ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ዘመንና ትውልድ ሲወስንና፣ ተከታዮቹም የትንቢቱን ፍጻሜ እርሱ ባመለከታቸው የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ ነቅተው እንዲጠባበቁት ሲያስተምራቸው፣ ጌታ ኢየሱስ ፈጽሞ አልተሳሳተም ነበር። እርሱ በዚያው በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ ዳግመኛ የሚመለስ ስለ መሆኑ በግልጽ የተናገረውን የትንቢት ቃል ለማብራራትም 'ዘግይቶ የመፈጸምን አስተምህሮ' ወይም የመመለሻውን ጊዜ የሚያራዝምና ለሌላ ጊዜ የሚያስተላልፍ 'ስነ መለኮታዊ መተጣጠፍ' እየሰራን ትንቢቱን ማቃናትም ሆነ ድጋፍ ልናደርግለት አያስፈልገንም፣ አይገባንምም። "ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም" ተብሎ እንደተጻፈ፣ የትንቢቱ ቃል ሌላ ሰብአዊ ምርኩዝ ሳያስፈልገው ብቻውን ብቃት ያለው፣ በራሱ የቆመና ራሱን የሚተረጉም ሕያው ነው። ትንቢቱ ተፈጻሚ ስለሚሆንበትም ጊዜ በራሱ ግልጽና እርግጠኛ ነው። ነብዩም ሆነ የትንቢቱ ቃል ለእውነተኝነታቸው ታማኞች ናቸውና።
ሁሉም ነገር ተፈጻሚ የሆነው "ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም"፣ "ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል"፣ "ይህ ሁሉ መሆኑን እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ" በሚል "ጊዜን አመልካች" በሆነ አነጋገር በተገለጠ፣ ደግሞም በተቀጠረው ዘመንና በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት ነው። በርካታ የስነ መለኮት ሰዎች በ70 አ.ም ላይ የሆነውን የኢየሩሳሌምን ውድመትና የቤተመቅደሱን መፈራረስ በተመለከተ በከፊል በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተንትኖአቸው ውስጥ በግርድፉ ቢያነሱትም ቅሉ፣ በእግዚአብሔር የደህንነት ታሪክ መርሃ ግብር ውስጥ የያዘውን ሙሉውን ዋጋና ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ቀዋሚነት የሚሰጠውን ትርጉም ደግሞም አስፈላጊነቱን በሚገባ አያስተውሉትም። በ70 አ.ም በእስራኤል ህዝብ ላይ የደረሰው እልቂተ መቅሰፍትና፣ በኢየሩሳሌም ከተማና በተወደደው ቤተመቅደስ ላይ የመጣው ውድመት አጠቃላይ ተዛምዶውና ግንኙነቱ ከደህንነት ታሪክ እቅድ ተጠቃሎ መፈጸም ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እግዚአብሔር ከዘላለም ያቀደው የደህንነት ታሪክ ተመርቆ የተሰጠው በመስቀሉ ስራ ሲሆን ተጠናቆ በይፋ የታወጀውና የተገለጠውት ሐዋርያቱ በነበሩበት በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ትውልድ ነው። በ70 ዓ.ም በኢየሩሳሌምና በቤተመቅደሱ ላይ በሆነው ፍርድ መንግስቱን ገለጠው። ቃሉም የሚናገርለት የዘመን ፍጻሜና የዘላለም ጅማሬ ይኸው ነው።
ብዙዎች ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የዘመን የቀመር ባለመረዳት ይህንን የአለም ፍጻሜና የዘላለም ጅማሬ ገና ወደ ፊት ይጠባበቁታል። እውነታው ግን ገና ወደ ፊት ፍጻሜውን እንድንጠብቅ የሚገፋን አንዳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትም ሆነ ሳይፈጸም የቀረ ምንም ተስፋ በቅዱስ ቃሉ ውስጥ አለመኖሩ ነው። ተስፋ የነበረው ነገር ሁሉ አሁን ተገኝቶአል እንጂ ተስፋ መሆኑ አልፎአል። ሙታንንም ሕያዋንንም ሁሉ ይገዛ ዘንድ የሞተውና ከሙታን የተነሳው፣ እመለሳለሁም ብሎ በሰጠው የተባረከ ተስፋ ወደ ሰማይ አርጎ በአብ ቀኝ የከበረው ክርስቶስ፣ ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ የጌታዎች ሁሉ ጌታና የነገስታት ሁሉ ንጉስ ሆኖ፣ በእግዚአቢሔር መንግስት በመንፈሳዊው አለም ከነገሰ ሁለት ሺህ አመት አልፎአል።
እንደው ለመሆኑ "ትንቢት ተፈጽሟል" ብለን ብንቀበል፣ ጊዜ መዳቢ (despensetionalist) ከሆኑና "በዚህ ቀን ይመጣል"፣ "በዚህ አመት ይመጣል ..." ከሚሉ ሃሰተኛ ነብያትና ቅዠታም መምህራን፣ መያዣ መጨበጫ ከሌለው የተሳከረ ትንታኔአቸው፣ የወንጌሉም መጽናናት ከሌለበት የሽብር ትምህርታቸውና ሐሰተኛ ከሆነ ትንቢታቸው እናርፋለን እንጂ ምን ይለናል? ምንስ ይቀርብናል? ጊዜ መዳቢ የሆኑ እነዚሁ "ትንቢት ገና ይፈጸማል" ባዮች በሚያዘጋጇቸው የጽሁፍና የኦዶ ቪዥዋል ገበያ፣ በተለይ በምእራቡ አለም ከሚገባው በላይ ቢዝነስ እየሰሩበት ሰለሆነ፣ በሚገጥማቸው ስነመለኮታዊ ተግዳሮት እውነቱን ለማወቅ ቢገደዱ እንኳ፣ እውነቱን ላለመቀበል ደግሞም ላለመስማት ጆሮቻቸውን ደፍነዋል ላይቀሰቀሱም አውቀው ተኝተዋል። ለምን? ፍራንኳ ትጣፍጣለቻ!
በኃላፋዊው ነገረ ፍጻሜ (preterism) የሚስተጋባው የተፈጸመ ትንቢትና የተጨበጠ ተስፋ የሚሰጠውን መጽናናት በእምነት እያጣጣምን ከዚህ ሥጋችን በሞት ተለይተን በተሰጠን የዘላለም ሕይወት ሙሉ ደስታ በቅጽበት አይን ተለውጠን እስክንወሰድ ድረስ በዚህ ህይወት አሁን በምድር ላይ ሰማያዊውንና ዘላለማዊውን ተልእኮ እየፈጸምን የክርስትናችንን ግርማና ክብር እንኑረው። የክርስቶስ መንግስት፣ እርሱም መንፈሳዊ መንግስት አሁንና እዚህ ነው፣ (ዮሐ 18 36)። ወደ ሕይወት መግባት አሁን በክርስቶስ ተሰጥቶናል፣ ከሞትንም በኋላ በሰማያት የሚቀጥለውን የዘላለም ሕይወት አሁን አግኝተናል። ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነስቶ በማያልቅ ሰላም የተሞላውንና ፍጻሜ የሌለውን ዘላለማዊ መንግስቱን ሰጥቶናል (ኢሳ 9፥ 6-7)።
የምጽአቱ ተስፋ (parousia) ያኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ላይ ሲነገር ያኔውኑ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ውስጥ፣ በጣም በቅርቡ ማለትም በ70 አ.ም ላይ "ከመሆን የማይቀር"፣ ቀንም የተቆረጠለት ጉዳይ ነበር እንጂ፣ 2000 አመታትና ከዚያ በላይ ተራዝሞ አሁን እኛ ባለንበት ዘመንም ሆነ ወይም ገና ወደ ፊት የሚጠበቅ የጌታ ምጽአትም ሆነ የዘገየ ተስፋ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም የመጻኢነት (futurism) ነገረ ፍጻሜ (eschatology) አስተምህሮ ፈተናውን የወደቀው፣ ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን ትውልድ ቤተ ክርስቲያንና ከእስራኤል ህዝብ ጋር የተቆራኘውን አጠቃላይ የሆነ የዳግመኛ ምጽአቱን ባህርይና፣ ይህንን ጊዜ ተኮር የሆነ የአዲስ ኪዳንን የቋንቋ አጠቃቀም እውነታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነጥብ ላይ ነው። የመጻኢነት አመለካከት በሚያቀነቅነው ያልተፈጸመና የዘገየ ተስፋ አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያቱ የተናገሩትን የትንቢት ቃል እውነተኛነቱን ማረጋገጥም ሆነ ክርስትናችንን ከጥቃትና ከስድብ መከላከል አይቻለንም። ኃላፋውያን (Preterists) ግን በትንቢት መጻህፍት ላይ የሚያቀርቡት የትርጉም ቀዋሚነትን የሚከተለው ትንታኔና ተስፋውም እንደ ተፈጸመ ለማስረገጥ ራሱን የቅዱሱን መጽሐፍ ቃል እና ታሪካዊ መዛግብትን መሰረት ማድረጋቸው በስነ ፍታቴ መርህ የሚረጋገጥ ንጹህ ትምህርት ነው።
No comments:
Post a Comment