Tuesday, November 15, 2016

"የአለም መጨረሻ" እውነት ነውን?

ማቴ 13፥ 40  እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።

ይህ የምንኖርበት "አለም መጨረሻ አለው" ብሎ ማመን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ነው? በእውኑ አለም መጨረሻ አለው ወይ?

"የአለም መጨረሻ" የተሰኘው  ይህ ርእሰ ጉዳይ በበርካታ የህትመትና የፊልም ስራዎች ላይ የሚራገብ አስተሳሰብ ነው። ማቆሚያ በሌለው ትንበያ ይህ አለም እንዴት እንደሚፈጸም እየተነገረ ነው። የክርስትናን የቆየ ልማድ ጨምሮ በበርካታ የአለም ታላላቅ ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ውስጥም የሚስተጋባ ነው። እግዚአብሔር ፈጽሞ እስኪያጠፋው ድረስ ይህ አለም እየከፋና እየባሰበት እንደሚሄድ በበርካታ የስነ መለኮትና የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራንና ሰባኪያን በተደጋጋሚ ሲነገረን ኖሮአል።

እንደመጽሐፍ ቅዱስ አማኝና ተማሪ በቅንነት ልጠይቅ ፤ ይህ አለም አንድ ቀን የሚያበቃለትና የሚጠፋ የመሆኑ ነገር በእርግጥም የቅዱስ ቃሉ ትምህርት ነው ወይ?

የቃሉ አክባሪና ተማሪ የሆናችሁ ወዳጆቼ ከላይ ያቀረብኩላችሁን ጥያቄ ቀጥሎ ባሉት ክፍሎች ብርሃን ተመልክታችሁ ሃሳባችሁን ሰንዝሩልኝ። በጉዳዩ ላይ የአንድን ሰው ትኩረት እንኳ ማግኘቴን ከተረዳሁ ወደቀጣዩ ሃሳቤ አልፋለሁ። እስከዚያው ጥቅሶቹን እነሆ፦

ዘፍጥረት 8፥ 21-22
መዝሙር 148፥ 4-6
መዝሙር 78፥ 69
መዝሙር 119፥ 90
መክብብ 1፥ 4
ማቴዎስ 13፥ 40

ክፍል አንድ
ቀደም ብዬ ላካፍላችሁ በጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ ስለ አለም መጨረሻ በብዙዎች ዘንድ የሚታመነው እምነት ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ አሳብ አንስቼ ነበር፣ ይህ አለም አንድ ቀን ያበቃለታል ወይ? መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ያስተምራል? የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር። በርእሰ ጉዳዩ ላይ የጥቂት ሰዎችን ትኩረት ማስተዋል ስለቻልኩ ቀጣዩን ነገሬን ላቅርብ። አለም መጨረሻ አለው፤ አንድ ቀን ያበቃለታል ለሚለው የቆየ አስተሳሰብ ወይም "እምነት" መጽሐፉ ቅዱስ ምን ይላል? በዚህ ጥያቄዬ እና በብዙዎች አስተሳሰብ ፊት ቆመው የሚፋጠጡንን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ለንጽጽር ትቼላችሁ ነበር፤ በዚህ ክፍል በመጠኑ ተጠግተን እናያቸዋለን፣ የምንባባቱ ሃሳብ ተቃራኒ የሚመስሉ ትንቢታዊ መልዕክቶችንም እያነሳሁ ለሚቀጥለው ጥናታችን የሚያዘጋጀንን ጥያቄ እጠቁማለሁ።

ዘፍጥረት 8፥ 21-22 " እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም።  በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።"

አንዳንድ ወገኖች እግዚአብሔር በአንድ ወቅት አለምን በውሃ አጥፍቶ ነበር፣ በሚቀጥለው መጻኢ ጊዜ ደግሞ በእሳት ያጠፋዋል ሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህም አስተሳሰባቸው በ2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 6 እና 7 ላይ " ... ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤  አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።" ተብሎ የተጻፈውን እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ።

ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ምንባብ ላይ ግን ያለው የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል "ምድርን ደግሜ አላጠፋም" የሚል መሆኑ ግልጽ ነው። ይህም "የማጠፋበትን ዘዴ እቀይራለሁ" የሚል እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል። ደግሞስ ምድርን በውሃ ከማጥፋት ይልቅ እልም አድርጎ በእሳት አቃጥሎ ማጥፋት ምን የሚያጽናና ተስፋ በውስጡ አለበት? ምንባቡ ግን በግልጽ እንዳስቀመጠው "ምድርን ደግሜ አላጠፋም" የሚል ተስፋ ነው የተሰጠው። መጻህፍት የየራሳቸው አውደ ምንባብ እንዳላቸው የሚያስተውል የቃሉ ተማሪ እነዚህን ተቃራኒ የሚመስሉ ነገር ግን በየራሳቸው አውድ መተርጎም ያለባቸውን ምንባባት አያምታታም አያደባልቅምም።

መዝሙር 148፥ 4-6 "ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት፤ የሰማያት በላይም ውኃ። እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት። ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም።"

ፈጽሞ እንዳያልፉ አድርጎ የመሰረታቸውን ሰማይንና ምድርን በተመለከተ የእግዚአብሔር ውሳኔ ምንድን ነው? ከላይ በዘፍጥረት 8፥ 21 ላይ ካየነው አሳብ ጋር አይመሳሰልምን? እግዚአብሔር ሕያው የሆነውን ነገር ሁሉ በድጋሚ እንዳያጠፋ ተናግሮአል። በእውነት እግዚአብሔር ሊታመን ይችላል ፣ ቃሉንም ይጠብቃል። ታዲያ በማቴዎስ 24፥ 35 "ሰማይና ምድር ያልፋሉ..." የተሰኘው ትንቢታዊ ቃል ከዚህ ጋር እንዴት ይታረቃል? የብዙዎቻችሁ ጥያቄ ይመስለኛል።

መዝሙር 78፥ 69 "መቅደሱን እንደ አርያም ሰራ፣ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሰረታት"

በሌላው ትርጉም "መቅደሱን እንደ አርያም ሰራ፣ ለዘላለም እንደመሰረታት እንደ ምድር" ይላል። እግዚአብሔር ምድርን ለዘላለም መስርቶአት ከሆነ እንዴትስ "ፍጻሜ ሊኖራት ይችላል" ብለን እናስባለን? ይህንንስ አይነት አሳብ ከየት ነው ያመጣነው? የእግዚአብሔር ውሳኔ ወይስ የሰው አሳብ፣ የትኛው ይበልጣል? ቀጣዮቹን ምንባባት ደግሞ ተመልከቱ።

መዝሙር 119፥ 90 "እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፤ ምድርን መሠረትሃት እርስዋም ትኖራለች።"

መክብብ 1፥ 4 " ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው።"

ልብ አድርጉ፣ እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት የሚያልፍ የሚሄደው ትውልድ እንጂ ምድር ግን ለዘላለም እንደምትኖር ፍጻሜም እንደሌላት ግልጽ ያደርጋሉ። ይህንን ግዑዝ ፍጥረተ አለም ለማጥፋት ለማሳለፍ እግዚአብሔር እንዳቀደ ሊያመለክተን የሚችል አንድ ጥቅስ ካገኛችሁ እባካችሁ አስረድታችሁ ንገሩኝ። ታላላቅ አጥፊ የጦር መሳርያ ያለው የሰው ልጅና አንባ ገነን የአለም መሪዎችም እንኳ አብረው የኒዩክለር ቦንቦቻቸውን ቢጠቀሙ ምድርን ለማጥፋት አይችሉም። ምክንያቱም "ምድር ለዘላለም ትኖራለች" ያለው እግዚአብሔር ነው። እርሱም "ምድርን ዳግመኛ አላጠፋም" ሲል በሰጠው በቃል ኪዳኑ ይዞአታል።

እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን መጻኢ እድል በዚህ መልክ የሚያቀርበው ከሆነ፣ በዚህ ጥናት መግቢያ ላይ "እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።" ሲል የተጠቀሰው የማቴዎስ 13፥ 40 አይነት ጥቅሶች መታየት ያለባቸው እንዴት ነው? የአለም መጨረሻ ምንድን ነው? ይህንን በሚቀጥለው ክፍል እንመለስበታለን። እስከዚያው ይህችን አጭር ሃሳብ ለማንበብ ጊዜ ስለወሰዳችሁ በእግዚአብሔር ቡራኬ ልሰናበታችሁ።
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት፣ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ክፍል ሁለት
አለም መጨረሻ አለው ወይ? በሚል ጥያቄ ቀደም ሲል ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት በቀረበው ርእሰ ጉዳይ በመግቢያውና በመጀመርያው ክፍል በተነሳው ሃሳብ ስለምንኖርበት ስለዚህ ግዑዝ አለም ሰማይና ምድር መጻኢ እጣ ፈንታ እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በግልጽ የሰጠውን ተስፋ የሚያወሱ ክፍሎችን በመጠኑ ለመመልከት ተሞክሮአል። በጥናቱም የተደረሰበት ድምዳሜ ቃሉ በግልጽ እንደሚመሰክረው ይህን ፍጥረተ አለም ለማጥፋት እግዚአብሔር ምንም እቅድ እንደሌለው የሚያረጋግጥ ነው።

"ይህ አለም አንድ ቀን ወደፊት በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል" የሚለው ትምህርትም የሰው ልብ ወለድ እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ድጋፍ የሌለው እንደሆነም ሊረጋገጥ ይችላል። ከዚህ ይልቅ ግን እግዚአብሔር የሰጠው ውሳኔ "ምድርን ደግሜ አላጠፋም" የሚል ሲሆን ቃሉም  "ምድር ትኖራለች፣ ምድር ለዘላለም ነው" ፣ የሚያልፈው የሚሄደው ትውልድ ነው ሲል ያስረዳል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው በተለይ ይህ ግዑዝ ፍጥረተ አለም ብን ብሎ ይጠፋል በለው የሚያምኑና የሚያስተምሩ ወገኖች ከሚጠቅሱአቸውና በአግባቡ ካላሰቡባቸው የንባብ ክፍሎች መካከል 2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 5-7 ያለው ዋነኛው ነው። አስቀድመን ይህንን ክፍል በእጭሩ ተረድተን እንለፍ።

2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 5-7  "ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤  አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።"

ጴጥሮስ የሚናገርለት "አለም" ሰማይንና ምድርን የሚያጠቃልለውን አለም ሲሆን፣ እነርሱም ያኔ በውሃ እንደጠፉና እንደሰጠሙ ይነግረናል። በውስጡ ይኖሩ የነበሩ ክፉ ሰዎች እንጂ፣ ይህ ተዳሳሹ ሰማይም ሆነ ምድር እንዳልጠፋና እንዳልተደመሰሰ እናውቃለን። ጴጥሮስ በኖህ ዘመን በውሃ ጠፍተው በነበሩ ሰማይና ምድር ደግሞም ያኔ በእሳት መጥፋት በነበረባቸው ሰማይና ምድር መካከል ልዩነትን አድርጓል።
ከጥፋት ውሃም በኋላ እንኳ ቢሆን እነዚያው ቀድሞ የነበሩት ተዳሳሾቹ ሰማይና ምድር ከዚያ በፊት በነበራቸው አይነትና መልክ ቀጥለዋል። በብሉይ ኪዳን ያለውን የሰማይና የምድር አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ ዘይቤ አጠቃቀም ካላወቅን በቀር ይህንን የጴጥሮስን ንግግር አሳስተን ልንረዳና፣ በኖህ ዘመን ጊዜ ያኔ የጥፋት ውሃ ያላደረገውን አሁን በእኛ ወይም በሚመጣው ሌላ ዘመን የጥፋት እሳት እንደሚያደርገው ሆኖ ተሳስቶ ይገባናል። አቡቀለምሲሳዊ ዘይቤ የሰማይና የምድር ጥፋት ያሚያመለክተው የሲቪልና የኃይማኖታዊ አገዛዝንና በዚያ ዙርያ የተሰባሰቡ ሰዎችን ጥፋት ነው።

በእውነት በጥፋት ውሃ ጊዜ እንዲጠፋ የተደረገው ምን ነበር? በቁጥር 6 ላይ ያለውን ተመልከቱ፦ "በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውሃ ሰጥሞ ጠፋ፤"  የጠፋው "ያን ጊዜ የነበረ አለም"  ነው እንጂ፣ ይህ ግዑዝ አለም አልነበረም፣ ይህንን ማስተዋል አያስቸግርም።  ሰለዚህ ታዲያ ይህ "አለም" የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? ይህ በጊዜው በሲቪልና በኃይማኖታዊ አስተዳደር በአግባቡ ተደራጅቶ የነበረው ማህበረብ ነው፣ እንጂ ተራውና ውዳቂው ነገር ሁሉ ማለት አይደለም። እግዚአብሔርን ከማያውቅና ከጠፋ ኃጢአተኛ ማህበረሰብ ጥፋት ወደመላው ፍጥረተ አለም ጥፋት እንዴት አልፎ መሄድና ማሰብ ይቻለናል? ያኔ በኖህ ዘመን በውሃ የጠፋችው ይህች ተዳሳሽዋ ምድር  አልነበረችም። እንግዲህ በዚህም ክፍል ላይ በእሳት ይጠፋል የተባለው እግዚአብሔርን የማያውቀው አመጸኛውና ከፉው የእስራኤል ህዝብ ነው እንጂ፣ የምንኖርበት ይህ ተዳሳሽ ፍጥረተ አለም አይደለም። በየትኛውም ገጹ ላይ ቢሆን ይህ ተዳሳሽ ፍጥረተ አለም ይጠፋል ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። በኖህ ዘመን ከሆነው የጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ላስታውሳችሁና ወደሚቀጥለው ልለፍ፦

በዘፍጥረት 8፥ 21   "እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም"

ታዲያ በመነሻ ጥቅሳችን በማቴዎስ 13፥ 40 "እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፣ በአለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል" ሲል ጌታችን በሰጠው ትንቢታዊ ቃል ውስጥ የተነገረለት "የአለም መጨረሻ" ምንድን ነው?  ቀጥሎ በዚህ ሁለተኛ ክፍል ጥናታችን ይህንንው በአጭሩ እንመለከታለን።

የትርጉም ችግር ካስከተላቸው የመረዳት ህጸጾች መካከል "አለም መጨረሻ አለው" የሚለው ይህ ሃሳብ በዋናነት ሊታይ ይችላል። ይህንንና መሰል ትንቢታዊ ጥቅሶች በግርድፉ የሚያይ ጠያቂ ያልሆነ አእምሮ የትርጉም ችግር ያስከተለበትን ግድፈት ሳይረዳ  "ይኸው አለም መጨረሻ አለው" ሲል ይከራከራል፤ የትንቢትና የራእይ መጻህፍትን ጨምሮ በአግባቡ ያላሰበበትን የጥቅስ እሩምታ ከአውደ ምንባቡ ነጥሎ በማከታተል ሊሞግትም ይሞክራል።

አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ በኩረ ቃል እዚህ ላይ ያለአግባብ "አለም" ተብሎ በትርጉም የገባው ቃል 'aion' የተሰኘው የግሪክ ቃል ነበር፤ ይህ 'aion' ደግሞ ፈጽሞ "አለም" ማለት እንዳልሆነ መዝገበ ቃላት ይነግሩናል። ቃሉ ይህንን የምንኖርበትን ነባራዊ አለም ለማለት ቢፈልግ ኖሮ 'kosmos' የሚለውን የግሪክ ቃል ይጠቀም ነበር። ይልቁኑ 'aion' የሚለው ቃል "ዘመንን"፣ ወይም "አንድ አይነተኛ ጊዜን"፣ ወይም "ወቅትን"፣ ወይም "ተለይቶ የሚታወቅ አይነተኛ ከፍለ ጊዜን" የሚያመለክት ትርጉም አለው።

በሁለተኛው ክፍል ምልከታችን ላይ ባነሳናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መሰረት ይህ የምንኖርበት ነባራዊ "አለም" ቀጣይ ሆኖ እንደሚኖር፣ በአንጻሩ ደግሞ "ትውልድ" ማለትም "ዘመን" ግን ፍጻሜ ያለው እንደሆነ ለማሳየት ተሞክሮአል። መጽሐፍ ቅዱስም ስለዘመን መጨረሻ በግልጽ የናገራል እንጂ ስለአለም መጨረሻ ምንም አይናገርም። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወደ በኩረ ቃሉ እየተመለሱ ይህንን የትርጉም ስህተት እያረሙ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል፤ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 13፥40 በተጻፈውና KJV [King James Version] በተሰኘው የእንግሊዝኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው 'World' (አለም) የተሰኘው ቃል  NKJV [New King James Version] በተሰኘው የእንግሊዝኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዴት 'age' (ዘመን) በሚል እንደተለወጠ ማየት ይቻላል።  አሉን በምንላቸው የአማርኛ ትርጉሞች ላይ ግን ይህንን ለውጥ ማየት ይከብዳል።

ጌታ ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው መጨረሻ ስላለው ዘመን ነው እንጂ፣ መጨረሻ ስላለው አለም አይደለም፤ የህም ዘመን እርሱና የመጀመርያዎቹ ደቀመዛሙርት የኖሩበትና ያገለገሉበት ዘመን ማብቂያ ነው። በዚያ በእነርሱ ዘመን ማብቂያ ወይም ፍጻሜ ላይ ስለሚሆነው ነገር እየተናገረ ነበር እንጂ ይህ የምንኖርበት አለም ተቃጥሎ ሲጠፋ ሰለሚከናወን ነገር እየተናገረ አልነበረም፤ ምክንያቱም ይህ አለም እንደሚጠፋ የሚያስተምር ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የለም። "አለም ይጠፋል" ብሎ ማሰብም ብሉይን መሰረት ላደረገው አይሁዳዊ አስተሳሰብና ለአይሁድ በተሰጠ ተስፋ ውስጥ ስርና መሰረቱን ለዘረጋው የአዲስ ኪዳን ክርስትና ባእድና እንግዳ  አስተሳሰብ ነው።

በዘመን መጨረሻ ላይ ምን ይሆን ዘንድ እንዳለው ልብ በሉ፦

ማቴዎስ 13፥ 49-50  "በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤  በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።"

እነማን ተለይተው እንደሚወሰዱ ልብ በሉ፣ "ኃጢአተኞች" ናቸው የሚለዩት። ከርእሰ ጉዳዩ ጋር ባይሄድም ይህ መለየት/ መወሰድ የንጥቀት ሌላው ገጽታ ይሆንን? ብሎ መጠየቅ የገባል። እርሱንም ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትና ትምህርት እንደሆነ  ወይም እንዳልሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።

ቤተክርስቲያን ልብ ካላለቻቸው ታሪካዊ ሁነቶች መካከል በ70 አመተ ምህረት በኢየሩሳሌምና በጠቅላላው በእስራኤል ህዝብ ላይ የደረሰው ጥፋትና ውድመት ነው። የህም ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት ንግሮችን ለመተርጎም በምታደርገው ጥረትና በአጠቃላይም በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮትዋ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖን አስከትሎአል። ይህንንና መሰል የሆኑ የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ የፍርድ ንግሮችን በ70 አመተ ምህረት በኢየሩሳሌም ላይ ከሆነው ጥፋትና ፍርድ ጋር የሚገናኙ መሆናቸውን አለማስተዋል ስነ ፍታቴአችንንም ሆነ ጠቅላላውን የመጽሐፍ ቅዱሳችንን እውነተኛነትና ታማኝነት  ትልቅ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ይሆናል።

ኢየሱስ እየተናገረለት ያለው "መጨረሻ" እነዚያ ኃጢአተኞች የሆኑ የአይሁድ ህዝብ በኢየሩሳሌም መቃጠል ስለሚደርስባቸው መጨረሻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የዘመኑ መጨረሻ ከአይሁዳዊው ቤተ መቅደስ መፈራረስ ጋር የተያያዘ አንድ መጨረሻ እንደሆነ አለማስተዋል "ይህ የምንኖርበት ነባራዊ አለም ገና ወደፊት ተቃጥሎ ይጠፋል" ወደሚል ሌላ ያልተጻፈ መጨረሻ ተረት ተረት ይመራል።

የሚከተለውን ቃል ልብ በሉ፦
ማቴ 24፥ 1-3  "ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ።  እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።  እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።"

ደቀ መዛሙርቱ ያቀረቡለት ጥያቄ ሁለት ነው። መጀመርያ የጠየቁት "ይህ መቼ ይሆናል?" የሚል ነው። ይኸውም "ይህ ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሆኖ የሚፈራርሰው መቼ ነው?" ማለታቸው ነበር። ሦስቱንም ተመሳሳይ ወንጌላት ብናመሳክር "መቼ?" የሚለው ጥያቄ የሁሉም ትኩረት እንደሆነ እናያለን፦
ማቴ 24፥ 3 " ...ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል?... አሉት።"

ማር 13፥ 4  "ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል?... "

ሉቃ 21፥ 7 "እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ... ብለው ጠየቁት።"

"ይህ" ወይም "እነዚህ ነገሮች" የሚለው ቃል ወይም ሐረግ የሚያመለክተው በቁጥር 2 ላይ ያለውን የቤተመቅደሱን መፈራረስ ነው።

በቁጥር 1 ላይ ደቀ መዛሙርቱ የቤተመቅደሱን ሕንጻ ማማር አይተው እየተደነቁ ለኢየሱስ ያመለክቱታል። በቁጥር 2 ላይ ደግሞ ኢየሱስ በተቃራኒው "ይህ ሁሉ ይፈራርሳል" ሲል ይናገራል ። እነርሱም "ቤተመቅደሱ መቼ ይፈርሳል?" ወይም "ቤታችን የተፈታ ሆኖ የሚቀረው መቼ ነው?" ብለው መጠየቃቸው ግልጽ ነው።

ኢየሱስ በማቴዎስ 23 ላይ በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣ ፍርድ ከተናገረ በኋላና ፣ በምእራፍ 24 መግቢያ ላይም "ድንጋይ በድንጋይ ላይ" እንደሚወድቅ ከተነገራቸው በኋላ፣ ያኔ የደቀመዛሙርቱ ምላሽ በጥያቄ የታጀበ ነበር፤ "መቼ?" ይህ ስሜት የሚሰጥ ይመስለኛል።

የጥያቄአቸው ሁለተኛ ክፍል ደግሞ "የመምጣትህና የአለም (የዘመን) መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?" የሚል ነው።

አሁንም ጥያቄውን ለመረዳት እንዲቻለን የሦስቱንም ተመሳሳይ ወንጌላት ዘገባ በንጽጽር ማየት ያስፈልጋል።

ማቴ 24፥ 3 "እርሱም.... ንገረን፥ የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።"

ማር 13፥ 7 "ንገረን፥ ... ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ... ጠየቁት።"

ሉቃ 21፥ 7 "እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥... ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት።"

የሦስቱንም ወንጌላት ዘገባዎች ስናነጻጽር ደቀመዛሙርቱ ምጽአቱንና የአለም (የዘመን) መጨረሻ ከቤተመቅደሱ መፍረስ ጋር የተገናኘ ሁነት እንደሆነ ይመለከቱ እንደነበር እናስተውላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው የአለም መጨረሻ የዘመንን መጨረሻ ነው፣ ይኸውም የዘመን መጨረሻ በቤተ መቅደሱ መውደም የሚወከል እና በእስራኤል የመከራ እልቂት የሚደመደም የአይሁድ አለም መጨረሻ የአሮጌው ዘመን ማብቂያ ነው እንጂ፣ የምንኖርበት የዚህ ነባራዊ አለም ፍጻሜ ማለት አይደለም።

ማርቆስ 13፥ 4  "ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት።"

በጥቅሱ የመጀመርያ ክፍል ጥያቄ "ይህ መቼ ይሆናል?" የሚለው የሚያመለክተው የቤተመቅደሱን መፈራረስ ነው። በጥያቄው የሁለተኛ አጋማሽ ደግሞ "ይህ ሁሉ ሊሆን እንዳለው ምልክቱ ምንድን ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል።

የመምጣቱና የዘመን መጨረሻ ምልክት በ70 አመተ ምህረት ከሆነው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መፈራረስ ጋር ከተጠቀሰውና "ይህ" ከተባለው ጋር አንድ ነው። እነዚህም በተለያየ የጊዜ ምህዳር የሚከፋፈሉ የተለያዩ ወይም የተነጣጠሉ ጥያቄዎች አይደሉም። ደቀመዛሙርቱ በአእምሮአቸው የነበራቸው ሃሳብ አንድ ብቻ ነው፣ ይኸውም የቤተመቅደሱ መፍረስ ጉዳይ ነው። ከዚህ የቤተመቅደስ መፍረስ ጋር የመሲሁን መምጣትና የዘመኑን ፍጻሜ አገናኝተው ይጠይቃሉ። ጥያቄውም፦ "መጨረሻው የሚሆነው መቼ ነው?" የሚል ነው። ኢየሱስም የሰጣቸው ምልክት ሉቃስ በወንጌሉ "ኢየሩሳሌም በጭፍራ (በጦር ኃይል) መከበብ" ሲል የተረጎመውን "የጥፋት ርኩሰት" የተሰኘ ምልክት ነው። ኢየሱስም ግልጽ አድርጎ የነገራቸው መጨረሻው ያሚመጣው "በዚህ ትውልድ" ነው ብሎ ነው (ቁ 34)። ትንቢቱን ይናገር ለነበረው ለኢየሱስም ሆነ ትንቢቱን ይሰሙት ለነበሩ ለነዚያ የመጀመግያዎቹ አድማጮች "ይህ ትውልድ" ማለት ያው እነርሱ የኖሩበት ዘመን ትውልድ እንጂ ልጆቻቸው ወይም የልጅ ልጆቻቸውን አልያም በመቶና በሺህ አመታት ርቀት ከእነርሱ በኋላ የሚፈጠረው ሌላ ትውልድ ማለት አይደለም። "ትውልድ" የሚለው ቃል ትርጉም በአንድ አይነት ወቅትና ጊዜ ውስጥ የሚኖሩ የአንድ ዘመን ነዋሪዎችን ማለት ነው።
ሰለዚህ ያበቃል እየተባለ የተነገረለት ዘመን የአይሁድ ዘመን ነው። ይኸውም የሙሴ ስርአት አሮጌ ዘመን ነው። የሚያበቃውም ከአይሁድ ቤተመቅደስና ከኢየሩሳሌም ከተማ መፈራረስ ጋር ነው። መስቀሉና በአለ ሃምሳ ዘመኑ ሊፈጸም እንደተጀመረ ሲያመለክቱ በ70 አመተ ምህረት ላይ የሆነው የኢየሩሳሌም መፈራረስ ግን የዚያ የአሮጌ ዘመን ስርአት በፍርድ መዘጋቱን ያሳያል። አለም ሳይሆን ይሁዲነትና የባርነት ጨለማ ስርአቱ ሁሉ ያበቃው እዚያ ላይ ነው። አዲስ ኪዳን ወደፊት እያየ የሚናገርለት አስፈሪ የኃጢአተኞች ፍርድና ጥፋት አመልካች የሆኑ የንባብ ክፍሎች ሁሉ በዚህ አውድና ብርሃን የተነገሩ ናቸው።

ደቀመዛሙርቱም የቤተመቅደሱ መውደቅና የከተማይቱ መፈራረስ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ማብቂያና የአዲሱ ዘመን ጅማሮ እንደሆነ ያውቁ ነበር። የህም በጣም አስፈላጊ ወደሆነ ዋና ጥያቄ ያደርሰናል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰንት ዘመን ያውቃል? ያለውስ ሰንት ዘመን ነው? በሚቀጥለው ጥናታችን እንመለስበታለን። እናንተም ዝም አትበሉ ቅዱሱን መጽሐፍ ዋቤ አድርጋችሁ ሃሳባችሁን አካፍሉን፣ እንማማር። እስከዚያው ይህችን አጭር ጽሁፍ ለማንበብ ጊዜ ስለሰጣችሁኝ በቅድስት ሥላሴ ስም ተባረኩ።
እግዚአብሔር ይባርካችሁ፣ ይጠብቃችሁ። እግዚአብሔር ፊቱን ያብራላችሁ፣ ጸጋውንም ይስጣችሁ። እግዚአብሄር ፊቱን ይመልስላችሁ፣ ሰላሙንም ይስጣችሁ። በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም፣ አንድ አምላክ። አሜን

ክፍል ሦስት
አለም መጨረሻ አለው ወይ? የአለም መጨረሻ የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? በሚል መነሻ በለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍል አጫጭር ጥናቶች አይተናል። የተደረሰበትም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድምዳሜ ይህ ግዑዝ የሆነ ፍጥረታዊ አለም ወደፊት ይጠፋል የሚለው አስተሳሰብ የሰው እንጂ የእግዚአብሔር አሳብ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የዚህን ግዑዝ አለም መጨረሻ ሳይሆን የዘመንን መጨረሻ እንደሆነ ለማስረዳት ተሞክሮአል። ዘመን ያልፋል እንጂ "ምድር ግን ለዘላለም ነው" (መክብብ 1፥ 4)፤ ታዲያ ያልፋል የተባለውና መጨረሻው እየተባለ በቅዱሳት መጻህፍት የተነገረለት ዘመን የትኛው ዘመን ነው? በዛሬው ጥናታችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው ስንት ዘመን እንዳለ በአጭሩ እንመለከታለን።

ስንት ዘመን ነው ያለው?
ዊልያም ባርክሌይ እንዲህ ይላሉ፦ "አይሁዶች ጊዜን በሁለት ከፍለው 'ይህ የአሁኑ ዘመን' እና 'የሚመጣው ዘመን' ብለው ይመድቡታል። 'የአሁኑ ዘመን' የተባለው በጥቅሉ መጥፎ የሆነውና በሰው ጥረት ሊታደስ የማይችለው ዘመን ነው። የሚታደስ የሚለወጥም ከሆነ የሚቻለው በእግዚአብሄር ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው። እግዚአብሔር ጣልቃ ሲገባ ደግሞ 'ሊመጣ ያለው ዘመን' የተባለው ወርቃማው ዘመን ይመጣል ይደርሳልም። በሁለቱ ዘመነት መካከል ግን የአዲሱን ዘመን መወለድ የሚያበስር ምጥ እንደሚሆን ያህል የጭንቀትና የፍርሃት ጊዜ የሆነው የጌታ ቀን ይመጣል። ዘካርያስ 14 ያ የጌታ ቀንና የኢየሩሳሌም ውድመት የተገናኘ እንደሆነ ይነግረናል። ስለሆነም የጌታ ቀን የተባለው የኢየሩሳሌም መፈራረስ፣ የአይሁድ ዘመን የተባለውን የአንድን ዘመን መጨረሻ ማብቃቱንና የክርስቲያን የአዲሱ ኪዳን ዘመን መጀመሩን የሚያመለክት ሁነት ነው። ለአይሁድ ጊዜ 'የሙሴ' እና 'የመሲሁ' ዘመን በሚል ለሁለት ይከፈላል። መሲሁም አዲሱን አለም የሚያመጣ እንደሆነ ይታወቃል። ስለሆነም የመሲሁ ዘመን /ክፍለ ጊዜ/ በምኩራባት ዘንድ "የሚመጣው አለም" ተብሎ ተለይቶ በዚህ ይጠራና ይታወቅ ነበር።"

በመላው አዲስ ኪዳንም በንጽጽር ቀርበው የምናያቸው ሁለት ዘመናት 'ይህ ዘመን' እና 'የሚመጣው ዘመን' የተባሉትን ብቻ ነው።

ማቴ 12፥ 32 " በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።"

ያለው "በዚህ " የተባለና "በሚመጥው" የተባለ ሁለት አለም ነው፤  በጥቅሱ መጨረሻ ላይ "የሚመጣው" የተሰኘው ቃል በግሪኩ 'mello' ነው፣ ይኸውም "ሊሆን ያለው" ወይም "ሊመጣ ያለው" (about to be) ማለት ነው። ይኸውም ዘመኑ ሊመጣ ያለው ገና ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ለነበሩት ሰዎች ማለት ነው። ብዙዎች ይህንን የሚመጣ ዘመን ኃጢአት የሌለበት የማይኖርበትም ዘመን እንደሆነ ያስባሉ፤ በዚህ ጥቅስ መሰረት ግን እንደዚያ አይደለም። በዚያ ይመጣል በተባለው ዘመን በመንፈስ ቅዱስ ላይም እንኳ ኃጢአትን የመስራት እድል ያለ ሲሆን፣ እርሱም ይቅር አይባልም፤ ይኸውም የሚያመለክተው የአሁኑን የእኛን ዘመን ሲሆን እርሱም የአዲሱ ቃል ኪዳን ዘመን ነው። ሁለቱም እነዚህ "በዚህ " እና "በሚመጥው" የተባሉ ዘመናት በውስጣቸው ኃጢአት ሊደረግባቸው የሚችል መሆኑን ጥቅሱ ያሳየናል።

ኤፌ 1፥ 21" ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤"

እዚህም ላይ በድጋሚ "በዚህ ዓለም" እና "ሊመጣ ባለው ዓለም" የተሰኙ ሁለት አለም ወይም ዘመናትን እናያለን። ስለዚህ አዲስ ኪዳን የሚናገረው ስለሁለት ዘመናት ነው፣ እርሱም "ይህ (የአሁኑ) ዘመን" እና "የሚመጣው ዘመን" የተሰኙ ናቸው። እነዚህን ሁለት ዘመናት በአግባቡ መረዳትና፣ መቼ እንደሚለወጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ጊዜ መለየት በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማችን ላይ በእጅጉ መሰረታዊ ነገር ነው። አዲስ ኪዳን ስለእነዚህ ሁለት ዘመናት ምን እንደሚያስተምር ተጠግተን እንይ። ልንመልሳቸውም የሚገቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፣ ለአሁኑ፦ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት በምን ዘመን ውስጥ ነበር? እኛስ አሁን እየኖርን ያለነው በምን ዘመን ውስጥ ነው? የሚለውን አንስተን በቀጣይ "ይህ ዘመን" የተሰኘው ጊዜስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በምን ባህርይ ነው የሚገለጠው? አዲስ ኪዳን "የሚመጣው ዘመን" ስለተሰኘው ጊዜ ምን የሚለው ነገር አለው? "ይህ ዘመን" የተሰኘው የሚያበቃበት ጊዜና "የሚመጣው ዘመን" የተሰኘው ጊዜ የሚጀምረውስ መቼ ነው? የሚሉትን አንስተን እንመለከታለን።

የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት በምን ዘመን ውስጥ ነበር?
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ይኖሩ የነበሩት እነርሱ "ይህ ዘመን" እያሉ ይጠሩት በነበረው ዘመን ላይ ነበር። ለአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን "የሚመጣው ዘመን" እየተባለ የሚጠራው ገና ወደፊት ይጠባበቁት የነበረ ነው፣ ነገር ግን "ይህ ዘመን" እያሉ የሚጠሩት እያበቃ ስለነበር "የሚመጣው ዘመን" ለእነርሱ በጣም ቅርብ ነበር።

1ቆሮ 2፥ 6-8 "በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤"

የዚህ አለም (የዚህ ዘመን) ጥበብና ገዥዎች እየተሻሩ ነበር። ምክንያቱም ዘመኑ እያለቀና እያለፈ ስለነበር ነው። እየተናገረ ያለው ስለአይሁድ ህዝብ መሪዎችና ስለአሮጌው ኪዳን ሥርዓት ነበር። "የዚህ አለም ገዥዎች" (የዚህ ዘመን ገዢዎች) ጌታን የሰቀሉቱ ናቸው። ዘመኑ ወይም ያ አለምና የአለም ሥርዓት እያለፈና እየተዘጋ ስለነበር እነዚህ ገዢዎች በቅርቡ ወደፊት የማይገዙበት ወይም የማይሰለጥኑበት ዘመንና አለም እየመጣ ነበር። እስቲ ይህንን አስቡ ብዙዎች እንደሚመስላቸው የአይሀድ ዘመን በመስቀሉ ላይ አብቅቶ ቢሆን ኖሮ እንዴት ገና ዘመኑን ወይም አለሙን ይገዛሉ ሊባል ይችላል? "የሚሻሩትን" የሚለው ቃል ያኔ የሚያመለክተው የዚያን አለም ወይም ዘመን መጻኢውን እድል ነው፣ አሁን ግን ያ አለም ተሽሮ አልፎ ሄዷል።

1ቆሮ 10፥ 11"ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።"

ጳውሎስ በግልጽ የሚናገረው የዘመናት መጨረሻ በእነርሱ ላይ መድረሱን ነው፣ እነርሱም ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የነበሩ ቅዱሳን ናቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ በሚሆን ምሪት በእያንዳንዱ ቀን በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደሆኑ ይሰማቸውና ያስተውሉ ነበር። ያኔም "ይህ ዘመን" ተብሎ የተጠራው ጊዜ ከአሮጌው ጥበቡና ከገዢዎቹ ሁሉ ጋር ሊያልፍና ሊያበቃ ተቃርቦአል። እንደመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ ለምናምን ለእኛ  ያበቃል ይተባለው ዘመን ይኸውም "የመጨረሻው ዘመን" ካለፈ ሁለት ሺህ አመት ተቆጥሮአል። አሁን ክርስቲያኖች ሆነን የምንኖርበት ይህ የጸጋ ዘመን፣ የአዲሱ ኪዳን ዘመን፣ እግዚአብሄር የሰጠን ዘላለማችን፣ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው።

ዕብራ 1፥ 1-2 "ጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤"

ኢየሱስ የተናገረው በዘመናት መጨረሻ ላይ ነው። የምን ዘመን መጨረሻ? መጽሐፍ ቅዱስ "ይህ ዘመን" እያለ የሚጠራው የአሮጌው ኪዳን መጨረሻ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ተናግሮ የጨረሰው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው። የዘመኑም ቁጥር ከጥንት ከአባቶች ጀምሮ ልጁ እስከተገለጠበት ጊዜ ያለውን ይሸፍናል። ልጁም የተገለጠው ያ ዘመን ሊያበቃ ሲቃረብ ነው። እግዚአብሔር በልጁ ከተናገረበት የዘመን መጨረሻ ሌላ የተለየ የመጨረሻ ዘመን የሚባል ነገር አሁንም ሆነ ወደፊት የለም።

ዕብራ 9፥ 26 "እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።"

አሁንም በድጋሚ ልብ በሉ፣ ኢየሱስ በሥጋው የተገለጠው መቼ ነበር? እርሱ የተወለደው በዘመኑ መጀመርያ ላይ ሳይሆን "በአለም ፍጻሜ" ይኸውም በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነበር። " ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤"   (ገላ 4፥ 4)። ኢየሱስ በስጋው ከሴት የተወለደው የዚህ ግዑዝ አለም መጨረሻ ወይም ፍጻሜ ሲቃረብ ነው ብሎ ማሰብ የተሳሳተ መረዳት ይሆናል ። ምክንያቱም እርሱ በስጋ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ይህ ግዑዝ አለም ገና ብዙ ዘመን እየኖረ ሳይፈጸም ቆይቶአልና። ከሙሴ ዘመንና ከዘጸአት ጀምሮ እሰከ ቤተመቅደሱ መፈራረስ ድረስ ያለው ጊዜ ረጅሙ ጊዜ ነው። ይኸውም ይህ ዘመን እየተሰኘ ሲጠራና ሲታወቅ የነበረው የአሮጌው ኪዳን ዘመን ሲሆን ኢየሱስም በሥጋው የተገለጠው በዚሁ በአይሁድ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው። ጴጥሮስም ተመሳሳይ ነገር ይናገራል።

1ጴጥ 1፥ 20-21 " ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።"

ኢየሱስ ወደ አለም የመጣው በዘሙኑ መጨረሻ ላይ ነው፣ እርሱም የአይሁድ ዘመን የሆነው የአሮጌው ኪዳን ዘመን ማብቂያ ነው። ዘመኑም እስከወዲያኛው ያበቃው በ70 ዓመተ ምህረት ላይ ቤተ መቅደሱ ሲፈርስ ነው። በማቴዎስ 24 ላይ በኢየሱስ የተሰጠ የትንቢት ቃል ሀሉ የተፈጸመው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው። ስለዚህም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ "ይህ ዘመን" እያለ በሚጠራው ዘመን የመጨረሻዎቹ አርባ አመታት ውስጥ ነው።
"ይህ ዘመን" የተሰኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊው የመጨረሻ ዘመን፣ ይኸውም የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ሁሉ የኖሩበት ዘመን በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ የተገለጠው እንዴት ባለ ባህርዩ ነው? ቀጣዩ ጥናታችን ይህንን የሚመልስ ይሆናል። ለብዙዎቻችሁ እጅግም ያልተለመደ አሳብ እያነሳሁ እንደሆነ አውቃለሁ። ሆኖም ጊዜ ወስዳችሁ ጭረቴን ለተመለከታችሁ ሁሉ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው። የበዛው ጸጋ ይደግፋችሁ! አሜን!!

ክፍል አራት
መግቢያ፦
ይህ አለም አንድ ቀን በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋልን? እንዲህስ ያለው አስተሳሰብ ከቅዱስ ቃሉ የተወለደ ትምህርት ነውን? የሚለውን ጥያቄ አንስተን የጀመርነው ጥናት፤ "የለም ይህ የሰው ልብ ወለድ እንጂ፣ በእግዚአብሔር ቃል ምንም ድጋፍ የሌለው ትምህርት ነው። እግዚአብሄርም ይህንን ሰማይና ምድር ለማጥፋት በቅዱስ ቃሉ የገለጠው ምንም እቅድ የለውም። ይልቁንም የሚያልፍ የሚጠፋው ትውልድ እንጂ ይህ ግኡዝ አለም እይደለም" በሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድምዳሜ ላይ እንዳደረሰን ይታወሳል። እስካሁንም በነበረን ቆይታ "ይህ ግኡዝ አለም እንዲጠፋ ተወስኖአል" የሚል አቋም ይዞና መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሶ ይህን ሃሳብ የሞገተ ሰው አላጋጠመኝም።  በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወራለት የአለም መጨረሻ፣ የአይሁድ አለም መጨረሻ፣ የአሮጌው ዘመን መጨረሻ የተሰኘውን እንጂ፣ የግኡዙ አጥናፍ አለም መጨረሻ እንዳልሆነ በብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ቀደም ያሉት የጥናት ክፍሎች አመላክተዋል። ቀዳሚዎቹን የጥናት ክፍሎች  ላላነበባችሁ በዚህ የፌስ ቡክ ገጽ በተከታታይ የለጠፍኳቸውን ጽሁፎች እንድትመለከቱአቸው እየጋበዝሁ፣ ምንም ክለሳ ማድረግ ሳያስፈልገኝ ወደ ቀጣዩና ወደ ማጠቃለያው ጥናት አልፋለሁ።

ለመሆኑ "ይህ ዘመን" የተሰኘውና  የአዲስ ኪዳን  ጸሐፍያን የኖሩበት ዘመን በጠቅላላው በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴት ባለ መልኩ ነው የተገለጠው? በዚህ ጽሁፍ የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን እነርሱ ለኖሩበትና ላገለገሉበት ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው የዘመኑ መጨረሻ የሰጡትን ስያሜና መግለጫ እያነሳን እንመለከታለን። (በሚነሱ ነጥቦች ላይ ወገንተኝነታችን ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው አውድ ከሆነና ለዘመናት ሲመስለንና ስንከተለው የነበረውን የለመድነውን አስተሳሰብ በቅን አሳብ የምንጠይቅ ከሆነ በእውነት ሳንማር አንቀርም።)
  
1. ክፉ ዘመን ነው፦
ገላ 1፥ 4 "ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።"

ለጳውሎስና ለገላትያ ክርስቲያኖች ክፉ የሆነው አለም ወይም ዘመን እነርሱ "ይህ የአሁኑ አለም"" ሲሉ የሚጠሩትን፣ ራሳቸውም የኖሩበትን ዘመን ነው እንጂ የሚመጣውን አለም ወይም ዘመን አይደለም። ሐዋርያው እዚህ ላይ የሚናገርለት "ይህ ዘመን"  የተባለው የዘመን ክፍል ደግሞ ሊያልፍና ሊዘጋ ያለ ክፉ ዘመን ነው። ክርስቶስም የመጣውና ራሱን የሰጠው ከዚህ የሞት ሕግ ከሚገዛበት "የአሁኑ ዘመን" ሊያድናቸው ነው፤ ምክንያቱም ዘመኑ በሕጉ ምክንያት ከሚሆን እርግማን የተነሳ ክፉ ነበርና። አጠቃላዩ የገላትያ መጽሐፍ አውድ ከሕጉ አርነት ስለመውጣት እንደሆነ ግልጽ ነው። በሕጉ ስር በሞትና በባርነት ፍርሃት ማደርን የመሰለ ክፉ የለም።
 
"ክፉ ዘመን" የተሰኘው የክርስትናን ዘመን ሊያመለከት ይችላልን? የክርስትያንስ ዘመን ክፉ ዘመን ተብሎ ሊጠራ ይችላልን? እኛስ ብንሆን መዳን ያለብን ከክርስቲያን ዘመን ነውን? በጭራሽ አይደለም። ክርስቶስ የመጣው ከክፉ ዘመን አድኖ በመንግስቱ ውስጥ ሊያኖረን ነው። በእውነት ያ የአሮጌው ኪዳን፣ የሕጉ ዘመን ክፉ ነበር። ይህ እኛ ያለንበት የአዲሱ ኪዳን ዘመን ግን ጽድቅና የዘላለም ሕይወት የሚገዛበት መልካሙ ዘመን ነው። ድነናልና በክርስቶስ ያገኘነውን ክቡር ነጻነት በእምነት እናጣጥም እንጂ ከዚህ የተሻለ ወይም የተለየ ሌላ መዳንና ነጻነት የለም።

2. የጨለማ ሥልጣን ዘመን ነው፦
ቆላ 1፥ 13 "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። "

ክርስቶስ የመጣው የሕዝቡን "ከጨለማው ሥልጣን" ሊያድን ነው። ይህ የሚያመለክተው አሮጌውን ኪዳን ወይም "ይህ ዘመን" የተባለውን ነው።

ዮሐ8፥ 12 " ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።"

ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ለአይሁድ ነው፣ የሚያቀርብላቸውም ጥሪ የአሮጌውን ኪዳን ጨለማ እየተዉ እርሱን እንዲከተሉት ነው።

3. ሰይጣን የሚገዛበት ዘመን ነው
ሐዋ 26፥ 18 " የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።"

"ይህ የአሁኑ ዘመን" የተባለው "የጨለማው ዘመን" ነው። ሰይጣንም የዚህ አለም (የዚህ ዘመን ገዥ) ተብሎ ተጠርቶአል።

2ቆሮ 4፥ 3-4 "  ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።"

"ይህ ዘመን" የተሰኘው የኛን ዘመን የሚያመለክት አለመሆኑን አስታውሱ። "ይህ አለም" ወይም "ይህ የአሁኑ ዘመን" የተሰኘው የመጀመርያው ከፍለ ዘመን ጊዜ ነው። ሰይጣንም የሚገዛው የእግዚአብሔርን ነብያት ባሳደደና በገደለ፣ ክርስቶስንም በገደለና በተከታዮቹም ላይ መከራን ባበዛባቸው በዚያ በአሮጌው ኪዳን አለም የይሁዲነት ስርአት ላይ ነበር፤ ኢየሱስም በሉቃስ 22፥ 53  ላይ "በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው"  ሲል በዘመኑ የነበሩትን የአይሁድ አለቆችና የጨለማውን ስልጣን እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ተመልክቶአቸዋል። ነገር ግን ያኔ ገና በመጀመርያው ኪዳን ዘመን ላይ ሲሰራ የነበረው ይህ  የአገዛዝ ስርአት ሊዘጋና ሊያበቃለት የቀረው አጭር ጊዜ ነበር። ኢየሱስም በዮሐንስ 12፥ 31 ላይ  "አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤" ሲል በዚያ አለም ላይ የፍርዱ ጊዜ መድረሱንና፣ የዚያ የአይሁድ አለም ገዥ የሚጣልበት ወሳኙ ጊዜ መድረሱን ያረጋግጣል። ጳውሎስም ያንንው ያረጋግጣል፦

ሮሜ 16፥ 20 "የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።"

"ይህ ዘመን" የተባለው የጨለማ ዘመን ሲያበቃ ያኔ ሰይጣን ይቀጠቀጣል። ኢየሱስ "ተፈጸመ" ሲል የመስቀሉ ላይ ሞቱ እና ትንሣኤው ያንን የሰይጣንን መቀጥቀጥ አውጆአል። ያንን የጨለማ ስርአት ፍጻሜውን ሰጥቶ በይፋ ለሁሉ የገለጠው ደግሞ በ70 አ.ም በኢየሩሳሌምና በመቅደስዋ ላይ በሆነው ፍርድ ነው፡፡ ጠላቶቻቸው በሆኑ አይሁድ ተከበው ሲጨነቁና በከፋ ስደት መከራ ሲቀበሉ የነበሩ እነዚያ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ከዚያ ክፉ ተጽእኖ ነጻ የሚወጡበት ቀን ፈጥኖ እየቀረበ ነበር፡፡ ይህም የሚሆነው ይህንን በጣም አደገኛ የሆነውን ጠላት በኃይል የሚያነሳሳውንና የሚያበረታታውን የቀድሞውን አሮጌ ሥርዓት በመለኮታዊ ፍርዱና በቁጣው ከእግራቸው በታች ጥሎት ሲቀጠቅጠውና ኀይሉን ሲያሳጣው ነው፡፡

ዮሐንስም የመጀመርያ መልዕክቱን በሚጽፍበት ጊዜ ያኔ ጨለማው ገና እያለፈ ነበር።

1ዮሐ 2፥8 "ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።"

እዚህ ላይ እየተናገረለት ያለው ጨለማ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ነው፣ እውነተኛው ብርሃን ደግሞ የሚያመለክተው የአዲሱን ኪዳን ዘመን ነው።

4. የሞትና የኩነኔ ዘመን ነው
2ቆሮ 3፥ 5-11 "ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤  እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥  የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና።"

ጳውሎስ እዚህ ላይ የሚያነጻጽረው ሁለቱን ኪዳናት ማለትም፣ የሞትና የኩነኔ ኪዳን የሆነውን አሮጌውን ኪዳን እና፤ የሕይወትና የጽድቅ ኪዳን የሆነውን  አዲሱን ኪዳን  ነው። ጳውሎስ ይህንን ለቆሮንቶስ ሰዎች በሚጽፍበት ጊዜ፣ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ይኸውም እነርሱ "ይህ የአሁኑ ዘመን" ሲሉ የሚጠሩት ዘመን እያለፈና እየተዘጋ ያለበት ሂደት ውስጥ ነበር።

ጳውሎስ ስለነዚህ ሁለት ኪዳናት ለገላትያ ሰዎችም ሲጽፍላቸው፣ አሮጌው ኪዳን ያኔ ገና በስራ ላይ የነበረ መሆኑን ያመለክታል።

ገላ 4፥ 21-26 "እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና።  ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።"

አጋር የምትወክለው አሮጌውን ኪዳን እና "አሁን" (ማለትም ያኔ የገላትያ መልእክት በሚጻፍበት ጊዜ) ከሕዝብዋና ከአለቆችዋ ጋር በሕጉ ባርነት ያለችውን ምድራዊቱን ኢየሩሳሌምን ነው። አሮጌው ኪዳን ያኔ ገና ያልተወገደ መሆኑን ይህ "አሁንም ያለችው" የሚለው ሃረግ ያሳያል፤ ሳራ ደግሞ የምትወክለው አዲሱን ኪዳን እና ከልጆችዋ ከአማኞች ሁሉ ጋር በነጻነት የምትኖረውን የላይኛይቱን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ነው፣ እርስዋም ያኔ ልትገለጥ ገና እየመጣች ነበር።

5. ዘመኑ ሌሊት ተብሎ የሚጠራ ዘመን ነበር
ሮሜ 13፥ 11-12 "ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። "

መዳናቸው ያኔ ወደ እነርሱ ገና እየቀረበ፣ "ሌሊቱ" ተብሎ የሚጠራው ከፍለ ጊዜ ደግሞ እያበቃና እያለፈ  ነበር። እስቲ ልጠይቃችሁ፣ የክርስቲያን ዘመን የሚወከለውና የሚጠራው ቀን ወይስ ሌሊት ተብሎ ነው? በእርግጥም ክርስትና ቀን እንጂ ሌሊት አይደለም። የአሮጌው ኪዳን የይሁዲነት ሌሊት እያበቃለትና እየተዘጋ ነበር፣ በአንጻሩ ደግሞ  የአዱሱ ኪዳን ቀን፣ የክርስትና ዘመን እየነጋና ወደ ምድር እየወረደ ነበር።

1ተሰ 5፥1-4 "ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤  የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።  እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥"

ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የሚነግራቸው በጨለማ አለመሆናቸውን፣ ይልቁንም የብርሃን ልጆች መሆናቸውንና ሊነጋ ያለው የቀን ልጆች መሆናቸውን ነው። ሰለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ "ይህ ዘመን" ብሎ የሚጠራው ዘመን ያኔ ገና በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ላይ ሊያልፍና ሊዘጋ የቀረበውን የአሮጌውን ኪዳን ዘመን ነው። ይህም ዘመን ከተገለጠባቸው ባህርያቱና መጠርያዎቹ መካከል "ክፉ"፣ "ጨለማ"፣ "የሰይጣን ስልጣን ወይም አገዛዝ"፣ "ኩነኔ"፣ "ሞት" እና "ሌሊት" ተብሎ ነው። "ይህ ዘመን" ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ የሚጠራው ዘመን እኛ የምንኖርበትን የክርስትና ዘመን እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት። ያኔ በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ላይ የአሮጌው ኪዳን ዘመን እያረጀ ሊጠፋ ቀርቦ ነበር፤ ፈጽሞ የሚወገደውም በ70 አ.ም ላይ ቤተመቅደሱ ሲወድም ነው።

እብ 8፥13 " አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።"

የእብራውያን መልእክት የተጻፈው ከ65-69 አ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ያኔ በዚህ ጊዜ አሮጌው ኪዳን ገና በይፋ በስራ ላይ ነበር፣ ሆኖም ግን "ሊጠፋ ቀርቦ" ያለበት ወቅት ነበር። ፈጽሞ እንዲጠፋ የተደረገው ኢየሩሳሌም በ70 አ.ም ላይ በጦርነት እልቂት ስትደመሰስ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ "የአሁን ዘመን" አሁን ላይ ሲታይ የጥንት ታሪክ ብቻ ነው። በአሮጌው ኪዳን ማብቂያ ላይ ፍጻሜአቸውን እንደሚያገኙ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተነገረላቸው በርካታ የነገረ ፍጻሜ ትንቢታዊ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ልጥቀስና ወደሚቀጥለው እንለፍ፦

1. የክርስቶስ ተመልሶ መምጣት
እብ 10፥ 37 "ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤"

2. የሙታን ትንሳኤ
ዮሐ 11፥ 24 " ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።"

3. የዘላለም ፍርድ
ማቴ 13፥ 40 "እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።"

(እነዚህን ርእሰ ጉዳዮች በየተራ በዝርዝር እንድናያቸው ለሌላ ጊዜ ተጠብቀው ይቆዩ)

እኛ የምንኖርበትስ ዘመን ምን አይነት ዘመን ነው?
አሁን እኛ ያለንበት ይህ ዘመን ለነዚያ ለመጀመርያው ከፍለ ዘመን ቅዱሳን "የሚመጣው ዘመን" ተብሎ የሚጠበቅ ዘመን ነበር። በርካታ ክርስቲያኖች አዲስ ኪዳንን ሲያነቡና "የሚመጣው ዘመን" የሚለውን ሃረግ ሲያዩ ጊዜ ተኮር የሆነውን የቃሉን አገባብ ከአውዱ በመነጠል፣ ዛሬም ከ2000 አመታት በኋላ የመልእክቱ ቀጥተኛ ተደራሲያን ራሳቸውን በማድረግ፣ ገና አሁንም ወደ ፊት የሚጠበቅ ዘመን እንደሆነ አድርገው ያስቡታል። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጽሐፊዎች ግን ሊያመለክቱ የፈለጉት እነርሱ ያኔ ከ2000 አመታት በፊት ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነው "አሮጌና ውራጅ ሆኖ ሊጠፋ በቀረበው" የድሮ ስርአት ቀንበር ስር እየኖሩ ወደፊት ሲጠባበቁት የነበረውን አዲሱን የክርስትናን የነጻነት ዘመን ነው። እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ግን እነርሱ "ሊመጣ ያለው ዘመን" ብለው በሚጠሩት ዘመን ውስጥ ሲሆን ይኸውም የአዲሱ ኪዳን ዘመን ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ "የአሁኑ ዘመን" ተብሎ የሚጠራው የዘመን ምዕራፍ ያበቃው በ70 አ.ም ላይ በሆነው፣ ያንን እሮጌ ስርአት ፈጽሞ ባስውገደው የኢየሩሳሌም ጥፋትና የቤተመቅደሱ ውድመት እስከሆነ ድረስ፣ እንግዲያውስ "የሚመጣው ዘመን" ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አዲሱ ስርአት አሮጌውን ተክቶ መጥቶአል። እኛ አሁን የምንኖረው "ሊመጣ ያለው ዘመን" ተብሎ በተገለጠው አዲስ ዘመን ውስጥ ነው።

ማር 10፥ 29-30 " ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥  አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።"

አሁን እኛ ያለነው "ሊመጣ ያለው ዘመን" እየተባለ ሲጠራና ሲጠበቅ በነበረው ዘመን ውስጥ ነው፣ አሁን የዘላለም ሕይወትም ጀምሮአል። እኛም የዘላለምን ሕይወት ተቀብለናል።

ሊመጣ ያለውን ዘመን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?
ፍጻሜ የሌለው ዘመን ነው። የዘመኑ መጨረሻ የመጣው ያኔ የመጀመርያው ከፍለ ዘመን አማኞች በነበሩበት ዘመን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመርያው ከፍለ ዘመን ላይ ከነበሩት የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ዘመን የዘለለ የሚናገርለት ሌላ "መጨረሻ" የለውም። መጨረሻው ሁልጊዜም ቢሆን ለእነርሱ ቅርብና ሊመጣ ያለ ነበር። የአዲሱ ኪዳን ዘመን ግን ፍጻሜ የለውም።

ኢሳ 9፥ 6-7 " ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።  ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።"

ኢሳይያስ የሚተነብየው ክርስቶስ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሊገዛ ስለሚመሰርተው ፍጻሜ ስለሌለው መንግስቱ ነው። የክርስቶስ መንግስትና አገዛዝ ፍጻሜ የሌለው ነው። ዳንኤልም በተመሳሳይ የክርስቶስ መንግስት ለዘላለም የማይፈርስና ለማንም የማይሰጥ እንደሆነ ይነግረናል።

ዳን 2፥ 44 "  በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች።"

በሮማውያን ነገስታት የአገዛዝ ዘመን፣ እግዚአብሔር መንግስቱን አቋቋመ ለዘለአለምም ጸንቶ ይኖራል አይፈርስምም።

ዳን 7፥13-14 "በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።  ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።"

የክርስቶስ አገዛዝ  የማያልፍና የማይጠፋ ዘላለማዊ መንግስት ነው።

ሉቃ 1፥ 32-33 "እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።"

ኤፌ 3፥ 21 " ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።"

ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእግዚአብሔር ከብርን መስጠት የቤተክርስቲያን ዘላለማዊ ተልእኮዋ ነው ሲል ጳውሎስ ይነግረናል። የአዲሱ ኪዳን ዘመን ይኸውም የክርስቲያን ዘመን ጊዜአዊ አይደለም። ይህ የምንኖርበት የኪዳን ዘመን ፍጻሜ የሌለው የማያልፍና የማያልቅ ዘላለማዊ ዘመን ነው።

እብ 13፥ 20 "በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥"

ማጠቃለያ፦
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ግኡዝ አለም በእሳት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ እንደማያስተምር ሁሉ፣ ገናም ያልመጣ ወደ ፊት የምንጠብቀው ሌላ ዘመን እንዳለም አያስተምርም። አሁን እኛ ያለንበት ይህ የክርስትና ዘመን ፍጻሜ የሌለው የአዲሱ ኪዳን ዘላለም ነው። የአዲሱ ኪዳን ዘመን ደግሞ የመጨረሻዎቹ ቀናት፣ ወይም ፍጻሜ የሚባል ማለቂያ የለውም፣ ያልተፈጸመና ገና ወደ ፊት ሊፈጸም የቀረም ምንም ነገር የለውም።

በዚህ በምንኖርበት የአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ስንኖር ማድረግ የተገባን ምን ነገር የኖር ይሆን? ወንዶችንና ሴቶችን ሰዎችን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑና የዘላለምን ሕይወት ስጦታ ይቀበሉ ዘንድ በንስሃ ወደ መንግስቱ እንዲገቡ በወንጌል ስብከት መጥራት አለብን። በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ሕልዎት፣ በመገኘቱ ውስጥ እየኖርንና ሳናቋርጥ ቀንና ሌሊት እያመለክነው፣ ሰዎች ከዘላለም በፊት ወደ ተዘጋጀላቸው ወደ መዳናቸው እንዲመጡ የመጋበዙ ስራ የማይቋረጠው ቀጣዩ ስራችን ነው። ከአዲሱ ሰማይና ምድር ወጥቶ ወደ ሁሉ የተላከውን ግብዣ ልብ በሉና ስሙ፦

ራእ 22፥ 17 " መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።"

ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ በመንፈስ ቅዱስና በቤተክርስቲያን የተጀመረው ሰዎችን ሁሉ ወደ መንግስቱ እንዲመጡ የመጋበዝ ስራ በትውልድ ሁሉ ውስጥ ሳይቋረጥ እየተሰማ እኛ ጋር ደርሶአል። እኛም የሰማን ላልሰማው ሁሉ እያሰማን የስብከቱ ስራ ለሌላ ትውልድ እንዲደርስና እንዲተላለፍ አደራና ጥሪ አለብን። መልእክታችንም ሰዉን ሁሉ "ና"፣ "ኑ" የሚልና "የተጠማ ሁሉ ይምጣ"  የሚል ነው። ትውልድ ሁልጊዜ አለ። ትውልድ ይሄዳል ትውልድ ይመጣል። ወንጌል ግን ለዘላለም ነው፣ አይለወጥም። ሁላችንም በመንግስቱና በዘላለማዊ ኪዳኑ ይምንኖር ይህንን የስብከት ተግባር እየፈጸምን፣ በታማኝነትም የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ መንግስት እያወጅንና ለተጠሙም ሁሉ መጥተው እንዲጠጡ እየጋበዝን በስራ ላይ እንዳለን ተስፋ አደርጋለሁ።

ዘመኑ ፈጽሞ አያበቃም፣ መጨረሻም የለውም፣ ነገር ግን አንድ ቀን እንሞትና ይህንን በስባሽ ና ሟች የሆነ ገላ አውልቀን ጥለን ለዘለአለም በሰማይ ልንኖር መንፈሳዊውንና የማይሞተውን አካል ተቀብለን እንለብሳለን። ስንሞት ወደ ጌታ እንሄዳለን።

2ቆሮ 5፥ 1 " ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።"
እንግዲህ በአራት ተከታታይ ጥናት ያዘጋጀሁትን ጽሁፍ እዚህ ላይ አበቃሁ። መጽሐፍ ቅዱሱን ለሚወድና የክርስቶስን ትምህርት ለሚያውቅ አንባቢ ጥናቱ እጅግም እንግዳ ሃሳብ እንደማይሆንበት ይሰማኛል። ቢሆንም ለተከታተላችሁኝ ሁሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው። ጽሁፎቹን ላይክና ሼር ብታደርጉአቸው ደግሞ ወደ ሌሎች ያላቸው ተደራሽነት ይፋጠናል። እኔ ግን ለምታነሱአቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያለኝን አክብሮት እየገለጽሁና ለውይይትም ያለኝን ዝግጁነት ሳልሸሽግ በሌላ ርእሰ ጉዳይ እስክንገናኝ "አምላክ ከእናንተ ዘንድ ይሁን!" ብዬ ልሰናበት።

ይህ አለም መጨረሻ አለውን?

የአለም መጨረሻ

በቄስ ግዛቸው ከበደ

መግቢያ፦

ማቴ 13፥ 40  እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።

ይህ የምንኖርበት "አለም መጨረሻ አለው" ብሎ ማመን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ነው? በእውኑ አለም መጨረሻ አለው ወይ?

"የአለም መጨረሻ" የተሰኘው  ይህ ርእሰ ጉዳይ በበርካታ የህትመትና የፊልም ስራዎች ላይ የሚራገብ አስተሳሰብ ነው። ማቆሚያ በሌለው ትንበያ ይህ አለም እንዴት እንደሚፈጸም እየተነገረ ነው። የክርስትናን የቆየ ልማድ ጨምሮ በበርካታ የአለም ታላላቅ ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ውስጥም የሚስተጋባ ነው። እግዚአብሔር ፈጽሞ እስኪያጠፋው ድረስ ይህ አለም እየከፋና እየባሰበት እንደሚሄድ በበርካታ የስነ መለኮትና የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራንና ሰባኪያን በተደጋጋሚ ሲነገረን ኖሮአል።

እንደመጽሐፍ ቅዱስ አማኝና ተማሪ በቅንነት ልጠይቅ ፤ ይህ አለም አንድ ቀን የሚያበቃለትና የሚጠፋ የመሆኑ ነገር በእርግጥም የቅዱስ ቃሉ ትምህርት ነው ወይ?

የቃሉ አክባሪና ተማሪ የሆናችሁ ወዳጆቼ ከላይ ያቀረብኩላችሁን ጥያቄ ቀጥሎ ባሉት ክፍሎች ብርሃን ተመልክታችሁ ሃሳባችሁን ሰንዝሩልኝ። በጉዳዩ ላይ የአንድን ሰው ትኩረት እንኳ ማግኘቴን ከተረዳሁ ወደቀጣዩ ሃሳቤ አልፋለሁ። እስከዚያው የማሰላሰያ ጥቅሶቹን እነሆ፦

ዘፍጥረት 8፥ 21-22 "እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም።
በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።"

መዝሙር 148፥ 4-6 " ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት፤ የሰማያት በላይም ውኃ። እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት። ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም።"

መዝሙር 78፥ 69 "  መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።"

መዝሙር 119፥ 90 "እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፤ ምድርን መሠረትሃት እርስዋም ትኖራለች።"

መክብብ 1፥ 4 "ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው።"

ማቴዎስ 13፥ 40 "እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።"
♦♦♦♦♦♦♦

ክፍል አንድ

ቀደም ብዬ ላካፍላችሁ በጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ ስለ አለም መጨረሻ በብዙዎች ዘንድ የሚታመነው እምነት ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ አሳብ አንስቼ ነበር፣ ይህ አለም አንድ ቀን ያበቃለታል ወይ? መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ያስተምራል? የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር። በርእሰ ጉዳዩ ላይ የጥቂት ሰዎችን ትኩረት ማስተዋል ስለቻልኩ ቀጣዩን ነገሬን ላቅርብ። አለም መጨረሻ አለው፤ አንድ ቀን ያበቃለታል ስለሚለው የቆየ አስተሳሰብ ወይም "እምነት" መጽሐፉ ቅዱስ ምን ይላል? በዚህ ጥያቄዬ እና በብዙዎች አስተሳሰብ ፊት ቆመው የሚፋጠጡንን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ቀደም ሲል ለንጽጽር ትቼላችሁ ነበር፤ በዚህ ክፍል በመጠኑ ተጠግተን እናያቸዋለን፣ የምንባባቱ ሃሳብ ተቃራኒ የሚመስሉ ትንቢታዊ መልዕክቶችንም እያነሳሁ ለሚቀጥለው ጥናታችን የሚያዘጋጀንን ጥያቄ እጠቁማለሁ።

ዘፍጥረት 8፥ 21-22 " እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም።  በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።"

አንዳንድ ወገኖች እግዚአብሔር በአንድ ወቅት አለምን በውሃ አጥፍቶ ነበር፣ በሚቀጥለው መጻኢ ጊዜ ደግሞ በእሳት ያጠፋዋል ሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህም አስተሳሰባቸው በ2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 6 እና 7 ላይ " ... ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤  አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።" ተብሎ የተጻፈውን እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ።

ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ምንባብ ላይ ግን ያለው የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል "ምድርን ደግሜ አላጠፋም" የሚል መሆኑ ግልጽ ነው። ይህም "የማጠፋበትን ዘዴ እቀይራለሁ" የሚል እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል። ደግሞስ ምድርን በውሃ ከማጥፋት ይልቅ እልም አድርጎ በእሳት አቃጥሎ ማጥፋት ምን የሚያጽናና ተስፋ በውስጡ አለበት? ምንባቡ ግን በግልጽ እንዳስቀመጠው "ምድርን ደግሜ አላጠፋም" የሚል ተስፋ ነው የተሰጠው። መጻህፍት የየራሳቸው አውደ ምንባብ እንዳላቸው የሚያስተውል የቃሉ ተማሪ እነዚህን ተቃራኒ የሚመስሉ ነገር ግን በየራሳቸው አውድ መተርጎም ያለባቸውን ምንባባት አያምታታም አያደባልቅምም።

መዝሙር 148፥ 4-6 "ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት፤ የሰማያት በላይም ውኃ። እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት። ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም።"

ፈጽሞ እንዳያልፉ አድርጎ የመሰረታቸውን ሰማይንና ምድርን በተመለከተ የእግዚአብሔር ውሳኔ ምንድን ነው? ከላይ በዘፍጥረት 8፥ 21 ላይ ካየነው አሳብ ጋር አይመሳሰልምን? እግዚአብሔር ሕያው የሆነውን ነገር ሁሉ በድጋሚ እንዳያጠፋ ተናግሮአል። በእውነት እግዚአብሔር ሊታመን ይችላል ፣ ቃሉንም ይጠብቃል። ታዲያ በማቴዎስ 24፥ 35 "ሰማይና ምድር ያልፋሉ..." የተሰኘው ትንቢታዊ ቃል ከዚህ ጋር እንዴት ይታረቃል? የብዙዎቻችሁ ጥያቄ ይመስለኛል።

መዝሙር 78፥ 69 "መቅደሱን እንደ አርያም ሰራ፣ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሰረታት"

በሌላው ትርጉም "መቅደሱን እንደ አርያም ሰራ፣ ለዘላለም እንደመሰረታት እንደ ምድር" ይላል። እግዚአብሔር ምድርን ለዘላለም መስርቶአት ከሆነ እንዴትስ "ፍጻሜ ሊኖራት ይችላል" ብለን እናስባለን? ይህንንስ አይነት አሳብ ከየት ነው ያመጣነው? የእግዚአብሔር ውሳኔ ወይስ የሰው አሳብ፣ የትኛው ይበልጣል? ቀጣዮቹን ምንባባት ደግሞ ተመልከቱ።

መዝሙር 119፥ 90 "እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፤ ምድርን መሠረትሃት እርስዋም ትኖራለች።"

መክብብ 1፥ 4 " ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው።"

ልብ አድርጉ፣ እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት የሚያልፍ የሚሄደው ትውልድ እንጂ ምድር ግን ለዘላለም እንደምትኖር ፍጻሜም እንደሌላት ግልጽ ያደርጋሉ። ይህንን ግዑዝ ፍጥረተ አለም ለማጥፋት ለማሳለፍ እግዚአብሔር እንዳቀደ ሊያመለክተን የሚችል አንድ ጥቅስ ካገኛችሁ እባካችሁ አስረድታችሁ ንገሩኝ። ታላላቅ አጥፊ የጦር መሳርያ ያለው የሰው ልጅና አንባ ገነን የአለም መሪዎችም እንኳ አብረው የኒዩክለር ቦንቦቻቸውን ቢጠቀሙ ምድርን ለማጥፋት አይችሉም። ምክንያቱም "ምድር ለዘላለም ትኖራለች" ያለው እግዚአብሔር ነው። እርሱም "ምድርን ዳግመኛ አላጠፋም" ሲል በሰጠው በቃል ኪዳኑ ይዞአታል።

እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን መጻኢ እድል በዚህ መልክ የሚያቀርበው ከሆነ፣ በዚህ ጥናት መግቢያ ላይ "እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።" ሲል የተጠቀሰው የማቴዎስ 13፥ 40 አይነት ጥቅሶች መታየት ያለባቸው እንዴት ነው? የአለም መጨረሻ ምንድን ነው? ይህንን በሚቀጥለው ክፍል እንመለስበታለን። እስከዚያው ይህችን አጭር ሃሳብ ለማንበብ ጊዜ ስለወሰዳችሁ በእግዚአብሔር ቡራኬ ልሰናበታችሁ።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት፣ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
♦♦♦♦♦♦♦

ክፍል ሁለት

አለም መጨረሻ አለው ወይ? በሚል ጥያቄ ቀደም ሲል ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት በቀረበው ርእሰ ጉዳይ በመግቢያውና በመጀመርያው ክፍል በተነሳው ሃሳብ ስለምንኖርበት ስለዚህ ግዑዝ አለም ሰማይና ምድር መጻኢ እጣ ፈንታ እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በግልጽ የሰጠውን ተስፋ የሚያወሱ ክፍሎችን በመጠኑ ለመመልከት ተሞክሮአል። በጥናቱም የተደረሰበት ድምዳሜ ቃሉ በግልጽ እንደሚመሰክረው ይህን ፍጥረተ አለም ለማጥፋት እግዚአብሔር ምንም እቅድ እንደሌለው የሚያረጋግጥ ነው።

"ይህ አለም አንድ ቀን ወደፊት በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል" የሚለው ትምህርትም የሰው ልብ ወለድ እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ድጋፍ የሌለው እንደሆነም ሊረጋገጥ ይችላል። ከዚህ ይልቅ ግን እግዚአብሔር የሰጠው ውሳኔ "ምድርን ደግሜ አላጠፋም" የሚል ሲሆን ቃሉም  "ምድር ትኖራለች፣ ምድር ለዘላለም ነው" ፣ የሚያልፈው የሚሄደው ትውልድ ነው ሲል ያስረዳል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው በተለይ ይህ ግዑዝ ፍጥረተ አለም ብን ብሎ ይጠፋል ብለው የሚያምኑና የሚያስተምሩ ወገኖች ከሚጠቅሱአቸውና በአግባቡ ካላሰቡባቸው የንባብ ክፍሎች መካከል 2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 5-7 ያለው ዋነኛው ነው። አስቀድመን ይህንን ክፍል በእጭሩ ተረድተን እንለፍ።

2ኛ ጴጥሮስ 3፥ 5-7  "ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤  አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።"

ጴጥሮስ የሚናገርለት "አለም" ሰማይንና ምድርን የሚያጠቃልለውን አለም ሲሆን፣ እነርሱም ያኔ በውሃ እንደጠፉና እንደሰጠሙ ይነግረናል። በውስጡ ይኖሩ የነበሩ ክፉ ሰዎች እንጂ፣ ይህ ተዳሳሹ ሰማይም ሆነ ምድር እንዳልጠፋና እንዳልተደመሰሰ እናውቃለን። ጴጥሮስ በኖህ ዘመን በውሃ ጠፍተው በነበሩ ሰማይና ምድር ደግሞም ያኔ በእሳት መጥፋት በነበረባቸው ሰማይና ምድር መካከል ልዩነትን አድርጓል።
ከጥፋት ውሃም በኋላ እንኳ ቢሆን እነዚያው ቀድሞ የነበሩት ተዳሳሾቹ ሰማይና ምድር ከዚያ በፊት በነበራቸው አይነትና መልክ ቀጥለዋል። በብሉይ ኪዳን ያለውን የሰማይና የምድር አቡቀለምሲሳዊ የቋንቋ ዘይቤ አጠቃቀም ካላወቅን በቀር ይህንን የጴጥሮስን ንግግር አሳስተን ልንረዳና፣ በኖህ ዘመን ጊዜ ያኔ የጥፋት ውሃ ያላደረገውን አሁን በእኛ ወይም በሚመጣው ሌላ ዘመን የጥፋት እሳት እንደሚያደርገው ሆኖ ተሳስቶ ይገባናል። አቡቀለምሲሳዊ ዘይቤ የሰማይና የምድር ጥፋት ያሚያመለክተው የሲቪልና የኃይማኖታዊ አገዛዝንና በዚያ ዙርያ የተሰባሰቡ ሰዎችን ጥፋት ነው።

በእውነት በጥፋት ውሃ ጊዜ እንዲጠፋ የተደረገው ምን ነበር? በቁጥር 6 ላይ ያለውን ተመልከቱ፦ "በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውሃ ሰጥሞ ጠፋ፤"  የጠፋው "ያን ጊዜ የነበረ አለም"  ነው እንጂ፣ ይህ ግዑዝ አለም አልነበረም፣ ይህንን ማስተዋል አያስቸግርም።  ሰለዚህ ታዲያ ይህ "አለም" የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? ይህ በጊዜው በሲቪልና በኃይማኖታዊ አስተዳደር በአግባቡ ተደራጅቶ የነበረው ማህበረብ ነው፣ እንጂ ተራውና ውዳቂው ነገር ሁሉ ማለት አይደለም። እግዚአብሔርን ከማያውቅና ከጠፋ ኃጢአተኛ ማህበረሰብ ጥፋት ወደመላው ፍጥረተ አለም ጥፋት እንዴት አልፎ መሄድና ማሰብ ይቻለናል? ያኔ በኖህ ዘመን በውሃ የጠፋችው ይህች ተዳሳሽዋ ምድር  አልነበረችም። እንግዲህ በዚህም ክፍል ላይ በእሳት ይጠፋል የተባለው እግዚአብሔርን የማያውቀው አመጸኛውና ከፉው የእስራኤል ህዝብ ነው እንጂ፣ የምንኖርበት ይህ ተዳሳሽ ፍጥረተ አለም አይደለም። በየትኛውም ገጹ ላይ ቢሆን ይህ ተዳሳሽ ፍጥረተ አለም ይጠፋል ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። በኖህ ዘመን ከሆነው የጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ላስታውሳችሁና ወደሚቀጥለው ልለፍ፦

በዘፍጥረት 8፥ 21   "እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ፦ ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም"

ታዲያ በመነሻ ጥቅሳችን በማቴዎስ 13፥ 40 "እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፣ በአለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል" ሲል ጌታችን በሰጠው ትንቢታዊ ቃል ውስጥ የተነገረለት "የአለም መጨረሻ" ምንድን ነው?  ቀጥሎ በዚህ ሁለተኛ ክፍል ጥናታችን ይህንንው በአጭሩ እንመለከታለን።

የትርጉም ችግር ካስከተላቸው የመረዳት ህጸጾች መካከል "አለም መጨረሻ አለው" የሚለው ይህ ሃሳብ በዋናነት ሊታይ ይችላል። ይህንንና መሰል ትንቢታዊ ጥቅሶች በግርድፉ የሚያይ ጠያቂ ያልሆነ አእምሮ የትርጉም ችግር ያስከተለበትን ግድፈት ሳይረዳ  "ይኸው አለም መጨረሻ አለው" ሲል ይከራከራል፤ የትንቢትና የራእይ መጻህፍትን ጨምሮ በአግባቡ ያላሰበበትን የጥቅስ እሩምታ ከአውደ ምንባቡ ነጥሎ በማከታተል ሊሞግትም ይሞክራል።

አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ በኩረ ቃል እዚህ ላይ ያለአግባብ "አለም" ተብሎ በትርጉም የገባው ቃል 'aion' የተሰኘው የግሪክ ቃል ነበር፤ ይህ 'aion' ደግሞ ፈጽሞ "አለም" ማለት እንዳልሆነ መዝገበ ቃላት ይነግሩናል። ቃሉ ይህንን የምንኖርበትን ነባራዊ አለም ለማለት ቢፈልግ ኖሮ 'kosmos' የሚለውን የግሪክ ቃል ይጠቀም ነበር። ይልቁኑ 'aion' የሚለው ቃል "ዘመንን"፣ ወይም "አንድ አይነተኛ ጊዜን"፣ ወይም "ወቅትን"፣ ወይም "ተለይቶ የሚታወቅ አይነተኛ ከፍለ ጊዜን" የሚያመለክት ትርጉም አለው።

በሁለተኛው ክፍል ምልከታችን ላይ ባነሳናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መሰረት ይህ የምንኖርበት ነባራዊ "አለም" ቀጣይ ሆኖ እንደሚኖር፣ በአንጻሩ ደግሞ "ትውልድ" ማለትም "ዘመን" ግን ፍጻሜ ያለው እንደሆነ ለማሳየት ተሞክሮአል። መጽሐፍ ቅዱስም ስለዘመን መጨረሻ በግልጽ የናገራል እንጂ ስለአለም መጨረሻ ምንም አይናገርም። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወደ በኩረ ቃሉ እየተመለሱ ይህንን የትርጉም ስህተት እያረሙ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል፤ ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 13፥40 በተጻፈውና KJV [King James Version] በተሰኘው የእንግሊዝኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው 'World' (አለም) የተሰኘው ቃል  NKJV [New King James Version] በተሰኘው የእንግሊዝኛ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዴት 'age' (ዘመን) በሚል እንደተለወጠ ማየት ይቻላል።  አሉን በምንላቸው የአማርኛ ትርጉሞች ላይ ግን ይህንን ለውጥ ማየት ይከብዳል።

ጌታ ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው መጨረሻ ስላለው ዘመን ነው እንጂ፣ መጨረሻ ስላለው አለም አይደለም፤ የህም ዘመን እርሱና የመጀመርያዎቹ ደቀመዛሙርት የኖሩበትና ያገለገሉበት ዘመን ማብቂያ ነው። በዚያ በእነርሱ ዘመን ማብቂያ ወይም ፍጻሜ ላይ ስለሚሆነው ነገር እየተናገረ ነበር እንጂ ይህ የምንኖርበት አለም ተቃጥሎ ሲጠፋ ሰለሚከናወን ነገር እየተናገረ አልነበረም፤ ምክንያቱም ይህ አለም እንደሚጠፋ የሚያስተምር ምንም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የለም። "አለም ይጠፋል" ብሎ ማሰብም ብሉይን መሰረት ላደረገው አይሁዳዊ አስተሳሰብና ለአይሁድ በተሰጠ ተስፋ ውስጥ ስርና መሰረቱን ለዘረጋው የአዲስ ኪዳን ክርስትና ባእድና እንግዳ  አስተሳሰብ ነው።

በዘመን መጨረሻ ላይ ምን ይሆን ዘንድ እንዳለው ልብ በሉ፦

ማቴዎስ 13፥ 49-50  "በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤  በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።"

እነማን ተለይተው እንደሚወሰዱ ልብ በሉ፣ "ኃጢአተኞች" ናቸው የሚለዩት። ከርእሰ ጉዳዩ ጋር ባይሄድም ይህ መለየት/ መወሰድ የንጥቀት ሌላው ገጽታ ይሆንን? ብሎ መጠየቅ የገባል። እርሱንም ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትና ትምህርት እንደሆነ  ወይም እንዳልሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።

ቤተክርስቲያን ልብ ካላለቻቸው ታሪካዊ ሁነቶች መካከል በ70 አመተ ምህረት በኢየሩሳሌምና በጠቅላላው በእስራኤል ህዝብ ላይ የደረሰው ጥፋትና ውድመት ነው። የህም ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት ንግሮችን ለመተርጎም በምታደርገው ጥረትና በአጠቃላይም በነገረ ፍጻሜ አስተምህሮትዋ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖን አስከትሎአል። ይህንንና መሰል የሆኑ የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ የፍርድ ንግሮችን በ70 አመተ ምህረት በኢየሩሳሌም ላይ ከሆነው ጥፋትና ፍርድ ጋር የሚገናኙ መሆናቸውን አለማስተዋል ስነ ፍታቴአችንንም ሆነ ጠቅላላውን የመጽሐፍ ቅዱሳችንን እውነተኛነትና ታማኝነት  ትልቅ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ይሆናል።

ኢየሱስ እየተናገረለት ያለው "መጨረሻ" እነዚያ ኃጢአተኞች የሆኑ የአይሁድ ህዝብ በኢየሩሳሌም መቃጠል ስለሚደርስባቸው መጨረሻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የዘመኑ መጨረሻ ከአይሁዳዊው ቤተ መቅደስ መፈራረስ ጋር የተያያዘ አንድ መጨረሻ እንደሆነ አለማስተዋል "ይህ የምንኖርበት ነባራዊ አለም ገና ወደፊት ተቃጥሎ ይጠፋል" ወደሚል ሌላ ያልተጻፈ መጨረሻ ተረት ተረት ይመራል።

የሚከተለውን ቃል ልብ በሉ፦
ማቴ 24፥ 1-3  "ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ።  እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።  እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።"

ደቀ መዛሙርቱ ያቀረቡለት ጥያቄ ሁለት ነው። መጀመርያ የጠየቁት "ይህ መቼ ይሆናል?" የሚል ነው። ይኸውም "ይህ ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሆኖ የሚፈራርሰው መቼ ነው?" ማለታቸው ነበር። ሦስቱንም ተመሳሳይ ወንጌላት ብናመሳክር "መቼ?" የሚለው ጥያቄ የሁሉም ትኩረት እንደሆነ እናያለን፦
ማቴ 24፥ 3 " ...ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል?... አሉት።"

ማር 13፥ 4  "ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል?... "

ሉቃ 21፥ 7 "እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ... ብለው ጠየቁት።"

"ይህ" ወይም "እነዚህ ነገሮች" የሚለው ቃል ወይም ሐረግ የሚያመለክተው በቁጥር 2 ላይ ያለውን የቤተመቅደሱን መፈራረስ ነው።

በቁጥር 1 ላይ ደቀ መዛሙርቱ የቤተመቅደሱን ሕንጻ ማማር አይተው እየተደነቁ ለኢየሱስ ያመለክቱታል። በቁጥር 2 ላይ ደግሞ ኢየሱስ በተቃራኒው "ይህ ሁሉ ይፈራርሳል" ሲል ይናገራል ። እነርሱም "ቤተመቅደሱ መቼ ይፈርሳል?" ወይም "ቤታችን የተፈታ ሆኖ የሚቀረው መቼ ነው?" ብለው መጠየቃቸው ግልጽ ነው።

ኢየሱስ በማቴዎስ 23 ላይ በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣ ፍርድ ከተናገረ በኋላና ፣ በምእራፍ 24 መግቢያ ላይም "ድንጋይ በድንጋይ ላይ" እንደሚወድቅ ከተነገራቸው በኋላ፣ ያኔ የደቀመዛሙርቱ ምላሽ በጥያቄ የታጀበ ነበር፤ "መቼ?" ይህ ስሜት የሚሰጥ ይመስለኛል።

የጥያቄአቸው ሁለተኛ ክፍል ደግሞ "የመምጣትህና የአለም (የዘመን) መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?" የሚል ነው።

አሁንም ጥያቄውን ለመረዳት እንዲቻለን የሦስቱንም ተመሳሳይ ወንጌላት ዘገባ በንጽጽር ማየት ያስፈልጋል።

ማቴ 24፥ 3 "እርሱም.... ንገረን፥ የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።"

ማር 13፥ 7 "ንገረን፥ ... ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ... ጠየቁት።"

ሉቃ 21፥ 7 "እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥... ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት።"

የሦስቱንም ወንጌላት ዘገባዎች ስናነጻጽር ደቀመዛሙርቱ ምጽአቱንና የአለም (የዘመን) መጨረሻ ከቤተመቅደሱ መፍረስ ጋር የተገናኘ ሁነት እንደሆነ ይመለከቱ እንደነበር እናስተውላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው የአለም መጨረሻ የዘመንን መጨረሻ ነው፣ ይኸውም የዘመን መጨረሻ በቤተ መቅደሱ መውደም የሚወከል እና በእስራኤል የመከራ እልቂት የሚደመደም የአይሁድ አለም መጨረሻ የአሮጌው ዘመን ማብቂያ ነው እንጂ፣ የምንኖርበት የዚህ ነባራዊ አለም ፍጻሜ ማለት አይደለም።

ማርቆስ 13፥ 4  "ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት።"

በጥቅሱ የመጀመርያ ክፍል ጥያቄ "ይህ መቼ ይሆናል?" የሚለው የሚያመለክተው የቤተመቅደሱን መፈራረስ ነው። በጥያቄው የሁለተኛ አጋማሽ ደግሞ "ይህ ሁሉ ሊሆን እንዳለው ምልክቱ ምንድን ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል።

የመምጣቱና የዘመን መጨረሻ ምልክት በ70 አመተ ምህረት ከሆነው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መፈራረስ ጋር ከተጠቀሰውና "ይህ" ከተባለው ጋር አንድ ነው። እነዚህም በተለያየ የጊዜ ምህዳር የሚከፋፈሉ የተለያዩ ወይም የተነጣጠሉ ጥያቄዎች አይደሉም። ደቀመዛሙርቱ በአእምሮአቸው የነበራቸው ሃሳብ አንድ ብቻ ነው፣ ይኸውም የቤተመቅደሱ መፍረስ ጉዳይ ነው። ከዚህ የቤተመቅደስ መፍረስ ጋር የመሲሁን መምጣትና የዘመኑን ፍጻሜ አገናኝተው ይጠይቃሉ። ጥያቄውም፦ "መጨረሻው የሚሆነው መቼ ነው?" የሚል ነው። ኢየሱስም የሰጣቸው ምልክት ሉቃስ በወንጌሉ "ኢየሩሳሌም በጭፍራ (በጦር ኃይል) መከበብ" ሲል የተረጎመውን "የጥፋት ርኩሰት" የተሰኘ ምልክት ነው። ኢየሱስም ግልጽ አድርጎ የነገራቸው መጨረሻው ያሚመጣው "በዚህ ትውልድ" ነው ብሎ ነው (ቁ 34)። ትንቢቱን ይናገር ለነበረው ለኢየሱስም ሆነ ትንቢቱን ይሰሙት ለነበሩ ለነዚያ የመጀመግያዎቹ አድማጮች "ይህ ትውልድ" ማለት ያው እነርሱ የኖሩበት ዘመን ትውልድ እንጂ ልጆቻቸው ወይም የልጅ ልጆቻቸውን አልያም በመቶና በሺህ አመታት ርቀት ከእነርሱ በኋላ የሚፈጠረው ሌላ ትውልድ ማለት አይደለም። "ትውልድ" የሚለው ቃል ትርጉም በአንድ አይነት ወቅትና ጊዜ ውስጥ የሚኖሩ የአንድ ዘመን ነዋሪዎችን ማለት ነው።
ሰለዚህ ያበቃል እየተባለ የተነገረለት ዘመን የአይሁድ ዘመን ነው። ይኸውም የሙሴ ስርአት አሮጌ ዘመን ነው። የሚያበቃውም ከአይሁድ ቤተመቅደስና ከኢየሩሳሌም ከተማ መፈራረስ ጋር ነው። መስቀሉና በአለ ሃምሳ ዘመኑ ሊፈጸም እንደተጀመረ ሲያመለክቱ በ70 አመተ ምህረት ላይ የሆነው የኢየሩሳሌም መፈራረስ ግን የዚያ የአሮጌ ዘመን ስርአት በፍርድ መዘጋቱን ያሳያል። አለም ሳይሆን ይሁዲነትና የባርነት ጨለማ ስርአቱ ሁሉ ያበቃው እዚያ ላይ ነው። አዲስ ኪዳን ወደፊት እያየ የሚናገርለት አስፈሪ የኃጢአተኞች ፍርድና ጥፋት አመልካች የሆኑ የንባብ ክፍሎች ሁሉ በዚህ አውድና ብርሃን የተነገሩ ናቸው።

ደቀመዛሙርቱም የቤተመቅደሱ መውደቅና የከተማይቱ መፈራረስ የአሮጌው ኪዳን ዘመን ማብቂያና የአዲሱ ዘመን ጅማሮ እንደሆነ ያውቁ ነበር። የህም በጣም አስፈላጊ ወደሆነ ዋና ጥያቄ ያደርሰናል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰንት ዘመን ያውቃል? ያለውስ ሰንት ዘመን ነው? በሚቀጥለው ጥናታችን እንመለስበታለን። እናንተም ዝም አትበሉ ቅዱሱን መጽሐፍ ዋቤ አድርጋችሁ ሃሳባችሁን አካፍሉን፣ እንማማር። እስከዚያው ይህችን አጭር ጽሁፍ ለማንበብ ጊዜ ስለሰጣችሁኝ በቅድስት ሥላሴ ስም ተባረኩ።

እግዚአብሔር ይባርካችሁ፣ ይጠብቃችሁ። እግዚአብሔር ፊቱን ያብራላችሁ፣ ጸጋውንም ይስጣችሁ። እግዚአብሄር ፊቱን ይመልስላችሁ፣ ሰላሙንም ይስጣችሁ። በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም፣ አንድ አምላክ። አሜን
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦

ክፍል ሦስት

አለም መጨረሻ አለው ወይ? የአለም መጨረሻ የተሰኘው ጽንሰ ሃሳብስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? በሚል መነሻ በለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍል አጫጭር ጥናቶች አይተናል። የተደረሰበትም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድምዳሜ ይህ ግዑዝ የሆነ ፍጥረታዊ አለም ወደፊት ይጠፋል የሚለው አስተሳሰብ የሰው እንጂ የእግዚአብሔር አሳብ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው የዚህን ግዑዝ አለም መጨረሻ ሳይሆን የዘመንን መጨረሻ እንደሆነ ለማስረዳት ተሞክሮአል። ዘመን ያልፋል እንጂ "ምድር ግን ለዘላለም ነው" (መክብብ 1፥ 4)፤ ታዲያ ያልፋል የተባለውና መጨረሻው እየተባለ በቅዱሳት መጻህፍት የተነገረለት ዘመን የትኛው ዘመን ነው? በዛሬው ጥናታችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው ስንት ዘመን እንዳለ በአጭሩ እንመለከታለን።

ስንት ዘመን ነው ያለው?
ዊልያም ባርክሌይ እንዲህ ይላሉ፦ "አይሁዶች ጊዜን በሁለት ከፍለው 'ይህ የአሁኑ ዘመን' እና 'የሚመጣው ዘመን' ብለው ይመድቡታል። 'የአሁኑ ዘመን' የተባለው በጥቅሉ መጥፎ የሆነውና በሰው ጥረት ሊታደስ የማይችለው ዘመን ነው። የሚታደስ የሚለወጥም ከሆነ የሚቻለው በእግዚአብሄር ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው። እግዚአብሔር ጣልቃ ሲገባ ደግሞ 'ሊመጣ ያለው ዘመን' የተባለው ወርቃማው ዘመን ይመጣል ይደርሳልም። በሁለቱ ዘመነት መካከል ግን የአዲሱን ዘመን መወለድ የሚያበስር ምጥ እንደሚሆን ያህል የጭንቀትና የፍርሃት ጊዜ የሆነው የጌታ ቀን ይመጣል። ዘካርያስ 14 ያ የጌታ ቀንና የኢየሩሳሌም ውድመት የተገናኘ እንደሆነ ይነግረናል። ስለሆነም የጌታ ቀን የተባለው የኢየሩሳሌም መፈራረስ፣ የአይሁድ ዘመን የተባለውን የአንድን ዘመን መጨረሻ ማብቃቱንና የክርስቲያን የአዲሱ ኪዳን ዘመን መጀመሩን የሚያመለክት ሁነት ነው። ለአይሁድ ጊዜ 'የሙሴ' እና 'የመሲሁ' ዘመን በሚል ለሁለት ይከፈላል። መሲሁም አዲሱን አለም የሚያመጣ እንደሆነ ይታወቃል። ስለሆነም የመሲሁ ዘመን /ክፍለ ጊዜ/ በምኩራባት ዘንድ "የሚመጣው አለም" ተብሎ ተለይቶ በዚህ ይጠራና ይታወቅ ነበር።"

በመላው አዲስ ኪዳንም በንጽጽር ቀርበው የምናያቸው ሁለት ዘመናት 'ይህ ዘመን' እና 'የሚመጣው ዘመን' የተባሉትን ብቻ ነው።

ማቴ 12፥ 32 " በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።"

ያለው "በዚህ " የተባለና "በሚመጥው" የተባለ ሁለት አለም ነው፤  በጥቅሱ መጨረሻ ላይ "የሚመጣው" የተሰኘው ቃል በግሪኩ 'mello' ነው፣ ይኸውም "ሊሆን ያለው" ወይም "ሊመጣ ያለው" (about to be) ማለት ነው። ይኸውም ዘመኑ ሊመጣ ያለው ገና ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ላይ ለነበሩት ሰዎች ማለት ነው። ብዙዎች ይህንን የሚመጣ ዘመን ኃጢአት የሌለበት የማይኖርበትም ዘመን እንደሆነ ያስባሉ፤ በዚህ ጥቅስ መሰረት ግን እንደዚያ አይደለም። በዚያ ይመጣል በተባለው ዘመን በመንፈስ ቅዱስ ላይም እንኳ ኃጢአትን የመስራት እድል ያለ ሲሆን፣ እርሱም ይቅር አይባልም፤ ይኸውም የሚያመለክተው የአሁኑን የእኛን ዘመን ሲሆን እርሱም የአዲሱ ቃል ኪዳን ዘመን ነው። ሁለቱም እነዚህ "በዚህ " እና "በሚመጥው" የተባሉ ዘመናት በውስጣቸው ኃጢአት ሊደረግባቸው የሚችል መሆኑን ጥቅሱ ያሳየናል።

ኤፌ 1፥ 21" ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤"

እዚህም ላይ በድጋሚ "በዚህ ዓለም" እና "ሊመጣ ባለው ዓለም" የተሰኙ ሁለት አለም ወይም ዘመናትን እናያለን። ስለዚህ አዲስ ኪዳን የሚናገረው ስለሁለት ዘመናት ነው፣ እርሱም "ይህ (የአሁኑ) ዘመን" እና "የሚመጣው ዘመን" የተሰኙ ናቸው። እነዚህን ሁለት ዘመናት በአግባቡ መረዳትና፣ መቼ እንደሚለወጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ጊዜ መለየት በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማችን ላይ በእጅጉ መሰረታዊ ነገር ነው። አዲስ ኪዳን ስለእነዚህ ሁለት ዘመናት ምን እንደሚያስተምር ተጠግተን እንይ። ልንመልሳቸውም የሚገቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፣ ለአሁኑ፦ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት በምን ዘመን ውስጥ ነበር? እኛስ አሁን እየኖርን ያለነው በምን ዘመን ውስጥ ነው? የሚለውን አንስተን በቀጣይ "ይህ ዘመን" የተሰኘው ጊዜስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በምን ባህርይ ነው የሚገለጠው? አዲስ ኪዳን "የሚመጣው ዘመን" ስለተሰኘው ጊዜ ምን የሚለው ነገር አለው? "ይህ ዘመን" የተሰኘው የሚያበቃበት ጊዜና "የሚመጣው ዘመን" የተሰኘው ጊዜ የሚጀምረውስ መቼ ነው? የሚሉትን አንስተን እንመለከታለን።

የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት በምን ዘመን ውስጥ ነበር?
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ይኖሩ የነበሩት እነርሱ "ይህ ዘመን" እያሉ ይጠሩት በነበረው ዘመን ላይ ነበር። ለአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን "የሚመጣው ዘመን" እየተባለ የሚጠራው ገና ወደፊት ይጠባበቁት የነበረ ነው፣ ነገር ግን "ይህ ዘመን" እያሉ የሚጠሩት እያበቃ ስለነበር "የሚመጣው ዘመን" ለእነርሱ በጣም ቅርብ ነበር።

1ቆሮ 2፥ 6-8 "በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤"

የዚህ አለም (የዚህ ዘመን) ጥበብና ገዥዎች እየተሻሩ ነበር። ምክንያቱም ዘመኑ እያለቀና እያለፈ ስለነበር ነው። እየተናገረ ያለው ስለአይሁድ ህዝብ መሪዎችና ስለአሮጌው ኪዳን ሥርዓት ነበር። "የዚህ አለም ገዥዎች" (የዚህ ዘመን ገዢዎች) ጌታን የሰቀሉቱ ናቸው። ዘመኑ ወይም ያ አለምና የአለም ሥርዓት እያለፈና እየተዘጋ ስለነበር እነዚህ ገዢዎች በቅርቡ ወደፊት የማይገዙበት ወይም የማይሰለጥኑበት ዘመንና አለም እየመጣ ነበር። እስቲ ይህንን አስቡ ብዙዎች እንደሚመስላቸው የአይሀድ ዘመን በመስቀሉ ላይ አብቅቶ ቢሆን ኖሮ እንዴት ገና ዘመኑን ወይም አለሙን ይገዛሉ ሊባል ይችላል? "የሚሻሩትን" የሚለው ቃል ያኔ የሚያመለክተው የዚያን አለም ወይም ዘመን መጻኢውን እድል ነው፣ አሁን ግን ያ አለም ተሽሮ አልፎ ሄዷል።

1ቆሮ 10፥ 11"ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።"

ጳውሎስ በግልጽ የሚናገረው የዘመናት መጨረሻ በእነርሱ ላይ መድረሱን ነው፣ እነርሱም ያኔ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የነበሩ ቅዱሳን ናቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ በሚሆን ምሪት በእያንዳንዱ ቀን በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደሆኑ ይሰማቸውና ያስተውሉ ነበር። ያኔም "ይህ ዘመን" ተብሎ የተጠራው ጊዜ ከአሮጌው ጥበቡና ከገዢዎቹ ሁሉ ጋር ሊያልፍና ሊያበቃ ተቃርቦአል። እንደመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሆነ ለምናምን ለእኛ  ያበቃል ይተባለው ዘመን ይኸውም "የመጨረሻው ዘመን" ካለፈ ሁለት ሺህ አመት ተቆጥሮአል። አሁን ክርስቲያኖች ሆነን የምንኖርበት ይህ የጸጋ ዘመን፣ የአዲሱ ኪዳን ዘመን፣ እግዚአብሄር የሰጠን ዘላለማችን፣ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር ነው።

ዕብራ 1፥ 1-2 "ጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤"

ኢየሱስ የተናገረው በዘመናት መጨረሻ ላይ ነው። የምን ዘመን መጨረሻ? መጽሐፍ ቅዱስ "ይህ ዘመን" እያለ የሚጠራው የአሮጌው ኪዳን መጨረሻ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ተናግሮ የጨረሰው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው። የዘመኑም ቁጥር ከጥንት ከአባቶች ጀምሮ ልጁ እስከተገለጠበት ጊዜ ያለውን ይሸፍናል። ልጁም የተገለጠው ያ ዘመን ሊያበቃ ሲቃረብ ነው። እግዚአብሔር በልጁ ከተናገረበት የዘመን መጨረሻ ሌላ የተለየ የመጨረሻ ዘመን የሚባል ነገር አሁንም ሆነ ወደፊት የለም።

ዕብራ 9፥ 26 "እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።"

አሁንም በድጋሚ ልብ በሉ፣ ኢየሱስ በሥጋው የተገለጠው መቼ ነበር? እርሱ የተወለደው በዘመኑ መጀመርያ ላይ ሳይሆን "በአለም ፍጻሜ" ይኸውም በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነበር። " ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤"   (ገላ 4፥ 4)። ኢየሱስ በስጋው ከሴት የተወለደው የዚህ ግዑዝ አለም መጨረሻ ወይም ፍጻሜ ሲቃረብ ነው ብሎ ማሰብ የተሳሳተ መረዳት ይሆናል ። ምክንያቱም እርሱ በስጋ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ይህ ግዑዝ አለም ገና ብዙ ዘመን እየኖረ ሳይፈጸም ቆይቶአልና። ከሙሴ ዘመንና ከዘጸአት ጀምሮ እሰከ ቤተመቅደሱ መፈራረስ ድረስ ያለው ጊዜ ረጅሙ ጊዜ ነው። ይኸውም ይህ ዘመን እየተሰኘ ሲጠራና ሲታወቅ የነበረው የአሮጌው ኪዳን ዘመን ሲሆን ኢየሱስም በሥጋው የተገለጠው በዚሁ በአይሁድ ዘመን መጨረሻ ላይ ነው። ጴጥሮስም ተመሳሳይ ነገር ይናገራል።

1ጴጥ 1፥ 20-21 " ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።"

ኢየሱስ ወደ አለም የመጣው በዘሙኑ መጨረሻ ላይ ነው፣ እርሱም የአይሁድ ዘመን የሆነው የአሮጌው ኪዳን ዘመን ማብቂያ ነው። ዘመኑም እስከወዲያኛው ያበቃው በ70 ዓመተ ምህረት ላይ ቤተ መቅደሱ ሲፈርስ ነው። በማቴዎስ 24 ላይ በኢየሱስ የተሰጠ የትንቢት ቃል ሀሉ የተፈጸመው በዘመኑ መጨረሻ ላይ ነው። ስለዚህም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ "ይህ ዘመን" እያለ በሚጠራው ዘመን የመጨረሻዎቹ አርባ አመታት ውስጥ ነው።

"ይህ ዘመን" የተሰኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊው የመጨረሻ ዘመን፣ ይኸውም የአዲስ ኪዳን ጸሐፍያን ሁሉ የኖሩበት ዘመን በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ የተገለጠው እንዴት ባለ ባህርዩ ነው? ቀጣዩ ጥናታችን ይህንን የሚመልስ ይሆናል። ለብዙዎቻችሁ እጅግም ያልተለመደ አሳብ እያነሳሁ እንደሆነ አውቃለሁ። ሆኖም ጊዜ ወስዳችሁ ጭረቴን ለተመለከታችሁ ሁሉ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው። የበዛው ጸጋ ይደግፋችሁ! አሜን!!
♦♦♦♦♦♦♦♦