Thursday, October 22, 2015

እውነትና ተግዳሮቱ

እውነትና ተግዳሮቱ
" እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም።" (መጽሐፈ ምሳሌ 23፥ 23)
ብዙዎቻችን በልዩ ለዩ አመለካከቶች የሚቀሰቀስ የትምህርት ንፋስ ወዲያና ወዲህ እያንሳፈፈ የሚወስዳቸውን አይነቶች ሆነናል። በዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች ሁሉ ያለው ማስጠንቀቂያ፦
" እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥"  (ኤፌ 4፥ 14)  የሚል ነው።
ይልቅስ ነቃ ብለን እንደ ቤርያ ሰዎች የምንሰማውን ሁሉ መጠየቅና እርግጠኛውን ነገር በቅዱሳት መጻህፍት ብርሃን መመራመርና መፈተን ይገባናል።
"እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ።"   (ሐዋ 17፥ 11-12)
በእርግጥም በእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ላይ ምናልባት ምቾት እንኳ ባይሰማን "ራሳችንን እየመረመርንና እየፈተንን በእውነትም ምን ያህል እውነትን ፈላጊዎች እንደሆንን ማረጋገጥ ይገባናል።
" በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?" (2ቆሮ13፥ 5)
 "ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤" (1ተሰ 5፥ 21)
አዎን በዙርያችን በሚነፍሰውና ሁሉን ጠራርጎ እንደሚወስድ ጎርፍ በሆኑ የስህተት ትምህርቶች በቀላሉ እንዳንወሰድና እንዳንታለል በእርግጥም እንደቤርያ ሰዎች የመጽሐፉ ሰዎች ልንሆን ያስፈልገናል።
በርካታ ሰዎች ግን እውነትን መያዝ አይችሉበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ምቾት ፈላጊዎችና ተድላ ፈላጊዎች ብቻ ናቸው። በዘመናችን ባሉ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ዘንድ ይህ ችግር ለብዙዎች አይነተኛ መገለጫ ሆኖአል። በእርግጥም ራሳችንን ሞት በሆነ ነገር እያዝናናን ያለን እንመስላለን። ይህም ለካ የእስራኤል ህዝብ ከመደምሰሳቸውና ወደምርኮ ከመወሰዳቸው በፊት እንደነበሩበት አይነት ያለ ህይወት ነው። ነብዩ ኢሳይያስ በኖረበት ዘመን የነበሩትን ህዝብ እንዴት እንደገለጣቸው ልብ አድርጉ፦
ኢሳ 30፥ 8 "አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘላለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው።"
ኢሳ 30፥ 9 "ዓመፀኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፤"
ኢሳ 30፥ 10 "ባለ ራእዮችን። አትመልከቱ ይላሉ፥ ነቢያትንም። ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥"
ኢሳ 30፥ 11 "ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ ይሉአቸዋል።"
ኢሳ30፥ 12 "ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል። ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና"
ኢሳ 30፥ 13 "ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።"
ኢሳ 30፥ 14 " የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቅቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት ወይም ውኃ ከጕድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም። "
ኢሳይያስ በዘመኑ ስለነበሩ ሰዎች ምን እያለ እንደነበር ይታያችኋልን? ለካህናቶቻቸውና ለአስተማሪዎቻቸው ንጹሁንና ጠንካራውን የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ማስተማር እንዲያቆሙና እንዲተዉ፣ በምትኩ ግን ደስ የሚያሰኙና የሚያጽናኑ፣ ለብ ያሉና የማይጎረብጡ ቃላትን፣  እንዲያመጡላቸው ይነግሩአቸዋል። ጆሮዎቻቸውን እንዲኮረኩርና እንዲያሳክክ ሰለሚፈልጉ፦
" ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።" (2ጢሞ4፥ 3)፣ ተብሎ እንደተጻፈ የየቤተክርስቲያኖቻቸውን ምስባኮች የሚያረካቸውን ቃላት በሚነግሩአቸውና ትንቢትን በሚናገሩላቸው አስደሳችና አዝናኝ ኮሜድያን-ወከያንያን በሆኑ ነብያቶቻቸው አጨናንቀውታል። እነርሱም ጥሪያቸው ማዝናናትና ማስደሰት የሆነ ይመስል አድማጮቻቸውና አድናቂዎቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ይነግሩአቸዋል።
እውነት ግን በባህርዩ ሁልጊዜ ይገዳደረናል፣ ያስቸግረናል፣ ምቾትም አይሰጠንም፣ ዝና የለውም፣ ታዋቂም ተፈላጊም አይደለም። ሁልጊዜም እንደዚያው ሆኖ ይኖራል። ኢየሱስም፦
" በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።" (ማቴ 7፥ 13-14)፤ ሲል የተናገረው ለዚህ ነው።
ወደ እውነት የሚያደርሰው መንገድ ጠባብ ዳገታማ እና አስቸጋሪ ነው። ዋጋ ሊከፍሉለት የሚሹ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። የሚበዙት ግን ቀላሉን የመውጫ መንገድ እየመረጡ በታዋቂነትና በዝነኝነት መንገድ ይጓዛሉ።
ኢየሱስ ስለዕንቁ ነጋዴው ምሳሌ በተናገረ ጊዜ፦
" ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።" (ማቴ 13፥ 45-46)፤ ሲል በእውነትም እውነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልና ብዙ ተግዳሮት እንዳለበት ማብራርያ ይሰጠናል።
በእርግጥም እውነት ያለ ብዙና ታላቅ ዋጋ በብላሽ አይገኝም። እውነትን ለመግዛት ያለንን ሁሉ አራግፈን ሸጠን ከፍ ያለ ዋጋ መክፈል ይጠበቅብናል። ያንን ዕንቁ ለማግኘት የሚከፈለው ታላቅ ዋጋ ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስ ራስን አሳልፎ ከመስጠት ያነሰ ዋጋ አይደለም።
የሚበዙ ሰዎች ለምን ስህተትን ይከተላሉ? (እንደው ለመሆኑ ስህተትስ አለ ወይ?)
ስህተት ቀላል ነው፣ ደግሞ ይመቻል ፣ አያጨናንቅም፣ አያካብድም፣ አዝናኝና ታዋቂም ነው (ሁሉም ሰው ሊያደርገውም ሊሞክረውም ደግሞ ይችላል) ። ስህተት ምንም ዋጋ አይጠይቀንም ወይንም ምንም ዋጋ አያስከፍለንም፣ ወይንም በአኗኗራችን ላይ ምንም አይነት መስዋእትነት ወይም ቁርጠኝነት ወይም ለውጥ አይጠይቀንም። ስህተት ለማመን፣ ለማስደሰትም ሆነ ለማዝናናት በጣም ቀላል ነው። ምንም አይነት ብርቱ ጥናትም ሆነ በምርምር የታገዘ ብርቱ አሳብ አይፈልግም። ወደ ገደል ጥፋት የሚያደርስ የምቾትና የመብት ብዛት እያስከተለ ለእርድ መንጋ ያጉራል።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን አይነተኛ የጥፋት አደጋ ሲያመለክት፦
" የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።" (2ጴጥ 3፥ 15-16) ብሎአል ።
በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ከማጥናትና እንዴት በአግባቡና በትክክል እንደሚተረጎም ከመማር ይልቅ ጆሮዎቻቸውን ማከክና መኮርኮር ይወዳሉ። ክርስቶስና ሐዋርያቱ ግን 'ምቾት ፈላጊዎችን'  ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመሳብ አንዳች ሙከራ ሲያደርጉ አይታዩም፣ የልቁኑ ግን ይህ ነገር እውነት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትን በየጊዜው ለመመርመር ፍላጎት ያላቸውንና እንደ ቤርያ ሰዎች ያሉ 'እውነት ፈላጊዎችን' ይፈልጉ ነበር።
እኛ የቃሉ አገልጋዮች ጠንካራውንና አስቸጋሪውን እውነት በማስተማራችን፣ ወይም ሰዎችን በእውነት ቃል በመገዳደራችን፣ እውነትን በመግለጣችን እንዱሁም ስህተትን በመንቀፋችንና ተቃውመን በማስተማራችን ምንም አይነት ይቅርታ ማንንም መጠየቅ አያስፈልገንም። የልቁኑ ግን ለታመነው እውነት የሚታመኑ ጥቂት ታማኞችን፣ በእውነት ላይ አብረውን የሚቆሙትንና አስቸጋሪውን የእውነት አቀበታማ መንገድ ለመሄድ የቆረጡ፣ ወደህይወት በሚያደርሰው ጠባቡ በርና በቀጭኑ መንገድ ገብተው ለመሄድ ፍላጎት ያላቸውን ብቻ እንፈልጋለን ።
ስለዚህ እውነት ፈላጊ ማን ነው? እውነትን መፈለግ እንዴት ነው? እውነትን ተራ በሆነ አካዳሚክ አቀራረብ ልንረዳው አንችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስን አብርሆት አጥብቀን በጸሎት መፈለግ አለብን፡፡ አብርሆት ማለት ደግሞ እግዚአብሔር በነዚያ ቅዱሳት መጻህፍት አማካኝነት ራሱን መግለጹ ነው፡፡ አብርሆት ት ጥ ቅ  የተባለ ሦስት ነገሮችን የሚጠይቅ እንደሆነ ተመልክተን እናጠቃልል፡፡
ትህትና (Humility) ›መደገፍ ነው፡፡ አይናችንን ለቅዱሳት መጻህፍት መረዳት እንዲከፍትልን በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ አለብን፡፡
ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።” (መዝ 119÷ 18)
“አለን የምንለው ላይብረሪ እና ጥናት ሁሉ እርሱን በትህትና ከመጠጋታችን ጋር ሲነጻጸር ባዶና ተራ ይሆናል” (ቻርልስ ስፕረጂዮን)
“ትህትና ጸጋን ሁሉ ሲመገብ ትዕቢት ግን ይራባል!” (ሪቻርድ ባክስተር)
ጥንካሬ (Hared Working) ቃሉን በጥልቀት ለመረዳት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል
“ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳ 2÷ 1-5)
የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ጊዜና ትጋት ይጠይቃል፡፡ ሥራው ለሰነፍ ሰዎች የሚሆን አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን እና ፈቃዱን ማወቅ ለየቀኑ ኑሯችን ጥንካሬን ይሰጠናል፣ ይኸውም ደግሞ ያለማቋረጥ ቃሉን ከማጥናት የሚመጣ ነው፡፡ በትጋት ውስጥ ለሚቆዩ ሰዎች መረዳቱ በጊዜ ውስጥ ቆይቶ ይመጣል፡፡ ይህንን ታላቅ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ለመረዳት እንደ ቤርያ ሰዎች የመጽሐፉ ሰዎች በመሆን ብርቱ ምርመራና ጥረት እያደረጋችሁ ደግማችሁ ደጋግማችሁ አንብቡት፡፡ ለራሳችሁና ለሚያስተምረው ሰው ጸልዩ፡፡
“ተግቶ ማሰብ ሕይወት/ ኑሮ ነው” (ስፕረጂዮን)
“ተግቶ ማሰብ ትግል ነው” (ሲ.ኤስ. ሎቬት)
ቅድስና (Holiness) እግዚአብሔር ራሱን በቃሉ በኩል እንዲገልጽልን የምንጠይቅ ከሆነ በቅድስና መመላለስ አለብን፡፡
“ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።” (ያዕ 1÷ 21)
“ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” (ዕብ 12÷ 14)
“እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።”  1ጴጥሮስ 2÷ 1-3
(የማጠቃለያ የምክር ቃል ከቶማስ ዋትሶን)
1. ለቅዱሳት መጻህፍት ከፍ ያለ ዋጋ ስጥ
"ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።" መዝ 119፥ 7
ከሌሎች መጻህፍት ሁሉ በላይ አስበልጠህ ሀብትህና የተሰወረ መዝገብህ አድርገው።
ማመንና ማድረግ ያለብንን ነገሮች ሁሉ በውስጡ አጭቆ የያዘ ውድ መጽሐፍ ነው።  ጸጋን የሚያጠባንና የሚመግበንም እርሱ ነው። በእውነት ቃል ዳግም የተወለደውና እርሱን እየተመገበ የሚያድገውም ሰው አማኝ ነው።
2. ቃሉን ስታነብ የምርህን ዋጋ ሰጥተህ አንብብ። ስራዬ ብለውና ዋጋ ሰጥተው ከምር ለሚያነቡት ሰዎች ብቻ የህይወት ማጣፈጫ ቅመማቸው ነው። እጅግ ዋጋ ካለው ነገራችንና ከምንወደውም ጉዳያችን ሁሉ ጋር የሚገናኝ ነው።
የዘላለም ሕይወት እና ሞት፣ መንግስተ ሰማያትና ሲዖል፣ የእምነትም ስራ የተሰኙትን፣ በውስጡ ያሉትን ርዕሰ ጉዳዮች ልብ በል። በእውነት የምሩን ዋጋ ሳይሰጣቸው እነዚህን ነገሮች ማንበብ የሚችል ማን ሰው ነው? ሰለዚህ ክቡር በሆነ የእርጋታ መንፈስ እና በተቀናበረ ስርአት  ሆነህ አንብበው።
3. መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ዘዴ ይኑርህ፣ ምናልባትም ለራስህ የምታነብበትን ስርዓት አብጅ። ለማንበብ ስርዓትና ዘዴ ሲኖር ያነበቡትን ለማስታወስና ለማሰላሰል ይቻላል።
4. ቃሉን ለማንበብ በእውነተኛና በቅን ልብ ቅረብ፤
ሀ- የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ለማወቅ በልብ ፈቃደኝነት አንብበው፣ ከውስጡም ያየኸውን ማንኛውም እውነት ለመደበቅ አትፈልግ።
ከቅዱሳት መጻህፍት አንተ የምትፈልገውንና የሚመችህን ብቻ ነጥለህ ልትወስድና ልትመርጥ አትችልም።
ለ- የተሻልክ ሰው ለመሆን እንድትችል አንብበው። ቃሉ የምንቀደስበት መንገድ ነው።
የበለጠ ክርስቶስን እንድትመስል ሊያደርግህ የሚችለውን እውነት እንድታገኝ ወደ እግዚአብሔር ቃል ቅረብና አንብበው
5. የሚያጽናናህን የተስፋ ቃል በብርቱ እንደምትፈልግ ሁሉ የአምላክንም ትዕዛዛት ፈልግ።
ልትወጣው ከሚገባህ ተግባርና ከኃላፊነትህ በላይ የበዛ መጽናናትን አትፈልግ፣ አለዚያ መጽናናትህን ሀሰት ሆኖ ታገኘዋለህ።
6. የምታነበውን ሁሉ ለመተግበርና ለመለማመድ ቁርጠኝነት ይኑርህ።
ክርስቲያኖች ሕያው የሆኑ፣ የተጻፈውን እውነት የሚኖሩ፣ ተንቀሳቃሽ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለባቸው። ቃሉም የመታዘዝ መመርያ ነው እንጂ የእውቀት መመርያ ብቻ አይደለም።
7. ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር መቀለድም ሆነ ቅዱሳት መጻህፍትን እንደዋዛ አቅልሎ ከማየት ዝንባሌ ተጠንቀቅ ተጠበቅም።  
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

Thursday, July 23, 2015

የመስቀሉ ወንጌል

የመስቀሉ ወንጌል
 (1ቆሮ 1፥ 18፤ ገላ 1፥ 3-4)        
በእግዚአብሔር ቃል እንደተገለጠው እውነተኛው ወንጌል የመስቀሉ ወንጌል ነው። ከዚህ የተለየው ተቃራኒው ደግሞ "ሌላ" እየተባለ የሚጠራውና፣ ሰውን እና ሥራውን ማዕከል ያደረገ በሥጋ ትምክህት የተሞላ የማያድን "ወንጌል" ነው ፤ እርሱም ሀሰተኛው ወንጌል ነው።

# አንዳንዶች በእውነተኛው ወንጌል፣ በስብከት ሞኝነት ሳያምኑና ሳይለወጡ ይጠፉ ዘንድ፣ ይህም ንጹህ ወንጌል ለወደቀው አዕምሮአቸው የማይመጥንና ሊቀበሉት የማይችሉት ስለሚሆንባቸው ሊደገፉት የማይፈልጉት ወንጌል ሲሆን፤

# ሌሎች ደግሞ በስጋቸው በመታመን፣ የህግን ሥራ በመፈጸም፣ እንደ መገረዝ ያሉ ልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ የሥጋ ሥርዓቶችን በመጠበቅ ለመጽደቅ ሲሞክሩ የሚያሳዩትን ከክርስቶስ የተለዩና ከጸጋው የወደቁ  መሆናቸውን የሚገልጥ አደገኛ የይሁዲነት ትምክህት ነው።

 "አይሁድ ምልክትን ይፈልጋሉ ግሪኮች ጥበብን ይሻሉ"

ይህ ከጸጋ ተነጥሎ ከእምነቱ የወደቀ ሰው አዙሪት ነው።

ይህ ሀሰተኛ ወንጌል በዘመናችን በርካታ ምሥባካትን ያጣበበው፣ ሰውን ያማከለው፣ ከቁሳቁስ የማይዘለው፣ ገበያ ተኮር የሆነውና ከመስቀሉ ተለይቶ ወደ ክርስቶስ የማይጠጋው፣ እኔ እኔ የሚል የሰብዓዊ ክብርና ዝና እንቶ ፈንቶ ነው።

እርሱም የክርስቶስን ትምህርት ላጣጣሙ ሰዎች እጅ እጅ የሚላቸውና የማይመጥናቸው አጉል ትምህርት ነው።

ከእነርሱም ገሚሶቹ ህግን ጠብቀን እንጸድቃለን ሲሉ፣ የተቀሩት ደግሞ ትንግርትንና ምልክትን ተከትለው ሥሜታዊ በሆኑ ንቅናቄዎች የተወሰዱ፣ በሞቱና ባልሞቱ ሰዎች ላይ እምነታቸውን ያሳረፉ፣ እዚህም ሰፈር እዚያም ሰፈር ያሉ ኃይማኖተኞች ናቸው።

የተቀሩትም በእምነትና በጸጋ የመለወጥ ምንነት ሳይገባቸው በሰው ስጋዊ ጥበብ እየተመኩ እግዚአብሔርንና የማዳን ስራውን በራሳቸው እውቀት፣ ርዕዮትና ፍልስፍናቸው ልክ መትረውና ወስነው አስቀድደው ያሰፉ 'ጠቢባን' ተብዬዎች ናቸው።

በተገለጠው የመስቀሉ ቃልና ትርክት ላይ ሳይሆን ባልተገለጠውና በተሰወረው፣ በማይታየውና ሊታይ በማይቻለው እግዚአብሔር በሰወረው ነገር ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሰው ወንጌል አማኝም ሆነ ወንጌላዊ ለመባል አይበቃም። ይህ ሰው በወንጌል ላይ እየተፈላሰፈና እየተራቀቀ በከንቱም እየሰበከና  ሰዎችን እያስገረመ ሊሆን ይችላል፤ ዳሩ ግን የስብከቱ ይዘት "ሌላ ወንጌል" እንጂ "በስብከት ሞኝነት" የተገለጠው የክርስቶስ የመስቀሉ ወንጌል አይደለም፤ ስራውም ከክርስቶስና ከመስቀሉ የተነጠለ ሌላ ጥንቆላና ድንቆላ እንጂ የእግዚአብሔር ስራ አይደለም።

"እኛ ግን የተሰቀለውን የክርስቶስን እንሰብካለን"

ማርቲን ሉተር ሥነ መለኮታዊ ስብከትን፦ 'የመስቀል' እና 'የክብር' በማለት ለሁለት ከፍሎ ልዩነታቸውን እና በመካከላቸው ያለውን ከፍተኛ ተቃርኖ ያስተምራል።

# አንዱና የእግዚአብሔር ያልሆነው የተጭበረበረው ወንጌል ፍልስፍናን ማዕከል ያደረገውና አመክንዮአዊነትን የሚደገፈው በማየት ላይ ያረፈው ኃይማኖታዊ ልምምድ ሲሆን፣

# እውነተኛውና የእግዚአብሔር የሆነው ወንጌል ደግሞ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ለማዳን የሆነው የተሰቀለው የገሊላው ሰው ታሪክ ነው።

 በወንጌል የሚታየው እና የተገለጠው የእግዚአብሔር መገለጥ የምንለው በክርስቶስ መከራና በመስቀሉ በኩል ተሸሽጎ የታየውን፣ የምህረቱንና የፍቅሩን ገጽታ ነው።

 ሰውን ሊያድን የሚችለው የዚህ ምስኪን ሰው የመስቀል ላይ ታሪክ ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ የሰው ድጋፍ "ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፣ ንፋስንም እንደመከተል" ብቻ ነው።

ዘጸ 33፥ 18 ጀምሮ ሙሴ፦ "እባክህ ክብርህን አሳየኝ" ባለ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሲመልስለት "እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምረዋለሁ...። ደግሞም ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም ....ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም" ብሎታል።

በሰንጣቃው አለት በክርስቶስ የታወቀልን መልካምነቱ፣ የተገለጠው ስሙ፣ ይቅርታው፣ ምህረቱና ማዳኑ ካልሆነ በቀር የእግዚአብሔር መለኮታዊ ግርማው ቢገለጥ ሰውን ያስደነግጠዋል፣ ያጠፋዋልም። ማንምም ቢሆን፣ ሱራፌልና ኪሩቤልም እንኳ፣ በዚህ መለኮታዊ ግርማ ፊት መቆም አይችሉም።

በዚያ አለት ተሸሽጎ ካልሆነ በቀር፣ ደግሞም የእግዚአብሔርን ጀርባውን እንጂ ፊቱን አይቶ ማንም አይድንም። የሚያድነን መገለጥ በእግዚአብሔር ጀርባ የተወከለው የክርስቶስ መከራው፣ ትህትናው እንጂ  'አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነው' ተብሎ እንደተጻፈ በግርማው ፊትማ ማን ሊቆም ይቻለዋል?

እግዚአብሔር የማይታይ የአምላክነት ዘላለማዊ ኃይል አለው። "የማይታየው ባህርዩ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ" ነው። እርሱም ሊታይ የማይቻለው የእግዚአብሔር  ፊት ነው።

የሰው ልጅ ያንን አይቶ በህይወት አይኖርም። የትኛውም ሰብዓዊ ብቃት፣ የህግ ሥራም ሆነ ኃይማኖታዊ ልምምድ ፣ ስጋዊ ጥበብም ሆነ ልዩ ልዩ ትንግርቶችና ምልክቶች ሰውን በእግዚአብሔር ፊት ከቶም አያቀርቡትም።

ነብዩ ኢሳይያስም፦
 "ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል፣ ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ?"
ብሎ ይጠይቅና፣ የጽድቅና የቅድስና መስፈርቱን፣ ከኃጢአትም ነጻ ሆኖ የመገኘት መመዘኛውን ዘርዝሮ ይነግረናል (ኢሳ 33: 14-15)።

ሰው ደግሞ ምንም ያህል በራሱ ቢጣጣር ከእግዚአብሔር ጋር ሊያኖረው በሚያስችለው ብቃት፣ ፍጹም በሚባል ደረጃና ልክ፣ በቅድስናውና በንጽህናውም መጠን የእግዚአብሔርንም ልብ ሊያረካ በሚያስችለው መጠን ራሱን ሊያነጻ ከቶም አይችልም።

ስለዚህም ሰው የገዛ ራሱን አሳፋሪ ጽድቅ ይዞ በእግዚአብሔር ጽድቅ ፊት ሲቀርብ የሚቀርለት ፍርሃት፣ ቅጥቃጤና ሽብር ብቻ ነው። ይልቁን ግን ክርስቶስን በመስቀል ላይ ሲሰቃይ፣ በድካምም ሲሞት  በእምነት ለሚያዩ ጽድቅም፣ ቅድሥናም፣ ቤዛነትም፣ መዳንም  አለላቸው።

እግዚአብሔርም ለሰው ያዘጋጀው ሰውን የሚያድን አስገራሚ መገለጥ ከሁሉ በፊት፦

 ፨ክርስቶስ በቤተ መንግስት ሳይሆን ክርስቶስ በበረት ውስጥ፣

፨ክርስቶስ በፈረስ ላይ ሳይሆን ክርስቶስ የዋህና ትሁት ሆኖ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ፣

፨ክርስቶስ በዙፋን ላይ ሳይሆን ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሆኑ ነው።

#በመስቀሉ ታሪክ አይኑ ያልበራለት ሰው በግርማው ብርሃን ይታወራል እንጂ መቼም ብርሃንን አያይም።

#ለንስሃ በሚሆን ቀላል እምነት በክርስቶስ ትህትናና በየዋህነቱ ፊት  የገዛ ራሱን ትምክህት ጥሎ ያልተንበረከከና ወድቆ ያልሰገደ ሰው በግርማው ፊት ይቀልጣል እንጂ ህይወትን አያይም።

ዘላለማዊ ጽድቅ ለኃጢአተኞች  ሞልቶም የተትረፈረፈውና፣ የፈሰሰው ከክርስቶስ መከራና ከሞቱ መስቀል ነው። በመስቀል ትይዩ የሚያለቅሱ ብቻ ከፈሰሰው የሕይወትና የመጽናናት ምንጭ ዘላለማዊ ደስታን ይጠጣሉ።

 ከዚህ ውጭ ያለውና ከእምነት የተለየው ሥጋዊ አቀራረብ ሁሉ ሰውን በትዕቢት ኮርቻ እያፈናጠጠ በኩራት ሰረገላ ላይ አሳፍሮ ወደ ጥፋት ያደርሰዋል እንጂ ከቶ አያድነውም።

ምንም ቢሆን የሰው የጽድቅ ሙከራ በቅዱሱ አምላክ ፊት የመርገም ጨርቅ ሆኖ ሰውን ያሳፍረዋል፣ ያሸማቅቀዋል ያፈርሰዋልም እንጂ ወደ ሕይወት አያደርሰውም።

መጽሐፉም ደግሞ፦

 "ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የሕግን ሥራ በመስራት አይጸድቅም" ሲል የሥጋን ትምክህት ሽሮ እርግጡን ይነግረናል።

እንግዲህ ሞትና ኩነኔ እንደሚገባቸው ኃጢአተኞች በእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ አንጻር በምንቀርብበት ጊዜ በእርሱ በተሰቀለው ክርስቶስ የተሰጠን የምህረት ተስፋ በእምነት ይረዳናል።

በራሳችን ሥራ በመታመን ሳይሆን በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ባቀረበው ሊቀካህናት-ወመስዋዕት በሆነው በክርስቶስና በመስቀሉ ደም በኩል ባለን ድፍረት ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ተጋብዘናል!!

እንግዲህ ከኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱም እንደተሰቀለ ከማወቅ በቀር ሌላ ዕውቀት፣ ደግሞም ከመስቀሉ ኢየሱስና ከኢየሱስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም ከእኔ ይራቅ! አሜን!!

'እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር' እንደሚባለው፣ ክርስቶስንና መስቀሉን ሰብከን ማደር አይደለም ምነው ሲመሽ ወይም ሲነጋ ብንሞት!

እንደወንጌል አማኝም ሆነ እንደወንጌል ሰባኪ ክብራችን ይህ ነበር፤ የዘመናችን ትውልድና 'ከዋክብት' የሆኑ ኮሜድያን ወከያንያን ሰባኪዎቹ ግን መልእክታቸውን ጥለውና "ሳር በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን እንደለወጡ" የእስራኤል ልጆች አገልግሎታቸውንና መልእክታቸውን ለውጠው ሰባቂዎች ሆነውብናል።

ዛሬ ንስሃ የሚያስፈልገው ከሁሉ በፊት ለእኛ ለሰባክያኑ ነው።  ማንንም ወደንስሃ የማያደርስ በሰው ጥበብና በስጋዊ ትምክህት በተሞላ ኃይማኖታዊ በሆነና ሰዎችን ለማስገረም፣ ገበያ ለመሰብሰብ ሲባል በተሰራ በገለሞተ አገልግሎትና በተለወጠ ወንጌል የቆሙ ሁሉ ከባሰው ፍርድ በፊት ንስሃ እንዲገቡ ያስፈልጋል።

የህንን የንስሃ ጥሪ እምቢ የሚሉና ገልሙተው ህዝብን የሚያስገለሙቱ ግን የእግዚአብሔር ፍርድ ሲመጣ እርቃናቸውን ይቆማሉ። ያኔ ወየው ለእነርሱ፣ አንዳንዶቹ በገንዘብ ቅሌት ሌሎቹም በሰው ሚስት ላይ ይያዛሉ። ይህንንም እያየን ነው። እነዚህም በውሸተኞች ግብዝነት የሚሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት የሚያድምጡና የሚያስደምጡ ካፉ ሰራተኞችና ጨካኞች ተኩላዎች፣ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ፣ ሐዋርያትም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉ፣ ስምና ከብር ለራሳቸው ያከማቹ ሃሰተኛ ነብያትና አሳሳች መምህራን ናቸው።

በጭብጨባ ብዛት የሰከሩትን የመድረክ ላይ ደፋሮችን የሚያበረቱ፣ የሚያድነውን ንጹህ መልእክት የመስቀሉን ቃል ንቀው እንደሚያስጠነቁል አህዛብ ትንግርትና ምልክትን የሚናፍቁ፣ 'ማን መጥቶ ባሳሳተን' እንደሚሉ ሁሉ እየተማሩ እውነትን ወደማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትና የማይፈልጉ፣ ምንም የማይጠይቁ፣ ሁሉን እንደወረደ የሚቀበሉ ወቅተኞችና ወረተኞች የሆኑ ደርሶ ተመላሾች፣  አጨብጫቢና አዳማቂ ተከታዮቻቸውንም ቢሆን እግዚአብሔር ገንዘባቸውን ለሚበሉ፣ ሕይወታቸውን ለሚያራቁቱ ገበያ ለሚሰሩባቸውና ለማይራሩላቸው ጨካኝ ተኩላዎች አሳልፎ ይሰጣቸዋል

የዘመናችን ምስባክና ሚድያ ሁሉ የተዘረፈ ገንዘብ ይዘው ባልተለወጡበት 'ወንጌል' እንደቁራ በሚጮሁ፣ ከዙረት ትርክታቸው በቀር የወንጌሉ ቃል ከመልዕክታቸው በማይገኝባቸው ዝና ናፋቂዎች፣ አካሄዳቸውንና ምስክርነታቸውን ሳይሆን መልካቸውን ባሳመሩ፣ ገጽታቸውን በሚገነቡ፣ ምልክት ናፋቂዎችና ስለራሳቸው ተናግረው በማይረኩ እኔ ባይ ትንግርት ፈላጊ ጠንቋዮች የተጨናነቀ ቢሆንም፣ በሰው እውቀትና በሥጋዊ ጥበብ በሚሄዱ ትምክህተኞች፣ ሌሎችንም በሚንቁ ኃይማኖተኞችና ሊማሩ በማይወዱ ልክ ነን ባዮች የተሞላ ቢሆንም፣ እኛ ግን "በወንጌል አላፍርም" ተብሎ እንደተጻፈ፣ አሁንም ዛሬም "የተሰቀለውን  ክርስቶስን እንስብካለን"። ከዚህ ውጪ ትምክህት የተለየም ስብከት የለንም።

     እኛ ግን የሞተልንን፣
     በደሙም የተቤዠንን፣
     አዳኝነቱን ንጉስነቱን፣
     ለፍጥረት ሁሉ እንሰብካለን!
     አሜን እንሰብካለን!!

Wednesday, February 11, 2015

እጅግ የላቀው የእግዚአብሔር መገለጥ፤
ትምህርተ ክርስቶስ
መግቢያ፡- እኛ ክርስቲያኖች ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው የሆነውን አምላካችንን የናዝሬቱን ኢየሱስን የምናመልክ ነን፡፡ ጌታን ኢየሱስን ማወቅ ደግሞ በክርስትና ሕይወት ቀዳሚውና የመጀመሪያው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ስለዚህ የላቀ የእግዚአብሔር መገለጥ በስፋት ያስተምራል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ዋና ዋና ትምህርቶች ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊ ማንነትና ሰብዓዊ ማንነት በተመለከተ የሚሰጥ ትምህርት ማለትም ሚስጥረ ክርስቶስ በታሪክ ሁሉ ውስጥ በርካታ ክርክሮች ሲያስተናግድ የነበረ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ርዕስ ካለው አስፈላጊነትና ካስተናገዳቸው ልዩ ልዩ የአመለካከት ውዝግቦች አንጻር በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመዳሰስ የተሞከረው የምዕመናንን መንፈሳዊ መረዳት ለማሳደግ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የታመነበትን ጥቂቱን ብቻ ነው፡፡ ጽሑፉ  በዮሐንስ 1.14 ‹ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።›  በሚለው ቃል ላይ የተመሰረተ ሲሆን “እጅግ የላቀው የእግዚአብሔር መገለጥ” በተሰኘ ርዕስ እንመለከተዋለን፤ ይህ ጥቅስ በሌላ አማራጭ ትርጉም ‹ክርስቶስም በዚህ በምድር ከእኛ ጋር ሊኖር አፍቃሪ የሆነ ይቅርታንና እውነትን ተሞልቶ ሰው ሆነ› በሚል ተተርጉሞአል፡፡ ጽሑፉም ሌሎች በርካታ ቅዱሳት መጻሕፍት የንባብ ክፍሎችን በማካተት በስምንት ተከታታይ የትምህርት ክፍሎች የሚሸፈን ነው፡፡ የጽሑፉም አቀራረብ ሥነ መለኮታዊ ዘገባ (Information) መስጠት ሳይሆን ትምሕርተ ክርስቶስ በያዘው ሥነ መለኮት ውስጥ ከህይወታችን ጋር ሊዛመድ የሚገባውን እውነት ማመልከት ነው፡፡ እግዚአብሔር የቃሉን ደጃፍ ይክፈትልን!! አሜን፡፡ 
በጽሑፉ የምንመለከታቸው ስምንት ክፍሎች የሚከተለውን ይመስላሉ፡-
ክፍል 1 ሎጎስ
ክፍል 2 ሀ. ቃልም ሥጋ ሆነ
ክፍል 3 ለ. አምላክ ሰው መሆኑ
ክፍል 4 ሐ. በመለኮቱና በትስብዕቱ መካከል ያለው ግንኙነት
ክፍል 5 ክብሩ
ክፍል 6 የባሕርይ ልጅ
ክፍል 7 የመለኮት መገለጫ ባህርይ
ክፍል 8 የእግዚአብሔር መገለጥ

                                                                                  አዘጋጅ ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ››
                   ክፍል አንድ ሎጎስ
‹‹ቃሉ››
ዮሐንስ 1.14 በቅዱሳት መጻሕፍት ካሉ ጥቅሶች ሁሉ ያለ ጥርጥር እጅግ አስገራሚው ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ከአንድ ጊዜ በላይ ደጋግመን ልንመለከተው የሚያስፈልገንን እጅግ የከበረ አስገራሚ የእውነት መዝገብ ታጭቆበታል፡፡ ለመነሻ እንዲሆነን አንዱን ቃል መዘን እንመልከት ‹‹ቃልም …››
1. ‹ቃሉ› (ቃልን መረዳት)
ስለዚህ ጉዳይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ቁጥር 1 የሚለውን በጥንቃቄ ካልተረዳን ቁ 14 ምን እንደሚል በትክክል መረዳት አለመቻሉ ነው፡፡ በተለይም ‹ቃል› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ አስፈላጊነት መረዳት አለብን፡፡ ቃል በቀጥታ ክርስቶስ ማለት ነው፣ እርሱም የእግዚአብሔር ጥበብና ሃይል ነው፣ እግዚአብሔር ለሰው ያለው የግሉ አካላዊ መታየትና መገለጥ ነው፡፡

ከቁጥር 2-13 ለመብራራት እንደተሞከረው የሐዋርያው ሃሳብ ግልጽ ነው፤ ‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ (ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር /አመት/) ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ….ቃልም ሥጋ ሆነ….››
አስቀድመን የዮሐንስ ወንጌል ሲጻፍ በምን ዓላማ እንደተጻፈ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በዮሐንስ 20.30-31 ‹ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል› በሚለው መሰረት አይሁድ የሆኑትንና ያልሆኑትን ሁለቱንም ወገኖች በጽሁፎቹ ወደ እምነት መምራት ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈበት ዓላማ ነው፡፡ አይሁድን በተመለከተ በእርግጥም ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲሁ ክርስቶስ መሆኑን እንዲያምኑ አይሁድ ያልሆኑትን በተመለከተ ደግሞ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እና እግዚአብሔር ወልድ መሆኑን እንዲረዱ ነው፡፡
ሐዋርያው ስለ ኢየሱስ መጻፍ ሲጀምር ዋናውን ሃሳብ እየነካ ለጽሑፉ መግቢያ በሚሰጥበት ጊዜ፣ በዚያው መጠን ግዙፍ ከሆኑ እውነቶች ጋር ይገናኛል፡፡  በመንፈስ ቅዱስ ከተመራ ጥንቃቄ ጋር ‹ክርስቶስ› እና ወይም ‹የእግዚአብሄር ልጅ› የሚሉት ቃላት ለአንባቢዎቹ ከበድ ያሉ ሃሳቦች በመሆናቸው መግቢያው እነዚህን ቃላት ወይም ሐረጎች እንዲያካትት አላደረገም፡፡ ሆኖም ጽሑፉን እየገፋ ሲሄድ ከነዚያ ቃላትና ሃሳቦች መካከል አንዳቸውንም ሊተዋቸው ምንም ፍላጎት አልነበረውም፡፡

አይሁድ የሚጠባበቁት፡- አይሁድ ዮሐንስ “ቃል” እያለ ስለ ክርስቶስ መጻፉን ሲያውቁ በእርግጥም ጆሮአቸውን ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን እነርሱ መሲሁን የሚጠብቁት ከሆነ ምድራዊ ተልእኮ ጋር ከተያያዘ የፖለቲካ ዓላማ ጋር ነበር፡፡ እንግዲህ ዮሐንስ የእነርሱን ጆሮ መግኘቱ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ኢየሱስ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ማወቅ ስላለባቸው ነው፡፡
የአህዛብ ግምት፡- ለአህዛብም ቢሆን ‹የእግዚአብሔር ልጅ› ስለመባሉ  በሚያነቡበት ጊዜ ከአማልክት መካከል አንዱ ከአንዲት ምድራዊት ሴት ጋር ባደረገው ግንኙነት ስለ ተወለደ አንድ ሰው ሊገምቱና ሊስቡ ይችሉ ይሆናል - ይህ አይነቱ አስተሳሰብ በግሪካውያን ተረት  የተለመደ አህዛባዊ አስተሳሰብ ነው፡፡
የዮሐንስ ሸክም፡- ዮሐንስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት እርሱ የሚጽፍለት “ቃል” የተባለው ሰው ፈጽሞ የተለየና የከበረ መሆኑን አንባቢዎቹ እርግጠኛ ሆነው እንዲረዱ ነው - እርሱ ከብዙዎች አንዱ አይደለም፣ ሌላ መሲህም አይደለም፣ ማንኛውም ክርስቶስ አይደለም፤ በእርግጥም ሌላ የአህዛብ ጣኦት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ጌታ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማብራራት ከመጀመሩ በፊት ስለ እርሱ የሚጽፍለት “ቃል” የተባለው ይህ ሰው በእውነትና በሙላት ራሱ እግዚአብሔር የመሆኑን ነጥብ በግልጽና በማያሻማ መንገድ እንቅጩን የሚናገረው፡፡
2. የተሳሳተ ግንዛቤን ለማስወገድ የተመረጠ መጠሪያ ‹ቃል›
የሆነ ሆኖ የትኛውንም የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስወገድ በመጀመርያ ዋነኛ ማንነቱን በሚገልጥ ስያሜ ይጠራዋል፤ ‹ክርስቶስ› ወይም ‹የእግዚአብሔር ልጅ› ብሎ ሳይሆን በሌላ አይነተኛ ስም ይገልጠዋል፡፡ ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የመረጠው ተገቢ የሆነ ስያሜ ‹ቃል› (በግሪኩ ‹ሎጎስ›) የሚል ነው፡፡
ቃል ለአይሁድ፣ ቃል ለአህዛብ፡- /በአመት የጥናት መግለጫ ‹‹ግሪኮች ‹ቃል› የተሰኘውን የሓሳብ መግለጫ ለተነገረው ፣ ለተሰማው ብቻ ሳይሆን፣ ላልተነገረው ላልተሰማውና ገና በአእምሮ ውስጥ ላለው ሓሳብ ጭምር ይጠቀሙበታል፡፡ ፍጥረተ አለምን በተመለከተ ሲጠቀሙበት ግን የፍጥረትን ሥርዓት የሚመራውን ሕግ በማሰብ ነው፡፡ አይሁድ ግን ‹ቃል› የሚለውን የሓሳብ መግለጫ የሚጠቀሙበት እግዚአብሔርን በተመለከተ ነው፡፡ ስለዚህም ዮሐንስ የተጠቀመው አይሁድም ሆኑ አሕዛብ በሚረዱት ቃል ነው፣››ይላል፡፡/ ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ይህ ቃል ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ ከሌሎች ቃላት ሁሉ ይልቅ ‹ሎጎስ› ለሁለቱም አይነት አንባቢዎች አዕምሮ ሰፊ ሃሳብን አጭቆ ይዞአል፡፡
ቃል በግሪክ ፍልስፍና ውስጥ፡- በአረማውያን ዘንድ “ሎጎስ” በሚለው ቃል የሚገለጠው ጽንሰ ሃሳብ በእጅጉ ተለመደና የታወቀ ነው፡፡ ግሪካዊው ፈላስፋ ሂራክሊቱስ (600 ቅክ) ሎጎስ የአጥናፍ አለም ነፍስ ነው ብሎ ያስባል- ይኸውም ሁሉም ነገር የተሰራበትና የሆነበት፣ ሁሉንም ነገር ጠብቆ የያዘ፣ እንዲሁም የመላውን ዩኒቨርስ ሚዛን የሚጠብቅ ፈጣሪ ነው ማለት ነው፡፡
የጠቢባኑ ግንዛቤ፡- በዘመኑ ያሉ ጠቢባን ሃሳቡን ሰፋ አድርገው ያዩታል፡፡ ለእነርሱም ሎጎስ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ የሚገኝ (omnipresent) ጥበብ ሲሆን በእርሱም ሁሉ እንደተፈጠረና እንደሚመራ ያስባሉ፡፡
አረማውያን ሎጎስን ከታላቁ አምላክ ጋር ያያይዙታል፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ የእርሱ የቃል ምርጫ ለአሕዛባዊ አንባቢዎቹ የሚያረጋግጥላቸው እየጻፈ ያለው ስለ ሁሉን ቻይ እና ለሁሉ ስለሚበቃ፣ የሁሉ ጀማሪ ስለሆነ፣ የሁሉ መሰረትና ምክንያት በመሆን ለራሱ ግን የመሆን ምክንያት ስለሌለው፣ በራሱ የሆነ ስለሆነው ማንነት እንደሆነ ነው፡፡
አይሁድም ፣ ‹ሎጎስ› የሚለው ቃል ከያዘው ጽንሰ ሃሳብ ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡ ለእነርሱም የዮሐንስ የመግቢያ ቃላት ማለትም ቁጥር 1 የዘፍጥረትን ‹በመጀመሪያ…› የሚለውን ቃል የሚያስታውሳቸው ነው፡፡ በእርግጥም “ሎጎስ”፣ ወይም “ቃል” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ እግዚአብሔር አለምን እንዴት እንደ ፈጠረ ያስታውሳቸዋል፣ ‹‹እግዚአብሔርም አለ›› የሚለው መግለጫ በዘፍጥረት 1 ላይ ዘጠኝ ጊዜ ተጠቅሶአል፡፡  “ሎጎስ” ለአይሁድ በእውነትም የእግዚአብሄር የሆነ “ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ቃል” ትርጉም ነው፡፡
የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃ፡- በመዝሙር 33. 6፣9 ‹‹በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ…..እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።›› የሚል እናነባለን፡፡ በኢሳያስ 55. 11 ‹‹ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።›› ይላል፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር አንድ ነገር እንደሚያደርግና እንደሚሆን እነዚህ ጥቅሶች ግልጽ ያደርጉልናል፡፡ አይሁድ ሎጎስ የተሰኘውን ቃል ከአምላካዊ ተግባር ጋር እንደሚያያይዙት በዚህ ማየት ይቻላል፡፡
ከዚህም በላይ አይሁድ ‹ያህዌ› የተሰኘውን የእግዚአብሔርን ሥም ሲያነሱ፣ ስለ እርሱም በሚናገሩበት ጊዜ፣ ስሙን መጥራት እርሱን እንደ አለማክበር ስለሚቆጥሩ በሌሎች አማራጭ ቃላትና መጠሪያዎች እርሱን መጥራት ይመርጣሉ፡፡ እንደ ‹ቅዱሱ›፣ ‹ስሙ›፣ ወይም ‹ቃል› ያሉትን ይጠቀማሉ፡፡ ስለዚህም  “ቃል” ለአይሁድ ሥነ መለኮት “ያህዌ” ነው፡፡ ዮሐንስ ‹ሎጎስ› የሚለውን ቃል በመጠቀሙ  ለአይሁድ አንባቢያኑ የሚነግራቸው “እኔ የምጽፍለት እርሱ ሃያሉ እና ቅዱሱ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነው”፣ እያለ ነው፡፡
3. የቃሉ መወድስ
ከቁጥር 14 በፊት ባሉት ቁጥሮች ውስጥ ዮሐንስ ስለ ቃሉ የተነገሩ  ወደ 8 የሚደርሱ የመወድስ ዓረፍተ ነገሮችን አስቀምጦአል፣ እያንዳንዳቸውም ለማንኛውም የአይሁድና የግሪክ ሰዎች አስተሳሰብ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው፡፡
1ኛ/ ‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ› (ቁ 1) በሌላ አባባል፣ ጊዜና ያለው ነገር ሁሉ ወደ መኖር ሲመጣ፣ ቃል ቀድሞውኑ እየኖረ ነበር፡፡ ከዘላለም ጀምሮ እርሱ በዚያ ነበር፡፡ ማንኛውም ነገር ሕልውና ከማግኘቱ በፊት ቃል ነበር፡፡

2ኛ/ ‹ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ›(ቁ 1) ቃሉ ሁልጊዜ ከእግዚአብሄር ጋር ነበረ፡፡ ከዘላለም ሁሉ በፊት በመካከላቸው (በእግዚአብሔርና በቃሉ መካከል) የማይከፈል አንድነት ነበራቸው፡፡

3ኛ/ ‹ቃልም እግዚአብሔር ነበረ›(ቁ 1) አዎ ቃሉ ከእግዚአብሔር ተለይቶ በራሱ ማንነት ይታወቃል፣ ነገር ግን የተፈጠረ ነገር (ፍጡር) አይደለም፡፡ በእርግጥ ከዘላለም በፊት እግዚአብሔር ሆኖ ኖሮአል፡፡ ዮሐንስ እዚህ ላይ በሥላሴዎች መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ይነካል፡፡ ነገር ግን ማናቸውም የማያምኑ የሆኑ አንባቢዎች ይህንን አይረዱትም፡፡

4ኛ/ ‹ሁሉ በእርሱ ሆነ›/ ‹ዓለሙም በእርሱ ሆነ›(ቁ 3ና10) እርሱ የዚህ አጥናፍ አለም (universe) ፈጣሪ ነው፣ የሚለው ዓረፍተ ነገር ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች የሚያስቸግራቸው አይደለም፡፡

5ኛ/ ‹በእርሱ ሕይወት ነበረች› (ቁ4) ሕይወት ሰጪ እና የሁሉ ነገር ምንጭ ከሆነው ቃል ህይወትን ያልተቀበለ ሕያው ፍጡር በፍጥረተ ዓለም ውስጥ የለም፡፡ ፍጥረት ሁሉ ሕያው የሆነው በእርሱ ሕይወት ነው፡፡

6ኛ/ ‹ሕይወትም የሰው ብርሐን ነበረች/ ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሐን…›(ቁ4፣9) ከእርሱ የተገኘች ሕይወት ለሰው ልጅ ሁሉ የምታበራ ብርሃን ናት፡፡ ዮሐንስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ቃሉ የእግዚአብሔር መገለጠ/ እግዚአብሔርን የሚገልጠው የመሆኑን እውነታ ነው፡፡ ነገር ግን አይሁድ በምሳሌ ምዕራፍ 8 ብርሃን ቃሉን በአካላዊ ማንነቱ እንዳለ ጥበብ ሲመለከቱት አሕዛብ ግን ዓረፍተ ነገሩን በፍልስፍናቸው የተረጉሙታል፡፡

7ኛ/ ‹የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም› (ቁ 11) እዚህ ላይ አንባቢዎቹ ይስማማሉ፣ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ ፈጽሞ የማያስተውሉና የማያስቡ ሞኞች አሉ ይላሉ፡፡

8ኛ/ ያም ሆኖ የሚቀበሉት ደግሞ አሉ ‹ለተቀበሉት…›(ቁ 12) ለሚያምኑበት፣ ለሚቀበሉትና ለሚያመልኩት አንባቢዎቹ በዚህ እንኳን ደስ ያላችሁ ሊባሉና በዚህ ደስ ሊላቸው ገባቸዋል፡፡

በእርግጥም የመጽሐፉን ዋነኛ ገጸ ባህርይ ለአንባቢዎቹ እንዲህ ባለ ተስማሚና ተቀባይነት ባለው አቀራረብ መግቢያ መስጠት የቻለ ጸሐፊ የለም፡፡
ማጠቃለያ
በአዲስ ኪዳን ውስጥ በክርስቶስ መለኮትነት ላይ የተሰጠውን ጠንካራ ትምሀርት እንዳንስተው መጠንቀቅ አለብን፡፡

ስለ እርሱን በተመለከተ  ከገጠሪቱ ናዝሬት እንደ ተነሳ ተራ እንደሆነ አንድ ድንቅ ሰው ማሰብ ሊቀል ይችል ይሆናል፣ በኖረው የፍቅርና ሌሎችን የመንከባከብ ምሳሌ ድንቅ የሆኑ የሕይወት ምሳሌዎችን እና ተሞክሮዎችን እንደተወልን አንድ አስገራሚ ሰው እናየው ይሆናል፡፡ አዎ በእርግጥም ቃሉ በታሪካችን ውስጥ ገብቶ ሥጋ ሆኖአል፣ እኛን መስሎአል፣ ደግሞም ፍጹም ሰው ነበር እስከ አሁንም ድረስ ነው፣ ነገር ግን ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት ከሰጠው ከዚህ ጠንካራ አጽንዖት ውጭ ወንጌላዊ የሆነው አስተምህሮተ ክርስቶሳችን በቀላሉ ሰውን ወደ አማከለ ተራ ደረጃ ማለትም  ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው መገለጥ ጋር ፈጽሞ ወደማይታረቅበት ደረጃ ወርዳል፡፡
በመካከለኛው ዘመን ሥነ ጥበብ በተሰሩ፣ ስሜትን የሚነካ የከሳና የገረጣ ፊት ባላቸው ወይም በእጅጉ ተውበው በደመቁ ኃይማኖታዊ በሆኑ ኢየሱሳዊ ሥዕላ ሥዕሎች ላይ የተመሰረተ የዛሬ ስብከት ማንንም ሊያድን አይችልም፡፡ በጣም በእርግጠኝነት መናገር እንደሚቻለው እንዲህ ያለው ሰው ሰራሽ የሆነ “ክርስቶስ” ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉም ሆነ በራዕዩ የሚጽፍለት የነገስታት ንጉስና የጌታዎች ጌታ አይደለም፡፡
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ያቀረቡልን ኢየሱስ እውነተኛ አምላክ፣ ደግሞም ሕያው ሰው መሆኑን በደንብ ማስታወስ አለብን፡፡ ስለዚህም ቃል የተባለው እርሱ የዮሐንስ አህዛባዊ አንባቢዎች ከሚመስላቸው አካል ካልሆነ አንድ መርህ ወይም ሃይል በላይ ያለ በራሱ የሚኖር ማንነት ነው፡፡
ሉቃስም ስለ ሐዋርያቱ ሲናገር ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት (ሉቃ 1.2) በማለት ‹ቃሉ› የሚለውን መግለጫ ይጠቀማል›፣ ፡፡ የሚናገረውው ስለ ጌታ ኢየሱስ ነው ወይንስ ሰለ ወንጌሉ? አንዳንድ ተርጓሚዎች ወንጌሉ ነው ሲሉ ከሁለተኛው ሃሳብ ጋር ቃሉን ለማዛመድ ሞክረዋል፣ ይሁንና ሉቃስ ሐዋርያቱን በተመለከተ ሲናገር ቃሉን ‹በዓይን ያዩት› ናቸው ይላል፣ የሚያመለክተውም ጌታ ኢየሱስን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቃሉ ‹አገልጋዮች› ብሎ ደግሞ ይጠራቸዋል፣ የኸውም ወንጌሉን ያመለክታል፡፡ ሐዋርያቱ ቃሉን ያዩት የቃሉ አገልጋዮች ናቸው፡፡
በጥንት ቤተከክርስቲያን ይህ አከራካሪ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ለነዚያ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለው እርሱ በማንነቱ በእርግጥም የወንጌሉ የዘት ነበር፡፡
ይህ በትክክል ጳውሎስ ፤‹መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን…› (1ቆሮ 1.22) ብሎ የተናገረለት ጉዳይ ነው፡፡ በገላትያ 3.1 ላይም ‹በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤› ይላል፡፡ስለዚህም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መናገር ማለት ለሐዋርያቱ በእውነትም የስብከታቸውን ይዘት የሚያመለክት ነው፡፡
ዮሐንስ በሚገርም አገላለጽ ይህንን ቃል “የሕይወት ቃል” ሲል ይጠራዋል፣ እርሱንም “ከመጀመሪያው የነበረውን የሰማነው በዓይኖቻችንም ያየነው የተመለከትነው እጆቻችንም የዳሰሱት” ይለዋል ጨምሮም “ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤” ሲል ሐዋርያቱ ከዚያ ቃል ጋር የነበራቸውን ቅርብ ግንኙነት ይመሰክራል፡፡
ከሞት የተነሳውን ሕያው የሆነና የከበረውን ክርስቶስ እያወቀ ያደገ ማንም ሰው ቢሆን፣ ሌላ ማንኛውንም ተራ ነገር ወይም ሌላ ማንንም ቢሆን ፈጽሞ ማወጅና መስበክ አይችልም- እጅግ ያነሰውን የስነ ምግባር መርህ ወይም መልካም ፈቃድን አልያም ደስ የሚል ድምጸት ያላቸውን ጥሩ ጥሩ አዝናኝ አባባሎችን በመስበክና በማወጅ ዘመኑን አያጠፋም፡፡ እንዲህ ላለ ሰብዓዊ ተራ ነገር ሐዋርያቱ ለመሞት አልተዘጋጁም ነበር፣ በእርግጥም እንደ ሰማዕት የሞቱለት ጉዳይ እንዲህ የወረደ ነገር አልነበረም፡፡ እስከሞት ድረስ ሰው ሆኖ በመካከላቸው ከእነርሱ ዘንድ ስላደረው አምላክ ከመናገርና እርሱን ከማምለክ ለአፍታም ቢሆን አላረፉም፡፡ በየዘመናቱ ሁሉ የተሰበከው ደግሞ እንዲሁ ነበር፡፡ አሁንም የሚሰበከው እንዲሁ ነው፡፡ ለዘላለሙም የሚሰበከው እንዲሁ ነው፡፡ አሜን!!

                                                                                 gizachewkr@gmail.com       

ትምህርተ ክርስቶስ መግቢያ እና ክፍል 1