Thursday, October 22, 2015

እውነትና ተግዳሮቱ

እውነትና ተግዳሮቱ
" እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም።" (መጽሐፈ ምሳሌ 23፥ 23)
ብዙዎቻችን በልዩ ለዩ አመለካከቶች የሚቀሰቀስ የትምህርት ንፋስ ወዲያና ወዲህ እያንሳፈፈ የሚወስዳቸውን አይነቶች ሆነናል። በዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች ሁሉ ያለው ማስጠንቀቂያ፦
" እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥"  (ኤፌ 4፥ 14)  የሚል ነው።
ይልቅስ ነቃ ብለን እንደ ቤርያ ሰዎች የምንሰማውን ሁሉ መጠየቅና እርግጠኛውን ነገር በቅዱሳት መጻህፍት ብርሃን መመራመርና መፈተን ይገባናል።
"እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ።"   (ሐዋ 17፥ 11-12)
በእርግጥም በእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ላይ ምናልባት ምቾት እንኳ ባይሰማን "ራሳችንን እየመረመርንና እየፈተንን በእውነትም ምን ያህል እውነትን ፈላጊዎች እንደሆንን ማረጋገጥ ይገባናል።
" በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?" (2ቆሮ13፥ 5)
 "ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤" (1ተሰ 5፥ 21)
አዎን በዙርያችን በሚነፍሰውና ሁሉን ጠራርጎ እንደሚወስድ ጎርፍ በሆኑ የስህተት ትምህርቶች በቀላሉ እንዳንወሰድና እንዳንታለል በእርግጥም እንደቤርያ ሰዎች የመጽሐፉ ሰዎች ልንሆን ያስፈልገናል።
በርካታ ሰዎች ግን እውነትን መያዝ አይችሉበትም። እንዲህ ያሉ ሰዎች ምቾት ፈላጊዎችና ተድላ ፈላጊዎች ብቻ ናቸው። በዘመናችን ባሉ አብያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ዘንድ ይህ ችግር ለብዙዎች አይነተኛ መገለጫ ሆኖአል። በእርግጥም ራሳችንን ሞት በሆነ ነገር እያዝናናን ያለን እንመስላለን። ይህም ለካ የእስራኤል ህዝብ ከመደምሰሳቸውና ወደምርኮ ከመወሰዳቸው በፊት እንደነበሩበት አይነት ያለ ህይወት ነው። ነብዩ ኢሳይያስ በኖረበት ዘመን የነበሩትን ህዝብ እንዴት እንደገለጣቸው ልብ አድርጉ፦
ኢሳ 30፥ 8 "አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘላለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው።"
ኢሳ 30፥ 9 "ዓመፀኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፤"
ኢሳ 30፥ 10 "ባለ ራእዮችን። አትመልከቱ ይላሉ፥ ነቢያትንም። ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥"
ኢሳ 30፥ 11 "ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ ይሉአቸዋል።"
ኢሳ30፥ 12 "ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል። ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና"
ኢሳ 30፥ 13 "ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።"
ኢሳ 30፥ 14 " የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቅቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት ወይም ውኃ ከጕድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም። "
ኢሳይያስ በዘመኑ ስለነበሩ ሰዎች ምን እያለ እንደነበር ይታያችኋልን? ለካህናቶቻቸውና ለአስተማሪዎቻቸው ንጹሁንና ጠንካራውን የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ማስተማር እንዲያቆሙና እንዲተዉ፣ በምትኩ ግን ደስ የሚያሰኙና የሚያጽናኑ፣ ለብ ያሉና የማይጎረብጡ ቃላትን፣  እንዲያመጡላቸው ይነግሩአቸዋል። ጆሮዎቻቸውን እንዲኮረኩርና እንዲያሳክክ ሰለሚፈልጉ፦
" ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።" (2ጢሞ4፥ 3)፣ ተብሎ እንደተጻፈ የየቤተክርስቲያኖቻቸውን ምስባኮች የሚያረካቸውን ቃላት በሚነግሩአቸውና ትንቢትን በሚናገሩላቸው አስደሳችና አዝናኝ ኮሜድያን-ወከያንያን በሆኑ ነብያቶቻቸው አጨናንቀውታል። እነርሱም ጥሪያቸው ማዝናናትና ማስደሰት የሆነ ይመስል አድማጮቻቸውና አድናቂዎቻቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ይነግሩአቸዋል።
እውነት ግን በባህርዩ ሁልጊዜ ይገዳደረናል፣ ያስቸግረናል፣ ምቾትም አይሰጠንም፣ ዝና የለውም፣ ታዋቂም ተፈላጊም አይደለም። ሁልጊዜም እንደዚያው ሆኖ ይኖራል። ኢየሱስም፦
" በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።" (ማቴ 7፥ 13-14)፤ ሲል የተናገረው ለዚህ ነው።
ወደ እውነት የሚያደርሰው መንገድ ጠባብ ዳገታማ እና አስቸጋሪ ነው። ዋጋ ሊከፍሉለት የሚሹ ጥቂቶች ብቻ ናቸው። የሚበዙት ግን ቀላሉን የመውጫ መንገድ እየመረጡ በታዋቂነትና በዝነኝነት መንገድ ይጓዛሉ።
ኢየሱስ ስለዕንቁ ነጋዴው ምሳሌ በተናገረ ጊዜ፦
" ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።" (ማቴ 13፥ 45-46)፤ ሲል በእውነትም እውነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልና ብዙ ተግዳሮት እንዳለበት ማብራርያ ይሰጠናል።
በእርግጥም እውነት ያለ ብዙና ታላቅ ዋጋ በብላሽ አይገኝም። እውነትን ለመግዛት ያለንን ሁሉ አራግፈን ሸጠን ከፍ ያለ ዋጋ መክፈል ይጠበቅብናል። ያንን ዕንቁ ለማግኘት የሚከፈለው ታላቅ ዋጋ ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስ ራስን አሳልፎ ከመስጠት ያነሰ ዋጋ አይደለም።
የሚበዙ ሰዎች ለምን ስህተትን ይከተላሉ? (እንደው ለመሆኑ ስህተትስ አለ ወይ?)
ስህተት ቀላል ነው፣ ደግሞ ይመቻል ፣ አያጨናንቅም፣ አያካብድም፣ አዝናኝና ታዋቂም ነው (ሁሉም ሰው ሊያደርገውም ሊሞክረውም ደግሞ ይችላል) ። ስህተት ምንም ዋጋ አይጠይቀንም ወይንም ምንም ዋጋ አያስከፍለንም፣ ወይንም በአኗኗራችን ላይ ምንም አይነት መስዋእትነት ወይም ቁርጠኝነት ወይም ለውጥ አይጠይቀንም። ስህተት ለማመን፣ ለማስደሰትም ሆነ ለማዝናናት በጣም ቀላል ነው። ምንም አይነት ብርቱ ጥናትም ሆነ በምርምር የታገዘ ብርቱ አሳብ አይፈልግም። ወደ ገደል ጥፋት የሚያደርስ የምቾትና የመብት ብዛት እያስከተለ ለእርድ መንጋ ያጉራል።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን አይነተኛ የጥፋት አደጋ ሲያመለክት፦
" የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።" (2ጴጥ 3፥ 15-16) ብሎአል ።
በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ከማጥናትና እንዴት በአግባቡና በትክክል እንደሚተረጎም ከመማር ይልቅ ጆሮዎቻቸውን ማከክና መኮርኮር ይወዳሉ። ክርስቶስና ሐዋርያቱ ግን 'ምቾት ፈላጊዎችን'  ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመሳብ አንዳች ሙከራ ሲያደርጉ አይታዩም፣ የልቁኑ ግን ይህ ነገር እውነት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትን በየጊዜው ለመመርመር ፍላጎት ያላቸውንና እንደ ቤርያ ሰዎች ያሉ 'እውነት ፈላጊዎችን' ይፈልጉ ነበር።
እኛ የቃሉ አገልጋዮች ጠንካራውንና አስቸጋሪውን እውነት በማስተማራችን፣ ወይም ሰዎችን በእውነት ቃል በመገዳደራችን፣ እውነትን በመግለጣችን እንዱሁም ስህተትን በመንቀፋችንና ተቃውመን በማስተማራችን ምንም አይነት ይቅርታ ማንንም መጠየቅ አያስፈልገንም። የልቁኑ ግን ለታመነው እውነት የሚታመኑ ጥቂት ታማኞችን፣ በእውነት ላይ አብረውን የሚቆሙትንና አስቸጋሪውን የእውነት አቀበታማ መንገድ ለመሄድ የቆረጡ፣ ወደህይወት በሚያደርሰው ጠባቡ በርና በቀጭኑ መንገድ ገብተው ለመሄድ ፍላጎት ያላቸውን ብቻ እንፈልጋለን ።
ስለዚህ እውነት ፈላጊ ማን ነው? እውነትን መፈለግ እንዴት ነው? እውነትን ተራ በሆነ አካዳሚክ አቀራረብ ልንረዳው አንችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስን አብርሆት አጥብቀን በጸሎት መፈለግ አለብን፡፡ አብርሆት ማለት ደግሞ እግዚአብሔር በነዚያ ቅዱሳት መጻህፍት አማካኝነት ራሱን መግለጹ ነው፡፡ አብርሆት ት ጥ ቅ  የተባለ ሦስት ነገሮችን የሚጠይቅ እንደሆነ ተመልክተን እናጠቃልል፡፡
ትህትና (Humility) ›መደገፍ ነው፡፡ አይናችንን ለቅዱሳት መጻህፍት መረዳት እንዲከፍትልን በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ አለብን፡፡
ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።” (መዝ 119÷ 18)
“አለን የምንለው ላይብረሪ እና ጥናት ሁሉ እርሱን በትህትና ከመጠጋታችን ጋር ሲነጻጸር ባዶና ተራ ይሆናል” (ቻርልስ ስፕረጂዮን)
“ትህትና ጸጋን ሁሉ ሲመገብ ትዕቢት ግን ይራባል!” (ሪቻርድ ባክስተር)
ጥንካሬ (Hared Working) ቃሉን በጥልቀት ለመረዳት ጠንክሮ መስራት ይጠበቅብናል
“ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳ 2÷ 1-5)
የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ጊዜና ትጋት ይጠይቃል፡፡ ሥራው ለሰነፍ ሰዎች የሚሆን አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን እና ፈቃዱን ማወቅ ለየቀኑ ኑሯችን ጥንካሬን ይሰጠናል፣ ይኸውም ደግሞ ያለማቋረጥ ቃሉን ከማጥናት የሚመጣ ነው፡፡ በትጋት ውስጥ ለሚቆዩ ሰዎች መረዳቱ በጊዜ ውስጥ ቆይቶ ይመጣል፡፡ ይህንን ታላቅ የእግዚአብሔር መጽሐፍ ለመረዳት እንደ ቤርያ ሰዎች የመጽሐፉ ሰዎች በመሆን ብርቱ ምርመራና ጥረት እያደረጋችሁ ደግማችሁ ደጋግማችሁ አንብቡት፡፡ ለራሳችሁና ለሚያስተምረው ሰው ጸልዩ፡፡
“ተግቶ ማሰብ ሕይወት/ ኑሮ ነው” (ስፕረጂዮን)
“ተግቶ ማሰብ ትግል ነው” (ሲ.ኤስ. ሎቬት)
ቅድስና (Holiness) እግዚአብሔር ራሱን በቃሉ በኩል እንዲገልጽልን የምንጠይቅ ከሆነ በቅድስና መመላለስ አለብን፡፡
“ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።” (ያዕ 1÷ 21)
“ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” (ዕብ 12÷ 14)
“እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።”  1ጴጥሮስ 2÷ 1-3
(የማጠቃለያ የምክር ቃል ከቶማስ ዋትሶን)
1. ለቅዱሳት መጻህፍት ከፍ ያለ ዋጋ ስጥ
"ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።" መዝ 119፥ 7
ከሌሎች መጻህፍት ሁሉ በላይ አስበልጠህ ሀብትህና የተሰወረ መዝገብህ አድርገው።
ማመንና ማድረግ ያለብንን ነገሮች ሁሉ በውስጡ አጭቆ የያዘ ውድ መጽሐፍ ነው።  ጸጋን የሚያጠባንና የሚመግበንም እርሱ ነው። በእውነት ቃል ዳግም የተወለደውና እርሱን እየተመገበ የሚያድገውም ሰው አማኝ ነው።
2. ቃሉን ስታነብ የምርህን ዋጋ ሰጥተህ አንብብ። ስራዬ ብለውና ዋጋ ሰጥተው ከምር ለሚያነቡት ሰዎች ብቻ የህይወት ማጣፈጫ ቅመማቸው ነው። እጅግ ዋጋ ካለው ነገራችንና ከምንወደውም ጉዳያችን ሁሉ ጋር የሚገናኝ ነው።
የዘላለም ሕይወት እና ሞት፣ መንግስተ ሰማያትና ሲዖል፣ የእምነትም ስራ የተሰኙትን፣ በውስጡ ያሉትን ርዕሰ ጉዳዮች ልብ በል። በእውነት የምሩን ዋጋ ሳይሰጣቸው እነዚህን ነገሮች ማንበብ የሚችል ማን ሰው ነው? ሰለዚህ ክቡር በሆነ የእርጋታ መንፈስ እና በተቀናበረ ስርአት  ሆነህ አንብበው።
3. መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ዘዴ ይኑርህ፣ ምናልባትም ለራስህ የምታነብበትን ስርዓት አብጅ። ለማንበብ ስርዓትና ዘዴ ሲኖር ያነበቡትን ለማስታወስና ለማሰላሰል ይቻላል።
4. ቃሉን ለማንበብ በእውነተኛና በቅን ልብ ቅረብ፤
ሀ- የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ለማወቅ በልብ ፈቃደኝነት አንብበው፣ ከውስጡም ያየኸውን ማንኛውም እውነት ለመደበቅ አትፈልግ።
ከቅዱሳት መጻህፍት አንተ የምትፈልገውንና የሚመችህን ብቻ ነጥለህ ልትወስድና ልትመርጥ አትችልም።
ለ- የተሻልክ ሰው ለመሆን እንድትችል አንብበው። ቃሉ የምንቀደስበት መንገድ ነው።
የበለጠ ክርስቶስን እንድትመስል ሊያደርግህ የሚችለውን እውነት እንድታገኝ ወደ እግዚአብሔር ቃል ቅረብና አንብበው
5. የሚያጽናናህን የተስፋ ቃል በብርቱ እንደምትፈልግ ሁሉ የአምላክንም ትዕዛዛት ፈልግ።
ልትወጣው ከሚገባህ ተግባርና ከኃላፊነትህ በላይ የበዛ መጽናናትን አትፈልግ፣ አለዚያ መጽናናትህን ሀሰት ሆኖ ታገኘዋለህ።
6. የምታነበውን ሁሉ ለመተግበርና ለመለማመድ ቁርጠኝነት ይኑርህ።
ክርስቲያኖች ሕያው የሆኑ፣ የተጻፈውን እውነት የሚኖሩ፣ ተንቀሳቃሽ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለባቸው። ቃሉም የመታዘዝ መመርያ ነው እንጂ የእውቀት መመርያ ብቻ አይደለም።
7. ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር መቀለድም ሆነ ቅዱሳት መጻህፍትን እንደዋዛ አቅልሎ ከማየት ዝንባሌ ተጠንቀቅ ተጠበቅም።  
ግዛቸው ከበደ /ቄስ/

No comments:

Post a Comment