Sunday, October 1, 2017

የዳግመኛ ምጽአቱ አስተምህሮ

  


















በዳግመኛ ምጽዓቱ አስተምህሮ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአመለካከት እርማት ማድረግ ይገባል።

ማቴ 16፥ 27-28 የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ”

ራዕ 22፥ 20 "ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና"

ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች፦
በዚህች አጭር ጽሁፍ ከጌታ ምጽአትና ከአጠቃላይ የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ አንጻር፣ በተከታታይ የማነሳቸውና የማተኩርባቸው ጉዳዮች፣ በወንጌላውያኑም ዘንድ የአመለካከትና የእምነት እቋም ለውጥ እንዲደረግ የሚጠይቁ መጽሐፍቅዱሳዊ ምክንያቶችን፣ በሚከተሉት ስድስት ነጥቦች ከፍዬ አቀርባለሁ ፦

፩. ጊዜን አመልካች የሆኑ አዲስ ኪዳናዊ ምንባባት (ፈጥነው ሊሆኑ ያሉና ከመሆን የማይቀሩ ጉዳዮችን የሚያመለክቱ የንባብ ክፍሎች)፤

፪. ብሉይ ኪዳናዊ መሰረት ያለው "አቡቀለምሲሳዊ" የቋንቋ አጠቃቀም፤

፫. የቃል በቃል ወይም የፊት ለፊት (litetal) ትርጉምን የሚቃረነው የትንቢት መንፈሳዊ ፍጻሜ (spiritual fulfilment)፤

፬. የእግዚአብሔር መንግስት ባህርይና ተፈጥሮ (በተለይ ከዳግመኛ ምጽዓቱ ጋር ካለው የቀረበ ግንኙነት አንጻር ሲታይ)፤

፭. የጌታ ምጽዓት ባህርይና ተፈጥሮ፤

፮. ይህ የአመለካከታዊ እርማት ጥሪ በመሰረታውያኑ የክርስትና የመጀመርያ አስተምህሮቶች ላይ ለውጥ የማድረግ ጥሪ አይደለም።

መግቢያ፦
አዲስ ኪዳን በግልጽ የሚያስተምረውን የክርስቶስን ዳግመኛ ምጽዓት፣ የዳግመኛ ምጽዓቱን አይነተኛ ጊዜ እና እና አጠቃላይ ባህርዩን ከቃሉ መመርመር፣ የኖረውንና እድሜ ጠገብ የሆነውን አመለካከትም ግልጽ ወደ ሆነው የቃሉ ትምህርት እየተመለሰ እርማት እንዲያደርግም በቃሉ እውነት መሞገት፣ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ ነው።

የነገረ ፍጻሜ ጥናትን (eschtological study) በተመለከተ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘርፉ የሚደረግ ምርምር፣ እያደገ በመጣ የቃሉ ቀዳሚ ተደራስያን (audience relevance) አውድ ተኮር (context oriented) በሆነ ሥነ ፍታቴና ሥነ ትርጓሜ (hermenutics) ተጽዕኖ የተነሳ በበርካታ የቅዱሳት መጻሕፍት ተማሪዎች ዘንድ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖአል።

በልዩ ልዩ የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ጎራ የተለያዩ የነገረ ፍጻሜ አመለካከቶችን የሚከተሉ የወንጌል አማኞች መኖራቸው እሙን ነው። እነርሱም በትንቢት ፍጻሜ ላይ በተለያየ የአተረጓጎም ጎራ ተሰልፈው የየራሳቸውን የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ የሚከራከሩ ናቸው። የሚበዙት የመጻኢነት (futurism) ተርጓሚዎች፣ "ትንቢት ሁሉ ገና ወደ ፊት ይፈጸማል እንጂ እስካሁን ምንም የተፈጸመ ነገር የለም" ሲሉ፤ ሌሎች የታሪካውያንነት (historicism) ተርጓሚዎች ደግሞ፣ "ትንቢት በታሪክ ውስጥ ራሱን እየደገመና እየተደጋገመ የሚፈጸም ነው" ይላሉ፤ በሌላ ወገን ያሉት የሃሳባዊነት (idealisms) ተከታዮች ደግሞ፣ "ትንቢት ምሳሌ እንጂ ምንም የተፈጸመም ሆነ የሚፈጸም ነገር የለውም" ሲሉ፤ አንዳዶች የከፊል መጻኢነት ወኃላፋዊነት (partial futurism and or partial preterism) መምህራን ደግሞ፣ "ትንቢት በከፊል ተፈጽሞ ሌሎች ያልተፈጸሙት ገና ወደ ፊት የሚፈጸሙ ናቸው" ሲሉ፣ ያስተምራሉ። በአንጻሩ ደግሞ የሙሉ ኃላፋውያን (full preterism) መምህራን "ያኔ ድሮ ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ሁሉም ትንቢት ተፈጽሞአል፣ ምንም የቀረ ነገር የለም" የሚል አቋም ይዘው የሚያስተምሩና የሚሞግቱ ናቸው።

ከሌሎች አመለካከቶች ሁሉ በተለየ ይህ በተቃራኒው የቆመና "ትንቢት ሁሉ ድሮ ገና በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ተፈጽሞአል" የሚለውን አቋም የያዘው፣ ምናልባትም በብዙዎችም ዘንድ በበቂ የማይታወቅ የአስተምህሮተ ነገረ ፍጻሜ አመለካከት ይህ የሙሉ ኃላፋውያን አመለካከት (full preterism) ነው። ሆኖም ከሌሎቹ አመለካከቶች ሁሉ ይልቅ፣ ትንቢትን በራሱ የትንቢት ቃል ተርጉሞ ለመረዳት የሚተጋው፣ የቅዱስ ቃሉን በመንፈስ ቅዱስ መሰጠትና ሥልጣኑን የሚቀበለው፣ ይህ የሙሉ ኃላፋውያን አመለካከት (full preterism)፣ "ቅዱሳት መጻህፍት ብቻ" የተሰኘውን የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት የእምነት አቋም አጥብቆ የያዘ አመለካከት እንደሆነ ተረድቼአለሁ።

ይኸውም የኃላፋውያን ወገን ትንቢታዊ አቀራረብ ያለውን የክርቶስን ዳግመኛ ምጽዓት አስተምህሮና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የነገረ ፍጻሜ ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ፣ የቅዱስ ቃሉን ትምህርት ብቻ መሰረት አድርጎ እንደገና ከልሶ የማየትና የአስተምህሮ እርማት እንዲደረግ ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ በመጣ ብርቱ ፍላጎት የዳግም ተሃድሶን ጥሪ እያቀረበ፣ ፣ "ትንቢት ገና ወደ ፊት ይፈጸማል እንጂ እስካሁን ገና አልተፈጸመም" ሲል የትንቢትን ፍጻሜ አሁንም ገና የሚጠባበቀውን የኖረ፣ የቆየና የተለመደ የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናትን የመጻኢነት (futurism) አመለካከትንና ሌሎቹን ሁሉ እየጠየቀና እያፋጠጠ ይገኛል።

ባለፉት ዘመናት ደግሞ በሁሉም ዘንድ ማለት በሚያስችል መልኩ በተለመደ ሁኔታ ገዢ አመለካከት እንደሆነ የሚቆጠረውና "በትንቢት የተነገረው ዳግመኛ ምጽዓቱም ሆነ እርሱን አጅበው ያሉ ሁነቶች እስካሁን ገና አልተፈጸሙም" ብሎ የሚያምነው የመጻኢነት አመለካከት (futurist position) ከፍ ሲል በተጠቀሱት "ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል" ብለው የሚያምኑና ሙሉ ኃላፋውያን በመባል የሚታወቁ ክፍሎች በሚያነሱዋቸው አውድ ተኮር (context oriented) በሆኑ ጥያቄዎችና በሚያቀርቡአቸው የሙግት አሳቦች በእጅጉ ተግዳሮት እየገጠመው ይገኛል። በውኑ መጻኢያንስ ቢሆኑ የኢየሱስን ዳግመኛ ምጽአት ባህርይና ጊዜውስ መቼ እንደሆነ በመረዳትና በመተንተኑ ጉዳይ የትርጉም ቀዋሚነት (consistency) ችግር የለባቸውምን? ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንጻር ነገሮችን እንዴት መየት እንዳለብኝ ሳስብ ለራሱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ታማኝ ሆኖ መገኘትና፣ እውነትን በትእግስት መፈለግና በፍቅ ማስረዳት እንዳለብኝ ይሰማኛል።

እነርሱ ከነበሩበት ጊዜ አንጻር ብዙም ሳይዘገይ ወደፊት በቅርብ ርቀት በሚታሰብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸም ባለ መለኮታዊ ፍርድ፣ ያንን አሮጌ የመስዋእቱን ስርአትና የአይሁድን ትምክህት ሁሉ ከቤተመቅደሱ ጋር በእሳት ሊያጠፋ፣ ለምእመናኑም መዳናቸውን ሊፈጽም "ተመልሼ እመጣለሁ" ሲል ተስፋና ማስጠንቀቂያ የሰጠው ኢየሱስ ይናገር የነበረው በራሱ ዘመን ለነበሩ ቀጥተኛና ቀዳሚ አድማጮቹ ነበር። ላለፉት ሁለት ሺህ አመታት ለመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች የተነገረውንና "እነሆ በቶሎ ይመጣል" የሚለውን ይህንን በግልጽ አማርኛ የተነገረ ቃል እያነበብን፣ አሁንም ለእኛ የተባለ ያህል ቆጥረን ምጽአትን የምንጠብቅ ከሆነ፣ በእውነት አስቀድሞ የሚያስፈልገን የአማርኛ መዝገበ ቃላት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይመስለኝም።

ይህችን አጭር ጽሁፍ ለማንበብ የታደለ የመጻኢነትን አመለካከት የሚከተል ማንኛውም ሰው፣ ከ70 አ.ም በኋላ በሚታሰብ የጊዜ ቀመር፣ አሁን እኛ ባለንበት በዚህ ትውልድ ዘመን ወይም በሚመጣው ትውልድ ዘመን ኢየሱስ በስጋው እንደሚመለስ የሚናገር አንድ ጥቅስ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ ላይ ያገኝ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱሱን ገልጦ እንዲያሳየኝ እጠብቃለሁ። እስካሁን ለመከታተል እንደቻልኩት መጻኢያኑም (futurists) ራሳቸው ቢሆኑ፣ አዲስ ኪዳን ከተጻፈበት አውድ አንጻር እየቀረበ ያለውን ይህንን "ዳግመኛ ምጽዓት በ70 ዓ.ም ላይ ተፈጽሞአል" ብለው የሚያምኑትንና የሚያስተምሩትን የኃላፋውያኑን (preterist) አቅዋምና ሙግት፣ እናምነዋለን ብለው በያዙት የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ማስተባበል ተስኖአቸዋል።

፩. ጊዜን አመልካች የሆኑ አዲስ ኪዳናዊ ምንባባት
(ፈጥነው ሊሆኑ ያሉና ከመሆን የማይቀሩ ጉዳዮችን የሚያመለክቱ የንባብ ክፍሎች)

መንደርደሪያ፦
የእግዚአብሔርን ቃል ስመረምር የመጀመርያ ትኩረቴ የዳግመኛ ምጽዓቱን የጊዜውን ወሰን (ማዕቀፍ) በተመለከተ በሚያተኩረው በአዲስ ኪዳን ትምህርት ላይ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው፣ አዲስ ኪዳን የሚያስተምረውና ሐዋርያቱ ሲጠብቁት የነበሩት የጌታ ምጽዓት አንድ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው ክርስቶስና ሐዋርያቱ ያስተማሩትና ሲጠባበቁት የነበረውም፣ ጌታ በእነርሱ የህይወት ዘመን (ትውልድ) ወቅት ዳግመኛ ተመልሶ እንደሚመጣ የተነገረውንና ተስፋ የተገባውን ብቻ ነው።

ለዚህ ትምህርትና የመጀመርያይቱ ቤተክርስቲያን አባቶች ለነበራቸው በመንፈስ ቅዱስ ለተመራ የጌታን ምጽአት መጠባበቅ የኃላፋዊነትን የነገረ ፍጻሜ አመለካከት የሚከተሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የሚያቀርቧቸውን ምስክሮች የሆኑ የአዲስ ኪዳን ምንባባት ከብዙ በጥቂቱ እንመለከታለን። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተመሰረተባቸው የቅዱሳት መጻህፍት ምንባባትና በዚህ ጥናት ያተኮርኩባቸው ሌሎቸ ተዛማጅ የሆኑ ምንባባት ሁሉ ነገረ ፍጻሜን ባጠኑ ምሁራን በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ሊከፈሉ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ እነርሱም “ጊዜውን አመልካች የሆኑ አጠቃላይ የንባብ ክፍሎች” (Gneric passeges) እና “ሊሆን ያለውን አመልካች የሆኑ ክፍሎች” (Mellonic passeges) በመባል ይከፈላሉ። ለአሁኑ አቀራረብ ከሁለቱም አይነት ክፍሎች ከብዙ በጥቂቱ የተወሰኑትን ብቻ እንይ።

ከዚህ ቀጥሎ በምናነባቸው በእነዚህ የዳግመኛ ምጽዓቱ አመልካች በሆኑ የአዲስ ኪዳን ምስክርነቶች ውስጥ የምናያቸው ጸሐፊዎችና በኩረ ተደራሲያን፣ ከአውድ አንጻር ከ30-70 ዓ.ም ባሉት የ40 ዓመታት ጊዜያት ውስጥ የነበረው የዚያ ትውልድ ሰዎች ማለትም የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች እንጂ፣ ከዚያ በኋላ በተከታይ የመጡ የየትኛውም ዘመን ትውልድ ሰዎች አለመሆናቸውን ወይም የዚህ ዘመን ትውልድ ሰዎች አለመሆናችንን በአእምሮአችን እንያዝ።

መጥምቁ ዮሐንስ፦
♦ማቴ 3፥ 2 "መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ"
♦ማቴ 3፥ 7 "እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?"
♦ማቴ 3፥ 10 "ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል"
♦ማቴ 3፥ 12 "መንሹም በእጁ ነው አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውንም በጎተራው ይከታል ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል"

ሐዋርያው ጴጥሮስ፦
♦ሐዋ 2፥ 16-17 "በመጨረሻው ቀን ... ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፍሳለሁ"
♦1ጴጥ 1፥ 20 "... ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ"
♦1ጴጥ 4፥ 5 "በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ"
♦1ጴጥ 4፥ 7 "ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል"

ሐዋርያው ጳውሎስ፦
♦ሐዋ 24፥ 15 "እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት ጻድቃንም ዓመጸኞችም ከሙታን ይነሱ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ"
♦ሮሜ 8፥ 18 "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ"
♦ሮሜ 13፥ 11-12 "ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአል"
♦ሮሜ 16፥ 20 "የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል"
♦1ቆሮ 7፥ 29 "ዳሩ ግን ወንድሞች ሆይ ይህን እናገራለሁ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ..."
♦1ቆሮ 7፥ 31 "በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና"
♦1ቆሮ 10፥ 11 " ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገስጸን ተጻፋ"
♦1ቆሮ 15፥ 51-52 "እነሆ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን"
♦1ተሰ 4፥ 15፣ 17፤  "በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና እኛ ሕያዋን የሆንን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም ... ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን። እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።"
♦1ተሰ 5፥ 4 "እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም"
♦1ጢሞ 6፥ 14 "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ"
♦2ጢሞ 4፥ 1 "በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመገለጡና በመንግስቱም እመክርሃለሁ"

የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ፦
♦ዕብ 1፥ 1-2 "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር ... ለአባቶቻችን በነብያት ተናግሮ ... በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤"
♦ዕብ 8፥ 13 "አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል"
♦ዕብ 10፥ 25 "... ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ"
♦ዕብ 10፥ 37 "ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም..."

ያዕቆብ፦
♦ያዕ 5፥ 8፣ 9 "ልባችሁን አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። ... እነሆ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል"

ተወዳጁ ዮሐንስ፦
♦1ዮሐ 2፥ 8 "ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል"
♦1ዮሐ 2፥ 17 "አለሙም ምኞቱም ያልፋሉ ..."
♦1ዮሐ 2፥ 18 "ልጆች ሆይ መጨረሻው ሰዓት ነው..." (1ዮሐ 2፥ 18፤ (ከማቴ 24፥ 23-34 ጋር አነጻጽሩ፤ 1ዮሐ 4፥ 3፤ ከ2ተስ 2፥ 7 ጋር አነጻጽሩ)

ይሁዳ፦
♦ይሁዳ 17-19 "እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ እነርሱ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና"

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት፦
♦ማቴ 16፥ 27-28 የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ” (ከማር 9፥ 1፤ ሉቃ 9፥ 27 ጋር አነጻጽሩ)
♦ማቴ 21፥ 40-41፣ 43፣ 45 "እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? እነርሱም። ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ"
♦ማቴ 24፥ 34 "እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም"
♦ማቴ 26፥ 64 "ኢየሱስም አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው" (ማር 14፥ 62፤ ሉቃ 22፥ 69)
♦ማር 1፥ 15 "ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና። ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ"

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ ባመለከተው ራዕይ፦
♦ራዕ 1፥ 1 "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ"
♦ራዕ 1፥ 3 "ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው"
♦ራዕ 2፥ 25 "ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ"
♦ራዕ 3፥ 10 "የትዕግስቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ"
♦ራዕ 3፥ 11 "እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ ማንም ኡክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ"
♦ራዕ 22፥ 7 "እነሆም በቶሎ እመጣለሁ"
♦ራዕ 22፥ 10 "ለእኔም ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው"
(ከዳን 8፥ 26 ጋር አነጻጽሩ "የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ")
♦ራዕ 22፥ 12 "እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ"
♦ራዕ 22፥ 20 "ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና"

ከላይ በዝርዝር ለቀረቡ ጥቅሶች ማጠቃለያ
እነዚህ ሁሉ አዲስ ኪዳናዊ ምስክሮች "የጌታ ዳግመኛ ምጽዓት፣ የመጨረሻው ቀን ወይም የዘመን ፍጻሜ የሚሆነው መቼ ነው ብለህ ታምናለህ ወይስ ታስተምራለህ?" ሲሉ እኔንና እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝና ተማሪ አጥብቀው ይሞግታሉ። ምክንያቱም ዳግም ምጽአቱ መቼ ሊሆን እንደሚችል ከበቂ በላይ በግልጽ ሊያመለክቱ የሚችሉ፣ ጊዜውን ጠቋሚ የንባብ ክፍሎች ናቸውና። እኛ ቃሉን የምንወድ የቃሉ አማኞችና የቃሉ ተማሪዎች የሆንን ሁሉ በጥቅሶቹ አንጻር ምን መመለስ እንዳለብን ለቃሉ ለታማኝ ሆነን በወጉ ማሰብ ይገባናል።

ከላይ በዝርዝር በቀረቡት የአዲስ ኪዳን የንባብ ክፍሎች ላይ ቆመን፣ ብዙዎቻችን ለብዙ ዘመን እውነት መስሎን ለቅዱሳት መጻሕፍት አጠቃላይ አስተምህሮ በማይመጥን መንገድ ስናምነውና ስናስተምረው ለኖርነው የመጻኢነት ትምህርት የሚቀርብ ጥያቄ፦

ጥያቄ አንድ፦
የመጻኢነትን የነገረ ፍጻሜ አመለካከት የሚከተሉ ወገኖች፣ ከላይ በተዘረዘሩ የንባብ ክፍሎች ላይ ተመስርተው "ክርስቶስ የምድራዊ አገልግሎቱ ምስክሮች በነበሩ ትውልድ የሕይወት ዘመን ይመለሳል ተብሎ ይጠበቅ ነበር" ብለው የሚያምኑትን የኃላፋውያንን ትርጉም ሊቃወሙ የሚችሉበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ መሰረት አላቸውን?

የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ብቻ እንጂ መጻኢያን እንደሚመስላቸው የዘመናት ልማዶቻቸው ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሊረዱአቸው እንደማይችሉ ገብቶኛል።

የእግዚአብሔርን ቃል በውል ለመረዳት በግሌ የነበረብኝ ፈተና፣ እድሜ ጠገብ ሰብአዊ የቤተክርስቲያን ልማድና አስቀድሞ አስተሳሰቤን የቀረጸና በአመለካከቴና በእምነቴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖን ያሳደረው፣ ሲነገረኝና ሳነበው የኖርኩት ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የሰው ትምህርት ነው። እንዲህ ያለውን የሰው ትምህርትና ጎጂ ልማድ ከአስተሳሰቤ ላይ ገፎ ለመጣል እስካሁን ድረስ ገና ብዙ ትግል ይቀረኛል። "ልማዳችን ወይም ደግሞ ለገዛ ራሳችን ሥሜት ልንሰማው የሚመቸን ነገር የሚለውን ሳይሆን፣  የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚሉትን አትኩሮት ሰጥተን መመልከት እንዳለብን ልብ እንበል" ሲል አንድ በስም የማላስታውሰው ጸሐፊ ተናግሯል።
 
የቤተክርስቲያን አዳሾችም ቢሆኑ "ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ" (sola scriptura) ሲሉ የእግዚአብሔር ቃል በየትኛውም የሰው አስተሳስብ ላይ ያለውን ገዢነት ከፍ አድርገው በማሳየት ዋጋ ከፍለዋል። ይህ "ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ" (sola scriptura) የተሰኘ የተሃድሶ መርህ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ሁሉ የመጨረሻው ወሳኝና የበላይ ስልስጣን ሆኖ እምነታችንን፣ ትምህርታችንንና ልምምዶቻችንን የሚቀርጽና የሚገዛ ብቸኛና በቂ ሥልጣን ነው። ይህም ማለት ለደህንነታችን እና ለመንፈሳዊ ህይወታችን አስተምህሮ አስፈላጊ የሆነው እውነት ሁሉ የሚፈልቀውና የሚቀዳው ከቅዱሳት መጻህፍት ብቻ ነው ማለት ነው። እኔም ባነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቃሉ ብቻ እንዲናገረኝና እንዲፈርደኝ፣ ትምህርቴን እንዲቀርጸውና እንዲገዛው፣ ቃሉን የልማዶቼ እና የሰብአዊ ሥሜቶቼ የበላይ ገዥ እንዳደርገው፣ ብቸኛው ሥልጣንና መስፈሪያ ሚዛን መሆኑንም አጥብቄ የመያዝ ኃላፊነትና ጥሪ እንዳለብኝ ይሰማኛል። ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ" (sola scriptura) የሚለውን የተሃድሶ መርህ እንደሚከተል እንደ አንድ ሉተራዊ ቄስ በዚህ አቋም ለመጽናት እምነቴም ጸሎቴም ነው።

እንግዲህ ከላይ ከፍ ሲል በተራ ቁጥር አንድ ላይ ላነሳሁት ጥያቄ መልሴ፦ መጻኢያን በጭራሽ መልስ የላቸውም የሚል ነው።

መጻኢያን፣ ከላይ በዝርዝር በቀረቡ የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት ቃላት ላይ የተመሰረቱትንና፣ "ክርስቶስ የምድራዊ አገልግሎቱ ምስክሮች በነበሩ ትውልድ የሕይወት ዘመን ይመለሳል ተብሎ ይጠበቅ ነበር" ሲሉ የሚያስተምሩትን የኃላፋዊያንን ትርጉም ለመቃወም፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ  ድጋፍ በጭራሽ የላቸውም። እነዚህንም ከላይ የተዘረዘሩ ምንባባትን ሊያስተባብሉና ክፍሎቹ እየተናገሩለት ካለው ነገር የተለየ ትርጉም እንዳላቸው አድርገው ሊያቀርቡ የሚችሉበት ውሃ የሚቋጥር ማስረጃም የላቸውም። በመሰረታዊነት የአመለካከት ለውጥ እንዳደርግ ገፊ ምክንያቴ ይህ ነው። በወጉ ሳላስብበት የሚበዛውን ዘመኔን የተከተልኩት የትኛውምየመጻኢነት ጎራ ከላይ ላነሳሁት ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ሊሰጠኝ አይችልም።

ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ሁሉ ግን አንድም ሳይቀር ተፈጽሞአል። ፈጽሞም አልተሳሳተም፤ እርሱ ስለ መመለሱ የተናገረውን ትንቢት ለማብራራት "ዘግይቶ የመፈጸምን አስተምህሮ" ወይም የመመለሻውን ጊዜ የሚያራዝምና ለሌላ ያልታወቀ ጊዜ የሚያስተላልፍ ስነመለኮታዊ መተጣጠፍ (gymnastic) እየሰራን ትንቢቱን ማቃናትም ሆነ ድጋፍ ልናደርግለት አያስፈልገንም። ነብዩም ሆነ የትንቢቱ ቃል ለእውነተኝነታቸው ታማኞች ናቸውና። ዳሩ ግን ቃሉ የሚለውን ሳይሆን እኛ እንዲልልን የምንፈልገውን በግድ ጠምዝዘን የምናናግረው ከሆነ የቃሉ ሎሌነታችንን ከመጣላችንም በላይ ኢየሱስን ሃሰተኛ እናደርገዋለን።

ሁሉም ነገር ተፈጻሚ የሆነው ቃሉ ከተነገረበት ጊዜ አንጻር "ሳይዘገይ በተያዘለት መርሃ ግብር ነው" ብዬ እንዳምን በራሱ በቃሉና በታሪካዊ ማስረጃ እገደዳለሁ። በርካታ የስነመለኮት ሰዎች በ70 አ.ም ላይ የሆነውን የኢየሩሳሌምን ውድመት በተመለከተ በእግዚአብሔር የደህንነት ታሪክ መርሃ ግብር ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት ቢያውቁም ቅሉ፣ ሙሉ ዋጋ የሚሰጠውን ትርጉም ግን አያስተውሉትም። የ70ው አ.ም ክስተት ግን አጠቃላይ ግንኙነቱ ከደህንነት ታሪክ እቅድ ተጠቃሎ መፈጸም ጋር የተያያዘ ነው።
 
እግዚአብሔር ከዘላለም ያቀደው የደህንነት ታሪክ ትእይንት ተጠናቆ የተፈጸመበት የመጨረሻ ሁነት ያበቃው ሐዋርያቱ በነበሩበት በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ትውልድ ላይ ነው (ከ70 አ.ም በፊት)። ሐዋርያቱ ሲጠብቁት የኖሩት የክርስቶስ መንግስት፣ እርሱም መንፈሳዊ መንግስት አሁንና እዚህ ነው እንጂ። ገና የምንጠብቀው አይደለም።

"መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው።" (ዮሐ 18፥ 36)

ወደ ሕይወት መግባት አሁን በክርስቶስ ተሰጥቶናል፣ ከሞትን በኋላ በላይ በሰማያት የሚቀጥለውን የዘላለም ሕይወት አሁን አግኝተናል። በዙፋኑ ላይ ያለው ንጉሰ ነገስት ክርስቶስ ኢየሱስ ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ በማያልቅ ሰላም የተሞላውንና ፍጻሜ የሌለውን ዘላለማዊ መንግስቱን ሰጥቶናል። (ኢሳ 9፥ 6-7)

ምጽአቱ (parousia) ገና ያኔ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ውስጥ በቅርቡ፣ ማለትም በ70 አ.ም ላይ፣ ከመሆን የማይቀር፣ ሊፈጸምም ቀን የተቆረጠለት ነበር እንጂ፣ 2000 አመታትና ከዚያ በላይ ተራዝሞ ገና ወደፊት የተላለፈ አይደለም። መጻኢያን የሚያቀነቅኑት ሁሉም የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮአቸው የወደቀው ይህንን እውነት ባለማስተዋልና ባለመረዳት ነው።

መጻኢያን እነዚህን የዳግመኛ ምጽዓቱ አመልካች የሆኑ ምንባባትን በመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ትውልድ ወቅት የሚፈጸሙ እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም ገና ያልተፈጸሙ መሆናቸውን  ወይም ገና ወደ ፊት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ለማስረዳት ብዙ ርቀት ሄደው የሚያቀርቡት መከላከያ እንዳላቸው እየመሰላቸው የሚያነሱት ጥቅስ 2ጴጥሮስ 3፥ 8 ላይ ይገኛል፦

2ጴጥ 3፥ 8 "እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ አመት ሺህ አመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ"

ይህ ጥቅስ ለመጻኢነት አቋም ድጋፍ ነው ተብሎ የሚታስብ እንደሆነ ይታወቃል። እኔም እግዚአብሔር ምሕረት ያድርግልኝና ይህንን ጥቅስ ዛሬ መጻኢያን በሚጠቀሙበት መንገድ ያለቦታው ስሰነቅረው ኖሬአለሁ።

ጥያቄ ሁለት፦
ኃላፋውያንስ ቢሆኑ ታዲያ፣ ጴጥሮስ በዚህ ጥቅስ ሊነግረን የሚፈልገው "ዳግምኛ ምጽዓቱ በሺህዎች ለሚቆጠር አመታት ክፍለ ጊዜ ይዘገያል ማለቱ አይደለም" ሲሉ ለሚያቀርቡት መከላከያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አላቸውን?

አዎን አላቸው፦
ቀደም ሲል ያነሳነው የጴጥሮስ ምስክርነትና የራሱ የጴጥሮስ እምነት ስለ ዘመኑ ግልጽ አድርጎ የሚናገረው በአመለካከቴ ላይ እርማት የሰጠኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። 

ሐዋ 2፥ 17-18 "እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ....ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ...."

1ጴጥ 4፥ 7 "ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ"

እነዚህ የጴጥሮስ ንግግሮች ግልጽ ያደረጉልኝ አንድ ነገር፣ ሐዋርያው ራሱም ሆነ፣ ወይም የመልዕክቱ አድማጮችና አንባቢዎች ራሳቸውም ቢሆኑ፣ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ላይ መሆናቸውንና የነገር ሁሉ መጨረሻም ቀርቦ እንደነበር ያምኑ የነበረ መሆናቸውን ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚያውቀው ጌታ የሚመለስበት የመጨረሻ ዘመን ራሱ ጴጥሮስና የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ይኖሩ የነበረበትን ዘመን ነው እንጂ እነርሱ ከነበሩበት ዘመን የዘለለ ወይም በሺህዎች አመታት ርቀት ወደፊት የሚታሰብ ሌላ ዘመን አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ በንግግሩም ሆነ በጽሁፉ በመንፈስ ቅዱስ የተመራ የሃሳብ ቀዋሚነትን (consistency) ያንጸባርቃል እንጂ ራሱን አይጣላም።

ቀጣይ የሆኑት የዚህ የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ምንባብ በርካታ ቁጥሮች በዚሁ ፍሰት ያንኑ ሃሳብ የሚያመለክቱ መሆናቸውንም አስተውያለሁ፦

2ጴጥ 3፥ 9-15 "ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኲሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀጥል ከሆነ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማያትም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይፈታል፣ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፣ የጌታችንም ትዕግስት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ። እንዲሁም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ"

እንግዲህ ጴጥሮስ "ዳግመኛ ምጽዓቱ ከሺህዎች አመታት በኋላ ይፈጸማል" ብሎ የሚያምንም የሚያስተምርም እንዳልሆነ ተረድቼአለሁ። ከዚያ ይልቅ ግን ጥቅሱ እግዚአብሔር ጊዜን አስመልክቶ ሰው ከሚያይበት አተያይ በተለየ እንደሚያየው ሐዋርያው ጴጥሮስ ያስተማረበት ሃሳብ ነው። የሆነው ሆኖ ግን ለእግዚአብሔር እንደ ቅጽበት አይን ጊዜ የነበረ ቢሆንም እንኳ፣ ለጴጥሮስ ትውልድ ሰዎች ግን "ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም" የተባለለትን የዳግመኛ ምጽዓቱን ተስፋ ፍጻሜ ረጅም ለሚመስል ጊዜ ማለትም ወደ አርባ አመታት ለሚጠጋ ጊዜ መጠበቅ ነበረባቸው።

አንዳንድ መጻእያን ደግሞ ከላይ በተራ ቁጥር አንድ በዝርዝር የቀረቡትንና "ፈጥነው ከመሆን የማይቀሩ ጉዳዮችን የሚያመለክቱ ጊዜን አመልካች የሆኑ ምንባባትን ለመከላከል በመልሦ ማጥቃት ከዚህ በታች ያሉትንና "የመዘግየት ምንባብ" የሚባሉትን ምሳሌአዊ የንባብ ክፍሎች ሲያቀርቡ ይደመጣሉ። እኔም ያለ በቂ ጥናት ይህንንው ሳደርግ ኖሬአለሁ፣ መሳሳቴ የገባኝ ግን ብዙ ሳይረፍድብኝ ነው።

ማቴ 24፥ 44-51 ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል"

ማቴ 25፥ 1-13 " በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊትም ሲሆን። እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን። መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው። ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ"

ማቴ 25፥ 14-19 " ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው"

በነዚህ የንባብ ክፍሎች ያሉት የመዘግየት ሃሳቦች የሺህ አመታት ጊዜ ወይም ሌላው ቢቀር የመቶ አመታት ጊዜ ቆይታ እንኳ ያላቸው እንዳልሆኑ ግልጽ የሆነልኝ ቆይቶ ነው። በሁሉም ምሳሌዎች "ይመጣል" ወይም "ይደርሳል" ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ጉዳይ፣ "ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል"፤ "ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ"፤ "ከብዙ ዘመንም በኋላ"  ተብሎ ቢገለጥና ቢዘገይም እንኳ መምጣቱም ሆነ መድረሱ ለነዚያው ይጠብቁት ለነበሩ ሰዎች ከመሆን አልቀረም፣ የመጣውም ይጠባበቁት በነበሩ ሰዎች የህይወት ዘመን ነው፦

ማቴ 24፥ 50 "የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል"

ማቴ 25፥ 10 "ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ"

ማቴ 25፥ 19 "ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው"

የነዚህ ምሳሌዎች አብይ ነጥብ  የሰውን ልጅ መመለስ  በጥቂት ወራት ወይም አመታት ውስጥ እንዲጠብቁ አድማጮቹን ለማስተማር አልነበረም፤ ይልቁንም በእነዚያው ምሳሌዎቹን ቆመው ይሰሙ በነበሩ አንዳንድ ሰዎች የህይወት ዘመን ጌታ የሚመጣ መሆኑን ማመልከት ነው። በምሳሌዎቹ ውስጥ እንደሚመጣ የሚጠበቀው ጌታም ሆነ ሙሽራው ሲመጣ የሚታየው፣"ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ በሾመው ....ባሪያ" ዘመን፤ ወይም "በአምስቱ ሰነፎችና በአምስቱ ልባሞች ቆነጃጅት" ዘመን፤ ወይም "እያንዳንዳቸው መክሊትን የተቀበሉ ባሮች" ገና በሕይወት ባሉበት ዘመን፣ ማለትም በራሳቸው በባሮቹና በቆነጃጅቱ የህይወት ዘመን ነው እንጂ፤ የጌታቸውን መመለስም ሆነ የሙሽራውን መምጣት ይጠባበቁ የነበሩ ባሮቹም ሆኑ ቆነጃጅቱ ካለፉ ሺህ አመታት በኋላ አይደለም። ይህም ኃላፋውያኑ አበክረው የሚያስገነዝቡት ትርጉም ነው።

ይህ የቃሉ ግልጽ ትርጉም ምንም ሌላ ማብራሪያ ሳያስፈልገው የጌታ ዳግም ምጽአት ተስፋ ከተገባለት ትውልድ ዘመን ዘሎና በረጅሙ ተለጥጦ እነርሱ ካለፉ ከብዙ ዘመን በኋላ ሊፈጸም የሚችል እንደሆነ የሚያስበውንና እንዲህም የሚያስተምረውን የመጻኢያኑንና የኔን የራሴን የቀደመ አስተሳሰብ ውድቅ ያደርጋል። ቃሉ የታመነ ነው።

በግሌ ለማድረግ በቻልኩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኢየሱስ ከሺህዎች አመታት በኋላ እኛ ባለንበት ትውልድም ሆነ ወይም ከዚያ በኋላ ተመልሶ እንደሚመጣ የሚያስተምር አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ክፍል አላገኘሁም። ስለዚህ በጌታ ዳግም ምጽአትና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ባላቸው የነገረ ፍጻሜ ርእሰ ጉዳዮች ላይ "ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ" የሚል የእምነት መሰረት ያላቸው አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች የአስተምሕሮና የእምነት መሰረታዊ ተሃድሶ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል የሚል አቋም ይዤአለሁ።

፪. አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀም፦
የደብረዘይቱ ተራራ የኢየሱስ ትንቢት (ማቴ 24፤ ማር 13፤ ሉቃ 21) እና አጠቃላዩ የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ፣ ቀደም ሲል ሥነ ጽሁፋዊና ሥነ መለኮታዊ መሰረታቸውን በብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ  ያደረጉና፣ በ70 አ.ም ላይ የሆነውን የኢየሩሳሌምን ውድመት ሳይሆን በፊት በትንቢታዊ ንግርት የሚያመለክቱ፣ በአንድ አይነት አቡቀለምሲሳዊ የአጻጻፍ ፍሰት የተሰለፉ፣ በተምሳሌታዊና ትዕምርታዊ ትርጉም መታየት የሚገባቸው እንደሆኑ በኃላፋውያን የሚሰጠው ትምህርት ሚዛን የሚደፋና የትርጉም ቀዋሚነትን (consistency) የሚጠብቅ ነው።

በመጻኢያን በኩል ግን በተቃራኒው የሚቀርበውና ቋንቋው እንዳለ በፊት ለፊት የቀጥታ ትርጉም (literaly) መተርጎም አለበት የሚለው ሙግት ብዙ ርቀት አያስኬድም።

ጥያቄ ሦስት፦
ይህንን በደብረዘይት ተራራ ላይ የተነገረ ትንቢት እና የራዕይን መጽሐፍ ንግግሮች 'ባቢሎን' በሚል ቅጽል ስም በምትጠራዋ በኢየሩሳሌም ላይና፣ ወይም በአጠቃላይ በእስራኤል ላይ እንደሚሆን ወይም ሊሆን እንዳለው ፍርድ፣ ተምሳሌታዊ ወይም ትዕምርታዊ ነው ብለን እንድንተረጉም የሚያስችለን መጽሐፍ  ቅዱሳዊ የሆነ ምሳሌ አለን ወይ?

አዎ፦
(በቋንቋ እንድንግባባ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ገልጣችሁ በዚህ ስር የቀረቡትን እነዚህን የብሉይ ኪዳን ትንቢት የንባብ ክፍሎች በጥንቃቄ ተመልከቱ፤)
♦ ኢሳ 13 /በባቢሎን ላይ የሚሆነውን ፍርድ በተመለከተ/

♦ ኢሳ 34፥ 4 /የኤዶምያስን ጥፋትና ውድመቷን በተመለከተ/

♦ ሕዝ 32፥ 7-8 /የግብጽን ንጉስ የፈርዖንን ጥፋትና ውድመት በተመለከተ/

♦ ኢዩ 2፥ 10፤ 3፥ 15-16 /ጌታ በጠላቶቹ ላይ የሚያመጣውን ፍርድ በተመለከት/

♦ አሞ 8፥ 9 /ጌታ በያዕቆብ ቤት ላይ የሚያመጣውን ፍርድ በተመለከተ/

♦ 2ሳሙ 22፥ 1-18 /እግዚአብሔር እንዴት ከጠላቶቹና ከሳኦል እጅ እንዳዳነው የዳዊት አገላለጽ

♦ በተጨማሪም /መዝ 68፥ 7-9፤ 144፥ 5-6፤ ዕንባ 3፤ ሚክ 1፥ 3-4 ተመልከቱ/

እነዚህ ከላይ በዝርዝር የቀረቡ ብሉይ ኪዳናዊ ምሳሌዎች በዚሁ አይነት የሥነ ጽሁፍ ዘይቤ የተገለጡትን የአዲስ ኪዳን ትንቢቶች መልእክት ለመረዳትና የትርጉም ቀዋሚነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ አይነተኛ መርሆዎች ናቸው።

ጥያቄ አራት፦
የደብረዘይቱን ፍካሬ እና የራዕይን መጽሐፍ የሚሰሙም ሆነ የሚያነቡት በኩረ ተደራሲያን የሆኑ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሰዎች፣ እነዚህን መልዕክቶች የሚተረጉሙት በብሉይ ኪዳን በተመሳሳይ አገላለጽ ከተላለፉ መልዕክቶች በተቃራኒው፣ ማለትም በተቻላቸው ሁሉ የቀጥታ የቃል በቃል (LITERALY) ትርጉምን ተከትለው እንደሆነ የሚያመለክት የቅዱሳት መጻህፍት ድጋፍ ይገኝ ይሆንን?

በጭራሽ፦
በእነዚያ የጥንትና የድሮ ብሉይ ኪዳናዊ በሆኑ የአይሁድ ህዝብ አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀምና መረዳት ላይ በዘመናት ውስጥ የትርጉም ለውጥ መደረጉን የሚያመለክት አንድም ድጋፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማቅረብ ፈጽሞ አይቻልም። ትንቢት ሁሉ ተፈጽሞአል ብዬ አሁን በያዝኩት አዲሱ አቋሜ ላይ መሰረታዊ ተጽእኖን ያሳረፈ አንድ ጉዳይ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የአቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀም ለውጥና ልዩነት አለመደረጉ ነው።
የብርሃናት አምላክ ሆይ፣ ወደ እውነትህ እስክንደርስ ድረስ አትተወን። አሜን!

፫. የቃል በቃል ወይም የፊት ለፊት (litetal) ትርጉምን የሚቃረነው የትንቢት መንፈሳዊ ፍጻሜ (spiritual fulfilment)

ነገረ ፍጻሜን አመልካች የሆኑ ትንቢቶች /ESCHATOLOGICAL PROPHESCY/ በእጅጉ የቃል በቃል ትርጉም (በቁሙ ማለትም LITERALLY) ሲተረጎሙ ከመኖራቸው የተነሳ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል በጌታ ዳግም ምጽዓት ላይና በእግዚአብሔር መንግስት ትርጉም ላይ ያስከተለው የቆየ የመረዳት ስህተትና ችግር እንዳለ ኃላፋውያን በጽኑ ይሞግታሉ።

ጥያቄ አምስት፦
በነገረ ፍጻሜአዊ አውድ የተነገሩ ትንቢቶችን በእጅጉ "መንፈሳዊ"፣ ወይም ምሳሌአዊ (SYMBOLIC) በሆነ መንገድ ለመተርጎም የሚያስችል የቅዱሳት መጻሕፍት ድጋፍ ይኖር ይሆንን?

አዎ፦
ኢየሱስ ሲያስተምር  የኤልያስ ምጽዓት ነገረ ፍጻሜአዊ ትንቢት መንፈሳዊ በሆነ መልኩ በመጥምቁ ዮሐንስ እንደተፈጸመ ተናግሮአል። ዮሐንስ የመጣውም ሆነ ያገለገለው በኤልያስ መንፈስ ነው። ከነዚያ ትንቢታዊ መልዕክቶች ጋር ተጣምረው የቀረቡት ዝርዝር ጉዳዮችም ይኸውም፣ የሸለቆ ሁሉ ከፍ ማለት፣ የተራሮች ዝቅ ማለት፣ የሥርጓጉጡ ቀጥ ማለት፣ የተንጋደዱ መንገዶችም ትክክል መሆን ወዘተ እንደ አውራ ጎዳና ወይም እንደ መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ተግባር የቃል በቃል ፊት ለፊት literal ትርጉምን አያመለክትም። ይልቁን ግን እነዚህ ትንቢታዊ ቃሎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜአቸውን ያገኙት የሕጉ ምትክ ሆኖ በሚሰራውና በተሰጠን በጸጋው ወንጌል ነው።

ኢየሱስ "ወደ እናንተ ቀርባለች" እያለ ሲናገርላት የነበረችውም "መንግስት" ከዚህ አለም እንዳልሆነች ጨምሮ አስተምሮአል፦

"ኢየሱስም መልሶ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው"ዮሐ 18፥ 36

የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ በትንቢተ ኤርምያስ 31፥ 31-34 " እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን። እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና" ሲል የተነገረውም የአዲሱ ኪዳን ፍጻሜ የሚያገኘው በወንጌል አማካኝነት በቤተክርስቲያን ውስጥ እና ከቤተክርስቲያን ጋር እንጂ በእስራኤል ዘሥጋ እንዳልሆነ ያስተምራል። (ዕብ 8)

ዕብ 8፥ 6-13 "አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል። ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና። እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤ ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ። ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል። እያንዳንዱም ጐረቤቱን እያንዳንዱም ወንድሙን። ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም። አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል"

ጥያቄ ስድስት፦
ለትንቢት አተረጓጒም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በእጅጉ "መንፈሳዊ" የሆነውን አቀራረብ ስንመለከት፣ እነዚህ እዚያና እዚህ ተበታትነው የሚገኙ ብቸኛ ምሳሌዎች መሆናቸውን አመልካች የሆነ፣ ወይም የበለጠ በፊት ለፊት ቀጥተኛ ትርጉም LITERALLY የሚወሰድና ይህንን መንፈሳዊ ትርጉም የሚሽር የታወቀ የንባብ ክፍል በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ይኖር ይሆንን?

በጭራሽ፦
ሊመጣ ያለውን የሚያስተምረው መንፈስ ቅዱስ ለአማኞች ከተሰጠበት ከበአለ ሃምሳ ቀን በኋላ፣ ከአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እንኳ በአይነቱ ፊት ለፊት (litetall) የሆነ የትንቢት ፍጻሜ ስለሚታወቅበት፣ ከዘላለማዊው የወንጌል ዘመን ስለሚያልፍና ተዳሳሽ ስለሆነ መጻኢ መንግስት፣ ወይም ስለሌላ የሚቆጠር ወይም የማይቆጠር መጻኢ ስለሆነ የሺህ አመታት (ሚልንየም) ዘመን አለማውራታቸው አስገራሚ ጉዳይ ነው።

ስለዚህ የትንቢትን መንፈሳዊ ፍጻሜ (spiritual fulfillment) መረዳት በጌታ ዳግም ምጽአትም ሆነ ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ባላቸው በሌሎች የነገረ ፍጻሜ ርእሰ ጉዳዮች ላይ፣ ከተለመደው የአብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ በተቃራኒው እንድንቆምና፣ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ለአስተምህሮና ለአመለካከት ለውጥ፣ ለተሃድሶ እንድንጋብዝ ይገፋፋናል። መንፈሳዊ ተሃድሶም በባህርዩ የሁልጊዜ ቀዋሚ ሂደት (the ongoing process) በመሆኑ የኖረው እድሜ ጠገብ ልማዳዊው ነገረ ፍጻሜአዊ አስተምህሮ ላይ ለውጥ ማድረግ ተገድጄአለሁ።

፬. የእግዚአብሔር መንግስት ባህርይና ተፈጥሮ (በተለይ ከዳግመኛ ምጽዓቱ ጋር ካለው የቀረበ ግንኙነት አንጻር ሲታይ)

ስለ እስራኤል ህዝብ የወደፊት ተሃድሶና መመለስ እንደሚናገሩ የተገለጡ የብሉይ ኪዳን የተሥፋ ቃል በሙሉ በእርግጠኝነት፣ በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ ፍጻሜአቸውን እንዳገኙ በኃላፋውያን (preterists) የሚሰጠው ትምህርት በመጻኢያን ከሚሰጡ እርስ በርሳቸው ከተሳከሩ ልዩ ልዩ ትርጓሜዎች ይልቅ በእጅጉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአማኒነትን እና የትርጉም ቀዋሚነትን አጥብቆ ያንጸባርቃል። ለምሳሌ ቀጣዮቹን ምንባባት እንመልከት፦

ዮሐ 18፥ 36-37 "ኢየሱስም መልሶ። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው። ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው"

ሉቃ 17፥ 20-21 "ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ። የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው"

ማቴ 12፥ 28" እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች"

ሮሜ 14፥ 17 " የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና"

1ቆሮ 4፥ 20 " የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና"

1ቆሮ 15፥ 50  "ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም"

ቆላ 1፥ 13 "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን"

2ጢሞ 4፥ 18 "ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን"

ዕብ 12፥ 18 " ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና"

ቁ 22-24 " ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል"

ቁ 28 " ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ"

1ጴጥ 2፥ 9 " እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ"

ጥያቄ ሰባት፦
በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተሰጠው ትርጉም የእግዚአብሔር መንግስት በባህርዩ ወይም በተፈጥሮው መንፈሳዊ ሆኖ ተገልጧል፣ ታዲያ ስለሚመጣ ተዳሳሽ ፖለቲካዊና መልክዓ ምድራዊ መንግስት የሚያስተምር አንድ የአዲስ ኪዳን ምንባብ ይኖር ይሆንን?

በጭራሽ፦
በአይሁዶችም ሆነ በመጻእያን ክርስቲያኖች literally የሚተረጎሙ የብሉይ ኪዳን ምንባባት፣ በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ አዲስ ኪዳንን በጻፉልን የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈሳዊ መልኩ ተተርጉመዋል። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ከበአለ ሃምሳ ቀን በኋላ መጻኢ ስለሆነ ተዳሳሽ የፓለቲካና የመልክዓ ምድር መንግስት የተሰጠ ምንም ትምህርት ሆነ ተስፋ በአዲስ ኪዳን የለም። በዚህ ንዑስ ርእስ ስር በምሳሌነት የጠቀስኩአቸውን የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባትም ሆነ ሌሎች ተዛማጅ ጥቅሶችን እያነበበ አሁንም ስለምድራዊ መንግስት የሚያስብ አማኝ የተታለለ አንባቢ ብቻ ነው።
 
፭. የጌታ ምጽዓት ባህርይና ተፈጥሮ፦
የጌታን ዳግመኛ ምጽአት፣ እንዲሁም የመንግስቱን ባህርይና ተፈጥሮ አጅበው ያሉ ሁነቶች የተብራሩበት ቋንቋ በቤተ ክርስቲያን ልማዳዊ አስተምህሮ ውስጥ ያለ አግባብና ከአውዱ ተነጥሎ በተሳሳተ መንገድ ሲተረጎም ኖሯል ብለው ኃላፋውያን የሚተቹና የሚነቅፉ ከሆነ፤ እንግዲያውስ የጌታ ዳግመኛ ምጽአት (parusia) ባህርይና ተፈጥሮ መተርጒም ያለበት በብሉይ ኪዳን ስለ ጌታ ምጽአት በተነገሩና በተስጡ መግለጫዎች አንጻር በአንድ መስመር ላይ የትርጉም ቀዋሚነትን ሕግ ጠብቆ መሆን ይኖርበታል። አዲስ ኪዳንም በደመና ስለሚሆነው የጌታ ምጽአት ሲያስተምር፣  እግዚአብሔር  ህዝቡን ለማዳን እና በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ እንዴት እንደሚመጣ ብሉይ ኪዳን በሚናገርበት መንገድ ያስተምራል እንጂ፣ አዲስ ኪዳን በብሉይ ኪዳን ያልታወቀ ሌላ አይነት የምጽአት ቅርጽና መልክ የለውም ሲሉ ከብዙ በጥቂቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን እነዚህን የአዲስ ኪዳን ምንባባት ዋቢ በማድረግ አጥብቀው ይሞግታሉ፦

ማቴ 24፥ 30 "የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል"

ማር 14፥ 61-62 " እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ"

ሐዋ 1፥ 9-11 " ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው"

1ተሰ 4፥ 17 "ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን"

ራዕ 1፥ 7 " እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን"

14፥ 14 "አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው"

ጥያቄ ስምንት፦
ህዝቡን ለማዳን እና በጠላቶቹ ላይ ለመፍረድ እግዚአብሔር በደመና የሚመጣ መሆኑን በተመለከተ የተነገረ የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ ከብሉይ ኪዳን ይኖር ይሆንን?

አዎ፦
መዝ 18፥ 7-15 "ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ። መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውኃ ነበረ። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ። እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፤ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም። አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከመዓትህም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ"

መዝ 104፥ 3 "እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ"

ኢሳ 19፥ 1 "ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል"

ኢዩ 2፥ 1-2 "የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፥ እርሱም ቀርቦአልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፤ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፤ ከዘላለምም ጀምሮ እንደ እነርሱ ያለ አልነበረም፥ ከእነርሱም በኋላ እስከ ብዙ ትውልድ ድረስ እንደ እነርሱ ያለ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም"

ናሆ 1፥ 2-3 "እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ተበቃይና መዓትን የተሞላ ነው፤ እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፥ ለጠላቶቹም ቍጣውን ይጠብቃል። እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም ንጹሕ ነህ አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው"

ሶፎ 1፥ 14-15 " ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል። ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን"

በብሉይ ኪዳን የተነገረው ደመናና የእግዚአብሔር በደመና መምጣት በአህዛብና በጣኦቶቻቸው ላይ የሚሆነውንና በየዘመኑ በሚነሱ የምድር ኃያላን ነገሥታት የጦር ሰራዊት አማካኝነት ተፈጻሚ የሚሆነውን መለኮታዊ ፍርድና በቀል የሚያመለክት ከሆነ፣ በአዲስ ኪዳን የተነገረው የአምላካችን የኢየሱስ በደመና መምጣትም ከዚህ የተለየ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። 

ጥያቄ ዘጠኝ፦
"በደመና መምጣት" ከጌታ ዳግመኛ ምጽአት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ለመቃወም የሚያስችል፣  ምጽአቱንም በእጅጉ literal ትርጉም የሚያላብስ አንዳች የአዲስ ኪዳን ማስርጃ ይኖር ይሆንን?

የጌታን ዳግመኛ ምጽአት ባህርይና ተፈጥሮ በዚህ አጭር የመግቢያ ጥናት ጠንቅቆ ለማቅረብ አስቸጋሪና ውስብስብ ነው። ሆኖም በጉዳዩ ላይ በአንክሮ ማስብ ለሚሻ አእምሮ ተከታዩን እይታ ማቅረብ እወዳለሁ፦

1ኛ/ በደመና የሆነው የጌታ ዳግመኛ ምጽአት በብሉይ ኪዳን ከተነገረውና በደመና የሚሆነውን የእግዚአብሔር መምጣት ከሚያመለክቱ ምንባባት ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነትና ተመሳሳይነት መካድ አይቻልም።

2ኛ/ ዳግመኛ ምጽአትን "በፍርድ ደመና ከመምጣት" በላይ ለጥጦ በተለምዶ በአብያተ ክርስቲያናት አስተምህሮ ውስጥ ያለ በቂ ጥናት ሲደረግ እንደኖረው፣ በስሜት ለመተርጎም መሞከር፣ አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ አጠቃቀምን እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንግስት ባህርይና ተፈጥሮ ከነገረ ፍጻሜ እስተምህሮ ውስጥ በግብታዊነት ገነጣጥሎና ቀድዶ እንደመጣል ይቆጠራል። እነዚህ ጉዳዮች ከተወገዱ ደግሞ "አካላዊና ተዳሳሽ" እንደሆነ በሚታሰበው የመጻኢያን የዳግመኛ ምጽአቱ ትርጉም ላይ ይጥለናል።

ምን ለማለት እንደፈለግሁ በሚከተሉት አምስት ነጥቦች ሃሳቤን አጠር አድርጌ ላቅርብ፦
1. ኃላፋውያን የክርስቶስ መመለስ በክርስቶስና በደቀመዛሙርቱ ትውልድ ውስጥ መሆኑን የሚደግፍ ከበቂ በላይ የሆነ ሊስተባበል የማይችል የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ አላቸው። መጻእያን ግን ለሺህ አመታት እንደሚዘገይ ሊደግፋቸው የሚችል ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የላቸውም።

2. ኃላፋውያን የደብረዘይቱ የጌታችን ፍካሬ እና የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍ አስቀድሞ በታወቀ ቀጣይ የአቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ ዘይቤ የተጻፈ መሆኑን የሚያሳይ ከበቂ በላይ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አላቸው። መጻእያን ግን የደብረዘይቱ የጌታችን ፍካሬም ሆነ ወይም የራዕይ መጽሐፍ አስቀድሞ ከተመሰረተውና ቀጣይ ከሆነው ዘይቤ በተለየና በተቃራኒው የሚተረጎሙ እንደሆነ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የላቸውም። እንዲህ ያለ የማስረጃ እጦት ደግሞ የኢየሱስን እና የዮሐንስን የመጀመሪያዎቹን አድማጮችና አንባቢዎች፣ አይሁድ ለዘመናት እንዲህ ያለውን አቡቀለምሲሳዊ ቋንቋ ሲተረጉሙ ከኖሩበት ተመሳሣይ መንገድ በተለየ እነዚህን መልዕክቶች  እንዲተረጉሟቸው ባደረገ ነበር።

3. ኃላፋውያን በእጅጉ "መንፈሳዊ" በሆነ መልኩ ትንቢትን ለመተርጎም የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃን ማቅረብ ይችላሉ። መጻእያን ግን ምንም እንኳን ለቃል በቃል የፊት ለፊት ትርጉም (literal interpretation) እስካሁን ድረስ ሽንጣቸውን ገትረው ቢከራከሩም በኃላፋውያኑ የሚቀርቡትን ማስረጃዎች በበቂ መከላከልም ሆነ ዋጋ ያለው የተቃውሞ ማስተባበያ ሊያቀርቡ አልቻሉም።

4. የእግዚአብሔርን መንግስት ተፈጥሮና ባህርይ አስመልክቶ  በተወሰኑ የንባብ ክፍሎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ አሻሚ የሆነ ትርጉም ያለው ቢመስልም፣ እነዚያ የሚበዙት ግልጽ የሆኑትና የማያሻሙት የንባብ ክፍሎች ግን አጠንክረው የሚወግኑት፣ በእስራኤል ሕዝብና መንግሥት መታደስ በኩል ይመጣል ተብሎ በብዙዎች ከሚጠበቀው ተዳሳሽ ከሆነው መንግሥት ይልቅ በተቃራኒው የቆመውን መንፈሳዊ የሆነውን መንግስት ነው። እነዚያም አሻሚ የሚመስሉ ጥቂት የንባብ ክፍሎች በአንድ ፍሰት በተሰጡና ግልጽ በሆኑት በሚበዙት የንባብ ክፍሎች አውድ ውስጥ ተገዝተው መተርጎም ይኖርባቸዋል።

5. የዳግመኛ ምጽአቱም ተፈጥሮና ባህርይ ከፍ ሲል ከቀረበው ነጥብ በቀላሉ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። የሆነ ሆኖ፣ ቀደም ሲል ለተጠቀሱት (4) ነጥቦች የቀረቡት ማስረጃዎች የኃላፋውያኑን ትርጉም ተመራጭ ለማድረግና በመጻእያኑ አቋም ላይ ሊቋቋሙት የማይችሉትን ከባድ ጫና ለማሳረፍ ከበቂ በላይ ናቸው።

፮. ይህ የአመለካከታዊ እርማት ጥሪ በመሰረታውያኑ የክርስትና የመጀመርያ አስተምህሮቶች ላይ ለውጥ የማድረግ ጥሪ አይደለም፦

ጥያቄ አስር፦
በዳግመኛ ምጽዓቱ አስተምህሮ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአመለካከት እርማት ማድረግ ይገባል ማለት በመሰረታውያን የክርስትና የመጀመርያ አስተምህሮቶች ላይ ለውጥ ማድረግ ነውን?

በጭራሽ አይደለም።

ወደ ማጠቃለያዬ ከማለፌ በፊት የብዙ ሰዎችን ጥርጣሬ ለማስወገድ ላስተላልፍ የምፈልገው የምከተለው የኃላፋውያን የነገረ ፍጻሜ አቋም መሰረታዊውን የክርስትና አስተምህሮ አጥብቆ የያዘ እንጂ በመሰረታዊው የክርስትና ትምህርት ላይ ያደረገው ለውጥ እንደሌለው ማረጋገጥ ነው።

ይህ የነገረ ፍጻሜ ትምህርት የክርስትና የመጀመርያ ነገሮችን በተመለከተ ምን ያምናል?

1. የእግዚአብሔርን ባህርይ በተመለከተ፦
የአጥናፍ አለሙ ሁሉ ፈጣሪና ጠባቂ መሆንኑን ያምናል። እግዚአብሔር ሥሉስ ቅዱስ መሆኑንና አንድ አምላክ ከዘላለም አብረው በሚኖሩ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሆኑ ሦስት አካላት የተገለጠ አምላክ መሆንኑን ይቀበላል። በኒቅያ የሃይማኖት መግለጫ እንደተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ እንደ እግዚአብሔር አብ ሁሉ አንድ መለኮታዊ ባህርይና መሰረታዊ ጠባይ እንዳላቸው፣ ማናቸውም በስራና በማእረግ ከማናቸውም የማያንሱ ወይም የሚበልጡ እንዳልሆኑ በጥብቅ ያምናል ያስተምራልም።

2. የሰውን ተፈጥሮ በተመለከተ፦
ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ መሆንኑንና የእግዚአብሔር ክብር የጎደለው መሆኑን ያምናል።

3. ኃጢአተኛው ሰው ከቅዱሱ አምላክ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ በተመለከተ፦

ወንጌል ብቻ መንገዱ መሆኑን ያምናል። የዳንነው በእግዚአብሔር ጸጋ በኩል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ በሚሆን ህያው እምነት ነው። ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ፍጹም የመታዘዝ ሕይወት፣ ለኃጢአት ቅጣት የተከፈለው መስዋእታዊ የቤዛነት ሞቱ፣ የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ሊሰጠን ከሙታን መነሳቱ፣ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን የተሰጠውን ተስፋ በኪዳኑ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅና መፈጸም መዳናችንን ያተመበት ዳግመኛ ምጽአቱ የደህንነታችን ሙላት መሆኑን ያምናል።

4. መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ፦
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተሰጠ  መሆኑንና፣ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ያምናል። ስለዚህም እጅግ ብዛት ባላቸው ምንባብቱ ስለ መጨረሻው ቀን ሲናገር ያንንው የመጀመሪያውን ምዕተ አመት እያመለከተ፣ የሙሴ ሥርዓት (despensation) የሆነው አሮጌው ኪዳን በ70 አ.ም ላይ ያበቃለት መሆኑን በመናገሩ ለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የዘመን ምድብ ይገዛል። በዚያን ጊዜ ኢየሩሳሌምና መቅደስዋ ተደምስሰው ጠፍተዋል፤ ያ ተፈላጊ የነበረው የዘር ሃረግ ፈጽሞ ከምድር ገጽ በመደምሰሱ እንዲቋረጥ ተደርጎአል። ጥንታዊውም የአይሁድ የኃጢአት መስዋእት ስርአት እንዳይቀጥል ተዘግቶአል።

5. ስለ ሰማይ የሚሰጠውን አስተምህሮ በተመለከተ፦
ሰማይ አማኞች የምድር ላይ ሕይወታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለዘላለም የሚኖሩበት ስፍራ መሆኑ፣ ኢየሱስ ስለ ዘላለም ሕይወት ከሰጠው የተስፋ ቃል ጋር አብሮ የተሰጠ ተስፋ መሆኑን ያምናል። ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ቢሆን ስለ ሰማይ ያላቸው መረዳት  ከምድር ላይ ኑሮ በተሻለና በሚበልጥ ሁኔታ አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖሩበት እንደሆነ ነው። መቼም ቢሆን ሰማይ የአማኞች የተረጋገጠ ተስፋ ነው።

6. ኃላፊነታችንና ግዴታችንን በተመለከተ፦
ለእግዚአብሔር ጸጋ በሚሆን ምላሽ በትህትናና በታማኝነት ቅንነትም በተሞላ አካሄድ ፈቃዱን ባወቅን ልክ እርሱን መታዘዝ እንደሚገባን ያምናል። ይህንንም ሰፋ ባለ መልኩ የሚገልጠው ጌታ አምላክን በፍጹም ልብ፣ ነፍስ፣ ሃሳብና ኃይል መውደድና ባልንጅራችንንም(ጠላቶቻችንንም ቢሆን እንኳ) እንደ ራስ መውደድ እንደሚገባን የተገለጠው ፈቃዱ ነው። ልናደርገው የሚገባንም ማናቸውም የርህራሔ ስራ ብዙ ሰዎችን ከክርስቶስ ጋር ወዳለ የመዳን ሕብረት የሚያመጣቸው መሆንም እንዳለበት ያስተምራል።
 
የሆነው ሆኖ በዚህ ጽሁፍ በግልጽ ለማስተላለፍ እንደሞከርኩት ስለ"መጨረሻ ነገሮች" የተነገሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶችን አስመልክቶ የሚበዙትና ታዋቂ የሆኑት ዘመናዊ አመለካከቶች ፈጽሞ የተሳሳቱ እንደሆኑ ደግሞ ያምናል። "የሚበዙትም አብያተ ክርስቲያናት ስለ መጨረሻው ቀንና ስለ ዳግም ምጽአት የተሳሳተ ትርጉም ተከትለው ስህተት እንደሚያስተምሩ እናምናለን። ይህንን ስንል ተቃውሞአችንና ወቀሳችንን አበክረን እናስታውቃለን እንጂ በቀላሉ አንመለከተውም" ሲሉ ኃላፋውያን በጥብቅ ያሳስባሉ።

ኃላፋዊ የተሰኘውና እኔም የተቀበልኩት ይህ የነገረ ፍጻሜ አመለካከት፣ ኢየሱስና የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ካስተማሩት ትምህርት ጋር የሚስማማ መሆኑን፣  እነርሱ ራሳቸውም በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ደጋግመው በግልጽ ማስተማራቸውን፣ የመጨረሻው ዘመንም ገና ወደፊት የሚመጣ አለመሆኑን አረጋግጦልኛል። የመጨረሻውን ዘመን በአግባቡ ለመረዳትና እርማት ለማድረግ  ክርስቲያኖች ከግልቢያ ንባብ ተቆጥበው ወደ አዲስና ብሉይ ኪዳን ገጾች በጥንቃቄ መመለስ እንዳለባቸውም እመክራለሁ።

ስለዚህም፦
♦ታዋቂ ከሆኑት የነገረ ፍጻሜ አመለካከቶች ርቄ፣ ምጽአቱን ጨምሮ ሁሉም ትንቢት በእርሱ ትውልድ ውስጥ የሚፈጸም መሆኑን በበርካታ የወንጌላት የንባብ ክፍሎች በግልጽ ሲናገር በእርግጥም ጌታ ኢየሱስ እንዳልተሳሳተ፣ እውነቱንም ይናገር እንደነበር ለማመን በቅዱስ ቃሉ እገደዳለሁ (ለምሳሌ፦ ማቴ 10፥ 23፤ 16፥ 27-28፤ 23 ፥36፤ 24፥ 34፤ 26፥ 64፤ ማር 8፥ 38-9፥ 1፤ ሉቃ 21፥ 22፣ 32፤ ራእይ 1፥ 1-3፤ 22፥ 6-20፤ ወዘተ..) እንደውም ጊዜ ጠቋሚ የሆኑትንና ከምጽአቱ ጋር ተቆራኝተው የተዘገቡትን የአዲስ ኪዳን ምንባባት በጥንቃቄ ለሚመለከት አንባቢ ፍጻሜአቸውን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን አውድ አውጥቶ በሌላ ዘመንና ትውልድ ውስጥ ለመጠባበቅ የሚያስችለው ምንም የቃሉ ድጋፍ እንደሌለው ይረዳል ባይ ነኝ።

♦የመጨረሻው ዘመንም ሆነ ወይም የመጨረሻው ቀን ማለት የአሮጌው ኪዳን ስርአት በ70 ዓ.ም ላይ በኢየሩሳሌምና በቤተመቅደሱ ውድመት ያበቃበት የመጨረሻ ቀን ማለት እንደሆነ ይህንን መረዳት ይዤአለሁ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የመጨረሻው ቀን ወይም የመጨረሻው ዘመን ተብሎ ከ15 ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ በንባብ ክፍሎቹ በአንዳቸውም ቢሆን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የዘለለ ሌላ ዘመን እንድናስብ የሚያግዘን አንዳች ሃሳብ የለባቸውም (ለምሳሌ፦ ሐዋ 2፥ 14-20፤ 1ቆሮ 7፥ 29-31፤ 10፥ 11፤ እብራ 1፥ 2፤ 9፥26፤ 1ጴጥ 1፥ 5፣ 20፤ 4፥ 7፣ 17፤ 1ዮሐ 2፥ 17-18፤ ወዘተ...)። የመጨረሻው ዘመን ማለት የአሮጌው አለም የሙሴ ዘመን መጨረሻ፣ የአሮጌው ኪዳን የአይሁድ ሥርአት (Despensation) ማብቂያ ማለት እንጂ፣ የፕላኔትና የተፈጥሮ ስርአት ማብቂያ ማለት ጨርሶ አይደለም።

ኃላፋውያን አፈንጋጭ የሆነውን የሺህ አመት መንግስት (Millennialism) አስተምህሮ፣ በተለይም ልዩ ወንጌል የሆነውን  የዘመን ቆጣሪነት (Dispensationalism) አመለካከት አንቀበልም። እምነታዊነት (Fideism)፣ ወግ አጥባቂነት (Nominalism)፣ ሕገ ወጥነት (Antinomianism)፣ ለዘብተኝነት (Liberalism)፣ ሕግ አክራሪነት (Legalsm)፣ እና ሁሉ አቀፋዊነት (Universalism) በእኛ በኃላፋውያን ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። በተለይም ከ70 ዓ.ም በኋላ እግዚአብሔር በሰዎች ላይ መፍረድ አቁሞአል ፣ የእግዚአብሔር የማዳን ስራ በ70 ዓ.ም ላይ አቁሞአል፣ የሰው ኃጢአት ከ 70 ዓ.ም በኋላ ፈጽሞ የሚታሰብና ከቁጥር የሚገባ ጉዳይ አይደለም፣ ሰማይ እዚሁ ምድር ላይ ነው፣ ወይም አሁን በምድር ላይ ካለንና ካገኘነው የሚበልጥ ነገር ሰማይ የለውም፣ ክርስቲያኖች ቅዱስ ጥምቀትንና ቅዱስ ቁርባንን መቀበላቸው አስፈላጊ አይደለም የሚል አስተሳሰብ የሚያራምደውንና ከወንጌላዊው ኃላፋዊነት (Evangelical Preterism) ያፈነገጠውን "ምጥቀ ኃላፋውያንነትን" (Hyper preterism) አጥብቀን እንቃወማለን።

ስለሆነም በዚህ መሰረት ዳግመኛ ምጽአቱን፣ ታላቁን ፍርድና የሙታን ትንሣኤን የሚያጠቃልለው ሁሉም ነገረ ፍጻሜአዊ ተስፋ በ 70 ዓ.ም ላይ መፈጸሙን ሳምን፣ የእግዚአብሔር ስራ ግን ከ70 ዓ.ም በኋላም ቀጥሎ ያለ፣ ያልተቋረጠና ቀጣይ እንደሆነም ጭምር አምናለሁ። የክርስቶስ ስራ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ጅማሬው ነበር እንጂ ፍጻሜው አልነበረምና። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱሳዊው የመዳን ተስፋ ክርስቶስ አሁን ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ ለዘላለም የነገሰ እስከሆነ ድረስ ለአለምና ለዘለአለም እየተሰበከና እየታወጀ፣ ሰዎችንም ወደ መንግስቱ እየጋበዘ ይኖራል (ኢሳ 9፥ 6-7፤ ሉቃ 1፥ 31-33፤ ኤፌ 3፥ 21)። የሰው ኃጢአተኛ ተፈጥሮ፣ ቀጣይ የሆነም የደህንነት ፍላጎት፣ በጽድቅ ላለው ምክር የሚጠቅም ተግሳጽና እርማት በ70 ዓ.ም ላይ ያበቃለት ጉዳይ እንዳልሆነም እረዳለሁ። በጥንታዊው የእምነት ማህበረ ሰብ ውስጥ ሥነ መለኮታዊ መሳሳቶችም የነበሩ መሆናቸውን ብረዳም፣ ከላይ በነጥብ ባሳየኋቸው የክርስትና የመጀመርያ አስተምህሮዎች አንጻር አንድነትን ጠብቆ ለመዝለቅ ከጥንታዊው ክርስትና ጋር ተጣብቆ መቆየት አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ክርስትና ታሪካዊ እምነት ነው፣ ቆመን ያለነውም ከእኛ አስቀድሞ በነበሩና ባለፉ ሰዎች ትከሻ ላይ ነው።

ስለዚህ ነገሬን ከመጠቅለሌ በፊት፣ በእርግጥ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ የሆነው ምንድር ነው? ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የኃጢአታችንን እዳ ከፍሏል፣ ያም የመዳናችንም ተመርቆ መሰጠት (inaguration) ነው። ይህንንም አስረግጦ የሚነግረን በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ግልጽ ነው (ሮሜ 8፥ 1-4፤ 1ቆሮ 15፥ 3፤ 2ቆሮ 5፥ 17-21፤ እብ 9፥ 15-26፤ ወዘተ..)።

ይሁን እንጂ የጌታችን የቤዛነት ዋጆአዊ ስራና አጠቃላዩ የደህንነት እቅድ የሚጠቃለለው በምጽአቱ እንደሆነም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል፣ - ይኸውም ክርስቶስ በ70 ዓ.ም ከተማይቱንና መቅደስዋን ለማጥፋት ሲመጣ ያኔ በይፋ እንደሚጠናቀቅ እና ለቅዱሳኑም ፍጽምናን የሚያቀዳጅ መሆኑ (Consummation) ነው (ሉቃ 21፥ 28፤ ሮሜ 13፥ 11-12፤ እብራ 1፥ 14፣ [በተለይም "ስላላቸው" ለተሰኘው የግሪኩ አቻ ግስ 'mello' በእንግሊዝኛው "about to" መሆኑን ስናስተውል ጉዳዩ ተፈጻሚ ስለሚሆንበት ጊዜ ላቅ ያለ ትርጉም ይሰጠናል]፤ እብራ 9፥ 26-28፤ 1ጴጥ 1፥3-9፤ ራእይ 12፥ 10 ወዘተ...)። ይህም የአማኞችን ሁሉ መዳን ለወደፊቱም አትሞ የሚያጸናውና በይፋ የሚያቀዳጃቸው ተግባር ነው።

እነዚያ ድነው የጌታን በፍርድ መመለስና የቤዛነታቸውን ቀን በትውልዳቸው ውስጥ በመቃተት እየተጠባበቁ፣ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናቸውን ይፈጸሙ የነበሩ የመጀመርያው ክፍለ ዘመን ቅዱሳን ከክርስቶስ እርገት እስከ70 ዓ.ም ባሉት አርባ አመታት በሚሸፍን የሽግግር ዘመን (The Olready not yet) ተብሎ በሚገለጥ ጊዜ ውስጥ ነበሩ። እነዚያ ምእመናን ኃጢአትን ሊሺር በተገለጠው በክርስቶስ ሞት ድነዋል፤ ደግሞም መገለጡን እየናፈቁ ለመዳን ሁለተኛ ጊዜ ያለኃጢአት ይታይላቸው ዘንድ ይጠባበቁታል። በ70 ዓ.ም ላይ የእስራኣልን ዘመን በእሳት ፍርድ እስከወዲያኛው በዘጋው በክርስቶስ ዳግመኛ ምጽአት ዘላላሙ ተጀምሮአል። እነሆ ክርስትናችን አዲሱ ሰማይና ምድር፤ ሃሌሉያ! በክርስቶስ ድል መንሳት በደስታ እንኑረው። "የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት።" (ምሳሌ 13፥ 12) ተብሎአልና። ስለሆነም፣ ነገረ ፍጻሜአዊ የሆኑና የተሰጡ የመጨረሻው ዘመን ተስፋዎች፣ ፍጻሜ የሌለውንና ከክርስቶስ ጋር የተቀበልነውን የአዲሱን ኪዳን የመጀመርያ ነገሮች አስተምህሮት አስፈላጊነት በጉልህ የሚያሳዩ ናቸው። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች ፍጻሜ ለጥንታዊው ክርስትና ያለንን አክብሮትና ታማኝነት በሚያጠናክር መረዳት ይሞላናል እንጂ፣ ብዙዎች ያለ እውቀት እንደሚጠረጥሩን ከእርሱ አይነጥለንም። በእኔም ውስጥ የሆነው እንደዚያ ነው።

"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?....ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" (ሮሜ 8፥ 35፣ 38-39)   

ማጠቃለያ፦
በኔ እምነትና በያዝኩት አቋም ግልጽ ላደርገውና ሁሉንም ሰው ላበረታታ የምፈልገው፣ ይህ የዳግመኛ ምጽአት ጉዳይ በሰከነ እና ክርስቲያናዊ በሆነ የሚያስብ አእምሮ የበለጠ ጥናትና ምርምር ሊደረግበት የሚያስፈልገው እውነት መሆኑን ነው። የመጻእያኑ አቋምም ቢሆን በራሱ በኩል ልማድን እና በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትን ያካበተ ቢሆንም፣ ባቀረብኳቸው ማስረጃዎች ቀዳሚና የመጀመሪያ ሆነው የሚበዙት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክርነቶች ግን የኃላፋውያኑን አመለካከትና አቋም መቶ በመቶ መደገፋቸውን ያሳያሉ።

በመጨረሻም፣ የትርጉምና የአመለካከት ለውጥ እንዳደርግ በግሌ የደረስኩበት ይህ ማጠቃለያ ጌታ ጸጋውን ባበዛልኝ መጠን፣ የአመታት ጥናትና ንባብ ውጤት መሆኑን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። ይኸውም ጽሁፍ የህትመት የጊዜውን ከሚጠብቀው የጀማሪ መጽሐፌ ላይ በከፊል የተወሰደ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ በከንቱ ሮጬ እንዳይሆን "ቅዱስ ቃሉ ብቻ" ቀኝ እጁን እንዲሰጠኝ፣ በአዲስና በብሉይ ኪዳን የተገለጠው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የሐዋርያቱና የነብያቱ ምስክርነት ብቻ እንዲያቆመኝ አምናለሁ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ የማከብራቸው የቃሉ ወዳጆች ምክርም እንዳይርቀኝም ተስፋ አደርጋለሁ።  

ይህንን የዳግመኛ ምጽአቱን ተፈጥሮና ባህርይ ባሰላሰልንበትና በዳግመኛ ምጽዓቱ አስተምህሮ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአመለካከት እርማት ማድረግ እንደሚገባ በሞገትከበት በዚህ አጭር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሁፍ ማጠቃለያ ላይ ላነሳ የምፈልገውና ለውይይትም ቀርቦ ሁሉም ሰው በቅንነት፣ በሰለጠነም የክርስቲያን መንፈሳዊነትና ምሁራዊ በሆነ የሚያስብ አእምሮ ሊመልሰው የሚገባ አንድ ትንሽ ጥያቄ፦ አግባብነት ያለው የነገረ ፍጻሜ አስተምህሮ አጠቃላይ ክለሳና የአመለካከት እርማት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? በእጅጉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ድሮ ገና ተፈጽሞአል" የሚለውን ይህንን የነገረ ፍጻሜ አመለካከትና አቋምስ ብዙ ሰዎች ለምን አይቀበሉትም? የሚል ነው።

ጽሁፌን በአርምሞ ላያችሁልኝ ሁሉ የቃሉ በረከት ያግኛችሁ! `

ግዛቸው ከበደ /ቄስ/
ተጻፈ ወርሃ የካቲት 2014 ዓ.ም
አንካራ፣ ቱርክ