካታ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ሓሳቦችም መካከል ለመረዳት ቀላል የሆነው ወይም እጅግ ግልጽ የሆነው ማብራሪያ በሌላ አስተማማኝ ማስረጃ ውድቅ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ከሌሎች ሓሳቦች ሁሉ ይልቅ ተመራጭ መሆን የሚገባው እንደ ሆነ መስማማት ወሳኝ ነው። ወዲያውም ደግሞ ራሳችንን በነዚያ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በነበሩ ሰዎች ጫማ ውስጥ እያስገባን እና እየጠበቅን ያ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ በእውነትም ለእነርሱ ያላለውንና ያልተረዱትን ለእኛ እንደማይለን ማስታወስ ይገባናል፡፡
ቢያንስ እነዚህን ሁለት የጥናት መርሆዎች የምንስማማባቸው ከሆነ፣ እንግዲያውስ የጥቅሱን ሓሳብ ሳናሳክርና ሳናምታታ ትርጉማቸንን መቀጠል እንችላለን፡፡ ጥቅሱን በጥንቃቄ ለመተርጎም በአጭሩ ትኩረት ሰጥተን ማጥናት የሚያስፈልገን ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችች አሉ። እነርሱም፦
1ኛ) በደመና የመምጣት ትርጉምን ምንነት፣
2ኛ)እንዳያችሁት (በአዲሱ መደበኛ ትርጉም /አ.መ.ት/ "ያያችሁት ኢየሱስ")፣ የተሰኘው ቃል አገባብ፣ እና
3ኛ) እንዲሁ፣ (አ.መ.ት "በዚሁ ሁኔታ") የሚለው ቃል ጠቀሜታ፣ የሚሉት ናቸው፡፡

ይህንን ክፍል የማብራራቱ ዋናው ዓላማዬ በወንጌላቱም ሆነ በተቀሩት የሐዋርያቱ መልዕክቶች ስለ ምጽዓቱ የተነገረውን የክርስቶስን ቃል በማክበርና አውዱን በመጠበቅ፣ እነዚህ ነጫጩን ልብስ የለበሱ ሰማያዊ አካላት በእርገቱ ወቅት ስለ መጻኢው የአመጣጡ ሁናቴ እንዴት እንደተናገሩ ማሳየት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይህንን አንድ ጥቅስ መሰረት በማድረግ በምንባቡ ላይ የመጻዒያን ወይም የሺህ ዓመት አማኞች የሚሰጡት የተለመደው  የትርጉም ዘይቤ ምን ያህል ቀዋሚነት የሌለው እና እርስ በርሱ የሚቃረን መሆኑንም ማመልከት ይሆናል፡፡ ከዚህም ጋር አያይዘን እነዚሁ ተርጓሚዎች ከሌሎቹ ምጽዓቱን አመልካች ከሆኑ ምንባባት ጋር ምን ያህል በትርጉማቸው የማይስማሙ መሆኑንም ጨምረን እናያለን፡፡ ይህንንም ለማድረግና ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን ሦስት ነጥቦች ዘርዝሮ ለመመልከት እንዲረዳን የንባብ ክፍሉን ከተለያዩ ሰባት ዐውዳዊ ነጥቦች አንጻር በአጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
1ኛ.ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንጻር፦
ይህ ምንባብ ዕረገቱንና የመመለሱን ተስፋ የያዘ ነው። ዕርገቱ በቁጥር አስራ አንድ የሚሆኑ አባላትን ለያዘ ቡድን፣ አካባቢያዊ ሁኔታውም በኢየሩሳሌም ከተማ አቅራቢያ ባለ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ በወቅቱ በነበሩ “የገሊላ ሰዎች” በተባሉ ግለሰቦች ፊት የተፈጸመ ነበር (ሐዋ 1÷ 12)፡፡ እነርሱም አስራ አንዱ ደቀ መዛሙርትና ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ናቸው፡፡ “እንዲሁ” የሚለው ንፅፅራዊ ቃል “ግላዊና፣ አካባቢያዊ ሆኖ በእርገቱ ወቅት እዚያው ለነበሩ ለነዚያው አሥራ አንድ ሰዎች የሚሆን የክርስቶስ መመለስ ነበር”፣ ሲሉ በታወቀውና Parousia በተሰኘው መጽሐፋቸው በገጽ 74 ላይ ራስል ያስረዳሉ፡፡ ጥቅሱ በውስጡ የመመለሻውን ጊዜ ጠቋሚ የሆነ ሃሳብ ባይገኝበትም ቅሉ፣ ምጽዓቱን ግን በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ በዚያው ለነበሩና ለእነዚያው እርገቱን ለተመለከቱ የገሊላ ሰዎች ያደርገዋል፡፡ ይህም መጻዒ ሆኖ ወደ ፊት ከሚጠበቀውና ተዳሳሽ ሆኖ በሚታይ መልኩ ይሆናል ከሚባለው ቁሳዊ የምጽዓት አስተሳሰብ ጋር በጽኑ ይቃረናል፤ ምክንያቱም ለዚህ አንድ ጥቅስ የሚሰጥ ትርጉም ብቻውን አጠቃላዩን የዳግመኛ ምጽአቱን ትምህርት እየወሰነ፣ በራሱ ዳግመኛ ምጽዓቱን ከሚያስተምሩ ከሌሎች ምንባባት ጋር የሚጣረስ ሊሆን አይገባውምና ነው፡፡
በቃሉ የምንመለከተው፣ አዲስ ኪዳን የሚያስተምረውና ሐዋርያቱ ሲጠብቁት የነበሩት የጌታ ምጽዓት አንድ ብቻ ነው። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተመሰረተባቸው የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባት በጠቅላላ ነገረ ፍጻሜን ባጠኑ ምሁራን በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ሊከፈሉ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ እነርሱም “ጊዜውን አመልካች የሆኑ አጠቃላይ የንባብ ክፍሎች” /Gneric passages/  እና “ሊሆን ያለውን አመልካች የሆኑ የንባብ ክፍሎች” /Mellonic passages/ ይሰኛሉ። በጉዳዩ ላይ ኮስተር ያለ ንባብ ማድረግ ለምትሹ አንባቢዎቼ እነሆ ጥቅሶቹ፦
[“ጊዜውን አመልካች የሆኑ አጠቃላይ የንባብ ክፍሎች” /Gneric passages/ የሚከተሉት ናቸው፡- ማቴ 10÷ 22-23፤ 13÷ 39-43፣ በተለይ ቁ 40ና 43 (ከዳን 12÷ 3 የተወሰደ)፤ ማቴ 24÷ 14-15 (ከዳን 9÷ 23 ጋረ የሚነጻጸር)፣ 30-31 (ከዳን 7÷ 13ና 22 ጋር የሚነጻጸር)፣ ቁ 34፤ ማቴ 26÷ 64፤ ዮሐ 21÷ 22፤ ሮሜ 13÷ 11-12፤ ፊል 4÷ 5 (ከማቴ 4÷ 17 ጋር የሚነጻጸር፣ ማቴ 3÷2 ላይ ያለውንስ እንዴት ትረዱታላችሁ?)፤ 1ጢሞ 6÷ 13-14 (ከቲቶ 2÷ 13 እና ከ1ቆሮ 1÷ 2-8 ጋር የሚነጻጸር)፤ ዕብ 10÷ 25፣ 37፤ ያዕ 5÷ 1-9፤ 1ጴጥ 1÷ 5፣ 9፤ 4÷ 7፣ 12፣ 17፤ 2ጴጥ 1÷ 19፤ 2÷ 3፤ 1ዮሐ 2÷ 18 (ከማቴ 24÷ 23-34 ጋር የሚነጻጸር) 2÷ 28፤ 4÷ 3 (ከ2ተሰ 2÷ 1-3 እና 7 ጋር የሚነጻጸር)፤ ራዕ 1÷ 1፣ 3፤ 2÷ 25፤ 3÷ 11 እና 22÷ 7፣ 12 እና 20፤ 11÷ 18፤ 14÷ 7 (ከ1ጴጥ 4÷ 17 ጋር የሚነጻጸር) ራዕ 22÷ 6፣ 10 (ከዳን 12÷ 4 ጋር የሚነጻጸር) ናቸው፡፡  “ሊሆን ያለውን አመልካች የሆኑ የንባብ ክፍሎች” /Mellonic passages/ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡- ማቴ 16÷ 22-28፤ ሐዋ 17÷ 31፤ 24÷ 15ና 25፤ ሮሜ 4÷ 23-24፤ ቆላ 2÷ 16-17፤ 1ጢሞ 4÷ 8፤ 6÷ 19፤ 2ጢሞ 4÷ 1፤ ዕብ 1÷ 14፤ 2÷ 5፤ 9÷ 11፤ 10÷ 1፤ 13÷ 14፤ 1ጴጥ 5÷ 1፤ ራዕ 12÷ 5 ናቸው፡፡]
ስለዚህም ባነሳነው አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመስርቶ ሁሉም የቅዱሳት መጻሕፈት ምንባባት የፍጻሜ ቀነ ቀጠሮውንና ጊዜውን ወስነው የሚመሰክሩለትን አንዱን ዳግመኛ ምጽዓት ከአውዱ ነጥሎ በመተርጎም ሁለትና ሶስት ማድረግ ደግሞ ለራስ መሳትና ሌሎችንም ማሳሳት ይሆናል፡፡
ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ለመመልከት ይህ የሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 1÷ 9-11 ያለው ቃል የኢየሱስን መመለሻ ጊዜ በተመለከተ በነዚያ ነጫጩን ልብስ በለበሱ ሁለት ሰዎች በውስጡ የተነገረበት ምንም የያዘው ዘገባ እንደሌለበት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጥቅስ ከላይ በሁለት ምድብ በዝርዝር ከቀረቡት የንባብ ክፍሎች በአንዳቸውም ውስጥ የማይመደብ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ኢየስሱስ የሚመለስበትን ጊዜ ጠቋሚ የሆኑ በርካታ የአዲስ ኪዳን የንብብ ክፍሎች ያሉ እስከ ሆነ ድረስ፣ ከመነሻው በዚህ አንድ ምንባብ ትርጉም ወይም ባህርይ ላይ ክርክር ከመክፈት ይልቅ፣ እነዚያን ለመረዳት ግልጽ ወይም ቀላል ሆነው የቀረቡትንና ፊት ለፊት በተገለጠ ንግግር ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ የሚያስተምሩትን ሌሎች የምጽአቱ ማጣቀሻ የሆኑ የንባብ ክፍሎችን በማስተዋል ማማከሩ እጅግ የተሻለው መፍትሄ ነው፡፡
እነዚህ ነጫጩን ልበስ የለበሱ ሰማያዊ አካላት ለደቀ መዛሙርቱ "ይመጣል" ሲሉ የነገሩአቸው ስለ ኢየሱስ መመለስ ነው (ቁ.11)። ይህ የሚያመለክተው የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽአት ነው። ይህ ይመለሳል የሚለው ተስፋም ለደቀ መዛሙርቱ አዲስና እንግዳ ዜና አይደለም። በዚህ አንድ ጥቅሰ ግን ምጽአቱን በተመለከተ ያልተለመደ አዲስ ነገር ቢኖር የምጽአቱ አመልካች በሆኑ በሌሎቹ በርካታ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች እንዳለው አይነት የመመለሻ ጊዜውን አመልካች የሆነ ግልጽ ንግግር አለመጠቀሱ ነው። ኢየሱስም ደቀመዛሙርቱን እንደሚመለስ እየደጋገመ አስተምሮአቸዋል፣ ነገር ግን በርካታ ክርስቲያኖች የሚስቱት ጉዳይ ለደቀ መዛሙርቱ ጊዜውን ወስኖ መቼ እንደሚመለስ የነገራቸው መሆኑን አለማስተዋላቸው ነው።
ስለዚህም ይህንን ስለ ምጽዓቱ የሚናገር አንድ ጥቅስ ስለ ምጽዓቱ በግልጽ እንደሚናገሩ በሚታወቁ ሌሎች ብዝሃናት ጥቅሶች ስር አስገዝቶ ማጥናቱ የግድ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ መጠናትና መተርጎም ያለበትም ደግሞ፣ በሌሎች ስለምጽዓቱ በተነገሩና የምጽዓቱን ጊዜ አመልካች በሆኑ የንባብ ክፍሎች (Gneric passages) እንዲሁም ሊሆን ያለውን አመልካች በሆኑ የንባብ ክፍሎች (Mellonic passages) መነጽር ነው፡፡
ሐዋ 1÷ 11 “ለዳግመኛ ምጽዓት የሚጠቀሱ ሌሎች ምንባባት ሁሉ በያዙት የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ተገዝቶ መያዝ ያለበት ጥቅስ ነው” ሲሉ ታዋቂው የሥነ ፍታቴ ሊቅ ሚልተን ቴሪ ያስተምራሉ፡፡ ቴሪ፣ ጥቅሱ የያዘው ተስፋ ለእነዚያ ለመጀመሪያዎቹ ክፍለ ዘመን ሰዎች የተሰጠውን ተስፋ ነበር (ማቴ 16÷ 27-28፤ 24÷ 3፣ 27፣ 30፣ 34)፡፡ የተስፋውም ፍጻሜ ያኔውኑ ለእነርሱ ቅርብ ወይም በደጅ ነበር (ሮሜ 13÷ 11፣ 12፤ ፊል 4÷ 5፤ ያዕ 5÷ 8፤ 1ጴጥ÷ 4 7፤ ራዕ 1÷ 3፤ 22÷ 6፣ 10፣ 12)፡፡ ሙሉ እና ፍጹም በሆነ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ባለው ስምምነት ያው የተሰቀለው እና ያረገው፣ ደግሞም እንዲሁ ወይም ባያችሁት አይነት፣ ሆኖም ተዳሳሽ በሆነ ቁሳዊ ሁኔታ ሳይታይ፣ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ሃልዎቱ እየታወቀ በደመና ይመጣል የተባለው ኢየሱስ ራሱ ነበር፣ በማለት ያብራራሉ፡፡
ሐዋርያት ይጠብቁት የነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ዳግመኛ ምጽዓት አንድ ብቻ ከሆነ፣ ያም ምጽዓት ይፈጸማል ተብሎ የሚታመነው አንዴ ብቻ ነው፡፡ የፍጻሜውም የጊዜ ማዕቀፍ እንደሚፈጸምላቸው ተስፋ ከተገባላቸው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ወቅታዊ አውድ የሚዘል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ከዚያ የጊዜ ማዕቀፍ ወጥቶ ጉዳዩን መለጠጥና ወደ ሌላ ሩቅ ዘመን ማለትም እኛ ወዳለንበት ሁለት ሺህ እና ከዚህም በኋላ ገና ሦስትና አራት ሺህ ዘመን አሳልፎ ፍጻሜውን መጠባበቅ የሌለ ነገር መጠበቅ ይሆንብናል፡፡
ክርስቲያኖች ሁሉ በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዐት ያምናሉ ብዬ አስባለሁ። የዳግመኛ ምጽዐቱን እውነታ መካድ በሁሉም ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ እንደሚታመነው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነትና በመንፈስ ቅዱስ መሰጠቱን እንደመካድ ይቆጠራል። በዚህ መቼም እንደምንስማማ ይመስለኛል። ዳግመኛ ምጽዓቱ የሚፈጸምበ ጊዜ እውነታም ቢሆን ልክ እንደ ዳግመኛ ምጽዓቱ ሁሉ ግልጽ መሆኑን አምናለሁ። ይህንን ለዳግመኛ ምጽዓቱ በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠውን የጊዜ አገላለጽ መካድም ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የተሰጡ መሆናቸውን መካድ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህስ ያስማማናል?
2ኛ ከአቡቀለምሲሳዊ የሥነ ፍታቴ መርህ አንጻር፦
በብሉይ ኪዳን "ደመና" የተሰኘውን ጽንሰ ሓሳብ ባልተረዳንበት ሁኔታ ይህንን ጥቅሰ ልንተረጉም ስንነሳ መሳሳታችን አይቀርም። ኢየሱስ በደመና ተሰውሮ የሄደበትም ነገር ፍጥረታዊ የሆነው ነጭ ጥጥ መሳይ የደመና ክምር ነው እንደማንል ተስፋ አደርጋለሁ። ሉቃስ "ደመና ከአይናቸው ሰውራ ተቀበለችው" ብሎ ሲጽፍ በዚያ የነበሩት የአይን ምስክሮች የሚያውቁት አንድ ነገር ወደ እግዚአብሔር መወሰዱን ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን ሲገልጥ መገለጡን አዘውትሮ በደመና ያደርገው እንደነበር፣ ይኸውም የእርሱ ሀልዎት እንደሆነ ከቅዱሳት መጻህፍቶቻቸው ያስተውላሉ (ዘጸ 16÷ 10፤ 19÷ 9፤ 34÷ 5፤ ዘሌ 16÷ 2፤ ዘሁ 11÷ 25)።
ብሉይ ኪዳንን በወጉ ያልተረዳ ሰው አዲስ ኪዳንን መረዳት አይችልም የሚል እምነት አለኝ። ሁሉም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች አንባቢዎቻቸው ብሉይ ኪዳንን የሚያውቁ እንደሆኑ ታሳቢ አድርገው ጽፈውላቸዋል ብዬም አስባለሁ። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱሳችንን የመጀመሪያውን ሶስት አራተኛ ክፍል ካልተረዳን የመጨረሻውን አንድ አራተኛ መረዳት ከቶ አንችልም። እንግዲህ የእግዚአብሔርን በደመና መምጣት በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ያለውን አገባብ ብንመረምር በፍርድ የሚሆን መለታኮዊ ሕልዎት ምልክት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ ኢሳይያስ በትንቢቱ ይህንን በደመና የሆነ የእግዚአብሔርን መምጣት አስመልክቶ ሲናገር “ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል” (ኢሳ 19÷ 1) ይላል፡፡  ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ይዕብራውያንን ቅዱሳት መጻህፍት በሚገባ ካላወቅን በአዲስ ኪዳን ግራ ልንጋባ እንችላለን። አዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ዳግመኛ ምጽዐት በሚናገርበት ጊዜ በብሉይ ኪዳን ባለው የእግዚአብሔር ተደጋጋሚ አመጣጥ ዓይነት ያስቀምጠዋል።
እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ለመፍረድ በደመና እየመጣ ነበር፣ ነገር ግን የደመናው ተፈጥሮ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ተዳሳሽ በሆነና በሚታይ አካል ወይም በነባራዊው ቁሳዊ ደመና ላይ ተፈናጦ ደመናን እየጋለበና እየበረረ እየመጣ አልነበረም፡፡ ይህ የእግዚአብሔር አመጣጥ በግልጽ መንፈሳዊና ትዕምርታዊ ሆኖ ነገር ግን ትክክለኛ የጌታ ምጽዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው። እግዚአብሔር በግብጽ ላይ በፍርድ የመጣበትን ሁኔታ ስንመረምር ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 20 እንደምንረዳው ግብጽን ለመቅጣት የቁጣው መሳሪያ አድርጎ የተጠቀመው አሶርን ነበር። ስለዚህ ˝እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ይመጣል………. ግብጽም…….. በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል” ይላል። ወደ ግብጽ የመጣው በፍርድ ነበር። ህልዎቱም በፍርዱ ይታወቃል። በግልጽ በአካል ያኔ የመጣው ግን አሶር ነበር። ይህ አይነቱ የእግዚአብሔር የፍርድ አመጣጥ ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን አቡቀለምሲሳዊ በሆነ የንግግር ዘይቤ ሲገለጥ ቃሉ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ለመመልከት ደመና የነበረውን አገባብ በሚከተሉት ክፍሎች ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ መዝ 18÷ 8 ጀምሮ፤ 97÷ 2፤ 104÷ 3፤ ኢዩ 2÷ 1፣ 2፤ ናሆም 1÷ 2 ጀምሮ፤ ሶፎ 1÷ 14፣ 15 ተመልከት፡፡
በመላው ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር በደመና መምጣት መለኮታዊ ሕልዎቱን እንዲሁም ሕዝቡን ለማዳን እና በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ “እንዲሁ ይመጣል” የተሰኘው መግለጫ ደመናውን የሚያመለክት ነው ቢባል እንኳ፣ እንግዲያውስ አሳማኝ ለሆነና ቀዋሚነት ላለው ትርጉም፣ በቅዱሳት መጻህፍት በደመና መምጣት ማለት ምን እንደሆነ ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልገናል፡፡ ኢየሱስን በእርገቱ ጊዜ “ደመና ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው”፣ ሲል ስለ መምጣቱ ግን “ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል”  ነው የተባለው እንጂ በዚህ ጥቅስ አካሄዱ ላይ ካልሆነ በቀር አመጣጡ ላይ ደመና አለመጠቀሱን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡   
በሌሎች በርካታ የምጽዓቱ ምስክሮች በሆኑ የአዲስ ኪዳን ምንባባት የተሰጠውን ተስፋ ታሪካዊ ፍጻሜ ብንመለከት፣ በ70 ዓ.ም በእስራኤል ላይ የሆነው ፍርድና የክርስቶስ መምጣት በተጨባጩ ተዳሳሽ ደመናም ሆነ ወይም በተዳሳሽ አካል የሆነ እንዳልሆነ እናስተውላለን፡፡ ይህም የ70ው ዓ.ም ምጽዓት ጭምር በብሉይ ኪዳን እንደተገለጹት ተደጋጋሚ የእግዚአብሔር መምጣቶች መንፈሳዊ መምጣት ሆኖ፣ ነገር ግን እውነተኛና ተጨባጭ ነበር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ብሉይ ኪዳን የማያውቀውን አይነት የመለኮት አመጣጥ ሊመጣ አልሄደም። የልጁ አመጣጥ ልክ እንደ አባቱ ነው።  “የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል” (ማቴ 24÷ 30)፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ መስተዋል የሚገባው አንድ እውነት “የሰው ልጅ ምልክት” የተባለው ˝በሰማይ˝ ማለትም በመንፈሳዊው ዓለም እንጂ በምድር አለመሆኑን ነው፣ ደመናውም ቢሆን የሰማይ ደመና ነው እንጂ ቁሳዊው የዝናብ ወይም የነፋስ ደመና አይደለም።
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ ምንባብ የተብራራው የክርስቶስ መምጣት ከብሉይ ኪዳን እንደ ተወሰዱትና የእግዚአብሔርን በደመና መምጣት እንደሚገልጹ ጥቅሶች አገላለጽ ቀጥተኛ (ትክክለኛ) እንደሆነ እንጂ፣ አካላዊና ተዳሳሽ እንዳልሆነ ይስማማሉ፣ ይኸውም ደግሞ የሚፈጸመው በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ፣ ማለትም የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት ነው (ማቴ 24÷ 34)፡፡ ሊኖረን የሚችለው የኢየሱስ በደመና መምጣት ቁሳዊ ያልሆነ፣ ይልቁንም መንፈሳዊ፣ ትክክለኛና እውነተኛ የሆነ፣ ያ መምጣት ራሱም ሆነ ደመናው ተዳሳሽ መሆን ሳያስፈልጋቸው የሚሆን መምጣት ብቻ እንደሆነ ስንስማማ እነዚህ ነገሮች እውነት ይሆኑልናል፡፡ ከዛ ያላነሰ አስፈላጊነት ያለው ጉዳይ ደግሞ ይህ ቁሳዊ ያልሆነ መምጣት በሁሉም የእስራኤል ነገዶች የሚታይ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡
     3ኛ.በፍጥረታዊውና በመንፈሳዊው መካከል ካለው ጉልህ ልዩነት አንጻር፦
ይህ አይነቱ ስጋዊ ወይም ቁሳዊ የሆነና በሚታይና ተዳሳሽ በሆነ መልኩ የሚሆን "የክርስቶስ  መመለስ"  ጉዳይ በየዘመናቱ ሲያከራክር የኖረ አሳብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ እንዲህ ያለው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በተለይም ወንጌላዊ የሆነውን ትምህርተ ክርስቶስን ለበርካታ መቃረኖች ይዳርጋል፡፡ በፍጥረታዊውና በመንፈሳዊው አካል መካከል ወይም በመሬታዊውና በሰማያዊው መልክ መካከል ግልጽ ልዩነት ተደርጓልና (1ቆሮ 15፥ 40-49)፡፡ ኢየሱስ ቅድመ ዓለም እንደ ቃል (በግሪኩ Logos) በእግዚአብሔር ዘንድ እግዚአብሔር ሆኖ በመንፈሳዊ ሁኔታ ከአባቱ ጋር በዘላለማዊነቱ አብሮ ነበር፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” (ዮሐ 1÷ 1-2) ይላልና፡፡
በቁጥር 2 ላይ “ይህ” የሚለውን (KJV ‘The same’) ትርጉሙ “ይህ ራሱ” ወይም “ያው እርሱ ራሱ ” ማለት ነው፡፡ እርሱም ክርስቶስ ነው፡፡ በቁጥር 14 እንዲህ ይለናል “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን”፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በምድር ላይ ከመሆኑ በፊት እንደ ቃል ከነበረው የዘላለም ማንነትና መንፈሳዊ መልክ ሥጋ ወደ መሆን ተዳሳሽ መልክ በገባ ጊዜ አሁንም ያው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነበር፡፡ እንግዲያውስ በእርገቱ ጊዜ እንደ ቃል ወደ ኖረበት መንፈሳዊ ኢ-ተዳሳሽ ሁኔታ ተመልሷል (ራዕ 19÷ 3)፣ ሆኖም አሁንም ያው ራሱ ኢየሱስ ነው፡፡ ይኸውም የተሰቀለውና ከሙታን የተነሳው፣ በሐዋ 1÷ 11 አጋማሽ ላይም በደመና ወደ ሰማይ ያረገው ያው ራሱ ኢየሱስ ነው፡፡
ከፍ ሲል ከአቡቀለምሲሳዊ የሥነ ፍታቴ መርህ አንጻር ጉዳዩን ለማየት እንደተሞከረው፣ በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ፍርድና ጥፋት የሆነው የክርስቶስ መምጣት፣ ፍጥረታዊና ቁሳዊ በሆነው ተዳሳሽ ደመናም ሆነ ወይም በተዳሳሽ አካል የሆነ እንዳልሆነ ሁሉ፤ ይህም ሀናታ ኢየሱስ ያው ራሱ ኢየሱስ እንዲሆን ተዳሳሽ አካላዊ መሆን እንደማያስፈልገው በግልጽ የሳየናል፡፡ ጳውሎስም “ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” (2ቆሮ 5÷ 16) ይላል፡፡
መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን (1ቆሮ 2÷ 13)፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምሀረት ለመረዳትና በዚያው መረዳት መናገር እንዲቻለን መንፈሳዊ እይታ ያስፈልገናል፡፡  “የመረዳታችን ዐይኖች” መከፈት አለባቸው (አፌ 1÷ 18)፡፡ በእርግጥ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሰዎች የሚመክራቸው የመረዳት ዓይኖቻቸውን ተጠቅመው “የመጠራታቸውን ተስፋ እንዲያውቁ” ነው፡፡ “ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን…ታውቁ ዘንድ ነው”  (ኤፌ 1÷ 18)፡፡ ይህንን ስናደርግ ተዳሳሽ ከሆነውና በአካላዊ አይን ከሚታየው ቁሳዊው በላይ መንፈሳዊ የሆነውንና የበለጠውን ማየት እንጀምራለን፡፡
ይህ እውነታ በሞት ከተለዩ በኋላ በተዳሳሽ ሥጋ ወይም በተዳሳሽ አካል የሌሉ ከሆኑ ሰዎችም አንጻር ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ባለጸጋው ሰው እና አላዛር ሁለቱም በሞቱ እና አንዱ ወደ ሲኦል አንዱም ወደ ገነት በተወሰዱ ጊዜ በተዳሳሹ አካላዊ ማንነታቸው አልነበሩም፤ ሆኖም በተለየ መልክና ሁኔታ የነበሩ እነዚያው ራሳቸው ሰዎቹ ነበሩ፣ (ሉቃስ 16÷ 19-23)፡፡ አንዱ ሌላውን ለማወቅ የሚችሉና መነጋገር መገናኘት የሚችሉ ነበሩ፡፡ ሥቃይን ወይንም ደስታን ሊለማመዱ የሚችሉ፣ የዳኑም ይሁኑ አይሁኑ በምድር ላይ የነበራቸውን የሕይወት ልምምድ ማስታወስ የሚችሉ ነበሩ፡፡ እርስ በርሳቸው እንኳ አንዱ ሌላውን የሚያውቁና መነጋገር የሚችሉ፣ የገዛ ራሳቸውን ማንነትም ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩ፣ ሆኖም በተወሰነ መልኩ ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው ለማለፍና ለመሻገር የተገደቡ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ያው ራሱን ሰውየውን ለመሆን ተዳሳሽ ወይም አካላዊ መሆን የግድ አይደለም፡፡
የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽዓት በአግባቡ መረዳት ካለብን የግድ ይህንን ማስተዋል ይኖርብናል። ተስፋ የተገባው ዳግመኛ ምጽዓቱ ቁሳዊና ተዳሳሽ አልነበረምና። የአመጣጡም ዘይቤ በብሉይ ኪዳን በተደጋጋሚ ሲከናወን እንደነበረው ልክ እንደ አባቱ ነው። የመጣውም በፍርድ ነው። ይኸውም ዳግመኛ ምጽዓት በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ፍርድን ለማስተላለፍና ኢየሩሳሌምን ፈጽሞ ለማውደም በ70 ዓ. ም ላይ የሮማውያንን ሰራዊት ያዘመተበት ነው። 
4ኛ.ከሰዋሰዋዊ የቋንቋ አጠቃቀም ሕግ አንጻር፦
“እንዲሁ” የሚለው ተሰውሮ የሄደበትን ደመናውን ሳይሆን ይልቁንም “ይመጣል” የሚለውን ሓሳብ የሚገልጥ ቃል ነው፡፡ ስለዚህ “እንዲሁ” የሚለውን “ልክ እንደዚሁ” ወይም “በዚሁ አይነት ሁኔታ” ብሎ ቃሉ የማይለውንና ያልተጻፈውን በማንበብ ክርስቶስ በምን አይነት መልኩ እንደሚመጣ ወይም እንደሚገለጥ አመልካች ቃል አድርጎ ማየት የቋንቋን ሰዋሰዋዊ ሕግ አሳስቶ መጠቀም ይሆናል፡፡ “He came in like manner’’ የሚለው የእንግሊዝኛው ትርጉም በተለያዩ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደሚከተለው የነበባል፣ ለምሳሌ፡- የ1962 ትርጉም፣ “እንዲሁ ይመጣል”፤ አዲሱ ትርጉም፣ “ባያችሁት ዓይነት ይመጣል”፤ አ.መ.ት፣ “እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል” ሕያው ቃል፣ “እንዳያችሁት እንደዚሁ ደግሞ ተመልሶ ይመጣል፤ አይቀርም” ይላሉ፡፡
በሰዋሰዋዊ እና በአውዳዊ አነጋገር ይህ “እንዲሁ” የሚለው ቃል ወይም “እንዳያችሁት፣ በዚህ ሁኔታ” የሚለው ሃረግ የሚያመለክተው በደመና ለማረጉ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም “እንዲሁ” ወይም “እንዳያችሁት፣ በዚህ ሁኔታ” ይመለሳል ማለት፣ ይመለሳል ማለት እንጂ በሄደበት አይነት ደመና ይመለሳል እንደ ማለት አይደለም፡፡ ያም ቢሆን እንኳ በክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ቁሳዊ የሆነ ተዳሳሽ ደመና መኖሩ ግን ግዴታ እንዳልሆነ በባለፈው ጽሁፌ ተመልክተናል፡፡
ሐዋ 1÷ 9-11 ስለ ኢየሱስ ስጋዊ አካል የሚሰጠን ዘገባ የለውም፣ በመሆኑም መጻዒያኑ አጽንኦት ሰጥተው ኢየሱስ በተዳሳሽ አካል ይመለሳል ሲሉ ማረጋገጫ ለማቅረብ በሚሞክሩበት በዚህ በቁ. 11 ያለው “እንዲሁ” የሚለው ቃል ወይም “እንዳያችሁት፣ በዚህ ሁኔታ” የሚለው ሃረግ ኢየሱስ ስለነበረው አካል ሊያረጋግጥ የሚችለው ምንም ነገር የለውም፡፡ ከዚህም በላይ ይህ ምንባብ እንዲሁ ወይም እንዳያችሁት ሲል፣ ስለ ኢየሱስ አካል የሚለው ነገር የሌለው ብቻ ደግሞ አይደለም፣ ከዚህም በላይ መጻዒያኑ  ጌታ ሲመለስ ዓይን ሁሉ ያየዋል  እንደሚሉ ወደ ሰማይ ሲሄድ ግን በጥቂቶች እንጂ በሰዎች ሁሉ ዓይን ፊት አልነበረም፡፡ መጻኢያን ጌታ ሲመለስ በመላእክት ታጅቦ ነው ሲሉ እንደሚናገሩት ሲሄድ ግን እንደዚያው በመላዕክት ታጅቦ አልነበረም፡፡ መጻኢያን ጌታ ሲመለስ በነበልባል እሳት ይገለጣል እንደሚሉት ሲሄድ ግን በዚያ ሁኔታ በእሳት ነበልባል አልነበረም፡፡ መጻእያን ጌታ ሲመለስ በዓለም ሁሉ በሚሰማ የመለከት ድምጽ ይሆናል ሲሉ እንደሚያውጁት ሲሄድ ግን በዚያ ሁኔታ መለከት እየተነፋ አልነበረም፡፡
ከላይ “እንዲሁ” በሚለው ቃል ወይም “እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ” በሚለው ሃረግ ላይ ለቀረቡት ሃሳቦች ደጋፊ እንዲሆን “የክርስቶስ በተዳሳሽ አካል መታየት” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ያመለክታል የሚለው የመጻኢያን አተረጓጎም መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ እንዲቃረንና፣ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የጻፉልንን ሰዎች ሃሰተኛ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ኢየሱስ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ ዮሐንስ በዚያው እንደ ነበር፣ ወደ ሰማይ ተመልሶ በሄደና ባረገ ጊዜም የእርሱን አካላዊ መታየት ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ሆኖ በአይኖቹ እንደ ተመለከተ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከሌሎች ተጨማሪ ሰላሳ ምናምን አመታት በኋላ በመልዕክቶቹ ሲጽፍ “ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን ” (1ዮሐ 3÷ 2) ይላል፡፡
በእርገቱ ጊዜ ዮሐንስ በዚያው የነበረና ኢየሱስን በአካላዊ መልኩ ያየና የዳሰሰ እስከሆነ ድረስ (ሐዋ 1÷ 1-2)፣ ታዲያ ከተወሰኑ ሦስት አስርት ዓመታት በኋላ መልዕክቱን ሲጽፍ “ገና አልተገለጠም” ሊል እንዴት ይችላል? ዮሐንስ ኢየሱስን በሚገባ ያውቀው እንደ ነበር እናውቃለን (ዮሐ 1÷ 1-2)፡፡ ከዚህም ባለፈ፣ የኢየሱስ አካላዊ መልክ በትንሣኤውም ሆነ  በእርገቱ ጊዜ ተዳሳሽ በሆነ የሚታይ መልክ ከታወቀ (ሉቃ 24÷ 39፤ ዮሐ 20÷ 17፣ 20፣ 25፣ 27)፣ ታዲያ ዮሐንስ መልዕክቱን በጻፈበት ጊዜ እርሱም ሆነ ሁሉም ሐዋርያት እንዴት  ገና እርሱን አልመሰሉም? ስለዚህ ከሙታን በመነሳት የከበረውና በደመና ያረገው ኢየሱስ እንደ ተስፋ ቃሉ ተመልሶ የሚመጣበት አካልም ሆነ ደመናው ተዳሳሽ ቁሳዊ መሆኑ የግድ አይደለም፡፡
5ኛ.ከትርጉም ቀዋሚነት አንጻር፦
አንድ ሰው “አዎ፣ ነገር ግን እየተነጋገርን ያለነው በትንሳኤ ስለ ከበረውና ስለ ማይሞተው መንፈሳዊ አካል ነው” ቢል፣ እርግጥ ነው ቀድሞውኑም ቢሆን  በዕርገቱ ሰዓት ኢየሱስ  የከበረ፣ የማይሞት መንፈሳዊ አካል የነበረው ሆኗል፤ ስለሆነም “እንዲሁ” የሚለው ቃል ወይም “እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ” የሚለው ሃረግ ተመልሶ የሚመጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው እንጂ፣ ልክ በዚሁ በሄደበት ዓይነት አኳኋን ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ በሌላ አባባል ኢየሱስ በዚያው ሁኔታ እነርሱ እንዳዩት ሆኖ ወደ ሰማይ እንዳረገ ሁሉ ተመልሶ እንደሚመጣ ሐዋርያቱ ቀድሞውኑ ያንንው በትንሳኤው የከበረ፣ የማይሞትና መንፈሳዊ አካል የነበረውን ራሱን ኢየሱስን አይተውት ነበር ማለት ነው፡፡
ከፍ ሲል ከሰዋሰዋዊ የቋንቋ አጠቃቀም ህግ አንጻር ጉደዩን አንስቶ ለማየት ተሞክሮአል። አሁንም የምጽዓቱ ምስክር የሆኑ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባባት እንደሚያረጋግጡት ጌታ የሚመጣው “በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና” ከሆነ (ማቴ 24÷ 30፤ 26÷ 64፤)፣ “መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲሁ ይሆናል” እንደ ተባለ (ሉቃ 17÷ 24) ቀኑ ይህ ዓይነት ሁነት የሚታይበት ከሆነ፣ የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን ሎጥ ከሰዶም እንደ ወጣበት ቀን ከሰማይ እሳትና ዲን  የሚዘንብ ከሆነ፣ (ሉቃ 17÷ 29-30)፤ ያም ቀን ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላዕክትም አለቃ ድምጽ ከሰማይ የሚወርድበት ቀን ከሆነ፣ (1ተሰ 4÷ 16)፤ ጌታ ኢየሱስ በመገለጡ የሚሽረው አመጸኛ ከኢየሱስ አፍ እስትንፋስ የተነሳ የሚጠፋበት ቀን ከሆነ (2ተሰ 2÷ 7-8)፣ ቀኑም እነዚህ እና ሌሎች መሰል ክስተቶች የሚስተናገዱበት እስከ ሆነ ድረስ የጌታን አመጣጥ በሐዋ 1÷ 9-11 በተገለጠው ዓይነት ብቻ ልንወስነውና ተዳሳሽ ቁሳዊ ልናደርገው አንችልም፡፡
ወዳጆቼ !  ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው ሐዋርያቱ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ሃሰተኛ ነገር ለማስገባት ተገደው እንደ ነበር ማሰብ አጣብቂኝ ነገር ይሆንብናል፡፡ እንደ ወንጌል አማኝ ስለ ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ያለ የወረደ ነገር እንድናስብ የሚጋብዘንን እይታ በጭራሽ ማስተናገድ አንችልም።
6ኛ.ከቃላት አገባብ አንጻር፦
“እንዲሁ” ወይም እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ (በግሪክ ‘hon tropon’ እንግሊዝኛው ‘in like maner’ ይለዋል፡፡ ይህ ማለት “በተመሳሳይ መንገድ፣ አኳኋን” ማለት ነው ፡፡ ይህ ሃረግ  በአንድ ሁኔታ ውስጥ ያለ ተመሳሳይ የሆነ ነገር፣ አኳኋን፣ ተግባርን ወይም ውጤትን ለመግለጥና ለማሳየት ጥቅም ላይ የዋለ ሃረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ጴጥሮስ አይሁድም ሆኑ አህዛብ በወንጌል የሚድኑበትን አንድ አይነት የሆነን ሂደት ለማመልከት፣ “ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን” (ሐዋ 15÷ 11) ሲል ተጠቅሞበታል፡፡ ሌላው ጥሩ ምሳሌ የአንድ ትክክለኛ ነገር ምንነት መግለጫ የሆነን ነገር ሲያመለክት፡፡ “ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ” (2ጢሞ 3÷ 8)፣ በሚለው ቃል ውስጥ ጥቅም ላይ ውሎአል፡፡ እነዚህ  ተቃዋሚ ሰዎች በአጠቃላይ በጥንቆላ ሥራቸው ሙሴን በፈርዖን ፊት የተቃወሙ ሰዎች ነበሩ (ዘጸ 7÷ 11-12)፡፡ ጳውሎስ “እንዲሁ” (hon tropon) ሲል ግብጻውያን ጠንቋዮች ሙሴንና አሮንን እንደ ተቃወሙት አንዳንዶች የጢሞቴዎስን አገልግሎት እንደሚቃወሙ ለማሳየት ነው። ይሄ ማለት ግን እንደ ቀድሞዎቹ የሙሴ ተቃዋሚዎች ሁሉ እነዚህ የእውነት ተቃዋሚዎች የግድ የጥንቆላን ሥራ ይፈጽማሉ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ “እንዲሁ” (እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ) የሚለው ሃረግ ወይም ቃል በሙሴ ሁኔታ እንደ ሆነው ሁሉ የእግዚአብሔርን መልዕክተኛ ጢሞቴዎስን የሚቃወሙትን ሰዎች አኳኋን ለማመልከት ነው፡፡ ይህ ተቃውሞ ግን በቀጥታ እንዳለ የአስማት እና የጥንቆላ ሥራ መስራትን ላይጠይቅ ይችላል፡፡
በተጨማሪም “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ …. ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም (ማቴ 23. 37) የሚለውን እንደ ምሳሌ ውሰዱት፡፡ ‘እንደ..’ ሲል የገባው ቃል በምን አገባብ ጥቅም ላይ እንደዋለ ያመለክታል፡፡ ኢየሱስ የኢየሩሳሌምን ልጆች ሊሰበስብ ብዙ ጊዜ የገለጠውን የርህራሄ ፈቃዱን ሲያመለክት ያንን ተግባሩን በእናት ዶሮና በጫጩቶቿ መካከል ያለውን ስዕላዊ ሁኔታ በማሳየት ይጠቀምበታል፡፡ ይኸውም ምሳሌአዊ አገላለጽ ነው እንጂ ኢየሱስ እንደ ዶሮ ወይም አሞራ ክንፍ አለው ማለትን አይደለም፡፡ ከላይ ባየነው መሰረት፣ የዚህ በሐዋርያት ሥራ 1÷ 11 ያለው “እንዲሁ” የተሰኘውም ቃል ተመሳሳይ የሆነ አጠቃቀም ያለው ይመስላል፡፡ ቁሳዊ የሆነ ተዳሳሽ ደመናም ሆነ የኢየሱስን በተዳሳሽ አካል መታየት የሚጠይቅ ግን አይደለም፡፡
ከፍ ሲል ከሰዋሰዋዊ የቋንቋ አጠቃቀም ህግ አንጻር እና ከትርጉም ቀዋሚነት አንጻር ጉዳዩን ለማየት እንደ ተሞከረው ይህንንም የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ከሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ጋር በማነጻጸርና በማመሳከር ግልጽ ማድረግ ይቻላል። ማቴዎስ ስለ አመጣጡ ያለውን ተመልከቱ “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና” (ማቴ 24÷ 27)። ይህ ጥቅሰ በሐዋርያት ስራ 1÷ 11 ካለው አመጣጥ ጋር ፈጽሞ የተለየ ነው። ምክንያቱም የሚመጣው በደመና እየታየ ነው ወይስ እንደ መብረቅ ነው? ጳውሎስ ደግሞ የክርስቶስን ምጽዐት እንዴት እንዳብራራው ተመልከቱ “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ” (1ተሰ 4÷ 16)። ይህም በሐዋርያት ሥራ 1÷ 11 ካለው አመጣጥ ጋር የተለየ ነው። በ2ኛ ተሰሎንቄ 1÷ 6-7 ያለውም “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና” ሲል በሐዋርያት ሥራ 1÷ 11 ካለው ጋር የተለየ ነው። እዚህ ላይ እንደውም በሐዋርያት ስራ የማናየው መልዓክ እና የእሳት ነበልባል አለ። ዮሐንስም ደግሞ በራእዩ የሚለውን ተመልከቱ “ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም” (ራእ 19÷ 11)፣ እርሱም አመጣጡን በፈረስ ላይ ተቀምጦ እንደሆነ ነግሮናል፣ እዚህ ላይ ደግሞ ደመና ጨርሶ የለም።
እንግዲህ ማንም ሰው ቢሆን ሐዋርያት ሥራ 1÷ 11 ላይ ያለውን ቃል በሌሎች የምጽዓቱ ምስክሮች በሆኑ ምንባባት ብርሃን ተመርቶ እያነበበ ፣ ኢየሱስ ተመልሶ የሚመጣው ልክ በሄደበት ተመሳሳይ መንገድ ወይም አይነት ነው ሊል እንዴት ይችላል? የእግዚአብሔርን ቃል በእግዚአብሔር ቃል አነጻጽረን ስናመሳክር ይህንን ለመለት አንደፍርም። ስለዚህ ይህ አንድ ክፍል ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ እንደሚመጣ አስቀድሞ በወንጌላቱ ለሐዋርያቱ የተገባውን ተስፋ ብቻ የሚያጸና ከመሆኑ በቀር ተመልሶ የሚመጣበትን የአመጣጡን ተፈጥሮ፣ ወይም መልክ፣ ወይም ቅርጽ፣ ወይም ትእይንት የሚናገር አይደለም።
7ኛ.ከትንቢታዊ ምልክቶች አንጻር፦
የክርስቶስን መምጣት አስመልክቶ የሚናገረው ይህ የሐዋርያት ሥራ 1÷ 11 በዳንኤል 7÷ 13 ላይ የተጻፈውን ያስተጋባል፣ ይኸውም የዳንኤል ትንቢት የዚህ ቃል ቀዳሚ መሠረት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ትንቢቱም “የሰው ልጅ የሚመስለው” የተባለው በሰማያት ደመና የሚመጣበት ትንቢት ነው፡፡ ይህ ትንቢት ከሐዋርያት ሥራ 1÷ 11 ባለፈ ክርስቶስ በደመና እንደሚመለስ ለተጠቀሰባቸው ለማቴዎስ 24÷ 30 እና ለራዕይ 1÷ 7  ለሁለቱም ክፍሎች ቀዳሚ መሠረት ነው፡፡ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ የጊዜ ማዕቀፍ በግልጽ እንደተቀመጠው በእነዚያ በዳንኤል ትንቢት በተገለጹ በባለ አሥር ቀንዶቹ አውሬ ቀናት ወቅት ነው (ዳን 7÷ 22-24)፡፡ ያ በዳንኤል የተጠቀሰው አስር ቀንዶች ያሉት አውሬ ደግሞ በራዕይ 13÷ 1-2 የታየው ሲሆን፣ ይኸውም ቀጥሎ በራዕይ 14÷ 14 "የሰው ልጅ የሚመስለው" ተብሎ  የተጠቀሰው በደመና ከመምጣቱ በፊት ቀደም ብሎ በተገለጠው ምዕራፍ የታየው ነው፡፡ እርሱም ˝አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው˝ (ራዕ 14÷ 14) ይላል። ይኸውም በትክክል ዳንኤል 7÷ 13 ላይ የተጻፈውን ቃል በቃል የሚያስተጋባ ነው፡፡ ስለሆነም በሐዋ 1÷ 11 ላይ የተገለጠው የሰው ልጅ በደመና መምጣት የተፈጸመው በነዚያ በሮም ነገስታት ዘመን፣ ማለትም በዳንኤል ትንቢት በአራተኛው አውሬ ዘመን ነው፡፡
ከዚህ ያለፈው ሌላው ማረጋገጫ በምስጢር ስሟ “ባቢሎን” ተብላ በራእይ መጽሐፍ የተጠራችው ያቺ ጋለሞታ ሴት፣ በባለ አስሩ ቀንድ አውሬ ላይ ተቀምጣ መታየቷ ነው፡፡ ያቺ በምስጢር ስሟ ባቢሎን ተብላ የተጠራችው ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት፣ እርስዋም “በኢየሱስ ደም እና በቅዱሳኑ ደም በሰማዕታቱም ደም ሰክራ የነበረችው” ናት (ራዕ 17÷ 6፤ 18÷ 20፣ 24)፡፡ እርስዋም ቅዱሳኑን እና ነቢያቱን ስለ ገደለች የእግዚአብሔርን ፍርድ እና በቀል ትቀበላለች የተባለችው፣ ኢየሱስ በተመሳሳይ ተጠያቂ አድርጎ የተናገራት ኢየሩሳሌም ናት (ማቴ 23÷ 33-37)፡፡ ይህ ፍርድ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ከማለፉ በፊት እንደሚፈጸም በተደጋጋሚ የተነገረ ሲሆን፣ ኢየሱስም “ይህ ትውልድ” እያለ ሲናገርበት የነበረውና በማቴዎስ 23÷ 36 እና 24÷ 34 በሁለቱም ክፍሎች የተጠቀሰው ትውልድ ነው፡፡ የታሪክ መዛግብት እንደሚያረጋግጡት ኢየሩሳሌም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ማለትም በ70 ዓ.ም በሮማውያን ተደምስሳለች፡፡ ሉቃስ 21÷ 20-22፤ ማቴ 24÷ 30፤ እና ዳንኤል 7÷ 13 ያኔ ተፈጽመዋል፡፡ ይህም የሐዋ 1÷ 11 በደመና መምጣትን የግድ የሚጠይቅ ፍጻሜ ነው፡፡ ደምናውም የእግዚአብሔር ሀልዎት ያለበት አቡቀለምሲሳዊ የፍርድ ደመና እንጂ ቁሳዊውና ተዳሳሹ አለመሆኑን ከፍ ሲል ተመልክተናል።
ማጠቃለያ፡-
እንግዲህ ይህንን ክፍል ስንጠቀልል፣ በዚህ አንድ ጥቅስ ላይ ያለው አጽንዖት የክርስቶስ መምጣት በደመና የሆነ መምጣት መሆኑን ነው፣ ይህም በደመና እንደሄደ በደመና የሚመጣ መሆኑን ማሳየት ነው። ይህም ደመና በፍርድ ለመምጣት ጥቅም ላይ የዋለ አቡቀለምሲሳዊ ምልክት ነው እንጂ፣ ተዳሳሽ የሆነ የሚታይ ፍጥረታዊ ወይም ቁሳዊ ደመና አይደለም። ኢየሱስ በተዳሳሽ ቁሳዊ ቅርጽ እንደሚመጣ የሚያስተምር ምንም አይነት የእግዚአብሔር ቃል ማስረጃ የለንም። የእግዚአብሔርን ቃል ቋንቋ መረዳት የእርሱ አመጣጥ ተዳሳሽ ቁሳዊ እንዳልሆነ እንድንረዳ ያግዘናል። አመጣጡ ግን በአሮጌው ኪዳን እስራኤል ላይ ፍርዱን ለማድረግ ነው።
እንግዲህ ይህንን ክፍል ለመተርጎም ስንነሳ፣ ስለ ምጽአቱ የሚናገሩ ሌሎችንም ብዝሃናት የንባብ ክፍሎች እያማከርን፣ በክፍሎቹም የተገለጡትንና "ይህ ትውልድ" በሚል የጊዜ ማእቀፍ የመመለሻ ጊዜውንና ዘመኑን አመልካች የሆኑትን ጉዳዮች ሳንስት፣ በዚያ አይነተኛ ትውልድ ዘመን ውስጥ ሆኖ ያለፈውን ታሪካዊ ክስተት በማገናዘብ በ70 ዓ.ም ላይ በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ፣ በከተማይቱ ላይ እና በአጠቃላይ በአመጸኛው ሕዝብ ላይ የሆነውን ጥፋት ከታሪክ መመልከት የግድ ነው፡፡ የዚህን ትንቢት ወይም ተስፋ ፍጻሜ ገና ወደ ፊት ከተወሰኑ ሺህ ዓመታት በኋላ በዓለም ታሪክ መጨረሻ ላይ የምንጠባበቅ ከሆነ ግን የትርጉም ድምዳሜያችን ከሌሎች ጊዜውን አመልካች ከሆኑ አጠቃላይ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ጋር፣ ከአቡቀለምሲሳዊው የሥነ ፌታቴ መርሆ ጋር፣ በፍጥረታዊውና በመንፈሳዊው መካከል ካለው ጉልህ የባህርይ ልዩነት ጋር፣ ከሰዋሰዋዊው የቋንቋ አጠቃቀም ሕግ ጋር፣ ከትርጉም ቀዋሚነት ጋር፣ እንዲሁም ለትንቢቶች ፍጻሜ ከተሰጡ ምልክቶች ጋር የሚጣረስብን ከመሆኑም በላይ፣ ትርጉማችን ጌታ ኢየሱስንና መልእክተኞቹን ኃሰተኞች ያደርግብናል። ይሄ ማለት ከእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ጋር ላንታረቅ እንለያያለን ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ምጽአቱ ገና ወደፊት ይፈጸማል ብለን የምናምንና የምንሰብክ ኃሰተኛ ምስክሮች ያደርገናል።
ጌታ ኢየሱስ በወንጌላቱ ስለ ዳግመኛ ምጽዓቱ ያስተማረውን በአውዱ ብንመረምር እርሱ ስለሚመለስበት ጊዜ በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ የተናገረ መሆኑን እንረዳለን። ስለ ዳግመኛ ምጽአቱ የወንጌላቱ ምስክርነቶች የሚያስተምሩትና በርካታ የዘመናችን ክርስቲያን መምህራን በተለምዶ የሚያስተምሩት ግን ፈጽሞ ሊታረቁ የማይችሉ ሃሳቦች መሆናቸው ግልጽ ነው። ቃሉን የሚወድና የሚያከብር አስተማሪ እድሜ ጠገብ የሆነውን ልማዳዊ አስተሳሰቡንና ክብሩን ወዲያ ጥሎ፣ ግልጽ እና የማይዋሽ በሆነው ቃሉ ፊት ራሱን እንዲያዋርድ ያስፈልገዋል። ምናልባት ከቃሉ ጋር ብቻ ስንቆም የለ ወዳጅ፣ ያለ አጃቢ በኃሰተኛ ትችትና በነቀፋ ውስጥ ብቻችንን የተተውን እንደሆንን እንዲሰማን ልንደረግ እንችላለን። ስለ ትንቢት ፍጻሜ ግን ከዚህ የተለየውን ላምንም ላስተምርም እንዳልችል በእግዚአብሔር ቃል ተደርጌአለሁ፤ የምጽፈውም ማንንም ለማስከፋት ወይም ለማስደሰት ሳይሆን መጻፍ ስላለብኝና ለህሊናዬ ስል ነው።
በትክክል ማሰብ የሚፈልግ የቃሉ ተማሪም ከላይ በዝርዝር ያየናቸውን ጉዳዮች በጥንቃቄ እንዲመረምር እጋብዛለሁ። አስተውሉ፣ ጌታችን ኢየሱስ በበርካታ የወንጌላቱ ምንባባት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ተስፋም ሆነ፣ ለአይሁድ ተቃሚዎቹ ያስታወቃቸው የፍርድ ማስጠንቀቂያ የሚፈጸመው፣ እነርሱ በሕይወት እያሉ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንደሆነ በግልጽ የተጻፈ እውነት ነው። ወንጌላቱ በዳግመኛ ምጽዓቱ ላይ ከዚህ ወጭ የሆነ ሌላ ትምህርት የላቸውም።
እንግዲህ በዝርዝር ልናየው የከፈትነው ይህ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 1፥ 9-11 ያለው ቃልም "ኢየሱስ ገና ወደ ፊት ተመልሶ ይመጣል" የሚለውን ልማዳዊውን የመጻኢነት መከራከርያና ትርጉም ደግፎ ሊያቆመው አይችልም። መጻኢያን ተርጓሚ ወንድሞቼ ሆይ፣ ይህ የንባብ ክፍል የትምህርታችሁ መከላከያ ሊሆን ካለመቻሉም በላይ ሌሎቹን የምጽአቱን ተስፋ የያዙ የንባብ ክፍሎች አስቀድሞና አስከትሎ በሃሳባችሁና በእምነታችሁ ላይ የተሰለፈ የማትቋቋሙት ሌጌዎን ሆኖባችኋልና እጅ ብትሰጡ አይሻልም? የለም 'በአቋማችን እንቀጥላለን፣ ምጽአቱም ገና ወደ ፊት ይፈጸማል እንጂ እስካሁን አልተፈጸመም' የምትሉም ከሆነ እንግዲያውስ ለትምህርታችሁ ድጋፍ የሚሆን የንባብ ክፍል አንድም ቢሆን እንኳ ይዛችሁ እንድትቀርቡ ትጠበቃላችሁ።
ግዛቸው ከበደ /ቄስ
[ግዛቸው ከበደ በ1972 አ.ም የ12 አመት እድሜው ላይ በጌታ ምህረት በወንጌል አምኖ የዳነ፤ በቤተክርስቲያን አገልግሎትና በክርስቲያን ተማሪዎች ሕብረት ውስጥ ተሳትፎ የነበረው፣ በውስጡም ያውቀው ለነበረው የወንጌል ጥሪ በ1982 ራሱንና ሙሉ ጊዜውን የሰጠ፣ በ1985 ከቤተክርስቲያኑ በቀረበለት የወንጌል አገልግሎት ጥሪ የተሰማራ፣ በመካነየሱስ ሴሚናርዩም በባችለር ኦፍ ቲኦሎጂ የሥነ መለኮትን ትምህርት  የተከታተለ፣ በ1993 አ.ም ቅስናን የተቀበለ ሉተራዊ ቄስ ነው። "የእግዚአብሔር ቃል ብቻ" በተሰኘው የወንጌላውያን ሉተራን የተሃድሶ መርህ እየተገፋ በተለይ በሥነ መለኮታዊ የነገረ ፍጻሜ ምልከታው የኃላፋውያንን ትርጉም ይከተላል። በሚከተለውና በሚያስተምረው የነገረ ፍጻሜ አቋሙ ብቻውን ይጠየቃል እንጂ፣ እናት ቤተክርስቲያኑንም ሆነ ማንንም ሰው አይወክልም። ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነውና ከጥቂት አመታት ወዲህ መኖርያውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው ይህ ታናሽ ሰው የትምህርቱን መጣጥፍ በማህበራዊ ሚድያ እያስተላለፈ ይገኛል።]

    ]