Thursday, July 23, 2015

የመስቀሉ ወንጌል

የመስቀሉ ወንጌል
 (1ቆሮ 1፥ 18፤ ገላ 1፥ 3-4)        
በእግዚአብሔር ቃል እንደተገለጠው እውነተኛው ወንጌል የመስቀሉ ወንጌል ነው። ከዚህ የተለየው ተቃራኒው ደግሞ "ሌላ" እየተባለ የሚጠራውና፣ ሰውን እና ሥራውን ማዕከል ያደረገ በሥጋ ትምክህት የተሞላ የማያድን "ወንጌል" ነው ፤ እርሱም ሀሰተኛው ወንጌል ነው።

# አንዳንዶች በእውነተኛው ወንጌል፣ በስብከት ሞኝነት ሳያምኑና ሳይለወጡ ይጠፉ ዘንድ፣ ይህም ንጹህ ወንጌል ለወደቀው አዕምሮአቸው የማይመጥንና ሊቀበሉት የማይችሉት ስለሚሆንባቸው ሊደገፉት የማይፈልጉት ወንጌል ሲሆን፤

# ሌሎች ደግሞ በስጋቸው በመታመን፣ የህግን ሥራ በመፈጸም፣ እንደ መገረዝ ያሉ ልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ የሥጋ ሥርዓቶችን በመጠበቅ ለመጽደቅ ሲሞክሩ የሚያሳዩትን ከክርስቶስ የተለዩና ከጸጋው የወደቁ  መሆናቸውን የሚገልጥ አደገኛ የይሁዲነት ትምክህት ነው።

 "አይሁድ ምልክትን ይፈልጋሉ ግሪኮች ጥበብን ይሻሉ"

ይህ ከጸጋ ተነጥሎ ከእምነቱ የወደቀ ሰው አዙሪት ነው።

ይህ ሀሰተኛ ወንጌል በዘመናችን በርካታ ምሥባካትን ያጣበበው፣ ሰውን ያማከለው፣ ከቁሳቁስ የማይዘለው፣ ገበያ ተኮር የሆነውና ከመስቀሉ ተለይቶ ወደ ክርስቶስ የማይጠጋው፣ እኔ እኔ የሚል የሰብዓዊ ክብርና ዝና እንቶ ፈንቶ ነው።

እርሱም የክርስቶስን ትምህርት ላጣጣሙ ሰዎች እጅ እጅ የሚላቸውና የማይመጥናቸው አጉል ትምህርት ነው።

ከእነርሱም ገሚሶቹ ህግን ጠብቀን እንጸድቃለን ሲሉ፣ የተቀሩት ደግሞ ትንግርትንና ምልክትን ተከትለው ሥሜታዊ በሆኑ ንቅናቄዎች የተወሰዱ፣ በሞቱና ባልሞቱ ሰዎች ላይ እምነታቸውን ያሳረፉ፣ እዚህም ሰፈር እዚያም ሰፈር ያሉ ኃይማኖተኞች ናቸው።

የተቀሩትም በእምነትና በጸጋ የመለወጥ ምንነት ሳይገባቸው በሰው ስጋዊ ጥበብ እየተመኩ እግዚአብሔርንና የማዳን ስራውን በራሳቸው እውቀት፣ ርዕዮትና ፍልስፍናቸው ልክ መትረውና ወስነው አስቀድደው ያሰፉ 'ጠቢባን' ተብዬዎች ናቸው።

በተገለጠው የመስቀሉ ቃልና ትርክት ላይ ሳይሆን ባልተገለጠውና በተሰወረው፣ በማይታየውና ሊታይ በማይቻለው እግዚአብሔር በሰወረው ነገር ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሰው ወንጌል አማኝም ሆነ ወንጌላዊ ለመባል አይበቃም። ይህ ሰው በወንጌል ላይ እየተፈላሰፈና እየተራቀቀ በከንቱም እየሰበከና  ሰዎችን እያስገረመ ሊሆን ይችላል፤ ዳሩ ግን የስብከቱ ይዘት "ሌላ ወንጌል" እንጂ "በስብከት ሞኝነት" የተገለጠው የክርስቶስ የመስቀሉ ወንጌል አይደለም፤ ስራውም ከክርስቶስና ከመስቀሉ የተነጠለ ሌላ ጥንቆላና ድንቆላ እንጂ የእግዚአብሔር ስራ አይደለም።

"እኛ ግን የተሰቀለውን የክርስቶስን እንሰብካለን"

ማርቲን ሉተር ሥነ መለኮታዊ ስብከትን፦ 'የመስቀል' እና 'የክብር' በማለት ለሁለት ከፍሎ ልዩነታቸውን እና በመካከላቸው ያለውን ከፍተኛ ተቃርኖ ያስተምራል።

# አንዱና የእግዚአብሔር ያልሆነው የተጭበረበረው ወንጌል ፍልስፍናን ማዕከል ያደረገውና አመክንዮአዊነትን የሚደገፈው በማየት ላይ ያረፈው ኃይማኖታዊ ልምምድ ሲሆን፣

# እውነተኛውና የእግዚአብሔር የሆነው ወንጌል ደግሞ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ለማዳን የሆነው የተሰቀለው የገሊላው ሰው ታሪክ ነው።

 በወንጌል የሚታየው እና የተገለጠው የእግዚአብሔር መገለጥ የምንለው በክርስቶስ መከራና በመስቀሉ በኩል ተሸሽጎ የታየውን፣ የምህረቱንና የፍቅሩን ገጽታ ነው።

 ሰውን ሊያድን የሚችለው የዚህ ምስኪን ሰው የመስቀል ላይ ታሪክ ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ የሰው ድጋፍ "ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፣ ንፋስንም እንደመከተል" ብቻ ነው።

ዘጸ 33፥ 18 ጀምሮ ሙሴ፦ "እባክህ ክብርህን አሳየኝ" ባለ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሲመልስለት "እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምረዋለሁ...። ደግሞም ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም ....ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም" ብሎታል።

በሰንጣቃው አለት በክርስቶስ የታወቀልን መልካምነቱ፣ የተገለጠው ስሙ፣ ይቅርታው፣ ምህረቱና ማዳኑ ካልሆነ በቀር የእግዚአብሔር መለኮታዊ ግርማው ቢገለጥ ሰውን ያስደነግጠዋል፣ ያጠፋዋልም። ማንምም ቢሆን፣ ሱራፌልና ኪሩቤልም እንኳ፣ በዚህ መለኮታዊ ግርማ ፊት መቆም አይችሉም።

በዚያ አለት ተሸሽጎ ካልሆነ በቀር፣ ደግሞም የእግዚአብሔርን ጀርባውን እንጂ ፊቱን አይቶ ማንም አይድንም። የሚያድነን መገለጥ በእግዚአብሔር ጀርባ የተወከለው የክርስቶስ መከራው፣ ትህትናው እንጂ  'አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነው' ተብሎ እንደተጻፈ በግርማው ፊትማ ማን ሊቆም ይቻለዋል?

እግዚአብሔር የማይታይ የአምላክነት ዘላለማዊ ኃይል አለው። "የማይታየው ባህርዩ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ" ነው። እርሱም ሊታይ የማይቻለው የእግዚአብሔር  ፊት ነው።

የሰው ልጅ ያንን አይቶ በህይወት አይኖርም። የትኛውም ሰብዓዊ ብቃት፣ የህግ ሥራም ሆነ ኃይማኖታዊ ልምምድ ፣ ስጋዊ ጥበብም ሆነ ልዩ ልዩ ትንግርቶችና ምልክቶች ሰውን በእግዚአብሔር ፊት ከቶም አያቀርቡትም።

ነብዩ ኢሳይያስም፦
 "ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል፣ ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ?"
ብሎ ይጠይቅና፣ የጽድቅና የቅድስና መስፈርቱን፣ ከኃጢአትም ነጻ ሆኖ የመገኘት መመዘኛውን ዘርዝሮ ይነግረናል (ኢሳ 33: 14-15)።

ሰው ደግሞ ምንም ያህል በራሱ ቢጣጣር ከእግዚአብሔር ጋር ሊያኖረው በሚያስችለው ብቃት፣ ፍጹም በሚባል ደረጃና ልክ፣ በቅድስናውና በንጽህናውም መጠን የእግዚአብሔርንም ልብ ሊያረካ በሚያስችለው መጠን ራሱን ሊያነጻ ከቶም አይችልም።

ስለዚህም ሰው የገዛ ራሱን አሳፋሪ ጽድቅ ይዞ በእግዚአብሔር ጽድቅ ፊት ሲቀርብ የሚቀርለት ፍርሃት፣ ቅጥቃጤና ሽብር ብቻ ነው። ይልቁን ግን ክርስቶስን በመስቀል ላይ ሲሰቃይ፣ በድካምም ሲሞት  በእምነት ለሚያዩ ጽድቅም፣ ቅድሥናም፣ ቤዛነትም፣ መዳንም  አለላቸው።

እግዚአብሔርም ለሰው ያዘጋጀው ሰውን የሚያድን አስገራሚ መገለጥ ከሁሉ በፊት፦

 ፨ክርስቶስ በቤተ መንግስት ሳይሆን ክርስቶስ በበረት ውስጥ፣

፨ክርስቶስ በፈረስ ላይ ሳይሆን ክርስቶስ የዋህና ትሁት ሆኖ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ፣

፨ክርስቶስ በዙፋን ላይ ሳይሆን ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሆኑ ነው።

#በመስቀሉ ታሪክ አይኑ ያልበራለት ሰው በግርማው ብርሃን ይታወራል እንጂ መቼም ብርሃንን አያይም።

#ለንስሃ በሚሆን ቀላል እምነት በክርስቶስ ትህትናና በየዋህነቱ ፊት  የገዛ ራሱን ትምክህት ጥሎ ያልተንበረከከና ወድቆ ያልሰገደ ሰው በግርማው ፊት ይቀልጣል እንጂ ህይወትን አያይም።

ዘላለማዊ ጽድቅ ለኃጢአተኞች  ሞልቶም የተትረፈረፈውና፣ የፈሰሰው ከክርስቶስ መከራና ከሞቱ መስቀል ነው። በመስቀል ትይዩ የሚያለቅሱ ብቻ ከፈሰሰው የሕይወትና የመጽናናት ምንጭ ዘላለማዊ ደስታን ይጠጣሉ።

 ከዚህ ውጭ ያለውና ከእምነት የተለየው ሥጋዊ አቀራረብ ሁሉ ሰውን በትዕቢት ኮርቻ እያፈናጠጠ በኩራት ሰረገላ ላይ አሳፍሮ ወደ ጥፋት ያደርሰዋል እንጂ ከቶ አያድነውም።

ምንም ቢሆን የሰው የጽድቅ ሙከራ በቅዱሱ አምላክ ፊት የመርገም ጨርቅ ሆኖ ሰውን ያሳፍረዋል፣ ያሸማቅቀዋል ያፈርሰዋልም እንጂ ወደ ሕይወት አያደርሰውም።

መጽሐፉም ደግሞ፦

 "ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የሕግን ሥራ በመስራት አይጸድቅም" ሲል የሥጋን ትምክህት ሽሮ እርግጡን ይነግረናል።

እንግዲህ ሞትና ኩነኔ እንደሚገባቸው ኃጢአተኞች በእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ አንጻር በምንቀርብበት ጊዜ በእርሱ በተሰቀለው ክርስቶስ የተሰጠን የምህረት ተስፋ በእምነት ይረዳናል።

በራሳችን ሥራ በመታመን ሳይሆን በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ባቀረበው ሊቀካህናት-ወመስዋዕት በሆነው በክርስቶስና በመስቀሉ ደም በኩል ባለን ድፍረት ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ተጋብዘናል!!

እንግዲህ ከኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱም እንደተሰቀለ ከማወቅ በቀር ሌላ ዕውቀት፣ ደግሞም ከመስቀሉ ኢየሱስና ከኢየሱስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም ከእኔ ይራቅ! አሜን!!

'እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር' እንደሚባለው፣ ክርስቶስንና መስቀሉን ሰብከን ማደር አይደለም ምነው ሲመሽ ወይም ሲነጋ ብንሞት!

እንደወንጌል አማኝም ሆነ እንደወንጌል ሰባኪ ክብራችን ይህ ነበር፤ የዘመናችን ትውልድና 'ከዋክብት' የሆኑ ኮሜድያን ወከያንያን ሰባኪዎቹ ግን መልእክታቸውን ጥለውና "ሳር በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን እንደለወጡ" የእስራኤል ልጆች አገልግሎታቸውንና መልእክታቸውን ለውጠው ሰባቂዎች ሆነውብናል።

ዛሬ ንስሃ የሚያስፈልገው ከሁሉ በፊት ለእኛ ለሰባክያኑ ነው።  ማንንም ወደንስሃ የማያደርስ በሰው ጥበብና በስጋዊ ትምክህት በተሞላ ኃይማኖታዊ በሆነና ሰዎችን ለማስገረም፣ ገበያ ለመሰብሰብ ሲባል በተሰራ በገለሞተ አገልግሎትና በተለወጠ ወንጌል የቆሙ ሁሉ ከባሰው ፍርድ በፊት ንስሃ እንዲገቡ ያስፈልጋል።

የህንን የንስሃ ጥሪ እምቢ የሚሉና ገልሙተው ህዝብን የሚያስገለሙቱ ግን የእግዚአብሔር ፍርድ ሲመጣ እርቃናቸውን ይቆማሉ። ያኔ ወየው ለእነርሱ፣ አንዳንዶቹ በገንዘብ ቅሌት ሌሎቹም በሰው ሚስት ላይ ይያዛሉ። ይህንንም እያየን ነው። እነዚህም በውሸተኞች ግብዝነት የሚሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት የሚያድምጡና የሚያስደምጡ ካፉ ሰራተኞችና ጨካኞች ተኩላዎች፣ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ፣ ሐዋርያትም ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉ፣ ስምና ከብር ለራሳቸው ያከማቹ ሃሰተኛ ነብያትና አሳሳች መምህራን ናቸው።

በጭብጨባ ብዛት የሰከሩትን የመድረክ ላይ ደፋሮችን የሚያበረቱ፣ የሚያድነውን ንጹህ መልእክት የመስቀሉን ቃል ንቀው እንደሚያስጠነቁል አህዛብ ትንግርትና ምልክትን የሚናፍቁ፣ 'ማን መጥቶ ባሳሳተን' እንደሚሉ ሁሉ እየተማሩ እውነትን ወደማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትና የማይፈልጉ፣ ምንም የማይጠይቁ፣ ሁሉን እንደወረደ የሚቀበሉ ወቅተኞችና ወረተኞች የሆኑ ደርሶ ተመላሾች፣  አጨብጫቢና አዳማቂ ተከታዮቻቸውንም ቢሆን እግዚአብሔር ገንዘባቸውን ለሚበሉ፣ ሕይወታቸውን ለሚያራቁቱ ገበያ ለሚሰሩባቸውና ለማይራሩላቸው ጨካኝ ተኩላዎች አሳልፎ ይሰጣቸዋል

የዘመናችን ምስባክና ሚድያ ሁሉ የተዘረፈ ገንዘብ ይዘው ባልተለወጡበት 'ወንጌል' እንደቁራ በሚጮሁ፣ ከዙረት ትርክታቸው በቀር የወንጌሉ ቃል ከመልዕክታቸው በማይገኝባቸው ዝና ናፋቂዎች፣ አካሄዳቸውንና ምስክርነታቸውን ሳይሆን መልካቸውን ባሳመሩ፣ ገጽታቸውን በሚገነቡ፣ ምልክት ናፋቂዎችና ስለራሳቸው ተናግረው በማይረኩ እኔ ባይ ትንግርት ፈላጊ ጠንቋዮች የተጨናነቀ ቢሆንም፣ በሰው እውቀትና በሥጋዊ ጥበብ በሚሄዱ ትምክህተኞች፣ ሌሎችንም በሚንቁ ኃይማኖተኞችና ሊማሩ በማይወዱ ልክ ነን ባዮች የተሞላ ቢሆንም፣ እኛ ግን "በወንጌል አላፍርም" ተብሎ እንደተጻፈ፣ አሁንም ዛሬም "የተሰቀለውን  ክርስቶስን እንስብካለን"። ከዚህ ውጪ ትምክህት የተለየም ስብከት የለንም።

     እኛ ግን የሞተልንን፣
     በደሙም የተቤዠንን፣
     አዳኝነቱን ንጉስነቱን፣
     ለፍጥረት ሁሉ እንሰብካለን!
     አሜን እንሰብካለን!!